Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ከሐይማኖታዊ ይዘቱ ይልቅ ፖለቲካ ለሚሸተው የቤተ ክህነቱ ስብሰባ የትውልዱ ፖለቲካዊ ምላሽም ያስፈልገዋል

$
0
0

የሰሞኑ በቤተክህነት በአቡነ ማትያስ ሰብሳቢነት የተደረገው ጉባኤ እና በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የተሰነዘረው የፈጠራ ክስ፣በመቀጠልም በኢቲቪ ዜና ላይ የተላለፈው ስብሰባውን አስታኮ ”ምዕመናን ነቅታችሁ ጠብቁ” መሰል ዜና ሁሉ አንድ ነገር ያሳያል – በቤተ ክርስቲያን ላይ አንድ የአደጋ ደወል ከቅርበት እየተሰማ መሆኑን።
Holy sinod addis ababa
ስብሰባው ላይ ወቀሳ የሰነዘሩት እና የፈጠራ ክሶችን በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ያወረዱቱ ባብዛኛው የሚጠቅሱት የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ሳይሆን የአቶ መለስን ንግግርን እና በዓለም ላይ አሉ የተባሉ የፅንፈኛ አሸባሪ ድርጅቶች ስምን መሆኑን ስንመለከት ጉዳዩ ፖለቲካዊ መሆኑን እና ፖለቲካዊ ምላሽ የሚሻ መሆኑንም ጭምር ያመላክታል።
ስብሰባው ቤተክርስቲያንን የተዳፈረ ነው

ከሁሉ በፊት ስብሰባው የቤተ ክርስቲያንን ሕጋዊ መስመር ተከትሎ አለመደረጉ ቤተ ክርስቲያንን የተዳፈረ ነው።የቤተ ክርስቲያን የበላይ አካል መንፈስ ቅዱስ ነው።በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው ደግሞ ቅዱስ ሲኖዶስ ነው።የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እስኪሰበሰብ የሚከናወኑ ተግባራት በቋሚ ሲኖዶስ ስር የሚታዩ መሆናቸው ይታወቃል።ይህ ስብሰባ ግን ቋሚ ሲኖዶስንም አላማከረም።አዲስ አድማስ ቅዳሜ ጥቅምት 1/2007 ዓም ስብሰባውን አስመልክቶ ”የጠቅ/ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፓትርያርኩን ተቃወሙ” በሚል ርዕስ ስር እንዲህ የሚል አስነብቧል ”ዋና ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ÷ ‹‹አኹን ወደ ስብሰባው ስገባ ነው መልእክቱን የሰማኹት፤ አጀንዳውም ከመቅረቡ በፊት ከቋሚ ሲኖዶሱ ወይም ከእኔ ጋራ ምክክር አልተደረገበትም፤›› በማለት ስብሰባው ከመዋቅሩና ከዕውቅናቸው ውጭ የተጠራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡” ይላል።

በአቡነ ማትያስ የተመራው ስብሰባ ከተለቀቁት ተንቀሳቃሽ ስዕሎች እና ተከትሎም በኢቲቪ ከቀረበው ዜና አንፃር አጠቃላይ ሂደቱ ሁለት ዋነኛ ዓላማዎች እና ሶስት የማስፈፀምያ ስልቶች ይታዩበታል።እነርሱም –

1/ የቤተ ክርስቲያን ሕግ አውጭ እና ውሳኔ ሰጭ የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስን በሕገወጥ እና የካድሬ ስብስብ ውሳኔዎች የመተካት፣ የማለማመድ፣ ብሎም የመቀየር ሂደት

በስብሰባው ላይ የተሰጡት አስተያየቶች፣ አቡነ ማትያስን የመጨረሻው የውሳኔ ሰጪ እያደረጉ የተሰጡ ነበሩ።በቤተክርስቲያናችን ስርዓት ግን የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ ቅዱስ ሲኖዶስ ነው።በስብሰባው ላይ የተነገረን ግን አቡነ ማትያስ እንደሆኑ ተደርጎ ነው።መንግስት በአቡነ ጳውሎስ ፕትርክና ዘመንም ሆነ ከዝያ ወዲህ በፈለገው (እሱ ያረካኛል ባለበት) ደረጃ የኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን ለመቆጣጠር ብዙ ጥረቶች ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል።ይህ ማለት ግን ላለፉት ሃያ-ሶስት ዓመታት አልተቆጣጠረም ለማለት አይደለም።ቁጥጥሩ አርክቶታል ወይንስ አላረካውም ነው ጥያቄው።

2/ የቤተ ክርስቲያንን ገንዘብ፣ተንቀሳቃሽ እና የማይንቀሳቀስ ንብረት በሙሉ በቁጥጥር ስር ማዋል
በእዚህ ስር አሁንም በግለሰቦች እና በሙሰኛ ባለስልጣናት ጭምር የምመዘበረውን የቤተክርስቲያንን ንብረት እና ገንዘብ ስልታዊ በሆነ መንገድ ሙሉ በሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር ማድረግ ሲሆን ይህም ቤተ ክርስቲያን በቀጥታ የስርዓቱ ርዕዮተ ዓለም አስፈፃሚ ለማድረግ የታለመ ነው።
እዚህ ላይ ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት ተግባራት ለማከናወን ሶስት የማስፈፀምያ ስልቶችን መከተል አስፈልጎታል።እንደርሱም –
ሀ/ እንቅፋት ይሆንብኛል ወይንም በከፍተኛ ደረጃ ይቃወመኛል ያለውን፣ ማኅበረ ቅዱሳንን ከወዲሁ ሰበብ አስባብ ፈልጎ ማስወገድ ወይንም (ለናሙና የተቀመጠ የተግባር ቤት ያልሆነ) ማኅበር ማድረግ፣
ለ/ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከውስጧ በሚነሱ የዶግማ እና የቀኖና ቀሳጮች እንድትታመስ ማድረግ እና ቤተክርስቲያንን ለሚገዳዳደሩ በእምነት የማይመስሏት በቤተ ክርስቲያኒቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ የወሳኝነት ሚና እንዲኖራቸው ማድረግ። ነገር ግን ይህ የሚሆነው በኢህአዲግ የጎሳ ፖለቲካ የተጠመቁ እስከሆኑ ድረስ ብቻ ማድረግ እና
ሐ/ ቤተ ክርስቲያን የሰው ኃይል እና የገንዘብ አቅሟን ሊያጎለብቱ ይችላሉ የሚባሉ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች፣ማሻሻያዎች ወዘተ የኢህአዲግን ርዕዮተ ዓለም እስካላራመዱ ወይንም በሚያራምዱት እጅ ሙሉ በሙሉ እስካልተዛወረ ድረስ ከወዲሁ ማክሸፍ የሚሉት ዋነኞቹ ስልቶች ናቸው።
ለእዚህ ነው እንግዲህ ማኅበረ ቅዱሳንን አይን ባፈጠጡ እና የተናጋሪዎቹ ህሊና ከሃይማኖታዊ ይልቅ ፖለቲካዊ ሽታው በሚሰነፍጥ ደረጃ ባልዋለበት ውሎ ሲወቅሱ የተሰሙት።
የችግሩ መፍትሄ ከእግዚአብሔር በታች በእያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን ልጅ እና እንደሀገር በሁሉም ኢትዮጵያውያን ላይ አርፏል።

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው እርምጃዎቹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን የህልውና ጉዳይ የሆኑትን ዋና ዋና ምሰሶዎችን የሚነካ ምናልባትም እንደ ሀገርም ለመቀጠል የሚያሰጋን አደገኛ ሂደቶች በስርዓቱ እየተፈፀመ መሆኑን አመላካች ነው።የችግሩ መፍትሄም ከእግዚአብሔር በታች በእያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን ልጅ እና እንደሀገር ደግሞ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ላይ አርፏል።እንደትናንት በቸልታ የሚታለፍበት ጊዜ ግን አብቅቷል።
በመሆኑም አሁን እያንዳንዱ ሰው ከእራሱ ጋር የሚማከርበት ወሳኝ ጊዜ ላይ ነው ።በመፍትሄነትም መታሰብ ከሚገባቸው ጉዳዮች ውስጥ ከእዚህ በታች የተጠቀሱት አምስት ነጥቦችን ላቅርብ።እነርሱም –

1/ቤተክርስቲያንን የሚያውካትን (ከሃይማኖት ቀሳጮች) በተጨማሪ የኢህአዲግን ተግባር አንጠርጥሮ መለየት፣
2/ ከሃይማኖታዊው መንገድ ባልተለየ ፖለቲካዊ ምላሽ መስጠት፣
3/ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የሁሉም ሳትሆን በጎጥ እና በመንደር በሚያስቡ ፖለቲከኞች ስር የከፋ ሁኔታ ወደ ፊትም እንደሚፈጠር ጠንቅቆ መረዳት እና ከጊዜያዊ ተግባር እና ብስጭት ይልቅ ተከታታይ እና ዘለቄታነት ያለው ተግባር ላይ ማተኮር፣
4/ በስልጣን ላይ ባለው መንግስት ፖሊሲ ሳብያ ቤተክርስቲያ የገጠማትን ችግር ለሁሉም አካላት ማስረዳት እና በቂ የቅስቀሳ ሥራ መስራት እና
5/ እናት ቤተ ክርስቲያናችን እና ኢትዮጵያ ሀገራችንን አይናችን እያየን ስትጠፋ ዝም የማለትን ውርስ አባቶቻችን እንዳላወረሱን እና የውዴታ ግዴታችን እንደሆነ ጠንቅቆ መረዳት የሚሉት ይጠቀሳሉ።

ጉዳያችን
ሰኞ ጥቅምት 3/2007 ዓም (ኦክቶበር 13/2014)


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>