Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ቂ.ቂ.ቂ.ቂ.ቂ.ቂ.ቂ.ቂ.ቂ.ቂ.ቂ.ቂ.ቂ.ቂ………. ጦቢያን ገረመው

$
0
0

ጦቢያን ገረመው

 

Penይህች አነስተኛ መጣጥፍ ለታዋቂው ጋዜጠኛና አክቲቪስት እስክንድር ነጋ መታሰቢያነት ትዋልልኝ፡፡ ምክንያት አለኝ፡፡ ርዕሱ በመጠኑ ተሻሽሎ የተወሰደው በእርሱ ባለቤትነትና አዘጋጅነት ይመራ ከነበረው ከምኒልክ ጋዜጣ ነው፡፡ ባጭሩ ለማስታወስ – የዛሬ 12 ዓመት ገደማ በ93 ዓ.ም ወያኔ ለሁለት ተሰንጥቃ ነበር፤ ከዚያ በፊትም በ90 አካባቢ ንፋስ ይገባባቸው እማይመስሉት ወያኔና ሻዕቢያ ባላሰቡትና ባልጠበቁት መንገድ መቃቃራቸው የሚታወስ ነው፡፡ ያኔ ወያኔ በተቸካይነትና በተሃድሶነት ተከፋፈለች በተባለበት የዘመነ ህንፍሽፍሽ ወቅት ታዲያ አንድ ጸሐፊ በምኒልክ ጋዜጣ ‹እልልልልልልልል…› በሚል ርዕስ አንድ መጣጥፍ ልኮ ‹አስነብቦን› ነበር፡፡ የሚገርማችሁ መጣጥፉ በእልልታ ጀምሮ ያለቀውም አንድም ሌላ ቃል ሳይጨምር በእልልታ ነበር፡፡ በምናባዊነቱ እየተገረምኩ በደስታ ‹ያነበብኩት መጣጥፍ› ስለነበር መቼም አይረሳኝም፡፡ ያቺን በማስታወስ ነው እንግዲህ ለኔ የዛሬዋ መጣጥፍ ተቀራራቢ ርዕስ የሰጠሁት፡፡

ዛሬ ጧት የግዛው ለገሰንና የብርሃኑ ዳምጤን ‹የእሁድ ወግ› በኢሳት እኮመኩም ነበርና አንድ በሣቅ የሚያፈነዳ ነገር ከውይይቱ አገኘሁ፡፡ በቅድሚያ ግን መተቸት ከሁሉ የቀለለ ነውና በኢሳት አቀራረብ ላይ እኔም ትንሽ ልበል – ኢሳቶች እንዳትቆጡኝ አደራ፡፡ ግዛው ለወደፊቱ እንግሊዝኛ ላለመጨመር ሞክር፤ የቋንቋ ‹ጥራት› ምናምን በሚሉት ሥነ ልሣናዊ አርበኝነት ተመርኩዤ አይደለም እንዲህ የምል፡፡ የወፍ ‹ቋንቋ› ከሰው ቋንቋ እየተዛነቀ ቢነገር እኔን እስከገባኝ ድረስ በበኩሌ ግዴለኝም፡፡ ግን ግን ኢሳትን የሚከታተለው ሕዝብ በአብዛኛው ጆሮውን ቢቆርጡት እንግሊዝኛ የማይሰማና የማይገባውም ከመሆኑ አንጻር በተለይ በጋዜጠኝነት ሙያ የተሰማራ ሰው ወደደም ጠላም ሚዲያው በኦፊሴል ሊጠቀምበት በወሰነበት ቋንቋ ነው የግዱን መጠቀም ያለበት፡፡ ከዚህ ነጥብ አኳያ ብዙዎች የኢሳት ጋዜጠኞች ጥንቃቄ ቢጨምሩ በሀገር ቤቱ ተከታታይ ዘንድ ተደማጭነትን ላለማጓደል ተገቢ ነው እላለሁ – እነሲሴንና አፈወርቅን ጨምሮ ብዙዎቹ የሚያደርጉትን ጥንቃቄ ግን ሳላደንቅ መቅረት ባልፍ ኅሊናየ ይቀየመኛል፡፡ እርግጥ ነው በዚህ የግሎባላይዜሽን ዘመን የቋንቋን ‹ጥራ› መጠበቅ እጅግ አስቸጋሪ መሆኑ ይገባኛል – ራሴም የችግሩ ሰለባ ስለሆንኩ ቋንቋን በጉራማይሌነት እያዛነቁ መናገር በተለይ በዚህ ዘመን በጣም እየተለመደ መጥቷልና አንዳንዴ በተለይም በሚዲያው አካባቢና የሚዲያው ሰዎች care መውሰድ ይገባናል በማለት ጉራማይሌያውያንን advise ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ otherwise የምንለው ነገር የማይገባቸው እንደኛ ጥቂትም ቢሆን ቋንቋ learn ያላደረጉ ዜጎች ስላሉ ይቸገራሉ የሚል ግምትና estimashin አለኝ because ብዙውን ጊዜ ሲቸገሩ ስለማይ፡፡ መቼም understand እንደምታደርጉኝ guess አደርጋለሁ፡፡ እሺ ok አሁን ወደሌላ አቃቂር ልለፍና ስለኢሳት toke ማድረጌን ላብቃ – by the way የእንግሊዝኛና የአማርኛ መምህሮቼ በspeilling puor ነህ ይሉኝ ነበርና አሁንም ድረስ እንደዚያው ሳልሆን እንደማልቀር እገምታለሁ፡፡ ብዙ ነገር ይቸግረኛል፡፡ አሁንም በሽምግልና ዘመኔ እንደዛው ሳልሆን የምቀር አይመስለኝምና በቀጣይ አንቀጾች ይህ ችግር ቢገጥመኝ አደራችሁን እንዳትዘከሩብኝ፡፡ ይህን የምለው አባመላ ስለ አንጋፋው ወያኔ ስለብስናት አማረ ሲናገር የሰማሁትን ማስከተሌ አይቀርምና ምናልባት እዚያ ገደማ ከተሳተኝ ብዬ ነው፡፡

ኢሳት ይህችን ፕሮግራምን በጣም የመደጋገም ነገር እንዴት እንደሚያሻሽላት እኔንም እየጨነቀኝ መጥቻለሁ – በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እያሳየ ያለውን መሻሻል ግን በዚህ አጋጣሚ ላደንቅ እፈልጋለሁ፤ ብዙ የመፈለግ ጣጣ ባለህ አለመርካትን እንደሚያስከትል እየተረዳሁበት የመጣሁበት ሁኔታ ተፎጥሯል ይመስለኛል፡፡ ከቤተሰቡ ጋር ጦርነት ውስጥ በመግባት እነ‹ሰው ለሰው›ንና የ‹ቤቶች› ድራማን ዘሩ ቀለጠንና እከደከ ማንችሎት … አበጀን ማየት እንዲችሉ መላ ቤተሰቡን ወደጎረቤት ለስደት በመዳረግ ሁሉንም ቲቪዎች ጠርቅሞ ዘግቶ ኢሳትን ብቻ ለሚከታተል ለእንደኔ ዓይነቱ ተስፈኛ ይቺ ነገር ቅር ታሰኛለችና እባካችሁን በብርቱው አስቡበት፡፡ የዐርብና የሐሙስን ዜናም ሰኞና ማክሰኞ በሰበር ዜናነት ከማቅረብ ተቆጠቡ፡፡ ምነው ሸዋ! እነሱው ምንም ባይሉን እኛው በኛው እንተቻችና እንተራረም፡፡ መተራረምን ደግሞ የባሕርይ ስጦታችን ካላደረግነው የአሁኑና የእስካሁኑ አስጠሊታ የመፈራራትና ባላስፈላጊ ሁኔታ በጎራዎች የመፈራረጅ ጅል ይትበሃል ምርኮኛ እንዳደረግን ይቆያል፡፡ ትችትን መፍራት ለባሰ ትችት ይዳርጋልና በግልጽነት መነጋገርን ባንቃወም መልካም ነው፡፡ በገምቢ ሁኔታ ብንተቻች እንጠቀምበታለን፤ በአእምሮም እናድግበታለን እንጂ አንጎዳም፡፡ መፈራራትና ‹ለጠላት በር ላለመክፈት ሲባል እንቻቻል› የሚሉት ፈሊጥም የትም አያደርሰንም ብቻ ሳይሆን ፍጹም ጎጂ ነው፡፡ ለመሆኑ ከፀሐይ በታች ምን አዲስ ነገር አለና ነው ትችትን እንደጦር የምንፈራው? ምናችንን ማንና እነማን ሳያውቅ/ቁ ሊቀር/ሩ? ሞኝነት ነው፡፡ እንደእውነቱና እንደኣካሄድ እንዲህ የምለው ለኢሳቶች አይደለም – በጭራሽ፡፡ ምክንያቱም ይህን የኔን መሰል ትችት በዚያው በኢሳት በኩል ዜጎች በተደጋጋሚ ሲናገሩ እሰማለሁና፡፡ እንዲህ የምለው ለማላውቃቸው ጥቂት ወገኖቼ ነው – ልክ እንደኔው ለኢሳት ለሚሳሱ ወገኖች፡፡ ግዴለም፤ ይህ ዓይነቱ እንስፍስፍነት አይጠቅምምና እንተወው፡፡ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን ይልቁናስ በአወንታዊና ገምቢ አስተያየቶች በቅድሚያ ራሳችንን በየሙያ ዘርፋችን አሳድገን በራሱ የሚተማመንና በፍርሀት ምክንያት ለሂስና ግለሂስ በሩን የማይጠረቅም ጀግና ትውልድ እንፍጠር፡፡ …

በሣቅ የገደለኝ ነገር – አባ መላ ሲናገር ከፍ ሲል የጠቀስኩት ብስናት አማረ የሚባል ወያኔ መለስ ከሞተ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ሊገባ ሲል በአንድ ግለሰብ ቀጭን ትዕዛዝ – በ‹ጄኔራል› መሀመድ የሎስ ጥብቅ መመሪያ ምክንያት ከቦሌ እንዲመለስ የተደረገበት ምክንያት ነው፡፡ የየሎስ እውነተኛ ቁርሾኣዊ ብስናትን ወዳገር እንዳይገባ የመከልከል ምክንያት የፈለገው ይሁን ግን ብስራት መጣ ሲባል “መለስ ሲሞት አለማልቀሱን የደኅንነት ሰዎቻችን ባደረጉት ሥውር ክትትል አረጋግጠዋልና ወደ ሀገር እንዳይገባ ታግዷል” በሚል ሰበብ ሰውዬው ማለትም ብስናት አማረ ወደ ሀገሩ እንዳይገባ መከልከሉን ስሰማ የሳቅሁት ሣቅ መቼም የሚደገም አይመስለኝም፡፡ ኢትዮጵያ የደረሰችበት የአስተዳደር ፈሊጥና የዘመናዊ መንግሥትነት ባሕርይ ቁልጭ ብሎ ታየኝና በምን ዓይነት ‹ሰዎች› እየተገዛን እንዳለን በማሰብ ለተወሰነ ጊዜ ወደማይታወቅ ሰማይ ጠፋሁ – በስላቃዊ ሣቄ ታጅቤ፡፡ እንዴት ያለ ጉደኛ መንግሥትና የመንግሥት ሹማምት ናቸው ያሉን ጃል? እስከዚህም ደርሰናል ለካንስ? ልቅሶና ዕንባም በሀገር ካጅነት ያስፈርጁ ጀመር? እንዴ፣ ስዬ አብርሃ በመለስ ሞት ጊዜ ለሰባት ቀናት ሀዘን ተቀምጦ ነበር ሲባል የሰማሁት ይህን በመፍራ ይሆን? የኔን ቢሰሙ አንቀው ይገድሉኝ ወይም ተቃርጠው ያነክቱኝ ነበር በሉኛ! (አንድ ወያኔን እምብዝም የማይወድ ትግሬ ወዳጄ ቤት ለሆነ ጉዳይ አንድ ጊዜ ሄጄ ምን ታዘብኩ መሰላችሁ – የሣሎኑ ግድግዳዎች ላይ የመለስ ሦስት የተለያዩ ትላልቅ የማስተዛዘኛ ፎቶዎች ገጭ ብለው ተሰቅለው የቤቱን አባላትና ወጪ ገቢን ይታዘባሉ – በተጉረጠረጡ ዐይኖቻቸውና የሚሞት በማይመስል ወያኔያዊ የተጋዳላይነት ስሜት፡፡ ይህም ከማዘን አለማዘን ግምገማና ያም ከሚያስከትለው በሀገር ከሃዲነት የማስፈረጅ አሰቃቂ ዕጣ ለመዳን ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምንድነው በሀገራችን የመጣብን ጉድ ውድ ጤናማ ነን የምትሉ ዜጎች? እንዴት ዓይነት ትንሽነትስ ነው ተፈጥሯዊ ስሜትን በሰውኛ መክሊት የመስፈርና ማዘን አለማዘንን በኣሃዛዊ ስሌት እያስቀመጡ ዜጎችን የማሳቀቅ አዲስና በሀገራችን ባህል ያልተለመደ ጠያፍ ነገር? ከሰሜን ኮሪያ ሌላ ይህ ዓይነት በሽታ ያለባቸው ‹መንግሥታት› ይኖሩ ይሆን? ኧረ ምን ዓይነት ውርደት ውስጥ ነው የምንገኘው? አንድ ሰው እኮ ለልጁም፣ ለሚስቱም፣ ለአባትና እናቱም፣ ለሌላ ለሚወደውም ሰው ላያለቅስና ፊቱን በባና ላይነጭ ይችላል፡፡ እንዴ – ይህ እኮ ፍጹም የግል ጉዳይ ነው፡፡ ከሀዘን ብዛት እንዲያውም ማንባቱንና ማልቀሱን ትቶ የሚስቅም እኮ እኮ አለ – ወደጤናማ ኅሊናው እስኪመለስ ድረስ፡፡ በዚያ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሰው በወያያዊ ፍርድ ሣቀ ተብሎ በጭፍን ብያ ይሰቀል ይሆን? ) ለማንኛውም ውስጥ ዐዋቂውን አባ መላን እግዜር ይስጠው – ቢያንስ በዚህች አስደስቶኛልና ልጅ ይውጣለት፡፡ በሌላስ ቅሬታ አለኝ – ወረድ ብዬ በትህትና ለመጠቆም እሞክራለሁ – ካልተቀየመኝና ‹መቃብርህ ላይ አያቁመኝ› ብሎ ካልረገመኝ፡፡(አንዳንዴ መንጌ ሲናገር – ‹እኛ እኮ እኮ ለውዲቷ አብዮታዊት እናት ሀገራችን …› ይል ነበር – በስሜት ማዕበል እየተናጠ፡፡)

በደርግ ዘመን አንዲት ጥንቸል ልቧ እስኪፈርጥ እየሮጠች በሁለቱም ሞያሌዎች በኩል የኢትዮጵያንና የኬንያን ድንበር አቋርጣ ማርሳቤት የሚባለው የስደተኞች መንደር ትደርሳለች አሉ፡፡ ማምለጧን አላመነችም – ዝም ብላ ማለትም እያለከለከች ሩጫዋን ታስነካው ይዛ ሳለ “ ምን ሆነሽ ነው እንዲህ የምትሮጪ አንቺ ጥንቸል? ያንቺ ስም እኮ ከሚፈለጉት እንስሳት የስም ዝርዝር ውስጥ የለም፡፡ የሚፈለገው ዝኆን ነው፡፡ ምን ሆንኩ ብለሽ ነው አንቺ ደግሞ እንዲህ በማይመለከትሽ ነገር እምትኳትኚ?” ብለው ይጠይቋታል፡፡ እሷም “አይ እናንተ፣ የኢትዮጵያን ነገር እያወቃችሁት? ዝኆን አለመሆኔ እስኪረጋገጥ ድረስ ታስሬ ከሚደርስብኝ ስቃይና እንግልት የሚበልጥ ስለሌለ ራሴን ለማዳን ነው እንዲህ እምሆነው!” ትላለች፡፡ አዎ፣ እውነቷን ነው፡፡ ዱሮ ‹ዝኆን› አለመሆንህ እስኪረጋገጥ ነበር የምትሰቃይ፡፡ ዛሬ ደግሞ ከዚያ በባሰ አስገዳጅና ቀፍዳጅ ሁኔታ ውስጥ ስለገባን በወያኔ የማሳደድ ቀለበት ውስጥ የምትገባው የወያኔ ደጋፊ ትግሬነትህ እስኪጣራና የሆዳም አማራነትህ ሊቼንሳ እስኪወጣልህ ድረስ እንጂ ከዚያ በኋላ ላለው ሕይወትህ ምርጫው በእጅህ ነው፡፡ ወያኔ ካልሆንክ በኢትዮጵያዊነትህ ኢትዮጵያ ውስጥ የመኖር ዕድልህ በዜሮና በእንድ የመቶኛ ምናልባታዊነት ግምት የሚሰላ በመሆኑ የሚደርስብህ ስቃይ ከኢዮብ የማይተናነስ ነው፤ በሕይወት ለመትረፍም ያለህ ብቸኛ አማራጭ እግርህ ባወጣህ ከሀገርህ ወጥተህ መሰደድ ነው፡፡ በምትሰደድበትም ቦታ ሁሉ እስስቱ ወያኔ ከአካባቢው ጋር እየተመሳሰለ ስለሚጠብቅህ ኅልውናህ ሁልጊዜ አደጋ ላይ ነው – ኬንያ ላይ በወያኔ ሠርጎ ገብ የተገደለውን መባጽዮን ጃተኒን አስብ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በሕይወት ላለመኖር ከፈለግህ ኅሊናውን የሚጠቀም አማራና ትግሬ ወይም ኦሮሞና አማራ ሁን – በቃ፡፡ ወያኔ መሆንህ ካልተረጋገጠ አትላንቲክና ፓሲፊክም ግባ እንጂ የሚለቅህ የለም፡፡ እንኳንስ ተወልደህና ወደዚህች እርጉም መሬት መጥተህላቸው ገና በማሕጸን ውስጥ ሳለህም አሳድደው ያጠፉሃል – ኢትዮጵያዊ ለመሆን ካሰብህ፡፡

አንዳንዴ ደግሞ በሃሳብ ካልተጣጣምህ ፣ ትዕዛዝን እንደወረደ ካልፈጸምህ ወይ ካላስፈጸምህ፣ በሥልጣን ተቀናቃኝ ሆነህ ከተገኘህ በመሰል የወያኔ አለቆችም ልትንገዋለል ትችላለህ – ልክ እንደነብስናት አማረ፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ከኋላችን ወያኔ ሲያሳድደን፣ በኢኮኖሚ ደረጃ ኑሯችን ክፉኛ ሲያንገላታንና በገዛ ሀገራችን መኖር ሲያቅተን ባገኘነው መንገድ ሁሉ እየወጣን ለስደተኝነት የተዋራጅ ሕይወት፣ ለቤት አሽከርነትና ገረድነት፣ ለሀብታም ሰውነት የሰውነት ስፔርፓትነትም እንዳረጋለን – ይህን ዘመን አልፎ አይተነው መቼም – ያልሆንነው እኮ የለም፡፡ ዱሮ መጠጊያቸው በነበርንባቸው የዐረብ ሀገራት ዜጎች ቤት ውስጥ እየተቀጠርን ከመስኮትና ከፎቅ ላይ እየተወረወርን እናልቃለን – በዚህም ሺዎች የመኖር ተስፋቸው ጨልሞ ያለ ጧሪና ቀባሪ ይቀራሉ፡፡ በየቀኑ በገፍ እየተሰደድን ዓለምን እናጥለቀልቃለን – በዚህም ሌሎች እየሰለቹን መጥተዋል፤ መውደቂያ አጣን – ምን ይዋጠን? እንዲህ ስንል ደግሞ እነገዛኢ ‹ከሀገር ቤት የምትወጡት ልማታዊ መንግሥታችን ያረጋገጠላችሁ ድሎትና ምቾት እንዲሁም አይታችሁት የማታውቁት ዴሞክራሲ መጠኑ በዝቶባችሁ (an overdose of democracy) አንጎላችሁ ውስጥ ገብቶ ጥጋብ ስለሚያናፍላችሁ ነው!› እያሉ ያላግጡብናል – ራሳቸው የፖለቲካ ሳይሆን የኢኮኖሚ ስደተኞች ሆነው ሲያበቁ ለዚያውም፡፡ አንድ መሆን አቅቶንና ለወያኔ የከፋፍለህ ግዛ ወጥመዶች ተንበርክከን ለተሸናፊነት ስሜትም አጎብድደን የዓለም መዘባበቻ ሆነን ቀረን፡፡ ይህ የማይቆጨው ገልቱ ዜጋ ሁሉ በየዘርና በየሃማኖት ጎራ እየተቧደነ እርስ በርስ ሲቆራቆስ የወያኔን ዕድሜ ያራዝማል፤ ለተሸራጭ ሠርጎ ገቦች የጥቃት ዒላማ ምቹ በመሆንም የነጻነት ትግሉ መቅኖ አጥቶ እንዲቀር ያደርጋል፡፡ በዚህም ሳቢያ ስደቱና መከራው እንደተባባሰ ይቀጥላል – አሁን አዲስ አበባን ለሚያይ ታዛቢ ስደት የወያኔ ቁጥር አንድ የዕድገት ትልም ይመስል በየኤምባሲው – ፊጂና ጂቡቲ ሳይቀር – ዜጎች ተኮልኩለው ሲታዩ በሀገር ውስጥ ከቱባዎቹ ወያኔዎች በስተቀር ሌላ ሰው ባገር የሚቀር አይመስልም – ቢሳካለት ሁሉም ለመሄድ አቆብቁቧል – ወያኔና ጌቶቹ በዚህ ሊኮሩ ይገባል፤ አጸፋውን ከቻሉት ያለሙት የጥፋት ድግስ ሁሉ ለጊዜው መስመሩን ይዞላቸዋል፡፡ በዚህም አለ በዚያ የወያኔ ሸፍጠኛ አገዛዝ በቁስላችን እየገባ ዕድሜውን ማራዘሙን ቀጥሏል፡፡ የሞኞች ጠብ ለብልጦች ሠርግና ምላሽ ነውና እኛ ስንከናታ/ስንጃጃል እነሱ በብልጥነታቸው ግመልነታቸውን አስከብረዋል – እኛም ውሻነታችንን፡፡ አይክፋህ ወንድሜ – አይክፋሽ እህቴ፡፡ እምናገረው እውነትንና እውነትን ብቻ ነው፡፡ ሰው በወደደው ይቆርባልና እኛም የወደድነውን ወያኔዎችም የወደዱትን አግኝተናል፡፡ የአንዱ ሀዘን ለሌላው ሠርግ ነው፡፡ ‹ላሊበላ በሰው ተዝካር ይዳዳራል› እንዲሉ ወያኔዎች ይበልጡን እኛው ለኛው  ባፋጠንነው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ መምነሽነሻቸው ተዓምር ሳይሆን አስቀድሞ የተገመተና የሚጠበቅም ነበር፡፡ መጥኖ መደቆስ ጥንት ነበር ወዳጄ!

ልደቱን ያዬ በአባ መላ የአነጋገር ላህይ ልቡ አይሸፍትም ብል ምን እሆን ይሆን? አባ መላ ወይም ብርሃኑ ዳምጤ በተቃውሞው ጉራ ማለትም ጎራ ሰሞነኛ ቀሲስ የሆነ ይመስለኛል – ባለወርተራ፡፡ ከአንገት ሣይሆን ከአንጀት ያድርግልን እንጂ በዚህ ኹነት ደስታየ ወሰን የለውም፡፡ ራሱም ተናግሮታል – የተቃውሞው ጎራ የወያኔን ያህል ጎራ ለዋጭን አያንገላታም፡፡ አባ መላ በአዲሱ ሕይወቱ የተደሰተ ይመስላል፡፡ ከልደቱ አያሌው የማይጋራቸው የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ባሕርያት እንደማይኖሩት የማረጋገጥ ኃላፊነት የማን እንደሆነ ግን እስካሁንም ሆነ ወደፊት አላውቅም፡፡ ፖለቲካ በጣም መጥፎ ነው፡፡ ጨምላቃ ጨዋታ ነው – ማን እንደሆነ ዘነጋሁት እንጂ politics is a nasty/dirty game. ብሎ አያ ፖለቲካን ልክ ልኩን ነግሮታል አሉ፡፡ አዎ፣ እጅግ ከሚያስፈሩኝ የዓለም ዜጎች መካከል ፖለቲከኞች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ጨውና ስኳር ወይም እሬትና ማር አይደሉ አትቀምሷቸውና አትለዩዋቸው፡፡ በመልክ በቁመት አትፈርዷቸው፡፡ በአነጋገር እንደሆነ ያነሆልላሉ፡፡ የማያነሆልል ንግግር የማያውቅ እንዲያውም ከናካቴው ወደፖለቲካ አይገባም፡፡ እንደሌባውና አጭበርባሪው ልደቱ አያሌው ያለ ሣተናና ሞጭላፋ ዱርዬ ማር በተቀባ ምላሱ የሕዝብን ሥነ ልቦና ተመርኩዞና ቦጥቡጦ፣ የወያኔን ገንዘብ ተንጠላጥሎና ድብቅ አጀንዳውን አሸምቆ ይዞ በተቃውሞው ጎራ ትልቅ ደረጃ ከደረሰ በኋላ የልቡን አድርሶ በ‹ሚሽን አኮምፕሊሽድ› ፖለቲካዊ ዕቃ ዕቃ ጨዋታ ሕዝብን ጨረቃ ላይ አስቀምጦ ወደተዘጋጀለት ቦታ የሚሄድ ወራዳ – እደግመዋለሁ – ወራዳ ዜጋ – አለ፡፡ ካለበት የተጋባበት ነው፡፡ መሌ ገሞራው ይህችን ቃል ይወዳት ነበር – ‹ወራዳ›ን፡፡ እኔን! – በየሄደበት እንዳሞሌ ጨው ራሱ እንደተዋረደና እንደቀለለ ጥርኝ አፈር ሆነ፡፡ በዚያች ያማሪካ ስብሰባ ላይ ያ ልጅ በመብረቃዊ ድምጽ ሲያምባርቅበት የሆነው መሆን አሁን ድረስ ይታየኛል፡፡ አየ የመጥፎ ሰው መጨረሻ!

ጥሎብኝ አባ መላን እወደዋለሁ – የምወደው ሁሉ እንደሚወደኝ የማረጋግጥበት ዘዴ በማጣቴ ግና ዘወትር እንደተጨነቅሁ አለሁ፡፡ ማን ናት ያቺ – ባል ያልነበራት አንዲት ሴት – ‹ገንዘብ ያለው ያግባሽ ወይንስ አፍ ያለው?› ተብላ ብትጠየቅ አሉ – ‹አፍ ያለው ያግባኝ!› ብላ መለሰች ይባላል፡፡ ግራ እየገባኝ ነው ወገኖቼ፡፡ ማመን አይገደኝም – እንዲያውም ካለማመን ማመን ሳይሻል አይቀርም – ሥነ ቃላችን “ያልጠረጠረ ተመነጠረ” እያለ ሆድ ያስብሳል እንጂ፡፡ ግን ማንን መቼና እንዴት ማመን እንደሚገባኝ አለማወቄ አንጎሌን እያሳመመኝ ነው፡፡ ሰዎችን እንዴት ነው የምናምናቸው? በአነጋገር ችሎታቸው? በተግባራቸው? በዘራቸው? በቀለማቸው? በሃይማኖታቸው? በትምህርት ደረጃቸው? በሥልጣናቸው? በተፅዕኖ ፈጣሪነታቸው? በአለባበሳቸው? በዝናቸው? በጨዋታና ቀልድ ዐዋቂነታቸው? በገንዘብና በሀብታቸው? በደም ምርመራ ውጤታቸው? በጎጣቸው? በእውኑ በምን እንመናቸው? ኣኣኣ… ትልቅ ችግር!!

አባ መላ ሲናገር ደስ ይለኛል – ወያኔን ከከዳ ወዲህ ነው ታዲያ፤ ከዚያ በፊት አላውቀውም – ማወቅ ከነበረብኝ ይቅርታ፡፡ ብዙ የንግግር ዐዋቂ ሰዎችን ዐውቃለሁ፡፡ ኢንጂኔር ኃይሉ ሻውል በኢትኦጵ መጽሔት ላይ በጣም ማራኪ ቃለ ምልልስ አድርገው ማንበቤ ትዝ ይለኛል – እንደተናገሩት ሆነው ስለመገኘታቸው ግን ጊዜው ስለራቀም ሊሆን ይችላል ትዝ አልልህ አለኝ፤ አብርሃም ያዬህንም በንግግር ለዛውና ጤፍ በሚቆላ ምላሱ በጣም እወደው ነበር፡፡ አሁን የት እንዳለም አላውቅም፤ ነገር ግን ለገዛ የታዋቂነት ዝናው አምላኪ ሆኖ ከቅድስት ቢዮንሴና ከ‹ብፁዕ አባታችን› ቀጥሎ በዐርባ ሰባተኛነት ታቦት ይቀረጽልኝ እያለ ባስቸገረን የዝነኝነት ልክፍት ተጠምዶ የደረጃ መዋዠቅ እንዳሳየና ከአንደኛ ዲቪዚዮን ይልቅ የወራጅ ቀጣናን መርጦ መቀላቀሉን ቀደም ሲል ሰምቻለሁ፡፡ የሆነው ሆኖ ማንም ምን ይናገር የኔ ግላዊ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ግን ከዚያን ጊዜው በመቶዎች ዕጥፍ አድጎ ይሄውና ዛሬ ካሉት በታች ከሌሉትም በታች ሆኛለሁ፡፡ የቅርቡን ልደቱዬንም በሚገባ አስታውሳለሁ፡፡ ‹እንደበርናባስ ታስሮልኛል፤ እንደክርስቶስም ተገርፎልኛል፤ ተጠምቶልኛል፤ በሚጠሉት ተጠልቶልኛል…› በመጨረሻም ብዙ ሚሊዮን ብር ከቱጃሩ ሰውዬ ‹ተቦጭቆለት› – እንዳነበብኩትና እንደገመትኩት – ሊማርልኝና በዶክትሬቱ ደግሞ ተመልሶ “ዶክተር ልደቱ አያሌው፣ የፌዴራላዊት ብጥስጣሽ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ራስ-ገዝና ራሰ-አገዝ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትርና የዕድሜ ልክ ፕሬዝደንት እንዲሁም የጦር ኃይሎች ኤታ ማዦር የይስሙላ ሹምና የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረትና አንድነት ድርጅት ሊቀ መንበር፣ የሕወሓት የክብር አባልና የብኣዴን ነባር ሥውር ስፍ፣ የጽላትና የንዋየ ቅድሳት ሽያጭ አስተባባሪ ኮሚቴ ሊቀ መንበር … “ (ያኔ ሳላምን አሁን ገና አመንኩ!) እየተባለ  በወያኔያዊ ሠርጎ ገብነት በወጣትነቱ ያመሳትን ሀገር በወመሽነቱ ደግሞ ሊያምሳት እየተዘጋጀልኝ ነው ( ወመሽ – ወጣት መሳይ ሽማግሌ – ማለት ነው ወንድሜ)፡፡ ይህ ሸለምጥማጥ በጣፋጭ አንደበቱ ከሲሳይ አጌናና ጥቂት እሱን መሰል ጥንቁቅ ዜጎች በስተቀር 80 ሚሊዮኑን ሕዝብ እንዲያ ያነሆለለ እግዜር ካልጠበቀን በስተቀር አባ መላን የመሰለማ እንዴቱን ያህል አያነሆልለን? ይህን የምለው ለአባ መላ ትልቅ የቤት ሥራ ለመስጠት አስቤ እንጂ እንደልደቱ ወይም እንደሌሎች ልደቱን መሰል ብሽቅ ዜጎች ሊያታልለን ከጠላት መንደር ተልኮብናል ለማለት ፈልጌ አይደለም – ቤዛይቴን፡፡ ሥጋቴንና ጥርጣሬየን በጨዋ ደንብ የማቅረብ መብት ግን አለኝ፡፡ ለነገሩ አሁን ሰዓቱ ለአሥራ ሁለት ምናምን ጉዳይ በሆነበት ሁኔታ ማንም ማንንም ሊያታልል የሚችልበት ዕድል ያለ አይመስለኝም – ሁሉም ‹ባኗል› እህቴ፡፡ ትንሽ ነው እምትይው ሊስትሮው ወይም ድንጋይ ፈላጩ ሁሉን ያውቃል፡፡ ለነገሩ ባለዲግሪ ኮብልስቶን አንጣፊ ሞልቶም አይደል? አይ መንጌ – ‹የት እንደምታመሹ፣ ምን እንደምትበሉና እንደምትጠጡ… ብታምኑም ባታምኑም ሕዝቡ ያውቃል› ነበር አይደል ያላቸው ሚኒስትሮቹን ሰብስቦ? አዎ፣ ወያኔም ሁሉም ነገር ተባኖበታል – በአራዳ ቋንቋ ተነቅቶበታል ለማለት ነው፡፡ ቀሪው ሌላ ጉዳይ ነው – ሌላ፡፡

በትግርኛ አንዲት ቆንጆ አባባል አለች፡፡ “ዝአኽለን ጥኽነን በዓል ማርያም ትብላ” ትሰኛለች፡፡ እንዴት እንደምወዳት አትጠይቁኝ፡፡ በውርስ ትርጉም “የሚበቃትን ያህል ከፈጨች በኋላ ‹ውይ! ረስቼው፤ ለካንስ ዛሬ ማርያም ናት!› ትላለች” እንደማለት ነው፡፡ ሰዎች ነን፡፡ ሰዎች ከባድ ፍጡራን ነን፡፤ ውሻ ከሰው ይበልጣል፡፡ ትንኝ ከሰው በእጅጉ የተሻለ ፍጡር ነው፡፡ ውሻና ትንኝ ተፈጥሯቸውን ስተው በሣቅና በቃላት እያታለሉ የልባቸው እስኪደርስ አይሸምቁም፡፡ ፍቅራቸውም ጥላቻቸውም፣ ርቀታቸውም ቅርበታቸውም ግልጥ ነው፡፡ ድብቅ ባሕርይ የላቸውም፡፡ ሰው ግን አሳቻ ሥፍራና ምቹ ሁኔታ እንዲሁም ምቹ ጊዜ እስኪያገኝ አንተን ተመሳስሎ በመቆየት አደባይቶ የሚጥልህ አካይስት ፍጡር ነው፡፡ ‹ሰውን ከመምራት ወይም ከማስተዳደር  በአውላላ ሜዳና በዳገት ላይ የተበተኑ አንድ ሺህ ፍየሎችን መጠበቅ ይቀላል› እያልኩ ጓደኞቼ ፊት ዘወትርና እንዳስፈላጊነቱ የምናገረው ወድጄ አይደለም፡፡ እባብን ያዬ በልጥ ቢበረይ፣ ያበራሽን ጠባሳ ያዬ በእሳት ባይቀልድ ማንም ሊፈርድበት አይገባም፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን በመታለልና በመሸወድ ከዓለም እንዲያውም ከዚያ ባለፈ እንደኛ ሳንሆን አንቀርም – ወዳማርኛ የተመለሰው “የመጀመሪያው ቂጣ ቢያርር ሁለተኛው አያርም” የምንለው የሃድይኛው ተረታችን በኛ ዘንድ በጭራሽ አይሠራም – ሁሉም እንዳረረብን እንገኛለንና፡፡ ብዙ ጊዜ ብዙ ሰዎች አሞኝተውናል፤ ልባችንን በልተው በሞራና በአኞ እየተኩ ባዶ አስቀርተውናል፤ እምነታችንን ሸርሽረውታል፡፡ ከአሁን በኋላ ማንንም እንዳናምን እየተደረግን ያለነው አለማመን ጠባያችን ሆኖ ተደንግጎ ሳይሆን ማመናችን ገደል እየከተተን ለበርካታ ዓመታት ስለተጎዳንበት ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር አባ መላ ብዙ የሚጠብቀው አለና ቀን ከሌት የሚለፋበት፣ ባለፉት ሰባት ዓመታት ያስከፋውን ወገን የሚክስበት አስቸጋሪ ጊዜ ከፊቱ ተደቅኗል ላለማለት አልፈልግም፡፡ እሱን መሰሎችን ግዴለም እንመናቸው – ግን ማመናችን ጉድ እንዳይሠራን መቀየጃ እናብጅለት፡፡ (እርግጥ ነው – ጎራ ለዋጮች ከልባቸው ከመጡልን የጨዋታን ሕግ በመቀየር ለድል እስከማብቃት የሚደርስ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ እረዳለሁ – I mean, we may be fortunate to get gamechangers from among those Abbamelas who can shorten the time of our victory, if they honestly dedicate their entierity to the freedom fighting.)፡፡ በሌላ አቅጣጫ አዲስ ተጠማቂዎችም ወደተቃውሞው ጎራ ሲመጡ ‹የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ› እንደሚባለው እንዳይሆን ከፓትርያርኩ የበለጡ አጥባቂ ክርስቲያን  ላለመሆንና ሰው ዐይን ውስጥ እንዳይገቡ ጠንቀቅ ቢሉ ለነሱም ጥሩ ነው – ‹የሰው ዐይን ድንጋይ ይሰብራል› ይባላል፡፡ ትንሽ ዕውቀት መቼም መጥፎ ናት ‘more catholic than the Pope’ ሲባል እኮ ተሰምቶ ነው ፓትርያርክ ቅብጥርስ የምል፡፡ ይህ ነገር በዝርዝር ቢወራ አያልቅም ወገኖቼ፡፡ መታመን አስቸጋሪ ነው – ይሁንና ከማመን የበለጠ አስቸጋሪ እንደማይሆን እገምታለሁ፡፡ ምክንያቱም በማመንና ባለመታመን መካከል የሚወለደው ነገር ይበልጥ የሚጎዳው ታማኙን ሳይሆን አማኙን ነውና፡፡ እኔ ምን ዐውቃለሁ – ስሜት ነው፡፡

መድረኮችም ከዚህ አንጻር ብዙ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ‹ፊት የበቀለ ጆሮ እያለ ኋላ የመጣ ቀንድ በለጠ› እንዲሉ እንዳይሆን ወዶገቦችን ጥንቃቄ በተሞላት ሁኔታ ሊያስተናግዱ እንደሚገባቸው ማሳሰብ ምቀኝነት አይመስለኝም፤ እንደዚያ ሊታሰብም አይገባውም፡፡ ሹመትና መታመን አቀያያሚ ናቸውና በነዚህ ሁለት ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ኑባሬዎች ረገድ መጠንቀቅ መጥፎ አይደለም፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ ላይ ብዙ ተቃውሞ በርክቶ የነበረው ማንን ከማን ለይተው መሾምና መሸለም እንደነበረባቸው እመለየቱ ላይ መጠነኛ ችግር ስለነበረባቸው ነበር ይባላል – በዘመኑ የአማካሪነትን ዕድል ባላገኝም እኔም ይህ ስሜት ነበረኝ፡፡ እውነት ነው – ለነጻነት የተዋጉና ደማቸውን ያፈሰሱ ችላ ተብለው ጣሊያንን በባንዳነትና በሹምባሽነት ያገለገሉ አሰለጥ ዜጎች በአፍ ጂዶኣቸው ንጉሡን ጠርበው በመጣላቸው ምክንያት ተሹመው ነበር መባሉ እውነት ከሆነ ችግር አልነበረም ማለት አይቻልም፤ እንዲህ የምለው ለጥንቃቄ ያህል እንጂ አሁንም ልድገመው በአባ መላ ወይም በመሰል ወዶገቦች ላይ ምቀኝነት ይዞኝ አይደለም፡፡ እውነቴን ነው – ‹አገባሻለሁ ያለ ላያገባሽ ከ(ሁነኛ) ባልሽ ሆድ አትባባሽ› ይባላልና ወዶገብም ወዶ አልገብም ሁሉም በየፊናው ራሱን ቢመረምር ከተደጋጋሚ ጸጸትና ጥቃት እንጠበቃለን፡፡ የሚያልፍ ጊዜ የማያልፍ ትዝብት ያስከትላልና ፍቅርንም ሆነ ጥላቻን በገደብና በመለኪያ ብናደርገው ከኋለኛ ነዳማ ወይም ቁጭት ነጻ እንሆናለን፡፡ ካጠፋሁ እታረማለሁ – ኧረ የምን መታረም ብቻ – ዝም ልልም እችላለሁ፡፡ እንዴ፣ በዚህ ነገር እኮ ብዙ ተሰቃየን!

ወደተቃውሞው ጎራ የሚመጡልን ወገኖቻችን ደግሞ ከልብ እንዲመጡልን መጸለይ ይገባናል፡፡ አመጣጣቸው ምክንያታዊ እንጂ ግብታዊ እንዳይሆንም እነሱም እኛም ሁላችንም መጸለይ አለብን፡፡ ሲመጡ መሠረታዊ የአስተሳሰብና የአመለካከት ልዩነት ካልኖራቸውና በተራ ቂምና በተራ ጠብ ከሆነ ወይንም የአሁንና የወደፊት የኃይል ሚዛን አሰላለፍን በታሳቢነት በያዘ መልኩ ለሥልታዊ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ጠቀሜታ ከሆነ ተጎጂዎቹ ይበልጡን እኛው ጭቁኖቹ ነን – እነሱ አይጎዱም የሚል እሳቤ የለኝም፤ እንክትክት ብለው ይጎዳሉ፡፡ የጉዳታቸው መጠን እንዲያውም ከመጀመሪያው በባሰ ይሆንና የቀዳሚ ስህተታቸውን ዕዳ ሁሉ ደርበው የሚከፍሉበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል – ስለዚህ የበለጠ ተጠንቃቂዎች እነሱ ሊሆኑ እንደሚገባ እረዳለሁ – እንደ አካሄድ፡፡

የማንወሻሽበት አንድ ነገር አባ መላን እንድጠይቅ ቢፈቀድልኝ ደስ ይለኛል – መለስ ከሞተ በኋላ ወደኅሊናህ ለመመለስ ምን አነሳሳህ?(የተመለስከው ከመለስ ሞት በፊት ከሆነ ግን ትልቅ ይቅርታ!) ሳይሞት ብትመለስ አይቻልም ነበር ወይ? ባክህ እንግሊዝኛ አማረኝ – well, መቼም ቢሆን መመለሱ ምንም ማለት አይደለም ይሆናል፡፡ ግን እስከምትመለስበት ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስቃይና የወያኔ ጀብደኝነት እንዴት ሳይታይህ ቀረ? ምን አሳወረህ – ጥቅም? ዝና? ተሰሚነት አጣለሁ የሚል ሥነ ልቦናዊ ችግር? የሕዝቡ ከቦታ ቦታ ፍልሰትና ወደውጪ ስደት፣ ሞት፣ እሥራት፣ የአንድ ዘር ፍጹማዊ የበላይነት፣ የሀገሪቱ በጎጥና በቋንቋ መሸንሸን፣ በአማራው ላይ የታወጀው የዘር ፍጅት፣ የጥቂቶች አለቅጥ መክበር፣ የብዙኃን አስከፊ ድህነት ውስጥ መግባት፣ የድንበር እየተቆረሰ ለባዕዳን መሸጥ፣ የገበሬው መፈናቀልና መሬቱ ለውጭ ባለሀብቶች መሰጠት፣ … በጥቅሉ የወያኔ በኢትዮጵያ ላይ ጢባጢቤ መጫወትና እንደልብ መፈንጠዝ ሳይከሰትልህ እስከመለስ ሞት ድረስ የመቆየትህ ምሥጢር በእውነቱ ምን ይሆን? እማምላክን – አባ መላን መጠራጠሬ አይደለም፤ ግን አንዳች ነገር ጠይቀው ጠይቀው አለኝ፡፡ አንድ ክፉ ነገር እስኪገባን ስንት ጊዜ መፍጀት ይኖርበት ይሆን? – ‹ረሀብ ስንት ቀን ይፈጃል – ነበር ያለው ጋሼ ፀጋዬ ገ/መ ዋቀዮ? አሁንስ የተመለስከው በእውነት ነውን? የብዙ ሰው ጥያቄ ስለሆነ ሳትንቀንና በምንምነትህ ሳትታበይ ብትመልስ(ልን/ኝ) መልካምና ወቅታዊም ነው – ሰውን አክባሪነትህንም ያመለክታል፡፡ አለበለዚያ ኅሊናችን የማያርፍልን ድንጉጥ ዜጎች እንጎዳብሃለን፡፡ እንደምታስታውሰው ክርስቶስ በምሳሌው ሲናገር መቶ በጎች ያሉት ሰው አንዷ ብትጠፋበትና … ራስህ ጨርሰው ወንድማለም፡፡ አዎ፣ አንዱ ለጠቅላላው ብቻ ሣይሆን ለግለሰብም መጨነቅ አለበት፡፡ ለተጨባጩ ግለሰብ ካልተጨነቅን ለረቂቁ ጥቅል ማኅበረሰባዊ ሕይወት እንጨነቃለን ማለት ውሸትና ታይታዊ ነው፡፡ ‹አጠገብህ ያለውን ወንድምህን የማትወድ ሆነህ ሳለ በመልክ በቁመት የማታየውንና የሩቁን እግዚአብሔርን እወደዋለሁ ብትል ከትዝብት በስተቀር ምን ታተርፋለህ?› የተባለውን ቁም ነገር እናስብ፡፡ እኔን በእኔነቴ የማይወደኝ ማንም ቢሆን ሀገሬንና ሕዝቧን አይወድም – አራት ነትብ፡፡ እኔን ሳይወድ ሀገርና ሕዝብ እወዳለሁ የሚል ሀሰተኛ ነው፡፡

የፈሰሰ አይታፈስም፡፡ አንዳንድ መያዣ መጨበጫ የሌላቸው ‹ቁም ነገሮችን› የወረወርኩ ይመስለኛል፡፡ ሁሉም ነገር ደግሞ በአንድ ቀን አያልቅም፡፡ ያስከፋሁት ወገን ካለ ይቅርታ የምጠይቀው ከልብ ነው – ባለፉ ደብዳቤዎቼ ከኃይሌ ገ/ሥላሤና ከዚያች መልቲ ጀማነሽ ሶሎሞን ጋር ‹ተጣልቻለሁ›፤ ዛሬ ደግሞ ከማን ጋር እንደተጣላሁ አላውቅም – የልደቱ ከጠብ አይቆጠርም – እስስትና ዓሣማ እንጂ ሰው አይደለምና፡፡ በመሰለህ ጊዜ አስተሳሰብህን ትለውጣለህ፤ በመሰለህ ጊዜ የመሰለህን ትናገራለህ ወይ ትጽፋለህ፤ ሲርብህ ካገኘህ ትበላለህ፤ እንቅልፍህ ሲመጣ ቦታ ካለህ ትተኛለህ፡፡ በቃ፡፡ ለምን አስተሳሰብህን ለወጥህ፤ ለምን ተናገርህ ወይ ጻፍህ፤ ለምን በላህ፤ ለምን ተኛህ … አይባልም፡፡ ብዙ ነገሮች የተፈጥሮ ሂደቶች ናቸው፡፡ መልስ መስጠት የሚያስፈልግህ ነገር ከገጠመህ እንዳመጣጡ ልትመልስ ትሞክራለህ፤ ሌሎች ያላቸው የቋንቋ ችሎታ አንተም ጋ በብዛት ስላለ በንዴት ከመንተክተክና በምናብ የሸሚዝ እጅጌህን ከመሰብሰብ ይልቅ ቋንቋህን በመጠቀም ጠላትህን በቃላት ‹ማደባየት› ትችላለህ፡፡ ግን እውነት ትኑርህ – ትንሽም ብትሆን የእውነትን ዘገር ካልያዝክ በመጨረሻው ወዳቂ ትሆናለህ – ምናልባት ውዳቂም፡፡ ‹ለምን ተነካሁ፤ ምን ሲባል ተደፈርኩ›ም አትበል፡፡ ይህን ለማለት አንተ ማን ነህ? በምድር ጠቅላላ የጊዜ ሥሌት መሠረት የአንተ ምድራዊ ዕድሜ ቢታይ ከአንዲት ቅማል የማትሻል መሬታዊ ገጸ ባሕርይ መሆንህን አትርሳ – የዕድሜህ አንጻራዊ መጠን ከተወርዋሪ ኮከብ የሰብኣዊ ዐይን ዕይታ የሚዘል አለመሆኑን ተገንዘብ፤ ይህችን ቅጽበታዊ ዕድሜያችንን ደግሞ ለመጥላትና ለመቀያየም ሣይሆን ለመዋደድና ለመፈቃቀር ብናውላት የማይሞት ስምና ዝናን ከመገንባት አንጻር ብዙ እንጠቀማለን፡፡ ዛሬ አለህ ወይም ያለህ ይመስልሃል – ከአፍታ በኋላ ግን እዚህ አጠገብህ አይተኸው በቅጽበት እንደሚጠፋ ጉም ነህና ራስህን ብዙም አክብደህ አትየው፡፡ ሁሉም ያልፋል – አንተም፡፡ ዘና በልና ዓለምን ቃኛት፡፡ የልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ልጅ ንጉሥ ሶሎሞን እንዳለው ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለምና በሚሆነው ሁሉ አለልክ አትደነቅ፡፡

 

AAAAAAAAAA

 

መብራት ጠፍቶ ከመጣ ከ8 ሰዓት በኋላ የታከለ ሃሳብ፡፡ ሰበር ዜና፡- ወያኔ አደጋ ለማድረስ እንዳሰበ ፍንጭ ሰጠ፡፡

የደሴዋ ዕብድ ‹የተነበየችው› ትዝ አለኝ፡፡ ‹ነገ ቤት ይቃጠላል!› አለች – ያቺው የደሴዋ ዕብድ፡፡ በማግሥቱ ብዙ ቤቶች ተቃጠሉ፡፡ ሁኔታው ሲመረመር ቤቶቹን ያቃጠለችው ለካንስ ያቺ እንደትናንትና ከተማውን እየዞረች ‹ነገ ቤት ይቃጠላል!› ያለችዋ ዕብድ ነበረች፡፡ ሴትዮዋ እንደወያኔ ዐውቆ አበድ ስለነበረች ያልተጠበቀ ኪሣራ አስከተለች – ሰውንም አስገረመች፡፡ የቆዬ እውነተኛ ታሪክ እንደሆነ ይነገራል፡፡

ወያኔ ዛሬ እንዳስታወቀው በመጪው ዐርብ ‹አሸባሪዎች› አደጋ ለማድረስ ዝግጅታቸውን ጨርሰዋል – ‹ወፍ ነግራዋለች› ማለት ነው፡፡ ‹የሽብር ጥቃቱን መታቀድ› ወያኔ በሚገባ ዐውቋል – ‹አሸባሪዎቹ› ለልብ ዐውቃው ወያኔ አማክረውትም ሊሆን ይችላል፡፡ ስላወቀም ከ30 ለሚበልጡ ኤምባሲዎች አስታውቋል – ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በማሳሰብ ጭምር፡፡ ወያኔን ‹ሂድና ሌላህን ብላ› በሉት እባካችሁን፡፡ እንደወያኔ ጀዝባና ደንቆሮ በዓለም ላይ የለም፡፡ ስንትና ስንት የከሸፉ ድራማዎችን የፈበረከው ወያኔ ሰሞኑን ለሚፈጥረው የሽብር ተግባር – ሊያውም ‹ዕድል ገጥሞት› ሁኔታዎች የሚመቻቹለት ሆኖ አደጋው የሚፈጠር ከሆነ – ሙስሊሞችን ተጠያቂ ለማድረግ የተዘጋጀ ይመስላል፤ ምሥኪን ሙስሊሞች – መንግሥትም ስማቸውን የሚጠቀም ሌላ ጅራቱን ውጭ ያሳደረ አክራሪ አካልም በመሀል አጣብቀው ሊያንገላቷቸው አቅደው ከሆነ ፈጣሪ ለንጹሓን ዜጎች ሲል ተራዳኢነቱን ቀድሞ ያሳየን፤ ዓለም የደረሰችበት የጭካኔ ትርዒት ትዕይንት አስከፊ በመሆኑ ብዙ ነገሮችን መገመትና መጠርጠር ይቻላል፡፡ እግዜር ባይጠብቀንና እንደወያኔ ተንኳሽነት ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያችን እስካሁን ከኢራቅ፣ አፍጋኒስታንና… ጎን ስሟ በየቀኑ የሚዲያዎች አፍ ማሟሻ በሆነ ነበር፡፡

የወያኔው ሞግዚት ታላቋ ሀገር አለኝ በምትለው መረጃ መሠረት የኤምባሲ ሠራተኞቿን ከ19 እስላማዊ ሀገሮች በማስወጣት ላይ እንደሆነች በዚሁ ሣምንት ተገልጧል፡፡ ጅሉ ወያኔም የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ወደዚሁ ዓለማቀፍ ሁኔታ በመጎተት ራሱ የሚፈጥረውን የሽብር ተግባር ከዓለማቀፉ ‹የሽብር ጥንስስ› ጋር ለማመሳሰል እየሞከረ ነው፡፡ ይቀናው ይሆን? የሁለት ቀን ዕድሜ ከሰጠን የምናየው ይሆናል፡፡ የገበያ ግርግር ለቀጣፊ ያመቻልና የታላቋን ሀገር የልብ ትርታ ለመግዛት ወያኔ በዕቅዱ ከገፋበት አደጋ አለው፡፡ እሱ ይሁነን፡፡

ለማንኛውም ወያኔ እንደለመደው ራሱ አሸብሮ ንጹሓን ዜጎችን በሽብርተኝነት በመክሰስ የጫካ ፍርዱን ሊያስተላልፍባቸው እንዳቆበቆበ ተረድተን የሚሆነውን በንቃት መከታተላችንን እንቀጥላለን፡፡ ሴትዮዋ ‹ወንዶቹ እንዳሳደሩን› እንዳለችው እኛም ወያኔዎቹ እንዳሳደሩን የመጪውን ዐርብ ሁኔታ ልናይ በጉጉት እየተጠባበቅን አለን፡፡ መልካም ዐርብ፡፡

ግን ግን እስላምና አማራ እየተባባልን የወያኔን ዕድሜ የማቱሣላን ያህል ማስረዘማችን እኔን መሰሉን ሞኝ ፍጡር ሳያስገርም እንዳልቀረ ሳልጠቁም መቅረት አልፈልግም፡፡ በዚህ አንገብጋቢ ወቅታዊ ጉዳይ ጥቂት ምክሮችን ብሰነዝር አልጠላም፡፡ እናም የወቅቱ ፋሽን በሆነው ሙስሊሞች ዐርብ፣ ዐርብ  ወያኔን በ‹ጩኸት›ና በ‹መፈክር› ‹ተዋጉት‹፤ ካቶሊክና ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ደግሞ ዕሑድ፣ ዕሑድ በ‹አንተ ያመጣኸውን አንተው መልሰው› የኪሪያላይሶን ጸሎት ‹ተፋለሙት›፤ ፕሮቴስታንቶች ቅዳሜ፣ ቅዳሜ በመንታ በመንታ እያነባችሁ ወያኔን ተግትጉት፣ ባለዛሮችና ባለአውሊያዎች በከሚስና በከድር ሁሴን የሐሙስና የቅዳሜ፣ የረቡዕ አብዶዬ ጅላሌና የማክሰኞ ኑራሁሴን መጀን በናንተ የአዶከርቤ ወዳጃ ፈጣሪ የምትሉትን ጠዝጥዙት፣ ኢአማኒያንና ጥዩር ምሁራን በብሔረ ብርጭቆ የክርክርና የፍልስፍና ቱማታ ውስጥ በትጋት በመሣተፍ በሞኝ አንግሥ የውጭና የሀገር ውስጥ ቁንድፍቶች(ኪል ሚ ኲክ) ተጀቡናችሁ የ‹ቢሆን ኖሮ› ሎጂካችሁን አሞስኩ፣… ኦሮሞዎች በመሪ የመታገያ ድርጅቶቻችሁ በነኦነግ፣ ኦብነግ፣ኦብኮ፣ኦፌዴን፣ኦህዴድ፣ ኦልማ፣ ኦስሌድ፣ኦቅሌድ… አማካይነት ወያኔን ሸጥሽጡት፣ ወዲታት ተጋሩ በአረና፣ በቲፒዲኤም፣ በትልማ፣ በኤፈርት…ሥር ተደራጅታችሁ ወያኔን ፈስፍሱት፣ አማሮችና ከኢትዮጵያ በስተቀር ጎጣዊ መጠሪያ አድራሻ  የሌላችሁ ምሥኪኖች ደግሞ በአርበኞች ግምባር፣ በኢሕአሠ፣ በአብግን፣ በኢሕዲን፣ በአድብን፣ በብአዴን፣ በበረከት ስምዖን፣ በኅላዌ ዮሴፍ፣ በአያሌው ጎበዜ፣ በአበጀ በለው፣ በአልማ፣ በወልማ፣ በጎልማ፣ በሸልማ፣ በደልማ፣… ሥር እየተደራጃችሁ ወያኔን መቆሚያ መቀመጫ አሳጡት፤ ጉራጌዎችና ሥልጢዎች በጉሕዲግ፣ በጉልዲግ፣ በጉምዲክ፣… ሥር እየተዋቀራችሁ ይህን ከፋፋይ ዘረኛ የወያኔ ‹መንግሥት› መተንፈሻ አሳጡት… ያኔ ምን አለ በሉኝ ወያኔ ድራሹ ይጠፋል፤ የኢትዮጵያ ትንሣኤም ይበሠራል፡፡

በቃ – ቢገባንም ባይገባንም አንድ ነገር እናስታውስ፡፡ በአንድ ጊዜ አንድም መቶም እየሆን ወያኔን አናሸንፍም ብቻ ሣይሆን ዝምቡን እሽ ማለት አንችልም፤ ይህችን ስለሚያውቁ በልዩነታችን የአፍዝ አደንግዛዊ ኃይል በመሳለቅ አውዳሚ አገዛዛቸውን እስከዓለም ፍጻሜ ለማቆየት ሁለ ገብ ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ዋና ንድፍ አውጪው ሰውዬኣቸው እንኳን ሞቶ አስደናቂው የኛ ቂልነት በመቀጠሉ ምክንያት ብቻ ይሄውና ካለግልጽ አመራር ሀገሪቱን እያበሻቀጧት በውር ድንብር እስካሁን ይዘዋታል – የሚገርም ልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው፡፡ ዋናው መሃንዲስ ከሞተ በኋላ በነርሱ ግዛት ለአንዲትም ቀን ልታድር የማይገባት ሥልጣን በተቃውሞው ጎራ መልፈስፈስና አለመተማመን እንዲሁም በአስተማማኝ ሁኔታ በተለይ በሀገር ውስጥ አለመደራጀት ምክንያት በዚህን ዓመት ሐምሌ ሰባት አንድ ዓመቷን ደፍና ሁለተኛዋን ያዘች – ከነርሱው ጋር እንደተንገላታች፡፡ ለአገዛዛቸው ምቹ ሆነን እስከተገኘን ድረስ ደግሞ በቅጡ ተደራጅተው ሌላ መለስ እስኪፈጥሩ ድረስና ከዚያም ባለፈ ለመቶዎች ዓመታት ይቺው በሸርሙጣነት የምትመሰል ሥልጣን ከነርሱው ጋር እንዳለች እስመለዓለም ትኖራለች፡፡ አንድና አንድ ብቻ ስንሆን ወያኔን እናሸንፋለን – አንድና አንድነት ደግሞ በግድ የሃሳብ ተመሳሳይነትን፣ የአመለካከት ፍጹማዊ መሳነትን አይጠይቅም – አንድነት የነጻነት ትግልን አስፈላጊነት ያጠይቃል እንጂ የሃሳብ ግዳዊ ቁርኝትን መሠረት አያደርግም፡፡ በነጻነት አስፈላጊነትና በሀገር ሉዓላዊነት አንድና አንድ ለመሆን ግን እንደገና መፈጠር የሚኖርብን ይመስለኛል – እርግጥ ነው በ‹ይመስለኛል› ተስፋ አንቆርጥም፤ አስተሳሰብን መቃኘትና አመለካከትን ማስተካከል ይቻላልና፡፡ በአካል ሳይሆን በአስተሳሰብ እንደገና ለመፈጠር ፈቃደኛ የሚሆን ማን ነው? ይህን እግዜር ይወቅ፡፡ ሰላም ለኢትዮጵያና ሕዝቧ! ስደት ወደ ኢትዮጵያ የሚሆንበት ዘመን …

 

እስከማዕዜኑ እግዚኦ ትረስዐኒ ለግሙራ፤

እስከማዕዜኑ ትመይጥ ገጸከ እምኔየ፡፡

እስከማዕዜኑ አነብር ኀዘነ ውስተ ነፍስየ፡፡

ወትጼዕረኒ ልብየ ኵሎ አሚረ፡፡

እስከማዕዜኑ ይትዔበዩ ጸላእትየ ላዕሌየ፡፡

ነጽረኒ ወስምዐኒ እግዚኦ አምላኪየ፡፡

አብርሆን ለአዕይንትየ ከመ ኢይኑማ ለመዊት፡፡

ወከመ ኢይበሉኒ ጸላእትየ ሞዕናሁ፡፡

ወእለሰ ይሣቅዩኒ ይትፌስሑ ለእመ ተሀውኩ፡፡

ወአንሰ በምሕረትከ ተወከልኩ፡፡

ይትፌሥሐኒ ልብየ በአድኅኖትከ፡፡

እሴብሖ ለእግዚአብሔር ዘረድአኒ፡፡

ወእዜምር ለስመ እግዚአብሔር ልዑል፡፡

የዳዊት መዝሙር 12


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>