Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

“በ2007 ቅማንት ራሱን ያስተዳድራል ብለን እናምናለን”

$
0
0

ከአለማየሁ አንበሴ

በአሁኑ ጊዜ በሃገራችን የብሄር እውቅና ጥያቄ ከሚያነሱ ህዝቦች መካከል በአማራ ክልል ጎንደርና አካባቢዋ ነዋሪ የሆኑት “ቅማንቶች” ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ይህን የቅማንቶች ታሪክና የብሄር ጥያቄ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አደባባይ ይዘው ብቅ ያሉት ደግሞ ከኒውዮርክ “ዩኒቨርሳል ፒስኮርፕ ኮርፖሬሽን” የሰላም አምባሳደርነት ማዕረግ ያገኙት አቶ ነጋ ጌጡ ናቸው፡፡ “የአማራ አቀፍ ልማት ማህበርን ካቋቋሙት አንዱ ነኝ” የሚሉትና በጎንደር የፋርማሲ ባለቤት የሆኑት አቶ ነጋ፤ ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ የቅማንትን ብሄረሰብ ለማስተዋወቅና የብሄር ጥያቄያቸው እንዲመለስ ብዙ መስዋዕትነት እንደከፈሉ ይናገራሉ፡፡ ምላሽ ለማግኘት ያልገቡበት የመንግስት መዋቅር እንደሌለም የሰላም አምባሳደሩ ይገልፃሉ፡፡
ethiopian flag
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የብሄረሰቡን የእውቅና ጥያቄ ተቀብሎ ከመረመረ በኋላ በድጋሚ እንዲጠና ትዕዛዝ ማስተላለፉን አቶ ነጋ ይናገራሉ፡፡ “የብሄረሰቡ ጥያቄ መቼም ተዳፍኖ አይቀርም፤ ቅማንት ቅማንት ነው፤ ማንም አይሽረውም” ባይ ናቸው፡፡ የአዲስ አድማስ ከፍተኛ ሪፖርተር አለማየሁ አንበሴ ለስራ ጎንደር በቆየበት ወቅት ከአቶ ነጋ ጌጡ ጋር በብሄረሰቡ ማንነት፣ ባህልና ቋንቋ ዙሪያ አውግቷል፡፡

እስቲ ስለቅማንት ብሄረሰብ ማንነት በዝርዝር ይንገሩኝ?

የቅማንት ብሄረሰብ ቀደምት ህዝብ ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ መገለጫው በኛ በቅማንቶች አባት፣ እሚታ፣ አያት፣ ቅድመ
አያት-ቅማንት – ምንዥላት-እንጃለት ብለን 7ኛ ቤት ድረስ ይሄዳል። 6ኛው ዙር ምንዥላት ሚባለው አሁን ጠፍቷል፡፡ አሁን ያለው የመጨረሻው ቅማንት ነው፡፡ እነዚህ ከአባት ተጀምሮ ወደ ላይ የሚጠሩት የዘር ተዋረዶች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊ ህብረተሰብ “እሚታ”ን አያውቀውም፡፡ ስም ከነአያት እየተባለ ነው የሚፃፈው፡፡ በኛ ግን ከአባት ቀጥሎ እሚታ፣ ከእሚታ ቀጥሎ አያት ይከተላል፡፡
አሁን እኔ ስጠራ ነጋ ጌጤ ለምለሙ ተስፋዬ ነው፡፡ እናንተ ግን ስትጠሩኝ ነጋ ጌጤ ተስፋዬ ብላችሁ ነው፡፡ ምክንያቱም እሚታዬን
ፃፍ አላላችሁኝም፡፡ በብሄረሰቡ አጠራር የአባት ስም መጀመሪያ ይሆንና የልጅ ስም ይከተላል፡፡ ለምሳሌ የእኔ “ጌጤ ነጋ” ነው በብሄረሰቡ አጠራር፡፡ እንግዲህ ቅማንት ማለት ስንተረጉመው፤ “ከመንታ” ማለት ነው፡፡ ከመንታ ማለት “አንተ ካም ነህ”
ማለት ነው፡፡ በመፅሃፍ ቅዱስ የምናውቃቸው ኖህ፣ ሶስት ልጆች አሏቸው -ሴም፣ ያፌት፣ ካም ይባላሉ፡፡ አፍሪካውያን የካም
ልጆች ናቸው። የካም ልጆች ደግሞ ኩሽ፣ ምዝራይብ፣ ፉጥ እና ከነአን ናቸው፡፡ ከዚህ መሃል የኛን ዘር የምናወጣው ከከነአን ልጆች
ነው፡፡ አራዲዮን – አደረኪን ወለደ። አደረኪ ሶስት ሚስቶችን አገቡ፡፡

አንደኛዋ ሚስታቸው አንዛኩና ትባላለች፣ ሁለተኛዋ ሚስታቸው ፌይኖባኩላ፣ ሶስተኛዋ ሚስታቸው ሰሜንድራ ትባላለች፡፡ ከአንዛኩና ቅማንትን፣ አገውን እና ቢሌንን (ኤርትራ ውስጥ ያሉ) ይወለዳሉ፡፡ ከሁለተኛ ሚስታቸው ካይላ፣ ሞረትን፣ አርጎባን እና ጋፋትን ይወልዳሉ፣ ከሶስተኛ ሚስታቸው ስራሁን፣ አከላጉዙ፣ ሐማስን፣ ሞንአሞርን፣ ቤጃን ይወልዳሉ።

ከእነዚህ ሶስት እናቶች የተወለዱ ልጆች ታላቁን አባት ሃገር የሚባለውን ይመሰርታሉ፡፡ “ታላቁ አባት ሃገር” የሚባለው በቅማንትኛ አቢሲኒያ ነው። አቢሲኒያ ማለት በቅማንትኛ “አባት ሃገር”ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ይሄ ሁሉ ዘረዘርነው ዘር እየተዋለደተበተነ፤ ቅማንት ግን እንዳለ አለ፣ አገው፣ አርጎባ፣ ሞረት፣ ብሌን፣ ከይላ (ፈላሻ) አሉ፡፡
ጋፋት አሁን ጠፍቷል፤በቆዳ መፋቅ ነበር የሚተዳደሩት፡፡ ሞረት ደግሞ ሸማና የእጅ ጥበብ ሰሪ ናቸው፤ ሰሜን ሸዋ ውስጥ ይኖራሉ፡፡
አርጎባ ደግሞ በተለያዩ ክልሎች ተበጣጥሶ የተቀመጠ ነው፡፡ አገውም ደቡብና ሰሜን አገው ተብሎ ተበታትኖ አለ፡፡ መሃል ላይ ያለው እንግዲህ ቅማንት ነው፡፡ ቅማንት ከዘረዘርናቸው ብሄሮች በቁጥር በብዛት ይበልጣል፡፡ በጎንደር ውስጥ በ4 ወረዳዎች ከሚሊዮን በላይ የሆኑ ቅማንቶች አሉ፡፡

ግን በጣም የታፈነ ብሄር ነው፡፡ እንዲታወቅ አይፈለግም፡፡ ከባድ ጫና አለብን፡፡ ለምንድነው እንዲታወቅ የማይፈለገው? ለኛም ሚስጢር ሆኖብናል፡፡ ወደፊት ይህን ሚስጢር እናወጣው ይሆናል፡፡ አሁን እያጠናነው ነው፡፡ የክልሉ መንግስት ለኛ እውቅና ለመስጠት የሞት ያህል ነው የሆነበት፣ ለምን እንደሆነ አይገባንም፡፡ በታሪክ ሂደት እየቀነሰ መጣ እንጂ ይህ ብሄር ከቀደምት የአፍሪካ ብሎም የኢትዮጵያ ዘሮች የፖለቲካና ማህበራዊ ስፋት የነበረው ብሄር ነው፡፡ እኛ ቅማንትን ስንገልፅ ከመጀመሪያው የዘር መነሻ ጀምረን ነው፡፡

አማራዎች የዘር መነሻችሁን ግለፁ ብንላቸው የዘር መነሻ የላቸውም፡፡ አማራነት የተስፋፋው ከክርስትና ሃይማኖት መስፋፋት ጋር
ተያይዞ ነው፡፡ የተጠመቀ አማራ ተባለ፡፡ አገው፣ ቅማንቱ፣ ከይላው ወዘተ ሲጠመቅ አማራ ተባለ እንጂ እገሌ፣ እገሌን ወለደ እያልክ የአማራን የዘር መነሻ አታስቀምጠውም፡፡ ይሄ ችግር ስላለ ቅማንት ስሙ እንዳይነሳ ይፈለጋል፡፡

እኛ ስለ ጎንደር፣ ለፋሲል ግንብ የሚወራውን ሁሉ በሬዲዮ እየሰማን ከመሳቅ ውጪ በአሁን ሰዓት ምንም ማለት አንችልም፡ ስለፋሲልና ስለጎንደር መናገር የሚችለው ቅማንት ብቻ ነበር፡፡ ሌላ ማንም ሊናገር አይችልም ነበር፡፡ ግን ማንም ተነስቶ ሲዋሽ ስታየው
ደምህን ያፈላዋል፡፡ የጎንደር ነገስታት የቅማንት ብሄር አባላት ናቸው ነው የሚሉት?

ባይሆንም ስለታሪኩ መናገር የሚችለው ቅማንት ነው፡፡ እርግጥ እነዚህ ነገስታት ከሸዋ ተሰደው የመጡ ናቸው፡፡ በዚያ ሰዓት ደግሞ ሸዋም ቢሆን ቅማንት ነው የነበረው፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ ወደ ክርስትና የተለወጠ በመሆኑ፣ ቅማንትነትን እየተወ አማራ ተባለ፡፡ እነዚህ ሰዎች ወደ ጎንደር ለመግባት ሲሞክሩ፣ ቅማንት አላስገባ ብሏቸው 70 ዓመት ፈጅቶባቸዋል፡፡ በኋላነው በስንት መከራ
የገቡት፡፡

ቅማንት እንግዲህ የሰሜን ኢትዮጵያን ከፈጠሩት አንዱ ነው፡፡ ከከነአን ቅማንት ሲወጣ፣ ከኩሽ ደግሞ የኦሮሞ ብሄርን እናወጣለን፡፡
ለእኛ ወንድሞቻችን ናቸው፡፡ ምዝራይብ የሚባለው ደግሞ መነሻው ካይሮ ነች፡፡ ጥንት ምስር ተብላ ትጠራለች፡፡ በዚያ አካባቢ
ያሉት ህዝቦች የምዝራይብ ዘሮች ናቸው፡፡ አሁን የቀሩት ጥቂት ናቸው፡፡ በአልጄሪያ የ”በርበር” ህዝቦች የሚባሉት ማለትነው፡፡ የ”ፋጥ” ደግሞ ፍልስጤማውያን ናቸው፡፡ አረቦች ከፐርሺያ፣ ከኢንዶኔዢያና ከሩቅ ምስራቅ የመጡ ህዝቦች ናቸው፡፡ የአረብ ምድር የኛ ነው፤ ሰዎቹ የመጀመሪያዎቹን ሰዎች አጥፍተው ኖሩበት እንጂ የእነሱ አይደለም፡፡ በቅማንትኛ “አረቢያ” ማለት የእህል ምድር ማለት ነው፡፡
ከውሃ ጥፋት በኋላ ሰምጦ ምድረ በዳ ይሁን እንጂ ከዚያ በፊት የበግ፣ የፈረስ፣ የእህል ምድር ነው፡፡ የቅማንት ሃይማኖት ምንድን
ነው? አሁን ከብሄረሰቡ 98 በመቶ ሚሆነው የተለያዩ የክርስትና እምነቶች ተከታይ ነው፡፡ ሙስሊምም አለ፡፡ የቀድሞውን ህገ ልቦናም የሚከተሉ አሉ፡፡ የእነ አብርሃም ሃይማኖት የሆነው ህገ ልቦና የቅማንቶች ቀዳሚ እምነት ነው፡፡ የህገ ልቦናው መሰረቶች የሆኑትን 5 መመሪያዎች ይከተላሉ፡፡

5ቱ መመሪያዎች ምንድን ናቸው? በአይሁድ እምነት ካሉት 10 ትዕዛዛት 5 ያህሉ ማለት ነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ ባላስታውሳቸውም አትስረቅ፣ አትግደል፣ አታመንዝር ወዘተ የሚባሉት ናቸው፡፡ ቄሶች አሉ፣ በጫካ ውስጥ ሆነው አብርሃምን ቅዳሴ ይቀድሳሉ፡፡ ለቅማንት ብሄር መዳከም ምክንያቱ ምንድን ነው? በሌላው የሚደርስበት ጫና ነው፡፡ በተለይም የክርስትና እምነት መስፋፋት፡፡ ክርስትና በአክሱም በኩል መጣ፣ ያመነ የተጠመቀ ይድናል የሚለው ታወጀ፡፡ ቅማንቶች ደግሞ “አባሽቲ ሸምዲ ደደብቲ” አሉ “ባባትህ እደር በሸማህ ተቀበር” ማለት ነው። በአዲስ መጤ ሃይማኖት አትታለል ማለት ነው። በዚህ የተነሳ በአክሱምና በአካባቢው መኖር የሚችሉት የተጠመቁ ብቻ ናቸው፤ ያልተጠመቁ ተከዜን ተሻግረው ወዲያ ማዶ ይሂዱ ተባለ፡፡ በዚያው ከተከዜ ወደዚህ በሶስት አቅጣጫ ፍልሰት ሆነ፡፡

አንደኛው አቅጣጫ በዋግ በኩል ነው፡፡ ዋግ የደረሱ የቅማንት አባቶች “ዋያ አክሱም ከውጋላትን ነው” አሉ፤ ይህ ማለት አክሱምን
የሚመስል ሃገር አግኝተናል ማለት ነው፡፡ ወደ ሰሜን አቅጣጫ የመጡት ደግሞ በብዛት የህገ ልቦናው የሃይማኖት መሪዎች ናቸው፡፡ ቦታው ሲደርሱ “ድቢ ሸልሚ ጋጋ ከውጋላትን ነው” አሉ። በተራራ የጨለመ ሃገር ውስጥ ገብተናል የሚል ትርጓሜ አለው፡፡በወልቃይት በኩል የመጡት ደግሞ “ውላጋ ከውጋላትን ነው” አሉ፡፡ እኛ ሜዳ በሆነ ሃገር ውስጥ ገብተናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የሰፈሩት ከሰሜን ተራራ አንስቶ እስከ ፓዌ ተራራ ነው፡፡ ወደ ተራራ የገፋቸውም ጦርነት ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ውጪስ የቅማንት ዘር አለ? በኑቢያ ዘመነ መንግስት ቅማንት ሰፊ፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ስሟ አራት ነው፡፡ የመጀመሪያው ኑቢያ፣ ቀጥሎ ኩሽ፣ ቀጥሎ አበሽ፣ ከዚያ ኢትዮጵያ ሆነ። በኑብያ ዘመን የቅማንት ግዛት እስከ ፐርሺያ፣ ምዕራብ ህንድእና ሁሉንም አፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅን ያጠቃልል ነበር፡፡ መጀመሪያ የቅማንትን የማንነት ጥያቄ ይዤ የተነሳሁት እኔ ነኝ ብለዋል፡፡
ታሪኩን እንዴት ሊያውቁ ቻሉ? ጥናቶችስ አድርገዋል? የአባቴ አባት በጣም ነብይ ነበሩ፡፡ አንድ ምክር መከሩኝ፤ ይሄን ህዝብ የምታስጠራውአንተ ነህ፡፡

ጊዜው ሲደርስ ያለፍርሃት ለብሄረሰቡ መብት ታገል፣ ስሙን እንደገና አንሳው፤ ያኔ ኛ ህዝብ ቋንቋውን ያሳድጋል፤ ማንነቱ ይከበራል፤
እንደገና ቅማንትነት ይነግሳል አሉኝ፡፡ የሳቸውን ቃል ይዤ ተነሳሁ። በዚህም ብዙ መከራና ፈተና ገጥሞኛል፡፡ በፊት ጥቂት ሆነን እንታገል ነበር፤ ዛሬ ህዝቡ ሁሉሆ! ብሎ ተነስቶ እየታገለ ነው፡፡

መጀመሪያ ላይ ህዝቡ “ቅማንት ነኝ” ማለትን እንደ ሃፍረት ይቆጥረው ነበር። የቅማንት ብሄረሰብ የልማት ማህበርን በ1984 መሰረትኩ። በዚያ ማህበር ስም እየዞርኩ “እኔ ቅማንት ነኝ” እያላችሁ ራሳችሁን ግለፁ፡፡ ህገ መንግስቱ ለኛ መጥቷል፤ ተጠቃሚ
መሆን አለብን” እያልኩ ከሃገር ሃገር በእግሬ እየዞርኩ አስተማርኩ፡፡ እግረ መንገዴንም “የቅማንት ህዝብ ታሪክ” የምትል ትንሽ
መፅሐፍ ፃፍኩ፡፡

እሷ ከወጣች በኋላ በብሄረሰቡ ዙሪያ ውይይቱ ተስፋፋ፡፡ መፅሃፏ ትኩሳት አጫረች። በዚህ የተነሳ ብዙ መከራ ደርሶብኛል፡፡

አሁን ታዲያ ምን ውጤት አገኛችሁ? ከክልሉ መንግስት እና ከፊውዳሉ ጋር የነበረው ትግል ቀላል አልነበረም፡፡ ቅማንት አይደለንም ስንል ኖረን እንዴት ቅማንት ነን እንላለን የሚል ሃፍረት ያደረባቸው፣ ያንን የስነ ልቦና ዝቅጠት ለማላቀቅ ብዙ ጊዜ ፈጅቷል፡፡ አሁን አማራውም ከኛ ጋ ነው፡፡
ለኛ የሚወግኑ አማራዎች፤ አገው የብሄርነት እውቅና ካገኘ ቅማንት ለምን አያገኝም ብለው ራሳቸው ጥያቄውን እየደገፉ ነው፡፡
ቅማንቱም “በቅማንትነቴ እኮራለሁ” እያለ ዛሬ በግልፅ እየተናገረ ነው፡፡ አመለካከቱ ተለውጧል፡፡ የቋንቋው ት/ቤቶችን በየቀበሌው ቤት ተከራይተን በመክፈት ማስተማሩን ተያይዘነዋል፡፡ የመንግስት ት/ቤትማ ማን አድርሶን፡፡ መንግስት እኮ እንደ ተቃዋሚ ነው የሚቆጥረን፡፡

እኔ ዚህ በጣም አፍሬያለሁ፡፡ ዚህ መልኩ አንዳንዶች ትግላችንን እያሰናከሉ፣ እስከዛሬ ቢያቆዩትም እግዚሃር ይመስገን አሁን እያለቀ ነው፤ እየተሳካም ነው፡፡ ኦሮሞውና ቅማንቱ አልተቀላቀለም? በአንድ ወቅት ኦሮሞዎች የሰሜን ኢትዮጵያን እስከማስተዳደር ደርሰው ነበር ብዬ ነው ጥያቄውን ያነሳሁት… ኦሮሞው፣ አገው እና ቅማንት የተቀራረቡ ህዝቦች ናቸው፡፡

ሜሮይ ላይ የሃማቲክ ህዝቦች የምንላቸው አገው፣ ቅማንት የመሳሰሉት ናቸው። የኩሸቲክ ህዝቦች የሜሮይ ስልጣኔ ሲወድቅ ካርቱምን የተቆጣጠሩ ናቸው፡፡ ከኦሮሞ፣ ከአገው፣ ከቅማንትና ከሌሎችም ህዝቦች የተውጣጣ ነው። በክርስትና የተነሳ ህዝቡ በሙሉ አንድ
ብሄር ሆኖ አማራ ተባለ። ኦሮሞውም በዚህ ሂደት አማራ ሆኗል፡፡
ቅማንት እንደውም የአማርኛ ቋንቋ ከኔ ላይ ነው ያደገው፣ የራሴ ቋንቋ ነው ብሎ ያምናል፡፡ አማርኛ ቋንቋ በጣም የጠራውና በእግሩ የቆመው ጎንደር ላይ ነው፡፡ የይኩኖ አምላክንም፣ የነአኩቶ ለአብንም አማርኛ አይተነዋል፤ የተሰባበረ አማርኛ ነበር፡፡ነገር ግን አማርኛ
በእግሩ የቆመው ጎንደር ላይ በቅማንት ህዝብ ጀርባ ላይ ነው፡፡
ስለዚህ ቅማንት ለኢትዮጵያ ቅርስ ነው፡፡ ቅማንትን ማጥፋት ማለት ትልቅ ቅርስ ማጥፋት ማለት ነው። ነገ ቅማንት ራሱን ሲያስተዳድር ጉዱ ይታያል፡፡ የታፈኑ እውነቶች ይወጣሉ፡፡ ቅማንቶችን በመልክ እና በቁመና አይተን ከሌላው ልንለያቸው እንችላለን? በባህል ረገድስ? የቀድሞው ቅማንት የዛሬ አማራ የዛሬ፣ ትግሬ ብለን ነው የምንወስደው፡፡ ባህሉም ሁሉ የቅማንት ነው፡፡ የጎንደር ዘፈንና እስክስታ የቅማንት ነው።
የነይርጋ ዱባለ ዘፈንና ዜማ የቅማንት ነው፣ ግን ሲዘፍኑ የቅማንትን ምድር ጎጡን አይጠሩትም፡፡ እሚጠሩት ቅማንት የሌለበትን ቦታ ነው፡፡ ትግሬ፣ አማራ፣ ቅማንት ነው፡፡ ባላገር ሄደህ ብታየው ምንም ልትለየው አትችልም፡፡ ምክንያቱም የዛሬ ማንነቱን የያዘው በእምነት ነው፡፡ ክርስትናን በመቀበሉ እንጂ በደም አልተለወጠም፡፡ ጎንደር የሚለው ቃል ትርጉሙ ምንድንነው? የጌታ መነሻ ማለት
ነው፡፡ የጌታ መነሻ ማለት? እንግዲህ አንዱን የውሸት ታሪክ ትንሽ ልምዘዝልህ ማለት ነው፡፡

ከውሃ ጥፋት በኋላ አባታችን ኖህ፤ መርከብ ሰርቶ በመርከብ ነው ቤተሰቡ የተጠለሉት፤ መርከቧ ተንሳፋ አራራት ተራራ ላይ ተሰቀለች፡፡ ውሃው ሲጎድል ወጥተው ሲያዩ፣ መውረጃ የሌለው ተራራ ላይ ነው የተሰቀሉት፡፡ በዚህን ጊዜ ያለቅሳሉ፣ እግዚአብሔር
በቅርበት ከሳቸው ጋር ስለነበር “አታልቅስ መውረጃ ተሰርቶልሃል፤ ሂድ ወደ አባትህ ሃገር ወደ ጊዮን” ይላቸዋል፡፡ ጊዮን ማለት ጣና እና አባይ ነው፡፡ መጡ፡፡
የተቀመጡበት ቦታዎች ሁሉ አሉ፡፡ ለወደፊት እናወጣቸዋለን፣ ህዝብ እንዲያውቀው ይደረጋል፡፡ ጥንቱ የቅማንት ታሪክ ንዲህ ነበር፤ ዛሬ ደግሞ እንዲህ ሆነ ተብሎ መቅረብ ነበረበት፡፡ ወደ ኖህ ታሪክ ልመልስህና እሳቸው እዚሁ ኖሩ፡፡ ልጆቻቸው ግማሾቹ ወደ ኤሽያ ሄዱ፣ ካም በአፍሪካ ምድር ተበተነ፡፡ እሳቸው ጎንደር መጥተው ኖረው፣ ሞቱ፣እዚሁ ተቀበሩ፡፡ መቃብራቸው ላይ ትልቅ ቤተ መንግስት ተተከለ፣ ያ ቤተመንግስት ዛሬ የፋሲል ግንብ እያለ ቱሪስቱ የሚጎበኘው ነው፡፡ ከስሩ የሳቸው አፅም ነው ያለበት፡፡ አፄ ፋሲል ቤተ-መንግስቱን ከመትከላቸው በፊት በቅማንቶች ህገ ልቦና እምነት ይቀደስበት ነበር፡፡ ሲቀድሱ በዜማው መሃል “ጎሃይደር” ይላሉ፤ ትርጉሙ “ጌታው ቢነሱ” የሚል ነው፡፡ ጎንደር የሚለው ስም ከዚህ የመጣ እንጂ እንደሚባለው “ከተራራው ጎን እደር
.. በዚያ እደር” የሚለው አይደለም፡፡ ከትግራይም የመጡ ሰዎች “ወይኒሰይኒ” የሚባሉ ህዝቦች ናቸው፡፡

ነገሩ “አፍ ያለሽ ያግባሽ ወይስ ከብት ያለሽ” ነው፡፡ በወቅቱ ቅማንት አፍ የለውም፤ መስማት ብቻ ነበር ያለው እድል፡፡ እና ታሪክ
ሁሉ ተዘበራርቆ ያስቅሃል… እኔ አንዳንዴ አምርሬ አለቅሳለሁ፡፡ በሚሊኒየሙ ጊዜ አንድ የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ስለ ጎንደር ነግሬው፣
ሙሉ በሙሉ በኔ ስም ሌላ ታሪክ ነው ያወጣው። ይህን ትክክለኛውን ለእናንተ የነገርኩትን ታሪክ አይደለም ያቀረበው፡፡

የጥንቱ ቅማንት በምን ነበር የሚተዳደረው?

በእርሻ ነው፡፡ የእህል ምግብ፣ የእንስሳት ምግብ፤ ይሄን ብሉ፤ ያንን ትብሉ… ተብሎ የተመረጠው ቅማንቶች አይደለም እንዴ?
ዋናው የቅማንት ታሪክ እኮ የነበረው አዲግራት ላይ ነው፡፡ ትግሬ ማለት በቅማንትኛ “ሰው ሳይመጣ” ማለት ነው። ከዚያ ደግሞ እንደርታ ተባለ፤ “ሰው መጣ” ማለት ነው፡፡

“አጋመ” ቅማንትኛ ነው፤ “የኛ ያልሆነ” ማለት ነው፡፡ ግዕዝ ቋንቋን ተቀበል ሲባል “የኛ ያልሆነን አንቀበልም” ብሎ በመቃወሙ
የተሰጠ ስያሜ ነው። “ይርትላ” ኤርትራ ነው፤ “ሰው አልመጣም” ማለት ነው፡፡ እነ ሙሴ ባህረ ኤርትራን ሲያቋርጡ፣ እነሱን የተከተሉት በባህር ውስጥ ሰጥመው ቀሩ፤ ዞረው ሲያዩ ሰው አልመጣምና በዚያው “ሰው አልመጣም” ብለው ሰየሙት፡፡ እንግዲህ ኤርትራም ሆነ ትግሬ ቅማንት ነው ማለት ነው፡፡ ትግሬ የሚለው ቃል ምን እንደመጣ ብዙ ፀሃፍትና የታሪክ ተመራማሪዎች
ለማወቅ ጥረዋል፤ አልተሳካላቸውም፡፡ እውነቴን ነው የምልህ በንፁህ ልቦና ለሚያጠናው በቅማንት ውስጥ ተዝቆ የማያልቅ ታሪክ
ነው ያለው፡፡

ይሄ ትውልድ ቅማንትን አላወቀውም፡፡ በ1987 ይሁን… በእርግጠኝነት አላስታውሰውም፡፡ አልማዝ መኮ የምትባል አፈጉባኤ
ለሶስት ሰአት ቢሮዋ ስታነጋግረኝ፣ ቅዳሴዎቹን ሁሉ አስደምጫት ነበር። እሷም “ቅማንት ሲባል ተማሪ እያለሁ እሰማለሁ፤ እንዲህ
ያለ ነገር ግን አይመስለኝም ነበር” አለችና “ግን የአማራው መንግስት እውቅናውን የሚሰጣችሁ አይመስለኝም፤ያለፉሃል አለችኝ፡፡ እንዴት አድርገህ እንደምታልፈው አላውቅም፤ እኔ ዛሬውኑ ቢሰጥህ ደስ ይለኛል፤ የክልልህ መንግስት ግን አስቸጋሪ ነው” አለችኝ፡፡ እሷም መሯት ስለነበር በዚያው ሄደች፡፡

ግራሃም ሃንኰክ ደግሞ በ”Sign and the Seal” መፅሃፉ የቅማንት ጉዳይ ሚስጥር ነው ብሎታል። እውነት እልሃለሁ ቅማንት ብዙ መከራን የተቀበለ የኢትዮጵያ ሚስጢር ነው፡፡ ደቡብ ኢትዮጵያም ስትሄድ እኮ ከዚሁ የሄዱ ናቸው፡፡ ለነሱ ማስታወሻ ጎንደር
ላይ የሚደረግ ነገር አለ፡፡ ቡናን ሶስት ጊዜ እንጠጣዋለን፤ አባ አቦል፣ አባ በረካ፣ አባቶና ብለን እንጠጣዋለን፡፡ እነዚህ ሰዎች ናቸው ወደ ደቡብ ሄደው አባት ሆነው ብሄሮቹን መሰረቱት፡፡

አባ አቦል ወደ ምዕራባዊ ደቡብ ሱዳንን ይዞ ወደታች ያለው ነው፤ አባቶና ደግሞ መካከለኛው ደቡብ ያሉትን መሰረቱ፡፡ አባ በረካ ከባሌ ጀምሮ እስከ ህንድ ውቅያኖስ ይደርሳል፡፡ ወሎ ላይ ስትሄድ ሶስት አባቶች አሉ፡፡ ወረባቡ፣ ወረይመኑ፣ ወረ ሸኩ ተብለው ይጠራሉ፡፡ የባቡ ልጆች፣ የይመኑ ልጆች፣ የሸኩ ልጆች ማለት ነው በቅማንትኛ፡፡ ወደ ጎጃም ስትሄድ ከዚህ ከኛ የሄዱት አንከሻ፣ ባንጫ፣ ኳኩራ፣ አዘና፣ ሜቲክሊ ናቸው፡፡

እዚህ የቀሩት ክድስቲ እና ክብሩ ናቸው፡፡ ክቡር፣ ክብርት እያልን የምንጠራራበት፣ ቤተክርስቲያን ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ የምንለው
የኛ አባቶች ስያሜ ነው፡፡ ለሰሜን ኢትዮጵያ ሙሉ ታሪክ የሚሰጠው የኛ ታሪክ ብቻ ነው፡፡ ይሄን በትክክል የሚቃረን አልተገኘም፡፡

ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀረባችሁት ጥያቄ ምላሽ ካገኘ፣ የራሳችሁን አስተዳደር ትመሰርታላችሁ ማለት ነው? አዎ! እንደሁኔታው የራሳችን አስተዳደር እንዲኖረን እንታገላለን፡፡ እኛም ኖርንበት አማራውም ኖረበት የሚጠቀመው ክልሉ ነው፡፡

በ2007 ዓ.ም ቅማንት ራሱን ያስተዳድራል ብለን እናምናለን። በህገ-መንግስቱ መሰረትም በፌደራል መንግስት የራሱ ወኪል ይኖሩታል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ምላሽ እንዴት ነው?

ያገኘነው መልስ በድጋሚ ይጠና የሚል ነው። በጥናት ከሄድክ በኢትዮጵያ እንደቅማንት የተጠና የለም፡፡ ክልሉ ራሱ ሶስት ጊዜ አጥንቷል፣ እኛም ሁለት ጊዜ አጥንተን ሰጥተናል፤ አልቀበል እያሉ እንጂ፡፡ የመጨረሻ ጊዜ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አጥንቶ ሄዷል፤ ለውሳኔ ሲያቀርብ ምን እንደገጠመው አናውቅም፤ በድጋሚ መጠናት ያስፈልጋል ነው ያለው፡፡ በኛ በኩል እንኳን በድጋሚ እየደጋገመም ያጥና፤ ቅማንት ቅማንት ነው፡፡ ጣቱም በሚገባ ቅማንትነቱን ውቋል፤ ጥያቄውንም እያነሳ ነው። እንደውም ባለፈው ብዙዎችን አስረውብን ነበር። ጥያቄውን ነገ ከነገ ወዲያ እያሉ ማሸት ተገቢ አይደለም፤ ቢለቁን ይሻላቸዋል፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>