Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የቀጣዩ መንግሥታችን ሸክም (ይሄይስ አእምሮ)

$
0
0

ይሄይስ አእምሮ

 

(ይህ ጽሑፍ የተጻፈው ግንቦት ውስጥ 2006 ዓ.ም ነው፤ ትቼው ከርሜ ሳበቃ አሁን ምን በል እንዳለኝ አላውቅም ደግሜ ቃኘሁትና ላክሁት፡፡)

 

“እሳቸው በመጡና ድንጋይ በበሉ” አለች አሉ አንዷ የዳግም ዘማች ባለቤትና የቤት ሙሉ ልጆች እናት፡፡ በደርግ ጊዜ ነው፤ ወጣት-ሽማግሌ ባሏ ለዳግመኛ ሀገራዊ ወታደራዊ ግዳጅ ተጠርተው ሄደዋል፡፡ “አባታችን ናፈቀን” የሚሉ ብዙ ልጆች አሏት፡፡ ከልጆቿ ጋር የሚኖሩት በድህነትና በጠባብ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ሰው ሊጠይቃት በመጣ ቁጥር የባለቤቷን ከዘመቻ መመለስ አጥብቃ እንደምትሻ ትናገራለች፡፡ አንዱ ጠያቂ ታዲያ “ይምጡ፣ ይምጡ፣ የምትይው ቢመጡ ምን ልታበያቸው ነው?” ሲል ይጠይቃታል፡፡ እሷም በወቅቱ ያጣቻቸው ባለቤቷ መመለስ እንጂ ቀጣዩ ነገር የሚያሳስባት እንዳልሆነ ለመግለጽ “በመጡና ድንጋይ በበሉ!” የሚል መልስ ሰጠች ይባላል፡፡

አዎ፣ የኛ የምንለው መንግሥት ይምጣ እንጂ የሸክሙ ነገር ሊያሳስበን አይገባም እያልኩ መሆኔን መጠርጠር ከነገር ዐዋቂ አንባቢ ይጠበቃል፡፡ ግን ግን እውነት ለመናገር በእጅጉ ፈራሁ! የፍርሀቴ መሠረትም የቀጣዩ መንግሥታችን ታሪካዊ ኃላፊነት መክበድ ነው፡፡ ወያኔ ሀገራችንን በቁሟ እንጦርጦስ ያወረዳት በመሆኑ መልሶ የመገንባቱ ነገር ሲታሰብ ከምንም ነገር በላይ ያስጨንቃል፡፡ እንዲያውም አለማሰቡም ሳይሻል አይቀርም፤ ቢሆንም ክርስቲያን ተስፋ አይቆርጥም – እንዲሁም እስላም – ይባላልና ሁሉን ነገር ማድረግ የማይሳነው ታላቁ የሰማይና የምድር ፈጣሪ በቅርቡ መልካም ነገርን እንደሚያደርግልን፣ እነዚህን መዥገሮችም በኪነ ጥበቡ እንደሚነቅልልን መጠበቁ በተለይ የትንቢቱን ፍጻሜ ከሥር መሠረቱ ስንከታተል ለነበርንና በዳግም ትንሣኤያችን የብሥራት ጫፍ ላይ እንደምንገኝ ለምናምን ጥቂት ወገኖች አግባብነት አለው፤ ይገባናልናም ያደርግልናል፡፡ እንግሊዝኛ አማረኝ – So I shall sincerely suggest that we deserve both independence and freedom; as a nation, we are not independent and as people we are not free. Understandably, Ethiopia is under colonial apartheid system, a system led by few Tigrian mercenaries who are clandestinely supervised by anti-Ethiopian foreign forces who crave to see the over-all downfall of Ethiopia and her historic people. In light of this, it is quite right to say that the country is neither independent nor the people are free from oppression and ethnic segregation run and sponsored by TPLF and its international. For instance, the Amharas have been exposed to genocide and ethnic cleansing since the time TPLF came to existence some 40 years back, first in Tigray and later in all parts of the country, while other ethnics are stifled or even victimizedif they don’t obey this crooked ruling junta.

ከአእምሮየ ሰሌዳ ሳትሰወርብኝ አሁን ትዝ ያለችኝን አንዲት በጣም የምታውቋትን ነገር ላስታውሳችሁ፡፡ በአፄው ዘመን አንዷ ትንሽዬ የቤተ መንግሥት ልዕልት ፣ የአሁኑን አያድርገውና “የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር እኮ በአስደንጋጭ ሁኔታ 20 ሚሊዮን ደረሰ፡፡” እያሉ መኳንንት መሣፍንቱ ሲያወሩ ብትሰማ ጊዜ “ለመሆኑ 500 እንሆናለን እንዴ?” ብላ በአግራሞት ጠየቀች አሉ፡፡ እኔም አሁን ማንም ሊመልስልኝ የማይችል ከባድ ጥያቄ – እንዲያው ለላንቲካው ያህል – ልጠይቅ “በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ስንት ይሆን?” 90 ሚሊዮን? 70 ሚሊዮን? 50 ሚሊዮን? 30 ሚሊዮን? አንድ ሚሊዮን? ወደ ዜሮ የሚጠጋ ሚሊዮን? ስንት ነን በውነቱ? አካላዊ ዐይናችሁን ለአፍታ ዝጉና በኅሊናዊ ዐይናችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፤ መልስ ለማግኘትም ሞክሩ፡፡ አንድ ሕዝብ፣ በሕዝብነት ታውቆ ሊመዘገብ የሚችለውስ ብዛቱ ስንት ሲሆን ነው? አንድ ማኅበረሰብ በዕውቀት፣ በጥበብ፣ በአስተሳሰብ፣ በሃይማኖት፣ በባህል፣ … ምን ዓይነት የልኬት ደረጃ ላይ ሲደርስ ይሆን “ሕዝብ” የሚባለውን ዓለማቀፍ መጠሪያ የሚያገኘው? በእውነቱ አሁን እኛ ‹ሕዝብ› ነን? የአንድ ሀገር ሕዝብ ሲባል ምን ማለት ነው? ቀጣዩ መንግሥት ሕዝብ የመፍጠር ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት አለበት – ሀገርና ሕዝብ የመፍጠር ግዴታና ኃላፊነት ደግሞ እጅግ ፈታኝና እልህ አስጨራሽ ነው፡፡

በመሠረቱ መልካም አስተዳደርና ለሀገርና ለሕዝብ የሚቆረቆር መንግሥት ካለ፣ እንደወያኔ ለጥቂቶች የሚያደገድግና በብዙኃን ሥቃይ የሚደሰት መንግሥት ሣይሆን እውነተኛ የመንግሥት መዋቅር ቢኖር ሕዝብ አንደኛውና ትልቁ የሀገር ሀብት ነው፡፡ የሕዝብ ብዛት እንደችግር የሚቆጠረው ጥቂት አምራችና ብዙ በላተኛ ሲኖር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሁሉንም ዜጋ እንደችሎታውና እንደዬአቅሙ በአግባቡ በማስተማርና በማሰልጠን ለሥራ ካሰማሩት መጽዋችም ተመጽዋችም አይኖሩም፡፡ ልመናና ስርቆት፣ ሙስናና ንቅዘት ይቀንሳሉ ወይም ከነአካቴውም ሊጠፉ ይችላሉ እንጂ መንገዶችና የአምልኮት ሥፍራዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ በለማኞችና ባጡ በነጡ ድሆች አይሞሉም፡፡ የማጭበርበርንና በአቋራጭ የመክበርን ጎጂ ልማድ ሣይሆን በሥራና በመልካም ሥነ ምግባር የታነፀ ትውልድን የመገንባት ባህል የሚያዳብር የሕዝብ ወገን የሆነ አምባገነንም ይሁን በሕዝብ የሚመረጥ መንግሥት በአንድ ሀገር ውስጥ ካለ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ፈጥጦ ያለው ችግር አይኖርም ነበር፡፡(በነገራችን ላይ አምባገነን መንግሥት በህዝብ ምርጫም ሊመጣ እንደሚችል ያሜሪካውን ትንሹን ጆርጅ ቡሽና የግብጹን ሞሀመድ ሙርሲን ማስታወስ በቂ ነው)፡፡  ሕዝብና ሀገር ሲባል ደግሞ ተጨባጩ የሀገር ሁኔታና ተጨባጩ የሕዝብ ኑሮ እንጂ በታሪክ ካባ ተጀቡኖ የአሁን ስቃይንና ኋላቀርነትን ለመርሳት መሞከር አይደለም፡፡ ወንዞችና ተራሮች፣ ሸለቆዎችና ዋሻዎች፣ ባህሮችና ኩሬዎች እንዲሁም በቱሪስት መስህብነት የሚያገለግሉ የታሪክ አሻራዎችም ወቅታዊ የሕዝብ ኑሮ መገለጫዎች ሊሆኑ አይችሉም፡፡ “በቅሎ አባትሽ ማን ነው?” ቢሏት “እናቴ ፈረስ ነች” አለች እንደተባለው እንዳይሆን መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ እዚህ ላይ ለኢሳቷ እሳት ለመታሰቢያ ቀፀላ አክብሮቴን መግለጥ እፈልጋለሁ፡፡ በቅርብ በተከታተልኩት አንድ ውይይት እውነቱን አፍረጥርጣ በመናገር ይህን ቆሎ የማያበላንን የቀድሞ ብሔራዊ የኢትዮጵያዊነት ኩራት አላግባብ እንዳንለጥጠውና በከንቱ እንዳንኮፈስ ወይም በከንቱ መኮፈሳችንን እንድንቀንስ በመረጃና በማስረጃ በተደገፈ ገለጻዋ በልጅነት አንደበቷ መክራናለች፡፡ እውነትን ብትመርም ብትጎመዝዝም መቀበል ይኖርብናል፡፡ ዘፈንንና ሽለላን ለተወሰነ ጊዜና ለተወሰነ ዓላማ ይጠቀሟል እንጂ ራስን ለማነሁለልና ምንም ያልተነኩ መስሎ ምናባዊ መቼት ውስጥ በሥነ ልቦናዊ የተደላደለ ጉዝጓዝ ላይ ለመዘርፈጥ ልናቀነቅን አይገባም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ምን አለ? የአስፋልቱና የመንገዱ ግንባታ፣ የኤልክትሪኩና የስልኩ ዝርጋታ፣ የሕንፃና ኢንዱስትሪው ጋጋታ፣ የትምህርትና ጤና ኬላዎች ‹ተደራሽነት›፣ … በጥቅሉ ይህ የምናየው የዕድገትና ብልጽና ምልክት ሁሉ እሰዬው የሚያስብል ነው፡፡ ግን “ሰው አለ ወይ?” ብለን ከመጠየቅ የሚያግደን ነገር የለም፡፡ ለዚህም ነው ታዋቂው መንግሥቱ ለማ ቀጣዩን ዘመን የማይሽረው ሥነ ግጥም የቋጠረው፤

 

ምን ሕንፃው ቢረዝም ቢንጣለል አስፋልቱ፤

ሰው ሰው ካልሸተተ የታለ ውበቱ፡፡

 

በተለይ ለዚህ ዘመን ተለክቶ የተሰፋ ልጨኛ ሥነ ግጥም ነው፡፡

 

ወጣም ወረደ፣ ግራም ነፈሰ ቀኝ፣ የኛ የምንለው መንግሥት ሊያውም በቅርቡ ይኖረናል፡፡ ቆሜም ተኝቼም የሚያስጨንቀኝ ግን የመንግሥታችን ሸክም ነው፡፡ እንደኔ ኢትዮጵያ ውስጥ አንዲት ሽርንቁላ ውስጥ ተወትፎ ኢትዮጵያን ከነአጠፋፏ ጭምር እየታዘበ ለሚገኝ ዜጋ ኢትዮጵያን ከነዚህ መዥገሮች ነፃ ለማውጣት ከሚደረገው ትግል ይልቅ ከሙታን ሀገራት ተርታ ፈልቅቆ ለማውጣትና ትንሣኤዋን ለማብሠር የሚደረገው ግብግብ ይበልጥ ያስጨንቀዋል፡፡ በቁማችን እኮ ሞተናል!

ወጣቱም በለው ጎልማሳው ከየኅሊናው ጋር ተኮራርፎ ለሥጋው ብቻም አድሮ ሌት ከቀን ሲባዝን የምታየው በባሌም ይሁን በ”ቦሌ” እንዴት አድርጎ ገንዘብ እንደሚያጋብስና በአንድ አዳር እንደሚከብር ነው፡፡ “ቦሌ”ን ያላገጥኩባት በአሁኑ ሰዓት በባሌ እንጂ በቦሌ መክበር እንደብርቅና እንዲያውም ከነአካቴው የሌለ መሆኑን ለመጠቆም ፈልጌ ነው፡፡ ባሌን እንደህገ ወጥ፣ ቦሌን እንደህገኛ መንገድ ካሰብነው ዛሬ ዛሬ በህገኛ መንገድ የሚያልፍለት ዜጋ የለም ቢባል ከእውነቱ አልራቅንም፡፡ ሕግ በጉልበተኞች መዳፍ ሥር ወድቃ እያቃሰተችና ለይቶላት እየሞተች ናት፡፡ በህጋዊ መንገድ መነገድ፣ በህጋዊ መንገድ ተሟግቶ ፍትህን ማግኘት፣ በህጋዊ መንገድ ሥራ ማግኘት፣ በህጋዊ መንገድ ተምሮ ሥራ መያዝ፣ በህጋዊ መንገድ ተከራክሮ መርታት፣ በህጋዊ መንገድ ጉዳይህን ማስፈጸም፣ በህጋዊ መንገድ የዜግነትና የሰብኣዊ መብቶችህን ማስከበር፣ በህጋዊ መንገድ የንብረትህ ባለቤት መሆን፣ ወዘተ. ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ፈጽሞ አይታሰብም፡፡ የሁሉም ነገር መሠረት ዘርህና እንዲያም ሲል አድርባይነትህ ወይም ሆዳምነትህና ኅሊናቢስነትህ ነው፡፡ የወደፊቱ መንግሥታችን – የኛ የምንለው መንግሥታችን – ሸክሙ እንደሚበዛ የምንረዳው ይህን የተንሸዋረረ የአሁን አካሄዳችንን ለማስተካከል የሚጠበቅበትን ከፍተኛ ትግል ስናስብ ነው፡፡

አሁንና ዛሬ ወያኔና አጫፋሪዎቹ የሀገሪቱን ቁልፍ ለብቻቸው ይዘውና ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረው ሁሉን ነገር ማድረግ ይችላሉ፡፡ ለቃሉ አጠራር ይቅርታ ይደረግልኝና ኮንዶሙ ደሳለኝ ኃ/ማርያም በሰሞኑ የግንቦት 20 (2006ዓ.ም) ንግግሩ – ያን ንግግርም ጌቶቹ አዘጋጅተው የሰጡት መሆኑን ማስታወስ አያስፈልግም ብዬ ነው – አንሻፍፌም ቢሆን እጠቅሳለሁ – “በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ‹ኢትዮጵያውያን› ዜጎች ሚሊዮኔሮችና ቢሊዮኔሮች መሆን የቻሉት በኢሕአዴግ አመራር ነው” ብሎ የተናገረው ማንን እንደሚያካትት ግልጽ ነውና ወደዚያ መግባት አይገባም፡፡ ለነገሩ ቢገባስ ምን ክፋት አለው? የዐዋጁን በጆሮ፡፡

ሀብታሞቹ በኔ ግርድፍ ግምት 95 ከመቶው በላይ ወያኔ ትግሬዎች ናቸው፡፡ የትም ይኑሩ የትም ከነሱ ውጪ ሀብታም ወይም እነሱ ሀብቱን የማይቆጣጠሩትና በፈለጉ ጊዜ ሊያደኸዩት የማይቻላቸው ኢትዮጵያዊ ሀብታም የለም፡፡ በቀላሉ ላስታውስ – የአማልጋሜትዱ ገ/የስ ቤኛ፣ የአያት ቤቶች ኮንስትራክሽን ባለቤት አያሌው (ተሰማ?)፣ ኤርምያስ አመርጋ፣ ብርሃነ መዋ፣ ያለምዘውድ (ጎጃሜው ሀብታም) … ስንቱን ዘርዝሬው … በዚህች ጠባብ ቅንጭላቴስ ስንቱን አስታውሼው … እነዚህ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከሀብትም ከሀገርም ሣይሆኑ የቀሩት ሌላ ወንጀል ፈጽመው ሣይሆን “ኢኮኖሚውን የማይቆጣጠር ዘውግ ፖለቲካውንም ሊቆጣጠር አይችልም፤ ስለሆነም ከኛ ሌላ ሀብታምና ከኛ ሌላ ተፅዕኖ ፈጣሪ ነጋዴ መኖር የለበትም ” በሚል ያረጀና ያፈጀ የአገዛዝ ፈሊጥ እስከዕለተ ሞቱ ድረስ በዕውር ድንብር የሚነዳው ወያኔ ባሳረፈባቸው ዱላ ነው፤ መላው ኢ-ትግራዋይ በወያኔ የቁጥጥር ራዳር ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ስለዚህ የተጋቦት ወያኔ ሆንክም አልሆንክም ወደሀብትና ሥልጣን ማማዎች ልትወጣ ካሰብክ እንደመናጆ ሊጠቀሙብህ እንጂ የእውነት ከመሰለህ ጊዜህን ጠብቀህ ቁልቁል ስትፈጠፈጥ ያኔ የእንሥራ ጆሮነትህ – ባዳነትህና ለኮንዶምነት አገልግሎት መዋልህ ይታወቅሃል፡፡ ይህን እውነት ለመረዳት የቅርብ ጊዜ መረጃ ልጠቁምህ – ኤርምያስ ለገሠ የተባለ ወጣት የቀድሞ የተጋቦት ወያኔ  በቅርብ ለኢሳት የሰጠውን ቃለ ምልልስ አድምጥና ዕርምህን አውጣ፡፡ ሀገሪቱ አልቆላታል ወደሚል አሳዛኝ ደረጃ ትደርሳለህ – እስካሁን ተስፋ አለኝ የምትል ከሆንክ ነው ሊያውም፡፡ የኤርምያስን ቃለ ምልልስ ያዳመጠ ሰው፣ ወያኔ – ትግሬ ምን ያህል ቅሌታም፣ ምን ያህል ዐይኑን በጨው ያጠበ ዘረኛ እንደሆነ በቀላሉ መረዳት ይችላል፡፡ ይህ ለቅጣት የመጣ የአንበጣ መንጋ የሰንበት ጽንስ ጥርቅም ኢትዮጵያን እንዴት እንዳዋረዳትና ዜጎቿን ከመጤፍ ባለመቁጠር እንዴቱን ያህል እላያቸው ላይ እንደሚጸዳዳ ማንም መገንዘብ አይከብደውም፡፡ አሣሪዎቹ እነሱ፣ ገራፊዎቹ እነሱ፣ መርማሪዎቹ እነሱ፣ ደብዳቢዎቹ እነሱ፣… አንድም ቅልቅል ሳይኖርባቸው ኢትዮጵያውያን ላይ የሰለጠኑ አልቃኢዳዎችና የአዲሶቹ የእስላሚክ ስቴት ካሊፌቶች እነሱ ናቸው፡፡ ሙስሊሞቹ ፀረ-ምዕራባውያን አሸባሪዎች በተቆጣጠሩት ነፃ ግዛት በምዕራባውያን ጋዜጠኞችና የረድኤት ሠራተኛ ላይ ሲፈጽሙ በቅርቡ እንደታዘብነው፣ ወያኔዎች አንድን ኢትዮጵያዊ ዜጋ በቢላዎ ጭንቅላቱን ከአንገቱ ቆርጠው ጀርባው ላይ ሲያስቀምጡ በበኩሌ አላየሁም እንጂ የነዚህ ትግሬ ወያኔዎች የጭካኔ ደረጃ ከነዚህ አረመኔ ፍጡራን ቢበልጥ እንጂ አያንስም፡፡ የሚገርመኝ ይህን ሁሉ አረመኔያዊ ባህርይ ከየት እንዳገኙት ነው፡፡ በውነቱ ሰዎች ናቸው? ማታ ማታ ቤታቸው ሲገቡ ከቤተሰብ ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት እንዴት ይሆን? ለመሆኑ እንቅልፍስ ይይዛቸዋል? … ይህንን መሰሉን የተበላሸ ስብዕና መለወጥም የወደፊቱ መንግሥታችን የኃላፊነት ሸክም ነው፡፡

በነገራችን ላይ “ዘባራቂ” አትበሉኝና በብርሃኑ ነጋ ቃለ ምልልስ ላይ ብርሽ ሸፋፍኖ ያለፋትን አንዲት ጥያቄ “እኔ ብሆን” እንዲህ አድርጌ እመልሳት እንደነበር በዚህ አጋጣሚ ልጠቁም፡፡ ጥያቄውን ለማስታወስ ያህል – “ወያኔ ሲወርድ በወያኔያውያን የተዘረፈው የሀገር ሀብትና ሥልጣን እንዴት ወደ ሕዝብ ይመለሳል? በትግሬዎች የተያዘው ቢሮክራሲና ቤትና ቦታ ሁሉ ለሕዝብ የሚሆነው በምን ዓይነት አግባብ ነው? አሁን እንደሚታየው የኢትዮጵያውያን ቤት ስደትና ከርቸሌ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ጊዜ ሲገለበጥ አሁን የሚታየው ሀገርንና ሕዝብን እያስለቀሰ ያለ የዝርፊያና የውንብድና ጎርፍ አመጣሽ ዐይን ያወጣ የዘመን ክስተት እንዴት ይስተካከላል?” (የሲሳይ አጌናን ጨዋነት በኔ ግልጽነት ለማካካስ መሞከሬን ልብ ብትሉልኝ ደስ ይለኛል – ለማለት የፈለገ የመሰለኝን ግን ያላለውን ብያለሁና!) የኔ መልስ ባጭሩ – “ያንተ ያልነበረ ያንተ አይሆንም፤ ከአፈር ነውና የተፈጠርከው ወዳፈር ትመለሳለህ” የሚል ነው፡፡ ቀኑ መምጣቱ አይቀርም፤ ቀኑም ቀርቧል፡፡ ያኔ የተዘረፈው ሁሉ ወደየቦታው ይሄዳል እንጂ አለበለዚያማ ትግል ለምን አስፈለገ? ሰው ሀኪም ቤት የሚሄደው ታክሞ ለመዳን አይደለምን? ነቀርሣ ያለበት ሰው ሀኪም ቤት ሄዶ “ነቀርሣየን በጣም እወደዋለሁ፤ እሱንና ያደረሰብኝን ጉዳት አትንኩብኝ፡፡ ነገር ግን ከአሁን በኋላ እንዳይጎዳኝ ምከሩልኝ፡፡” ሊል ይችላልን? እንዴት ተድርጎ! አዎ፣ ፍትህ ለተጎዱ ይበየናል እንጂ ማለባበስ የሚነግሥበት ነፃነት አይኖርም፡፡ ሁሉም እንደዬሥራው፡፡

ሊሆን የሚችለው – ያድርሰንና በቻልነው ሁሉ የምንጥረውም ፍትህ እንድትገኝ ነው፡፡ የቀማ የቀማውን ነገር ለተቀማው ወገን ይመልሳል – መመለስ ብቻም አይደለም፤ ከነኪሣራውና ከነሞራል ካሣው እንዲከፍል በህግ አግባብ ሊበየንበት ይገባል፡፡ ከየትኛው ጊዜ ጀምሮ ምን በነማን እንደተደረገ ይታወቃል፡፡ ሕዝብ ደግሞ መዝገብ ነው፡፡ ሐጎስ የቀማኝን ንብረት ለማስመለስ የሚያስፈልገኝ ነገር የሕዝብ ውሳኔ የደገፈው የመብት ማስከበሪያ ቀላጤ እንጂ ይሉኝታ አይሆንም፡፡ እንደዚያ ከሆነ ነፃነትም የነፃነት ትግልም አያስፈልግም፡፡ አምባቸው በተላላኪነትና በሙስና ያካበተው መቶ ሚሊዮን ብር የሕዝብ ገንዘብ ወደመጣበት ካዝና የማይመለስ ከሆነ በጥፊ አቀርንቶ ይቅርታ እንደመጠየቅ ነው፡፡ ጥፋትን ማስተካከልና ይቅርታ ለዬቅል ናቸው፡፡ የተዘረፈ ወደተዘረፈበት ቦታ ይመለሳል እንጂ አንዴ ተዘርፏልና በዘረፈው ገንዘብ እየተንፈላሰሰ ይኑር ብሎ በፍርደ ገምድልነት መበየን ዝርፊያን ቅድስና መስጠት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ግን የወደፊቱ መንግሥታችን ሸክም ነው፡፡

አሁን ገንዘቡንም በባንክ በፈለጉት ስም ያከማቹ፡፡ ሕንፃውንም የትም ይገንቡት – በማንምም ስም ይገንቡት፡፡ ግን ግን ነገ ይህ ሀብትና ንብረት የሀገርና የቀጣዩ መንግሥት ሀብትና ንብረት ይሆናል፡፡ የህግ ዐዋቂዎች አንድ ጥፋት  በሁለት መንገድ ይታያል ይላሉ – በፍትሐ ብሔርና በወንጀል፡፡ ስለዚህ ወያኔም ይሁን ግብረ በላው ሁላ በሚሠራው የፍትሐ ብሔር ነክም ይሁን የወንጀል ድርጊት ይጠየቅበታል እንጂ ዝም ብሎ የሚታለፍ ሊሆን አይገባም፡፡ ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው ከሕዝብ ዐይን የሚሠወር ደግሞ ምንም ነገር የለም፡፡

የቀጣዩ መንግሥት ሸክም ብዙ ነው፡፡ አንደኛው እየመረረውም ቢሆን ከዚህ ከፍ ሲል የጠቀስኩትን የሕዝብ ብሶት በፍትህ አደባባይ ቆሞ በደለኞች ተበዳዮችን እንዲክሱ የማድረጉ ጣጣ ነው፡፡ ጥፋት እንዳይደገም ማድረግ የሚቻለው አጥፊነት የሚያሳድግ ሳይሆን የሚያቀጭጭ፣ የሚያለማ ሳይሆን የሚያኮስስ መሆኑን በገሃድ በማሳየት ነው፡፡ አለበለዚያ “እንዲህ ባደርግም ምንም አልሆንም” የሚል ስሜት በአጥፊዎች ዘንድ እየፈጠረ ጥፋት መሥራት ባህል እንደሆነ ይቀጥላል፡፡

አንድ ችግር ግን አለ፡፡ ፍትህን ለማስፈን ማን ነው የሞራል ብቃት የሚኖረው? የክርስቶስን ቃል እዚህ ላይ ያስታውሷል፡፡ የዚያችን በአመንዝራነት የተከሰሰች ሴት ታሪክ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ ኃጢኣት ያልሠራ የመጀመሪያውን ድንጋይ እንዲወረውርባት ክርስቶስ ሲናገር ሁሉም ሹልክ ሹልክ እያሉ ጠፉና ተከሳሹዋ ብቻ ቀረች፡፡ ማን ይድፈር? … ለመሆኑ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ስንት ነን? ራሳችንን እንጠይቅ፡፡ ማን ነው በማን ላይ መፍረድ የሚችል? ማን ነው ንጹሕ? ማን ነው ዕድፋም? በሰው ዐይን ውስጥ የሚገኝን ስንጥር የሚያህል ጉድፍ ለማውጣት ከመሞከራችን በፊት በራሳችን ዐይን ውስጥ እርፍ እሚያህል ጉድፍ ላለመገኘቱ እርግጠኞች ልንሆን ይጠበቅብናል፡፡ ትግል ከራስ ብላለች ዘፋኟ፡፡

የነገዎቹ መሪዎቻችን አሁን የት ነው ያሉት? ምን እያደረጉ ነው? ከደሙ ንጹሕ ናቸውን? እየተጠላለፉ ነው ወይንስ ምቹ ሁኔታ እስኪፈጠር በአርምሞ እየተጠባበቁ ናቸው? ራሳቸውን ከወንጀልና ከሙስና አጽድተው በጥሩ ድህነት እየኖሩ ነው ወይንስ በ“ሲሞቅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ” ዓይነት እንደአየሩ ጠባይ ድርጊታቸውንም አነጋገራቸውንም እያስተካከሉ በእስስታዊ ባሕርይ ቀን ይጠብቃሉ? አሮጌው ወይን በአዲስ አቅማዳ ይገለበጥና ከአንዱ የመከራና የሥቃይ አዙሪት ወደሌላው እንዛወር ይሆን ወይንስ ፈጣሪ በቃችሁ ይለናል? የአዲሱ መንግሥታችን ሰብኣዊና መዋቅራዊ ቅርጽና ይዘት ከአሁኑ ያስጨንቀኛል፡፡ ለምን ቢሉ እባብን ያዬ በልጥ ይበረያልና፡፡ ስንቱ ቂጣ ይረረብን? ምጣዱስ፣ ማገዶ እንጨቱስ፣ ጊዜውስ፣ ትውልዱስ … አያሳዝኑምን? ኧረ ወደቀልባችን እንመለስ!

ስለሆነም ቀጣዩ መንግሥት ብዙ ዕዳ አለበት ነው ባጭሩ፡፡ ቀዳሚው ዕዳው ራሱን የማወቅና ካለፉት በርካታ እንቶ ፈንቶ ሰይጣናዊ አገዛዞች የተለዬ መሆኑን በተግባር የማሳየት ኃላፊነት ነው፡፡ ጨካኝ መሆን ሩህሩህ ከመሆን ያነሰ ወጪ እንዳለው ግልጽ ነው – የዞረ ድምሩ ግን ብዙ ኮተት አለው፡፡ ከሞላ ጎደል የሁሉም ጨካኝ ገዢዎች የመጨረሻ ዕድል ተመሳሳይ ነው፤ ቢያንስ በታሪክ ስማቸው ሲወቀስ ይኖራል፡፡ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው በሀፍረት እየተሸማቀቁ አንገታቸውን ደፍተው ለመኖር ይገደዳሉ፡፡

በተረፈ የቀጣዩ መንግሥታችንን ሸክም የሚያበዙ ሀገራዊ ጉዶችን ዘርዝረን አንጨርሳቸውም፡፡ በትምህርት ረገድ “ A,B,C,D” ን በቅጡ ያልለዩና ስማቸውን እንኳንስ በእንግሊዝኛ በሀገርኛ ቋንቋም መጻፍ የማይችሉ ወይም የሚከብዳቸው የቢኤና ኤምኤ ዲግሪ ተመራቂዎችን እንደገና ለማስተማር ራሱ ትልቅ ሥራ ይጠብቀዋል፡፡ በዜግነትህና በሰውነትህ ብቻ ተንቀባርረህና “ጎይታይ እምበይተይ” ተብለህ ሊፈጸምልህ ለሚገባ አንድ ጉዳይ እጅ እጅህን  የሚመለከት ሲቪል ሰርቫንት የሚዋኝበትን የመንግሥት ቢሮክራሲ ለማጽዳት የፈጣሪ ተዓምር ካልታከለበት በስተቀር መቶ ዓመትም የሚበቃ አይመስለኝም፡፡ ወደ ሆድ ወርዶ የተሸጎጠውን የሚሊዮኖች ጭንቅላት ከቦርጭ አውጥቶ ወደ ትክክለኛ ሥፍራው ለመመለስና በአንጻራዊ አነጋገር እንደቀድሞው ያለ የመተሳሰብና የመተዛዘን ዘመን ለማምጣት 90 ሚሊዮን ሕዝብን እንደገና የመፍጠር ያህል ከባድ ሥራ ነው፡፡ ግን ግን ኢትዮጵያውያን ስንት እንሆን ይሆን?(እኔ በበኩሌ ከቁጥር የማልገባ ቦቅቧቃ መሆኔን ከአሁኑ እቅጩን መናገር እፈልጋለሁ – ለከንቱ ውዳሤ እንዳይመስላችሁ!! ከእውነት ፈሪና ሀገሬ የኔን አስተዋፅዖ በምትፈልግበት ወቅት ተደብቄ የምኖር ወሬ ጠራቂ ነኝ፡፡)

በአንድ ወይ በሌላ ነገር ያልጠፋን ዜጎችን ለማግኘት አይቻልም፤ እንዲያ ባንሆን ኖሮ ቢያንስ ሀገር በኖረን ነበር፡፡ ትልቁ የመጥፋታችን ምልክት በጥቂት ወንበዴዎች መቶ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ መቅኖ አጥቶ መቅረቱ ነው፡፡ የሎጥን ታሪክ አስታውስ፡፡ “ጌታ ሆይ አምሳ ሰው እንኳን ባገኝ ቁጣህን አትመልስልኝምን?” – ከተሳካልህ እሺ ይሁንልህ፡፡ ፈለገ፡፡ አጣም፡፡ … “ጌታ ሆይ! አምስት ባገኝስ?” – ከተሳካልህ እሺ ይሁንልህ፡፡ አሁንም ፈለገ፤ ግን አጣ፡፡ ታሪኩን ራስህ ጨርሰው፡፡ የሆነውንም አስብ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ደረጃውን የጠበቀ ጥሩ ዜጋ ለማግኘት እግርህ እስኪነቃ ብትሄድ የምታገኝ አይመስለኝም፡፡

ነጋዴው ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር እየተመሣጠረ በየቀኑ በሚቆልለው የሸቀጦች ዋጋ ኑሮው የሰማየ ሰማያትን ድምበር ጥሷል፡፡ ለጠቅላላ ዕውቀትህ ያህል የቀዳማዊ ኃ. ሥላሴ ዘመን አንድ ብር በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ ዕቃዎች 30 እና 40 ብር ሲሆን በአንዳንድ ውድ ዕቃዎች ደግሞ ከ500 ብር የሚበልጥባቸው ምንዛሬዎችም አሉ፡፡ ሆድ ተምቦርቅቆ ጤናማ ኅሊና ቁልቁል በመውረድ ቦርጭ ውስጥ ተወሽቆ ሕዝብ ደም እያለቀሰ ነው፡፡ በሕዝቡ መካከልም ፍቅርና መተሳሰብ ጠፍቶ፣ መተዛዘንና መከባበር ተረት ሆነው፣ ሃይማኖት በፍቅረ ንዋይ ተለውጦ፣ ቄሱና ጳጳሱ ሳይቀሩ ከዓለማውያን በበለጠ ሥጋውያን ሆነው የደም ግብር ለለመደውና ካለደም ግብር እስትንፋሱ ለማትቀጥለው የደራጎን መንግሥት አድረው ለዲያብሎስ መንግሥት እየሰገዱ፣ ሞራልና ትውፊት ባህልና ወግ ልማድ አጥራው ተደረማምሶ ዜጎች ወደ አውሬነትና ወደ እንስሳነት እየተለወጡ፣ መስጊድና ቤተ ክርስቲያናት ለግብር ይውጣ ካልሆነ በሃቅ አምልኮት የማይካሄድባቸው የአጋንንት መፈንጪያ ሆነው፣ ከህገ አምላክና ከህገ ተፈጥሮ ባፈነገጠ ሁኔታ ልቅ ወሲባዊነትና አመንዝራነት እንዲሁም አፈንጋጭ የሴሰኝነት ልማዶች ሀገር ምድሩን ሞልተውትና ይህንን ሰይጣናዊ አፈንጋጭነትም በህግ ለማስረገጥ በሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄ ለማቅረብ የማያፍሩ ዜጎች እየበዙ፣ ቅድስቲቷን ሀገር ለማርከስ ዓለም አቀፍ ዘመቻ ተከፍቶ ለብልግና ሥራዎች ማስፋፊያ የውጭ የገንዘብ ድጎማና በክፋት ሥራ የሰለጠነ የሰው ኃይል ድጋፍ እየተደረገ፣ ዘረኝነት ሀገሪቱን እንደብል እምሽክ አድርጓት ሁሉም ነገር በወያኔዎች ቁጥጥር ገብቶ… ባለበት ሁኔታ አዲሱ መንግሥታችን ቢመጣ የሚገጥመውን ሁለንተናዊ እንቅፋትና የሥራ ብዛት ከአሁኑ አስቡት፡፡ ጓዶች – የአዲሱ መንግሥታችን ሸክም እጅግ ከባድና ካለፈጣሪ ዕርዳታም የማይሞከር ነው፡፡ በሰው አምሳል የሚንቀሳቀስን አገር ሙሉ አውሬና ነቀዝ ወደሰውነት ለመለወጥ ብዙ ትግስት፣ ብዙ መንፈሣዊና ሥጋዊ መልካም ዕውቀት፣ ብዙ ጥበብ፣ ብዙ ልምድና የአስተዳደር ችሎታ፣ ብዙ ትምህርት፣ ብዙ ተሞክሮ፣ ብዙ መለኮታዊ እገዛና ብዙ የእምነት ጥንካሬ … ያስፈልጋል፡፡ ማይማኑና ደናቁርቱ ወኔያዎች ከ23 ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ ያበለሻሹትን የመንግሥት ቅርጽና ይዘት ለማስተካከል ሌት ከቀን የሚሠሩ ሀገር ወዳድና ለሆዳቸው የማያድሩ ቆራጥ ዜጎች ያስፈልጉናል፡፡ እንዲሁ ስለማይገኙ በየምነታችን ወደዬምናመልከው እንጸልይ ምዕመናን፡፡

ግን ግን ካንጀቴ ልጠይቃችሁና በአሁኑ ወቅት እኛ ኢትዮጵያውያን ስንት እንሆን ይሆን? ጥያቄዬ የሚመለከተው በትልቁ እሥር ቤት ማለትም በዞን ዘጠኝ ውስጥ የምንገኘውን እንጂ በጠባቡ የቃሊቲና መሰል ኢትዮጵያውያን የወያኔ ኦሽቲዊዞች ውስጥ እየተሰቃዩ የሚገኙትን እንዲጨምርብኝ አልፈልግም፡፡ በነዚህ እሥር ቤቶች ውስጥ የሚማቅቁ ዜጎች የኔን ፍርሀት በነሱ ወኔና ጀግንነት አሸንፈው የኔንም የነሱንም ስቃይ እየተሰቃዩ የሚገኙ ዳግማዊ ክርስቶሶች ናቸውና በነገይቱ ኢትዮጵያ የድል አክሊል የሚቀዳጁ የነፃነት አርበኞች ናቸው፡፡

(ዲባቶዎች መሣይ ከበደ፣ ብርሃኑ ነጋና ተስፋዬ ደምመላሽ በግዛው ለገሰ የኢሳት ቲቪ ውይይት ላይ ስከታተላቸው ከመሣይ አስተሳሰብ የፈለቀ አንድ አመለካከት ገረመኝ፡፡ ሌላ ቦታ ስለማላገኝ አሁኑኑ ባጭሩ ልተች፡፡ መሣይ የሚለው  “ወያኔዎች ጋር ሰላምና ዕርቅ ለመፍጠር መከላከያውንና ፀጥታውን በነሱው ቁጥጥር ሥር እንደሆኑ ትተን በሌሎች የፖለቲካ መስኮች አብረን መካፈል እንድንችል ለድርድር እንጋብዛቸው” የሚል ነው፡፡ መሣይ ውስጥ በእንግሊዝኛው የቃላት አጠቃቀም naivety ቁልጭ ብሎ ይታየኛል፡፡ ዋናዎቹ የወያኔ መሣሪያዎች ምን ምን ሆኑና ነው? እነዚህን ጡንቻዎች የያዘ አካል ምን ዓይነት መብት ነው ለሕዝብ የሚሰጥ? ዋናው የተቃዋሚም ሆነ የህዝብ ትግልስ እነዚህን የወያኔ እንደልብ መፈንጠዣ ተቋማት ለመቀማትና ለሕዝባዊና ሀገራዊ ዓላማ ለማዋል አይደለምን? ለዚህ ለዚህማ ምን ድርድር ያስፈልጋል? ልክ እንደነልደቱ አያሌውና አሁን አሁን ደግሞ እንደግዛቸው ሽፈራው መሰል የወያኔ አጫፋሪዎች ከወያኔ ጋር አብሮና ተባብሮ የሕዝብን ሰቆቃ ማራዘም ይቻላል፡፡ ብርሃኑ እንዳለው አምባገነኖች በምንም ዓይነት መንገድና ሁኔታ ለድርድር አይቀርቡም፡፡ ሞተውም ሞታቸውን የማያምኑ ገልቱዎች ናቸው፡፡ ጋዳፊ በሰደፍ እየተወገረና ሣንጃ በእንትኑ እየገባበት የሀገሩ መሪ እርሱ እንደሆነና እስከዚያን ቅጽበት እንኳን በሊቢያ እየተካሄደ ያለውን ሕዝባዊ አመፅ ለማመን ባለመፈለግ እንዲያውም ምን እንደተፈጠረም ለማወቅ በሚመስል የልብ መደፈን “ጠባቂዎቼ የት አሉ? ምን ሆናችኋል? ግርግሩ ምንድንነው?…” ይል ነበር አሉ፡፡ አምባገነኖች እስከዚህን ድፍን ቅል ናቸው፡፡ እናም የመሣይ የቀቢፀ ተስፋ ንግግር አስገርሞኛል፤ አስቆኛልም፡፡ “ራስዋ ሄዳ ጣፊያ የከለከሏት ‹ምላስ ሰምበር ላኩልኝ› አለች” ይባላል፡፡ ወያኔ እንዴትና መቼ እንደሚወድቅ ለምንገምት ወገኖች የመሣይ ሃሳብ ምን ያህል ሞኝነት እንዳለበት መረዳት አይከብደንም፡፡)

ለማንኛውም እንኳን ለ2007 ዓመተ ፍዳ በሰላም አደረሳችሁ፡፡ እንዳይመስልህ – ይህም ያልፋል ደግሞ፡፡

Comment

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>