የጅዳ ቆንስል መስሪያ ቤት ኋላፊ ቆንስል ጀኔራል አቶ ዘነበ ከበደ ከኃላፊነታቸው ተነሱ !
* ትናንት ረፋዱ ላይ በገደምዳሜ “ጉልቻ ቢቀያየር …” ብለን ያንሹካሾክነው መረጃ ተረጋገጠ !
* ለጊዜው ቆንስል ጀኔራሉን ተክተው በጊዜያዊነት ቆንስል መስሪያ ቤቱን ለቀጣይ ሁለት ወራት የሚያስተዳድሩት በቆራጥ አመራራር ብቃታቸው የማይመሰገኑት ቆንስል ሸሪፍ ከይሩ ናቸውም ተብሏል ።
* ቆንስል ጀኔራል አቶ ዘነበ ከበደ ትናነት ምሽት ጉዳዩን ለማሳወቅ የኢህአዴግ ድርጅት አባላት ስብሰባ ጠርተው እንደነበርና አብዛኛው አለመገኘታቸው ታውቋል። ድርጅት አባላት በተለይም ከጎናቸው የማይጠፉ የነበሩት ተጽዕኖ ፈጣሪ የህወሃት አባላት እንኳ አልተገኙም ተብሏል።
* አቶ ዘነበ ከበደ በቆንስሉ ዙሪያ የህወሃት አባላትን አምባገነንነትን በማውረድና በማቀዝቀዝ ፣ በሙስና ፣ በድለላ ፣ በማጭበርበር ስራ በቆንስሉ ዙሪያ የነበሩትን በማጥፋት እና በሌብነት አካባቢውን በማጽዳት ይታወቃሉ።
* ህግ አዋቂ ሆነው በህግ ማዕቀፍ የመጡ ዜጎች ግፍ ሲፈጸምባቸው በመከላከሉ የረባ ስራ አልሰሩም የምላች ሃላፊው ስልጣን ከተረከቡ ወዲህ ሶስት ከባባድ የህዝብ ማዕበል የተነሳባቸውን ፈተናዎች በጽናትና በቆራጥ አመራራቸው ድል ነስተው ማለፋቸውን አውቃለሁ። ሃላፊው በአንጻሩ በመረጃ ልውውጥ የማያምኑ ፍትሃዊ በመሆኑ ሳይሆን በግላቸው ላመኑበት ጉዳይ ግንባራቸውን የሚሰጡ ኋላፊ ነበሩ ።
* አቶ ዘነበ ከበደ በሳውዲ ከፍተኛ ሃላፊዎች ዘንድ ክብር የሚሰጣቸው በአማርኛም ሲናገሩ ወጋቸውን ለማስረዳት ተረት የሚያበዙ ፣ ከዚህ በፊት ከነበሩት ኃላፊዎች እንግሊዝኛ አቀላጥፈው የሚናገሩ አንደበተ ርቱዕ ግርማ ሞገስ ያላቸው ፣ በአለባበሳቸው ጸዳ ያሉ ትክክለኛ የአንድ ሃገር ዲፕሎማት ክብርን የተጎናጸፉ ኃላፊ ነበሩ ።
* ከግማሽ ሚሊዮን የማያንሱ ኢትዮጵያውያን የኮንትራት ሰራተኞች ባለፉት ሶስትና አራት አመታት የገቡ ሲሆነ ኮንትራት ሰራተኞች ስለመጡበት ውል አቶ ዘነበ በጀርመን ራዲዮ ውይይት ፕሮግራም ተጠይቀው በኢትዮጵያና በሳውዲ በመንግስት መካከል የሁለትዮሽ የስራተኛ ልውውጥ ስምምነት አንደሌለ በግላጭ የነገሩን ኀላፊም ናቸው ።
* አቶ ዘነበ ከበደ ከዚህ በፊት በቆንስሉ ውስጥ የነበረውን የበከተ ቢሮክራሲና ኢ ፍትሃዊ አመራር በአደባባይ የተናገሩ ደፋርም ናቸው። ነዋሪው በግዳጅ ምንም የገንዘብ መዋጮ ሲጠይቁ ያልተሰሙ ፣ ኮሚኒቲው ያልሆነ ምንገድ ሲሄድ እንደ በላይ ጠባቂነት ኢ ፍትሃዊ አካሔዱን እያዩ ሲያልፉም ታይተዋል። ለዚህ ተጠቃሹ ትምህርት ቤቱ በኮሚኒቲው ለከፋ አደጋ ሲዎድቅ የተመለከቱበት አካሔድ ሲሆን በመጨረሻው ሰአት ገብተው 120 ሽህ የሳውዲ ሪያል ከዝርፊያ አዳንኩ ብለው ቢነግሩንም ዛሬ ድረስ የ3000 ታዳጊዎችና የ200 መምህራንና ሰራተኞች ያቀፈው መመኪያችን በጅዳ የኢትዮጵያውያን አለም አቀፍ ትምህርት ቤቱን ከአደጋ አላወጡትም ። ያም ሆኖ ለትምህርት ቤቱ የተዝረከረከ አሰራር ምክንያትየየተባሉ አንዳንድ መሰረታዊ ለውጦችን ግን በቅርብ ተንቀሳቅሰው አምጥተዋል!
* አቶ ዘነበ ከበደ እንደርሳቸው ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ እንደ እርሳቸው ከስልጣን የተነሱትን አምባሳደር መርዋንን እና 12 አመት የጅዳን ቆንስል አንቀጥቅጠው የመሩት የህወሃት ከፍተኛ ሰው አምባሳደር ተክለ አብ ከበደን አስተዳደር ብልሹ አካሔድ ብቻ ሳይሆን የቆንስሉን ሰራተኞች በአደባባይ መመንቀፋቸው በኢህአዴግ የድርጅት አባላትና በሰራተኞች ዘንድ የተፈሩ ሲያደርጋቸው ለዛሬ ከስልጣናቸው መነሳትም የህወሃት አባላት ተጽዕኖ እንዳለበት ራሳቸው ህወሃቶች እየነገሩን ነው። ትናንት አንባሳደር መርዋንን ከስልጣን በማስነሳቱ ረዥም እጅ የነበራቸው ህዎሃትን ጨምሮ የተቀሩት የኢህአዲግ አባል ድርጅቶች ዛሬም በውጭ ጉዳ ከፍተኛ ሃላፊዎች ተጽዕኖ ፈጣሪነት በገሃድ ማሳያው ቀድምው የነገሩን እየደረሰ ማየት መጀመራችን ነው ! ዛሬም ማን ሊመጣ የሚችለው ሃላፊ የዲፕሎማሲያዊ እና የአስተዳደር ብቃት ሳይሆን አነጣጥሮ ተኳሽነቱና የዋለበትን የጦር አውድማ ድረስ በአድናቆት የህወሃት ካድሬዎች ይነግሩን ጀምረዋል።
መዝጊያ …
ለመዝጊያ ፣ ለመደምደሚያ ያህል ትናንት መረጃው ከምጣዱ እንደ ወጣ ስሰማ ያጫወጥኳችሁ አጭር ገደምዳሜ ወግ መዝጊያ መደምደምደሚያ ላድርግ …
ጉልቻ ቢቀያየር …
ከረፋድ እስከ ቀትር ( ትናንት ማክሰኞ መሆኑ ነው) አንዱ መረጃ ከተለያየ አቅጣጫ እዚህም እዚያም ደረሰኝ ፣ በሹክሹክታ ስሰማው የሰነበትኩትን መረጃ እውነትነት ለማረጋገጥ ቢገደኝም የጭምጭምታውን አንድምታ ለማጣራት መሞከሬ አልቀረም። ብዙ ጣርኩ ግን ከመንግስት የቀረቡት ምንጮቸ እያወቁ “አናውቁም ” ያሉኝ ! ወደው ሳይሆን የእንጀራ ነገር ሆኖባቸው እንጅ አዲስ ነገር እንዳለ በከባቢው የሚታየው ድባብ ያሳብቃል … ይህን እያሰብኩ እያለሁ አንድ የማለዳ ወግ ርዕስ ከአፊ ገባ ” ሳያልቅ የተጠናቀቀው ዘመቻና አልረጋ ያለው የጅዳ ቆንስል ወንበር … ” ብየ ጀመርኩት … መቀጠል ግን አልቻልኩም !
በሰሞነኛው በባጀንበት የሳውዲ ኢትዮጵያውያን ክራሞት ዙሪየ የወገን እንግልት የሚያማቸው ወንድም አሉኝ። እኒሁ ከወደ ጅዳ ቆንስል መስሪያ ቤት ሁሌም መረጃ የሚያጋሩኝን ወዳጀን ” ሹም ሽር ይደረጋል !” ተበሎ ሰምተው ያልተረጋገጠውን መረጃ ሲያቀብሉኝ “ስማው ብየ እንጅ ፣ እውነት እንኳ ሆኖ ወንበር ቢቀያየር ምን ዋጋ አለው ፣ ለፖለቲካቸው የሚጠቅማቸውን እንጅ ለስደተኛው የሚፈይደውን አይልኩልን ! ” ነበር ያሉኝ … … ” ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም !” እንዲሉ …
የሚፈለገው ሁሉ ይሆናል … የሚያቆመው የለም ! ለሁሉም አንድየ የሚበጀንን ይስጠን ፣ ከሁሉም በላይ ለሃገራችን ምድር አብቅቶ በሰላም በፍቅርና በህብረት የምንኖርባት ሃገር ፣ መድልኦ የማያውቅ ፣ ሃገርና ህዝቡን የሚወድና ለዜጎቹ መብት የሚቆረቆር መንግስት ይሰጠን …ትናንት የሚፈለገው ሁሉ ይሆናል… የሚያቆመው የለም ብለን ነበር የተለያየነው ! አዎ የሚፈለገው ሁኗል ፣ ይሆናል … የሚያቆመው የለም ! …
” ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይሾማል ፣ የኢህአዴግ የድርጅት አባላትና ካድሬዎች ተጽዕኖ ፈጥረው በተናጠልና ተሰብስበው ያሽሩታል ፣ እንዲህ ተጉዘን የት እንደርስ ይሆን? ” ነበር ያሉኝ አንድ አልረጋ ያለውን የጅዳ ቆንስል ሹም ሽር ያስገረማቸው እህት …
እስኪ ቸር ያሰማን
ነቢዩ ሲራክ
የሳውዲ ጉዳይ …ሰበር የመረጃ ግብአት
በፍቅር ቀንን ለገዥዎቻችን ቀይ ካርድ
ከጌታቸው ሽፈራው
የቫላንታይን ዳይ አብዛኛው ወጣት ቀይ ይለብሳል፡፡ በዚህ ቀን ታዲያ ለምን ይህን ቀይ ምልክት እንደ ቀይ ካርድ ተጠቅመን ምልክት አናደርገውም? በዚህ ቀን ቀዩን የታሰሩትን፣ የሚበደሉትን፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ከፍቅር የነጣጠለ ስርዓት ላይ ምልክት አድርገን አንጠቀመውም?
በቅርብ አመታት ውስጥ በአገራችን ‹‹Valentine’s Day›› በተለይ በወጣቱ ዘንድ መከበር ጀምሯል፡፡ ካፌዎች፣ ሆቴሎችና ሌሎች መዝናኛዎች ቀኑን በስፋት ለገበያ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ ሆኖም አብዛኛዎቹ ወጣቶች ‹‹ፋሽኑን›› ከማሯሯጥ ያለፈ ትርጉሙን አውቀውት ነው የሚያከብሩት ለማለት ይከብዳል፡፡ የውጭ ባህል ከሆነ ባናከብረው ይመረጣል፣ ፍቅር ምን ባህልና አገር ያስፈልገዋል? ከተባለ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ብናደርገው የተሻለ ነው፡፡
ቅዱስ ቫላንታይን የታሰረበት፣ ከዛም የተገደለበት ዋነኛው ምክንያት በሮማውያን ዘመን እንዲያገቡ ያልተፈቀደላቸውን ወታደሮች አጋብቷል ተብሎ ነው፡፡ ይህ ለእኛ አገር ጠቃሚ ተምሳሌት ነው፡፡ የእምነት አባቶች ለተከታዮቻቸው ማድረግ ያለባቸውን እምነታዊ ተግባር መፈጸም ግዴታቸው ቢሆንም ከመንግስታት ጥቅም ጋር በተጋጨ ጊዜ ሲያስሩና ሲገድሉ ተስተውለዋል፡፡ ቫላንታይን የዚህ ጥቃት ሰለባ ነው፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን እሱ የሚከተለው እምነት በመንግስት ጣልቃ ገብነት ውስጥ ወድቆ ነበር፡፡ ይህ የእኛ የወቅቱ ትክክለኛ ገጠመኝ ነው፡፡
ከወራት በፊት መጅሊስ በቀበሌ ተመርጧል፡፡ በእምነታችን ጣልቃ አትግቡ ያሉት ሙስሊም ወንድሞቻችን እስር ቤት ውስጥ ታስረዋል፡፡ በእድሜ ጠገቡ የዋልድባ ገዳም የሀይማኖት አባቶች አጽም የተቀበረበት ቦታ ሳይቀር ለሸንኮራ አገዳ ማምረቻ ተከልሏል፡፡ በእምነታችን ጣልቃ አትግቡ ያሉት ሙስሊምና የማህበረ ቅዱሳን አባላት ‹‹በጽንፈኛነት›› እየተከሰሱ ነው፡፡
ቅዱስ ቫላንታይን የተከለከሉት ወታደሮቹን እንዳያጋቡ ነው፡፡ በዛን ዘመን ወታደሮቹ ትዳርን ጨምሮ በርካታ ተፈጥሯዊ መብቶቻቸውን እንዳይጠቀሙ ተከልክለው ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባለች አገር መሳሪያ ከያዙትም በላይ ለህዝብ ጥቅምና ለአገር መብት ወታደር ሆነው የሚያገልግሉት አክቲቪስቶች፣ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ እነሱ ወታደርም ብቻ ሳይሆኑ እንደ ቫላንታይን በየ መስካቸው ቄሶች ሆነው ከህዝብ ጎን የቀሙ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ህዝብ ዴሞክራሲያዊና ተፈጥሯዊ መብቱን በተነጠቀበት ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኞቻችን፣ አክቲቪስቶቻችንና ፖለቲከኞቻችን ልክ እንደ ቅዱስ ቫላንታይን እጣቸው እስር ቤት ሆኗል፡፡ በመሆኑም ይህን የ‹‹ፍቅር ቀን›› ስናከብር በርካታ መቶ አመቶችን ወደኋላ ተጉዘን ሳይሆን አሁን ቃሊቲና ቂሊንጦ፣ ማዕከላዊ እንዲሁም በየ ቦታው ታጉረው የሚገኙትን የእኛዎቹን ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች፣ የእምነት መሪዎች፣ ፖለቲከኞችና ህዝብ ብናስታውስ ምን አለበት?
ይህን ቀን ወደ ጾታ ፍቅር እናቅርበው ካልንም የውጭ ባህል፣ የውጭ ታሪክ፣ የቆየ አባባል ከምናስታውሰው ይልቅ ለእኛው ነባራዊ ሁኔታ ቅርብ ነው፡፡ መቼም አገር ሰላም ካልሆነች፣ ህዝብ በሰላምና በፍቅር ካልኖረ የፍቅር ጓደኛሞች፣ የባለ ትዳሮች…..ፍቅር ፍቅር ሊሆን አይችልም፡፡ በአገራችን ባለፉት አመታት ‹‹ብሄር›› የሚሉት መከፋፈያ ባልና ሚስት አፋትቷል፡፡ ወጣቶች ቢዋደዱ እንኳ ቤተሰቦች ‹‹ብሄሯ/ሩ ምንድን ነው?›› የሚል አስቀያሚ ጥያቄ ማንሳት ጀምረዋል፡፡ የጓደኛ፣ የዘመድ አዝማድ ምክርም ተመሳሳይ ሆኗል፡፡ በአጠቃላይ በብልሹ ፖለቲካችን፣ በከፋፋይ ፖለቲከኞቻችንና ፓርቲዎች ምክንያት ሁለት የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪዎች በፍቅር የማይኖሩበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡
ይህ ብቻ ግን አይደለም፡፡ በዚህ 23 አመት ህወሓት/ኢህአዴግ አገሩን የሚጠላ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በመወለዱ የሚያፍር፣ ‹‹ጎሳ›› እንጅ ዜግነት እንደሌለው የሚያስብ ወጣት ለመፍጠር ታትሯል፡፡ ሮማውያኑ ፖለቲከኞች ወታደሮች ትዳር እንዳይዙ እንጅ ሮማን እንዳይወዱ አላደረጉምና ከእኛው ስርዓት በእጅጉ የተሻሉ ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን አገራቸውን እንዳይወዱ አንዴ ‹‹ቅኝ ገዥ›› ሌላ ጊዜ በዝባዝና ጨቋኝ….ተብለው የፈጠራ ታሪክ ሲማሩ አድገዋል፡፡ እናም ይህን የፍቅረኞች ቀን ፍቅረኞች የተወለዱባትን፣ የሚኖሩባት ኢትዮጵያን እያሰብን፣ ስለ አገር ፍቅር እየተነጋገርን፣ አገራችንን እንድንጠላ የሚያደርጉትን ‹‹ቀይ ካርድ!›› እያሳየን ብንውል ትልቅ ቁም ነገር ይመስለኛል፡፡
እስኪ አሁን ደግሞ የፍቅርን ቀን ወደ ጥንዶች እናውርደው! ይህን ቀን ‹‹የፍቅር ቀን›› አድርጎ ለማክበር መጀመሪያ ሰላም መሆን ያስፈልጋል፡፡ ጓደኛዋ/ባሏ የታሰረባት፣ አገሩ ውስጥ ስቃት በዝቶበት የተሰደደበታ፣ ከዚህም አለፍ ሲል በእግፍ የሞተባት ወጣት ይህን ቀን ‹‹በፍቅር›› ቀንነት ልታከብረው አይቻላትም፡፡ በተመሳሳይ ቀኑ ሚስቱ/ጓደኛው ለታሰረችበት፣ ፤ተሰደደችበትና ለተገደለችበት ወጣትም ‹‹የፍቅር ቀን›› ሊሆን አይችልም፡፡ እነዚህ ወጣች የቀድሞውን ቄስ ከማስታወስ ይልቅ ስለ እውነት መስዋት የሆኑትን ጓደኞቻቸውንና ይህ መከራ የተንሰራፋባትን ኢትዮጵያን እንዲያስታውሱ ይገደዳሉ፡፡ ይህን መከራ ያደረሰውን፣ ከጓደኞቻቸው የነጠላቸውን አካል ሊያወግዙ፣ ሊቃወሙና ምልክት (ቀይ) መስጠት ሊኖርባቸው ነው፡፡
የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጓደኛና ባለቤት ባይታሰር፣ ባይሰቃይ፣ ባይሰደድና ባይሞትም ነገ እንደማይፈጠርበት እርግጠኛ ሊሆን ግን አይቻልም፡፡ ምንም ያህል በ‹‹ፍቅር ቀን›› ደስተኛ መሆን ቢቻል ነገ ወንዱ እንደ ርዕዮት ሚስቱ እንደማትታሰርበት እርግጠኛ ሊሆን አይችልም፡፡ ሴቷም ባሏ ልክ እንደ አንዱ ዓለም፣ አቡበክር፣ እስክንድር፣ በቀለ፣ ውብሸት ….ቧላ እንደማይታሰር እርግጠኛ የምትሆንበት ስርዓት የላትም፡፡ እናም በ‹‹ፍቅር ቀን›› እውነትን በመናገራቸው፣ በእምነታቸው በመጽናታቸው፣ አገራቸውን በመውደዳቸው ከባልና ሚስቶቻቸው፣ ፍቅረኞቻቸው ብቻ ሳይሆን ከልጆቻቸው ተነጥለው የዋሉትን ኢትዮጵያውያን ማስታወስ ሊኖርብን ነው፡፡ የ‹‹ፍቅር ቀን››ን ልታከብሩ ያሰባችሁ! እስኪ ፍቅረኞቻችሁንና የትዳር ጓደኞቻችሁን እነዚህ ካለ ፍትህ የታሰሩ ኢትዮጵያውያን አድርጋችሁ እሰቡ?
እውነት የቀኑ ትርጉም ከገባን፣ ስለ ፍቅር ከተጨነቅን ስለ ኢትዮጵያ፣ አገሩን እንዳይወድ፣ እርስ በእርሱ እንዲናቆር ስለተደረገው ህዝብ፣ ስለ ጋዜጠኞቻችን፣ ስለ ፖለቲከኞቻችን፣ ስለ አክቲቪስቶቻችን….ስለ እኛ ስለ ኢትዮጵያውያን እያሰብን ልናከብረው ይገባል፡፡ መከራ ፈጣሪውን ስርዓት፣ ህዝብን የሚያናቁረውን ፓርቲና ፖለቲከኞች፣ አገርን የከፋፈለውን አካል፣ ፍቅረኛና ባለትዳሮችን ያለ ፍትህ የነጣጠለው ህወሓት/ኢህአዴግ ልንወቅስ ይገባል፡፡ ቀኑን የምንወክልበትን ቀን መለዮ ሁሉ የቀይ ካድር ምልክት ልናደርገው ይገባል፡፡
የአብርሃ ደስታ የሰሞኑ ምርጥ ዘገባዎች
የህወሓት የኮብልስቶን ፖለቲካ (መቐለ)
========================
የመቐለ ወጣቶች (የዩኒቨርስቲ ምሩቃን) ተደራጅተው በኮብልስቶን ስራ ለመሳተፍ ቢወስኑም የህወሓት መንግስት ሊያስሰራቸው እንዳልቻለ ገለፁ። ወጣቶቹ በኮብልስቶን ስራ ተሰማርተው ስራ ለመፍጠርና ህይወታቸው ለመቀየር በተገባላቸው ቃል መሰረት ቢደራጁም መንግስት ግን በዝቅተኛ ዋጋ (ትርፍ የሚገኝበት ሳይሆን ለኪሳራ በሚዳርግ) እንዲሰሩ እያስገደዳቸው ይገኛል።
የኮብልስቶን ገንዘብ በእርዳታ ከዎርልድ ባንክ የሚገኝ ሲሆን የህወሓት ባለስልጣናት የኮብልስቶኑ ፕሮጀክት ተከናውኖ ለሚመለከተው አካል እንደለመዱት የዉሸት ሪፖርት ማቅረብ ይፈልጋሉ። ይህ እንዳለ ሁኖ ከዓለም ባንክ ከተገኘው ገንዘብ ከወጣቶቹ ተቀንሶ ለሐላፊዎቹ የሚተርፍበት ሁኔታም ያመቻቻሉ።
አሁን ግን አንድ ችግር ተፈጠረ። ወጣቶቹ በስራቸው ትርፍ ማግኘት ይፈልጋሉ። ወጣቶቹ ትርፍ ካገኙ ለባለስልጣናቱ የሚተርፍ ገንዘብ (የሚመዘበር ገንዘብ) አይኖርም። ባለስልጣናቱም የኮብልስቶን ገንዘቡ መመዝበር ይፈልጋሉ። የኮብልስቶን ገንዘቡ ከተመዘበረ ግን ለወጣቶቹ የሚሰጥ ገንዘብ ያንሳል። ካነሰ ደግሞ ወጣቶቹ ይከስራሉ። ወጣቶቹ ደግሞ ኪሳራውን አልፈለጉትም። እናም አሁን ከባድ ዉጥረት ነግሷል።
ባለስልጣናቱ የኮብልስቶን ተጫራቾች በትንሽ ዋጋ እንዲሰሩ ያስገድዳሉ፤ ምክንያቱም የኮብልስቶን ስራ መቋረጥ የለበትም። ምክንያቱም የዓለም ባንክ ገንዘቡ ስለሰጣቸው ስራው ተሰርቷል ብለው ሪፖርት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ገንዘብ ደግሞ ማትረፍ ይፈልጋሉ። ወጣቶቹም መክሰር አይፈልጉም። እናም ወጣቶቹ ፍቃደኞች አይደሉም። ባለስልጣናቱ ደግሞ ወጣቶቹን ባለስልጣናቱ በፈለጉት የዋጋ መጠን እንዲሰሩ ያስገድዷቸዋል።
ከዚህ አልፎ የህወሓት ባለስልጣናት የኮብልስቶን ገንዘብ ከዓለም ባንክ የተገኘው በህወሓት ትብብር ስለሆነ በኮብልስቶን ስራ የሚሰማራ ማንኛውም ወጣት የህወሓት አባል መሆን እንዳለበት ትእዛዝ አስተላልፈዋል። የህወሓት አባል መሆን ብቻ በራሱ በቂ እንዳልሆነና በኮብልስቶን ስራ ለመሰማራት ባለስልጣናቱ ባዘዙት የዋጋ መጠን መስራት እንዳለበትም አክለዋል። በተጨማሪም ወጣቶቹ የሚያገኙትን ገንዘብ በደደቢት ማይክሮፋይናንስ (የህወሓት ነው) ማስቀመጥ እንዳለባቸው ተነግሯቸዋል።
ወጣቶቹን እንዲሰሩ ማስገደድ ምን አመጣው? የሚያዋጣቸው ቢዝነስ ከሆነኮ በፍቃዳቸው ይሰራሉ? በዓለም ባንክ ገንዘብስ ለምን የፓርቲ አባል እንዲሆኑ ይገደዳሉ? የዓለም ባንክ ገንዘብ የሰጠው ለህወሓት አባላት ብቻ ነው እንዴ? ወጣቶቹ ፍቃደኛ ሳይሆኑ ሲቀሩስ ለምን ማስፈራርያና ማስጠንቀቅያ ይሰጣቸዋል? ሐሳባቸው የመግለፅ መብት የላቸውም እንዴ?
እስከመቼ ነው በህወሓት የባርነት ቀንበር ስራ የምንኖረው? የህወሓት የአገዛዝ ስትራተጂ ከ”ከፋፍለህ ግዛ” ወደ “አስርበህ ግዛ” የተሸጋገረበት አጋጣሚ ነው ያለው። ህዝብ በሆዱ ተይዟል። ከተቃወመ የሚበላና የሚሰራ ያሳጡታል። በህወሓት አገዛዝ የወደቅንበት ምክንያት ድሆች ስለሆንን ነው። ህይወታችን በህወሓቶች (የመንግስት) እርዳታ ስለተጠለጠለ ነው። መቃወምን የሚያስፈራን ሆዳችን አቅፈን ስለምንኖር ነው።
ግን እስከመቼ? ከተባበርን ህወሓትን ከስልጣን ማውረድ እንችላለን። ከስልጣን ካወረድነው ደግሞ ነፃነታችን እናገኛለን። ነፃነታችን ካስመለስን የስራ ዕድል ይከፈትልናል። የስራ ዕድል ከተከፈተልን በልተን በሀገራችን በነፃነት መኖር እንችላለን።
__________________________________________________________________________________________
የመንግስት ጣልቃ ገብነት በሀይማኖት: የስብሃት ነጋ ምስክርነት
==========================
በሀይማኖት ጣልቃ ገብነት ጉዳይ በኢትዮጵያ ሙስሊም ማሕበረሰብና በኢህአዴግ መንግስት መካከል አለመግባባት መስፈኑ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መንግስት በሀይማኖታቸው ጣልቃ መግባቱ እንዲያቆም ሲጠይቁ መንግስትም የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ማሳሰሩ ይታወሳል። (ኮሚቴዎችን በማሳሰር የህዝብን ጥያቄዎች ማዳፈን ይቻል እንደሆነ እንጂ መመለስ ግን አይቻልም)።
መንግስት በሀይማኖት ጣልቃ የሚገባው በተለያዩ መንገዶች ሊሆን ይችላል። አንዱና ዋነኛው ግን የሀይማኖት መሪዎችን በመደለል የፖለቲካ መሳርያ እንዲሆኑ ማድረግና የፖለቲካ ካድሬዎች የሀይማኖት መሪዎች አድርጎ መሾም ነው።
የፖለቲካ ሹመት (ካድሬነትና አገልጋይነት) ሌላ የሀይማኖት መሪነት ሌላ። ፖለቲካና መንፈሳዊ ህይወት የተለያዩ ናቸው። የፖለቲካ ሹመት ከሆነ በገዢው ፓርቲ ሊመረጥ ይችላል። የሀይማኖት መሪ ግን በምእመናን ነው መመረጥ ያለበት። ስራውም ፖለቲካ ሳይሆን ሀይማኖታዊ ነው የሚሆነው። ሀይማኖታዊ መሪው በፖለቲካ ተፅዕኖ ስር መውደቅ የለበትም።
የኢህአዴግ መሪዎች ሁሉንም የሀይማኖት ተቋማትን ለመቆጣጠር የራሳቸው የፓርቲ አባላት የሀይማኖት መሪዎች አድርገው ይሾማሉ። ጓደኛዬ ናስሩዲን በፌስቡክ ገፁ እንዳስቀመጠው ከሆነ አቶ ስብሃት ነጋ እንዲህ ተናግረዋል:
“ቅድም የፌደራሉ መጅሊስ ምክትል ሰብሳቢው ሸህ ከድር እንዳለው የዱሮው እስልምና ሌላ ነው፡፡ እኔ ከድርን በፊት ጀምሮ ትግራይ ውስጥ አውቀዋለሁ፡፡ ምርጥ የሕወሓት ታጋይ ነበር፡፡ አብሮን ታግሏል፡፡ አሁን ደግሞ ሙስሊሙን እያገለገለ ነው፡፡ እስልምና እነዚህ የታሠሩት ሰዎች እንደሚሉት አይመስለኝም፡፡ እስልምና እነዚህ ሰዎች እንደሚያሳዩት ዓይነት እምነት ከሆነ እንደ እምነት አያስፈልግም፡፡ ፈፅሞ ሰዎቹ ለሀገር አይሆኑም፡፡”
ሼህ ከድር የሙስሊሞች ሀይማኖታዊ ተቋም የመጅሊስ ምክትል ሰብሳቢ ነው (ወይም ነበር)። ግን ሼህ ከድር የህወሓት ታጋይ ነበር። የህወሓት አባል ነው። ስለዚህ ሼህ ከድር የፖለቲካ መሪ እንጂ የሀይማኖት መሪ አይደለም። መጅሊስ የፖለቲካ ተቋም አይደለም። የፖለቲካ ሰው አይደለም የሚፈልገው። መጅሊስ የሀይማኖት ተቋም ነው። የሀይማኖት መሪ ይፈልጋል። እንደምናየው ግን የመጅሊስ አመራር አባላት የሀይማኖት መሪዎች ሳይሆኑ ፖለቲከኞች (እንዲሁም የጉሪላ ታጋዮች) ናቸው። እንዴት ይሆናል? ይሄ ተግባር ጥያቄ አያስነሳም? በዚህ መሰረት የሙስሊሞች ጥያቄ ትክክል ነው ማለት ነው።
ሙስሊሞቹ እንደ ምእመናን የሀይማኖት መሪ አያስፈልጋቸውም? “በሀይማኖታችን የፖለቲካ ካድሬዎች አያስፈልጉንም። የሀይማኖቱ እውቀት ያላቸውና በምእመናኑ እውቅና ያላቸው ሀይማኖተኞች እንዲመሩን እንፈልጋለን!” ብለው ቢጠይቁ አግባብነት የለውም? ከመቼ ጀምሮ ነው በማርክሲስታዊ አስተሳሰብ ያደገ የህወሓት ታጋይ ሀይማኖት ኖሮት የመጅሊስ ምክትል ሰብሳቢ የሚሆነው? ወይስ ሙስሊሞችን ለመቆጣጠር ነው የተፈለገው? ደግሞ የሀይማኖቱ ተከታዮች ሳይደግፉት?! የሀይማኖት መሪ’ኮ የምእመናኑ ድጋፍና እውቅና ያስፈልገዋል።
ሙስሊሞች ስለሀይማኖታቸው ሲጠይቂ ሌላ ስም ከመስጠት መጀመርያ መንግስት ከሀይማኖቱ እጁ ያንሳ። ካድሬዎቹን የሀይማኖት መሪዎች እያደረገ አይሹሙብን! ካድሬ በትምህርትቤት ይሾማል፣ በቤተክርስትያን ይሾማል፣ በመጅሊስ ይሾማል!??? ኧረ ተዉ ኢህአዴጎች! ፖለቲካና ሀይማኖት እንለይ!
ሁሉም ሃይማኖቶች ከፖለቲካ ነፃ የሆኑ የሀይማኖት መሪዎች ያስፈልጉዋቸዋል። የሀይማኖት ጉዳይ የመንግስት ጉዳይ ሳይሆን የምእመናኑ ጉዳይ ነውና።
ሙስሊሞች (ና ክርስትያኖች) ሆይ! መንግስት በሀይማኖታቹ ጣልቃ እንዲገባ የማትፈልጉ ከሆነ የመንግስትን በሀይማኖት ጣልቃ የመግባት ተግባሩ አጥብቃቹ ተቃወሙት። እየተቃወማችሁት ነው። ግን መፍትሔ የለም፣ ሰሚ የለም። ለጥያቅያቹ መልስ ከመስጠት ይልቅ መንግስት እያሰራቹ፣ እያሰቃያቹ ይገኛል። የመንግስት መፍትሔ ኮሚቴዎችን ማሳሰር ከሆነ በኢህአዴግ እምነት ሊኖራቹ አይገባም። እናም ኢህአዴግ መፍትሔ ሊያመጣላቹ እንደማይችል አረጋግጠዋል። ስለዚህ ምን ይደረግ? የሀይማኖት ጥያቄው ታፍኖ ይቅር?
የሀይማኖት ጥያቄማ መፍትሔ ይሻል። ምክንያቱም የሀይማኖት ጥያቄው ትክክለኛና አስፈላጊ ነው። ጥያቄው ሁላችን የምንደግፈው ነው። ጥያቄው ትክክል ከሆነ መልስ ያስፈልገዋል። መልስ የሚሰጥ አካል (መንግስት) ከሌለስ? መንግስት መልስ ሊሰጥ እንደማይችል ካረጋገጠልን ለህዝብ የሚቆረቆር፣ የህዝብን ጥያቄዎች መመለስ የሚችል፣ የሀይማኖት ችግሮች የሚፈታ፣ የሀይማኖት ነፃነት የሚፈቅድ፣ ሰብአዊ መብት የሚያከብር ዴሞክራሲያዊ መንግስት ያስፈልገናል ማለት ነው። ስለዚህ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ለመመስረት ጥረት እናድርግ። የምርጫ ድምፃችን የህዝብን ጥያቄዎች ሊመልሱ ለሚችሉ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲዎች እንስጥ። የህዝብን ጥያቄ መመለስ የሚያስፈራው ኢህአዴግ ከስልጣን (በዴሞክራሲያዊ መንገድ ወይ ምርጫ) እናውረደው። ሌላ ፓርቲን በመምረጥ ኢህአዴግን አውርደን ጥያቄያችንን የሚመልስልን ሌላ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ስልጣን እንዲይዝ እናድርግ። ከዛ የሀይማኖት ይሁን የሌላ ነፃነታችን ይከበርልናል። ካልተከበረ ትግላችን ይቀጥል።
__________________________________________________________________________________________
ኢትዮጵያዊው ዓረናና ኤርትራዊው ህወሓት!
=======================
ዓረናዎች “ህወሓት ኤርትራን ያስቀድማል። በመሆኑም ህወሓት የሻዕቢያ ተላላኪ ነው” ስንል ህወሓቶች ደግሞ “ዓረና ከትግራይን ህዝብ ጠላቶች ከሆኑ እንደነ አንድነት ፓርቲ ጋ ለመዋህድ ጥረት እያደረገ ነው” ይላሉ።
እርግጥ ነው፤ ዓረና ኢትዮጵያዊ ነው። ከኢትይጵያውያን ድርጅቶች ጋርም አብሮ ይሰራል። ከአንድነት፣ ደቡብ ሕብረት፣ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ እና ሌሎች ኢትዮጵያዊ ፓርቲዎች ጋር ለመዋሃድና አብሮ ለመስራት ዝግጁ ነው።
ዓረና እንደ ህወሓት ኤርትራዊ አይደለም። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ለመጉዳት ከሻዕብያ ጋር በማበር አይሰራም። ኢትዮጵያውያንን በጠላትነት እየፈረጀ የሻዕብያ አገልጋይ አይሆንም። ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያውያን እንጂ ኤርትራውያን አይደለንም። ኤርትራውያንን ለመጥቀም ኢትዮጵያውያንን አንበድልም። ስለዚህ ከሻዕብያ በላይ አንድነት ፓርቲን እናስቀድማለን። ምክንያቱም አንድነት ፓርቲ ኢትዮጵያዊ ነው። ኢትዮጵያም የሁላችን የጋራ ነች። ምናልባት ከሻዕብያ ጋር አብረን የምንሰራው የኢትዮጵያና የኤርትራ የጋራ ጥቅም የሚከበርበት መድረክ ሲፈጠር ብቻ ነው።
ዓረናና ህወሓት አልተሳሳቱም። ዓረና ከኢትዮጵያውያን ጋር ይሰራል። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ነው። ህወሓት የሻዕብያ ተላላኪ ነው። ምክንያቱም ህወሓት ኤርትራዊ ነው። ህወሓት ኤርትራዊ መሆኑ ችግር የለውም። ችግር የሆነው ህወሓት ኤርትራዊ ሁኖ፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ለኤርትራ አሳልፎ እየሰጠ ግን የኢትዮጵያ መንግስትነት መቆጣጠሩ ነው። ለኤርትራውያን እየሰራ ኢትዮጵያውያንን እወክላለሁ ማለቱ ነው ችግሩ። ህወሓት ለኤርትራ መቆም የሚያስደስተው ከሆነ ኤርትራን ያስተዳድር፤ የኤርትራን ህዝብ ይወክል። ኢትዮጵያን እያስተዳደረ፣ የኢትዮጵያ ህዝብን እወክላለሁ እያለ ለኤርትራ ጥቅም መስራቱ፣ ኤርትራውያንን መወከሉ ግን ወንጀል ነው። ህወሓት የኢትዮጵያ መንግስትነት ከተቆጣጠረ ለኢትዮጵያውያን ጥቅም መስራት ነበረበት።
ህወሓት የኢትዮጵያ ስልጣን ይዞ ኤርትራን ለማስገንጠል ይሰራል፣ ዓሰብን ለኤርትራ ይሰጣል፣ ዓሰብ የኛ መሆኑ ስንከራከር ህወሓት ከኤርትራውያን በላይ ዓሰብ የኤርትራ መሆኑ ይሟገታል። ለኤርትራውያን መቆም ካለበት ለምን ወደሚወክለው ኤርትራ አይሄድም?
ዓረና ከኢትዮጵያውያን ድርጅቶች መዋሃዱን ይቀጥላል። ህወሓትም ለኤርትራውያን ማገልገሉ ይቀጥል። በዚሁ መሰረት “ዓረና ከአንድነት ፓርቲ ጋር እየተወሃደ ነው” ብላች ሁ ክሰሱን። ለኛ ችግር አይሆንም፤ ምክንያቱም በኢትዮጵያውነታችን አምነን በኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውያን አማራጭ የፖለቲካ አቅጣጫ የሚያቀርብ ጠንካራ ሀገራዊ ፓርቲ የመመስረት ዕቅድ አለን። ህወሓትም ሻዕብያን ማገልገሉ ይቀጥል ምክንያቱም ህወሓት የኤርትራ ተወካይ (በኢትዮጵያ) መሆኑ እናውቃለን።
ህወሓት ግን ዓረና ከአንድነት ጋር የመዋህዱ ዜና ሲሰማ እንዲህ ከተደናገጠ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ጭምር ስንዋሃድስ ምን ሊሆን ነው? ዓረና ከአንድነት ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ብዙ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋርም ይወሃዳል። ጠንካራ ሀገራዊ ፓርቲ መመስረት እንፈልጋለንና።
ህወሓት ኤርትራን ሲያስበልጥ ዓረና ግን ኢትዮጵያንን ያስቀድማል።
__________________________________________________________________________
“የካቲት 11″ን እናክብረው?!
=============
የየካቲት 11 ዓላማ ዴሞክራሲ፣ ነፃነት፣ ሰላምና ልማት ነበር። ህዝቦች ታገሉ፤ መስዋእት ከፈሉ፤ ለነፃነት ሲሉ። ግንቦት 20 ሆነና ስልጣን ተያዘ። መስዋእት የተከፈለበት ዓላማ ፍሬ አፍርቶ ከሆነ ለማረጋገጥ በህይወት የተረፉ ታጋዮች ጠየቁ። ታጋዮቹ በጠላትነት ተፈርጀው በ1985 ዓም ተባረሩ፣ ታሰሩ፣ ተገደሉ። የወላጆቻችን መስዋእትነት ፍሬ ለመቅመስ ሞከርን። በድንጋይ ተወገርን። ወላጆቻችን መስዋእት የከፈሉ ለኛ ነፃነት ነበር።
ነፃነት የመቃወም፣ የመደገፍ ወይም ከሁለቱም ዉጭ መሰለፍን ያጠቃልላል። ወላጆቻችን የተሰዉለት የነፃነት ዓላማ አለን ብለን የፈለግነውም ሐሳብ ለህዝብ ማቅረብ መረጥን። ስለተቃወምን ታፈንን። እናም የየካቲት 11 መነሻ ዓፈና ነበር፤ መድረሻውም ዓፈና ሆነ። ፀረ ዓፈና መታገል እንዳለብን ገባን። የወላጆቻችን ዓለማ ነፃነት ነበር። የኛ ዓላማም ነፃነት ነው። ስለዚህ የኛና የወላጆቻችን ዓላማ አንድ ነው፤ ነፃነት። ያሁኗ ህወሓት ዓላማ ግን ዓፈና ሆኗል።
ያሁኗ ህወሓት በተግባር እያፈነች በሚድያ ግን “የካቲት 11″ን ማክበሯ አይቀርም። “ለካቲት ብርሃን ዉፁዓት እያ!” እያለችም እንደተለመደው ማደንቆሯ አይቀርም። የየካቲት 11 ዓላማ የተለየ ሐሳብ የሚያራምዱ የሰማእታት ልጆችን በድንጋይ መውገር ነበር ማለት ነው? ነፃነት ማለት ጭቆና ማለት ነው?
በተግባር ስንቃወም ታፈንን። ስንቃወም ከታፈንን መቃወማችን ትክክል ነው ማለት ነው። ምክንያቱም እኛ ወጣቶች የመቃወም መብት አለን። “ስንቃወም ለምን እንታፈናለን?” ብለን መቃወም እንችላለን። የህወሓት የዓፈና ተግባር የኛን የመቃወም አስፈላጊነት የሚያረጋግጥ ነው።
ስለዚህ የወላጆቻችን የትግል ዓላማ ተጠልፎ ለስልጣን ማራዘምያ ሆኗል። ስልጣንም ልማት ለማፋጠንና ነፃነትን ለማረጋገጥ ከማዋል ይልቅ ዜጎችን ለማፈን እየዋለ ነው። ስለዚህ የወላጆቻችን መስዋእት ግቡ አልመታም።
በኔ አመለካከት ህወሓት በሁለት ይከፈላል፤ ስልጣን ፈላጊ መሪዎቹና ነፃነት ፈላጊ ታጋዮቹ። ስልጣን ፈላጊ የህወሓት መሪዎች ስልጣን ጨብጠው ህዝብ እየጨቆኑ ይገኛሉ። ነፃነት ፈላጊ ታጋዮቹ ደግሞ ለነፃነት ሲሉ መስዋእት ከፍለው ለራሳቸውም ነፃነት ተነፍገው እየተጨቆኑ ይገኛሉ። ጭቆናን መቃወም ሲጀምሩ ደግሞ በድንጋይ ይወገራሉ (አስገደ ገብረስላሴ በዓዲግራት)። ስለዚህ የህወሓት የነፃነት ታጋዮች ተጨቁነው ይኖራሉ። የህወሓት መሪዎች ደግሞ ታጋዮቹን በማባረር፣ የራሳቸውን ቤተሰብ ይዘው የሀገር ሃብት እየበዘበዙ ህዝቦችን በማሸበር ይገዛሉ።
ስለዚህ የህወሓት ታጋዮች የነፃነት ዓላማ ተኮላሽተዋል። የወላጆቻችን የነፃነት ተልእኮም ተጠልፏል። የወላጆቻችን ዓላማ አሁን ለምናየው ዓፈና የታለመ ነበር ካላችሁኝ አላምናችሁም። ካመንካችሁ ግን ዓላማው ስህተት ነበር እላችኋለሁ። ምክንያቱም የመስዋእትነት ዓላማ ነፃነት ነው። የወላጆቻችን ዓላማም ነፃነት ነበር። ስለዚህ ነፃነታችንን በተግባር መከወን አለብን። ነፃነታችንን ከተነፈግን ግን ነፃነታችንን ለማስመለስ መታገል ይኖርብናል።
ነፃነት የሌለው ህይወት አንፈልግም። እየኖርን አንሞትም።
ወያኔ ለምን ይሸበራል?
ዳዊት መላኩ( ከጀርመን)
አባቶች ሲተርቱ ’’ፈስ ያለበት ዝላይ አይችልም ’’ ይላሉ፡፡ዝላዬን ተከትሎ ምን እንደሚመጣ ስለሚያውቅ በዝላይ አይሳተፍም ዝላይም አይወድም፡፡የወያኔ አንባገነን መንግስት ለምን ይሸበራል ብልን ስንጠይቅ መልሱ ቀላል ነው፡፡ከባዱ እና አስካሁን ብዙ በስልጣን እንዲቆይ ያስቻለው ግን በመፍትሄው ላይ በጋራ መስራት አለመቻላችን ነው፡፡ወያኔ የሚሸበረው የህዝን ሀብት ስለሚዘርፍ፤ህዝብን ስለሚገድል፤ህዝብን የሚጎዳ ስራ ስለሚሰራ የገንዛ ስራው ነው ጥላ እየተከተለ እንደሸበር የሚያደርገው፡፡
በራሱ የሚተማመን እና መልካም ስራ የሚሰራ መንግስት ማንም ምንም ይፃፍ ማንም የፈለገውን የፖለቲካ ድርጅት ይደግፍ ፤ማንም የፈለገውን የፖለቲካ ድርጅት ያቁዋቁም የሰራው መልክም ስራ ዋስትናው ስለሆነ ምንም ይመጣብኛል ብሎ አይሰጋም፡፡ወያኔ ግን ይዞት የተነሳውም አላማም ይሁን የስልጣን ኮርቻ ላይ ከተቆናጠጠም በሁዋላ የሚሰራው ስራ የተሳሳተ በመሆኑ በራሱ ስራ እና ክፉ ሀሳብ ዘወትር ይሸበራል፡፡ወያኔ ነፃ አውጪ ነኝ እያለ የዜጎችን ነፃነት በአደባባይ የሚገፍ የመደራጀት የመጻፍ መብትን የማይፈልግ የራሱ ጥላ የሚያሰደነብረው ተሸብሮ የሚያሸብር ድርጅት ነው፡፡አንድ ወቅት የወያኔው መስራች መለስ ዜናዊ የወያኔ ስልጣን የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው ብለው ነበር፡፡ እሳቸው ቃሉን የተጠቀሙበት ለሌላ አላማ ቢሆንም እውነታው ግን ወያኔ ሁሌም ክፉ ስራው እያባነነው ፤የንጹኃን ደም እረፍት እየነሳው ሲቃዥ እንደሚድር ሳያስቡት ያጋጠማቸውን የስነልቦና ችግር ነው ባደባባይ የዘረገፉት፡፡ለወያኔ የሽብር ምንጮች
1. ከመነሻው ዘርን መሰረት ያደረገ አደረጃጀት ይዘው ሲነሱ እና የኢትዮጵያ ህዝብ እንደቀስተ ደመና በልዩነቱ ውስጥ ባንድነት አሸብርቆ ለዘመናት ተጋብቶ ተዋልዶ አብሮ የኖር የራሱ የሆነ የፍልስፍና የባህል የአኑዋዋር ዘዴ የሚከተል በመሆኑ የስታሊን ፍልስፍና ኢትዮጵያ ውስጥ በቀላሉ እንደማይተገበር ያውቃል፡፡ስለዚህ ከመነሻው የነበረውን ታሪክ ፤ባህል፤አንድነት ማፈራረስ በመሆኑ ሰዎች ባንድነት በሀገራዊ ስሜት የጋራ አጀንዳ ይዘው የሚመጡ፤ የህዝብን ጥቅም ያስቀደሙ ጥያቄዎች ሁሉ ያሸብራቸዋል፡፡
2. ወያኔዎች ዋናው ችግራቸው የስልጣን ጥማት በመሆኑ ስልጣኑንም የሚፈልጉት ህዝብን በማስተዳደር ለሀገር እና ለወገን የሚጠቅም ስራ ከመስራት ይልቅ ስልጣንን መሰረት አድርገው የህዝብን ሀብት ያላግባብ ስለሚዘርፉ ስልጣናቸውን ባጡ ማግስት ያን ሁሉ ነገራቸው የሚያጡ ስለሚመስላቸው የሚዘርፉት የሀብት መጠን ፤ሀብቱን ያገኙበት ምንገድ ህገወጥነት ሁሌም ከዛሬ ነገ ይነቁብናል እያሉ ይሸበራሉ፡፡
3. የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎችን በማጥፋት በአማራው መቃብር ላይ ስልጣናቸውን ማደላደል ስለሚፈልጉ ከዚህ ወገን የሚመጣ የህዝብ ጥያቄ ሁሌም ያሽብራቸዋል፡፡በተለይ ጫካ ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ በአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ላይ የፈፀ ሙት ከፍተኛ ወንጀል ያሸብራቸዋል፡፡ለአማራው ያላቸውን ጥላቻ ባያክልም በሌሎች ብሄረሰቦች ላይም ምንም እምነት የላቸውም፡፡በተለይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ብሄሮች አትብቆ ይፈራቸዋል፡፡ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የኦሮሞ ተናጋሪ አንድ ቀን ሊያምጽብኝ ይችላል መቢል ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በጮሁ ቁጥር የለመደው የሽብር ዛር ተነስቶ ያነገፈግፈዋል፡፡
4. ሌላው ወያኔን የሚያሸብረው የመገናኛ ብዙሀን ነው፡፡ ለህዝቡ እውነቱን በመደበቅ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ሲለሚግተው ህዝቡ እውነቱን ካወቀ ስልጣኔን ላጣ ነው፡፡ስልጣን ካጣሁ ደግሞ እንደሰው ለመኖርም የሚያስችለኝ መልካም ነገር ስለሌለኝ እጠፋለሁ ብሎ ማሰብ ሌላው የሽብር ምንጩ ነው፡፡ለዚህ ነው እንግዲህ ኢሳትን ጨምሮ የነፃው ፕሬስ ለወያኔ የሽብር ምንጪ የሚሆኑት፡፡
5. ወያኔ ህዝብን አደንቁሮ ፣አደህይቶ እና አዋርዶ መግዛት ስለሚፈልግ ሰዎች ባወቁ ቁጥር ፤በኩራት ቀና ማለት ከጀመሩ ፤ እንዲሁም የዕለት ኑሮዋቸውን ባሸነፉ ቁጥር ነገ ከምግብ ያለፈ ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ ብሎ በማሰብ በሰዎች ማወቅ፤በማግኘታቸው እና በልበ ሙሉነታቸው ሁሉ ይሸበራል፡፡ከምን ተነስቶ ነው እንዲህ ኩራት የተሰማው ማን አይዞህ ብሎት ነው ከጀርባው ምን ቢኖር ነው በማለት ይሸበራል፡፡
6. ሌላው ትልቁ የወያኔ የሽብር ምንጭ የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው፡፡በዚህ በኩል የሚመጣው ችግር ከሁሉ የከፋ እንደሚሆን ያውቃል፡፡ የስርዓት ለውጥ ለማምጣት ህዝቡን አደራጅቶ የሚመራ ሁሉን አቀፍ የሆነ የዜጎችን መሰረታዊ ጥያቄዎች አንግቦ የተነሳ የፖለቲካ ድርጅት የወያኔን አንባገነን መንግስት ነፍስ ለመውሰድ የተላከ መላከ-ሞት ስለሚመስላቸው ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት በተፈጠረ ቁጠር የወያኔ መሰረት ያናጣል ፡፡ከላይ እስከታች በከፍተኛ ሽብር ስር ይወድቃሉ፡፡
7. ወያኔ የዜጎችን በነጻነት የማምለክ ሰባዊ መብታቸውን በመግፈፍ ህዝቦች እምነት የለሽ የወያኔ ተላላኪ እና ጋሻ-ጃግሬ እንዲሆኑ ስለሚፈልግ እና ማንኛውም እምነት ደግሞ መልካም ስራን ፣ፍቅርን፣ሰላምን፣ይቅር ባይነትን አልፎተርፎም ከሞት በሁዋላ ስላለው ህይወት በማስተማር ህዝብን ለእውነት እንዲቆም ስለሚያደርጉ የምዕምናን ህብረት ያሸብረዋል፡፡ ለዚህም ነው ማህበረቅዱሳን ፤መጅሊስ ሳማቸው ሲጠራ ቁጥር የሚያንዘፈዝፈው፡፡
8. ሌላው ወያኔን የሚያሸብረው ምርጫ ነው፡፡በህዝብ ያልተመረጠ መንግስት ስልጣን ከሕዝብ በሚወጣ ድምጽ ብቻ ነው ስልጣን መያዝ ያለበት በተባለ ቁጥር መበርገግ መሸበር የሚያስገርም ነገር አደለም፡፡ምርጫ በመጣ ቁጥር የሚይዝ የሚጨብጠውን ነው የሚያጣው፡፡ሰራዊቱን ከቦታ ቦታ ያዘዋውራል፤መድፍ ታንክ ሳይቀር ቤከተማው እንዲርመሰመስ ያደርጋል፡፡
ከላይ ለማየት አንደሞከርነው አንድ ሻንበል ጦር የሌላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ወያኔን ስማቸው በመጠራቱ ብቻ ያሸብሩታል፡፡ዛሬ ወያኔ የሚሸበረው በሰማያዊ ፓርቲ፤ በአንድነት ፣በግንቦት ሰባት እና በሌሎችም ነው፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ሰራዊት ስላላቸው የጦር መሳሪያ ስለታጠቁ አደለም ወያኔን የሚያሸብሩት፡፡እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች ጥያቄዎቻቸው የህዝብ ጥቄዎች በመሆናቸው ወያኔን ማሸበራቸው የማይቀር ነው፡፡ የሚያነሱዋቸው የፍትህ ፤የነፃነት እና የዲሞክራሲ ጥያቄዎች ወያኔ አስቦት የማያውቀው ነገር በመሆኑ ከራሱ የተፈጥሮ ባህሪ በመነሳት ስማቸው በተጠራ ቁጥር ይሸበራል ፡፡ ነገር ግን እየተሸበረ ያለው በግድ ሳይፈልጉት ስልጣን ኮርቻ ላይ ተቆናጦ እንደመዥገር ደም እየመጠጠ ያለው የወያኔ መንግስት እንጅ ህዝቡ የነጸነት አየር የሚተነፍስበት ቀን እንዲመጣ በመጠባበቅ ላይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ባሁኑ ሰዓት አሸባሪ ድርጅት ወይም ግለሰብ ሳይኖር ወያኔ በራሱ ተሸብሮ እያሸበረ ይገኛል፡፡በአለም አቀፍ ደረጃም እስካሁን ከተቋቋሙ የኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ አሸባሪ የተባለ ወያኔ እና ወያኔ ብቻ ነው፡፡ወያኔን የሚያሸብረው እንግዲህ ክፉ ስራው እና ፍርሀቱ ነው፡፡እንግዲህ ለወያኔም እንዲህ እየተሸበረ ከሚኖር መፍትሄ እንዲሆነው እና ከሽብር እንዲላቀቅ የሸብር ምንጪ የሆነውን ስልጣኑን ለህዝብ በማድረግ ፍትህ ሠላም እና ዲሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁላችንም የድርሻችንን እንወጣ እላለሁ፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ህዝቦች!
የአባይ ግድብና የአገዛዙ ተቃርኖዎቹ
በአለም የወንዞች ታሪክ እንደ አባይ የተዘፈነለት፤ የተዘመረለት ወንዝ ያለ መቸም አይመስለኝም በአለም በእረጅምነቱ የሚስተካከለው የሌለው አባይ በትውልድ ሃገሩ ከዘፈን ግጥምና ከእንጉርጉሮ አድማቂነት ያለፈ ጥቅም ሳይሰጥ ለዘመናት ያለማቋረጥ መፍሰሱ እርግጥ ነው። ከወቀሳ እስከ ሙገሳ ከቁጭት እስከ ብስጭት ብዙ ብዙ ተብሎለታል ለአባይ ያልዘፈነ ዘፋኝ ያልገጠመ ገጣሚ ያልተቀኘ ባለቅኔ ማግኝት ይከብዳል እናም አባይ ለቁጥር የሚታክቱ የስነጥበብ ጉዳዮችን አስተናግዷል።
የማለዳ ወግ …ሳውዲ ጉዳይ –ዛሬም ድጋፍ በምድረ አሜሪካ –ዋሽንግተን ዲሲ !
ትናንት በሳውዲ ሰአት አቆጣጠር እኩለ ሌሊት ፣ በምድረ አሜሪካ ዋሽንግተን ከቀትር በኋላ እልፍ አዕላፍ ከሚቆጠሩት በምድረ አሜሪካ ነዋሪ ከሆኑ ኢትዮጵያውያን መካከል “የወገናችን ጉዳይ ያገባናል !” ያሉት ጥቂቶች በአለም አቀፉ እርዳታ አሰባሳቢ ቡድን በተጠራው Global Alliance የድጋፍ ማሰባሰቢያ ተገኝተው ነበር ። እኔም በሳውዲ ስላለው ነባራዊ ሁኔታ አጭር ንግግር እንዳደርግ በተጋበዝኩት መሰረት ዝግጅቱን በ Skype በእስካይፒ ተከታትየዋለሁና መረጃውን ላካፍላችሁ …
በትናንት ምሽቱ የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ከተገኙት ታዋቂ ሰዎች መካከል የአለም አቀፍ ስደተኞች IOM የዋሽንግተን ዲሲ ተወካይ Mr. Luca Dall’Oglio, የክርስትና እምነት ተወካይ ዶር ቀሲስ አማረ ካሳ ፣ ከፕሮቴስታንት ፖስተር ዳንኤል ጣሰው ፣ ከእስልምና እምነት ተወካይ ሸህ ካልድ ኦመር እና የእርዳታ አሰባሳቢው ሊቀ መንበር ታዋቂው አክቲቪስት እና አርቲስት ታማኝ በየነ በድጋፍ ማሰባሰቢያው ተገኝተዋል ። እኒሁ ስመ ጥር ታዋቂ ተጋበዥ እንግዶች ለወገናቸው ያላቸውን የተቆርቋሪነት ስሜት የታየበት ንግግርም አድርገዋል።
እኔም በተያዘልኝ ሰአት በሳውዲ አረቢያ ስላለው ነባራዊ ሁኔታ አጥር ያለ ማብራሪያ ሰጥቻለሁ። እርግጥ ነው በአሁኑ ሰአት ሳውዲ አረቢያ የምንኖር ኢትዮጵያን በህገ ወጥነት የተፈረጁ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ የበረደ የቀዘቀዘ ቢመስልም ዳሩ አሁንም መጭው አሳሳቢ ለመሆኑ የሰሞኑ ፍተሻዎች ጠቋሚ ናቸው ። ከሁሉም አስጊ የሆነው ያለ አሰሪዎች የሚሰሩት በህገ ወጥነት የተፈረጁበት እና በኮንትራት ስራ ስም በመላ ሳውዲ እንደ ጨው ተበትነው የቀሩት ዜጎች ይዞታ አሳሳቢ መሆኑን ለማስረዳት ሞክሬያለሁ። በአሁኑ ሰአት ወደ በተለያዩ የሳውዲ ከተሞች ሃገር ለመግባት እጃቸውን የሰጡ ዜጎች በየእስር ቤቱ ከወር በዘለቀ ጊዜ በእስር ላይ የሚገኙበትን ሁኔታ አሳሳቢነት እና በኮንትራት የመጡ ዜጎች እንግልትና በቀጣይ ጊዜያት በአስፈሪ አደጋ የተከበበ መሆኑን ግንዛቤ ለማስጨበጥ ጊዜው ባይበቃም አቅም የፈቀደውን መረጃ ለመስጠት ሞክሬያለሁ ።
በሳውዲ ኢትዮጵያውያን በደል ሲፈጸም በተለይም በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በዚህ መሰሉ ሰብዕና መሰረት ባደረገ አለምን ያስደመመ ህብረት ላደረጉት ተቃውሞ ሰልፍና ተጽዕኖን ፈጥረው በውጭ የሚኖሮ ኢትዮጵያውያን ታላቅ ውጤት አስገኝተዋል። በእርግጥም አለም አቀፍ ሰፊ ተቃውሞን በማድረግ ተጽዕኖ መፍጠር ባይቻል ኖሮ 180 ሽህ የሚደርሱ ዜጎችን በአጭር ጊዜ ወደ ሃገር ሊገቡ ይችሉ ነበር ብሎ መገመት ያዳግታል። ለዚህም ታላቁን ስራ በመስራቱ ረገድ ቀዳሚው ተመስጋኝ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ናቸው ። ዲያስፖራ የምንላቸው ። እውነት ነው ፣ በፖለቲካ ዘባተሎ የተለያየው ዲያስፖራ በሳውዲ ጉዳይ ልዩነትን አሰወግዶ በህብረት በመነሳቱ ትልቅ ስኬትን ለማየት በቅተናል። በወገኖቻችን ኮርተንባችኋልም! ያም ሁሉ ሆኖ በአሁኑ ሰአት ድጋፍ ለማሰባሰብ በሚደረገው ጥረት መለያየቱን ትተን በህብረት እንሰራ ዘንድ ባደረግኩት ንግግር በመማጸን ለተደረገልን ሁሉ አክብሮትን ከምስጋና አቅርቤያለሁ ።
በአለም አቀፉ እርዳታ አሰባሳቢ ቡድን Global Alliance የድጋፍ ማሰባሰቢያ ለሁለት ጊዜ ያህል ያሰባሰበውን ገንዘብ ለአለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት IOM ማስረከቡ አይዘነጋም !
በሰብዕና ወገን ለወገን እንዲህ ቀናኢ ሲሆን ያስደስታል ! ያኮራልም !
ቸር ይግጠመን !
ነቢዩ ሲራክ
እየተዋረዱ መገዛት እስከመቼ!?
በቅዱስ ዬሃንስ
አለምነው መኮነን የተባለ የብአዴን ወኪልና የባንዳ አስፈፃሚ የአለቆቹን የዘወትር አባባል በማስረገጥ እመራዋለሁ የሚለውን የአማራ ህዝብ <<ሰንፋጭ የሆነ ትምክህተኝነት የተጠናወተው፤ ትምክህተኝነቱን ያልተው፤ በባዶ እግሩ እየሄደ መርዝ ንግግር የሚናገር ወዘተ>> ካለ በኋላ <<የትምክህት ልጋጉን ማራገፍ አለበት>> በማለት እንደሌሎች ብሄረሰቦች ሁሉ ደከመኝ፡ ሰለቸኝ ሳይል ዋጋ የከፈለውን የአማራ ህዝብ ዋጋ በማሳጣት የሌሎቹ ጠላት አድርጐ በማቅረብ፡ የዘረኞች ተባባሪነቱን አስመስክሯል።
የአማራው ህዝብ የወያኔ ዘረኞች ዋነኛ ዒላማ ሆኖ የአገዛዙን የግፍ ፅዋ ያለማቋረጥ መጋት ከጀመረ ድፍን 23 አመታት ተቆጠሩ። ፋሽስቱ ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ ብሔራዊ ስሜት በማምከን ፣ የዘመናት ተገዥነቱን ለማረጋገጥ በቅድሚያ የአማራን ሕዝብ ማንነት ማጥፋት ፣ የአማራን ሕዝብ ስነ ልቦናዊ ጥንካሬ መስለብ እና አንገቱን ማስደፋት አስፈላጊ መሆኑን በጽናት ያምናል። ይህ በመሆኑም ፣ በአማራ ህዝብ ላይ በወያኔ የሚፈፀመው ግፍ እና በደል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ስር እየሰደደና እየከፋ በግልፅም በስውርም በተቀነባበረ መንገድ ቀጥሏል።
ይህ የህወሀት የጸረ አማራ ፕሮፓጋንዳ ማሽን የሚመራው በዋና ዋናዎቹ የወያኔ ሹሞች ቢሆንም ወያኔ የአማራን ህዝብ የሚገድለዉ፤ የሚያዋርደዉና የሚያሳደድዉ አማራ ነን በሚሉ ነገር ግን የአማራን ህዝብ በጅምላ በሚሰድቡና አማራዉ ሲገደል፤ ሲታሰርና ሲፈናቀል ይበልህ በሚሉ በእነ አለምነው መኮንን አይነት ወፍ ዘራሽ ካድሬዎች ነው። አንበሳ ሲያረጅ የዝንብ መጫወቻ ይሆናል እንዲሉ፡ የአማራው ህዝብ ዛሬ ቀን ጣለውና፣ በጠላቶቹ እጅ ወደቀ፣ የድፍን ስድና መረን ያደገ ዋልጌ ሁሉ የስድብና የዘለፋ አፍ ማሟሻ የመሆን ዕጣ ደረሰው። አለምነው መኮነን የተባለ የብአዴን ወኪልና የባንዳ አስፈፃሚ የአለቆቹን የዘወትር አባባል በማስረገጥ እመራዋለሁ የሚለውን የአማራ ህዝብ <<ሰንፋጭ የሆነ ትምክህተኝነት የተጠናወተው፤ ትምክህተኝነቱን ያልተው፤ በባዶ እግሩ እየሄደ መርዝ ንግግር የሚናገር ወዘተ>> ካለ በኋላ <<የትምክህት ልጋጉን ማራገፍ አለበት>> በማለት እንደሌሎች ብሄረሰቦች ሁሉ ደከመኝ፡ ሰለቸኝ ሳይል ዋጋ የከፈለውን የአማራ ህዝብ ዋጋ በማሳጣት የሌሎቹ ጠላት አድርጐ በማቅረብ፡ የዘረኞች ተባባሪነቱን አስመስክሯል።
በርግጥ ወያኔ እንደፈረስ የሚጋልበው ብአዴን በታሪኩ አንድም ለህዝቡ የቆመ መሪ ሲያፈራ አልታየም። የአማራ ህዝብ ብአዴንን የመሰለ አሳፋሪ ድርጅት በታሪኩ ገጥሞት አያውቅም። በባዕድ ወረራ ጊዜ ለጣልያን ያደሩ ባንዶች እንኳን ከዛሬዎቹ ብአዴኖች የተሻለ ክብር ነበራቸው። ከዛሬዎቹም በተሻለ በጌቶቻቸው ጣሊያኖችን ይሰሙ ነበር። ብአዴን ግን ራሱን ከባንዳነትም አውርዶ ባርነት ደረጃ ላይ የጣለ ከመሆንም አልፎ በባርነቱ የሚደሰት ድርጅት ነው። ብአዴን የህወሓት ወያኔ ወኪል እንጅ የአማራው ህዝብ ወኪል አይደለም፡፡ ብአዴን ሁሌም የአማራውን ህዝብ እንደ ሰደበ፣ እንዳዋረደ፤ እንዳስገዛ ነው፡፡ የብአዴን ፍሬ የሆነው አለምነው የተባለው የእናት ጡት ነካሽም በድጋሚ ያረጋገጠልን ይንኑ ነው። አለምነዉ እነዚያን እጅግ አሳፋሪና ከፋፋይ ንግግሮች የተናገረዉ ፀረ አማራና ፀረ-ኢትየዮጵያ ጌቶቹን ያስደሰተ መስሎት ወይም የሥልጣን ቆይታውን ያመቻቸና በሥልጣን መሰላል ሽቅብ የተወነጨፈ መስሎት ሊሆን ይችላል፤
ሆኖም የአማራ ህዝብና ወገኑ የሆነዉ ሌላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን የአንድን ህዝብ ስብእናና ክብር የሚያጎድፍ ንግግር በምንም መልኩ ችላ ብሎ ሊያልፈዉ አይገባም፡፡
እንደሚታወቀው ዘረኛው ወያኔ የጸረ አማራነት አቋሙ እጅግ የከፋ ፣ ስር የሰደደ እና በድርጅት የታቀፈ ነዉ፤ እኛም በድርጅት ታቅፈን በድርጅት ካልገጠምነዉና ካልደመሰስነዉ በቀር የወያኔ ዘረኝነት መቆሚያና ማለቂያ የለዉም። ለምሳሌ ፋሽስቱ ወያኔ በቅርቡ በቤኒሻንጉልና በቤንች ማጅ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ ዉስጥ አማራውን በማፈናቀል አማሮች ከአማራ ክልል ዉጭ መኖር አትችሉም ብሏል። የወያኔ ዘረኞች እነሱ በዘጠኙም ክልል እንዳሻቸዉ እየዞሩና ኃብት እያጋበሱ አማራዉን ግን እንደ ውጭ ዜጋ በማየት በገዛ አገሩ ውስጥ ከቦታ ወደ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ በማድረግ አማራዉ ሳይወድ በግዱ የስደት ገፈት ቀማሽ እንዲሆን አድርገዉታል። ኧረ ለመሆኑ ይህ የግፍ ፅዋ ሂትለር በጀርመን በይሁዳዎች ላይ ከፈፀመው በምን ይለያል? እንደምናስታውሰው በሽግግሩ ወቅት ጠቅላይ ሚንስትር በነበረው ታምራት ላይኔና በወቅቱ ፕረዜዳንት በነበረው ሟቹ መለስ ዜናዊ በተፈራ ዋልዋ አቀናባሪነት በተሰጠ ትእዛዝ በወተር፤ አርባ ጉጉና በበደኖ ኦህዴድና ኦነግን በየፊናው አስማርተው የኋላ ድጋፍ እየሰጡ ውድ ወገኖቻችን ህይወታቸው ስታልፍ እንደ እንሰሳ ቆዳቸው መገፈፉ፤ ሳይሞቱ በገደል ሲጣሉና ሕጻን ሽማግሌ ሴት ወንድ ሳይለይ በጅምላ የማለቃቸውን ሃዘን ሳንረሳው ዛሬ ደግሞ ዳግም የጠብ አጫሪነቱን፡ በምን ታደርጉኛላችሁ እብሪት ተወጥሮ በባንዳው አለምነው መኮነን አስፈፃሚነት ለክልሉ ህዝብ ያለውን ከፍተኛ ንቀት ሬት ሬት በሚሉና አጥንትን የሚሰረስሩ ስድቦችን በመጠቀም አንካችሁ አሉ። አለምነው መኮነን የረጨውን መርዝ እስኪ አስቡት ወገን? ማንን ተማምኖ፡ የልብ ልብ ተሰምቶት ይመስላችኋል ይህ የመርገምት ልጅ ይህን ያህል ልሃጩን በጨዋው የአማራ ህዝብ ላይ የሚተፋበት? አረመኔውን የፋሽስት አገዛዝ አደለምን። ኧረ ግን አማራው እስከመቼ በዚህ የፋሽስት ስርአት እየተገደለ፡ እየተሰደደና እየተዋረደ መኖርን መረጠ? ኧረ ዝምታው ምንድነው? ግን እስከመቼስ ይሆን?
ውድ የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ!
ፋሽስቱ ወያኔ በአማራ ህዝብ ላይ በተከታታይ በማድረስ ላይ ያለዉ በደል፤ ግፍና ዉርደት የወያኔ ዘረኞች ሊነግሩን አንደሚፈልጉት የአማራዉ ጉዳይ ነዉ ተብሎ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም።ይህ ዛሬ በአማራዉ ላይ እየፈጸመው ያለው ዘርን የማዋረድና የማጥፋት ርካሽ ስራ ነገ በእያንዳንዳችን ላይ የሚደርስ መሆኑን ልንረዳ ይገባል። የወያኔ ወንጀል አሁን የተጠነሰሰ ሳይሆን ወያኔ ገና ደደቢት በረሃ ላይ ሲጠነሰስ አብሮት የተጠነሰሰ ሴራ ነዉ። ወያኔና ዘረኛ ስርአቱ እስካልተወገዱ ድረስ ይህ የተጀመረው አማራን የማዋረድ፡ የመጨፍጨፋ፣ የማፈናቀልና የማሳደድ ዘመቻ፣ ተጠናክሮ መቀጠሉ አይቀርም። ወያኔ አማራዉን ካዳከምኩ ሌላዉ አያቅተኝም በሚል ዘረኛ ስሌቱ ዛሬ አማራዉ ላይ አተኮረ እንጂ በወያኔ የተደበደ ፣ የታሰረ፣ የተሰደደ፤ የተፈናቀለ ፤ እንዲራብ የተደረገ፤ የተዋረደና የተገደለ ኢትዮጵያዊ ስፍር ቁጥር የለዉም። ዛሬ የአማራው ህዝብ ብቻ ሳይሆን ድፍን የኢትዮጵያ ህዝብ በወያኔ ጨካኝ ስርአት አማካኝነት በጨለማ ሂዎት ውስጥ እየማቀቀ ነው። ስለዚህ ችግሩ የአገርና የወገን የህልውና ጉዳይ እንጅ የፖለቲካ ጨዋታ ባለመሆኑ የወጣት፣ አዋቂ፣ ጎልማሳ፣ ሽማግሌ፣ ጾታ ሳይለየን ወያኔን ለማስወገድ በሚደረገው ትግል ምላሽ በመስጠት አለበት ባይ ነኝ። በአማራው ህዝብ ላይ የጠቆረውን ጨለማ በብርሃን መተኪያ ጊዜው አሁን ነው። ይህ ትውልድ የታሪክ ባለእዳ አይሁን። በወያኔ ዙሪያ ተሰብስባችሁ የሥርዓቱ ጠባቂና ተጠቃሚዎች የሆናችሁ በሙሉ ባሳለፋችሁት የግዛት ዘመናችሁ የአማራውን ዘር ብትሰድቡትም፡ ብትገድሉትም፡ ብታስሩትና ብታስርቡትም፤ ብታሰድዱትም፤ ሀብት ንብረቱን ብትዘርፉትም፤ በአገሩ በኢትዮጵያ የመኖር መብቱን ብትገፉትም ሕዝቡ መሃሪ ነውና ዛሬውኑ የሕዝቡን ትግል ብትደግፉና ብትቀላቀሉ ይሻላል። በተለይ አማራ ሆናችሁ ብአዴን የሚባል የፋሽስቱ ወያኔን የጥፋት ክንፍ ስታገለግሉ፡ እስከ ዛሬ በሆዳችሁ ስትገዙ የኖራችሁ እንደ አለምነው መኮንን አይነት የእፉኝት ልጆች ሕዝባችሁን የማዋረድና፤ የማድማት ተልኮዋችሁን አቁማችሁ፤ ወያኔ በወገኖቻችሁ ላይ እየፈጠረ ያለው ችግር ተሰምቷችሁ፤ ህዝባችሁን ይቅርታ ጠይቃችሁ፤ አሁኑኑ ለትግሉ ምላሽ በመስጠት መከታ በመሆን አዝሎ ያሳደጋችሁን ህብረተሰብ ከባርነት ቀንበር ታላቅቁት ዘንድ ወገናዊ ጥሪየን አቀርባለሁ። ለውሳኔው አለማርፈዳችሁን በዚሁ አጋጣሚ ላረጋግጥላችሁ ጭምር እወዳለሁ።
ድል ለጭቁኑ የኢትዮጵያ ህዝብ!
ለአስተያየትዎ፡ kiduszethiopia@gmail.com አድራሻየ ነው።
የማፊያ ከበርቴዎች!!
ከነብዩ አለማየሁ (ኦስሎ)
በኢትዮጵያ አንድ ግለሰብ ወይም company ቢዝነሱ የሚሳካው ወይ ካጭበረበረ ወይም መንግስት አካባቢ ሰው ካለ ወይም ጉቦ ከሰጠ ነው።ለነገሩ ዋና ዋናው ቢዝነስ የተያዘው በህውሀት ሰዎችና ጀሌዎቻቸው ነው። በሌላው ሀገር ተራውን ህዝብ መንግስት የሚያገለግለው በታላላቅ የንግድ ተቑማት ላይ ጠቀም ያለ ታክስ በመጣል ነው። እኛ ሀገር ግን በርካታ ከገዢውፓርቲ ጋር ግንኙነት ያላቸው በጣም አነስተኛ ታክስ የሚከፍሉና ጭራሽ የማይክፍሉም ሞልትዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በትክክለኛው መንገድ ታክስ የሚከፍለው የመንግስት ሰራተኛ ብቻ ነው። የኑሮ ጫና ግራ ያጋባው አነስተኛ ገቢ የሚያገኘው በስግብግብ ነጋዴዎች ገንዘብ የሚዘረፈው ሀይ ባይ መንግስት ያጣው ይህው የህብረተሰብ ክፍል ነው። በጣም የሚገርመው መንግስት በተለያዩ ነገሮች መዋጮ ሲፈልግ እፋጦ የሚቀበለው ይህንኑ የህብረተሰብ ክፍል ነው። ይህ የህብረተሰብ ክፍል የበይ ተመልካች ሆኖ ኑሮውን መግፋት የለበትም በቃ ማለት አለበት ።ምክንያቱም ቅኝ መገዛት ከዚ በምን ይለያል።
የወያኔ መንግስት የሀገሪቱን የንግድ ህግ እንዳሻው እየለዋወጠ በሀገሪቱ በሌሎች ግለሰቦችና ድርጅቶች የተያዘውን ቢዝነስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የራሱ እያረገ ለ23 ዓመት ዘልቋል። ወያኔ እንደመንግስት የማያሰራ የንግድ ፍሰት የሚያሰራ የቢዝነስ ህግ በማውጣትና በመተግበር ፈንታ እንደተራ ማፊያ ሆኖ ነጋዴዎችንና የቢዝንስ ሰዎችን በማዳከም የራሱን ኤፈርት የተባለ የማይጠረቃ ድርጅቱን ያጠናክራል። ለምሳሌ በቅርብ ጊዜ ውዲህ የሃገር ውስጥ አስመጪዎችን ናላ አያዞረ ያልው የውጭ ምንዛሬ እጥረት የሃገሪቱን የንግድ ስርአት አደጋ ውስጥ ሲጥለው የህውሀት አባሎችና ጀሌዎቻቸው ግን ባንኮችን እንደ ግል ካዝናቸው ይጠቀማሉ። በጣም የሚገርመው ደግሞ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ነጋዴዎች አሰልቺ በሆነው የውጭ ምንዛሬ ወረፋ ለወራት ሲጉላሉ የባንኮች ገዥ ተብልው የሚሾሙት የህውሀት አሻንጉሊቶች በቲቪ እየቀረቡ የውጭ ምንዛሬ ሞልቶ ተርፉል ይላሉ።
ከሁሉም በላይ እጅግ በጣም የሚያስገርመው ደግሞ የዚህ የንግድ ጉዳት በሀገር ኢኮኖሚ እድገት ላይ የሚያመጣውን አደጋ ዞር ብለው ማስተዋል አለመቻላቸው ነው ። በቅርብ ጊዜ እንደሰማነው የህውሀት ማፊያ መንግስት ሲያያቸው ያላማሩትንና የወያኔ አባላት ያልሆኑትን በርካታ ድርጅቶች ታክስ አጭበርብራቹሀል ብሎ ሲከሳቸው ሰምተናል ሲጀመር ወያኔ ድርጅቶችን በታክስም ሆነ በአንፃር ህግ በመጣስ የመክሰስ የሞራል ሆነ የህሊና ብቃት የለውም። በርካታ የህውሀትና የጀሌዎቻቸው ድርጅቶች ታክስ በማጭበርበር ና ማሀበረሰቡን የሚጎዱ ምርቶችን ለገበያ እንደሚያቀርቡ እናቃለን። ለአብነት ያሀል ከወራት በፊት እንድ የህውሀት ጀሌ የባሀር ዳሩን ጊዎን ሆቴል በጥቂት ሺ ብሮች ኪራይ የግሉ እንዳረገው ሰምተን አዝነናል።
ህውሀት ወያኔ በየትኛውም መልኩ ቢሆን የሀገር መምራት ብቃት የሌለው የወንበዴዎች ስብስብ ነው የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን የወንበዴዎች ስብስብ የባሰ ችግር ውስጥ ሳይከተው ልጅ አዋቂ ሳይል ሆ ብሎ ተነስቶ ማስወገድ አልበት።
ሞት ለአምባገነኖች ኢትዮጵያችን ለዘላለም በክብር ትኑር!!!!!!!!
ሐውልቱ ሥር ሆኜ እነዚያን ሰማዕታት ሳስብ!
ክፍል.1
በላይ ማናዬ
ስድስት ኪሎ አደባባይ የካቲት-12 ሰማዕታት ሐውልት ሥር ሆኜ ያን ዘመንና የወቅቱን አሰቃቂ ድርጊት ባሰብኩ ጊዜ ስቅጠት ተሰማኝ፡፡ የቆመው ሐውልት ማንን ለመዘከር እንደተጀነነ ባወኩ ጊዜ ደግሞ አንገቴን ቀና አድርጌ እኔም እንደ ሐውልቱ መጀነን ከጀለኝ፡፡ እናማ ሐውልቱ ሥር ሆኜ….ስሜቴ ዝብርቅርቅ ነው፤ ቋንቋዬ ብዙ ነው፤ መንፈሴ ጠንካራ ሐዘኔ መራራ ነው፤ ምናቤ የኋሊት ጎታች ምኞቴ ወደ ፊት ሸምጣጭ ነው፤ ሐውልቱ ለኔ የውስጠቱን ይገልጥልኛል፤ ታሪኩን ይነግረኛል….የተጋድሎ ታሪክ ይተርክልኛል፡፡
እንዲህ እያለ….
የካቲት 12 ከመባቱ በፊት የአዲስ አበባ ነዋሪዎችና ሌሎች መምጣት ያለባቸውና መገኘት የሚችሉ ሁሉ በዚህ በስድስት ኪሎ እንዲሰባሰቡ ጥሪ ቀረበ፡፡ እምቢልታ ተነፋ፤ ስማ በለው ተለፈፈ፤ ነጋሪት ተጎሰመ፤ ጥሩምባ ከወዲህም ከወዲያም አምባረቀ፡፡ ጥሪውን የሰማው ወገን ሁሉ በዕለቱ ለት ከተተ፡፡ የጥሪው መነሻ ፋሽስት ጣሊያን ሀገራችንን ከሞላ ጎደል ድል አድርጋ አዲስ አበባ ላይ ከከተመች ወዲህ መሪ ነኝ ባዩ ማርሻል ሮዶልፍ ግራዚያኒ «ሰርግና ምላሽ» የሚያደርግ መሆኑ ነበር፡፡ በዕለቱ የሮማ መንግስት ልዕልና እና የልጇ ልደት የሚዘከርበትም ጭምር ነበር፡፡
እናም ህዝብ አዳሜ ስድስት ኪሎን በዕለተ ሚካኤል አጥለቀለቀው፡፡ ህጻኑ፣ አዛውንቱ፣ ወጣቱ፣ ቆነጃጅቱ፣ ባንድ ቦታ ታደመ፡፡ ግራዚያኒ በጠባቂዎቹ ታጅቦ ግብር ለማብላት የንግስናው መንበር ላይ ተቀመጠ፤ ሰገነቱ ላይ ተንቆራጠጠ፡፡ ነጭና ሐበሻ ድምበር ለይቶም ቢሆን ተቀራርቦ የበረታው ቆሞ፣ የደከመው ተቀምጦ ሁኔታውን ያጤን ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ፈረሰኞችም አለፍ አለፍ ብለው ይታያሉ፤ ባንዳዎችም ሲያሸረግዱ የጉድ ነበር፡፡
ሰርግና ምላሹ ተጀምሮ ጥቂት ነገሮች በሰላም ከሄዱ በኋላ አካባቢው ተረበሸ፤ ከዚያ በሗላማ….
* * *
ሐውልቱ ሥር ሆኜ ታሪኩን አጣጣምኩት፤ ወደ ህይወት መለስኩት፤ ጊዜውን ጎትቼ አሁን ላይ አጫወትኩት፡፡ እናም እነዚያ ወጣቶች በሐገር ፍቅር ሲነዱ አየኋቸው፤ የወገን ጥቃት ሲያንገበግባቸው ተመለከትኩ፤ አውጥተው አውርደው መክረው ዘክረው ስለወሰኑት ውሳኔ አሰላሰልኩ፡፡ ውሳኔያቸውን የሚተገብሩበት ሰዓት ሲደርስ ተሰማኝ፤ ኢትዮጵያዊነት ወኔያቸው ወደ ፊት ሲገፋቸው፤ እምቢ ለሀገሬ ብለው ሲሸልሉ በውስጣቸው ሰመጥኩ፡፡
ባቀዱት መሰረት ወደ ተሰበሰበው ህዝብ ዘልቀው ገቡ፤ የያዙትን ነገር ደብቀው ወደ ግራዚያኒ እና ጠባቂዎቻቸው በቻሉት መጠን ተጠጉ፤ የወራሪዎች ትዕቢትና ንቀት ካሰቡት በላይ የሆነ መሰላቸው፡፡ የተሰበሰበው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ያለበትን ስሜት አጤኑ፤ ከፋቸው! አዎ፣ ሀበሻ የበላይነት ተወስዶበታል፤ ችግረኛ ተምበርካኪ ሆኖ ታያቸው፡፡ በዱር በገደሉ ከወራሪው ጋር የሚፋለሙትን አርበኞችም አሰቧቸው፤ ልባቸው ደነደነ፡፡ በገጠር የሚፋለሙትን አርበኞች ማገዝ፣ መተባበር አለባቸው፡፡ ስለዚህም ያቀዱትን ሁሉ ዛሬ የካቲት 12 ቀን በግራዚያኒ ላይ መፈጸም አለባቸው፡፡
ሰዓቷ ደረሰች፤ የያዙትን የእጅ ቦምብ ፈቱት….ወደ ኢላማቸውም ሰነዘሩት! ግ…ር!….ሽብ..ር…..ሽብርብር! ምስቅልቅል! የድርጊቱ ፈጻሚዎች ወዲያውኑ አካባቢውን ከግርግሩ መሐል ገብተው በመሹለክለክ ተሰናበቱ፡፡ ግራዚያኒ በጥቃቱ ቆስሎ ተንገዳገደ፤ ጠባቂዎች ተረባበሹ፣ ቆሰሉ፣ ሞቱ…የአለቃቸው መጎዳትም ጎዳቸው፡፡
ግራዚያኒ ትዕዛዝ አስተላለፈ፤ «ይሄን ሐበሻ በሉት፤ እረዱት!!»
ወዲያው የፋሽስት ሰይፍ ተመዘዘ፡፡ የሚካኤል ሰይፍ ግን ተጠቂዎችን ለማዳን ሰገባውን ሾልኮ አልወጣም ነበር፤ የካቲት 12…ዕለተ ምካኤል በአዲስ አበባ መርገምት ወረደ፡፡ ውጥንቅጡ የወጣ ነገር….. የህጻናት ዋይታ…የእናት እሪታ…..የባንዳ ሽለላ…..የፋሽስት ጥይት ጨኸት….የአዛውንቶች እግዚኦ…..የእግሬ አውጭኝ ሩጫ…..የታጣቂ ጡጫ….የፈረሶች ርግጫ….የቀሳውስት ከንቱ ምልጃ…..የቆነጃጅት መቅበዝበዝ…..የጎልማሶችና ጎበዛዝት መደንዘዝ…ኦህ! ያማል!
የደም ጎርፍ….የተቀላ አንገት….የተቦደሰ ታፋ…..የተጎለጎለ አንጀት….የተቆረጠ እጅ…..የታረደ ጉሮሮ….የተገመሰ ጭንቅላት…..የተቆራረጠ ጣት…..የሚያቃስቱ ነፍሳት…..የተጋደመ ሬሳ….የተነባበረ የሰው ልጅ ክምር…..የአልሞት ባይ ተጋዳይ ትንቅንቅ…..የውስጥ አርበኞች ሽምቅ…..በደም ስካር….በግዳይ ሽለላ….ተጨማሪ ነፍሳትን ለመንጠቅ መታተር….ሐበሻን የመጨረስ ሩጫ…..እድሜ፣ ዖታ፣ እቴ…አባቴ ሳይሉ በያዙት መሳሪያ ማንከት….መሰየፍ….መቀልጠም….መረሸን…..አቤት ጭካኔ!! አቤት የግራዚያኒ ጭካኔ! አቤት አረመኔነት!
የሺዎች ጩኸት፣ የሺዎች ዋይታ፣ የሺዎች መሰዋት፣ የሺዎች እልቂት….መች በዚህ አበቃ፡፡ ግራዚያኒ ህክምናውን ተከታተለ፤ ሐበሻ ግን ጥራሞቱ እየተደመጠ፣ ማቃሰቱ እየታዬ፣ እስትንፋሱ እየተፈተሸ እንዲጨረስ ተደረገ፡፡ ግራዚያኒ እልቂቱን ባዬ ጊዜ ደስ አለው፤ እርካታ ሊያገኝ ግን አልቻለም፡፡ ስለዚህም ጭፍጨፋው ለሶስት ቀናት እንዲቀጥል አዘዘ፤ ገዳማት እንዲወድሙ መመሪያ ሰጠ፡፡
አዲስ አበባ በደም ጨቀየች፡፡ ስድስት ኪሎ በደም ጎርፍ ተጥለቀለቀች፡፡ ኢትዮጵያ ወገቧን በገመድ አስራ አዘነች፤ እምምም ብላ ወደ ፈጣሪ ተመለከተች፤ አንገቷን ከመድፋት ይልቅ ቀና ብላ ፈጣሪ ያለበትን ሰማየ ሰማያት አየች፡፡ ፋሽስትም አንገት ከመድፋት ይልቅ ቀና ማለትን የሐበሻ ይትብሓል ባዬ ጊዜ ፍርሃት ናጠው፤ የሀበሾች ንግርት ‘ስታጠቃኝ ጠንክሬ እዋጋሃለሁ’ የሚል ሆነበት፡፡ አርበኞችን ባሰበ ጊዜ የእንሺርት ውሃው ፈሰሰ፡፡
እነዚያን ጥቃት ፈጻሚ ወጣቶች ክፉኛ ኮነናቸው፤ የሮማን ሃያልነት መቀበል አንሻም ብለው «ኢትዮጵያ!!» ያሉትን ጀግኖች በአዕምሮው አመላልሶ አያቸው፡፡ የምር ቆራጦች ናቸው! የምር አርበኞች ናቸው! የምር ኢትዮጵያዊያን ናቸው! የምር አድዋ ላይ የግራዚያኒን አባቶች ያንበረከኩት ልጆች ናቸው!
ግራዚያኒ ስለነዚህ ወጣቶች በቀል በአዲስ አበባ ያደረገውን ተዘዋውሮ ተመለከተ፤ በእብሪት የተሞላው ልቡ ቅንጣት ታህል ሀዘን አልተሰማውም፤ እንዲያውም «በግዳዩ» ላይ በንቀት ምራቁን ጢቅ አደረገ፡፡ በሰማዕታት በድን ላይ በመኮፈስ ተራመደ፡፡
ግራዚያኒ የመግደል ሙከራ የተደረገበትን ስድስት ኪሎ ተመለከተ፡፡ የሬሳ መዓት አንዱ በአንዱ ላይ ተነባብሯል፤ እናት ልጇን እንደያዘች ባፍጢሟ ተደፍታለች፤ ጎልማሶች እጆቻቸውን ለጡጫ እንደጨበጡ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ተጋድመዋል፡፡ ግራዚያኒ እነዚህን መሰል ሬሳዎች ሲያይ እንደገና ደም ደም ይሸተዋል፡፡ ትንሽ አለፍ ሲል ደግሞ ሽለላ ላይ የነበሩ አዛውንቶች አፋቸውን ከፍተው ወድቀዋል፤ «አድዋ!!» ሲሉ እንደነበር እያሰበ በንዴት ይተክናል፡፡
ግራዚያኒ የባንዳ ሬሳ ሲመለከት ብቻ ሳቁ ይመጣበታል፤ እንዴት እርስ በእርሳቸው እንዳገዳደላቸው እያሰበ ይረካል፤ ባንዳዎች ሀገራቸውንና ወገናቸውን ከድተው ለሱ በማደራቸው ይንቃቸዋል፤ ፍርፋሪ ለመለቃቀም ሲሉ ከጎኑ ስለሆኑ ከሰውነት ተራ ያስወጣቸዋል፤ ጀግንነታቸው የፈሪ ጀግንነት እንደሆነ አድርጎ ያስባቸዋል፤ በህይወት ባሉ ባንዳዎች ዘንድም ትዝብት ያሳድርባቸዋል፡፡
ዋ አረመኔው ግራዚያኒ!…..ስንቱን ጦስ ይዘህ መጥተህ ነበር! በሶስት ቀናት ብቻ በአዲስ አበባ ከተማ 30,000 ንጹሐን ተጨፈጨፉ፤ በታሪካዊው ደብረ ሊባኖስ ገዳም ያሉ መነኮሳት ተረሸኑ፤ ቤተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፤ መኖሪያ ቤቶች ፈርሰዋል፡፡ ዋ አረመኔው ግራዚያኒ!
* * *
ሐውልቱ ስር ሆኜ ያስታወስኩት ይህን ብቻ አልነበረም፤ ስለ የካቲት 12 ቀን፣ ስለነዚያ ወጣቶች እና ስለ ሌሎች የታሪኩ ተዋናዮችም ሳውጠነጥን ነበር፡፡ እነዚያ ወጣቶች ያልኩህ አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስግዶምን ነው፡፡ በቀጣይ ስለነዚህ ወጣቶችና በዙሪያቸው ስለነበሩ የአርበኝነት ተጋድሎው አጋሮች እናወሳለን፡፡ ከዚያ በፊት ግን የሐውልቱን ምስክርነት የሰማዕታቱን ሞገስ ስድስት ኪሎ ተገኝተህ ጎብኝ፡፡
እነዚያ ወጣቶች ጋር በቀጣይ እንገናኝ፡፡
ምንጭ ፦semayawiparty.org
ተራ ኢትዮጵያዊ መሆናችንን አንናቀው ! ግርማ ካሳ
አገሬን ለቅቄ ስደት የጀመርኩት በ1984 ነዉ። ኢሕአዴግ ስልጣን በጨበጠ በአንድ አመቱ። ከአስራ አራት አመታት በኋላ ለአንድ ወር ጉብኘት ቦሌን ረገጥኩ። እሑድ ቀን ፣ ግንብት ሰባት 1997 ነበር።
ከዚያ በፊት ብዙም የፖለቲካን ነገር አልከታተለም ነበር። ምርጫ እንደሚደረግ፣ ቅንጅት ሕብረት እየተባለ የምርጫዉ ዘምቻ እንደተጧጧፈ ያወኩት ትኬት ከቆረጥኩ በኋላ፣ ከምርጫዉ 15 ቀናት በፊት ነበር። በአጭሩ አባባል፣ በአገሬ ዉስጥ እየተደረገ ከነበረዉ ሁኔታ የተለየዉ፣ ዲስኮንቴክትድ የሆነ ነበርኩ ማለት ይቻላል።
በወቅቱ የነበረዊ አንጻራዊ ዴሞክራሲ አስደሰተኝ። ቅንጅት አዲስ አበባን ሙሉ ለሙሉ አሸነፈ። ከሌሎች ቦታዎች የሚመጡም ዉጤቶች ቅንጅቶችን የሚያስደስት ነበሩ። በዚህ ጊዜ ችግሮች መፈጠር ጀመሩ። ኮሮጆ መቀየር የመሳሰሉት። አገሪቷ ወደ ቀውስ መግባት ጀመረች።በየቀኑ ጋዜጦችን እገዛለሁ። (አዲስ ዘመንን ግን ገዝቼ አላወቅም) የምወዳት ቡና ቤት ነበረች። ካፌ ማሩ ትባላለች። ቡናዬን ይዤ ጋዜጦችን አነባለሁ። አንድ ቀን እንደለመድኩት ገዝቼ ሳገላብጥ፣ ሁሉም የአንዲት ሴት ልጅን ፎቶ፣ በትልቁ አውጥተዋል። በቆምኩበት እንባ ይፈሰኝ ጀመር።
የአሥራ ስድስት አመት ወጣት ነበረች። በኮተቤ አካባቢ በተነሳዉ ሕዝባዊ ሰላማዊ ተቃዉሞ፣ ከኢሕአዴግ ታጣቂዎች በተተኮሰ ጥይቅ ተመታ የወደቀች። ሽብሬ ደሳለኝ ትባላለች። የዘጠና ሰባቱ ምርጫ የመጀመሪያዋ ሰላባ። ይሄን ጊዜ የ23 አመት ሴት፣ ምናልባትም የልጅ እናት ትሆን ነበር። ሽብሬን መቼም ቢሆን አልረሳትም። ስምንት አመት ቢሆነኡም፣ በርሷ ላይ የተፈጸመው፣ ትላንት እንደተፈጸመ አድርጌ ነዉ አሁን የማስበው።
ጋዜጦቹን አንብቤ እንደጨርስኩ፣ ወደ ሜክሲኮ በእግሬ አመራሁ። ሌላ አስደንጋጭና አሳዛኝ ክስተት የዚያኑ ቀን አጋጠመኝ። ነጭ መስታወት ቢጤ በፊታቸው ባደረጉ ፖሊሶች፣ የተግባረ እድ ተማሪዎች ይደበደቡ ነበር። በሰደፍ ሲመቷቸው በአይኔ በብረቱ ተመለከትኩ። ዉስጤ ተቆጣ። «እንዴት ዜጎች በአገራችዉ እንደ ከብት ይደበደባሉ ? » አልኩ። ያኔ ወሰንኩኝ።
እርግጥ ነዉ፣ እኔ ላይ የደረሰብኝ ነገር የለም። በአሜሪካን የስደት ኑሮ ጀምሬ፣ በሁሉ መስክ ደህና ሁኔታ ላይ ነዉ ያለሁት። እግዚአብሄር ይመስገን። ነገር ግን አሜሪካ እና ኢትዮጵያ አንድ ስላልሆኑ፣ በኢኮኖሚ እንደ እኔ ለምን አይሆንም ባልልም፣ እኔ እንደ ኢሚግራት በአሜሪካን አገር ያለኝን መብትና ዲግኒቲ፣ ጥቂቷን እንኳን ወገኖቼ በአገራቸው ማጣቸውን ሳሰበዉ ዉስጤ ቆሰለ። ያንንም መቀበል ከበደኝ። ኢትዮጵያ ዉስጥ የሰብአዊ መብት እንዲከበር ፣ ዜጎችን የመደብደብ፣ የማሰር፣ የማፈናቀል ተግብራት እንዲወገዱ፣ ዉጤት ያምጣም አያምጣም፣ ማድረግ ያለብኝ ሁኑ ለማድረግ ወንንኩ። ለራሴ ቃል ገባሁ።
በብዙ ሺሆች እንደሚቆጠሩ የቅንጅት ደግፊዎች፣ እኔም የቅንጅት ድጋፍ ማህበራትን ተቀላቀልኩ። ምርጫ ቦርድን በመጠቀም፣ የ«ቅንጅት» ሕጋዊ ስም ለነ አየለ ጫሚሶ ቡድን ፣ ገዢው ፓርቲ በመስጠቱ፣ ቅንጅቶች በቅንጅት ስም መንቀሳቀስ ስላልቻሉ «አንድነት» የሚል ስም ይዘው ትግሉን ቀጠሉ። የቅንጅት ድጋፍ ማሀብራትም ወደ አንድነት ድጋፍ ማህበራት ተቀየሩ። የቅንጅት ወራሽ የሚባለዉን አንድነትም መደገፍ ቀጠልን።
የአንድነት ፓርቲን በመደገፍ የማደርጋቸውን አንዳንድ ተግባራት የታዘበ፣ ቅንጅትን ይደገፍ የነበረ አንድ ወዳጄ «ተቃዋምዊዎች የሚረቡ አይደሉም። ለምን ጊዜህን በነርሱ ላይ ታጠፋለህ ? ያኔ ስትደክመለት የነበረዉ ቅንጅት እንኳን ፈራርሶ የለም እንዴ ? » አለኝ።
ይህ አባባል ብዙዎች የሚሉት አባባል ነዉ። ብዙ ጊዜም ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ እንዲህ አይነት አስተያየቶች አንብቢያለሁ። «ቅንጅት ፈርሷል» የሚለዉን አባባል ግን በጭራሽ አልቀበለም። የቅንጅት ስም ላይኖር ይችላል። አሁን «ቅንጅት» ላንል እንችላለን። ያኔ የቅንጅት መሪ የነበሩ፣ ያኔ በነበሩበት ሁኔታ ላይኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን ያኔ ቅንጅትን ቅንጅት ያሰኘው፣ ከምርጫ ቦርድ የተገኘ ስም፣ ወይንም መሪዎቹ አለነበሩም። ሕዝቡ ለነጻነት፣ ለዴሞክራሲ፣ ለሰብአዊ መብት መከበርና ለኢትዮጵያዊነት የነበረዉን ግለትና ጥማት ማመላከቱ እንጂ። የቅንጅት ነገር፣ በዋናነተና በቀዳሚነት የተገናኘዉ ከሕዝብ ጋር ነበር። ስለዚህ «ቅንጅት ፈርሷ”» ማለት «ሕዝብ ተመችቶታል፤ ሕዝብ ደልቶታል፣ ሕዝቡ መብቱ ተከበሮለታል …. » እንደማለት ነዉ።
አሁንም የሕዝቡ ጥያቄ ያኔ የነበረዉ ጥያቄ ነዉ። አሁንም ህዝብ «የፍትህ ያለ ፣ የሰላም ያለህ፣ የሕግ በለያነት ያለህ፣ የመልካም አስተዳደር ያለህ» እያለ ነዉ። አሁን ሕዝብ «የዘር ፖለቲክ አልፈለግም፣ ኑሮ ተወደደ፣ ቀንበር በዛብኝ ፥» እያለ ነዉ።
ለምሳሌ ያኔ በቅንጅት ስም ይደረግ የነበረዉ እንቅስቃሴ አይነት፣ በሚሊዮኖች ለነጻነት ድምጽ በሚል እንቅስቃሴ ሥር ኢትዮጵያ ዉስጥ እየተፋፋመ ነዉ። የአንድነት ፓርቲ እና መኢአድ በባህር ዳር ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ጠርተዋል። የሚሊየምም ድምጽ ለነጻነት ክፍል ሁለት በቅርቡ ይታወጃል ተብሎ ይጠበቃል። መርሳት የሌለብን ደግሞ፣ እነዚህ አገር ቤት ያሉ ወገኖቻችን፣ ይህን አይነት እንቅስቃሴ የሚያደርጉት፣ እየታሰሩ፣ እየተደበደቡ፣ ከሥራቸው እየተባረሩ ወዘተረፈ ነዉ። ፈረንጆች እንደሚሉት፣ “They are not talking the talk; they are walking the walk”::
ያኔ ቅንጅትን ስንደገፍ የነበርን፣ በጥቂት መሪዎች ስህተት፣ ተስፋ ቆርጠን ፣ ኢሕአዴግን እንደ ግዙፍና የማይነቃነቅ አድርገን ማየት የጀመርን፣ ከትግሎ ጎራ የሸሸን በጣም ብዙ ነን። ትግሉን የጎዱ፣ የሕዝቡን ኃይል አሳንሰው፣ ተስፋቸዉን በሌሎች አገሮች ላይ የጣሉ ግለሰቦችንና የፖለቲክ መሪዎች ላይ በማተኮር ወደ፣ ወደ ኋላ የተጎተትን ብዙ ነን። ነገር ግን ዋጋ እየከፈሉ ያሉትን፣ እነ እስክንደር ነጋ፣ አንዱዋለም አራጌ፣ ርዮት አለሙ፣ ናትናኤል መኮንን የመሳሉትን እናስብ እላለሁ። ተስፋ መቁረጥ፣ በቀላሉ አቅጣጫችንን መቀየር፣ ሌሎችን ደካም ማለት፣ እጅ አጣምሮ እያወሩ መቀመጥ ቀላል ነዉ። የአላማ ጽናት ኖሮ፣ የደከሙትን እያገዙ፣ የሥራ ሰው መሆን ግን ከባድ ነዉ።
እንግዲህ በቅንጅት ወቅት አኩሪና ትልቅ ሥራ እንሰራ ለነበርን፣ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቼ፣ እንደገና ጽናቱ ይኖረን ዘንድ፣ አክብሮት የተሞላበትን ጥሪዬን አቀርባለሁ። «አንተ ምንድን ነህና ነው እንደዚህ አይነት ጥሪ የምታቀርበው ? ልትሉኝ ትችላላችሁ። አዋ የፖለቲካ ፓርቲ መሪ ወይንም የአንድ ድርጅት ሃላፊ አይደለሁም። እንደ ማናችሁም ፣ አንድ ተራ ኢትዮጵያዊ ነኝ። ነገር ግን አንድ ነገር አውቃለሁ። እንደኔና እንዴናናት ያሉ ተራ ኢትዮጵያዉያኖች ናቸው ለኢትዮጵያ መፍትሄ የሚሆኑት። በዳያስፖራ ያሉ በሜዲያዉ የምናያቸውና የምንሰማችደው ጥቂት የታወቁ ሰዎች ሳይሆን፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተራ ኢትዮጵያዉያን ሲንቀሳቀሱ ነው የኢትዮጵያን ትንሳኤ ማወጅ የምንችለው።
ዉድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፣ ወደ ቀድሞዉ ቦታችን ተመልሰን፣ ከስሜትና ከጥላቻ በጸዳ መልኩ፣ ሕዝባችን መብቱ እንዲከበር የሚያደርገዉን ትግል እንደገፍ። ከሚሊዮኖች አንዱ እንሁን !
የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት እንቅስቃሴ ፌስቡክ ላይክ በማድረግ፣ እየተሰራ ያለዉን ነገር ይከታተሉ። የአንድነት ድህረ ገጽን በመጎብኝት የገንዘብ ፣ የሃሳብ ድጋፎዎትን ያበርክቱ።
https://www.facebook.com/MillionsOfVoicesForFreedomUdj
http://www.andinet.org/
የአውሮፕላን ጠለፋውና የኢህአዴግ ማአከላዊ ኮሚቴ አስቸኳይ ስብሰባ (አጭር ወግ)
የኢህአዴግ አመራሮች ለአስቸኳይ ጉዳይ ቤተመንግስት ተጠርተዋል:: ሊቀመንበሩን የስብሰባውን አጀንዳ መናገር ጀመሩ::
እንደምታውቁት መጪው 2007 የምርጫ ጊዜ ነው:: እና ጠላቶቻችን ከአሁኑ ምርጫው ; ፓርቲው እና አገሪትዋ ላይ አደጋ ለማድረስ እየሞከሩ ነው:: ለዛ ምሳሌ የሚሆነው እና ዛሬ የተሰበብንበት ምክንያት ትላንት የተጨናገፈው የአውሮፕላን ጠለፋ ነው:: ፓርቲያችን እንደ ትላንት አይነቱ ጸረ-ልማት የሆነ ተመሳሳይ ተግባር እንዳይፈጸም ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት:: ለዚህም አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ይጠበቅብናል::
በእዚህ አጀንዳ ላይ ያላችሁን አስተያየት ስጡና እንወያይበት::
አንዱ አመራር እጁን አወጣ:: እንዲናገርም ተፈቀደለት::
<<ሁሉም የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ጋር ፌዴራል ፖሊስ መመደብ አለበት:: ለሚኒባስ ታክሲ አንድ ;ለአውቶቡስ ሁለት ከፊት እና ከኋላ ይመደብ:: ምንም እንኳን ኢኮኖሚ ው የሚጎዳ ቢሆንም መጪው ምርጫ ላይ ፈጽሞ አደጋ እንዲጋለጥ መፍቀድ የለብንም::>>
እሱ ተናግሮ እንዳበቃ ሌላኛው እጁን አወጣ::
<<ይሄ የጠለፋ ተግባር ጥልቅ ምርመራ ያስፈልገዋል:: የጠለፋ ወንጀል ጉዳቱ የከፋ ነው:: ለዚህ አደገኛ የአሽባሪዎች ስራ ሊጋለጡ የሚችሉ የህብረተስብ አካላቶችን ለይተን ማውጣት አለብን:: ከዚህ ቀደም በሌላ የጠለፋ ወንጀል እንዲሁም ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ፖሊስ የቅርብ ክትትል ሊያደርግባቸው ይገባል:: ሴት የጠለፉ ; ሊጠልፉ ሲሉ የተያዙ ; ወይም የሴት ጠለፋቸው የከሸፈባቸው ሰዎች ፖሊስ የትኩረቱ አካላት ያድርጋቸው:: ጠለፋ እንደሌሎች ወንጀሎች ተዛማጅ ነው:: ከዚህም አንጻር የሀገር ቀሚስ ጠለፋ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ለሴት ጠለፋ ወንጀል የተጋለጡ እንደሆነ ከዚህ በፊት የተደረገ ጥናት ያሳያል:: ስለዚህም ፖሊስ ጨርቆስ እና ሽሮሜዳ አካባቢ ያሉ ጥልፍ እና ቀሚስ ጠላፊዎችን ትኩረት ቢያደርግባቸው ክፋት ያለበት አይመስለኝም:: ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ እንዲሉ ለጠለፋ የሚያጋልጡ ቀዳዳዎች ን ሁሉ መድፈን አለብን::>>
ሌላኛው ቀጠለ
<<ፓርላማው አሸባሪ ተብሎ ከፈረጃቸው ከእነ ግንቦት ሰባት እና አል-ሸባብ በተጨማሪ ጠላፊዎችን መጨመር ይጠበቅበታል:: ለዚህም ህግ አርቃቂው ኮሚቴ ህጉን እንዲያሻሽል ይደረግ::>>
ሌላኛው አከለ
<<ለጥንቃቄ ያህል ከእንግዲህ አይሮፕላኖቻችንን ማብረር ያለባቸው የፓርቲ አባላቶች ብቻ መሆን አለባቸው::በተለይ ከፍተኛ ባለስልጣኖች የሚጓዙበት አይሮፕላኖች በታማኝ አባሎቻችን መሆን አለባቸው:: አባል ያልሆኑ ፓይለቶች ሆኑ ኮፓይለቶች እንዲሁም ሆስተሶች አባል የሚሆኑበት መንገድ ይመቻች:: አድር ባይ እና ኪራይ ሰብሳቢ ያልሆኑ ሀቀኛ የአይሮፕላን ሰራተኞች ማፍራት ይጠበቅብናል:: አባል መሆን የማይፈልጉ ወይም ተቃዋሚ ፓርቲን የመደገፍ ዝንባሌ የሚያሳዩ ሰራተኞች ከስራቸው መሰናበት አለባቸው:: በምትኩም ታማኝ እና አንጋፋ አባሎቻችን የማብረር ትምህርቱ ተሰጥቷቸው ስራውን እንዲቀላቀሉ ይደረግ::>>
ሌላኛው የህወሃት አመራር እንዲህ አለ
<<ይሔ ጠለፋ የተካሄደው በጠላቶቻችን የተቀነባበረ ሴራ ነው:: ለካቲት 11ን የትግራይ ህዝብ እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በደስታ እንዳያከብር ለማድረግ ሆን ተብሎ የታሰበ ስለሆነ የህውሃት አባላት እና ደጋፊዎች እንዲሁም የብአዴን ; ኦህዴድ እና ድህአዴግ እንዲሁም አጋር ፓርቲዎች ጠለፋውን የሚያወግዝ ሰልፍ ህዝቡ እንዲወጣ የተለመደውን ቅስቀሳ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል::>> አለ
በስብሰባው መጨረሻ ፓርቲው ጠለፋውን የሚያወግዝ ጽሁፍ አውጥቶ እና ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ ላይ በመወሰን አምራሩ ተበተነ::
በነጋታውም በከተማው የታክሲ እና አውቶቡስ ተሳፋሪ መጫኛ እና ማውረጃ ቦታዎች ላይ የፌዴራል ፖሊሶች ተመድበው ተሳፋሪው ጥብቅ ፍተሻ እየተደረገበት መሳፈር እና መውረድ ጀመረ::
(የአውሮፕላኑ ጉዳይ) ምንድን ነው ኩራት?
ከሥርጉተ ሥላሴ (ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ)
ዘጠና ደቂቃ በኢንተቤ በሚል እርስ በታዋቂው ጸሐፊ ማሞ ውድነህ የተተረጎመ አንድ የእውነት መጸሐፍ በልጅነቴ ማንበቤን አስታውሳለሁ። ግን በጣም በተደራጀና በርካታ ጉዳዮችም በቅንብር የተከወነበት ነበር። ዛሬ ደግሞ በአንድ ዕጣ ነፍስ ቀንበጥ እጅግ የተጠና የታቀደ የቀደመ ሥልጡን ተግባር ተከወነ። ትውልዱና ታሪኩ በአዲስ መልክ አዲስ ምዕራፍ ከፈቱ። ለእኔ ኩራት ማለት የወገንን ጥቃት በረቀቀ ግን በታቀደ በተረጋጋ መንፈስ የሚከወን ተግባርን ነው።
እርግጥ ሌትና ቀን ወያኔና አጃቢዎቹ ተደናብረዋል። የኢትዮጵያ አዬር መንገድ ክብር፤ ዝናና ታሪክ ጎደፈ ሲሉም ይደማጣሉ። ኩራትና ዘረፋ ቀረ አይነት። መጀመሪያ ነገር አይደለም የኢትዮጵያ አዬር መንገድ ኢትዮጵያ ከነሙሉ አካሏ አለችን? የትናንት የኩራት የነፃነት አንባ አይደለም ለእኛ ለጥቁር ህዝብ አርማ የነበረችው ሀገራችን ከነሙሉ ወርድና ቁመናዋ አሉን? ለእኔ የለችም ነው የምለው። ….. ይህቺ ናት እኮ ኢትዮጵያ ስንት ጊዜ ቀዶ ጥገና ያደረጋላት ወያኔ …. ያፈረሳት፤ እንደ ሰንጋ ለባዕዳን ያቀራመታት። ባህሏም፤ ታሪኳም፤ ጥሪቷም፤ ቅርሷም፤ የዕምነት ሥርዓተ ህግጋቷም፤ ህይወቷም ጠረናቸው የተበከለ ሆነው ከእኛነታችን ውስጥ እንዲፋቁ መርዝ የነሰነሰባት። ባዕዳን ሲገቡ ከነሁለመናቸው ነው። ለጆሮ ከሚዘገንኑ ልማዳቸው ጋር …. በቻይና ሃብታሞቹ ምን እንደሚበሉ ታውቃላችሁ? በልጅነታችሁ ሲተረትላችሁ የነበረውን የጭራቅ ታሪክ እሰቡት …. ይቀፋል ….
በወያኔ – ትራፊ በሰልፍ የሚጠበቅባት፤ ሚሊዮን የነገ ፍሬዎች ነገ ሳይመጣ ተስፋቸው ደርቆ እራብ እዬቆላቸው የሚያልቁባት። ሊለምኑ ያፈሩ ሚሊዮኖች እንደ ተዘጋባቸው የሚያልፉባት። ህጻናት እንደ አወጡ ለንግድ ጨረታ የወጡባት፤ ሴት ታዳጊ ወጣት ደመ ከልብ ሆነው አረብ ሀገር ተደፍረውና ተዋርደው የሚቀቀሉባት፤ ሀገር ውስጥ ያለው ወጣት በቤንዚን አርከፍክፎ እራሱን የሚያቃጥልባት፤ ታንቆ ወንዝ ገብቶ የሚሞትባት፤ በዘሩ በሃይማኖቶ እዬተለቀሙ ዕልፎች ከሥራ ገበታቸው የሚባረሩባት የዕንባ ባዕት … ለእለት ጉሮሮ፤ ለመጠለያና ለከፈን ያልተበቃባት።
አዬሩ የስጋት ዓውድ ያፈናት፤ ስደት ከሃይማኖት አባቶች ጀምሮ በፆም በጸሎት የሚናፈቅባት፤ ሰው በነፃ ቤቱ በሰላይ ታፍኖ የሚኖሩባት የረመጥ ሀገር እኮ ናት ኢትዮጵያ ዛሬ። መሬቷ ለነገ ሳይታሰብ ተሸጦ በኬሚካል የሚቃጠልባት ኖሪዎቿ እዬተፈናቀሉ ባለቤት አልባ የትም የሚበተኑባት፤ ህጻናት ወላጅ አልባ የሚቀሩባት እኮ ናት ዛሬ እናት ሀገር። የሰው ልጅ በአስተሳቡ የሰበውን ያለመውን እንዳይናገር ጉሮሮውን የተዘጋበት መንፈሱ የተቆለፈባት ወጥቶ ለመግባት ማስተማመኛ የሌለበት፤ የክትና የዘወትር የሚለይባት፤ ለዘመንተኞች ገነት ለብዙኃኑ ሲኦል የሆነች ሀገር እኮ ናት።
በደም በአጥንት በክብር የተከበረች ሀገር ለውጪ ኃይል ለገጸ በረከት የተሸለመች ሀገር ሆና … እንዴት ኩራት ይታሰባል?
ይህ ያንገፈገፈው የመረረው የዘገነነው ወጣት እንሆ ቆረጠ ወሰነ አደረገውም። ገድል ነው። ብቻውን ከሀገርም ሲዊዘርላንድ መረጠ – ረቂቅ። በተረጋጋ መንፈስ ሳይታወክ ፍላጎቱን በጥቂት ቃላት ብቻ ልብን እንደ ቅል አንጠልጥሎ ገለጸ። ምንም ዓይነት አይደለም የድርጊት የቃል እንኳን ግድፈት ሳይኖርበት። ምንም አይነት የቅድመ ሁኔታ ድርድር ሳይጠይቅ፤ እጅግ በቀደመ ጨዋነት ለሚሊዮኖች እራሱን ሰጠ። በቃ! ፍቅር ይሏችኋል ይህ ነው! ኩራትም ይሏችኋል ይህ ነው! ጀግንነትም ይሏችኋል ይህ ነው! የእናት ሀገር ጥሪ ከሰማያተ ሰማያት ፈቅዶ ተቀበለ። የተሳካ በፍጹም ሁኔታ የተሳካ ድርጊትም እንሆ ከወነ። በድርብ አንጎል። ሌላው ወያኔ ሊደበቅበት የሚገባው ጉዳይ ለኣለም ድንቅ ትምህርት ቤት የሆነው አዬር መንገዳችን የትውስት ዋና አብራሪ ሲኖረው ይህ ነው ታላቁ ውርዴት ለወያኔ … ይህን የመሰለ ጭንቅላት ያለው ወጣት ረዳት፤ ጣሊያናዊ አብራሪ ዋና …. ዓለም ከሃቅ ጋር እስኪ ይፋጠጥ ….
ትውልዱ ይህን ይመስላል ወያኔ ቢማርበት። 40 ዓመት የደከመበት መና ከንቱ መቅረቱን። ዛሬም እናት ጀግና ትወልዳለች። ዛሬም ኢትዮጵያዊነት ግብግብ ቅጥል ርምጥምጥ የሚያደረገው አርበኛ እንዲህ በልበ ሙሉነት ሙያ በልብን ከውኖ ገዢ መሬቱን ካለምንም ብክነት የሚቆጣጠር ቀንዲል ትወልዳለች አምላኳ አልረሳትም እና።
ዓለም ፊቱን አዞረ፤ ሰንደቃቸውን እንደ ለሰበሱ በትቢተኛው ሳውዲ አደባባይ ወገኖቻችን ደማቸው ሲንዶለዶል ሚዲያው ሁሉ ዘጋን፤ እኮ ታምረኛውን አምላክ አዘጋጅቶ ኖሮ ዛሬ አንደበታቸውን አስከፈተ። ጀግናው አብራሪ ኃይለመድህን አበራ ተገኘ በክፉ ቀኗ ለእናት ሀገሩ የተገኘ የቁርጥ ቀን ልጅ። ሥሙ እራሱ ሥም ነው።
እኛ ስለ እስራቱ፣ ስለነገ ህይወቱ ተጨንቀን ይሆናል። እሱ ግን ሁሉንም ዓይነት መስዋዕትነት ለመቀበል አውቆ የቆረጠ የወሰነ ምርጥ ዘር ነው። ቀደምቶቹ – አብርኃም ደቦጭ፤ ሞገስ አስገዶም፤ አብዲሳ አጋ፤ ኃይለማርያም ማሞ፤ በላይ ዘላቀ፤ ዘርአይ ደረስ – ተፈጠሩ። ዳግም ተነሱ። የትንሳኤ መግቢያ ዋዜማ …..
በተጓዦች ዘንድ አንድም የመንፈስ ቅንጣት ጭንቀት ሳይፈጠረ፤ በረቀቀ ጥበብ በአውሮፕላኑ ድንበር ወስጥ ሳይሆን ከዛ ውጪ በሆነ ሁኔታ በመስኮት የላቀ ትዕይንት …. ፈጸመ። በሰለጠነው አለም ቢሆን ስንት ኪኖ ያሰራ ይሆን ይህ ታዕምር? …. ይህን የዘመናችን አዲስ ትውልድ እኮ ለመተርጎም የሰማይ ጸጋ ይጠይቃል አባቶቼ ያመሳጥሩት እኔስ አቅም የለኝም።
አጓጒ ሂደቱ ልብን እንደ አንጠለጠለ ይቀጥላል። የተረጋጋችውም ሲዊዝም ሰከን ብላ ለየት ባሉ ህጎቿና ተፍጥሯዋ ትንሽ በትንሽ እያቃመሰች የኢትዮጵያን መከራ ፈተና ስቃይና ዕንባ በዓለም አደባባይ ታስፈትሻለች ….
በጀግናው ፊት ለፊት በጎኑ በስተኋላው ያለው ነፃነት የናፈቃት እናት ሀገሩና የፈጠረው አምላኩ ደግሞ ከመቼውም በላይ ጥበቃቸው አይለዩትም። ሲፈጠር የተቀባበትን ጸጋ ነው የፈጸመው አትርፏል። ትርፉ 150% ነው። እነሱ ዋስ ጠበቃ ይሆኑታል። በእኛ በኩል ደግሞ ለዚህ ለላቀ መስዋዕትነቱ እኛ ነፍስ ያለው ጠበቃ አቁመን መሟገት። የጠነከረ ተከታታይነት ያለው የሎቢ ተግባር መሰራት። ለምናውቃቸው ሁሉ የኢትዮጵያን መከራና ሰቀቀን እስካሁን ድረስ በኣለም ዐቀፍ ሰብዕዊ መብት ድርጅቶች የተዘገቡትን ሪፖርቶችን ሊንኮችን እያሰባሰብን መላክ። ከጎኖ መቆም ያስፈልጋል። አብሶ በእንግሊዘኛ ቋንቋ አጫጭር ጹሑፎች በምልሰት በደሎች እዬተቃኙ ማቅረብለወቅቱ ተስማሚዎች ይመስሉኛል።
ዜግነት እንዲህ ሲያምርበት፤ እንዲህ በድርጊት በጥበብ ልቆ ባለማዕረግ ሲሆን ከማዬት በላይ ምን ሐሴት አለ?! የጉዞ አቅጣጫ ካለምንም የሰው ህይወት ጥፋትና ንብረት እንዲሁም ወድምት መሆኑስ አይገርምም! በሌላ በኩል ብልሹውን የወያኔን ሴራ ከመሰረቱ ተተራመሰ። የዘመኑ ምርጥ ወጣት ታላቅ ተጋድሎ …. ሳይ በህይወት መኖሬን ዛሬ ወደድኩት። ለእኔስ ኩራቴ ወጣት ኃይለመድህን አበራ ተገኘ። የኢትዮጵያዊነት ሚስጢሩም ተዚህ ላይ ተገኘ። እግዚአብሄር ይስጥልን የ እኛ ብቁ የተስፋ ቡቃያ! እናመሰግንኃለን፤ እናከብርህምአለን። እንወድህምአለን። ታሪክ-በትውልድ፤ ትውፊት -በድርጊት፤ አደራ – በጀግነነት በልበ ሙሉነት ተፈጸመ። ተመስገን!
ኢትዮጵያን በልጆቿ መስዋዕትነት ከዘላለማዊ ክብሯ ጋር አምላካችን ያኑርልን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
የኢትዮጵያ የድህነት አዙሪት መንስኤና መፍትሄዎች “በጥቂቱ”
(ክፍል አንድ)
ናትናኤል ካብቲመር (ኦስሎ ኖርዌይ)
አርእስቴን በጥቂቱ ያልኩበት ምክንያት የተነሳሁበት ርእስ ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ ስለማውቅ ነገር ግን ልንወያይበት እንደሚገባ በመረዳቴ ለውይይት መክፈቻ ይሆን ዘንድ እንጂ እኔ ባለኝ እውቀት ብቻ ሙሉ በሙሉ ልተነትነው እንደማልችል በማመኔ ነው። ይህም ቢሆን እንደዜግነቴ ሃገሬን ለዘመናት ለተቆራኛት የድህነት ችግር መንስኤና መፍትሄ ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ ያሰብኳቸውን ዋና ዋና ነጥቦች በመጠኑ ለመተንተን ለመሞከር ነው።
በአንድ ሃገር ወይም አካባቢ የሚኖር ማህበረሰብ ለግላዊም ሆነ ማህበራዊ ፍላጎቶቹ በበቂ ሁኔታ መሟላት አጣጥሞና አስማምቶ በእኩልነት ሊያኖረው የሚችል ህግና ስርዓት በብዙሃኑ ፍላጎትና ስምምነት ላይ ተመስርቶ መቀረፅ አለበት። የሰውን ልጅ ከእንሰሳት የሚለየውና የተሻለ ያደረገውም አንዱ ሌላውን በእኩልነት ማየቱ እንዲሁም ሰው በጉልበቱ የበላይ መሆን የማይችልበት ሁናቴ መፈጠሩ ነው። ነገር ግን አንድ ጉልበተኛ ሌላውን አቅመ ደካማ በጉልበትና በማስፈራራት ፍላጎቱን ከተጫነው ከሰውነት ደረጃ ወርዶ በሰውና በእንስሳ መሃከል ሆነ ማለት ነው። ለዚህም ነው የሰብዓዊ መብት መነሻ ሃሳቡ ሰውን ሁሉ እኩል አድርጎ የማየት ላይ የተመሰረተው።
እንግዲህ ከላይ እንደጠቀስኩት ለአንድ ሃገር ወይም ማህበረሰብ የኑሮ ግብዓቶች መሟላት ማህበረሰቡን አንድ የሚያደርገው በብዙሃኑ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ህግና ስርዓት መኖሩ ነው። የእያንዳንዱ ግለሰብ ለተቀረፀው ህግና ስርዓት በመገዛት የሚያደርገው የግል አስተዋፅኦ የማህበረሰቡን አባላት ፍላጎት ከማሟላቱም ባሻገር በመተባበር ክድህነት ወደተሻለ የኑሮ ደረጃ ያሸጋግራል። ይህም ስኬት የሚገኘው ማህበረሰባዊ ወይም ሃገራዊ ህጉ በእኩልነት ላይ ሲመሰረት ነው። ጤናማ የሆነ እኩልነት መኖር በዜጎች መካከል የምርት ፣ የሞያና የክህሎት ፍሰት ፈጥሮ የዛን ሃገር ወይም ማህበረሰብ መሰረታዊ ፍላጎቶች ብቻ ሳይሆን የኑሮ እርካታን የሚፈጥሩ ተጨማሪ ፍላጎቶችንም ወደ ማሟላት ሊሻገር ይችላል።
ነገር ግን ልክ እንደ አሁኑ የአትዮጲያ መንግስት የወጡትና የሚወጡት ህጎች አቀራረፃቸው እንዲሁም አተረጓጎማቸው ለተወሰነ የማህበረሰብ አካል በአድሎአዊነት ከተንጋደዱ በዜጎች ወይም በጠቅላላ ማህበረሰቡ መካከል ፍትሃዊ የሆነ እኩልነት ከማስፈን ይልቅ የእርስ በእርስ ቂምና ግጭት በመፍጠር ሃገርን ከድህነት ለማውጣት ወሳኝ ግብዓት የሆነውን “በጋራ የማደግና የመግባባት እሴት” ያመነምናል። የዚህ የህግ አተረጓጎም መጣመም ጥቂቶችን ብቻ ጠቅሞ ብዙሃኑን ስለሚጎዳ የሃገር ሁለንተናዊ ብልፅግና ገላጭ የሆነው የወል እድገት ይቀጭጭና የድህነት አዙሪት ይፈጠራል።
አሁንም ሃገራችንን የተቆራኛት ይኸ ችግር ነው። ከዚህ አስከፊ ችግር ለመውጣት ወሳኝ ግብዓቶች ናቸው ብዬ ያሰብኳቸውን ዋና ዋና የ ሃገራዊ መዋቅር መሰረቶች በተናጠል እንደሚከተለው ለማስቀመጥ ልሞክር።
ማህበረሰባዊ አንድነት
ማህበረሰባዊ አንድነት በአንድ ሃገር የሚኖሩ ዜጎችን በመግባባትና በመዋደድ እርስ በእርስ የሚያስተሳስር እንደ ሀግ የተፃፈም ሆነ ያልተፃፈ ነገር ግን በዜጎች መካከል የመንፈስ አንድነት የሚፈጥር ጠንካራ የሆነ የሃገራዊ መዋቅር እሴት ነው።ማህበራዊ አንድነት በሃገራችን ከቅርብ ግዜ ወዲህ እየተገፋ ከሄደበት አዲስ የአመለካከት ጠርዝ ማለትም “ማህበረሰባዊ አንድነት የሚኖረው ተመሳሳይ ብሄር ፣ ዘር ወይም ሃይማኖት ላላቸው ሰዎች ነው” የሚባለው ውስን እይታ እንደ ኢትዮጲያ ያሉ የበርካታ ብሄርና ብሄረሰቦች ያሏት ሃገር ሁለንተናዊ ብልፅግና የማይበጅ በዜጎች መካከልም ተከባብሮና ተዋዶ አብሮ ሰርቶ የማደግን ትልም የሚንድ ፣ ምርታማነትን አቀጭጮ ሃገራችንን ጥልቅ የድህነት አዙሪት ውስጥ የሚጨምር ክፉ የአመለካክት ደዌ ነው።
ማህበረሰባዊ አንድነት ለብሄራዊ አንድነት የጀርባ አጥንት ነው። ቢሆንም የአንድን ሃገር አንድነት በማጠንከርም ሆነ በማበላሸት በኩል የዛ ሃገር መንግስታዊ አወቃቀር ወሳኝ ግብዓት መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ነፃ በሆነ የብዙሃን ህዝብ ምርጫ ስልጣን የጨበጠ መንግስት የሃገር አንድነት ስጋት እምብዛም አይኖርበት ይሆናል ነገር ግን በመፈንቅለ መንግስት ወይም በጦርነት ስልጣን ላይ የወጣ መንግስት አገራዊ አንድነትን በዘላቂነት ከማረጋግጥ አንፃር የከበደ ችግር ሊያጋጥመው ይችላል።
ይህንን የከበደ ችግር በሁለት አቅጣጫ ላስቀምጠው።
የመንግስት ስልጣኑን በጉልበት የያዘው ቡድን የተመሰረተው በርእዮተ አለም መመሳሰልና መግባባት ከሆነ ስልጣኑን ለማደላደል የተቀረውን ህዝብ በርእዮተ አለም በመከፋፈል የራሱን የተመረጠና ለዛች ሃገር ሁነኛ መሆኑን ለማሳየት ይጥራል ከቻለም በህዝቡ ውስጥ በማስረፅ ተከታዮችን ለማፍራት ይጥራል ወይም ከባሰበት በአምባገነናዊነቱ ይቀጥላል።
በሌላ መልኩ ደግሞ የመንግስት ስልጣኑን በጉልበት የያዘው ቡድን የተመሰረተው በዘር ላይ ከሆነ ስልጣኑን ለማደላደል የተቀረውን ህዝብ በዘር ላይ በተመሰረት የፖለቲካ አይዲዮሎጂ ይከፋፍላል። ይህኛው ከላይ ከጠከስኩት እጅግ የከፋ ሃገርን ሊከፋፍል የሚችል እንዲሁም የሃገራዊና ማህበራዊ አንድነት ፀር የሆነ አደገኛ አካሄድ ነው። ለምሳሌም በኢትዮጲያ የሰፈነው ዘር ላየ የተመሰረተው የፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት ከተወሰነ ግዜ ወዲህ እየፈጠረ ያለው እንድምታ በሃገራችን እንጭጭ የፖለቲካ ባህል ከጅምሩ የጥላቻ ስሜት ከመፍጠሩም ባሻገር የሃገራችንን የወደፊት የፖለቲካ ባህል ወደ አሳሳቢ ደረጃ ምን ያህል እንደገፋው ልብ ይሏል።
በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ አንዱ ካንዱ የመማር እና በመከባበር ላይ የተመሰረተ የሃሳብ መለዋወጥ ሊኖር ግድ ነው። ይህም ደግሞ በዛ ማህበረሰብ ውስጥ እኔ አቅልሃለው እንዲሁም እኔ የምለውን በግድ ተቀበሉኝ የሚል የተፅእኖ ስሜት ሳይኖር ማንኛቸውም ውሳኔዎች የአብዛኛውን የማህበሩን አባላት ፍላጎት በሚዛናዊነት ሊያሟላ በሚችል መልኩ የውሳኔ ሃሳብ አመንጭዎችን እይታ (perspective) በአክብሮት ማስተናገድ አለበት። ነገር ግን የአንድ ግለሰብ ወይም ቡድን የበላይነት ከሰፈነ አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ከዚሁ ቡድን ወይም ግለሰብ ጥቅምና ፍላጎት አንፃር ብቻ ይሆኑና የጋራ ብልፅግና በእጅጉ ይጎዳል።
በዚህ ዘመን የአለማችን ህዝቦች በልዩነት ተዋዶ አብሮ የመኖር መንፈስ ጠንካራ ደረጃ ላይ ያደረሱት ሲሆን እንዲሁም በርካታ ፍፁሞ የተለያየ ባህል ፣ ቋንቋና እሴቶች ያሏቸው ሃገራት በጋራ ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ ህብረቶችን እየፈጠሩ ሃገራቸውንና ህዝባቸውን ተጠቃሚ እያደረጉ ይገኛሉ። በሚያሳዝን መልኩ ደግሞ እንደ ኢትዮጲያ ያሉ አምባገነናዊ ስርዓት የተጫናቸው ሃገራት ለስልጣን ቆይታ አንድነትን ከማጠናከር ይልቅ ህዝባቸውን በጎሳ እየለያዩ የስልጣን እድሜያቸውን ለማራዘም ሲጥሩ እየተስተዋሉ ነው።
በጠነከረ ማህበረሰባዊ አንድነት ላይ ተመስርቶ ስለሚገኝ አመርቂ የሃገር እድገት አንድ ጥሩ ምሳሌ ላቅርብ በ1940ዎቹ የሁለተኛው የአለም ጦርነት በእጅጉ የጎዳትና በርካታ ወጣቶቿ በጦርነት ያለቁባት ጃፓን ማህበረሰብ በቁርጠኛነትና በፅኑ ሃገር ወዳድነት ላይ የተመሰረተ ሁሉን አቀፍ ሃገራዊ እቅድ ከጦርነቱ ማብቂያ ማቅስት ለማውጣት ተስማሙ። በ 1950 ያስቀመጡት እቅድ እስከ 10 አመት ግዜ ውስጥ በጨርቃ ጨርቅ ምርት ከአለም አንደኛ መሆን ነበር ሆነላቸው። እንደገና በ1960 ከአለም በብረታ ብረት ምርት አንደኛ ለመሆን አቀዱ በ 1970 ተሳካላቸው። እንደገና በ1970 ከአለም በመኪና ምርት አንደኛ ለመሆን አቀዱ ተሳካለቸው። እንደገና በ1980 በኤሌክትሮኒክስ ምርት አንደኛ ለምሆን አቀዱ ተሳካላቸው። ለነዚህ ሁሉ ተከታታይ አመታት በቁርጠኝነት ለፍተው ሃገራቸውን አሳደጉ። አሁን ጃፓን ምን አይነት የእድገት ደረጃ ላይ እንዳለች ሁላችንም እናውቃለን። በአንድ ወቅት የኢትዮጲያ ኢኮኖሚ ከጃፓን ኢኮኖሚ እኩል ነበር ሲባል ሰምቻለሁ ምንም እንኳን ይህ ነው የሚባል መረጃ ባይኖረኝም ሆኖም ከሆነ እኛ መላ ቅጥ በሌለው የፖለቲካና የርስ በርስ ጦርነት ስንታመስ እነሱ ግን ማህበረሰባዊ አንድነት ላይ በተመሰረት የሃገር እድገት ውጥን የት እንደደረሱ አሁን ያሉበትን ደረጃ አይቶ መረዳት ይቻላል።
የሃገር እድገት ያለውን ማህበረሰባዊ ጥቅም የገባቸው እንደ ጃፓን ያሉ ሃገራት እንደዚህ ሲያድጉ በአንፃሩ ደግሞ እንደ ኢትዮጲኣያ ያሉ የተወሰነ ቡድን ፍላጎት ማሟላት ላይ የተመሰረተ አምባገነናዊ ስርዓት ያላቸው ሃገራት በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሰነዘሩ አንፃራዊ አማራጭ ሃሳቦችን አለመቀበል ብቻ ሳይሆን የአንፃራዊ ሃሳብ አመንጪውን ቡድን ፣ ማህበር ወይም ግለሰብ ሰብአዊ መብትን በእጅጉ በሚጥስ መልኩ ማሰር ፣ ማንገላታት እንዲሁም ከሃገር ማባረርና ህይወትን እስከመንጠቅ ይደርሳሉ።
የዚህም የጉልበት ሚዛን ባለው ግለሰብ ወይም ቡድን በሌላው አማራጭ ሃሳብ አመንጪ ግለሰብ ወይም ቡድን ላይ ይዞት በተነሳው ሃሳብ ሳቢይ ጉዳት ሲደርስበት የሚመለከቱ የተቀሩት የማህበረሰብ አባላት ለጋራ እድገት የሚበጅ አመለካከት ቢኖራቸውም አንኳን ለሚደርስባቸው ነገር እርግጠኛ ስለማይሆኑ ያላቸውን አመለካከት በግልፅ ከማውጣት ይቆጠባሉ ለሃገር ከማሰብ ይልቅ ለግላቸው ወይም ለቡድናቸው ብቻ ማሰብ ይጀምራሉ። ለሃገር ቢያውሉት ከፍተኛ ጥቅም ሊያስገኝ የሚችለውን እውቀታቸውንና ጉልበታቸውን ወይ ለባዕድ ሃገር ያውሉታል ወይም ደግሞ ጥቅም ላይ ሳይውል ባክኖ ይቀራል።
በዚህም ሳቢያ አቅም ያለው የማህበረሰብ አካል ሌላውን ሊጠቅም የሚችልበትን እንዲሁም ሃገር ከዜጎቿ ልትጠቀመው የሚገባትን በእጅጉ ያስቀራል፡ ይህ ደግሞ ማህበረሰባዊ የሆነ የወል እድገትን ፣ ማህበረሰባዊ መተሳሰብና አንድነተን እንዲሁም ለሃገርና ለህዝብ የመቆርቆር ስሜትን ቀስ በቀስ ሸርሽሮ ሊያጠፋውና ሃገርና ህዝብን መጠኑ የሰፋ የድህነት አዙሪት ከመክተት ባለፈ የሀገርን ጨርሶ የመበታተን አደጋ ሊያስከትል ይችላል።
ሰብዓዊ መብትና እኩልነት
ከላይ በዝርዝር ያስቀመጥኩት የማህበረሰባዊ አንድነት ሙሉ በሙሉ በእኩልነት ላይ ተመስርቶ ባይሆንም እንኳን በ አንፃራዊ መልኩ የኑሮ ህበረት ያላቸው ሃገራት ቀጣይ አጀንዳቸው የሚሆነው ለሁለንተናዊ ማህበረሰባዊ እድገት ወሳኝ የሆነው በእኩልነት ላይ የተመሰረት የዜጎች ሰብዓዊ መብት ማረጋገጥ ነው። እንደው ለፅሁፌ ዝርዝር አቀራረብ እንዲሚቸኝ ብዬ ነው እንጂ ሰብዓዊ መብት መከበርና እኩልነት የህብረተሰባዊ አንድነት ቁልፍ አካል መሆኑን ልብ ይሏል። ምንም እንኳን እውነተኛ ዲሞክራሲ እጅግ ፍፁም የሆነና የጠለቀ መሆኑ እንዲሁም ትርጉሙና ፍፁም የሆነ ተግባራዊነቱ አሁን ባሉት የአለማችን መንግስታት “በዚህ ሃገር እንዳለው” ለማለት ሙሉ ለሙሉ የሚያስደፍር ባይሆንም በንፅፅር ከመጥፎ እስከ እጅግ በጣም የተሻለ እያልን መመዘን እንችላለን። ምንም እንኳን በዲሞክራሲ ተግባራዊነት ዙሪያ የጠለቀ ትንተና ባላቀርብም የተውሰኑ ግብዓቶቹን ለተነሳሁበት ወሳኝ የዲሞክራሲ አካል ለሆነው የዜጎች ሰብዓዊ መብትና እኩልነት ስል በመጠኑ ነካካዋለሁ።
ባለፈው ምዕተ አመት ማለትም ከ1900 እስከ 2000 ባሉት መቶ አመታት በጉልበትና ዕብሪት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ስልጣን ወይም ርእዮተ አለም የበላይነት ማግኘት ሳቢያ ወደ መቶ ሚሊዮን የሚጠጋ ህይወት እንደጠፋ የታሪክ መዛግብቶች ያስረዳሉ። የዚሁ ሁሉ መነሻ አንዱ ካንዱ በግድና በጉልበት የበለጠ ለመሆንና አንዱ ቡድን የሚከተለውን የፖለቲካ ርዕዮተ አለም በግድ በሌሎች ሃገራት ወይም ማህበረሰቦች ላይ ለማስረፅ በመነሳቱ ነው። አሁን በርካታ የአውሮፓ ሃገራት ያንን ሁሉ አልፈው የሚስማማቸውንና የሚያስማማቸውን የሃገር አስተዳደር ርዕዮተ አለም እንዲሁም የዜጎች ሰብዓዊ መብት የተረጋገጠበት እጅግ በጣም የተሻለ የሚባል የዲሞክራሲ ስርዓት ፈጥረዋል። ዜጎቻቸውም የዚሁ መልካም ስርዓት ፍሬ የሆነውን ከድህነት ነፃ የሆነ የኑሮ ደረጃ ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስደፍር ደረጃ ተጎናፅፈዋል።
እነዚህ ሰብዓዊ መብት በበቂ ሁኔታ የተረጋገጠባቸው ሃገራት ብዙ ነገር ካጠፋባቸው በውሃላ በብዙ ጥረት ያረሙትን ስህተት እንደ ኢትዮጲያ ያሉ በጉልበተኞች የሚተዳደሩ ሃገራት በፓርላማ ደረጃ እየተስማሙ ስህተቱን ሲደግሙት ይታያል። የተለመደው ብሂላችን “ብልህ ከስህተቱ ይማራል” ቢሆንም የተሻለ ብልህ ደግሞ ከሌሎች ስህተት መማር ይገባዋል እላለሁ። በኢትዮጲያ የሰብዓዊ መብትን ያዘቀጡትና የዜጎችን እኩልነት ጥያቄ ውስጥ የከተቱት ከብሄራዊ ጥቅም አንፃር የሚነሱ ጠቃሚ ሃሳቦችን ከቡድናቸው ወይም ከጎሳ ጥቅም አንፃር የሚመነዝሩ የሃገር አመራሮች ስልጣኑን መቆጣጠራቸውና የሃሳቡን አመንጪዎችንና የደጋፊዎችን ፍላጎት ማፈናቸውና መጫናቸው እንዲሁም ለተለያየ እስርና እንግልቶች መዳረጋቸው ነው።
የሰብዓዊ መብቱ የተጣሰና እኩልነቱ ያልተከበረለት ማህበረሰብ ሃገርን ከድህነት ለማውጣትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው የጋራ ጥረት ከመሳተፍ ይቆጠባል እንዲሁም የችግሩ ተጠቂ ያልሆነ የማህበረሰብ አካልም ቢሆን የሰውን ልጅ መሰረታዊ መብት ከሚጥስ መንግስት ጋር ለመተባበር አይነሳሳም። ዜጎችም የሃገር ልማት ላይ ከመሳተፍ ይልቅ መብታቸውን ለማስከበር ትግል ይጀምራሉ። መብት የማስከበር ትግሉ ዘርፍ እየበዛ ሲሄድ ተነጋግሮ መግባባት ጭራሽ ይጠፋና ዲሞክራሲያዊ የሆነ አሳታፊ የወል እድገት ህልም ሆኖ ይቀራል። ይህ ደግሞ ሃገርን ማለቂያ የሌለው የድህነት አዙሪት ውስጥ ይከታል።
የሚቀጥለውን በክፍል ሁለት ይመልከቱ . . . . .
የኢትዮጲያ የድህነት አዙሪት መንስኤና መፍትሄዎች “በጥቂቱ” (ክፍል ሁለት)
በክፍል አንድ ፅሁፌ ሃገርንም ሆነ ዜጎችን ከድህነት አዙሪት ለማውጣት አስፈላጊ ስለሆኑት ስለ ማህበራዊ አንድነት እንዲሁም ስለ ሰብዓዊ መብትና እኩልነት አንዳንድ ነገር ብያለሁ የቀሩትን ዋና ዋና ነጥቦች ደግሞ እነሆ።
የዜጎች ነፃነት
የዜጎች ነፃነት ዘርፈ ብዙ መገለጫ አለው። የዜጎች ነፃነት ለሃገር ሁለንተናዊ እድገት ሌላው ወሳኝ ግብአት ነው። በጥቅሉ የዜጎች ነፃነት ጥሩ የሆነ ደረጃ ላይ ደረሰ የሚባለው በፖለቲካዊም ሆነ በማህበራዊ ዘርፍ አንፃራዊ የሆነ ነፃነት ሲሰፍን ነው። በነዚህ ሁለት ዘርፎች ነፃነት አለው የመባል ደረጃ የደረሰ ማህበረሰብ ከሌሎች በእጅጉ የተሻለ ምርታማነትን የማሳደግም ሆነ ከድህነት የመላቀቅ እድል አለው። ለመተንተን እንዲመች ፖለቲካዊና ማህበራዊ ነፃነትን ለየብቻ ላስቀምጣቸው።
ሀ.ፖለቲካዊነፃነት
ዜጎች በሃገራቸው ፖለቲካ ውስጥ በግልም ሆነ በቡድን የሚንቀሳቀሱበት ፣ ለሃገራቸው ይጠቅማል ብለው ያመኑበትን ሃሳብ በተለያዩ መድረኮች ወይም ሚዲያዎች የሚገልፁበትን አሰራር እንደመንግስት የተቀመጠው ቡድን ወይም አካል የመቅረፅ ሃላፊነት አለበት። የዚህ አይነት አሰራር አለመኖርና የዜጎች የፖለቲካ ነፃነት ታፍኖ እንደወንጀል መቆጠር ለሃገር እድገትና ምርታማነት የመረባረብና የመጨነቅ ባህልን ከዜጎች አመለካከት ያጠፋና ከፍተኛ የሆነ የፍርሃት ስሜት በጠቅላላ ማህበረሰብ ላይ እንዲሰፍን ያደርጋል።
ከዚህ መሰል የአፈና ስርዓት ከሚፈጥረው ፍርሃት በመጠኑም ቢሆን የተላቀቁ የማህበረሰብ አባላት ለሃገር ምርታማነትና እድገት ቢውል ይህ ነው የማይባል ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚኖርውን አቅማቸውን ፣ እውቀታቸውን አንዲሁም ግዜና ገንዘባቸውን ባስ ሲልም ህይወታቸውን ለዜጎች የፖለቲካ ነፃነት መከበር ይሰዋሉ። በተቃውሞ ሰልፎችና የፖለቲካ ክርክሮች የበርካታ ዜጎች ውድ ግዜ ይባክናል። እንደ ኢትዮጲያ መንግስት ያሉ አምባገነኖችም የመብት ጥያቄዎችንና አማራጭ ሃሳቦችን የሚያመነጩ አካላት ማስራቸውን ፣ ማዋከባቸውን ባስ ሲልም እንደህዝብ ጠላት መቁጠራቸውን ይቀጥላሉ። እዚህ ደረጃ ላይ ነው እንግዲህ የፖለቲካ ነፃነት መጥፎ ደረጃ ላይ ደረሰ የሚባለው።
የዜጎች የፖለቲካ ነፃነት አለመከበር የአንድን ሃገር የፖለቲካ ምህዳር ያጠባል እንዲሁም ከፖለቲካ በተያያዘ የፍርሃት መንፈስ ያነግሳል። ይህ ደግሞ ሰፋ ካለ የፖለቲካ ምህዳር ከሚሳተፉ አቅም ያላቸው ዜጎች የሚመነጩ ሁነኛ የሃገር እድገት አምጪና ምርታማነትን አሳዳጊ እይታዎች ከናካቴው እንዲጠፉ ያደርጋል። ሃገርም በተወሰኑ ግለሰቦች ወይም ቡድን አመለካከትና ፍላጎት ብቻ መመራት ትጀምራለች። ከዚህ መሰል ሃገራዊ አመራር ዜጎችን ከድህነት አዙሪት መላቀቅ መጠበቅ በአንድ እጅ እያጨበጨቡ ድምፅ መጠበቅ ማለት ነው።
ለ.ማህበረሰባዊነፃነት
በአንድ ሃገር ወይም አካባቢ ተሰብስበው የሚኖሩ ማህበረሰቦች በሃገር ወይም መንግስት ደረጃ ከተደነገገው ህግ ባሻገር ሲወርድ ሲዋረድ የኖረ ያልተፃፈ ህግ አላቸው። ማህበረሰባዊ ነፃነት በጥቅሉ የዛ ማህበረሰብ አባላት ውስጥ አንዱ ያንዱን አመለካከት፣ ግላዊ ማንነት እንዲሁም እምነት የሚያከብርበት የተፃፈም ሆነ ያልተፃፈ የነፃነት መርህ ነው። ይህ የማህበረሰብ ነፃነት ለፖለቲካ ነፃነት እንደ አይነተኛ ግብዓትም ያገለግላል። ዜጎች የተለያዩ ፖለቲካዊም ሆነ ማህበራዊ አጀንዳዎችን እያነሱ በተዘጋጁም ሆነ ባልተዘጋጁ የማህበራዊ የውይይት መድረኮች ተቃራኒ ሃሳቦችን በመከባበር ላይ በተመሰረተ ሁኔታ ሃሳቦችን የሚያንሸራሽሩበትና የሚከራከሩበት ፍላጎታቸውን በነፃነት ሌላውን ባለመጫን ወይም መብቱን ባለመጋፋት የሚገላለፁበትን ባህል ካጎለበቱ ፡ ይህም ባህል ሃገራዊ መልክ ከያዘና ወደ መንግስት ደረጃ ካደገ በውይይትና በበሳል ክርክር የተፈተነ ሃሳብ ነጥሮ ይወጣና ሃገርን የማሳደግ ህልም እውን ይሆናል።
ይህ ተቃራኒ ሃሳብን የማዳመጥና የማንሸራሸር ባህል ከማህበረሰብ ወደ መንግስት ደረጃ የማደግ ወይም ከመንግስት ወደ ማህበረሰብ የመስረፅ እድል አለው። ከማህበረሰብ ወደመንግስት የሚያድገው የዛ ማህበረሰብ አባላት ሁለንተናዊ ማህበረሰባዊ እድገት ለማምጣት በሚል ተነሳስተው በነፃነት የራሳቸውን መንግስታዊ አካል ሲያዋቅሩ ወይም በቀላል ቋንቋ መንግስታቸውን ሲመርጡ ነው። በዚህ መልኩ ለስልጣን የበቃ መንግስት የመረጠውን ህዝብ ለማገልገል ስለተነሳ የህዝቡን ነፃነት አያፍንም ባህሉን እንደጠበቀ ይቀጥላል። ነገር ግን እንደ ሃገራችን ኢትዮጲያ አይነት በህዝብ የተመረጠ መንግስት ማለት ምን አይነት እንደሆነ በታሪካቸው አጋጥሟቸው የማያቁ ሃገራት መንግስት ላይ የማህበረሰባዊ ነፃነት ባህልን ማሳደር እጅግ ከባድ ይሆንባቸዋል።
በጦርነት ወይም በመፈንቅለ መንግስት ወደ ስልጣን የመጣ መንግስት አብዛኛውን ግዜ በማንነትም ሆነ በሃሳብ ልዩነት ላይ የተመሰረቱ ነፃ የሆኑ ማህበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ውይይቶች ባህልን አሳድጎ ወደ ህዝብ ሲያሰርፅ አይታይም። የሃገራችን መንግስት የሚያደርጋቸው የሃሳብ ነፃነትን የማፈን ሂደትና እንዲሁም አማራጭ ሃሳብ አመንጪና የመብት መከበር ጠያቂ አካላት ላይ የሚያደርገው ኢሰብአዊ ተፅዕኖ በተጠቂዎች ላይ ከሚፈጥረው የአካልና የስሜት ጉዳት ባሻገር እጅግ አሳሳቢ የሆነው በተለያየ የማንነት ወይም የርዕዮተ አለም ልዩነት የሚፈጠሩ ማህበራት አባላትና ደጋፊዎች መካከል አንዱ አንዱን እንደጠላት የማየት እንድምታን ባስ ሲል ደግሞ የርስ በርስ ግጭትን መፍጠሩም ነው። ይህ ደግሞ በዜጎች መከባበርና መዋደድ ላይ የተመሰረተ መተባበር ብቻ ሊገኝ የሚችለውን የምርታማነት መጨመርና እድገትን እንዲሁም ከድህነት አዙሪት የመውጣት ጥረትን በከፍተኛ መልኩ ያቀጭጨዋል።
ዘላቂነት ያለው የፖለቲካ ስርዓት
ሁነኛ የፖለቲካ ስርዓት ማለት በጥቅሉ አንድን ሃገር ወይም ማህበረሰብ የአገዛዝና አስተዳደራዊ መዋቅር በአለማቀፍ ደረጃ ከተቀመጡት ስርዓቶች ጋር በማዛመድ ለዛ ሃገርና ማህበረሰብ እንዲመች ተደርጎ የተቀረፀ ማለት ነው። በፖለቲካ ስርዓት ዜጎች መንግስት እንዲሆን በመረጡት ወይም መንግስት ሆኖ በተቀመጠው አካል ጤናማና ሚዛናዊ የሆነ የህግና ስርዓት ፣ የኢኮኖሚ ስርዓት ፣ የባህላዊና ማህበረሰባዊ ስርዓት የማዋቀርና የማስተዳደር ሃላፊነት ሲሰጡት ያም መንግስት ዘላቂነት ያላቸው ህግጋትና ፖሊሲዎችን ለመረጠው የፖለቲካ መንገድና ለማህበረሰቡ እሴቶች በሚስማማ መልኩ ቀርፆ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ የአገዛዝ ስርዓት ሲመሰርትና ይህንንም ለማስከበር በአግባቡ ሃላፊነቱን ሲወጣ ማለት ነው።
በአለማችን በርካታ ሃገራት ለዜጎቻቸውና ለነባራዊ ሁኔታቸው በሚመች መልኩ የፖለቲካና የአገዛዝ ስርዓት ገንብተዋል ለአብነት ለመጥቀስ ያህልም የአሜሪካ መንግስት የሚከተለው የፖለቲካ ስርዓት ከሁለት ምዕተ አመት በላይ መሰረታዊ መርሁን ሳይለቅ ሊቀጥል ችሏል። ከዚህም ወጥነት ካለው የፖለቲካ ስርዓቱ የመነጩት የኢኮኖሚና ማህበራዊ ስርዓቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ እየጠነከሩ አሁን ላሉበት ደረጃ ደርሰዋል። በአንፃሩ እንደ ኢትዮጲያ ያሉ ያላደጉ ሃገራት ለአለማደጋቸው እንደምክንያት ከሚጠቀሱት ውስጥ ዋነኛው የሆነው በየግዜው የሚቀያየር ስርዓት መኖሩ እንዲሁም ጭራሽ ይህ ነው የሚባል ስርዓት አለመኖሩ ነው። በኢትዮጲያ የሚመጣው መንግስት ሁሉ የራሱን ስርዓት እንደ አዲስ መጀመሩ ከፖለቲካው ስርዓት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸውን የኢኮኖሚና ማህበረሰባዊ ስርዓቶች እንደገና ፈርሰው እየተሰሩ የተወሰኑትም “የቀደመው መንግስት አሻራ አለባቸው” በሚል ምክንያት እየፈረሱ አጠቃላይ የሃገር እድገትን ባለበት እንዲሄድ አርጎታል።
የአሁኑ የኢትዮጲያ መንግስት ስልጣኑን በእርስ በርስ ጦርነት አግኝቶ ያዋቀረው የአገዛዝ ስርዓት ስልጣኑን ያገኘው በህዝብ ምርጫ ስላልሆነ ስርዓቱ ለተወሰኑ የማህበረሰቡ አካላት ብቻ ሲያደላ ቆይቷል። በዚህም ሳቢያ መጠነ ሰፊ የሆን የፍትህ መጓደል ይስተዋላል። ከማህበረሰብ ውይይትና ይሁንታ ውጪ ስልጣኑን ለማደላደል የሚያወጣቸው የተለያዩ ህግጋት በህዝብ ዘንድ በግድ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ሲያደርግ የለየለት አምባገነን ሆኗል።
እንደ ኢትዮጲያ መንግስት አይነት አምባገነናዊ ባህሪይ ያላቸው መንግስታት በተለየ መልኩ አማራጭ የፖለቲካ ስርዓት ወይም በተመሳሳይ ስርዓት የተለዩ ዝርዝር ፖሊሲዎችን ይዘው ለተነሱ የፖለቲካ ማህበራት በግልፅ ውይይትና ክርክር ማንኛቸው ለህዝብ እንደሚሻሉ ከማሳየት ይልቅ አማራጭ ሃሳብ አመንጪዎችን ይዘው የተነሱትን አላማ ለህዝብ እንዳያስተዋውቁ በማፈን ፣ በማዋከብ ፣ በማሰርና ውድ ህይወትን እስከመንጠቅ ይደርሳሉ።
የኢትዮጲያ መንግስት የራሱን ፖሊስዎችና መርሆች በግልም ሆነ በህዝብ ሚዲያ እንደልቡ እያስነገረ ነገር ግን አማራጭ የፖለቲካ ማህበራትን መሰብሰብ እስከመከልከልና ብሎም እንደ ህዝብና ሃገር ጠላይ ይፈርጃል። ይህ መረን የወጣ አምባገነናዊ ስርዓት ዜጎች ሃገራዊ እድገት ላይ ሊኖራቸው የሚገባውን ተሳትፎ አሳንሶ በገዛ ሃገራቸው ባይተዋር የሚያደርግ እንዲሁም ሃገርን ከድህነት የማውጣት ጥረት እጅግ ጠቃሚ ተሳትፎ እንዳያረጉ የሚያስቀር ለተወሰኑ ቡድንና ግለሰቦች የስልጣን ጥምና ጥቅም ሲባል ሃገርን የድህነት አዙሪት ውስጥ የመዝፈቅ ሃላፊነት የጎደለው ስርዓት ነው።
አስተማማኝ የኢኮኖሚ መዋቅር
የኢኮኖሚ መዋቅር ወይም ስርዓት ማለት በጥቅሉ በአንድ ሃገር ወይም ማህበረሰብ ውስጥ ያለ ምርትና አገልግሎትን የማምረትና የማሰራጨት እንዲሁም የተለያዩ ግብዓቶችን በተገቢው መልኩ የማዳረስ ስርዓት ማለት ነው። በዚህ ስርዓት ውስጥ የማህበረሰቡን የተለያዩ ምርትና አገልግሎቶች አቅራቢ ተቋማት ፣ ማህበራትና ድርጅቶች እንዲሁም ተጠቃሚዎች መካክል ጤናማ የሆን ፍሰት እንዲኖር የሚያደርግ ስርዓት ማለት ነው። ይህም ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር የተስተካከለና ጤናማ እንዲሆን መንግስት የተለያዩ ህግጋቶችንና ድንጋጌዎችን በማውጣት ከአለማቀፍ ኢኮኖሚ ስርዓቶች ጋር የማጣጣም ሃላፊነት አለበት።
ጤናማ የኢኮኖሚ ስርዓት መኖር የአንድን ማህበረሰብ ወይም ሃገር የኑሮ ደረጃ በማሳደግ በኩል ቀጥተኛ አስተዋፆ አለው። ኢኮኖሚያዊ መዋቅሩ በተገቢው መልኩ እንዲቀጥል ሰላማዊና በፍላጎት ላይ የተመሰረተ ሃገራዊ አንድነት መኖር ወሳኝ ሚና አለው። አንድ መንግስትም የሃገርን ኢኮኖሚ በተገቢ መልኩ እየመራ ነው የሚባለው አጠቃላይ ፍሰቱን ለሁሉም ዜጋ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ሲያስተዳድር ፣ ሲዳኝ እንዲሁም ሲያበረታታ ነው።
ፍሰቱ ሚዛናዊ አደለም የሚባለው ለተወሰኑ የንግድ ተቋማት መንግስታዊ የሆነ አድልዎ በማድረግ የተቀሩትን የመጫን ሂደት ሲኖር እንዲሁም ኢኮኖሚውን የማስተዳደር ሃላፊነት የተሰጣቸው መንግስታዊ ተቋማት በገለልተኝነት በማስተዳደር ፈንታ በአድሎአዊነት ጣልቃ ሲገቡና በጥቅማ ጥቅም ሲያዙ ነው። ይህ ሚዛናዊነቱን የማሳት ተግባር ለተወሰኑ ግለሰቦች ጥቅም ሲባል በሃገር ኢኮኖሚ እድገት ላይ ከፍተኛና ቀጥተኛ ሚና የሚኖራቸውን ድርጅቶችን ለክስረትና ለመዘጋት ይዳርጋል ፣ ሃገርና ህዝብ ከንግድ ፍሰቱ የሚያገኙትን ጥቅማ ጥቅሞች ያሳጣል ፣ ወደ ንግድ ስራዎችና መሰል እንቅስቃሴ ለመግባት ያቀዱ ሃገራዊም ሆነ አለማቀፋዊ ድርጅቶችን ፍላጎት ይገታል ፣ የስራ አጡን ቁጥር ይጨምራል እንዲሁም በርካታ መሰል ችግሮችን በመፍጠር ሃገር ወይም ማህበረሰብ ከድህነት አዙሪት ለመውጣት የሚያረገውን ጥረት ያቀጭጨዋል።
ለምሳሌ በሃገራችን ኤፈርት የተባለው የንግድ ተቋም በመንግስት በሚደረግለት ግልፅና ቀጥተኛ ድጋፍ በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚንቀሳቀስ ፣ ከዛ ሁሉ የኢትዮጲያ ብሄርና ክልል አንድ ክልልና ብሄርን ለማልማት በሚል የተዋቀረ ድርጅት አለ። የዚህ ድርጅት በተለያዩ ውድድር በሚያሻቸው የንግድ ዘርፎች ተሰማርቶ ነገር ግን በመንግስት ድጋፍ በሞኖፖል መንቀሳቀሱ ሌሎች ቀድመው የነበሩ እንዲሁም አዲስ የሚፈጠሩ የንግድ ተቋማትን ምን ያህል እንደጎዳ በዘርፉ ባለሞያዎች ብዙ ተብሏል። መሆን የነበረበት ግን የኢትዮጲያ መንግስት እከተለዋለው ያለውን የኢኮኖሚ ስርዓት በአግባቡ ቢያስተዳድር ፣ ጤናማ የውድድር መንፈስ ቢፈጥር እንዲሁም የሁሉንም ሃገራዊ ድርጅቶች ምርቶች ከአድልዎ ውጪ በሆነ መልኩ አለማቀፍ ገበያ ውስጥ እንዲታወቁ በቅንነት ቢጥር ሃገራችን በቅርቡ ከድህነት አዙሪት ትወጣ ነበር።
እንግዲህ ከተነሳሁበት ሃሳብ ስፋትና ጥልቀት አንፃር በእኔ አቅም ይህችን ብያለው። አንባቢዎች የማይስማሙባቸው ወይም የቀረ የሚሉት ብዙ ሊኖር ይችላል ነገር ግን እኔ ሃገር የምትገነባው በጎ መሰረት ያለው ግልፅ ውይይት ሲኖር ነው ብዬ ስለማምን እንደ አንድ ተቆርቋሪ ዜጋ ይህችን አዋጥቻለሁ።
ሃገራችን ከአምባገነናዊ ስርዓት የምትላቀቅበትን ህዝቦቿም ከድህነት አረንቋ የሚወጡበትን ቀን ቅርብ ያርግልን !!
በሃገሪቱ የተነሰራፋው ዘረኝነት፣ የደህንነት ሥጋትና አድልዎ አውሮፕላን እንዲጠለፍ አድርጓል
ከምኒልክ ሳልሳዊ
በሃገሪቱ የተንሰራፋውን የደህንነት ስጋት በመልካም አስተዳደር እና በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ አድልዎ ተከትሎ የተደረገው የአይሮፕላን ጠለፋ ህዝቦች በገዛ አገራቸው በደህንነት ላይ ምን ያህል ስጋት እንዳጠላበት እና በመኖር ህልውናቸው ላይ ኢትዮጵያውያን የስርአቱ ፖሊሲዎች እያሸማቀቋቸው እንደሚገኙ አለም ካለፈው ጊዘ በተሻለ እውነታውን ፍንትው አድርጎ እየመሰከረ ነው።
የሕወሓት መራሹ ጁንታ ወደ ስልጣን በጠበንጃ ሃይል ከመጣ ጀምሮ በአለም አቀፍ ደረጃ የተደነገጉ የሰብኣዊ መብት ህጎችን ካለምንም ማርቅርቅ እና ድካም ከሌሎች በመገልበጥ በወረቀት ላይ ከማስፈሩም በተጨማሪ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በአለም ላይ የሰው አገር ህግን እና አለማቀፍ ድንጋጌን ከሃገራችን ሁኔታ ጋር ሳይገናዘቡ በስፋት በደመነፍስ ለፍጆታ የተጻፈበት ሃገር ኢትዮጵያ ብቻ ሲሆን በየትኛውም አለም ሃገራት ያልተከሰተ የአለም አቀፍ ህጎችን ግልባጭ በከፊል በህገመንግስት እንዲሁም የገዢ ፓርቲን የፖለቲካ ፕሮግራም በከፊል ደባልቆ በጋር እንደ አውራ ህግ የወጣባት ሃገር ብትኖር ኢትዮጵያ ብቻ ናት::ኢትዮጵያ በታሪኳ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የመብቶች ሕጋዊነት በተጨበጨበለት ሁኔታ እና ይህ በማይባል ደረጃ የተደነገጉባት አገር ነች፡፡ እንግዲህ ይህ ሆኖ እያለ ነው በአገሪቱ የመብቶች ጥሰት ጉዳይ ከአገሪቱ ብሔራዊ አነታራኪ ፖለቲካዊ አጀንዳነት አልፎ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ጥላቻ በፈጠረው ፍርሃት ብቻ የሃገሪቱን ህጎች ዜጎች ለመጥለፍ እያዋሉት ነው::
የቀድሞ መንግስትን ሽንፈት ተከትሎ በኢትዮጵያ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች የፍፃሜ ምዕራፍ ይሆናል ተብሎ ተስፋ ተደርጎ ነበር፡፡ ነገር ግን ጭራሽ ብሶበት ቁጭ አለ፡፡ የሕወሓት ወንበሩን መቆጣጠር ተንተርሶ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በተለይም ሒዩማን ራይት ዎችና አምነስቲ ኢንተርናሽናል የወያኔን ጁንታ በሰብዓዊ መብት ጥሰት በማብጠልጠል ነበር የተቀበሉት፡፡ ባለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት የሰብኣዊ መብት ጥያቄዎች አቤቱታ ማሰማታቸውን አላቆሙም፡፡ ጋዜጠኞችን የሃሳብ ነጻነት ከሚገድብ ጥቃት በመከላከል ላይ የተሰማሩ የመብት አስከባሪ ድርጅቶችም ወያኔ በሚፈጥረው ከባድ የሰብኣዊ መብት ጥሰት በየጊዜው መክሰስ ሥራቸው ሆኗል::የአሜሪካው ስቴት ዲፓርትመንት በየጊዜው በሚያወጣው ዓመታዊ መግለጫው ወያኔን በሰብዓዊ መብት ጥሰትና የፖለቲካ መብቶችን ማፈን ይከሰዋል፡፡ ባሁን ወቅትየእነኚህን አካላት መግለጫዎች የታወቁ ዓለም አቀፍ መገናኛ ድርጅቶች በመቀባበል ኢትዮጵያ የዜጎቿን መብቶች በመጣስና በማፈን ወደር የሌላት አገር እንደሆነች ዓለም እንዲረዳው እያደረጉ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በአስከፊ ድርቅና ረሃብ ለመታወቅ እንደበቃችው ሁሉ ወያኔ የዜጎችን መብቶች በመጣስና በማፈን እንዲሁም በሰብዓዊነት ላይ በሚፈጽመው ወንጀል በዓለም ላይ ታዋቂነትን እያተረፈ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም;ወያኔ የፖለቲካ ተቀናቃኞችን መብቶች ለመጣስ ስለሚጠቀምባቸው ዘደዎች የሚቀርቡ ማስረጃዎች እና ማብራሪዎች እጅግ ዘግናኝ ናቸው፡፡የወያኔ መሪዎች የፖለቲካ ተቀናቃኖችን ለማዳከም ሲሉ ንፁኃንን ወንጀለኛ የሚያደርግ ዘዴዎችን ሥራ ላይ እንደሚያውሉ በተለያዩ ይፋዊ ሪፖርቶች ላይ ሁሉ ከነማስረጃው እየተነገረ ይገኛል::
የህ የሰብኣዊ መብጥ ጥሰት እየተባባሰ የሚሄድበት ምክንያት ወይኔ በአብዛኛው ካድሬዎች ዘንድ በስፋት ሰርጾ እንዲገባ ያደረገው የተቃዋሚዎች ጥላቻ እና እንዲሁም የተቃዋሚው ቡድን የትግል አቅጣጫው በተመሳሳይ መልኩ በጥላቻ ላይ የተመረኮዘ መሆኑ ነው::ተቃዋሚዎች የታጠቁ ሃይላት ባለመሆናቸው የመርሃቸው እንቅስቃሴ የተገደበ እና ለፖለቲካ እና ለሚዲያ ፍጆታ የዋለ ተዳፍኖ የሚገኝ ሲሆን የወያኔው ግን በታጠቁ የጸጥታ ሃይሎች እና በፖለቲካ ማጭበርበሮች ላይ ስለተመረኮዘ ካድሬዎቹ በተሰጣቸው የጥላቻ ተግዳሮት እና ወያኔያዊ ስልቶች የፈጠሩትን ጥቅማጥቅሞች ጠብቀው ለማቆየት ሲባል ጥላቻ በፈጠረው ፍርሃት ብቻ የሃገሪቱን ህጎች ዜጎች ለመጥለፍ እያዋሉት ነው::
ይህ ፍርሃት እና ጥላቻ በወያኔ ከትልቅ እስከ ትንሽ ካድሬዎች አናት ውስጥ ስር ለስር በመስደድ የፈጠረው ነገር ቢኖር ማንኛውም ዜጋ ተቃውሞ ካሰማ በወንጀለኛነት በመፈረጅ በማሳደድ በማጥፋት እረፍት ለማግኘት እና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲራወጡ የህዝብን የበላይነት አፈር ከተውታል::ማእከላዊ የወያኔ ጁንታ በዲሞክራሲ ባለመወቀጣቸው የህጎችን የበላይነት ማረጋገጥ ካለመቻሉም በተጨማሪ በህዝብ እና በዲሞክራሲ ላይ በደሎችን የሚያደርሱ ባለስልጣናት የሚጠየቁት በሃገሪቱ የበላይ ህጎች ሳይሆን በወያኔያዊ የፓርቲ መመሪያዎች በመሆኑ በጥቅም መተሳሰር በፈጠርው ዝግ መንገድ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች እየተብራከቱም ከመሆኑ አልፎ የእለት ተእለት ተግባራት አካል ሆነዋል:: የአይሮፕላን ጠለፋዉም ከላይ ከገለጽኩት ጉዳዮች ጋር ቁርኝት ያለውና በሃገሪቱ እየተተገበረ ያለውን የቡድን አምባገነንነት በማጋለጥ ረገድ ትልቁን ሚና ተጫውቷል።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ከዚህ ቀደም የተደረጉ 8 የአውሮፕላን ጠለፋዎች (ለጠቅላላ እውቀት)
1
እ.ኤ.አ ህዳር 1991 ዓ.ም ሁለት የሌላ ሃገር ግለሰቦች እና አንድ ኢትዮጵያዊት ሴት ተመሳስሎ የተሰራ እና የማይሰራ መሳሪያ በመጠቀም 88 ሰዎችን አሳፍሮ በሀገር ውስጥ በረራ ላይ የነበረውን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጀት በመጥለፍ ጅቡቲ ላይ ካሳረፉት በኋላ ሁሉንም ተሳፋሪዎች ለቀዋቸዋል።
2
እ.ኤ.አ ነሐሴ 1992 ዓ.ም አራት ኢትዮጵያውያን በሃገር ውስጥ በረራ ላይ የነበረን አውሮፕላን ከጠለፉ በኋላ ጅቡቲ ላይ በማረፍ ያገቷቸውን መንገደኞች የለቀቁ ሲሆን በመቀጠል ወደ ጣሊያን በመብረር ጥገኝነት ጠይቀዋል።
3
የካቲት 1993 ዓ.ም አንድ ኢትዮጵያዊ አብራሪው ላይ መሳሪያ በመደቀን ከፍራንክፈርት ወደ አዲስ አበባ ይጓዝ የነበረውን የሉፍታንዛ ንብረት የሆነውን አውሮፕላን በመጥለፍ አሜሪካ ጆን ኤፍ ኬኔዲ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲያርፍ አድርጓል።
4
እ.ኤ.አ በህዳር 1995 ዓ.ም አንድ ኢትዮጵያዊ ከአውስትራሊያ በመጠረዙ ምክንያት የኦሎምፒክ አየር መንገድ ንብረት የሆነውን ጀት የምግብ ቢላዋ በመጠቀም በመጥለፍ ወደ ሀገሩ እንዳይላክ የጠየቀ ቢሆንም በመንገደኞች ላይ ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል።
5
እ.ኤ.አ መጋቢት 1995 ዓ.ም አምስት የታጠቁ ሰዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነውን ጀት ሊነር አውሮፕላን በመጥለፍ እና ሱዳን ላይ በማሳረፍ ወደ ግሪክ ከዛም ወደ ስዊድን እንዲበር ከሞከሩ በኋላ የሱዳን መንግስት ጠላፊዎቹ በስዊድን ጥገኝነት እንዲያገኙ እንደሚረዳቸው ቃል በገባላቸው መሰረት አውሮፕላኑ በ24 ሰዓታት ውስጥ ሊለቀቅ ችሏል።
6
እ.ኤ.አ ህዳር 1996 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ወደ አይቮሪኮስት በኬንያ በኩል ይበር የነበረውን አውሮፕላን አብራሪዎቹን በማሰገደድ ወደ አውስትራሊያ እንዲሄድ በማስገደዳቸው እና የአውሮፕላኑ ነዳጅ በማለቁ በኮሞሮስ ደሴት ላይ የመከስከስ አደጋ ገጥሞት እውቁ የኬንያ ፎቶ ጋዜጠኛ መሐመድ አሚንን ጨምሮ ለ175 ሰዎች ህልፈት ምክንያት ሆኗል።
7
እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2001 ዓ.ም አምስት የጦር አውሮፕላን ሰልጣኞች የሚሰለጥኑበትን የጦር አውሮፕላን ከባሕር ዳር ከተማ በመጥለፍ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ለመሄድ ቢያስቡም አውሮፕላኑ የነበረው ነዳጅ አነስተኛ በመሆኑ ሱዳን ላይ ለማረፍ ተገዷል።
8
እ.ኤ.አ ሰኔ 2002 ዓ.ም ስለታማ እና ተቀጣጣይ ነገር የያዙ ሁለት መንገደኞች የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገር ውስጥ በረራን ለመጥለፍ ቢሞክሩም በበረራ ደህንነት ሰራተኞች በተተኮሰባቸው ጥይት በመሞታቸው የጠለፋው ሙከራ አልተሳካም።
መከላኪያ የህዝብ ወይስ የህወሓት?
ከበላይ ገሰሰ
Addera5021@yahoo.com
ህወሓት ደርግን ማሸነፍ ማለት የኢትዮጵያ ህዝብን ማሸነፍ ማለት ነው ብሎ ስለሚያስብ ተግባሩ ሁሉ የንቀት፣ የማንቋሸሽና የማዋራድ ስራ እየፈፀመ ይገኛል። ሌላውን ትተን ጥቂት የሻዕቢያ ተላላኪ የሆኑትን የህወሓት መሪዎች የግንጠላ አጀንዳቸውን ይዘው በረሃ የሸፈቱበት ቀን ልክ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም የትግራይ ህዝብ “ደደቢት ሂዳችሁ ታገሉሉኝ” ብሎ ወክሎ የላካቸው ይመስል “እኛ ታግለን ነፃ ስላወጣንህ እንደፈለግን እናደርጋሃለን” በማለት ዓይን አዉጣ በሆነ መንገድ ሰሞኑን “የካቲት 11 የትግራይ ህዝብ ዳግም ልደት ነው” እየተባለ በመከላኪያ ሰራዊት ታጅቦ በመከበር ላይ ስለሚገኘው የህወሓት አስቂኝ፣ አስገራሚና አሳዛኝ ድራማ የሚከተሉትን ጥቂት ነጥቦችን በአጭሩ እንመልከት።
የህወሓት ድራማ ቁጥር 1.
የህወሓት መሪዎች እናስተዳድራለን የሚሉት 90 ሚሊዮን የኢ/ያ ህዝብ ነው እየገዙ ያሉት። ከፍተኛ ባለስልጣናቱን ጨምሮ ካድሬዎቻቸው፣ አባላቶቻቸውና ደጋፊዎቻቸው በቀጥታም ሆነ በስውር እየጋጡ ያሉት የኢትዮጵያ ህዝብ ሀብት ነው። የገጠሩን ትተን በሀሪትዋ ዋና ዋና ከተሞች ቁልፍ ቦታዎችን በመያዝ 90 ከመቶ የትግራይ ባለሀብቶች የቢዝነስ እንቅስቃሴያቸውን የሚያካሂዱትና ባለቤት የሆኑት በሌሎች ክልሎች ነው። በአጠቃላይ የሀገሪትዋ ሀብት በተለያየ መልኩ የተቆጣጠሩት የህወሓት መሪዎች፣ ካድሬዎችና አጃቢዎቻቸው ናቸው። በመሆኑም በመሬት ላይ ያለው ህዝቡ የሚያውቀው ሐቅ ይህ ሆኖ ሳለ እነሱ የሚሉን ግን “የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ነን” ነው። ልብ በሉ!! ስልጣን ላይ ያሉት እነሱ። ሀገሪቱን የተቆጣጠሩት እነሱ። ሀገሪትዋን እየዘረፉ ያሉት እነሱ። ነገር ግን ነፃ እናወጣለን የሚሉት ህዝብ አንድ ክልል ነው። ታዲያ!! ቆም ብሎ ላሰበውና ላስተዋለው ሰው ይህ መንግስት ከኛ አብራክ የወጣ ኢትዮጵያዊ መንግስት ነው ለማለት ያስችላልን?።
የህወሓት ድራማ ቁጥር 2.
የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያን ከነ ባንዴራዋ ከፈጠሩት የታሪክ አስኳል አንዱ መሆኑን ዋቢ የሚያስፈልገው አይደለም። ቢያንስ አንድ ሶስተኛው የትግራይ ህዝብ በመላ ሀገሪቱ ከሌላው ወገኑ ጋር ተሳስሮ፣ ሀብት አፍርቶ፣ ተጋብቶና ተሰባጥሮ በነፃነት ይኖራል። በኢትዮጵያ የትግራይ ተወላጅ የሌለበት መንደር የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ሲኖርም እንደ መጤ ወይም እንደ ስደተኛ አይደለም ራሱም ሆነ ሌላው ሰው የሚያስበው “ሀገሬ!! መብቴ!! ነው” በማለት በልበ ሙሉነትና በመተማመን ይኖራል። በሌላ አነጋገር ህዝቡ ለዘመናት በጋራ የኖሮው በመልካም ጉርብትና ብቻ ሳይሆን በራሱ ፈቃደኝነት በፍቅር፣ በወንድማማችነት፣ በመከባበርና በመተማመን ላይ የተመሰረተ ባንድ እናት ሀገር ጥላ ስር ተቃቅፎ ባህሪያዊ ዝምድናን በመመስረት ነው። ዛሬ 90 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ እሴት አለን የምንለውም ይኸው ነው።
ታዲያ!! ይህ ከሆነ ሐቁ የትግራይ ህዝብ ነፃ የሚወጣው ከማን ነው? ነፃ የሚያወጣውስ ማን ነው? እውነት ለራሱ ነፃ ያልወጣና የሻዕቢያ ሎሌ የሆነውን ዘራፊና ከሃዲ ድርጅት የትግራይ ነፃ አውጪ ነኝ ማለቱ ለታላቁ ህዝብ ውርደትና ሀፍረት አይሆንም ወይ? ለመሆኑ ባድመን ጨምሮ የትግራይን መሬትና ህዝብ የተደፈረው በሀይለ ስላሴ ግዜ ነውን? በሀይለ ስላሴ ስርዓት በትግራይ ምድር ሰው እንደ አራዊት በአደባባይ ተደብድቦስ ያውቃልን? ሀገርን እያፈረሱ ነፃ አውጪ ነኝ ማለቱስ የትግራይ ህዝብ ፍላጎትና ጥቅም መጠበቅ ማለት ነውን? በኢትዮጵያ ደረጃ ትክክለኛ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትና ፍትሕ ሳይረገጋጥ በትግራይ ብቻ ትክክለኛ ለውጥ ሊረጋገጥ ይችላል ወይ? ህወሓት የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪና መድህን ቢሆን ኖሮ ህዝቡን ከሻዕቢያ ወረራ ያዳነው ማን ነው? እናንተ የትግራይ ነፃ አውጪ ነን ትላላችሁ ነገር ግን ሌሎች ከሰማንያ በላይ ብሄር ብሄረሰቦችስ ማን ነፃ ያውጣቸው?
አዎ!! ይህ ዓይነቱ ድራማና ጥያቄ ላለፉት ሶስት ዓሰርተ ዓመታት እንቆቁልሽ ሆኖ የቆየና ገና በሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ዘንድ በሆድ ውስጥ ታምቆ አንድ ቀን ሊፈነዳ የተቃረበ እሳተ ጎመራ መሆኑን አልጠራጠረም። ከላይ ለተጠቀሱት ጥያቄዎች ህወሓቶች መልስ ይሰጡኛል ብዬም አልጠብቅም። “ከኛ በላይ ወንድ የለም። ተልባ ቢንጫጫ በአንድ መውቀጫ። እኛ እንብላ እነሱ ይጩኹ። እኛ እንግዛ እነሱ ያልቅሱ። ያበጠው ይፈንዳ!! ብለው በንፁኃን ደም የሰከሩ፣ በፍቅረ ንዋይ ዓይናቸው የታወሩ፣ በቂም በቀል አእምሮዋቸው የደነዘዙና በጠባብነት ሻማ የተሸበቡ ካድሬዎችና መሪዎች ዛሬ ዊስኪ እየተራጩና ጮማ እየቆረጡ የልደት በዓላቸውን ቢያከብሩ ብዙም አዲስ ነገር አይደለም።
የህወሓት ድራማ ቁጥር 3.
የህወሓት መሪዎች ህዝቡን ለማታለል ከሚሰሩት ድራማ አንዱ በሀገሪትዋ ላይ ሕገ መንግስት፣ መድብለ ፓርቲ ስርዓት፣ ነፃ የመከላኪያ ኃይልና ፍትሕ መኖሩን ለማስረዳት ይሞክራሉ። እነዚህ መሰረታዊ መርሆዎች ለኢትዮጵያ ህዝብ ሳይሆን የአንድ ድርጅት ሞኖፓላዊ ስልጣን ለመጠበቅና ለማገልግል ሲባል ሌላ ቀርቶ ሰሞኑን የህወሓት መሪዎች ልደት ለማከበር እንዴት እንደሚጠቀሙበት ከሚከተሉት ጭብጦች መረዳት ይቻላል።
ሕገ መንግስት አለ ይሉናል። ነገር ግን በሕገ መንግስቱ የሰፈሩ መብቶች ሌላ ዜጋ እንዳይጠቀምባቸው በተግባር ተገድበዋል። ሕገ መንግስቱ በነፃ መደራጀት ይፈቅዳል በነፃ መንቀሳቀስ ግን በሽብርተኝነት አዋጅ ተገድበዋል። ሕገ መንግስቱ የመናገርና የመፃፍ ነፃነት ይፈቅዳል ነገር ግን በህዝብ ሀብት የሚተዳደሩ የብዙሓን መገናኛ አውታሮች በአንድ ድርጅት በሞኖፓል ተይዟል። የፃፈ ወይም የተናገረ ዜጋ ሁሉ ሰፈሩ ቃሊቲ ወህኒ ቤት ሆኗል። ሕገ መንግስቱ ምርጫ ይፈቅዳል ነገር ግን የምርጫው መወዳደሪያ ሜዳ ተዘግቷል። በአጠቃላይ አንድ ድርጅት ራሱ ሕግ አውጪ፣ ራሱ ሕግ ፈፃሚ፣ ራሱ ገዳይ፣ ራሱ ከሳሽ፣ ራሱ ዳኛ የሆነበት ስርዓት ነው ያለው።
በሀሪቱ መድብለ ፓርቲ ስርዓት አለ ይሉናል። ነገር ግን አውራ ፓርቲ ወይም ልማታዊ መንግስት በሚል ፓሊሲ ትርጉም ያለው ተቀናቃኝ የፓለቲካ ድርጅት እንዳይበቅል በሩ ተዘግቷል። በሕገ መንግስቱ ላይ አንድ ፓርቲ ከሌሎቹ ፓርቲዎች የበለጠ መብት እንዲኖረው ወይም በአውራ ፓርቲነት የሚፈርጅ አንቀፅ የለም። ነገር ግን ህወሓት ከሌሎቹ የተለየ መብት ያለው የበኩር ልጅ በመሆን የሀገሪትዋን ገንዘባዊ፣ ተቋማዊ፣ ማተሪያላዊና ሰብኣዊ ሀብት በቀጥታም ሆነ በተለያየ መልክ በመጠቀም በዓሉን ሲያከብር እናያለን። ሌላው ሀገር በቀል ኢትዮጵያዊ ድርጅት ያልተሰጠው መብት ለህወሓት ግን ከደደቢት በረሃ በመምጣቱና የመከላኪያ ሰራዊት ከጎኑ ስላሰለፈ ብቻ ሀገርንና ህዝብን እንደፈለገ እንዲንድ፣ እንዲዘርፍ፣ እንዲገድልና እንዲያፍን መብት ተሰጥቶታል።
መከላኪያ ሰራዊት ከፓለቲካ ነፃ ነው፣ የሕገ መንግስት ዘብ ነው፣ የህዝብ ሰራዊት ነው፣ የልማት ሰራዊት ነው፣ ወዘተ ይሉናል። ነገር ግን በተግባር ሲታይ የአንድ ድርጅት ህወሓት ጠበቃና አጃቢ እንጂ የህዝብ ወገንና መድህን ሲሆን አላየንም። ለምሳሌ ሰሞኑን እንዳየነው ሁሉ የመከላኪያ ሰራዊት ሳምንት በሚል ሽፋኝ እየተካሄደ ያለው ሰልፍና ኤግዚቪሽን ሆን ተብሎ ከህወሓት ልደት ጋር የተያያዘ እንዲሆን ተደርጓል።
“አትረፍ ያለው በሬ ቆዳውን ለከበሮ ይውላል እንዲሉ” የትግራይ ህዝብ ላለፉት አርባ ዓመታት ያሳለፈውን መከራና ስቃይ እንዳይበቃው ዛሬም ከጀርባው አልወረዱም። እንደ ህዝብ መከበር ሲገባው በአንፃሩ ህወሓት ከሕግ በላይ በመሆን አማራጭ መንገዶችን በመዝጋት የአንድ ድርጅት አገልጋይ ሆኖ እንዲኖር ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።
ስለዚህ ኢትዮጵያውያን በተለይም የትግራይ ወንድሞችና እህቶች በሙሉ!! ድርጅትና ግለ መሪዎች አላፊ ናቸው።ህዝብና ሀገር ግን ነባሪ መሆናቸውን አምነን ህዝባችንን ከጅብ ምንጋጋ እንዲላቀቅ እጅ ለእጅ ተያይዘን መነሳት አለብን እላለሁ። ዋስትናችን፣ መድህናችንና ጋሻችን አንድ ድርጅት ሳይሆን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዝብ መሆኑን አማራጭ የሌለው የህልውና ጥያቄ ነው። ስለዚህ አንድ ድርጅት ወይም ግለሰቦች መምረጥ እንችላለን ነገር ግን አንዲት እናት ሀገር ነው ያለችን ሌላ አማራጭ የለንም።
(የሳዑዲ ጉዳይ) የማለዳ ወግ …በጭካኔ እየተገዳደልን ፣ ወዴት እየሔድን ነው ? –ነብዩ ሲራክ ከሳዑዲ አረቢያ
” ጩኸት ሰሚ ሲያጣ እንዴት ያናዳል … ሀበሻ የድሮወቹ የሉም … ወድ የሆነውን የሰውን ደም በከንቱ የሚጠጡ እርኩስ መንፈስ የተጠናውታቸው ውሾች ናቸው .so ሰሞኑን በ ጅዳ አካባቢ ሸር ሄራ አካባቢ የተደረገውን ግፍ ልንገርክ …በሀበሾች ጭካኔ የተገደለውን ልጅ በአካል አውቀዋለሁ አብዱ ሁሴን ይማም ይባላል … በሳንጃ ገደሉት ! ልብ በል … የሳውድ መንግስት ታዲያ እንዴት አያሳድደን ! እንደነዚህ አይነት እርኩሶች እያሉ እኛ ቤተሰብ እንዴት እንርዳ? ልጅስ እንዴት እናስተምር? ..ነብዩ ሰው እንዴት …የሰውን ነፍስ ያጠፋል? ደግሞም ሳውዲ ውስጥ ? ከተሰራ ለሚገኝ ገንዘብ እጅግ ያሳዝናል ይጎመዝዛል ! ጌታ እውነቱን ይፍረድ ለሀበሻ ጩኸት በቃኝ እኔም ሀበሻ ነኝ!!! ” ይላል !
ሰሞኑን “ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያዊ ላይ በግፍ የግድያ ወንጀል ተፈጸመ !” የሚለው ወሬ ከጓዳ እስከ አደባባይ ሲናኝ አስከፊውን ሂደት የታዘቡ ወገኖች ኢትዮጵያውያን ብቻ አልነበሩም። ጉዳዩን በቅርብ ከሚያውቁና ከሚከታተሉ የሃገሩ ሰዎችም መልዕክቶችና አስተያየቶች ደርሰውኝ በሃፍረትም ቢሆን ለማስተናገድ ተገድጀም ነበር … የሟችን ጉዳይ በቅርብ የሚከታተሉ ፣ ኢትዮጵያን የሚወዱና ስለኢትዮጵያ የሚጽፉ ፣ አንድ ከፍ ያለ ሃላፊነት ያላቸው የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያና ሃያሲ የሃገሩ ሰው አዝነውብን አግኝቻቸዋለሁ ። በቁም ነገር በቢሯች አስጠርተው ያሉኝ እንዲህ ነበር ” ምንድን ነው እየሆነ ያለው? ምንድ ነው እንዲህ የመሰለ የዘቀጠ በሃበሾች ያልተለመደ ጉዳይ ተደጋገመሳ ? ሀበሾች ምን ገባባችሁ? ከአመታት በፊት በሪያድ መንፉሃ ፣ ከወራት በፊት በመዲና በአብሃ እና በዙሪያው ያን ሰሞን ደግሞ በኪሎ ተማንያ እና በዙሪያው በሃበሾች መካከል መጨካከን የተሞላበት ድርጊት ታይቷል። ከሁሉም የሚያሳዝነው የግድያ ምክንያቶቹ ጊዜያዊ ጸብን ፣ ጥቅምንና ጥቃቅን የሰው ህይዎትን በጭካኔ ሊያስጠፉ የማይገባቸው ምክንያቶች ናቸው ። ግን ምንድን ነው እየሆነ ያለው? ወደ የትስ እየተኬደ ነው? ” ሲሉ በጥያቄ ላፋጠጡኝ ሳውዲ ወዳጀ የሚሆን መልስ ግን አልነበረኝም ! ብቻ የሆነው አሳዝኖ ፣ አሳፍሮ አንገቴን አሰበረኝ …
እርግጥ ነው ፣ ባሳለፍናቸው አመታት በሪያድ መንፉአ አካባቢ አልፎ አልፎም በኢትዮጵያውያኑ መካከል በሚፈጠር ግጭት ቁጥራቸው ከፍ ያሉ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ዜጎች በሰላ ጩቤ አሰቃቂ ጥቃት ተፈጽሞባቸው የመቁሰልና የመገደል አደጋ ምክንያት እንደ ነበር የአይን እማኞች አጫውተውኝ ነበር ። በጩቤ ለመወጋጋቱ ዋንኛ ምክንያትም ደግሞ ተራ ከገንዘብና ከሴት ጋር የተያያዙ እዚህ ግቡ የማይባሉ መሆናቸው ማጤንና መገንዘብ ደግሞ በእጅጉ ያሳዝናል …በቀደሙት ጥቂት አመታት በሳውዲና የመን ድንበር ከተሞች ይህ መሰሉ ወንጀል የከፋ እንደ ነበር አውቃለሁ። በተለይም በጀዛን ፣ በአብሃና በከሚስ ምሽት በሚባሉ አካባቢዎች በዙሪያው ባሉ የከተማና የገጠር ከተሞች በከተሙ ኢትዮጵያውያን መካከል ተፈጸሞ የምንሰማው ግድያ ፍጹም ጭካኔ ያልተለየው መሆኑ ይጠቀሳል ! ወደ አብሃና ከሚስ ምሸት ለስራ ባቀናሁባቸው ቀናት በእኛ ዙሪያ እየሆነ ያለውን ለመስማት የከበደ መረጃ በእጀ መድረሱን አስታውሳለሁ። በህገ ወጥ መንገድ ዜጎቻችን ከየመን ሳውዲ በሚያመላልሱ ለገንዘብ በገንዘብ እየሸጡ የሚተዳደሩ ደላሎችና አቀባባዮች በጎሳ ተቧድነውና ብሔርን ለይተው የሚከሰተውን ግጭት ከጩቤ ያለፈ እንደ ነበርም በቦታው ተገኝቸ ታዝቤያለሁ። በተለይም በአብሃ አካባቢ በግጭቱ ስለተቀጠፈው ህይዎት ፣ ፍርድን ይጠባበቁ ስለነበሩ የእኛ ገዳዮችም የፍርድ ሂደት በቅርብ እከታተል ነበር ። ከሁሉም የሚያሳዝነው የሰውን ልጅ ያህል ታላቅ ፍጡር በስለት የሚጠፋበትን ምክንያት መስማት እንደ ነበርም ትዝ ይለኛል። ከሃገር ቤት ያለ የዘር ፣ የግል ጥላቻና ጸብን መሰረት ያደረገው የደም መቃባት ፣ በገንዘብ መካካድ ” ጓደኛየን ነጠቀኝ!” ፣ “የሰማንያ ሚስቴን ደፈረ !”፣ በሚሉትና በመሳሰሉት ክሶች የሚያጠነጥነው ብቀላ በፍትህ ሳይሆን በጭካኔ ለመወጣት የሚፈጸም ያረጀ ያፈጀ ይትበሃል ሳውዲ ተከትሎን መጥቶ ስማችን ማርከሱ ደግሞ ከሁሉም በላይ ያማል!
በያዝነው አመት ከጅዳ በ400 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘው በሙስሊማን ቅዱስ ከተማ በመዲናም በዜጎቻች መካከል በተፈጠረ የቨዛ ሽያጭ እና ተጓዳኝ የገንዘብ መካካድ ያስከተለው አምባጓሮ በቅዱሷ ከተማ ቅዱስ የማይባል ግድያ ለመፈጸሙ ምክንያት ነበር ። ይህም የጭካኔ ወንጀል የተፈጸመበት ኢትዮጵያዊ ፣ ወንጀል ፈጻሚው ኢትዮጵያዊው መሆኑ ደግሞ ጉድ አሰኝቶ አሳፍሮን አልፏል። ከወራት በፊትም እዚሁ ጅዳ በተለያዩ አካባቢዎች በኢትዮጵያውያን መካከል የተነሱ አምባጓሮዎች በተመሳሳይ ጭካኔ በተሞላባቸው የግድያ ድርጊቶች የተከበቡ ወንጀሎች ምክንያት ነበሩ ማለት ይቻላል። እናም ጉዳዩ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል ….
ባሳለፍነው ሳምንት በጭካኔ የተገደለው ወንድም ወንጀል ተጠርጣሪ ፣ ተጠያቂ የቅርብ ጓደኛ ወዳጁ እንደነበረና ከቀናት በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉን ሰማን ! አብዱ በማጣታቸው ትልቁ የሃዘን መርግ የወደቀባቸው፣ የሚይዙት የሚጨብጡ ያጡት ፣ ቤታቸው የጨለመባቸው አንዲት ሴት ልጂና የስድስት ወር ነፍሰ ጡር ባለቤቱ ሃዘን የከበደ ነው…ስለአብዱን ቅንነት፣ ሰው አማኝ ፣ ትጉህና ታታሪነቱን የሚመሰክሩት ባልንጀሮቹም ሃዘናቸው መሪር ያደረገው የተፈጸመው የጭካኔ ወንጀል ብቻ ሳይሆን የወንጀሉ ቀዳሚ ተጠርጣሪ የቅርብ ወዳኛ መሆኑ ነበር ። በዚህም ሊያምኑት በከበደ ድርጊት እርር ድብን ብለው አዝነዋል! ዛሬ የማይሰማ የማያየን አብዱ ሁሴን በሰላሳዎቹ የእድሜ ክልል ይገኝ እንደነበር በቅርብ ጓኞቹ ጨምረው አጫውተውኛል ። የወንድም አብዱ ሁሴን ይማም የቀብር ስነ-ስርዓት ትናንት የካቲት 12 / 2006 ረቡዕ ከቀትር በኋላ በጅዳ ከተማ ተፈጽሟል ! አብዱ የሔደው ሁላችንም ወደ ማንቀርበት የላይኛው ቤት ነው ! ነፍሱን ይማረው ! ” አላህ ይርሃሙ !”
ወንጀሉን በትኩሱ ለማቅረብ በፖሊስ ክትትክ መሆኑና ተጠርጣሪ ወንጀለኛው ባለመያዙ የማለዳ ወጌን እንዳዘገየው ቢያስገድደኝም መረጃውን ባሳለፍናቸው ቀናት ከበርካታ ነዋሪዎች አስተያየቶችን ለመሰብሰብ ሞክሬ ነበር ። በዚህ መሰል ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ዙሪያ እየተነጋገረ የሚገኘውን አብዛኛው የጅዳ ነዋሪ ” ህጋዊ ህገ ወጥ ” ነገን ምን ይከተል ይሆን እያለ በጭንቀት በሰቀቀን እየጠበቀ ባለበት ሰአት የዚህ መሰሉ ድርጊት መፈጸም ” እንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ !” ሆኖበት ተመልክቻለሁ! ለእኔም የሆነብኝ እንዲያ ነው …
ድርጊቱ አሳዝኖኝ ለማውገዝ ያነሳሁት ብዕር መቋጫ የሚሆነው ሳውዲው ሃያሲ ወዳጄ ያጫወቱኝን ዘልቆ የሚሰማ ያልመለስኩት ጥያቄ ነው ። ሃያሲው ሃበሾች በዚህ መሰል ድርጊት እንደማንታወቅ ተንትነው ከቅርብ አመታት የሰበሰቧቸው መረጃዎች ቢያሳስቧቸው ቆጣ ብለው በንዴት ሲያጠይቁ “ግን ምንድን ነው እየሆነ ያለው? ወደ የትስ እየተኬደ ነው? ” ነበር ያሉኝ …እኔም ተጠርተን የማናውቅበት ወንጀል ሲደጋገም አሞኛልና ድርጊቱን አወግዘዋለሁ! ወደ መጨረሻም አሳፍሮ መልስ ያጣሁለትን የሃያሲውን ወዳጀ ጥያቄ ላጠይቅ ግድ አለኝ … ግንስ … በጭካኔ እየተገዳደልን ፣ እየተጠላላን ወዴት እየሔድን ነው ? ምንድን ነው እየሆነ ያለው?
ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ
[የረዳት አብራሪው ጉዳይ] ሕዝብን አፍኖ እና ረግጦ በመግዛት የስልጣን እድሜን ማራዘም አይቻልም
ዘረኛው እና አምባገነኑ የወያኔ ኢህአዲግ መንግስት ወደስልጣን ወንበር በሀይል ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያን ሕዝብ አፍኖና ረግጦ መግዛትን ተያይዞታል:: በአሁኑ ጊዜ ወያኔ የሚያራምደው በዘረኝነት የተሞላው የተሳሳተ እና የተወላገደ ፖለቲካ ሕዝቡን ከማማርር ባለፈ የኑሮ ውድነቱ፣ ስራ አጥነቱ፣ እና በሀገሪቷ ላይ ክፉኛ ወንጀል መበራከቱ እና በየሁሉም መስሪያ ቤቶች ከቀን ወደ ቀን ሙስና፣ ሌብነትና አይን ያወጣ ዝርፊያ እየጨመረ መምጣቱ የኢትዮጵያ ህዝብ የሰቋቋ እና የመከራን ኑሮ መኖርን ተያይዞታል:: ወያኔ እያራመደው ያለው በዘር የተሞላ ፖለቲካ አንዱን ዘር ከአንዱ ዘር በማበላለጥ እና በመከፋፈል አንዱን ዘር ከፍ ሌላውን ዘር ዝቅ በማድረግ ፣ እያወረደ እና እየናቀ ዜጓች በገዛ ሀገራቸው እና ምድራቸው ላይ በሰላም እና በነጻነት እንዳይኖሩ ይኼው የወያኔ መንግስት ሲፈልግ ነፍጠኛ፣ ጉርጠኛ፣ትምክህተኛ፣ ተገንጣይ፣አሸባሪ ወዘተ….. በማለት ሕዝቦችን በማስፈራራት እና ነጻነትን በማሳጣት በሀይል እና በጉልበት አፍኖ እየረገጠ በመግዛት ላይ ይገኛል::
በአሁኑ ወቅት ተማሪው ተምሮ ስራ ለማግኘት እና ለመቀጠር ሰራተኛውም በስራው ገበታው ላይ ለመቆየት እና ስራውን በነጻነት ለመስራት በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ የታወቀ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ጥራት በሌለው የወያኔ የትምህርት ፖሊሲ ከመንግስትም ሆነ ከግል ዩንቨርስቲ እና ኮሌጆች ብዙ ወጣት ተማሪዎች በሀገሪቷ ላይ ትምህርታቸውን ጨርሰው ቢመረቁም በስራ አጥነት እየተንከራተቱ የሚገኙ ዜጓች ቁጥራቸው ከቀን ወደቀን እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን በአሁን ጊዜ በኢትዮጵያ አንድ ሰው የሆነ መስሪያ ቤት ውስጥም ሆነ ድርጅትውስጥ ስራ ለማግኛት እና ለመቀጠር የግድ የወያኔ ኢህአዲግ አባል መሆን የሚጠበቅበት ሲሆን በስራ ገበታም ላይ ያሉ ሰዎች ቢሆንም እንኮነ በሚሰሩበት ቦታ የግድ የወያኔ አባል እስካልሆኑ ድረስ ነጻነት እንደሌላቸው ፣ ስራቸውንም በነጻነት መስራት እንደማይችሉ የተለያዩም ግፍ እና ጭቋናዎች እንደሚደርስባቸው የታወቀ ነው::
በቅርቡ መምህር አማኑኤል መንግስቱ የተባለ የማዝገበ ብርሀን አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ትምህርት ቤት መምህር የአንድነት አባል በመሆኑ በሚያስተምርበት ትምህርት ቤት የወያኔ ካድሬ በሆነ በትምህርት ቤቱ አስተዳደር የተለያዩ ዛቻዎችና ማስጠንቀቂያዎች እየደረሱበት እንደሆነ እና ከስራም ሊባረር እንደሚችል የማስንጠቀቂያ ደብዳቤ ከትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር እንደደረሰው የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ መዘገቡን አስታውሳለው:: ይህን እንደምሳሌ አልኩኝ እንጂ በጣም ብዙ ዜጓች ናቸው በየሚሰሩበት መስሪያ ቤቶች በዘር በተበላሸ በወያኔ ፖለቲካ አመለካከት የኢህአዲግ አባል ባለመሆናቸው የሚጨቁኑት ነጻነታቸውን አተው በሀገራቸው ተሸማቀው በወያኔ ካድሬዎች ታፍነውነው እና ተረግጠው የሚኖሩት ::
የወያኔ ባለስልጣናት ሊያውቁ የሚገባው ነገር ሕዝብን አፍኖ እና ረግጦ በመግዛት የስልጣን እድሜን ማራዘም እንደማይቻል ነው :: ለዚህም በዚህ ሳምንት የተከሰተው እና የአለም መነጋገሪያ እየሆነ ያለው እና የብዙ አለማት ሚዲያን ቀልብ የገዛው የረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራ የአውሮፕላን ጠለፋ ትምህርት ሊሆናቸው ይገባል :: ረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራ በእኔ አመለካከት ጀግና ነው ክብርም ይገበዋል :: ምንም እንኮን የሰራው ስራ የሚያስፈራ እና ዋጋ የሚያስከፍልም ቢሆንም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የወያኔ የተበላሸ የፖለቲካ አካሂድ ምን ያክል የከፋ እንደሆነ ፣ የደህንነት ስጋት ፤የአስተዳደር ብልሹነት እና የዘረኝነት መድልዎን ከመቼውም ጊዜ የባሰ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለአለም ሕዝብ ያመላከተበትን ጀብዱ ፈጽሞል:: ስለዚህ ፓይለት ሃይለመድህን አበራ በዘር ለተረገጦ ፣ ለተገፉ እና ለተጨቋኑ ኢትዮጵያኖች ድምጽ ሆኖል ነው የምለው ::
ፓይለት ሃይለመድህን አበራ አስቦ እና አቅዶ የተነሳበት ዋንኛው አላማ ይኼው ይመስለኛል:: የመንግስት ቃል አቀባይ ተብዪው አቶ ሬድዋን ፓይለት ሃይለመድህን ሙሉ ጤነኛ ሰው እንደሆነ ለአምስት አመታት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አብራሪ ሆኖ እንዳገለገለ ፣ የሽንገን ቪዛ እንዳለው ፣ነጻ ትኪት እንደሚያገኝ እና የትም ሀገር ሂዶ ትምህርቱን መቀጠል እንደሚችል ነገር ግን ፓይለት ሃይለመድህን ለእራሳቸውም እንደገረማቸው እና እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው ሲናገሩ ተደምጠዋል በርግጥ ልክ ነው ወጣቱ ፓይለት ሃይለመድህን የትም ሀገር ሂዶ አሳይለም የመጠየቅ እድል (opportunity) ይኖረው ነበር ብዙም ሰዎች በዚህ ጉዳይ ላይ የራሳቸውን ሀሳብ እየሰነዘሩ ሲሆን በኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ ደህንነት ስራ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ያገለገለውና በክትትልና ደህንነት ስጋት ከአመት በፊት ድርጅቱን ለቆ በስዊዘርላንድ ጥገኝነት የጠየቀው አንድ የቀድሞው የድርጅቱ ሰራተኛ አቶ ሚካኤል መላኩ የካፒቴን ሃይለመድህን አበራ የጠለፋ ምክንያት በአየር መንገዱ ውስጥ የሚታየውን የአስተዳደር መበላሸት ለአለም ለማሳየት ሊሆን ይችላል የሚለው ምክንያት አሳማኝ ነው ሲል ከኢሳት ጋር ባደረገው ቃለምልልስ የተናገረው ነገር ትክክል ነው ብዪ አምናለው::
ፓይለት ሃይለመድህን አበራ በድፍረት የተሞላ ጀብዶ መፈጸሙ የወያኔን ባለ ስልጣናቶች ያስደነገጠ፣ ያሳፈረ እና ያሸማቀቀ ተግባር ሲሆን በወያኔ መንግስት በዘር፣በሀይማኖት ተገፍቶ እና ተጨቆኖ ላለው ምስኪኑ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ደስ የሚያሰኝ ተግባር ነው :: ምክንያቱም ህወሃት መራሹ መንግስት እያራመደ ባለው የዘረኝነት ፖለቲካ በሀገሪቱ ላይ ያላው የደህንነት ስጋት፣ አፈና እና ሰበሃዊ መብት ረገጣ ምን ያህል እየከፈ መምጣቱን ለአለም ሕዝብ ያመለከተበት ተግባር በመሆኑ:: ስለዚህ የወጣት ፓይለት ሃይለመድን ጀግንነት የተሞላበት ተግባር ወኔ እና ብርታት ሆኖን በወያኔ ታፍኖ እና ተረግጦ መገዛትን እንቢ በማለት እና የወያኔን በዘረኝነት የተሞላውን ፖለቲካ በመቃወም በአደባባይ በማውጣት ወያኔን በማስረበሽ እና በማስደንገጥ የስልጣን እድሜውን ማሳጠር የመላው ኢትዮጵያኖችን ነጻነት መወጅ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የዜግነት ግዲታ መሆን ይጠበቅበታል::
ፍትህና ነጻነት ለሚናፍቅ ኢትዮጵያዊ የማስተላልፈው መልህክት ህወሃቶች ዜጎችን ከሰው በታች አድርገው ለመግዛት እንዲመኙ ያደረጋቸው በእብሪት የተሞላ የፖለቲካ አካሄድ የሚተነፍስበት ዘመን እሩቅ አይሆንምና አሁንም አትፍሩ።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
gezapower@gmail.com
ቦይንግ 767 –እገታ እና እንድምታው –ክንፉ አሰፋ (ጋዜጠኛ)
አንድ የኢህአዴግ ካድሬ፣ ቤት ለመከራየት ወደ አንዲት ወይዘሮ መኖርያ ይሄዳል። ስፍራው እንደደረሰ ሌላ ተከራይም ከወይዘሮዋ ቤት ብቅ እንዳለ አስተዋለ። ሌላኛው ተከራይ ሰይጣን ነበር። ሁለቱ ተከራዮች ሰርቪስ ቤቱን ለመያዝ እንደ ጨረታ ብጤ ጀመሩ። ሰይጣኑ 400 ሲጠራ፣ ካድሬው ግን 500 ሊሰጥ ተስማማ። በመጨረሻ፣ ወይዘሮዋ ቤቱን ለሰይጣኑ በትንሽ ዋጋ ማከራየቱን መረጡ። የወይዘሮዋ ውሳኔ እንግዳ ነገር ነበር። ለሰይጣን፣ ለዚያውም በትንሽ ዋጋ ቤታቸውን ለመስጠት የወሰኑበትን ምክንያት ሲጠየቁ፤ “ሰይጣኑ አልወጣ እንኳን ቢል በጸበል ይለቃል። ካድሬው ገብቶ ቤቴን አልለቅም ቢለኝ ምን ላደርግ ነው?” ነበር ያሉት ወይዘሮዋ። ከፍ ባለ ገንዘብ ለኢህአዴጉ ሰርቪስ ቤታቸውን ቢያከራዩት ኖሮ ባጭር ጊዜ ዋናውን ቤታቸውን ለቀው የመውጣት ክፉ እድል ይገጥማቸው ነበር።
ዶ/ር መረራ ጉዲና ባለፈው ሳምንት ዘ ሄግ ላይ ስለ ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ሲነግሩን ጣል ያደረጓት ቀልድ ናት። የዚህች ቀልድ የፖለቲካ እንድምታ ቀላል አይደለም። መልእክትዋ ሲጠቃለል የኢትዮጵያን ህዝብ እየለቀቀ መሆኑን ትነግረናለች። እየከፋ የመጣው የኑሮውና የፖለቲካ ሁኔታ የህዝቡን አእምሮ ብቻ አይደለም እየነካው ያለው። ህዝቡ እየተገፋ ሃገርሩን ለቆ እንዲሰደድ እየተገደደም ይገኛል። በተለይ ደግሞ ሃገሪቱ በድህነት ያስተማረቻቸው ምሁሮችዋንና ባለሞያዎችዋን እንደዋዛ እያጣች ከመጣች እነሆ ሁለት አስርተ-ዓመታት ተቆጠሩ።
እለተ ሰኞ የካቲት 10፣ 2006 ዓ.ም.።
የአለም ዜና ርዕስ ሁሉ ትኩረት የጣለው በኢትዮጵያዊው ፓይለት ጉዳይ ላይ ነበር። እንደዚህ አይነት ክስተት ሲፈጸም አዲስ አይደለም። ግን ይኽኛው ልዩ ነው። ይዘቱ ለየት ይበል እንጂ በ 1998 (እ.ኤ.አ.) ዩዋን ቢን በተባለ ቻይናዊ ፓይለት ከተፈጸመው ድርጊት ጋር ይመሳሰላል። የ30 አመቱ ወጣት የበረራ ቁጥር CA905 የሆነውን የቻይና አውሮፕላን በመያዝ የታይላንድን የአየር ጠረፍ ሰብሮ ገባ። የ27 አመት እድሜ ያላት ሚስቱን ይዞ ታይዋን ላይ ያረፈው ፓይለት ለዚያ አደገኛ ውሳኔ የሰጠው ምክንያት የኢኮኖሚ ችግር ነበር። የደረጃ እድገት፣ የደሞዝ ጭማሪ፣ የመሳሰሉ ከራስ ወዳድነት ያላለፉ ጥያቄዎች በማንሳት የፓይለቱ የራሱን ክብር ዝቅ አደረገው።
በ 1995 (እ.ኤ.አ.) ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ በግዳጅ ከአውስትራልያ ወደሃገሩ እንዲመለስ ተደረገ። ኢትዮጵያዊ ግን የኦሎምፒክ አየር መንገድ ንብረት የሆነውን ጀት ግሪክ ላይ ለመጥለፍ በመሞከሩ የአለምን ዜና ርእስ ሆኖ ነበር። ጋዜጠኛው የፕላስቲክ ቢላዋ የበረራ አስተናጋጅዋ አንገት ላይ በመደገን ወደ ሀገሩ እንዳይላክ ጥያቄ አቀረበ። በመጨረሻም ኢትዮጵያዊ ወገን ባደረገው ርብርብ የዚህ ወጣት አላማ ተሳካለት።
የሃይለመድህን አበራን ጉዳይ ለየት የሚያደርገው ለዚህ ከባድ ውሳኔ የሰጠው ምክንያት ነው። የግል ሳይሆን የሃገር፣ የራስ ሳይሆን የወገን ጉዳይ። ረዳት ፓይለቱን እብድ ያሰኘውም ይኸው ነገር ይመስለኛል። ሃይለመድህን የ40 ሺህ ብር ደሞዝተኛ ነው። በኑሮው ምንም የጎደለበት ነገር የለም። ከመካከለኛው ኢትዮጵያዊ ዜጋ በላይ ይኖራል። የስደት ጥማት እንኳን ቢኖርበት ለመሰደድ በዚህ ሁኔታ አውሮፕላን ማገት እንደማይኖርበት ጠንቅቆ ያውቃል። ለዓለም ህዝብ ማስተላለፍ የሚፈልገው አንድ መልእክት ነበር። “ሜይዴይ… ሜይዴይ… የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር ላይ ነው!”
ተልእኮው በሚገባ ተሳክቷል።
ሰኞ ማለዳ የመስርያቤታችን የውይይት ርእስ የነበረው ጄኔቭ ላይ ሳይታሰብ ያረፈው ቦይንግ 767 ጉዳይ ነበር። የረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራ ታሪካዊ ውሳኔ የስራ ባልደረቦቼን ከሁለት ጫፍ ከፍሎ ለረጅም ውይይት ጋብዟቸውዋል። አንደኛው ወገን ፓይለቱ ያደረገው ጠለፋ ነው ብሎ ሲከራከር፤ ሌላኛው ወገን ደግሞ ድርጊቱ እንደጠለፋ መታየት የለበትም ይላል። የሁለቱን ወገን ክርክር እየሰማሁ ምንም ሳልተነፍስ ለረጅም ግዜ ቆየሁ። አእምሮዬ ግን አንድ ነገር ላይ ተጠምዶ ነበር። ክስተቱ ለፖለቲካ ደንታ የሌላቸውን እነዚህ ነጮች ማነጋገር መቻሉ እጅግ ደንቆኛል። “ወጣቱ ፓይለት ምን ያህል በደል ቢበዛበት ይሆን ለዚህ ካባድ ውሳኔ የበቃው?” የሚለው ጥያቄ በብዙዎች አእምሮ ይመላለስ የነበረ ጉዳይ ነው። አብዛኞቹ ስለ ኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ሁኔታ በደንብ እንዲረዱ ማድረጉም አልቀረም። ጅብ በቀደደው ውሻ ይገባል’ ነውና ሁሉንም ነገር ለማስረዳት አሁን በጣም ቀላል ሆነ።
ሃይለመድህን አበራ ‘እብድ ነው’ የሚሉም አልጠፉም፤ ልክ እንደ አፈቀላጤው ሬድዋን። ለነጮቹ ነገሩ እንግዳ መሆኑ አልቀረም። ፓይለት ሆኖ፣ ጥሩ ኑሮ እየኖረ፣ ቤት- ንብረቱን፤ የሚወዳት ሃገሩንና ቤተሰቡን ትቶ ለእስራት፣ ለስደትና ለእንግልት ራስን ማዘጋጀት እብደት ነው ሊባል ይችላል።
በኢትዮጵያ ተመክሮም የፓይለት ሞያ ያስከብራል። በሃገራችን የፓይለቶች የኑሮ ደረጃ አንደኛውን ረድፍ ይይዛል። ይህንን የመሰለ ህይወት ጥሎ የስደትን ኑሮ መምረጥ የሚያስችል ውሳኔ ላይ መድረስ ደግሞ እብድ ቢያስብል የሚደንቅ አይደለም። የሚገርመው የስርዓቱ ካድሬዎች ይህንን አባባል መደጋገማቸው ነው። ከራሳቸውም አልፈው የፓይለቱ ቤተሰቦችን በማስፈራራት ይህንን እንዲመሰክሩ ሲያደርጉ ይታያል። ወትሮውን በእብዶች መሃል አንድ ጤነኛ ሰው ካለ፣ እሱ እብድ ነው። እነሱ በሰብአዊ መብት ላይ ሲቀልዱ በዚያ የማይተባበራቸው ሁሉ እብድ ነው። ለህሊናው ሳይሆን ለመኖር ሲል ሰበአዊ መብቱ ላይ የማደራደር ሁሉ ሽብርተኛ – አልያም የአእምሮ በሽተኛ ነው።
እብድ ሰው ያንን ግዙፍ አውሮፕላን በስርዓት አብርሮ፤ በስርዓት ካሳረፈ፤ በኢትዮጵያ ፓይለት ለመሆን የቅጥር መስፈርቱ እብድ መሆን ነው። ግና በአውሮፕላኑ የነበሩ 202 ተሳፋሪዎችን ምን እንደተፈጠረ እንኳን ሳያውቁት ጄኔቭ ላይ ማረፋቸው ብቻ እነሱ የሚሉት ይጻረራል። ሃይለመድህን ዋናውን ፓይለት በሃይል አላስገደደውም። ተሳፋሪዎች እንዳይረበሹም ስለድርጊቱ አንዳች ነገር አልተነፈሰም።
ለባለስልጣናቱ ጥያቄ አለኝ። የሃይለመድህን እብድ መሆኑን እያወቁ ለምን ፓይለት አድርገው ቀጠሩት? የእሱ እብድ መሆኑ ለባለስልጣኖቹ እንዴት አሁን ታያቸው?
ያም ታባለ ይህ – የካቲት 10፣ 2006 ዓ.ም. በስዊስ ላይ የተፈጠረው ነገር “ከሺ ቃላት… ” እንደሚሉት አይነት ነው። አንዲት ትንሽ ድርጊት የአለምን ህዝብ ከጫፍ እስከጫፍ አነጋገረች። ሃይለመድህን በአንዲት ቅጽበት እና በአንዲት ቃል ብቻ ላለፉት 20 አመታት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ይፈጸም የነበረውን ግፍ ሁሉ ለአለም አሳወቀ። ይህንን ለማድረግ ግን ራሱን መስዋዕት ማድረግ ነበረበት። ወጣቱ ሊደርስ የሚችልበትን ነገር ሁሉ አስቀድሞ ያውቀዋል። ከሃገር አመራረጥ ጀምሮ የወሰዳቸው እርምጃዎች በሙሉ የተጠኑ እና በጥንቃቄ የተደረጉ መሆናቸውን ሂደቱ ራሱ ይመሰክራል።
ወጣቱ ፓይለት ሃገሩን ይወዳል። የልጅነት ህልሙን እውን ያደረገበትን የፓይለትነት ሙያም ያከብራል። ለኢትዮጵያ አየር መንገድም የተለየ ክብር አለው። ራስ ወዳድ ቢሆን ኖሮ ፓይለት ሁሉ እንደሚኖረው በሃገሩ እየሰራ መኖር ይችላል። እንደ እብደት ያስቆጠረበት የዚህ ውሳኔ ምክንያቱ ግን ለህሊናው ብቻ ተገዥ መሆኑ ነው። ለሱ ቅርብ የሆኑትም ይህንኑ መስክረዋል።
በሃገራችን ሰርቶ የመኖር ዋስትና በአንባገነኖች እጅ ላይ ወድቋል። በነጻነት የመስራት፣ በነጻነት የመናገር፣ በነጻነት ሃሳብን የመግለጽ…ወዘተ ዋስትና ሳይኖር የመኖር ትርጉሙ ምንድነው? ሰው ያለ ነጻነት ምንድነው? ለመኖርማ እንስሳትም እየበሉ ይተኛሉ እየተነሱም ይበላሉ – ከዛ ይተኛሉ። ከእንስሳ የሚለየን ነጻነታችን መሰለኝ። ያለ ነጻነት ህይወት ትርጉም የለውም።
በኢትዮጵያ 80 ሚሊየን ህዝብ ያለነጻነት ይኖራል። ሃይለመድህን በአንዲት ቅጽበት የዚህ ሁሉ ህዝብ ድምጽ ሆነ። የ80 ሚሊየን ህዝብ ድምጽ ሆኖ በራሱ ላይ መፍረድ መቻል ደግሞ እብደት ሳይሆን ጀግንነት ነው። አንድ ሰው እንዴት መኖር እንዳለበት፣ ምን መናገር እንዳለበት…ወዘተ ሲወሰንት ለአንባገነኖች ብቻ ሳይሆን ለራሱ ህሊናም ባርያ ይሆናል። በተለይ የራስ መተማመን እና የሙያው የተካነ ሰው ተገዥ የሚሆነው ለህሊናው ብቻ ነው። እንዲህ አይነቱ ሰው መብቱን ለድርድር አቅርቦ ራሱን በባርነት አያስገዛም። በመብቱ ላይ የሚደራደር ካለ ህሊናውን የሸጠ ሰው ብቻ ነው። ነጻነት የሚገዛ ውይንም የሚሸጥ ነገር አይደለም። ነጻነትን ሊገዛው የሚችለው ህሊናችን ብቻ ነው። ያለ እራሳችን መልካም ፈቃድ ደግሞ ማንም ሃይል ነጻነታችንን ሊደፍር አይቻለውም። ሰዎች በአካል ሊታሰሩ ይችሉ ይሆናል። የሰውን ህሊና ግን ማንም ሃይል ሊያስረው አይችልም። ኔልሰን ማንዴላ ለ27 አመታት ሲታሰር ህሊናው ነጻ ነበር። በአንጻሩ አሳሪዎቹ ነጮች የአካል ሳይሆን የህሊናቸው እስረኞች ነበሩ።
ሃይለመድህን የህዝብ ድምጽ በመሆን ከህሊናው ጋር የገጠመውን ሙግት ያሸነፈ ጀግና ነው። አላማው በውስጡ የቆሰለበትን የኢትዮጵያ ህዝብ ሰቆቃ ለአለም ለማሳወቅ ነበር። ይህ ባይሆን ኖሮ ችግር ውስጥ ያማያስገቡት ሌሎች ብዙ አማራጮች እና እድሎች ነበሩት። “ዘ ክርስቲያን ሳይንስ ሞኒተር” የተባለው ጋዜጣ የሃይለመድህንን ስደት መጠየቅ አስመልክቶ ባሰፈረው ዘገባ የኢህ አዴግ ስርአት ብልሹነትና የሰብአዊ መብት ረገጣው መባባሱን በስፋት ዘግቧል። ሌሎች መገናኛ ብዙሃንም የሃገሪቱን ሁኔታ ትኩረት ሰጥተው እንዲመረምሩት አድርጓቸዋል።
ዶ/ር መረራ ጉዲና ሲነግሩን የኢሕአዴግ እድገትና ትራንስፎርሜሽን ሃገሪቱን ወደ ጥርነፋ ፖለቲካ እና ቁምራ ኢኮኖሚ አሸጋግሯታል። ጥርነፋ እና ቁምራ አዲሶቹ ኢህአዲግኛ ቋንቋዎች ናቸው። ጥርነፋ ማለት አንድ ሰው አምስት ሰዎችን እየሰለለ በማገት ከገዥውፓርቲ አሰራር እንዳያፈነግጥ የማሰርያ ዘዴ ነው። ማንነትን የሚፈታተነው ይህ አሰራር አየር መንገድን ጨምሮ በሁሉም መንግስታዊ ተቋማት ተግባራዊ እየሆነ መጥቷል።
ቁምራ ደግሞ ቁርስ፣ ምሳና ራት በአንድ ግዜ ማለት ነው። ነብሳቸውን ይመርና አቶ መለስ በአንድ ወቅት ሲጠየቁ የኢትዮጵያ ህዝብ ሶስቴ በልቶ እንዲኖር ነበር ህልማቸው። እነሆ ዛሬ 70 በመቶው የኢትዮጵያ ህዝብ ሶስቱንም የእለት ምግብ አንድ ግዜ በቁምራ እንዲያጠቃልል አበቁት። 10ሺህ የሚሆን የአዲስ አበባ ነዋሪ የሚተዳደረው ከቦሌ አየር መንገድ እና ከሆቴሎች የሚጣል ቆሼ እየበላ ነው። በአንጻሩ ደግሞ እነ ስብሃት ነጋ ለአንዲት ጠርሙስ ሉዊስ ኮኛክ 260፣ 000 (ሁለት ሞቶ ስልሳ ሺህ ብር) ያወጣሉ። የ100 ሺህ ብር መጋረጃ ያለው፤ የ60 ሚሊየን ብር መኖርያ ቤት ውስት በሚዋኙ እጅግ ጥቂቶች እና ቆሻሻ እየተመገቡ በሚኖሩ ብዙሃን ወገኖች መሃል ያለው ክፍተት ይህ ነው አይባልም። ይህንን የኑሮ ሚዛን መዛባት የሚቃወመውን ስም ያወጡለታል። ኢ-ፍትሃዊ የሆነውን ይህንን የሃብት ድልድል ለመቀበል ህሊናው የማይፈቅደውን ሁሉ “እብድ” የሚል ስም ይሰጡታል።
የ”እብዱ” ፓይለት ጉዳይ በህግ አይን ሲታይ ጠለፋ ሳይሆን እገታ ነው – የስዊዘርላንድ አቃቢ ሕግ እንደገለፀው። እገታ እና ጠለፋ እጅግ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ድርጊቱ ጠለፋ ቢባል ኖሮ ቅጣቱም የከፋ ይሆናል። እገታም ቢሆን በስዊስ ህግ ከ3 እስክ 20 አመት ሊያስቀጣ ይችላል። የዳኝነት ስልጣኑም ያለው አውሮፕላኑ በግዛቷ ያረፈበት የስዊዘርላንድ ፌዴራል መንግስት ላይ ነው። ለግዜው ሃይለመድህን አበራን አግኝቶ ማነጋገር ስለማይቻል ወጣቱን ያቆሰለው ጉዳይ ላይ ከዚህ የበለጠ ማለት አይቻልም። የአቃቤ-ህጉ ምርመራውን እንዳበቃ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣል። ያን ግዜ የበለጠ መረጃ ይኖራል።
ኢትዮጵያዊ ወገን በሙሉ፣ ራሱን አሳልፎ ለሰጠው ለዚህ ፓይለት ባገኘው መንገድ ሁሉ ድጋፉን መግለጽ ይጠበቅበታል።
የኢትዮጵያን ገጽታ አደባባይ ያወጣው አውሮፕላን አብራሪ ሃይለመድህን አበራ
ዳኛቸው ቢያድግልኝ
ልማታዊ ግስጋሴ እስከ ግድበ ህዳሴ በደረሰበት ታሪካዊ ወቅት፣ ኢትዮጵያ በፈጣን የእድገት መስፈርት ውስጥ ከአፍሪካ አንደኛ ከአለም
ከቻይና ቀጥሎ ሁለተኛ ነች እየተባለ በመሪዎቿ በሚነገርላት ጊዜ። አሸባሪዎችን ከመነሻቸው ለማምከን በአይነቱ ልዩ የሆነ የአንድ
ለአምስት አደረጃጀት የሰዎችን ድርጊት ብቻ ሳይሆን አስተሳሰብን ጭምር የሚመረምር ምትሃታዊ ሃይል ተደራጅቶ ባለበት ሁኔታ
የዴርቶጋዳን ልብወለድ መሰል ነገር መታየቱ ብዙዎችን አስደምሟል። ለመሆኑ የዛሬ ልጆች ጀግና አይደሉም የሚል ማን ነው?
በውጭ ሃገር የዜና ማሰራጫዎች ወሬው እንደተሰማ አስተያየት ለመክተብ ጣታቸው እንደ ክላሺኒኮቭ ፊደል የሚያንጣጣ ሁሉ ፓይለቱ
ጥገኝነት ለማግኘት ብሎ እንዲህ ማድረጉ አሳፋሪ ነው፣ አላዋቂ አፍሪካዊ መሆን አለበት፣ ይቀጣ! ይቀጣ! የሚሉ ሃረጎች በርክተው
ነበር። እነዚህ በአብዛኛው አፍሪካ ማለት አንድ ሃገር የሚመስላቸው የእውቀት ብርሃን የጨለመባቸው ናቸውና ምንም ማድረግ
አይቻልም።
ሁለተኛው ሰሞኑን ነገረ ስራው አያምርም ነበር የሚልና አእምሮው ለየት ያለ ነገር የሚያሳየው ‘ሺዞፍሬንያ’ እሚሉት ነገር
እየጀማመረው ነበር የሚለው ነው። እህት ሁሉም ይስማልኝ በማለት በመረጃ መረቦች በተነች የሚባለውን ያነበበ ሰው ለበረራ ብቁ
ነው የሚለውን ፈቃድ ሰጪም ወፈፍ ያደረገው መሆን አለበት ቢል አላጋነነም። ይሄ እብድ እየመሰለ ሲሰልል የኖረ ወያኔ ወፈፌነትን
በጣም ስለተለማመደው አማኑኤል ሆስፒታልን የደህንነት ማሰልጠኛ ኮሌጅ አድርጎ ቢመለከት አይፈረድበትም ብለን መሳቅም
መብታችን ነው። ቁም ነገሩ ግን የበረራውን ደህንነት ለማስጠበቅ የአብራሪዎችንምጤናና ደህንነት መከታተል ስለሚገባው ያንንም
ማድረግ ባለመቻሉ ወደ ትልቅ ስህተት ራሱን እየጨመረ ነው። በዚህ ሁኔታ ምን ያህል ወፈፌ ፓይለቶች ይኖሩ ይሆን ብሎ
መጠየቅም ያስፈልጋል። ከሆነም ምን አይነት አስተዳደር ቢኖር ነው ጨርቅ ጥሎ የሚያሳብደው፣ ሃገር ጥሎ የሚያስኮበልለው ብሎ
መጠየቅም ተገቢ ነው። የአይጥ ምስክሯ ድንቢጥ እንደሚባለው በአንድ-ለአምስት ተጋግዞ መዋሸት ይቻል ይሆናል ከዚያ መረብ ውጪ
ላለነው ግን አስቂኝ ትዕይንት ነው።
እኔ አውሮፕላኑን ጠለፈ የሚለው አገላለጽ እጅግም አልተመቸኝም። ረዳት አብራሪው ድምጼ ይሰማልኝ በማለት ማቆም የማይገባው
ስፍራ ላይ አውሮፕላኑን አቆመ ለዚያውም ያለ ፍርሃትና ሽብር መደናገጥና መርበትበት ተሳፋሪውም ኮሽታ ሳይሰማ። አቅጣጫ
በቀየረው አውሮፕላን ውስጥ የነበሩ ሰራተኞች ለተሳፋሪዎቻቸው ቡና ሻይ እያቀረቡ ምቾታቸውን እየጠበቁ ዋናው አብራሪ
ጋዜጣቸውን እያነበቡ ምቾታቸው ሳይጓደል አረፉ። ተሳፋሪዎች የሆነውን ሁሉ ሳያዩ ረዳቱ አብራሪ በገመድ ወርደው ለፖሊሶች
እጃቸውን ሰጡ። እንግዲህ የአእምሮ በሽተኛ እንደዚህ ከሆነ ተጋግዘን ብንታመምስ ምን ነበረበት?
ረዳት አብራሪው ሃይለመድህን አበራ ማስተላለፍ የፈለገው መልዕክት ስለመኖሩ መጠራጠር አውቆ መጨፈን ይሆናል። በአንድም
ይሁን በሌላ መልኩ የሀገሪቱ አስተዳደርን ገጽታ የሚያበላሽ ድርጊት ተከናውኗል። ስለምን የሃገሪቱን ገጽታ የሚያጎድፍ እንደሚባል
አይገባኝም። የሀገሪቱን ገጽታ የሚያጠለሹት ጎጠኞችና አምባገነኖች ናቸው። የነርሱ አስተዳደር መበስበሱን፣ ሁሉንም ዘርፍ ማለትም
ብዙሃኑን የሀገሪቱ ሕዝብ ማሳዘኑን በዚህም ምክንያት ምሬት መኖሩን ነው ይህ ወንድማችን አደባባይ ያወጣው። አዎ የአስተዳደሩን
ብልሹነትና እንዳይድን ሆኖ መታመም ነው አደባባይ ያወጣው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ገጽታ ሳይሆን ዓለም የተመለከተው የአስተዳደሩን
መጥፎነት ነው።
ቤተሰቦቹ ተገድደው የሚያወጧቸው መግለጫዎች ይበልጥ የሚያጋልጡት ይህ ማፍያ ቡድን እስከምን ድረስ ሊሄድ እንደሚችልና
በቤተሰብ ችግርና ሃዘን ውስጥ እንኳን በመግባት ሊፈጽም የሚችለውን አረመኔያዊ ድርጊት ነው። ቤን የሚሉት ለማጅ ጋዜጠኛ ወሎ
ሄዶ ባላቸውን አለቆቹ ገድለው እርሱ ደግሞ በሙስሊም አክራሪዎች እንደተገደሉ ለማስመሰል ሃዘንተኛዋን ባለቤት ሌላ ፖለቲካ
ሲያሰራ እንደነበረው ያለ ዜናን ማስታወስ ተገቢ ነው። ያለንበት ዘመን የራሽያ አብዮት የፈነዳበት ጊዜ አይደለም በአይነቱ በተለይም
በመረጃ ቅብብሎሹ ረገድ እጅግ በጣም የተለየ ዘመን ነው። የዚያን ጊዜ ታክቲክ በመጠቀም አሁን የሚታየውን አመጽ ማፈን
አይቻልም። ይልቁኑ እብዶቹ መንግስት ነኝ ባዮችና ወፈፌዎቹ ጋዜጠኛና ካድሬዎች ከአሳፋሪ ተግባር ቢታቀቡ ነው የሚሻላቸው።
ረዳት አብራሪው ሃይለመድህን አበራ ቃል ሳይተነፍስ ማለት የሚፈልገውን የተናገረ ይመስለኛል። የምቾት ህይወትን ትቶ ሙያውን
ተሰናብቶ መሄዱ ጀግንነት ነው። የብዙዎችን ሰቆቃና ቁጣ ያለውን የአስተዳደር በደልና ዘረኛነት ማጋለጡ ጀግንነት ነው። ራሱን ከዚህ
ጨቋኝ ስርዓት ነጻ ማውጣት ለርሱ ቀላል እጅግ በጣም ቀላል ነገር ሆኖ ሳለ በሙያው በክህሎቱ የአለምን ትኩረት የሚስብን ነገር
የአንድ ሰው ሕይወት ሳያጠፋ ማስተላለፍ መቻሉ ጀግንነት ነው። ይልቁንም ደግሞ የታወከ አእምሮ ኖሮ(አዋኪውና አስቀዋሹ ምክንያት
ምን እንደሆነ ይታወቃልና) በዚህ አይነት የተረጋጋ መንፈስ እንዲህ ያለ መልዕክት ማስተላለፍ መቻሉ ይበልጥ አስደናቂ ያደርገዋል።
ምናልባትም በሽታ መሆኑ ቀርቶ ልዩ ስም የሚሰጠው የመንፈስ ጥንካሬ ተብሎ የሚታወስ ይሆናል። ለወንድማችን ሃይለመድህን አበራ
መልካም ጤንነትና ፍትህን እመኛለሁ። ቤተሰቡና ወዳጆቹ ተመሳሳይ የመንፈስ ጥንካሬ ያድርባቸው ዘንድም አሳስባለሁ።
biyadegelgne@hotmail.com