ዮፍታሔ
የሕወኀት አገዛዝ በዚህ ሳምንት የአቶ አንዳርጋቸውን ምስል በ“ኢትዮጵያ ቴለቪዥን” አሳይቶናል። ሕወኀት ይህን በማሳየት ምን ለማስተላለፍ እንደፈለገ በመጠኑ መዳሰስ መልካም ነው።
በመጀመሪያ ነገር አቶ አንዳርጋቸውን አግቶ መውሰዱን በተደጋጋሚ በቃል አቀባዮቹ ዲና ሙፍቲና ጌታቸው ረዳ አማካኝነት ሲያስተባብል የነበረ አገዛዝ ያስገደደው ወይም ቪዲዮውን በመልቀቅ ለማስተላለፍ የፈለገው ሳይኖር ይህን እንደማያደርግ መገመት ቀላል ነው። ሲያስተባብል ከአንድ ሳምንት በላይ የቆየ “መንግሥት” ወዲያው ደግሞ አቶ አንዳርጋቸው “በቁጥጥር ሥር” ውሎ ኢትዮጵያ መሆኑን በ“ጠቅላይ ሚኒስትሩ” በኩል በተናገረ በማግስቱ የአቶ አንዳርጋቸውን ምስል በቴለቪዥን አሳይቶናል።
ሕወኀት ይህን ለምን አደረገ? አራት ዋና ዋና ምክንያቶችን በቀላሉ ማቅረብ ይቻላል። ሌሎችም ከዚህ በፊት ተጠቅሰዋል። ወደፊት የምንደርስባቸውም ይኖራሉ።
የመጀመሪያው ሕዝቡና ተቃዋሚዎች በሚያዩት ነገር ተስፋ ቆርጠው እንዲያፈገፍጉ ለማድረግ፤ ሁለተኛ አቶ አንዳርጋቸውንና ከርሱ ጀርባ የተሰለፉትን ተቃዋሚዎች በሕዝብ ፊት አጣጥሎና አሳንሶ ለማሳየት፤ ሦስተኛው በተቃዋሚዎች መካከልና በሕዝቡና በተቃዋሚዎች መካከል ጥርጣሬ እንዲፈጠር ለማድረግ፤ አራተኛው ደግሞ በሕዝቡና በአገዛዙ ደጋፊዎች ሳይቀር እየተቀጣጠለ ያለውን የትግል ስሜት “ተመልከቱ ጨካኝ አይደለሁም፤ በአንዳርጋቸው ላይ ያደረስኩት ጉዳት የለም” በማለት ለማብረድ የሚሉ ናቸው። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የሕወኀትን ስሌት በመጠቆም ሁላችንም በነዚህ ወጥመዶች እንዳንገባ ለማሳሰብ ነው።
ቪዲዮውን በአጭሩ እንመልከተው። በ “Facebook” በመጀመሪያ የተለቀቀው ዜና (http://www.youtube.com/watch?v=oBxG4pTRNWA) የሚጀምረው የአቶ አንዳርጋቸውን ስም በመግደፍ ነው። የመጀመሪያዋን “አ” ፊደል በ “እ” በመቀየር “በጥብቅ ሲፈለግ የነበረው እንዳርጋቸው” ይለናል። መቸም ይህን ያህል “በጥብቅ ሲፈለግ የነበረ”፣ ከፖሊስ እስከፍርድቤቶች፣ ደኅንነትና ጦር ሠራዊት ድረስ አበጥሮ የሚያውቀውን ሰው ጋዜጠኛው ስሙን እንደማያውቅ ሆኖ ተሳስቶ ያነበዋል ማለት የማይታሰብ ነገር ነው። ዜናው በስቱዲዮ የሚሠራ እንደመሆኑ ቢሳሳት ኖሮ እንደገና ተስተካክሎ ሊቀረጽ የሚችልበትም እድል ነበረው። ያ ግን አልተደረገም። ምክንያቱ ሆን ብሎ የተደረገ እንደሆነ እንድንጠረጥር የሚያደርግ ነው። ይህ የተደረገው አቶ አንዳርጋቸውን ዝቅ ለማድረግም ብቻ አይደለም። እውነት ነው ይህን በማድረግ ስሙን አሉታዊ ትርጉም እንዲኖረው ለማድረግም ተሞክሯል። ነገር ግን ከዚህ ሁሉ በላይ ‘አንድአርጋቸው’ የሚለው ስም በሕዝቡ ዘንድ የአንድነት ስሜት በመፍጠር ትልቅ መነሣሣትን እየፈጠረ እንደሆነ አገዛዙ ተረድቷል። ጋዜጠኛው የአቶ አንዳርጋቸውን ስም በኋላ ሁለት ጊዜ አስተካክሎ ቢጠራውም አንዴ እንዳርጋቸው በኋላ አንዳርጋቸው እያለ መጥራቱ የአቶ አንዳርጋቸው ስም ‘በሚገባ እንኳን የማይታወቅ፤ ምንም ትርጉም የሌለው’ እንደሆነ ሲነግረን ነው። ይህን ስም አገዛዙ በቀጥታ በቴሌቪዥን እንዲጠራው ቢገደድም አስተካክሎ በመገናኛ ብዙኀን መጥራቱ የአንዳርጋቸው ስም በሕዝቡ ዘንድ የፈጠረውን ስሜት እንደመቀበልና እንደማበረታታት አድርጎ እንደተመለከተው በአስተማማኝ መገመት ይቻላል። ይልቁንም አብዛኛው አማርኛ ቋንቋን የሚረዳ ኢትዮጵያዊ በሚገኝበት በገጠራማው የአገራችን ክፍል ሕዝቡ አንድአርጋቸው የሚለውን ስም በሚሰማ ጊዜ የሚፈጠርበትን የጥቃትና የመነሣሣት ስሜት ሕወኀት ጠንቅቆ ያውቃል። ይህ ደግሞ አብዛኛው የኢትዮጵያ ገጠራማው ክፍል ከአገዛዙ መገናኛ ብዙኀን ውጪ ስለማይደርሰው ይህን ስም ከዚህ ቀደም አያውቀውም ከሚል ስሌት የመነጨ ነው። ስለዚህ ሆን ብሎ የአቶ አንዳርጋቸውን ስም አንዴ እንዳርጋቸው በሌላ ጊዜ አንዳርጋቸው ብሎ አደናጋሪ በማድረግ ከጠራ በኋላ በሌሎችም ተጨማሪ ‘የባዕድ’ ስሞች እንደሚጠራ ደግሞ ዘረዘረልን።
መቸም ሕወኀትን ለሚያውቅ እነዚህን ተጨማሪ የቅጽል ስሞች የዘረዘረው ለተጨማሪ መረጃ ነው ለማለት አይደፍርም። ነገር ግን መደበኛ የመረጃው አካል በማስመሰል ‘ስሙ አንዳርጋቸው የሚባል ቢሆንም ወገናችሁ እንዳይመስላችሁ እርሱ የፈረንጅ ስሞችን ጨምሮ በሌሎችም ስሞች የሚጠራ ከሀዲ ነው’ ለማለት ነው። “የሌሎች አገሮች ፓስፖርት መያዝ አያስጥልም” በማለት በዜናው የተጨመረውም ከማስፈራሪያ ሌላ “ዜግነታቸውን የቀየሩ” ለማለት እንደሚሆን መገመት ይቻላል። እንግዲህ ማጣጣልና ማንኳሰሱ ከዚህ ይጀምራል። አገዛዙ ያልተረዳው ግን የአንዳርጋቸውን ትክክለኛ ስም በመሸሽና በማሳሳት ሕወኀት በሕዝብ አንድነት ላይ ከፍተኛ ፍርኀት እንዳለው ቁልጭ አድርጎ ያሳየ መሆኑን ነው። ከዚህም በተጨማሪ የአንዳርጋቸው ትክክለኛ ስም ይህ ነገር ከመፈጠሩም አስቀድሞ በአገሪቱ እንደቋያ እሳት የተዛመተ መሆኑን ከሕዝቡ ጋር በቅርብ የሚኖሩት ካድሬዎች ያላደረሱት መሆኑን እንገነዘባለን።
ከዚያ በመቀጠል “በጥብቅ ሲፈለግ የነበረው” በማለት በመቶ ሺህ ጦር ሠራዊትና የጦር ጀት አለኝ የሚለው አገዛዝ የአቶ አንዳርጋቸው ድርጅት ምን ያህል የሚያስፈራው መሆኑን ራሱ በተዘዋዋሪ ሲመሰክር ይደመጣል። ምነው ይህ ድርጅት እንዲህ ሕወኀት የሚፈራውን ያህል ሆኖ በተገኘ ብለን የምንጓጓው በዚህም ምክንያት ነው።
በመቀጠል ‘የስለላ ድርጅቱ አስቀድሞ የአቶ አንዳርጋቸው የጉዞ ቀንና ፕሮግራም ደርሶት ከየመን ባለሥልጣናት ጋራ ባደረገው የተቀናጀ ሥራ’ በየመን ታግቶ “በዕለቱ” ወደኢትዮጵያ እንደተወሰደ ይናገራል። “አቶ አንዳርጋቸውን ለምን አገትከው?” እንጂ ‘በምን መረጃ ያዝከው?’ ብሎ አገዛዙን የጠየቀው ሳይኖር “የጉዞ ቀኑና ፕሮግራሙ አስቀድሞ ስለደረሰኝ” ያለበት ምክንያት የመረጃ ድርጅቱን ጀብዱ ብቻ ለመግለጽ ነው ማለት የዋህነት ነው። ከዚህ ይልቅ ‘የአቶ አንዳርጋቸውን የጉዞ መረጃ ማን አሳልፎ ሰጠ?’ በማለት በተቃዋሚዎች ላይ ሌሎች ተቃዋሚዎችና ሕዝቡ ጥርጣሬ እንዲፈጠርባቸው ለማድረግ እንደሆነ መገመት ይቻላል።
“በዕለቱ ወደኢትዮጵያ ተወስዷል” ያለበት ምክንያት ደግሞ እስካሁን የአቶ አንዳርጋቸው ድርጅት የሆነው ግንቦት ሰባት አቶ አንዳርጋቸው ከየመን ወደኢትዮጵያ ተላልፎ የተሰጠበትን ቀን በሚመለከት ሲያስተላልፈው የነበረውን “ውሸት ነው” ለማለትና ሕዝቡ ‘ለምን አቶ አንዳርጋቸው ከመጀመሪያው እንደታገተ አልተነገረንም?’ በሚል በድርጅቱ ላይ ቅሬታ እንዲፈጠርበት ለማድረግ ነው። የግንቦት ሰባት ድርጅት እንደማንኛውም ድርጅት በየጊዜው እያስተካከላቸው የሚሄዱ አሠራሮች ሊኖሩት ቢችልም ከአቶ አንዳርጋቸው መታገት ጋራ በተያያዘ ያደረጋቸውን ውሳኔዎች በሚመለከት የምንወያይበት ጊዜ ላይ ያለመሆናችንን ልብ ማለት ያስፈልጋል። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ የግንቦት ሰባትም ሆነ የሌላ የፓለቲካ ድርጅት አባል አይደለም። ሆኖም ከአጠቃላይ ሂደቱ ግንቦት ሰባት የወሰዳቸው ውሳኔዎች ከመልካም ዝንባሌ መሆናቸውን ለመገመት ይቻላል የሚል እምነት አለው።
አቶ አንዳርጋቸው ወደሚታይበት ምስል እንሂድ።
በመጀመሪያ ነገር የአቶ አንዳርጋቸው ምስል፣ የአፉ እንቅስቃሴና ድምፁ አንድ ላይ አይሄድም። ይህን ለመረዳት ፊልሙን በቅርበት መመልከት ብቻ ይበቃል። ይህ ማለት ድምፁ ለብቻ ምስሉ ለብቻ ነው የተቀረጸው ማለት ነው። ይህም ብቻ አይደለም። ምስሉ ተቆራርጦ የተቀጣጠለ ነው። አቶ አንዳርጋቸው በጠቅላላ የሚታየው ለ 0፡42 ሰከንድ ሲሆን (ማለትም በጠቅላላው በዜናው ቪዲዮ ከደቂቃ 0፡57 – 1፡39) በዚህ ጊዜ ውስጥ ይህ እርሱ የሚታይበት ፊልም ቢያንስ 5 ጊዜ ተቆርጧል። የተቆረጠበት ቦታ በቅደምተከተል፦
- አቶ አንዳርጋቸው ሰው ጨብጦ እጁን ሙሉ ለሙሉ ከመሰብሰቡ በፊት (በዜናው ቪዲዮ 0፡59 ሰከንድ)
- ድምፁ በእንግሊዝኛ “I was really really exhausted/ በጣም ደክሞኝ ነበር” ብሎ እንዳበቃ – በዜናው ቪዲዮ 1 ደቂቃ ከ20 ሰከንድ ላይ (1፡20)
- ድምፁ “ተረጋግቸ ያለሁበት ዓይነት ሁኔታ ነው ያለው” በማለት ላይ እያለ (1፡25)
- “ምንም ዓይነት despair (ተስፋ መቁረጥ) የለም” ካለ በኋላ (1፡34)
- “የመጨረሻ እርጋታና እረፍት ውስጥ ነው ያለሁት” ካለ በኋላ (1፡38)።
ከዚህበኋላአቶአንዳርጋቸውለአንድሰከንድፈገግሲልይታይናፊልሙያበቃል።
አቶ አንዳርጋቸው በዚህ ቪዲዮ ለ “ወንጀል ምርመራ” ቃል እየሰጠ ሳይሆን በሚገባ ከሚያውቀው ሰው ጋራ እየተጫወተ እንደተቀረጸ የሚያመለክት ፍንጭም ከዚሁ ጋራ ተያይዞ ይገኛል። ምክንያቱም አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ፈገግ ሲል የሚታይባት በመጨረሻ የተቀጠለችው የአንድ ሰከንድ ቪዲዮ ትክክለኛ ቦታ የሚመስለው በመጀመሪያ ከሚታየው ከእጅ መጨባበጡ በኋላ ነው። ነገር ግን አገዛዙ የሚያውቀውን ሰው እንደጨበጠ ተመልካቹ እንዳይጠረጥርና “አቶ አንዳርጋቸው ከወዳጁ ጋር የተጫወተውን እንደማስረጃ ቀርጾ አቀረበ” በሚል እንዳይወነጀልና “መረጃ”ውም ውድቅ እንዳይሆን የዚህን ጨካኝ ትዕይንት መጨረሻ ለማለስለስ ሲል ፈገግታውን ቆርጦ በመጨረሻ ወስዶታል። አገዛዙ የሚያቀርበው ነገር በሕዝብ ዘንድ አስቀያሚና የአገዛዙን ጭካኔ የሚያሳይ እንደሆነ ያውቃል። ያንን በተቻለ ለማለዘብ መግቢያውን በመጨባበጥ አድርጎ መዝጊያውንም በአቶ አንዳርጋቸው ፈገግታ አድርጎታል።
ዓላማው በ“ሰላምታ” ጀምሮ በአቶ አንዳርጋቸው ፈገግታ በመጨረስ ተመልካች ይህን መንፈስ በአእምሮው ይዞት ከትእይንቱ እንዲለይ ማድረግ ነው። ይህ ያነጣጠረው ደግሞ በሕዝቡና በአገዛዙ ደጋፊዎች ሳይቀር እየተቀጣጠለ ያለውን የትግል ስሜት “ተመልከቱ ጨካኝ አይደለሁም፤ በአንዳርጋቸው ላይ ያደረስኩት ጉዳት የለም። በሰላም ስንጨብጠው እርሱም ፈገግ ሲል እዩ” በማለት ለማብረድ መሆኑ አይጠረጠርም። ነገር ግን ይህ ቪዲዮ የተቀረጸው በአቶ አንዳርጋቸው ላይ ከፍ ያለ ድብደባና ጉዳት ከመድረሱ ቀደም ብሎ ባሉት ቀናት ሊሆንም የሚችል መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል። ይህን የሚያጠናክርልን የአቶ አንዳርጋቸው ጺም ነው። ከእንግሊዝ በተነሳበት ቀን ጺሙን ተላጭቶ ነበር ብለን ብንነሳ በፊልሙ ላይ የሚታየው የጺሙ እድገት ፊልሙ የተቀረጸበት ጊዜ ከእንግሊዝ በተነሣ ከ3 እስከ 5 ባሉት ቀናት ውስጥ እንደነበረ በቀላሉ እንድንገምት ያደርገናል። ያ ደግሞ ገና በመጀመሪያ በታገተበት ሰሞን መሆኑ ነው። ይህም ብቻ አይደለም። ይህ ሲጨብጠው የሚታየው ሰው “ወዳጅ”ነቱ ተቀባይነት እንዲኖረውና ተፈላጊውን ውጤት እንዲያስገኝ አንዳርጋቸውን ሊያገኘው የሚችለው ወደኢትዮጵያ በገባበት ሰሞን ነው። ከዚያ በኋላስ አቶ አንዳርጋቸው የት ነው ያለው? ከዚህ ቀደም በድብደባ ጉዳት ያደረሰበት አገዛዝ ዛሬስ ምን እያደረሰበት ነው? ማናችንም ይህን አናውቅም። ከዚህም በተጨማሪ ማሰቃያ መንገዶች ሁሉም በአካል ላይ በጉልህ የሚታዩ አይደሉም። እነዚህ ማሰቃያ መንገዶች አንዳንዶቹ ከድብደባም የሚብሱ እንደሆኑ በግልጽ ይታወቃል። አንድን ሰው በቪዲዮ ብቻ አይቶ ይህ የተፈጸመበት መሆኑንና ያለመሆኑን መናገር አይቻልም። ይህ ባልታወቀበት ሁኔታ ትግሉን አፋፍሞ ከመቀጠል በስተቀር ሌላ ምርጫ የለም።
አቶ አንዳርጋቸው ከሚያውቀው ሰው ጋር እየተነጋገረ እርሱ ሳያውቀው የተቀረጸ ስለመሆኑ ሌሎችንም ጠቋሚ ማስረጃዎች ማቅረብ ይቻላል። ከአቶ አንዳርጋቸው አጠቃላይ ንግግር መረዳት የሚቻለው ለመርማሪ ቀጥተኛ ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ሳይሆን አስተዛዛኝ ለሆነ አስተያየት መልስ የሚሰጥ መሆኑን ነው። “ይህ ችግር መድረሱ ያሳዝናል! አይዞህ!” የሚል ዓይነት አስተያያት ተሰንዝሮለት “እኔ በጣም ደክሞኝ ነበር። እንዲህ መሆኑ ለበጎ ነው/ It is a blessing in disguise ምክንያቱም እረፍት እፈልጋለሁ። ምንም ቅሬታ የለኝም። በልቤ ውስጥ ተስፋ መቁረጥም የለም” በማለት ለዚህ ዓይነት አስተያየት ተገቢ የሆነ መልስ ሲሰጥ ነው የምናዳምጠው። ባለቤቱና ቤተሰቦቹ ንግግሩ እውነተኛ የአቶ አንዳርጋቸውን ተፈጥሮ የሚያመለክት ስለመሆኑ በአሜሪካ ድምፅ ሬድዮ ቀርበው የገለጹት ትክክለኛ የሆነበት ምክንያትም አቶ አንዳርጋቸው እየተቀረጸ መሆኑ ሳይገለጽለት ከሚያውቀው ሰው ጋር ይነገገር ስለነበረ ነው።
ፊልሙን በቅርበት ደግሞ እንየው። የፊልሙ ጥራት፣ የተቀረጸበት ቦታና ብርኃን የደበዘዘና የጨለመ መሆኑ አቶ አንዳርጋቸውን እንደ“ወንጀለኛ” እንዲታይ በተመልካቹ ዘንድ ድባብ ለመፍጠርና ጀግናውንና ከጀርባው የቆመውን ድርጅት በሕዝብ ዘንድ አሳንሶ ለማሳየት መሆኑ አይጠረጠርም። አቶ አንዳርጋቸው “የሆነው ነገር ለበጎ ነው/It is a blessing in disguise። እኔ በውስጤ ቅሬታ የለም። እረፍት ይሰማኛል” ሲል በማሳየት ሁሉም የያዘውን ትግል ተስፋ በመቁረጥ እንዲተው ማድረግ ሌላው የፊልሙ ዓላማ ነው። ነገር ግን እርሱ በትክክል ያስተላለፈው የተሟላ መልእክት “መታሰርህ ያሳዝናል!” ለሚል የ”ወዳጅ” አስተያየት “በጣም ደክሞኝ ስለነበር እንዳርፍ እድል አገኝበታለሁ። ተስፋ መቁረጥ ግን በልቤ ውስጥ የለም” የሚል ነው። ማንም ደጋግሞ ቪዲዮውን በዚህ መንፈስ ቢመለከተው ያለጥርጥር በተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ አይቸገርም። ለዚህም ነው ከዚህ በኋላ ምንም ዓይነት ከዚህ የተለየ “መረጃ” በአገዛዙ ቢቀርብልንም ልንቀበለው የማንችለው። ምክንያቱም አቶ አንዳርጋቸው በእንዲህ ዓይነት መጎሳቆል ውስጥ ሆኖ እንኳን “በልቤ ውስጥ ተስፋ መቁረጥ የለም” በማለት እቅጩን ተናግሯልና። ወደፊት ከዚህ የተለየ ነገር ብንመለከት ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰበት አመልካችና ትግሉን እንደቋያ እሳት በስፋት የሚያቀጣጥለው ብቻ ነው የሚሆነው።
የአቶ አንዳርጋቸው ጺም ማደጉ ብቻ ሳይሆን በድምፁም ላይ ለውጥ እንዳለ መገንዘብ ይቻላል። ከዚህ ጺሙን የሚላጭበት ጊዜና ቦታ እንዳይኖረው ከመንፈግ ጀምረው ካደረጉት ድርጊትና በድምፁ ላይ ከምናስተውለው ለውጥ በነዚህ በመጀመሪያዎቹ ቀናት እንኳን ምን ያህል እንደተጎዳ መገመት ይቻላል። ይህም ብቻ አይደለም። እጁ ብቻ የሚታየውን ሰው በሚጨብጥበት ጊዜ የአቶ አንዳርጋቸውን የእጅ እንቅስቃሴ በቅርበት ማስተዋል ያስፈልጋል። ከላይ እንደተጠቀሰው ፊልሙ የተቆረጠው አቶ አንዳርጋቸው እጁን ሰብስቦ ከመጨረሱ በፊት ነው። ከዚህም በላይ በሚጨብጥበት ጊዜ ከተቀመጠበት ለመነሳት የፈለገ ቢመስልም በትንሹ እንኳን ብድግ ሊል አልቻለም። ለምን እጁን ሰብስቦ ሳይጨርስ ፊልሙ ተቆረጠ? በምስሉ ከሚታየው የሰውነቱ ክፍል በታች ምን ደርሶበታል? እነዚህንና የመሳሰሉትን ነገሮች ስናስብ የኢትዮጵያው አገዛዝ ጭካኔ አንድ ቀን እንኳን ሊያስተኛን አይገባም።
እንግዲህ አገዛዙ ያቀረበልን ዜና ይህን ይመስላል። ይህን ፊልም ለ92 ሚሊዮን ሕዝብ እንደማስረጃ ማቅረብ ከውርደትም በላይ ውርደት ነው። ይሁን እንጂ ሕወኀት ይህን ፊልም በማሳየት “ማስረጃ” ነው ለማለት ከፈለገው ይልቅ በቪዲዮው ለሕዝቡ ሊያስተላልፈው የፈለገው የፕርሮፖጋንዳ መልእክት አመዝኖ ነው የሚታየው። ሊያስተላልፈው የፈለገው መልእክት ከላይ በአጭሩ እንደተገለጸው ግልጽ ከሆነ ሕዝቡና ተቃዋሚዎች እርሱ ያዘጋጀውን የፕሮፖጋንዳ ወጥመድ ሰባብረው በመሻገር ትግሉን ማጧጧፍ ይጠበቅባቸዋል።
በፓለቲካ ትግል የአቶ አንዳርጋቸው መታገትና መንገላታት የፈጠረውን የመሰለ ዕድል ብዙ ጊዜ የሚገኝ አይደለም። አንዳርጋቸው ጽጌ በሠራው አንጸባራቂ ሥራ ጀግንነቱን በታሪክ ምርጥ ከሆኑት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች መካከል አድርጓል። እርሱ መላ ሕይወቱን የሰጠበትን ትግል ከፍጻሜ በማድረስ ሁላችንም ድርሻችንን መወጣት ይጠበቅብናል። ስለዚህ እጅ ለእጅ ተያይዘን ወደፊት እንግፋ።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!