ከሙስሊም ወገኖቻችን ጎን እንቁም። እናውግዝ፣ ከሙስሊም ወገኖቻችን ጎን እንቁም።
የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች፣ በየትኛውም አለም ክፍል፣ የኢድ አል ፈጢር በአል በደስታ አክብረው ሲውሉ፤ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ብቻ በአገራቸው መንግስት ተብዬ ሲዋከቡና ሲሸበሩ ውለዋል። በብዙ የኢትዮጵያ ከተሞች፣
በተለይ ባዲስ አበባ፣ የኢድ አል ፈጢር በአሉን ለማከበር የተሰበሰበውን ሕዝበ-ሙስሊም፣ ፖሊስ በዱላና በጠመንጃ ባካሄደው ሺብር፣ ህፃንና ነፍሰጡር ጨምሮ ህይወት ማለፉ፣ ብዙ ሰው መቁሰሉና ቁጥሩ ከግምት በላይ የሆነ ሕዝብ መታሰሩ በሰፊው ተነግሯል።
ይህ በኢድ አል ፈጢር ክብረ-በአል ወቅት የተካሄደው ሺብር፤ ወያኔ/ኢህአዴግ ከአንደ አመት ተኩል በላይ የቀጠለውን፣ ”ድምፃችን ይሰማ፣ መብታችን ይከበር”oበማለት ሙስሊሙ ህብረተሰብ የሚያካሂደውን ሰላማዊ ትግል ለማፈን በተለያዩ ወቅቶችና በተለያዩ ቦታዎች ሲያካሂደው የኖረው ሺብር አነዱ አካል ነው። ከኢድ አል ፈጢር ክብረ-በአል ሁለት ቀን ቀድሞ፣ በኮፈሌ ወረዳ (አርሲ) የተካሄደው ጪፍጨፋ የቅርብ ምሳሌ ነው።
ወያኔ/ኢህአዴግ የኢትዮጵያን ሕዝብ በቁጥጥሩ ዉስጥ አስገብቶ እንደፈለገው ሲያመሳቅል ከ20አመት በላይ ያለምንም ተጋፊ ሃይል ቢቆይም፤ ለቀጣዩ እድሜው ተፃራሪ ሃይል እንዳይነሳበት፣ ለማንኛውም ድርጅት፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ፣ የሙያ፣ የሃይማኖት ወዘተ፣ ”ምስል-ጥጃ”oበማበጀት ሃቀኛ ድርጅቶችን ሲያኮላሺ ኖሯል። እስካሁን ድረስ ቀጣይና ጠንካራ ተቃዉሞ ያጋጠመው ከሙስሊም ኢይዮጵያዊያን ብቻ በመሆኑ፣ በህዝበ-ሙስሊሙ ላይ እዬከፋ የመጣ ሺብር ቀጥሏል።
በዚህ የሺብር ዘመን፣ ሆዳቸውን ወድደው ነፍስ የማትፋት ትዛዝ የሚፈጽሙትንና በተሰጣቸው ስልጣን በመመካት ህዝብ የሚያሸብሩ ግለሰቦችን በወቅቱ ፍርድ ላይ ማቅረብ አይቻልም። ዘመኑ ”አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ”oእንደሚባለው
ነውና። ነፍስ አስገዳዩ የወያኔ/ኢህአዴግ ሥርዓት፣ ፍርድ ሰጪም የወያኔ/ኢህአዴግ ሥርዓት በመሆኑ ነፍሰ-ገዳዮች በነፃ ይኖራሉ። ይሁንና የአገራቸው ጉዳይ የሚያስጨንቃቸው ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ሁሉ በነፍስ ግዳይ መጠየቅ ያለባቸውን ግለሰቦች፤ ቀን የወጣ እለት ለፍርድ የሚቀርቡበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይኖርባቸዎል።
የህዝበ-ሙስሊሙ ’’ድምፃጭን ይሰማ፣ መብታችን ይከበር”oጥያቄ ህዝባዊ ጥያቄ እንደ መሆኑ መጠን የሁላችንም ጥያቄ ነው። ስለሆነም የወያኔኢህአዴግን የሺብር ተግባር ከማውገዝ ባሻገር ከሙስሊም ወገኖቻችን ጎን መሰለፍ ግዴታችን
መሆን አለበት።
ህዝባዊ ትግል ይፋፋም፣
ዴሞክራሲ ይስፋፋ፣ አንድነት ይጠንክር፣
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር።
መኢሶን
ነሃሴ 3 ቀን 2005 ዓ ም