Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የትንሳኤ ጥሪ ለኢሕአፓ –ቁጥር 2

$
0
0

የትንሣኤ ጥሪ ነሀሴ 2006
ቁጥር 2

‘’we must accept finite disappointment, but never lose Infinite hope.”
MARTIN LUTHER KING JR

“በትግል መሞት ህይወት” ብለው የተነሱት የኢሕአፓ ልጆች አሁንም እንደትናንቱ የሕዝብን መብት፥ የሀገርን ሉአላዊነት እና ክብር ከማንኛዉም ነገር አብልጠው ይታገሉለታል። ይህንንም ሲያደርጉ በድርጂቱ በኢሕአፓ ውስጥ ያገኙትን ልምድ ለሕዝብ በማካፈል ሕዝብን የስልጣን ባለቤት ለማድረግ ነዉ።

በአሁኑ ወቅት ያለብንን ትልቅ ፈተና ለማለፍና ሕዝብን ለድል ለማብቃት በመጀመራያ ሀገርን ከሁሉም በላይ ማስቀደም፤ በውስጣችን ያለዉን መከፋፈል ማጥፋት፡የድርጅትን ህይወት ከግለሰቦች በላይ ማየት፤ ሌት ተቀን ጠንክሮ መስራትን፡ ብሎም ለራስ ጥቅም ተገዢ እለመሆንን ይጠይቃል። የኢሕአፓ መሪወችም ሆነ አባላት እንደማንኛዉም ታጋይ የድርጂታቸዉና የኢትዮዽያ ሕዝብ አገልጋዮች መሆናቸዉን በመገንዘብ ድርጂቱ በኢሕአፓነቱ ሳይሆን፣ ታጋዩ በታጋይነቱ ሳይሆን በመሪዎቹ ሥም ሲጠራና ሲክፋፈል በግዴለሽለት ከአዩት በታሪክ ፊት ይጠየቃሉ።
ውድ ወገኖቻችን በሚያዝያ ወር ትንሳዔ በሚል የመሰባሰቢያ ርእስ አንድ ጽሁፍ አውጥተን መበተናችን ይታወሳል ከዚህም ጽሁፍ ቦኋላ በአንዳንድ የዜና ማሰራጫዎች በመቅረብ የሰብስባችን አላማ ምን እንደሆነ ማብራሪያዎች ለመስጠት ሞክረናል ሆኖም አሁንም የተነሳንለትን ዓላማ እንደገና ማብራራት አስፈላጊ በመሆኑ ትንሳኤ ቁጥር ሁለትን አውጥተናል።
Tensaye
አላማችን አንድና አንድ ነው ይሄውም በኢትዬጵያ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችን የሚያከብር ለህግ የሚገዛ በህዝብ ውክልና ያለው ስርአት እንዲገነባ ጠንካራ ትግል ማካሄድ ነው። ለዚህ ትግል በቆራጥነታቸው የተመሰከረላቸውና ከፍተኛ ልምድ ያላቸውን የኢህአፓ ልጆች እንደገና ማሰባሰብ ከፍተኛ ጥቅም ይኖረዋል ብለን እናምናለን። ቅሬታዎቻችንና እና ልዩነታቸውን አስወግደን ስርዓት በአለው መልክ በዴሞክራሲያዊ አሰራር ድርጅታችን አጠናክረን ብንወጣ ትግሉን ለውጤት ለማብቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
የትንሳኤ ንቅናቄ ጥረት አንድና ጠንካራ ኢህአፓ እንዲኖር ነው፤ በኢህአፓ ውስጥ የደረሰው መከፋፈል መሰረታዊ በሆኑ የመርህ ልዩነቶች የመጣ ሳይሆን ጓዶች በሰከነ መንፈስ በመግባባትና እንደቀድሞው በመተማመን ባለመወያየታቸው የተፈጠረ ችግር ነው ብለን እናምናለን። ስለዚህ መሰረታዊ ልዩነት በኢህአፓ ታጋዮች ማህል የለም እያልን አስታራቂ ሆነን መቅረብ አንችልም እኛም እራሳችን የሂደቱ አካል ነንና።

ይህ የአንድነት እንቅስቃሴ ሁሉንም የኢህአፓ ልጆች በማሰባሰብ ጠንካራ የሃገርና የህዝብ ሃይል እንዲሆኑ የማድረግ ጥረት በመሆኑ በትግሉ ውስጥ ያለፋችሁ ሃይሎች ሁሉ የኔ ጉዳይ ነው ብላችሁ ልትሳተፉበት ይገባል። ይህ ጥሪ ሀገራችን የገጠማት ችግር እንዲወገድላትና የሰላም፤ የፍትህ፤ የእኩልነትና የብልጽግና ሃገር እንድትሆን ለሚመኙ ወገኖች ሁሉ የሚቀርብ ጥሪ ነው። እንደገና እንዳንሰባሰብ ተጠናክረንም እንዳንወጣ ያልሆነ ቀለም የሚቀቡ ግለሰቦች ካሉ እባካችሁን ወደ ህሊናችሁ ተመለሱ ሁላችንም የምንኮራባቸው የተሰውት ጔዶች አጽም እና ደም ይፋረደናል እንላቸዋለን።
የኢሕአፓ መዳከምና መከፋፈል ለዘረኞችና ለጎጠኞች የልብ ልብ ሰጥቷል። ጠባቡም የወያኔ በድን ኢትዮጲያን እንደዘመነ መሳፍንት በጎሳና በጎጥ ከፋፍሎ ለማጥፋት ታጋዮችን ያስራል፡ይገድላል፡ይደበድባል፡ያሳድዳል፡ሲያስፈልግም ከጎረቤት አገሮች ጋር በመመሳጠር በማንአለብኝነት እስሮ ይወስዳል። ከዚህ በፊት ሱዳን በነበሩ ታጋዮች ላይ ያደረገውን በቅርቡ የመን ላይ በአቶ አንንዳርጋቸዉ ጽጌ ላይ አድርጎታል። የኢሕአፓ ልጆች ከተመክሮ እንደተማርነዉ አንድ ታጋይ መሰዋእትነት ሲከፍል በሺ ታጋዮች እንደሚተካ ስለምናውቅ የብዙሀን ድል ይገኛል በቆራጥ ትገል እያልን ድርጊቱንም በጥብቅ እናወግዛለን። እንዲያዉ ነገርን ነገር ያነሰዋልና በአረመኔዉ የደርግ መንግስት የታጋይ ጓዶቻችን እሬሳ መንገድ ላይ ዘርረዉ የዝንብ መጫወቻ ያደረጉትን ታላቁን ታጋይ ዮወሴፍ አዳነን አይኑን እየሸነቆሩ ቁዋንጃዉን እየቆረጡ የገደሉትን የፋሺስቱን ደርግ አባሎች ህይወት ወያኔ ሲያተርፍ ህይወታቸዉን በሙሉ ለህዝብ ሥልጣን ባለቤትነት እና ለዴሞክራሲ ሲታገሉ ሲወድቁ ሲነሱ የቆዩት ታጋዮች እነፀጋዬ ገ/መድህንን(ደብተራዉ)፡ እነ አበራሺ በርታን፡ እነ ስጦታዉ ሁሴንን ,,,ወዘተ የት እንዳደረሳቸዉ እስከ አሁን እንኩዋን አናዉቅም። ወያኔና የወያኔ መሪወችም ይህን ሚስጥር እንደያዙ አንዳንዶቹ እየሞቱ ቢሆንም ቀሪዎቹ ነገ በህዝብና በህግ ፊት ይጠየቁበታል።

አዎን የኢሕአፓ ጀግኖች ሙሾ ተወርዶላቸዉ፡ ደረት ተመቶላቸዉ፡ የስርዓተ ቀብር ተደርጎላቸዉ ባያዉቅም ያሞራ ቀለብ የዝንብ መጫወቻ ቢሆኑም፡ሰልፋቸዉ ከህዝብ ጋር ነዉና ሕዝብ ሲያሸንፍ ያን ግዜ ያን ቀን ታሪካቸዉ ይዘከራል። አሁንም ቢሆን ቀሪዉና ቀጣዩ ትዉልድ ሰንደቃቸዉን አንስቶ፡ መፈክራቸዉን አንግቦ በመታገል ከዓለሙት እና ከተሰዉለት ግብ ይደርሳል። በሕዝብ ሀይል የሚያምን ሁሉ ይህን አይጠራጠርም።ለዚህ ነዉ ትንሥኤ ኑ በቤታችን እንሰባሰብ ኑ እንታገል የትግላችን ጉዞ እንደ ኩሬ ዉሀ አንድ ቦታ ላይ ተገድቦ መንቀሳቀስ አልቻለምና መፍትሄ እንፈልግለት እያለ ጥሪውን የሚያቀርብ።
መሪነት ታላቅ ሀላፊነት እንደመሆኑ መጠን እንደ ሺልማት የሚሰጥ ገፀ በረከት አይደለም።ታግሎ ማታገልን ቀድሞ መገኛትን ከቂም ነጻ ሆኖ አርቆ አስተዋይነትን ይጠይቃል። “ከሊቀመንበር መንግሥቱ ጋር ወደፌት” ያሉትን ወይም በሙት መለስ “ራዕይ” የሚመሩትን ስናወግዝ ወደ ራሳችንም ዘወር ብለን እራሳችን ልንፈትሽ ይገባል። ከዚህ አንጻር በየትኛውም እርከን የታገላችሁና በመታገል ላይ ያላችሁ ጔዶች ሃላፊነታችሁን በአግባቡ እንድትወጡ አጥብቀን እንጠይቃለን።

ከዚህም ባሻገር የትንሥኤ ቡድን ህልም ኢሕአፓን አጠናክሮ ማውጣት ብቻ ሳይሆን ድርጂቱ እሱን ከመሳሰሉ ጠንካራ ድርጂቶች ጋር በመቀናጀት የጋራ ትግል እንዲያደርግም ይገፋፋል።ወቅቱ በጋራ መሥራትን አጥብቆ ይጠይቃልና።ሕዝቡም “ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ” የሚለውን ጥሪ አሁንም እያቀረበ ነው፤ ለሕዝብ የሚሰራ ሁሉ የሕዝብን ድምፅ መስማት አለበት።በህዝብ ያልታቀፈና የሕዝብን ቃል የማያከብር ድርጂት ብቻዉን እነደቆመ ግንድ ነዉ። የሳለ መጥረቢያ በቀላሉ ይቆርጠዋል ለሕዝብ ለመቆም የሕዝብን ድምፅ መስማት፡የሕዝብን ፍላጎት ማወቅ፡ ያንንም ተግባራዊ ማድረግን ይጠይቃል። ያለሕዝብ ድጋፍ ድርጂት ሊኖር አይችልም።ድጋፉን የሚሰጥ ሕዝብ ድምፁን የማሰማት መብት አለዉ የድርጂት መሪወች ይህንን ተገንዝበዉ መተባባር አለባቸዉ እልህ ግትርነትና በድርጅት ውስጥ ለራስ ከፍተኛ ቦታ መስጠት የተከፈለውን መስዋእትነት ያበላሻል። ልዩነትን በነጻ መድረክ ተወያይቶ መፍታት የግድ ባህልና የውዴታ ግዴታ መሆን አለበት። አባላትም መሪዎቻቸውን መከታተል የድርጅታቸውን ፖሊሲ መመርመር ልዩነትን ከማራገብ ይልቅ አንድነትን ማጠናከር ይኖርባቸዋል። በዚህ ዙሪያ ያሉትን ድክመቶቻችን ካስወገድን ኢህአፓን በማጠናከር ተባብሮ በመስራት የሕዝብን ትግል ከግብ ማድስ እንችላለን ብለን እናምናለን።

ለዚህም የተቀደሰ አላማ ኢህአፓ የከፈለውን መስዋእትነት የምናከብር በኢሕአፓ ዙሪያ እንደገና ለመሰባሰብና ኢህአፓን አጠናክሮ እንደቀድሞዉ ቆራጥና የተባበረ ትግል ለማካሄድ ለምትፈልጉ ሁሉ የትንሥኤ ቡድን በድጋሚ ጥሪዉን ያቀርባል። ይህንም እንቅስቃሴ ተካፋይ ለመሆን የምትፈልጉ ሁሉ በነዚህ ኢሜል አድራሻወች ልትገናኙን ትችላላችሁ

TINSAE64@GMAIL.COM
ስለ ሀገር ፍቅራችሁ እና ቅን አመለካከታችሁ አስቀድመን እናመሰግናለን
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>