Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የማይዝሉ ጀግኖች! (በላይ ማናዬ)

$
0
0

ጫማ ማውለቅን ጨምሮ እጅግ አሰልቺና አሳቃቂ የሆነውን ፍተሻ አልፈን ወደ ውስጥ ዘለቅን፡፡ በጋራ ሰብሰብ ብለን ወደ ስፍራው ካቀናነው ወጣቶች መካከል ግማሻችን በዞን አንድ ሌሎቻችን በሌላኛው ዞን ተከፋፍለን ወደ ወዳጆቻችን ገሰገስን፡፡

አሁን ያለነው በፌደራል መንግስቱ ስር ከሚተዳደሩት እስር ቤቶች መካከል አንዱ በሆነው ቂሊንጦ ውስጥ ነው፡፡ እዚህ እስር ቤት ውስጥ ልናያቸው የናፈቅናቸው የአርነት ታጋዮች፣ የብዙሃን ድምጾች አሉ፡፡ ከሁለቱ ቡድኖች ከአንደኛው ጋር በመቀላቀል ወደጀግኖቹ አመራሁ፡፡ ከፊት ያሉት ቀድመው አስጠርተዋቸው ኖሯል፡፡ ሁሉም በፈገግታ ታጅበው ከአጥሩ ማዶ ሰላምታ ሰጡን፡፡ ውብ በሆነ ፈገግታና የናፍቆት ስሜት ውስጥ መሆናችን ከጠያቂዎችም ከተጠያቂዎችም በኩል በጉልህ ይታያል፡፡

10616558_581452168647112_4041948437710460738_n

በቀጭን ሰውነቱ ላይ ስስ ነጭ ቲሸርት ለብሶ ሲታይ በእድሜ በጣም ለጋ አስመስሎታል፡፡ ረጂም ቁመቱ ደግሞ ቅጥነቱን አጉልቶታል፡፡ ፍልቅልቅ ነው፤ ሙሉ ደስተኛ ገጽታው ማንንም ቢሆን በፍጥነት የሚያላምድ ይመስላል፡፡ ሲናገር የሚደመጥ፣ ሲናገሩ የሚያደምጥ ግሩም ወጣት ነው፡፡ ይህ ወጣት የዞን 9 ጦማሪያን ቡድን አባልና በ2006 ዓ.ም የቡድኑ አስተባባሪ የሆነው ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀ ነው፡፡ ሌሎች አብረውኝ የነበሩት ወጣቶች ከሌሎች ሁለት ታሳሪ ጋዜጠኞች ጋር እያወሩ ሳሉ እኔ ከናቲ ጋር አንዳንድ ጉዳዮችን እያነሳን እያለ ስለወቅታዊ አያያዛቸውና ስላለፈው ሁኔታ ወደ ኋላ መለስ ብዬ ጥያቄዎችን አነሳሁለት፡፡ ‹‹ሀገሬ ላይ እርግጠኛ የሆንሁበት ጉዳይ ቢኖር እኔን እንደ ዜጋ የሚጠብቀኝ መንግስት የሌለኝ መሆኑን ነው፡፡ ህገ-መንግስቱ አልጠበቀኝም፡፡ ህገ-መንግስቱ ጥሩ ቢሆንም አልተከበረም›› አለኝ ወጣቱ ጦማሪ፡፡

በ2006 ዓ.ም ሚያዚያ ወር አጋማሽ ላይ ነበር መንግስት የዞን 9 አባላትን ለቃቅሞ ወደ ማዕከላዊ ማጎሪያ ያጋዛቸው፡፡ የጡመራ ቡድኑ አባላት በሽበር ወንጀል ተጠርጥረው እንደታሰሩ ተገልጾላቸው ለረጂም ጊዜያት በምርመራ ላይ መደበኛ ክስ ሳይመሰረትባቸው ከቆዩ በኋላ፣ መደበኛ ክሱ ሲመሰረት ‹ከሽብር ቡድኖች ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ ህገ-መንግስቱን በኃይል ለመናድ…› በሚሉ ‹ወንጀሎች› ተከሰው በቂሊንጦ እስር ቤት ሆነው የፍርድ ሂደታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡ ከቡድኑ አባላት መካከል ናትናኤል ፈለቀ፣ አቤል ዋበላ፣ በፍቃዱ ኃይሉ፣ አጥናፍ ብርሃኔ እና ዘላለም ክብረት እንዲሁም አብረው በተመሳሳይ ክስ የተያዙት ሁለቱ ጋዜጠኞች ተስፋለም ወልደየስ እና አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ በዚሁ በቂሊንጦ ሲገኙ ጦማሪት ማህሌት ፋንታሁን እና ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ ደግሞ ቃሊቲ በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡

እነዚህን እና ሌሎች ቀደም ብለው በእስር ላይ የሚገኙትን ጋዜጠኞች፣ የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኪሚቴ አባላትን፣ ፖለቲከኞችን እና ሌሎችንም ታሳሪዎች 2007 ዓ.ም አዲስ አመት መባቻን አስመልክተን ወጣቶች ሰብሰብ ብለን በዋዜማውና በበዓሉ ዕለት ጠይቀናቸው ነበር፡፡ በተለይ ባለፈው ሳምንት በማህበራዊ ሚዲያው ‹‹ጥቁር ሳምንት›› (black week) በሚል ለአምስት ቀናት ዘመቻ (campaign) በተካሄደ ጊዜ በዘመቻ መጨረሻው ቀን የዘመቻው አስተባባሪዎች አዲስ አመትን በማስመልከት ‹አዲስ አመት በዓልን ከነጻነት ታጋዮች ጋር› በሚል የታሰሩ የነጻነት ታጋዮችን እንድንጠይቅ ጥሪ ማስተላለፋቸውና ጥሪውን የተቀበሉ ወጣቶች መበርከት የእስረኞችን የጥየቃ ፕሮግራም ልዩ አድርጎት ነበር፡፡

እስር ቤት ታጉረው የሚገኙ የነጻነት ታጋዮችም በወጣቶቹ ድርጊት እጅግ መደሰታቸውን በመግለጽ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ እኒያ የማይዝሉ ጀግኖች እስክንድር ነጋና አንዱዓለም አራጌ በቃሊቲ በተገኘንበት ወቅት በወጣቶቹ ድርጊት እንደኮሩና ትግሉ እንዳልቆመም ማሳያ መሆኑን ከመግለጽ አልተቆጠቡም፡፡ ‹‹እኛ ገና በሰላማዊ ትግሉ ጅማሮ ላይ ነው የታሰርነው፡፡ ትግሉ ገና መጀመሩ ነው፡፡ ትግሉ በተግባር የሚፈትናቸው በርካታ ጀግኖች አሉ›› ሲል ነበር ትንታጉ ጋዜጠኛና የፖለቲካ ተንታኝ እስክንድር ነጋ ወጣቶችን ያበረታታው፡፡

እስክንድር የታሰረ አይመስልም፡፡ አልታሰረምም! በእስር ቤቱ ፖሊሶችና በአንድ ሲቪል በለበሰ ጆሮ ጠቢ ታጅቦ ወደ እኛ ቢቀርብም እስክንድር ፍጹም ነጻ ሆኖ ነበር የሚያወራን፡፡ እስክንድር ነጋን ይፈሩታል እንጂ እሱ አይፈራቸውም፡፡ ይህንን ደግሞ በተግባር ያሳየ ጀግና ነው፡፡ ‹‹አንተ እኮ የምንግዜም ጀግናችን ነህ፤ እንኮራብሃለን!›› አለው ከመካከላችን አንዱ፡፡ እስክንድር መለሰ፤ ‹‹ለእኔ ደግሞ እናንተ ከውጭ ያላችሁ ወጣቶች ናችሁ ጀግኖቼ!››

የእስክንድር መንፈስ ወደ ሌሎች የመጋባት ኃይል አለው፡፡ የዞን 9 የጡመራ ቡድን አባላት የጥንካሬ ምንጭ ይህ የማይዝል ጀግና እስክንድር ነጋ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ቂሊንጦ በነበርንበት ወቅት ፍልቅልቁ ወጣት ናትናኤል የሚያረጋግጠውም ይህንኑ ነው፡፡ ‹‹ያኔ ወደ እስር ቤት ሳንገባ በፊት እስክንድር ነጋን ልንጠይቅ ቃሊቲ ስንሄድ እስክንድር ሁሌም ይገርመን ነበር፡፡ ሁሌም ጠንካራ፣ ደስተኛና አስተዋይ ሆኖ ነበር የምናገኘው፡፡ እና፣ እሱን እያየን መታሰር፣ መስዋዕትነት መክፈል ሌላውስ ለምን ይፈራል ታዲያ ስንል ራሳችንን እንጠይቅ ነበር፡፡ እስክንድር ልዩ ሰው ነው፤ የሚጋባ መንፈስ ያለው ጀግና!››

ተስፋለም፣ ናትናኤል፣ አስማማው እና ሌሎችንም ወጣቶች ‹‹እስክንድር አክብሮቱን ገልጾላችኋል እኮ፤ ሰምታችኋል?›› ሲባሉ በደስታ አወንታዊ ምላሽ ሰጡ፡፡ እስክንድር ጀግኖችን የሚያፈራ ጀግና ነው፡፡ ዛሬ ሌሎች ወጣት የአርነት ንቅናቄው የማይዝሉ ጀግኖች የአርዓያቸው እስክንድርን ቃል ለሌሎች ሲናገሩ ይደግሙታን፡፡ ወጣቱ ጦማሪ ናትናኤል ከቂሊንጦ ተናገረ፣ ‹‹ለሀገር የሚያስቡ ብዙ ወጣቶች በየጊዜው ማበባቸው አይቀሬ ነው፡፡ እየታየ ያለውም ይሄው ነው፡፡ ምንግዜም የሚበረቱ ሰዎች ለውጥ ያመጣሉ ብዬ አምናለሁ፡፡››

የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባል የሆነው ያሲን ኑሩ ደግሞ እዛ ቂሊንጦ እስር ቤት ልንጠይቅ ለሄድነው ወጣቶች እንዲህ አለን፤ ‹‹መንግስት በኃይማኖቶች መካከል ልዩነት መፍጠር ይፈልጋል፡፡ እናንተ ክርስቲያኖች የኃይማኖት ድንበር ጥሳችሁ ከእኛ ከሙስሊም ወንድሞቻችሁ ጋር መቆማችሁን እናደንቃለን፡፡ እኛን ለመጠየቅ እስር ቤት ድረስ ስለመጣችሁ በጣም እናመሰግናለን፡፡ ትግሉ ከዚህም በላይ መስዋዕትነት ያስከፍላልና በርቱ፡፡››

ከሁሉም ታሳሪዎች አንደበት የሚወጣው መልዕክት አስገራሚ ነው፤ ሊያበረታቸው ወደ እነሱ የሚሄደውን ጠያቂ ሁሉ መልሰው አበርትተው ይልኩታል፡፡ እነሱ የማይዝሉ ጀግኖች ሆነው የዛለውን የሀገሬ ወጣት ‹‹በርታ!›› ይሉታል፡፡ አጠር ቀጠን ያለ ቆፍጣና ወጣት ነው፤ ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ፡፡ ‹‹በጥቁሩ ሳምንት ዘመቻ ያደረጋችሁትን ነገር ሰምተናል፡፡ በጣም ደስ የሚል ስራ ሰርታችኋል፡፡ መጥታችሁ ስለጠየቃችሁን ደስ ብሎናል፡፡ እስሩ ቀጣይነት እንደሚኖረው ቢታወቅም፣ በየትኛውም ሁኔታ በርታትችሁ እንድትቀጥሉ እፈልጋለሁ›› ሲል እሱም የማበረታቻ ቃሉን ተናገረ፡፡

ፖለቲከኛ አንዱዓለም አራጌ በበኩሉ የማሃተመ ጋንዲን የሰላማዊ ትግል አስተምሮ በምሳሌነት ሲያነሳ ከቆየ በኋላ፣ እሱን አብነት አድርገን በሰላማዊ ትግላችን እንድንበረታ አሳሰበን፡፡ ‹‹የሁላችንም ተስፋ ያለው እዚህ እስር ቤት አይደለም፡፡ ከዚህ ውጭ ካላችሁት ነው ሁሉም ነገር ያለው፡፡ በርቱ! ኢትዮጵያ እንደ እናንተ ያሉ እጅግ ብዙዎችን ትፈልጋለች፡፡ ደግሞም አሉ! በበዓል ቀን ስለመጣችሁና ስለጠየቃችሁን ኮርተንባችኋል፡፡››

ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የባለሙያ እጥረት እጅጉን እንደሚያሳስበው ይናገራል፡፡ በእስር ላይ ካለ ጀምሮ የሚያየው የባለሙያ እጥረት ሳይታሰር በፊት ከሚያውቀው በላይ ሳይሆንበት አልቀረም፡፡ ‹‹ታስሬ ባለሁባቸው ቀናት ሁሉ የታዘብኩት ነገር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የባለሙያ እጥረት በሁሉም ዘርፍ መኖሩን ነው፡፡ አቅም ያላቸው ዜጎች ከስርዓቱ በመገፋታቸው ክፍተቱ እንዲሰፋ ሆኗል፡፡ በጣም ነው የሚያሳዝነው፤ የሚሰሩ ሰዎች በተገቢው ቦታ ላይ አለመኖራቸውን አይቻለሁ፡፡ የሚያሰራ ስርዓት ስለሌለ ብዙዎች ህሊናቸውን መርጠው በመራቃቸው ይመስለኛል አቅም ያላቸው ሰዎች የራቁት፡፡ ይህ ለሀገር አሳሳቢ ነው፡፡››

ለመሆኑ በተለየ ሳላከናውነው (ወይም እንደ ቡድን ሳናከናውነው) በመታሰሬ እቆጫለሁ የምትለው ነገር ይኖር ይሆን ስል ጥያቄ አነሳሁለት፡፡ ‹‹የሚቆጨኝ ነገር በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና በሌሎች ተቋማት በእንግሊዝኛ የተሰሩ የጥናት ስራዎችን በመምረጥ አሰባስበን በአማርኛ ቋንቋ በጆርናል መልክ ለመስራት አስበን ያን ሳንሰራ በመታሰራችን ነው›› አለኝ ትክዝ ባለ ስሜት፡፡ ሆኖም አለ ናትናኤል፣ ሆኖም ‹‹አሁን በተለያዩ ሁኔታዎችና ጉዳዮች ላይ ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያው በኩል የሚሰሩ ስራዎች እንዳሉ ስሰማ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ እኛን አስረው ሌላው ዝም እንዲል ፈልገው ኖሮ ከሆነ እንዳልተሳካላቸው የሚያሳይ ነው፡፡ ለሀገር የሚያስቡ ብዙ ወጣቶች በየጊዜው ማበባቸው አይቀሬ ነው፡፡ እየታየ ያለውም ይሄው ነው፡፡ ምንግዜም የሚበረቱ ሰዎች ለውጥ ያመጣሉ ብዬ አምናለሁ›› አለ ቀጭኑ ቁምነገረኛ ወጣት፡፡

በግሌ እንደዘንድሮ አይነት አዲስ ዓመት በማይረሳ መልኩ ያሳለፍኩ አይመስለኝም፡፡ ከእነዚህ ባለብሩህ አዕምሮ ባለቤቶች፣ ሰላማዊ ታጋዮች፣ ሀገር ወዳዶች ጋር በዓልን ከማሳለፍ የበለጠ ምን ደስ የሚያሰኝ ነገር ይኖራል!

እናንተ የማትዝሉ ጀግኖች…የእናንተን ፈር በሚከተሉ እልፍ ኢትዮጵያውያን ነገ ብሩህ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊና የዘመነ አስተዳደር ይገባታል!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>