እስከመቼ ቅፅ ፲፯ ቁጥር ፲፯
አንዱ ዓለም ተፈራ
መስከረም ፲፭ ቀን ፳ ፻ ፯ ዓመተ ምህረት ( 9/25/2014 )
በስታቲስቲክስ የተደገፈ የጥናትና ምርምር ዘገባ ማቅረብ ባልችልም፤ ባካባቢዬ ያለውን ሀቅ ተከታትዬ የሚኖረኝ ግንዛቤ፤ መንገዱኝ ይከፍትልኛል። የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎት ሰብስቤ፤ ይሄ ነው ብዬ የማቀርበው የጥናት ዘገባ የለኝም። ውጪሰው ኢትዮጵያዊያን ስለሚፈልጉት ወይንም ስለሚያደርጉት ተጨባጭ ማስረጃ ያጠራቀምኩት ዝርዝር የለኝም። ነገር ግን፤ በመጀመሪያ እኔ ራሴ የውጪሰው ኢትዮጵያዊያን አካል በመሆኔ፤ በዙሪያዬ ከምገናኛቸው እንደኔው የውጪሰው ኢትዮጵያዊያን ጋር ስለሀገራችን ሁኔታ እወያያለሁ። ለጥቆም በየድረ ገጹ የሚጻፈውን አነባለሁ። ባጠቃላይ በማንኛውም የዜና መለዋወጫ መንገዶች ሁሉ የሚካሄደውን የሀገሬ ጉዳይ ሳላሰልስ በቀን ሳይሆን በየሰዓቱ ማለት በሚቻልበት ሁኔታ እከታተላለሁ። ከሞላ ጎደል ሁላችን በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ሀቅ መለወጥ እንዳለበት እናምናለን። ከዚያ አልፎ እያንዳንዳችን ለዚህ ለውጥ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት እንዳለብን እናምናለን። እናም ዝግጁ ነን። ታዲያ እንዴት አድርገን ነው ይኼን ኃላፊነት፣ ፍላጎትና ዝግጁነት፤ በትክክለኛና በተሰባሰበ የአንድነት መንገድ ለትግሉ እንዲሠለፍ የምናደርገው?
በተከታታይ፤ ኢትዮጵያዊነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ፣ በሀገራችን ያለው ምን ዓይነት መንግሥት እንደሆነና ምን ዓይነት ትግል እንደሚያስፈልገን በዚሁ ድረገጽ አስፍሬያለሁ። ( የጎደለና ያላነበቡ ካሉ፤ nigatu. wordpress.com በመሄድ ሙሉ ጽሑፎችን መመልከት ይቻላል። ) በዚህ ጽሑፍ ደግሞ የሚከተሉትን በቅደም ተከተል የማቀርባቸው ነጥቦች፤ ሀ) ይህ የወራሪ መንግሥት ሀገራችንንና ሥልጣኑን ወዶ እንደማይለቅ፤ ለ) ከዚህ መንግሥት ጋር የሚደረገውን ትግል፤ ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያዊነት ብቻ ለስኬት እንደሚያበቃው፤ ሐ) ትግሉ በአንድ ማዕከል መመራት እንዳለበት፤ መ) ትግሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ የነፃነት ንቅናቄ እንደሆነ፤ ሠ) ትግሉ የግድ የሰላም ትግል እንደሆነ እና ረ) አሁን የተያዘው አወቃቀሩ የተሣሣተ የድርጅቶች መንገድ መሰረዝ እንዳለበት በመዘርዘር፤ ምን ማድረግ እንዳለብን አመላክታለሁ።
ሀ) ይህ የወራሪ መንግሥት ሀገራችን እና ሥልጣኑን ወዶ አይለቅም።
አንዳንዶች፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወራሪውን መንግሥት ስለማይወደው፤ “በምርጫ አቸንፈነው ሥልጣኑን ይለቃል”፤ ብለው ያምናሉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ወራሪውን መንግሥት ስለማይወደው የሚለው፤ ትክክል ነው። ቀጥሎ ያሉት ሁለት ነጥቦች ግን አጠያያቂ ናቸው። በመጀመሪያ በምርጫ አቸንፈነው! የሚለውን እንመልከት። ምርጫን ማቸነፍ የሚቻለው፤ ትክክለኛ የሕዝብ ወኪልነትን ለማግኘት ትክክለኛ መፍትሔ መያዝ ቅድሚያ ያለው ሆኖ፤ ትክክለኛ የምርጫ ቅንብርና አስተማማኝ የአመራረጥ ሂደት ሲኖር ነው። የወራሪው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር በምንም መንገድ ትክክለኛ የምርጫ ቅንብር እንዲኖር አይፈልግም። እንዳልነው ሕዝቡ አይወደውምና! ምርጫ የሰላም የፖለቲካ ትግልን መሠረት ያደረገ ነው። ለዚህ ደግሞ፤ መንግሥቱ የኢትዮጵያ ሆኖ፤ የሚያስተማምን ሕጋዊ መንገድ ሲኖር ነው። ይኼ የለም።
ሰላማዊ ትግልን በተመለከተ፣ ያልተስተካከሉ ሁለት አፅናፋዊ አመለካከቶች አሉ። የመጀመሪያው “ሰላማዊ ትግል አይሠራም!” ብሎ አጠቃሎ የሚኮንነው ክፍል ነው። ሌላው ደግሞ “ሰላማዊ ትግሉን እንደ እንቁላል ተሽቆጥቁጦ አቅፎ መጓዙ!”ን ያመነበት ክፍል ነው። ሰላማዊ ትግል፤ በነዚህ መካከል ነው በተግባር የሚካሄደው። ሰላማዊ ትግሉን የሚያምኑ ታጋዮች፤ ባለው ሕገ መንግሥት ተገዝተው ማጌጫ፤ ያንገት ጌጥ የሚሆኑ አይደሉም። ማኀተማ ጋንዲ ወራሪ እንግሊዞችን፤ ፓርላማ እንዲያስገቡት ከምርጫቸው ውድድር አልገባም። በጥቅማቸው ላይ ተነስቶ አመጽ ነው ያካሄደው። እሰሩን እንጂ አናደርግም ብሎ ነው ያመጸው። “የናንተን ጨው ከምንቀበል፤ በእግራችን ረጂም መንገድ ተጉዘን የራሳችን እናገኛለን!” ነው ያሉት። ማርቲን ሉተን ኪንግና አፍሪቃዊ አሜሪካዊያን ሰላማዊ ታጋዮች ለሚያደርጉት ሰላማዊ ሰልፍ፤ ፕሬዘዳንቱና አቃቤው “እባካችሁ ታገሱን፤ እስካሁን ያገኘነውን ድል ያስተጓጉልብናል!” ሲሉ፤ “ያ የናንተ ጉዳይ ነው። ለኛ ከነፃነታችን የበለጠ የናንተን አቋም አክብደን ቦታ አንሠጠውም!” በማለት ሰልፋቸውን ቀጠሉ።
ሰላማዊ ታጋዮች እንግዲህ ዋና ዓላማቸውን ለማግኘት፤ የሚከፈለውን መስዋዕትነት እያወቁ፤ እምቢታን ማስቀደማቸው ነው ትግሉ። ይህ ወራሪ መንግሥት ነው። በሱ ፓርላማ መግባትና አለመግባት፣ በዚህ ምርጫ ቁጥር ማግኘትና አለማግኘት፤ ዋጋ እንደሌለው ታሪኩ አስተምሮናል። ይህ ወራሪ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት፤ ምንም ዓይነት የመግባባትና አብሮ ነገሮችን የመመልከት አእምሮ የለውም። ስለዚህ የምርጫ ጉዳይ ለሱ ጌጥ ከመሆን ሌላ ምንም ትርጉም የለውም።
ወራሪው መንግሥት የፈለገውን ገደብ ቢያደርግም፤ የሕዝቡ ታጋይ ክፍል ባንድነት የሚነሳበትን መንገድ ማበጀት አለብን። ለሕዝቡ የሚቀርቡት ምርጫዎች፤ ወራሪው በሚያዘጋጃቸው የሱ መደነቂያ መድረኮች ሳይሆኑ፤ ታጋዩ ክፍል በሚያዘጋጃቸው የራሱ መድረኮች መሆን አለባቸው። የራሱ መድረኮች በሙሉ ለራሱ የተዘጋጁ ናቸው። እኒህን ማስወገድና ከኒህ መራቅ አለብን። በታጋዩ ክፍል ለሕዝቡ የሚቀርቡት፤ ኢትዮጵያዊነት ወይንም የወራሪው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ፀረ-ኢትዮጵያዊነት ብቻ መሆን አለባቸው። በዚህ ታጋዩ ራሱ በሚያዘጋጀው ምርጫ፤ ወገን ይለያል። አንድም ከሕዝቡ ጋር መቆምን፤ አለያም ከወራሪው ጋር መቆምን። ትግሉ በኢትዮጵያዊነት ላይ ብቻ ያተኮረ መሆን አለበት። ይህ እንዳይሆን ወራሪው መንግሥት ሰማይ ይቧጥጣል፣ ይለምናል፣ ያስፈራራል፣ ጦር ይቀስራል፣ የማያደርገው ነገር የለም። እኛም ተመችተንለታል። ስለዚህ ራሳችንን ካላስተካከልን፤ ወደፊት መሄድ አይቻለንም። እናም በምርጫው ለሱ ጃኖ አልባሽ ከመሆን ይልቅ፤ የመውደቂያው አለት ድንጋይ እንዲሆን ማድረግ አለብን። በሱ ድግስ እናቸንፋለን የሚለው ተቀይሮ፤ የምርጫውን ምንነት በማሳወቅ በራሱ ድግስ መውደቂያዉን ለማዘጋጀት እንጣር።
በሌላ በኩል ደግሞ ወራሪው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ሥልጣኑን ስለመልቀቁ ነው። ይህ እኮ ወራሪ ነው። ወራሪ በየትኛው ታሪክና ቦታ ነው ወዶ ሥልጣኑን የለቀቀው? ወራሪው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግምባር እኮ ሥልጣኑን የሚለቀው፤ መቃብሩ ላይ ሲደርስ ብቻ ነው። እናም በአንድነት እንግፋው። ወዶ ይለቃል ማለታችንን ትተን፤ አስገድደን ለማስለቀቅ ወስነን በተግባሩ እንሰማራ። የምናስገድደው ጦር መዘን ሳይሆን በሕዝብ የአንድነት እምቢታ ነው። ጠመንጃችን እምቢታችን ነው። ይህ ወራሪ ሕግ ያወጣል መልሶ ያፈርሰዋል። የሚያውቀው ቢኖር እሱ ዘለዓለም ገዥ ሆኖ መቀመጥ እንዳለበት ብቻ ነው። ስለዚህ ምንም መያዣ መጨበጫ ስነ ሥርዓት የለውም። እናም በዚህ ወይንም በዚያ የሚለው መንገድ አይሠራም። ራሱ የገነባቸውን ሕጎች የሚያፈርስ መንግሥት፤ ለማናቸውም የሕዝቡ አቤቱታ ፈቱን ሠጥቶ ያስተናግደዋል የሚል፤ ራሱን መመርመር አለበት። የራሱን ሕጎች በማፍረሱ፤ ሕጎችን ማፍረስ ትክክል ነው! እያለ እኮ ነው። ሕዝቡ ለምን የሱን ሕጎች መከተልና ማከበር ይገደዳል? ይህ መንግሥት በምንም መንገድ ሥልጣኑን ወዶ አይለቅም።
አንዶንዶች በውጭ መንግሥታት ተገፍቶ ትክክለኛ ምርጫ ያደርጋል ብለው ያምናሉ። የውጭ መንግሥታት እኮ የቆሙት ለራሳቸው ጥቅም ብቻ ነው። ለኢትዮጵያዊያን የተመሠረተና የቆመ የውጭ መንግሥት የለም። ወራሪው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ሎሌያቸው ሆኖ፤ የነሱን ጥቅም እስካስጠበቀላቸው ድረስ፤ በምንም መንገድ እንዲወግድባቸው አይፈልጉም። እኛኮ ዳር ደንበራችንን እናስከብራለን፣ ለሙን የሀገራችን መሬት ለራሳችን አራሾችና የመሬቱ ባለቤቶች እናስመልሳለን፣ ይህ ወራሪ መንግሥት ያለእውቅናው ያደረጋቸውን ሀገር የማስገንጠል፤ ወደብ የማሳጣት፣ የአባይን ዕድል በሌሎች እጅ የማስገባትና የመሳሰሉትን ዓለም አቀፍ ውሎች ልናፈርስ የተነሳን ነን! ኢትዮጵያን ለኢትዮጵያዊያን ብለን የተነሳን ነን! እንዴት ብለው እኛን ይደግፉ? ወይንስ የዋህነት ውጦናል? ስለዚህ፤ ለውጭ መንግሥታት አቤቱታ ማቅረባችንን ትተን፤ በአንድነት በመሰባሰብ፤ ጠንካራ ሆነን በመገኘት፤ ወደኛ እንዲመጡና እንዲለምኑን እናደርግ።
አንዳንዶች ዴሞክራሲያዊ አሠራር ሊከተል ይችል ይሆናል ብለው ያምናሉ። ከእባብ እንቁላል እርግብ እንዲፈለፈል እንጠብቃለን ወይ? ምንነቱና የሕልውናው ምሰሶ የሆነውን ፀረ-ኢትዮጵያዊነት እንዴት አድርጎ ይገፈዋል? ምኞት ጥሩ ነው። ምኞት ገሃድ ሆኖ በራሱ ይቆማል ብሎ መጠበቅ ግን የዋኅነት ነው። ወራሪው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር በምንም ተዓምር ዴሞክራሲያዊ አሠራርን ይጎራበታል ማለት ቅዠት ነው። በታሪኩም ሆነ ዛሬ፤ በዛሬው ዕለት በሚያደርገው ተግባር፤ ዴሞክራሲያዊነትን ከአጥሩ ወዲያ በጎሪጥ በጠላትነት የሚያይ ነው። የአዲስ አበባን መሬት እንዳሻው ከሕዝቡ እየነጠቀ ለራሱ ጄኔራሎችና ደጋፊዎች የሠጠ ድርጅት፤ ምን ይከተላል ብሎ ነው ዴሞክራሲያዊ አሠራርን የሚቀበል? ዴሞክራሲን ሊማረውም የማይችለው ጉዳይ ስለሆነ፤ በፀረ-ዴሞክራሲያነቱ እንደዳቆነ በዚያው ቀስሶ ይቀበርበት።
ለ) ይህን ትግል፤ ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው ለስኬት የሚያበቃው።
የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመከፋፈልና ይሄንን ክፍፍል ዘለዓለማዊ ለማድረግ፤ የወራሪው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ያልፈነቀለው ደንጋይ፤ ያልገባበት ጉድጓድ የለም። የዚህ ፀረ-ኢትዮጵያ ቡድን እምነቱ፤ “ደጋግሜ ካሰቃየኋቸውና ጊዜ ከወሰደ፤ የኔ ፍላጎትና ተግባር ዘለዓለማዊ ሆኖ ይቀመጣል።” ነው። “ኢትዮጵያዊነትን አጥብቀው የሚሟገቱለትን ግለሰቦች በማሰቃየትና ኢትዮጵያዊነትን የሚያጠብቁ ድርጅቶችን መፈናፈኛ በማሣጣት፤ ደፍረው ወደ ኢትዮጵያዊነት የሚመጡትን ቁጥራቸውን እቀንስና፤ ያለትክ የሚያልፉት ሲያልቁ፤ ለኢትዮጵያዊነት ቋሚ አይኖርም።” ብሎ ነው። ይህ መንግሥት ምንም ዓይነት ጠንካራ እምነት በዚህ ላይ ቢኖረውም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢትዮጵያዊነቱን በነጠላው ጫፍ ቋጥሮ የያዛት ዕቃ ሳትሆን፤ በልቡ ውስጥ ያለ የደሙ ቀለም፣ የእምነቱ ማሠሪያ ስለሆነ፤ ሕዝቡ ኢትዮጵያዊነቱን ይዞ፤ ኢትዮጵያዊነት ደግሞ ሕዝቡን ይዞ ይኖራሉ። የሚጠፋው፤ ጊዜ ያበቀለው የወራሪው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ከነመንግሥቱ ነው።
አሁን በሀገራችን በኢትዮጵያ ያለው የወራሪና የተወራሪ ግዛት ነው። ይህ የዴሞክራሲ ጥያቄ አይደለም። ይህ እኔ በዚህ ተበድያለሁ ብሎ የራስን በደል የሚቆጥሩበት አይደለም። ይህ ርስ በርስ የምንወዳደርበት የቁንጅና ምርጫ ዝግጅት አይደለም። ይህ የወገን ደራሽ የሀገር አዳኝ ትግል ነው። ይህ ትግል እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊና እያንዳንዷን ኢትዮጵያዊት በአንድነት የሚያሰልፍ ትግል ነው። እናም ኢትዮጵያዊነት ነው። ስለዚህ ትግሉ ለድል የሚበቃው መላ ኢትዮጵያዊያን የኔ ብለን አብረን ስንነሳ ነው። ለዚህ ደግሞ የሁላችን ፍላጎትና እምነት የያዘ የትግል ራዕይ መቀመር አለበት። ባሁኑ ሰዓት ይህ ራዕይ አራት የትግሉ ዕሴቶችን ያካተተ ይሆናል።
አንደኛ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ መሆኑንና ሉዓላዊነቱን መቀበል ነው።
ሁለተኛ፤ የኢትዮጵያን አንድ ሀገር እና አንድ ብሔር መሆን መቀበል ነው።
ሶስተኛ፤ የየአንዳንዱ/ዷ/ን ኢትዮጵያዊ/ት/ የግለሰብ ዴሞክራሲያዊ መብት መከበር መቀበል ነው።
አራተኛ፤ በሀገራችን በኢትዮጵያ የሕግ የበላይነትን መስፈን መቀበል ነው።
እኒህ ናቸው ሁላችን የምንጋራቸው አሁን የኢትዮጵያ መታገያ ዕሴቶቻችን።
ሐ) ይህ ትግል በአንድ ማዕከል መመራት አለበት።
አሁን በፊታችን የተዘረጋው አንድ ትግል ነው። አሁን ሀገራችን ኢትዮጵያን ወጥሮ የያዛት፤ ወራሪው መንግሥት በሕዝቡ ላይ የሚያደርገው በደል ነው። በዚህ በደል የሚማቅቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በትግል ላይ ነው። ይህ ትግል በኢትዮጵያ ሕዝብና በወራሪው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት መካከል ያለ ትንቅንቅ ነው። ትግሉ፤ ሕዝቡ ነፃ ለመውጣት፤ ወራሪው የፈለገውን በሕዝቡና በሀገሩ፣ በሕዝቡ ነፃነትና በሕዝቡ እምነት ላይ የሚያላግጥበትን ሁኔታ ለመቀጠል፤ እያደርጉ ያሉት ግብግብ ነው። ስለዚህ ያለው የትግል ሠፈር፤ ሁለት ብቻ ነው። አንዱ የወራሪው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ሠፈር ሲሆን፤ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሠፈር ነው። እናም ትግሉ አንድና አንድ አጥር ብቻ ነው ያለው። የሚቻለው አንድም ከአጥሩ ወዲህ ሆኖ ከሕዝቡ ጋር መቆም ነው፤ አለያም ከአጥሩ ወዲያ ሆኖ ከወራሪው ጋር መቆም ነው።
ይህ በግልፅ የሚያሳየው የዚህ የወራሪ መንግሥት ጠላትና ድራሹን አጥፊ፤ ኢትዮጵያዊነት ብቻ መሆኑን ነው። ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሣሪያ ነው። ለዚህ የሚያስፈልገው ደግሞ አንድ ማዕከል ነው። ኢትዮጵያዊ ማዕከል። የትግሉ ማጠንጠኛ በሆነው ኢትዮጵያዊነት ዙሪያ አንድ ማዕከል ማበጀት ነው። ይህ ሕዝባዊ ንቅናቄ ብቻ ነው፤ ሕዝቡን ለድል የሚያበቃው። ይህ ማዕከል ነው ትግሉን መምራት ያለበት።
መ) ይህ ትግል የኢትዮጵያ ሕዝብ ንቅናቄ ነው።
የትግሬዎችን ነፃ አውጪ ግንባር ለማጥፋት፤ ድርጅት መመሥረትና መታገሉ አንድ ነገር ነው። መዋቅርና በዚህና በዚያ ማስፋፋቱ አንድ ነገር ነው። ቆም ብሎ፤ እያንዳንዱ የድርጅት አባል፤ ድርጅታችን ከተመሠረተ አንስቶ ምን ሠራን? ከጀመርንበት ነጥብ እስካሁን ምን ያህል ፎቀቅ አልን? ተሳክቶልናል? ወይንስ አልተሳካልንም? አደግን? ወይንስ ደከምን? የዚህ ሂደት ዕድገታችን መመዘኛው ምንድን ነው? ባገኘነው ስኬትስ ጠግበናል ወይ? እያልን መለካት አለብን። በዚህ ምርምራችን ደስተኞች ከሆን መቀጠሉ ተገቢ ነው። ካልተደሰትን ደግሞ፤ አንድም ድርጅቶቻችንን መቀየር አለያም ግባችንን መቀየር ይኖርብናል። አለያ ትግሉን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ተዘጋጅተናል ድርጅታችንም ጌጣችን ነው፤ ማለት ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ጊዜም በሚደርስበት በደል አንገቱን ደፍቶ አልተቀመጠም። በየወቅቱ በደሉን በመቃወም የተለያዩ ትግሎችን አድርጓል። ከነመንግሥቱ፣ ግርማሜ ንዋይና ወርቅነህ ገበየሁ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ጀምሮ፤ በተማሪዎች እንቅስቃሴ፤ በየክፍለ ሀገሮች የገበሬዎች መነሳሳትና በየካቲት ፷ ፮ቱ የታየው ሕዝባዊ እምቢታ የዚህ ምስከር ነው። በየጊዜው የተደረጉት መነሳሳቶች በተለያዩ ምክንያቶች ለስኬት አልበቁም። ይኼንን መርምረን ትምህርት መውሰድ አለብን። ሀገራዊ ውይይቶች የተደረጉባቸው ሀገራዊ ጉዳዮች ያማረ ውጤት ያስከትላሉ። ይሄን ለማድረግ ግን ጥረቶች አልታዩም። ለምን?
አሁንም ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች አሉ። ችግራቸው ምንድን ነው? ብለን አልጠየቅንም። ለምን? ለምሳሌ፤ የእስልምና ተከታይ ወገኖቻችን ለረጅም ጊዜ እየታጋሉ ነው። ይህ እንቅስቃሴያቸው በአብዛኛው የሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ ተቀባይነት አለው። ታዲያ ለምን ግቡን አልመታም? በተጨማሪ፤ በኤርትራ የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴ እናደርጋለን ብለው የተነሱ ብዙ አሉ። እኒህም ለረጅም ጊዜ መግለጫዎችን ሲያወጡ ስምተናል። ለምን ከፍተኛ ደረጃ ላይ አልደረሱም? እንቀጥል። በውጭ ሀገር ያለን ኢትዮጵያዊያን ነፃነት፣ ጊዜ፣ ንብረት፣ ሀገር ወዳድነት፣ ለወገን ተቆርቋሪነት ሞልቶናል። ታዲያ ለምን በአንድነት ተሰልፈን አልተነሳንም? ልጨምርበት። በሀገር ቤት የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች አሉ። ለምን እንቅስቃሴያቸው ወደፊት አልተራመደም? በማዕከላዊነት ደግሞ፤ የየድርጅቶቹ መሪዎችና የትግሉ ልሂቃን፤ ለምን ይሄን ማድረግ እንዳልቻልን ጥናት አድርገን መፍትሔ ለምን አላቀረብም? ይሄ በተደጋጋሚ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው።
ለዚህ ሁሉ ጥያቄ መልስ የግድ መኖር አለበት። እንግዲህ ሁሉም በያሉበት ያነሱት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄዎችን ነው። አንዱ ከሌላው የሚለየው፤ በራሳቸው ዙሪያ ብቻ ያለው ላይ ማተኮራቸው ነው። ቁም ነገሩ ግን የያዳንዳቸው ጥያቄዎች የሁሉም ጥያቄዎች ናቸው። የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የጠየቁት የመብት ጥያቄ ነው። መምህራንና ተማሪዎች የጠየቁት ይኼኑ ነው። ነጋዴዎች የጠየቁት መብትና እኩልነትን ነው። ይህ የሁሉም ጥያቄ ነው። ቤት ተከራዮችና ቤት ለመሥራት የተዘጋጁት የጠየቁት መብታቸውን ነው። ይሄ የሁሉ ጥያቄ ነው። በደቡብ የተፈናቀሉት ኢትዮጵያዊያንና በኦጋዴን የሚሰቃዩት ኢትዮጵያዊያን የጠየቁት ኢትዮጵያዊ መብታቸውን ነው። ይህ የሁሉ ጥያቄ ነው። ስለዚህ የጎደለው እኒህን ጥያቄዎች በማያያዝ የሁሉም ማድረግና ሁሉም በአንድ ላይ የሚነሱበትን ማዘጋጀቱ ነው። ሁሉም የመብት፣ የነፃነት፣ የሕግ፣ የእኩልነት ጥያቄዎችን ነው ያነሷቸው። ሁሉም የሁሉም ጥያቄዎች ናቸው። ስለዚህ ሁሉም በአንድ ላይ ሁሉንም ማንገብ ያለባቸው ጥያቄዎች ናቸው። የድርጅት ሚና ይሄን ማድረግ ነው። ድርጅት የራሱን መርኀ-ግብር ብቻ አንግቦ ለራሱ ሥልጣን ማግኛ መንገድ ማስላት ሲይዝ፤ ፉክክር ይነግሳል። በርግጥ ነግሷል። እናም ቁጥር ለማብዣ ያለው እሽቅድድም፤ ዋናው ቁም ነገር ሆኗል። ከዚህ መውጣት አለብን። ይህ ትግል የኢትዮጵያ ሕዝብ መነሳሳት ነው። የሕዝቡ ንቅናቄ ነው።
ሠ) ይህ ትግል የሰላም ትግል ነው።
አሁን ያለንበትን የደበዘዘ የትግል እንቅስቃሴ ሕይወት ሠጥተን ወደፊት ለመጓዝ፤ ማመንና መከተል ያለበን የትግል ቅደም ተከተል ዝርዝር፤ በግልፅ መስፈር አለበት። ነፃነት የመጀመሪያው ነው። ወራሪውን፤ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ማስወገድ አለብን። የተለያዩ ክፍሎች በተለያየ መንገድ በትግሉ ተጠምደዋል። የተለያዩ ድርጅቶች በመድረኩ ተጋግረዋል። በትጥቅ ትግል ላይ “ተሰማርተናል” የሚሉም አሉ። እንግዲህ ማን ከማን ጋር እንደሚታገልና ድሉ በምን እንደሚተረጎም ግራ የተጋባበት ሀቅ በመካከላችን ሰፍኗል። ይህ ትግል ወራሪውን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ማስወገድ ብቻ ሳይሆን፤ ከዚያ ቀጥሎ ለሚመጣው ሥርዓትም ጭምር ነው። ወራሪውን ማስወገድ ብቻ የትግሉ ዋና ማውጠንጠኛ ማድረግ አጓጉል ነው። ከዚያ ቀጥሎ የሚመጣው ሥርዓትም በእኩል ደረጃ መቀመጥ አለበት። አንድን ትግል በሌላ ትግል የመተካት አባዜ በሺታ ነው። ይህ ለኔ ብቻ ብለው በራሳቸው ድርጅት ተጎናንፈው የተቀመጡ ክፍሎች አጀንዳ ነው። ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ አጀንዳ አይደለም። ስለዚህ የዚህ ትግል ባለጉዳዮች መላ ኢትዮጵያዊያን ነን። እናም ትግሉ አሁን ባለበት ደረጃ፤ ሰላማዊ ነው። የትግሉን ተሳታፊዎች መሰባሰብ እና አንድነትን መፍጠር፤ ዋና የቅድሚያ ተግባሩ ነው። ሕዝቡ የትግሉ ባለቤት ነው፣ ሕዝቡ ሉዓላዊነቱ መጠበቅ አለበት፣ ሕዝቡ ትግሉን ይምራ ስንል፤ በአንድነት ሆነን ትግሉን ሁላችን እንቀላቀልበትና የሕዝቡን መብት እናስከብር ማለት ነው። “የኔ ድርጅት ሲያቸንፍ መብቱን ለሕዝቡ እሠጣለሁ።” የሚለው የቁጮ አባባል፤ ትናንት አልፎበታል። የዛሬ ሰዎች ነን። የዚህ ትርጉም፤ በቀጥታ ሲቀመጥ፤ “እኔ ገዥ መሆን እፈልጋለሁን በኔ ሥር ሆናችሁ እኔን ለማንገሥ ታገሉ።” ማለት ነው።
ረ) አወቃቀሩ የተሣሣተው የድርጅቶች መንገድ መሰረዝ አለበት፤
አዎ! ሳይደራጁ ትግል የለም። ጣሊያን ፋሽስቱን የተጋተሩት ጀግኖች አርበኞቻችን፤ በየጎጡና በየመሪያቸው ከመንደር እስከወረዳ፣ ከወረዳ እስከ አውራጃ፣ ከአውራጃ እስከ ንጉሣቸውና ከንጉሣቸው እስከ ንጉሠ ነገሥታቸው ባንድ ሀገር፤ ባንድ መንግሥት ስም ተደራጅተው ነው። በየግሉ የሚደረግ እንቅስቃሴ ለድል አያበቃም። ከራሳችን ከዚህ ታሪክ የምንወስደው ትምህርት፤ ድርጅት ለወቅታዊ ጥያቄው መልስ የሚሆን መሣሪያ ነው። አሁን ደግሞ የሚያስፈልገን መሣሪያ፤ መላ ኢትዮጵያዊያንን በኢትዮጵያዊነት አሰብስቦ፤ በወራሪው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ላይ የሚያስነሣና፤ ለድል አብቅቶ የሽግግር መንግሥት የሚያቋቁም ነው። ይህ የሀገር ነፃነትን ለማስገኘት የሚደረግ መደራጀት ነው። ይህ መደራጀት የሚያስከትለው የሽግግር መንግሥት፤ ሕገ መንግሥት ተረቆ የሚጸድቅበት፤ ሕገወጥ በሆነ መንገድ የተደረጉት የወራሪው መንግሥት ዓለም አቀፍም ሆነ የሀገር ውስጥ ውሎችና ሕጎች የሚሰረዙበት፤ የፖለቲካ ድርጅቶች ምዝገባ ተደርጎ፤ እኒህ ድርጅቶች የሚወዳደሩበትና ተቀባይነት የሚያገኘው ወገን ሥልጣኑን የሚያስረክብበት ወቅት ነው።
ለዚህ ሂደት የሚያስፈልገን ኢትዮጵያዊ የሆነ አንድ ሕዝባዊ የነፃነት ንቅናቄ ነው። ይህ ንቅናቄ ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ ክፍት ነው። “ጉዳዬ ነው” ያለ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በግሉ ገብቶ የሚሳተፍበት ንቅናቄ ነው። መደራጀት ለሆነ ተግባር የሚደረግ የሰዎች መሰባሰብ ነው። አሁን በኢትዮጵያ የትግል ምኅዳር፤ ለዚህ ንቅናቄ ተወዳዳሪ ሌላ ድርጅት አይኖርም። ያሁኑ ሰዓት መደራጀት ሀገርን ነፃ አውጥቶ የሕዝቡን የበላይነት ለማስከበር ብቻ ካልሆነ፤ ኢትዮጵያዊም ሕዝባዊም አይደለም። ከዚህ ይልቅ የራሴን ድርጅት ነው የማጠናክረው ብሎ የሚሯሯጥ ድርጅት፤ ከወራሪው የትግሬዎች ነፃ ወጪ ግንባር የተለዬ አጀንዳ የለውም። አሁን ቅድሚያ ቦታ ያዥነት ኖሮኝ፤ ሌሎችን ዘግይተው ሲመጡ አቸንፋለሁ የሚል ድርጅት፤ ከመርኀ ግብሩና ከቆመለት ዓላማ ይልቅ ብልጣ ብልጥነትን የተካነ፤ ድርጅቱን ከሀገሩ ያስቀደመ፤ ግለኛ ድርጅት ነው። ይህ የሕዝብ ወገን አይደለም። ይህ ኢትዮጵያዊ አይደለም። እናም ይኼን የኢትዮጵያ ሕዝብ የነፃነት ንቅናቄ በአንድነት እንመሥርተው። ሃሳብ ላለው በ eske.meche@yahoo.com እገኛለሁ።