Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የኢትዮጵያ ጠላቶችና የአምላክ እጆች –አበራ ሽፈራው

$
0
0

አበራ ሽፈራው /ከጀርመን/

ኢትዮጵያ ለዘመናት ተከብራና ሳትደፈር የኖረች አገር ለመሆኗ ታሪክ ምስክር ነው። ይሁንና አገሪቷ ለዘመናት የተለያዩ ትልልቅ ችግሮችን አሰተናግዳለች ።ከነዚህ ችግሮች ውስጥም የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ይገኙባቸዋል ።ካጋጠሟት ችግሮች ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ሀገሪቷንና ህዝቦቿን ለማጥቃት ከውስጥም ከዉጭም የተነሱ ጥቃቶች ቀላል አልነበሩም።እነዚህ ጥቃቶች በተለያዩ ሀይሎች ተፈጽመዋል።ከዉስጠ አገሪቷን በሚመሩ መሪዎችና ሥርዓቶቻቸዉ፣ ከጐረቤት አገራትና መሪዎቻቸዉ፣ከሩቅ አገራትና መሪዎቻቸው፣በአረብ አገራትና መሪዎቻቸዉ፣የአገር በቀል ሀይሎችና ቡድኖች ይገኙባቸዋል። ይሁንና የህዝቡ አገር ወዳድነትና የአምላክ ድጋፍ ጠላቶቿን እያዋረደ እንደጣላቸው አይተናል ፣ሰምተናል፣አንብበናል።

የኢትዮጵያ ጠላቶች እነማን ናቸዉ? ምን አይነት የአምላክ እጅ አገኛቸዉ? ለምንል ዛሬ የምላችሁ አለኝ። እነዚህ በግለሰብ፣ በአገር ደረጃና በቡድን ተደራጅተዉ ይችን አገር የወጉ አወዳደቃቸዉ እጅግ የከፋ ከመሆኑ የተነሳ ይህ የሰው ብቻ ሳይሆን  መለኮታዊ ሃይል ከኋላው አለ ፤እነዚህም የአምላክ እጆች ናቸው ለማለት ተገደድኩኝ። ለምን? ብትሉኝ የአወዳደቃቸው ሚስጥር ስንመለከት አገሪቷና ህዝቦቿ ካለን አቅምና ጉልበት በላይ የሆነ ሀይል በጠላቶቿ ላይ እየወደቀ ትላንትም ሆነ ዛሬ የአገሬ ጠላቶች አልቀናቸውም እና ነዉ።ለዚህ ነው በርዕሴ ላይ «የአምላክ እጆች» የሚለውን ሀረግ ለመጨመር የተገደድኩት።

የኢትዮጵያ ጠላቶች ያልካቸው እነማን ናቸው? ለሚለኝ በእኔ ዕይታ ኢትዮጵያና ህዝቧን ለመበታተንና ጉዳት ላይ ለመጣል ፣ጥቅሞቿን አሳልፈው ለመስጠትና ለመጉዳት፣አገሪቷን በጦርነት ለመውጋት የተነሱና የወጉ፣ለግልጽ የኢትዮጵያ ጠላቶች በባንዳነት ያገለገሉና እነዚህን ተግባራት በቀጠታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያቀዱና የተገበሩ ሁሉ የኢትዮጵያ ጠላቶች ናቸው ብዮ አስባለሁ። እነዚህ ጠላቶቿም የተነሱት ከውስጥም ከውጭም እንደነበርና ዛሬ የኢትዮጵያ ጠላቶች፦ግለሰቦች፣ አገሮችና መሪዎቻቸዉን ምን እንደገጠማቸውና የአምላክ እጆችም በነዚህ የኢትዮጵያ ጠላቶች ላይ እንዴት አንደተሰነዘሩ እንመልከት። ይህን ስል ግን የሀገሬ ህዝቦች ከእነዚህ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በአምላክ ድጋፎች ያደረጓቸው ትግሎች ቀላል እንዳልነበር እና አምላክም እየረዳቸው ኢትዮጵያ ለዛሬ እንደደረሰች ሳልናገር አላልፍም።

1.ግብፅ

ግብፅና መሪዎቿ ለዘመናት የኢትዮጵያ ቀንደኛ ጠላት በመሆን መኖራቸውን የማያውቅ ኢትዮጵያዊ የለም ።ይህንን ያልኩበት ምክንያት የአባይ ጉዳይና የግድብ ግንባታው ትኩሳት በሁለቱ አገሮችና ባለስልጣናት አካባቢ ያለው እሰጣ-ገባ በቅጡ ያልበረደ ትኩሳት ሆኖ ያለ በመሆኑ ነው። ግብፅና ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝና በመንፈሳዊ ጉዳዮች ለዘመናት ትስስር ያላቸው ቢሆንም በግብጽ በኩል  ለዘመናት የተፈረጀብን ጠላትነት ግን እኛን ሲጐዳን ቆይቷል። ግብጽ በኢትዮጵያ እድገቶች ላይ ስትፈጥራቸው የነበሩ ማነቆዎችን ልንቋቋማቸው ያልቻልንባቸው ሁኔታዎች ሲገጥሙን ቆይተዋል። በቅርቡ የነበሩትን የግብፅ መሪዎችንና በህይወት ያሉትን በጥቂቱ እንመልከት።

ሀ. ሙባረክና መንግስታቸው

በሙባረክ  መንግስት ጊዜያት ግብፅ በመካከለኘው ምስራቅ አገራትና በአረቡ ዓለም አካባቢ ባላት የፖለቲካ ተጽዕኖ ፈጣሪነትናና ተሰሚነት እንዲሁም ይህንን ጉዳይ ለማስፈፀም ይረዳት ዘንድ ከአሜሪካ በምታገኛቸው ወታደራዊ ድጋፎች ጡንቿዎቿን አዎፍራ በአገራችን ላይ በተለይም ከአባይ ወንዝ ጋር በተያያዙና በሌሎች የውሃ ነክ የእድገት እቅዶቻችንን ለመተግበር የሚያግዙ ብድሮችንና እርዳታዎችን በማስከከል፣ በማደናቀፍና ጭራሹን አንዳይከናወኑ እንቅፋቶችን በመፍጠር ያደረገቻቸው መጠነ ሰፊ የዲፕሎማሲ ስራዎች በአገራችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርስ ቆይቷል።

ግብፅ ኢትዮጵያን ለመበተን በተለያዩ ጊዜያት በኝሁ መሪ ዘመን በተደረገው እንቅስቃሴ  ውስጥ የኤርትራዉን የሻዕቢያ ቡድንና የህወሓት/ኢህአዴግ ቡድንን በማስታጠቅ በኢትዮጵያ ላይ ትፈጥራቸው የነበሩት ቀጥተኛ ያልሆኑ የጦርነት ዘመቻዎች በሀገራችን ላይ ትልቅ ጥፋት ሲፈጥር ቆይቷል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ግብፅ የአረቦችን ዕቅድና የራሷን ግብ ለማስፈጸም እነዚህን የአገር ውስጥ ጠላቶችን በማስታጠቅ ቀላል ግምት የማይሰጠው ወታደራዊ ድጋፍ ሰታደርግ ቆይታለች፤ዛሬም ሆነ ትላንት ግብፅ ለምትፈጽማቸው ግልጽ ጥቃቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ወታደራዊም ሆነ የዲፕሎማሲ አቅም ባለመኖሩ ከእኛ በላይ የሆነዉ አምላክ በተለያዩ ጊዜያት ለዓመታት በኢትዮጵያ ላይ እጁን ሲቀስር የነበረዉን የሙባረክን መሰሪ መንግስት ለመጣል እንደፈርኦን ዘመን መለኮታዊ እጁን በግብፅና በሙባረክ ላይ በመጣሉ ዛሬ ሙባረክ ስለኢትዮጵያ ሊያስቡ ቀርቶ እራሳቸዉንና አስተሳሰባቸውን ይዘው የሰዉን ፍርድ እየተጠባበቁ ይገኛሉ፤ ግብፅንም ለማተራመስ ትልቅ ምክንያት ሆነዋል።

ለ. ሞርሲና መንግስታቸው

ሌላኛው የግብፅ መሪ ሞርሲ የአባይ ግድብ ግንባታ የሚል ሀሳብ በኢትዮጵያ መንግስት ሲነሳና ግንባታው መጀመሩ ሲበሰር እንደአባቶቻቸዉ ዘመን ዛሬም የአባይ መነሻ የሆነችውን ሀገራችንን እንደሚፋለሙ ዛቱ «እስከ ደም ጠብታም እንታገላለን አሉ» አስከመቼ በወንበር ላይ አንደሚቀመጡ ሳያውቁ፤ይህንን ንግግራቸውን በቅጡ ሳያጣጥሙ የአምላክ እጅ ፈጣን የሆነ ምላሽን በመስጠት በእሳቸው ላይ ብቻ ሳይሆን በተከታዬቻቸዉም ላይ ትልቅ ድንጋጤ ወዳቀባቸው፤ የሳቸዉም ዕጣ-ፋንታ በግልጽ አስከአሁን አልታወቀም።

በነገራችን ላይ የአባይ መገደብ የኢትዮጵያን ጥቅም እስከአስጠበቀ ድረስ ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የአባይ መገደብ መብት እንዳለዉ እስከታመነበት ድረስ ፣በገለልተኛ አካል በቂ ክትትልና ቁጥጥር እስከተደረገበት ድረስ ፣ከግንባታዉ ከሚገኘዉ ግዙፍ የገንዘብ በጀት ለመመዝበር ከቋመጡ የህወሓት/ኢህአዴግ ቡድን ብዝበዛ ነፆ እስከሆነ ድረስ ፣በተጠናና የአገሪቷን የወደፊት ጥቅምና የግድቡን ደህንነት ባስጠበቀ መልኩ እስከተገነባ ድረስ መገደቡን አልቃወምም። ይሁንና እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች ለህዝብና ለሀገሪቷ ጥቅም ካልዋሉና እንደተለመደው ህወሓት/ኢህአዴግ የፓርቲዉን የንግድ ተቋማት የሚያደልቡ ሰፋፊ ፐሮጀክቶችን መርጦ በማሰራት የታወቀና የአገር ኪስ አውላቂ በመሆኑ በአባይ ግድብ ግንባታ ላይ ሳይሆን በህወሓት/ኢህአዴግ ቡድን ድርጊት ላይ ቅሬታዬ ከፍተኛ ነው።

2 .የሶሪያው አል-አሳድና መንግስታቸው

ዛሬ በአለማችን በትርምስ የምትታወቀው ሶሪያ ለአለፉት ሁለት አመት ከግማሽ አሳዛኝ ክስተቶችን አሳልፋለች፤በሶሪያ ያለው መከራ አሳዛኝ ቢሆንም ሶሪያ ኢትዮጵያን ለመበታተን ታደርገው የነበረው ሴራና ተንኮል ቀላል አልነበረም፤ የተወሰኑ የአረብ አገራትና ሌሎች የኢትዮጵያ ጠላቶች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውስጥ ሶሪያ የነበራት ሚናና ኢትዮጵያን ወደብ አልባ አገር አንድትሆን የነበራት ህልም ቢሳካም ለራሷም አልበጃትም፤ሶሪያ የኤርትራዉን ሻዕቢያን ወታደራዊ ስልጠና በመስጠትና  ወታደራዊ ትጥቅ በማስታጠቅ የብዙ  የኢትዮጵያንንና የኤርትራውያንን ደም በማፋሰስ የነበራት ሚና ቀላል አልነበረም ፤ ሶሪያ ነግ በኔ ባለማለቷና የመሪዎቿም አምባገነንነት ተጨምሮ ዛሬ ሶሪያና መሪዎቿ ትልቅ የአምላክ እጆች አግኝቷቸዋል።

3. አቶ መለስና ርቲያቸው

ሁላችንም በዚህ ዓለም የማይቀር ሞት አለብን ፤ ሙት ወቃሽ አያድርገኝ ብዮ ጉዳዩን አላልፈውም።«ባለዕራዩ መሪ» ተብለው በደጋፊዎቻቸው የሚጠሩት አምባገነኑ አቶ መለስ የሚሊዮኖችን አይንና ጆሮ በግዳጅ ሽፍኑ ብለው በዘረኝነት ፣በተንኮል፣ የአገሪቷን ገንዘብ በማሸሽ፣ ለሽማግሌዎችና ለምሁራን ምንም ክብር ባለመሥጠት፣ የአገሪቷን አካልና መሬቶች ለባዕዳን አሳልፈው በመስጠት፣ የብዙ ወጣት ኢትዮጵያውያንን ህይወት በየምክንያቱ በሚፈጠሩ ግጭቶች በማስጨረስ ፣የጅምላ ግድያን በመምራት፣ ህዝቦችን ከመኖሪያ ቀያቸው በማፈናቀል በግልጽ ይታወቃሉ ። አኚሁ አምባገነን መሪ ከራሳቸው ፓርቲም ሆነ ከፓርቲያቸው ውጪ ማንም ሊበገራቸው እንዳይችል አደርገው የፈጠሩት ሥርዓት ሊከልላቸው አልችል ብሎ በፍጹም ባልታሰበና ባልተጠበቀ ሁኔታ በድንገት ከዚህ ዓለም መለየታቸው ትልቅ ደውል በአገራችንና በፓርቲያቸው ላይ የተደወለ ደውል ነው ብዬ እገምታለሁ። እኚሁ ሰውና ፓርቲያቸው የህወሓት ትግል በተጀመረባቸው ወቅቶች «እግዚአብሔር የለም» በሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰው እንደነበርና ይህንኑ ዓለማቸውን ለማስፈጸም እንደሞከሩም የቀድሞ የትግል ጓዶቻቸው በጻፏቸው ጽሑፎች ላይ ማንበብ ይቻላል፤ ይሁንና የኝህ ሰው አሟሟት ምንአልባት ወደ አይምሮአቸው ለመመለስ ለሚፈልጉ ለህወሓት ጨካኞች ደውል የደወሉ የአምላክ እጆች ናቸው፤ ዛሬ ህወሐት ወዴት እየተንደረደረ እንዳለ ማንም የሚያውቀው ሀቅ ነው «ሌቦች ሲካፈሉ እንጂ ሲሰርቁ አይጣሉም»ና የሰረቁትን የሚካፈሉበት ግዜ ደርሷል የዛን ግዜ እናያቸዋለን።

 

4. የሊቢያው ጋዳፊና መንግስታቸው

የሊቢያው መሪ ጋዳፊ በተለያዪ ጊዜያት ኢትዮጵያን ለመበታተንና በኢትዮጵያ ጥቅሞች ላይ ሲያነጣጥሩ፣ ሲያሴሩና እንደቆዩ የሚታወቅ ሲሆን ከድርጊቶቻቸው ውስጥ ህወሓቶች በትጥቅ ጠንክረው ዛሬ አገራችን ከአፓርታይድ ሥርዓት ባልተናነሰ የጭቆና ቀንበር ውስጥ  እንድትወድቅና ለትልቅ ውርደት እንድትዳረግ ማድረጋቸውን ታሪክ መዝግቦላቸዋል። በተጨማሪም እኚሁ የሊቢያ መሪ በኢትዮጵያ ጥቅሞች ላይ በተደጋጋሚ የጥቃት ሙከራ ያደረጉ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ የአፍሪካ ህብረት ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ሊቢያ እንዲሄድ ለማድረግ ያደረጉት ሙከራና ወደ ኢትዮጵያ ለስብሰባ በሚሄዱባቸው ጊዜያት እሳቸውና አጃቢዎቻቸው የሚያሳያቸው ተገቢ ያልሆኑ ሥነምግባሮች እጅግ አሳፋሪ የነበሩ ሲሆን እሳቸውም ቢሆኑ በሊቢያ ጨቋኝነታቸው ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያም ጠላትነት የአምላክን እጆች የቀመሱና በአሳዛኝ ሁኔታ ከዚህ ዓለም የተለዩ መሪ ለመሆን በቅተዋል፤ ሊቢያም ብትሆን ዛሬም በልዩ ልዩ ምስቅልቅል ውስጥ እንድትወድቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

 

5. የሱዳኑ መሪ አልበሽርና መንግስታቸው

 

ሱዳን ሰፊ ግዛትን ከኢትዮጵያ ጋር የምትጋራ ስትሆን ለብዙ ኢትዮጵያውያን በመጠለያነት ያገለገለች አገር ነች ፤ዛሬም ሱዳኖች ብዙ ኢትዮጵያውያንን በማስጠለል ባለውለታነታቸውን አስመስክረዋል፤ በሌላ በኩል ግን የሱዳኑ መሪ አልበሸርና ከሳቸውም በፊት የነበሩት የሱዳን መሪዎች ኢትዮጵያን ለማጥቃት በተለያዩ ጊዜያት ያደረጉት ቀጠተኛ ያልሆነ የጦርነት አዋጅና ጥቃቶች ቀላል እንዳልነበሩ ይታወቃል።

 

ሱዳን ኢትዮጵያ ተበታትና ለማየት ያደረገችው ጥረትና ህልም ባይሳካም ኢትዮጵያን ለመበታተን ህወሓት/ኢህአዴግን በማሰልጠን ሻዕቢያን በመርዳትና በማሰታጠቅ የፈጸመችው ደባ ቀላል ግምት ቀላል የሚሰጠው አይደለም ። ሱዳን ዛሬ ለሁለት የተከፈለች አገር፣ በማያቋርጥ ጦርነት እየተተራመሰች የምትገኝና ደረቃማዉንና በርሃማዉን መሬት ይዛ እንድትቀር የተገደደች አገርም ሆናለች ።

 

መሪዋም አልበሽርም ቢሆኑ በፈጸሙት የዘር ማጥፋት ተግባር የተነሳ በዓለም የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የሚፈለጉና በሄዱበት ቦታ ሁሉ የአይጥና የድመት ኑሮ ለመኖር የተገደዱ መሪ ለመሆን በቅተዋል። ሱዳን ያለችበትን ሁኔታ ስንመለከት እሷም ነግ በኔ ባለማለቷ የአምላክ እጆችን ከቀመሱ የኢትዮጵያ ጠላቶች አንዷ ለመሆን በቅታለች።

 

6. የኢራቁ ሳዳም-ሁሴንና መንግስታቸዉ

 

የኢራቅ አምባገነን  መሪ የነበሩት ሳዳምሁሴንና መንግስታቸው  እንደሶራያዉ መንግስት ሁሉ  አረቡ ዓለም  በአገራችን ላይ በነበረው የተሳሳተ ዕቅድና ሀሳብ ኢትዮጵያንን ለማተራመስና ለመበታተን  በሚደረገዉ ትግል ዉስጥ የሻዕቢያን  ጦር በማስታጠቅና ከፍተኛ የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ይታወቃሉ ። እኝሁ ሰው በሃገራቸውም ሆነ በአገራችን ላይ ለፈፀሙት በደል በእርግጠም የእጃቸውን ያገኙ ሰው ለመሆን በቅተዋል። አገራቸው ኢራቅም ብትሆን እስከዛሬ ላልበረደ ግጭት ተዳርጋለች ።

 

7. የሱማሌዉ ሲያድባሬና መንግስታቸዉ

 

ሶማሊያ ሃገራችን በመስቀለኛ መንገድ ላይ በነበረችበት በመጀመሪያዎቹ የደርግ መንግስት ወቅቶች ኢትዮጵያን ለመውረር ሰፊና ግዙፍ የሆነ ጦር ያዘመተችና የብዙ ኢትዮጵያውያንን ነፍስ የቀጠፈና ንብረት ያወደመ ጦርነት ያደረገች ሲሆን የኢትዮጵያ ሠራዊት፣ የኢትዮጵያ የሚኒሻ ሠርዊትና የሶሻሊስት አገራት ወታደሮች በተለይም የኩባ ወታደሮች ድጋፍ ታክሎበት ወራሪውን ጦር ለማሶጣት የተደረገው ትግል ቀላል አልነበረም።

 

ሶማሊያ ኢትዮጵያን ከወረረችበት ጊዜያት ጀምሮ እርሷም ብትሆን ሰላሟን ማጣት ብቻ ሳይሆን መሪዋም ሲያድባሬም ወደ ማክተሙ በመምጣታቸውና አገሪቷ በመበታተኗ ሶማሊያ ለሁለት አስርት ዓመታት ካለመሪ ለመኖር የተገደደች አገር በመሆን ቆይታለች። በእግጥም ኢትዮጵያን የወጉ ሁሉ ዋጋቸዉን ከአምላክ እጅ እንደሚያገኙ ሌላኛው ምስክር ነው።

 

8. የደርግና የንጉሱ መንግስታትና መጨረሻቸው

 

ሁለቱም ስርዓቶቸ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በማስጠበቅ ደረጃ የነበራቸዉ ጥንካሬ ቀላል ባይባልም በሌላ በኩል በህዝቦቻቸው ላይ የነበረዉ የአስተዳደር ዝቅጠት፦ የህዝቦችን እኩልነትና መብት በመንፈጋቸዉ፣ ህዝቦች ለሚያነሷቸው የመብት ጥያቄዎች ተገቢዉን መልስ ከመስጠት ይልቅ በሃይል በመጠቀማቸዉ፣ በነዚህና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ተያይዘዉ በተፈጠሩ ትልልቅ ጉዳዮች ምክንያት ኢትዮጵያ ዛሬ ለገጠሟት ችግሮች ያደረጉት አስተዋፅኦ ቀላል አይደለም። ለሁለቱም መንግስታቶቸ አምላክ የሰጠዉ ምላሽም ውድቀታቸዉንም አሳዛን አንዲሆን አድርጐታል። እነዚህ ሁለት መንግስታቶች በህዝቦቻቸዉ ላይ ከፈፀሙት በደል ብንነሳ በተለይም የደርግ መንግስት የብዙ ወጣቶችን ህይወት በመቅጠፍ የፈፀማቸው ወንጀሎች፣ በአምላክ ላይ የተፈጸሙ ግልፅ ክህደቶችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለውድቀት አጋልጠውታል። ንጉሱም ቢሆኑ በተመሳሳይ ድርጊታቸው ፍፆሜያቸው መጥፎ ሆኖባቸዋል።

 

መጠቃለያ

 

ዛሬም ኢትዮጵያና ህዝቦቿ በለየላቸው ጨቋኞች ሥርዓት እጅ ወድቀናል፤ የእነሱም ዕጣፋነታ ከላይ ካየናቸው የተለየ እንደማይሆን እርግጠኛ ነኝ ፤ ይሁንና ለውጥ የሚፈለግ ቢኖር መታገል ይኖርበታል።

 

የጽሑፉ ዓላማ ተቀምጦ የአምላክን እጆች እንድንጠብቅ አይደለም ፤ ተነስቶ መታገል ለፍትህና ለነፆነት ትልቁ መንገድ ነዉና እንነሳ ለማለት ነው፤ የኢትዮጵያን ጠላቶች ለመጣል የአምላክ እጆችም ያግዙናል።

 

እግዚአብሔር  ኢትዮጵያን ይባርክ።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>