ከማስተዋል ይኑረን
ለዚህ ጽሑፍ ምክንያት የሆነኝ አቶ ወርቁ ፈረደ ፋክት መጽሔት ቅጽ ሑለት ቁጥር አርባ ሰባት ላይ ግንቦት 2006 ዓ/ም “ምኒልክና አርሲ” በሚል ርእስ ያቀረቡት ጽሑፍ ነው፡፡ ይህ ጽሑፍ በኢትሚዲያ ድሕረ ገጽም ለንባብ ቀርቧል፡፡የጽሑፌ ዓላማ አቶ ወርቁ ፈረደን በመደገፍ ወይም በመቃወም ለመተቸት ሳይሆን እርሳቸውም፤ ጽሑፉን ያነበበ ሁሉም፤ ወይም በአጋጣሚ የእኔን ጽሑፍ የሚያነብ ሁሉ የዘር ግንድን ወይም ቋንቋን መሰረት ያደረገ ማንነትን ተንተርሶ ፍርድ እንዳይሰጥ በስብእናው ብቻ ለራሱ ፍርድ እንዲሰጥና እግዚአብሔር ከረዳን አስተውሎት እንዲኖረን ለማድረግ ነው፡፡ በአማርኛ ሥነ ቃል “ምንትስን ያየ በእሳት አይጫወትም” የሚል አባባል አለ፡፡ “ምንትስ” የሚለውን ቃል የተጠቀምኩት ወድጄ ሳይሆን ይትበሃሉ ከሰው ስም ጋር ግንኙነት ሰለአለው ለመጥቀስ ስላልፈለኩ ነው፡፡ አንባቢ በዚህ ረገድ ይረዳኛል/ይገነዘበኛል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ለወንድሜ ለአቶ ወርቁ ፈረደ (በእድሜ ተቀራራቢ ከሆንን) ወይም ለአባቴ አቶ ወርቁ ፈረደ (በእድሜ ስለ አባት ያክል የሚበልጡኝ ከሆነ) ወይም ለልጄ ለአቶ ወርቁ ፈረደ (ስለ አባት ያክል የምበልጠው ከሆነ) ላስታውሳቸው/ላስታውሰው የምፈልገው ነገር አለ፡፡ ይህ የማስታውሰቸው ጉዳይ በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀል (Genocide crime) ላይ የተሰሩትን ሁለት ፊልሞችን እንዲመለከቱልኝ ነው፡፡ እነዚህም Hotele Ruwanda እና Shake Hands with Devil ናቸው፡፡ ሁለተኛው ፊልም ታሪኩ በመጽሐፍ ታትሞ ከወጣ በኋላ “የተተወነ” ነው፡፡ ወዳጄ አድራሻቸውን ከሰጡኝ መጽሐፉን ላውሳቸውና እንዲያነቡ እድል ልሰጣቸው እችላለሁ፡፡ ያላነበቡ ከሆነ፡፡ ቢያነቡ በዘር ጉዳይ እንዲህ ያለ መከራከሪያ ጭብጥ ያቀርባሉ ብዬ ስለማልገምት ነው፡፡ እነዚህን ሁለት ፊልሞች ያየ ወይም መጽሐፉን ያነበበ በእግዚአብሔር መልክና አምሳልየተፈጠረ ሰው ይህን ዓይነት በአንደበት ለመግለጽ፤ በአእምሮ ለማስብ፤ በጽሑፍ ለማስፈር የሚያስቸግር፤ የሚያም፤ የሚቆረቁር፤ የሚያፈዝ፤ የሚያደነዝዝ፤ የሚያቆስል፤ የሚጠዘጥዝ ድርጊት ይፈጽማል ብሎ ለማስብ ያስቸግራል፤ እራስንም ሌላውን ሰው የተባለውን ፍጥረትም በዘመናችን ሁሉ እንድንጠራጠር ያደርጋል፡፡
አቶ ወርቁ ፈረደ ሌላም መጽሐፍ እንዲያነቡልኝ በእግዚአብሔር ስም ልለምናቸው፡፡ ይህ መጽሐፍ የተጻፈው በቄስ ዴዝሞንድ ቱቱ ነው፡፡ ርእሱ፡- “The Future of Forgiveness” የሚል ሲሆን መጠኑም በጣም ትንሽ ስለሆነ አንድ ቀን ከሰዓት ቁጭ ብለው ቢያነቡት ጊዜ የሚወስድ አይደለም፡፡ ይህ መጽሐፍ ቄስ ዴዝሞንድ ቱቱ የደቡብ አፍሪካ የእርቅ ኮሚሺን ሊቀመንበር ሁነው በሰሩበት ጊዜ ከቀረቡላቸው እጅግ አሳዛኝ ነገሮች አንኳር አንኳሩን ሰው እንዲያውቀው መረጃ የሰጡበት ሲሆን መጽሐፉን የጀመሩበት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከጢሞቲዎስ መልእክት የተወሰደ፤ እግዚአብሔር በፈቀደ ጊዜ ሁሉም እንደሚከናወን በሚያሳይ ጥቅስ ነው፡፡ ላስተዋለውና ላጤነው የደቡብ አፍሪካዎች መንገድ እንደ ኢትዮጵያ ላለ አገር ፈውስ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፡፡
አቶ ወርቁ ፈረደ ለጽሑፋቸው ማጣቃሻ ያደረጓቸውን መጽሐፎች ጠቅሰውልናል፡፡ እጅግ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ጽሑፌ ከመረቀነ አእምሮ ሳይሆን ከደለበ እውቀት፤ ማስረጃ ካለው ምንጭ የተገኘ ነው ለማለት ነው፡፡ ዋቢ መጽሐፎች ምን ያክል ታማኝ ናቸው? የሚል ጥያቄ ከማንሳቴ በፊት በ1974 ዓ/ም ከብሪቲሽ ካውንስል ተውሼ ያነበብኩትን አንድ መጽሐፍ አስታወሰኝ፡፡ ጊዜው በመርዘሙ (ሰላሳ ሁለት አመት ስለሆነው) ጸሐፊውን ለማስታወስ ቢቸግረኝም ርአሱን ግን በደንብ አስታውሰዋለሁ፡፡ “The public Image of Casar” የሚል ሲሆን ወደ ዋናው ምንባብ ከመግባታችን በፊት መግቢያው ላይ፡- “When you study history study the historian, when you study the historian study the time in which that history is written” ይላል፡፡ ታሪክን ስታጠና ታሪክ ጸሐፊውን አጥናው፤ ታሪክ ጸሐፊውን ስታጠናው ታሪኩ
የተጻፈበትን ጊዜም አጥና እንደማለት ነው በግርድፉ ሲተረጎም፡፡ የትርጉም ባለሙያ የሆነ ከእኔ በተሻለ ሁኔታ አሳምሮ ሊተረጉመው/ ልትተረጉመው እንደሚችል/ እንደምትችል እገነዘባለሁ፡፡ ይህን ካልኩ በኋላ ወደ ዋናው ጉዳዬ ልምጣ፡፡
የጸሐፊው አቶ ወርቁ ፈረደ ጽሑፍ በእኔ እምነት ለአማራውም ለኦሮሞውም ቂም አስታዋሽና በቀል ቀስቃሽ ነው፡፡ ለዚህ ነው በቃለ አጋኖ የታጀበ የጥያቄ ምልክት በማድረግ ጠማማነትን ለማቅናት ወይስ ቂመኝነትን ለማጉላት?! የሚል ርእስ የመረጥኩት፡፡ በጥንቃቄ ጽሑፉን ለመረመረው ሰው ዋና ጭብጡ ምኒልክ አገር ለማቅናት አሬመኔ ጨካኝን፤ መንገድ አላስኬድ ያለን “ነውጠኛ” ለመግራት ሄዱ እንጂ ለሌላ ጉዳይ አይደለም፤ ተግባራቸው በሌላ አኋን ሊታይ አይገባውም የሚል እንድመታ ያለው ነው፡፡ ይህ አባባል በወንድሜ በአቶ ወርቁ ፈረደ የተጀመረ አይደለም፡፡ ጣሊያን አገራችንን
ኢትዮጵያን በእብሪተኝነት ስትወር በአለም መንግስታት መድረክ መሟገቻ ጭብጥ አድርጋ ያቀረበችው ምክንያት “ተግባሬ ወረራ ሳይሆን ይህን በጨለማ ውስጥ ያለ ሕዝብ “ለማሰልጠን” ነው::” የሚል ነው፡፡ የጣሊያን ጭብጥ አግባብ ነው በማለት የኢትዮጵያ ህዝብ ለጣሊያን አልተገዛም፡፡ ለአገራችን በዱር በገደሉ በፈፋውና በሽነተረሩ እየወጣንና እየወረድን አልገዛም ባይነታችን ላልተቋረጠ አምስት አመት ትግል ካሳየን በኋላ ነጻነታችንን በትግላችንና በመስዋእትነታችን ደማችንን አፍስን፤ አጥንታችንን ከስክሰን፤ ስጋችንን ነስንሰን መልሰን አግኝተናል፡፡ ሃያላን መንግሥታት ሙግታችንን፤ የድረሱልን ጩኽታችንን ሰምተው ከጎናችን ለመቆም፤ ፍትሐዊ የሆነ ዳኝነት ለመስጠት የጀርመንና የጣሊያን ጊዜያዊ ሕብረት፤ የሞሶሎኒና የሒትለር እብደት ቢያሰጋቸውም እሳቱ ሲለበልባቸው ግን ሳይወዱ በግድ ከጎናችን ቆመዋል፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በተባበሩት መንግሥታት መድረክ ያሰሙት ታሪካዊ የትንቢት ንግግርም ይህን በእሳት የመለብለባቸው ጉዳይ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ለእነርሱም የማይቀርላቸው መሆኑን ያረጋገጠ ነበር፡፡ ሲጠቃለል የአቶ ወርቁ ፈረደ ጽሁፍ አገር ለማቅናት፤ አረመኔን ለመግራት በሚል ሰበብ ያን ያክል ርቆ መሄድ ባላስፈለገ ነበር፡፡ ከውጭ ሲደርስብን እንቃወመው እርስ በርስ ሲሆን
እንቀበለው ካልተባለ በስተቀር፡፡ ግዳይ እየጣሉ ወንድነትን ማስመስከር በኦሮሞ ማሕበረሰብ ታሪክ ብቻ የተገደበ ተግባር አይደለም፡፡ ሕጻናት እየታረዱ ለመስዋእትነት የሚቀርቡበት ባህል እንደነበር ብሉይ ኪዳንን ጠንቅቆ ያነበበ ይረዳል፡፡ ሞሎክ ለተባለው “አምላክ” ህጻናት ይሰውለት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም ቢሆን ይህ ጉዳይ ይተገበር ነበር፡፡ አይደለም በዚያ በጨለማው ዘመን በደርግ ጊዜ የኢትዮጵያ አንዱ ክፍል (ከኦሮሞ ማሕበረሰብ ውጭ በሆነ አካባቢ) በውሃ ኃይል የሚንቀሳቀስ የእህል ወፍጮ አልሰራልኝ አለ ብሎ ሕጻን በማረድና ለሰይጣን መስዋእት በማቅረብ ለማስነሳት የተደረገን የወንጀል ድርጊት የፖሊስ ጋዜጣ በወቅቱ አስነብቦናል፡፡ ዝርዝሩን መረዳት ለፈለገ ፖሊስ ላይብረሪ በመሄድ ወይም ብሔራዊ ቤተ መዘክር (ወመዘክር) በመሄድ መረዳት ይቻላል፡፡ እኔ እራሴ የፎረንሲክ ምርመራ ዘርፍ የወንጀል ምረመራውን ያጣራሁትን የነፍስ ግድያ ወንጀል ምርመራ ልንገረዎት አቶ ወርቁ ፈረደ፡፡ ሰዎች እነማን ነበሩ ካሉ ከኦሮሞ ማሕበረሰብ ውጭ የሆኑ ሰዎች ናቸው (ዘር ወይም የሚናገሩትን ቋንቋ ያልገለጽኩት እኔም በዘር ፍረጃ እንዳልሰምጥ ስለፈራሁ ነው)፡፡ በቤታቸው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን ገብስማ ዶሮ ይታረዳል፡፡ በአንድ ወቅት ሚስት ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ በአይሮፕላን በረራ ስትጓዝ አድራ ጠዋት አዲስ አበባ ትገባለች፡፡ የገባችው ወር በገባ የመጀመሪያው ቀን ጠዋት አስራ ሁለት ሰዓት ላይ ነው፡፡ እጅግ ደክሟት ስለነበር እንቅልፍ ስለአሸነፋት ዶሮውን ማረድና መስራት አልቻለችም፡፡ ለገዳይዋ ባለቤቷም ይህን ነግራው ነበር፡፡ ዶሮው በወር
መግቢያ ለምን እንደሚታረድ ግን እርሷ አታውቅም ነበር፡፡ እርሷ የምታውቀው ታርዶ ተሰርቶ መበላቱን ብቻ ነው፡፡
ከድካሟ ለመለቃቅ ተኝታለች፡፡ አጅሬ ባል ዶሮ ካልታረደ የቤት ጣጣ ምን ሊያደርስበት እንደሚችል የሚያውቀው ሲወርድ ሰዋረድ የመጣ እምነትና ስጋት ነበረው፡፡ ይህን በመፍራት የሦሥት አመት ልጁ ባለበት የልጁን እናት በዶሮው ምትክ አረዳት፡፡ ቤቱን ዘግቶባት ሕጸኑንን ከእናቱ አስከሬን ጋር እንዲሆን ትቶ ሄደ፡፡ የወንጀል ድርጊቱን የፈጸመው ከወንድሙ ጋር በመሆን ነው፡፡ ለምርመራው ፍንጭ የሠጠን እቤት ተዘግቶበት ከእናቱ አስከሬን ጋር የተገኘው ድርጊቱን የተመለከተው ሕጻን ነበር፡፡ ሲጠቃለል በእያንዳንዱ ማሕበረሰብ ከልምድ ወይም ከግንዛቤ ሕጸጽ የሚመነጩ አስከፊና አሳዛኝ በሰብአዊ ፍጡር ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶች እንዳሉ አነዚህ ተግባራዊ ምሳሌዎች ያስረዱናል፡፡ በኦሮሞው ማሕበረሰብ ብቻ ሳይሆን ዓለም ሁሉ ቢፈተሽ በብዙ ማሕበረሰብ ታሪክ ብዙ ነገሮችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ እነዚህ ከሰው ልጅ ኋላ ቀርነት፤ ከእውቀት ማጣት/ማነስ ለወንድነት ወይም ለጀግንነት መለኪያ የሆኑ ተገቢ ያልሆኑ በሰብአዊ ፍጡር ላይ የሚፈጸሙ ዘግናኝ ነገሮች የሚቀሩት አእምሮአችን የተቃኘበት ያለማወቅ ስፍራውን ለእውቀት ሲለቅ ነው፡፡ በመሆኑም አሁን እነዚያ ነገሮች ፍጹም የሉም ባይባልም አዘውትረው አይሰተዋሉም፡፡ ሰው በራሱ መጥፎ አይደለም፡፡ ዛሬ ጨካኝ የሆነው ሰው ነገ ርህሩህና አሳቢ ወገን ሊሆን ይችላል፡፡ ጊዜ መስታውቱ ይህን አሳይቶናል፤ እናያለንም፡፡ ሌላው በጽሑፈዎ ውስጥ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ የአኖሌ ሀውልት ጉዳይ ነው፡፡ የሀውልት ነገር ከተነሳ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያሉ ሀውልቶችን አንድናስብ ያደርገናል፡፡ በእኔ እምነት ሀውልት በማስታወሻነት የሚቆመው መልካም ነገርን ለማስታወስ ብቻ አይደለም፡፡ ለዚህ አስረጂ አለኝ፡፡ የምኒልክ ሀውልት እርሰዎ እንዳሉት ቢስማርክነታቸውን ለማስታወስ መሆን ይችላል፡፡ ከዚያም ያለፈ ለኢትየጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው ጥቁር ሕዝብ ታሪካዊ ፋይዳ አለው፡፡ በጥቁሮችና በነጮች
መካከል በተደረገ ጦርነት ለመጀመሪያ ጊዜ በአመራራቸው ብስለት ነጭን ድል የነሱ ንጉስ ናቸው ምኒልክ፡፡ ለጥቁር ሕዝብ ትግል አይን የከፈቱና ወኔን ያቀጣጠሉ ናቸው፡፡ ምኒልክን በዚህ እንስታውሳቸዋለን፡፡ ይህ አንዱ ገጽታቸውና ሲወደስ ሲሞገስ የሚኖረው ነው፡፡ ሌላም ገጽታ አላቸው፡፡ ሰው ናቸውና ያለደካማ ጎን አልተፈጠሩም፡፡ ፍጹም እግዚአብሔር ብቻ ነውና፡፡
መሀል ስድስት ኪሎ ያለው የሰማእታት ሃውልት፤ አራዳ ጊዮርጊስ በታች ያለው የአቡነ ጴጥሮስ ሀውልት ደግሞ ግፈኞች በእኛ ላይ የፈጸሙትን በደል ያስታውሰናል፡፡ እንዴት ተባብረን ወራሪ ኃይልን እንዳሰወገድን የትግላችን ሕያው ምስክሮች ናቸው፡፡ የተፈጸመብንን ግፍና አልበገር ባይነታችንን የምናስታውስባቸው ናቸው፡፡ እንዚህ የጣሊያን የግፍ ጭፍጨፋ ማስታወሻ ሀውልቶች ጉዳዩ የውስጥ ጉዳይ ቢሆንና ከወገን በወገን ቢፈጸሙ ኖሮ በአገር ውስጥ ለተፈጸመ ግፍ አስታዋሽ አይሆኑም ነበር ማለት አይቻልም፡፡ የእነዚህ ሀውልቶች በማስታወሻነት መቆየት መጪውን ትውልድ የደረሰብንን በደል፤
ያደረግነውን ተጋድሎ ብቻ የሚያሳዩ ሳይሆን ለኢትዮጵያና ለጣሊያን ሕዝቦች አዲስ ግንኙነት መሰረት ናቸው፡፡ ጣሊያን ኢትዮጵያ ይህን ሀውልት ሰራች ብላ ቂም አልያዘችም፤ እንደውም ጣሊያን በሰጥችው ካሳ የቆቃ ግድብ ተሰርቷል፡፡ አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያና የጣሊያን ግንኙነት በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ ለምን ቢባል ሞሶሎኒ ወይም ወኪሉ ግራዚያኒ ለፈጸመው የግፍ ሥራ የአሁኑ የጣሊያን ትውልድ ተጠያቂ አይሆንም፡፡ ሀውልቶች የሚያሳዩት ከአልበገር ባይነትና ከመስዋእትነት ባሻገር ይቅር ባይነትን፤ አስተዋይነትን፤ ያ አሳፋሪና ዘግናኝ ነገር እንዳይደገም፤ ስህተት እንዳይፈጸም
አስተማሪነትን፤ ከዚህ በመነሳት መልካም የዓለም ማሕበረሰብ አብሮነትና ተምሳሌነትን ነው፡፡
የአኖሌ ሀውልት ለምን በዚህ መልክ አይታይም አቶ ወርቁ ፈረደ? የአኖሌን ሀውልት ከመስራት ለህዝቡ ለምን የመብራትና የውሃ አገልግሎት አቅርቦት አልተመቻቸልትም? በማለትና ጥያቁ በማቅረብ አቶ ወርቁ ፈረደ ለሀውልቱ የወጣው ወጪ ከንቱ እንደሆነ ነግረውናል፡፡ የምኒልክ፤ የአቡነ ጴጥሮስ፤ የሰማእታት ሀውልቶቸች ሲሰሩ የአዲስ አበባ ሕዝብ መብራትና ውሃ በበቂ ሁኔታ ነበረው? በቂ ት/ቤት፤ በቂ መኖሪያ ቤት ነበረው? ጉዳዩ “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” ካልሆነ የአኖሌ ሀውልት በአገራችን ዋና ከተማ በአዲስ አበባ ካሉት ከላይ ከፍ ብሎ ከጠቀስኳቸው ሀውልቶች የሚለይ አይደለም፡፡ መልካም ያልነበረውን የግንኙነት ታሪካችንን በማስታወስ ያ እንዳይደገም፤ በመተባበር፤ በመፈቃቀር፤ በመደጋገፍ፤ እንዴት ወደፊት አብረን መኖር እንዳለብን የሚያሳይ እንጂ በአያት ቅደመ አያት ለተፈጸመ ጉዳይ የዛሬው ትውልድ እዳ ከፋይ፤ ተበዳይም ካሳ ጠያቂ እንዲሆን አይደለም፡፡ ምናልባት ሀውልቱ ሲመረቅ የተደረጉ ንግግሮች፤ የተሰጡ አስተያየቶች የኦሮሞን ሕዝብ የሚወክሉ ተደርገው ተወስደው ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ መልክ ሊወሰዱ ግን አይገባም፡፡ መንግስታት ያልፋሉ ሕዝብ ግን አብሮነቱ ይቀጥላል፡፡ የአኖሌ ሃውልት መልካም ላልነበረው ግንኙነታችን ማስታወሻ፤ ለወዲፊት አብሮነታቸን ማስተማሪያ፤ ከስህተት መታቀቢያ እንጂ ቂም በቀል ቀስቃሽ ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ ለምን ቢባል የሰማእታት ሀውልት በኢትዮጵያና በጣሊያን መካከል ጦር አላማዘዘም፤ የጣሊያን ነጋዴ፤ ወይም ቱሪስት፤ ወይም ዲፕሎማት ኢትዮጵያ ሲመጣ አሉታዊ ተጽእኖ አልፈጠረም፡፡ ይልቁንስ አሁን በአቶ ወርቁ ፈረደ ስለ አኖሌ ሀውልት የቀረበው ጽሑፍ አሉታዊ ተጽእኖ አለው፡፡ ሊስተዋልና ሊታይ ይገባል ቂም ይቀሰቅሳል በሚለው ብቻ ሳይሆን በመልካም ጎኑ ተገቢ ያልነበረውን ግንኙነት እያስታወሰ ግንኙነታችን በእኩልነት ላይ እንዲመሰረት በማድረግ የጋራ ተጠቃሚ ያደርጋል ብለን ልንቀበለው ይገባል፡፡
ሦሥተኛው በአቶ ወርቁ ፈረደ ጽሑፍ ያለተመቸኝና ለአማራውም ለኦሮሞውም ቂም በቀል ቀስቃሽ ነው የምለው የቃላት አጠቃቀማቸው ነው፡፡ “ነውጠኛ”፤ “ገባር”፤ “መመጻደቅ” የመሳሰሉት ለጽሁፋቸው የሚመጥኑ ሆነው አላገኘኋቸውም፡፡ ነውጠኛ የሚለውን ቃል ለእንግሊዝኛው violent የሚል ቃል አቻ አድርገው ተጠቀመውበታል፡፡ አቶ ወርቁ ፈረደ እንደ ዋቢ የተጠቀሙበት ታሪክ ጸሐፊው የአርሲ ኦሮሞዎችን የውጊያ ችሎታ ፍጥነታቸውን ከጭልፊት፤ የፈረስ ውጊያ ችሎታቸውን ሁለት ሰው በአንድ ፈረስ ላይ በመሆን እንዴት በሃይለኝነት እንደሚዋጉ በመግለጽ ኃይለኛና ፈጣን ተዋጊዎች እንደነበሩ ሲገልጽ በጽሑፉ ወስጥ violent የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል ተጠቅሟል፡፡ ይህን ቃል የተጠቀመው የአርሲ ኦሮሞዎቸችን የውጊያ ጥበብ፤ ጀግንነታቸውን፤ ፍጥነታቸውንና ኃይለኛነታቸውን ለመግለጽ እንጂ ነውጠኛ ለማለት አይደለም፡፡ እረ ለመሆኑ የራሴን የግሌን አላስነካም በማለት የሚዋጋ ሰው እንዴት ነውጠኛ ይባላል? እንዲህማ ከሆነ አብዲሳ አጋ፤ አሉላ አባ ነጋ፤ ሞገስ አስገዶም፤ አብርሃም ደቦጭ፤ ዘርዓይ ደረስ ነውጠኛ ናቸው ማለት ነው? የአድዋው ድል የነውጠኞች ድል ነው ማለት ነው? “ገባር” እና “መመጻደቅ” የሚለው አገላለጽም በቀል ቀስቃሽ ሰውን ተንኳሽ ነው፡፡
ባይጠቀበሙት ይመረጥ ነበር፡፡
አቶ ወርቁ ፈረደ በገዳ ሥርዓት ውስጥ ሰው ያልገደለ ሥፍራ የለውም በማለት አትተዋል፡፡ እስካሁን ድረስ በታላላቅ ምሁራን ስለገዳ ሥርዓት ከተጻፉት መጽሐፎች አቶ ወርቁ ፈረደ ያነበቡት የተለየ ነው፡፡ እንደውም አይደለም ነፍሰ ገዳይ በሌላ የወንጅል ድርጊት የተቀጣ ወይም የተጠረጠረ ሰው በገዳ ሥርዓት ውስጥ ስፍራ የለውም፡፡ ለዚህ ነው በመግቢያዬ ላይ ከሰላሳ ሁለት አመት በፊት ስላነብብኩት መጽሐፍ የጠቀስኩለዎት፡፡ እነዚህ ታሪክ ጸሐፊዎች አንደኛው ወዶ ገብ ተዋጊ ሲሆን የተዋጋው ደግሞ ለአጼ ምኒልክ ነው፡፡ አጼውን ደግፎ ጦር ሜዳ ውሎ ግዳይ የጣለ (ምናልበትም ቅጥረኛ ተዋጊ
የሆነ) ከዚህ ውጭ ምን ይጽፋል ተብሎ ይጠበቃል? አቶ ወርቁ አንባቢ ይመስላሉ፤ ይሁን እንጂ በአንድ ጭብጥ ላይ በአንድ መጽሐፍ ንባብ ድምዳሜ ላይ የሚደርሱ ከሆነ ወጀብን መቋቋም ያቃታት ጀልባ እንዳይሆኑ እሰጋለሁ፡፡ አራተኛው ነጥብ በአቶ ወርቁ ፈረደ ጽሑፍ ላይ ሳላነሳ የማላልፈው የመስፋፋቱ ጭፍጨፋ ምክንያት በኦሮሞ የሚሰለቡ ሰዎችን ለመታደግ ነው መባሉና በጭፍጨፋው ጊዜ ኦሮሞዎች እናቶችንና ሕጻናትን ገደል ከተዋል መባሉ ነው፡፡ በአንኮበርና በአርሲ መካከል ሰፊ የሽዋ መሬት ዛሬም ሕያው ምስክር ሆኖ ይኖራል፡፡ አርሲዎች አንኮበር ወይም መንዝ፤ ሸንኮራ ወይም ቡልጋ ወይም ተጉለት ሂደው ሰልበው ነው የነፍስ አድን ጦርነት የታወጀው? ታሪክ በዚህ መልክ አልዘገበውም፡፡ አጼ ምኒልክም ከውጭ መንግስታት ጋር ስለመስፋፋታቸው የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች ይህን አያስረዱም፡፡ መስለብን ለመከላከል ሲባል ነው ምኒልክ ይህን እርምጃ የወሰዱት የሚለው ምክንያት ውሃ አይቋጥርም፡፡ ለምን ቢባል የወረራው ምክንያት መስፋፋት መሆኑ በግልጽ በራሳቸው በንጉሱ ታምኗልና፡፡ አቶ ወርቁ ፈረደ የምኒልክን ቢስማርክነት (አገር ፈጣሪነት፤ ግዛት አስፋፊነት) ከተቀበሉ ለምን የአርሲን መወረር ሰለባን ለመከላከል እንደሆነ አድርገው ምክንያት
ያቀርባሉ? ምክንያቶቸዎ እርስ በእርስ አይጣረሱም?
አንድ የሕዝብ ክፍል ሌላውን ሲወር ወራሪው ሴትና ሕጻን ይዞ ወረራ ሊሔድ የሚችልበት ምክንያት የለም፡፡ ባይሆን ተወራሪው ሴቶችም ህጻናቶችም ሊኖሩት ስለሚችል ተጠቁብኝ ቢል ምክንያታዊ መሆን የቻላል፡፡ ተደርጎም ከሆነ እጅ መገንጠል ጡት መዘንጠል የደረሰበት ልቡ የቆሰለ አእምሮው በበደል ከሰከረ ተጎጂ እንዴት ማስተዋል የተመላበት የዘመናዊ ተዋጊ ጦር ተግባር ይጠበቃል? በአርሲው ወረራ ጊዜ ሴቶችና ሕጻናቶች ከወራሪው ወገን ያን አክል አለቁ ቢባል ጉዳዩ ወረራ መሆኑ የቀርና ሰፈራ ወይም ስደት ይሆናል ማለት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ለጥናተዎ መነሻ የሆነው መጽሐፍ ተአማኒነት ይጎድለዋል ማለት ነው፡፡
ሲጠቃለል አቶ ወርቁ ፈረደ ጽሑፈዎ ከገንቢነቱና ከአቀራራቢነቱ ይልቅ ለሁለቱም ወገን ለተሰለበውም ለተቆረጠውም ቁስል አመርቃዥ በመሆን ፍጻሜ የሌለው አዙሪት (Vicious Circle) ውስጥ እየገባን እንድንዳክር የሚያደርገን እንጂ የሚያቀራርበን አይደለም፡፡ ጽሑፉን ሲጽፉት በቁጭት የጻፉት እንጂ ጊዜ ወስደው አስበውበት የጻፉት አይመስልም፡፡ ጽሑፉን ሲጽፉት ከስነ አመክንዮ ይልቅ ስሜት የገዛዎት የመስላል፡፡ ክርስቶስ ለስጋው ሳያደላ እንደተሰቀለልኝ ባምንም “ክርስቶስ ለስጋው አደላ” እንደሚባለው የማድላትና የመቆጨት ነገር ይስተዋልበዎታል፡፡ ዘር በደም ቢሆን ኖሮ ወሎ ዛሬ
ኦሮሞ ነበር፤ ጎጃምም ጎንደርም በከፊል፡፡ እኔና እርሰዎ አሁን ካለንበት ህልዎት ሌላ መሆን ባንችልም ልጆቻችን፤ የልጅ ልጆቻችን ነገ ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ አናውቅምና ይረጋጉና ጠማማነት ለማቅናት ወይስ ቂመኝነት ለማጉላት?! በሚለው ርእስ ላይ ያስቡ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻው kahalilukas@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡