መስከረም ፳፻፯ ዓ.ም.
http://www.medhanialemeotcks.org/
መግቢያ
ለአዘማሪ ሙያ ተስማሚ የግብር መግለጫ መሆን ያለበት የቱ ነው? አዘማሪ ወይስ አርቲስት? በሚል በአቶ ዓለም ነጻነት ሬድዮ የቀረበው ውይይት ለዚህች ጦማር መነሻ ሆኖኛል።ከቀደሙ አባቶች እንደሰማሁት አዘማሪ ብቻውን የቆመ አይደለም። ከብዙ ነገሮች ጋራ ከቅኔያችን፣ ከዜማችንና ከስሜታችን ጋራ የተያያዘ ነው። አዘማሪ የሚለውን ቃል ከነዚህ ነጥሎ ለማቅረብ መሞከር ያዘማሪን ክብርና ቦታ ዝቅ ያደርገዋል የሚል ስጋት አለኝ።
ስለዚህ አዘማሪ ወደሚለው ቃል ዘው ብለን ከመግባታችን በፊት የአዘማሪን ተልእኮ መዳሰስ ሊኖርብን ነው። አዘማሪ የሚለው ቃል የግብሩ (የተልእኮው) መግለጫ ነው። ተልእኮውም ራሱ አዘማሪ ተቀኝቶም ሆነ ገጥሞ ወይም ሌላ የተቀኘውን በዝማሬው ቅላጼ ከጉሮሮውና ከመሳሪያ ጋራ አስማምቶ፣ ቀምሞና አስወድዶ አስውቦ ለህዝብ ማቅረብ ነው። ህዝቡንም ከባህሉ ከታሪኩ ከኢትዮጵያዊነቱ ከስሜቱ ጋራ እርስ በርሱ የበለጠ ያጣብቃል። እርስ በርሱ ያቀራርባል። ያዋህዳል። ያስተባብራል። እንደ ኢትዮጵያ ከመሰለ በቅኝ ግዛት ሳይወረር የራሱን ጠብቆ ከሚኖር አገር የሚፈልቅ አዘማሪ የሚያስተላልፈው ቅኔ፦ ኅብር፤ ሰምና ወርቅ፤ ሰረዝ፤ ጎዳና፤ ውስጠ ወይራና ሌላም ዓይነቶች አሉ። ያዘማሪን ክብርና ቦታ ዝቅ ላለማድረግ ስለአዘማሪ ከመናገሬ በፊት ስለኢትዮጵያዊ ቅኔ ትንሽ ማብራሪያ መስጠት ፈለኩ።