1.ለ6 ወር የታገደው “ሕገመንግስታዊ መብት”፤ 9 ወር ሞላው – ለአገር ገፅታ ሲባል
- ወደ አረብ አገራት ለስራ መጓዝ ከታገደ ወዲህ ወደ የመን መሰደድ ተባብሷል
- ባለፉት ሶስት ወራት ከ18ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የመን ገብተዋል
- አምና በተመሳሳይ ወራት ወደ የመን የተሰደዱት ኢትዮጵያውያን 14ሺ ናቸው
2.በደቡብ ኦሞ በአመት 300 “እርጉም” ሕፃናት ይገደላሉ – ለብሔረሰብ ባህል ሲባል
- በደቡብ ኦሞ ስለ ሐመር ድንቅ ባሕላዊ አኗኗር ምሁራንና ጋዜጠኞች ይነግሩናል
- በባሕላዊ እምነት ሳቢያ የወላድ መካን የሆኑ እናት፤ ባህላችንን እጠላዋለሁ ይላሉ
- የደቡብ ኦሞ ሸለቆ ላይ ያተኮረው የኤንቢሲ የቪዲዮ ዘገባ “የሞት ሸለቆ” ይሰኛል
3.በዋጋ ቁጥጥር የተነሳ የዳቦ ቤቶች ቁጥር እየተመናመነ ነው – ለህዝብ ጥቅም ሲባል
- ለምሳሌ በሙዝ ላይ የተጫነው የዋጋ ቁጥጥር ሲሰረዝ የሙዝ ዋጋ አልጨመረም
- ዳቦ ላይ የዋጋ ተመን ሲታወጅበት፣ የዋጋ ተመን ያልወጣለት አንባሻ ይበራከታል
- የታክሲ እጥረቱንም ተመልከቱ። የዋጋ ተመን በደርግ ጊዜ ለአገሬው አልበጀም
“ለስራ ወደ አረብ አገራት መጓዝ ለ6 ወር ታግዷል” የሚለውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ የሰማን ጊዜ፤ ብዙዎቻችን በግርምት “እኮ እንዴት?” ብለን አልጠየቅንም። እንደዘበት የተነገረንን መግለጫ እንደተራ ጉዳይ አደመጥነው። ይሄውና ዘጠኝ ወር አለፈው። እንግዲህ አስቡት። የሌላ ሰው ኑሮና ንብረት እስካልነካን ድረስ፤ በግል ሕይወታችን ውስጥ ወዲህ ወዲያ ለመንቀሳቀስ፤ መንግስትን የምናስፈቅድበት አንዳችም ምክንያት የለም። ለዚህም ነው፤ በደርግ ዘመን “የመውጫ ቪዛ” በሚል ሲደረግ የነበረው ቁጥጥር ሙሉ ለሙሉ እንዲቀር የተደረገው። በአገር ውስጥ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስም ሆነ ከአገር ውጭ የመጓዝ መብት፤ “ተፈጥሯዊ የሰው ነፃነት” ነው። ለነገሩማ፤ በሕገመንግስት ውስጥም ከመሰረታዊ ነፃነቶች ተርታ በጥቁርና ነጭ በግልፅ ሰፍሯል።
“ማንኛውም ኢትዮጵያዊ… በፈለገው ጊዜ ከአገር የመውጣት ነፃነት አለው” ይላል – አንቀፅ 32። እንግዲህ፤ ለነፃነት ወይም ለሕገመንግስት ክብር እንሰጣለን የምትሉ ሁሉ ይህንን አስተውሉ።
በፅሁፍ ላይ የሰፈረው አንቀፅ ቀላል አይደለም። መንግስት፤ መሰረታዊ መብቶችን በይፋ ማገድ የሚችለው፤ ለፓርላማ ቀርቦ በሚፀድቅ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” አማካኝነት ብቻ ነው። ለዚያውም ከፓርላማ አባላት መካከል 51 በመቶ ያህሉ ስለደገፉ ብቻ አይፀድቅም፤ ቢያንስ 67 በመቶዎቹ መደገፍ አለባቸው። ለዚያውም ከ6 ወር ላልበለጠ ጊዜ ብቻ ነው እገዳው የሚቆየው። ይህም ብቻ አይደለም። ስርዓት አልበኝነት ካልነገሰ ወይም የውጭ ወረራ ካላጋጠመ በቀር፤ አልያም አደገኛ ወረርሺኝና የተፈጥሮ አደጋ ካልተፈጠረ በቀር፤ መሰረታዊ መብቶችን ለማገድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣት አይቻልም።
ይሄ ሁሉ የተባለለት መሰረታዊ የሰዎች መብት ነው፤ በአዋጅና በፓርላማ ሳይሆን፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ የታገደው። እገዳውን ለማራዘምማ፣ አዋጅ ይቅርና ብጣሽ መግለጫ ማውጣትም አላስፈለገም። ለመሆኑ፤ ተፈጥሯዊውና በሕገመንግስት የሰፈረውን “የመንቀሳቀስ ነፃነት” እንደ ተራ ነገር ያለገደብ ለመጣስ፤ ምን ምን ማመካኛዎች ቀርበዋል? ሁለት ማመካኛዎች ናቸው የቀረቡት። አንደኛ፤ “እናውቅላችኋለን” የሚል። ሁለተኛ ደግሞ፤ “የአገር ገፅታንና ክብርን እናስጠብቃለን” የሚል።
የመጀመሪያውን ማመካኛ እንመልከት። በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ወጣት ኢትዮጵያዊያን በየአመቱ የሚሰደዱት፣ “ትክክለኛ መረጃ ስለሌላቸውና የስደትን አደጋ ስለማይገነዘቡ ነው” ሲባል እንሰማለን። ግን፤ ይሄ አባባል ሃሰት ነው። በሃረር በኩል ድንበር ለማቋረጥ ሲጓዙ ከተገኙት 700 ሰዎች መካከል ብዙዎቹ፣ ዘንድሮ ከሳዑዲ አረቢያ የተባረሩ ወጣቶች ናቸው። አደጋውን አያውቁም ልንል ነው?
በእርግጥ፤ የስደት ጉዞው ስንት ቀን እንደሚፈጅ እቅጩን አያውቁ ይሆናል። በጉዞ ላይ የሚገጥማቸው የውሃ ጥም፣ ዝርፊያ፣ እገታ… የቱን ያህል አደገኛ እንደሆነ በቁጥርና በመቶኛ አስልተው ለመግለፅ አይችሉም። ነገር ግን፤ ከሞላ ጎደል ሁሉም ስደተኞች በርካታ ፈተናዎች እንደሚገጥሟቸው ያውቃሉ። እንዲያውም ከሰማኒያ በመቶ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፤ ገና ከመነሻው ዋና ዋናዎቹን ፈተናዎች በዝርዝር ጠንቅቀው እንደሚያውቋቸው ዘንድሮ የተካሄደ ሰፊ የጥናት ሪፖርት ይገልፃል። ዩኤንኤችሲአር፣ አይኦሜ እና ሌሎች አለማቀፍ ተቋማት ያቋቋሙት ፅ/ቤት (RMMS) ነው ጥናቱን ያካሄደው። በሰኔ ወር ይፋ የተደረገው የጥናት ሪፖርት ላይ እንደተገለፀው፤ አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በጉዞ ላይና ከዚያ በኋላ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በዝርዝር ከማወቅም በተጨማሪ ህይወታቸው ለአደጋ እንደሚዳረግ ይገነዘባሉ።
ስለዚህ፤ “አያውቁም፤ መረጃ የላቸውም” የሚለው ማመካኛ፤ መሰረት የለሽ ውሸት ነው። ደግሞስ፤ የመረጃና የእውቀት ጉድለት ካለባቸው፤ መፍትሄው መረጃ በስፋት ማቅረብና ማሳወቅ እንጂ፤ “አትጓዙም” ብሎ በግድ መከልከልና ነፃነታቸውን መጣስ ምን አመጣው?
ከዚሁ ጋር አብሮ የሚነሳ ሌላ ማመካኛ አለ – በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ወጣት ኢትዮጵያዊያን በየአመቱ የሚሰደዱት፣ “በደላሎች ስለሚታለሉ ነው” የሚል። ይሄም፤ መሰረት የለሽ ውሸት ነው። ካልተሰደድክ ብሎ የሚያስገድድ ደላላ የለም። ደግሞም፤ አዲሱን የጥናት ሪፖርት መመልከት ትችላላችሁ። በስደት ወደ የመን ለመጓዝ የወሰኑት በደላሎች አማካኝነት እንደሆነ ከተጠየቁ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች መካከል፤ 98 በመቶ ያህሉ “አይደለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። በደላሎች ውትወታና ማታለያ ለስደት የተነሳሱት ወጣቶች፤ እጅግ ጥቂት ናቸው – ሁለት ከመቶ ብቻ።
እውነታው እንዲህ በግልፅ ቢታወቅም፤ ስለ ስደት በተወራ ቁጥር፣ እንደተለመደው “ስደተኞች መረጃ የላቸውም፤ ተጠያቂዎቹ ደላሎች ናቸው” የሚል ውንጀላ ከየአቅጣጫው እንደሚዥጎደጎድ አያጠራጥርም። ለምን? ለእውነታ ብዙም ክብር የለንም። ለነፃነትም ዋጋ ስለማንሰጥ፤ በመግለጫ ብቻ “የጉዞ እገዳ” እንጥላለን – “እናውቅላችኋለን” ወይም “የአገርን ገፅታ ታበላሻላችሁ” በሚል ማመካኛ።
ነገር ግን፤ በሕጋዊ መንገድ መጓዝ ቢታገድም፣ በዘፈቀደ መሰደድ መች ይቀራል? ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ ከ18ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ የመን ገብተዋል። በዚህ ከቀጠለ፤ በአመት ከ90ሺ በላይ ይሆናል። አደጋውን አስቡት። ከ2000 ዓ.ም ወዲህ፣ ወደ የመን ሲጓዙ ሁለት ሺ ያህል ሰዎች መንገድ ላይ ሞተዋል። በህጋዊ ምዝገባ ወደ አረብ አገራት የሚደረገው ጉዞ ስለታገደ፤ ያለ ቪዛ ወደ የመን የሚሰደዱ ሰዎች ሲበራከቱ በአመት ውስጥ ምን ያህሉ ሊሞቱ እንደሚችሉ አስቡት። በአማካይ ከ40 በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያዊያን በጉዞ ላይ እንደሚሞቱ ልብ ማለት ያስፈልጋል – በአንድ አመት ውስጥ። “አገር” ወይም “የአገር ገፅታ” ለሚባል ጣኦት መስዋእት እያደረግናቸው እንደሆነ አስቡት። በህጋዊ ቪዛ ሲጓዙ ከነበሩት ውስጥ የዚህን ያህል ሰዎች አይሞቱም ነበር።
“እናውቅላችኋለን” ከምንል ይልቅ “አናውቅላችሁም” ብንል ይሻላቸው ነበር። ምክንያቱም፣ በሺ የሚቆጠሩት ወጣቶች ያለ ቪዛ ለመጓዝ የመረጡበትን ምክንያት ሲጠየቁ፤ ህጋዊው ጉዞ በተንዛዛ ቢሮክራሲ ሳቢያ እንቅፋት ስለበዛበት ነው ብለዋል። ዘንድሮ ደግሞ ከነጭራሹ ታግዷል። ምን ይሄ ብቻ! ጭራሽ በድንበር በኩል ከአገር ልትወጡ ስትሞክሩ ተገኝታችኋል ተብለው እዚሁ አገራቸው ውስጥ የሚታሰሩ ወጣቶችን አይተናል። ወንጀላቸው ምንድነው? የትኛውን የወንጀል አንቀፅ ጥሰዋል? ማንን ጎድተዋል? ምንም!
በአጠቃላይ ሲታይ፤ የኛ ችግር፣ የአገራችን ችግር በአጭሩ ሊገለፅ ይችላል – ለእውነታ ዋጋ አንሰጥም። ለነፃነትስ? ለህገመንግስትስ? ለሰው ሕይወትስ? ለሰው ምርጫና ጥረትስ? ለሰብአዊ ክብርስ ዋጋ እንሰጣለን? አንሰጥም። በዚህም ምክንያት፤ “እናውቅላችኋለን” በሚል ወይም “የአገር ገፅታ” በሚሉ ሰበቦች፤ የሰዎች ተፈጥሯዊ ነፃነትና ሕይወት ላይ እንጫወታለን።
“አይ፤ ለእውነታ፣ ለነፃነትና ለሕይወት ክብር እንሰጣለን” የሚሉ ሰዎች እንደሚኖሩ ይገባኛል። “እገዳው ተገቢ ባይሆንም፣ ቢያንስ ቢያንስ በቀጥታ የሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ያነጣጠረ የመብት ረገጣ አይደለም” የሚል መከራከሪያም ያቀርቡ ይሆናል። በቀጥታ የሰው ሕይወት ላይ ያነጣጠረ ሲሆንስ ደንታ ይኖረናል?
ኢትዮጵያዊቷ የደቡብ ኦሞ ተወላጅ ቡኮ ባልጉዳ ይመስክሩ።
ሕፃናት ወደ ገደልና ወደ ወንዝ ይወረወራሉ
የ45 ዓመቷ ቡኮ ባልጉዳ የወላድ መካን ናቸው። ልጆቻቸውን በሞት የተነጠቁ እናት። የወለዱትን ህፃናት በአንዳች በሽታ ወይም በአንዳች አደጋ ማጣት ልብን ይሰብራል። በግድያ ሲሆን ግን፣ ለማሰብም ይከብዳል። እንደ ብዙዎቹ የደቡብ ኦሞ ሴቶች፣ ቡኮ ባልጉዳ ልጅ የወለዱ ጊዜ የደስታና የስጋት ስሜት ቢቀላቀልባቸው አይገርምም። የጎሳ መሪዎች መጥተው የህፃኑን አፍ ከፍተው ድዱን ያያሉ። ህፃኑ የመጀመሪያ ጥርሱን በላይኛው ድዱ ካበቀለ፤ ይዘውት ይሄዳሉ – “ሚንጊ” (እርጉም) ነው በሚል። “በጎሳችን ላይ መዓት የሚያመጣ እርጉም!” የተባለው ሕፃን ወደ ገደል፣ ወደ ወንዝ ይወረወራል። ይሄ ባህል ነው። ለዘመናት የዘለቀ ማይሞገት አይነኬ ባህል! “ለጎሳው” እና “ለባህሉ” ሲባል፤ ሰዎች መስዋእት ይሆናሉ።
ቡኮ ባልጉዳ የመጀመሪያ ልጅ ከተገደለባቸው በኋላ እንደገና ወልደዋል። እንደገና “ሚንጊ ነው” በሚል ተገደለ። እንዲህ ሲወልዱና ሲገደልባቸው ነው የኖሩት። በሕይወት ዘመናቸው ስምንት ወንድ ልጆችንና ሰባት ሴት ልጆችን ወልደዋል። 15ቱም ሕፃናት “ሚንጊ ናቸው” ተብለው ተገድለዋል። የወላድ መካን ያደረጋቸውን ባህል እንደሚጠሉት ይናገራሉ – ቡኮ ባልጉዳ። ዴይሊ ሜይል እንዳለው፤ 300ሺ የሕዝብ ቁጥር በያዙት የሃመር እና የባኮ ማሕበረሰብ ውስጥ በየአመቱ 300 ሕፃናት፣ “ሚንጊ ናቸው” ተብለው እንደሚገደሉ ገልፀዋል። ይሄው የሚንጊ ባህል በመላ አገሪቱ የተለመደ ቢሆን ኖሮ፣ በየአመቱ ከመቶ ሺ በላይ ሕፃናት በተገደሉ ነበር።
አሰቃቂ ነው። ግን ስለ አሰቃቂነቱ ሲነገር ሰምተናል? ተፅፎ አንብበናል?
ብዙውን ጊዜ የሚነገረንና የሚፃፍልን፤ ስለ ሐመር ወይም ስለ ደቡብ ኦሞ ድንቅ ባሕል ነው። እንዲያውም ብዙዎቹ ተናጋሪዎችና ፀሃፊዎች፤ በጋራ የተመካከሩና የተስማሙ፤ አልያም የታዘዙ ይመስል፤ ስለ ሚንጊ አይናገሩም፤ አይፅፉም። ግን የትዕዛዝ ወይም የምክክር ጉዳይ አይደለም። ለእውነታ፣ ለነፃነት፣ ለሰው ሕይወት እና ለሰብአዊ ክብር የላቀ ዋጋ ስለማንሰጥ ነው። በየአመቱ 300 ሕፃናት! ባሕልን ወይም ብሔር ብሔረሰብን በማክበር ስም ነው ይሄ ሁሉ የሚደረገው። ለዚያ ለዚያማ፤ በየአመቱ እንደ ቡኮ ባልጉዳ የመሳሰሉ የብሔረሰቡ ተወላጅ የሆኑና ልጆቻቸውን የሚነጠቁ 300 እናቶች እና 300 አባቶችስ? ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ ፀሐፊዎች … ለእውነታ፣ ለነፃነት፣ ለሰው ሕይወትና ክብር የማትቆሙ ከሆነ፣ ሥራችሁ ምንድነው? ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ለነፃነትና ለሰው ሕይወት የማትሟገቱ ከሆነ፣ አላማችሁ ምንድነው? እርስበርስ እየተጠላለፋችሁ ስልጣን መያዝ ብቻ!
ከዳቦ ወደ አንባሻ
በ2003 ዓ.ም ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ አዳዲስ የገንዘብ ኖቶችን በማሳተም ከፍተኛ የዋጋ ንረት የፈጠረው መንግስት፤ የዋጋ ንረቱን በነጋዴዎች ላይ በማሳበብ የዋጋ ቁጥጥርና የዋጋ ተመን እንዳወጣ ታስታውሳላችሁ። ከመነሻው፤ የገበያ ጠቃሚነቱኮ፣ ሰዎች በፈቃደኝነት የሚያካሂዱት መሆኑ ነው። ለምንድነው መንግስት በሰዎች ንብረት ላይ አዛዥ ናዛዥ የሚሆነው? “ለህዝብ ጥቅም” ሲባል ነዋ። “ለድሃው ጥቅም” ታስቦ ነዋ። ለሰፊው ሕዝብና ለድሃው ሕብረተሰብ ይጠቅማል እስከተባለ ድረስ፤ የሰዎችን ነፃነት መጣስ ይቻላል። አያችሁ? ለነፃነት ያን ያህልም ክብር የለንም። የዋጋ ቁጥጥርና የዋጋ ተመን የታወጀ ጊዜ ተቃውሞ አሰምተናል እንዴ? ብዙዎቻችን ደግፈናል። መንግስት ከጥቂት ወራት በኋላ የዋጋ ተመኑን ለመሰረዝ የወሰነው፣ ኢኮኖሚውን ይብስ እያቃወሰ እንደሆነ በግልፅ መታየት ስለጀመረ ነው። ነገር ግን፤ ሁሉም የዋጋ ተመን አልተሰረዘም – ለምሳሌ የዳቦ።
እንግዲህ አስቡት። የዋጋ ቁጥጥርና ተመን፣ የሰዎችን ነፃነት የሚጋፋ ቢሆንም እንደግፈዋለን – ለነፃነት ዋጋ ስለማንሰጥ። የዋጋ ቁጥጥርና ተመን፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን የሚያበላሽ እንደሆነ በግልፅ ቢታይም እንደግፈዋለን – ለእውነታ ዋጋ ስለማንሰጥ። ቢያንስ ቢያንስ ለእውነታ ክብር ቢኖረንኮ፣ የዋጋ ተመን እንደማያዋጣ ተገንዝበን ተመኑ እንዲሰረዝ ማድረግ እንችል ነበር። እስቲ ይታያችሁ። በመንግስት የገንዘብ ህትመት ሳቢያ የዋጋ ንረት ሲከሰት፣ እንደሌላው ሸቀጥ የስንዴ ወይም የዱቄት ዋጋም ይጨምራል። ዳቦ ጋጋሪው ግን፤ ዋጋ መጨመር አትችልም ተብሏል።
ይሄ ሊያስኬድ አይችልም። መንግስትም ይህንን ያውቃል። እናም፤ ዳቦ ቤቶች በድሮው ዋጋ የስንዴ ዱቄት እንዲያገኙ አደርጋለሁ አለ። አንደኛ ነገር፤ የመንግስት ቢሮክራት፣ “ምን አተርፋለሁ፣ ምን አገኛለሁ” ብሎ፣ በጊዜ ስንዴ ለማቅረብ ይተጋል? ከደሞዙ ውጭ ምንም አያገኝም። በጊዜ ስንዴ ባያቀርብ ኪሳራ አይደርስበትም። የወር ደሞዙ አይቀነስበትም። እናም፤ እንደምታዩት ዳቦ ቤቶች በየጊዜው የስንዴ እጥረት እየገጠማቸው ስራቸው ይስተጓጎላል። ነገር ግን፤ የስንዴ ዱቄት በፍጥነትና በድሮ ዋጋ ለዳቦ ቤቶች ቢቀርብላቸውም እንኳ ብዙም አያስኬድም። ዳቦ እያመረቱ በድሮው የዋጋ ተመን መሸጥ እንዴት ይሆናል? የቤት ኪራይ፣ የማገዶ፣ የትራንስፖርት… ብዙ ነገሮችኮ ዋጋቸው ጨምሯል። ለዚህም ነው፤ በየሰፈሩ ብቅ ብቅ ሲሉ የነበሩት ዳቦ ቤቶች እየተዳከሙና እየተዘጉ፣ ቀስ በቀስ የየከተማው የዳቦ ቤቶች ቁጥር ሲመናመን የምናየው።
በዳቦ ምትክ፤ አሁን አሁን የአንባሻ ጋጋሪዎች ቁጥር እየተበራከተ መጥቷል። አንባሻ ላይ የዋጋ ቁጥጥር አይደረግማ። ግን፣ ውድ ነው። ምክንያቱም እንደዳቦ፣ አንባሻ በብዛት ማምረት አይቻልም። ለነገሩ፤ በብዛት ማምረት ቢቻል እንኳ ዋጋ የለውም። ያኔ፣ አንባሻ ላይም የዋጋ ቁጥጥር ይጀመርና እሱም ይዳከማላ።
የዋጋ ቁጥጥር ለሰዎች ኑሮ እንደማይበጅ በተደጋጋሚ አይተነዋል። የታክሲዎች ቁጥር የተመናመነውና የትራንስፖርት እጥረት የተባባሰው ለምን ሆነና! ለነገሩማ፤ በደርግ ዘመን በስፋት ተግባራዊ የተደረገው የዋጋ ቁጥጥር፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከማቃወስና ድህነትን ከማባባስ ያለፈ ጥቅም አላስገኘም።
እንዲያም ሆኖ፤ የዋጋ ቁጥጥር ላይ ብዙም ቅሬታ የለንም። ለምን? እውነታውን ብናውቀውም፣ ነፃነትን የሚጥስ ቢሆንም፣ ኑሮን የሚረብሽ ቢሆንም፤ ለእውነታ፣ ለነፃነትና ለሕይወት ብዙም ክብር ስለሌለን የዋጋ ቁጥጥርን አንቃወምም።
ምንጭ፥ -አዲስ አድማስ