ጌታቸው ሺፈራው
አምባገነኖችን በሰላማዊ መንገድ ለማንበርከክ ይውላሉ የሚባሉ ከ180 በላይ የትግል ስልቶች እንዳሉ ይጠቀሳል፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ በተለያዩ መንገዶች ግለሰብ ላይ ጫና ማሳደር ነው፡፡ በዚህ የትግል ስልት ውስጥ የሚጠቀሰው ደግሞ መሪዎች በስራቸው እንዲሸማቀቁ ማጋለጥ ይገኝበታል፡፡ አንዳንዶቹ ባለስልጣናትን ማሸማቀቅ፣ ማጋለጥ ባለፉት አስርት አመታት እንዳልተጀመረ ያስረዳሉ፡፡ ሮማውያንና ቻይናውያን ስር የነበሩ ተገዥ ህዝቦች የድሮዎቹ ገዥዎችን ንግግር በማቋረጥ፣ የእነዚህ አገዛዞች ወረራ፣ ፖሊሲ አላግባብ የሆነ ግብር አሊያም በግለሰብ ደረጃ ለመሪዎቻቸው ያላቸውን ተቃውሞ በመጮህ ይገልጹ እንደነበር ይገለጻል፡፡ ይህ መሪዎችን የማሸማቀቅ የሰላማዊ ትግል ስልት ከድሮዎቹ በበለጠ ባለፉት በተለይም የሶቬትን መፈረካከስ ተከትሎ የሰላማዊ ትግል ስልቶች ይበልጡን የህዝብ መሳሪያ በሆኑበትና አምባገነኖች ስልጣናቸውን በመልቀቅና ባለመልቀቅ መሃል ሲወዛገቡ በነበሩበት ዘመን ጀምሮ በስፋት እየተሰራበት ይገኛል፡፡
የሙታድሃር አልዛይዲ መንገድ
ሙንታድሃር አል ዛይዲ የኢራቅ የመንግስት ቴሊቪዥን ውስጥ የሚሰራ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ይህ ጋዜጠኛ ኢራቅ ውስጥ የነበረው የአሜሪካ ሰራዊት በኢራቃውያን ህጻናት፣ እናቶችና ወጣቶች ያደርሰው የነበረውን ግፍ በቀዳሚነት ተመልክቷል፡፡ ኢራቃውያን በአሜሪካ ሰራዊት ፍዳቸውን ማየታቸውን ይፋ ለማውጣት የተቀጠረበት የመንግስት ሚዲያ ባያመቸውም በግሉ ግን የቡሽ አስተዳደር የሚፈጽመውን ግፍ በሰላማዊ መንገድ ማጋለጥ ችሏል፡፡ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ጥር 14/2008 ላይ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሎው ቡሽ በኢራቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤተ መንግስት ውስጥ ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጡ በመሆኑ ሁኔታውን እንዲዘግብ ሲላክ ይህን ትግሉን የሚያካሂድበት አመች ሜዳ አግኝቷል፡፡ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የኢራቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ሆነው የአሜሪካ መንግስትና ህዝብ ኢራቅን ለመታደግ የወሰዱትን ፖሊሲ፣ የአሜሪካ ሰራዊት ለኢራቃውያን የሚያሳየውን ርህራሄና ደጀን አስመልክተው ድስኩር እያሰሙ በነበረበት ወቅት አንድ በአሜሪካ ፕሬዝንት ላይ፣ ያውም በኢራቅ ቤተ-መንግስት ውስጥ ይሆናል ተብሎ የማይታሰብ፣ አንድ የመንግስት ሚዲያ ውስጥ የሚሰራ ጋዜጠኛ ይፈጽመዋል የማይባል አስደንጋጭ ነገር ተከሰተ፡፡ ከቡሽ ዲስኩር ይልቅ ‹‹ይህ ከኢራቅ ህዝብ የተላከ የመሸኛ ሰላምታ ነው!›› የሙንታድሃር አል ዛይዲ ድምጽ አስተጋባ፡፡ ድምጹን አጅቦት የጋዜጠኛው ጫማ የአሜሪካኑን ፕሬዝዳንት ለጥቂት ሳተው፡፡ ለጋዜጠኛው ይህ ሌላ ጊዜ የማያገኘው ጦር ሜዳው ነውና ‹‹ይህኛው ደግሞ ኢራቅ ውስጥ ለሞቱት፣ ባል አልባና አባት አልባ ለቀሩት ኢራቃውያን ማስታወሻ›› ይሁን በሚል ሁለቱንም ጫማዎች ወደ ቡሽ በመወርወር የኃያሏን አገር አሜሪካ ፕሬዝደንት በጫማ አስጨነቃቸው፡፡ ቡሽ በሚያዙት የአሜሪካ ሰራዊትና ይሁንታ ስልጣን ላይ የነበሩት የኢራቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ‹‹እኔን ይምታኝ›› ብለው ለተደናገጠው ቡሽ ሲደረቡ ታዩ፡፡
የዚህ ጋዜጠኛ ተግባር ሰላማዊ ለመሆኑ ቡሽ በወቅቱ የሰጡት አስተያየት በግልጽ አሳይቷል፡፡ ከስድብ ጋር በጫማ ባራወጣቸው ጋዜጠኛ ተግባት ተበሳጭተው ‹‹ተደፍረናል፣…›› አላሉም፡፡ ይልቁንስ ‹‹ይህ ጉዳይ ምንም አያስጨንቀኝም፡፡ ሰዎች ትኩረት ለማግኘት የሚወስዱት ስልት ነው›› በማለት ሰላማዊ እንደሆነ ተገንዝበው አልፈውታል፡፡
በእርግጥ የኢራቁ ጋዜጠኛ የወሰደውን እርምጃ ቡሽ ‹‹ይህ ጉዳይ ምንም አያስጨንቀኝም›› ቢሉም በቡሽ ይሁንታ ስልጣን ላይ የነበሩት የአገሪቱ ገዥዎች እንዲሁ ሊያልፉት አልቻሉም፡፡ በወቅቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠባቂዎች ጋዜጠኛውን እየደበደቡ ለስርዓቱ መከላከያ ሰራዊት አሳልፈው ሰጥተውታል፡፡ ከፍተኛ ደብደባ እንደደረሰበትም ታውቋል፡፡ በዛች የወደቀች አገር የስርዓቱ እጅ የሆነ ፍርድ ቤት የሶስት አመት እስር ወስኖበታል፡፡ በተቃራኒው ህዝብ ጋዜጠኛው ጀግና መሆኑን በመግለጽ እንዲለቀቅ ጎዳና ላይ ወጥቶ ጭምር ጠይቋል፡፡ ተወሰደበት የተባለውን እርምጃ ተቃውሟል፡፡ የኋላ ኋላ ጋዜጠኛው ከ9 ወር በኋላ መልካም ጸባይ ያለው ሰው ነው ተብሎ ተለቅቋል፡፡ በዛች በፈራረሰችውና በአሜሪካ ስር በምትተዳደር ኢራቅ ውስጥ ያውም በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ላይ ጫማ የወረወረ ኢራቃዊ ጋዜጠኛ የወሰደው እርምጃ ሰላማዊ በመሆኑ ሰላማዊ ነው ተብሎ ተለቋል፡፡ አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ እንጂ ለአንድም ቀን የሚያሳስት አልነበረም፡፡ በኋላ ላይ የወረወረውን ጫማ ቅርጽ የሚያሳይ ሀውልት የተቀረጸለትም ትግሉ ሰላማዊና አርዕያ የሚሆን ስለነበር ነው፡፡
የዚህ ኢራቃዊ ጋዜጠኛ ስምና ዝና እንዲሁም የትግል ስልት ኢራቅ ብቻ ተወስኖ አልቀረም፡፡ ጫማ መወርወር አንድን ሰው ምን ያህል እንደሚጠሉት ለማሳየት በአረቡ ዓለም የተለመደ ባህል ነው፡፡ ከዓረቡ ዓለም ውጭም በመላው ዓለም አዲስ አምባገነኖችን የማሸማቀቂያ ስልት ሆኖ የታየ ሲሆን ሙንታድሃር በፕሬዝዳንት ቡሽ ላይ ጫማ ከወረወረ በኋላ በፖለቲከኞችና በሌሎች ታዋቂ ሰዎች ላይ ቢያንስ 44 ያህል ጊዜ ጫማ ተወርውሮባቸዋል፡፡
ቡሽ ከተወረወረባቸው በኋላ ጦርነቱን የተቃወሙ የአሜሪካ ዜጎች በሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው ወደ ዋይት ሃወስ ጫማቸውን በመወርወር የኢራቁን ጋዜጠኛ ተግባር አሜሪካ ውስጥ ደግፈውታል፡፡ በተመሳሳይ ካናዳ ውስጥም ሰላማዊ ሰልፈኞች ከአሜሪካ ቆንጽላ ፊት ለፊት በርካታ ጫማዎችን በመወርወር ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፡፡ እ.ኤ.አ 2008 ጥር ወር መጨረሻ ላይ የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ወይንጃባው ካምብሪጅ ዩኒቨርሰቲ ውስጥ ከጎርደን ብራውን ጋር ስለ ኢኮኖሚ ትብብር እያወሩ በነበረበት ወቅት ከአንድ ጀርመናዊ ተሳታፊ ወጣት ጫማ ተወርውሮባቸዋል፡፡ በወቅቱ ስለ ቻይና እድገት ሲደሰኩሩ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ አምባገነንነታቸውና ውሸታቸው ተቃውሞውን ካቀረበው ወጣት ውርጅብኝ ተርፈዋል፡፡ ጀርመናዊው ወጣት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቻይናውያን ላይ የሚያደርሱትን በደል በመቃወም ጫማ መወርወርን ዓለም አቀፋዊ የሰላማዊ ትግል ስልት አድርጎ ተጠቅሞበታል፡፡
የቻይና ባለስልጣናት ወጣቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና የሁለቱን አገር ግንኙነት ለመጉዳት ነው በሚል ቅጣት እንዲጣልበት ጫና ቢያደርጉም ወጣቱ ግን ይህን ለማድረግ የሚያሳይ መረጃ በመታጣቱ ተለቅቋል፡፡ በተመሳሳይ አመት ስዊድን ውስጥ ይገኙ የነበሩ የእስራኤል አምባሳደር ስለ ጋዛ በሚያወሩበት ወቅት ‹‹ገዳይ›› በሚል ድምጽ ንግግራቸውን በማቋረጥ ጫማ ተወርውሮባቸዋል፡፡ ሄላሪ ክሊንተን ግብጽን እየጎበኙ በነበሩበት ወቅት ‹‹ሞኒካ›› ከሚል የማሸማቀቂያ መዝሙር ጋር ግብጾች ጫማቸውን ወርውረውባቸዋል፡፡ የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር በሌላ ቀንም እየተናገሩ በነበረበት ወቅት አንድ ተማሪ ‹‹ዘረኛ›› ከሚል ማሸማቀቂያ ጋር በጫማ ተስተዋል፡፡ አህመዲን ኒጃድ ግብጽና አገራቸው ውስጥም ጫማ ተውርውሮባቸዋል፡፡
ከእነዚህ በተጨማሪ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ማንሞናህ ሲንህ፣ የዓለም ገንዘብ ድርጅት ዳይሬክተር ዶሚኒኩ ስትራውስ ካህን፣ በሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር (ካርቱም ውስጥ)፣ የቱርኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርዶጋን፣ የፓኪስታኑ ፕሬዝዳንት አሲፍ አሊ ዛርዳሪ፣ ቶኒ ብሊየር (ጫማና እንቁላል)፣ የቀድሞ የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔርቬዝ ሙሻራፍና ሌሎችም የጫማ ውርወራ ተቃውሞ ሰለባና የዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ መነጋገሪያ ሆነው ተሸማቅቀዋል፡፡
ይህ ጫማ በመወርወር ባለስልጣናትን ማሸማቀቅ አንዳንዶች ሰላማዊ አይደለም ቢሉትም የተወረወረባቸው አካላት ሳይቀሩ እንዲሁ ሲያልፉት ተስተውሏል፡፡ በባለስልጣናት ጫማ ከወረወሩት መካከል ከበድ ያለ ቅጣት የተጣለበት ሰው እምብዛም አይነገርም፡፡ የኢራቁ ጋዜጠኛ ጫማ በወረወረበት ወቅት እውቅ የሆኑ የሰላማዊ ትግል ጠበብቶች ‹‹ጋዜጠኛው ቡሽን ለመጉዳት ሳይሆን ጫማ መወርወር በዓለቡ ህዝብ ዘንድ ለሚጠላ ሰው የሚደረግ ተግባር በመሆኑ ነው›› ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ ጋዜጠኛው ለ9 ወር ከታሰረ በኋላም መልካም ስነ ምግባር ያለው ሰው ነው ተብሎ ከመለቀቁም ባሻገር በአሁኑ ወቅት ለኢራቃዊያን ሰብአዊ እርዳታ በመስጠት ላይ የሚገኝ መሆኑ ይህን ሰላማዊነቱን የሚያሳይ ነው፡፡ በቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ ጫማ የወረወረው ጀርመናዊ ወጣት ‹‹የወረወርኩት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመምታት ብዬ አይደለም፡፡ ጫማውን መድረኩ ላይ ስጥለው የጋራ መግባባት እንደሚፈጥር አውቃለሁ፡፡ ይህ አንድ የተቃውሞ ምልክት ለመሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ሰው ለመጉዳት ፍላጎት የለኝም›› በሚል የተቃውሞውን ሰላማዊነት ገልጾ ነበር፡፡
የአበበ ገላው (የዲያስፖራው መንገድ)
የባለስልጣናትን ንግግር በማቋረጥ የሚፈጽሙትን በደል ለሚዲያና ለዓለም ማህበረሰብ ማሰማት አንዱ የሰላማዊ ትግል ስልት ነው፡፡ በህዝብ ላይ በደል በፈጸሙ ባለስልጣናት፣ የኩባንያ ባለሃብቶች፣ ግለሰቦች ለሚዲያ በቀረቡበት ወቅት አሊያም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ አሜሪካ ውስጥም ጮኸት እንደተደረገባቸው ይነገራል፡፡ ለአብነት ያህል በምርጫ ክርክሮች መሃከል በመናር ላይ የነበሩ ባለስልጣናት በፖሊሲያቸው የማይስማሙ ዜጎች ንግግራቸውን በማቋረጥ መቃወም፣ ማሸማቀቅ ተደርጎባቸዋል፡፡
በግንቦት ወር 2004 ዓ.ም በባራክ ኦባማ ግብዣ ወደ አሜሪካ ያቀኑት የወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊም በሌሎች የአፍሪካ መሪዎች፣ የአሜሪካ ተወካዮችና የዓለም ሚዲያ ፊት ተመሳሳይ እጣ ፈንታ ገጥሟቸዋል፡፡ ልክ እንደ ኢራቁ ጋዜጠኛ የውይይት መድረኩን እንደ ሰላማዊ የጦር ሜዳ የተጠቀመው ጋዜጠኛ አበበ ገላው ‹‹መለስ ዜናዊ አምባገነን ነው፣ ነጻነት እንፈልጋለን፣ እስክንድርና ሌሎች የህሊና እስረኞች ይፈቱ›› የመሳሰሉትን መፈክሮች ሲያስተጋባ መለስ ዜናዊ አቀርቅረው ታይተዋል፡፡ ጋዜጠኛው ያደረገው ነገር ሰላማዊ በመሆኑ የውይይቱ አስተባባሪዎች አበበ ገላው መፈክሩን እንዲያቆም ‹‹ሰምተናል፣ እናመሰግናለን›› ከማለት ውጭ ሌላ እርምጃ አልተወሰደበትም፡፡
የኢራቁ ጋዜጠኛ ካደረገውም በበለጠ እጅግ ሰላማዊ በሆነና የዓለም ማህበረሰብ በሰፊው በሚሰማበት አጋጣሚ በኢትዮጵያ ዲያስፖራ የተጀመረው ተቃውሞ በአንድ ወቅት መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ምንም እንኳ ሰላማዊ ትግልን ይህን ያህል ለውጥ እንደማያመጣ በሚያምነው ማህበረሰብ ውስጥ የአንድን ባለስልጣን ንግግር ማቋረጥ ባንዳንዶቹ ከዚህ ግባ የማይባል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ብልግና ተደርጎ ቢወሰድም በስርዓቱ ደጋፊዎችና ባለስልጣናት ላይ ከፍተኛ መደናገጥን መፍጠሩ የሚታወስ ነው፡፡ ሰላማዊ ትግል ለውጥ ያመጣል ብለው በሚያምኑት ዘንድም እንደ ድል የተቆጠረ ሲሆን ሌሎች መንገዱን እንዲመርጡት አድርጓል፡፡ አበበ አቶ መለስ ‹‹አምባገነን ነው!›› ከተባሉ ከሁለት አመት በኋላ አርብ ሜይ 9/2014 እ.ኤ.አ በፕሬዝዳንት ኦባማ ላይ ዳግመኛ ተግብሮታል፡፡
‹‹ሚስተር ኦባማ እኛ ኢትዮጵያውያን እንወድወታለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ነጻነት እንፈልጋለን›› በማለት የጀመረው ጋዜጠኛ አበበ ገላው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ጨቋኝ ስርዓት መደገፍ አቁመው ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን እንዲቆሙ አሳስቧል፡፡ ከጋዜጠኛ አበበ ገላው ጋር እንደሚስማሙ የተናገሩት ፕሬዝደንት ኦባማ ስለ ጉዳዩ ከአበበ ጋረ እንደሚያወሩበት በዓለም ሚዲያ ፊት ቃል ገብተውለታል፡፡ በስተመጨረሻ አበበ ለፕሬዝዳንቱ ደብዳቤ ሰጥቷቸዋል፡፡ የአበበ ገላው ተቃውሞ ሰላማዊ በመሆኑ ፕሬዝዳንት ኦባማ ከመበሳጨትና እንደ አቶ መለስ አንገታቸውን ከመድፋት ይልቅ ‹‹እኔም እወድሃለሁ!›› ብለው ሰላማዊነቱን ገልጸውለታል፡፡
አበበ ገላው የአቶ መለስን ንግግር ካቋረጠ ከሁለት አመት እንዲሁም ፕሬዝዳንት ኦባማን ካቋረጠ ከሁለት ወር በኋላ በርከት ያሉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት በተመሳሳይ የትግል ስልት የኢትዮጵያን ባለስልጣናት ማሸማቀቅ፣ ጉዳዩን የሚዲያ መነጋገሪያ ማድረግና ሌሎችም በተመሳሳይ ሰላማዊ ትግል ስልት እንዲሳተፉ ማነቃቃት ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ ለአብነት ያህል ከአንድ ወር በፊት ወደ አሜሪካ አቅንተው የነበሩት የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ ዋሽንግተን ውስጥ በሚገኝ አንድ የኢትዮጵያ ሪስቶራንት ውስጥ በነበሩበት ወቅት በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞ እንዳሰሙባቸው ታውቋል፡፡
በተመሳሳይ የአሜሪካ መንግስት የአፍሪካን መሪዎች በጋበዘበት ወቅት በአሜሪካ የተገኙ የኢትዮጵያ ባለስልጣናትም ከዳያፖራው ቀላል የማይባል ተቃውሞ ገጥሟቸዋል፡፡ ለአብነት ያህል የኮሚኒኬሽ ሚኒስትሩ አቶ ሬድዋን ሁሴን በአንድ የገበያ ማዕከል ውስጥ በነበሩበት ወቅት ‹‹ገዳይ ነህ! ተላላኪ!›› የሚሉትን ጨምሮ ስድብና ተቃውሞ ሲደርስባቸው ተመልክተናል፡፡ ምንም እንኳ በአቶ ሬድዋን ላይ ከተቃውሞም ባለፈ ተራ ስድብ ጭምር የተሰነዘረባቸው ቢሆንም ምንም ቢሆንም እንቁላልና ጫማም በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞን መግለጫ በሚያገለግሉበት በአሁኑ ወቅት ሰላማዊ አይደለም ለማለት አይቻልም፡፡ ከቪዲዮው ማየት እንደተቻለው ተቃውሞውን ያቀረቡት ኢትዮጵያውያን አቶ ሬድዋን ጋር ከነበራቸው የአካል ቅርርብ አንጻር ከሰላማዊ መንገድ በሆነ መልኩ እርምጃ ሊወስዱ የሚያስችል አጋጣሚ ነበራቸው፡፡ በመሆኑም ተቃዋሚዎቹ ሰላማዊ የሆነውን መንገድ መምረጣቸውን ያሳያል፡፡
ሱቅ ውስጥ ሲዋከቡ አቶ ሬድዋን ሁሴን የመጀመሪያው ፖለቲከኛ አይደሉም፡፡ የሰለጠኑት አገራት ባለስልጣና ያውም አገራቸው ውስጥ ጭምር ተመሳሳይ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል እ.ኤ.አ በ2012 የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አገራቸው ላይ ተመሳሳይ ተቃውሞ ደርሶባቸዋል፡፡ በአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ደስተኛ ያልሆኑ ዜጎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገቡበት ሱቅ ውስጥ ጩኸታቸውንና ተቃውመዋቸውን አሰምተዋል፡፡ ይህ አውስትራሊያ ውስጥ ተገለልን በሚሉ ህዝቦች የተደረገ ጮኸት አሜሪካንና አውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ከአውስትራሊያ ውጭ ያለውን የዓለም ህዝብ አነጋግሯል፡፡ ከዚህ በኋላም በእነዚህ ህዝቦች ላይ ተፈጸመ በተባለው ወንጀል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቅርታ እስከመጠየቅ ደርሰዋል፡፡ አቶ ምንም እንኳ አቶ ሬድዋን ሁሴን በገጠማቸው ተቃውሞ ሲሸማቀቁ ቢታዩም እንዲህ እንዲሸማቀቁ ላደረጋቸው ተግባር ግን ይቅርታ ይጠይቃሉ ብሎ መጠየቅ የዋህነት ይሆናል፡፡
ከአቶ ሬድዋን በተጨማሪ ኢትዮጵያውያን ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ያረፉበት ሆቴል በመሄድ ተቃውሞ ለማሰማት ጥረት እንዳደረጉና ዶክተር ቴዎድሮስን ደብቀዋል ያሏቸውን ሰዎች ለይ ጫና ሲያደርጉ የሚያሳይ ቪዲዮም ተለቅቋል፡፡ በተመሳሳይ ዳያስፖራው ተቃውሞ እንደሚያቀርብባቸው አውቀዋል የተባሉት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እነ አበበ ገላውና ‹‹Global Alliance for the Rights of Ethiopians›› የተባለ አካል እያደራጁት በነበረ ተቃውሞ ምክንያት አዙሳ ፓስፊክ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በሌሎች በተያዘላቸው ፕሮግራም መገኘት አለመቻለቸው የዳያስፖራው አዲስ መንገድ ምን ያህል ባለስልጣናቱን እያሸማቀቀ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
የሌሎች የአፍሪካ አገራት በመኪናቸውና በአረፉበት ሆቴል ላይ የየአገራቸውን ሰንደቅ አላማ ሲያውለበልቡ አቶ ኃይለማርያምን ጨምሮ ሌሎች የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በመኪናቸውም ሆነ ባረፉበት ሆቴል ላይ ሰንደቅ አላማ አለማድጋቸውንና ዳያስፖራው በተጠናከረ መንገድ ከሚያደርግባቸው ተቃውሞ ለመደበቅ ያደረጉት መሆኑን የዳያስፖራው ሚዲያዎች ‹‹Ethiopia: Prime Minster Hailemariam in Hiding›› ሲሉ ተቀባብለውታል፡፡ በአቶ ሬድዋን ሁሴን ላይ ተቃውሞ ያደረሱት ኢትዮጵያውያን ከተናገሩት መረዳት እንደሚቻለው ዳያስፖራው ስለ ባለስልጣናቱ መረጃ በመስጠትና በየግሉ ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ መደራጀቱን ነው፡፡ ይህ የዳያስፖራ ተቃውሞ በሰላማዊነቱና በተጠናከረ መልኩ ከቀጠለ አሜሪካ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ሊያቀኑባት የሚፈሯት አገር እንድትሆን ያደርጋታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አፈና፣ የባለስልጣኑ ተደራሽነትና በመሳሰሉት ምክንያቶች ይህ የትግል ስልት እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ነው የሚባል ሚና ባይኖረውም የዳያስፖራው የትግል ስልት አገር ቤት መለመድ አለመለመዱ ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡