Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የአማርኛ ሰዋስው ንፅፅራዊ ምልከታ – (ከቋንቋ መምህራን)

$
0
0

 እንደመግቢያ

ይህ ስራ ባዬ ይማም (1987/2000)ን እና ጌታሁን አማረ (1989)ን የሚመለከት ነው። ጽሁፋችን ከባዬ ስራ ይልቅ የ“ጌታሁን አማረ” ስራ ላይ ያተኮረ ነው። ባየ ይማም እና ጌታሁ አማረ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባልደረቦች ናቸው። የባዬ ስራ ሁለት ጊዜ ታትሟል። የመጀመሪያው በ1987፣ ሁለተኛው የተሻሻለው እትም ደግሞ  በ2000 ወጥቷል። በጌታሁን ስም የቀረበው እስከ 2002 አስር ጊዜ ታትሟል/ተባዝቷል። በእዝባር ተባዝቷል ያልንው የመሻሻል ህትመት (Revised edition) ስላልሆነ ነው። የባዬ የመጀመሪያ ህትመትና የጌታሁን 10ኛ እትም ዋቢ መረጃ የሚከተሉት ናቸው፤ (1) ባዬ ይማም። 1987። የአማርኛ ሰዋስው።አዲስ አበባ፤ የትምህርት መሳሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት ማተሚያ ቤት። እና (2) ጌታሁን አማረ። 1989/2002። ዘመናዊ የአማርኛ ሰዋስው በቀላል አቀራረብ። አዲስ አበባ፤ አልፋ አታሚዎች። (ለተጨማሪ መረጃ ከዚህ መጣጥፍ መጨረሻ ላይ ዋቢጽሁፍ የሚለውን ክፍል ይመልከቱ።)

Pen-4ሊነሱ ይችላሉ ብለን የምናስባቸውን ሁለት ጥያቄዎች ከመነሻው ግልፅ እናድርግ። አንደኛ፣ እነዚህ መፅሀፎች ከታተሙ በርካታ አመታትን አስቆጥረው ሳለ አሁን ላይ ማንሳቱ ለምን አስፈለገ ነው። ሁለተኛው፣ እውነት በተለይ በጌታሁን የታተመው ዘመናዊ የአማርኛ ሰዋስው በዚህ ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት ለግምገማ የሚበቃ ስራ ነው ወይ የሚል ነው። ምክንያታችን ከትምህርት ጥራት ጋርና ዘመናዊ የአማርኛ ሰዋስው በቀላል አቀራረብ ለተማሪዎች ካለው አሉታዊ ተምሳሌትነት ጋር የተያያዘ ነው።

የትምህርት ጥራት እያሽቆለቆለ መምጣቱ ብቻ ሳይሆን ባሁኑ ግዜ በተማሪዎች ስራ ላይ እየታየ ያለው ግልበጣ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህ ሁኔታ ለዶክተሬት ድግሪ ማሟያ የሚቀርቡ ስራዎችንም ይመለከታል። ሁለትና ሶስት ቃላት በመለወጥ የራስ አድርጎ ማቅረቡ በጣም እየተዘወተረ ነው። እንደዚህ ሲደረግ ብዙውን ግዜ ምንጩ ቢጠቀሰም አንዳንዴ እስከጭራሹም ምንጩ የማይገለፅበት ሁኔታ አለ። አሳሳቢው ጉዳይ፣ ጥቅል ስራው ብቻ እየተጠቀሰ በራስ ስራ ላይ ማስገባቱ መለመዱ ብቻ ሳይሆን ስህተት መሆኑን በአድራጊው ያለመቀበሉ ነው። ዛሬ ተማሪዎችን ይህን ለማስተው መቸገር ብቻ ሳይሆን ድርጊቱ ትልቅ ወንጀል መሆኑን ለማሳመን ያልቻሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የቋንቋ መምህራን አምርረው ይናገራሉ። ተማሪዎች አግባብ ባልሆነ መልኩ የገለበጡት ነገር ስህተት መሆኑን ላለመቀበል አብዛኛውን ጊዜ ማጣቀሻቸው በጌታሁን አማረ የታተመው ዘመናዊ የአማርኛ ሰዋስው በቀላል አቀራረብ  ከባዬ ይማም የአማርኛ ሰዋስው ጋር ያለው መመሳሰል ነው።

መምህራኑ ከሩቅ ሳይዘሉ እዚያው በእዚያው ከመቀዳዳት አልፎ በዚህ ድርጊታቸው የማያፍሩ ከሆነ እንዴት አድርጎ ተማሪውን ከሰው መቅዳት ትክክል እንዳልሆነ ማስረዳት ይቻላል? ጉዳዩ  በርግጥ  የማሳመንና የመለወጥ ብቻ አይደለም ─ግልበጣ በየትኛውም (የትምህርት) አለም ወንጀል ነው። ወንጀልነቱ ደግሞ በእድሜ ገደብ የሚፈታ አይደለም። የዛሬ ሀያ አመትም ሆነ ሀምሳ አመት የተከናወነ ስርቆት ዛሬ ላይ ቢታወቅ ሰውዬው በአካል ካለ ከተጠያቂነት አያመልጥም።

በርግጥ የትምህርት ስርቆት ብዙውን ግዜ ፍርድቤት አስቁሞ ወህኒ አያስወርድም። ስርቆት የተረጋገጠበት ሰው ግን ከማናቸውም ትምህርት ነክ ስራዎች እንዲገለል መደረግ ብቻ ሳይሆን ስርቆት ባለበት ስራ የተገኘ ድግሪ ከሞተም በኋላም ቢሆን መነጠቅ ያስከተላል። በቅርቡ የጀርመን የመከላከያ ሚኒስትር ላይ የደረሰውን ማስታወሱ የሚበቃ ይመስለናል። የዛሬ ተማሪዎቻችን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ድግሪውን ወስደው ከአመታት ቆይታ በኋላ ቢነጠቁ ምን እንደሚሰማቸው ካሁኑ እናስበው።

ይህ ስራ በሁለቱ መጽሀፎች ላይ ጥልቅ ግምገማ አያደርግም። አላማው ችግሩን በግልፅ በማሳየት የሚመለከተው ክፍል፣ የዩንቨርሲቲው አስተዳደርም ሆነ ትምህርት ሚንስቴር፣ የራሱን ማጣራት አድርጎ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ ለማሳሰብ ነው። ጽሁፉ ለሚመለከተው ክፍል እንዲደርስ ይደረጋል።

የመፅሀፎቹ መመሳሰልና መለያየት

የእነዚህ መጽሀፎች መመሳሰል ምኑ ላይ ነው የሚል ጥያቄ መነሳቱ ግድ ይላል። ይህን ጥያቄ የምናነሳው ግን መፅሀፎቹን ጨርሶ ያላየናቸው ከሆነ ብቻ ነው። መፅሀፎቹን ያየ የሚጠይቀው እነዚህ ስራዎች የሚለያያቸው ነገር ምንድነው የሚለውን ነው። በእርግጥ መፅሀፎቹን ያሳተሙት ሁለት የተለያዩ እውናዊ ሰዎች መሆኑን ያላወቀ፣ በብዕር ስም አንዱ ሰው ሌላውንም ያሳተመ ነው የሚመስለው። እስቲ የተወሰኑ ነጥቦችን እንመልከት።

ከባዬ መቅድም የሚከተለውን እናገኛለን፤

“አማርኛ በትምህርትነት መሰጠት የጀመረው ገና ዱሮ ነው። በዚያን ዘመን፣ ችግሩ የተሰማቸው እንደ ብላታ መርስዔ ሀዘን ወልደ ቂርቆስና እንደ ተክለማርያም ፋንታዬ ያሉ ሊቃውንት ካዘጋጁዋቸው ሁለት መፃህፍት ሌላ፣ ዛሬ ምንም ነገር የለም ለማለት ይቻላል። እነዚህም ቢሆኑ በይዘታቸውም ሆነ ባመለካከታቸው ለዛሬው ዘመን ትምህርት በቂ አይደሉም። ብዙ ይጎድላቸዋል። ….

“የስርዓቱ ትምህርት ካንደኛና ከሁለተኛ ደረጃ አልፎ በየኮሌጁ መሰጠት ከጀመረ በርካታ አመታትን ቢያስቆጥርም፣ በዚሁ ቁዋንቁዋ ተዘጋጅቶ የቀረበ መደበኛ ማስተማሪያም ይሁን መመሪያ ወይም ማጣቀሻ መፅሀፍ አሁንም በብቃት የለም። ባለመኖሩም ትምህርቱ የሚሰጠው የተለያዩ የስ-ነልሳን ሰዎች በልዩ ልዩ  የውጭ ቁዋንቁዋዎች ስለ ቁዋንቁዋው ከፃፉዋቸው የምርምር ስራዎች ላይ እየተቀነጨበ በሚወጣ ተበታኝ ወረቀት አማካኝነት ነው። ይህም በመሆኑ፣ መምህራን በተቀያየሩ ቁጥር የትምህርቱ ይዘትና አቀራረብ እንደመምህራኑ ዳራ እና እንደሚያጋጥማቸው የምርምር ስራ ሲቀያየር ኖሮአል። በዚህም ምክንያት የአንዱ ዘመን ተማሪ የተማረውን፣ የሌላው ዘመን ተማሪ አያገኘውም። ስለዚህም ተመጣጣኝ ችሎታና ግንዛቤ ያላቸውን ተማሪዎች ማፍራት ሲያስቸግር ቆይቶአል። ከዚህ ችግር ለመውጣት የሚቻለው፣ አንድ ወጥ የሆነ የማስተማሪያ መፅሀፍ በባዕድ ቁዋንቁዋ ሳይሆን፣ በዚሁ ቁዋንቁዋ ሲዘጋጅና ሁሉም በዚህ መነሻነት እያስተማረ ተፈላጊውን ግንዛቤና የአጠቃቀም ክህሎት ሲያዳብር ነው።

“እነሆ፣ በዚህ መፅሀፍ ለማድረግ የተሞከረውም ይኸው ነው። አንድ  ወጥና አጠቃላይ የሆነ የአማርኛ ሰዋስው ማዘጋጀት” (ባዬ 2000: xxvii)።

ከላይ ከቀረበው ከባዬ አንድምታ/ተጠየቅ ጋር ሁሉ ሰው ይስማማል ማለት አይደለም። በአማርኛ የተጻፈ የአማርኛ ሰዋስው በብዛትና በብቃት አለመኖሩ  ትክክል ቢሆንም፣ በዩንቨርሲቲው  ቋንቋውን የሚያጠኑ ተማሪዎች ተመጣጣኝ ችሎታና ግንዛቤ እንዳይኖራቸው ያደረገው በአማርኛ የተጻፈ የስዋስው መጽሀፍ በብቃት አለመኖሩ ነው የሚለው ተቀባይነት የሚኖረው አይመስለንም። “መምህራን በተቀያየሩ ቁጥር የትምህርቱ ይዘትና አቀራረብ እንደመምህራኑ ዳራ እና እንደሚያጋጥማቸው የምርምር ስራ ሲቀያየር ኖሮአል” የሚለው የባዬ አስተያየት እንደጥፋት የሚታይ ሳይሆን በዩንቨርሲቲ ደረጃ የሚጠበቅ ነው። መምህራኑ ለሚያስተምሯቸው ኮርሶች በየጊዜው ከተለያዩ የምርምር ስራዎች ሀሳብን እየጨመቁ ማስተማር ይጠበቅባቸዋል። በየጊዜው አዳዲስ ከሚወጡ የምርምር ስራዎች ጋር እራሳቸውን ማስተዋወቅ ብቻ ሳይሆን ኮርሶቻቸውንም ማደስ ይገባቸዋል። እንኳን በዩንቨርሲቲ ደረጃ በቅድመ-ዩንቨርሲቲ ትምህርት በአንድ ወጥ የማስተማሪያ መጽሀፍ (Textbook) የሚማሩ፣ ማስተማሪያ መጽሀፎቹ በየጊዜው ቢበዛ በአራትና በአምስት አመት መታደስ ግድ ይላቸዋል። እንደባዬ አይነት አጋዥ መጽሀፍ በዩንቨርሲቲ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የትምህርት ደረጃ መኖሩ አስፈላጊነቱ የሚያጠያይቅ ባይሆንም፣ “ተመጣጣኝ ችሎታና ግንዛቤ ያላቸውን ተማሪዎች [ለ]ማፍራት [...] አንድ ወጥ የሆነ የማስተማሪያ መፅሀፍ በባዕድ ቁዋንቁዋ ሳይሆን፣ በዚሁ ቁዋንቁዋ ሲዘጋጅና ሁሉም በዚህ መነሻነት እያስተማረ ተፈላጊውን ግንዛቤና የአጠቃቀም ክህሎት ሲያዳብር ነው” የሚለው የባዬ አስተያየት ተቀባይነት አይኖረውም። የዩንቨርሲቲ ትምህርት በዚህ፣ ባዬ ባለው መልክ የሚሄድ አይደለም። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማር-ማስተማር ፍልስፍናም በአንድ ወጥ የማስተማሪያ መጽሀፍ (Textbook) ተማሩ የሚል አይደለም። እንደውም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ከሁለተኛ ደረጃና ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ተቋማት የትምህርት አሰጣጥ የሚለያቸው አንዱና ዋንኛው ነገር በአንድ ወጥ የማስተማሪያ መጽሀፍ የማስተማርና ያለማስተማር ጉዳይ ነው።

ከላይ የባዬን መግቢያ ቀንጭበን ሰፊ ትንታኔ የሰጠንው አስተሳሰቡ የባዬ የራሱ መሆኑን ለማሳየት ነው። ጌታሁን ይህን የባዬን ግላዊ አመለካከት እንዴት የራሱ አስመስሎ  እንዳቀረበው እንመልከት።

“የአማርኛ የሰዋስው ትምህርት ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ሲሰጥ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ትምህርቱ መሰጠት የተጀመረበትን ጊዜና ለትምህርቱ የተዘጋጁትን መፃህፍት ስናነፃፅር ዝግጅቱ በየወቅቱ ከሚገኝ የሰዋስው ንድፈ ሃሳብ ጋር እየተጣጣመ ሲያድግ አልታየም። በተለይም መርስኤ ሃዘን  ወልደ ቂርቆስ (1948)ና ተክለማርያም ፋንታዬ (1964) ካዘጋጇቸው መፃህፍት በኋላ ባየ ይማም በ1987 ዘመናዊ የሰዋስው መፅሀፍ እስከታተመበት ድረስ የአማርኛን ሰዋስው ለማስተማር የተዘጋጀ የሰዋስው መፅሃፍ አልታየም። የምክነት ዘመን ነበር ማለት ይቻላል። በዚህም ምክንያት ተማሪዎቹ የቋንቋ መምህራን እራሳቸው እንደተማሩበት የዘመንና የቦታ ልዩነት የተለያየ ዳራ ይዘው ይገኛሉ። በዚህ ሁኔታ አንድ አይነት ቀርቶ የተቀራረበ ግንዛቤ ያላቸው ተማሪዎችን ማፍራት አይቻልም። ለዚህ ችግር መፍትሄ የሚሆነውና የሰዋስውን ትምህርትም ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚበጀው ከዘመናዊ የሰዋስው ንድፈ ሃሳብ በተጣጣመ ዘዴ ማስተማሪያና መርጃ መፅህፍትን (sic.) ማዘጋጀት ነው። በዚህ መፅሃፍ ዝግጅትም የተደረገው ይኸው ነው” (ጌታሁን 1989:vi)።

ከላይ በቀረቡት ጥቅሶች መሀከል ያለው መመሳሰል በሀሳብ ብቻ አይደለም። በአባባልም ነው። ለምሳሌ መዝጊያቸውን ብቻ እንመልከት፤ “በዚህ መፅሀፍ ለማድረግ የተሞከረውም ይኸው ነው” (ባዬ)፣ “በዚህ መፅሃፍ ዝግጅትም የተደረገው ይኸው ነው” (ጌታሁን)። በርግጥ በጥቅሶቹ መሀከል ልዩነትም አለ። በጌታሁን የቀረበው አጠር ያለ ከመሆኑም በላይ በአንዳንድ ቃል ከባዬ ተለይቷል። አሳጥሮና ቦታ ቀይሮ ማቅረብ በጌታሁን በታተመው በዘመናዊ የአማርኛ ሰዋስው በቀላል አቀራረብ በሁሉም ምዕራፎችና ንኡሳን ክፍሎች የሚታይ ነው። መስረቅ የለመደ … ካልሆነ በስተቀር እንዴት ሰው መግቢያ ሳይቀር ከሌላ ይገለብጣል?

ከመግቢያው ዘለል ብለን የባዬን “ምዕራፍ አንድ ስነድምፅ”፣ ገጽ 1 እንመልከት፤  “ማንኛውም ቁዋንቁዋ መሰረቱ ድምጽ ነው” (ባዬ 2000:1)። ማንኛውም ቋንቋ መሰረቱ ድምጽ አይደለም። መስማት የተሳናቸውና መናገር የተሳናቸው የሚጠቀሙባቸው በርካታ የምልክት ቋንቋዎች በአለማችን አሉ። ድምጽን አእምሯዊ ካላደረግንው በስተቀር እነዚህ ቋንቋዎች ድምጽ የላቸውም። እንደማንኛውም ቋንቋ ግን ስርእት አላቸው። ይህን የባዬን ብያኔ ጌታሁን፣ እሱም በመጀመሪያ ገጹ በ“ምእራፍ አንድ ስነድምፅ” ላይ እንደሚከተለው ያቀርበዋል፤ “ቋንቋ መልዕክት ማስተላለፊያ መሳሪያ ነው። … ለመልእክት ማስተላለፊያው ቋንቋ መሰረቱ ድምጽ ነው ለማለት ይቻላል” (ጌታሁን 1989:1)። ጌታሁን የባዬን ሀሳብ የራስ ለማስመሰል ባደረገው ለውጥ የበለጠ  ስህተት ውስጥ መውደቁን ልብ ይሏል።

ባለቤቱ ይደርስብኛል ብሎ ተጣድፎ የሚጠቅመውን የማይጠቅመውንም አግበስብሶ እንደሚዘርፍ ሌባ፣ በባዬ ላይ የታዩ ጉልህ ስህተቶች (ሳይቀሩ) የበለጠ “ጣፍጠው”ና የራስ መስለው በጌታሁን በታተመው ስራ ላይ ይገኛሉ። መጽሀፎቹ  ከይዘታቸው መመሳሰል በላይ ጭንቅላት በማይጠይቀው በምሳሌ እንኳ አይለያዩም። ገና ከመነሻው ከምዕራፍ አንድ የመጀመሪያ ገጽ ሳናልፍ ይህን ያህል መመሳሰል ካገኘን ውስጡ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ከዚህ በላይ እያንዳንዱን ነጥብ ማንሳቱ አንባቢን ማሰልቸት ብቻ ሳይሆን መቆምያው በእነደዚህ አይነት አጭር መጣጥፍ አይሆንም። ተጨማሪ ዝርዝር የሚመለከተው ክፍል ከፈለገ በራሱ የባለሙያ ኮሚቴ አቋቁሞ ማስገምገም ያስፈልገዋል። ሌላው አንባቢ ከዚህ ባለፈ በዝርዝር ማወቅ ከፈለገ መጽሀፎቹን ተመልክቶ የራሱን ግንዛቤ እንዲወስድ መተዉ ይሻላል።

የአማርኛ ሰዋስውና ባዬ

በላይኛው ክፍል ከባዬ ስራ ጋር የማንስማማባቸውን አንዳንድ ነጠቦች አንስተናል። ስህተት የመሰሉንን ብቻ ሳይሆን በእርግጠኝነት ስህተት ናቸው ብለን ልናወጣ የምንችላቸው ሌሎች ነጥቦችም አሉ። ለምሳሌ ጉልህ ስህተት ከምናገኝባቸው ውስጥ ቁጥርና የጊዜ ስርዓትን መጥቀስ ይቻላል። ከአንድ ስራ የማይስማሙበትን ነጥብ ማግኝትና ስህተት መልቀም ከባድ አይደለም። ቁምነገሩ ስህተት የሆነው ነገር የሚታረምበትን መንገድ በጨዋ ደንብ መጠቆምና ቢቻል ደግሞ አለኝ የሚባለውን ማሻሻያ ራሱን በቻለ ስራ ማቅረብ ነው።

እስካሁን በሚታወቀው፣ የአማርኛን ሰዋስው ጉዳዬ ብለው ከተሰሩት ውስጥ ቀደምቱ የእዮብ ሉዶልፍ/Hiob Ludolf (1698) ስራ ነው። ከዚህ በማስከተል በጥራትም ሆነ ሰፊ ጉዳይ ዳስሰው በጥልቀት ከተሰሩት ውስጥ የ19ኛው ክፍለዘመን  የፕሬቶሪየስ/Praetorius (1879) እና የቅርብ ጊዜው የዎልፍ ሌስላው/Wolf Leslau (1995) የአማርኛ  ሰዋስው መጽሀፎች ግንባር ቀደሙን ስፍራ የሚይዙ ይመስለናል።

የባዬ ስራ በበኩሉ በአማርኛ ደረጃ የራሱ የሆነ ትልቅ ታሪካዊ ቦታ አለው። እያንዳንዱ አረፍተ ነገር በጥንቃቄ መታየት የሚገባው የፀሀፊው ብስለት የታየበት ስራ ነው። ባዬ በአማርኛ እንግዳ የሆነ ፅንሰ ሀሳብን እንኳ ሲገልፅ፣ አንድ ቦታም አንባቢን የሚያደናቅፈው ነገር አይገኝም። በትንታኔውም እያንዳንዱን በራሱና በገባው መንገድ ለመስጠት ሞከረ እንጅ ልጥፍ ነገር አላመጣም። ካለማጋነን፣ ምናልባትም፣ የባዬን የአማርኛ ሰዋስው  ያህል በሌሎች የሀገራችን የቋንቋ ምሁራን ላይ ተፅእኖ ያሳደረ ስራ ያለ አይመስለንም።  ባሁኑ ግዜ በሀገራችን ልጆች ከድግሪ መመረቂያ ጽሁፎች ጀምሮ እስከ መጻህፍት ድረስ ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል የባዬን መንገድ ተከትለው የተሰሩ ስራዎችን ማግኘት አይከብድም። ለምሳሌ የአንበሳ ተፈራን/Anbessa Teferra (2000) የሲዳምኛ ሰዋስው እና የተስፋዬ ተወልደን/Tesfaye Tewolde (2002) የትግርኛ ሰዋስው መጥቀሱ በቂ ይመስለናል።

የባዬ ሰዋስው በአማርኛ መቅረቡ የራሱ የሆነ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። እስከምናውቀው ድረስ፣ በአማርኛም ሆነ በማናቸውም የሀገራችን ቋንቋ (ግዕዝን ጨምሮ) የባዬን ያህል ጥልቅ የሰዋስው ትንታኔ በማቅረብ የተዘጋጀ ስራ እስካሁን ድረስ የለም። በዚህ ብቻ ለትምህርት ትኩረት የሚሰጥ አካል፣  ለባዬ ትልቅ ሽልማት ሊሰጠው በተገባ ነበር። ይህ ስለመደረጉ የምናውቀው ነገር የለም። በሀገራችን እንደዚህ የሚያደርግ የመንግስት አካልም ሆነ በጎ አድራጊ ድርጅት ጨርሶ ስለመኖሩም  የምናውቀው የለም። ችግሩ ሀገራችን ያለችበት የኢኮኖሚ ደረጃ ነውና ለምን ይህ አልተደረገም ብለን ወቀሳ የምናቀርብበት ጉዳይ አይደለም። ሽልማቱ ቢቀርበት፣ ከስርቆት ግን ልንጠብቀው ይገባል። የባዬ ስራ ተገቢውን ስፍራ ይዞ መቆየት እንዲገባው የሁሉም ስራ መሆን አለበት።

መደምደሚያ

በጌታሁን የታተመውን ዘመናዊ የአማርኛ ሰዋስው በቀላል አቀራረብ ተማሪዎች  “ባዬ በቀላል አቀራረብ” ይሉታል። ይህ ቅፅል የወጣለት ገና መፅሀፉ እንደወጣ አካባቢ ቢሆንም እስካሁን ስሙ እንዳለ ነው። ገና የመጀመሪያ ድግሪ ያልያዘ ተማሪ የመፅሀፉን መመሳሰል በቀላሉ የለየበት ሁኔታ እያለ ሌላው ምሁር እንዴት ዝም አለ የሚለው በጣም የሚገርም ይሆናል። የሁሉንም ልብ መርምሮ ምክንያቱን ማወቅ ባይቻልም፤ ልንገምት የምንችለው ነገር ግን አለ።

አንድም በሌባና በተሰራቂው መሀከል ያለው ግንኙነት ነው። በጌታሁን በታተመው ዘመናዊ የአማርኛ ሰዋስው በቀላል አቀራረብ  የጀርባ ሽፋን ላይ አስተያየት ሰጪው ባዬ ይማም ነው፤ “ከመምህሩ ደቀ መዝመሩ እንዲሉ፣ እኔ በቀላሉ ልገልፃቸው ያልኳቸውን ፅንሰ ሀሳቦች አቶ ጌታሁን በሚገባ ሊገልፃቸው ችሏል” (ዘመናዊ የአማርኛ ሰዋስው በቀላል አቀራረብ  ከጀርባ ሽፋን ላይ የተወሰደ)። የሰዉ ዝምታ፣ “የተሰረቀው ሰው አቤት ማለት ቢቀርበት ለድርጊቱ ቡራኬ ከሰጠ እኔ ምን አገባኝ” በሚል ስሜት ሊሆንም ይችላል።

ሁለትም፣ ኢትዮጵያዊው ይሉኝታ ነው ─“አብሮ  በሚሰራ ሰው ላይ እንዴት እንደዚህ ይፃፋል” በሚል ይሉኝታ። በጌታሁን በታተመው በዘመናዊ የአማርኛ ሰዋስው በቀላል አቀራረብ ጀርባ ላይ የባዬም የሙገሳ አስተያየት መስጠት ከዚሁ ከይሉኝታ የመነጨ ይመስለናል። ገንዘብ የተበደረው ደረቱን ነፍቶ ሲሄድ አበዳሪው የሚያፍርበት ባህል ነው ያለን።

እንደባዬ አይነት እንደ እንቁ ልንጠብቀው የሚገባንን ምሁር የዋህ ይሉኝታውን ተጠቅመው ሲዘርፉት ዝም ማለት ከማናችንም የሚጠበቅ አይመስለንም። ጉዳዩ፣ አንድ ሌባ መስረቁ ሳያንሰው ተበዳዩን በይሉኝታ አጥሮ ቡራኬ እንዲሰጠው ከማድረጉ ወይም ከኢኮኖሚ ጥቅም ጋር ብቻ የሚታይ አይደለም። የትምህርት ጥራት ላይ ትኩረት እናድርግ ሲባል ለትኩረቱ በመጀመሪያ ቅድሚያ የሚሰጠው ሌብነትን ማስወገድ ነው። ሌብነት በትምህርት አለም ትልቁ ወንጀል ነው። ባለቤቱ ስላላመለከተ ወይም ስላልተቃወመ ተብሎ የሚተው ጉዳይ አይደለም። የትምህርት ጉዳይ የሚመለከተው ክፍል ሁሌም እርምጃ መውሰድ አለበት። ያ ካልሆነ፣ በሀገር ደረጃ ሳይቀር ይህ ድርጊት መጥፎ ስም የሚያሰጥ ነው የሚሆነው።

ዋቢ ጽሁፎች

ባዬ ይማም። 1987 ዓም። የአማርኛ ሰዋስው።አዲስ አበባ፤ የትምህርት መሳሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት ማተሚያ ቤት።

ባዬ ይማም። 2000 ዓም። የአማርኛ ሰዋስው(የተሻሻለ2 እትም). አዲስ አበባ፤ ብርሀንና ሰላም ማተሚያ ቤት።

ጌታሁን አማረ። 1989/2002 (10ኛ እትም)። ዘመናዊ የአማርኛ ሰዋስው በቀላል አቀራረብ። አዲስ አበባ፤ አልፋ አታሚዎች።

Anbessa Teferra, 2000. A Grammar of Sidaama. PhD Dissertation: Jerusalem; Hebrew University.

Leslau, Wolf. 1995. Reference Grammar of Amharic. Wiesbaden: Harrassowitz Verlag.

Ludolf, Hiob. 1698. Grammaticæ Linguæ Amharicæ. Francofurti ad moenum/ Frankfurt am Main: J. D. Zunnerum.

Praetorius, Franz. 1879. Die amharische Sprache. Halle.

Tesfaye Tewolde. 2002. A Modern Grammar of Tigrinya. Rome: U. Detti.

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>