ባለፈው ሳምንት በማህበራዊ ሚዲያው ‹‹ጥቁር ሳምንት›› (black week) በሚል ለአምስት ቀናት ዘመቻ (campaign) መካሄዱ ይታወሳል፡፡ በዚያ የጥቁር ሳምንት ዘመቻ ወቅት በመጨረሻው ቀን አስተባባሪዎቹ አዲስ አመትን በማስመልከት ‹አዲስ አመት በዓልን ከነጻነት ታጋዮች ጋር› በሚል የታሰሩ የነጻነት ታጋዮች እንዲጠየቁ ጥሪ መተላለፉ አይዘነጋም፡፡ በመሆኑም የሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶችና የነገረ ኢትዮጵያ ዝግጅት ክፍል ጳጉሜ 5 ቀን 2006 ዓ.ም በቂሊንጦ የሚገኙ የዞን 9 የጡመራ ቡድን አባላትንና የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን በመጠየቅ የዘመቻውን አካል አከናውነዋል፡፡ ቀጥሎም የጥቂት እስረኞችን መልዕክት በአጭር በአጭሩ አቅርበናል፡፡
ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀ
‹‹ሀገሬ ላይ እርግጠኛ የሆንሁበት ጉዳይ ቢኖር እኔን እንደ ዜጋ የሚጠብቀኝ መንግስት የሌለኝ መሆኑን ነው፡፡ ህገ-መንግስቱ አልጠበቀኝም፡፡ ህገ-መንግስቱ ጥሩ ቢሆንም አልተከበረም፡፡ ይህ ሁሌም የሚያሳዝነኝ ጉዳይ ነው፡፡
ታስሬ ባለሁባቸው ቀናት ሁሉ የታዘብኩት ነገር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የባለሙያ እጥረት በሁሉም ዘርፍ መኖሩን ነው፡፡ አቅም ያላቸው ዜጎች ከስርዓቱ በመገፋታቸው ክፍተቱ እንዲሰፋ ሆኗል፡፡ በጣም ነው የሚያሳዝነው፤ የሚሰሩ ሰዎች በተገቢው ቦታ ላይ አለመኖራቸውን አይቻለሁ፡፡ የሚያሰራ ስርዓት ስለሌለ ብዙዎች ህሊናቸውን መርጠው በመራቃቸው ይመስለኛል አቅም ያላቸው ሰዎች የራቁት፡፡ ይህ ለሀገር አሳሳቢ ነው፡፡
የሚቆጨኝ ነገር በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና በሌሎች ተቋማት በእንግሊዝኛ የተሰሩ የጥናት ስራዎችን በመምረጥ አሰባስበን በአማርኛ ቋንቋ በጆርናል መልክ ለመስራት አስበን ያን ሳንሰራ በመታሰራችን ነው፡፡
አሁን በተለያዩ ሁኔታዎችና ጉዳዮች ላይ ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያው በኩል የሚሰሩ ስራዎች እንዳሉ ስሰማ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ እኛን አስረው ሌላው ዝም እንዲል ፈልገው ኖሮ ከሆነ እንዳልተሳካላቸው የሚያሳይ ነው፡፡ ለሀገር የሚያስቡ ብዙ ወጣቶች በየጊዜው ማበባቸው አይቀሬ ነው፡፡ እየታየ ያለውም ይሄው ነው፡፡ ምንግዜም የሚበረቱ ሰዎች ለውጥ ያመጣሉ ብዬ አምናለሁ፡፡››
አይመዲን ጀበል፣ ሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባል
ልትጠይቁን ስለመጣችሁ በጣም እናመሰግናለን፡፡ በተለይ ወጣቶቹ እያደረጋችሁ ያለው እንቅስቃሴ እንሰማለን፡፡ በጣም ደስ ይላል፡፡ እስካሁን በአገር ጉዳይ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ የቆዩት የ1960ው ትውልድ አባላት ናቸው፡፡ አሁን ወጣቶች እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡ ይህ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ነገር ግን በቂ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ስለሆነም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡
ያሲን ኑሩ፣ የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባል
‹‹እስር፣ እንግልትና ሌሎችም በደሎች የአምባገነኖች እርምጃ መለያ ባህሪያት ናቸው፡፡ አምባገነኖችን አንድ የሚያደርጓቸው እነዚህ ባህሪያት ናቸው፡፡ አምባገነኖች ከታሪክ አይማሩም፡፡ የዛሬ 20 አመትም ሆነ 50 አመት ወደ ስልጣን የሚወጣ አምባገነን ይህን ነው የሚደግመው፡፡
መንግስት በኃይማኖቶች መካከል ልዩነት መፍጠር ይፈልጋል፡፡ እናንተ ክርስቲያኖች የኃይማኖት ድንበር ጥሳችሁ ከእኛ ከሙስሊም ወንድሞቻችሁ ጋር መቆማችሁን እናደንቃለን፡፡ በተለይ ሰማያዊ ፓርቲ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ መብት በመቆም የሚያደርገውን ጥረት እናደንቃለን፡፡ እኛን ለመጠየቅ እስር ቤት ድረስ ስለመጣችሁ በጣም እናመሰግናለን፡፡ ትግሉ ከዚህም በላይ መስዋዕትነት ያስከፍላልና በርቱ፡፡››
ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ
‹‹ማዕከላዊ የገባነውን የመጀመሪያ ሰሞን ለእኛ አስቸጋሪ ነበር፡፡ በማንኛውም ጊዜ እስር ሊኖር ይችላል በሚል ማዕከላዊ የሚደረጉትን ነገሮች ለማሳወቅ እንጥራለን፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የጻፍናቸው ጽሁፎች ለዚህ ያግዛሉ ብየ አምናለሁ፡፡ በመሆኑም በእኛ ላይ ከደረሱብን ነገሮች ሌሎች ይማሩባቸዋለን ብለን እናምናለን፡፡ ይህ ሲሆን የሚታሰሩ ሰዎች የሚደርስበት ችግር አዲስ እንዳይሆን ያደርጋል፡፡ ወደ ቂሊንጦ ከመጣን በኋላ የተሻለ ነገር ቢኖርም አሁንም ድረስ መጽሃፍና ጋዜጣ አይባልንም፡፡
በጥቁሩ ሳምንት ዘመቻ ያደረጋችሁትን ነገር ሰምተናል፡፡ በጣም ደስ የሚል ስራ ሰርታችኋል፡፡ መጥታችሁ ስለጠየቃችሁን ደስ ብሎናል፡፡ እስሩ ቀጣይነት እንደሚኖረው ቢታወቅም፣ በየትኛውም ሁኔታ በርታትችሁ እንድትቀጥሉ እፈልጋለሁ፡፡
በየቀኑ ጋዜጠኞች በሚደርስባቸው ጫና አገራቸውን ጥለው መሰደዳቸውን እንሰማለን፡፡ ይህ በጣም ያሳዝናል፡፡››
ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ
‹‹ከመታሰሬ በፊት ማዕከላዊ ውስጥ ስለሚፈጸሙ በደሎች በተለያዩ ሪፖርቶች ላይ ማንበብ ችዬ ነበር፡፡ ማዕከላዊ ከገባሁ በኋላ ያየሁት ግን ሰፊና ከጠበኩት በላይ ነው፡፡ በተለይ ትጥቅ ትግልን የመረጡ ተቃዋሚዎች አባላት ናቸው የተባሉ አሊያም በሚዲያው የማይታወቁና ጠያቂ የሌላቸው አካላት ላይ የሚደርሰው በደል ዘግናኝ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ተመሳሳይ ድብደባ ደርሶባቸዋል፡፡ ድሮ ማዕከላዊ ውስጥ ይደረጉ እንደነበር ሰምቼ ነገር ግን ይሆናሉ ብዬ የማላምናቸውን ነገሮች ሁሉ እንደሚፈጸሙ ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡
የማዕከላዊ መርማሪዎች አስቸጋሪዎች ናቸው፡፡ ምርመራ ማድረግ ሳይሆን ጥፋተኛ መሆናችንን እንድናምንላቸው ነው ሁሌም ተመሳሳይ ጥያቄ የሚያነሱልን፡፡ አንዳንዶቹ ጥያቄዎች በጣም የሚገርሙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል በምርመራ ወቅት ‹‹እከሌ ጋር ሻይ እየጠጣን›› ብለን የተናገርነውን ነገር እነሱ ‹‹ስብሰባ አድርገን›› ብለው ይጽፉታል፡፡ ሻይ መጠጣት በእነሱ ስብሰባ ተብሎ ይተረጎማል፡፡ አንድ ጋዜጠኛ የሚሰራው ህጋዊ ስራ ህገወጥ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ለአብነት ያህል ሰማያዊ ፓርቲ ግንቦት 25/2004 ዓ.ም ባደረገው ሰልፍ ተገኝቼ ፎቶ አንስቼ ነበር፡፡ ይህ ፎቶ ግራፍ በክስ ቀርቦብኛል፡፡ አስቡት በዚህ ሰልፍ ኢቲቪና ሌሎች የመንግስት ሚዲያዎችም ፎቶ አንስተዋል፣ ቪዲዮ ቀርጸዋል፡፡ መርማሪዎቹን ‹‹ይህ ስራዬ ነው፡፡ አያስወነጅለኝም›› ብትል አያምኑልህም፡፡ ጋዜጠኛ አስማማው ኃ/ጊዮርጊስም ሰማያዊ ፓርቲ ባዘጋጀው ሰልፍ ላይ ተገኝተሃል የሚል ጥያቄ ቀርቦለታል፡፡
በተመሳሳይ ዩጋንዳ እያለሁ ባቋቋምኩት ጋዜጣ ላይ ሙሃመድ ሰልማን ‹‹ፒያሳ ሙሃመድ ጋ ጠብቂኝ›› በሚል ከጻፈው መጽሃፍ ላይ ያሉ ጽሁፎችን ጋዜጣው ላይ አውጥቻቸው ነበር፡፡ ሆኖም ይህም በክስ ቀርቦብኛል፡፡ ‹‹መጽሃፍ ላይ ነው የወሰድኩት፡፡ መጽሃፉ ህጋዊ ሆኖ አገር ውስጥ ይሸጣል›› ብትል ማንም አይሰማህም፡፡ ፖሊስ ህዝብን ለመጠበቅ የቆመ አካል ተደርጎ ነው የሚወሰደው፡፡ ነገር ግን ከገባንበት ጊዜ ጀምሮ ገና ሳይፈረድብን ‹‹እናንተስ ለምን ሽብር ትፈጥራላችሁ?›› ያሉን ፖሊሶች አጋጥመውናል፡፡ ቀድመው ፈረዱብን ማለት ነው፡፡
በምርመራ ወቅት በጣም የሚያስገርሙ ነገሮች ተነስተዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል ጆን ኬሪ ወደ ኢትዮጵያ የመጣ ወቅት መርማሪዎቹ የሚገርም ጥያቄ አንስተውልን ነበር፡፡ ‹‹ጆን ኬሪ ጓደኛችሁ ነው?›› ብለው ጠይቀውናል፡፡ በጣም የሚገርም ነው፡፡ አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን የእኛ ጓደኛ እንደሆነ አድርገው አቅርበውታል፡፡ ደግሞም ይህንንም ህገወጥ አድርገው ነው የሚያቀርቡት፡፡ በሌላ በኩል አንዴ ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር፣ ሌላ ጊዜ ከግንቦት ሰባት ሌላ ጊዜ ደግሞ ከኦነግ ጋር ግንኙነት እንዳለን ይገልጹልናል፡፡ እነዚህ ድርጅቶች በምንም መልኩ የሚገናኙ አይደሉም፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ጋዜጠኛ የሚከሰሰው በመጻፉ አይደለም፡፡ በጋዜጠኝነት ብትከሰስ አንድ ነገር ነው፡፡ እነሱ ግን የሚያነሱብህ ክስ ሌላ ነው፡፡
ፌስቡክና ሌሎች ሚዲያዎች ላይ ንቁ ተሳታፊ የነበርን ሰዎች ያለመረጃ ስንቀመጥ ከባድ ነው፡፡ በተለይ በመጀመሪያዎቹ 75 ቀናት ነገሮች አስቸጋሪ ነበሩ፡፡ ከዛ በኋላ ግን ቢያንስ ኢቲቪን መመልከት ችለናል፡፡ ኢቲቪ በሚያቀርባቸው ጉዳዮች ላይ የየራሳችን ትርጉም እየሰጠን አገራችን ውስጥ በጥቂቱም ቢሆን ምን እየተካሄደ እንዳለ መረዳት እንችላለን፡፡ ወደ ቂሊንጦ ከመጣን በኋላ ነገሮች የተሻሉ ናቸው፡፡ ከጠያቂዎቻችን መረጃዎችን ማግኘት እንችላለን፡፡››
ምንጭ ነገረ ኢትዮጵያ