ዘ-ሐበሻ ከጥቂት ሳምንታት በፊት መምህር ግርማ ወንድሙ በቅዱስ እስጢፋኖስ ቤ/ክ እንዳያጠምቁና ትምህርት እንዳይሰጡ መታገዳቸውን እስከ እግድ ደብዳቤው በማቅረብ መዘገቧ ይታወሳል። የርሳቸው ጉዳይ አሁንም አነጋጋሪነቱ እንደቀጠለ ይመስላል። ለዚህም ነው በአዲስ አበባ ታትሞ የሚወጣው ላይፍ መጽሄት መምህር ግርማን ቃለ ምልልስ አድርጎ አቅርቧል። ለግንዛቤ ከጠቀመ በሚል በድረገጻችን አካፍለናችኋል።
ላይፍ፡- ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን የጥምቀትና የትምህርት አገልግሎት እንዳይሰጡ የታገዱበት ምክንያት ምንድነው?
መምህር ግርማ፡- ምክንያቱም ሰው በመዳኑ እና የዲያቢሎስ ሚስጥር በመጋለጡ እንዲሁም ህብረተሰቡ ለከፋ መንፈስ ግንዛቤው እየጨመረ መምጣቱ ነው፡፡ የሆነው ሆኖ እኔ እየሩሳሌም አገልግሎት ሄጄ እያለ የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ መልክአ ኃይል አባ ሚካኤል የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ነን በሚሉ ግለሰቦች አማካኝነት ቤተክርስቲያኑ ውስጥ ብዙ ወጪ ወጥቶበት ተገንብቶ የነበረውን መድረክ እና የምዕመና መቀመጫዎች በመንቀልና በመሰባበር ከጥቅም ውጪ አደረጉት፡፡ እነኚህ ሰዎች ያልተረዱት ቢረዱትም ግድ የማይሰጣቸው ያወደሙት ንብረት የእኔ ሳይሆን የእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን መሆኑ ነበር ፤ በቤተክርስቲያን ዙሪያ በሰንበት ትምህር ቤት ብዙ ችግሮች ይሰማሉ፡፡ እነኚህ የሰንበት ትምህር ቤትን ምግባርና ስርዓት ሳይኖራው በስም ብቻ የተጠለሉ አንዳንዶቹ እንደ ክርስቲያን ሳይሆን የእርኩሳን አሰራር የሚፈጽሙ እንደነበር ብዙዎች አገልጋዮች ያውቃሉ፡፡በተጨማሪም ማታ ማታ በድራፍትና በመጠጥ ዙሪያ ሲንካኩና ሲጨፍሩ አምሽተው ጠዋት መጥተው ከበሮ የሚደበድቡ ናቸው፡፡ ጸጉራቸው እንኳን ምስክር ነው፡፡ የተንጨባረሩ ፍጹም ቦዘኔና ዘላን መልክና ገጽታ ያላቸው ናቸው፡፡ ለአባቶቻቸው ክብር የሌላቸው፡፡ ማዋረድ ስራቸው የሆነ ፤ የስነ ምግባር መንፈሳዊ ትምህርትን ከምንም ቦታ ያልያዙ እንደዚሁ የመደዴነት ባህሪ ያላቸው ናቸው፡፡ በእነዚህ ነው የቤተክርስቲያኗ መድረክና ንብረት ያወደሙት፡፡
ላይፍ፡- ከዚህ በፊት በማን ጥሪ መሰረት ነው እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አገልግሎት ሲሰጡ የነበረው ?
መምህር ግርማ፡- በደብሩ አስተዳዳሪ መላከ ሰላም አማካኝነት ነበር፡፡ ከዚያ በፊት ቦሌ አቦ ፤ ኪዳነምህረት ፤ ፉሪ ሥላሴ ፤ ጭቁኑ ሚካኤል ፤መገናኛ እግዚአብሔር አብ በጠቅላላው በከተማይቱና ወጣ ባሉ ያሉ ደብሮች አገልግያለሁ፡፡
ላይፍ፡- ለስንት ዓመት አገልግሎት ሰጥተዋል?
መምህር ግርማ፡-ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ እዚህ አዲስ አበባ ያልተቋረጠ አገልግሎት ሰጥቻለሁ፡፡
ላይፍ፡- በእነዚህ አገልግሎት ዘመናት ለቤተክርስቲያን ምን አስተዋጽ አበርክተዋል ?
መምህር ግርማ፡- በእስጢፋኖስ ደብር ጣሪያው ውሃ ያስገባበት ወቅት 3 ሚሊየን ብር ገቢ አሰባስቤ አድሳት አድጌአለሁ፡፡
ላይፍ፡- ለምን ያህል ህሙማን ከህመማቸው የመፈወስ እና ትምህርት አገልግሎት ሰጥተዋል..?
መምህር ግርማ፡- ለ4 ሚሊየን ሰው የፈውስ አገልግሎት ሰጥቻለሁ፡፡
ላይፍ፡- በተለይ በምን አይነት ህመም ሲሰቃዩ የነበሩ ሰዎችን አድነዋል ?
መምህር ግርማ፡- አይናቸው የጠፋ ፤ ሰውታቸው አልታዘዝ ብሎ አልጋ ላይ ውለው የነበሩ ፤ እጅና እግራቸው ሽባ የነበሩ ሰዎችን ፈውሻለሁ፡፡
ላይፍ፡- ሁላችሁም የእግዚአብሔር ቃል የእመቤታንን በረከት የምታስተምሩበት ቤተክርስቲያን ለምን እንዲህ አይነት መከፋፈል መጣ ብለው ያስባሉ ?
መምህር ግርማ፡- በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ እንክርዳድ በስንዴው መሀል እንደሚዘራው ሁሉ ያም በቤተክርስቲያን ውስጥ አለ፡፡ ገበሬው መልካም ስንዴን ዘራ የሚለው ከውጭ አይደለም፡፡ ዘሩ እዚያው ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ በቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ህይወትና በልቦና ውስጥ መጀመርና በስጋ ህይወት መጀመር ልዩነት አለው፡፡ አምኖ መጀመርና ሳያምኑ መጀመር የእዚያን ያህል ነው፡፡ ሰሞኑን ወደ ቤተክርስቲያን ገብተው የሚኖሩ በጣም ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ከተለያዩ የአስማት ስራ ጋር ወደ ቤተክርስቲያን ሲጠጉ ብዙ መልካም ነገር አይጠበቅባቸውምና ይህንን የሚመለከት ‹‹በማለዳ መያዝ›› የሚለው መጽሀፌ ላይ ሰፋ ባለ መልኩ አስቀምጬዋለሁ፡፡ ንጹህ የአምልኮት ፍላጎትና እንዲሁ ደግሞ በደብዛዛው በሚመላለሱ ሰዎች መካከል ዲያቦሎስ በደንብ ይሰራል፡፡ በተለይ ኦርቶዶክስ እምነት ላይ ሰይጣን ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል፡፡ ከታሪክ እውነታም አንጻር እነዚህ ሰዎች ህይወት ውስጥ የተለየ እድል አለ፡፡ ገብቶ ይቀመጥና በጎው መጥላት መልካሙን እንደክፉ ማየት ማሳደድ ያለው መናፍቆች ላይ ሳይሆን እኛ ጋር ነው ያለው፡፡ ይህ ደግሞ የሃይማኖቱ አንዱ በረከት ነው፡፡ ለምን ፈሪሳውያንን ክርስቶስ በመጣ ጊዜ እምነቱን ተራ ወግና ተራ የሆነ የይስሙላ አድርገውት ነበር፡፡ ያ ሂደት ደግሞ እንደዚሁ በቆየን ቁጥር የአዲስ ኪዳንንም ህይወት እንደዚያ ነው የሚሆነው፡፡ ወደ ፈሪሳውያን ጠላት ይሄዳል፡፡ በዚህ ጊዜ እውነቱ እየጠፋ በቤተክርስቲያን ውስጥ ጣልቃ ይገባሉና ያንን ለመለየት የመንፈስ ቅዱስ ስራም የአጋንንት የቅንነትም ስራ ስለሚያስፈልግ ዛሬ ያ ቅንነቱ እና በጎነቱ በክፋት በተንኮል በምቀኝነት የተሞላ ስለሆነ ያ ሂደት ሊያደርገን አልቻለም፡፡
ላይፍ፡- ብዙ ሰባኪያን ወደ እርስዎ ፕሮግራም የማይመጡት ለምንድነው?
መምህር ግርማ፡- ይህንን የፈውስ ሂደት ስላለመዱት ልክ እንደ መተት እንደ ጠንቋይ አሰራር አድርገው እስከዛሬ ድረስ ሲያወሩ እንደቆዩ ያው የተለመደ ነገር ነው፡፡ስላልተለመደ እንግዳ ነገር ነው የሆነው፡፡ በተለይ በግለሰብ ጸጋ አልተለመደም፡፡ ይህንን ያልተለመደ ነገር እንዲህ ሲወጣ ሁሉም እየተረባረበ ማጨለም ነው የሚፈልገው፡፡ የእግዚአብሔር ስራ ደግሞ ስለማይጨልም ሂደቱን ጠብቆ ይበራል፡፡ ከዚህም በፊትም የተደረጉብኝ ዘመቻዎች ብዙ ናቸው ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ይህ እንዲያውም የመጨረሻው ደካማ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ሰዎች መንፈሳዊ አንድነታቸው በክፉ ሰዎች መንፈስ ተመቷል፡፡ በራስ እይታም ተመቷል፡፡ የምቀኝነት መንፈስ አጠናክረው በመያዛቸው ምክንያት የእግዚአብሔር ጸጋ በረከት መለያ መንፈስ አጥተዋል፡፡ አንድነትና ተስማምቶ መዝለቅን በዚህ ዘመን ውስጥ የምንጠብቀው ጉዳይ አይደለም፡፡ ግን እውነት ዞሮ ዞሮ ደረጃዋን ጠብቃ ስለምትወጣ ያን ያህል አስጊ አይደለም ማለቴ ነው፡፡
ላይፍ፡- ከአስተዳዳሪው ጋር የነበራችሁ አለመግባባት ከየት የመጣ ነው?
መምህር ግርማ፡- አስተዳዳሪው መልአከ ኃይል አባ ሚካኤል በአንድ ላይ ቁጭ ብለን በተካፈልንበት ጉባኤ ላይ ሁለት ክፍል ያለው ኮንዶሚኒየም ገዝቼ እንድሰጣቸው ጥያቄ አቅርበውልኛል፡፡
ላይፍ፡-ለቤተክርስቲያን የሚገባውን ሙዳይ ምጽዋት ይካፈላሉ ?
መምህር ግርማ፡- ኧረ በጭራሽ ምጽዋቱ ለቤተክርስቲያን ነው የሚሆነው፡፡
ላይፍ ፡- ታዲያ ከየትኛው ገቢዎ ላይ ነው አስተዳዳሪው ኮንዶሚኒየም ገዝተው እንዲሰጧቸው የጠየቁዎት ?
መምህር ግርማ፡-እንዲያው ለትራንስፖርት ፤ ለምንም ወይም ሲዲ ወይም መቁጠሪያ የምሸጠው አለ፡፡ ከእሱ እንደምንም አቻችልና ግዛልኝ ፡፡ አለበለዚያ ደግሞ ሕዝቡን አስተባብረህ የበረከቱ ነገር ወደ እኔ አዙረው ነው ያሉት ሰውየው፡፡
ላይፍ፡- እኛ ከዚህ በፊት ስለዚህ ኮንዶሚኒየም ግዙልኝ ብለው ጠይቀው እንደሆነ ጠይቀናቸው በጭራሽ አልጠየኩም በማለት መልስ ሰጥተው ነበር ?
መምህር ግርማ፡- እውነት በቃል ማስተባበር ይቻል ይሆን ? ከህሊና እና ከእግዚአብሔር መሰወር ግን እንዴት ይቻላል ?
ላይፍ፡- ታዲያ ምን ምላሽ ሰጠዋቸው ?
መምህር ግርማ፡-በወቅቱ ያንን ማድረግ አቅሙ ስለሌለኝ ጥያቄያቸውን እንደማልቀበል ገልጬላቸዋለሁ፡፡
ላይፍ፡- ምላሽዎ በግሳጼ ወይስ ሌላ ገጽታ ነበረው…?
መምህር ግርማ፡- በግሳጼ መልኩ አልመለስኩም፡፡ ለምን ያው የሕዝቡ ችግር ስለማውቅ ሁኔታዎችን ስጠብቅ በራሱ ጊዜ ገነፈለና የሰውየው ኃይል ወጣ፡፡ እኔ መገሰጽ አልፈለኩም፡፡ ምክንያቱም ችግሩን አውቃለሁ፡፡ እንዲህ የተወሳሰበ የሙስና አሰራሮች ከመጀመሪያው ጀምሮ በየደረጃው ስር ሰደዱ ናቸው፡፡ በአንድ ዘመን ሳይሆን እየተንከባለሉ የመጡ ችግሮች ናቸው፡፡ ሰውየው ወደ ማዕረጉ እና ወደ አስተዳደሩ ሲመጡ 60 ሺህ ብር ከፍለው ነው ለዚህ የበቃሁት ይላሉ ፤ ያንን በተለያዩ መንገዶች ማቻቻል አለብኝ ማለት ነው፡፡
ላይፍ፡- የኮንዶሚኒየም ግዢ ይህን ያል ያወጣል ብለው ግምቱን ነግርዎት ነበር ?
መምህር ግርማ፡- በቃ ሁለት ክፍል ያለው ኮንዶሚኒም ነው ይገዛልኝ ያሉት ፡፡ ግምቱንም ያውቁታል፡፡
ላይፍ፡- እርስዎ አለኝ የሚሉት የፈውስ ጸጋ ከየት የመጣ ነው ይላሉ ?
መምህር ግርማ፡- ይህ እኮ አንድና ሁለት ነው እንደሚባለው አይነት ፎርሙላ ወጥ አድርገህ የምታሳየው ነገር አይደለም፡፡ ይህ በጸሎት በስግደት በቅዱስ ቁርባን በመመጽወት ከሰማይ የሚለቀቁት እንጂ ከማንኛውም ሰው የምትገዛው ወይም የምትለውጠው ትርፍ ያለው ነገር አይደለም፡፡ ይህ ከሰማይ የሚሰጥ እንጂ በስጋዊ ጥበብባ ዘዴ ወይም ምርምር ወደ ላብራቶሪ የሚመጣና የሚገኝ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር አሰራር ነው፡፡ የእግዚአብሔር አሰራር ደግሞ አለምም ሆነ ስጋውያን አያውቁትም፡፡ መንፈሳውያንም ተቸግረዋል፡፡ በዚህ ዘመን ያሉ የገዛ አባቶቼ እንኳን ሳይቀሩ ይህንን መንፈሳዊ ጸጋ ለመቀበል በጣም ይቸገራሉ፡፡ ምክንያቱም ከእኛ በኩል ካፈሰሰ ነው እኮ አሁን ችግሩ፡፡ ከእኔ በኩል ካልፈሰሰ እንዴት በዚህ ዘመን ከእግዚአብሔር ይመጣል ፤ የሚል ዋጋ ቢስ እና ተስፋ አስቆራጭ የመንፈሳዊ ህይወት ጉዞን የለመዱት ባህሪ ለማንጸባረቅ ሲሞክሩ ነው አሁን ነገሮች ወደዚህ አይነት አጣብቂኝ ውስጥ የሚገቡት፡፡
ላይፍ፡- እርስዎ ተሰጥቶኛል የሚሉት የመንፈስ ጸጋ ስያሜ ሰጥተውታል ?
መምህር ግርማ፡- እንደዚህ ያለ ነገር የለም እንጂ ምን ስሜ ይሰጠዋል ? ክፉ መናፍስን የሚቃወም የእግዚአብሔር መንፈስ ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስና ክፉ መንፈስ ደግሞ አይገናኙም፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ስጦታ ደግሞ ክፉውን መለየት ፤ ክፉው ማስወገድ ነው፡፡ በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ አጋንንትን አወጡ ይል የለም እንዴ? በአሁኑ ዘመን አጋንት አስገባ ቢባል ሁሉም ይወደኛል፡፡ አጋንንት ማስወጣት እኮ ነው የተለየ ጠንቋይ ያደረገኝ፡፡
ላይፍ፡-አለኝ የሚሉት የመንፈስ ጸጋ ወደ ሌላ ሰው ማስተላለፍ ይችላሉ ? ወይስ እርስዎ ጋር ነው ሊቀር የሚችለው ?
መምህር ግርማ፡- የኤልያስ መንፈስ በኤልሳ እንዳደረ ሁሉ የፈለገው ሁሉ ያገኛል፡፡ እኔም የማስተምረው እኮ ክርስቲያኑ ራሱን ችሎ እንዲቆም ነው፡፡ ጠላቱን እንዲጋፈጥ ፤ ክፉ መንፈስ እንዲያሸንፍ ፤ የዲያቢሎስ ትውልድ መሆኑ እንዲቆም ፤ ከዚያም በላይ የመንፈስ ቅዱስ ስራ የእግዚአብሔር ክብርና ኃይል እየጨመረ እንዲመጣ ፤ የአለም ጥበብ ከእግዚአብሐየር መላዕክ አሰራር ጋር ክርስቲያኖች በረከት ውስጥ እንዲገቡ ነው፡፡፡ አሁን ለምሳሌ በአሜሪካ በስልክ የሚሸኝላቸው ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ በእጄ ማስረጃ አለኝ፡፡ በስልክ የሚሸኝላቸው ራዲዮ አቢሲኒያ ላይ ከቁትር 1 ጀምሮ እስከ 34 ድረስ ያለውን ትምህርት በመከታተል እየጸለዩ እየሰገዱ በመቁጠሪያ እየቀጠቀጡ መንፈሱን ያዳክሙታል፡፡ ከዚያ በኋላ መንፈሱ ራሱ እኔ አይ ጥላ ነኝ ፤ ቡዳ ነኝ ፤ አብሬ ነው የተወለድኩት እያለይነግራቸዋል፡፡ በመጨረሻ ከተዳከመ በኋላ አንዳዴ ራሱ ‹‹ሸኙኝ›› ብሎ ይደውላል፡፡ በእጄ የቀረጽኳቸው ከ200 በላይ በስልክ የሸኝሁላቸው ሰዎች አሉ፡፡ አሁን አባቶች ይህ ነገር ሲሰሙ ይደነግጣሉ፡፡ ምክንያም እንዴት በስልክ ሰይጣን ይወጣል ብለው አንድ ወቅት ላይ አቅርበው ጠይቀውኛል፡፡ ስለዚህ ጸጋው የቤተክርስቲያን እንጂ የእኔ አይደለም፡፡ መቁጠሪያው የቤተክርስቲያን ነው፡፡ ውዳሴው የቤተክርስቲያን ነው፡፡ መላከ ትግሉ የቤተክርስቲያን ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የእኔ የያዝኳቸው የምትሀት አሰራር የለም፡፡ ስለዚህም ሁሉም ህዝብ በውጭ አለም ያለው በተለይ ከክፉ መንፈስ ጋር ያለውን ፍልሚያ በሚገባ ስለተገነዘበ እያንዳንዱ ራሱ በመቁጠሪያ እየተጠቀመ የሸኝውም አለ፡፡
ላይፍ፡- አባቶች እርስዎ የሚሰጡት መንፈሳዊ ጉባኤ ተገኝተው በረከት ይሰጡ ነበር ወይ ?
መምህር ግርማ፡- እኔ በማገለግለው ላለመገኝት ብዙዎች ይሸሻሉ ተሰልፈው ዝቅ ብለው የህዝብን ችግር ለማየት እስከ አሁን በጎ ህሊና አላገኝሁም፡፡ ሃገር እንደ አቡነ እስጢፋኖስ የጅማው ኃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አይነቱ በተደጋጋሚ የህዝቡን ችግር ተረድተው በተደጋጋሚ ወደዚያ እየሄድኩ ሳገለግል መንፈሳዊ ድጋፋቸውን ለህዝቡ ካለው ችግር ለልማቱም ከማሰብ ቢርሌ የሰጡት ቦታና ስራ አለ፡፡
ላይፍ፡- አባቶች እርስዎ የሚሰጡት መንፈሳዊ አገልግሎት አስተያየታቸው ምንድነው ?
መምህር ግርማ፡- ብዙዎች ይህንን መንፈሳዊ ድርሻ ለመወጣት በማደርጋቸው ጥረቶች ላይ በጎ ድጋፍ የላቸውም፡፡ ከተለያዩ አይነት መንገድ ለመዳንም ይሰጣሉ፡፡ ነገር ግን አንዳዶች እንዲያውም የሸናሻም መተት ይህን ያደርጋል፡፡ የሸናሻም አስማት ይህንን ይሰራል እያሉ ለአስት አሰራር ትልቅ ድጋፍና የሰይጣን አሰራር ትልቅ ሞራል ሲሰጡ ነው የሚሰማው፡፡
ላይፍ፡- ይህንን እርስዎ የሚያደርጉትን መንፈሳዊ አገልግሎት ሌሎች አባቶች ያምኑበታል ?
መምህር ግርማ፡- እኔም በጣም ግራ የሚገባኝ ዲያቢሎስ የሚያደርገው ጥቃት በመጽሀፍ ቅዱስ በረጅሙ እና በስፋት ጥልቀት ባለው ሁኔታ ገልጿል፡፡ ሐዋርያት አጋንንትን እያወጡ የሰዎችን ደህንነት ሲያበለጽጉ ይታያል፡፡ በቤተክርስያንም እደዚሁ በመንፈሳዊ አገልግሎት በመንፈስ ቅዱስ ስራ እንደሚሰራ ይታወቃል፡፡ እንግዲህ ሰዎች በክፉ መንፈስ አሰራር ወይም አያምኑም አልያም በእዚአብሔር አሰራር አያምኑም፡፡ በዚህ መንታ መንገድ ላይ መታየት አሁን አይቻልም፡፡ ምክንያም የእግዚአብሔር ሕዝብ በዲያቢሎስ ተጠቅቷል፡፡ ወይ ዲያቢሎስ እንዲበላ ማድረግ ነው አልያም በቤተክርስቲያን መንፈስና ጸጋ ህዝቡ ችግር ውስጥ ገብቶ ችግሩን ማየት ነው፡፡ ገለልተኛ ሆኖ መኖር አሁን አሁን ጊዜው አይደለም፡፡ ስለዚህ ያምናሉ አያምኑም የሚለው ነገር እርሳው እኔን ቢረዱኝ ደስ ባለኝ፡፡ በተሰጣቸው ጸጋ ክፉ መንፈስ ነው ካሉ የእኔን መንፈስ ማወጣት መቻል፡፡ ሁሉም ቢተባበሩኝ መልእክት አስላልፋለሁ ፡፡ እንዲያውም በቤተክርስቲያን ይኖር የነበረ አስማተኛ መንፈሱን አስወጣንለት ብለው ለአለም ዜና ቢያቀርቡ ደስ ባለኝ ነበር፡፡
ላይፍ፡- ቤተክርስቲያኗ ወታደርና ነጋዴ የቤተክርስቲያን አገልጋይ አይሆንም የሚል ሕገ ደንብ አላት፡፡ እርስዎ ግን መንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ከመግባትዎ በፊት ወታደር እንደነበሩና እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ በኋላ 1.5 ሚሊየን የሚገመት ቤት ገዝተው እየኖሩ ነው ይባላል በዚህ ላይ ምን ይላሉ ?
መምህር ግርማ፡-ዛሬ ሰማዕቱ ሀገር ጠባቂ የምንለው ቅዱስ ጊዮርጊስም የመቶ አለቃ ወታደር ነበር፡፡ ግብጽ ውስጥ ያሉ ብዙ ታላላቅ አባቶችም እንደዚያው ናቸው፡፡ በአሁንም ዘመን ያሉ ብዙ መነኮሳቱ እስከ ጳጳሳቱ ወታደር የነበሩ ናቸው፡፡ ወታደር ማለት የእግዚአብሔርን ስራ አይሰራም ማለት አይደለም ፡፡ እኔ ደግሞ ልቀድስ ላቁርብ አላላኩም ፤ በተሰጠኝ ጸጋ ላገልግል ነው ያልኩት፡፡ ቤት ምናምን የሚሉት ቤቱን የገዛልኝ የተፈወሰ ሰው ነው፡፡ ቤቱን የገዛልኝ እግዚአብሔር በሰው በኩል ነው ፡፡ ቤቱን የገዙልኝ ሰው በተጨባጭ ከጎኔ አሉ፡፡ ይህንን እንደ አንድ እንደ ትልቅ ነገር ማንሳት በራሱ ምንን ያመለክታል ፤ ምቀኝነትን ነው ፤ ያው ከደማችን ውስጥ የተለመደ ምቀኝነት ስላለ እንጂ ከነዚህ ሁኔታዎች በሙሉ እንዳሰራ የሚያደርጉ አይደሉም፡፡
ላይፍ፡- እርስዎን አስማተኛ እና ጠንቋይ ናቸው የሚሉዎት ሰዎች ምላሽ ምንድነው ?
መምህር ግርማ፡- እኔ አስማተኛ ከሆንኩ እኔ ጋር መጥተው አስማቱን ማውጣት ነው፡፡ እኔ ጋር መጥተው አስማቴ የት ጋር እንደተቀበረ ፈልገው ማውጣት ነው፡፡ ክንዴ ላይ ወይም እግሬ ላይ ወይም ጭንቅላቴ ላይ እንዳለ ደንበኛ ራጅ ይዘው መጥተው ፈልገው ማውጣት፡፡ ወይም መንፈስ ከሆነ ያስወጡልኝ፡፡ ቢረዱኝ እኮ ለእኔም ደስ ይለኛል፡፡ ግልግል ነበር፡፡ እስቲ አስማቴን ኑ እና አስወጡልኝ እባካችሁ ስለ እግዚአብሔር ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ብዬ እለምናችኋለሁ፡፡