Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የመጨረሻው ሱባኤ

$
0
0

ሙሉነህ ዮሃንስ
ከሲያትል ዋሽንግተን

Mulunehየፍልሰታ ልደታ ቀን 2005 ዓ.ም. ተጻፈ
ክፍል አንድ፡-ንግርት፣ የመጨረሻው መጀመሪያ ሱባኤና የመንግስት ትንቅንቅ
በታላላቅ የበቁ የቤተ-ክርስቲያን አባቶች ዘንድ ዘመን የተቆጠረለት የኢትዮጵያን መጻኢ እድል የሚተነብይ ጥንታዊ ንግርት አለ። ኢትዮጵያ እግዚአብሔርን በካዱ ጨቋኝ መንግስታት ለአርባ አመታት ወድቃ እንደምትገዛ በታላላቆቹ የኢትዮጵያ ገዳማት አባቶች በለሆሳስ ሲነገር ከርሟል። ይህ ዘመን የሚቆጠረው ጃንሆይ ከተፈናቀሉበት ዘመን ጀምሮ ነው። ይህም ሲሰላ መነሻው 1966 ዓ.ም. መሆኑ ነው። አዎን አርባ አመት ከዛ ላይ ስትጨምሩ የዘመን ባቡር በፍጥነት የፊታችን መስከረም 2006 ዓ.ም. ላይ ያደርሰናል። ይህ ትንቢት ይተገበር ዘንድ ግን በግድ መፈጸም ያለበት በመጨረሻዎቹ ሁለት አመታት ከታላላቅ የኢትዮጵያ ገዳማት የተውጣጡ አባቶች በሕብረት ሱባኤ መያዝ አለባቸው። ይህን ብርቱ ሚስጥር በየገዳማቱ አስርጎ በሰገሰጋቸው የበግ ለምድ በለበሱት “ካድሬ” መነኮሳት አማካኝነት ቀድሞ ያወቀው መንግስት ከፍተኛ የሰውና የገንዘብ ሃይል በመመደብ ሱባኤውን የማክሸፍ ዘመቻ ከፈተ።
በኢትዮጵያ ገዳማትና አብያተክርስቲያናት ዘመን የሚቆጠረው በሱባኤ እየተጠቀለለ ሲሆን፣ አበይት በሆኑ አጽዋማት ወቅት ልዩ ሱባኤ ስለሃገር፣ ስለሕዝብ፣ ስለሰላም፣ ይያዛል። በነዚህ ሁለት አመታት የተያዙት ሱባኤዎች ግን እጅግ ፈተና የበዛባቸው ሆነዋል። ሰርጎገብ የመንግስት “ካድሬ” መነኮሳት ባቀረቡት መረጃ የተደናገጠው መንግስት ሱባኤዎቹን ለማደናቀፍ ሰፊ እቅድና ዘመቻ ይዞ ከተነሳ አንድ አመት አለፈው። ለዚህ እቅዱ ማስፈጸሚያ ይረዳው ዘንድ ሽፋን መጠቀም ነበረበት። ለዚህም ነው በታላቁ ዋልድባ ገዳም ክልል ውስጥ የስኳር ፋብሪካ እክፍታለሁ የሚል አደናጋሪ ፕሮጀክት የጀመረው። መንግስት ተጠናክሮ በደረሰው መረጃ መሰረት የሱባኤ መያዣ ታላቁ የዋልድባ ገዳም ነው ብሎ አምኗል።
በተባለው የስኳር ፋብሪካ ሽፋን አማካኝነት የዋልድባ “ጠፍ” መሬቶችን በስፋት ለመቆጣጠር ሲያቅድ፤ በተለያዮ የገዳሙ አብያተክርስትያናት የተያዙትን ቦታዎች ደግሞ በመረጣቸው “ካድሬ” መነኮሳት አማካኝነት ይቆጣጠራል። በዚህ እኩይ ምግባር የተነሳ ከታላላቅ የኢትዮጵያ ገዳማት ተጉዘው ዋልድባ ገዳም ለሱባኤ የደረሱ አባቶች ፈተና ላይ ወደቁ። በነዚህ መንፈሳዊያን ላይ ብዙ ስቃይ ደረሰባቸው። ብዙዎች ተደበደቡ፣ ብዙዎች ለእስር ተዳረጉ፣ ብዙዎች ተፈናቀሉ። ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ የሆኑ መገናኛ ብዙሃን የመንኮሳቱን እንግልትና የህዝቡን ተቃውሞ በተከታታይ ሲዘግቡት ቆይተዋል። እስካሁን ግልጽ ሆኖ ያልወጣው ጉዳይ ግን የመንግስት ድብቅ ሱባኤ ማስተጓጎያ ዘመቻ ነው። አዎን ለመንግስት በደረሰው የካድሬ መነኮሳት መረጃ መሰረት ትንቢቱ የሚሰምረው ሱባኤዎቹ ሲፈጸሙ ነው። እናም የግዛት ዘመናቸውን ለማራዘም በሰውኛ የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም።
ክፍል ሁለት፡- የተረሱ መቋሚያዎች
ሰዎች ወደንስሃ እንዲገቡና እንዲድኑ የሚወደው አምላክ መላእክተኞቹን በትእቢት ለታወሩት እንኳ ይልካል። ሰዎች ግን በክፉ ምርጫቸው መጥፊያቸውን ሲመርጡ በመጽሃፍ ደጋግመን አይተናል። ለሱባኤ ዋልድባ ገዳም የተሰባሰቡ መነኮሳት መንግስት የከፈተባቸውን መጠነሰፊ የጥፋት ዘመቻ በመገንዘብ የእግዚአብሔርን የንስሃና የድህነት መልእክት

አስይዘው ተወካዮቻቸውን ወደቤተ-ክህነት እና ወደ ቤተ-መንግስት ላኩ። እንደፈርኦን ልባቸው በትእቢት የታወሩት የቤተ-ክርስቲያን እና የመንግስት መሪዎች ለሰላምና ለምህረት የተዘረጋላቸውን እድል አበላሹ።
የቀድሞው ጳጳስ አቡነ ጳውሎስ እና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በይፋና በአደባባይ ስለዋልድባ መነኮሳት እንግልት ሽምጥጥ አድርገው ካዱ። ተወካይ መነኮሳቱ መጀመሪያ ያመሩት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ መለስ ዜናዊ ጽህፈት ቤት ነበር። አራት ኪሎ ቤተ-መንግት ድረስ ለመሄድ ድፍረት ማግኘታቸው ያስገረማቸው የስርአቱ ባለስልጣናት በለመዱት አይን ያወጣ ብልጣብልጥነት መነኮሳቱን ሊደልሉና ሊያግባቡ አልሆን ሲልም በሃይል አስገድደው መንግስትን ደግፈው በቴሌቪዥን እንዲቀረጹ ከባድ ትንቅንቅ አደረጉ። ፍርሃትን ያሸነፉት መነኮሳት የተቀረጹት ቃል ግን ለመንግስት የተሰጠውን የመጨረሻ እድል ነበር። እናም ይህ ቃላቸው በልዮ ሚስጥር እንዲጠበቅ ታዘዘ። ይህንን ተመሳሳይ ጥሪ ለአቡነ ጳውሎስ ይዘው የሄዱት መነኮሳት እዛም የእብሪትና የእምቢታ መልስ ጠበቃቸው። ነገር ግን አንድ አስደንጋጭ ክስተት ተፈጠረ።
ለሰላም መልእክት ወደ አቡነ ጳውሎስ ቅጽረ-ጊቢ የተጓዙት መነኮሳት አንድ ነገር “እረስተው” መሄዳቸው የተነገራቸው አቡነ ጳውሎስ ልባቸው ተንጠልጥሎ ምንነቱን ይጠይቃሉ። የጉዳዩን ክብደት ያልተረዱት አገልጋዮቻቸው ነገሩን አቅለው “መቋሚያ” እረስተው መሄዳቸውን ሲነግሯቸው አቡኑ በድንጋጤ ወደመሬት ይወርዳሉ። አገልጋዮቻቸው የደረስባቸው “ቅስፈት” አስደንግጧቸውና ግራ ገብቷቸው አፋፍሰው ወደ ሃኪም ያደርሷቸዋል። አባ ጳውሎስ ሃኪም ዘንድ ደርሰው ነፍሳቸውን ሲያውቁ አንድ ነገር ይከነክናቸውና በጥድፊያ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ደውለው ስለመነኮሳቱ ቆይታ ይጠያይቁ ገቡ። ጊዜ ሲከዳ ከባድ ነውና የሚፈሩትን ዜና መስማት ግድ ሆነባቸው።
አዎን እነዚያ መነኮሳት በዛም ሰፈር “መቋሚያ እረስተዋል”! ይህንን እንደ ክፉ መርዶ የተረዱት አባ ጳውሎስ እየደጋገሙ “ተቀሰፍን” “ተቀሰፍን” እያሉ በታላቅ ድምጽ ሲጮሁ ያረፉበትን ሃኪም ቤት ሰራተኞችና እረዳቶቻቸውን ድንጋጤ ላይ እንደጣሉ ይታወቃል። ጥንታዊ በሆነው የቤተ-ክርስቲያን ልማድ፣ የንስሃና የድህነት መልእክታቸው የተገፋባቸው መነኮሳት መቋሚያ ጥለው ከሄዱ እንደመርገምት ይቆጠራል። ውድ አንባቢያን እንደምታውቁት ልክ የዛሬ አመት የሆነውና እንደ ተአምር የተቆጠረው ጣምራ ሞት የጣምራ መቅሰፍት እዝ እንደሆነ ከዚህ መረዳት ይቻላል። ከዚህ መለኮታዊ መልስ ውጭ ቤተ-ክርስቲያንን እና ህዝቡን በጋራ አስጨንቀው የሚገዙት ሁለት የስርአቱ ቁንጮዎች በአንድ ላይ ላይ ለቅስፈት ሲዳረጉ ሌላ ምን ሊባል ይቻላል!
ክፍል ሶስት፡-ደረስጌ ማርያም
ይህች ታሪካዊት ቤተ-ክርስቲያን የምትገኘው በጎንደር ክፍለ ሃገር፣ በወገራ አውራጃ፣ ዳባትን አልፎ የወቅን ተራራን ተሻግሮ የዳሸን ተራራ እግርጌ በሆነቸው በደባርቅ ከተማ አቅራቢያ ነው። ታሪካዊ የሚያደርጋት ጥንታዊት መሆኗ ብቻ ሳይሆን የዘመናዊ ኢትዮጵያ መስራች የሆኑት አባ ታጠቅ ካሳ፤ አጼ ቴዎድሮስ ተብለው በአቡነ ሰላማ ተቀብተው የነገሱባት ሚስጥር የተቋጠረባት ደብር ናት። አምና ደግሞ ሌላ ታሪካዊ ጉባኤ አስተናገደች። ዋልድባ ገዳም ሱባኤ እንዳያደርጉ እጅግ ውስብስብ መሰናክል የተጋረጠባቸው መነኮሳት በአካባቢው የሚገኝ ተለዋጭ፣ የማይገመት እና አሳቻ ቦታ መፈለግ ነበረባቸው። ሽሚያቸውም ከሰአት ጭምር ነበር። የመጨረሻው-መጀመሪያ ሱባኤ መፈጸም የነበረበት የፍልሰታን ጾም ተንተርሶ ነው። ስለሆነም አዲስ አበባ የመጡበት የሰላም ጉዞ እንደተደናቀፈ ባስቸኳይ ሱባኤው መጀመር ስለነበረበት ቀሪዎቹ መነኮሳት መርጠው በቆዩት የደረስጌ ማርያም ተከናወነ።
የደብሯ ምእመናን እና ቀሳውስት ከተለመደው ውጭ በርከት ብለው የሚገኙት መነኮሳት ጉዳይ ግር ቢላቸውም ክርስቲያናዊ እንክብካቤያቸውንግን አልነፈጓቸውም። መነኮሳቱም ራቅ ወዳለ ገዳም እየተጓዙ እያለ በማሃሉ የፍልሰታ ሱባኤ እንዳይስተጓጎል በአቅራቢያው ካገኘናት ደብር ተጠጋን ብለው ሚስጥሩን ቀበሩት ጥርጣሬንም አጠፉ። እንዲያውም ህዝበ-ክርስቲያኑ ከበረከታቸው ለመሳተፍ ልባዊ አገልግሎት አቅርቧል። የእግዚአብሔርም ልዮ ሚስጥር በዚህች ታሪካዊት ደብር ተገልጾ ደረስጌ ማርያም ዳግም ታሪክ ተፈጸመባት። የመጨረሻው-መጀመሪያ ሱባኤ በዚህ መልኩ በአምላክ ፈቃድ ተፈጸመ። ያ ሱባኤ የትንቢቱ ፍጻሜ መዳረሻ የሆኑ አበይት ክስተቶች ታዮበት። በገዥው መደብ መደናገጥን ፈጠረ። የስርአቱም ሹማምንት እንደባቢሎን ሰዎች አልሰማማ ብለዋል። ከክርስቲያኑ ከተቆራረጡ ቆዮ፣ ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ከተካረሩ አመት አለፋቸው፣ አንቀላፍተው የነበሩት ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንኳ እረፍት በሚነሳ ሕዝባዊ የተቃውሞ ሰልፎች

አጨናንቀዋቸዋል። ታዲያ ቀጣዮ ምን ይሆን? ትንቢቱ እና የአርባ አመቱ ቀጠሮስ ደርሶ ይሆን? ለዚህ ቁልፍ የሆነው የመጨረሻው ሱባኤስ እክል ይገጥመው ይሆን ወይስ የተስፋይቱ ቀን ሳናስበው ጎበኘችን!
ክፍል አራት፡- የተስፋው ምእራፍ፣ የአርባ አመት ቀጠሮ
ከባዱ እና ውስብስቡ የመጨረሻው-መፈጸሚያ ሱባኤ የተያዘው ደግሞ በዚህችው የእመቤታችን የመታሰቢያ ጾመ-ፍልሰታ ላይ ነው። ለመሆኑ ከብዙ ገዳማት የተውጣጡት እነዚያ መነኮሳት የመጨረሻውን ሱባኤ የት እያደረጉ ነው? የመንግስት ሴራስ እንዴት ይታለፋል?
በመላ ኢትዮጵያ የሚገኙ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በዘንድሮ ፍልሰታ ለየት ያሉ ገዳማውያን መነኮሳትን ማስተናገዳቸውን በውል ሳይገነዘቡት እጅግ የበቁ አባቶች ከህዝበ ክርስቲያኑ ጋር ተመሳስለው ሱባኤውን ይፈጽማሉ። ለመጨረሻው ሱባኤ የተመረጡ የታላላቅ ገዳማት አባቶች በሁለት አበይት ምክንያቶች በአብያተክርስቲያናት ተበትነው እንዲያሳልፉ ወስነዋል። የመጀመሪያው ምክንያት ከመንግስት ውስብስብ መሰናክል እና እይታ ውጭ ለመሆን ይጠቅማል። በዋናነት ግን መላ ሕዝበ ክርስቲያኑ ለትንቢቱ ስምረት በግድ የሱባኤው ተሳታፊ መሆን ስላለበት ነው። ይህን የአርባ አመት የጦርነት፣ የአፈና፣ የርሃብ፣ የስደት፣ የውርደት፣ የግድያ እና የመለያየት ዘመን አልፎ የፍቅር፣ የደስታ፣ የሰላም፣ የብልጽግና፣ የአንድነትና የተስፋ ሃገር ለመድረስ ይህችን የመጨረሻ ሱባኤ ከእግዚአብሔር ጋር ተገናኝቶና ፈቃዱን ፈጽሞ መገኘት ግድ ይላል። ማነው አይኑን የገለጠ?
ምን እንደ ሙሴ ለፈጣሪ የቀረብን ብንሆን በዚህች የመጨረሻ ሱባኤ ፍጹም ታዛዥ ካልሆንን የምንጓጓላትን የተስፋይቱን ምድር እንኳን ልንረከባት ላናያትም እንችላለን። ታዲያ በእኛ አመጸኛ ልብ እንዴት ይህ ሊሆን ይችላል? ግን ለአምላክ የሚሳነው አለን! እንኳን እንደ አሸዋ የሞሎ የበቁ አባቶች ላላት ኢትዮጵያ ለአንድ ጻድቅ ሲል እንኳ ሰዶምና ገሞራን አላተረፈም! በጻድቁ ኖህ መርከብ ፍጥረትን ለዘር አልታደገም!
ግን ግን የአምላክ ልዩ ትእዛዝ በኢትዮጵያ ላይ በተለየ መልኩ መጥታለች። ሕዝበ ክርስቲያኑ ከገዳማውያን፣ መናንያን ጋር የመጨረሻውን የሃገር ሱባኤ እንዲያደርሱ በላካቸው መልእክተኞቹ በየምኩራቡ ሲነገር ከርሟል። ጆሮዎች ያድምጡ፣ አይንም ተገልጦ ይይ፣ ልቦናም ያስተውል። የመጨረሻው ምእራፍ ላይ ደርሳቹሃልና ተግታቹህ ጸልዮ። ስለቤተክርስቲያን ጸልዮ። ስለኢትዮጵያ ጸልዮ። ስለህዝቡ ጸልዮ። የተስፋይቱን ምድር አጥብቃቹህ እሿት ታገኟትማላቹህ።

ማስገንዘቢያ
ይህ ጽሁፍ ከምናብ ነው ከእውን፣ ከታሪክ ነው ከንግርት፣ ከምኞት ነው ከተጨባጭ፣ ከእምነት ነው ከፍላጎት፣ ከሸክም ነው ከተስፋ፣ እያላቹህ እንዳነበባቹህት እገምታለሁ። ልቦናችሁ እንደተቀበለው ተቀበሉት።
ሃሳብ መለዋወጥ ከፈለጋቹህ muleur@yahoo.com


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>