በብሄራዊ ትያትር አካባቢ አንዲት አነስተኛ ምግብ ቤት ነበረች። «ገሊላ ምግብ ቤት» ትባል ነበር። በአዲስ አበባ «ቁምራ» ከመግባቱ በፊት በአካባቢው ያሉ የመንግስት ሰራተኞች በምሳ ሰዓት ይህችን ምግብ ቤት ያጨናንቋት ነበር። ቁምራን የማታውቁ ካላችሁ፤ ለጽድቅ የሚደረግ መንፈሳዊ ጾም እንዳይመስላችሁ። እድገትና ትራንስፎርሜሽኑ ያመጣው አዲስ ክስተት ነው – ቁርስ ምሳና ራት በአንድ ጊዜ የመመገብ ዘዴ። «ኑሮ በዘዴ፣ ጾም በኩዳዴ» ይባል ነበር። ይህ አባባል አሁን መኖ በዘዴ በሚል ተቀይሯል። መቼም ሁሉም ነገር በነበር እየቀረ ነው።
ጋዜጠኛ አቤል አለማየሁ በቅርቡ ባሳተመው “የአዲስ አበባ ጉዶች” የሚል መጽሃፉ ላይ ስለዚህች ታሪካዊ ምግብ ቤትም ትንሽ ብሏል። የምግብ ቤትዋ ባለቤት “ገሊላ ምግብ ቤት” የሚለው ጽሁፍ በከፊል አጥፍተውታል። አሁን ምግብ ቤት የሚለው ተነስቶ “ገሊላ” የሚለው ብቻ ነው የቀረው። ጉዳዩ በህግ እንዳያስጠይቃቸውም ይመስላል ጽሁፉ ላይ ነጭ ቀለም ነው የደፉበት። የምግብ ቤቷ ትራንስፎርሜሽን መሆኑ ነው። የዚህ ትራንስፎርሜሽን ትርጉም የገባቸውም ሆነ ያልገባቸው ተስተናጋጆች ወደ ገሊላ (ምግብ ቤት) ጎራ ማለታቸው አልቀረም። የዚህች ቤት አዲሶቹ ደንበኞች በአነስተኛና ጥቃቅን የተደራጁ ወጣቶች ናቸው። እዚያ ሲገቡ ሰልፍ ይጠብቃቸዋል። ይህች ስፍራ ስፋትዋ ለምግብ ቤት በቂ ነበር። ለቀን አልጋ አገልግሎት ግን ትንሽ ስለጠበበች ነው ሰልፍ ሊከሰት ያቻለው። ተራ የደረሳቸው በመጀመርያ ሜኑ ይቀርብላቸዋል። የቀድሞው የምግብ ሜኑ በወይዛዝርት ፎቶ ተቀይሯል።….
ይህ ዘርፍ አሁን ከኮብልስቶንም የበለጠ አዋጭ እየሆነ በመምጣቱ፤ ምግብ ቤቶች የአገልግሎት አይነታቸውንና የሜኑ ደብተራቸውን እየቀየሩት መሆናቸው እውነት ነው።
የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ወሬ መሰማት ከተጀመረ ትንሽ ዘገየ። ይህ አዋጅ ከተሰማ በኋላ የእርሻ፣ የኢንዱስትሪና የሃይል አቅርቦቶች በሙሉ በአስር እጥፍ ነው ያደጉት። እድገታቸው ታዲያ ወደላይ ሳይሆን እንደባህር ዛፍ ወደታች ነው። በእርግጥ የለውጥ ምልክቶች በሀገሪቱ እየታዩ ነው ከተባለ የዝሙት ኢንደስትሪው በደንብ ለመጠቀስ ይችላል። ይህ ዘርፍ በተለይ ከአረብ ሃገር የበርካታ ቱሪስቶች መስህብ ሆኗል። በዚያን ሰሞን አንድ በአዲስ አበባ የሚታተም ጋዜጣ ድንግልና በአስር ሺህ ብር እንደሚሸጥ አስነብቦን ነበር። አንዲት ደናግል ለዚህ ጸያፍ ነገር ስትዳረግ ድህነትን ብቻ አይደለም የምትሰናበተው። የማንነትዋ መግለጫ የሆነው የሞራል ጉዳይም አብሮ ይሄዳል።
የአገልግሎት ክፍያው የሚከናወነው በዶላር መሆኑ ደግሞ በዚህ ዘርፍ ላይ የግሽበት ችግር አይደርስበትም። ኢንደስትሪው ለሃገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ምንጭም ስለሆነ ይመስላል ከመንግስት በኩል እየተበረታታ የመጣው። የውጭ ምንዛሪ በማስገኘቱም «ልማታዊ» ተግባር ተብሏል። መንግስት ከዚህ ሴክተር ምን ያህል እንደሚጠቀም በውል ባይታወቅም አገልግሎት ሰጭዎቹ (ደላሎቹ) ግን ሃብታም እንደሆኑ ይነገራል።
ወደ ጎተራ አካባቢ በተሰራው የኮንዶሚንየም መንደር ደግሞ ሌላ ታሪክ አለ። ይህ ኮንዶ «ፌስቡክ» የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ለምን ፌስቡክ እንደተባለ ለማወቅ ብዙም ግዜ አይፈጅም። የቆነጃጅት ኮረዳዎች ሁሉ መሰብሰቢያ ነው። ትምህርት አቋርጠው ወይንም ከቤተሰብ ተኮራርፈው የተሰወሩ የቤት ልጆችን ለማግኘት ወላጆች ወደ ፖሊስ ጣብያ መሄድ አቁመዋል። ወደ ጎተራው «ፌስቡክ» ብቅ ካሉ የጠፉትን ሁሉ እዚያ ያገኙዋቸዋል። ባለሃብቶች እና ባለግዜዎች ወጣት ሴቶችን እየወሰዱ እዚያ እንደ እቃ ያስቀምጧቸዋል። ይህን የሚያጫውቱኝ ወዳጆቼ እየሳቁ ነበር የነገሩኝ። ነገሩ ያሳዝናል እንጂ አያስቅም!
በዚህ ልማታዊ «ቢዝነስ» ውስጥ ጨቅላዋ ማሪቱም ገብታበታለች። የማሪቱን ነገር ማንሳቱ ብቻ ሁኔታውን በደንብ ይገልጸዋል።
ይህች ጨቅላ ጉብል በወግና በማዕረግ ያደገችበትን ቀዬ ለቃ ከወጣች አመታት አልፈዋል። በሃገሬው ሹሩባ ተጎንጉኖ የነበረው ያ ዞማ ጸጉርዋ በፈረስ ጸጉር ተተክቷል። እንደምንጭ ውሃ ጥርት ብለው የነበሩት አይኖችዋ በህብረቀለማት ኩል ተበርዘዋል። በአረንጓዴ ካኪ የተሰፋላት ሽንሽን ቀሚሷ ካላይዋ ላይ ተጥሎ በዘመናዊ ሚኒ-ስከርት ተቀይሯል። ኮንጎ ጫማዋም በሂል ተለውጦ ምቾትዋን ወስዶባታል። ማሪቱ አሁን አዲስ ዓለም ውስጥ ናት። እንደ አሻንጉሊት ሁለመናዋ ሰው-ሰራሽ ሆናለች። ስምዋም ተቀይሯል። አሁን ሜሪ ናት። ማሪቱን ሜሪ ለማድረግ ደላሎቹ ችግር የለባቸውም። ዘመናዊ ልብስ እንጂ ዘመናዊ ስም ወጪ አያስወጣም። ለማሪቱ ከሜሪ ይልቅ ማርታ ወይንም መስከረም ይቀርብ ነበር። እነዚህን ሁለት እርከኖች ዘልሎ ፈረንጅኛው ላይ መሄዱ፣ ምን ያህል ፈጣን የእድገት ጎዳና ላይ መሆናችንን ያሳየናል።
እርግጥ ነው። ማሪቱ በትምህርቷ ገፍታ ሰዎች የደረሱበት ለመድረስ ችሎታውና ፍላጎቱ እንጂ አቅሙ አልነበራትም። እድሜዋ ለአቅመ ሄዋን እንደደረሰ እንደከተሜ እኩዮችዋ ለኮሌጅ ትምህርት አልታደለችም። ወላጆችዋ ብዙም ቅሪት የላቸውም። ለችግር ግዜ አስቀምጠዋት የነበረችውን ገንዘብ ለ«ህዳሴው ግድብ» መዋጮና ቦንድ መግዣ አውለዋት በተስፋ መኖር ጀምረዋል። አዎ ተስፋቸውን ሁሉ በህዳሴው ላይ አድርገዋል። ግና ተስፋ የእለት ጉርስ አይሆንም።
ሜሪ ድህነትን ለማሸነፍ ስትል የማትወደውን ስራ የመስራት ውሳኔ ላይ ደርሳለች። በውሳኔዋ እንዳትጸጸት የሚያጽናናት ነገርም አለ። «ትምህርት ምን ያደርጋል? የተማረ የት ደረሰ?» የሚለው የወላጆችዋ አባባል በእምሮዋ ውስጥ ያቃጭል ነበር። ይህንን አባባል እንደ ጥቅስ እቤትዋ ላይ ሰቅላዋለች። ከህሊና ወቀሳ ለመሸሽ ስትፈልግ ቀና እያለች ይህንን ጥቅስ ታነብና ትጽናናለች። ታላቅ ወንድምዋ የኢንጅነሪንግ ምሩቅ ነው። የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ከልጅነቱ ጀምሮ ይመኝ የነበረውን ስራ ሊያገኝ አልቻለም። ይህም፣ ወላጆቹ በትምህርት እና በእውቀት ላይ ተስፋ እንዲቆርጡ አድርጓቸው ነበር። የኋላ-ኋላ ግን የስራ አጡን ጎራ ለማምለጥ አዲስ ስልት ቀየሰ። የኢህአዴግ አባልነት ፎርም ሞልቶ በጥርነፋ መያዙ ግድ ሆነበት። ከዚያም በ«አነስተኛና ጥቃቅን» ዘርፍ ተደራጅቶ ኮብልስቶን ላይ ተሰማራ። ድንጋይ ሲፈልጥና ሲሸከም ለመዋል መስፈርቱ መብዛቱ ሜሪን አምርሯታል። በመጀመሪያ የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ መሆን፣ ከዚያ የአባልነት ፎርም መሙላት፣ ከዚያ በአነስተኛና ጥቃቅን መደራጀት፣ ከዚያ መጠርነፍ…።
በደርግ ግዜ ኑሮ መሯቸው በሱዳን ድንበር ሊጠፉ የነበሩ ወጣቶች፤ ጠረፍ ላይ ሲደርሱ አንድ መፈክር አዩ። “ትግላችን መራራ፣ ጉዟችን እሩቅ፤ ግባችን ረጅም ነው!” የሚል መፈክር። ወጣቶቹ ተስፋ ቆርጠው ጉዟቸውን አቋረጡ። ከዚያም ጫካ ገቡ ይባላል። ያሁኑ ዘመን ጫካ «ቼቺንያ» የሚባለው መንደር ነው። ሜሪም ወንድሟ ያለፈበትን ረጅም መንገድና አስቸጋሪ መስፈርቶች ማሟላት ስለሚሳናት አጭሩን መንገድ መምረጥ ነበረባት።
በተለይ ከመካከለኛው ምስራቅር የሚመጡ ቱሪስቶች፣ አየር ባየር ነጋዴዎችና ባለስልጣናትም ጎራ እያሉ የሚዝናኑባቸው ማሳጅ ቤቶች እንደአሸን ነው የፈሉት። ከታይላንድ የዝሙት እንደስትሪ የተወረሱ “ሃፒ እንዲንግ” ተግባራት የሞራል ውድቀታችን ምን ያህል እንደወረደ ያሳየናል። እንደዚህ አይነቶቹ ነውር ነገሮች ሁሉ ገቢ እስካስገኙ ድረስ አዋጭ ስራዎች ናቸው። በልማታዊው መንግስታችንም ይበረታታሉ።
ሁሉን ነገር ተነጠቀን የቀረችን አንዲት ነገር ሞራል ብቻ ነበረች። የሞራል እሴቶቻን ግን እንዴት ነው እንዲህ የራቁን? መልካም ስነ-ምግባር፣ ጨዋነት፣ ግብረ-ገብነት እና ፈሪሃ እግዚአብሄር የጠፋበት ህብረተሰብ መጨረሻው ምን ሊሆን ይችላል? ሃገር ማለት መሬት ብቻ አይደለም። ሃገር ማለት ሕዝብና አንድ ሉዓላዊ አካል ብቻም አይደለም። መልካም ስርዓት እና የሞራል እሴት የሌለው ሃገር ከማፍያ ጉረኖ የተሻለ አይሆንም።
ሌት ተቀን የምንደኖቅርበት እድገትና ትራንስፎርሜሽም የሚመጣው በመጀመርያ ሃገር ስትኖር መሆኑን መገንዘብ ይበጃል። …. የሃይማኖት አባቶችስ ይህንን እያዩ ለምን ዝም አሉ? ስራቸው ፍትሃት ማድረግ እና እና ግብር መሰብሰብ ብቻ መሆን ነበረበት? ወይንስ እነሱንም ይኸው ልማታዊ አስተሳሰብ ተጸናወታቸው?
አያስቅም! አጭር ወግ (ከክንፉ አሰፋ) ጋዜጠኛ
ሰሞነኛ ትዝብቶች …..
ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com
ኢህአዴግ የሚባል ገዢ በሄድንበት ሁሉ ለትዝብት የሚሆኑ ነገሮችን ማስቀመጥ አይተውም እኛም አንጀታችን ማረሩ ይቀጥላል፡፡ አንዳንዶቻችን ለአንጀታችን ማረር መፍትሔ ብለን በፅሁፍ አስፍረን እንገላገላለን ያለበለዚያ ለስንቱ አውርተን እንዘልቃለን፡፡ የሚያነብ ካለ ደግሞ ማስተካከያ ይወስዳል፡፡ ለሚስተካከሉት ማለት ነው፡፡ ተጠያቂ ካለ ደግሞ እንዲጠየቅ ማድረግ የእርምጃው አንድ አካል ይሆናል፡፡ ኢህአዴግ ግን አፍ እንጂ ጆሮ የለውም ሰለሚባል ተጠያቂነት ያሰፍናል ብሎ ማመን አስቸጋሪ ነው፡፡ አባላቶቹ ሲያጠፉ ለአሽከርነት ቀብድ እንደከፈሉ ተቆጥሮ ይመዘገብና ሲፈለግ ይመዘዛል እንጂ በወቅቱ እርምጃ አይወስድም፡፡
አንድ ሰሞን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ኃላፊ የነበረ አስቻለው የሚባል ጓደኛዬ በከተማው ውስጥ መንገድ ዘግተው አጥር የሚያጥሩ ባለስልጣናትን ማሾር ጀምሮ ነበር፡፡ በዚያ መነሻ ብዙ የከተማ መንገዶች ተከፍተው መተንፈሻ አግኝተን ነበር፡፡ ባላስልጣናቱ በመንግሰት ገንዘብ ህገወጥ ግንባታ ማካሄዳቸው ከተጠያቂነት እንደማያድናቸው አስረግጦ ሲነገራቸው ማፍረስ ጀመሩ፡፡ እኛም ጉድ ተሰኝተን በቀጣይ መከላከያም ሆነ ቤተ መንግሰት የእግረኛ መንገድ እየዘጉ ማለፍ ክልክል ነው ማለት አይቻሉም ጥበቃቸውን ውስጥ ግቢያቸው ያደርጋሉ ብሎን በቴሌቪዥን መስኮት ተመለከትነው፤ ይህም ሳይተገበር እርሱም ተገፍቶ ከሀገር ወጥቶ ይኖራል፡፡ ይህን ጉድ ያስታወሰኝ በቅርቡ ቂሊንጡ እስር ቤት ሄጄ ያየሁት ጉድ ነው፡፡ አቶ አስራት ጣሴን በገደብ ከተጣለበት እስር የሚታሰብ ይሁን አይሁን ባይታወቅም በጣቢያ ለሶሰት ቀን እና በቂሊንጡ ለሰባት ቀን ቆይቶዋል፡፡ እንዳሰቡት አስራት ጣሴን አንገት ያስደፉት አልመሰለኝም ይልቁንም ውስጥ ገብቶ ተምሮ የወጣ ይመስለኛል፡፡ ብዙ ወዳጆች እንዳፈራ ነው የነገረኝ፡፡ አቶ አስራትን ለማውጣት እንደ ማስገባት ቀላል አልነበረም፡፡ የማውጣት ሂደቱም ግምገማ/ቢ.ፒ.አር ሊሰራለት እንደሚገባ የሚያሳብቅ ነው፡፡ ውስጥ ገብቼ ምን ያህል ደቂቃ እንጠብቅ ብዬ ሰሟገት ከ20 -30 ደቂቃ ቢሆን ነው ውጪ ጠብቁ ተብለን ወጥተን አላፊ አግዳሚ መታዘብ ጀመርን የተባለው ደቂቃ አለፈ ከሁለት ሰዓት በላይም ሆነ፡፡ ከቅጥር ጊቢ ውጭ ያለስራ መቀመጣችን አንድ ነገር ይዞ ብቅ አለ፤ ወዲህ ወዲያ ማየት እና መንቀሳቀስ፡፡ እየተንቀሳቀስን እያለ የጊቢው አጥር በግምት ርዝመቱ ከሁለት መቶ ሜትር እና ቁመቱ ከሁለት ሜትር በላይ የሚሆን ነው፡፡ ይህ አጥር ከጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ወደ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሚሄደውን አዲስ መንገድ ዘግቶ ተገትሮዋል፡፡ የመንገድ ሰራውን አስቁሞታል፡፡ ይህ አጥር የተሰራው በቅርብ ሲሆን ለምን 12 ሜትር ከፕላን ወጥቶ እንደ ተሰራ ግርምት ፈጠረብኝ፡፡ ይሄኔ ነው አሰቻለው ትዝ ያለኝ መፍትሔውን ሳሰብ አጥሩ መፍረስ አለበት ግን ይህ የሚፈርስ አጥር የተገነባው በህዝብ ሀብት ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ መፍትሔው መፍረስ ብቻ ነው፡፡ ይህ አጥር በዚህ ሁኔታ ከፕላን ወጥቶ እንዲሰራ ያደረገ መጠየቅ አለበት፡፡ ከፕላን አልወጣንም የሚል መከራከሪያ ካላ ይህን ፕላን አዘጋጅቶ የሰጠ መሃንዲስ መንገድ መኖሩን አላውቅም ነበር ሊለን ስለማይችል ተጠያቂ መሆን ይኖርበታል፡፡ በማነኛውም ሁኔታ ግን የተጠያቂ ያለ ብለን እንድንጮህ ይህን ሀሳብ ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡ ከአጥሩ ጋር ተያይዘው የሚፈርሱ ብዙ የመብራትና ሌሎች መሰረተ ልማቶች መኖራቸውን መዘንጋት ያለብን አይመስለኝም፡፡ ለማነኛውም ይህን ፅሁፍ ያነበበ ጋዜጠኛ የእስር ቤቱንም ሆነ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ሰዎቹን አነጋግሮ ለህዝብ ይፋ ያድርግልን፡፡ አንገታችን ታንቆ በምንከፍለው ግብር የሚሰራ መንገድም ሆነ አጥር እንደፈለገ የሚፈርስ መሆን የለበትም፡፡
ሌላው ሰሞነኛ ጉዳይ ደግሞ የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ወንበራቸውን በቅጡ ሳያደላድሉ ፈተና የበዛባቸው መሆኑ ነው፡፡ አንዱ የፈተናቸው ምንጭ ደግሞ አቶ አለምነው መኮንን የተባለ ካድሬ ነው፡፡ አቶ አለምነውን አንተ ያልኩት ከተመስገን ደሳለኝ ተውሼ ነው፡፡ አምባገነን ሰርዓትን የሚመሩ ሰዎች አንተም ሲበዛባቸው ነው ሰለሚል ማለቴ ነው፡፡ ለነገሩ እኛም ሰፈር ቢሆን አንቱ ብሎ ስድብ የለም፡፡ አቶ አለምነው ደግሞ ሰድበውናል ስለዚህ መሰዳደብ ሊጀመር ከሆነ አንቱታው አይገባቸውም፡፡ ብአዴን ለአማራ ህዝብ ክብር ሲል ይህን ካድሬ ይቅርታ እንዲጠይቅ በማድረግ ከኃላፊነቱ ማንሳት ሲገባው በየቦታው እየዞረ ማስተባበሉን ቢያቆም ጥሩ ነው፡፡ ለነገሩ የዚህ ዓይነት አካሄድ በኢህአዴግ መንደር የተለመደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናው በምክር ቤት ቀርበው ይሁን በጋዜጣው መግለጫ አንድ ፋውል መስራታቸው የተለመደ ነበር፡፡ ታዋቂዎቹ ፋውሎች ባንዲራ ጨርቅ ነው፣ የአክስሙ ሐውልት ለወላይታ ምኑ ነው? የመሳሰሉት አሁንም ትዝ ይሉናል፡፡ በዚህ ጊዜ በህዝቡ ዘንድ ጫጫታ ሲነሳ እርሳቸው ማለት የፈለጉት የግል ሚዲያ፣ የድሮ ስርዓት ናፋቂዎች፣ ኒዎሊብራሎች እንደሚሉት ሳይሆን ይህን ለማለት ነው በማለት እንደምታ ትርጉም ይስጠው ነበር፡፡ አለቆቻቸው ውሃ እየተጎነጩ የፈለጉትን ይናገራሉ፤ ካድሬዎች ምራቃቸው እስኪደርቅ በውሃ ጥም እየተሰቃዩ ለማስተባበል ይሞክራሉ፡፡ ይህ የማስተባበል ዘመቻ በፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው መታወቅ ይኖርበታል፡፡
የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውም ቢሆን በማስተባበል ጫወታው የገቡ ይመስላል፡፡ አቶ አለምነው መኮንን ፀያፍ ስድብ ተሳድቦዋል፡፡ ድምፁ የእኔ ነው ሰድቡ ግን የእኔ አይደለም የሚለውን ቀልድ ትቶ ማሰተባበል ካልቻለ ይቅርታ ይጠይቅ፣ ብሎም ከሃላፊነቱ ይነሳ፡፡ የአቶ ገዱ “አቶ አለምነው ለአማራ ሕዝብ ዕድገትና ብልፅግና ሌት ተቀን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሚሰሩ ናቸው” የሚለው ምስክርነት እውነት ከሆነ ጥፋት ማቅለያ እንጂ ከጥፋተኝነት መዳኛ አይደለም፡፡ በፍርድ ቤት ጥፋት አጥፈተሃል አላጠፋህም ተብሎ ሲጠየቅ የቤተሰብ ሃላፊ ነኝ ብሎ እንደ መመለስ ነው፡፡ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አሁን የያዙት ተግባር ደረጃቸውን አይመጥንም የሚጠበቅባቸው ለተሰደበው ህዝብ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ነው፡፡ እኔ አቶ አለምነው ይሰቀል አላልኩም፤ ይውረድ ነው፡፡
ሌላኛው አስገራሚ ዜና ደግሞ ፖሊሶች ማን ፍርድ ቤት እንደደፈረ አላወቅንም አሉ፡፡ ኮምሽነር ጄነራሉም ማወቅ አልቻልምን አሉ፡፡ አሰቂኝ ዜና ነው፡፡ እኔ የገባኝ ግን ፍርድ ቤት በመድፈር ከተጠረጠሩት ውስጥ ባለ ከፍተኛ ማዕረጎች ፍርድ ቤቱን እንደደፈሩ የሚያሳይ ነው ፍንጭ ነው፡፡ ተራው ወታደር ቢሆን ኖሮ ታንቆ ይስጥ ነበር፡፡ ተራ ወታደሩ አለቆቹ እንዳጠፉ አውቆ ቢናገር ደግሞ የሚከተለውን ያውቃል፡፡ ስለዚህ ዝም ማለት መርጠዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ በእለቱ ተረኛ የነበሩት አስራ አምስቱም በጋራ ተባብረው ነው ያጠፉት ማለት ነው፡፡ ለጥፋታቸው የሚመጥን ቅጣት ይገባቸዋል፡፡ በነገራችን ላይ ፍርድ ቤት ባይደፍሩም ጥፋተኛ እንዲታወቅ ትብብር ባለማድረጋቸው ሁሉም ጥፋተኞች ናቸው፡፡ ዳሬክተር ጄነራሉ እንደሚሉት ጉዳዩን ወደ እኛ መልሱትና እኛ በተቋም ደረጃ እርምጃ እንውሰድ የምትለውም ፌዝ ቢጤ ነች፡፡ ለማነኛውም ግን ፍርድ ቤቱ አስተማሪ የሆነ ነገር ያደርጋል ብለን እንጠብቃለን፡፡ ይህ ጉዳይ በህዝብ ዓይን እና ጆሮ ሰር ገብቶዋል፡፡ ዘጠና ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ ለሚደርስ ጥፋት መርምሮ እንዲይዝ የተቀመጠ አካል ከአስራ አምስት ሰዎች ውስጥ ጥፋተኛ መለየት አልቻልኩም ሲል ግን ትዝብት ውስጥ እንደሚገባ ያለማወቁ ያስተዛዝባል፡፡
በመጨረሻም ለመሰናበቻ የሚሆን ሰለ የካቲት 11 ክብረ በዓል እናንሳ፡፡ ይህ በዓል በየአምሰት ዓመት በሰፊው ይከበር የነበረ ሲሆን አሁን ግን በተለየ ሁኔታ እንደተከበረ አብርሃ ደስታ ነግሮናል፡፡ ይህ ለምን እንደሆነ ባይገባኝም ምን አልባት በቀጣይ ዓመት በምርጫ ውጥረት ምክንያት ሊሆን ቢችል ብሎ መጠርጠር የአባት ነው፡፡ ግን ምን ችግር አለው በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ ከዚህ በበለጠ ቢያከብሩት ገንዘቡ እንደሆነ የፓርቲ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ እኔ ግን ግርምት የፈጠረብኝ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ ከፍተኛ አመራሮችን(እነ ተፈራ ዋልዋን ጨምሮ) ይዞ ወደ አዲስ አበባ ሊመጣ ሲል ችግር ገጥሞት የነበረው የሱዳን አውሮፕላን ለምን ለህውሓት ብቻ መታሰቢያ እንዲሆነ ተፈለገ የሚለው ነው፡፡ የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ይህን አሮጌ አውሮፕላን አይደለም አዲስ ጀት ገዝተው ቢሰጡን የሚበዛብን አይደለም፡፡ ምክንያቱም በነብሰ ገዳይነት ለእስር የሚፈለጉ ሰውዬ እንደፈለጉ የሚወጡበትና የሚገቡበት ሀገር ከዚያም አልፎ ክሳቸው ይነሳላቸው ብሎ የሚከራር መንግሰት ይህ ስጦታ ቢያንስ እንጂ አይበዛም፡፡ የእነ ተፈራም ነብስ የህውሓት ነብስ ነች እንዴ እረ እየተስተዋለ፡፡
የማለዳ ወግ .. . ዓድዋ የእኛ …የትውልድ ኩራት !
* የጦርነቱ መነሻ ምክንያት …
የዓድዋ ጦርነት መነሻ ምክንያት የሆነው የውጫሌ ውል አንቀጽ 17 ሲሆን ይህ አንቀጽ የኢትዮጵያን ህልውና የሚፈታተን ሆኖ በመገኘቱ እንዲሰረዝ የተደረገው ሙከራም በጣሊያን እምቢተኝነት በመክሸፉ እንደ ነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።
* የጣሊያን ወረራ መሰማትና እቴጌ ጣይቱ …
የጣልያንን እምቢተኝነት ተከትሎ ሚኒስትሮች፣ የጦር አለቆችና መኳንንቱ ባካሄዱት የምክክር ጉባኤ ላይ እቴጌ ጣይቱ ብጡል «እኔ ሴት ነኝ፣ጦርነት አልወድም፣ሆኖም ግን ኢትዮጵያን የጣሊያን ጥገኛ የሚያደርግ ውል ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ ፡፡ » ሲሉ የሰጡት አስተያየት ነበር፡፡
* የኢትዮጵያው ንጉሰ ነገስት የዳግማዊ አጤ ምኒሊክ የክተት አዋጅ …
ጣሊያን ውል አፍርሶ ኢትዮጵያን ሲወርር በጉልበቱ የጀግኖችን ሃገር ሊፈታው እንደማይችል ያውቅ ነበር። ጣልያን በልዩነታችን ገብቶ ሊለያየን እቅድ አቅዶም ነበር ። ይህንንም ለማሳካት በተለያየ አስተዳደር ግዛት ለይተው በሚቆራቆሱ የጦር አበጋዞችና በንጉሱ መካከል የነበረውን የከፋ ልዩነት መጠቀም ለድል እንደሚያበቃው አልሞ መነሳቱ እውነት ነበር ። ያም ሆኖ የንጉሰ ነገስቱ መኳንንቱን ፣ ሹመኞችን እና የጦር አለቆችን ሰብስበው በመምከር ብሔራዊ ክብርን ማስጠበቁ ይቅደም አንድምታ ያለው ሃሳባቸው ተቀባይነት ያገኝ ዘንድ በሰለጠነ መንገድ ከመግባባት ላይ ደረሱ። ይህም ምክክርና ስምምነት ሁሉም በአንድነት ለነጻነትና ክብሩ ይተጋ ዘንድ ታላቅ አስተዋጽኦ ያደርግ ዘንድ ሁሉም በየስራ ድርሻው ተመድበው መስራት ጀመሩ ።
መስከረም 1888 ዓ.ም ወር ላይ ንጉስ ምኒሊክ ጣሊያንን ለወረራ መዘጋጀቱን በስለላ ባለሟሎቻቸው በቅርብ አረጋገጡ። በወረራ ዝግጅቱ የተቆጡት ዳግማዊ አጤ ምኒሊክ የክተት አዋጅ እንዲህ በማለት አስነገሩ …
‹‹እግዚአብሄር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአ ብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ ከእንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለእኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡ አሁንም አገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖትን የሚለውጥ፣ በፊት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል፡፡ እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ፤ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ የአገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሃዘንህ እርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፡፡ አልምርህም፡፡ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም…››
* ዓድዋና የጦሩ ዝግጅት …
የዓድዋው ጦርነት በጣልያኖች በኩል የቆየ የቀኝ ግዛት ጥማቸውን ለማሳካት ቀድሞ የተጠነሰሰ ነበር። በኢትዮጵያውያን ዘንድ ግን የጦርነት ዝግጅቱ እስከ ሰባት ወር የፈጀ እንደነበር ይነገራል። ዝግጅቱ ተጠናቆ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ጎህ ቀዶ እስኪጠልቅ በቀድሞዋ ትግራይ ጠቅላይ ግዛት በዛሬዋ ክልል አንድ ትግራይ ውስጥ በምትገኘው በዓድዋ ከተማ ይገጥም ዘንድ ቀኑ ደረሰ ! በዓድዋው ዘመቻ በመቶ ሺሕዎች ሆኖ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር ከጥቂቱ በስተቀር አብዛኛው ጦር፣ ሰይፍ፣ ጋሻና የነፍስ ወከፍ መሳሪያ ይዞ እንደ ነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። ጣሊያን በአስር ሽዎች የሰው ሃይል ፣ በዘመናዊ የጦር መሳሪያና በወታደራዊ ሳይንስ የሰለጠነ አውሮፓዊ ጦር ነበርና ከፍ ባለ ስንቅና ትጥቅ ተደግፎ ወረራ መጀመሩ ይጠቀሳል።
* አንጸባራቂው የዓድዋ ድል … የጥቁሮች ድል !
የጣሊያን ጦር በጄኔራል ባራቴሪ እየተመራ ባህር ተሻግረሮ ሲመጣ የተወረረችው የኢትዮጵያውያን ጦር የሚመራው በንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አጤ ምኒሊክ ነበር። ጀግና ብልህና አርቆ አስተዋይዋ ባለቤታቸው እትየ ጣይቱ ብጡል በዚያ ባልሰለጠነ ዘመን ስልጡን ነበሩና በባለቤታች ከሚመራው የአርበኞች ግንባር እኩል ተሰልፈው ሃገሬውን ስንቅ ትጥቅ በማስታጠቅና በማበረታታት የከፈሉት መስዋዕትነት ቀላል አልነበረም። ኢትዮጵያውያን በንጉሱ ብልህ አመራርና ክተት ብለው በህብረት ተነሱ ። ከሽኩቻና ዝብሪት ተዘፍቀው የባጁት የየግዛቱ ሹሞች እና የጦር አበጋዞችም በንጉሰ ነገስት አጤ ምኒሊክ የክተት አዋጅ ልዩነታቸውን አስወግደው በህብረት ተመሙ !
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ከ118 ዓመታት በፊት በዕለተ ሰንበት ክብሩ የተነካው አርበኛ ህዝብ ዓድዋ ላይ ቀፎው እንደተነካበት ንብ ተንቀሳቅሶ ባካሔደው ውጊያ እብሪተኛውን ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀ የጣሊያን ጦር ጋር ገጠመ ! ከማለዳ አንስቶ ጀንበር እስክታዘቀዝቅ ባለው ጊዜ የተካሄደው ጦርነት እልፍ አእላፍ መስዋዕት ሆነው በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት በዓድዋ ተደመደመ !
ጣሊያን ከአንባላጌ እስከ አድዋ ተጠራርጎ እንዲወጣ ያደረገው ” የጥቁሮች ድል!” በሚል አለም ባወደሰው የዓድዋ ድል የጣሊያን መንግስት የሃፍረት ማቅን በግዱ ተከናነበ። የዓድዋ ድል በመላ በአለም ከተበሰረ በኋላ የወረራው መነሻ የሆነውን የውጫሌ ውል ፈርሶ የጣልያን መንግስት በውጫሌ ውል የነበረውን አጉል ምኞቱን ይሰርዝ ዘንድ ግድ ሆነበት ። ወራሪው በሽንፈቱ አፍሮ የኢትዮጵያን ሙሉ ነፃነት አውቆ እና ተቀብሎ የሰላም ስምምነት ያደርግ ዘንድ ተገደደ ! የስምምነት ውሉም ለአለም መንግስታት ተሰራጨ። ውሉ የደረሳቸው መንግስታት እና ሃገራት የኢትዮጵያን የተረጋገጠ ሉአላዊ መንግስትነት በውድም ሆነ በግድ ተቀብለው አረጋገጡት !
* የዓድዋ ድል በዳግማዊ አጤ ምኒሊክ ድብዳቤዎች …
ዳግማዊ አጤ ምኒሊክ የዓድዋን ድል አስመልክተው ለፈረንሣዊው ሙሴ ሞንዶን የዛሬ 118 ዓመት የጻፉለት የምሥራች ደብዳቤ እንዲህ ብለው ነበር “የምሥራች በእግዚአብሔር ቸርነት የየካቲት የቅዱስ ጊዮርጊስ ዕለት ኢጣልያንን ድል አድርጌ መታሁት፡፡ በጨረቃ ሲገሰግስ አድሮ እሰፈሬ ድረስ መጥቶ ገጠመኝ፡፡ አምላከ ኃያላን ረድቶኝ ፈጀሁት፡፡ ደስ ብሎኛል ደስ ይበልህ››
አጤ ምኒሊክ በመጋቢት 23 ቀን 1988 ዓ.ም. ለፈረንሳዊው ሙሴ ሸፍኔ በላኩለት ደብዳቤ ያቸው እንዲህ ብለዋል ‹‹… ከአላጌ ጦርነት በኋላ፣ ጣሊያኖችን ጦርነት ይቅር፣ የክርስቲያንም ደም በከንቱ አይፍሰስ፣ እርቅ ይሻላል ብላቸው እምቢ ብለው መጥተው በጥጋባቸው ዓድዋ ላይ ተዋግ ተው ድል ሆኑ፡፡ እኔ ግን በድቁርናቸው ብዛት የነዚያን ሁሉ ክርስቲያን ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ ድል አደረግኳቸው ብዬ ደስ አይለኝም፡፡ ነገር ግን በግፍ የመጡ ሰዎች ናቸውና እግዚአብሔር ግፉን አነጣጠረን…፡፡›› በማለት ያስታወቁ ሲሆን ምኒልክ ለሞስኮብ ንጉሥ ኒቆላዎስም መጋቢት 23 ቀን 1988 ዓ.ም በጻፉት ደብዳቤያቸውም ‹‹እንደ አውሮፓ ነገሥታት ሥራት ሁሉ ጠብ መፈለጋቸውን ሳያስታውቀኝ፣ እንደ ወምበዴ ሥራት ሌሊት ሲገሰግስ አድሮ ሲነጋ ግምባር ካደረው ዘበኛ ጋር ጦርነት ጀመረ፡፡ ጥንት ከአህዛብና ከአረመኔ አገራችን ጠብቋት የሚኖር አምላክ ከእኛ ባይለይ በእግዚአብሔር ኃይል ድል አደረግሁት…›› ብለው መጻፋቸው ይጠቀሳል ፡፡
* አልፋና ኦሜጋ የማይረሳው መስዋዕትነት … አልፋና ኦሜጋ በክብር ይዘከራል !
ልክ የዛሬ 118 ኛ አመት እሁድ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓም ታላቁ የዓድዋ ድል በዓድዋ ሰንሰለታማ ተራሮች ላይ ተበሰረ ! ይህ የጥቁር ህዝብ በቅኝ ገዥዎች ከተቀዳጃቸው የዓድዋ ድል እውን እንዲሆን አቀበት የወጡ ፣ ቁልቁለት የወረዱ ፣እርጥብ የጨሰባቸው ፣ ደረቅ የነደደባቸው ፣ ከቤታ ቸው የተፈናቀሉ ፣ የቆሰሉ ፣ የሞቱ ፣ መዳረሻቸው የጠፋ ጀግኖቻችን አልፋና ኦሜጋ የማይረሳው መስዋዕትነት ነው … ይህ አንጸባራቂ ድልም እነሆ አልፋና ኦሜጋ በክብር ይዘከራል !
ልክ የዛሬ 118 ዓመት ከዘመነው የፋሽሽት ጣሊያን ጦር እና ጦር ሰራዊት በላይ የጥቁር ህዝብ ብሔራዊ ክብርና ኩራት ልቀው የታዩበት የጦርነት አውድማ ነው ! ዓድዋ !
በዓድዋ ድል እንኮራለን ! የዓድዋን ድል በክብር እናዘክራለን !
ክብር ለደሙ ለቆሰሉና በክብር ለሞቱ ሰማዕታት !
ክብር ለጀግኖቻች አርበኞቻችን !
ከብር ለእምየ ምኒሊክ ! ክብር ለእቴጌ ጣይቱ !
ክብር ለኢትዮጵያ !
እንኳን ለታላቁ የዓድዋ የድል በአል አደረሳችሁ !
ነቢዩ ሲራክ
የመረጃ ምንጮቸ :
* በታዋቂ የታሪክ አዋቂዎች ከተጻፉት የታሪክ መዛግብት፣
*ከአድዋው ጦርነት ዙሪያ ከቀረቡት የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ፣
* በተለያዩ በጊዜ ስለ ዓድዋ ድል ገድል ዙሪያ ከተጻፉ ጋዜጦችና መጽሔቶች ሲሆን ለአንባብያን እንዲመች አድርጌ አቅርቤዋለሁ ።
የአፍሪካ ቀንድ፤ ዙሪያው እሳት መሀሉ ብሶት –በፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም
የአፍሪካን ቀንድ ሰሞኑን ትኩሳት ይዞታል፤ ሁኔታውን ለማብራራትና ለመተንተን ሰፊ ቦታን ስለሚፈልግ አንባቢው ራሱ እንዲያስብበት በመተው ሁነቶችን ብቻ ማቅረቡ የተሻለ ነው፤ የኢትዮጵያን የውስጥ ሁኔታ ትተን በአፍሪካ ቀንድ የሚከተሉትን የተለያዩ ግጭቶችን እንመለከታለን፤
1. በጦርነት ሁኔታ ሁኔታ ላይ ያሉ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች፤–
.ኤርትራና አትዮጵያ
.ሰ.ሱዳንና ደቡብ ሱዳን
1. በውስጥ ብጥብጥ ላይ ያሉ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች
.ሰ.ሱዳን በውስጥ
.ደ.ሱዳን በውስጥ
.ሶማልያ
በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ለጊዜው ግጭት የማይታይባቸው አገሮች ኬንያና ጂቡቲ ብቻ ናቸው፤ ኬንያ ከብሪታንያ ጋር ባለው የቆየ ትስስርና በኬንያ በሚኖሩ የብሪታንያ ሰዎች ምክንያት ጋሻ አለው፤ ጂቡቲም የቆየ የፈረንሳይ ጋሻ ቢኖረውም በአሁኑ ጊዜ አሜሪካም ተጨማሪ ጋሻ ስለሆነ የውጭ ኃይል አይደፍርም፤ ጂቡቲና ኬንያ በእውነትም እንደጌታዋን የተማመነች በግ ናቸው!
የአፍሪካ ቀንድን ውስብስብ የፖሊቲካ ሁኔታ ለመገንዘብ አገሮቹን የሚያካትቱ ማኅበሮች ብዛት መመልከት ነው፤– የአረብ ማኅበር፤ የአሜሪካ ማኅበር፤ የፈረንሳይ ማኅበር፤ የአፍሪካ ማኅበር፤ የትኛው አገር የየትኛው ማኅበር አባል መሆኑን ብቻ ሳይሆን የየትኛው ማኅበር ተቃዋሚ መሆኑንም መረዳት አካባቢው ያለበትን ውስብስብ ሁኔታ ያሳያል፤ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማልያና ጂቡቲ የአሜሪካ ማኅበር አባሎች ናቸው ለማለት ይቻል ይሆናል፤ ጂቡቲና ሶማልያ የአረብ ማኅበር አባሎችም ናቸው፤ በዚያ ላይ አራቱም የአፍሪካ ማኅበር አባሎች ናቸው፤ የማኅበር ትርጉም ትንሽ ያሳስባል።
የአረብ ማኅበር በሰሜን ሱዳን በኩል ሌሎች የማኅበሩን አባላት ግብጽንና ሊብያን ኤርትራን (ተመልካች አባል) ይነካል፤ በሁለቱ ሱዳኖች በኩል የማእከላዊ አፍሪካና የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ነበልባል ይታያል፤ በተጠቀሱት የምዕራብ አፍሪካ አገሮች የሚነደው እሳት በሁለቱ ሱዳኖች በኩል አድርጎ ወደሶማልያና ወደኦጋዴን ሲዘልቅ ከግብጽና ከሊብያ የሚወጣው ነበልባልም ወደሰሜን ሱዳን ይደርሳል፤ በዚህ በእሳት በታጠረው የአፍሪካ ቀንድ ሰፈር አንድ የአሜሪካን አውሮጵላን ተመትቶ ጉዳት ሲደርስበት ሁለት ያህል ሰዎችም ቆስለዋል፤ ይህ ሁሉ በኢራቅ፣ በአፍጋኒስታንና በፓኪስታን የተከፈተውን የአሜሪካንን ‹‹በሽብር ላይ ጦርነት›› ወደአፍሪካ መሻገሩን የሚያመለክት ይመስላል።
ዛሬ በሁለቱ ሱዳኖች፣ በሶማልያና በኦጋዴን ሰላማዊ ሰዎች ምኑንም በማያውቁት ምክንያት ቤታቸው እየተቃጠለና እየፈረሰ፣ ንብረታቸው እየወደመ፣ በደሀነታቸው ላይ መፈናቀልና ስደት ተጨምሮ እየተሰቃዩ ናቸው፤ ነገ አንዳንዶቹ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች እንደኢራቅ፣ እንደአፍጋኒስታንና እንደፓኪስታን ሉዓላዊነታቸውን ያጡ አይሆኑም ለማለት ይቻላል? ከአፍሪካ ቀንድ አገሮች ውስጥ እስካሁን ለአሜሪካ ያልገበረው ኤርትራ ብቻ ነው፤ ይህንንም ሁኔታ ለመለወጥ ኤርትራን ማባበል የተጀመረ ይመስላል።
የአፍሪካን ቀንድ ከከበበው ነበልባል ኢትዮጵያ እንዴት መውጣትና ማምለጥ ትችላለች? የውስጥ ጉዳይ አመራሩ ሳይለወጥ የውጭ ጉዳይ አመራሩ አንዴት ይለወጣል? የውጭ ጉዳይ አመራር አብዛኛውን ጊዜ የውስጥ ጉዳይ አመራር ነጸብራቅ ነው ይባላል፤ እስቲ በዚህ አስተሳሰብ እነዚህን በእሳት የተከበቡ አገሮች እንመልከታቸው፤ ከአዲሱ አገር ከደቡብ ሱዳን እንጀምር፤ ገና በሕጻንነት እሳት ነደደበት፤ እሳቱን የፈጠረው ብሶት ነው፤ አዲሱ ፕሬዚደንት እንደኢትዮጵያ የአገዛዙ ሎሌዎች በቤተ ክርስቲያንም የማይወልቅ ሰፊ ባርሜጣ አድርጎ በሱፍ ልብስ እየተንሳፈፈ በጎሣ አድላዊነት መሥራት ሲጀምር ምክትሉ ተቃውሞውን በመግለጽ ሸፈተ፤ ከሠላሳ ዓመታት በላይ ከሰሜን ሱዳን ጋር በጦርነት ሲደማ የኖረው ሕዝብ አሁን ወደሌላ የጎሣ የእርስበርስ ጦርነት ውስጥ ገባ።
ለየጎሣው ራሳቸውን በመወከል ሥልጣንን መጋራት የሚፈልጉ ሁሉ ለራሳቸው እንጂ ለሕዝብ የሚያስቡ አይደሉም፤ በመሀከላችንም ብዙ ሰዎች፣ የፖሊቲካ መሪዎች ነን ባዮችም የፖሊቲካ መብትን ጉዳይ በሚገባ ያላሰቡበት ናቸው፤ ለምሳሌ በአንድነት ፓርቲ ውስጥ ከጥቂት ዓመታት በፊት በአመራር ላይ የነበሩት ሰዎች በፓርቲው ፕሮግራም ላይ የነበረውን የግለሰብ የፖሊቲካ መብት የግለሰብና የቡድን መብት በእኩልነት ደረጃ እንዲታይ በሚል የለወጡት ይመስለኛል፤ ይህም የሆነው አቶ ግዛቸው፣ አቶ ዓሥራትና ዶር. ኀይሉ አቶ ስዬንና ዶር. ነጋሶን ለመያዝ ሲሉ ነው፤ ግለሰብ የሚያዝ፣ የሚጨበጥ ፣ግዙፍ አካል ያለው ነው፤ ቡድን የፈቃደኛች ግለሰቦች ስብስብ ነው፤ ግለሰቦች ሲገቡና ሲወጡ ይለዋወጣል፤ ግለሰቦች ሳይስማሙ ሲቀሩ ይፈርሳል፤ ግለሰቦች ተስማምተው ዓላማቸውን ሲለውጡ ይለወጣል።
በጎሣ ማኅበረሰብ ውስጥ ብጥብጥ የሚፈጠረው በብሶት ነው፤ ብዙውን ጊዜ የሥልጣን ጥሙን ያላሙዋላ ጎሠኛ በድንገት ጎሣው ከረጢት ውስጥ ይገባና የሙጥኝ ይላል፤ የግሉን ሥልጣን ማጣት ብሶት ወደጎሣው የሥልጣን ማጣት ብሶት ይለውጠውና የፖሊቲካ እንጀራውን መጋገር ይጀምራል፤ በእንደዚህ ያለ የግለሰብ ብሶት የጀመረ መሬት እነዚህን ጎሠኞች ብቻ ሳይሆን፣ ጎሣቸውንም፣ አገሩንም መከራ ውስጥ ይከታሉ፤ ቆስቁሰው እሳት ያነዳሉ፤ የሚቃጠልላቸው ሲጠፋም ራሳቸው እየነደዱ ያልቃሉ፤ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ውስጥ የጎሣ እሳትን የሚቆሰቁሱትን ሰዎች ብንመለከት አብዛኛዎቹ ከሕዝቡ ጋር እየኖሩ ሲጠቃና ሲበደል ሲጮሁለት አይደሉም፤ በየፈረንጅ አገሩ ያገኙትን እየቃረሙ ራሳቸውን ያበለጸጉና በተደላደለ ጡረታ ሠላሳና ዓርባ ሺህ ብር በወር የሚያገኙ ናቸው፤ ለጎሣ መቆርቆር በስተርጅና ሥራ ሲጠፋ የተፈጠረ ፐሮጄክት ነው፤ በሥልጣን ላይ ላሉትም ቢሆን ጥልቅ ሕንጻ ሠርቶ በአምስት ሺህ ዶላር ማከራየት የራስን የሥልጣን ብሶት ወደጎሣ ብሶት በብልጠት በመለወጥ የተገኘ የፖሊቲካ ጥቅም ነው።
የአፍሪካ ቀንድ ሕዝብ እስካልነቃ ድረስ፣ ለራሳቸው ጥቅም የሻረ የጎሣ ቁስል የሚያሹትንና በእውነት ለአጠቃላይ የአገር ጥቅም የሚሠሩትን ለይቶ ካላወቃቸው የጀመረው እሳት እየተስፋፋ የእልቂት ዘመን እንደሚያመጣ መገንዘብ የሚያሻ ይመስለኛል።
ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ለችግሮቻችን የመፍትሄው ቁልፍ
ከገለታው ዘለቀ
የሃገራቸው ነገር ሲነሳ የሚከነክናቸው ወገኖቻችን ኢትዮጵያ ላለባት ችግር መፍት ሄው ምንድነው? እያሉ ኣጥብቀው ሲጠይቁ ይደመጣል። መፍትሄውም ብቻ ሳይሆን ችግሩ ማለትም እውነተኛው ችግር የት ላይ ነው ያለው? ብለውም ኣጥብቀው ሲደመሙ ይታያል። በዛሬዋ ኣጭር ጽህፌ በነዚህ መራራ ጥያቄዎች ዙሪያ ቁንጥል ኣሳብ ለማቀበል ኣስቢያለሁ።
በርግጥም ሁላችን ኢትዮጵያዊያን የሆንን ችግሩ ምንድነው? ብለን ከጠየቅን ኣንዳንዶች ሊገረሙብን ይችላሉ። የችግሩ ተካፋይ ሆነን ሳለ፣ እየተጉላላን ያለነው እኛው ሆነን ሳለ፣ እንደገና መልሰን የሃገራችን ችግር የት ጋር ነው? ብለን ስንጠይቅ የምናወጋቸው ሰዎች ምናልባትም ግራ ሊጋቡ ቢችሉ ኣይደንቅም። ነገር ግን መጠየቃችን ትክክል ነው።
በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ትንቢተ ዳንዔል ላይ ኣንድ ናቡከደነጾር የተባለ ንጉስ ኣንድ ጊዜ ጠቢባንን ጠርቶ የህልም ፍቺ ይጠይቃል። ጥበበኞቹም ህልሙን ንገረንና ፍቺውን እንነግርሃለን ሲሉት ህልሙ ጠፍቶብኛል ስለዚህ ህልሙንም ፍቺውንም ውለዱ ብሎ ጉድ እንዳፈላ እናነባለን።
እኛ ኢትዮጵያዊያን የዋናው ችግር ተጽእኖዎች የየእለት ኑሮኣችንን ሲያምሱት ብናይም ዋናውን የችግሩን ምንጭ መፈለጋችን ግን ኣሁንም ትክክል ነው።
የሃገራችንን ዋና ችግር የት ጋር ነው ብለን ኣጥብቀን ከጠየቅን በርግጥ የስርዓት ችግር ነው ወይ? ስርዓት በማጣታችን ነው ወይ የከፋ ችግር ላይ የወደቅነው? ብለን እንጠይቃለን። በዚህ ኣገባብ ስርዓት ስንል የኣይዲዮሎጂውን ጉዳይ ሳይሆን ፍትህና ተጠያቂነት፣ ግልጽነትና የህዝብ የበላይነት የሚንሸራሸርበት ሲስተም ተዘርግቷል ወይ ብሎ የመጠየቅ ያህል ነው። ስለ ስርዓት ስናነሳ ደግሞ በዋናነት የሚታየው ህገ- መንግስታዊ ስርዓቱ ነው። ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ምን ያህል ለዜጎች ይጨነቃል፣ ምን ያህል ለፍትህና ለነጻነት ለህዝቦች ጥቅም መንሸራሸሪያ ይህናል? ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል። በዚህ ረገድ በርግጥ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም በዋናነት ግን ችግራችን የስርዓት ችግር ሆኖ ኣናይም። ለኣብነት የ1955ቱን ህገ መንግስት ስናይ የፕሬስ ነጻነትን ይሰጣል፣ እኩል የህግ ከለላ ይሰጣል፣ የመሰብሰብ፣ ሰልፍ የማድረግ መብትን ሁሉ ይሰጣል። የደርጉም ቢሆን ለዜጎች የሚጨነቅ ኣይነት ነው። “ኢትዮጵያዊያን በህግ ፊት እኩል ናቸው” ይላል። ከሁሉ በላይ ደግሞ የ1995ቱን ስናይ “ሰብዓዊ መብቶችና ነጻነቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚመነጩ የማይጣሱና የማይገፈፉ ናቸው” ብሎ እጅግ ኣጠንክሮ ለዜጎች መብት መቆሙን ይደነግጋል። በውነቱ ይህ ኣንቀጽ ብቻውን ለኛ ለኢትዮጵያዊያን ዋስትና ይሆን ነበር። ይሁን እንጂ ተግባራዊው እውነት ደግሞ ለብቻው በተቃራኒው ተንሰራፍቶ ይታያል። ይህ ለምን ሆነ? እንዴት እንዲህ ሊሖን ይችላል? ብለን ነው መጠየቅ ያለብን። እንዲህ ስንጠይቅ የችግሩ ዋና ጉዳይም የስርዓት እጦት ሳይሆን ሌላ ጉዳይ መሆኑን እንረዳለን። በርግጥ ለወደፊቱዋ ኢትዮጵያ የተሻለ ስርዓት ማምጣት ያስፈልጋል። በተለይም ብዙህነቱዋን ተንከባክቦ የሚይዝ ማህበራዊ የፖለቲካ ስርዓት ያሻናል። ያ ማለት ግን ከችግራችን እንድንወጣ ብቻውን ዋስትና ነው ማለት ኣይደለም። የቱንም ያህል ጥሩ ስርዓት ዘርግተን ከችግራችን ሳንወጣ ልንቆይ እንችላለን። ርግጥ ነው የማንነት ፖለቲካ ማህበራዊ ቀውስን ያመጣ ችግሮች የበለጠ እንዲነዱ የሚያደርግ ጉዳይ በመሆኑ ከዚህ መንግስት ውድቀት በሁዋላ ከዚህ የፖለቲካ መዋቅር መውጣታችን ለመፍትሄ ትልቅ በር ኣለው። ይሁን እንጂ ኣሁንም ቢሆን የቱንም ያህል ቆንጆ ስርዓት እናምጣ ኢትዮጵያን ከመከራና ከርሃብ የሚያወጣት እሱ ብቻውን ኣይደለም። ታዲያ ምንድነው? የሚል ጥያቄ መምጣት ኣለበት። ኣዎ፣ ዋናው የሃገራችን ችግር ያለው የፖለቲከኖች ስብእና ተክለሰውነት ወይም ፐርሰናሊቲ ጋር የተገናኘ ነው።
ሃገራችን ከችግር እንድትወጣ ከተፈለገ የፖለቲካ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል። የችግሮቻችን ቁንጮም የፖለቲካ ቁርጠኝነት እጦት ነው ብሎ መደምደም ይቻላል።የፖለቲካ ቁርጠኝነት ስንል ኣንድ ፓርቲ ስልጣን ከያዘ በሁዋላ የፍርድ ቤቱን ልጓም ለቀን መልሶ ከበላንም ይብላን፣ በራሳችን ላይ ይፍረድብን፣ ብሎ በራስ ላይ የመወሰን ኣቋም ነው። ወታደሩን ኣገርህን ጠብቅ የፓርቲ ጠባቂ ኣይደለህም ኣንተ ኣገር ጠባቂ ነህ ለማለት የፖለቲካ ሰዎችን ቁርጠኝነት ይጠይቃል። ፖሊሱን፣ ባንኩን፣ ሚዲያውን ሁሉ ልጓሙን ለቆ በሙያህ ኣገልግል ብሎ መወሰን ሲቻል ነው ከገባንበት ኣረንቋ የምንወጣው። የናፈቀንን ዴሞክራሲ በህይወት የምናየው። ጥያቄው ይህ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንዴት ሊመጣ ይችላል ነው። የፖለቲካ ቁርጠኝነት ከጥቂት የፖለቲካ መሪዎች ከራስ ጥቅምና ዝና በላይ የህብረተሰብን ዝናና ጥቅም በተጠሙ ሰዎች ሊነቃነቅ ይችላል። ኣንድ ቁርጠኛ መሪ ኣገር ሊለውጥ ይችላል። በታሪክ የታዩ ኣንዳንድ ቁርጠኛ መሪዎች በየሃገሩ ተነስተው ጥሩ መሰረት እየጣሉ ኣልፈዋል። በሃገራችንም የተጠማነው ይህንን ነው።
በኣሁኑ ጊዜ ተቃዋሚው ክፍል መንግስትን ኣጥብቆ ማውገዙ ትክክል ነው። የህዝቡም ልብ ነጸብራቅ ነው። ይሁን እንጂ ይህ መንግስት በማንኛውም መንገድ ሲወድቅ ስልጣን ይዞ ጥሩ ስርዓት መዘርጋቱ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ቁርጠኝነት (political commitment) ያላቸውን ሰዎች ይዘዋል ወይ? ብለን እንድናስብ ያደርገናል። በዚህ ረገድ ተቃዋሚው ጥቃቅን በሆኑ ፖሊሲዎች ከመከፋፈል ይልቅ ወደ ጋራ እያመሩ ከሁሉ በላይ የፖለቲከኞችን ስብእና የመገንባቱ ላይ ማተኮር ለነገይቱ ኢትዮጵያ ዋስትና ይሆናል። ይህን ስብእና ወይም ተክለሰውነት የመገንባት ስራ ፓርቲዎችን ቢዚ የሚያደርግ ወቅታዊ ስራ መሆን ኣለበት። ኢትዮጵያ በኣሁኑ ደረጃዋ ጥቃቅን ፖሊሲዎችን በማነጻጸር የምታማርጥበት ጊዜ ላይ ኣይደለችም። መሰረታዊ የሆኑ ጉዳዮችን ያጣች በመሆኑዋ የስካንዲኒቪያው ኣይነት ዴሞክራሲ ይሻልሻል የኣሜሪካው ኣይነት? ማለቱ ያልበላትን የማከክ ያህል ነው። ሁሉቱም ሆኖላትስ ነው?
ዋናው በኣሁኑ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጉዳይ ፓርቲዎች እኔ እሻላለሁ ለማለት ዋናው መመዘኛቸው የተሰባሰቡት በተለይም ኣመራር ላይ ያሉት ግለሰቦች የፖለቲካ ቁጠኝነት ኣላቸው ወይ? ቁርጠኝነት በሞላቸው ሰዎች ቁጥር የትኛው ፓርቲ ያይላል? የሚል ልብ ያለው ድጋፍ ነው በተግባር የሚታየው ወይም መታየት ያለብት።
በቲየሪ ደረጃ በኣሁኑዋ ኢትዮጵያ በፍርድ ቤት ጉዳይ መንግስት ጣልቃ ኣይገባም። ይሁን እንጂ በተግባር ይገባል። ይገባል ብቻም ሳይሆን ፍርድ ቤት የፖለቲካ መሳሪያ ነው። ኣሁን እዚህ ጋር የጎዳን የስርዓቱ ወይም የኣሰራሩ ጉዳይ ሳይሆን መከራ ውስጥ የከተተን ጉዳይ የግለሰቦች ስብእና ጉዳይ ሆኖ ነው የምናየው። ለምን እነዚህ ግለሰቦች ስርዓቱን ይጥሳሉ፣ ህጉ ለምን ኣቅም ያጣል? ካልን የፖለቲከኞቹ ላእላይ ስብስብ በተለያየ የግል ጥቅማጥቅም የተተበተበ በመሆኑ ነው። ድህነታችንም ኣንዱ ኣስተዋጾ ያደረገ ይመስላል። የተሻለ ስራ ለማግኝነት፣ ከድህነት ለመላቀቅ፣ ፖለቲካን መሳሪያ ማድረጉ የተለመደ መሆኑና ወደዚያ ጠጋ ያሉ ሃላፊዎች በዚህ ሞቲቭ የተሞሉ ስለበዙበት ስርዓቱ በቁሙ እንዲሞት ኣድርጎታል።
ባለፈው ጊዜ ኢትዮጵያ ብሄራዊ እርቅ ኮሚሽን ማቋቋም ያስፈልጋታል የሚል ኣንድ ኣርቲክል ጽፌ ነበር። በርግጥም በኣሁኑ የነጻነት ትግል ኣሰላለፍ በኩል ጎድሎ የታየው ይሄ ነውና ይህንን ማቋቋም ተገቢ ነው። ይህ ኮሚሽን ፓርቲዎችን እያበራታታ ይህን ተፈላጊ ስብእና በመገንባቱ ረገድ ከፍተኛ ኣስተዋጾ ያደርጋል። ፓርቲዎችን በማቀራረብ ረገድ፣ የመፍትሄ ኣሳቦችን በማጠናቀር ረገድ፣ ለኣዲሲቱዋ ኢትዮጵያ የሚሆነውን ኣዲስ ሰውነት በመጠቆሙ ረገድ ከባድ ሚና ሊጫወት ይችላል። ከዚያ በተረፈ ደግሞ እኛ ተራ ዜጎች መሪዎቻችንን የማጎልበትና ወደ ህብረት የመግፋት እንዲሁም ስብእናቸውን የመገንባት ሃላፊነት ኣለብን።
የብዙ ኣፍሪካ ሃገሮች ችግር ይሄ ይመስለኛል። ታግለን በብዙ መስዋእትነት ኣንድ ኣምባገነን ከጣልን በኋላ መልሰን በሌላ ኣምባ ገነን እንተካለን። ሌላው ኣለም እየተሻሻለ ሲሄድ ይሄኛው ክፍለ ኣለም ወደ ኋላ የቀረበት ትልቁ ምክንያት የነጻነት ታጋዮች ራሳቸው በሚገባ ለኣመራር የሚበቃ ስብእና ሳያዳብሩ ወደ ስልጣን ስለሚመጡ ነው።ደቡብ ሱዳን ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናት። ለብዙ ኣመታት የነጻነት ትግል ታግለው፣ ብዙ ደም በመፍሰሱ ዓለም ሁሉ እነዚህ ሰዎች ቢገነጠሉ ይሻላል ብሎ ፈርዶላቸው ተገነጠሉ። የዳርፉሩን እልቂት የማያውቅ፣ ያልሰማ ያለም ክፍል የለም። ያ ሁሉ ሆኖ ኣዲስ ኣገር ከመሰረቱ በኋላ ገና ኣንድ ጊዜ እንኳን ምርጫ ሳያካሂዱ፣ በህዝብ የተመረጠ መንግስት ሳይመሰርቱ፣ ከሁለት ዓመት ያልዘለለ እድሜ ያላትን ኣገር በጎሳ ከፋፍለው ማመስ ጀመሩ።
ያለ መታደል ሆኖብን በኣንዳንድ ኣፍሪካ ሃገራት የሚነሱ መሪዎች ስልጣን ላይ ከመጡ በሁዋላ ሁለት ነገር በጣም ይወዳሉ። ኣንደኛው ዝና ሲሆን ሁለተኛው ገንዘብ ነው። ሁለቱም እጆቻቸው ይዘዋል። ባንዱ ስልጣን በሌላው ገንዘብ። ዝናውን ወደው ገንዘቡን ችላ የሚሉ ቢሆኑ ትንሽ ይሻል ነበር። ነገር ግን ሁለቱንም በሃይል ስለሚወዱና ለዚህ የተሰጠ ስብእናቸው በውስጣቸው ስላልሞተ ክብ በሆነ ችግር ውስጥ እንድንወድቅ ኣድርጎናል።ኢትዮጵያዊያን በዚህ ላይ ልንነቃ ይገባናል። በተለይ የፖለቲካ ሰው መሆን የፈለጉ ወገኖቻችን፣ መሪ መሆን የሚሹ ወገኖቻችን በየጊዜው የባህርይ ለውጥ እያሳዩ በኣመለካከትና በሃላፊነት ስሜት እያደጉልን እንዲሄዱ እንሻለን። ከፍ ሲል እንዳልኩት እኛ ተራ ዜጎች ከውጭ ሆነን መፍረድ ብቻ ሳይሆን መሪዎቻችንን መንከባከብና ፍቅርን ክብርን ማሳየት ለፖለቲካ ቁርጠኝነታቸው ሃይል ይሰጣል።
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!
geletawzeleke@gmail.com
“ኢትዮጵያ በተደራጀ ምዝበራ እየደማች ነው”–ዶ/ር አክሎግ ቢራራ (ሊያደምጡት የሚገባ ቃለምልልስ)
“ኢትዮጵያ በተደራጀ ምዝበራ እየደማች ነው፤ ይሔ ውጭ ውጭውን የሚታየው ህንጻ በአገሪቱ ላይ የተንሰራፋው ድህነት ግርዶሽ ነው”
- ዶ/ር አክሎግ ቢራራ
ዶ/ር አክሎግ ቢራራ የቀድሞ የዓለም ባንክ የኢኮኖሚ አማካሪና ተመራማሪ በህብር ሬዲዮ አራተኛ ዓመት በዓል ላይ በመገኘት ካቀረቡት ጥናታዊ ሪፖርት የተወሰደ
የህብር ሬዲዮ 4ተኛ ዓመት በዓል ላይ ባለፈው ረቡዕ የካቲት 26 /2014 በቬጋስ በመገኘት ዶ/ር አክሎግ ቢራራ በልማት ስም ግርዶሽ የሚለውን ጥናታቸውን ለበዓሉ ተሳታፊዎች አቅርበዋል። ከበዓሉ ማግስት ለዶ/ር አክሎግ የተለያዩ መሰረታዊ ጥያቄዎችን ሕብር ራድዮ አቅርባ መልሰዋል። ይከታተሉት።
የተምቤን ስብሰባችን ጉድ አደረገን (አብርሃ ደስታ)
ህወሓቶች በተለያየ አከባቢ የሚገኙ ወጣቶች ሰብስበው እያነጋገሩ ነው። የስብሰባው ዓላማም “በተቃዋሚዎች እንዳትሸወዱ፣ ከህወሓት ዉጭ ሌላ አማራጭ የላችሁም፣ ስራ እንሰጣችኋለን፣ በተቃዋሚዎች ስብሰባ እንዳትሳተፉ …” ወዘተ እያሉ ወጣቶቹን ለማስጠንቀቅ ነው።
ህወሓቶች ከልክ በላይ ፈርተዋል። ዓላማቸው ሁሉ ህዝብ በዓረና ስብሰባ ላይ እንዳይሳተፍ ማድረግ ነው። ለምን ይህን ያህል ፈሩ? የተምቤን ስብሰባችን ነው ጉድ ያደረገን። በተምቤን ዓብይዓዲ ስብሰባ በጠራንበት ግዜ ህወሓቶች የተከተሉት ስትራተጂ መጀመርያ ህዝብ ወደ ስብሰባ እንዳይገባ መከልከል፣ በድፍረት በስብሰባው ለመሳተፍ ከገባ ግን የህወሓት ካድሬዎችን በመላክና “ጠንካራ” ጥያቄዎችን በማንሳት የዓረና መሪዎችን ህዝብ ፊት ማዋረድ፣ ካድሬዎቹ የመከራከርና የመጠየቅ ዕድል ከተነፈጉ ደግሞ “ዴሞክራሲያዊ አይደሉም” በማለት በህዝብ ፊት ማጋለጥ የሚል ነበር።
ህዝብ በስብሰባው እንዳይሳተፍ የነበረ ዕቅድ አልተሳካም። ምክንያቱም ህዝቡ የካሬዎች ማስፈራራት ሳይበግረው ገባ። ካድሬዎችም ለመከራከርና ለመጠየቅ ገቡ። ጠየቁ፤ ተከራከሩ። እኛም በቂ መልስ ሰጠን። ተሳታፊም ገመገመን። በስብሰባው የተሳተፉ ካድሬዎች ሳይቀሩ በኛ ሐሳብ ተስማሙ። በህወሓት ስብሰባዎችም የዓረና አመራር አባላት ያነሱት ሐሳብ ተነሳ። እንዲረብሹን የተላኩ ካድሬዎች ጭራሽ የኛ ተወካዮች ሁነው በራሳቸው (በህወሓት) ስብሰባ የዓረና አጀንዳ እያነሱ መከራከር ጀመሩ። ህወሓቶች በዓረና ስብሰባ የተሳተፉ የህወሓት አባላት በሙሉ ዓረና ሁነዋል ብለው ደመደሙ። ከዛ በኋላ ማንም የህወሓት አባል ዓረና በሚጠራው ስብሰባ እንዳይሳተፍ ትእዛዝ ተሰጠ። (በየዞኑ ይካሄድ በነበረ የህወሓት ካድሬዎች ስብሰባ የተምቤን ካድሬዎች ጤነኞች አይደሉም በሚል ምክንያት ከሌሎች ጋር ሳይቀላቀሉ ለብቻቸው እንዲሰበሰቡ ተደርጓል)።
ከተምቤን ስብሰባ በኋላ ዓረና ህዝብ ሰብስቦ ማነጋገር አልቻለም። የሽረ፣ ዓዲግራትና ሑመራ ተረብሿል። አሁን ህወሓቶች እየተከተሉት ያለ ስትራተጂ ህዝብ በዓረና ስብሰባ እንዳይገኝ መከልከል ብቻ ነው። ምክንያት: በዓረና ስብሰባ የተሳተፈ ሰው (የህወሓት አባል ጭምር) ዓረና የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ ነው የሚል ነው።
አሁን በብዙ አከባቢዎች እየተደረገ ያለው ጥረትም ህዝብ ሌላ አማራጭ የፖለቲካ ድርጅት ሐሳብ እንዳይሰማ በራሳቸው ፕሮፓጋንዳ ማደንቆር ነው። ዓረና ህዝብ እንዳይሰበስብ በመከልከል ራሳቸው ስብሰባ እየጠሩ በዓረና ስብሰባ እንዳይሳተፍ ያስጠነቅቁታል። ህዝብ ግን ለውጥ ይፈልጋል፣ ተነሳስቷል።
የትግራይ ህዝብ ለምንድነው የራሱ የፖለቲካ አስተሳሰብ እንዲያዳብር የማይፈቀድለት? ለምንድነው በህወሓቶች ትእዛዝ እንዲያስብ፣ እንዲጓዝ የተፈረደበት? የትግራይ እናት የህወሓት ሰዎች ወልዳ መክናለች ያለ ማነው? የትግራይ ህዝብ የፈለገውን የመከተል መብቱ የተነፈገው ብዙ መስዋእትነት ስለከፈለ ነው? በነፃነት ለመኖር መስዋእት መክፈል አያስፈልግም ማለት ነው? እልህ አስጨራሽ ትግል አድርጎ፣ ብዙ መስዋእትነት የከፈለ ህዝብ ለምን በነፃነት እንዳያስብ ታፈነ? ወጣቶችን በመሰብሰብ ህወሓቶች ከሚጓዙበት መንገድ ዉጭ ሌላ አቅጣጫ መከተል ስህተት እንደሆነ መስበክ ለወጣቶቹ ያለንን ንቀት አያሳይም? ወጣቶችኮ የራሳቸው መንገድ አላቸው። ለምን ነፃ እንዲሆኑ አይፈቀድላቸውም?
አዎ! በዓረና ስብሰባ የተሳተፈ ሁሉ ዓረና እንደማደርገው አልጠራጠርም፣ የህወሓት አባላትም ጭምር። ያለኝ ዕቅድ በዓረና ስብሰባ የተሳተፈ ሁሉ ዓረና ማድረግ ነው፤ እንደ ህወሓት በጠብመንጃ በማስፈራራት ወይ ገንዘብና ስልጣን በመስጠት አይደለም። በሐሳብ በማሳመንና የለውጥ አስፈላጊነት በማስረዳት እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን የመገንባት ተልእኮአችን በመጠቆም እንጂ።
ወጣቶች ሆይ! በስብሰባ እንዳትሳተፉ የሚደረግ ማንኛውም ትእዛዝ አትቀበሉ። ምክንያቱም በየትኛውም ስብሰባ የመሳተፍ መብት አላቹ። በስብሰባ ለመሳተፍና ላለመሳተፍ የሚወስንላቹ ህወሓት ሳይሆን እናንተ ናችሁ። ምክንያቱም በህይወታቹ ላይ ተፅዕኖ ላለው ጉዳይ የመወሰን ነፃነቱ ሊኖራቹ ይገባል። ህወሓት ከናንተ በላይ ስለናንተ አያውቅም። በለውጥ ሂደቱ ተሳታፊ ሁኑ። ህልውናችሁን አረጋግጡ። ህወሓት እየሰራው ያለው ተግባር በራሱ ዓፈና ነው። ጭቆና ነው። ፀረ ዓፈና ተነሱ። ጭቆናን አስወገድን ነፃነታችንን እናስመልስ።
እዛው በነፃነት ሥፍራው እንገናኝ። እጠብቃችኋለሁ።
It is so!!!
የፈራ ይመለስ! (ከተመስገን ደሳለኝ)
በ2004 ዓ.ም የካቲት 23 ቀን በታተመችው ‹‹ፍትሕ›› ጋዜጣ ላይ፣ ‹‹የፈራ ይመለስ!›› በሚል ተመሳሳይ ርዕስ፣ ከሰላማዊ አብዮት ውጪ አማራጭ ካለመኖሩም ባለፈ፣ ኢህአዴግ ቢያንስ ሕገ-መንግስታዊ ጥበቃ ላላቸው ሕዝባዊ ጥያቄዎች ምላሽ የመስጠት አቅምም ፍላጎትም እንደሌለውለመሞገት ሞክሬ ነበር፡፡ ግና፣ አገዛዙ ለእንዲህ ያሉ ግዴታዎች የተዘጋጀ ባለመሆኑ ከማድመጥ-መዳ–መጥን፤ ከመመከር-መከራን፤ ከማሰብ-ቃሊቲ መሰብሰብን፤ ከመሻሻል-ከሀገር ማሸሽን፤ ከማመን-መርገጥን… በመምረጡ፤ ዛሬም ድረስ ነፃነት ናፋቂው ዘመነኛ ትውልድ፣ በፀጥታ አርምሞ ወደተዋጡት አደባባዮች ከማማተር ያለፈ አማራጭ እንዳያገኝ ገፊ-ምክንያት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ያንን ጽሑፉም ከዓመት ከስድስት ወር በላይ ፍርድ ቤት ከምመላለስባቸው ክሶች የአንዱ መወንጀያ አድርጎ በተከበረችዋ ፍትሕ እየተሳለቀባት ነው፡፡ በርግጥ ጉዳዩ ገና እልባት ያላገኘ በመሆኑ፣ በዚህ ተጠየቅ አናነሳውም፡፡
ያ ጽሑፍ የታተመባት ‹‹ፍትሕ›› ጋዜጣ የስርዓቱ ቅጥ ያጣ አፈና ሰለባ የመሆኗን ጉዳይ ግን ሁሌም ስናወሳው እንኖራለን፤ ምክንያቱም የ‹‹ቅድመ-ምርመራ›› (ሳንሱር) ግብአተ-መሬት በግላጭ በሕገ-መንግስቱ ሳይቀር ከታወጀ ሃያ ዓመት ባስቆጠረበት ኢህአዴጋዊ ዘመን የተፈፀመ ታላቅ መብት ረገጣ ነውና፤ ያውም ተራ የወሮበሎች ረገጣ መሆኑን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ፡፡ በመንግስታዊው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ለዚሁ ሕገ-ወጥ ተግባር አድፍጠው እንዲጠብቁ የተመደቡ ‹ግልገል› ካድሬዎች ጋዜጣዋ የምትታተምበትን ሐሙስ ቀንን በዝምታ አሳልፈው ነገር ግን ድንገት በዕለተ አርብ ማለዳ ‹‹ይህንን ዜና ማውጣት አትችሉም! ቆርጣችሁ አውጡ›› ማለታቸው ነው፤ ምን ዋጋ አለው ትዕዛዛቸው ተቀባይነት ባለማግኘቱ፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ገንዘብ ውጪ የተደረገበትን፣ 30 ሺህ የጋዜጣዋ ህትመት እንዲቃጠል በፍርድ ቤቱ አማካኝነት በጭካኔ በየኑ፤ ‹‹ፍትሕ››ንም በሕገ-ወጥ መንገድ ዳግም እንዳትታተም አገዱ፤ ይህ ሁሉ ከሆነ እነሆ ሃያ ወራት ተቆጥሯል፡፡ ግና፣ የተከፈለው ሁሉ ስለነገ የተሻለች ኢትዮጵያ ሲባል ነውና ባለፈ ጉዳይ ማለቃቀሱን እዚሁ ገታ አድርገን፣ ኩነቱንም ከነጋዴነት ለተሻገሩ ታሪክ ጸሐፊዎች ትተን፣ በአዲስ መስመር ወደ አጀንዳችን እንለፍ፡፡
የፈራ ይመለስ!
አዎ፣ ይመለስ!! ፍርሃቱን ‹‹አሜን›› ብሎ ተቀብሎ ለመመለስ ከወሰነ በመረጠው የጭቆና ቀንበር እየተቀጠቀጠ ማደር መብቱ ነው፤ ግና፣ አንዳንድ ፈሪዎች፣ አንዳንድ መሀል ሰፋሪዎች በስመ ‹‹ጸሐፊነት›› ጥያቄውን በማጣጣል ለውጡን ለማራዘም (ለማደናቀፍ) የሚያደርጉት ሙከራ ከንቱ እንደሆነ በቅድሚያ ላስገነዝብ እወዳለሁ፡፡ ደግሞም እነኚህ የጭቆና ዘመን አራዛሚዎች እያገለገሉት ያለው ስርዓት የሚያከፋፍለው ብሔራዊ ዳቦ እየተመናመነ መምጣቱን፣ ገዥዎቹ ራሳቸው የፓርቲያቸው ችግር (7 ሚሊዮን የሚደርሱ ካድሬዎችን ከማግበስበሱ አኳያ) ‹‹የጥቅመኞች መብዛት›› እንደሆነ በይፋ አምነው ከተቀበሉት ጋር ስንገምደው የነገ ቀናቸው ‹‹ከኢህአዴግ ጋር ብሩህ›› እንዳልሆነ እግረ መንገዴንም ልጠቁማቸው እፈልጋለሁ፡፡ በአንፃሩ እነዚያ ሀገሪቷን እያሰመጠ ያለውን የመከራ ረግረግ ተረድተው አብዮቱን ተስፋ ያደረጉ ጎበዛዝት እና ወይዛዝርት ደግሞ ይበልጥ እንዲነቁ፣ ይበልጥ እንዲበረቱ… የጊዜውን መቃረብ ላስታውሳቸው እወዳለሁ፡፡ ምክንያቱም በቁጣ አደባባይ ለመውጣት እንቅፋት የሆነው ብሔራዊ ፍርሃት ይሰበር ዘንድ ለመስበክ፣ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በነፃነቷ ትበጽህ ዘንድ ካስረገጠው ከዚህ መቶ አስራ ስምንተኛው የዐድዋ ድል ዋዜማ የበለጠ ምቹ ጊዜ የለምና (ይህ ድል በነፃነት የሚያምን የሰው ልጅ ሁሉ፣ ያለቀለም ልዩነት ሊዘክረው የሚገባ ስለመሆኑ ለእነርሱም ጭምር መመስክር ግዴታ ይመስለኛል)
እንዲህ በጽሑፍ ሲገለፅ በእጅጉ የሚቀለው የዐድዋ ገድል፣ እልፍ አእላፍ የሀገሬ ሰዎች መተኪያ አልባ ህይወታቸውን የገበሩበት በመሆኑ፣ በየዓመቱ ደግመን ደጋግመን የመዘከርና አደራውን የመቀበል ታሪካዊ ግዴታ ውስጥ ጥሎን ማለፉ እውነት ነው፡፡ ‹‹የተሰጠኝ ህይወት ዛሬ በነፃነት፣ ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት›› እንድትል እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ)፤ እኒያ ሰማዕታት ከዳር እስከዳር ነቅለው ‹‹…ሀገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል?›› በሚል መታመን ተቀስቅሰው፣ ባሕር አቋርጦ፣ አድማስ ተሻግሮ የመጣውን ወራሪ ሀፍረት አልብሰው፣ ሀፍረት አስታጥቀው፣ ሀፍረት አጉርሰው… የመመለሳቸው ብርታት ባለዕዳዎች መሆናችንን ዘመን ሊሽረው አይችልም፡፡ ያ ጣፋጭ ድል ኢትዮጵያችንን በዓለም ፊት ‹ነፃ ሀገር› የተሰኘ የታሪክ ሜዳሊያ አጥልቃ ትኮራ ዘንድ ካባ ማጎናፀፉም ዓመታዊ ዝክሩ መቼም ቢሆን በቸልታ እንዳይታለፍ አድርጎታል፡፡ እናም እነዛን ባለውለታዎች ከታላቅ የክብር ሰላምታ ጋር እንዲህ ስል ላወድሳቸው እገደዳለሁ፡-
ዘላለማዊ ክብር ለዐድዋ ጀግኖች!!!
የፈራ ይመለስ!
እንግዲህ ጀግኖች አባቶቻችን በዚህ መልኩ ላለፉት ሶስት ሺህ ዘመናት ለነፃነታችን ሲዋደቁ ኖረዋል፡፡ በውጤቱም ነፃ ሀገር አስረክበውናል፡፡ ይሁንና ዛሬም እኛ ዘመነኛ ትውልድ ‹‹ነፃነት›› እያለን የምንጮኽለት ይህ ክቡር ጉዳይ ገና ምላሽ ላገኘም፡፡ በርግጥ ጥያቄው ከባዕድ ወረራና ተወራሪ ጋር የሚጋመድ አይደለም፤ ከሀገር ልጆች ጭቆና እንጂ፡፡ እንዲህ ‹ነፃነታችንን!› እያልን የምንጮኽለት መንፈስም፣ ወራሪውን ጣሊያን ያሸነፉ ቀዳሚ አባቶች ያላቆዩልን፣ ግን ደግሞ በጥያቄው ስም ጥተው፣ መልሰው መንፈሱን የጨፈለቁት ገዥዎቻችን የነጠቁንን መብት የሚወክል ነው፡፡ በአናቱም የትግሉ መንገድ በቅኝ ግዛት ለማሳደር በቀቢፀ-ተስፋ ተሞልቶ ወሰን የተጋፋው ጣሊያን ተሸንፎ ከተባረረበት ጋር ዝምድና የሌለው መሆኑን መረዳት ያሻል፡፡ ምክንያቱም ዘመነኛው የነፃነት ጥያቄ፣ እንደ ዐድዋው መድፍ አጓርቶ፤ መትረየስ የሳት-ላንቃውን ከፍቶ ሞት እየረጨ ሊፈታው አይችልምና ነው፡፡ ይህ አይነቱ የፋኖ መንገድ አንድም ጊዜው ያለፈበት ሲሆን፤ ሁለትም ህወሓት-ኢህአዴግን ለአራት ኪሎው ቤተ-መንግስት ቢያበቃውም፣ የታየው ለውጥ መለዮ ለባሽ ወታደርን፣ ገና ዝላዩን ባልጨረሰ የተማሪ አምባገነን ከመተካት አለመዝለሉ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
ስለሆነም ዛሬ ጭቆናን የማሸነፊያ ብቸኛ መንገድ የፍርሃት ሰንሰለትን ሰባብሮ፣ በጨቋኞች ፍቃድ ለቆመው ስርዓትም ሆነ በድምፀ-አልባ ተወካዮቹ አጃቢነት ለፀደቁት ሕግጋት አለመታዘዝ ላይ የተመሰረተ ብቻ ነው፡፡ በእምቢተኝነት ደም-አልባ ሰላማዊ አመፅ የገዥዎችን ሰፈር ማራድ፤ እኩይ አላማዎቻቸውን የሚያስፈፅሙ ተቋማትን ጥርስ አልባ ማድረግ፤ አደባባዮችን በሰው ጎርፍ ማጥለቅለቅ፤ የትኛውንም አይነት ተቋማዊ ትብብርን መንፈግ፤ ኤፈርትና መሰሎቹን የንግድ ድርጅቶቻቸውን ማግለል፤ ሁሉም ፖለቲካዊ ፍላጎቶቻችን በኢትዮጵያዊ ዜግነት ስር እንደሚፈቱ ከልብ በማመን-ነገን ማለም፤ ለጥያቄው እስኪንበረከኩ ድረስ በሰላማዊው ተቃውሞ ፀንቶ መቆምንና መሰል ስልቶችን መተግበር ብቸኛ አማራጭ ነው፡፡ ይህ ይፈፀም ዘንድም በራስ ጉያ ፀለምት ለብሶ የተሸሸገ ፍርሃትን የተሻገሩ ጎበዛዝትና ወይዛዝርት ሊፈተኑበት፤ ከሽፈው የቀሩት ደግሞ ጥያቄውን በማጥላላትም ሆነ የተራራ ያህል በማግዘፍ ፍርሃትን አንብረው የአገዛዙን ዕድሜ ለማራዘም ደፋ-ቀና ከማለት ይታቀቡ ዘንድ የሚገደዱበት ዕለት ከደጅ መድረሱን ለመተንበይ ነብይ መሆንን አይጠይቅም፤ አይኖች-ያያሉ፤ ጆሮዎችም- ይሰማሉና፡፡
ግና፣ ይቺም ኑሮ ሆና እንዲህ የትውልድ ተጋሪዬ ጭሮ ግሮ ለማደር (አነስተኛና ጥቃቅንን ልብ ይሏል) በፖለቲካ አቋም እና በዘውግ ማንነት ተፈትኖ ማለፍ ግድ በሆነበት የሀገሬ ምድር፣ እውነት መመስከርን ስለምን በጀብደኝነት አንድምታ ታቃልለዋለህ? የተጠናወተህን ገደብ አልባ ፍርሃት፣ ለውጥ የሚጠይቁ ድምፆችን በማጣጣል ለመሸፋፈን መዳከር የት ያደርስሀል? የወላዋይ ብዕርህን ‹‹የለሁበትም!!›› ቅኔ ለበስ አቤቱታ እና ‹እውነት ለመናገር ጊዜና ቦታ አለው› የሚል ፍርሃታዊ ማምለጫህንስ ስለምን ለታናናሾችህ ለመጋት ትደክማለህ? በአገዛዙ መዝገበ-ቃላት ‹‹ፅንፈኛ፣ ጀብደኛ…›› ብለህ ማምታታትስ ባለፈ ዘመን ላይ መከተር አይደለምን? እውነት እውነት እልሀለሁም፡- በሰላማዊ መንገድ የስርዓት ለውጥን መጠየቅ፣ በ‹አትነሳም ወይ!› የሀገር ባለቤትነት ከፍታ ለአደባባይ ተቃውሞ ዘመነኞችን በእሪታ መጣራት፣ በየትኛውም የታሪክ ስፍር ጀብደኝነት ሆኖ አያውቅም፤ ለሕሊና መታመን እንጂ፡፡
በግልባጩ ነፃነትን ያህል ውድ ነገር የሚጠይቀውን ክቡድ መንፈስ ለማራከስ መሽቀዳደም፣ በንፁሀን ደም ከተጨማለቀው ጨቋኝ ገዥ የታማኝ ባለሟልነትን ማዕረግ ለማግኘት መባተል፣ ከዘመን መንፈስ ቀልባሽነት፣ በሞቀበት ከሚዘፍን ሆድ- አዳሪነት… ከቶስ ቢሆን በምን ይለያል? እመነኝ ‹ከአንድ እጅ ጣት በላይ የሚቆጠሩ ሀገራዊ የለውጥ ዕድሎች ስለምን ባከኑ ?› ብለህ ብታንሰላስል፤ ተጠያቂው የአገዛዙ አፈ-ሙዝ ብቻ አለመሆኑ ይገባሀል፤ ይልቁንም ሕዝብን በ‹ጎልያድ›፣ መንግስትን በ‹ዳዊት› መስለው የሚሰብኩ ሃሳዊያን ጻሐፍት ያነበሩት ታላቅ ፍርሃትም ድርሻ እንዳለው ትረዳለህና፡፡ ግና፣ ይህ ሁሉ ሆኖም አንድ ነገር እውነት ነው፤ ከገዘፈ የአመድ ተራራ ስር ፍንጥርጣሪ የጋሉ ፍሞችን የሚያገላብጥ ትውልድ እየመጣ ነው፡፡ ያን ጊዜም አንተን ዘንግቶ የትውልዱ መንፈስ ወካዮችን ብራና ላይ በክብር ይከትባል፡፡ ለነገሩ ቢዘገይም ታሪክ ከእውነት እንጂ ከፍርሃት ውል ኖሯት አያውቅም፡፡
የፈራ ይመለስ!
ጥቂት ጉልበታሞች ለሚንደላቀ ጥቂት ጉልበታሞች ለሚንደላቀቁበት፣ ዘጠና ሚሊዮን ሕዝብ ለምን ይሰቃያል? ጭቆናን በዚህ ደረጃ ታግሶ መሸከምስ ከግዑዝነት በምን ይለያል? የወፍን ያህል የራስ ጎጆ መመኘት እንኳ እንደ ህብስተ መና በራቀበት ምድር፣ ግብር-ነጠቃን ባስከነዳበት ሀገር፣ ዜጎች በምርኮኛ ሕግ ተቀፍድደው ውለው በሚያድሩበት ክልል፣ መማር ድንጋይ ከመፍለጥ በማያሻግርበት ዘመን፣ የመኖርና ያለመኖር ግድግዳ ተደርምሶ ሁሉም ነገር ትርጉም የለሽ በሆነባት፣ ፍዘት፣ ቁዘማ ባረበበባት ኢትዮጵያ… ዝምታ ስንት ዘመን ይፈጃል? ኢህአዴግ እንዲህ በክፋት ጎዳና እየተመላለሰ፣ በጭካኔ በትር እያስገበረ፣ ፍትሕን የ‹አመፃ ድምፅ ማፈኛ›› አርጩሜ አድርጎ እያሴሰናት… ከሁለት አስርት በላይ ተደላድሎ እንዲቀመጥ ያደረገው የቀደሙት ትውልዶች ርግማን አይምሰልህ፤ አገር-ለበስ ፍርሃት እና ቸልተኝነት እንጂ፡፡ በአናቱም ስደት የስርዓቱ ማስተንፈሻ እንጂ የለውጥ ኃይል ሆኖ አያውቅምና ሲገፉህ- አትንደርደር፤ ሲያስሩህ-አትሸበር፤ ሲከሱህ-አትደንብር፤ ሲወነጅሉህ-አትሸማቀቅ፤ ሲያስፈራሩህ-አትደንግጥ፣ ሲያባራሩህ- አትሩጥ… ምክንያቱም ፍርሃትን የመስበሪያ ፅኑ አለት ይህ ብቻ ነውና፡፡ በተቀረ እነርሱ የሚለፍፉለት ‹‹ምርጫ›› ከአንድም አራቴ ሲያፋፍሩበት በመታየቱ ካለፈው ለውጥ ይኖረዋል ብለህ አትሞኝ፤ ከዚህ በኋላ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው ሰላማዊ እምቢተኝነት አንጂ፣ አባዱላ ገመዳን ተሸክሞት እስከመሮጥ ያደረሰው ያ የይስሙላ ኮሮጆ አይደለም፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገትም ብቻውን የፖለቲካ ለውጥ አያመጣም፡፡ ዳሩ፣ ሲጀመርስ ዕድገቱ የት አለና?! ኢህአዴግ በነቢብ ‹መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ አፋፍ ደርሻለሁ› በሚል ፕሮፓጋንዳ ቢያሰለቸንም፤ በገቢር አዳዲስ ምሬቶችን እያቆረ ስለመሆኑ በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ‹‹አደህይቶ ማዳከም!›› እንዲሉ ፕሮፌሰር መስፍን፣ ድህነትን የሚፈለፍሉ ኩሬዎችን በየመንደሩ ከመቆፈር ቸል ብሎ አያውቅም፡፡ ይሁንና የፍትህ መዛባት፣ ስራ-አጥነት፣ የመኖሪያ ቤት ችግር፣ መቆጣጠር የተሳነው የዋጋ ግሽበት፣ ማቆሚያ ያጣው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ፣ ባልተጠና እቅድ ተቆፋፍረው ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ መንገዶች፣ አመቺ የስራ ቦታን በድርጅት የድጋፍና ተቃውሞ ሚዛን ማከፋፈል፣ አድሎአዊ አሰራር…
ብሶት የሚወልዳቸውን ነፃነት አብሳሪ አናብስት ጋላቢ ጀግኖችን ማበራከቱ አይቀሬ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ዶ/ር መረራ ጉዲና ‹‹የራበው ሕዝብ መሪዎቹን ይበላል›› የሚል ቅድመ-ትንቢያ ቢነግረንም፣ ሰሞኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላንን ጠልፎ ከመድረሻው ውጪ ያሳረፈው የኃይለመድህን አበራ ክስተት ደግሞ በአንፃሩ ርሃብን ያሸነፈው የማህበረሰብ ክፍልም ሰዋዊ ነፃነቱን ለማስረገጥ ሲል መሪዎችን ሊባላ እንደሚችል የሚያመላክት ነው፡፡ ይህ ሰው ማህበራዊ አክብሮትን በሚያጎናፅፍ ሙያ የተሰማራ ከመሆኑም በላይ፣ በኢትዮጵያ የሲቪል ሰርቪስ እርከን እጅግ ከፍተኛ ሊባል የሚችል ደሞዝ ተከፋይ ነው፡፡ ከዚህ አኳያም በአስከፊ ደረጃ የተንሰራፋውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም ብዙም እንደማይቸገር በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ ሀገር ቤት መኖር ካልፈለገም፣ ወደበለፀጉት ሀገራት ተሻግሮ ስራ ማግኘት እንደማይሳነው ያውቃል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ግና፣ ይህ ሁሉ እውነት ቢሆንም የመረጠው መንገድ በራስ ላይ ቀድሞ ሊገመት
የማይችል አደጋ የሚጋብዝን ነው፡፡ እንግዲህ ከእነዚህ ተጨባጭ እውነቶች ተነስተን (እርሱ ራሱ ድርጊቱን የፈፀመበት ምክንያት ለስዊዘርላንድ ፍርድ ቤት እስኪናገር መጠበቁን ታሳቢ አድርገን) መላ-ምቶችን ማስቀመጥ እንችላለን ብዬ አስባለሁ፡፡ ለድርጊቱ በዋናነት መግፍኤ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው አየር መንገዱ የገባበት ችግር ነው፤ ምክንያቱም ድርጅቱ በሂደት ህልፈቱን ወደሚያውጅበት መስቀል (ችንካር) እንዲያዘግም ገፊ ከሆኑ ጉዳዮች አስተዳደራዊ በደል የአንበሳውን ድርሻ ይይዛልና፡፡ አገዛዙ አንዳንድ የድርጅቱን ሰራተኞች በመዓት አይኑ ወደሚመመለከትበት ጠርዝ ያደረሰው ከዚህ ቀደም ‹በአውሮፕላኖቹ ላይ ባለኮከቡን ባንዲራ አትማለሁ› በሚል የፈጠረው አንጃ-ግራንጃ፣ በተወሰኑ ነባርና በጣም ወሳኝ ሰራተኞች ፊት-አውራሪነት በተቀሰቀሰ ተቃውሞ የተስተጓጎለበት ደረቅ እውነታ አንዱ ተደርጎ ይጠቀሳል፤ ሌላው ደግሞ ጠንካራና በሚገባ የተደራጃ የነበረውን የሰራተኛ ማህበር ለመቆጣጠር ያደረገውን ሙከራ ተከትሎ የገጠመው ተግዳሮት ነው (ዛሬ ማህበሩን ማስገበር መቻሉ ሳይዘነጋ)፡፡ እንዲህ አይነት ሕገ-መንግስታዊ ድፍረቶችን የስርዓቱ ኤጲስ-ቆጶሳት በቸልታ የሚያልፏቸው ባለመሆኑ፣ የተወሰዱት የማባረርና ከቦታ ዝቅ የማድረግ ፖለቲካዊ እርምጃዎች አየር መንገዱ ዛሬ ለደረሰበት ውድቀት መንገድ ከመጥረጉም በላይ፣ ተማራሪ ሰራተኞች እንዲበዙ አድርጓል፡፡ በአመክንዮ ድርጅቱ ከባለሙያ እጥረት (አቅም ማነስ) ጋር ብቻ ተያይዞ እየደረሰበት ያለውን ችግር ለመረዳት በስምንት ወር ውስጥ ብቻ ያጋጠመውን አራት ትላልቅ አደጋዎች ልጥቀስ፡- ካርጎ (Cargo MD-11F) አውሮፕላን ልምድ ያላቸው ኦፕሬተሮች በመባረራቸው፣ አዳዲሶቹ አበባ ለመጫን ሲሞክሩ በቆመበት ቦታ በቂጡ ወድቆ ጉዳት ደርሶበታል፤ ቦይንግ 767 (Boing 767) ከሞተር ጋር በተያያዘ ችግር ሮም ላይ ተገዶ አርፏል (በኋላ በተደረገለት ምርመራም ጥቂት ደቂቃዎች በአየር ላይ ቢቆይ ኖሮ ሊጋይ ይችል እንደነበረ ታውቋል)፤ ፎከር (Foker) አውሮፕላን ሞተሩ ተቃጥሎ ካርቱም ላይ አርፏል (ይህም ጥቂት ደቂቃ ቢዘገይ ኖሮ ተመሳሳይ አደጋ ይደርስበት እንደነበር ተነግሯል)፤ ቦይንግ 767-383 ኢ.አር (Boing 767-383 ER) ታንዛኒያ ውስጥ ማረፍ የነበረበትን ቦታ ስቶ፣ ትናንሽ አውሮፕላኖች የሚያርፉበት አሩሻ አየር ማረፊያ ለማረፍ ባደረገው ሙከራ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዞ ትልቅ የእርሻ ማሳ ውስጥ ሊቀረቀር ችሏል፡፡ እነዚህና መሰል ችግሮች ከኃይለመድህን አበራ እርምጃ ጋር ሲደማመሩ አየር መንገዱ ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ ለመረዳት ያስችላሉ፡፡
በአናቱም የጄኔቫው ክስተት የመሪዎቻችንን ውሸታምነት ከመቼውም በላይ የከፋ ደረጃ መድረሱን አሳይቶ አልፏል፡፡ ይኸውም የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤትን በሚኒስትር ማዕረግ የሚመራው አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ ጠለፋው በተሰማበት ሰዓታት ውስጥ ለሮይተር በሰጠው ቃለ-መጠይቅ ‹‹ድርጊቱን የፈፀሙት ካርቱም ላይ የተሳፈሩ አሸባሪዎች ናቸው›› ከማለቱ ጋር ይያዛል፡፡ ይህ ንግግር እንደቀላል ስህተት መታየት ያለበት አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም መንግስት በሀሰት ንፁሀንን ለማሰር ሲያሴር የሚሰጠው ሰበብ እንዲህ አይነት ፈጠራ መሆኑን ያስረግጥልናልና (ይህንን ጽሑፍ እያዘጋጀሁ ሳለሁ እንኳ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የሰማሁት ዜና ሀገር ውስጥ ያሉ የተወሰኑ የግል ሚዲያዎችን ሁለት ኢምባሲዎች እንደሚያሽከረክሯቸው የሚወነጅል መሆኑ ተጨማሪ ማሳያ ይመስለኛል)፡፡ በርግጥ ስርዓቱ በከረባት ታንቀው የሀሰት ወሬዎችን ሚዲያ ፊት ቀርበው የሚያወሩ ደፋር ሚኒስትሮችን በብዛት መሰብሰቡ እውነት ቢሆንም፣ ከሬደዋን ሁሴን በፊት አቶ በረከት ስምኦን እንዲህ አይነት እጅና እግር የሌላቸውን ነጭ ውሸቶች ራሱ ከመጋፈጥ ይልቅ ብዙ ጊዜ በምክትሉ አቶ ሽመልስ ከማል በኩል ያስነግር እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይሁንና በረከት ቦታውን ለሬድዋን ካስተላለፈ በኋላ በሬድዋንና ሽመልስ መካከል ያለው የፖለቲካ ጉልበት ያን ያህል የሚበላለጥ ባለመሆኑ፣ እንደቀድሞ ሁሉ ሬድዋን፣ በምክትሉ ለመጠቀም አስቸጋሪ እንደሆነበት ሰምቻለሁ (በነገራችን ላይ የአቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝም ‹አለቃ እኔ ነኝ› የሚለው የሰሞኑ መከራከሪያ፣ እነበረከት-ደብረፅዮንን ከጣራ በላይ ሳያስቃቸው የሚቀር አይመስለኝም)
የሆነው ሆኖ ከላይ የተጠቀሱት ክስተቶች ከፍተኛ ደሞዝ የሚከፍል ድርጅት ሰራተኞችንም ያሳተፈ መሆኑን፤ በአምስት መቶ ብር አምስት ቤተሰብ ለማስተዳደር ከሚባትለው ኢትዮጵያዊ ጋር ካጋመድነው ሀገሪቱ ያለችበትን የፖለቲካ ክስረት፣ የኑሮ ውድነት ያነበረው ምሬት፣. አድሎአዊ አስተዳደር፣ መንግስታዊ ሙስና የደረሰበት አስከፊ ገፅታ፣ ተጠያቂነት ያሌለባቸው የፀጥታ ሰራተኞች የሚፈፅሙት ሕገ-ወጥ ተግባር፣ የአጠቃላይ መብት ጭፍለቃ… ተደማምረው መነሻና መድረሻው የታወቀውን የለውጥ ንቅናቄ መቀላቀልን ብቸኛ አማራጭ ያደርገዋል ብዬ አስባለሁ፡፡
የፈራ ይመለስ!
የስርዓቱ ልዝብ ተቃዋሚዎች ቀጣይ የሀገሪቱ ዕድል አብዮት ስለመሆኑ በተነሳ ቁጥር በግርድፍ ትንታኔ ሊነግሩን የሚሞክሩት ‹ኢትዮጵያ በ40 ዓመት ውስጥ ሶስት አብዮት ማስተናገድ አትችልም› የሚል ነው፡፡ ይሁንና ሙግታቸው ሁለት ግድፈቶችን ያዘለ ይመስለኛል፡፡ የመጀመሪያው የብሉይ አብዮትን መሰረታዊ ባህሪ ካለመረዳት ይነሳል፤ ዛሬም ድረስ የ66ቱን አብዮት አስመልክቶ የሚነሳው ተዋስኦ፣ ክስተቱ ብሉይ ማህበራዊ አብዮቶች ከሚባሉት መካከል እንደሚያስመድበው የሚያስረግጥ ነው፡፡ ይህ ስሌትም ብሉይ አብዮቶች ራሳቸውን በተለያዩ የዘመን ወቅቶች የመደጋገም ተጨባጭ ባህሪ እንዳላቸው ያመላክታል፡፡ እናም የሙግቱ ጥራዝ ነጠቅ አቀንቃኞች በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ከሚመደቡት መካከል ሩሲያና ፈረንሳይ በሁለትና ሶስት አብዮቶች ከመናጣቸው አኳያ ‹ኢትዮጵያንስ ምን ያህል የተለየች ሊያደርጋት ይችላል?› ለሚለው ጥያቄ በቂ መልስ የሚኖራቸው አይመስለኝም፡፡ በ66ቱ ከተነሱት ሁለት ዋነኛ (የመሬትና የብሔር) ጥያቄዎች፣ በ83ቱ ማህበረ- ፖለቲካዊ ሽግግርም ተነስተው አለመመለሳቸውን፣ ያሳለፍናቸው ሃያ ሁለት ዓመታት በበቂ ሁኔታ አስረጅ ናቸው፡፡ ይህ እውነታም ነው ሀገሬ ሶስተኛውን አብዮት ከማስተናገድ ውጪ የተሻለ ምርጫ እንዳይኖራት ያስገደደው፡፡
ሁለተኛው ጭብጥ በኢህአዴግ ስር ያዘገመችው ኢትዮጵያ ለአብዮት መነቃቃት የሚያበቁ ስርዓታዊ ክሽፈቶች መኖራቸውን ክዶ ከማለፍ ጋር የሚያያዝ ይሆናል፡፡ ለከተማ አብዮት መፈንዳት ወሳኝ ሆነው ከሚጠቀሱ ጭብጦች ብዙዎቹን የእኛይቷም ምድር እንደምታሟላ ከዚህ በፊትም ለማስታወስ ሞክሬያለሁ፡፡ በተለይም ሥራ-አጥ የተማሩ ከተሜ ወጣቶች አለቅጥ መብዛት እና ወጣቶች ከአጠቃላዩ ሕዝብ ወደ 37% የሚጠጉ መሆናቸውን ከአረቡ ፀደይ መንፈስ አኳያ ስንቃኘው አብዮቱን አይቀሬ ያደርገዋል፡፡ በአናቱም የሁለቱ ኃይማኖት ተከታዮች በመንግስት ላይ የያዙት የቅራኔ ልክ፣ የተቋጠረ የምሬት ፅንስ ስለመኖሩ በድፍረት ለመናገር ያስችላል፡፡ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የሙስሊሙ ጥያቄም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የለዘበ ቢመስልም በሂደት እንደገና መቀስቀሱ አይቀሬ ነው፡፡ ምክንያቱም የእምነቱ ተከታዮች መሰረታዊ ጥያቄ የኃይማኖቱን ሙሉ ነፃነት መከወን ከመሆኑ ላይ ተነስተን፣ የተሰጠው መልስ መዋቅራዊ እንደነበረ ካስተዋልን ‹‹እንቅስቃሴው መለዘብ አለበት›› ያሉ ልሂቃንም ሳይቀሩ የነፃነቱ ጥያቄ በድጋሚ ተነስቶ መጅሊሱን እንዲነቀንቅ መፈለጋቸውን አምነን እንድንቀበል ያስገድደናል፡፡
ሌላው ጉዳይ የኦርቶዶክስ ኃይማኖት ተከታዮች ጉርምርምታ እና ማህበረ ቅዱሳን ላይ በሲኖዶሱ በኩል የሚካሄደው መንግስታዊ ጉንተላ፣ ምን ይዞ እንደሚመጣ ለመገመት የግድ ነገ ላይ መቆምን የማይጠይቅ መሆኑ ነው፡፡ በተጨማሪ ዛሬም5 እየተነሱ ካሉት የማንነት ጥያቄዎች አልፎ፣ በቅርምቱ ከአያቶቻቸው መሬት ከተፈናቀሉ ወጣቶች ምሬት ጋር የኢኮኖሚውን ድቀት አዛምደን ስንመለከት፣ ፍርሃትን አቸንፈው ወደኋላ ላለመመለስ የደፈሩ ወጣቶች ስርዓቱን እንደሚንዱት ለመመልከት ጥቂት ወራትን ብቻ መታገስ ይበቃል፡፡ ‹‹አብዮት የወይን ዘለላ ነው፤ እስኪበስል እንጂ መሬት እስኪወድቅ አትታገሰውም›› እንዲል ቼ ጉቬራ፤ ያረገዘውን አብዮት ከማዋለድ ያለፈ ምርጫ የለም፡፡
በድጋሚ ክብር ለዐድዋ ጀግኖች!!!
“የትግራይ ህዝብ የህወሓት ደጋፊ አይደለም”–አብርሃ ደስታ (ከአዲስ ጉዳይ መጽሔት ጋር ያደረገው ቃለ-ምልልስ)
አዲስ ጉዳይ መጽሄት ቅጽ 8 ቁ. 205/ የካቲት 2006
አዲስ ጉዳይ፡- የህወሓት የ39 ዓመታት ጉዞ በግልህ እንዴት ታየዋለህ?
አብርሃ ደስታ፡- በእኔ አመለካከት የህወሓት ጥረት ከመጀመሪያ አንስቶ ስልጣን ለመያዝ ነው፡፡ አሁንም በስልጣን ለመቆየት ሲሉ ኢኮኖሚውን እየተቆጣጠሩት ነው፡፡ የህዝቡን መረጃ የማግኘት መብት፤ የህዝቡን አስተሳሰብ ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ ነው ያሉት፡፡ ጉዞው ስልጣን የመያዝ እና በስልጣን የመቆየት ጉዳይ ነው።
አዲስ ጉዳይ፡- ፓርቲው ግን ‘‘ለመመስረቴ ምክንያቱ የህዝብ ብሶት ነው’’ ይላል፡፡
አብርሃ ደስታ፡- ይህ ፕሮፓጋንዳ ነው። መጀመሪያ ለትግል ሲነሱ ህዝቡ የስርዓት ለውጥ ፈልጎ ታግሏል። ነገር ግን የህወሓት መሪዎች ስልጣን የመያዝ ዓላማ እንጂ ህዝቡን የስልጣን ባለቤት ማድረግ አልነበረም። በመሆኑም የህዝቡን ብሶት ስልጣን ለመያዝ ተጠቅመውበታል። ከዚህ ውጪ ለእኔ የእነርሱ ደርግን አስወግደው ስልጣን መያዝ የደርግን ሚና ለመጣወት እንጂ ህዝቡን ለመጥቀም አልነበረም።
አዲስ ጉዳይ፡- አንዳንዶች ህወሓት ወደ ኋላ አካባቢ የትግል መስመሩን ስቷል ሲሉ ሌሎች ደግሞ ፓርቲው ከመመስረቱ አንስቶ ዓላማው ስህተት ነበር ይላሉ። የአንተ አስተያየት ምንድነው?
አብርሃ ደስታ፡- እዚህ ላይ እኔ ህወሓትን የማየው በሁለት ከፍዬ መሆኑ ይታወቅልኝ። ስልጣን ፈላጊው የህወሓት አመራር እና ነፃነት ፈላጊው የህወሓት ታጋይ፡፡ ደርግ ገና ስልጣኑን ከያዘ ከወራት በኋላ ወደ ጫካ ገቡ። ስለዚህ የህወሓት አመራሮች ጫካ የገቡት የደርግ መንግስትን ጭካኔ ስላዩ ወይም የደርግን አምባገነንነት ስለተገነዘቡ ነው ለማለት አልደፍርም። ምክንያቱም በጥቂት ወራት ውስጥ ብቻ የህወሓት አመራሮች የደርግን ጨቋኝነት የሚያውቁበት ሁኔታ አለ ማለት በጣም አስቸጋሪ ነው። ዓላማቸው ስልጣን ነበር። ሲነሱም እንደሚታወቀው ትግራይን ለማስገንጠል ነበር፡፡ ይሄም ሆኖ ህወሓቶች ሲንቀሳቀሱ የደርግ መንግስት የወሰደው የኋይል እርምጃ ነበር። ይሄ እርምጃ ግን በጣም በስህተት የተሞላ ሆነ፡፡ ደርግ ጫካ የገቡትን ሰዎች ለማንበርከክ ሲል ህዝቡን በማስፈራራት ብሎም የመግደል እና ሌሎችም እርምጃዎችን ይወስድ ነበር፡፡ ይሄን ተከትሎም ህዝቡ የደርግን ግፍ በመቃወም ተነሳስቷል። ህዝቡ ለትግል በተነሳበት ወቅት ህወሓትን ተቀላቅሏል፡፡ የአብዛኛው የህወሓት ታጋይም ሆነ የትግራይ ህዝብ ዓላማ ከጭቆናና ከግድያ ለመዳን እንጂ ስለ ትግራይም ሆነ ስለ ኤርትራ መገንጠል ምንም የሚያስቡበት ጊዜ አልነበራቸውም፡፡ ይሁን እንጂ ይሄን የኅብረተሰቡን ጭቆና የማስወገድ እንቅስቃሴ ለራሳቸው ፍላጎት አውለውታል፡፡
አዲስ ጉዳይ፡- ኢህኣዴግ የአራት ፓርቲዎች ግንባር ቢሆንም ፍፁም የህወሓት የበላይነት በግንባሩ ነግሷል የሚሉ አሉ። ይህን ሀሳብ እንዴት ታየዋለህ?
አብርሃ ደስታ፡- አብዛኞቹ የኢህኣዴግ አባል ፓርቲዎች የህወሓት ውጤቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ህወሓት እንዲመሰረቱና እንዲደራጁ ያደረጋቸው ናቸው፡፡ በዚህ አምናለሁ፡፡ ይህንን ሃሳብም እቀበለዋለሁ፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይ አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ጉዳይ ህወሓት ራሱ የጥቂት ግለሰቦች ስብስብ መሆኑ ነው።
አዲስ ጉዳይ፡- ይህንን ሃሳብ ዘርዘር አድርገህ ብታብራራው?
አብርሃ ደስታ፡- በትግሉ ወቅት በጊዜው በነበረው ጨቋኝ ስርዓት የተነሳ ህዝቡ ሌላ የተሻለ አማራጭ ስላልነበረው ህወሓትን ደግፏል፡፡ ይሁን እንጂ ህወሓት ስልጣን ከያዘ በኋላ በሺኅ የሚቆጠሩ ታጋዮችን ሆን ተብሎ እንዲባረሩ ተደርገዋል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ገና ፓርቲው ስልጣን እንደያዘ የአመራሩ ተነኮሎች ግልፅ እየሆኑ ሲመጡ የህወሓት ታጋዮች መቃወም በመጀመራቸው ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ነው ህወሓት የተወሰኑ ግለሰቦች ስብስብ መሆኑ መረሳት የለበትም የምለው፡፡
አዲስ ጉዳይ፡- አንድ ወቅት ህወሓት በትግራይ የሚከተለው የፖለቲካ ስልት ‘‘እኔ ከሌለሁ ደርግ ይመጣባችኋል’’ ዓይነት መሆኑን ተናግረህ ነበር።
አብርሃ ደስታ፡- አዎ! ይሄ እውነት ነው፡፡ እንደውም ዋናው የህወሃት የትግራይ የፕሮፓጋንዳ መሳሪያው እኔ ከሌለሁ ሌሎች መጥተው ይበሉሃል የሚሉት ሃሳቦች ናቸው፡፡ በእርግጥ የደርግ ስርዓት እንዳይመለስ መፈራረሱ የታወቀ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይሄ ፕሮፖጋንዳ እየሰራ አይደለም። በትግራይ ውስጥ ብዙ ተቃውሞ አለ። በእርግጥ ይሄ ‘‘ደርግ መጣ’’ የሚለው ቃል የትግራይን ህዝብ ማስደንገጡ አይቀርም። በጊዜው ብዙ ስቃይና ግድያ ያየ ህዝብ ስለሆነ ማለቴ ነው፡፡ ስለዚህ ይደነግጥና ‘‘ከደርግማ ህወሓት ይሻለናል’’ ይላል፡፡ ይሁን እንጂ ደርግ ሊመለስ እንደማይችል ከዚህ በኋላ በጥቅሉ ወደ ወታደራዊ ስርዓት ልንመለስ እንደማንችል ለህዝቡ በማስረዳት ለውጥ የምናመጣበትን መንገድ እናመቻቻለን የሚል ዕምነት ነው ያለኝ፡፡ ይሄ ፕሮፖጋንዳም ካሁን በኋላ አይሰራም።
አዲስ ጉዳይ፡- ይህን የምትልበት ምክንያትህ ምንድነው?
አብርሃ ደስታ፡- ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ህዝቡ ደርግ ሊመለስ እንደማይችል በሚገባ እያመነ መምጣቱ ነው። እኛም በዚህ ላይ በስፋት እንሰራበታለን። ህዝቡም ዲሞክራሲያዊ አሰራር እና ዲሞክራሲያዊ መንግስት እንደሚያስፈልገው እየተረዳ ነው። ይሁን እንጂ የህዝቡ ግንዛቤ እያደገ በመጣ ቁጥር የህወሓት አፈናም በዚያው መጠን እያደገ መምጣቱ አይቀርም። በዚህ የተነሳም ህዝብ እየታፈነ ነው። የመሰብሰብ፤ የመደራጀትና የመናገር ዲሞክራሲያዊ መብቶቹን አሁን እየተነጠቀ ነው። በዚህ ላይ ተገቢውን መልካም አስተዳደር እያገኘ አይደለም። በዚህ የተነሳም ህወሓት ደርግ ይመጣል ብሎ ለሚነዛው ፕሮፖጋንዳ የትግራይ ህዝብም ‘‘እናንተም እኮ ሌላው ደርግ ናችሁ’’ እያለ ነው። ‘‘ደርግም የሚደበድበንና የሚገድለን ስንናገር መብታችንን ለማስከበር ስንሞክር እንጂ እናንተም ማፈኑንና መግደሉን ጀምራችኋል። እናንተ እራሳችሁ እያፈናችሁ በመሆኑ ደርግ መጣ አትበሉን፡፡ እናንተ እራሳችሁ እንደ ደርግ እየሆናችሁ ነው’’ በማለት ህዝቡ ግልፅ መልዕክት አስተላልፏል። በዚህ የተነሳ ይህ ደርግ ይመጣባችኋል የሚለው ፕሮፖጋንዳ የሚሰራ አልሆነም።
አዲስ ጉዳይ፡- ብዙዎች በትግራይ የህወሓት ደጋፊ እንጂ ተቃዋሚ አለ ብለው አያምኑም። አንተ ደግሞ ተቃውሞ አለ እያልክ ነው . . . .
አብርሃ ደስታ፡- አዎ! በትግራይ ተቃውሞ አለ ብዬ ለእነዚህ ሰዎች ላረጋግጥላቸው እፈልጋለሁ። እንደውም በሙሉ ነፃነት ህዝቡ ምርጫ ማድረግ ቢፈቀድለት ህወሓት በትግራይ ይመረጣል የሚል እምነት የለኝም። ለምን ብትል እኛ በተለያዩ ቦታዎች ተዟዙረን ህዝቡን በደንብ አናግረናል። በሄድንበት የትግራይ አካባቢ በሙሉ ግን ተቃዋሚ አለ። ህዝቡ እኛን እንደሚደግፍ እየገለፀልን ነው። ነገር ግን ህዝቡ የሚጠራጠረው ‘እኛ ሰው እንፈልጋለን ነገር ግን ህወሓት በምርጫ ቢሸነፍ ስልጣን ያስረክባል የሚል ግምት የለንም። እናንተን ሆነ ሌሎች ተቃዋሚዎችን ያፍናል። ከዚህ በባሰ መልኩም ሊያጠፋችሁ ይችላል። በተለይ ለዲሞክራሲያዊ አሰራር ዕድል መሆኑን ስለምናውቅ በዚህ መንገድ ለውጥ ለመምጣቱ እርግጠኞች አይደለንም’ እያሉ ነው ያሉት። ስለዚህ እኔ ከዚህ ሃሳብ የወሰድኩት ከሌሎች ግምት በተቃራኒው አፈናው በትግራይ የባሰ መሆኑን ለማሳየት ነው። ይብዛም ይነስ በሌሎች አካባቢዎች እኮ ሰላማዊ ሰልፍ እየተፈቀደ ነው። በትግራይ ግን ሰላማዊ ሰልፍም ሆነ መሰብሰብ እንኳን እየተከለከለ ነው።
አዲስ ጉዳይ፡- አፈናው ባይበዛ በትግራይ ተቃዋሚዎች በብዛት ይኖሩ ነበር ብለህ ታስባለህ?
አብርሃ ደስታ፡- በየትኛውም የትግራይ አካባቢ ከተወሰኑ ካድሬዎች በቀር ህወሓትን የሚደግፍ የለም። ጥቂት ደጋፊዎችን ፖሊስንና መከላከያውን ይዞ ነው ህዝቡን በዘዴ የሚያቀናው እንጂ እንደ ህዝብ የትግራይ ህዝብ የህወሓት ደጋፊ ነው የሚለው ለእኔ አሁን የማይሰራ ሃሳብ ነው።
አዲስ ጉዳይ፡- መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመደመር ህወሓት/ኢህኣዴግ እስከ 40 ዓመት በስልጣን መቆየት እንዳለበት እየተናገረ ነው።
አብርሃ ደስታ፡- ህወሓት ገና 50 ዓመት ይገዛል የሚለውን ነገር በትግራይ አዘውትረው በአደባባይ የሚናገሩት ነው። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን እንዲህ ያለው አቋም የተሳሳተ ነው። በእርግጥ የእነርሱ ኋይማኖት በስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችላቸውን ነገር ብቻ ማድረግ ነው። ልማት ያለ ዲሞክራሲ አይመጣም። ልማትን የሚያመጣው መንግስት ብቻ ሳይሆን ህዝቡ ነው። ህዝቡ የልማቱ አምጪ እስከሆነ ድረስ በሙሉ ነፃነት ህዝቡ መስራት፤ በማንኛውም ቦታ በእኩልነት የመታየት መብቱ መከበርና ሰው በስራው እንጂ በሌላ አመለካከት መገምገሙ መቆም አለበት። ይሄ ነገር እስካልመጣ ድረስ ዘላቂ ልማት አይኖርም።አሁን ባለው ሁኔታ እንኳን ለውጥ ሊመጣ ቀርቶ ለውጡ እንዳለ እንኳን ለመቆየት የሚችል አይደለም፡፡
አዲስ ጉዳይ፡- ህወሓትን ለረጅም ዓመታት ከመግዘት የሚያግደው ምንድን ነው?
አብርሃ ደስታ፡- ህወሓት በከፍተኛ ደረጃ በሙስና የበሰበሰ ነው። እንኳን በውጪው ህዝብ ይቅርና በራሱ ውስጥ እንኳን በጣም ብዙ ቅሬታዎች አሉ። በዚህ መሰረት ህወሓት ጊዜ ቢሰጠውም ለውጥ ሊያመጣ የሚችል አይደለም። ምክንያቱም ሙስናና አድልዎ በቡድኑ ውስጥ ተበራክቷል። በህዝቡም ያለው ተቀባይነት ዝቅ በማለቱ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ እየቀነሰ ነው።
አዲስ ጉዳይ፡- የተለያዩ ሰዎች በህወሓት የተነሳ የትግራይ ህዝብ በሃብት ክፍፍሉ የተለየ ተጠቃሚ እንደሆነ ያምናሉ።
አብርሃ ደስታ፡- ምን አለ መሰለህ። በእርግጥ በህወሓት የስልጣን ዘመን እየበለፀጉ ያሉ ግለሰቦች አሉ። ነገር ግን እነዚህ የበለፀጉ ግለሰቦች ለባለስልጣነቱ የቅርብ የስጋ ዝምድና ያላቸው ናቸው። ወይም ራሳቸው ባለስልጣናቱ ናቸው። በመሆኑም በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች እነዚህ ትግርኛ ተናጋሪዎች ፎቅ ሲገነቡ ወይም የተለያዩ ቢዝነሶችን ሲሰሩ እያዩ የትግራይ ተወላጆች ሃብታም እየሆኑ ነው ብለው ቢናገሩ አይፈረድባቸውም። ምክንያቱም እነማን መሆናቸውን አያውቁም። ከዚህ ውጪ አብዛኛው የትግራይ ህዝብ በድህነት ውስጥ ስለመኖሩም መረጃ ላይኖራቸው ይችላል። ስለዚህ አብዛኛው የትግራይ ህዝብ በድኅነት እየኖረ የባለስልጣናት ዘመዶች ሃብት እየሰበሰቡ መሆናቸውን በደንብ የምናውቀው እኛ የትግራይ ሰዎች ነን። በሌላ ቦታ በአማራ፣ በኦሮሚያም ሆነ በሌላው ክልል ሃብት የሚሰበሰብ ትግርኛ ተናጋሪ ብታይ አንተም የትግራይ ሰው ሃብት እያካበተ ነው የሚል ሃሳብ ልታዳብር ትችላለህ። በመሆኑም የሌላው ክልል ነዋሪ እንዲህ በማለቱ ሊፈረድበት አይገባም። ጉዳዩን በሚገባ ማስረዳት የሚኖርብንም እኛው የትግራይ ህዝቦች ነን። ባለስልጣናቱና ዘመዶቻቸው ከህዝብ የተሰጣቸውን ሃላፊነት አላግባብ በመጠቀም ሃብት እየሰበሰቡ መሆናቸውን ማጋለጥ ያለብን እኛው የትግራይ ሰዎች ነን።
አዲስ ጉዳይ፡- ህወሓት በኢኮኖሚው ላይ በበርካታ ድርጅቶች መሳተፉ፣ የደህንነት ኃይሉን መጠቀሙና ነፃ ሚዲያውንም ማዳከሙ ለሰላማዊ ትግሉ ተስፋ አስቆራጭ ነው የሚል ሃሳብ ይነሳል . . .
አብርሃ ደስታ፡- እውነት ነው። እንደተባለው ህወሓት ኢኮኖሚውን በስፋት መቆጣጠሩ ሚዲያውንም መቆጣጠሩ ወይም የግል ሚዲያውን አለመፈለጉ፤ በሰላማዊ ትግሉ ላይ እንቅፋት ይፈጥራል። ነገር ግን እንቅፋት ስለሚፈጥር፤ መንግስት አፋኝ በመሆኑ እና ለሰላማዊ ትግሉ በሩን በመዝጋቱ የተነሳ ተቃውሞ እንዳስፈለገ መታወቅ አለበት። እኛም እየተቃወምን ያለነው ይህንኑ አካሄድ ነው። እኛ እንደምናምነው ሚዲያውን ስለተቆጣጠረ፣ ህዝቡን ስላፈነ የሰላማዊ ትግል መንገድ ችግር ሊያደርስበት ይችላል እንጂ ሊያስቆመው አይችልም። ህዝቡ ለውጥ እስከፈለገ ድረስ መንግስት የፈለገውን አፈና ቢያካሂድ አስፈላጊን መስዋዕትነት በመክፈል ህዝቡን እያደራጀንና እያስተማርን ለውጥ ማምጣት ይቻለናል የሚል እምነት ነው ያለኝ።
አዲስ ጉዳይ፡- የህወሓት ምስረታ ሲታሰብ የተለያዩ መስዋዕትነት የከፈሉ ታጋዮች ስማቸው አብሮ ይነሳል። አንተ በግልህ መስዋዕት የሆኑት ታጋዮች ዓላማ ዳር ደርሷል ትላለህ?
አብርሃ ደስታ፡- ይሄ ነገር ሲነሳ ጉዳዩን በጥንቃቄ በሁለት ከፍለን ማየት ይኖርብናል። የመሪዎቹ ዓላማ ስልጣን መያዝ ነበረ ብዬ ነው የማምነው። የእኛ ወላጆች ዓላማ ግን ነፃነት ነበር። ስለዚህ ለእኔ የትግሉ ዓላማ አልተሳካም ባይ ነኝ። ምክንያቱ ደግሞ የታጋዮቹ ዓላማ ለሰው ነፃነትን ማምጣት ነበር። አሁን ግን ነፃነት የለም። አፈና ነው ያለው። ስለዚህ የታጋይ ወላጆቻችን ዓላማ ህዝቡን ለማፈን እስካልነበረ ድረስ ዓላማው አልተሳካም የሚል እምነት ነው ያለኝ።
አዲስ ጉዳይ፡- የትግራይ ህዝብ እና የህወሓት መሪዎች በኤርትራ መገንጠልም ሆነ በኢትዮጵያዊ ህብረብሄራዊ ስሜት የተለያየ አቋም ያላቸው መሆኑ ይነገራል። እውነት ነው?
አብርሃ ደስታ፡- አዎ! የህወሓት መሪዎች ዓላማ ኤርትራን ማስገንጠልን የሚጨምር ነበር። ይሄን አቋማቸውን ደግሞ የተለያዩ ዶክመንቶች ጭምር ይመሰክሩታል። ህዝቡም ሆነ ታጋዮቹ ግን የኤርትራን መገንጠል የሚደግፉ አልነበሩም። ይሄን የህወሓት ኤርትራን ማስገንጠል ዓላማ የማይደግፉ ታጋዮች ሲገኙ ይቀጡ እና ይባረሩ ነበር። በተለይ ለኤርትራ ህዝብ ባርነት ወይስ ነፃነት የሚል ሪፈረንደም ሲቀርብ ብዙ ታጋዮች ተቃውመውታል። ይህ የህወሓት አመራር ድጋፍ ያለውን ሃሳብ በመቃወማቸው፤ የአሰብ ወደብ ጉዳይንና የዲሞክራሲ ጥያቄን በማንሳታቸው ባንድ ጊዜ ወደ 32 ሺኅ የሚጠጉ ታጋዮች ከህወሓት ተባረዋል። ከእነዚህ ውስጥ የታሰሩም የተገደሉም አሉ።
አዲስ ጉዳይ፡- ህወሓት የኢትዮጵያን የባህር በር አስነጥቋል ብለህ ታምናለህ?
አብርሃ ደስታ፡- አዎ! በትክክል አስነጥቋል ነው የምለው። ህወሓት ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታጣ ምክንያት ሆኗል።
አዲስ ጉዳይ፡- የህወሓት አመራሮች የአማራ ህዝብን ከገዢው መደብ ጋር ደብሎ በመሳል የብሄር ጥላቻ እንዲከሰት አድርገዋል ተብለው ይተቻሉ። አንተ ምን ትላለህ?
አብርሃ ደስታ፡- የህወሓት አመራሮች የአማራ ህዝብን ከገዢው መደብ ጋር አንድ አለመሆኑን ያውቃሉ። ነገር ግን ሆን ብለው ህዝቡንና ገዢ መደብን አንድ አድርገው የሚያቀርቡት ደግሞ ህዝቡ ተባብሮ በአንድ ላይ መቆም ከቻለ ለስልጣናቸው ስለሚያሰጋቸው ጭምር ነው። ይህ ዓይነቱ አቋም ደግሞ ከድሮም ጀምሮ የሚያራምዱት ነው። እኛ ልጆች ሆነን የሚነገረን ደርግ ማለት አማራ ማለት ነው ተብሎ ነበር። አማራ ማለት ደግሞ ደርግ ነው። በመሆኑም አማራ ገዢና ጨቋኝ ነው የሚሉ ነገሮች ናቸው። እስካሁን ድረስ ፀረ አማራ የሆኑ ዘፈኖች አሉ። ምክንያቱም ፀረ አማራ ማለት ፀረ ደርግ እንደማለት ስለነበር ነው። ይህ አስተሳሰብ የከፋፍለህ ግዛ ስትራቴጂ እንጂ የትግራይ ህዝብ በሙሉ ህወሓት አለመሆኑ እንደሚታወቅ ሁሉ የደርግ ስርዓት እና የአማራው ህዝብ አንድ አለመሆናቸው ይታወቃል። እነርሱ ግን ይሄን ይጠቀሙበታል፣ ከስልጣን በላይ የሚያስቡት ነገር ስለሌለ ማለቴ ነው።
አዲስ ጉዳይ፡- ያለህበት አረና ፓርቲ በትግራይ ውጤታማ የሚሆን ይመስልሃል?
አብርሃ ደስታ፡- በእርግጥ ብዙ አፈናዎች እየተካሄዱ ነው። ህዝቡን ለማወያየት ስንሞክር ስብሰባ እየተሰረዘብን፤ ከዚያም አልፎ ድብደባ እየደረሰብን ነው። ይሁን እንጂ የትግራይ ህዝብ ለውጥ እንደሚፈልግ ለእኛ ተስፋ ስጥቶናል። በመሆኑም እኛ ውጤታማ እንሆናለን ብዬ ነው የማስበው።
አዲስ ጉዳይ፡- አቶ ስብሃት ነጋ ‘‘አረናዎች የተቆጡ ህወሓቶች ናቸው’’ የሚል ሃሳብ ሰንዝረዋል። በእርግጥ አረና ህወሓት ነው?
አብርሃ ደስታ፡- አረናን እንደ ፓርቲ ከህወሓት ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም። ነገር ግን ጥቂት የቀድሞ የህወሓት ሰዎች ወደ አረና ስለገቡ በቂም ተበሳጭተው ነው በሚል ነገር ያነሳሉ። እነዚህ ሰዎች በእርግጥ ህወሓት ነበሩ። ነገር ግን ህወሓት ችግር እንዳለበት ሲረዱ ከፓርቲው በመውጣት አረና የተሻለ አካሄድ እንዳለው ሲረዱ የእኛን ፓርቲ ተቀላቀሉ። ከዚህ ውጪ ከፖለቲካ ርዕዮተ ዓለምም ሆነ ከአሰራር አንፃር በዓረናና ህወሓት መካከል ብዙ ልዩነቶች አሉ።
አዲስ ጉዳይ፡- ልዩነታችሁን በምሳሌ ልታስደግፍ ትችላለህ?
አብርሃ ደስታ፡- ለምሳሌ በእኛ ፓርቲ ውስጥ ማዕከላዊ ዲሞክራሲያዊነት ብሎ ነገር የለም። ሌሎች አካሄዶቻችንም በስፋት ከህወሓት የሚለዩ ናቸው። እነርሱ ወደ ኃይል እርምጃ የገቡት እኮ ለህዝቡ የእኛን አቅጣጫ በዝርዝር ስናስቀምጥ ጎልቶ በወጣው ልዩነት የተነሳ ነው። ስለዚህ ህወሓት ለስልጣን የሚቀናቀነውን ማንኛውንም ፓርቲ ማጥላላት ልማዱ ነው። ይህንን እኛም ስለምናውቀው ከህወሓቶች ለሚሰነዘር አስተያየት እኛ ያን ያህልም የምንጨነቅበት ጉዳይ አይሆንም።
አዲስ ጉዳይ፡- ህወሃት በትግራይ ወይም ኢህአዴግ በኢትዮጵያ በምርጫ ስልጣን የሚለቅ ይመስልሃል?
አብርሃ ደስታ፡- ህዝቡን መቀየር ከቻልንና ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብለን ህዝቡን ካስተባበርን በምርጫ ፓርቲው ስልጣን ሊለቅ ይችላል። በእርግጥ ፓርቲው በምርጫ ስልጣን ለመልቀቅ ፍቃደኛ አይደለም። የፈለገውን ያህል ኀይል ተጠቅሞ ህወሓት በስልጣን ላይ ለመቆየት እንደሚፈልግ ይታወቃል። ነገር ግን በምርጫ ተቀጥቶ ስልጣን እንዲለቅ ማስገደድ ይቻላል። ምርጫውን የሚሰርቅበት መዋቅሩን በማሳጣት ለህዝብ ድምፅ የሚንበረከክበት ዕድል አሁንም አለ።
አስተያየት፣ በሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስ “እኛና አብዮቱ” መጽሀፍ ላይ
ከፈቃደ ሸዋቀና
የሻምበል ፍቅረ ስላሴን ባለ 440 ገጽ መጽሐፍ ላነብ ስነሳ ጸሐፊው በሃያ ዓመታት የእስር ቤት ቆይታቸው በስልጣንና የሃላፊነት ዘመናቸው የነበሩትን ብዙ ክንዋኔዎች ፣ ውሳኔዎችና ተዋናዮችን አስመልክቶ የነበራቸውን እይታ እንደገና ለማጤንና ለማሰላሰል እድል አግኝተው የጻፉት ሊሆን ስለሚችል ሚዛናዊ የሆነ ዕውቀት፤ እንዲሁም የመንግስታቸውን የውስጥ ለውስጥ ሥራዎች ከሩቅ እናይ የነበርን ተራ ዜጎች ሳናውቃቸው የቀሩ ነግሮችን የምናገኝበት ይሆናል የሚል ጉጉት ነበረኝ። በተጨማሪም በመግቢያው ሊተርኩልን ቃል የገቡትን የደርግን የግዛት ዘመን ዋና ዋና ቁም ነገሮችና ክንዋኔዎች እንደወረደ አቅርበውልን አንባቢዎች የሁሉንም ነገር ፋይዳ የራሳችንን ሚዛን ተጠቅመን እንድንረዳው ይተውልናል ብዬ አስቤም ነበር። ይህ ከንቱ ምኞት መሆኑን ወደ ገጾቹ ውስጥ ርቄ ሳልሄድ ነው ያረጋገጥኩት። በሁሉም የደርግ የግዛት ዘመን ክንዋኔዎችና የፖለቲካ ተዋናዮች ላይ የራሳቸውን ዳኝነቶች አመለካክቶችና ግለ-አይታዎች (bias) ጨምረውበታል።
ሻምበል ፍቅረ ስላሴ ከእስር በወጡ ባጭር ጊዜ ውስጥ ጊዜያቸውን ወስደው ይህን መጽሀፍ በመጻፋቸው ሊመሰገኑ ይገባል። ወደፊትም ሌሎች መጽሐፎች እንደሚጽፉ ቃል ገብተዋል። የሚቀጥሉት ላይ በበለጠ የሃላፊነት ስሜት እንዲጽፉ ለማሰቢያ የሚረዳ ነገር ካስተያየቴ ሊያገኙ ይችላሉ የሚል ግምት አለኝ። እውነት በመናገርና በሀቅ በመመስከር ከሚገኘው ብዙ ጥቅም ውስጥ አንዱ ለተናጋሪው የህሊና ፈውስ የሚያስገኝ መሆኑ ነው። ለሻምበል ፍቅረስላሴና ለቤተሰባቸው መልካሙን ነገር ሁሉ እመኝላቸዋለሁ። መጽሀፋቸው ላይ በማቀርበው አስተያየት ላይ ግን ርህራሄ የለኝም። የምንሟገትበት ጉዳይና ታሪክ ከያንዳንዳችን ስብዕና በላይ ስለሆነ።
የዚህን ጽሁፍ ርዕስ ግምገማ (Review) ከማለት ይልቅ አስተያየት(Observation) ያልኩት እውቄ ነው። መጽሀፉ እንደመጽሀፍ የሚገመገም ባህርይ የለውም። ብዙው የደራሲው ነጻ እይታ ዘገባ ነው። ትልልቅ ድምዳሜዎች ላይ የደረሱባቸውን ነጥቦችና በፖለቲካ ባላንጦቻቸው ላይ የሚያቀርቡትን ክስ ተዓማኒ የሚያደርግ ወይም የሚያረጋግጥ ወይም ደርግን ከክስ የሚያነፁበት ማስረጃ የሚሆን የግረጌ ማስታወሻም (Footnote) የዋቢ ዝርዘርም (Reference list) የለበትም። መጽሀፉ ባቀራረቡ ከሞላ ጎደል የደርግ በተለይም የኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም ገድል ነው። ለበርካታ ደርግ ላይ ለሚቀርቡ ወንጀሎችና ጥፋቶች ሁሉ የተገቢነት ማረጋግጫ (justification) ለመስጠት ደራሲው ሙከራ ሲያደርጉ ይታያል። ስለዚህ ግምገማ የሚገባው መጽሀፍ ነው ማለት ለመጽሀፉ የማይገባውን ነገር ማድረግ መስሎ ታይኝ። ማድረግ የሞከርኩት ፈጣን ወፍ በረር ቅኝት ብቻ ነው። ምሳሌ የሚሆኑ ነገሮችን አሳይቼ ብዙውን ነገር ትቼዋለሁ።
በደርግ የግዛት ዘመን ከደረሰው የጥፋት ከምር ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ሀይሎችና ተራ ዜጎች የሚወስዱት የተለያየ መጠን ያለው ድርሻ እንዳለ ብዙ የሚያከራክር አይመስለኝም። ከዚህ የጥፋት ከምር ላይ እያንዳንዱ የደርግ አባልና በተለይ በከፍተኛ ሀላፊነት ላይ የነበሩ ደራሲውን የመሰሉ መሪዎች የሚያነሱት ትልቅ ድርሻ አለ። በሚያሳዝን ሁኔታ ሻምበል ፍቅረስላሴ ለይሉኝታ ያህል ብለው እንኳን በግልም ይሁን በጋራ ምንም ሀላፊነት አይወስዱም። የመንግስታቸውን ጥፋት ሁሉ በሌላ ያመካኛሉ። ኢህአፓን አጥብቆ በመወንጀል የደርግን ለመሸፈን ይቻላል በሚል ሀሳብ ይመስላል ኢህአፓ ገደላቸው የሚሏቸውን 271 ሰዎች ዝርዝር ከምጽሀፉ 21 ገጾች ሰጥተው አስፍረዋል። (ከገጽ 275 – 296). ዝርዝሩ ደርግ ራሱ እየገደለ ኢህአፓ ገደላቸው የሚባሉ ሰዎች ስም ሁሉ ይዟል። ለምሳሌ ዶክተር መኮንን ጆቴን የገደላቸው ራሱ ደርግ መሆኑን እንደሚያምኑ የመኢሶን አባላት የነበሩ ጓደኞቼ ነግረውኛል። በአጸፋው ኢህአፓ ብለው የፈጁትን ሰው ዝርዝር ይቅርና ጠቅላላ ቁጥር እንኩዋን ሊነግሩን ፈቃደኛ አይደሉም። ተራ ተመልካች ካለችግር የተረዳውንና ብሎ ብሎ የጨረሰውን የኮሎኔል መንግስቱንና የደርግ መንግስት ጥፋቶችና ሀገርን አደጋ ላይ የጣለ ግትርና እምባገነናዊ አመራር በጨረፍታ እንኩዋን ለመተቸት አለመሞከራቸው ወይ ቀጥተኛ ክህደት ፣ ወይም የውሻ አይነት ቅድመ-ሁኔታ አልባ ታማኝነት ፣ ከዚህ ከዘለለ ደግሞ “በምኒልክ ጊዜ የደነቆረ ምኒልክ ይሙት እንዳለ ይኖራል” የሚባለው አይነት ነገር አስመስሎባቸዋል።
በመከረኛይቱ ሀገራችን ላይ ብዙ መታከም የሚገባው ትልልቅ ቁስል አለ። የሚሻለው ወደማከሙ መዞር እንጂ ቁስሉ ላይ ጨው መነስነስ አይደለም። ሻምበል በመጽሀፋቸው ብዙ ቦታ ይህንን ጨው ቁስላችን ላይ ካለሀሳብ ነስንሰውታል። በህይወት የሌሉና ሊከራከሯቸው የማይችሉ ሰዎችን ሳይቀር በስልጣን ዘመናቸው ጊዜ እንደሚደረገው አሁንም በመደዳው ይወነጅሏቸዋል። ይህ አጻጻፍ በውድቀታቸው ላገኛቸው ለራሳቸው ቁስል ፈውስ ይሆነኛል ብለው አስበው ከሆነም ተሳስተዋል። ንጹህ ራስን እንደገና ማግኘት (redemption) የሚቻለው ለዕውነት ክብር በመስጠት ብቻ መሆኑን የተረዱት አልመሰለኝም። ዛሬ የሚገዙንን ገዥዎች እካሄድና አገዛዝ ስለጠላን የደርግን ዘመን ግፍ እንዳለ የረሳነው መስሏቸው ከሆነም በጀጉ ተሳስተዋል። የወጋ እንጂ የተወጋ አይረሳም። ደጉ፣ ቸሩና አስተዋዩ የአትዮጵያ ህዝብ በወደቀ እንጨት ምሳር ማብዛት አይገባም ብሎ ስለተወውና እነሻምበል ፍቅረስላሴ ትተውለት በሄዱት ምስቅልቀል ላይ በመጠመዱ እንጂ የደረሰበትን ግፍ ረስቷል ማለት አይደለም። ወዳጅ ዘመድ በግፍ የሞተበት ፣ ጧሪ ልጃቸውን ያጡ እናት አባቶች ፣ ቤቱ የፈረሰበት ቤተሰብ ፣ ከነጠባሳው የሚኖር ዜጋ፣ ከገበያ ላይ ሳይቀር ካለፈቃዱ ታፍሶ ጦር ሜዳ የተማገደው ማገዶ ትራፊ አሁንም አለ እኮ!
በመጽሀፉ ላይ የምሰጠው አስተያየት ርሳቸው የሚወነጅሏቸውን ድርጀቶች ወይም ሰለባዎች ወይም ግለሰቦች ወክዬ ለመሟገት አይደለም። ከሻምበል ፍቅረስላሴ መጽሀፍ ጋር ያጣላኝ አንዳንዱ ነገር በቅርብ በምናውቀው ታሪክ ላይ ያሳዩት ይሉኝታ የሌለው አጻጻፋቸው ነው። በጊዜው ያልተወለደውና ለዕውቀት ያልደረሰው ትውልድ የተሳሳት ግንዛቤ እንዲወስድ ሲጋበዝ ዝም ብሎ ማየትም ተገቢ አልመሰለኝም። ስለዚህ በዚህ መጽሀፍ ላይ የምሰጠው አስተያየት ጨከን ያለ መስሎ ታይቷችሁ ከሆነ ከዚህ አቅጣጫ እዩልኝ። ሌላ የግል ወይም የቡድን ሂሳብ የማወራርደው የለኝም። የኛ ሀገር ሰው እንደሚለው ከጅብ የሚያጣላ ጓሮዬ ያሰርኩት አህያ የለኝም።
እኔ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት ተፈንቅሎ ደርግ ስልጣን ሲወስድ 19 ሊሞላኝ ጥቂት ወራት የቀሩትኝ የአዲስ አበባ ዩኒቭርሲቲ የሁለተኛ አመት ተማሪ ነበርኩ። በደርግ ዘመን ለነበረው ሁሉ እንግዳ አይደለሁም ማለት ነው። እንደብዙ ወጣቶች ኢህአፓ አካባቢ ልሳተፍ እንጂ ያደረኩት ተሳትፎ ብዙ አልነበረም። ካስተዳደጌ ይሁን ከሌላ በልጅነቴ ጀምሮ አንዳንድ ገዜ አስተማሪና ጉዋደኛ እስቲጠላብኝ ድረስ ጨቅጫቃ ተማሪ ነበርኩ። አንድ ነገር እስኪገባኝ ድረስ ሰው አስቸግር ነበር። በ1968 ዓም መጀመሪያ ኣካባቢ አንድ የኢህአፓ የጥናት ክበብ ላይ ስሳተፍ ደርግ የወዛደሩ ፣ ኢህአፓ ደግሞ የላብ አደሩ እምባገነንነትን እናሰፍናለን በሚሉት ነገር ላይ ችግር ነበረብኝ። ለካርል ማርክስ ጭንቅላት እስከዛሬ ድረስ ትልቅ አድናቆት ቢኖረኝም የሶሻሊዝም ሳይንስነትም አይገባኝም ነበር። የጥናት ቀጠሯችን ዕለት በኢትዮጵያ ያለውን የላባደር ቁጥር ፈልጌ ጠቅላላ ከ45ሺ እንደማይበልጥ አረጋግጬ መጣሁ። አዲስ አበባና አቃቂ አካባቢ ያለው ብቻ 20 ሺ አይሞላም ነበር። 35 ሚሊዮን ህዝብ ባለበት አገር ላይ ሀምሳ ሺ ለማይሞላ ሰው ሺ ጊዜ ተበዝባዥ ሲሆን ቢውል አምባገነን እንዲሆን የምንታገልበት ምክንያት እልገባ ብሎ አስጨንቆኝ ነበር። ይህን ነገር ሳነሳ ሰብሳቢያችን የነበረው ልጅ ሳቀብኝ። ከማርክስ እየጠቀስ ሊያስርዳኝ ሲሞክር ይበልጥ አዞረብኝ። ማርክስ የሚያወራው አይነት ላባደርማ ጭራሹኑ እዚህ አገር የለም ብዬ ድርቅ እልኩ። የኛ አገር ላባደር ማርክስ እንደሚናገርለት እንዳውሮፓው ሳይሆን እንዴውም የተፈናቀለ (depeasantised) ገበሬ ነው ብዬ ተከራከርኩ። ሰብሳቢያችን ስደብ አዘል ሽሙጥ አሽሟጠጠኝና ተጣላን። ከዚያ ሴል ውስጥም ወጣሁ። እዚያ ሴል ውስጥ አብረውኝ የነበሩ ልጆች የነበራቸውን የህዝብና ሀገር ፍቅር በፍጹም አልጠረጥርም። እኔ የህዝብና ያገር ፍቅራቸውን እንደሆን እንጂ በጀግንነትና በመስዋዕትነት ስሜት አልወዳደራቸውም። እነሱ ለህዝብ ሲሉ ለመግደልም ሆነ ለመሞት ዝግጁ ነበሩ። እኔ የሚያገዳድል ነገር ባለበት አካባቢ መገኘት አልወድም። ሰው የሚገድል ሰው ምን አይነት ህሊና እንዳለው እስከዛሬ አይገባኝም። ሁሉም ማለት ይቻላል በኋላ አልቀው ተገደሉ። ብዙ ሊሞቱ የማይገባቸውና በህይወት ቢኖሩ ትላልቅ ሳይንቲስት የሚወጣቸው የቅርብ ጉዋደኞቼ በደርግ ተገለዋል። እኔ ቀጭኑን የቀይ ሽብር ዘመን አስተማሪ ሆኜ ገጠር ውስጥ አለፍኩት። መጨረሻ ላይ የቀይ ሽብሩ ዶፍ ሊያባራ አካባቢ ያበዱ ካድሬዎችና ባለስልጣኖች ርዝራዥ ኢህአፓ ብለው እኔንና ጥቂት ጉዋደኞቼን ሊበሉን የምኖርበት ወረዳ አብዮት ኮሚቴ ውስጥ መዶለታቸውን ሰማሁ። አምልጬ ባንድ ትልቅም ባይሆን ጠቃሚ ስልጣን በነበረው አጎቴ ርዳታ ተረፍኩ። አጎቴ ለኔና ለታናሽ ወንድሜ ብቻ ሳይሆን ለጓደኞቼም መዳን ረዳ። ከሁሉ በላይ አብዱል ቃድር የሚባል የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የደሴ ልጅ፣ አሁንም በህይወት አዲስ አበባ የሚኖር የጓደኛዬ ጓደኛ ባጎቴ ርዳታ ሞት ከሚጠብቅበት እስር ቤት ለማውጣት ስለቻልኩ እስከዛሬ ደስ ይለኛል። ከዚያ በኋላ ያለውን የደርግ ዘመን አጎንብሼና ትምህርት ላይ አተኩሬ የሆዴን በሆዴ ይዤ ባድርባይነት ነው ያሳለፍኩት። ስለዚህ የብዙ ሰው ያህል ቂም የለኝም። እነሻምበል ፍቅረስላሴ ላይ አሁን ከደረሰባቸው በላይ እንዲደርስባቸው አልፈልግም። ጉዳያቸውን ያየው ዳኛ እኔ ብሆን ኖሮ የሀያ ዓመት ቀርቶ የሁለት ወር እስራትም እልፈርድባቸውም ነበር። ሰው ሲዋረድና ሲሰቃይ ማየት አልወድም። የሰሩትን ስራ አልቅሼ ነግሬና ወቅሼ ንስሀ እንዲገቡ መክሬ ነበር የምለቃቸው። ግፈኛን በደግነት እንጂ በግፍ በመቅጣት ርካታ የሚገኝ አይመስለኝም።
ሻምበል በመጽሀፋቸው ሊሰጡን የሚሞክሩትን የማህበራዊ ሳይንስ ትንታኔ ቢተውት ይሻል ነበር። ኮሎኔል መንግስቱም መጽሀፋቸው መጀመሪያ ላይ እንዲህ አይነት የምሁር ተግባር ውስጥ ሲንጠራሩ ተመልክቼ ነው ሳላነብላቸው የወረወርኩት። ሻምበል ፍቅረስላሴ ሊቃውንት ተንታኞችን ሊጠይቅ የሚችለውን ማህበራዊ ሳይንስ ቀርቶ በተመክሮ እንኳን ሊታወቁ የሚችሉ ነገሮችን ስተዋቸዋል። ለምሳሌ በጊዜው ተነስቶ ስለነበረው ስለጊዚያዊ ህዝባዊ መንግስት ጥያቄ አንስተው በተቹበት ክፍል ውስጥ ጊዜያዊ ህዝባዊ መንግስት ሊመሰርቱ ይገባል ተብለው የተጠቀሱትን የህብረተሰብ ክፍሎች በየተራ እያነሱ እንዴት እንደማይችሉ ያስረዳሉ። የገበሬውን ተሳትፎ በተመለከተ፣
“ገበሬው ንቃቱ እጅግ በጣም ዝቅተኛ ከመሆኑም በላይ የመንግስትን አወቃቀርና አሰራር ማወቅ ቀርቶ የሚኖርበትን አካባቢ እንኩዋን እንዴት እንደሚተዳደር ለይቶ ለማወቅ ችሎታ የሌለው መደብ ነበር” ይሉናል። (ገጽ 226)።
ተማሪዎችን አስመልክቶ ሲናገሩ ደግሞ፥
“ተማሪዎች የስራም ሆነ የኑሮ ልምድ የላቸውም። ቤተሰብ ማስተዳደር እንኩዋን በቅጡ አያውቁም። . . . . . . . መንግስት ስልጣን ውስጥ ተካፋይ መሆን አለባቸው የሚል ሀሳብ ማቅረብ ከግዴለሽነት ወይም ግራ ከመጋባት የመነጨ ይመስላል” ይላሉ። (ገጽ226)”.
ይህን የሚጽፉት ሻምበል ፍቅረሰላሴ ከስልጣን አባሮ እስር ቤት ያጎራቸው ተማሪዎች የነበሩ ልጆች አደራጅተው ያሰማሩት የገበሬ ሰራዊት መሆኑን ፈጽሞ ረስተውታል። በታሪካችን ውስጥ ትንሽ ወደኋላ መለስ ብለው ቢያዩ ሀገሪቱን ለየዘመናቸው እንዲመች አድርገው አደራጅተው ፣ ሕግ አውጥተው ፣ ዳኝነት አይተው ፣ ገበያ አቋቁመው፣ ሲያስፈልግ የጎበዝ አለቃ መርጠው ፣ ጦርነት ተዋግተው ያቆዩልን አባቶቻችን ገበሬዎች መሆናቸውን መገንዘብ ይችሉ ነበር። የገዳን ስርዓት የሚያክል አስደናቂ የመንግስት ዘይቤ የፈጠሩት ያገራችን ከብት አርቢዎች እንደነበሩ ሻምበል የሚያውቁ አልመሰለኝም። ደርግን ከመሰረቱትና ሻምበል በመጽሀፉ እንደሚነግሩን አህያ የከበቡ የጅቦች ስብስብ በሚመስል ጉብዔ ላይ 60 ሰዎች ላይ እጅ እያወጡ ካለፍርድ ይገደሉ ብሎ ከሚወስን ወታደር የተሻለ ፍርድ ሊሰጡ የሚችሉ ብዙ ያገሬ ገበሬዎች እንዳሉ አውቃለሁ።
በደርግ የግዛት ዘመን ብዙ ሰው ከሀገር የሚሰደደው ደርግ ሀገሪቱን ለልጆችዋ የሲዖል ጎሬ ያደረጋት በመሆኑ መሆኑን ከሀያ አመት በሁዋላ እንኩዋን ማየት አለመቻላቸው ገርሞኛል። ገጽ 440 ላይ ሻምበል እንዲህ ይላሉ።
የኛን መንግስት ለማዳከም ታዋቂና የተማሩ ግለሰቦችን ጠላቶቻችን አስከድተዋል። የአሜሪካ መንግስት የስለላ ድርጀት (ሲ አይ ኤ) ከፍተኛ በጀት በመመደብ የመንግስት ባለስልጣናትን ፣ ይዩኒቨርሲቲ ምሁራንን ፣ ታዋቂ ስፖርተኞችን በብዛት አስኮብልሏል”።
ሻምበል ስደቱን ነው ኩብለላ የሚሉት። አሜሪካ ተሰዶ መኖር ለግል ኑሮ የሚጠቅም መሆኑ ከደርግ በፊት የማይታወቅ ነገር አስመሰሉት። በደርግ ጊዜ የነበረውን አንድ ከስደት ጋር የተያያዘ ቀልድ ሻምበል አልሰሙም መሰለኝ። ቀልዱ እንዲህ ነው። አንድ ቀን ቦሌ አይሮፕላን ጣቢያ የሚጀምር ብዙ ሺ ህዝብ ተሰልፎ ኮሎኔል መንግስቱ አዩና “ይህ ሁሉ ህዝብ ምንድነው” ብለው ጠየቁ አሉ። “ጓድ መንግስቱ ከሀገር ሊወጣ የተሰለፈ ህዝብ ነው” ብሎ አንድ ባለሙዋል ይነግራቸዋል። ታዲያ ይህ ሁሉ ሰው ከወጣ እኛስ ምን እንሰራለን ብለው ከኋላ ተሰለፉ አሉ። ሰልፈኛው ቅድሚያ እየሰጠ ስላሳለፋቸው መጨረሻ ላይ ከፊት አንደኛ ሆነው ተሰለፉ አሉ። ያን ጊዜ ያ ሁሉ እልፍ ሰው ሰልፉን ትቶ የበተናል። ኮሎኔል ግራ ገብቷቸው “ምን ሆኖ ነው ሰልፈኛው የሚበተነው” ብለው ባለሙዋሉን ሲጠይቁት “አይ እርሶ መጀመሪያ ከተሳፈሩና ከሄዱማ ለምን እንሄዳለን ብለው ነው” አላቸው ይባላል። ከደርግ በፊት ውጭ ሀገር ትምህርታቸውን የጨረሱ ምሁራን ዲግሪያቸውን እስከሚረከቡበት ድረስ ላለመዘግየት በፖስታ እንዲላክላቸው ጠይቀው ወደ ሀገራቸው ይመለሱ እንደነበር የማናውቅ አስመሰሉት።
ሻምበል መጽሀፉ ውስጥ የነበረውን የኢኮኖሚ ችግር በሙሉ እንዱን እንኳን እኛ ስለተሳሳትን የተፈጠረ ነው እይሉም። በራሳቸው የፖሊሲና የማኔጅሜንት ችግር በጊዜው በነበሩት የመንግስት እርሻዎችና ሌሎች የኢኮኖሚ ተቋሞች ላይ የደረሰውን ውድቀትና ኪሳራ ሁሉ በኢህአፓ ላይ ለጥፈውታል። በጊዜው ኮሎኔል መንግስቱና ተራው የደርግ አባል ሁሉ የኤክስፐርት ቦታ ተክተው ካልሰራን ሲሉ እንደነበር እዚህ ጊዜና ቦታ የለኝም እንጂ ብዙ ምሳሌዎችን መጥቀስ እችል ነበር። አንዲት እንኳን ምስሌ ሳይሰጡን በደፈናው ኢህአፓ “በተለያዩ የተንኮል ዘዴዎች የማምረቻ መሳሪያዎች በማበላሸት ወይም በማቃጠል የምርት እንቅስቃሴ እንዲቋረጥ አድርጓል”። ይሉናል። (ገጽ 253)
ሻምበል ከ1967 ዓም ጀምሮ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ያመጹባቸውንና የደመሰሷቸውን ሰዎች ሁሉ ጨፍልቀው መሬታቸው የተወረሰባቸው የመሬት ከበርቴዎች ይሏቸዋል። ያመጹ ባለመሬቶች መኖራቸው እውነት ነው። ታሪኩ ግን ይህ ብቻ አይደለም። ጠመንጃቸውን እንደጌጥ የሚወዱ በርካታ ድሀ ገበሬዎች መሳሪያ አስረክቡ ሲባሉ እንደውርደት ቆጥረው ለወንድ ልጅነት ክብራቸው ሲሉ የሸፈቱ ብዙ ነበሩ። እኔ በግል ጅባትና ሜጫ አውራጃ ውስጥ ጀልዱ በሚባል አካባቢ አስተማሪ በነበርኩበት ቦታ የሆነውን አውቃለሁ። አማራና ኦሮሞ ገበሬዎችና አነስተኛ ነጋዴዎች ናቸው። መሳሪያችንን ተውልን ብለው ለምነው ሲያቅታቸው የሸፈቱ ሰዎች በስም የማውቃቸው ነበሩባቸው። የተወሰነ ጊዜ ቢሆንም ተዋግተው የሞቱት ሞቱ። የመሬት ከበርቴ በሌለበት ሰሜን ሸዋም ተመሳሳይ ነገር መሆኑን አውቃለሁ።
ደርግ ገበሬዎችን መሳሪያ ሲገፍ ትልቅ ጠቃሚ የህብረተሰብ ባህሪ እየቀየረ መሆኑ አልገባውም። በየጥምቀቱና በየበአላቱ በዘፈን ላይ “ምንሽሬ ፣ ቤልጅጌ” የሚባሉ ዘፈኖችና “መራዥ ተኳሹ” የሚባሉት የጀግንነት ፉከራዎች ቆሙ። የጀግንነት መንፈስም አብሮ ተሰበረ። እሱ ዱሮ ቀረ ተባለ። የወያኔ ጦር ሰሜን ሸዋ ከደረሰ በኋላ ኮሎኔል መንግስቱ ደብረ ብርሃን ሄደው “ጀግናው የመንዝ የመራቤቴና የቡልጋ ህዝብ ሲዘምት እንጂ ሲዘመትበት አይተን አናውቅምና ተነስ” የሚል ሰበካ ካካሄዱ በሁዋላ አንድ ዘመዴ ገበሬ ያለኝን አልረሳውም። “ይቺ ሰውዬ” ፣ አለ መንገስቱን። ፊቱ ላይ የንቀትና የጥላቻ ገጽታ አይበት ነበር። “ያኔ መሳሪያችንን ገፍፋ ሴት አድርጋን ስታበቃ ዛሬ ባንድ አዳር ወንድ ልታደርገን ፈለገች አይደል? እንግዲህ እንደፎከረች ራሷ ትቻለው። እኛማ አንድ ጊዜ ቁጭ ብለን ሸንተናል” ነበር ያለኝ። ትንሽ ማሰብ የሚችል አንጎል ያለው ሀገር እመራለሁ ፣ አገር እወዳለሁ የሚል ሰው አንድ ሶሺዎሎጂስት ወይም ከባላገሮቹ መሀል ሽማግሌዎች ጠርቶ የሚሰራው ስራ ምን እንደሚያስከትል ይጠይቅ ነበር። እርግጠኛ ነኝ ብዙ ዓመታት ከደርግ ቀደም ብለው ሀገራችንን የመሩት አፄ ምኒልክ ቢሆኑ ኖሮ አዋቂ ሳያማክሩ እንዲህ አይነት ነገር አይሞክሩም ነበር። ሕዝቡን ቢፈሩት እንኳን እንደማትነካኝ ማልልኝ ብለው መሳሪያውን ይተውለት ነበር።
ደርግ በችሎታ ማነስና በማያውቀው ነገር ገብቶ ሳይሳካለት የቀረውን ነገር ሁሉ ሻምበል ፍቅረስላሴ በተለይ በኢህአፓ ላይ ብዙ ጊዜም ከተጠቀሙባቸው በሁዋላ በፈጁዋቸው መኢሶንን በመሳሰሉ ደርጅቶችና መሪዎቻቸው ላይ እየወስዱ የለጠፉት ነገር አስተዛዛቢ ነው። ለምሳሌ በሶማሊያ ወረራ ጊዜ ደርጉ ውስጥ የነበረውን ያመራር መዝረክረክና የሰራዊት ሽሸት ሁሉ በኢህአፓ ያመካኛሉ።እንዲህ ይላሉ፤
“የኢትዮጵያ ጦር የያዘውን ቦታ እየለቀቀ እንዲያፈገፍግ የተደረገው በሶማሊያ ጥንካሬና ግፊት ብቻ ሳይሆን በጦሩ ውስጥ የተሰገሰጉት የኢህአፓ አባላት ጦሩን በማሸበራቸውና እንዲሸሽ ቅስቀሳ በማካሄዳቸው ጭምር ነው። ……………… የኢህአፓ አባላት በጦሩ ውስጥ ሽብር ነዙ።….. ከዚህም አልፈው በግርግርና በተኩስ መሀል መሪዎችን ከጀርባቸው እየተኮሱ ገደሉ” (ገጽ 364)
በመጽሀፉ ውስጥ ብዙ ቦታ እንደሚያደርጉት ይህን ከባድ ክስ ያስቀምጡና ክሱን የሚያስረዳላቸው አንዲት መረጃ ወይም ምሳሌ አይሰጡም። ነገሩን በደርግ ዘመንም ሰምተነዋል። ይህ የተደረገበት ልዩ ምሳሌ (specific case) በጊዜ ፣ በቦታ ፣ በስም ተለይቶ ሲሰጥ ሰምተን እናውቅም። የሻምበል አይነት ስልጣን የነበረው ሰው ደግሞ ለመረጃ ቅርብ ስለሚሆን ማስረጃ ማቅረብ ሊቸገር አይገባም።
ሻምበል ፍቅረ ስላሴ በስልጣን ዘመናቸው የደረሰውን ታሪካችን የማይረሳውን ግፍ ሁሉ እንዳለ በኢሕፓና ትግሉን እናግዛለን ብለው ከውጭ ሳይቀር በረው ሀገር ገብተው ሂሳዊ ድጋፍ በመስጠት ትግሉን ለመምራት በተሳተፉ ወግኖቻችን ላይ ካለምንም ይሉኝታ ለመደፍደፍ ያደረጉት ሙከራ በጣም ያሳዝናል። ተገኘ የተባለ ጥሩ ነገር ሁሉ የደርግና የመንግስቱ ኃይለማሪያም ይሆንና የተበላሸ ነገር ሁሉ ደግሞ በነዚህ ሀይሎች ላይ ይላከካል። ሐላፊነት መውሰድ ብሎ ነገር የለም። ሌላው ቀርቶ ደርግ ከውስጥ ኢህአፓ ከውጭ አጣብቀው መከራቸውን በሚያሳዩዋቸው የመኢሶንና የሌሎች ደጋፊዎቻቸው ድርጀት መሪዎችንም ካለይሉኝታ ይከሷቸዋል። መንግስቱና ደራሲው ራሳቸውን ሳይቀር የሚመጻደቁበትን የሶሻሊዝም ሀሁ እጃቸውን ይዘው ያስቆጠሩዋቸውን ደርጅቶች መሪዎች እነ ኃይሌ ፊዳን ስልጣን ባቁዋራጭ ሊይዙ ሲሉ ደርሰው እንደገደሏቸው እያማረሩ ይነግሩናል። ካለፍርድ የተገደሉበትን ሁኔታ ሁሉ ተገቢ አስመስለው ያቀርቡታል። ከአምቦ ከተማ አለፍ ብሎ ቶኬ ከምትባል ቦታ ተደብቀው የተያዙትን የመኢሶን መሪዎች እስር ቤት እንኩዋን ሳያደርሷቸው ሜዳ ላይ እንዳረዷቸው በዚያው አካባቢ እኖር ስለነበር እየተሸማቀኩ ሰምቻለሁ። የደርግ ሎሌ ሆነው ሲያገለግሉ ጥሩ ይሆኑና በነጻነት ለመንቀሳቀስ የዜግነት መብታቸውን የተጠቀሙ ዕለት ርኩስ ይሆኑባቸዋል ለሻምበል።
ሻምበል ፍቅረስላሴ ደርግ በጥይት የፈጀውን ሠራተኛና ወጣት ሁሉ ኢህአፓ አስገደላቸው ይላሉ እንጂ እኛ ገደልናቸው አይሉም። ያየር መንገድ ሰራተኞች መንግስት ያገተባቸውን የስራተኛ ማህበር መሪ ይለቀቅልን ብለው በተነሳ ግርግር ላይ 6 ሰራተኞች በመንግስት መገደላቸውን ይነግሩንና ይህም ስለሆነ “ኢህአፓ ድል አድራጊ ሆኖ ወጣ” ብለው ያሽሟጥጣሉ። እንዴውም ግርግር ላይ “የመጀመሪያውን ተኩስ የተኮሱት የአህአፓ አባላት እንደነበሩ በተደርገ ማጣራት ተረጋግጧል” ይሉናል (ገጽ 251) ። የተጣራበትን መንገድም ይሁን ሰነድ ላንባቢው ዋቢ ለመስጠት አይጨነቁም። ደርጎቹ ከስዎቹ መሀል የተወስኑ ሰዎች አስረው ዘቅዝቀው እየገረፉና ጥፍር እያወለቁ የመረመሩዋቸው ሰዎች እንደሚኖሩ የምንገምት ሰዎች አለን። ከዚያ ያገኙትን ማስረጃ ይሆን ወይ ብዬ ለማሰብ እንድገደድ አደረጉኝ። ሻምበል ፈቅረስላሴን አወዛጋቢና አከራካሪ ሊሆን የሚችል መጽሀፍ መጻፍ ያማከራቸው ሰው ዋቢ መጥቀስና ማስቀመጥ ተገቢ መሆኑን የነገራቸው አልመሰለኝም።
ደርግ የገደላቸውን የመኢሶን አባላትም በራሱ በመኢሶን ያመካኛሉ። ለምሳሌ እንዲህ ይላሉ።
“የመኢሶን መሪዎች ከኮበለሉ ብኋላ በርካታ አባሎቻቸው ላይ የመጉላላት ፣ የመታሰርና ከሥራ መባረር በሎም የመገደል አደጋ ደርሶባቸዋል። ይህ የመኢሶን የስልጣን ጉጉትና የአመራር ድክመት ውጤት መሆኑ ነው”። (ገጽ 342)
የመሪዎቹ መኮብለል በምን ተአምር ነው ደርግ ካለፍርድ ተራ አባሎቹን እንዲፈጅ ምክንያት የሚሆነው? መሪህ ስለኮበለለ ተብሎ ተከታይ የሆነ ያገር ዜጋ ካለፍርድ ይፈጃል እንዴ? ሻምበል አንዳንዱ ሎጂካቸው የተዘቀዘቀ ነው። የደርግን ወንጀል በዚህ አይነት የተውገረገረ ዘዴ ለመሸፈን መጣር በታሪክ ላይ ትልቅ የሽፍትነት ስራ መሆኑ ሻምበል የገባቸው አልመሰለኝም።
ሌላ አንድ ልጨምር። የጄነራል ተፈሪ በንቲ፣ የሻምበል ሞገስ ወልደሚካኤልና መቶ አለቃ አለማየሁ ሀይሌ በኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም የተፈጸመባቸውን ዘግናኝ አገዳደል ድራማ ይተርኩልንና መደምደሚያ ላይ እንዲህ ይላሉ።
“የኢህአፓ መሪዎች በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ጉዳዮች ላይ የመወሰንና የማዘዝ ሙሉ ስልጣን ያለውን መንግሥት በመለመሏቸው ጥቂት የደርግ አባላት አማካይነት አንበርክከው ስልጣን ለመያዝ ይቻላል ብለው በቀየሱት ከጀብደኝነት የመነጨ ስልት ምክንያት የደርግ አባላትን ለእሳት ዳረጉ” ይሉናል(ገጽ 127)።
በራሱ በደርግ አሰራር ተመርጠው ሀላፊንት ላይ የተቀመጡትን የደርግ መሪዎች በግል ውሳኔ ከደርግ ውጭ አሲረው የገድሉዋቸውን ኮሎኔል መንግስቱን አረዷቸው እንደማለት ኢህአፓ ለሳት ዳረጋቸው ሲሉ ትንሽ አያፍሩም። የሚገርም ነው። የቀድሞ የጃንሆይ የመኪና ማቆሚያ ጋራጅ ውስጥ ከታሰሩ በሁዋላ ድምጽ በማያወጣ ጠመንጃ አስቀድመው አዘጋጅተው የረሸኗቸውን መንግስቱን ነፃ አውጥቶ ሌላ የሚከስ ሰው ምን አይነት ህሊና እንዳለው ለመገመት ይከብዳል። ጄኔራል ተፈሪ ፣ መቶ አለቃ አለማየሁና የሻምበል ሞገስን በጊዜው የነበረውን የርስበርስ መጨፋጨፍ ለማስቆም መላ ያሰቡና በስልጣን ጥም ያበዱትን ኮሎኔል መንግስቱን ገለል ለማድረግ ህልም የነበራቸው ቅን ሰዎች ነበሩ፣ ሆኖላቸው ቢሆን ኖሮ የተሻለ የሰላምና የእርቅ አቅጣጫ ሊመጣ ይችል ነበር፣ ብለን የምናስብ ብዙ ኢትዮጵያዊያን መኖራችንን እንዳይገምቱ ሻምበል ፍቅረ ስላሴ ህሊና ላይ አንዳች የሚያህል መርግ የተቀመጠበት ይመስላል። ለነገሩ ሶስቱንም የደርግ አባሎች የኢህአፓ ስርጎ ገቦች ይሉዋቸዋል እንጂ ለመሆናቸው ወይም ያደረጉትን ያደረጉት ከኢህአፓ በተሰጠ ትዕዛዝ ስለመሆኑ ምንም የቀረበ መረጃ የለም። ሙዋቾቹ የደርግ አባሎች በጊዜው የያዙትን ስልጣን ያገኙት ግን በዚያ ጨለማ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ በምትመስል የምርጫ አካሄድ መሆኑን ደራሲው ራሳቸው አልደበቁም። ሙዋቾቹ የሰሩት ነገር ጥፋት ነው ብለን ብንስማማስ እንኩዋን በዚያ ሁኔታ ከሚታረዱ ለምን ታስረው ቃላቸውን ሰጥተው ለፍርድ መቅረብ ነበረባቸው ብሎ የሚከራክር ህሊና አጡ። ያን ጊዜ ህሊናው ባይኖራቸው አይገርመኝም። ዛሬ ከብዙ ዘመን በኋላ ይህን ማሰብ አለመቻላቸው ግን ይገርማል።
ሻምበል ሁሉንም የደርግ መንግሥት ክንዋኔ በዚህ መጽሀፍ ላይ ማጠቃለል እንደማይቻል መጽሀፉ መጨረሻ ላይ ነግረውናል። ሳይነግሩን የቀሩት ነገሮች ግን ሊያልፉዋቸው የማይገቡና እዚህ መጽሀፍ ላይ የደርግ ጥሩ ተግባራት አድርገው ከነገሩን ስራዎች ጋር የሚነጻጸሩ ትልልቅ ነገሮች ናቸው። በደርጉ የመጨረሻ እድሜ አካባቢ ተነስቶ የነበረውን የከሸፈ መፈንቅለ መንግስት በተመለከተ ምንም አልነገሩንም። በጃንሆይ ጊዜ ስለደረሰው ችጋር በሰፊው ተርከዋል። በ1977 ዓ.ም ስለደረሰው ዘግናኝ የችጋር እልቂት ትንፍሽ አላሉም። የሚያመካኙባቸውን ሁሉ ጨርሰው ስለፈጁ የሚለጥፉበት አካል ስላጡ አስመሰለባቸው። አከራካሪ ስለነበረው ቤተሰብን መተከልና ጋምቤላ እስከመክፈል ስለደረስው ቅጥ ያጣ የሰፈራ ፕሮግራም ምንም አላሉም። ስለዚያ በጅጉ በድንቁርና ላይ ስለተጀመረ መንደር ምስረታ ስለሚባል የዕብደት ስራ ምንም አላሉም። እኔ ከገበሬዎች እንደተማርኩት ገበሬዎች ዳገታማና ጭንጫማ ጥግ እየፈለጉ መኖሪያ ቤት የሚሰሩት መሬቱ ጭንጫማ ስለሚሆንና ተፋሰስም ስለሚኖረው በክረምት ከብቶቻቸው አረንቋ እንዳይገቡ ፣ የማይታረስ መሬትም ላይ ስለሚሰፍሩ የርሻ መሬት ለማትረፍ ፣ ለጥ ያለው ሜዳ ደግሞ ውሀ ስለሚተኛበት ለሳርና ለግጦሽ እንጂ ተፋሰስ ስለሌለው ለቤት መስሪያና ለከብት በረት ስለማይሆን ነው። ይህን ነገር አቅርበው መንደር ምስረታውን ስለሞገቱ የታሰሩ ገበሬዎች አጋጥመውኛል። ደራሲው የደርግን ጥፋቶች ላለመንካት ሲሉ ብዙ ትንንሽ ነገሮችን እንድናስታውስ የሚወተውቱተን ያህል እነዚህን ትልልቅ የጥፋት ተግባራት ወደጎን የገፏቸው ይመስላል።
የፖለቲካ አመራር በውሱን አቅም ውስጥ ማድረግ የሚቻለውን ነገር ባግባቡ የማድረግና በተለይም አስቸጋሪ ቅራኔን የመፍታትና ስምምነት የመፍጠር (compromise) ጥበብ ነው። ይህንን የማያውቁ ፣ አንዴ እንዲቀናቸው የጠቀማቸው ዘዴ ለሁሉም ችግር መፍቻ የሚጠቅም የሚመስላቸው የፖለቲካ መሪዎችና ሀይሎች ከውድቀት አያመልጡም። ብዙ የፖለቲካ መሪዎች የሚፈልጉትን ነገር ወይም ለፕሮፓጋንዳ ብለው የሚያወሩትን ነገር ራሳቸው ደጋግመው ይሰሙና እንደውነት ያምኑታል። ያን ጊዜ ነገር ይበላሻል። ማስተዋል ሁሉ ቦታውን ለዕብሪት ይለቃል። በደርግም ላይ ሆነ በሌሎች አምባገነኖች ላይ የሆነው ይህ ነው። የደርግ ታሪክ ባጭሩ ሲጠቃለል ይኸው ነው። ሌተና ኮሎኔል መንግስቱን ሀገር ወዳድ እያሉ ሊሸጡልን የሚፈልጉ ሰዎች አሉ። ሻምበልም ሊሸጡልን እንደሚሞክሩት ኮሎኔል መንግስቱ ከስልጣናቸው በላይ ሀገራቸውን የሚወዱ ሰው አልነበሩም። በግትር አምባገነንነትና ራስ ወዳድነት ሀገርና ህዝብ ክፉኛ የጎዱ አምባገነን ናቸው። በተግባር ያየነው ይህንን ነው።
ስላለፈ ነገር መጻፍ ጥሩ የሚሆነው መማሪያና ማስተማሪያ የሆነ እንደሆን ነው። ሻምበል ስለደርግ ይኖራቸዋል ብለን የገመትነውን የሚያክል ከደርግ ጥፋትና ልማት የምንማርበት መማሪያ ነገር በዚህ መጽሀፍ ላይ አልሰጡንም። ወደፊት ይክሱን ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ።
Fekadeshewakena@yahoo.com
[የረዳት ፓይለቱ ጉዳይ] ጀግናችን አጀንዳችን!
በትርጉም የሚቃኑትን ወልቻማና የተወኩ ዕሳቤዎች በትርጉም ፋክት በማንጠር ለሚነሱ ማናቸውም ጥያቄዎች የነፃነት ትግሉ ቤተሰቦች መልስ መስጠት ግድ ይላቸዋል። ለዚህም ነው ሥርጉተና ብዕሯ ታጥቀው በጀግናቸው ዙሪያ ትንሽ ማለት የወደዱት። ለሚሰጠን ጊዜ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ምስጋናችን ፍቅር ሰንቆ ይደረስ እንላላን – ጥንዶች።
የዝምታ ድል ባለቤት ረዳት አውሮፕላን አብራሪ ኃይለመድህን አበራ ተገኘ።
ሥም።
ረዳት የአውሮፕላን አብራሪ ኃይለመድህን አበራ፤ ይህ ሥም የወጣት ጀግናችን ሥም ነው። ወላጆቹ መንፈስ ቅዱስ አቅብሏቸው በጥንቃቄ የሰዬሙበት። ደፍረን ስሙን እንጥራው። ድህነት ነው። ኃይል ያለው መድህን የሚበራ ስለ መገኘቱ ያበሥረናል – ይፈውሳልም!
በዚህ ሥም ፓል ላይ የሚጠሩ ወንድሞቼን አመስግናለሁ። በሌላ በኩል ግን ሺ ሚሊዮን ጊዜ „ኮ ፓይለት፤ ረዳት አብራሪ“ እያሉ የሚጠሩትን ቅን ወገኖቼ እንዲያስተካክሉ በትሁት ቅን መንፈስ አሳስባለሁ።፡ሥሙን ቅርባችን አድርገን እናስጠጋው። ከማንነታችን ጋር እናዋህደው። „ረዳት አውሮፕላን አብራሪ፣ ወይንም ኮ ፓይለት“ የወል ሥም ነው። ልክ „ሰው“ በሰውነት ለተፈጠረ ሁሉ የተጸዎ ሥም እንደሆነው ሁለ። እኔ አንድ „ሰው“ መጣ ብል። የምነግረው ሰው „የትኛው ሰው?“ ብሎ ማንነቱንና ልዩ የሚያደርገው ሥም ይጠይቀኛል „አቶ ሀ“ ጎረቤታችን ሃኪሙ በማለት መልስ እሰጣለሁ። „ረዳት አውሮፕላን አብራሪ ወይንም ኮ ፓይለት“ የሙያ የተጸዎ የወል ሥም ነው። „እሱ“ ስል ተወላጠ ሥም ይሆናል። ነገር ግን እንዲህ ላላ ለበቃ ተግባርና ተልዕኮ የተፈጠረን ወጣት የወሰደውን ልዑቅ እርምጃ ለመደገፍም ሆነ ለመቃወምም ስንነሳ ድርጊቱን ፈጻሚ ባለቤቱ መለያ ሥም አለው። እጅግ የሚያመራምር የሚያምርም „ኃይለመድህን አበራ“ አሁን በቤተሰብ ሥም ስለሚጠር ለሰላማዊ ስለፍና ለፒቲሽን „አበራ ኃይለመድህን“ ይህ በዚህ እንዲስተካክል አበክሬ ላሳስብ እወዳለሁ። እርግጥ ነው የገዢው የጎሳ ፓርቲ ተጠሪዎች ወይንም ደጋፊዎች በሽታችሁ እንደሚሆን አስባለሁ። ተፈጠረ ጀግና ባላሰባችሁት – ባላቀዳችሁት ሁኔታ …. ምን ትሆኑ? ፈጣሪን ጠይኩት …. አቤ ሄሮድስን ከነ ከነጓዙ ገርድሷል ማን ያውቃል ኃይሌ ደግሞ እነ ይሁዳን …. ቡሉ ወደ ሁለተኛው ጉዳዬ … ለእኔዎቹ
የነፃነት ትግል እርምጃን ቅንጦተኞች ዝነጣቸው አላማረባቸውም።
ባልተለመደ ሁኔታ፤ ዓለም በሌላ ወጣ ገብ ጉዳይ ሲባዝን ከኢትዮጵያ አንድ የቆረጠ ወጣት የተዘገን መከራን ለመግለጽ የተሳነውን የሚዲያ አንደበት በዝምታ አስገድዶ አስከፈተ። የትግሉ አይነት ሰላማዊ ነበር። ለነገሩ “ትግል“ ብሎ ሰላማዊ የለም የሚሉም አሉ። ቀደም ያሉትን የነፃነት ትግሎች ታሪክ መጸህፍት እንዲያነቡ እዬገባዝኩ፤ በተጨማሪም በህይወታችው ውስጥ ትዳር መስርተው ሲኖሩ ያለውን የመንፈስን የአካል መስከም ዳሰስ አድርገው ስለትግል ትምህርት እንዲወስዱ እጠቁማለሁ ያው በትህትና።
የነፃነት ትግል፤ አንቢተኛነት ነው። አሻም ማለት ነው። ለገዢው ለመገዛት ፈቃድን መንሳት ነው። አሻም ደግሞ በውድ ሊጀመር ይችላል። አድማጭ ካጣ ግን በህግ ጥላ ሥር ህግ መጣስ ግድ ይላል። አሁን ራህብ አድፍጦ ቹፌውን ወያኔን እዬጠበቀ ነው። „ዝምታ“ በእናት ሀገራችን በኢትዮጵያ „ልብን የሚሰነጥቅ የብዙኃን ዝምታ“ በእጅጉ ሰፍኗል። ኑሮው ራህብ ሆኖ አብሮ ከራህቡ ጋር በዝምታ የታመቀ ቃጠሎ አለ። ይህ ዝምታ ሲገነፍል ግን ምድር ቀውጢ ይሆናል። „ሀገርን ህዝብ ካልጠበቀ ሰራዊቶች በከንቱ ይደክማሉ“ ይለናል አካል የሌለው የመዳህኒተዐለም አገልጋይ ቃለ ወንጌል። ዛሬ ያለው የአጋዚ በላህሰብ ሞገዱ የተነሳ ዕለት መግቢያ ያጣል። ወያኔን በልስሉስ ቅምጥል ፈሰስ ባላች መንገድ እንታገል፤ ግን ይህችን ሳትነኩ፤ በዚህ አልፋችሁ፤ ያቺኛዋን ብቻ …. ራህብ ላይ ተሆኖ፣ ሞትም ላይ ተሆኖ፣ ዕንባ ላይ ተሆኖ፣ ሳቅ የለም እንጂ ይህ ቀበጥ ያለ የዝነጣ ትችና አገላለጽ አንድ የኮሜዲ ትራጄዴ በቅይጡ ልዩ ኪኖ ሆኖ ባሰራ ….. ነበር። አዬ! ዘማናይነት … የደላው ገንፎ ….
በመጀመሪያ ነገር በጫካ ተመክሮ የነፃነት ትግል አይመራም። ጎጥ ላይ ተሁኖም አይታሰብም። በንክኪ ፖለቲካም አይታሰብም። በቆረጠ ሥልጡን ዕይታን የነቃ ግንዛቤን ከዘመኑ ጋር እራስን በማቀራረብ መለወጠን አብስሎ ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ አይደለም ኢትዮጵያን አኽጉሩን ዓለምንም ቆሞ የሚያስተምር፤ የሚሰበክ ለሁለት ዓመት የዘለቀ የምንም ዓይነት ግድፈት ያልታዬበት ድንቁ “የድምጻችን ይሰማ“ እጅግ ብቁ ሥልጡን የእምነት የነፃነት ሰላማዊ ጥያቄና ግብዕቱ ከበቂ በላይ ትዕግሥትን አምርቶ ያቀና ገድል ነበር። ከዚህ በላይ ምን መረጃ እንድናቀርብ ይሆን የቅንጦት ፖለቲከኞች የሚጠይቁን?! …. ሰማያዊ ፓርቲ በቢሮ ሰልፍ በጠራ ዋዜማ ተደብድቦ ተገርፎ መዘረፉስ? የአንድነት ከፍተኛ አመራር በግልና በጋራ የሚደርስባቸው መራር እጅግ አሰቃቂ በሀገር ኢትዮጵያ ታይቶ ተሰምቶ የማይታወቅው ድፍረትስ ምን ይባል ይሆን? ጻፋችሁ ተብለው የካቴና ጓደኛ የሆኑት ቅኖችስ? እኔ አንዳንድ ጊዜ ይህ ህሊና የሚባለው ነገር በምን ላይ እንዳለ ይገርመኛል …. ግን የእውነት እንደ ሰው ማሰብ እንዴት …. አይቻልም ….
ሰማቱ አሰፋ ማሩ በጠራራ ጸሐይ በባሩድ የተቃጠለው ይረሳልን?! የኔሰው ገብሬ በቤንዚን እራሱን አመድ ማድረጉስ ህሊናን አይፈትሽምን? ያቺ ምስኪን ሴት ባልሽ መሳሪያ ደብቋል ተብላ የባለቤቷን ምንድ ነው በትርሷ እንድተጊትት ብቻ ሳይሆን የነገ ተስፋ ጥንስስ በግፍ ሲያሰወርዳት የት ነበርን? ስንቱ …. በእውነት ይህን እውነት ስንዳፈር ጠረናችን ባዕድ ሆኗል። ባላፈው ሳምንት አንድ ወጣት እራሱን በመዲናዋ ላይ ሲያጠፋስ ከቶስ የሥርዓቱን ገነትን ይነግረን ይሆን? በሳውዲ በግፍ ደማቸው በባዕድ ሀገር የጎረፉት ደመ ከልብ ወጣቶችን አቤቱታ በግል ኃላፊነቱን ወስዶ ሰማያዊ የጠራው ሰልፍ በምን አይነት ዱላ ነበር የተወራረደው? አለን ወይንስ የለንም?!
….. እራቅ ብልን ምልስትን ስንቃኝ ለእርቀ ሰላም ከውጪ ሀገር የሄዱት ወገኖች ምን ጠበቃቸው? ቅንጅናትና ቃሊቲ፤ ብዕርና እግር ብረት …. ህም! አለም ያወቀውን የሄሮድስ መለስ ዜናዊ ህልፈት ዘገበች ተብላ 30000 _የፍትህ“ ጋዜጣ የእሳት እራት የሆነቸው …. ምንድን ነው ነው የሚፈለገው?! …. አይደለም አቅጣጫን ቀይሮ በሰላም ያረፈ አውሮፕላን ቀርቶ ነገ ከዚህ የከፉ ያልታቀዱ ጨርሶም ያልተሳቡ የፋሙ ጥቃቶችን ወያኔ መጠበቅ ግድ ይላዋል። ቀለደ – ዘፈነ – ደለቀ – ዳነሰ …. ኢትዮጵያ እንደ ጥንቸል ማንኛውም ዓይነት መሞከሪያ ጣቢያ አድርጎ መሰረቷን ነቀለ። ዕንባ እያለ እንቅልፍ የለምና ነገም ሌላም ይጠበቅ ሙጃው ወያኔ። ከዚህም ባለፈ ይጋያል። እደግመዋለሁ ከዚህ ያለፈ ይጋያል። የአሽዋ ድርድሮች ላንቲካ የጨው ሃውልት ሆነውም ይቀራሉ ….. „ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው“
የትም ቦታ፤ በእጅ በገባ ማናቸውም መሳሪያ „እንቢተኝነት ይሞሸራል“ ነገ አይቀሬ መሆኑን ሙጃው ወያኔና ደጋፊዎቹ ብትረዱት እጅግ መልካም ነው። በዚህ ዙሪያ ቃል፣ ድምጽ፣ ክብር፣ ተቀባይነት፣ ሚዛን አያነሱም። ዜሮ ሲባዛ ዜሮ ዜሮ ይሆናል። የሃሳብ ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ መስመር የሳቱ ሂደቶች ግን ሊቀ ይገባቸዋል። ወያኔ ሃቅን ተጭኖ እንዲቀብል ማሰገደድ አይቻልም። ፈጽሞ! ወያኔ ያለወቀው ይህን ነው። ቀድሞ ነገር ወያኔ የብዙኃኑ አንጡራ ጠላት ነው። ሀገርን ያህል ታላቅ ክብር ለቀደመ ጠላት የሚሸልም አሽኮኮ … ይጠብቅ ጊዜውን። „እፉኙቱ ወያኔ“ ራሱን ሳይደግም አመድ ይሆናል ከነምናምቴው – ድሪቶው። ኢትዮጵያዊነት ፈተና የደረገው እሱ በሰራው ሴራና ደባ ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያዊነት ህሊናን ተውሶ ወይንም ተበድሮ የሚኖሩበት ማንነት አይደለም – በፍጹም። ለዚህ ደግሞ አልተማረበትም እንጂ ወያኔ የሰማዩ ታምር ከአናቱ ነበር ግማቱን በአንድ ሰሞን ትቢያ ያደረገው። አሁንም ይቀጥላል ፈንግል ይፈነገላል …. ግፍና እንባ ባክነው አይቀሩም … አስከ ልጅ – ልጅ ….
ከዚህ ጋር የሚነሳው ነገ አንድም አብራሪ ታምኖ አውሮፕላን አይሰጠውም፤ መልሱ ነገን የሚያውቅ መዳህኒአለም ብቻ ነው። የታፈነ ህዝብ ግን በር ሲዘጋ በመስኮት፤ መስኮት ሲዘጋ በጣሪያ፤ ጣሪያ ሲዘጋ በምድር ድምጹን እንብተኝነቱን በማንኛው ጊዜና ሁኔታ ያፈነዳዋል። ፉኛ ታውቃላችሁ? ከልክ ባላይ ከተነፋ ይፈነዳል …. ከፈነዳ የሚተርፍ አንድም የቅንጦት ምናንምን አይኖርም።
ወይ መዳህኒታአለም አባቴ ደግሞ ከመቼ ወዲህ ነው ስለ ኢትዮጵያዊነት ተቋማት ስብከት የተጀመረው? የወያኔ ጠላቱ ማንና ምን ሆነና?! ለመሆኑ ዬት አሉና ጥብቅና የሚቆምላቸው ተቋማት፤ ቀፏቸውን የቆሙት። ካላ ቀለም እስክርቢቶ አይጽፍም ሞክሩት …. በዘመነ ወያኔ አለን የምንለው የኢትዮጵዊነት ተቋም፤ ቅርስና ውርስ፤ ትውፊትም የለንም። የሰሞኑ የወ/ሮ ዘነቡ መልእክት ምን ይመስላችኋል? እስከዚህ ድረስ የገማ ነው ወያኔ! ከዚህ በላይ ምን እርቃን መቅረት አለና?ክብሮቼ – ስለዚህም የቤት ሥራችን ጥልቅና የገዘፈ መሆኑን ልብ ልንለው ይገባል። መርዝ ያልተነሰነሰበት አንዳችም ፃዕዳ ቦታ የለንም። በተረፈ የጀግኖች ጀግና! የተስፋ ተስፋ! የብርኃን ብርኃን መድህናችን ኃይላችንና ጉልበታችን እንደ ሲዊዝ ሰልፈኞች አገላለጽ „ሃይለመድህን አበራ የነፃነት መጸሐፋችን ነው።“ በጀግናችን ኮርተንበታል። በዚህ ጀግንነት መንፈስ ኢትዮጵያ ዳግም ታበራለች። ህሊና ተሸጠ እንጂ እነ ወያኔ ትውልዱ ባገኘው አጋጣሚ እኮ ማንፌስቶችሁን እዬቀጠቀጣ አመድ ዱቄት እያደረገላችሁ ነው። የጎጥ ረግረግ ለጨፈረበት መንፈሳችሁም ሽንፈትን አስገድዶ እዬጋታችሁም ነው።
ወይ ዘመናይነት …. ቅድመ መሰናዶ አስፈላጊ አይደለም፣ ሂደቱን ታከሩበታለችሁ የሚሉም አዳመጥኩ … ከእንቅልፎች … አይገርሙም? እኮ! ጅሎች እንዲህ ይሉናል። ቂሎች እንዲህ ይቀልዳሉ። „ልብ ያለው ሸብ“ ይላል ጎንደሬ። እኛ ስለምንሰራው ተግባር ለእኛ ተውሉን እነ ውሽልሽል የሙጃ አጨብጫቢዎች። የእናንተን የፍርሰት ቲወሪ ተንዶ አፈሩ እብቅ እስኪያድረጋችሁ ድረስ። መሬት የያዘ፤ መሰረት ያለው ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ነገን የሚሞሽር ተግባር በግልና በጋራ ተግተን እንሰራበታለን። እዬተኛን ሳይሆን የምንኖረው እዬኖርን እናበራለን – ብርኃን አለንና። ሥጦታውም የመዳህነታችን ነው። „ቁርጥ ያጠግባል“ ቁርጣችሁን ታውቁ ዘንድ ሊነገራችሁ ይገባል። አዲሱ ዓምት የፈረንጆች እንዴት ነበር ዶልታችሁ በአዲስ ትወና ቃጠሎ የነበር — አሁን እኮ ከጀግንነት መልስ ረብ አለና አታሞው ተዘቀዘቀ -። ኢትዮጵያ አምላክ አላት። ኢትዮጵያዊነትም ታግላችሁ የማታሸንፉት ሚስጢር ነው – ተግባባን?!
ህም!
“ሊያመልጥ ሲል ተያዘ፡“ ወይ ጉድ! — ይህ ደግሞ የዓይን እከክ ነው። ለመሆኑ ታድኖ የተያዘው ምን ከሚባል ጫካ ውስጥ ነው? ቀድሞ ነገር በአደጉት ሀገሮች እኮ ጫካዎችም የእረፈት ጊዜ ማሳለፊያ፤ መዝናኛዎች ሲሆኑ በአቅራቢያቸው ለሰው ልጅ የሚስፈልጉ ነገሮች ሁሉ የተሟላባቸው፣ የሰው መኖሪያ አካባቢዎች ናቸው። ሌላው የዱር አራዊት መኖሪያዎችም ቢሆኑ ለዱር አራዊቶች ጥበቃ የሚደረግላችው የተከለሉ አካባቢዎች ሆነው፤ ነገር ግን በአቅራቢያቸው ሁለመናቸው ሙሉ ነው። በመሆኑ የሰው ልጆች ለሰላማዊ ኑሯቸው ለመኖሪያ የሚመርጧቸው ቦታዎች ናቸው። „መሳቂያው ፓርላማ“ አለ አቤ ቶኪቻው መሳቂያዎች ለነገሩ በረቀቀ በሰማይ ታምር፤ እኛ ልንፈታው በማንችል ሁኔታ በፈረንሳይና በኢጣሊያን አውሮፕላን በክብር ታጅቦ በመስኮት በገመድ እወርዳለሁ፤ ከዛ ጠብቁኝ ሲል በግልጽና በልበ ሙሉነት፤ በረጋ መንፈስ ነበር የገለጸው። ወረደ – ፈቅዶ እራሱ እጁን ሰጠ። በቃ! ጀግናው ኃይለመድህን አበራ። „ያዙት“ የሚለው ቃል ለሂደቱ ሆነ ለሰብዕናው ከእውነት ውጪ ነው። ጄኔባ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ጫካ የለም። ጫካ ያለው በደመንፈሶች ህሊና በነወያኔ ብቻ ነው … እንደ አውሬ እንዲያስቡ ስለሚያግዛቸው፣ ተፈጥሯቸውም ስለሆነ፣ እንኳንስ ከድርጊቱ ከቃሉ ጋር ከ40 ዓመት በኋላ መፋታት አልቻላችሁም … እም!
እገታ ወይንስ ጠለፋ ወይንስ አቅጣጫ ቅይራ ….
ብብዙ ሚዲያዎች እመሰማው „ጠለፋ“ ነው። የሃሳብ ልዩነቱን አክብሬ እኔ እንደማስበው ግን ረዳት አውሮፕላን አብራሪው ሀይለመድህን አበራ እንደ ጣሊያናዊ ባእድ አብራሪ ሙሉ መብት አለው በአውሮፕላኑ ደህንነት ጉዳይ። ረዳትም የሚመደበው ዋናው ቢታመም ወይንም በረራ ላይ እያለ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ቢገጥመው ተክቶ እንዲያበር ነው። ሊቀመንበሩ ሳይኖር ምክትሉ ተክቶ እንደሚሰራው፤ ስለዚህ ኃላፊነቱን ወስዶ በንብረትና በተጓዦች ላይ ምንም የመንፈስ ጫና ሳይፈጥር እቅጣጫ መቀዬሩ „ጠለፈ“ ሊያሰኘው አይችልም ባይ ነኝ።
በሌላ በኩልም „ተሳፋሪን አገተ“ ለማለትም የሚያስችል ሂደት አላዬሁበትም „ አዬር ላይ እያለ ለቅድመ ሁኔታ ተሳፋሪውን አቅርቦ ቢሆን ኖሮ“ „አገተ“ የሚለውንም መጠቀም ባስቻለ። ባለሙሉ መብት ስለነበር አቅጣጫውን ቀይሮ ከታቀደው ቦታ ሳይሆን ሌላ ቦታ አሳረፈ። ይህ ደግሞ የአዬር ሁኔታ ቢዛባ፣ ሊያርፍበት የታሰበው አውሮፕላን ጣቢያ በጊዚያው ምክንያት ሊያሳርፍ ባይችል መሰሉ ተግባር ይፈጸማል።
በአውሮፕላኑ ላይ ሙሉ መብት ያለው አብራሪ በኢትዮጵያ ያለው የአንድ ዘር ተኮር የጎጥ ሥርዓት ጫናን በቃኝ ብሎ እንቢተንኝነቱን በእጁ በገባ አጋጣሚ ገልጦበታል። ወይንም ሰላሙን የነሳውን የጎሳ አስተዳደር አሻም ብሎ ገፍትሮበታል። እንዲያውም ከዚህ ጋር ተያይዞ በ28.02.2014 „የጀግናችን ድምጽ ድምጻችን ነው“ ለሚሉ ወገኖች ሲዊዘርላንድ በርን ላይ በተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ቀድም ብዬ ሄጄ ሰለነበር ከሁለት ኢትዮጵያዊ እህቶቼ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ለመወያዬት ዕድሉን አግኝቼ ነበር።
ወ/ሮ/ት እዬሩስ የምትባል ሰልፈኛ ስትነግረኝ እ.ኤ.አ በ1970 ከፖላንድ ወደ ሲዊዝ አንድ አብራሪ መሰል ተግባር እንደ ፈጸመና በዛን ወቅት ሲዊዞች ለዲክታተር አልገዛም ብሎ በመምጣቱ አጨብጭበው እንደተቀበሉት የሰማችውን አጫውታኛለች። ታሪክን ያጫወታት ሰው „ዛሬ ሲዊዝ ስደተኛ በመብዛቱ እንጂ እኔ እጠብቅ የነበረው አጨብጭበው እንደሚቀበሉት ነበር“ ሲሉ አንድ የሀገሬው ሰው እንደ አጫዋቷት ገለጸችልን። በዚህ መንፈስ ወስጥ ሆኜ እኔ ስለማስበው ጋር ግጥም ስለነበር ተስፋን ሰነቁኩኝ። እኔ ደግሞ „በዝምታ ዲክታተርን ያንበረከከ ለድልም የበቃ የጀግንት የላቀ ተግባር ስል አዘከርኩት። የጥንቃቄው ልባምንት ፍልስፍና ነው – ልእኔ። ሌላው ቀርቶ አውሮፕላን ውስጥ ሆኖ አውሮፕላኑ የማረፍያ ቦታውን እንደቀዬረ እንጂ በምን ምክንያት ዬት ለማረፍ እቅድ እንደነበረው፤ ፈጻሚውም ማን እንደሆነ እንኳን ፈጽሞ ፍንጭ አልሰጠም። ጠንቃቃነቱን በ30 ዓመት ዕድሜ ሲሰላ ታምር ነው። ይህም ስለሆነ ነው ተሳፋሪዎች መንፈሳቸው ሳይታወክ ጄኔባ የገቡት። ረቂቅ።
ስለምን በመስኮት?
ይህንንም ሲያጣጥሉት አድምጫለሁ። ረዳት አውሮፕላን አብራሪ ኃይለመድህን አበራ በመስኮት መወረዱ የተጓዡንም ሰላም ጠብቋል። ለሲዊዝ የደህንነት ቢሮም ብዙ ያላዬናቸው ተግባራትን ቀድሞ ሰርቶላቸዋል፤ አስተካክሎላቸዋል። ግብግብ ተፈጥሮ ቢሆን ብዙ ነገር መልኩ በተቀዬረ ነበር። ኃላፊነት በብቃት ያቀለመ ወርቅ ህሊና ማስተዋልን ፈጥሮ በህይወትም አቁሞ አሳይቷል። በሌላ በኩል በበሩ ሲወጣ ችግር ባይፈጠር እንኳን፤ የአውሮፕላኑ ውስጥ ከኢትዮጵያ ደንበር ጋር በብዙ መልኩ የተቆራኘ ሊሆን ይችል ስለነበረ፤ ለሙጃው ወያኔ ዬይገባኛል ጥያቄም ትንፋሽ በዘራለት ነበር። ይህን ሁሉ ብልሁ ቀድሞ ደፍኖታል እራሱ የሚስጢር ቁልፍ ነውና። እኔስ እላለሁ … ምነው ስትወለድ አስር ሆነህ በነበር … የኔ ጌታ!
ሥነ ምግባርና ኑሮውን
ይህን በሚመለከት ወላጅ እናቱ የተከበሩ ወ/ሮ የህዝብአለም ሥዩም „ብሩክ“ ሲሉ ገልጸውታል። ከዚህም በላይ በመኖሪያ አካባቢው የእረፍት ጊዜውን እንዴት ያሳልፍ እንደ ነበር አዲስ አድማስ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ አንብቡት። ጫማ ሲያስጠርግ፤ ኢንተርኔት ካፌ ተጠቃሚነቱ፤ የሚያዘወትራቸው ሱቆች፤ ጎረቤቶቹ፤ እቃ እዬጋዘ የሚቀርብለት ወጣት የሰጡት አስተያት እጅግ ያኮራል። ሁሎቹም የሰጡት አስተያዬት ወጥና የውስጡን ንጽህና ፍንተው አድርጎ ያሳያል። እኔ በዚህ ዕድሜ የማይታሰብ ብቃት ቡሁሉም ዘርፍ ከመልስ ሰጪዎች መገንዘብ ችያለሁ። እኛም ታድለናል፤ ተተኪዎቻችን በዚህ የኢትዮጵያ ጠላት በሆነ የጎጥ አስተዳደር በወያኔ ዘመን ተፈጥረው ግን በድርጊት እንደወርቅ እዬነጠሩ በሚወጡ ጀግኖቻችን ተስፋችን ልንጥል ይገባል። ኃላፊነቱንም ቀድመን ልንለቅላቸውም ይገባል። በምስከርነት በተሰጡት አስተያቶች ምርኩዝነት ወልገድጋዳ መላመቶች ሃግ ሊሉም ይገባሉ ….. ፎቶውንም የወሰድኩት ከዛው ነው ሊስቅም ይገባል የዝምታው ድል ዘመንን ሰርቷልና! ገዢ መሬቱን በሙሉ ተቆጣጥሮታል – ካለ ባሩድ ጢስ …
ጀግናችን አጀንዳችን ነው!
ጀግንነት ታሪክ ነው። ጀግንነት ትውፊት ነው። ጀግንነት ማንነት ነው። ስለሆነም ማንነታችን ዘለን ሌላ ነገር ማቀድ አንችልም። የፍላጎታችን እንብርት፤ የራዕያችን መሰረት፤ የተስፋችን ማረፊያ ሟተት ማንታችን በጀግንነት የጠለፈው የአድዋ፣ የማይጨው ወዘተ ታሪካችን ነው። የማንነታችን ምንጭና ግኝት ማህጸን የቀደምት ታሪካችን በተጋደሎ የቀለመ ከመሆኑ ላይ ነው። ስለ ትናንት ጀግኖቻችን ስናነሰ ይህ ብቻ በቂ አይደለም፤ በታሪካችን እኛም የእነሱን የሚመጥን ተግባር ዘመኑ በፈቀደው ልክ መሆን አለበት ብለን ተስማምተናል። ትናንት በፈረስ በበቆሎ ዛሬ ደግሞ ምዕቱ በፈቀደው በሠለጠነ እምቢተኝነት የተዘከረው የወርኃ የካቲት ደማቅ ገድል የጀግናችን የኃይለመድህ አበራ ታሪክ ታሪካችን ነው። ምዕራፉ በሰለጠነው ዐለም በሀገረ ሲዊዘርላንድ ጀኔባ ላይ ነው የተፈጸመው። እቅዱና ስኬቱ በትርጉም ሲለካ ጣሊያንን፤ እንግሊዝን፤ ፈረንሳይን፤ ቱርክን ፖረቹጋልን ቀደምት ሆነ ዛሬ አቅደው እያጠቁን ያሉትን ሁሉ ጠላቶቻችን ድል ያደረገ ምንም ብክነት ያልዞረበት ገድል ነው። ተፈታተሸን – ጣሊያን ዳግም ታሸ …. በአኽጉሩ። አሽከርነቱን የተቀበሉት ባንደዎችም አንገታቸው ተቀረቀረ፤ አንደበታቸው ተለሰነ።
ስለሆነም አጀንዳችን ከዚህ ገናና ገድል ይነሳል። አቅጣጫችን በዚህ ይመራል። ይዘከራል – ይወደሳል – ይከበራል። ለትውልዱ መንፈስ የሚስማማ፣ የሚጥን ፣የሚመችም ወርቅ በእጅ ገብቷል። ለመሆኑ መቼ ነው መኢህድንና አንድንት በጋራ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ አቅደው የሚያውቁት? ይህን ጥበብ መርምሩት። የጀግና እትብት በተቀበረበት ቦታ በዕለተ ሰንበት በሰባተኛው ቀን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በአኃቲ ድምጽ „ከባዶ ጭንቅላት ባዶ እግር ይሻላል „ ሲሉ አረሙ ወያኔ ከመጣ የተወለዱ ታዳጊዎች፤ ወጣቶች ታሪክንንና ማንንትን ያከበረ የወል ፍላጎትን በቁርጠኝት ሃዲድ በመንፈስም ጄኔባና በባህርዳር፤ ባህርዳር በጄኔባ ቃል አሰሩ — ውል ተዋዋሉ ኢትዮጵያዊነት ታተመ በመንፈስ ማህጸን! የበቃ የተግባር አብነት ተፈጸመ። ይህንስ ሰው ሰራሽ ነው ትሉት ይሆን …. እነ እንቶ ፈንቶ? ….
መቋጫ። ሁለት የዳዊት ፍሬዎች የተከበሩ የወ/ሮ የህዝብአለም ሥዩምን ቃለ ምልልስ ከባህርዳር የተጠነቀረውን ቃለ ምልሱን እጅግ በሚገርም ፍጥነት ቃል በቃል በ አማርኛ ከአትላንታ ጋዜጠኛዳዊትተሰርቶ እንደዛ መቅረቡ እጅግ ያኮራል። እንዲህ ብንደጋገፍ እንዴት መንገዳችን ቅርብ፤ ተስፋችን በመዳፋችን ውስጥ ተደላድሎ በገባ በነበረ …. እኔ የሲዊዝን ዘገባ ፃፍኩ ፎቶውን አርቲስት ሚሊዮን ላከልኝ … እስኪ ይህን አምሮት በመሆን እናክብረው … እባካችሁ?!
ቆዬን በጀግናችን ዙሪያ። የሀገሬ ልጆች ጀግና ነፍሳችሁ ነው። ስለምን? እናንተም አጋጣሚውን ካገኛችሁ ጀግንነቱን በድርጊት ትጠልፉታላችሁና … አትርሱት ጀግናችን አቡነዘሰማያታችን – ድርሳናችን ይሁን! አቅም ያለን ሱባኤ ላይ ስለሆን እንሰበው … ኃይልዬን! ሱባኤ ላይ ባንሆንም እንደ እምነታችን ከልባችን ውስጥ ካላቸው ሙዳይ መስጥረን ቸር ወሬ እንዲያሰማን ፈጣሪያችን እንጠይቅ የሁሉ ጌታ ይሰማናል። ሲዊዝዬ በመሆኑ በግሌ ተመችቶኛል። እኔ በተረጋጋ መንፈስ ሐሤትን እዬጠበኩ ነው። „ቸር ተመኝ ቸር እንድታገኝ“ …. ከሁሉ በላይ ሲዊዝ ሁሉም እንዳሻው የሚፈልገውን የሚዝቅበት ሀገር ስላለሆነ „የተከደነ ሲሳያችን ይፈልቃል“
ብልህ – ቆረጠ
ስልትነን – ታጠቀ
ተባይ ተጣበቀ
ትእቢት ተወቀጠ
ትንቢት – ተመረጠ።
በጀግኖቻችን ከጠላት የሚነሱ ማናቸውም ወጀቦች ሁሉ በድል ይሰክናሉ!
ኢትዮጵያዊነት ከቀስት እንድንበት ዘንድ የተሰጠን ልዩ አቅም ነው።
ፈተናን ከመፈጠሩ በፊት አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ኢትዮጵዊነት!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
[የኦሞ ወንዝ ጉዳይ] በግድቡ ሕይወታቸው የተገደበ ኢትዮጵያውያንን ለማትረፍ የሚደረገው እርብርብ –ከፕ/ር ዓለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
ከሁለት ዓመታት በፊት በዚህ በያዝነው ወር “ግድቡ እና አደጋው፡ ግልገል ጊቤ ሦስት በኢትዮጵያ“ በሚል ርዕስ በደቡብ ኢትዮጵያ በኦሞ ወንዝ ሸለቆ ከሚካሄደው ልማት ጋር በተያያዘ መልኩ ግድቡ ሊያስከትል በሚችለው እንደምታ ላይ ትኩረት በማድረግ ትንታኔ አቅርቤ ነበር፡፡ በዚያ ትንታኔዬ በዚህ የልማት ሰበብ እየተካሄደ ያለው እንቅስቃሴ በአካባቢው ስነምህዳር ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽእኖ እና ግድቡ በአካባቢው ለዘመናት ሰፍረው በሚኖሩት ህዝቦች ህይወት ላይ የሚያስከትለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ እና ማህበራዊ ቀውስ ከግምት ውስጥ በማስገባት በተለያዩ ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብት ተሟጋች እና የአካባቢ ጥበቃ ድርጅቶች መንግስት ከዚህ ድርጊቱ እንዲታቀብ ድምጻቸውን ሲያሰሙ እኔም የሀሳቡ ተጋሪ በመሆን የነበረኝን ጥልቅ ስጋት በተደጋጋሚ አሰምቸ ነበር፡፡
ከዚህም በተጨማሪ “በኦሞ ወንዝ ሸለቆ ያለውን ምቹ ያልሆነ ሁኔታ እና ተጋርጦ የሚታየውን የወደፊት አደጋ አስቀድመው ግንዛቤ በመውሰድ ታላላቆቹ ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳወቃቸውን በማስመልከት የነበረኝን ልዩ አድናቆት እና ምስጋና አቅርቤ ነበር፡፡“ በይበልጥም ደግሞ የዓለም አቀፍ ወንዞች/International Rivers፣ የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዎች/Human Rights Watch፣ የኦክላንድ ተቋም/Oakland Institute፣ የዓለም አቀፉ የኑሮ ዋስትና/Survival International፣ እና የአፍሪካ ሀብቶች የስራ ቡድን/the Africa Resources Working Group በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት የአካባቢውን የተፈጥሮ ስነምህዳር ለመጠበቅ እና ለዘመናት ሰፍረው የኖሩትን ህዝቦች ህይወት ለመታደግ በኦሞ ወንዝ ሸለቆ ላይ ለመተግበር የተያዘው መጠነ ሰፊ ዕቅድ ወደ ተግባር እንዳይሸጋገር ባደረጓቸው እና አሁንም በማከናወን ላይ ባሏቸው ጉልህ እና አንጸባራቂ ተግባራት ላይ የተሰማኝን አድናቆት እና ጥልቅ የሆነ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ እነዚህ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በግልገል ጊቤ ሦስት የሀይድሮኤሌክትሪክ ግድብ ግንባታ ምክንያት ህይወታቸው ለከፋ አደጋ ተጋልጦ የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን/ት ህይወት ለመታደግ በሚደረገው የህይወት ማዳን እርብርብ ለዓመታት በመጀመሪያው ረድፍ ላይ በጽናት ተሰልፈው የሚገኙ ናቸው፡፡
የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የህዝቡን ግንዛቤ ከፍ በማድረግ እና የቅስቀሳ ዘመቻዎችን በማካሄድ በኦሞ ወንዝ ሸለቆ ላይ ሊከሰት በሚችለው የከፋ የአካባቢ ስነምህዳር አደጋ ላይ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የጠራ አቋም እንዲይዝ በማድረግ እረገድ በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት በጥንቃቄ የተዘጋጁ ዘገባዎችን፣ የጥናት ውጤቶችን እና ዝርዝር የፖሊሲ ትንተናዎችን እንዲሁም ሌሎች ሳይንሳዊ እና አሀዛዊ ዘገባዎችን በማዘጋጀት በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያለው ገዥው አካል በሚተገብራቸው “የልማት መርሀግብሮች” ሰበብ በኦሞ ወንዝ ሸለቆ ግራ እና ቀኝ ለዘመናት ሰፍሮ በሚኖረው ህዝብ የዕለት ከዕለት ኑሮ እና አጠቃላይ ህልውና ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ውጤት በሰነድ አስደግፈው አቅርበዋል፡፡ እነዚህ ዓለም አቀፍ የአካባቢ ስነምህዳር ጥበቃ እና የመብት ተሟጋች ድርጅቶች በጊቤ ሦስት የሀይድሮኤሌክትሪክ ግድብ ግንባታ አማካይነት በወንዙ ሸለቆ የሚገኙትን የተለያዩ ጎሳዎች መሬት በማይመጥን የኪራይ ተመን ሰበብ ገዥው አካል በመንጠቅ ለወጭ ገበያ ምርትነት የሚውሉ የስኳር እና ሩዝ ልማቶች ዘርፍ ተግባራዊ በማድረግ በሸለቆው ግራ እና ቀኝ ሰፍሮ ለዘመናት ሕይወቱን ሲመራ የኖረውን ህዝብ በግዳጅ “የመንደር ሰፈራ” (“villagization”) በሚል ከቀየው ለማፈናቀል እያደረገ ባለው ጭካኔ የተሞላበት አካሄድ ላይ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የጋራ ግንዛቤ እንዲጨብጥ እና የኗሪውን ህዝብ ተጠቃሚነት አሽቀንጥሮ የጣለው የስመ ልማት ከንቱ ሙከራ ተግባራዊ እንዳይሆን ለማስቆም እና ተጽዕኖ መፍጠር እንዲችል በመፈጋቻቸው ነው፡፡
እ.ኤ.አ በ2012 ባቀረብኩት ትችቴ የዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እና የአካባቢ ስነምህዳር ጥበቃ ድርጅቶች እንዲሁም ቡድኖች በኦሞ ወንዝ ሸለቆ የልማት መርሁግብር ሰበብ ህልውናቸው ለከፍተኛ አደጋ ተጋልጦ የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን/ት ህይወት ለመታደግ ከልማት ሰለባው ህዝቦች ጎን በመሰለፍ ድርጊቱን በማውገዝ እና ለመቀልበስ እንዲቻል የሞት ሽረት ትግል እያደረጉ ባሉበት ወቅት እኛ ኢትዮጵያውያን/ት በተለይም ደግሞ የዲያስፖራው ማህበረሰብ አባላት እጃችንን አጣጥፈን ከዳር የመቆማችን እውነታ ለምን እንደሆነ በመጠየቅ ለዚህ አንገብጋቢ አደጋ ልዩ ትኩረት ባለመሰጠቱ ጉዳይ ላይ በማብሰልሰል የተሰማኝን ቅሬታ ለወገኖች በይፋ ገልጨ ነበር፡፡ እነዚህ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ተቋማት እና ቡድኖች ለእኛ ብለው እንደዚህ ያለ ከባድ እና ቀጣይነት ያለው ስራ እያከናወኑ እያሉ እኛ ግን በጸጥታ እየተመለከትን ነው፡፡ በዚያን ጊዜ “ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት እና ከአካባቢ ስነምህዳር ጥበቃ ድርጅቶች ጋር በመቀላቀል ለአካባቢያችን ለመሟገት እራሳችን ንቁ ተሳታፊ በመሆን እገዛ እናድርግ በማለት ለኢትዮጵያውያን/ት ወገኖቸ ሁሉ የተማጽዕኖ ጥያቄ አቅርቤ ነበር፡፡” እንዲሁም “በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገው እና የተለያዩ ብዝሀ ህይወት ዝርያዎችን አካትቶ የያዘው የኢትዮጵያ ሀብት አሁን ላለው እና ለወደፊቱ ትውልድ ጠቀሜታ እንዲውል ክብካቤ እና ጥበቃ እንዲደረግለት የእራሳችንን የአካባቢ ጥበቃ ሲቪል ድርጅት እኛው ኢትዮጵያውያን/ት በተለይም የዲያስፖራው ማህበረሰብ እናቋቁም” የሚል የተማጽዕኖ ጥሪ አቅርቤ ነበር፡፡ የሁኔታውን አሳሳቢነት በመገመትም እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቸ ነበር፣ “ይህንን ማድረግ ካልቻልን በኦሞ ወንዝ ሸለቆ ግራ ቀኝ በሚኖሩ ወገኖቻችን ላይ ግድቡ እያደረሰ ያለው አደጋ ዓይነት እጣ ፈንታ ውስጥ እራሳችንን ማግኘት እንደምንገደድ መገንዘብ ይኖርብናል፡፡“
ያንን ትችት ጽፌ ካቀረብኩ ከሁለት ዓመታት በኋላም ቢሆን እስከ አሁን ድረስ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መበቶች እና የአካባቢ ስነምህዳር ጥበቃ ድርጅቶች ለእኛ ብለው ያንን ሁሉ እልህ አስጨራሽ ትግል እና ጥረት እንዲሁም የእኛን ወገኖች ህልውና ለመታደግ እርብርብ እያደረጉ ባሉበት ወቅት እኛ ከዳር ቆመን እየተመለከትን የመገኘታችንን ሁኔታ ሳስበው ለመቀበል በጣም ይቆጠቁጠኛል (በግልጽ ለመናገር ሀፍረት ይሰማኛል፡፡) እነዚህ ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡት ተመሳሳይ ጥያቄዎች ምንም ምላሽ ባይኖራቸውም ደግሜ ደጋግሜ እንዳነሳቸው እገደዳለሁ፡ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የአካባቢ ስነምህዳር ጥበቃ ድርጅቶች በኦሞ ወንዝ ሸለቆ ላይ እየተካሄደ ላለው የከፋ አደጋ የሚያመጣ መርሀግበር መቀልበስ ለእኛ ሲሉ ሁሉንም እልህ አስጨራሽ ስራዎች እንዲሰሩ መጠበቅ በእውነቱ ፍትሀዊ ነውን? እነዚህ ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ለወጎኖቻችን እና ለሀገራችን ሲሉ ይህንን የመሰለ ጥንቃቄ እና ክብካቤ ሲያሳዩ እኛ የጉዳዩ ባለቤቶች ምንም ዓይነት ትኩረት ያልሰጠነው ለምን ይሆን?
ለወገኖቻችን ህልውና ሲሉ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ከሚያሰሙት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የማንቀላቀል እና ድጋፍ የማናደርግላቸውስ ለምን ይሆን? ጨቋኙ ገዥ አካል የጭቃ ጅራፉን እያጮኸ በእነዚህ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ላይ ቅጥፈት የተሞላበት እና አሳፋሪ መግለጫ እየሰጠ መልካም ስራቸውን እና ስማቸውን ሲያጠለሽ ለምንድን ነው ወደ እነዚህ ድርጅቶች በመጠጋት የማናግዛቸው እና የማንከላከልላቸው? ተመሳሳይ የአካባቢ ስነምህዳር ጥበቃ ወንጀሎች እና የሰዎችን ሰብአዊ መብቶች የመደፍጠጥ ወንጀሎች በስመ “ልማት” ሰበብ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ቢፈጸሙ ኖሮ በእውነት ግድየለሾች እና በዝምታ የምንመለከተው ይሆን ነበርን? በኦሞ ወንዝ ሸለቆ ግራ እና ቀኝ የሚኖሩ ወገኖቻችን የተገለሉ አናሳ ጎሳዎች በመሆናቸው ብቻ ለእነርሱ መብቶች መደፍጠጥ ግድየለሾች መሆን ይኖርብናልን? በኦሞ ወንዝ ሸለቆ ግራ እና ቀኝ የሚኖሩ ወገኖቻችን እንደሌሎቻችን ሁሉ “ዘመናዊነትን” የተላበሱ ባለመምሰላቸው በእነርሱ አፍረንባቸው ወይም ደግሞ በቅርቡ ያረፉት አቶ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት የእነዚህ ህዝቦች አኗኗር “ኋላቀር ስልጣኔ“ ነው በማለት በግልጽ እንደፈረጇቸው ቆጥረነው ሊሆን ይችል ይሆን? በምን ዓይነት ሁኔታ ነው እረፍት በሌላቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከፍተኛ ተጋድሎ አማካይነት በኦሞ ወንዝ ሸለቆ ግራ እና ቀኝ ለሚኖረው ህዝብ የተገኘ የአካባቢ ክብካቤ እና ጥበቃ ቅርስ ነው እናም ኑ ተረከቡን ብለን የወደፊቱን ትውልዶች ለማሳምን የምንሞክረው? ውድ አንባቢዎች በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ በአንክሮ እንድታስቡ እጠይቃለሁ፡፡
እኛን እየረዱን ያሉትን ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ቢያንስ በገንዘብ ልናግዛቸው የሚገባ መሆኑ ፍትሀዊ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በኦሞ ወንዝ ሸለቆ ግራ እና ቀኝ ለሚኖሩት ወገኖቻችን ሰብአዊ መብት ጥበቃ ይህን ያህል ተጋድሎ እያደረጉ ባለበት ሁኔታ እኛ ድጋፋችንን በተጨባጭ ሁኔታ ለወገኖቻችን የማናሳይበት ምክንያት ሊኖር አይችልም፡፡ ከእነርሱ ጋር በጋራ መቆም ይገባናል እናም ከዳር ቆመን የእነርሱ ተመልካች መሆን አይኖርብንም፡፡
የግልገል ጊቤ ሦስት ግድብ በኦሞ ወንዝ ሸለቆ ግራ እና ቀኝ በሚኖሩ ህዝቦች ላይ የሚያስከትለው ግልጽ እና ወቅታዊ አደጋ፣
የጊቤ ሦስት ግድብ ግንባታ በአሁኑ ወቅት በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ በኦሞ ወንዝ ሸለቆ ግራ እና ቀኝ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን/ት ወገኖቻችን ማለትም በቦዲ፣ ካሮ፣ ሙጉጂ፣ ሙርሲ፣ ኒያንጋቶም እና ዳሰነች ከብዙዎች ጥቂቶቹ ሲሆኑ ለሺህ ዓመታት “ባህረ ሸሽ ግብርና” እየተባለ የሚጠራውን የግብርና ስራ በመስራት ህይወታቸውን ሲመሩ በኖሩት ላይ ግልጽ ወቅታዊ አደጋ አንዣቦ ይገኛል፡፡ የዝናብ ወራት ከተጠናቀቁ በኋላ ውኃው ሲሸሽ በወንዙ ዳርቻዎች አካባቢ ተሸፍኖ የነበረው መሬት ለም የሆነ ደለል በርካታ የአዝዕርት ዓይነቶችን ማለትም ማሽላ፣ በቆሎ እና ባቄላ ለማምረት ያስችላል፡፡ የእነዚህ ኢትዮጵያውያን ህልውና የተመሰረተው በየጊዜው በሚለዋወጡት የጎርፍ ወቅቶች አማካይነት ነው፡፡ የጊቤ ሦስት ግድብ የወንዙ የላይኛው ክፍል ወደ ውጭ አገር ለሚላክ የኤሌክትሪክ ምርት ማመንጫነት ሲባል በሚገደብበት ጊዜ ወንዙ በሸለቆው ውስጥ የሚያደርገውን የተፈጥሮ የውኃ ፍሰት መጠን በመሰረታዊ መልኩ ያናጋዋል፡፡ ወደግድቡ ማጠራቀሚያ እና ለስኳር ልማት የመስኖ ስራ ለሚውለው ውኃ ፍጆታ ሲባል የውኃው የፍሰት አቅጣጫ ሲቀየር አጠቃላይ የኦሞ ወንዝ የውኃ መጠን ዘለቄታዊ ባለው ሁኔታ በእጅጉ እንደሚቀንስ በመስኩ የተሰማሩ ባለሙያዎች አሳማኝ በሆነ መልኩ ሞግተዋል፡፡
በዚህም ምክንያት በሸለቆው ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች በእርግጠኝነት ባህረ ሸሽ እየተባለ የሚጠራውን የግብርና ዘይቤ ለማካሄድ አይችሉም፡፡ እ.ኤ.አ በ2012 በዓለም ዕውቅናን ያተረፉት የተፈጥሮ ሀብት ክብካቤ እና ጥንታዊ የሰው ዘር ተመራማሪ የሆኑት ባለሙያ ዶ/ር ሪቻርድ ሊኬይ የጊቤ ሦስት ግድብ ግንባታ የግል ጥቅም ማሳደጃ “ሳይንሳዊ” ጥናት በስነምህዳሩ ላይ ሊከሰቱ የሚችሉትን ውጤቶች አሳንሶ የሚያይ መሆኑን የምር በመሞገት “ግድቡ በርካታ የሆኑ አሉታዊ ውጤቶችን እንደሚያስከትል እንዲያውም አንዳንዶቹ በሁለቱም በኩል ማለትም በአካባቢው ስነምህዳር እና ለዘመናት ህይወቱን በዚህ ወንዝ የታችኛው ክፍል ላይ መስርቶ ለሚኖረው ማህበረሰብ ህይወት ውድመት እና ዕልቂት“ ሊሆን እንደሚችል አስረግጠው ተንብየዋል፡፡
የኦሞን ወንዝ “ማልማት”፣
እ.ኤ.አ በ2011 መጨረሻ አካባቢ አቶ መለስ ዜናዊ በደቡብ ኦሞ ዞን በጅንካ ከተማ በመገኘት ንግግር አድርገው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ አቶ መለስ ረዥም እና የማስመሰያ፣ እንዲሁም ጠንከር ያለ እና እብሪት የተሞላበት ንግግር ነበር ያደረጉት፡፡ “በኋላ ቀር ስልጣኔ” ተተብትበው የሚገኙት ላሏቸው በኦሞ ወንዝ ሸለቆ ግራ እና ቀኝ ለሚኖሩ ህዝቦች ከሰማይ መና እንደሚያወርዱላቸው ነበር ቃል የገቡት፡፡ እነዚህን ህዝቦች ከድንጋይ ዘመን መንጥቀው በማውጣት ወደ ስልጣኔው ዘመን በእልልታ በማምጣት “የፈጣን ልማት ምሳሌ” እንደሚያደርጓቸው ምለው ተገዝተው ነበር፡፡ እንዲህ በማለት ነበር ለማህበረሰቡ የመተማመኛ ንግግር ያደረጉት፣ “በኦሞ ወንዝ የሚገነባው ግድብ የጎርፍ አደጋውን ያስወግድላችኋል፣ ግዙፍ የሆነ የመስኖ ልማት ስርዓት ይዘረጋል፣ እናም ከቦታ ቦታ የምትዘዋወሩት የማህበረሰብ አባላት (pastoralists) ዘለቄታዊ የሆነ ገቢ ያስገኝላችኋል፣ እንዲሁም ደግሞ ዘመናዊ ህይወት ትኖራላችሁ”::
ለጊቤ ሦስት ግድብ ግንባታ ሂደት ጥንቃቄ እና ትኩረት በመስጠት እንዲከናወን እና ለዘመናት በኦሞ ሸለቆ ግራ እና ቀኝ ኑሮውን በመግፋት ላይ የሚገኘውን ህዝብ የህይወት ዘይቤ እና ባህል በጠበቀ መልኩ የልማት ስራው እንዲከናወን ተማዕጽኗቸውን ላቀረቡ ዓለም አቀፍ የአካባቢ ስነምህዳር ጥበቃ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አቶ መለስ በአጻፋው ጥላቻ በተሞላበት መልኩ ስራቸውን ስማቸውን በማጠልሸት እና በነገር በመሸንቆጥ የአቅማቸውን ያህል ተግትገዋቸዋል፡፡ እነዚህን ዓለም አቀፍ ድርጅቶች “ወንዞቻችንን የመጠቀም ነጻነታችንን ለመገደብ እና ህዝቦቻችንን ከድህነት እንዳናወጣ“ ሁልጊዜ ለተቃውሞ የተዘጋጁ እና እልቂት ናፋቂ ሟርተኞች ናቸው በማለት ፈርጀዋቸዋል፡፡ እንዲሁም አደገኛ የልማት አደናቃፊዎች የሚል ታርጋ ለጥፈውላቸዋል፡፡ እንዲህ በማለትም አክለውላቸዋል፣ “ግዙፍ የሆነ ፕሮፓጋንዳ በመፍጠር ላይ ናቸው… የልማት ፕሮጀክቶቻችንን እንዳናጠናቅቅ ከውጭ የገንዘብ ብድሮችን እንዳናገኝ መሰናክል በመፍጠር ላይ ናቸው፡፡“ እንዲህ ሲሉም ተሳልቀውባቸዋል፣ “የኋላቀርነት እና የድህነት ሁነኛ ጓደኞች…በእርግጥ ምንም ዓይነት ተጨባጭነት ያለው ነገር የማይሰሩ” ብለዋቸዋል፡፡ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ለእራሳቸው ጥቅም ብቻ የቆሙ ዘረኞች ብለዋቸዋል፣ ምክንያቱም ይላሉ፣ “ሁሉም እንዲሆን የሚፈልጉት ነገር እነዚህ ዘላኖች የቱሪስት መስህብ ሆነው እንዲቀሩ ነው፡፡“ እናም የኦሞ ወንዝ ሸለቆ ህዝቦች፣ “ለሳይንቲስቶች እና ለተመራማሪዎች ለጥንታዊ የሰዎች የአኗኗር ዘይቤ የተናጠል ጥናት“ ማድረጊያ ማዕከል ሆነው እንዲቀሩ ለማድረግ አስበው ነው ብለዋል፡፡
አቶ መለስ እና ሎሌዎቻቸው ከዚህ ቀደም የተደረገውን እና በአሁኑ ጊዜም በጊቤ ሦስት ግድብ እና ሸለቆውን “ለማልማት” በሚል ሰበብ እየተደረገ ያለውን የአካባቢ ውድመት ለመደበቅ ብዙ ርቀቶችን ተጉዘዋል፡፡ እ.ኤ.አ በጁላይ 2008 በግድቡ ላይ የግንባታ ስራ ከተጀመረ ከሁለት ዓመታት በኋላ እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እና የአካባቢ ስነምህዳር ጥበቃ ድርጅቶች ዓለም እንዲገነዘብ ደወሉን ማሰማት ከጀመሩ በኋላ አቶ መለስ “የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን መስሪያ ቤታቸው” የጊቤ ሦስትን ፕሮጀክት የአካባቢ ስነምህዳር እና ማህበራዊ እንደምታ ጥናት አሳትመው እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ ያ የጥናት ዘገባ ለማስመሰያነት የአቶ መለስን የማይቀየር ጽኑ ውሳኔ ህጋዊ በማስመሰል ወዲያውኑ በህገወጥ መልክ የፕሮጀክቱን የወደፊት ስራ ለማስቀጠል የተደረገ አሳፋሪ ክንውን ነበር፡፡ ያ ዘገባ ዓይን ያወጡ ቅጥፈቶች የታጨቁበት ነበር፡፡ የጊቤ ሦስት ግድብ የውኃ ማጠራቀሚያ አካባቢ ለሰው ልጅ መኖሪያነት ምቹ አይደለም፣ ምክንያቱም ገዳይ በሆኑት የወባ ትንኝ እና የቆላ ዝንቦች/tsetse flies (“ለእንቅልፍ በሽታ” የሚዳርጉ) ተህዋስያን የተወረረ አካባቢ መሆኑን ሀፍረተቢስ በሆነ መልኩ ያቀረበ ዘገባ ነበር፡፡
ዘገባው እንዲህ ይላል፣ “ወደፊት በግድቡ የውኃ ማጠራቀሚያ አካባቢ ምንም ዓይነት ሰፈራ አይኖርም፣ እናም ሰፈራዎች የሚኖሩት በላይኛው ከፍታ ቦታዎች ከሸለቆው ውጭ በሆኑ አካባቢዎች ብቻ ነው… በታችኛው የኦሞ ወንዝ ሸለቆ የመጨረሻ ጠርዝ አካባቢ መሬቶች ላይ በጣም ውስን የሆነ የእርሻ ስራ አለ… በመርሀግበሩ በተያዘው ግድብ ዙሪያ የሚኖረው ህዝብ እና በውኃ ማጠራቀሚያው መካከል ያለው የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት/UNESCO ከያዘው የባህል ቅርስ ቦታ በቅርብ ርቀት የሚገኙ አይደሉም፡፡ በግድቡ እና በዙሪያው ባሉ አካባቢዎች ሳይንሳዊ፣ ባህላዊ፣ የዘር እና የታሪክ ጠቀሜታ ያላቸው በግልጽ የሚታዩ ቅሬተ አካሎች የሉም፡፡“
የአቶ መለስ የኦሞ ወንዝ ሸለቆን “ኋላቀርነት” ወደ “ዘመናዊነት” ኑሮ የመቀየር ዘይቤ ሸለቆውን ለሳውዲ አረቢያ እና ለሌሎች የውጭ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች እና ለጓደኞቻቸው ለማዛወር የታቀደ ነበር፡፡ አቶ መለስ በንግግራቸው በመቀጠል “መንግስት ዕቅድ ያወጣል፣ እናም 150,000 ሄክታር የስኳር አገዳ ልማት ከዚህ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ያደርጋል“ በማለት መንግስታቸው ጠንክሮ እንደሚሰራ ገልጸው ነበር፡፡ በእርግጠኝነት እንደ አይሲ/IC የተባለው መጽሔት ከሆነ “የሳውዲ አረቢያው ባለሀብት አልሙዲ በከፍተኛ ደረጃ ካሉት የመንግስት አመራሮች ጋር ጥብቅ የግንኙነት ትስስር ስላለው ለሩዝ ምርት የሚሆን 10,000 ሄክታር መሬት ተሸንሽኖ ተሰጥቶታል፡፡“ የእርሱ ግዙፍ ፕሮጀክት በአካባቢው ስነምህዳር ማለትም በብሄራዊ ፓርኩ እና በዱር እንስሳት መጠለያ ላይ እንዲሁም ለዘመናት በአካባቢው ሲኖሩ በነበሩ ትውልዶች ማህበረሰብ አባላት ላይ ታላቅ ጉዳትን አስከትሏል፡፡”
አቶ መለስ በኦሞ ወንዝ ሸለቆ በኦሞ ኩራዝ የስኳር ልማት ፕሮጀክት ስር አምስት የስኳር ፋብሪካዎች ይቋቋማሉ በማለት ተናግረው ነበር፡፡ እንደ “ኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት” ከሆነ “መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ/Mesfin Industrial Industry (MIE) የተባለው ድርጅት በአማራ ክልል ከሚገኘው ጣና በለስ የተቀናጀ የስኳር ልማት ፕሮጀክት እና በኦሞ ሸለቆ ከሚገኘው ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ከሚባሉ መንግስታዊ ድርጅቶች ጋር የብር 3 ቢሊዮን (162.2 ሚሊዮን ዶላር) የሚያወጣ ዋጋ ያላቸው ማሽነሪዎችን ለማቅረብ የስምምነት ውል ተፈራርሟል…“ መስፍን ኢንዱስተሪያል ኢንጅነሪንግ “ከድሬዳዋ እስከ አዲስ አበባ ለሚዘረጋው የባቡር መስመር ግንባታ ፕሮጀክት እና በተመሳሳይ መልኩ ከጅቡቲ በአፋር በኩል አድርጎ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ለሚዘረጋው የባቡር መስመር አገልግሎት የሚውሉ የባቡር ሃዲዶችን የመዘርጋት የማጠናቀቅ ስራ ያከናውናል፡፡“
እ.ኤ.አ በጁን 2011 “የጊቤ ሦስት ግድብ በቱርካና ሐይቅ ላይ ጉልህ የሆነ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል አስተማማኝ ያልሆነ የውኃ መጠን በመልቀቅ በውኃ ውስጥ ያሉ ህይወት ያላቸው ዝርያዎችን እና ከእርሱ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የስነሕይወት ስርዓቶች ለአደጋ እንደሚጥል“ እናም “በኢትዮጵያ ያለው መንግስት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በሌላ መንግስት ግዛት ውስጥ የተመለከተን ባህላዊ ቅርስ ከጉዳት ላይ ላለመጣል በጊቤ ሦስት ላይ የጀመረውን የግንባታ ስራ በአስቸኳይ እንዲያቆም“ በማለት የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት/UNESCO ከድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡
በአቶ መለስ “የልማት” ዕቅዶች በኦሞ ወንዝ ሸለቆ ግራ እና ቀኝ የሚኖረው በድህነት የሚማቅቀው እና ተከላካይ የሌለው ህዝብ ፍትሐዊነት በጎደለው መልኩ ግፍ የተፈጸመበት ሲሆን የእርሳቸው ሞራለቢስ ጓደኞች ግን የናጠጡ ሞራለቢስ ሀብታሞች ሆነዋል፡፡ እ.ኤ.አ በጃንዋሪ 2014 የታተመ አንድ የአካባቢ ምህዳር ጥናት ከሆነ “የኩራዝ ስኳር ልማት (161,285 ሄክታር መሬት ይሸፍናል ተብሎ ይገመታል) ግንባታ እና ከዚህ ጋር የተያያዙ የመሰረተ ልማት ስራዎች የስኳር ማምረቻ መሳሪያዎችን ጨምሮ እና በመንደር የማሰባሰብ ስራዎች የጊቤ ሦስት ግድብ ከመጠናቀቁ በፊት ቀደም ሲል የተጀመሩ ስራዎች ናቸው፡፡ የኩራዝ ስኳር ልማት እና ሌላ ተጨማሪ ለሸንኮራ አገዳው ልማት እርሻ አገልግሎት ምቹ የሆነ የተጠና መሬት (47,370 ሄክታር) እንደ መስኖው ሀብትን በአግባቡ የመጠቀም ባህሪ በእርግጠኝነት የኦሞ ወንዝን 50 በመቶ የውኃ ፍሰት ይፈልጋል፡፡“
የአቶ መለስ የኦሞ ወንዝ ሸለቆ “ስልጣኔ” መርሀግብር ለጓደኞቻቸው ነፋስ አመጣሽ ዘረፋ ነው፣ ሆኖም ግን የኦሞ ወንዝ ሸለቆን ኗሪ ህዝቦች ያነጠፈ እና ያደረቀ ዕቅድ ነው፡፡ የአቶ መለስ ስለኦሞ ወንዝ ሸለቆ እና ህዝብ ራዕይ “ለሳውዲ አረቢያው ባለሀብት ለአላሙዲ እና ለመስፍንኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ ጥሩ የሆነ ነገር ሁሉ በኦሞ ወንዝ ሸለቆ ህልውናቸውን መስርተው ለሚኖሩ ህዝቦችም ጥሩ ነው“ በሚል ዕይታ ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ ለዚህም ነው በኦሞ ወንዝ ሸለቆ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን/ት ለስግብግብነት እና ከሀዲነት ዓላማ መጠቀሚያ እየሆኑ ያሉት!
የኦሞን ወንዝ እና የኗሪውን ህዝብ ህልውና ለመታደግ ቀጣይ እርብርብ፣
ባለፈው ሳምንት ዓለም አቀፋዊ ወንዞች/International Rivers የተባለው ድርጅት በለቀቀው የቪዲዮ መልዕክት መሰረት ግድቡ እና የመከነው ያልታሰበበት “የልማት” ፕሮጀክት ተብሎ የቀረበው ዕቅድ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያለው ገዥው አካል እንደገና ካላሰበበት እና ካልተቋረጠ በኦሞ ወንዝ ሸለቆ የሚያስከትለው ከፍተኛ ስጋት እና በሸለቆው ግራ እና ቀኝ በሚኖረው ህዝብ እና ስነምህዳር ላይ ሊቀለበስ የማይችል አደጋ እንደሚያስከትል አስጠንቅቋል፡፡ ቪዲዮው በአሁኑ ጊዜ በኦሞ ወንዝ ሸለቆ ላይ የተጋረጠውን አደጋ በግልጽ የሚያሳይ ስለሆነ መመልከቱ ጠቃሚነት አለው፡፡
የጊቤ ሦስት ግድብ ግንባታ እና ለመስኖ ስራ ተብሎ የኦሞን ወንዝ ውኃ አቅጣጫ ማስቀየስ በደቡብ ኢትዮጵያ እና በሰሜን ኬንያ በሚኖሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ህዝቦች ህልውና ላይ ግልጽ እና ከፍተኛ የሆነ አደጋን ሊያስከትል እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የወንዙን የተፈጥሮ የውኃ ፍሰት ኡደት ማቋረጥ ማለት ከዓለም በትልቅነቱ ከፍተኛ የሆነው የቱርካና የበረሀ ሐይቅን ህልውናው አድርጎ የተመሰረተው የእርሻ፣ የግጦሽ መሬት፣ እስከ ቱርካና ሐይቅ ድረስ በወንዙ ዳርቻ የሚገኘው የዓሳ ሀብት ሁሉ እንዳለ ይወድማል፡፡ ግድቡ በታችኛው የኦሞ ሸለቆ እና በቱርካና ሐይቅ ሁለቱም በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት/UNESCO የዓለም የልዩ የባህል እና ስነምድር ቅርስነት የተመዘገቡትን ሀብቶች ሙሉ በሙሉ ያጠፋል፡፡
“የጊቤ ሦስት ግድብ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት/UNESCO በዓለም የቅርስነት መዘገብ የሰፈረውን ቦታ፣ ለ300,000 ተጨማሪ ህዝብ ህልውና መሰረት የሆነውን እና እስከ ቱርካና ሐይቅ ድረስ የተዘረጋውን እንዲሁም፣ 90 በመቶ የሚሆነውን የውኃ ፍላጎቱን የሚያገኘው ከኦሞ ወንዝ የሆነውን” የተፈጥሮ ስነምህዳ በቋፍ ላይ ሊጥለው እንደሚችል የመስኩ ባለሙያዎች ያላቸውን ስጋት ይገልጻሉ፡፡
በኦሞ ወንዝ ሸለቆ ሊደርስ የሚችለውን የአካባቢያዊ ስነምህዳር አደጋ መጠን እና በግድቡ መሰራት ምክንያት በሰው ላይ የሚደርሰውን ኪሳራ ኢትዮጵያውያን/ት ሁሉ እንዲገነዘቡት ማድረግ ከፍተኛ የሆነ ጠቀሜታ አለው፡፡ በተለይም ኢትዮጵያውያን አንባቢዎቸ የዓለም አቀፍ ወንዞች ቪዲዮንን ( የአማርኛውን ትርጉም አዚህ ይጫኑ ወይም http://www.internationalrivers.org/amharic-video-translation-omo-cascade ) አንድትመለከቱት እጠይቃለሁ፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት መምሪያ/USAID እና በኢትዮጵያ የለጋሽ ድርጅቶች እገዛ ቡድን/Donors Assistance Group (በኦሞ ወንዝ ሸለቆ የሚኖረውን ህዝብ ህልውና ከአደጋ ለመታደግ ከሚደረገው እርብርብ ጋር በተያያዘ መልኩ “ምንም ዓይነት መከራ የማይታያቸው፣ ምንም ዓይነት ስቃይ የማይሰማቸው፣ ስለምንም ዓይነት መከራ የማይናገሩ” ሆኖም ግን ለህዝብ መብት እና እድገት የቆሙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ናቸው፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት መምሪያ (USAID) እና የ26 አገሮች ስብስብ የሆነው በኢትዮጵያ የለጋሽ ድርጅቶች እገዛ ቡድን (DAG) ከኦሞ ወንዝ ሸለቆ ጋር በተያያዘ መልኩ በኗሪው ህዝብ ላይ በሚፈጸሙት የሰብአዊ መብት ድፍጠጣዎች ከሚነሱ ጥያቄዎች ጋር ላለመተባበር ጆሮ ዳባ ብለው ተቀምጠዋል፡፡ በጨዋ አነጋገር እነዚህ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚያራምዷቸው አቋሞች በሚከተለው መልክ ሊመሰሉ ይችላሉ፣ “ምንም ዓይነት መከራ አላየንም፣ ምንም ዓይነት ስቃይ አልሰማንም፣ እናም በኦሞ ወንዝ ሸለቆ ምንም ዓይነት የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ የለም፡፡“
እ.ኤ.አ ኦክቶበር 2010 በዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት በሂዩማን ራይትስ ዎች/HRW በኢትዮጵያ እርዳታ ለሰብአዊ መብት ድፍጠጣ መዋል የሚለው ዘገባ ከመውጣቱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት መምሪያ (USAID) እና በኢትዮጵያ የለጋሽ ድርጅቶች እገዛ ቡድን (DAG) በሰብአዊ መብት ድርጅቱ “በኢትዮጵያ የተስፋፋው ስልታዊ ሙስና በልማት እርዳታ“ በሚል የወጣውን ዘገባ በመካድ እንዲህ የሚል መግለጫ አውጥተው ነበር፣ “የእኛ ጥናት ምንም ዓይነት ሙስናን የሚያመላክት ስልታዊ ወይም የተስፋፋ ሙስና መረጃ አላገኘንም፡፡“ እ.ኤ.አ በ2012 የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት መምሪያ (USAID) የሚከተለውን ዘገባ አቅርቦ ነበር፣ “ደቡብ ኦሞን በጎበኘሁበት ወቅት [የሰብአዊ መብት ረገጣን] የሚያጠናክር ምንም ዓይነት መረጃ አላገኘሁም፡፡“ እ.ኤ.አ ጃኗሪ 17፣ 2014 በተጻፈ ደብዳቤ የዩኤስኤአይዲ/USAID በኢትዮጵያ የአሁኑ ተልዕኮ ዳይሬክተር ዴኒስ ዌለር ድርጅታቸው እና ሌሎችን በሚመለከት እንዲህ ብለው ነበር፣ “ድርጅቴ እና ሌሎች ለጋሽ ድርጅቶች በጋራ ሆነን በደቡብ ኦሞ ያለውን ሁኔታ ስንከታተል ነበር“ እናም “ከእነዚህ ጉዞዎች የተገኘው ዋና ግኝት የሚያመለክተው ምንም ዓይነት የተስፋፋ ወይም ስልታዊ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት ዘገባ አልተገኘም፡፡ የእኛ ምልከታዎች ቀደም ሲል በአጽንኦ ሲባሉ እና ሲነገሩ የነበሩትን…ማለትም በሰፈራ የማሰባሰብ ሂደቶች በስልታዊ እና በተስፋፋ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የታጀቡ ናቸው የሚባለውን ነገር የሚደግፉ ሆነው አልተገኙም፡፡“
የሚገርመው ነገር ግን በኦሞ ወንዝ ሸለቆ ኗሪ ህዝቦች ላይ የተፈጸሙት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንደሌሉ የዌለር ትችቶች ያጣጣሉትን ከእርሳቸው ቀደም ብለው በእርሳቸው ቦታ ከነበሩት ከቶማስ ስታል አስተያየቶች ጋር ፍጹም በተቃራኒው መሆናቸው ነው፡፡ ከኢትዮጵያ በእራሳቸው ፈቃድ ወደ ባግዳዳድ ለመሄድ ከመነሳታቸው በፊት እ.ኤ.አ በኦክቶበር 2010 ቃለመጠይቅ የተደረገላቸው ስታል እንዲህ የሚል ትኩረትን የሚስብ የእምነት ቃል ሰጥተው ነበር፣ “የፖለቲካ ተሳትፎን በሚመለከት ጥሩ ስራ አልሰራንም፡፡ በተለይም ከሁለት ዓመታት በፊት የተካሄደውን ምርጫ በሚመለከት ዴሞክራሲን ለማስፋፋት ምንም ብዙ የሰራነው ነገር የለም…ይህ ደረቅ እውነታ ተስፋ እንድንቆርጥ አድርጎናል፡፡“ ለዌለር ግን በኦሞ ወንዝ ሸለቆ ኗሪዎች ላይ የሚካሄደው የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ “ተስፋ የሚያስቆርጥበት” ምንም ዓይነት ምክንያት አይኖርም!
በኦሞ ወንዝ ሸለቆ በሚኖረው ህዝብ የሚካሄደውን የሰብአዊ መብት ጥሰት አስመልክቶ የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት መምሪያ (USAID) እና በኢትዮጵያ የለጋሽ ድርጅቶች እገዛ ቡድን (DAG) ይፋ አቋም በሁለት ሀሳቦች ሊጠቃለል ይችላል፣ 1ኛ) በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት እና የአካባቢ ስነምህዳር ጥበቃ ተሟጋች ድርጅቶች በግድ ስለማፈናቀል፣ ስለመንደር ምስረታ፣ ስለሰፈራ ፕሮግራም፣ ለህልውና የሚሆንን መሬት ስለመነጠቅ፣ ድብደባዎች፣ ግድያዎች፣ አስገድዶ መድፈር፣ እስራት፣ ማስፈራራት፣ የፖለቲካ ጭቆና እና የመንግስት እገዛ ያለማድረግ የሚወጡ ዘገባዎች ሁሉም አስመሳይ ፍብረካዎች እና ተራ ቅጥፈቶች ናቸው፡፡ 2ኛ) ዘገባዎቹ ትክክለኛ ቢሆኑም እንኳ የተዘጋጁት በተበጣጠሱ እና የሁለተኛ የመረጃ ምንጭን መሰረት አድርገው ስለሆነ “ለስልታዊ እና የተስፋፉ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣዎች“ ተጨማሪ ግብዓት ሆነዋል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት መምሪያ (USAID) በኢትዮጵያ “ስልታዊ እና የተስፋፉ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣዎች“ እንደሌሉ መካዱ ማንንም ሊያስደንቅ አይችልም፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት መምሪያ (USAID) ለዓመታት “ለስልታዊ እና የተስፋፉ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣዎች“ የሚለውን እውነታ እንደ ባዶ ሀረግ በመቁጠር ሀቅን በመሸፋፈን ከለላ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ እ.ኤ.አ በ2010 አቶ መለስ ፓርቲያቸው በ99.6 በመቶ በፓርላሜንታዊ ምርጫ ድል ተጎናጸፍኩ ብለው ሲያውጁ የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት መምሪያ (USAID) ምንም ዓይነት “ለስልታዊ እና የተስፋፉ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣዎች“ የመብት ጥሰቶች አላገኘም፣ አላየም፣ አልሰማምም፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ በጋምቤላ እና በኦጋዴን አካባቢዎች በሰው ልጅ ዕልቂት ወንጀል በፈጸሙበት ጊዜ የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት መምሪያ (USAID) የሚለውን የተከበረ መጠሪያ ስሙን እራሱ ወደ የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ዓለም አቀፍ ክህደት (USA In Denial) በሚል ስያሜ ቀይሮታል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ተሟጋቾች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የፍትሀዊነት አመጸኞች፣ የድረገጽ አዘጋጆች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በጅምላ ለእስር ወደ ዘብጥያ ሲጣሉ የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት መምሪያ (USAID) ምላሽ “ስልታዊ እና የተስፋፉ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣዎች“ የሉም የሚል ነበር፡፡ ምንም! ጭራሽ! በፍጹም! “የተስፋፉ እና ስልታዊ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣዎች“ ማለት በእርግጠኝነት ምን ማለት ነው? የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት መምሪያ (USAID) “ነጠላ ሞት አሰቃቂ ነው፣ የሚሊዮኖች ሞት ግን ለቁጥር ያህል ነው“ ለማለት ፍልጎ ነውን? ምናልባትም ለዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት መምሪያ (USAID) በኦሞ ወንዝ ሸለቆ የአንድ ሰው ሰብአዊ መብት መደፍጠጥ አሰቃቂ ነው፣ ነገር ግን በኦሞ ወንዝ ሸለቆ የሚኖረው የጠቅላላው ህዝብ ሰብአዊ መብት መደፍጠጥ ለቁጥር ነውን?!
እውነታው ግን የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት መምሪያ (USAID) እና ሌሎች እ.ኤ.አ በጃንዋሪ 2012 የኦሞን አካባቢ የጎበኙት ሰዎች በግዳጅ “በተለያዩ የታችኛው ኦሞ ማህበረሰብ የተደረጉትን የቪዲዮ ቃለመጠይቅ ቅጂዎች“ እንዲሰጣቸው ተደርጓል፡፡ እነዚህ ቅጅዎች “ለጥርጣሬ ቦታ አይሰጡም፣ ለጋሽ ድርጅቶች ለሰብአዊ መብት ጥሰት በጣም አስተማማኝ የሆነ የመጀመሪያ የመረጃ ምንጭ አድርገው ስለወሰዱት በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት መምሪያ (USAID) እና በኢትዮጵያ የለጋሽ ድርጅቶች እገዛ ቡድን (DAG) የመስክ ጉብኝ አድርገው“ ካጠናቀቁ በኋላ ጉዳዩን ችላ እንዲሉት አስችሏል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ ኮንግረስ በኦሞ ወንዝ ሸለቆ የሚኖሩ ህዝቦችን ህልውና ለመታደግ ከሚደረገው እርብርብ ጋር ተቀላቅሏል፣
እ.ኤ.አ በጁላይ 2013 ሴናተር ፓትሪክ ሊሂ (ዲ ቬርሞንት) በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ እርዳታ አስተዳደር ላይ የተወሰኑ ማብራሪያዎች በሴኔት ቢል 1372 ላይ እንዲጨመር አድርገዋል፡፡ የሊሂ ማብራሪያ “በ2014 የተጠናከረው የድርጊት መርሀግብር“ እ.ኤ.አ ጃንዋሪ 3፣ 2014 ሁለቱንም ምክር ቤቶች በመዝለል በሰነድ ላይ እንዲካተት ተደርጓል፡፡ የሰነዱ ክፍል የሆነው ቁጥር 7042 (d) የድርጊት መርሀግብሩ የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የመንግስት ጽ/ቤት “በድርጊት መርሀግብሩ ኮሚቴ አማካይነት የኢትዮጵያ መንግስት 1ኛ) የፍትህ ነጻነት፣ ሀሳብን በነጻ የመግለጽ፣ በነጻ የመደራጀት መብት፣የመሰብሰብ እና የእምነት ነጻነት፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መብቶች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ጋዜጠኞች ያለምንም መሸማቀቅ ወይም ጣልቃገብነት እና የህግ የበላይነት መንቀሳቀስ የሚችሉ መሆናቸውን፣ 2ኛ) የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እና የሰብአዊ እርዳታ በኢትዮጵያ ወደ ሶማሊ ክልል እየገቡ መጎብኘት እንዲችሉ የመፍቀድ“ የሚሉትን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በኦሞ ወንዝ የታችኛው ክፍል እና በጋምቤላ አካባቢዎች ላይ የዩናይትድ ስቴትስ “የልማት እርዳታ” እና “የኢኮኖሚ ድጋፍ ገንዘብ” ሀ) በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አስገድዶ ማስፈርን ለሚተገብሩ እንቅስቃሴዎች ሊውል እንደማይችል፣ ለ) የአካባቢ ማህበረሰቦችን ህይወት ሊለውጡ ለሚችሉ ተነሳሽነቶች ማዋል እንደሚቻል እና ሐ) ጉዳት ከመድረሱ በፊት ከማህበረሰቦች ጋር ለሚደረግ ምክክር በማለት በማያሻማ መልኩ በግልጽ ተቀምጠዋል፡፡ ህጉ የሚጠይቀው “የገንዘብ ግምጃ ቤቱ ዋና ጸሀፊ የዩናይትድ ስቴትስ የእያንዳንዱ የገንዘብ ተቋም ኃላፊ የሆኑት ሁሉ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ በኢትዮጵያ ዜጎችን ሊያፈናቅሉ ለሚችሉ ተግባራት መዋል እንደሌለበት መቃወም እንዳለበት“ ያመላክታል፡፡ “የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እና የአካባቢ ስነምህዳር ጥበቃ ድርጅቶች በኦሞ ወንዝሸለቆ እና በጋምቤላ ተፈጥሯዊ ስነምህዳር እና ለዘመናት የህልውናቸው መሰረት አድርገው በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ህዝቦች መብቶቻቸውእንዲጠበቁላቸው ሲያደርጉት የቆዩት ጥረት ፍሬ ያፈራ ይመስላል፡፡!!
የኦሞ ወንዝ ሸለቆን እና በዚያ ሰፍሮ የሚኖረውን ህዝብ ህልውና ለመታደግ በሚደረገው እርብርብ ኢትዮጵያውያን/ት የት ላይ እንገኛለን?
የይስሙላው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ስለውኃ ልማት እና ስለአካባቢ ንፅህና እውቀት እንዳላቸው ይነገራል፡፡ እንደሚቀርቡት ዘገባዎች ከሆነ በአርባ ምንጭ የውኃ ቴክኖሎጂ ተቋም “የድህረ ምረቃ የአካዳሚ ቦታ“ ይዘው እንደነበር ይነገራል፡፡ እንደዚሁም ደግሞ የእርሳቸው የዘር ግንድ “ዋናው የህብረተሰብ ምድብ ከሆነው ከደቡብ ብሄሮች ብሄር እና ብሄረሰቦች ክልል ከኦሞቲክ ማህበረሰብ“ የመጡ እንደሆኑ ይነገራል፡፡
አቶ ኃይለማርያም በኦሞ ወንዝ ሸለቆ እየተከሰተ ስላለው አካባቢያዊ የስነምህዳር ውድመት እና “ከልማት” ጋር በተያያዘ መልኩ እየደረሰ ስላለው የማህበራዊ ኪሳራ የግል እና የሙያ ፍላጎት እንዲኖራቸው ሀሳብ ማቅረብ ምክንያታዊ ነው፡፡ ሆኖም ግን አቶ ኃይለማርያም በተደጋጋሚ “አገሪቱን ወደ እድገት ለማሸጋገር የአቶ መለስን ራዕይ ለማስፈጽም ነው ያለሁት“ በማለት በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡ እናም ከዚህ መንደርደሪያ መርሀቸው በመነሳት አቶ ኃይለማርያም የኦሞ ወንዝ ሸለቆ የአካባቢ ስነምህዳር ውድመት እና በሸለቆው ውስጥ የሚኖሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ህዝቦች ህልውና አደጋ ላይ መውድቅን ከላይ ከቀረበው አስተሳሰባቸው ጋር አቆራኝቶ ማየት ይቻላል፡፡
እርግጥ ነው በዚህ ጉዳይ ላይ የማደርገው ትግል ባልጬት ድንጋይ ላይ ውሃ ማፍስስ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ሆኖም ግን አቶ ኃይለማርያም እና ገዥው አካል በኢራን አገር ከሚገኘው ኦሮሚህ/Oroumieh ከሚባለው ሐይቅ አሰቃቂ ተውኔት ትምህርት እንዲቀስሙ አጥብቄ እማጸናለሁ፡፡ ያ ሐይቅ ዕውቀትን ባላካተተ መልኩ በተፈጸመበት የግድብ እና የመስኖ ስራ ፕሮጀክት ምክንያት በ10 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የውኃው መጠን በ80 በመቶ በመቀነስ ተኮማትሯል፡፡ የኢራን አዲሱ ፕሬዚዳንት ሃሰን ሮሃኒ በሐይቁ መንጠፍ ስለደረሰው አካባቢያዊ ውድመት የሰጡት ምላሽ “ለችግሩ መፍትሄ ለመፈለግ እንዲቻል በአስቸኳይ ቡድን ማቋቋም እና በዘርፉ ክህሎት ያላቸውን ምሁራን መጋበዝ“ ነበር፡፡
አቶ ኃይለማርያም እና የስራ ጓዶቻቸው የኦሞ ወንዝ እንዲነጥፍ ሲደረግ ስለቱርካና ሐይቅ መድረቅ ወይም ደግሞ በኦሞ ወንዝ ሸለቆ ላይ ስለሚደርሰው አካባቢያዊ እና ስነምድራዊ እንዲሁም ማህበራዊ ውድመት ደንታ የላቸውም፡፡ በእብሪት እና በድንቁርና የታወሩ የገዥ አካል መሪዎች ምሁራንን እና በመስኩ ተፈላጊው ክህሎት ያላቸውን ባለሙያዎች በመጋበዝ ለተደቀነው አደጋ ዘለቄታዊ መፍትሄ ይሰጣሉ የሚል እምነት እንደሌለኝ አውቃለሁ፡፡ የገዥው አካል አመራሮች የወሰን ልክን እንደሰበረ ሁሉ በእራሳቸው የይሆናል ባዶ ተስፋ ከሚቦርቅ፣ ስለኦሞ ወንዝ ሸለቆ ጥንቃቄ እና ክብካቤ እንዲደረግ በተደጋጋሚ የሚማጸኑትን ወገኖች ከማውገዝ የዘለለ እርባና የሌለው ንግግር ከመደጋገም ውጭ የገዥው አካል አመራሮች የሚቀይሩት ነገር አይኖርም፡፡ ያም ሆነ ይህ አቶ ኃይለማርያም እና የተግባር ጓዶቻቸው በኦሞ ወንዝ ሸለቆ ላይ የሚደረገውን የአካባቢያዊ ስነምህዳር ውድመት እና የማህበራዊ ቀውስ መግታት እንዲችሉ የህግ ኃላፊነት ያለባቸው የመሆኑን እውነታ ለታሪክ ተመዝግቦ ለተተኪው ትውልድ እንዲቀመጥ ሰለፈለግሁ ነው፡፡ ከዚህም በላይ “እውነት በመቃብር ለዘላለም ተቀብራ እንደማትቀር፣ሁሉቅጥፈትም ለዘላለም በዙፋን ላይ ተሰይማ እንደማትኖር“ ከአንገት ሳይሆን ከአንጀት መገንዘብ አለባቸው፡፡
የኢትዮጵያ የዲያስፖራው ማህበረሰብ አባላትስ ምን እያደረጉ ነው?
የዲያስፖራው ማህበረሰብ ኢትዮጵያውያን/ት ወገኖቻችንን በጊቤ ሦስት ግድብ ምክንያት ህልውናቸውን ለመታደግ ከሚደረገው እርብርብ ጋር እንቀላቃለለን? በኦሞ ወንዝ ሸለቆ ለሚኖሩ ድምጽ፣ መጠለያ፣ አቅም እና ድጋፍ ለሌላቸው ወገኖቻችን በአንድ ላይ ቆመን ልንናገርላቸው አንችላለን? ከኦሞ ወንዝ ሸለቆ ህዝቦች ጋር በአንድ ላይ ቆመን እንሟገትላቸዋለን ወይስ ደግሞ አቶ መለስ ዜናዊ እንደተናገሩት “በኋላቀር ስልጣኔ” ውስጥ ያሉ በመሆናቸው ምክንያት ጆሮ ዳባ ልበስ እንላቸዋለን? ዓለም አቀፍ ወንዞችን/International Rivers፣ ሂዩማን ራይትስ ዎችን/Human Rights Watch፣ ዓለም አቀፍ የኑሮ ዋስትናን/Survival International፣ እና የአፍሪካ ሀብቶች የስራ ቡድን/the Africa Resources Working Group በመቀላቀል የኦሞን ወንዝ ሸለቆ ኗሪን ህዝብ ህልውና ለመታደግ እና በላያቸው ላይ የተጫነውን ታላቅ መርግ ከጫንቃቸው ላይ ፈንቅሎ ለማንሳት ጥረት ልናደርግ እንችላለን?
የእነዚህን ጥያቄዎች መልሶች አላውቅም፣ ሆኖም ግን ሁልጊዜ እንደማደርገው አደርጋለሁ፡ ትልቁን ሸክም ተሸክመው በመታገል ላይ ላሉት እናአቀበቱን ለመውጣት እየተፍጨረጨሩ ላሉት ውኃ እናቀብል (ከኦሞ ወንዝ ባይሆንም እንኳ)!
“እንደስብስብ ወይም ደግሞ እንደ ግለሰቦች በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ/Universal Human Rights Declaration of Human Rights እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ህግ መሰረት ለዘመናት የኖሩ የአንድ አካባቢ ቋሚ ዝርያ ያላቸው ህዝቦች ባሉበት ቦታ ተደስተው የመኖር መብት እና መሰረታዊ ነጻነቶቻቸው ተከብረውላቸው የመኖር መብት አላቸው፡፡“ (የተባበሩት መንግስታት ድንጋጌ የአንድ አካባቢ ዝርያ ያላቸው ህዝቦች 61/295)
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር! የካቲት 25 ቀን 2006 ዓ.ም
ሰላማዊ ወይስ የትጥቅ ትግል ወይስ ማንፈራጠጥ –ከፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም
የተማረ ወይም የእውቀት ባለቤት እንደሆነ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ሕዝብ ክፍል ከወያኔ ጋር የሚደረገው ትግል ሰላማዊ ይሁን ወይስ በትጥቅ ትግል የሚለውን የጦፈ ክርክር ሲያደርግ ሃያ ሁለት ዓመታት ሆነው፤ ዳኛ የሌለበት ክርክር ስለሆነ የመደማመጥ ግዴታ ታይቶበት አይታወቅም፤ ስለዚህም በሁለቱ መሀከል ያለው ልዩነት ግልጽ ሆኖ አያውቅም፤
አንድ፣ ከሁሉ በፊት ሰላማዊ ትግል በሀሳብ ደረጃ መሆኑንና የትጥቅ ትግል ደግሞ በተግባር መሆኑን ለይቶ ለመረዳት ችግር ሆኖ ቆይቶኣል፤ በሌላ አነጋገር ሰላማዊ ትግል በሀሳብ፣ በንግግር፣ በተለያዩ ሀሳብን ለማስለወጥ መቀስቀሻ በሚሆኑ መንገዶች ተቃውሞን መግለጽ ነው፤ በአንጻሩ የትጥቅ ትግል በጠመንጃ ወይም በጉልበት ያለውን የአገዛዝ ሥርዓት ለመለወጥ የሚደረግ ሙከራ ነው፤
ሁለት፣ እንዲህ ከሆነ በሰላማዊ ትግል ለሚያምኑ ሰዎች ያለምንም ጥርጥር በተለያዩ ዓላማዎችና ዘዴዎች ላይ መከራከርና ሀሳብን ማጥራት አስፈላጊ ነው፤ በሰላማዊ ትግል ተግባር አለ ቢባልም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የድጋፍ ወይም የተቃውሞ አቅዋሞችን ከማሳየት አያልፍም፤ አገዛዞች ጃዝ! ብለው ውሻና ፖሊስ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ሲለቁ የጉልበት ጥርስና ዱላ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያርፋል፤ ጉዳት ይደርሳል፤ ሰላም ይቃወሳል፤ በሕዝብና በአገዛዙ መሀከል ቂም ይጀመራል።
ሦስት፣ የትጥቅ ትግል ደግሞ በተዋረድ በሚተላለፍ ትእዛዝ የሚፈጸም ግዴታ ነው፤ በትጥቅ ትግል ጉልበተኛ ከጉልበተኛ ጋር፣ ብረት ከብረት ጋር ይጋጠማል፤ የሰው ልጅ ለእርድ ይቀርባል፤ በሕይወታቸው በልተው ያልጠገቡ ምስኪኖች ለጥቂት ሰዎች የሥልጣን ጉጉት ይታረዳሉ፤ ያለቀባሪ በጅብና በአሞራ ይበላሉ፤ ዕድለኞች የሚባሉት እጆቻቸው፣ ወይም እግሮቻቸው ተቆርጠው፣ ወይም ዓይኖቻቸው ጠፍተው፣ ወይም ከዚህ ሁሉ የባሰ ጉዳት ደርሶባቸው በሕይወት የሚቀሩት ናቸው፤ ከነዚህ በሕይወት በቀሩት የጦር ጉዳተኞችና በጦርነቱ ላይ በሞቱት መሀከል የትኛው የተሻለ አንደሆነ የሞቱት ባይናገሩም ጉዳተኞቹ ይናገራሉ፤ ‹የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ!› እያሉ።
አራት፣ ሁለቱ የትግል ስልት ዓይነቶች በባሕርይ የተለዩ ናቸው፤ አንዱ ሌላውን የሚደግፍ አይደለም፤ ሰላማዊ ትግል የትጥቅ ትግልን ለመደገፍ ሰላማዊ የሚለውን ስያሜ መጣል አለበት፤ የትጥቅ ትግልም ሰላማዊ ትግልን ለመደገፍ ትጥቅ የሚለውን ስያሜ መተው አለበት፤ ሰላማዊ ትግልና የትጥቅ ትግል አራማጆች ድል ቢያደርጉ ማን ወንበሩ ላይ እንደሚወጣ ሳይታለም የተፈታ ነው፤ ጠመንጃ የያዘው ሥልጣኑን ሲይዝ ሰላማዊ ትግሉ ይቀጥላል! ያውም ከተፈቀደለት!
በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ አርበኞች ሳይቀሩ በሩ ተዘግቶባቸው ለደጅ ጥናት እንደተዳረጉ አይተናል፤ መልኩን ለወጥ ቢያደርግም ደርግን ከተፋለሙት ውስጥ በአዲስ አበባና በአስመራ ወንበሮች ላይ ሲወጡ የተሸነፉት ወይ ለወያኔ ገብረው ሎሌነት ገቡ፤ ወይም በአሜሪካ መሽገው ያቅራራሉ፤ ዘመኑ እንዳለፈባቸውም ገና አልተረዱም።
አምስት፣ ሰላማዊ ትግልና የትጥቅ ትግል ሁለቱም ብርቱ ቃል ኪዳንን ይጠይቃሉ፤የቃል ኪዳናቸው ልዩነት አንዱ እስከሞት ለመታገል፣ ሌላው ደግሞ እስከመግደልና እስከመሞት ለመታገል መሆኑ ነው፤ ለሰላማዊው ትግል ከፍተኛ መንፈሳዊ ወኔ የሚያጎናጽፈው ለመግደል ያለው ተቃውሞ ነው፤ ሕይወትን ለማልማት ሕይወትን መቅጠፍ የአስተሳሰብም የመንፈስም ጉድፍ ያለበት ሥራ ነው።
የሰላማዊ ትግል ዋናውና ቀጥተኛው ተልእኮ ሕዝብን ለሥልጣን ባለቤትነት ማብቃት ነው፤ ሥልጣንን ለመያዝ አይደለም፤ ስለዚህም ኢላማው ሕዝብ ነው፤ በሥልጣን ወንበሩ ላይ ያሉት የሰላማዊ ትግሉን የሚቃወሙት በሕዝብ ዘንድ ተሰሚነትና ተቀባይነት እንዳያገኝ ለማድረግ ነው፤ ሰላማዊ ትግሉ የሚያተኩረው በሕዝቡ ጆሮ፣ አእምሮና ልብ ላይ ነው፤ አገዛዙ በበኩሉ ጸጥ-ለጥ ብሎ የሚገዛለት ሕዝብ እውቀቱ ዳብሮ፣ መብቶቹን ሁሉ ተገንዝቦ፣ በሕግ ለሕግ እንጂ ለሰው አልገዛም በማለት ልቡ እንዳይሸፍት አፈናውንና ማነቆውን በማጠናከር እያደነቆረ ለመግዛት ይፈልጋል፤ የሰብአዊ መብቶችን የሚያስተምሩና በአገዛዙ አካላት የሚፈጸሙትን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን የሚያጋልጡ ድርጅቶችን ማዳከም ወይም ማጥፋት ለአገዛዙ አስፈላጊ የሚሆነው ለዚህ ነው፤ ኢሳት የሚባለው የቴሌቪዥንና የራድዮ ፐሮግራም ለወያኔ የውስጥ እግር እሳት የሆነበት ለዚህ ነው፡፡ በሰውነት ደረጃ ሕዝቡ መብቶቹን ሁሉ እንዲያውቅና እንዲረዳ ማድረግ፣
በዜግነት ደረጃ ሕዝቡ ለሥልጣን የሚያበቃውን የዜግነትና የፖሊቲካ መብቶች እንዲያውቅና እንዲረዳ ማድረግ፣ ሕዝቡ የሰውነትና የዜግነት መብቶቹን ተገንዝቦ በአገዛዝ ስር አልተዳደርም የማለት መንፈሳዊ እምቢተኛነት እንዲያድርበት ማድረግ፣ በግልጽ ጭቆናን የሚጠላና ለመብቶቹና ለነጻነቱ በቆራጥነት የሚቆም ሕዝብ እንዲፈጠር ማበረታታት፣ መብቶቹንና የሥልጣን ባለቤትነቱን የተረዳና ከጭቆና ጋር የተጣላ ሕዝብ በፖሊቲካ መስመር ቡድኖችን እየፈጠረ እንዲደራጅ ማድረግ፣ ያወቀና የነቃ፣ በፖሊቲካ መስመር የተደራጀና ማናቸውንም ዓይነት ጭቆና የሚጠላ ሕዝብ ለማንም ጉልበተኛ የማይንበረከክ ሕዝባዊ ኃይል እንዲሆን መጣር፣
የትጥቅ ትግል ዋናውና ቀጥተኛው ተልእኮ በሥልጣን ላይ ያለውን አገዛዝ አውርዶ ወንበሩን ለራሱ ለመውሰድ ነው፤ ይህንን ሲያደርግ ሕዝቡን ወደጎን ትቶ ወይም ዘልሎ ነው፤ ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ በጠመንጃ ሥልጣን የሚይዙ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥልጣኑን ለሕዝብ እናስረክባለን፤ ትክክለኛ ምርጫ እናካሂዳለን በማለት ሕዝቡን በተስፋና በጠመንጃ ይዞ ነው፤ ነገር ግን ሥልጣንን ሕዝብ ለፈቀደው አስረክበው ከቤተ መንግሥት ሲወጡ አናይም፤ ሲሸሹ ወይም ሬሳቸው ሲወጣ እንጂ።
ብዙውን ጊዜ የማይታሰብ ወይም ብዙዎች የሚዘነጉት የሁለቱ ትግሎች የገንዘብ ወጪ በጣም ከፍተኛ ልዩነት ያለው መሆኑን ነው፤ ሰላማዊ ትግል በሕይወትም፣ በንብረትም፣ በመሣሪያም በዝግጅትም የሚያስከፍለው ዋጋ ከትጥቅ ትግል ጋር ሲወዳደር በጣም አነስተኛ ነው።
ስለዚህም በሁለቱ በተለያዩ ስልቶች አራማጆች መሀከል የሚደረግ ክርክር ምን ዓይነት ነው? የሰላማዊው የመጀመሪያ ደረጃ ኢላማው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፤ የትጥቅ ትግል የመጀመሪያ ደረጃ ኢላማው የወያኔ አገዛዝ ነው፤ በሌላ አነጋገር በሰላማዊ ትግል ሕዝቡ በሰላማዊ ትግል ትንሽም ቢሆን የነጻነትን አድማስ ለማስፋት እንዲችል ድፍረትን በማስተማር በኩል የማይናቅ አስተዋጽኦ ቢያደርግም አገዛዙን የመነቅነቅ ኃይል ገና አላዳበረም፤ አንድም ውጤት አላሳየም፤ የትጥቅ ትግሉ ከፉከራና ከሽለላ እስካሁንም አልወጣም፤ የሰላማዊ ትግል ዓላማ ሕዝቡ መብቶቹን እንዲያውቅ ለማንቃትና ለመብቶቹ እንዲታገል የሚያስችለውን ብቃት ለማስጨበጥ ነው፤ ስለዚህም ዘዴው በሕዝቡ ላይ ነው፤ የትጥቅ ትግሉ ዘዴ አገዛዙን በጉልበት ገልብጦ በዚያው ባልተለወጠ ሕዝብ ላይ ሌላ አገዛዝ ለመመሥረት ነው።
በኢትዮጵያ ለውጥ እናመጣለን የሚሉ ሁሉ የቆሙበትንና የቆሙለትን ዓላማና ዘዴ በግልጽ ተገንዝበው ካልተሰለፉ በተንፈራጠጠ አስተሳሰብ የተባበረ ተግባር ሊገኝ አይችልም።
ኦኖሌ፡-ሀርከ-ሙራ
እንዲህ ነው በ1860ዎቹ ንጉስ ሚኒሊክ ገና አፄ ሳይባሉ አፄ ቴዎድሮስ ሸዋን ባስገበሩበት ወቅት የተወሰኑ የጎንደሬ ሰራዊት አባላት በሸዋ እንዲቀሩ ተደርጎ ነበር፡፡ እነዚህ የጎንደርና የወሎ ፈረሰኞች ከንጉሥ ሣህለሥላሴ ዘምን ጀምሮ በአርሲና በጨርጨር ሰፍረው ነበር፡፡ አፄ ምኒሊክ ብዙውን ጊዜ በአርሲና በሐረርጌ በማቅናት ዘመቻው በኦሮሞ ላይ ጭፍጨፋ እንደፈፀሙ ተደርጎ ተወርቷል ብዙ ተብሏል፡፡
መራሩ ሀቅ ግን ይህ ነው፡፡
ኦኖሌ፡-ሀርከ-ሙራ
ከማርቆስ ወልደዮሀንስ ዶ/ር
drmarkjohnson@yahoo.com
በአኖሌ የተቆረጠው የማን እጅ ነው? በሂጦሳ አኖሌ የአንድ ኩሩ ኢትዮጵያዊ አርበኛ እጅ ተቆርጧል፡፡ ይህ ሰው ልጅ አበበ ኮላሴ ብሩ ይባላል፡፡ታሪክ ፀሃፊዎቹ ተክለፃዲቅ መኩሪያና ብላቴን ጌታ ኀሩይ ወልደሥላሴ በታሪክ መዛግብቶቻቸው የልጅ አበበን ስም በመጥቀስ የአባታቸውን ስም ለመጥቀስ ያልፈለጉበት ዐብይ ምክንያት ቤተሰቡ በሐረርጌና በሸዋ በነበረው ከፍተኛ ተሰሚነት ነው፡፡ ፊታውራሪ ተክለሃዋሪያት ኃይለሥላሴን ለማንገስ በቅድሚያ የጎንደሬውን ጦር ማሳመን ያስፈልጋል እንዳሉት ለልጅ አበበ አባት ሰም አለመጠቀስ ዋነኛው ምክንያት ፊታውራሪ ኮላሴ ብሩ ይመሩት የነበረው የጎንደሬ ጦር የነበረው ተዳማጭነት እንዲሁም በፍርድ አሰጣጡ ላይ ፍትሐ ነገስቱ በሚያዘው መሰረት ንጉስን ለመግደል መሞከራቸው ይቅርታ የማያሰጥ ወንጀል በመሆኑ ቤተሰቡም እንደዘመኑ ህግ በማመኑ ነው፡፡
በዐፄ ምኒሊክ አጎት በመርዕድ አዝማች ኃይሌ በተጠነሰሰው መፈንቅለ መንግስት ጎንደሬው ደጃዝማች መሸሻ ወርቄን ጨምሮ ከመቅደላው እስር ቤት አፄ ምኒልክን እንዲያመልጡ የረዱ የምኒሊክ ዘመን ታላላቅ ሰዎች ምኒሊክን በመርዕድ አዝማች ኃይሌ ለመተካት የወጠኑት ውጥን ከሸፈ፡፡ ልጅ አበበ ኮላሴ የተመረጠው ለአፄ ምኒልክ ከነበረው ቅርበት የተነሣ ምኒልክን ከደርብ ላይ ገፍትሮ በመጣል ለመግደል ስምምነት አድርጎ ነው፡፡ ልጅ አበበ ኮላሴ የስሜኑ ራስ ውቤ እና የእቴጌ ጣይቱ የስጋ ዘመድ ነበረ ለእቴጌይቱ ከነበረው ቀረቤታና በንጉስ ምኒልክና በእቴጌ ጣይቱ መሃከል በሰተመጨረሻ ጋብቻ እንዲፈጸም ምክንያት የሆኑ የሰሜኑና የሸዋን መሳፍንቶች በማቀራረብ ረገድ ክፈተኛ ሚና የነበራቸው ልጅ አበበ ኮላሴ በእልፈኝ አስከልካይነታቸው ከእራሳቸው የተሻለ ምኒልክን የሚቀርብ ባለመገኘቱ የዐፄ ምኒልክ አጎት በሆኑት በመርእድ አዝማች ኃይሌ አማካኝነት ተመለመሉ፡፡ ልጅ አበበ ኮላሴ ወደ ሸዋ የመጣው ምኒሊክ ገና የሸዋ ንጉስ በነበሩበት በ1860 ዎቹ አጋማሽ ነው፡፡ ከመቅደላው ጦርነት በኋላ አባታቸው ሰራዊታቸውን ይዘው ወደ ምኒልክ በመግባታቸው የጎንደሬ የላስቴ እንዲሁም የሸዋ ሰራዊት እጅግ የተከበረ ነበር፡፡በዚህ ሰራዊት ውስጥ ፊታውራሪ ዋዠቁ እንዲሁም የአቶ አዲሱ ለገሰ አያት ቀኛአዝማች ቀረኩራት ነበሩበት፡፤ ይህ ጦር የጎንደሬ ጦር በመባል የሚታወቅና በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች አገርን በማቅናት ረገድ ተወርዋሪ ኃይል የነበረ የሰራዊት ክፍል ነው፡፡
ይህ ታላቅ ሰራዊት በመጀመሪያ በእንጦጦ ቀጥሎም አሁን ግቢ በሚባለው ስፍራ ከከተመ በኋላ ምኒልክ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በአደረጉት እንቅስቃሴ ከፍተኛና ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡በእነዚህ የተለያዩ ዘመቻዎች አንቱ የተባለ ክንውን ከፈፀሙ በኋላ ስማቸውን የታሪክ መዝገብ ሳያየው ካለፈ ቤተሰቦች ውስጥ ቤተ-ኮላሴ ወይም ወረ-ኮላሴ የሚባሉት ቤተሰቦች ዋንኞቹ ናቸው፡፡
በሶዶ ፣በቤተ ጉራጌ ፣በአርሲና ባሌ ፣እንዲሁም በሐረርጌ ወደ ማዕከላዊ መንግሰት መምጣት የዚህ ቤተሰብ ሚና ቀላል አልነበረም፡፡ ምስጋና ለፈታውራሪ ተክለሐዋሪያት ኦቶ ባዮግራፊ ወደ አድዋ የዘመተው አብዛኛው የራስ መኮንን ጦር በበላይነት የሚመራው በወንድማማቾቹ በፊታውራ ኮላሴ እና በፊታውራሪ አለሙ የጎንደሬ ሰራዊት መሆኑ በአፅንኦት የተጠቀሰ ቢሆንም ይህንን ታሪክ ፈልፍሎ በማውጣት ረገድ የታሪክ ምሁራኖቹ ከተወሰነ ስፍራ ላይ በመወሰናቸው ዛሬ ኦነግና አህዴድ ለሚያናፋሱት አዳዲስ የፈጠራ ወሬዎች ህዝቡ ሰለባ ሆኗል፡፡በአድዋ ጦርነት የሐረርጌን ሰራዊት አድዋ ድረስ ይዘው በመሄድ የተዋጉት ፊታውራሪ ኮላሴ ብሩና ቤተሰባቸው ወደ አድዋ የዘመቱት ልጃቸው ልጅ አበበ ኮላሴ በምኒሊክ አጎት በተጠነሰሰው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ እጅና እግር ካጡ ከአስራ አምስት ዓመት በኋላ ነው፡፡ የልጅ አበበ እጅና እግር መቆረጥ የፈታውራሪ ኮላሴ ብሩ ና ልጆቻው እንዲሁም ከጎንደርና ላሰታ ተሰባስቦ የተከተላቸውን ሰራዊት በአገሩ ላይ እንዲደራደር አላደረገውም፡፡ በአድዋ ጦርነት በራስ መኮንን መሪነት ታላላቅ ጀብዱዎችን ፈፅመው አገራቸውን ኢትዮጵያን አኩርተዋል፡፡ በአፄ ምኒልክ ይህንን መሰል ቅጣት ለመቀጣት የመጀመሪያው ቤተሰብ ኦሮሞ ወይም ትግሬ ሳይሆን የአማራ ልጅ ነፍጠኛ ነው፡፡ ይህም የተፈፀመው በልጅ አበበ ኮላሴ ላይ ነው፡፡ፊታውራሪ ኮላሴ ብሩ ከእረፍታቸው በኋላ የደጃዝማችነት ማእረግ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ደጃዝማች ኮላሴ ብሩ(ሐረርና የአውራጃዋ ግዛት የሚለውን በ1950ዎቹ ይታተም የነበረ መጽሔት) ማየት በቂ ነው፡፡
በልጅ አበበ ኮላሴ ላይ የደረሰውን ቅጣት በአሁን ዘመንና መነፅር አይቶ ምኒልክ ትክክል ሰርተዋል አልሰሩም ለማለት በወቅቱ የነበረውን የዕውቀት የንቃተ ህሊና ደረጃና የፍትህ ስርዓት አንፃር መገምገሙ ተገቢ ነው፡፡ በተመሳሳይ ዘመን በአውሮፓ ጊሎቲን የአንገት መቁረጫ ማሽን ተዘጋጅቶ አንገት የሚቆረጥበት ዘመን ጋር ብናስተያየው በእኛም ሀገር ይፈፀም የነበረው ተመሳሳይ ድርጊት መሆኑን ማስተዋል ይገባል፡፡እንደአጋጣሚ በአኖሌ ጦርነት አልተደረገም፡፡ ጥንትም ይሁን ዛሬ አኖሌ ከተማ ሳትሆን ጥቂት ባለርሰቶች ይኖሩባት የነበረች ጠፍ መሬት ነበረች፡፡ መቶ ሃያም ሆነ መቶ ሰላሳ ዓመት ሩቅ አይደለም፡፡ በጣም ያልራቀ ዘመን በመሆኑም ድርጊቱ የተፈጸመባቸው ቤተ-ኮላሴዎች ጦር ሰብቀው አገር ተሳድበው አልኖሩም፡፡ ስርዓቱን እንዲሁም የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በማስከበር ተፋለሙ እንጂ፡- ከእረፍታቸው በኋላ የደጃዝማችነት ማዕረግ የተሰጣቸው የኮላሴ ብሩ ቤተሰቦች ንጉሰ ነገስቱ በጄነቭ የተባበሩት መንግስታት ስብሰባ ሲሄዱ አገሪቱን አደራ ብለው ከተሰናበቷቸው ውስጥ ናቸው፡፡ ፊታውራሪ ጓንጉል ኮላሴ በአኔሌይ ከኢጣሊያ ወታደሮች ጋር ተፋልመው ያገኙትን ውጤት በማድነቅ ወደ ጄኔቫ ያመሩት አፄ ኃይለስላሴ ከስደት መልስ እነዚህን የታሪክ ባለውለታ ቤተሰቦች አላኮሯቸውም ታሪካቸው ደምቆና ጎልቶ እንዲወጣም አላደረጉም፡፡ ይህ ታሪክን አድበስብሶ ማለፍ አዳዲስ የፈጠራ ታሪኮች እንዲፈበረኩና በዚህም ብዙዎች ዕዳ ከፋይ የሆኑበት ሁኔታ ታይቷል፡፡የምጣዱ ሳለ የዕንቅቡ ተንጣጣ እንዲሉ እጅና እግር የገበረው የአማራ ብሔር ነፍጠኛው ሆኖ ሳለ በኢትዮጵያ የጦርነት ታሪክ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ የማይታወቅ የክርስቲያን ጦር ጡት ቆረጠ የሚል ማስረጃ የማይቀርብበት የሐሰት ታሪክ ትንታኔዎችን በማቅረብ በተራ አሉባልታና በሬ ወለደ የፈጠራ ታሪክ ሕዝብን መንዳት መሞከር ታላቅ ወንጀል ነው፡፡ታቦት ይዞ የሚዘምት ሰራዊት ሴትን በጥፊ መምታት እንኳን እንደወንጀል የሚመለከት ማህበረሰብ ምን ለማግኘት ምን ለማትረፍ የሴት ጡት ይቆርጣል፡፡ የአበበ ኮላሴን እጅና እግር መቆረጥና መቀጣት እንዲሁም የኤርትራ ባንዳ ሰራዊትን እጅና እግር መቆረጥ የተረኩ የታሪክ ጸሐፍት ማንን ፈርተው ለምን ብለው ይህንን ታሪክ ሳይዘግቡት ቀሩ ቢባል፡ መልሱ ድርጊቱ ፈጽሞ ያልተካሄደ በመሆኑ ብቻ ነው፡፡በጣም የሚያኮራውና የሚያስደስተው ቤተ-ኮላሴዎች የፖለቲካ ትርፍም ሆነ ሌላ ነገር ለማግኘት በየትኛውም ስርዓትም ሆነ ዘመን ይህንን ታሪክ አጉልተው አልተናገሩም አልዋሹም አልቀጠፉም፡፡ኢትዮጵያን ግን ጠበቁ፡፡ ሞቱላት ደሙላት፡፡ይህ ታሪክ የኦህዴድ ታሪክ የኦነግ ታሪክ ቢሆን ስንት ዘርፍና ቅጥያ ወጥቶለት ሌላ ሃውልት በቆመ ነበር፡፡ይህ ታሪክ የአንድ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ ታሪክ ነው፡፡
ልጅ አበበ የተቀጣበት ስፍራ የአሁኗ አኖሌ ነበረች፡ በስፍራው የነበሩ ሰዎች ልጅ አበበ ኮላሴን በኦሮሚኛ ሃርከ ሙራ -እጀ ቆራጣ ለማለት የሰጡት ስም ዛሬ ከበሮ እየተደለቀበት ያለ በተለይም ድህረ ኢህአዴግ ሀርመ ሙራ የምትል ቅጥያ የኦነግና የኦህዴድ ካድሬዎች በማከላቸው ጡት ጭምር ተቆርጧል አስብሎ በሀሰት የፖለቲካ ትርፍ ፕሮፓጋንዳና ሃውልት በመስራት በሚለዮኞች የሚቆጠር ብር ቢዝነስ በሚያጧጡፉ ግለሰቦች ሀሰት እውነት ተደርጎ መዘገቡ አሳፋሪ ነው፡፡ እውነት ነው የልጅ አበበ ኮላሴ ቀኝ እጅና ግራ እግር የተቆረጠው በንጉሳዊ ትእዛዝ ነው ፈፃሚዎቹም ከአሁኗ እንጦጦ ወደ አርሲ ሄደው የሰፈሩት ወረ-ሂጦመሌ በሚባል የሚታወቁት የኦሮሞ ጎሳዎች ነው፡፡ የተገላቢጦሽ እንዲሉ በፈሰሰው የነፍጠኛው የልጅ አበበ ኮላሴ ደም ዛሬ ከፍተኛ የፖለቲካ ትርፍ ለማትረፍ የሚንቀሳቀሱ ዋሾዎችን ማየት አሳፋሪ ከመሆኑም በላይ መንግስት ጉዳዩን በዝምታ መመልከቱ አሳሳቢም ጭምር ነው፡፡መንግስት በዚህ ሃውልት መቆም አምንበታለሁ ካለም በበደኖ በአሶሳ በአርሲ ነገሌ በአርባጉጉ በጂማ አንገታቸው ለተቀላ ደማቸው እንደጅረት ለፈሰሰ ሰማዕታት ሃውልት የማቆም ግዴታ ይኖርበታል፡፡
የፊታውራሪ ኮላሴ ቤተሰቦች በሁለተኛው የኢትዮ ኢጣሊያ ወረራ ወቅትም ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገዋል፡፡
ፊታውራሪ ጓንጉል ኮላሴና ወንድማቸው ኃይለማሪያም ኮላሴ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ታንክ የማረኩ መሆናቸውን ጳውሎስ ኞኞ አልተወራላቸውም እንጂ በማለት በኢትዮጵያና በኢጣሊያ ጦርነት ወቅት ስለፈፀሙት ተጋድሎ በመጽሐፉ ዘግቧል፡
ሻምበል መብራቴ ኮላሴ የጥቁር አንበሳ ሰራዊት አባል ማይጨው በጀግንነት ወድቀዋል ተክለፃዲቅ መኩሪያ ዘግበውታል
የይፍቱ ስራ ኮላሴ ልጅ ፊታውራሪ ነገደ ዘገየ በጎንደርና በሐረር ከኢጣሊያ ጋር በመዋጋት ከፍተኛ ተጋድሎ ፈጽመዋል፡፡ ልጅ አበበ ኮላሴ በፈጸሙት ስህትት ተቀጥተዋል፡፡ እጅና እግራቸው ከተቆረጠበት አርሲ አኖሌ በተቆረጠ እጃቸው አንበሳ ገድለው ለአፄ ምኒልክ የአንበሳ ጎፈር ልከዋል፡፡ ምኒልክም የእጄን በእጄ በማለት መፀፀታቸው አሁን ድረስ የሚወራ ታሪክ ነው፡፡ እናም በአማራው ላይ ለተፈፀመው ድርጊት በኦሮሞ ላይ እንደተፈፀመ ተደርጎ በፈጠራ ድርሳን የሚወራው ወሬና ሕዝብን ከሕዝብ የማለያየት እንቅስቃሴ በአስቸኳይ መቆም አለበት፡፡
[ያ ትውልድ] የኢትዮጵያ ሴቶች፤ የትግል እመቤቶች (ማርች 8 ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን 103ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ)
ማርች 8 ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን፤ ሴቶች በፆታቸው ምክንያት የሚደርስባቸውን በደል አድልዎና ጭቆና ለማስቀቅ፣ ለማስወገድ ከአደረጉት ትግል ጋር በመያያዝ የሚታሰብ፣ የሚከበር ዓለም አቀፋዊ በዓል ነው። እ.አ.አ በ1911 መከበር የጀመረው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ማርች 8 (የካቲት 29 ቀን,
2006 ዓ.ም.) እነሆ 103 ዓመቱ። ዕለቱ ዓለም በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መድረኳ ሴቶችን እኩል ታሳትፍ ዘንድ፣ ጾታን መሰረት ያድረጉ መድልዎች ይወገዱ ዘንድ መከበር የጀመረው ዓለም አቀፍ የሴቶችን ቀን ስናከብር ሀገራችን የሴቶችን ጥያቄ መልሳለችን? እንድንዳሥ ግድ ይለናል።
[የዓለማየሁ አቶምሳ ቀብር ጉዳይ] እነዚህ ሰዎች የሚናገሩትንም አያውቁም
ሲሳይ አባተ (ከአዲስ አበባ)
`ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለትግሉ ሰማዕታት` (ጠቅላይ አሽከር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከደቂቃዎች በፊት የተናገረው)
ታጋይ አለማየሁ አቶምሳ
ጓድ አለማየሁ አቶምሳ
ለትግሉ መስዋእት የሆኑት ታጋይ አለማየሁ አቶምሳ
(የማን አስከሬን ተሸፍኖ የማን ሊገለጥ?)
የሕወሓት መንግሥት በአገዛዝ ዘመኑ ከተሳኩለት ነገሮች አንዱና ዋነኛው የቀብር ሥነ ሥርዓቶችን ባማረ ሁኔታ ማከናወን ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት ከተከናወኑ የቀብር ሥነ ሥርዓቶች ውስጥ ለምሳሌ የሀየሎም አርአያ፣ የጭራቁ መለስ ዜናዊና የትዳር አፋቹ የወንበዴው ጳጳስ የጳውሎስ ደማቅ የልቅሶና የቀብር ሥነ ሥርዓቶች በዋቢነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የጥላሁን ገሠሠን ያላካተትኩት የሕዝብና የሀገር ልቅሶና ሀዘን ስለነበረ ነው፡፡ እንጂ በሀገር ደረጃ ካየነው የጥላሁንን የመሰለ ደማቅ ልባዊ ሀዘን የተገለጸበት ልቅሶ ታይቶ የሚታወቅ አይመስለኝም፡፡ በጥላሁን ቀብር ሕዝብ በዐዋጅና በማባበያ ወጥቶ እንዲለቀስ አልተደረገም፡፡ በጥላሁን ቀብር የሀገር ሀብት ከካዝና እየተመዘረጠ ከናቴራና ኮፍያ እየተገዛ ፖስተርም እየተለጠፈ፣ የውሎ አበልም እየተከፈለ በመቶ ሚሊዮኖች የሚገመት ገንዘብና ማቴሪያል እንዲባክን አልተደረገም፡፡ በጥላሁን ቀብር ሕዝብ በግዳጅ እንዲያለቅስና ከሥራ እየቀረ ከአንጀቱ ሳይሆን ከአንገቱ እንዲያላዝን አልተደረገም፡፡ የሰሜን ኮርያን ልቅሶ የሚያስንቅ የግዳጅ ልቅሶ ያዬነው በመለስ ዜናዊ ቀብር ነው – በሀፍረት የለሹ ወያኔ አስገዳጅነት፡፡
ዛሬ ደግሞ ግራ የተጋባ ልቅሶ እያየን ነው፡፡ የሰዎች መሞት በውነቱ ያሳዝናል፡፡ አቶ አለማየሁ አቶምሳ ሞቷል – በሰውነቱ ከልብ እናዝናለን፡፡ በሆዳምነቱና ከታሪካዊ ጠላቶቹ ጋር ተባብሮ ለሀገር መቀበር በመታገሉም እንዲሁ እናዝንበታለን፤ ለማንኛውም ፈጣሪ ነፍሱን ይማር – አፈሩንም ገለባ ያድርግለት፡፡ ለልጆቹና መላ ቤተሰቡ አጽናኝ መላእክትን ይዘዝላቸው፡፡ በመሠረቱ ሰውዬው የሞተው ዛሬ አይደለም፡፡ የሞተው የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ናዝሬት ውስጥ ታካሄደ በተባለ የኦህዴድ ጉባኤ ላይ ጓደኞቹ ይሁኑ ሌላ ወገን በሚጠጣው ይሁን በሚበላው ነገር ላይ መርዝ በሰጡት ጊዜ ነው፡፡ ወያኔ ራሱ ገድሎ ሙሾ ማውረድን የተካነበት በመሆኑ ራሱ የገደለውን አለማየሁ በድምቀት እየሸኘው ነው፡፡ ዕንቆቅልሹ ወያኔ ክንፈ የሚባለውን የደህንነት ኃላፊውን ባስገደለበት ወቅት እንዴት በመሰለ ሁኔታ ቁንጮው ጭራቅ መለስ እያለቀሰ እንደሸኘው የምናስታውሰው ነው፡፡ እስስቶች ናቸው፡፡
የዛሬው ግራ አጋቢ የልቅሶ ሥነ ሥርዓት ምን ይመስላል? ሬሣው በዓለም እንደሚታወቀው ከአንገቱ በላይ እንዲታይ አልተደረገም፡፡ በኔ ግምት ይህ ያልሆነበት ምክንያት የፈራረሰው የመለስ አስከሬን ተሸፍኖ እንደተሸኘ ሁሉ ይህንንም ሰውዬ የእርሱ መናጆ በማድረግ የመለስ አስከሬን ሁኔታ እንዳይታወስና መነጋገሪያ እንዳይሆን ነው፡፡ አስከሬንን አለማሳየት ባህላቸው ነው እንዲባልና የመለስን መፈራረስ ለማስረሳት የፈለጉ ይመስለኛል፡፡ እንጂ የአለማየሁ ሰውነት እንደመለስ የፈራረስ አይመስለኝም፡፡ አንደኛ ነገር ይህ ሰው የሞተው ሰሞኑን ስብሰባ እያካሄደ በነበረበት ጊዜ ድንገት ተስለምልሞ በመውደቅና ከዚያም ወዲያውኑ ወደውጪ ተልኮ የህክምና ርዳታ ተደርጎለት ነው፡፡ ስለዚህ ጭንቅላቱም ሆነ ፊቱ ገና ‹ፍረሽ› ነው፡፡ ሁለተኛ ከሞተም በኋላ እንደመለስ ለወራት አልተደበቀም፤ የተፋጠነ የቀብር ሥነ ሥርዓት ነው እየተደረገለት ያለው፡፡ በዚህች በቀብር ሥርዓት እንኳን ከሕወሓት ውጪ ያሉ ሌሎች ወገኖች መወሰን አልቻሉም ማለት ነው፡፡
ይህ ሀዘን ክልላዊ እንጂ ፌዴራላዊ አይደለም፡፡ የፕሮቶኮል ጉዳይ ያነጋግራል፡፡ ባንዴራ ዝቅ ተደርጎ መውለብለብ ያለበት ሰውዬው ይመራው ነበር በሚባለው “ክልላዊ መንግሥት” እንጂ በመላዋ ኢትዮጵያ መሆን አልነበረበትም፡፡ ስህተት ነው፡፡ አወሳሰኑ ራሱም ስህተት ነው፡፡ አንድ ግለሰብ ወይም የጥቂት ግለሰቦች ውሳኔ ይመስላል፡፡ የተሰበሰበ የፓርላማ ጉባኤ ሳይኖር ጥቂት ሽፍቶች እንደፈለጉ የሚያዙበትና የሚናዝዙበት መንግሥት ያለን ለመሆናችን አንደኛው ዋቢ ነው፡፡ ለማስመሰልም እንኳን አልቻሉበትም፡፡ ለወትሮው የማስመሰል ሁኔታ ይታይ ነበር፤ የዐይን ጥቅሻ ብቻ እያዬ የሚያጨበጭብና በረጃጅም ዲስኩሮች ወቅት ደግሞ እያዛጋና እያንጎላጀ እንቅልፉን የሚለጥጥ ፓርላማ ያለን እኛ ብቻ ነን – ዕድሜ ለወያኔ፡፡ አሁን አሁን የነበረው ጥቂት የማስመሰል ትያትር በጭራሽ ጠፍቷል፡፡ ከአንድ ጎሬ ውስጥ የተደበቀ ሥውር መንግሥት ሳይኖር አይቀርም፡፡ ያ ሥውር ወያኔዊ ኃይል የመንግሥት ወንበሮች ላይ በጎለታቸው እነኃይለማርያምንና ተሾመን የመሳሰሉ ሆዳሞች አማካይነት በስልክ በሚተላለፍ ቀጥተኛ ትዕዛዝ ሀገሪቱን እንደፈለገ መንዳቱን ቀጥሏል፡፡
ሬሣው መልበስ ያለበት የክልሉን ባንዴራ መሆን ሲገባው በአንድ በኩል የወያኔን የኢትዮጵያ ባዴራ አልብሰው በሌላ በኩል ደግሞ ኦሮምያ የሚባለውን አዲስ ወያኔ ሠራሽ ሀገር ባንዴራ አልብሰውታል፡፡ አስከሬኑ የሚመስለው አስከሬን ሳይሆን የተለያዩ ቀለማት ባላቸው ጨርቃ ጨርቆች ያሸበረቀ የጠንቋይ ቤት የመጠንቆያ ክፍል ነው፡፡ ቋንቋቸው ደግሞ የበለጠ ግራ ያጋባል፡፡
እነዚህ ሰዎች የቃላት አጠቃቀማቸው ራሱ አስገራሚ ነው፡፡ ጭራቁ መለስ ሲሞት ደደቧ ሚስቱ “መለስ ተሰዋ” ብላ በሀዘናችን መሃል አሳቀችን፡፡ አንድ ሰው ተሰዋ የሚባለው በጦርነት ላይ ሲሞት ወይም ለግዳጅ በሄደበት ሳይመለስ ሲቀርና ሕይወቱ በዚያው ሲያልፍ ነው፡፡ እንጂ በሰላም ሀገር ታሞ የሞተን ሰው ተሰዋ ማለት የቋንቋ ችግርን ከማሳየቱ በስተቀር ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ በውነቱ ማይምነት ነው፡፡ በሌላ ወገንም የመንግሥት ሥልጣን ከያዙ ከ23 ዓመታት በኋላ “ታጋይ” እያሉ ሰዎቻቸውን ሲጠሩ ስንሰማ ምን ማለት እንደፈለጉ አይገባንምና መቸገራችን አይቀርም፡፡ ታጋይ የሚባለው በትግል ወቅት ነው፡፡ አሁን ባለሥልጣን ሊያውም የአሜባን ቅርፅ ይዞ ከኤርትራ በስተቀር በመላዋ ኢትዮጵያ እዚያና እዚህ ጉች ጉች ያለ የተንጣለለ የኦሮሚያን ክልላዊ መንግሥት “ከነሙሉ ክብሩና ማዕረጉ በነፃነት ሲያስተዳድር” የነበረ ዕንቁ ዜጋ! አይ ወያኔ፡፡ ስንቱን ነው እያሳየን የሚገኘው፡፡ ይብላኝልህ አንተ ታሪክ የምትባል ሀገራዊ ደደብ መዝገብ፡፡ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ሀገር ከነዚህ መዥገሮችና ነቀዞች ነፃ ስትወጣ ሀፍረትህ ምንኛ የበረታ ይሆን?
ደንቆሮው ኃይለማርያም ደግሞ ያሳዝነኛል፡፡ የተሰጠውን እንዳነበበ “የሥልጣን ጊዜው”ን ሊጨርስ ነው፡፡ ምን ዓይነቱ ገልቱ ሰው ነው? እሱም ዛሬ ልክ እንደዚያች የመርገምት ፍሬ እንደአዜብ ጎላ አለማየሁን ‹መስዋእት የሆነ ታጋይ› ብሎት ዐረፈው፡፡ የት ዐውደ ውጊያ ሲፋለም ይሆን አቶ አለማየሁ የተሰዋው? በዚህ ብቻም አላበቃም፡፡ ለመለስ የተናገረውን ትንሽ ለወጥ አድርገው ጽፈው ሰጡትና “ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለሰማዕታት” ብሎ ተናገረ፤ አለማየሁም ሰማዕት መሆኑ ነው (ሰማዕት የሚባለውንም ቃል ከሃይማኖታዊው ዐውድ አውጥተን ለዓለማዊ ፍጆታ ካዋልነው በትግል ወቅት የተሰዋ ማለት እንጂ በአገር አማን በበሽታ የሚነጠቅን ዜጋ ለማመልከት አይደለም)፡፡ ለውጡ በፊተኛው ጊዜ ይህን መፈክር የተናገረው ለመለስ ነበር፡፡ አሁን ግን ለሞቱትና ለመሞት ለተዘጋጁት ለነሳሞራና ሥዩም እንዲሁም ለሌሎቹም ተራቸውን እየተጠባበቁ ላሉ ሟቾች ጭምር ነው፡፡ የወደፊቱ ጊዜ የወያኔዎች መረፍረፊያ ጊዜ ነው፡፡ (ኢቲቪን አሁን ስመለከት ካህናት ጸሎተ ፍትሃት እያደረጉ ነው፡፡ የታደሉ ወያኔዎች ናቸው ጃል! ቤተ ክርስቲያንን ሲፈልጉ ያጠፏታል ሲፈልጉም የማስመሰያ ፍትሃት እንድታደርግላቸው ያስደርጓታል፤ ሁሉ በጃቸው ሁሉ በደጃቸው – ማን ሃይ ሊላቸው፡፡ አለማየሁ እየተፈታ ነው፤ ሊያውም ከስንት አድባራት በልዩ ትዕዛዝ በተጠሩ ጳጳሳትና ካህናት፡፡ ይሄኔ ተቃዋሚ ቢሞት ኖሮ መንግሥትም ቤተ ክርስቲያንም ያን የሞተ ሰው እንደሥጋት በመቁጠር የውሻ ያህልም ክብር ባልሰጡት፡፡ ምን ዓይነት ቤተ ክርስቲያንና ምን ዓይነት መንግሥት ናቸው ያሉን? ያሉ የሚመስሉ ግን የሌሉ፡፡ ለሞተም የሚያዳሉና ሙታንንም የሚከፋፍሉ አስገራሚ ጉዶች!)…
ብዕር ካነሳሁ አይቀር በእግረ መንገድ አንድ ሌላ ጉዳይ ላንሳ መሰለኝ፡፡ ፕሮፌሰር መስፍንን ምን እየነካቸው ነው? ትናንት አንድ መጣጥፋቸውን ከዘሀበሻ ድረገፅ ላይ አነበብኩ፡፡ ጽሑፋቸው ቆንጆ ነው፡፡ እንደሁልጊዜው ሁሉ በፍቅር ነው ያነበብኩት፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ አዝንባቸዋለሁ፡፡ ግራ የገባቸውም ይመስለኛል፡፡ ግራ ተጋብተውም እኔንም ግራ ያጋቡኛል፡፡ ምን ያለ ግራ አጋቢ ዘመን ላይ ደረስን እባካችሁ!
ግንቦት ሰባትን ለምን ትኩር ጥምድ አድርገው እንደያዙት አልገባህ ብሎኛል፡፡ እርሳቸው እደግፋዋለሁ በሚሉት ሰላማዊ የትግል ሥልት የኢትዮጵያን ሕዝብ ነፃ ማውጣት እንደማይቻል የተረዱ አልመሰለኝም፡፡ የትጥቅ ትግልን እንዳናናቁና ሕዝቡ ለባርነት እንደተጋለጠ በሰልፍና በወረቀት ላይ ብቻ ተወስኖ እየተጯጯኸ ዕድሜውን እንዲጨረስ ይፈልጋሉ መሰለኝ፡፡ ምን ማለታቸው ነው? “ያውጡብሽ እምቢ፤ ያግቡብሽ እምቢ” ይባላል እንደዚህ ያለ የማይፈታ ዕንቆቅልሽ ሲገጥም፡፡
መካሪ ማጣት ነው፡፡ ወይም ሰውን መናቅ ነው፡፡ እንደ አካሄድ ትልቅነት ጥሩ ነው፡፡ አባትነት መልካም ነው፡፡ ታዋቂነት ደግ ነው፡፡ መማር መመራመር ውብ ነው፡፡ በሥራ ጉዳይ ሀገርን ተዟዙሮ መቃኘትና ለትውልድ የሚተርፍ ምሁራዊ ትሩፋት ማስገኘት ብዙዎች ተመኝተው የማያገኙት መታደል ነው፡፡ በነዚህ ሁሉ ፕሮፌሰሩን አከብራለሁ፤ እወዳቸውማለሁ፡፡ ብዙዎች ወገኖቼ እንደሚቸሯቸው ያለ እውነተኛ ፍቅር እኔም ለእኚህ ሀገራዊ ቅርስ አባት አለኝ፡፡ ይሁንና ተሰሚነታቸውን በመጠቀም ለሀገር አንዳች ነገር እንሠራለን ብለው ገንዘባቸውን፣ ዕድሜያቸውን፣ ጊዜያቸውንና መላ ትኩረታቸውን የሚያውሉ ወገኖችን ማወክ ተገቢና ወቅታዊም አልመስለኝም፡፡ አንገት የተፈጠረው አዙሮ ለማየት ነው፡፡ አዙሮ ማየት ደግሞ በትልቅና በትንሽ ስብዕና የሚወሰን አይደለም፡፡ ስህተትን መሥራት በሰውነት ደረጃ የሚገታ እንዳልሆነ ሁሉ ከስህተት ጎዳና ለመውጣት መጣርና ራስን ለመፈተሸ ጊዜና አቅል መግዛትም ለተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ እናም ክቡር ፕሮፌሰር ነገሬን በጥሞና እንደሚረዱልኝ እገምታለሁ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለበትን ሁኔታ የተገነዘቡ አልመሰለኝም፡፡ እርሳቸው በፋክት መጽሔት የፈለጉትን ስለተነፈሱና በጡረታም ሆነ በሌላ መንገድ በሚያገኙት (መጠነኛ) ገንዘብ ሕይወታቸውን ከብዙዎች ዜጎች በተሻለ ሁኔታ ስለመሩ ሕዝቡ ተመችቶታል ብለው የሚያስቡ ከሆነ ተሳስተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለበትን የባርነት ሰቆቃ መረዳት አለባቸው፡፡ ችግሩ የአምባገነንነትና የዴሞክራሲ ጉዳይ አይደለም፡፡ በነፕሮፌሰር ቀለል ተደርጎ እንደሚገለጠው የዴሞክራሲ ዕጦትና የአምባገነን መንግሥት ጉዳይ የሀገራችን አንገብጋቢ ችግር አይደለም፡፡ ይሄን መሰሉ የነፕሮፌሰር ገለጣ ቅንጦት ነው – እዬዬም ሲደላ ነው ወገኖቼ፡፡ የኛ ችግር በነፃነትና በባርነት መካከል የሚዋልል የጠበበ አማራጭ ነው፡፡ ነፃነቱ ከተገኘ በኋላ ስለአምባገነን መንግሥትም ሆነ ግለሰቦች መነጋገር ይቻላል፡፡ አሁን ግን በአፓርታይድና በቅኝ ግዛት ውስጥ በመከራ ሥጋ በመከራ ነፍስ ውስጥ ተጣብቀው እየኖሩ ስለወደፊት አምባገነን ሥርዓት መነጋገር በትንሹ ቂልነት ነው፡፡ አለፍ ሲልም ዕብደትና ወፈፌነት ነው፡፡ አሁን በሌለ ሥልጣን፣ ባልተገኘ ምቹ ሀገራዊ የሥልጣን አያያዝ ሁኔታ ገና ለገና ግንቦት ሰባት ሥልጣን ይይዝና ጭቆናን ያራምድ ይሆናል ብሎ ሕዝብን ማደናገርና ማደናበር ከሀበሻዊ የምቀኝነት አባዜ ነጻ አለመውጣትን እንጂ ቀናነትን የተላበሰ ሀገራዊ መቆርቆርን አያመለክትም – It is really a far-fetched and more of imaginary concern for the time being. ትግላችን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው አቢይ ትኩረት ይህን በስብሶ ያበሰበሰንንና ተረካቢ ትውልድ ሳይቀር እንዳይኖረን እያደረገን የሚገኘውን የዘረኝነት ሥርዓት አስወግደን ቢያንስ ቢንስ ሁላችንንም በእኩል የሚጨቁን ወይም በእኩል የሚገድል ሥርዓት ማምጣት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ያለው ትግል ቀላል ነው፡፡ የራሳችንን ጨቋኞች ካገኘን በኋላ ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገው ጉዜ በግማሽ አጠረ እንደማለት ነው፡፡ አሁን ግን በቅዠት ዓለም እየዋኙ እንደዶክኪሾት በምናብም በእውንም ከሚያስቡትና ከሚያገኙት “ጠላት” ጋር መላተም የህመም ካልሆነ የጤና ሊሆን አይችልም፡፡ ያስተዛዝባልም፡፡ እንዴ፤ ልብ እንግዛ እንጂ፡፡ እስከመቼ አንድ ዓይነት አንቺ ሆዬ ቅኝት እንዘፍናለን? “ሦስተኛውን” ዐይናችንን እንግለጥ፡፡
አንዲት ሴት እንዲህ አለች አሉ – ለባሏ፡፡ “ስንደዶ ቀጭቼ፣ አከርማ ቆረጬ ወስከምቢያ ሰፍቼ እሸጥና አንዲት ላም እገዛለሁ፡፡ ላሚቱን አስጠቅቼ አርግዛ ስትወልድ ጥጃዋን እዚያች እግገኗ ላይ አስራታለሁ፡፡” ሞኙ ባል ደግሞ “የለም፣ የለም፤ ምን ማለትሽ ነው? እግገኑ ላይማ አናስርም፤ ሰው ይገባል ይወጣል፡፡ የሰው ዐይን ደግሞ እንኳንስ ጥጃ ድንጋይ ይሰብራል፡፡ ስለዚህ ጓዳ ውስጥ እንጂ እዚህ አናስራትም፡፡” ሚስትዮዋም ቀጠለች፡- “ምን ማለትህ ነው፤ ጓዳ ውስጥማ አናስርም፤ እዚሁ ነው የምናስራት፡፡ ደግሞስ አንተን ምን ጥልቅ አደረገህ? ለፍቼ ደክሜ ላሟን እምገዛና አሰጠቅቼ ጥጃዋን እማስወልድ እኔ፡፡ …” ክርክሩ ጦፈ፤ ወደ ከፍተኛ ግጭትም አመራና ባልዮው አጠገቡ የነበረ የቡና ዘነዘና አንስቶ አናቷን በርቅሶ ገደላት – ነፍሷን ይማር፡፡ ይታያችሁ – በላም አለኝ በሰማይ ምኑም ምኑም በሌለበት ሁኔታ በባዶ ሜዳ ተጨቃጨቁና ተገዳደሉ፡፡ የብዙ ሰዎች ችግር ይህን ይመስላል፡፡ የሌለ ሥጋት እየፈጠሩ በማውራትና በማስወራት ከፊት ለፊት የተጋረጠብንን ትልቅ ተራራና አለት በጋራና በቻልነው መንገድ ሁሉ ገፍተን እንዳንጥል ደንቃራ እየሆኑብን ነው፡፡ የሚሆነው ሁሉ ከመሆን ባይዘልም እነዚህን መሰል የ“ሳይቸግር ጤፍ ብድር” ዜጎች ወደየኅሊናቸው እንዲመለሱ እንጸልይ፡፡ እንቅፋትነታቸው ግልጽ ነውና፡፡
ግንቦት ሰባት ስህተት ሊሠራ ይችላል፤ “እንከን የለሽ ነው፡፡ ምሉዕ በኩልሄም ነው” የሚል እምነትም ሆነ አስተሳሰብ የለኝም – በሰዎች ስለሰዎች የሚመራ በመሆኑ ፍጹም ነው ማት አንችልም፡፡ ግን ከስህተታቸው እየተማሩ ወደ መልም ዘለቄታ የሚያመሩ ይመስሉኛል፡፡ (አንዲት ቀልድ ቢጤ ጣል ላድርግ፤ አንድ ሰው የሚጋልበው ፈረስ ዐመለኛ ኖሮ ተቸግሯል፡፡ አልታዘዝለት ብሎ ገደል ሊከተው ደረሰ፡፡ ተመልካቾችም አንዳቸው “አንገቱን ያዘው”፣ ሌላኛቸው ልጓሙን ጨብጠው” ደግሞም ሌላኛቸው “እርካቡን እርገጠው” ወዘተ. ሲሉ የሰማቸው ችግር ውስጥ የሚገኝ ሰውዬ “አይ መሬት ያለ ሰው!” አለ አይባላል፡፡ ልክ ነው – ያልተነካ ግልግል እንዳለማወቁ ቁጭ ብሎ ወሬ የሚጠርቅ የኔ ዓይነቱ ሥራ ፈት ሰው የሚለው አያጣምና ብዙ ሊፈላሰፍ በዚያ ፍልስፍናውም ብዙ ሊሳሳት ይችላል፡፡ ተሳስቶ ከማሳሳት ይሰውረን ወገኖቼ፡፡) በመሠረቱ እኔ የግንቦት ሰባት አባልም ሆነ አቦካቶው አይደለሁም፡፡ ግን አዳሜ እየተነሣ የጭቃ ጅራፉን ሲለጥፍበት ያሳዝነኛል – ብዙ የምታዘበው ነገር ስላለ ነው እንደዚህ በምሬት የምናገረው፡፡ በእውነቱ የማንሠራና የማናሠራ ዜጎች ብዙ ነን፡፡ ባሕርያችን ለያዥ ለገራዥ የሚያስቸግር ክርት ዐመል ያለን ብዙ ነን፤ ምን እንደሚሻለን አላውቅም፡፡ አለቃ ገ/ሃና “ለቦና ጥጃ ውስ ምን አነሰው” አሉ አሉ፡፡ እናስ ስንትና ስንት የሚወራበትና የሚጨነቁለት ችግር እያለ አሁን በምትወዱት ሞት ይሁንባችሁና ግንቦት ሰባት ለኢትዮጵያ ከወያኔ የበለጠ ራስ ምታት ሆኖ ነው ይህን ያህል ሰዎች እንቅልፍ አጥተውለት ከወያኔ ባልተናነሰ ለውድመቱ የሚቋምጡለት? ከማንም ጋር ይሥራ – የሚያዋጣውን የሚያውቅ ራሱ ነው፡፡ ስህተቱን መጠቆም፣ ማረም፣ ማስተማር፣ ማስተካከልና በተቻለ አቅም ሁሉ መርዳት ሲገባ ቤተስኪያን እንደገባች ውሻ ችው ችው ማለት ከአንድ ጤናማ ኢትዮጵያዊ ዜጋ አይጠበቅም፤ ሁል ጊዜ በምቀኝነት አባዜ መጠመድም ተገቢ አይደለም፡፡ ትንሽዬ ዝናና ስመጥርነት ስላገኘ ብቻ ባለን የቆዬ የምቀኝነት ባህል እየታወርን ሳቢን ለመግረፍ መጣደፍ አግባብ አይደለምና አንዳንዶቻችን ከምንጓዝበት እርምጥምጥ መንገድ በአፋጣኝ እንውጣ፡፡ ቢያንስ ዝም እንበል – ቆርጠን እየቀጠልን በምንፈጥራቸው ስድቦች ሰድበን ለሰዳቢ አንስጠው – “የምታሸንፈውን ምታ” ቢሉት ወደ ሚስቱ እንደሮጠው ፈሪ ባል ወያኔ ሲያቅተን በዚህ የትናንት ድርጅት አንረባረብ፤ ባይሆን ወፌ ቆመች እንበለውና የበኩሉን እንዲጥር እናግዘው፡፡ ከፈራነውም አሁኑኑ በእማኞች ፊት እናስፈርመውና ሥልጣኑን ከወያኔ እንደቀማ – ህልሙ ተሳክቶለት መቀማት ከቻለ – ሕዝብ ለሚመርጠው ሰው እንዲያስረክብ ቃል እናስገባው፡፡ በበኩሌ ምነው ግንቦት ሰባት በተሳካለትና በኢትዮጵያዊ አምባገነን በተገዛሁ እላለሁ፡፡ የራሴን አምባገነን መታገል እመርጣለሁ በባርነት የአፓርታይድ ሥርዓት ውስጥ ከሰውነት በታች ሆኜ ከምኖር፡፡ የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ ግንቦት ሰባት በሁኔታዎች አስገዳጅነት ሊሠራቸው በሚችላቸው ስህተቶች ምክንያት በጭካኔና በኢዴሞክራሲያዊነት ከወያኔ ጋር መፈረጅ የጤና አይመስለኝም፡፡ በእግረ መንገድም ኢሳትን ከግንቦት ሰባት ጋር እያያያዙ ይህን የሕዝብ ብሶት መተንፈሻ ጣቢያ እንዲጠላ የማድረግ ዘመቻ አሁኑኑ ማቆም የሚገባ ይመስለኛል፡፡ ኢሳትን ሲዘልፉትና ሲሰድቡት ስሰማ እነዚህ ሰዎች በተጠናወታቸው ሥነ ልቦናዊ ደዌ አዝናለሁ፡፡ ከወያኔ ምንዳ ተቀብለው ይሆን ብዬም ለማሰብ እገደዳለሁ፡፡ ኢትዮጵያውያን እንደዚህ ዘመን ክፉኛ የተከፋፈልንበትና በጦዘ የርስ በርስ ቅራኔ የገባንበት ዘመን ይኖር ይሆን? ለማንኛውም ስንናገርና ስንጽፍ ከአንዴ በላይ አሰብ እያደረግን ቢሆን መልካም ነው፡፡ ወደ ቀብር ልሄድ ነው – ቻዎ፡፡
ህዝብን በመጨቆን ሀገርን መምራት አይቻልም!
በአሸናፊ ንጋቱ
የፖለቲካ ስርአትና የአንድ ሀገር እድገት ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት አላቸዉ። አንድ አገር ትክክለኛ ባልሆነ የፖለቲካ አገዛዝ ይበለፅጋል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ሃገራችን ኢትዮጵያም የወያኔ መንግስት ባነገሰው የተዛባ አገዛዝ ሳቢያ ህዝባችን ለከፋ ችግር መዳረጉ በገሃድ የሚታይ ሃቅ ነው። ታዲያ በዚህ ወያኔያዊ የተዛባ አገዛዝ እንዴት ከችግር ልንወጣ እንችላለን? አገራችን ኢትዮጵያ ምንም እንኳ የጥንት ስልጣኔ ባለቤት ብትሆንም በአየር ንብረትም ሆነ በተፈጥሮ ሀብት ጥሩ ከሚባሉት ሀገሮች አንዷ ብትሆንም እንደ እድል ሆኖ መሪዎች ግን አልተሳኩላትም። ለምን ኢትዮጵያ የረሃብ አገር ተባለች ለምን ዜጎቿ ተደስተው በነጻነት መኖርን እንደተመኙ ህልማችዉ ከንቱ ሆነ? ብዙዎች የሞቱላት አገር አንገታቸዉ ለሰይፍ ደረታቸዉ ለጥይት የሰጡላት አገር ኢትዮጵያ በህዝቦቿ ታታሪነት አለም ያደነቃት ለምን ተዋርዳ ተገኘች!?
እውቀትን፣ ስልጣኔን፣ ጥበብን ለአለም ያበረከተች ሃገር ዛሬ ላይ በቤተ መንግስቱም ይሁን በቤተ ክህነቱ የተማሩ ሰዎችን ናፊቂ ሆናለች፡፡ ምክንያቱም ምሁራኑ በሃገራቸው ሊኖሩ የሚያስችላቸው እድል ስላልተመቻቸላቸው ሁሉም ጉዟቸው ወደ ውጭው አለም ስደት በመሆኑ ነው፡፡ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህዝቦች በረሃብ አለንጋ የሚገረፍባት ሲኦልም ከሆነች ዘመናትን አስቆጥራለች፡፡ እንዲሁም መለያየትን ወይም ዘረኝነት በግልፅ የምትሰብክ የዘረኞችና የጎሰኞች መሰማሪያ ሜዳ ሆና ክፉ አድራጊዎች እንደፈለጉ እየዘፈኑባት ትገኛለች፡፡ በቃል ከሚወራ ዲሞክራሲ፣ እድገት፣ ብልፅግና በስተቀር በተግባር የሚታይ አንዳችም መልካም ነገር የማናይባት አሳፊሪ ሃገር ሆናለች፡፡ በደልና ጭቆና በዝቷል ድህነትና ጉስቁልና ከመቼዉም በባሰ ተንሰራፍቷል እስርና ሰቆቃ ተራ ነገሮች ሆነዋል። በአሸባሪዎች ስም እራሳቸዉ ቦንቦች አጥምደው ህዝቦች እየፈጁ ሰላማዊ ዜጎች በአሸባሪነት እየተፈረጁ ለስቃይ እየተዳረጉ ነዉ። ዛሬ በሃገራችን አርሶም ሆነ ነግዶ መኖር አይቻልም። መኖር የሚቻለዉ ኢሕአዴግ ልማት ነዉ የሚለዉን መዝሙር በመዘመር ብቻ ነዉ።
የሁሉም ነገር መሰረት እንደሆነ የሚታመንበት ትምህርትን ብንመለከት እንኳ ትምህርት በኢትዮጵያ ሞቷል ለማለት በሚያስደፍርበት ጀረጃ ደርሷል። ከተለያዩ ሀገሮች ያለምንም ጥናት በኩረጃ የሚያመጧቸዉ የትምህርት ፖሊሲዊች ምንም እንኳን ብዙ ወጭ ቢወጣባቸዉም የሚሰራባቸዉ ለአንድ የትምህርት መንፈቀ አመት ብቻ ነዉ። በኢትዮጵያ ወያኔ ልማት ነዉ በሚል አባዜ የተለከፈ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል። ልማታዊ መንግስት፣ ልማታዊ፣ ዘፋኝ፣ ልማታዊ አስተማሪ፣ ልማታዊ የእምነት ዘርፍ፤ ወዘተ… በማለት ከወያኔ ጎን ካልተሰለፉ ኢ-ልማታዊ/ ሽብርተኛ የሚል ስም ይሰጣቸዋል ይህንንም ተመርኩዞ ለእንግልትና ለእስራት ይዳረጋሉ። ‘‘ዶሮ ጭንቅላቷ ላይ ስጋ ተሸክማ ወይ አትበላዉ ወይ አታስበላዉ‘‘ እንደተባለዉ ማንንታቸዉና እዉቀታቸዉን ትተዉ የወያኔ መዝሙር ብቻ በመዘመር የሚኖሩ ጥቂት ሰዎች በኢትዮጵያ ዉስጥ የማይጠበቅ ኑሮን ሲኖሩ ይታያሉ። የሚላስ የሚቀመስ በጠፋበት በአሁኗ ኢትዮጵያ ዘይትና ሽንኩርት ለመግዛት እንኳ አንድ ግለሰብ የወር ደሞዙ በቂ አልሆን ባለበት ግዜ እንዴት ጥቂት ባላባቶች ፎቆችና ቪላዎች ይገነባሉ? የህዝብ ንብረት ካአልተዘረፈ በቀር እነሱ ከየት አመጡት? ወይስ ኢትዮጵያ ሲባል እነሱን አይጨምርም? ከአዉሮፓ
መንግስታት የሰዉ ፍጥረት በረሃብና በህክምና እጥረት ህይዎቱን ለማዳን ተብሎ የሚላከው ገንዘብ እነሱ ዉስኪ ሲራጩበት ሊሞዚንና አሉ የተባሉ ምርጥ በአለም ከታወቁ ካምፓኒዎች የተሰሩ መኪናዎች ሲገዙበት ለህዝቡ ድህነት ባህላችን መሆኑን ዘላለም በመተረክ ይኖራሉ። በስብሰባ ፍቅር ብቻ የተለከፉ ባለስልጣናቶቻችን ስብሰባዉን እንደጨረሱ አበል በሚል ስም ገንዘብ ይከፋፈላሉ። ይህንን እንስሳዊ የሆነ አስተሳሰብ አልደግፍ ያሉት ደግሞ ፀረ ልማትና አሸባሪ በሚል ስም ለእንግልት ይዳረጋሉ። አሸባሪነት ለምን የፖለቲካ መጠቀሚያ ሆነ? አሁን የታሰሩት ዉብ የኢትዮጵያ ልጆች አሸባሪዎች እንደሆኑ የሁል ግዜ ለጆሮ የሰለቸ ንዝንዝ ነዉ፤ ስለዚህ አሸባሪነት ለአምባገነናዊ መንግስት አለመዘመር ከሆነ ወደድክም ጠላህም መኖርም ሆነ መስራት የሚቻለዉ ይህንኑ ስትዘምር ብቻ ነዉ። ለዚችው በሺህ የሚቆጠሩ የነፃነት ታጋዮች የታሰሩባት; ረሃብ፣ ጦርነት፣ሞትና ግድያ መለያየት የሰፈነባት፤ ዜጎችዋ በሰላም ወጥተው በሰላም ለመግባት ለሚሸማቀቁባት ሃገር ለታሪኳ ሁለ መበላሸት ተጠያቂው ወይም ተወቃሹ ገዳዩ የወያኔ አገዛዝ ነው፡፡
ስለዚህ የኢትዮጵያ የድንቁርና ፣ የመለያየት፣ የጦርነት፣ ያለማወቅ፣ የግድያ ጭለማ እንዴት ይወገድ ወደሚለው መፍትሄ ሃሳብ ስንመጣ፤ በኢትዮጵያ ያለው የክፉ ነገሮች ሁሉ ጨለማ የሚወገደው በወለደቻቸው እና ባሳደገቻቸው ኢትዮጵያውያን ሃገር ወዳድ ልጆቿ ነው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላም ናፍቋት የሰላም ያለህ እያለች ነው፡፡ ውድ ልጆቿም አረመኔው የወያኔ መንግስት በየጊዜው እየቀሰፈባት እረፍትን ትሻለች፡፡ በመሆኑም ይህን አምባገነናዊ የወያኔ ስርዐት በማስወገድ ; በሃገራችን የእውቀትና የሰላም ብርሃን እንዲፈነጥቅ ; ዜጎቿም በሰላም ወጥተው በሰላም እንዲገቡ; መብቶቻቸውም ሊጠበቁ የሚችሉበትን እንዲሁም የምንፈልገውን ነፃነት፣ እድገት፣ፍትህ፣ ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ ለማምጣት የራሣችንን ቁርጠኝነት ማሣየት ይጠበቅብናል!!!
ድል ለጭቁኑ ህዝብ!!!
በ andethiopia16@gmail.com አስተያየትዎን ይላኩልኝ።
ወጣቱ አና ለነጻነት የሚደረግ የትግል መስዕዋትነት (ገዛኸኝ አበበ ከኖርዌይ)
የአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ህልውና የሚወሰነው ወጣቶች ባላቸው ሚና ላይ ሲሆን በብዙ ሀገራት እንዳየነው እና እንደተመለከትነው ወጣቶች ስለ ነፃነታቸው ፊት ለፊት መንግስታትን በመጋፈጥ ለመብታቸው ታግለዋል መስዋህትነትም በመክፈል የፈለጉትን አለማና ግብ አሳክተዋል::ለዚህም የሰሜን አፍሪካ አገሮችንና የመካከለኛው ምሥራቅን የለውጥ አብዮት ያቀጣጠሉትን ወጣቶች ዞር ብሎ መመልከት ያሻል:: የአንባ ገነኖች የስልጣን አገዛዝ አልዋጥላቸው ያላቸው እነዚህ የሰሜን አፍሪካ አገሮች እንደነ ግብጽ ፣ ቱኒዚያ እና ሊቢያ ያሉ ሀገሮች የሚኖሩ ወጣቶች በጊዜው ለናፈቁት እና ለተመኙለት ነጻነት ብዙ መስዋትነትን በመክፈል ዓላማቸውን አሳክተዋል:: በወቅቱ የነበረው የዓረብ የፖለቲካ ትኩሳት መነቃቃት ለብዙ ሀገራት ወጣቶች ትምህርት ሰጥቶ ያለፈ ታሪክ ነው::
ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ስንመለስ የኢትዮጵያን የፖለቲካ አካሄድ ወደ ኋላ ዞር ብለን በምናይበት ጊዜ በኢትዮጵያ ሲደረግ በነበረው የፓለቲካ እንቅስቃሴ ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ትልቁን ሚና ይጫወት እንደነበር ከታሪክ መረዳት እንችላለን::እነሆ በኢትዮጵያ ረዥም ታሪክ ውስጥ እያንዳንዱ ትውልድ በተለያየ ጊዚና ወቅት የራሱን አሻራ ጥሎ አልፏል፡፡ በተለይ በንጉሡ ጊዜ የመሬት ላራሹንና ሌሎችንም የፖለቲካዊ ጥያቄዎች አንግቦ ሲንቀሳቀስ የነበረው የተማሪ ንቅናቄ ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ የታሪክ ጉዞ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሲሆን በዚያን ጊዜው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የነበሩትና ግንባር ቀደሞቹ ዋለልኝ መኮንንና ጥላሁን ግዛው በድንገት በወታደራዊው ኃይል ቁጥጥር ሥር ለወደቀው የተማሪው አብዮት ተጠቃሾች ሲሆኑ፣ በዘመኑ ለነበረው ሃይለኛ እና ወኔን የታጠቀ ትውልድም መታወቂያ ሆነው ማለፋቸውን የታሪክና የፖለቲካ ተንታኞች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሚያወሱት የታሪክ ትውስታ ነው፡፡
ከቅርብ አመታት በፊትም ማለትም በ97 ምርጫ ሁሉም ሰው እንደሚያስታውሰው ይህ ወቅት ኢህአዴግ ወጣቶችን ሙሉ በሙሉ የገፋበት ወቅት ጊዜ እንደነበር እና መንግስት ስራ አጥተው የሚንከራተቱ ወጣቶችን “አደገኛ ቦዘኔ” የሚል ታፔላ በመስጠት የተለያዩ እስሮችና የማንገላታት እርምጃዎችን የወሰደበት እና የፈፀመበት ወቅት እንደነበር በብዙዎች ዘንድ ይታመናል፡፡ ይህ አይነቱ የመንግስት ግብታዊ እርምጃ ወጣቱን ወደ ተቃውሞ ጐራ እንዲያዘነብል አድርጐታል፡፡ ለዚህም ይመስላል በወቅቱ በምርጫ 97 ዋዜማ ኢህአዴግ ያቀረባቸውን የተለያዩ ማባበያዎች “አደገኛ ቦዘኔ ራሱ ወያኔ” የሚል ዜማ በማቀንቀን ለተቃዋሚዎች ድጋፍ የሰጠው፡፡ ኢህአዴግ በምርጫ 97 የደረሰበትን አስደንጋጭ ሽንፈት ተከትሎ በተፈጠረው ውዝግብ ቀዳሚ ተጠቂ የሆነውም ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል እንደነበር እናስታውሳለን፡:ለዚህም ነው ምርጫ 97 ተከትሎ በጊዜው በአቶ መለስ መንግስት ከሃያ ሺ በላይ ወጣቶች በእስር ቤቶችና በወታደራዊ ካምፖች ታሰረው የተሰቃዩት እና ከ200 በላይ የሆኑ ባብዛኛው ወጣት የሆኑ ንፁሀን ዜጐች በግፍ በአደባባይ የተገደሉት::ይህንን ለነጻነት ትግል የተደረገን የወጣቶች የህይወት መስዋትነት ሁል ጊዜ ስናስታውሰው የምንኖረው ነው::
እንደሚታወቀው በአሁን ወቅት በሀገራችን ኢትዮጵያ ከሚኖረው ህዝብ ከፍተኛውን ቁጥር ይዞ የሚገኘው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል መሆኑ ይታወቃል:: ይህንንም ተከትሎ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከወጣቶች ብዙ የምትጠብቀው ነገር መኖሩ የማያጠያይቅ እውነታ ነው;; ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሀገራችን የወደፊት ሁለንተናዊ ህልውናዋ ያለው እና የሚወሰነውም በእነዚሁ በዛሬዎቹ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስለሆነ :: ከላይ እንደገለጽኩት በሀገራችን ኢትዮጵያ ከሚኖረው ሕዝብ አብዛኛውን ቁጥር የያዘው ወጣቱ እንደመሆኑ ይሄ ወጣት የህብረተሰብ ክፍል በስልጣን ላይ ባለው ስርዓት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ፍላጐቱ ሊሞላለት አልቻለም:: ከዚያም ባለፈ ወጣቶች የነጻነትም ሆነ የመብት ጥያቄያቸውን ወይም ፍላጐታቸውን መግለጥ እና መናገር የሚችሉበት አግባብ የተዳፈነ በመሆኑ፣ በአለም ላይ ኢትዮጵያን የተገፉ ወጣቶች የበረከቱባት ሀገር እና ሀገራቸውን እየጣሉ ከሚሰደዱ ወጣቶች መካከል ቅድሚያውን እንድትይዝ አድርጓታል፡፡
የወያኔ ኢህአዲግ መንግስት በስልጣን በቆየባቸው ባለፉት አመታቶች እየበደለ እና እያሰቃየ ያለው በመላ ሀገሪቱ ላይ የሚኖረውን ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ቢሆንም ይበልጥኑ በወያኔ ራዳር ውስጥ በመግባት በአገዛዙ ጭቆናና ግፍ እየደረሰበት ያለው በሀገራችን የሚኖረው ወጣቱ ዜጋ መሆኑ የታወቀ ነው:: ዛሬ የአማራው፣ የትግራዩ፣ የጋምቤላው፣ የኦሮሞው ፣የደቡቡ፣ የአፋሩ መላው የኢትዮጵያ ወጣት ዜጋ ለነጻነቱ በሚያደርገው ትግል በወያኔ ጨካኝ መንግስት እያተደበደበ፣ እየታሰረና እየተገደለ ለነጻነቱ መስዕዋትነትን በመክፈል ላይ ይገኛል :: ለዚህ ማሳያ የሚሆነን በሀገራቸው ፖለቲካ በመሳተፍ የተቃዋሚዎችን ጐራ የተቀላቀሉ እንደነ አንዱ አለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን እና ኦልባና ሌሊሳ የመሳሰሉ ወጣት ፖለቲከኞች እንዲሁም እንደነ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ እና ርዮት አለሙን የመሳሰሉ የወደፊቶ ኢትዮጵያ ተስፈኞች ብዙ የምትጠብቅባቸው ወጣት ጋዜጠኞች የወያኔ መንግስት እያራመደ ካለው የዘረኝነት ፖለቲካ የተለየ አቋም በመያዛቸው እና በተለያዩ ጋዜጦች ላይ ሀሳባቸውን በመግለፃቸው ብቻ በአሸባሪነት ተከሰው ወደ እስር ቤት በግፍ መወርወራቸው የኢትዮጵያ ወጣቶች በገዥው ስርዓት ምን ያህል መብታቸው እየተረገጠ እና ነጻነታቸው እየታፈነ በወያኔ የግፍ አለንጋ እየተገረፉ እንደሚኖሩ አመላካች ነው፡፡
የወያኔ መንግስት በወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል እየወሰዳቸው ያለው እነዚህ በግፍ የተሞሉ እርምጃዎች ወጣቶች እጃቸውን አጣጥፈው እንዲቀመጡ አላደረገም፡፡ ይባሱኑ ወጣቱ ሀይሉን እያጠናከረ እና ወደ ተቃዋሚ ጎራ በመግባት ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለወያኔ ኢህአዲግ መንግስት የእግር እሳት እየሆነበት ይገኛል.: በዚህ አጋጣሚ ዛሬ በአዲስ አበበ በተካሄደው የሴቶች 5ሺ ሜትር ሩጫ ላይ ተሳታፊ የነበሩትን እና የተለያዩ ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን በማንሳት ነጻነት፣ እኩልነት፣ ፍትህ፣ ዴሞክራሲ እንዲሁም ርዕዮትና ሌሎች የህሌና እስረኞች ይፈቱ እያሉ ሲጮኹና ድምጻቸውን ሲያሰሙ የዋሉትን የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ወጣት ሴቶች እህቶቻችንን ሳላደንቅ አላልፍም :: በጣም የሚያኮራ ተግባር በመፈጸም ምንም ነገር ሳይፈሩ ለወያኔ መንግስት የፍም እሳት በመሆን የተነሱለትን አላማ ‹‹ለነጻነት እንሩጥ›› የሚለውን መሪ ቃል በማሳካተቸው ጀግኖች ብያቸዋለው:: በነገራችን ላይ እነዚህ ወጣት ሴት እህቶቻችን ሮጫቸውን ጨርሰው ሲገቡ ለታገሉለት ነጻነት መስዋዕትነትን ከፍለዋል:: ሲከታተሏቸው በነበሩት የወያኔ ተላላኪዎቸ በሆኑት የፖሊስና የደህንነት ኃይሎች መያዛቸውና መታሰራቸው ተገልጾል::
የነጻነት፣ የእኩልነት፣ የፍትህ፣ እና የዴሞክራሲውን ጥያቄ የሰማያዊ ፓርቲ ፣ የአንድነት ፓርቲ ወይም የሌሎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ በተለይም የኢትዮጵያውያን ወጣቶች ጥያቄ መሆን ይገባዋል:: ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወጣት የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ በተለያየ የትግል መስክ በመሰማራት ኢትዮጵያችንን ከወያኔ ፋሽስታዊ ስርዓት ለመታደግ፣ የሀገራችንን ሕልውናና ክብር ለመመለስ በወያኔ መንግስት ላይ የፍም እሳት በመሆን መነሳት በእንቢ አልገዛም ባይነት መንፈስ በጽናት በመታገል ከወያኔ የዘረኝነት አገዛዝ ኢትዮጵያንና እራሱን ነጻ በማውጣት ለታሪክ የራሱን አሻራ ጥሎ ማለፍ ይጠበቅበታል::
የድል ቀን እንዲፋጠን ሁላችንም ወጣቶች እጅ ለእጅ ተያይዘን እንነሳ !
gezapower@gmail.com
“ሣንሞት መቀባበር መቼ ይሆን የሚቆመው?
“እውነት ቤት ሥትሰራ ውሸት ላግዝ ካለች፤
ሚሰማር ካቀበለች
ማገር ካማገረች
ጭቃም ካራገጠች
ቤቱም አልተሰራ እውነትም አለቆመች።”
ለእውነት መቆምና እውነትነት በሌለው ነገር ግን ; እውንት በሚመሰል; ማንኛውም አይነት መሀበርም ሆነ እድር;
መሰባሰብ እውነቱ ሲገለጥ መጨረሻው መፈረሱ ሀቅ ነው።
በሀገራችን ባሕል ሰው በደል ሲበዛበት ሲጨንቀው ይጮሃል፤ ጎረቤትም ይደርሰለታል። ሊደርሰብት ካለው
ችግርም ይድናል። ይኸ ሲወረድ ሲዋረድ የመጣውና ዘመናት የማይሽረው ታላቁ ባሕላችን ነው። ዛሬም በትውልድ አገሩ
ፈትህ አጥቶ መከራውና ፈተናው ቁም ሰቅሉን ሲያሳየው “በዘር” እንዲያሰብ፣ እንዲበተንና እንዲሰደድ ተጽእኖ
ሲደረገበት አሁንም እየታደገው እና እያቻቻለ በጽናት ያቆመው ይኸው ታላቁ የመቻቻል ባሕሉ ነው።
በሰለጠነው አገር እነዲህ ያለውን ጩኸትና የፍትህ መዛባት ግን የሚሰማ የህግ ቦታ አለና የሰው ጩኸት ከንቱ ሆኖ
አይቀርም።
ከላይ እንደመንደርደሪያ አድርጌ የተጠቀምኩበትን የመገቢያ ሀሳብ ሰትመለከቱ ምን ሊልን ነው ደገሞ፤ የምንሰ
ቀብር ነው በሚል ልትገረሙና ልትደነቁ እንደምትችሉ ለመገመት አልቸገርም። ሆኖም የመልዕክቴ ፍሬ ሃሳብ ግን ይኸ
ሳይሆን የሚከተለው ነው። ሰሞኑን አነድ የሕግ ኮርሰ በሰትረጅና መጦሪያ ይሆነኛል በዬ በአነድ ኮሌጅ እየተከታተልኩ
ነበርና “መምኸሩ” ለመወያያ ብሎ ያቅረበው የሕግ ምሳሌ የእኛው ጉድ በመሆኑ እጅግ አሰደነቀኝ እጅግም አሰደነገጠኝ።
እናንተንም ለግምገማው ያመቻችሁ ዘንድ እሰቲ ተመልከቱት ? እኔን ያሳዘነኝ ጉዳዩ ባሰተዳደር በኩል ሊፈታ
የሚቸል እንደነበር ከ 20 በላይ የሆኑት ተማሪዩዎች በመሰማማታቸው እና አሰተዳደሩ ምን ያሕል ደካማና የውሰጥ ችግር
ያለበት እንደሆነ ያሳያል። ነፃ በሆነ አካልም (Independent investigation) ሊመረመር የሚገባና ጥፋቱ ከተረጋገጠ በሆላ
አሰተዳደሩ በሙሉ እሪዚይን (Resign) ማድረግ አለበት የሚል አሰተያየት መሰጠታቸው ነው። ለምን አሳዘነህ ብትሉኝ
በየትኛውም መሀበራዊ ሰብሰባችን ውሰጥ ጎልቶ እየታየ የመጣው ሹክቻ ምን ሊሆን እንደሚችል ሰለምረዳና አንባቢያንም
እንደምትረዱ ሰለማምን ነው። የሚከተለውን ሊንኩን በጥሞና አንብባችሁ ሌላውን የራሰን አሰተያየትና ፍርዱን አሁንም
ለናንተ ትቼዋለሁ። http://www.canlii.org/en/on/onhrt/doc/2014/2014hrto208/2014hrto208.html
ታዲያ በዚየው ሰሞን ከአንድ ወዳጄ ጋር በከተማው መካከለኛ ቦታ ላይ በሚገኝው ሰታርባክሰ (Starbucks
Coffee) ቤት ቁጭ ብልን ቡናውን ፉት ዕያልን ሰለሀገራችን ችግር አንድ ባንድ እያነሳን ሰናወጋ ከቆየን በሆላ ፤ እንደው
እኮ ይገርማል አለኝ ወዳጄ ጫወታውን ሲጀምር፣…. እንደው…… በሁለት ዶላር ($ 2.00) አንድ ኪሎውን ቡና ካገራችን
ገዝተው በሶሰት ($ 3.00) ዶላር አንድ ሲኒ ቡና ለኛ እዚህ ሲሸጡልን አይገርምም ? በሚል ሁለታችንም ተደንቀን ፈገግ
በማለት ጫወታውን ቀጠልን።
ወዲያው ወዳጄ እንዲህ ሲል ጀመረ፡ ሰሞኑን አንድ የሚያሳዝን ነገር ሰምቼ አዝኛለሁ አለኝ። እኔም ለመሰማት
በመጓጓት ምን ተፈጠረ ? ብዬ ጆሮዩን ኮርኩሬ መሰማቴን ቀጠልኩ። ይገርምሃል አንድ ለበርካታ አመታት እንደተነገረው ለ
14 አመት ነው። በኮሚቴ አባልነትና በአባልነት በመልካም ተሳትፎዋ የምትታወቅን እህት የእደሩ የኮሚቴ አባላት ግንባር
ፈጥረው ከአባልነት በማሰወገዳቸው፤ በርካታ አባላት ተበሳጭተዋል። የሚገርመው ነገር ጉዳዩን በቀላሉ መፍታት
ባለመቻሉ ወደ ሂዩማን እራይት (Human right ) ተላልፎ ጉዳዮ በፍረድቤት እየታየ ነው። ሲለኝ እኔም በመገረምና
መደነቅ ፤ ተሞልቼ በትምህርት ቤት የተወያየንበት ጉዳይ እንደሆነ እንኳን ሳላጫውተው፤ ግን ለመሆኑ የእድሩ አላማ
ምንድነው? ለምንሰ ተቋቋመ ? ብዬ ጠየቅኩት ? መልሱንም ሲሰጥ እንዲህ ሲል ጀመረ፤
አላማውማ የተቀደሰ ነበረ። በውጪ የሚኖርውን ኢትዩጲያዊ በማሰባሰብ የተቸገረውን ለመርዳት፣ አልፎ ተረፎም
ሀዘን ሲደርሰ በቅርብ ሆኖ እርሰ በርሰ መጽናናት የሚቻልበትን ሁኔታ በማመቻቸት ለመረዳዳትና፣ ከዚህም በላይ አንድ
አባል በድንገት በሞት ቢለይ አሰከሬኑን ወደሃገርቤት መላክ ካለበት የሚያሰፈልገውን ወጪዎችን በመሸፈን ትብብርና
እርዳታን የሚያደርግ ። መላክ ከሌለበትም በዚሁ በሚኖርበት አገር አሰፈላጊውን ወጪ በመሸፈን ተዋጾ የሚያደርግ በጎ አላማ ያለው በከተማችን የተቋቋመ አንጋፋው ማህበር ነው በመልካም ሰነምግባሩ ለሌሎች አዲሰ ለተቋቋሙት መልካም
አራአያ በመሆን ፋንታ ድርጊቱ አሳዛኝ ሆነ እንጂ።
ዳሩ ምን ያደርጋል በአሰተዳደር ድክመትና ብቃት ማነሰ፤ በቁም እየተቀባበርን ተቸገርን እንጂ፤ በማለት ቀጠለ ።
ወቸው ጉድ፤- በውሰጥም በውጪም በርካታ በጎ ሰራዎችን እንዳልሰራን፤ አሁን ግን እየሄድንበት ያለነው አቅጣጫ እጀግ
አሳዝኖኛል። “እረ ፤ ሰንቱ” ብሎ…በረጅሙ በመተንፈሰ ሃዘኑን ሲገልጽልኝ፤ በእውነትም ልቤ ተነካ፤ አዘንኩ አባል ሆኜ
በሰበሰባ ቦታ በመገኝት መሰተካከል ሰለሚገባቸው ነገሮች ሀሳብ መሰጠት ባልችልም በኢትዮጲያዊነቴ የተሰማኝን መገለጽ
እችል ዘንድ ብዕሬን አነሳሁ እላችዃለሁ። አዎ ያሳዝናል። እኛ ኢትዮጲያዊያኖች ከሕብረታችን ይልቅ ልዩነታችን እየጎላ
ባደባባይ እየወጣ መሰማቱ በጣም ያሳዝናል፤ያማልም። እሰቲ ልብ ብላችሁ ተመልከቱት ቸግር ሲደርሰብኝ ይረዳኛል ሰሞት
ይቀበረኛል ብለው ወደውና ፈቅደው ለ አመታት የአባልነት መዋጮ ሲከፍሉ ቆይተው በተልካሻ ምክነያት ውጣ፤ ውጪ፤
የሚል ፍርደገምድላዊ የአሰተዳደር ወሳኔ ሲፈጸምና ጉዳዩን በውሰጥ አሰተዳደር ቅን በሆነ መንገደ ተመልክቶ በጎ የሆነ ውሳኔ
መሰጠት ሳይቻል ቀርቶ ወደ ፍርድቤት መድረሱ በግሌ እጀግ አሳዝኖኛል፡፡
የበርካቷችንም ወንድሞችና እህቶች ልብም ሰብሯል አሰቆዘሟል። ለምን ቢባል እንደባሕላችን “እድር” በሀገራችን
ከፍተኛ የሆነ የመሀበራዊ መገናኛ ምሰሦ ነውና ነው። እሰከማውቀው ድረሰ ከእድር ሰው ተባረር ሲባል ሰምቼ አላውቅምና
ነው። የእድር መዋጮ መክፈል ላልቻለ ድንኳን እንዲተክል ወይም የእድር እቃ እንዲያወጣ ሲወሰነበት እንጂ ሲባረር
አላውቅምና ነው። እሱ ድሮ ቀረ ብላችሁ እንደማትመልሱልኝ ተሰፋ በማድረግ።
ፍርድቤቱም ምን ያኸል እንደሚታዘበን፣ አልፎ ተርፎ ኢትዮጲያዊያኖች፤ እንኳን በቁማቸው ተሰማምቶ
መኖርና፤ ለመሞትም አልታደሉም፤ ብለው ከፍተኛ ትዝብት ላይ እንደሚጥሉን ለመገመት አልችገርም።
በእኔ እይታ ለዚህ አይነት አሳፋሪና አሳዛኝ ውደቀት ያበቃን በግልጽና በጋሀድ እንደሚታየው ያሰተዳደር ብቃት ማነሰ ነውና
፤ እንዲህ አይነት የማቻቻል፤ የማግባባትና እንደ ባሕላችን የማሰማማት አሰተዳደር በመሀበራዊ ኑሮአችን እንዳይጎለብት
በክፋትና በጠባብነት በሰመ ኮሚቴ አባልነት ተሰልፈው ያሉትን ወንድሞችም ሆኑ እህቶች ልቦና ይገዙ ዘንድ ከህሊናችው
ጋር ይነጋገሩ ዘንድ፣ ከራሳቸውም ጋር ይታረቁም ዘንድ የዘወትር ጸሎቴ ነው። ወያኔዎችም ከሆኑ ፍርዱ ከላይም አይቀርምና
ወደሕሊናችሁ ተመለሱ ከማለት አልቦዝንም።
አባላትም እንዲህ ያለ የራሰን ገበና በመወያየትና በመቻቻል ኮሚቴው መፍታት ለምን እንዳልቻለ የመጠየቅ
መብታቸውን ተጠቅመው ብቃት የሌላቸውን ኮሚቴዎች ብቃትና አርቆ ማሰተዋል በሚችሉ መተካቱ፤ አላሰፈላጊ ካልሆነ
የፍርድቤት ውጣውረድና የፈርድቤት ወጪ አልፎተርፎም መሳለቂያ ከመሆን ያድናል እና ይታሰብበት እላለሁ። ከዚህ
የከፋም አሳዛኝ ደርጊት ከመፈጸሙ በፊት መቻቻልን እናዳብር። ሳይሞቱሰ በቁም መቀባበር መቼ ይሆን የሚያበቃው
እያልኩ አባካችሁ ሌላ አሳዛኝ ድርጊት ከመፈጸሙ በፊት በፍጥነት መላ በሉ። ለዛሬው የታዘብኩትን በዚህ መልክ ጀባ ልበል
ብዪነውና፤ በጥሞናና በቅንነት እንድትመለከቱት አደራ እላለሁ። በቸር ይግጠመን።
አመሰግናለሁ ። ከታዛቢ አነዱ
ሞትን የመረጡ ወጣት ሴቶች የመጀመሪያውን ብቻኛ የነፃነት ተጋድሎ ምዕራፍ ከፈቱ። የምዕተ ዓመቱ ማህጸን ተስፋን ሰነቀ!
ከሥርጉተ ሥላሴ (ሲዊዘርላንድ ዙሪክ)
„የእመቤት ጣይቱ የመንፈስ ንጥር ፍላጎት „ሚሚ ሳራ ለምለም ሜላት እሙዬ“ ቀድመው ዓወጁት፤ ይህንን የጥበብ ውጤት እንደ ዘወትር ጸሎት ቁጭ ብዬ አዳምጠዋለሁ። ፍለጎቱና ሊያስተላልፍ የፈለገው መልዕክት ምንድ ነው በማለት። ፍልስፍናውስ? ነጻ የሆነች ሀገር ፤ ትንቢት፤ ራዕይ፤ ተስፋ የትናንት የሴቶች ብቃት፤ የዛሬ መጋፋትና መገለል፤ መረሳት ለምን? ነገስ በዚህ ከተቀጠለ ምን ይሆን ዕጣው? መፍትሄውስ? የልጆቹ የከበረ ተግባር ሁሉንም አመሳጥሯል። ጥያቄውንም እራሱ ቁልጭ አድርጎ መልሷል። እጠብቀዋለሁ! ለእኔ በጣም ትርጉም አለው። እንዲሁ አልተመልኩት ነበር። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ህዝብ ፍጹም የተለዬ ህዝብ ነው። ሲወድም ሲጣል አስተምሮ ነው። ዬኢትዮጵያ ህዝብ መምህር ነው ተንባይም!
በተጨማሪ እኔ የረዳት አውሮፕላን አብራሪ ሃይለመድህን አበራ ወላጅ እናት የሰጡት ቃለምልልስ አጋጣሚ እሱ ባለቤቱ ያሰናደው ነው። በዬትኛውም ሁኔታ የትም ቦታ የምትገኝ ሴት ብቃቷን እንድናይ፣ እንድናስተውል መስታውት እንዲኖረን እግዚአብሄር ሁኔታውን አመቻችቶ የፈቀደበት አጋጣሚ ነው ብዬ ነው ያሰብኩት። አሁን ማን ይሙት ከዛች የጣነ ሃይቅ ዳርቻ ነፋሻማ በጣም ትንሽዬ የቅመም ምርት ገጠራማ ከተማ ከደልጊ ተፈጥረው፤ እርግጥ በኑሯቸውም ባህርዳር ከተማም ትልቅ ቢሆንም ሴት ቀና እንዳትል ያለው ማህበራዊ ተጽዕኖ ሁሉ ተቋቁሞ የበለጸገው ብቃታቸው እንደዛ አይነት የለማ የመንፈስ ብስለት ሳዳምጥ ፈጽሞ የማይገመት ነበር። እኔ ብቻ ሳልሆን ያዳመጠው ሁሉ በተመስጦና በአድናቆት ነበር የገለጸው። ይህ ሁሉ ለሁላችንም አንድ ነገር ይነግረናል „ሴቶችና የተመሰጠረው ብቃታቸው ከጊዜ ጋር መምጣቱን“ ዓይናችን – እዝነ ልቦናችን ከፍተን እንድንመረምረው …. ከልብ ሆነንም እንድናዳምጠው አሳስቦናል። „አስተውሉ“ ይላል ቃሉ ….
ስለሆነም ነው የዘንድሮ የ2006 የካቲት መግቢያና መሸኛው ገድል እዬሠራ ያለው። እነሆ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያዊ ወጣት ሴቶች ውስጣቸው የተቃጠለበትን መራራ ዬጎጥ አስተዳደር፤ ፊት ለፊት ወጥተው አወገዙ። „አትከፋፍሉን! አሉ በድፍረት። አንዲት ሀገር! አንድ ህዝብ! በማለት አወጁ። ኑሮ ከበደን፣ ኑሮውን መቋቋም አልቻልንም ሲሉም የሽፍታውን አስተዳደር የወያኔን ልማትና ፖሊሲው ቅብ ጭላጭ መፈክር አፍርድሜ አሳጋጡት።
ነፃ ትውጣልን አብነታችን ርዕዮት አለሙ ሲሉ በአንድ ድምጽ አስተጋቡ። ወንድሞቻችን አርበኞቻችን ይፈቱልን በማለት በቁርጠኛ ድምጽ ገለጹ አቡበከር፣ እስክንድር፣ ውብሸት፣ አንዷለም፣ ናትናኤል፣ በቀለ፣ የፖለቲካ እስሮኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይፈቱ! ነፃነት፣ ነፃነት፣ ነፃነት እንዴት ያለ ዕጹብ ድንቅ የሚመረምር የገዘፈ ተግባር ከወኑ።
ይህ ንጹህ መንፈስን ዘረኛው ወያኔ እንዴት መግፋት እንዴት መገፍተር ይቻልል? የፍርሃቱ ማስታገሻ ካቴና ነውና አደረገው። ነገም ግን ህዝባዊ አመጽ ከዚህም ብሶ ጠንክሮ ይቀጥላል። ዛሬ ጸጥ ለጥ ብሎ የሚገዛው የወያኔ ህግ „እንብኝ“ ሲገንፍል ቦታ የለውም። የተከፋ ህዝብ፤ የተባሰ ህዝብ በማናቸውም ጊዜ አምቆ ያዘውን እሳታዊ ቁጣ ያፈነዳዋል … ዋ! ያች ዕለት! ዋ! ያቺ ሰ ዓት!
ይህ መሰል የአደረጃጃትና የእንቅስቃሴ መንገድ ማቆሜያ የለውም፤ ሰንሰለት፤ ባሩድ፤ አፈና፤ ማስፈራራት፤ ወቀሳ፤ አይገድበውም። ሱናሜን የትኛው ሳይንስ አስቆመው፤ ገታው። የህዝብን አመፅም ምንም ማንም ኃይል ሊያስቆመው ከቶውንም አይችልም። የነፃነት ራህብ፤ የዜግነት ራህብ፤ የዴሞክራሲ ራህብ ፈጽሞ የማይቆም መገድ ነው። ብራቦ! ሰማያዊ የልብ አድርሶች ናችሁ።
ተመስገን! ነገ ሰው አለው። እናት ሀገር ኢትዮጵያ ተተኪ አላት፤ ዳምኖ ጨፍግጎ የነበረው ተስፋችን ብሩኽ ጨረር በወጣቶቻችን በራ! ደመቀ! አንድነትና መኢህድድ አዘጋጅተውት በነበረው ሰልፍም ወጣት ሴቶቻችን አብረው በአጋርነት በግንባር ቀደምትነት „ከባዶ ጭንቅላት በዶ እግር ይሻላል“ ሲሉ ነበር የተደመጡት። ተደገመ!
በአፍሪካው አህጉራዊ ጽ/ቤት፤ በኢትዮጵያ ዋና ከተማ በአዲስ አባባ የጣይቱ ልጆች፤ የምንቴ ልጆች፤ የዘውዲቱ ልጆች
„እንብኛ! አሻም! በቃህ ጎጠኛ ወያኔ!“ ከረፋኽን አሉት ነገሩት …. ያንገሸገሻቸውን የጎጥ የከፋፍለህ አስተዳደር በሰላማዊ ትግል ድምፃቸውን አሰሙ። ይህ ነው የሚፈለገው። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ „በቃኝ“ ማለት። ትግሉ አሁን እዬተከላከለ አይደለም። እያጠቃ ነው። ይግርማል ሴቶች በዚህ ደፋር ድንቅ ሞገዳም ድምጽ የነፃነትን አንደበት ሞሸሩት! ኮራንባችሁ እነ – አርበኛ! ተስፋችን ጣልንባችሁ እነ – ሰማዕት! እግዚአብሄር ይስጣችሁ። ይጠብቅልንም። እኛም ከጎናችሁ ነን።
ሴቶች በቃኝን በብዙ መልኩ መግለጽ ይችላሉ። ሆድ አደሩ ቢወዳችው፤ ቢያፈቅራቸው ሀገርንና ህዝብ ከገደለ ጋር
አብሬ ጎጆ አልመሰርትም በማለት፤ ሲሞት ቀብር ባለመገኘት፤ የወያኔ ቡችላ ሱቆች ላይ ግብይትን በማቆም፤ በወያኔ ማናቸውም ተቋምት አማራጭ አስከ አላቸው ድረስ ማዕቀብ በመጣል፤ በማህበራዊ ኑሮ የወያኔ ቀንዶኞችን ሰላምታ በመንሳት „ እንቢተኝነት“ በሁሉም ቦታ በማናቸውም ጊዜ ማደረግ ይችላሉ። ከዚህ በላይ ምን መከራ ሊመጣ ነው?! በሀገር በህዝብ ታሪክና ክብር የሚቀና ምቀኛ የሽፍታ አስተዳደር እኮ ነው ኢትዮጵያን እየገዛ ያለው።
እንደ እኔ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ምቹ የሆኑ ህሊናዊ ሁኔታዎች ተሟልቷዋል። ሙሴው ደግሞ „ዕንባ“ እራሱ ነው። የወ/ሮ ዘነቡ እራቅን ስለመሆናቸውም በዚህ ተገለጠ። „በቃን! ገማህን!“ ባዶ ቀፎ ባዶ ሳጥን ነው። ልቅላቄ የሌለው ሙጣጭ አተላ …..
እነክላራ ትግሉን ሲጀመሩት በዚህ መልክ ነበር። ልክ በ103ኛ ዓመቱ የመጀመሪያው ብቻኛ የኢትዮጵያ ሴት እህቶች ድምጽ ራሱን ችሎ ተደመጠ። ተስተጋባ። ኮፐን ሀገን አዲስ አበባ ላይ – ወሸኔ የእኛ ቀንበጦች። ይህ የተጋድሎ ታሪክ ነገ አፍሪካንም ሊያካልል የሚችል አዲስ ገድል ነው። አፍሪካ ተማሪ ኢትዮጵያ አስተማሪ። ወያኔ እንዲህ ይራገፋል። ወያኔ እንዲህ መለመላውን ይቀራል። በወያኔ ላይ ያልሸፈተ ልቦናና መንፈስ ከቶውንም የለም። ከሊቅ እሰከ ደቂቅ፤ ከታዳጊ እሰከ አዛውንት።
እሺ እኛስ የእነኝህ እህቶቻችን እስር ቢቀጥል ምን ማድረግ ይኖርብናል? አዲስ ፈንድ አቋቁመን ቤተሰቦቻቸውን ቀጥ አድርገን መያዝ አለብን። ለእኩልነት መታገል ማለት ይሄው ነው። ለኣለም አቀፉ ማህበረሰብ ዝርዝሩን እዬተከታተልን
በባለቤትንት ማሳወቅ አለብን። ድምጻችን፣ ፍላጎታችን፤ ውስጣችን፤ ለገለጸ ኃይል ማናቸውንም መሰዋዕትነት ለመቀበል መዘጋጀት ይኖርብናል። ቀጠሮ የለም ዛሬውን መጀመር አለብን። ጊዜ ሳናባክን። በማናቸውም ሁኔታ ተገናኝተን። እኛ ሴቶች ውጭ የምንኖረው የነፃነት ትግሉ ቤተኞች ለእህቶቻችን አጋርነታችን በተግባር መግለጽ ይኖርብናል። ይህ አመት በሁሉም ቀዳዳ ተገኝተን ትንቢቱን ዕውን ለማድረግ መትጋት ይኖርብናል። የእኛ ነፃነት ከሀገራችን ነፃነት፤ የእኛ የእኩልነት ጥያቄ ከህዝባችን እኩልነት ጋር የተጋባ ነው። ለዘለቄታ ሥር ነቀል ለውጥ ጠንክረን እንሥራ።
ለነበረን የከበረ ጊዜ ምስጋናዬ በፍቅር ላኩኝ – ለእኔዎቹ።
ሴቶች በመሆን ይገለጻሉ!
ሴቶች በበልህነት ይተረጎማሉ!
ሴቶች አስቀድሞ በማዬት ይታወቃሉ!
ፈተናን ከመፈጠሩ በፊት አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ኢትዮጵያዊነት!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።