እመ-ሰብ፣ እምዬ – ደጓ ያልታደሉ፣
ቆንጥጠው ያሳደጉህ – “አትዋሽ” እያሉ፣
የአደይ ምክር፣ ተግሳጽ.. ባክኖ ሲቀር ቃሉ፣
እናትህ ምን ይሉ?!
“ኮትኩቼ ያሳደግሁት፣ ክብሬን የሚጠብቅ..” የሚሉህ ልጃቸው፣ “አሳዳጊ የበደለው..” በሚሉት እርግማን ሲነሳ ስማቸው፣
አባ-ወራ፣ አባትህ – የቤቱ ምሰሶ ምንድን ይሰማቸው?!
ባለቤትህ ምን ትል? – የኑሮህ “ተጋሩ”፣ “ያ! ውሸታም ባልሽ..” – ስትባል በ”ዕድሩ”፤
በብሩህ ተስፋ ስንቅ ጉዞ የጀመሩ – ልጆችህ ምን ይሉ?!
አንገት እሚያስደፋ – አባት ሲታደሉ፤
ባልንጀሮችህስ፣ ወይ አብሮ አደጎችህ፣ ወይ ባልደረቦችህ.. ህሊና ያላቸው፣
ከጎንህ ለመቆም እሚሸማቀቁ – ጊዜ ፈርዶባቸው፤
ህሊናስ ወዴት ነው? – ማተብስ ምን ዋጠው?!
ሲወርድ-ሲወራረድ – ከትውልድ የመጣው፤
ምን ዓይነት “ባህል” ነው? – ከወዴት የመጣ፣
ሰብዕናን ሽሮ – ይሉኝታን ያሳጣ፤
እግዚኦ! ያሰኛል – እኔስ ላነተ አፈርኩ፣
አምላክ ይታረቅህ – ኧረግ! አበስኩ-ገበርኩ!
ጌታቸው አበራ
ነሐሴ 2006 ዓ/ም
(ኦገስት 2014)
——
የሕዝብን መሰረታዊ የነጻነት፣ የፍትህና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን በቀጥታ መመለስ ሲሳናቸው፣ (ወጣቱ ሀገር ተረካቢ ትውልድ በመልካም ስነ-ምግባር ታናጾ እንዳያድግ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ እስከሚፈጥር ድረስ) በግልጽ ባደባይ፣ በእጅጉ ዘቅጠው በውሸት ለተዘፈቁ የወያኔ ባለሥልጣኖች እና ለተላላኪዎቻቸው።