ጉዳያችን
በባህር ዳር የአንድ እንግሊዛዊን ድንገተኛ ሞት እየመረመርኩ ነው ያለው ወያኔ/ኢህአዲግ ”በታህሳስ 9/2007 ዓም የአምስት ሰዎችን ሞት እና የአንድ መነኮሳይትን ጨምሮ የሌሎች በርካታ ኢትዮጵያውያን ደም መፍሰስ ትክክል ነበር” የሚል ሰልፍ እያዘጋጀ ነው።
ወንበዴ መሪ በሆነበት ሀገር ፍትህ መቀለጃ ትሆናለች።ሕግ፣ስርዓት እና ምክንያታዊነትን ዜጎች ቢናፍቁም ህገወጦች ስልጣን ከተቆናጠጡ ዙርያቸውን በሀገር ውስጥ እና በባህር ማዶም ጭምር የሚኮለኩሏቸው ለሆዳቸው እና ለጥቅማቸው ብቻ የሚሰለፉቱን ነውና ብዙ ጆሮ የሚጠልዙ ነገሮችን መስማት ይለመዳል።
ታህሳስ 9/2007 ዓም በባህር ዳር ከተማ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስቲያን ይዞታነት የመስቀል ደመራ እና የጥምቀት በዓል የሚከበርበት ቦታ ለግል ባለ ሀብት የሚተላለፍ መሆኑ እና ከቀሪው ቦታ ላይ ደግሞ ተቆርጦ ለመንገድ ሥራ የሚውል መሆኑ እንደተሰማ የባህር ዳር ነዋሪ የእምነቱ ተከታይ በከፍተኛ ቁጣ ወጥቶ ተቃውሞውን መግለፁ ይታወሳል።
በወቅቱ የስርዓቱ ታማኝ ወታደራዊ ፖሊሶች በሰላማዊ ሰልፈኛው ላይ በወሰዱት ጨካኝ እና አረመኔያዊ ተግባር 5 ሰዎች ሲሞቱ አንድ ደካማ መነኮሳይት እና በርካቶች በዱላ እና በጥይት ጉዳት እንዲደርስባቸው ሆኗል።ጉዳዩን አስመልክቶ በዕለቱ በምሽቱ 2 ሰዓት የስርዓቱ ልሳን በሆነው በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የተላለፈው ዜና ሰላማዊ ሰልፈኞቹን ”ከሽብርተኛ ወገኖች ጋር የወገኑ፣”ወዘተ የሚል አሳፋሪ ዜና ከመለቀቁም በላይ ምንም አይነት ይቅርታ ከመንግስት አለመጠየቁ እና ይልቁንም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታት ቤተ ክህነት አንዳችም አይነት መግለጫም ሆነ አሁን በመንበሩ ላይ የተሰየሙት ፓትሪያርክ አቡነ ማትያስ አንዳችም የሚያፅናና ቃል ለምእመናን በቦታው ተገኝተው አለማስተላለፋቸው ይታወቃል።
የእዚህ አይነቱ አሳፋሪ ተግባር ምዕመናንን በእጅጉ አስቆጥቶ ሳለ ነው እንግዲህ ሌላ አሳፋሪ አረመኔያዊ ተግባር በሕዝቡ ላይ ሊፈፀም መሆኑ የተሰማው።በባህር ዳር የአንድ እንግሊዛዊን ድንገተኛ ሞት እየመረመርኩ ነው ያለው ወያኔ/ኢህአዲግ ”በታህሳስ 9/2007 ዓም የአምስት ሰዎችን ሞት እና የአንድ መነኮሳይትን ጨምሮ የሌሎች በርካታ ኢትዮጵያውያን ደም መፍሰስ ትክክል ነበር” የሚል ሰልፍ እያዘጋጀ መሆኑ የታወቀ ሲሆን ዜናውን ”ነገረ ኢትዮጵያ” በማኅበራዊ ድረ-ገፁ ለቆታል።ጉዳዩ ከፍፁም የለየለት ዘረኛ እና አረመኔያዊ ድርጊት ከመሆኑም በላይ የስርዓቱ ቡድን መሪዎች እና ጀሌዎቻቸውን ፋሽሽታዊ ባህሪ በትክክል የሚያሳይ ነው።
የነገረ ኢትዮጵያን የዛሬ ታህሳስ 17/2007 ዓም ዜና ከእዚህ በታች ያንብቡት።
ገዥው ፓርቲ ባህርዳር ላይ የተደረገውን ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ የሚቃወም የድጋፍ ሰልፍ ሊጠራ ነው በሰልፉ የማይገኝ ቅጣት ይጠብቀዋል ተብሏል።
ገዥው ፓርቲ በአማራ ክልል አስተዳደር ባህር ዳር ከተማ የቤተ ክርስቲያን ንብረት የሆነውን የታቦት ማደሪያ ለመንገድና ለጥቃቅንና አነስተኛ ሱቆች መስሪያ እንዲነጠቅ ማዘዙን ተከትሎ በባህር ዳር ቀደም ሲል የተካሄደውን ህዝባዊ ተቃውሞ ሰልፍ የሚቃወም የድጋፍ ሰልፍ ሊጠራ መሆኑን የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ገለጹ፡፡
መንግስት ታህሳስ 9/2007 ዓ.ም የተደረገውን ህዝባዊ ተቃውሞ የ‹‹ፀረ ሰላም ኃይሎች እጅ እንዳለበት›› በመግለጽ ‹‹ህገ-ወጥ ሰልፍ›› ማለቱ የሚታወስ ሲሆን ባህር ዳር ከተማ የሚገኙት የቀበሌ ካድሬዎች የተደረገውን ህዝባዊ ተቃውሞ የሚቃወም የድጋፍ ሰልፍ ለማድረግ እያስተባበሩ እንደሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ የቀበሌ ካድሬዎች በየ ቤቱ እየሄዱ የነዋሪዎችን ስም በመመዝገብ በሰልፉ የማይሳተፍ ሰው ቅጣት እንደሚጠብቀው እያስጠነቀቁ እንደሆነ ተገልጾአል፡፡ የድጋፍ ሰልፉ ታህሳስ 21 ወይንም 22 ቀን 2007 ዓ.ም ይደረጋል ተብሎ ይታሰባል፡፡
ጉዳያችን
ታህሳስ 17/2007 ዓም