ናኦሚን በጋሻው
የአንድነት ፓርቲ ከመኢአድ ጋር ሲዋሃድ ዉህዱን ፓርቲ ለመምራት በአንድነት በኩል ዉድድሮች ተጧጡፈዋል። ሶስት እጩዎች የቀረቡ ሲሆን በአብዛኛው ቅስቀሳው እየተደረገ ያለው በአቶ በላይ እና በኢንጂነር ግዛቸው ደጋፊዎች መካከል ነው።
“ኢንጂነር ግዛቸው ?” ነው ብላችሁ የጠየቃችሁኝ። አዎን፣ የጥንቱ፣ የጠዋቱ ፣ የነ ዶር ኃዩ አራያ፣ የነ አቶ ሃይሉ ሻወል ጓደኛ ፣ የቀድሞ የቅንጅት አመራር አባል ኢንጂነር ግዛቸው !
ኢንጂነር ግዛቸው ትግሉ፣ ፍሬሽ አዲስ አመራር በሚያስፈልግበት ጊዜ፣ ራሳቸው እጩ አድርጎ በማቅረብ ለመወዳደር ለምን እንደፈለጉ በራሱ እንቆቅልሽ ነው የሆነብኝ። “ሰውዬው ስልጣን አይበቃቸውም እንዴ ? ስልጣን የሚወዱ ናቸው ማለት ነው”” ብዬ አሰብኩ።
ከስድስት ወራት በፊት የረቀቀ ዉስጣዊ አሰራር ስለነበራቸው፣ የቀረቡ እጩዎች በቀላሉ በብዙ ድምጽ አሸንፈው ድርጅቱን እንደገና ለመምራት ብቅ አሉ። (በነገራችን ላይ በኮንስፒራሲ ዉስጣዊ ሴራ ኢንጂነርግ ግዛቸው አደጋኛ ናቸው ተብሎ ይነገራል። በዚህ አደገኛ ዉስጣዊ ሰራቸውም ሳይሆን አይቀርም እነ ግርማ ሰይፉን የዘረሩት)
በበርካታ የአንድነት ደጋፊዎች ዘንድ የኢንጂነሩ ተመልሶ መምጣት ትልቅ ቅሬታን ፈጠረ። ኢንጂነር ግዛቸው፣ ያደረጉት ብዙ መልካም ተግባራት ቢኖሩም፣ የሰሯቸው በርካታ ስህተቶችም ነበሩ፣ አሉምም። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ታስራ የነበረ ጊዜ ፣ የአንድነት ፓርቲ በተጠባባቂ ሊቀመንበርነት ይመሩ ነበር። ያኔ ነበር የአንድነት ፓርቲ የተከፈለው። አሁን ሰማያዊ ፓርቲን የመሰረቱት በርካታ ወጣት አመራሮች፣ ከፓርቲው ታግደው የተባረሩት በኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ሲሆን፣ በፓርቲ መከፋፈል ምክንያት ለተፈጠረው ጉዳት የሚጠየቁት በዋናነት ኢንጂነር ግዛቸው ናቸው።
ሰማያዊና አንድነት፣ ከተቻለ ዉህደት፣ ካልሆነም ትብብር እንዲመሰርቱ ህዝቡ ከየአቅጣጫዉ ግፊት እያቀረበ ነው። የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ፣ አብሮ የመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ይናገራሉ። ነገር ግን የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም እንደሚባለው፣ የአንድነት አመራር አባል ሆነው፣ በኢንጂነር ግዛቸው የተደረገባቸውን ስለሚያስታወሱ፣ ትልቅ የአመኔታ ችግር አለባቸው። በመሆኑም የኢንጂነር ግዛቸው መኖር፣ በአንድነት እና በሰማያዊ መካከል ትልቅ መቀራረብ እንዳይኖር እንቅፋት ሆኗል።
በመሆኑም ለትግሉ ሲሉ ኢንጂነር ግዛቸው ቢበቃቸው ጥሩ ነው። ሃላፊነቱን ለአዳዲሶች ያስረክቡ። ከዶር ኃይሉ አራአያ ፣ ከዶር ነጋሶ ጊዳዳ ይማሩ። አዲስ አመራር ከመጣ፣ ከመኢአድ እና አንድነት ዉህደት ቀጥሎ፣ ሰማያዊ ፓርቲ የሚከተልበት ሁኔታ ሰፊ ነው የሚሆነው። ያ ደግሞ ለወያኔ ትልቅ መርዶ ነው የሚሆነው።
ኢንጂነር ግዛቸው እባክዎትን ወያኔ አይደሰት ! ሰላማዊ ታጋዮች እንዳይሰባሰቡ እንቅፋት አይሆኑ ! በአንድነት ዉስጥም፣ በርስዎ የተነሳ፣ ቀውስ አይፈጥር ! እረ በመድሃኔ ኣለም ይብቃዎት !!! ሁሌ ዝንተ አለም ተመሳሳይ መሪ አሁንስ ሰለቸን ።