Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

“ያልተሄደበት መንገድ” – ሊነበብ የሚገባው ድንቅ መጽሐፍ! (ነፃነት ዘለቀ)

$
0
0

ነፃነት ዘለቀ

ይህን የአንዱአለም አራጌን በራሱ አገላለጽ ከጠባቧ የቃሊቲ እስር ቤት የተጻፈ ግሩም መጽሐፍ ሳነብ የተሰማኝን ስሜት ባጭሩ ለመግለጽ እንጂ ሥነ ጽሑፋዊ ደንብ የተከተለ ሂስ ወይም የመጽሐፍ ግምገማ ለመስጠት አለመነሳቴን መግለጽ እፈልጋለሁ – መሆኑን እንዴት ከረማችሁ?

ከሁሉ በፊት ግን ከሰሞነኛ ጉዳዮች መካከል ቂላቂሉ ወያኔ በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ የሠራውን አስቂኝ ድራማ ስመለከት እያዘንኩ የታዘብኩትን በዓለም ወደር የማይገኝለት ምርጥ የምርመራ ውጤት በሚመለከት ትንሽ ልበል፡፡

Yeltehedebet-Menged-300x200የኢትዮጵያን ቴሌቪዥን በውነቱ አልመለከትም፤ አለመመልከቴ ስህተት መሆኑ ቢገባኝም ጤንነቴን አጥብቄ ስለምፈልገው ይሁነኝ ብዬና ቁም ነገር አገኝበታለሁ ብዬ ኢቲቪን አላየውም – ብዙዎች እኔን መሰሎች ስላሉ “የዐዋጁን በጆሮ” እንዳትሉኝ እንጂ፡፡ የሆኖ ሆኖ በቀደምለታ ከሰዎች ጋር የሆነ ቦታ ቁጭ ብዬ ቁርስ ቢጤ ስንቀምስ በፖሊስ ፕሮግራም የተከታተልኩት በዓይነቱም ሆነ በይዘቱ ድንቅ የሆነ የወያኔ የወንጀል ምርመራ ቴክኒክና ውጤት ያጫረብኝን ልዩ ስሜት በዚህ አጋጣሚ ሳላነሳው መቅረት አልፈለግሁም፡፡ ከእውነት ሰው መሆኔን ጠላሁ፡፡

“መርማሪው” ወያኔ አይታይም፤ ይህን የለመድነው ነው፡፡ ወያኔዎች ራሳቸውን እንደወንጀለኛ አድርገው ስለሚቆጥሩና ከአልቃኢዳ ጋር የሚያመሳስሏቸውን ድርጊቶች የሚፈጽሙ መሆናቸውን ሕዝቡ የተረዳው መሆኑን ስለለተገነዘቡ ይመስለኛል የመንግሥትን ሥልጣንና ኃይልም የጨበጡ “ምሁራኑ መርማሪዎች” በግልጽ በሚዲያ መታየትን የሚወዱ አይመስሉም ፤ እነዚህ ጭራቅ ገራፊዎችና ሀዘን አምላኪዎች (ሳዲስቶች) በራሳቸውም በመንግሥታቸውም የሚተማመኑ እንዳልሆኑና በሆዳቸውና በዘረኝነት ቁርኝታቸው ብቻ ተለክፈው በስሜት ፈረስ የዕውር ድምብር ግልቢያ ዜጎችን የሚያሰቃዩ ናቸው – ቀናቸው ሲደርስ ምን እንደሚውጣቸው ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው፤ አሣር አለባቸው – የቁናው ሥፍር እየተንደረበበ ይጠብቃቸዋል – እዚህ ወይም እዚያ፡፡ ከሞራል ዕሤቶቻችንና ከምርመራ ህግ በወጣ ሁኔታ አቡበከር የሚባለውን የሙስሊም ተቃውሞ አመራር አባል እጆቹን በእጀሙቅ አስረው የሚያካሂዱትን “ምርመራ” በአደባባይ በቲቪ ለዓለም ሕዝብ ሲያሳዩም “መርማሪው ሊቅ” መታየትን አልወደደም – አስጠሊታ ሣቁ ግን ከአንጀቱ ጥርስ ሳይሆን ከማተብ የለሽ አንገቱ ይሰማ ነበር፡፡ ስለዚህ የአንዲ ልዩነት እጆቹ አለመታሰራቸው እንጂ ሂደቱ ልክ እንደአቡቦከር ነው፡፡ ይህ የምርመራ ሂደትና ውጤቱ የሀገራችን የለየለት ውርደትና የወያኔን ማንአለብኝነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ ወያኔዎች ከግዑዝ ድንጋይ የማይሻሉ የመጨረሻ ደደቦች መሆናቸውን ምናልባትም ለሚሊዮንኛ ጊዜ የገለጡበት ማፈሪያ ድርጊት ነው፡፡ የሚታዘነው በተመርማሪዎቹ ሳይሆን በመርማሪ ተብዬዎቹ ነው፡፡ ከመነሻው የዘረኝነት ልክፍት ያሽመደመደውና ከዘር ማዕቀፍ ውጭ የማያስብ ደንቆሮ ማይምና ሳዲስት እንዴት አንድን የተማረን ሰው ይመረምራል? እንዲያው ትንሽም ቢሆን የተማረ ዘረኛ ወያኔ ጠፍቶ ነው ወይ? ይህ ዓይነቱ የአደባባይ ግፍ ሄዶ ሄዶ የሚያስከትለውን መዘዝ እንዴት አጡት? ድንቁርና ይህን ያህል በጀብደኝት ያሳውራል?

ወደአስቂኙ ድራማ ልለፍ፡፡ አንዳርጋቸው በ“ነፃ ኅሊናው” የሰጠውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ በደናቁር የወያኔ ወንበዴዎች እሳቤ ሊተላለፍ የተፈለገው መልእክት ይህን ይመስላል፤ “የግንቦት ሰባት ኅልውና ከእንግዲህ ግፋ ቢል ለሁለት ወራት ቢዘልቅ ነው፤ ወዲያም አለ ወዲህ ዕድሜው ከሁለት ወር አይበልጥም፡፡ የአውሮፓና አሜሪካ ምቾቱን ትቶ እንደኔ በረሃ ወርዶ የሚያታግል ቆራጥ ሰው አይኖረውም፡፡…”  የግንቦት ሰባት ቀሪ ዕድሜ ሁለት ቀንም ይሁን ሁለት ወር እሱ ሌላ ጉዳይና ወደፊትም የሚታይ ሆኖ ይህን የተናገረው ግን አንዳርጋቸው ጽጌ መሆኑን ልብ ይሏል – አንዲን በሚዲያም ቢሆን ባላውቀው ኖሮ ከአሁን በፊት “የተናገረውን”ና ገና ወደፊት “እንደሚናገረው በጉጉት” የሚጠበቀውን ሁሉ በበኩሌ ሳላንገራግር በሙሉ ልቤ አምኜ በተቀበልኩና ከወያኔ የሸፈተውን ልቤን ወደወያኔ በመለስኩ ነበር – ይህ ሁሉ ድካማቸው ታያ የማንን ቀልብ ለመሳብ ? በመሠረቱ እስካሁን ወያኔ የነበረ በአንዳርጋቸው ንግግር ምክንያት የወያኔነት ደረጃው አይጨምርም – በተቃራኒውም እስካሁን ወያኔ ያልነበረ በዚሁ የአንዲ ንግግር ምክንያት ንዴቱና ቁጭቱ ይጨምርና ወደድርጊት ይገባ እንደሆነ እንጂ ከተቃዋሚነቱ የሚያፈገፍግ አይመስለኝም፤ እናም የወያኔዎች የጅልነት ምጥቀት ያሳዝነኛል ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያንንና ዓለምን በጠቅላላው እስከዚህን ያህል መናቃቸው ምን ያህል ወራዳዎች – እደግመዋለሁ ምዕመናን – ምን ያህል ወራዳዎች መሆናቸውን ከማሳየት በስተቀር የአንዲ ስቃይና የሙሌት ኑዛዜ የሚጨምርላቸው አንዳችም አወንታዊ ነገር የለም – ይህን ነባራዊ እውነት ለመናገር ደግሞ የክር ወይም የሃቂቃ ጉዳይ እንጂ የግንቦት ሰባት አባልም ሆነ ደጋፊ መሆንን አይጠይቅም፡፡ የወያኔዎችን ውስጠ ምሥጢርና የግፍ ታሪክ በየመድረኮች ሲዘከዘክ ሚሊዮኖችን በዕንባ ሲያራጭና በትካዜ ባህር ሲያሰምጥ የምናውቀው አንዳርጋቸው ጽጌ በምትሃታዊ ፍጥነት ወደማፊያው መንግሥት ተገልብጦ ተናገረው የተባለውን እንዲያ ሲናገር ይታያችሁ፡፡ የምናውቀው አንዳርጋቸው የምናውቅለትን ጽኑ ፀረ-ወያኔ አቋሙን በሻጥርና በብዙ ገንዘብ ክፍያ በየመኖች ተይዞ በወያኔዎች እጅ በገባ በሁለት ሣምንታት ጊዜ ውስጥ ሲለውጥ በዐይነ ኅሊናችሁ ይታያችሁ፡፡

ግሩም የምርመራ ውጤት! ዓለምን የሚያስደምም ሣይንሳዊ የወንጀል ምርመራ ግኝት! በዚህ በአንዳርጋቸው ቃልና የመከራ ኑዛዜ ማፈር ያለበት ቀደም ሲል ለመጠቆም እንደሞከርኩት ወያኔ ብቻ ነው፡፡ ከወያኔ ውጭ ማንንም ሊያሳፍር አይችልም፡፡ እንዲያውም እኔ ብሆን ኖሮ “ግንቦት ሰባት የሚባል ድርጅት ከነአካቴው በሕይወት አለ እንዴ? አሁን እናንተ ስትሉ ሰማሁ፡፡ ማን ተናገር እንዳለኝ አላውቅም ዝም ብዬ ነበር እኮ በኢሳት ያንን ሁሉ ንግግር የምዘባርቀው፡፡ ደግሞ ብርሃኑን ብሎ ግንቦት ሰባት! ከመነሻው ግንቦት ሰባት ብሎ ነገር ሲኖር አይደለም ወርቆቼ! …” ብዬ አስደስታቸው ነበር እንጂ የሌለን ምሥጢር ለመደበቅ በመሞከር ሰውነቴን ለስቃይ አልዳርግም – ሊያውም በዚያ ኑዛዜየም ስቃዩን ቢቀንሱልኝ አይደል? ግን አይቀንሱልኝም – ስለዚህ ብናገርም ባልናገርም ለውጥ የለውም፤ ጠባችን በደም የሚጠራ እንጂ በውሃ ታጥቦ የሚጸዳ አይደለምና፡፡

እንደውነቱ ታዲያ አንዳርጋቸው ሊሰጠው የሚችለው የማይታወቅ የተከደነ አዲስ ምሥጢር ሊኖር ይችላል? ሁሉም ነገር እኮ ግልጽ ነው፤ ወያኔ የሚባል ሀገር አጥፊና ፀረ-ሕዝብ የሆነ የማፊያዎች ቡድን አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ውስጥ መሽጎ አለ – እሱን ለማስወገድ ደግሞ ዜጎች በተበታተነ ሁኔታም ቢሆን በየፊናቸው ጥረታቸውን እያደረጉ ነው፤ ምሥጢር ከተባለ ይህ ነው ምሥጢሩ፡፡  አንዳርጋቸው የትግል መስመሩ ስላበሳጫቸውና እየሠራ ያለው ነገር ለኅልውናቸው አስጊ ሆኖ ክፉኛ የሚያሳስባቸው በመሆኑ እርግጥ ነው እሱን ከመድረክ ገለል እንዲል ማድረግ ቢፈልጉ ያንን መቀበል ይቻላል – ሰይጣናዊ ፍላጎታቸውን ለማርካት የሄዱበት ርቀት ብዙ የሕግና የሞራል ችግር ማስነሳቱ እንዳለ ሆኖ፡፡ ከዚያ ውጪ ምሥጢር አውጣ ብሎ የዓለማችን ቤት ባፈራው የማሰቃያ ዘዴ ሁሉ ሰውን ማሰቃየት፣ በዚያም ሂደት ራስን ለትዝብትና ለስላቅ የሚያጋልጥ ነውረኛ የምርመራ ሂደት ማካሄድና ተመርማሪዎች የማያምኑበትን ነገር እንዲናገሩ ማድረግ በእግረ መንገድም “በሰላም አንገዛም፣ አንገብርምም ያሉንንና ሕዝብን የሚያሳምጹብንን ቀንደኛ ጠላቶቻችንን ‹እንዲህ አሸናናቸው!›፣ የወንዶች ወንዶች መሆናችንን ብልታቸውን እየቆረጥን አሳየናቸው…” በማለት ስብዕናን ለማዋረድ መሞከር ወደራስ የሚዞር አሉታዊ ውጤትን መጋበዝ መሆኑን መረዳት ይገባቸው ነበር፡፡ ለነገሩ ወያኔ ልብሱም ጉርሱም ቅሌትና ውርደት በመሆኑ በዚህ ረገድ የሚሰማው አንድም የሀፍረትም ሆነ የይሉኝታ ስሜት የለም፡፡ ጃዝ ብለው የለቀቁት 13 እና 33 ቁጥሮችም እየሳቁበትና እየተዝናኑበትም ቢሆን ወያኔ ለሚሠራው ግፍና በደል ሁሉ ቡራኬያቸውን አይነፍጉትም፡፡ እነሱስ ቢሆን በጭፍሮቻቸው አማካይነት በጓንታናሞና ኢራቅ ውስጥ አስከሬኖች ላይ እስከመሽናት በሚዘልቅ ኢሰብአዊነት ስንትና ስንት ግፍ ይፈጸሙ የለም? ልጅ ከአባት ቢማርና የጭካኔ ደረጃውን አዘምኖ ምሥኪን ኢትዮጵያውያንን ምድራዊ ገሃነም ውስጥ ቢዘፍቃቸው ዋኖቹ ሀዘን አምላኪዎች ይደሰታሉ እንጂ ከከንፈር ሽንገላ ባለፈ ሕዝቡን ሊታደጉት አይፈልጉም – ይህንንም አሳምረን እናውቃለን፡፡ ጭምብሉን ፖለቲካዊ የተለሳለሰ የሚመስል አካሄድም አንዘነጋም – አገም ጠቀሙን፡፡

በነገራችን ላይ 13 እና 11 ወይም 33 ደግሞ ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ ለሚያምንበት ሁሉም የትልቁ ቁጥር የአውሬው መገለጫ የ666 ቅንስናሾች ናቸው፡፡ አሥራ አንዶች በ110 የለበጣ ቀመር ቢያላግጡም እውነቱ ቀፎ የመለዋወጥ – የትሮይን ፈረስ ቅርጽ የማሻሻል ጉዳይ እንጂ ሲሙ ያው ነው – አሥራ አንድ፡፡ ለነገሩ ዝናር ባንገቴም ይሁን 11 ወይም ዜሮም ይሁን አንድ ሽንትር ዋናው ነገር ተግባር ነው፡፡ ሌላው ትርፍና ጨዋታን ለማሳመር ያህል በአጃቢነት የገባ ነው፡፡ እናም በሀገራችን ሁኔታ የሰውዬው ማንነት ምንም ይሁን ምን በስቃይና በግድያ የሚያምን ሁሉ እናት ክፍሉና ጥንተ አመጣጡ ከአውሬው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ክፉና ደግ መንፈሶች ኅብረት የላቸውም፡፡ ሩህሩህ መሐሪና አረመኔ/ጨካኝ ገዳይ አንድነት የላቸውም፡፡ መጽሐፉም ጣፋጭ ፍሬ በዛፍ ላይ ሳለ ይታወቃል እንደሚል ማን የማን ወገን መሆኑ በተለይ በዘመናችን በግልጽ ይታወቃል፡፡ ማን ነው የበሽታ ሕዋሳትን በቤተ ሙከራ እየፈለሰፈና እያራባ ለዓለም በተለይም ለኋላቀር ሀገሮች እንደ ዕርዳታ ስንዴ የሚያከፋፍል? ማን ነው የዓለማችንን የአየር ንብረት እያዛባና ዕድሜዋን በብርሃን ፍጥነት እያሳጠረ የሚገኘው? የዓለምን ጠቅላይ ገዢነት በትረ መንግሥት በጉልበት የተቆጣጠረውና “ለኔ ካልሰገዳችሁ ሀብትና ሥልጣን አይኖራችሁም” ብሎ ሁሉን እያስደገደገ የሚገኘውና በትዕምርተ ኅቡኣታዊ ባለአንድ ዐይን ፒራሚዳዊ ቅርጽ ወይም በፔንታጋራማቲን የኮከብ ቅርጽ የሚታወቀው ምሥጢራዊ ኃይል ማን ነው? ማን ነው አሁንም ሆነ ከአሁን በፊት መካከለኛውን ምሥራቅ እያተራመሰ ያለው? መፍለቂያው የሆነችን የአንዲት ትንሽዬ ሀገር ኅልውናና የበላይነት ለማስጠበቅ ሲል ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቱ የዓለምን የመንግሥታት ኅብረት እንደአሽከር ሰጥ ለምበጥ አድርጎ የሚገዛ ማን ነው? አይኤም ኤፍ፣ ዩኤን፣ ወርልድባንክ፣ ኔቶ፣ ሲአርኤፍ፣ … የማን አድቃቂ ክንዶች ናቸው? ለመሆኑ የዚህ ሞገደኛ የወቅቱ የዓለማችን ገዢ ዋና መሥሪያ ቤትና ቅርንጫፍ ቢሮዎቹ የት የት ናቸው? ጽዮንና ሀማስ የማን ልዑካን ናቸው? የግጭቶች መንስኤና የምክንያታዊነት ሚዛኑ ለማንም ያጋድል ዋናው የሁለቱም ተልእኮ ግና ለአውሬው ግብር የሚሆን ብዙ የደም ባህር ማቆር መሆኑን መዘንጋት የዓለም ነገር አያገባኝም ብሎ እንደመመነን ይቆጠራል፡፡ በየትኛውም የዓለም ክፍል – ማን ነው የጦር ኃይሎችን በሁለት ጎራ እየከፈለ በተፃራሪነት በማሰለፍ የሚሊዮኖችን ደም በከንቱ እያፋሰሰ ያለው? ኢራንና አሜሪካ በርግጥም ባላንጣዎች ይሆኑ እንዴ? በፍጹም፡፡ ጠላቶች መስለው ትያትር በመከወን ለአንድ ዓላማ ስኬት የሚተጉ የአንድ ገዢ አንድ አምሳል አንድ አካል ናቸው፡፡  ማን ነው በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከአፍ እስከገደፋቸው በንጹሃን ተሣፋሪዎች ጢም ብለው የሞሉ የሲቪል አውሮፕላኖችን(የማሌዥያን) ባልታወቀ ዕፀ መሠውርና በሚሳኤይል ድራሻቸውን ያጠፋው? ምን ዓይነት ወያኔያዊ ጨካኝ አንጀት ያለው ፍጡር ይሆን ይህን ያደረገ? ለምን ዓላማ? ቫቲካንንና መለስተኛ አውሮፕላን የምታህል የነጭ እርግብ ምስል ለማስመሰል ያህል በሰላም ምልክትነት በዋና የፓትርያርክ ጸ/ቤቱ በር ላይ ያቆመውን የኛኑ ኦርቶዶክስ ሳይቀር ከሞላ ጎደል ሁሉንም የሃይማኖት ተቋማት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ተቆጣጥሮ ሁሉንም ሃይማኖት አለኝ ባይ በአውሬው ትዕዛዝ ሥር ያደረገው ማን ነው? ለመሆኑ በአሁኑ ሰዓት ቅዱስ ሊባል የሚችል ቦታና ሰው አለ ወይ? ፖፕ ጆን ፖል አንደኛ፣ ፖፕ ቤኔዲክት 16ኛ፣ ‹አቡነ› ጳውሎስ የኛ… ሌሎችም የማን ወኪል ነበሩ? ፍየሎች በበጎች ጋጣ ውስጥ መሽገዋል፡፡ በጎች እያለቁ ነው፡፡ አውሬው ሆሊውድና ቦሊውድን ብቻ ሳይን ገዳማትንና ካቴድራሎችንም ከተቆጣጠረ ምዕተ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ጭካኔን በሚያስተምሩ ፊልሞች፣ በልቅና ባልተገሩ ኢ-ሞራላዊም በሆኑ ፖርኖግራፊዎች በተለይ የዓለምን ወጣት ትውልድ ጡጦ ከመጣሉ በእንጭጩ ለማምከን  ይህችን ዓለም ማንና ከየትስ ሆኖ እየገዛት እንዳለ መች አጣነው? የዚያ ‹ታላቅ› የጨለማ ንጉሥ የእጅ ሥራዎች የሆኑ ወያኔዎችም ባቅማቸው ቅድስቲቱን ሀገር ድራሽዋን ቢያጠፏት ከድጋፍ በስተቀር ማን ከልካይ አላቸው? በጎችስ ቢጮኹ አለጊዜው ማን ይደርስላቸዋል? ግን ግን አይዞን፤ የፍየሎችና የበጎች የመጨረሻ ዕድል ተለይቶ የሚታወቅበት የፍርድ ቀን በፍጥነት እየመጣ ነው፡፡ ብሎም ቢሆን ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ድል በምኞት ሊገኝ እንደማይችል ልብ ማለት ይገባናል፡፡ ብቻ ይህን መሰሉን ነገር በሆድ ይፍጀው ለሌላ ቀን በይደር ማቆየቱ ሳይሻል አይቀርም፡፡ ለነገሩ እኛን ምን አገባን? ሁሉም ከልኩ አይዘል፡፡

 

ከሰው ተውሼ እያነበብኩት ነበር – “ያልተሄደበት መንገድ”ን፡፡ በቅርብ ካነበብኳቸው በሀገር ችግር ዙሪያ ከሚያጠነጥኑ የቅርብ ጊዜ መጻሕፍት ውስጥ በኔ ዕይታና ለኔ ፍጆታ ይሄኛውን ወደር አላገኘሁለትም፡፡ አንዱአለም አራጌ ዋለ የተዋጣለት መጽሐፍ በመጻፉ – ሊያውም በዚህ አፍላ የጎልማሳነት ዕድሜውና በመከራ ውስጥ ሆኖ – ባለበት አድናቆቴ ይድረሰው፡፡ ወላድ በድባብ ትሂድ የሚባለው በዚህ ዓይነት አጋጣሚ ነው፡፡ ሚሊዮኖች ፈርተንና ለሥጋችን አድረን በየሽርንቁላው ተወትፈን በፍርሀት ቆፈን ስንርድ ሊያውም በእስር ቤት ውስጥ ሆኖ ይህን የመሰለ አብሪ መጽሐፍ ካለበቂ ማጣቀሻና ዋቢ መጻሕፍት በአዩኝ አላዩኝ ሰቀቀን ሌሊት ሌሊት እየተደበቁ መጻፍ ልዩ ጀግንነትና ተሰጥዖም ነው፡፡ አንዱአለምና መሰል የብዕርና የፖለቲካ ታጋዮች ለነፃይቱ ኢትዮጵያ በሕይወት እንዲደርሱ እግዚአብሔር ይታደገን፤ ይታደጋቸው፡፡ ቤተሰባቸውንም ይባርክ፡፡ ለእኛም ለባከንነውና ለራሳችን ጥቅምና ፍላጎት ስንል በ‹እስኪያልፍ ያለፋል› ተረት ራሳችንን እያታለልን የወያኔ ባርያ ሆነን ለጠፋነው ዜጎችም ፈጣሪ ረድኤቱንና ወኔውን ይስጠን፡፡ እንደዚህ ያሉ ዜጎች ባይኖሩን ኖሮ ሕይወት በጠቅላላው ለይቶላት ጨለማ በሆነች ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር እግዜር የተመሰገነ ይሁን፡፡ እርሱን መሰል ሌሎች ጸሐፊዎችንና ታሳሪዎችንም ጭምር እግዜር ይባርክልን፡፡ ለቤታቸውም ያብቃልን፡፡ የሚሳነው ነገር የሌለው የኢትዮጵያ አምላክ የመከራ ደብዳቤያችንን የሚቀድድና ሃራ የሚያወጣን አንዳች ኃይል ይዘዝልን፡፡ አሜን፡፡

ይህ መጽሐፍ የዋቢ መጻሕፍትን ገጽ ጨምሮ በጠቅላላው 320 ገጾች አሉት፡፡ በአራት ዋና ዋና ክፍሎች ሥር የተካተቱ 18 ርዕሶችንም ይዟል፡፡ ጠቅጠቅ ብሎ የተጻፈ በመሆኑ እንደሌሎች በርካታ መሰል መጻሕፍት በቀላሉ አይገፋም፡፡ የሆኖ ሆኖ በተለይ እስከማገባደጃው ድረስ ስሜትን ቆንጥጦ በመያዝ መነበብ የሚያስችለው ሥነ ጽሑፋዊ ውበትና ይዘታዊ ግርማ ሞገስ አለው፡፡ እናም አንብቡት፡፡ በነገራችን ላይ ይህን መጽሐፍ እያነበብኩ ወደ ገጽ 100 አካባቢ ስደርስ የተዋስኩትን እንደምመልስ ገባኝና ወዲያውኑ ከተማ ወጥቼ ገዛሁት፡፡ ተውሼ ያነበብኩትን ወይም እያነበብኩት ያለሁትን መጽሐፍ ስገዛ ይህ የመጀመሪያ ጊዜየ ነው፡፡ አንጡራ ሀብቴና የመጻሕፍት መደርደሪያየ አንዱ ፈርጥ እንዲሆን ተመኘሁ፡፡ ተመኝቼም አልቀረሁ፡፡ ለልጆቼ ውርስ ይሆናል፡፡ እናንተም አሁኑኑ ግዙና ንብረታችሁ አድርጉት፡፡ መጽሐፉ “ኩሎ አመክሩ ወዘሰናየ አጸንዑ” እንዲል፡፡

አመስጋኝ አማሳኝ እንዳልባል በዚህ መጽሐፍ የታዘብኳቸውን አንዳንድ ግድፈቶችም በዚሁ አጋጣሚ ብጠቁም ደስ ይለኛል፡፡ ጥቂት የማይባሉ የአርትዖት ችግሮች አሉበት፡፡ አሉታዊ መሆን ያለበት በአወንታዊ ወይም የዚህ ተቃራኒ ሆኖ የሚጻፍበት አጋጣሚ አልፎ አልፎ ይስተዋላል፡፡ አማርኛ ላይ ብዙውን ጊዜ የምታስቸግር ነገር አለች – ለምሳሌ “እኔን እንደሚያገባኝ እንዴት ረሳኸው?” በሚለው ዐረፍተ ነገር ውስጥ “ሚ”ን “ማ” ብናደርጋት ትርጉሙ ሙሉ በሙሉ ይለወጣል፡፡ “ጽንፍ” ለማለት “ቅንፍ” ብንል አንዳንዶችን ግር ሊያሰኝ ይችላል፡፡ የአርትዖት ሥራ ሽንፍላ እንደማጠብ ነው፡፡ በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች በብዙ አዳዲስ ዐይኖች ሊተባበሩበት የሚገባው አስቸጋሪ ሥራ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ የማይጠራበት ጊዜ አለ፡፡ ከዚህ አኳያ ይህን ቆንጆና ለታሪክ የሚቀመጥ መጽሐፍ ዐዋቂ ሰው እንደገና “ኤዲት” ቢያደርገው የበለጠ ማለፊያ ይሆናል፡፡ የግሌ አስተያየት ነው፡፡ (አንድ ወዳጄ የነገረኝ አንድ አርትዖታዊ ስህተት በጭንቅላቴ ብልጭ እያለ ‹እዚህ ላይ ካልጻፍከኝ ሞቼ እገኛለሁ!› ብሎ አስቸገረኝ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ የመሥሪያ ቤቱ የብድር ኮሚቴ ስብሰባ ይጠራል፡፡ ለተሰብሳቢዎችም “ከብድር ኮሚቴ…. ለጠቅላላ አባላት” የሚል ጽሑፍ ተበትኗል፡፡ ሁሉን ያስፈገገው ግን ጸሐፊዋ “ከብድር ኮሚቴ” ከሚለው ሐረግ ውስጥ የአንዱን ቃል የመጨረሻ ፊደል ሳትጽፈው መቅረቷና እስከዚያን የስብሰባ ጊዜ ድረስ ማንም ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ስህተቱን ልብ አለማለቱ  ነበር፡፡ ያቺ “ነገረኛ” ጸሐፊ የትኛዋን ሆሄ እንደዘነጋቻት እኔም አሁን ዘነጋኋት፡፡ )

ከሆሄያት ግድፈትና ሞክሼ ፊደላትን  በነባሩ ሰዋስዋዊ ልማድ ከመጠቀም አኳያ ከሚታዩ አንዳንድ ጥቃቅን “ስህተቶች” በተጓዳኝ ጥቂት የመረጃ መዛባትና የዘይቤና ፈሊጥ አጠቃቀም እጅግ አነስተኛ ችግር ሳይኖር እንደማይቀር እገምታለሁ፡፡ ለምሳሌ “ኢሕአፓ” የሚለው ምሕጻረ ቃል ሲፈታ እኔ የማውቀው “የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ” በሚል ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ግን “የኢትዮጵያ ሕዝብ አደራጅ ፓርቲ” በሚል ከአንዴም ሁለቴ ገደማ ቀርቧል፡፡ ፈሊጥን በተመለከተ “ለያዥ ለገራዥ” ለማለት “ለያዥ ለገናዥ” ተብሏል፡፡ በተጨማሪም የሃሳብ ድግግሞሽ በስፋት ይታይበታል፡፡ በዚያም ምክንያት አንድ አንባቢ በጀመረበት የስሜት ሞቅታ መጨረስ ባይችል ችግሩ ከዚህ የሃሳቦች መደጋገም የሚመነጭ ይመስለኛል፡፡ የሆኖ ሆኖ የመጽሐፉ አጻጻፍና ለኅትመት መብቃት በብዙ ችግር የታጠረ በመሆኑ የአሁኑ ይዘቱ ራሱ ከሚጠበቀው በላይና በአንጻራዊ ሁኔታ ከሌሎች በርካታ መሰል ጸሑፎች(እኔ ካነበብኳቸው) በጣም የተሻለ መሆኑን በበኩሌ ልገነዘብ ችያለሁ፡፡ በመሆኑም ይህ ጥረቱ ደራሲውን በእጅጉ ያስመሰግነዋል፡፡ እዬዬም ሲደላ ነው ጓዶች፡፡ እነኚህንና መሰል ሌሎች እንከኖችን አስተካክሎ በቀጣይ ኅትመት ለንባብ የሚያበቃው ወገን ከተገኘ መልካም ነው፡፡ ደግሞም የማይቻል አይመስለኝም፡፡

 

አንዱአለምን በዚህ መጽሐፉ ደርቤ እንዳነበብኩት የፕሮፌሰር መስፍን ደቀ መዝሙር ይመስለኛል፡፡ ይህን የምለው ፕሮፌሰሩ አንድ ወቅት እነብርሃኑ ነጋ “ሁለገብ ዘዴን በመጠቀም ወያኔን እንታገላለን” ባሉ ወቅት ክፉኛ ይተቿቸውና “እኛ ወደዚህ ‹የማይረባና ውዳቂ› የአስተሳሰብ ደረጃ አንወርድም”  ማለታቸውን በማስታወስና አንዱአለምም በዚያው ቅኝት አሁንም ድረስ በዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ ወንዝ ቀርቶ የደረቀ ምንጭ በማያሻግር የሰላማዊ ትግል ሥልት ወያኔን እንጥላለን ብሎ የሚያምን በመሆኑ ነው፡፡ እርግጥ ነው አንዱአለም አሁን ባለበት ሁኔታ በኃይል ወይም በጦር መሣሪያ ወያኔን እንታገል ብሎ ቢጽፍ የሚደርስበትን ተጨማሪ መከራና ፍዳ ስለምንገነዘብ ይህን አቋም ያርምድ ብለን በሰው ቁስል እንጨት አንሰድም፡፡ ይሁንና ቢያንስ ዝም ማለት ሲገባ ወያኔ የፈጠረው የኢትዮጵያ ውጥንቅጥ ችግር የሚፈታው ወያኔን በሰላማዊ መንገድ በመታገል ብቻ ነው የሚል እምነት በጭፍን ማራመዱን አልወደድኩለትም፡፡ (በነገራችን ላይ ኤርምያስ ለገሰ ቅድም በኢሳት አንድ ውይይት ላይ ሲናገር እንደሰማሁት የአንዳርጋቸውን በወያኔዎች መያዝ ኔልሰን ማንዴላ በኢዲያሚን ዳዳ እንደተያዘ ያህል እቆጥረዋለሁ ማለቱን እኔም በጣም እደግፋለሁ፡፡) ሰው ከሰው ጋር ቢታገል አሸናፊውና ተሸናፊው ይለያል፡፡ ከአውሬ ጋር ግን እንዴት መታገል ይቻላል? ውሾች በ“አስተሳሰብ” ከሚበልጡት ወያኔ ጋር እንዴት ስለሰላም መወያየት እንደሚቻል አንዱአለም ቢያስረዳኝ ደስ ባለኝ፤ ውሾ ሲሸናነፉ በሚያሳዩት ተፈጥሯዊ ምልክት ይግባቡና ጦርነቱን ያቆማሉ፤ ከዚያም በመካከላቸው ሰላም ይሰፍናል፡፡ ሁኔታዎችም ወደጥንቱ (statusquo ante) ይመለሱና ማኅበረከልባዊ ሕይወት ትቀጥላለች (“ከልብ” ውሻ ማለት ነው – “ል” ጠብቃ አትነበብም)፡፡ ወያኔ ግን ያሸነፈውን ሁሉ በሕይወት ያለውን ብቻም አይደለም የሞተውን ሳይቀር እስከመቃብር ድረስ የፕሮፓጋንዳ ሠራዊት እያዘመተ የቅርብ አጥንቶችንና የሩቅ አፅሞችን የሚፋለም ዶንኪሾት ነው፡፡ ይህን ባሕርዩን ለማወቅ በግድ እንደነአሥራት ወ/የስ መሞትና እንደነእስክንድር ነጋ መታሰር አያስፈልግም፡፡ ዛሬ ላይ ቁጭ ብሎ ወያኔን በሰላማዊ መንገድ ከሥልጣን አስነሳለሁ ብሎ መቃዠት በርግጥም ቅዠትና ሲያንስም የዋህነት እንጂ አንዱአለምን ከመሰለ በሳል የፖለቲካ ሰውነት የሚጠበቅ አይመስለኝም፡፡ ከዚህ ውሱን ነጥብ አኳያ ምን እንደነካው ሊገባኝ አልቻለም፡፡

አክራሪ ኦርዶቶክሳውያን እንዳይቀየሙኝ እንጂ የአንዱአለም የዋህነት (naivety?) ከ‹ቅድስት› ክርስቶስ ሠምራ ጋር ይመሳሰልብኛል፡፡ ‹ቅ.› ክርስቶስ ሠምራ – በገድሏ ላይ ተጽፎ እንደሚነበበው – ሰይጣንን ከእግዚአብሔር ለማስታረቅ ዕቅድ ትነድፋለች አሉ፡፡ … እርሱ ወዳለበት ሲዖል በቀጥታ ትሄዳለች፡፡ “ስፈልግሽ ኖሮ እዚሁ መጣሽልኝ?” ይላትና የክርስቶስ ሠምራን ነፍስ ይዞ ወደግዛቱ ሊያስገባት ሲል መላእክት ደርሰው ወደመጣችበት ወደገነት ይወስዷታል፡፡ በአጋጣሚው ግን 78 ሺህ የተኮነኑ የሲዖል ነፍሳት በቅድስቲቷ መንፈሳዊ አካል ላይ በመጣበቅ ወደገነት ይገባሉ፡፡ እምነት ነው፡፡ በየዘመናቱ በገዢዎችና በሃይማኖት መሪዎች ፈቃድ እንዲካተቱ የተደረጉና እነዚህን አሳሳች ይዘት ያላቸውንና እርስ በርስ የሚቃረኑ፣ “በእግዚአብሔር መንፈስ የተነዱ” ሰዎች ስለመጻፋቸው የሚጠቁም አንዳችም ማስረጃም የሌላቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ የተካተቱ አንዳንድ ጽሑፎችንና ሰይጣናዊ ሳጋዎችን ሳይቀር ላለመቀበል አንድ ሰው መብት ያለው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህን ኢትዮጵያዊ ሃይማኖታዊ ድርሰት ማመን አለማመን የማንም ውዴታ እንጂ ግዴታ ሊሆን አይገባም – እዚያው ውስጥ በሚገኙት ዘንድም ቢሆን፡፡ ታርጋ ሳይለጠፍብኝ ስለሃይማኖቴ ልናገር እንዴ? አይ፣ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ግን ማንኛውንም ሃይማኖታዊ አክራሪነትና ጽንፈኝነት የምጠላ አማኝ(theist) መሆኔን ብገልጽ ደስ ይለኛል፡፡ አነሳሴ ወዳልሆነ ነገር በመንሸራተቴ ይቅርታ – ምን ላድርግ ሁሉም ነገር አንሸራታች ሆኖ ዐረፈው እኮ፡፡ ብቻ አንዱአለም የዚህችን ቀና ሴት ባሕርይ የተላበሰ ግን በአፀደ ሕይወት የሚገኝ የማይቻልን ነገር ለመሞከር የሚተጋ የወንድ ክርስቶስ ሠምራ ይመስለኛል፡፡  

ሰላማዊ ትግል የራሱ መደላድል አለው፡፡ በቅድሚያ የሀገርህ ሰው ከሆነ ሰው ጋር፣ ዜጋህ ከሆነ ሰው ጋር፣ እንደዜጋው ከሚቆጥርህ ወይም ከሚመለከትህ የአገዛዝ ኃይል ጋር፣ በትንሹ ደግሞ ሰው መሆንህን አምኖ ከሚቀበል ሰው ጋር እንጂ ከአውሬና ከለዬለት የዲያብሎስ መንጋ ጋር በሰላማዊ መንገድ እታገላለሁ ብለህ ወርቃማ የመቶዎች ዓመታት ጊዜህን አታባክንም – አንዱአለም የሚለው ግን ዝንታለሙን እየታሰርንና እየተገደልን ነፃነታችንን ከወያኔ በችሮታ እንቀበል ነው – ምናልባትም በወዲያኛው የምፅዓት ዘመን፡፡ ሰዎች ወያኔን መረዳት እንዴት እንዳልቻሉ ወይም እንደማይችሉ ሳስበው ይገርመኛል፤ እንዲያውም ወያኔዎች፣ ሰዎች እንዲህ እንዲሆኑ – ማለትም በሰላማዊ መንገድ ከነሱ ጋር መታገል እንደሚቻል እንዲያምኑና እንዲያሳምኑ – የሚያደርግ ድግምት ቢጤ ሳይኖራቸው የሚቀር አይመስለኝም፡፡ አለበለዚያስ የሰላማዊ ትግልን ገፈት ቀማሽ ከሆነ አንዱአለምን ከመሰለ ብርቅዬ ዜጋ እንዲህ ያለ ተሳስቶ የሚያሳስት አነጋገርና እምነት ሊደመጥ ባልተገባ ነበር፡፡ ይቅርታ ይደረግልኝና ዝምታ ማንን ገደለ? በከንቱ መነቃቀፍ ከትዝብት በስተቀር ምን አወንታዊ ውጤት ያስገኛል? እንዳለመታደልና እንደርግማንም ሆኖ በኅብረት መታገል ቢያቅት ሁሉም ባመነበት ቢንቀሳቀስ ምን ክፋት አለው? ከአድማስ ማዶ ሊኖር ይችላል ተብሎ በሚታሰብ ሥጋት ከወዲሁ መቆራቆስ አግባብ ነው ወይ? ለዚህማ ወያኔ አለ አይደል? ይህን ስል አንዱአለማውያንና መስፍናውያን – በተወሰነ ደረጃ እኔንም ጨምሮ – ስሜታችን እንደሚጎፈንን ይሰማኛል፡፡ ግን ምርጫ የለኝም፡፡ የሚሰማኝን መናገሬ እንደወንጀል ሊቆጠርብኝ አይገባም፡፡ አውቃለሁ – አንዱአለም እሳት ውስጥ ነው፡፡ አልክድም – እኔም ከርሱ ባልተናነሰ ሁኔታ እሳት ውስጥ አለሁ፡፡ ልዩነታችን እርሱ ባመነበት ገብቷል፡፡ “ደስ”ም ያለው ይመስላል፡፡ የኔ ግን ከሁሉ ያጣ ሆኜ በዕብደትና በስክነት መካከል አንዴ ሰው አንዴ ዐፈር በመሆን እየተቀያየርኩ መረጋጋትና ሰላም የሌለው ሕይወት እገፋለሁ፡፡ ኅሊናህን አፍነህ መኖር ከመታሰር በበለጠ እንደሚጎዳ አውቄያለሁ፡፡ ሰው እንኳን ሳያውቅልህ በአእምሮ ስቃይ ምክንያት ከቤተሰብህም ከጓደኞችህም ‹እየተናጀስክ› ሰላምህን አጥተህ በትልቁ እስር ቤት መኖር በትንሹ እስር ቤት ከመኖር የበለጠ እንደሚያሰቃይ ተረድቻለሁ፡፡ መብላት፣ መጠጣት፣ መዳራትና በሰፊ ጎዳና መመላለስ ትርጉም የሚያጡበትና አንጎልህ ተቀፍድዶ ተይዞ ሰዎችን ሰላም በምትነሳበት ሁኔታ ለመኖር ያህል ብቻ መኖር ከለዬለት ከርቸሌ ያልተሻለ መሆኑን ከተረዳሁ ቆይቻለሁ፡፡ ስለሆነም ከአንዱአለም ባልተናነሰ የኔም እስረኝነት የዋዛ አይደለምና ሁላችንም አንድ ነን፡፡ እንዲህ የምለው ስለኔ ብቻ አይደለም – ስለሌሎች እኔን መሰሎችም እንጂ፡፡ እንዲህ የምለው ግን ለምንድነው? የማንን አንጀት ለማላወስ? ማንስ ነው ሆዴ ላይ ቆሞ ያናዘዘኝ? ሆ!   

በውሸት መከሰሱን፣ በውሸት ምሥክር (አዳፍኔ በሚላቸው) ዘብጥያ መውረዱን፣ በውሸት የግንቦት ሰባት አባልና የሽብር ጥቃት ሊፈጽም ከምንደኞች ጋር እያቀነባበረ ነው መባሉን፣ …. ሁሉንም ዘንግቶ ከእባብ ዕንቁላል እርግብ እንደሚፈለፈል ሊያስረዳን መሞከሩ አንዱአለም ወያኔን ለማወቅ ገና ብዙ ጊዜ የሚፈጅበት መሆኑን አመልክቶኛል – ጠሊቅ ሀገራዊና ታሪካዊ ዕውቀት ያለው መሆኑ ተይዞልኝ፡፡ እናም እላለሁ – ሰማይ ዝቅ መሬት ከፍ ቢሉ ወያኔ በሰላማዊ ትግል ሥልጣን አይለቅም፡፡ ይህን ፀሐይ የሞቀውንና ሀገር ያወቀውን ሃቅ በመካድ ከዚህ የተለዬ ህልም ማለም – እንደአካሄድ ባይከለከልም – ትዝብት ላይ ይጥላል፡፡ በነገራችን ላይ ክርስቶስም ለትግስቱና ለፍቅሩ ገደብ ነበረው፤ ለዚህም ነው በመሳም አሳልፎ የሰጠውን ይሁዳን የረገመው – በአንገቱ የወፍጮ መጅ ታስሮ ወደጥልቅ ባህር ቢወረወር እንደሚሻለው በምሬት በመናገር፡፡

ይቅርታችሁንና በዚህስ አንዱአለምን ተናድጀበታለሁ፡፡ ምን ነካው ግን? እንግዲያውስ ያበጠው ይፈንዳ በኢትዮጵያ እንደእስካሁኑ የስግብግብነትና ራስ ወዳድነት በሽታችንና የሥልጣን አራራችን ከሆነ በሰላማዊ መንገድ እንኳንስ ወያኔ ኢንጂኔር ግዛቸው ሽፈራውም ሥልጣን አይለቅም፤ እንኳንስ ወያኔ ኢንጂኔር ኃይሉ ሻውልም አይለቅም (በጤና ምክንያት …ካልሆነ)፤ እንኳንስ ወያኔ ፕሮ. በየነ ጴጥሮስም አይለቅም፤ እንኳንስ ወያኔ ዶር. መረራ ጉዲናም አይለቅም፤ እንኳንስ ወያኔ ዶር. ፍስሐ እሸቱም አይለቅም፤ እንኳንስ ወያኔ በቁሙ የሞተው ከሃዲው ልደቱ አያሌውም አይለቅም … (ዝርዝሩ ብዙና ብዙ ነው – ስንተዋወቅ? ግን እባብ ልቡን ዐይቶ እግሩን ነሣው ሆነና …)፡፡ የኢትዮጵያ መሬት አዲስ በሚፈልቅ ፍቱን ጠበል ካልተረጨ ይሄ የሥልጣንና የገንዘብ እንዲሁም የሴሰኝነት ጠንቆች በቀላሉ አይለቁንም – በኛ ባሱብን እንጂ እርግጥ ነው እነዚህ መሰናከያዎች የአጠቃላዩ የሰው ዘር መደናቀፊያዎች መሆናቸው የታወቀ ነው (ለምሳሌ የሰሞኑንና የቅርብ ሩቅ ጊዜውን የኢራቁን አልማሊኪንና የግብጹን አልሲሲን የሥልጣን ሱስ ብናይ በሰው ልጅ ራስ ወዳድነት መገረማችን አይቀርም – ይህ ነገር ወደኛ መጥቶ ከማይምነታችን፣ ከሥልጣን ወዳድነታችንና ከቦክሰኛው አስተዳደጋችን ጋር ሲደመርማ ምን ያሳይ፡፡) በኛ ሀገር ለሁሉም ነገር በተለይም ለጥላቻችንና ለራስ ወዳድነታችን ልጓም አጣን፤ ለከት ጠፋ፤ በቃኝን ተጸየፍን፤ ጠገብኩን ጠላን፤ ከይሉኝታና ሀፍረት ተፋታን – ስንገርም፡፡ እናም ለነዚህ ነገሮች ያለን ጥብቅ ቀረቤታ ከሌሎች የጥፋት ሰበዞች ጋር ተደማምሮ እንደሀገርም እንደሕዝብም ከናካቴው ከምድረ ገጽ ልንጠፋ – መለኮታዊ ጣልቃገብነት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ካልተከሰተ –  ዘመኑ ቀረበ፡፡ ውሸት ነው? ውሸት ነው ካልክ እውነት ነው ማለት ነው፡፡ “አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም” የሚል መጽሐፍ ዱሮ አነበብኩ ልበል? አዎ፣ ‹ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል› እንዲሉ ካልሆነ ለይቶልን ጠፍናል፡፡ አንወሻሽ፡፡

አንዱአለም ወያኔ በሰላማዊ መንገድ ሥልጣን እንደማይለቅ አሳምሮ ያውቃል፡፡ መጽሐፉ ላይ በገደምዳሜ ገልጾታል፡፡ እንደመፍትሔ በየገጾቹ የሚያቀርበው ግን ያንኑ የሰላማዊ መንገድ የትግል ሥልት ነው፡፡ “የሰላማዊ መንገዱ ካልሠራ” ይላል አንዱአለም ፈገግ ባደረገኝ ሁኔታ “የሰላማዊ መንገዱ ካልሠራ ሌላ የሰላማዊ መንገድ መሞከር ነው፡፡” ከመሰነባበታችን በፊት በመጽሐፉ መጨረሻ አካባቢ ገጽ 312 ላይ የሚገኘውንና ወያኔን በሰላማዊ መንገድ ማስወገድ ባይቻል በማስከተል ምን ማድረግ እንደሚገባ አንዱአለም የመጨረሻ መፍትሔ ብሎ የሚሰነዝረውን እንመልከት – ወጣቱ ፖለቲከኛ አይፈረድበትም፡፡ የት ነው ያለውና? አያድርስ ነው – እነዚህ ሰዎች አስጨንቀው ያዙንና እምንለውንም እያሳካሩ ግራ አጋቡን እኮ፡፡ አንዱ ለጓደኛው “ያዋስኩህን ዕቃ ባትመልስ ዋልህ! አሳይሃለሁ!” ይለዋል፡፡ “ምናባህ ልታደርገኝ አንት የውሻ ልጅ!” ብሎ ቢያፈጥበት “አይ፣ ምን አድርግሃለሁ ያው ታዝቤህ እቀራለሁ እንጂ” አለው ይባላል፡፡ እርግጥ ነው መናገር የማድረግን ያህል እንደማይከብድ አውቃለሁ፡፡ “አይ መሬት ያለ ሰው!” ብሏል አሉ የሚጋልበው ፈረስ የደነበረበት አንድ ሰው – “እንዲህ አድርገው፤ እንዲህ ያዘው” ባሉት ጊዜና፡፡ አሁንም እርግጥ ነው – ለተቀማጭ ሰማይ ቅርብ ነው፡፡ እርግጥ ነው – አታሞ በሰው እጅ ስታምር በገዛ እጅግ ግን ልታደናግር ትችላለች፡፡ ቢሆንም የሚሰማኝን ብናገር ቢያንስ ዴሞክራሲያዊ መብቴን “ባልተሸራረፈ” መልኩ እንደተጠቀምኩበት ከመረዳቴም በተጨማሪ የተወሰነ እፎይታን አገኛለሁ፡፡ ለማንኛውም ወደአንዱአለም የመጨረሻ የችግሮቻችን መፍትሔ እናምራና ለአፍታ እንመልከትለት፤

 

ትልቁ ጥያቄ ኢሕአዴግ የብሔራዊ ዕርቁን ጥያቄ አሁንም “የባልና የሚስት ፀብ አይደለም” ብሎ ቢያጣጥለው ምን ማድረግ ይቻላል? የሚለው ነው፡፡ በእኔ እምነት ኢሕአዴግ ከዚህ በኋላም (እስካሁን) ለ21 ዓመታት የዳከረበትን መንገድ የሚመርጥ ከሆነ ተቃዋሚዎች ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሆነው የሚጓዙ(በ)ት የራሳቸው አዲስ መንገድ መፈጠሩ አይቀሬ ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያን በአስተማማኝ መሠረት ላይ ለመገንባት (የ)ሚያስችለውን የብሔራዊ ዕርቅ መንገድ በመጓዝ ለፍትሃዊ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መንገድ መጥረግ የማይፈልግ ኃይል በኢትዮጵያ ሕዝብ ሰቆቃ ላይ የራሱን ግላዊ ወይም ቡድናዊ ጥቅም ብቻ የሚያስቀድም መሆኑን ያመለክታል፡፡ ኢሕአዴግም ይሄን መንገድ እስከመረጠ ድረስ የኢትዮጵያን ሕዝብ በኃይል ረግጦ የመግዛት ፍላጎቱን አሁንም ለመቀጠል እንደሚፈልግ ያሳያል፡፡ የማንወጣው መንገድ ቢሆንም ከተገደድን ግን ኢትዮጵያውያን በፀና ሰላማዊ ትግል ኢሕአዲግን ልኩን እንዲያውቅ ብሎም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ፈቃድ እንዲገዛ ማድረግ አማራጭ የለውም፡፡ … (መስመር የተጨመረ) 

ወያኔ ልኩን የሚያውቀው በሰላማዊ ትግል ነውን? ይህ ነገር እውነት ይሆን? ይህች ነገር አጭር የክበበው ገዳን ቀልድ ትመስለኛለች፡፡

በመሠረቱ ጥሩ መመኘት በራሱ መጥፎ አይደለም፡፡ ነገር ግን የምኞትን ገደብ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ አንዱአለም ከዕድሜ አንጻርም ይሁን ከገጠመኝ ማጠጥ/ማጠር የተነሣ በኢትዮጵያ ምድር አይመኙትን ምኞት በመመኘት እርሱን መሳይ የዋሃንን በተስፋ ዳቦ ለመቀብተትና በከንቱ ለማስገሳት ሲጥር እንመለከታለን፡፡ እዚህም ላይ ወያኔን አለማወቁ ያሳዝነኛል፡፡ ማንበብ ጥሩ ነው፤ ማወቅና መመራመርም ጥሩ ነው፡፡ ተስፈኝነት መልካም ነው፡፡ ተስፋ አለመቁረጥና ሩቅ ማሰብም ደግ ነው፡፡ ይሁንና ጓዳችን ውስጥ እንደመዥገር ተለጥፎ በመርዘኛ ጥርስና ምላሱ እያንገበገበን የሚገኘውን ወያኔ በሰላማዊ ትግል ይወገዳል ብሎ ማሰብና መስበክ አንድም ባለማወቅም ቢሆን የወያኔን ዓላማ የማራመድ ያህል ነው አለዚያም ሞኝነት ነው፡፡ ቢሆን በወደድን፡፡ ግን ፈጽሞ አይሆንም – ተምኔታዊነት (ዩቶፒያን መሆን) ነው፡፡ ኔልሰን ማንዴላ ለኢትዮጵያ አብነት ሊሆን አይችልም፤ ማኅተመ ጋንዲ ለኢትዮጵያ አብነት ሊሆን አይችልም፡፡ እነዚህ ምርጥ የዓለማችን ዜጎች የታገሉት ከሰዎች ጋር ነው፡፡ የኛን የሚለየው ትግላችን ከድፍን ቅል ዘረኞችና መቼም በማይበርድ እንዲያዉም እየሰላ በሚሄድ የጥላቻና የቂም በቀል አባዜ ከተሞሉ የባንዳ ልጆች ጋር ነው፡፡ ምናልባት አንዱአለም ያልተገነዘበው ይህንን ሃቅ ሊሆን ይችላል ብዬ እገምታለሁ፡፡ በዚያ ላይ በሰላማዊ ትግል ቀርቶ በመሣሪያም የሚነቀንቃቸው እንዳይኖር ሕዝቡን በማይምነት ጋርደው፣ ፍጹም ከደረጃ በታች በሆነና “A,B,C,D”ን በቅጡ በማያስለይ እንዲሁም ዜጎችን በሚከፋፍል የትምህርት ሥርዓት ትውልድን አደድበው፣ ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውያንን በማይረባ የጥቅም ፍርፋሪ ከፋፍለው፣ በዘረኛ የፌዴራል ፖሊስ፣ በደንቆሮ ካድሬና መከላከያ አፍነው፣ በቅንድብ ጥቅሻና በስልክ ቀጭን ትዕዛዝ ወንበዴዎቹ የሚፈልጉትን ፍርድ በሚያስተላልፍ ኮንዶም ዳኞችና ፍርድ ቤቶች ሀገር ምድሩን ሞልተውት፣ ዜጎችን በጎጠኛ የፀጥታና ደኅንነት መዋቅር ቀፍድደው፣ በድህነት ኮድኩደው፣ በተለይ ወጣቱን በልዩ ልዩ ሱሶችና በወሲብ የአዶከብሬ ዛር ዳንኪራ አስረግጠው፣ በመርዘኛ የጎሰኝነትና የዘረኝነት በሽታ ሕዝበ አዳምን በክለው፣ … ከጠማማ ጎጆው ባለፈ – የሰኞን ነፍሱን ወደማክሰኞ በማሳደሩ ከመደሰት በዘለለ ለሀገርና ለወገን የሚቆረቆር ዜጋ እንዳይኖር አድርገው የሀገሪቱን ኅልውና ገደል ጫፍ ላይ ጥለውታል፡፡ ይህን ኃይል በሰላማዊ መንገድ እጥላለሁ ብሎ ማሰብ ዕብደት ነው የምለውም ለዚህ ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካው አፓርታይድ ሥርዓት የመጨረሻ ፕሬዝደንት ኤፍ ደብልይው ደክለርክ ጭንቅላቱ ውስጥ ተሸክሞት ይዞር የነበረው ሊማር የሚችል ጤናማ ነጭ አንጎል እንጂ እንደወያኔ በድንቁርና የታጀለ ከመግደልና በሰው ስቃይ ከመደሰት ውጪ ምንም የማያውቅ የገማና የበሸቀጠ ጥቁር ጭቃ አልነበረም፡፡ ወያኔን በሰላማዊ መንገድ እታገላለሁ ማለት ለወያኔ አዲስና ለራሳቸው ለአባላቱም ቢሆን ግርታን የሚፈጥር ልዩ ተፈጥሮን እንደማላበስ ይቆጠራል፡፡…     

አፄ ኃ/ሥላሴ ለጉብኝት ይሁን ለሥራ ወዳንድ ቦታ ሲሄዱ አንዲት ችግረኛ ሴት ከነልጆቿ መንገድ ዳር ቆማ “ወድቃ በተነሳችው ባንዲራችን፣ በልዑል እግዚአብሔር ይሁንብዎ…” በማለት ባንዴራ ዘርግታ ታስቆማቸዋለች፡፡ ያኔ እንደዛሬው ዘመን መሪ ሲወጣና ሲገባ ግድግዳ እያስደገፉ (የሚገርም እኮ ነው!) ለገዢዎች የኅለውና መሠረት ከመሆናቸው አንጻር ውድና ብርቅ ሊሆኑ የሚገባቸውን ዜጎች በኢሰብአዊነት ማሰቃየት አልነበረምና ጃንሆይ መኪናቸውን አስቁመው በመውረድ “ችግርሽ ምንድነው?” ብለው ይጠይቋታል፡፡ ሴትዮዋም፣ “ጃንሆይ፣ ለምግብ ያላነሱ ለሥራ ያልደረሱ ስድስት ልጆችን ጥሎብኝ ባለቤቴ ሞተ…” ብላ ችግሯን መናገር ስትጀምር በቀልደኛነት የሚታወቁት የቀድሞው ንጉሣችን አጠገባቸው አጅበዋቸው ወደቆሙ መኳንንት ዘወር ብለው “አግባኝ ነው የምትለው?” ብለው እንደዋዛ ጣል ያደረጓት ቀልድ በሴትዮዋ ጆሮ ገብታ ኖሮ ድሃ መቼም ሞኝ ነውና “ጃንሆይ! ሆኖልኝ ነው! አ’ርጎት ነው!” አለች ይባላል፡፡ ቀልድ በአግባቡ ጥሩ ነው፡፡ ኃ/ሥላሴ ሴትዮዋን እንደማያገቧት ግልጽ ነው – ሴትዮዋ ግን ድሃና በዕውቀትም ዝቅተኛ ናትና በጣለችው ተስፋ አንፈርድባትም፡፡ ከወያኔ ጉያ ሕዝባዊ ሥልጣን በሰላማዊ መንገድ ይገኛል ተብሎ ተስፋ ማድረግ ግን ከሴትዮዋ የበለጠ ጅል መሆንን የሚያመለክት እንጂ የወያኔን ተፈጥሮ ከመገንዘብ የሚመነጭ ገምቢ ዕውቀትና ጥበብ አይመስለኝም፡፡ ይህን የሚመር ቀልድ የሚቀልዱ ሰዎች ራሳቸውን ቢመረምሩ የተሻለ ነው፡፡ ሰላማዊ ትግል ደግሞም በኢትዮጵያ – ሆ!

በጦርነት የሚገኝ ነገር መልካም ነው እያልኩ እንዳልሆነ ግን ይመዝገብልኝ፡፡ ምርጫ ከጠፋ ግና ምን ይደረጋል? ከሁለት መጥፎዎች የተሻለውን መምረጥ የምንገደድበት ጊዜ ይኖራል፡፡ እናም ሰው ካልሆነ አውሬ ጋር እየታገሉ ከማለቅ ቢያንስ የራሴ ነው ከሚሉት ጨካኝና አምባገነን መሪ ጋር መፋለም ይመረጣል – ለዚያም መብቃት እኮ መታደል ነው፡፡ እንደሚመስለኝ አሁን ሰዎችን እያሳሰባቸው ያለው የማያሳስብ ነገር ነው፡፡ ቀድሞ የመቀመጫየን ያለችው ፍጡር ወድዳ እንዳልሆነ መረዳት ተገቢ ነው፡፡ “ሌላውን እሾህ በመቀመጫየ ተቀምጬ ራሴው እነቅለዋለሁ” ማለቷ ነው፡፡ እና ያልበላንን የሚያኩልን ወገኖች አደብ ቢገዙልን ብዙ እንደረዱን ይቆጠራል፡፡ ለነገሩ ወያኔን ማንም ደገፈው ማን – በማወቅም ይሁን ባለማወቅ -  ወቅቱን ጠብቆ ወረደ መቃብሩን ሳይወድ በግዱ መቀበሉ አይቀርም፡፡ አንድዬ በመንበሩ ካለ – አለም- ይህን ሁሉ ግፍና በደል የፈጸሙ ሰው መሳይ “ሰዎች” የቁናቸውን ሳይከፈሉ ይቀራሉ ብሎ ማሰብ የታሪክንና የፈጣሪን ፍርድ አለመረዳት ነው፡፡ የሞተ ይነሳል፤ የተኛ ይነቃል፤ የቆመ ይቀመጣል፤ የተጋደመ ይቆማል፡፡ ለሁሉም ጊዜ እንዳለው ዛሬ አይደለም የምናውቀው፡፡ ታሪክና እግዜሩ ወያኔ ላይ ሲደርሱ ሥራቸውን ያቆሙ ይሆን? ለጅላጅሎቹ ወያኔዎች እንዲያ ሳይመስላቸው የሚቀር አይመስለኝም፡፡ ለኔ ግን በፍጹም! ጊዜው ቀርቧል፡፡

አገባቤና አወጣጤ የተምታታ ነገር ያለበት መሆኑ ይሰማኛል፡፡ ለዚህ የተምታታ ነገሬ ማንን ይቅርታ መጠየቅ እንዳለብኝ ግን አላውቅም፡፡ የሆኖ ሆኖ የዚህ ዘመን እውነት ባብዛኛው የተዘበራረቀ በመሆኑ አላግባብ ሊፈርድብኝ የሚቃጣ እንደማይኖር እገምታለሁ፡፡ ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራልና ወደማይቀረው ድል እየተጠጋን ስንመጣ እንጫወታለን፡፡ ማርቲን ሉተር ባይቀድመኝ እኔም “ህልም አለኝ!” ብል በወደድኩ፡፡

“ቀኒቷን ማንም አያውቅም፡፡ ከጥቂቶች በስተቀር ብዙኃኑ ጎጋም እንኳን የምፅዓትን የመጨረሻ ቀን አያውቃትም፡፡ እናንተ የሚገባችሁ ታጥባችሁ ታጥናችሁ መጠበቅ ነው – ከሙስናና ከዕድፍ ርቃችሁ፤ ከዘረኝነት አረንቋና ከሆዳምነት ተቆጥባችሁ፤ አስተዋይነትን ተላብሳችሁ፣ በወረተኛ ወጀባዊ ንፋስ እንዳትወሰዱ ተጠንቅቃችሁ … ፡፡ ይሁንና ምልክቶቹን ስታዩ የቀኒቷን መቅረብ ትረዳላችሁ፡፡ ምልክቶቹን ያዬ ትውልድ ከምፅዓት በፊት የምትገለጠዋን የኢትዮጵያን ትንሣኤ ቀን ያያታል፡፡ …” (‹መጽሐፈ ትንሣኤ ኢትዮጵያ› ፣ ምዕራፍና ቁጥር የማይነበብ!)  

በየነ

 More on —-http://www.freeandualemaragie.org/?p=359

- See more at: http://www.freeandualemaragie.org/?p=456#sthash.4FvUnrPp.dpuf


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>