ስብሃት አማረ
እንደሚታወቀው ላለፉት 23 አመታት በኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ የተቀምጠውን ዘራፊውን እና ጨቋኙን የወያኔ ጁንታ በጀመርነውና በተያያዝነው አዲስ አመት ለመቅበር የአንድነት እና የለውጥ ሃይሎች ልዩነቶቻችንን በማቻቻል በጋራ ልንታገል የሚገባና ለህዝባችንና ለሃገራችን ስር ነቀል ለውጥ ልናመጣ የሚያስችለንን ምዕራፍ የምንጀምርበት አመት መሆን አለበት። ባሳለፍናቸው በርካታ የትግል አመታት ውስጥ የተቃዋሚዎች እርስ በእርስ መፈራረጅና መወነጃጀል የወያኔን እድሜ ከማራዘም ውጪ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያተረፈው አንዳችም ነገር የለም። የአንድነት የተቃዋሚ ሃይሎች ጥንካሬ እንዲጎለብት በየድርጅቱ ውስጥ ያሉትን እንከኖች በማጥራት በጋራ እና በተቻቻለ የሃሳብ መግባባት ተቻችሎ እና ተግባብቶ ሁለገብ የትግል ስትራቴጂን ከግብ ለማድረስ ጠንክሮ መስራት ይጠበቅብናል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለውጥ ይፈልጋል። ኢትዮጵያውያን ለውጥ እንፈልጋለን ስንል እውነተኛና ዴሞክራስያዊ የሆነ ለውጥ እንፈልጋለን ማለታችን ነው ። ለለውጥ፣ ለፍትህና ለእኩልነት ነገ የምንጠብቀውንና የምንናፍቀውን የማይቀረውን ዴሞክራሲያዊ የመንግስት ለውጥ እስከምናገኝ ድረስ እንደትናንቱ ዛሬም አሁንም ድምጻችን እንዲሰማ እንጮሃለን።
በሃገሪቱ ያለውን ሁኔታ በትክክለኛው መንገድ የማያስቀምጡ የወያኔ ሚዲያዎች እርስ በእርሳቸው የሚጋጩ ዘገባዎችን በመስራት እና እውነትን ለመሸፋፈን በመትጋት የሕዝቦችን የማወቅ መብት ያለርሕራሄ እየተጋፉት/እየገፈፉት ይገኛል። ይህ በወያኔ የፕሮፓጋንዳ አካላት የሚፈጸም ማጭበርበር እና ማደናገር የገዢውን ፓርቲ ውስጣዊ ዝርክርክነት በይፋ ያሳብቃል። የሌለውን እንዳለ፤ ያልተሰራውን እንደተሰራ፤ ሕዝቡ የማያገኘውን አገልግሎት እንደሚያገኝ፤ ወዘተ በማድረግ በተጋነነ ሁኔታ ባልሆነ ስሌት በማባዛት በመቶኛ በማስላት በመደመር በማባዛት የሌለ ምስልን በመፍጠር ሕዝቡንና እርዳታ ሰጪ መንግስታትን ለማደናገር ይሞክራሉ።
ፍትሕ አጣን፣ ፍትሕ ዘገየብን፣ ፍትሕ ተነፈግን የሚሉ በርካታ ዜጎች ባሉበት አገር ውስጥ የፍትሕ ሥርዓቱ ተደራሽነት ወደር እንደሌለው የሚደሰኩሩ የመንግስት ሪፖርቶችና መግለጫዎች የሚያስገርሙ ናቸው፡፡ ሕዝቡ በየፍርድ ቤቱ በተጓደለ ወይም በተነፈገ ፍትሕ ምክንያት ከላይ ታች ሲባዝን/ሲንከራተት እየታየ የማይመስልና የሌለ ነገር ይነገራል፡፡ ከሰሞኑእንኳን ጋዜጠኞችና ጦማሪያኑ መንግስት ያወጣውን ህግ እንዲያከብር ስለጠየቁና በአደባባይ ስለጻፉ ግፍ እየተፈጸመባቸው እንደሚገኝ የአለም ህዝብ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ያወገዙት የወያኔ ተግባር ነው። በየእስር ቤቱ የሚማቅቁትንና የግፍ ግፍ እየተፈጸመባቸው ያሉት በነርዕዮት፣ ውብሸት፣ አንዷለም፣ እስክንድርና በሌሎችም ላይ እየተደረገ ያለው ስቃይና እንግልት ሳያንስ ሰሞኑን ደግሞ የሚወዱትን ህዝብ፣ የሚወዱትን ሃገርና የሚወዱትን ሞያቸውን በመተው የተሰደዱትን ጋዜጠኞች ማስታወስና እየከፈሉ ያሉትን መስዋእትነት መዘከር ያስፈልጋል። እኚህ የተሰደዱትና የታሰሩት ጋዜጠኞችና ጦማሪያን ያሸበሩት ሀገርና ህዝብ የለም፥ መንግስት ያወጣውን ህግ እንዲያከብር ለህግም ተገዢ እንዲሆን ጠየቁ እንጂ ።
ሌላው በየአካባቢው ‘ቀና ብለህ ባለስልጣን ተናገርክ፣ አግባብነት የሌለው ጥያቄ ጠየቅህ፣ ባለስልጣን ተዳፈርክ፣ ከሁለት በላይ ተሰብስበህ አየንህ’ ወዘተ እየተባለ የሚገረፈው፣ እንደ እንስሳ እየተገደለ የሚጣለው ኢትዮጵያዊ የሰራው ወንጀል የለም። በፍጹም አሸባሪም አይደለም! በየቦታው ቦንብ እየቀበረ ወይንም እያስቀመጠ አፈንድቶ ንጹሃንን ገድሎ ሲያበቃ ‘ሊያፈነዱ ሲሉ ተደረሰባቸው’፣ ወይንም ‘ፈንድቶባቸው ራሳቸውን ገደሉ’ ብሎ ውዥንብር የሚነዛው አሸባሪው ህወሃት እንጂ ንጹሃኑ ኢትዮጵያዊ እንደአይደለ የታወቀ ነው።
ተደጋግሞ ከተለያዩ የህግ ባለሙያዎች እንደተገለጸው አለምዓቀፍ ህግን በተጻረረ መልኩ ኦኬሎ አኳይንና አንዳርጋቸው ጽጌን ከመንገድ ያውም ከሰው አገር በጉቦ አስጠልፈውና አፍነው በመውሰድ ያው የተለመደ ግፋቸውን እየፈጸሙ ይገኛሉ፣ ይህ የሚያሳየው ወያኔ እጁ ምን ያህል ረጅም እንደሆነ ነው። እነዚህ ሁለት የፍትህና የእኩልነት ታጋዮች ኦኬሎ አኳይንና አንዳርጋቸው ጽጌ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው እንደ ሌሎች የተቃዋሚ መሪዎች የበኩላቸውን ለማበርከት ደፋ ቀና ሲሉ በወያኔ መረብ ውስጥ ቢገቡም ለፍትህና ለእኩልነት እንዲሁም ለሃገር ነጻነት የከፈሉት አስተዋጽኦ መቼም የማይረሳ ታላቅ መስዋእትነት ያበረከቱ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ናቸው።
በአጠቃላይ ሲታይ ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ አሳሳቢና አስጊ የመሆኑን ያህል የወያኔ አባልና ደጋፊ ‘ጤነኛ’ ለሃገር አንድነትና ለፍትህ የሚከራከረው ተቃዋሚው ወገን ደግሞ ‘አሸባሪ’ የሚል አጸያፊ ተቀጥላ በማበጀት ንጹሃኑን በየእስር ቤቱ በማጎር ህዝባዊውን ትግል ለማኮላሸት በመፍጨርጨ ላይ ይገኛል፡፡
ትግልን በጋራና በውህደት ማቀናጀት ወቅቱ የሚጠይቀው ሁኔታ እንደሆነ እየታዩ ያሉት አንዳንድ ምልክቶች አሉ፣ በመሆኑም ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ካሉበት አዘቅት በማውጣት ሕዝቡ የስልጣን ባለቤት የሚሆንበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የጋራ ትግልና መስዋዕትነት የግድ የሚል ደረጃ ላይ በመድረሱ፤ የወያኔን ቡድን በሁለገብ ትግል በመፋለም በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምኑ ድርጅቶች ተጣምሮና አንድ ሆኖ መታገል እንዳለባቸው ከሰሞኑ የተወሰዱት የ3 ድርጅቶች የውህደት ንግግርና ስምምነት ያሳያል።
ወቅቱ ለጠየቀው የሀገር አድን ጥሪ ምላሽ በመስጠት የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር የአርበኝነት ትግል ችቦውን በመለኮስ እንደ ሻማ በመቅለጥ ብርሃን እየሰጠ ያለ ግንባር እንደመሆኑ መጠን የተለኮሰውም የትግል ችቦ ሳይጠፋ የታለመለትንና ለታቀደለን አላማ እስከግብ ድረስ እንዲዘልቅ የወያኔን አገዛዝ እድሜ ለማሳጠር ትግሉን በማጠናከር በአሁኑ ሰዓት ግንባሩ ከግንቦት 7 የፍትሕ የነፃነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ እንዲሁም ከአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ ጋር ውህደት ለማድረግ መስማማታቸው የሚያስመሰግንና ለሌሎችም የአንድነት ሃይሎች ተባብሮ የመስራትን ነገር ማሳያ በመሆን አስፈላጊ የሆነ ጥርጊያ መንገድ ይከፍታል/ከፍቷል። ውህደቱ ተጠናቆ የድሉን ፍሬ ተቋዳሽ የምንሆነበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን አምናለሁ።
ስለዚህ ኢትዮጵያውያን የአንድነት ሃይሎች በመተባበር፣ በመጣመርና በመዋሃድ ሃይልን፣ እውቀትን፣ ህብረትን እንዲሁም ገንዘብን በማቀናጀት የወያኔን አገዛዝ ከኢትዮጵያ ምድር ወደ ከርሰ መቃብር ለአንዴና ለመጨረሻ አሸቀንጥሮ ወርውሮ ሃገርንና ህዝብን ለነጻነት ለማብቃት በጋራ መታገል ግዴታችን መሆኑን አውቀን በአንድነት ስርዓቱን ማስወገድ ማንኛውም ሃገሬንና ህዝቤን እወዳለሁ የሚል ዜጋ ሊነሳለት እና ሊተገብረው የሚገባ መሆኑን በመግለጽ የበኩሌን ሃሳብ ለማቅረብ እወዳለሁ::
አንድነት ኃይል ነው !!
ድል ለሰፊው ለኢትዮጵያ ሕዝብ !!