Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የማለዳ ወግ …የኢትዮጵያ አፈር የጠራው ጠቢብ የክብር ጉዞ ፍጻሜ !

$
0
0

መልካም ስም ከመቃብር በላይ ይውላል …!

image-9d7f88cbdecd3715a84ff1e923f19a265e6c 3ebc9096e18394f23acdc537c8db-V_resized_1አርአያነታቸው ፋና ወጊ ሆኖ እያለ ብዙ ያል ተነገረላቸውን ዶር በርናርድ ብሬድሊ አንደር ሰንን ባዘከርኩበት የማለዳ ወጌ የጠቢቡን ህይዎት ከጃማይካ እሰከ አሜሪካ ለመቃኘት መሞከሬ እውነት ነው ። ዛሬም የምቀጥለው ከዚያ ለጥቆ ያለውን የዶር በርናርድን አፍሪካና ኢትዮጵያ ያደረሰውን መንገድ ሲሆን እንደ መግቢያ በአንድ የጥምቀት ዋዜማ ጎንደር ከዶር በርናርድና ከባለቤታቸው ከሲስተር እማዋይሽ ገሪማ ጋር የነበረንን አጭር ቆይታ በጨረፍታ በመቃኘት መጀመሩን ልቤ ፈቅዷል … የፈቀዳችሁ ተከተሉኝ !

ጎንደር በጥምቀት ዋዜማ …

ባልሳሳት ወርሃ ጥር 2004 ዓም ይመስለኛ ል … ጥምቀትን በጎንደር ለመታደም ሲገሰግስ የሚመጣ አውቶቡስ በአባይ በርሃ ተገልብጦ ተሳፋሪው በማለቁ ጎንደርና ጎንደሬው ማቅ ለብሰው ፣ አዝነው ተክዘዋል … ምክንያት አላቸው ፣ ምክንያቱም ከጎንደር ጥምቀት ክብረ በአል ጋር የቴዎድሮስ ሃውልት ምረቃ ሊከበር በዝግጅት ላይ እያለ ከወደ አባይ በርሃ የተሰማው መርዶ የከፋ ነበርና ነው ። መርዶው በመይሳው ካሳ ሃውልት ምረቃና በጥምቀቱ የደመቀ ዋዜማ ስሜታቱ በደስታ ላይ የነበርነውን በአል አክባሪ ሁሉ ቅስም የሰበረ ነበር። በርሃው ወገኖቹን በልቶታልና ፣ ጎንደሬውን አንገቱን በሃዘን ደፍቶ ማቅ ያለበሰው ቀን ቢኖር ይህ ቀን ነበር። ደስታቸውን ለመግለጽ ሳግ እየተናነቃቸው ለቴዎድሮስና ለሚናፍቋት አንድነቷ የተጠበቀች ኢትዮጵያ ያላቸውን ፍቅር በመግለጽ ላይ የነበረው ኢትዮየጵያዊ ከትንሽ እስከ ትልቅ በርሃው በበላቸው ወገኖቹ በሃዘን ቅስሙ መሰበሩና ስሜቱ መጎዳቱን በእያንዳንዱን ፊት ይነበብ እንደነበር አይረሳኝም …

በአባይ በርሃ ገደል ገብቶ ሰው የጨረሰው አውቶቡስ እኔ ፣ ልጆቸና እህቴ በአንድ ሆነን በተሳፈርንበት አውቶቡስ እኩል ከአዲስ አበባ ነበር የተነሳው። ከአዲስ አበባ እስከ አባይ በርሃ ድረስ ከበስተኋላችን ይጓዝ ነበር ። በአባይ በርሃ ደልደል ባለ መንገድ ዳር በአንድነት ለደቂቃዎች እረፍት አድርገንም ነበር ። እኛ ቀድመን አቀበቱን ወጠን ደጅን እንደደረስን ፣ የማይታመነውን አደጋ መርዶ ሰማን… ይከተለን የነበረው አውቶቡስ ከሃምሳ በላይ አብዛኛው እንደኛ ጥምቀትን በጎንደር ሊያከብር የተሳፈረው ወገን ገደል ገብቶ ሰው አንዳለቀ በቀትር የራዲዮ ዜና እወጃ ሰማን! ያ ቀን ለእኔ የሚረሳ እና የሚዘነጋ አይደለም ! በአባይ አፋፍ አንድ ጫፍ እረፍት ባደረግንባት ደቂቃ ሰላምታ የተለዋወጥኳቸውን ወገኖች በሰአታት ልዩነት የማለቃቸውን አሰቃቂ ዜና የሰማሁባት እለት ሆዳችን ተላውሶ አዝነን ከፍቶን ነበር ጎንደር በጥምቀት ዋዜማ የገባነው …

ሃዘን የጎዳው ጎንደሬ ግን በሃዘን ልቡ ተሰ ብሮም ቢሆን ሽርጉዱ ከጓዳ እስከ አደባባይ አድርቶታል። ጎንደሬው ከዘመድ አዝማዶቹ አልፎ ተርፎ ” ኑ በጥምቀት ኢትዮጵያን ተመል ከቱ ! ” በሚል እንግዳ ተጠርቷልና ሃገሬው እን ግዶቹን ሊቀበል ከጓዳ ጥንስስ እስከ አደባባይ ከተማ ማስዋብ ዝግ ጅት ተጠምዷል … ደግ ሞም ወቅቱ የቋረኛው አጼ ቴወድሮስ ሃውልት የሚመ ረቅበት ልዩ አጋጣሚ ሆኖ ተገጣጥሟ ልና አጋጣሚው መሪር ሃዘን እያዘኑ መሳቅም ከመሆን ጋር ተደባልቋል …

የዶር በርናርድ ባለቤት ፣ የታዋቂው አርበኛ ደራሲ ገሪማ ታፈረ ልጅ ፣ ወይም የታዋቂው የፊልም ደራሲና የታሪክ ተመራማሪ የፕሮፊሰር ኃይሌ ገሪማ እህት ሀገር ወዳዷ ትጉህ እመቤት ከሲስተር እማዋይሽ ገሪማ ጋር በየተናኘነው በዚህ በጨነቀው የጥምቀቱ ዋዜማ ነበር ። ሲስተር እማዋይሽና ለጀግናው አጴ ቴዎድሮስ መታሰቢያ ቤተ መዘክር ለማቆም ደፋ ቀና የሚሉት የአስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ባደረጉት ጥረት አንድ እርምጃ የሄዱበት ወቅትም ነበር ፣ ለቴዎድሮስ መታሰቢያ ቤተ መዘክር መስሪያ መሬቱ ተሰጥቷቸው የመሰረት ድንጋይ ተጥሏል ፣ ከተደረገልኝ ገለጻ አልፎ ተርፎ በቦታው በመገኘት የመሰረት ድንጋዩ ያረፈበትን ቦታ ተመልክቻለሁ … በዚሁ አጋጣሚ ሲስተር እማዋይሽ ገሪማን ጎንደሬው አንስቶ ስለማይጠግባቸው ባለቤታቸው ዶር በርናንር ደጋግሜ ጠየቅኳቸው ፣ እማዋ ግን ስለራሳቸውም ሆነ ስለባለቤታቸው ብዙም አይናገሩም ። ሁኔታው ተመቻችቶ እግሬን ጎንደር ላይ ሳሳርፍ ብዙ ስለሚባልለት ጠቢብ ጥቂት ያወሩኝ ዘንድ መወትወቴ ገፋሁበት ፣ ከሲስተር እማዋ ጋር በአንዱ ቀን አብረን ታሪካዊዋን ከተማ ስንዘዋወር ላላሰለሰው ውትወታየ ጀሮ የሰጡት እማዋ በቁልምጥ ስሜን ጠርተው እንዲህ አሉኝ ” ነብያለም ስለዚህን ቅን ፣ ደግና ቸር ባለቤቴን ማንነት እኔ እንዲህ ነው አልልህም ፣ ደግሞም ስጋየ ነውና እኔ ብናገረው አያምርም ፣ ከምን ም በላይ ግን የሃገሬን አፈር ፣ ባህልና ወጉን እንዲያውቅ አድርጌዋለሁ ፣ ዛሬ ከእኔና ከአንተ በላይ ስለምትወዳት እናት ኢትዮጵያ የሚመሰክር የታሪክ ሊቅ ባይባል ተመራማሪ በመሆኑ ደስታየ ወሰን የለወም ፣ እኔ ለኢትዮጵያ ያደረግኩት ስጦታ በርናርድ ይመስለኛል ፣ የሚገርምህ እኔም ሆንኩ እሱ የምንሰራው ለነፍሳችን ነውና ማንም ይህንን ተመልክቶ እንዲያመሰግነን አንፈልግም ፣ በርናርድም የሚልህ ይህንኑ ነው ፣ አትቸኩል ፣ ሰውየውን ታገኘውና ታወጋላችሁ ” ነበር ያሉኝ ፈገግ እያሉ …

ብዙም ሳይቆይ ከቀናት በኋላ ከሲስተር እማዋይሽ ጋር ተገናኘን ፣ በተያዘልኝ ጠሮ መሰረት ከጎንደር ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘውና አባ ሳሙኤል ተብሎ በሚታወቀው መናፈሻና የከብት ማድለቢያ መንደር ስናመራ ቀዝቃዛ ንጹህ ነፋሻማ የቸቸላንና የሳሙና በርን አየር እየማግን ነበር ። … ከጎንደር ወደ አየር ማረፊ አቅጣጫ ፣ የአዘዞ መዳረሻ ሳሙና በር ድሮ ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ነበር። በዚሁ ትላልቅ የጽድ ዛፎች በሚበዙበት አንድ ጫፍ ጀርባውን ለአንድ ቋጥኝ ሰጥቶ የተገጠገጠ ቤተ መንግስት የሚመስል ቪላ ተገንብቷል። ሲስተር እማዋይሽ መኪናቸውን እንደማብረድ እያደረጉ ወደ ቪላው ሲጠጉ ከውጭ በኩል እያመላከቱ ” አየህው በርናርድ ሃኪም ፣ ታሪክ ተመራማሪ ብቻ አይደለም ፣ ይህንን ቪላ ውስጡን በአስገራሚ የጥንታዊ ኢትዮጵያ ቁሳቁስ አሟልቶ የሰራ ” አርክቴክት ነው ! ” ሲሉ በፈገግታ ጠቁመውኝ ወደ ግቢው ገባን …


ከመኪና ወርደን ወደ እንግዳ መቀበያ አዳ ራሹ ስናመራ በግቢው አጥር ስር የተተከሉ አትክልቶችን ውሃ የሚያጠጣ እድሜው መጠ ጥ ያለ ጸጉረ ልውጥ ሰው ተመለከትኩ ። በአ ግራሞት ስቁለጨለጭ ሲስተር እማዋ በሁኔታ ፈገግ አሉና “ሰውየው ይህውልህ ” አይነት ምልክት በፊታቸው እየተነበበ ሰውየውን አስተዋወቁኝ። ሰውየው ዶር በርናርድ ነበሩ …

ዶር በርናርድ በፍልቅልቅ ፈገግታቸው ተቀብለው ሲኮተኮቱ ነበርና አፈር የነካ እጃቸውን እስኪተጣጠቡ ለሲስተር እማዋይሽ አስረከቡኝ ፣ እማዋይሽም በተንጣለለው የእንግዳ መቀበያ አስገቡኝ ። እግሬን ከግቢው ሳስገባ ጀምሮ ኢትዮጵያዊነትን የሚገለጽባቸው በሚያምር ሸክላ በእውቀት የተሰሩ የአበባ ማስቀመጫ እንስራዎች ፣ ድስቶችና ከመሳሰሉት አልፎ ተርፎ አዳራሹ በደረጃው ከፍ ባለ ቅርሳ ቅርስ ፣ ብሔር ብሔረሰቦችን አጉልቶ የሚያሳየው ቁሳቁስ ያጌጠው ቤት ቀልቤን ሳበው ። የቆመው ልቤ መቀመጥን አልወደደውም ፣ ዙሪያውን ማየት ፈልጓል ! ደግነቱ ብዙም ሳይቆይ ዶር በርናርድ ” ይቅርታ ዘገየሁ አይደል? ” ብለው ከተፍ አሉ! ልነሳ የተቁነጠነጥኩት ጎረምሳ ከሃኪሙ ፣ ከታሪክ ተመራማሪው እና ከስነ ህንጻው ባለሙያ ጋር መቀመጥና አፍ ላፍ ግጥሞ ማውራት አማረኝ … ወጋችን ቀጠልን ፣ ዶር በርናርድንና የእህታቸውን ወንድም ፕሮፎሰር ሃይሌ ገሪማ አንድ ሳይሆን በርካታ የሚያመሳስላቸው ነገር እንዳለ ታዘብኩ … ዶር በርናርድ እንደ ፕሮፎሰር ሃይሌ ገሪማ የሚናገሩት ደረቅ እውነት ጥልቅ ነው ፣ የእኔ ትውልድም ሆነ ያ ትውልፍ ስለሚጎድለውና መሆን ስላለበት የሰላ ሂስ ከነ መፍትሔው ፣ ስለ ኢትዮጵያዊነት ባህል ፣ ስለ ታሪክ አሻራውና ስለይትበሃሉ የቅብብሎሽ ጉድለት ጥልቅ ምክክር ሳይሆን ምክርን ሰጡኝ ! ብዙውን ተደምሜ ግራ ቢገባኝ እርስዎ ዜግነትዎ ከወዴት ነው ? አልኳቸው ፣ ሳቁና አላፊ አግዳሚው ግራ እየተጋባ ስለሚጠይቃቸው መሰል ጥያቄ ሲመልሱ ” እኔ 400 አመት በፊት በአሜሪካና በጃማይካ ከምወዳት ሃገሬ ተለያይቸ የቆየሁ ኢትዮጵያዊ ነኝ ! ” በማለት መለሱልኝ ፣ በርናርድ ስለኢትዮጵያ ቀዳማዊ ታሪክ ፣ በባሪያው ንግድ ዘመን ስለተሰደዱት አፍሪካውያን ታሪክ በአስገራሚ ሁኔታ ተንትነው አስረዱኝ … ዝም ጭጭ ነበር ያልኩት … በህዎታቸው ዙሪያ ሰፊ ግንዛቤ የሰጡኝም በዚህ ወቅት ነበር ! እናም ካጫወቱኝና ከተሰራጨው የህይዎት ታሪክ መካከል የበርናርድን የአፍሪካና የኢትዮጵያ ትስስር እነሆ …

ዶር በርናርድ አፍሪካና ኢትዮጵያ …

ከሁሉ አስቀድሞ አንድ ለዚህ ዝክር ቅኝቴ ምንጭ የሆነኝ መረጃ ያገኘሁት የዶር በርናርድ ሬሳ በምድረ አሜሪካ የመጨረሻ ሽኝት የቀረበው የህይዎት ታሪካቸው መሆኑን መሆኑን ልብ በሉልኝ ፣ ከዚሁ መረጃ ጋር ዶር በርናርድን በአካል አግኝቸ ካጫዎቱኝን የመረጃ ግብአት እያዋሃድኩ ለአንባቢያን በሚመች መልኩ እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ ።

የጠቢቡ ሀኪም የህይወት ተልዕኮና የውስጥ ነፍስ ፍላጎት የሚጀምረው ከጃማይካውያን ብርቱ የኢትዮጵያ ወዳጆች ነው ። ከእነ ማርከስ ጋርቬ … በርናርድ ማርከስ ጋርቬ‘ ወደ የስፋዋ የራሳችን መሬት እንመለስ’ ወዳሉባት ጥንታዊ ት ቅድስት የኢትዮጵያ ምድር ሄዶ የማገልገል ፍላጎት በአሜሪካው የተደላደለ ህይዎት ቢወጠንም ምክንያት በባርነት ዘመን የተሰደ ድን የዚያች ሃገር ዜጎች ነን የሚል ብርቱ ምክንያት ነበረው ። ያ ህልሙና ራዕዩን እንዲሳካ ደግሞ የኑሮ አጋሩ የአርበኛው ደራሲ የገሪማ ታፈረ የአብራክ ክፋይ ሀገር ወዳዷ ሲስተር እምዋይሽ ምክንያት ሆነች። እናም ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ ከምድረ አሜሪካ የተጸነ ሰው ቅዱስ ሃሳብ አፍሪካን በመጎብኘት አሃዱ ብሎ ተጀመረ … !

ዶር በርናርድ ታንዛኒያን እና ኬንያን ቀዳሚ ጉብኝት ሲያደርግ በአይኑ በብሌሉ የተመለከ ተው ፣ በአካል ያዳመጠውና የዳሰሰው የአፍሪ ካ ልጆች ገና ያልተቀረፈ ችጋር ነፍሱን አደማት ፣ የቀደምቷ “የዳቦ ቅርጫት “የአህጉረ አፍሪካን የኋልዮሽ ጉዞ ታዝቧልና ነፍሱን አስጨነቃት … አፍሪቃ የምትቃትትበትን የሰቆቃ መንገድ ፣ ጫንቃዋን የያዛትን የትላንቱ የቅኝ አገዛዝ ዛር እንዳልለቀቃት አይቶ አዘነ ፣ ተከዘ ! አጭሩን የታንዛንያ እና የኬንያ ጉብኝት አጠናቆ የሃገሩ ልጆች ጃማይካዎች “የተስፋዋ ምድር !” ብለው ወደሚያምኑባት ኢትዮጵያ አቀና …

ዶር በርናንድ ቅድስት ኢትዮጵያ …

የሚሰገመገመው አውሮፕላን የኢትዮጵያን ምድር ነካ ፣ የተቆለፈው የአውሮ ፕላን በር ተከፈተ ፣ በርናርድ እና ነፋሻው ውብ የተፈጥሮ ጣዕም ያለው የተስፋዋ ምድር መዲና የአዱ ገነት ቀዝቃዛ ንጹህ አየር ተገናኙ ፣ አየሩን ሲምገው – ህልሙን አስታወሰው ! … እንዲያ እያለ ጉብኝቱን ጀመረ ! ዶር በርናርድ ሀኪም ነውና በሚያውቀው ሙያ ዳሰሳ ለማድረግ ይመቸው ዘንድ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ቀናት ቆይታው የህክምና ተቋማቱን ጎበኘ ። በየህክምና ተቋማቱ ሕሙማኑ ተኮልኩለው እርዳታ ለማግኘት ሲጠባበቁ ቢመለከት ልቡ ተሰበረ። አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልና የህክምና መካነ ጥናት እንዲሁም ቅዱስ ገብርኤል የግል ሆስፒታል ሲጎበኝ፤ ረዠም ራዕዩን ፣ የህክምና ልሂቅ የመ ሆን ዝናውን ያወቁበት ህልሙን የነቁበት ” የእኛ ሁንልን ” ሲሉ ተማጸኑት ! በንዋየ ፍቅር ደንታ ለሌለው ፣ ለሰብዕና ቅድሚያ ለሚሰጠ ው ለዶር በርናርድ ይህ ግብዣ ተቀባይ አልነበረውም ፣ አልተቀበለውም ! የጠቢቡ ጉብኝት ቀጥሏል …

አኩሪ ታሪክ ባህሏን ጠንቅቆ እንዲረዳ ፣ እንዲማርና እንዲመራመር ፣ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን ፍቅር እንዲነደፍ ፈር በቀደደ ችው የትዳር አጋሩ በሲስተር እማዋ ገሪማ እየተመራ ኢትዮጵያ አሳምሮ ጎበኛት ። ጠቢቡ ከሰማ ካነበበው የኢትዮጵያ ታሪክና ባህል በላይ ያጣ የነጣው አብዛኛው ህዝብ ሰው አክባሪና እንግዳ ተቀባይነትና ታማኝነት በኩራት ሲያስደምመው ። የድህነቱና የችግሩን መክፋት ግን ህመም ሆኖ አስከፋው ! ዶር በርናርድ አንደርሰን ድህነት ፣ በሽታው መገፋት የሚችል እንደሆነ ከማውጠንጠን መፍትሄ ፈልጎ በእሱ መደገፍ የሚችለውን ድርሻ አውጥቶ መተግበር ጀመረ እንጅ ድህነት ፣ ችግሩ አንገሽግሾት ወደ መጣበት ሽሽትን አልመረጠም ! ከተሜውን ጎብኝቶ ወደ ገጠሮቹ ሊመለከት አዘገመ። የሀኪም እጅ ማየት አይደለም መልኩና ገጹ የናፈቃቸውን ወገኖች አጋጠሙት። በርካታ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው መጥተው ከየሆስፒታሉ ደጃፍ ተኮልኩለው አምላካቸውን እየተማጸኑ፤ ከእለታት አንድ ቀን የሀኪም እጅ እንዲነካቸው ሳምንታትን የሚጠብቁ ምስኪኖች ልቡን አሳዘኑት ፣ መንፈሱን ነኩት …

ጎንደርም በፍቅሯ ነደፈችው ፣ እንግዳዋን በፍቅር ተቀብላ ” የእኔ ሁን ፣ ቅርልኝ! ” አለች ው ። ዶር በርናርድ የእናት ጎንደር ጥሪዋን በጸጋ ተቀበለ ! ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ እድሜን ላስቆጠረው ብቸኛው የጎንደር ሆስፒ ታልን ለማገልገል ለህክምና ኮሌጁ የአሁን ብሩህ ተስፋ እጁን ሰጠ። ከህክምና ድጋፉ ፣ በተጓዳኝ ጥናትና ምርምሩ አንቱ በሚያሰኘ ውን ተመክሮ ራሱን እያጎለበተ ጉዞ የጀመረው ሃኪም ህክምና ድጋፍ ከመስጠት ርቆ ሔዶ በመምህርነት ሙያው ተተኪ ትውልድን የማነጽ ህልሙን ከሞላ ጎደል አሳካ ! በጎ ስራውን የዋሽንግተን ዲሲ በርካታ ኢትዮጵያ ውያንን ጨምሮ የጎንደር ተወላጆች የዶ/ር በርናርድ አንደርሰን ቅን በጎ አድራጎት በመረ ዳት ስህክምናው በሰፊው እጆቻቸው አቀፉት። ዶር በርናርድ ፋታና እረፍት አላስፈለገውም።

ቀድሞውንም እረፍትና ምቾቱ ለህሙማን መድረስ – ለተቸገረ ዋስ መሆን ነበርና ደከመኝ ሰለቸኝ ለዶ/ር በርናርድ ዋጋ አልነበራቸውም። ከአጸደ ስጋ እስከተለየበት ጊዜ ድረስ የስራና ሰውን የማገልገል ቀናት ናቸውና። ከሁሉም የሚያስገርመው ደግሞ “እስመ ትህትና ረከበ ልዕልና” እንዲባል የህክምናው ሊቅ እኔን እዩኝ ሳይል – አለሁ ብሎ ሳይፎክር – እወቁኝ ብሎ ሳያውጅ – ካልተለወደበት ወገን መካከል ከእግር ስር ሆኖ አገለገለ። እንደ ሀገሬው ቋንቋውንና ባህሉን አጥንቶ ፣ እጅ ነስቶ – በባላገሩ ምርቃት ተመርቆ ትሁት እንደሆነ ኖረ። የአሜሪካ ኑሮና ገንዘቡ ሳያሳሳው ይልቁንም ለዘመናት ለፍቶ ያፈራውን – ሰርቶ ያቆመውን ይዞ – ጎንደር ከሆስፒታል ደጃፍ ለሚጠኑት ዋለላቸው ፣ በፍቱን እጁ ዳሰሳቸ ው ፣ ለወሮታው አመሰገኑት !

ከየህክምናው ተቋም ተኮልኩለው የሚያያ ቸው ህሙማን ቢያሳዝኑት – መጠለያ ለማሰራ ት ወጠነ። ሀገር አቆራርጠው ለህክምና የሚ መጡን ለመታደግም ሆስፒታል አስገነባ። በአዘዞ በዶ/ር በርናርድና በባለቤቱ የተገነባው ይህ ሆስፒታልም ለመቶ ህሙማን ማርፊያ መኝታ እንዲኖረው ተደርጎ ተገነባ ፣ ምንም እንኳን ሆስፒታሉን ስራ ጀምሮ ለማየት ዶ/ር በርናርድ በስጋ ቢለይም እንደሙሴ የቃል ኪዳን ሀገር – ስሙን የተከለበትን ራዕይ ለእኛ ትቶልን በክብር ተሸኝቷል !

ዶር በርናርድ አንደርሰን የህክምና ሊቅ ብቻ አልነበረም። ዘርፈ ብዙ ተሰጥኦም ነበረው። በስነ ህክምናው በጣፊያና በጉበት ህመም ለሚሰቃዩ በልዩ ጥበብ ብልቶቹ የሚሰሩበትን ዘዴ በምስል ነድፎ የባለቤትነት (ፓተንት) ያለው ባለሙያ ነበር። ዛሬ መዝገብ የያዛቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የባለቤትነት ዕውቅና የያዘባቸው ሁለት መሳሪያዎች አሉት። በታሪክ እውቀቱና አስተምህሮ የአፍሪቃን አስተሳሰብ የተከተለ – እውነተኛን ስር ፈልፍሎ በማውጣት በምስል – በጥናታዊ ጽሁፍ ያቀናጀ ፤ በህንጻና በቤት ውስጥ ማስዋብ ጥበብ የተካነ ( ሆስፒ ታሉም – የዶ/ር አንደርሰን ዲዛይን በዶር በርና ርድ የተሰራ ነው) በስነ ግጥም መጽሀፍ የጻፈም ብዕረኛ ነበር። የስነ ግጥሙ ስብስብ መጽሀፍ ርዕስ Limbic glimpses ይሰኛል።
ዶር አንደርሰን ኢትዮጵያን አውቋት ነው የወደዳት። እኛ አልታይ ያለንን ውበቷን አየው ፣ ፣አኛ አልታይ ያለንን ፣ አለያም አይተን መፍትሔ ያጣንለትን የወገን ችግር ተረድቶ በተግባር ችግሩን ለመቅረፍ የተጋ ሰው የኢትዮጵያ ወዳጅ ነበር ። እኛ ጥለን በምንሸሻትን ሃገር ፣ እኛ የምንለያይበትን ታሪክ አንጠርጥሮ ተረድቶታል ፣ በፍቅሯን እርሱ ሁሉን ተሸከመው። እኛ ጥለናት የሸ ሸናትን እሱ በህይወት በሞትም እንደፈለጋት “ልሁንልሽ፣ በቀሪ ህይዎቴ አገልግልሻለሁ! ” እንዳላት ብቻ አላለፈም ከዚህ ሁሉ ባላይ መንፈሳዊ ህይወቱንም ከጥንታዊው እምነቷ ጋር አዋህዶ – በህልፈተ ህይወቱም አፈሯን ሊለብስ ጸሎተ ፍታት እንዲደረግለት ከእርሷ ማህጸን ሊመለስ ተናዘዘም። እንዳለው ይሆንለት ዘንድ ውድ ባለቤቱ ወዳጆቹና አፍቃሪዎቹ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተጠምቆ – ፍታቱንም በመንፈሳዊ ስርዓት እንዲሆንለት እንተደመኘ ሆነለት !

ከዶ/ር በርናርድ የህክምና ጥበብን ብቻ ሳይሆን ርህራሄን – ሌሎችን የማገልገል መርሀ ጽድቅን – ራስን ከመውደድ የመውጣት ትልቅነትን ተማርን። ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ – ምንምን ሳይንቁ ሰው የመሆንና የመባልንም እውቀት ቀሰምን። ዶ/ር በርናንድ ተናግሮና አውርቶት ሳይሆን ኖሮት አሳየን። በዚህች ቅጽበት መለስ ብለው ሲያስቡት ዶ/ር በርናርድ እኛ ቀረብን – አመለጠን እንጂ እሱማ ክቡር የህይወት ተልዕኮውን አጠናቋል። ሩጫው ለእኛ አጠረብን እንጂ እሱማ ህልሙንና ራዕዩን አከናውኗል። የማገልገልን የቃል ኪዳኑን ምድር አሳይቶናል። ክቡር ሞቱ ለሰማዕቱ ይባልለታል። ዶ/ር በርናርድ ኖሮና ሰርቶ – እኛ ያለወቅናትን ኢትዮጵያ አውቋትና አሳውቆን – የመሆንና የማድረግን ምስጢር አስቃኝቶን ነው ከአጸደ ስጋ የተለየው። ህይወት የእግዚአብሔር ስጦታ ናትና ለአፍታም ቢሆን ዶ/ር በርናርድን ያህል ሰው ሰጥቶና አሳይቶን ወሰደብን።

የህክምና ጠቢቡ ለራሱ አልሆን ብሎ በውስጥ ደዌ ተቀስፏልና በአሜሪካን ዋሽንግተን ለወራት በህክምና ሲረዳ ቢቆይም የተቆረጠችው ቀን ደረሰች ፣ ዶ/ር በርናንድ እድሜውን ድሆችን በመደገፍ ፣ አቅመ ደካሞችን በመንከባከብ ፣ በውስጥ ደዌ የተጎዱትን አክሞ በመፈዎስ የተጋው ዶ/ር በርናንድ አንደርሰን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አሸለበ ! ዶ/ር በርናርድ የሁለት ወንድ ልጆች አባት ነበር። ታህሳስ 24 ቀን 2007 ዓም ወይም እጎአ ጥር 2 ቀን 2015 ዓም በህክምና ለጥቂት ወራት ሲረዳ ቆይቶ ከዚህ አለም በሞት ተለየን … !

ዶር በርናርድ ብራድሊ አንደርሰን “በቀሪ ህይዎቴ ኢትዮጵያን አገለግላለሁ ” ብሎ ቃሉን ፈጽሞ የጉዞው ፍጻሜ ሲቃረብ የሬሳው የመጨረሻ ማረፊያ የተወለደባት ጃማይካ አለያም የተማረ ያደገ ፣ የተሸለመና ዜግነት ሰጥታ ባኖረችው ሀገረ አሜሪካ እንዲያርፍ አላደረገም ። ከጎንደር ታሪካዊ ቦታዎች አንዷ በሆነችው በታሪካዊዋ ቁስቋም ማርያም ደብር እንጅ … ጥር 2 ቀን 2007 ዓም የዶር በርናርድ ብራድሊ አንደርሰን የቀብር ሥነ ሥርዓት ወዳጅ ዘመድ ፣ ተማሪ ዎቹ ፣ የስራ ባልደረቦቹና ሀገሬውና አድናቂዎቹ በነቂስ በመገኘት “ስምህ ህያው! ” ነው ሲሉ በእንባ ተራጭተው በክብር አፈር አልብሰው የመጨ ረሻው ሽኝት በሃዘን በተሰበረ ልብ ተከው ኗል…እነሆ ኑዛዜ ቃሉም ተፈጸመ ! ጠቢቡ ጃማይካዊ ዶር በርናንድ መቀበሪያውን ኢትየጵያ / ጎንደር ውስጥ በአንድ ኮረብታ ማማ ላይ በምትገኘው በታሪካዊዋ የቁስቋም ማርያም ደብር ሆነ !

የዶር በርናርድ ብራድሊ አንደርሰን ! ክብርና ሞገስ ይገባሃል ! እንዎድሃለን እናከብርሃለን !

Dr. Bernard Bradley Anderson we are very proud of you & Thank you !

ነፍስ ይማር !

ነቢዩ ሲራክ
ጥር 3 ቀን 2007 ዓም


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>