ከጌታቸው ሽፈራው
ባለፈው ሰኞ ዕልት ነው፡፡ ምን አልባትም ከአንድ ሰዓት በላይ ሊያስጠብቀን የሚችለውን የታክሲ ሰልፍ ትተን ከቤተ መንግስቱ በስተ ቀኝ ያለውን መንገድ ይዘን ወደ አራት ኪሎ አቀናን፡፡ በስተመጨረሻም ስላሴ በተክርስቲያን ደረሰን፡፡ በወቅቱ ማን የት ጋ እንደተቀበረ የተሻለ መረጃ የነበረው ብርሃኑ ተክለያሬድ የአስጎብኝነቱን ሚና እየተወጣ ነው፡፡ ‹‹እዚህ ጋር 60ዎቹ የተቀበሩበትን ነው፣ እዚህ ጋር አብዲሳጋ፣ እዚህ ጋ ጥላሁን ገሰሰ፣ ይህኛውን አዳራሽ ደግሞ ለሰርግ ያከራዩታል…..››፡፡
ብርሃኑ ቀጥሏል! ‹‹‹ስብሃት ገብረግዚያብሄርም እዚህ ነው የተቀበረው፡፡››
አሁን ስማቸውን የማላስታውሳቸውን የዘመኑን በርካታ ካድሬዎች የተቀበሩበትን ካሳየን በኋላ (አለማየሁ አቶምሳን አስታወስኩት) ከስላሴ ወደታች እያሳየ ‹‹በዛ ታች ባለው ቤተክርስቲያን ደግሞ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን ቀብር ታገኛላችሁ››፡፡ ያሳዝናል ስንት ካድሬ ስላሴ ተቀብሮ ስንቶቼ ደግሞ ‹‹ስላሴ አይመጥናችሁም!›› ተብለዋል፡፡
ትንሽ አለፍ ስንል አንድ በየ አቅጣጫው መብራት የሚንቦገቦግበት ቦታ ይታያል፡፡ ለካስ የመለስ ዜናዊ ቀብር ነው፡፡ ቤተክርስቲያኑ አጥር ግቢ ውስጥ ከሚታየው ሁሉ ደመቅ ያለው ቦታ ይህ መቃብር ብቻ ነው፡፡ በየ ቦታው ሻማዎች ይበራሉ፡፡ በርካታ መብራት አንፖሎች ይንቦገቦጋሉ፡፡ በርካታ አበቦች ዙሪያውን ተኮልኩለዋል፡፡ ቦታው ከመጠን በላይ ከበራው መብራት ጋር ተዳምሮ ያንጸባርቃል፡፡ ሁለት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወዲህና ወዲያ ይንጎራደዳሉ፡፡
ወታሮች ከሚንጎራደዱበት ቀበር ፊት ለፊት የሚታየው ቤተክርስቲያን በር ላይ በርከት ያሉ አማኞች መሬት ላይ ተደፍተው አምላካቸውን ይለምናሉ፡፡ ወታሮቹ ደግሞ የድሮ ገዥያቸውን አስክሬን በመሳሪያ እየጠበቁ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያኑ ላይ ብዙም ደመቅ ያለ ነገር (መብራት) አይታኝም፡፡ ምን አልባትም የቀብሩ መብራት ደመቅ ብሎ ስለበራ ይሆናል፡፡ ምዕመናኑ ከሚሰግዱበት በማይመጣጠን መልኩ ቀብሩ ዙሪያ የተነጠደው እብነ በረድ ያዳልጣል፡፡ ዙሪያውን የዕለት ደማቅ አበቦች ተደርድረዋል፡፡ ቀብሩና አካባቢው የሚገኙ አትክልቶችና ሳር በየ ቀኑ ብቻ ሳይሆን በየ ሰዓቱ እንክብካቤ እንደሚደረግላቸው በቀላሉ መገመት ይቻላል፡፡ ቀሪው የቤተ ክርስቲያኑ ክፍል ላይ እንዲህ አይነት ልምላሜም ሆነ እንክብካቤ አይታይም፡፡ እንዲያውም ምእመናን የሚሰግዱበት አብዛኛው የቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ወለሎቹ የተራቆቱ ናቸው፡፡
ለአቶ መለስ ቀብር ከፍተኛ እንክብካቤ ይደረግለታል፡፡ ቀን ላይ የዋሉ ሁለት የሰራዊት አባላት አሉ፡፡ መቼም ማታም ላይ ይቀየራሉ ማለት ነውና ሁለትና ከዚያ በላይ ጠባቂዎች ሊመደቡ ነው፡፡ በ6 ሰዓት ከሆነ የሚቀያየሩት ደግሞ ቢያነስ ከ10 በላይ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ያስፈልጋሉ፡፡ አትክልት የሚያጠጣ፣ ጽዳት የሚያጸዳና እነዚህን ሁሉ የሚያዝ አካል ያስፈልጋል፡፡ ሌሎች የቀብሩ ተቀጣሪዎችም ይኖራሉ፡፡ ያ ‹‹ቤተ ክርስቲያን (ቀብር)›› ከ10 እስከ 20 ሰው ሰራተኛ አለው ማለት ነው፡፡ አንዳንድ ቀበሌዎች 10 ፖሊስ የላቸውም፡፡ አብዛኛዎቹ የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች 20 ሰራተኛ የላቸውም፡፡ ሌሎች ተቋማትን እንዲሁ! ቤተ ክርስቲያኗ ራሷ ይህን ያህል ቋሚ ሰራተኛ ይኑራት አይኑራት እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
አዎ! ከዛ አጥር ግቢ ውስጥ ከቤተ ክርስቲያኑ በላይ ‹‹ቤተ ክርስቲያን›› ሆኖ ከፍተኛ እንክብካቤ የሚደረግለት የአቶ መለስ ቀብር ነው፡፡ ከታቦቱ በላይ ጥበቃ የሚደረግለት የአቶ መለስ አስከሬን ነው፡፡ በአጠቃላይ ከስላሴ ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ ከቤተ ክርስቲያኗም በልጦ ክብር እየተሰጠው የሚገኘው የአቶ መለስ ዜናዊ ቀብር ነው፡፡ ይገርማል! ለእነዚህ ሰዎች አቶ መለስ ከስላሴም በላይ ናቸው ማለት ነው?