Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ካልፎ ሂያጁ ማስታወሻ የተቀነጨበ(ክፍል ሦስት)- ከበእውቀቱ ስዩም

$
0
0

እንደምነሽ ሸገር

እንደምነሽ ሸገር
ማሽተት የተሣነው፤ የጋሽ ጣሰው ኣገር፡፡

ልክ እንደነ ፓሪስ፤ እንደሎንደን ሁላ
ፏፏቴም ባይኖርሽ፤ ሽቅብ የሚፈላ
ወንዝሽ ከማን ያንሳል
ከፈነዳ ቱቦ፤ የወጣ ሰገራ፤ ሰንጥቆሽ ይፈስሳል

Bewketu Seyoum – Hagere Mariam (Maryland) USA [Must Listen)
ሲያቀብጠኝ ያን ሜሪላንድን የመሰለ ኣገር ትቸ ወደ ሸገር ተመለስሁ ፡፡ የተመለስኩበት ምክንያት ግልጥ ነው፡፡ ኣሜሪካን ኣገር ጥገኝነት ለመጠየቅ ውስጥ ውስጡን በምዘጋጅበት ሰኣት ዲሲ የሚኖሩ ጓደኞቼ የስንብት ፓርቲ ኣዘጋጅተው ጠሩኝ፡፡“የወጣው ሰው ሁሉ ወጥቶ በሚቀርበት በዚህ ቀውጢ ሰኣት ወደ ኣገርህ ለመመለስ ያሳየከው ቁርጠኝነት በጣም የሚያኮራ ነው” እያሉ ትከሻየን ተምተም ተምተም ኣረጉት፡፡ ሼም ይዞኝ ወደ ሸገር ተመለስሁ፡፡ ጸጸት የለበለበኝ ገና ኣውሮፕላኑ ሲነሣ ነው፡፡ እንድያውም ዱባይ ላይ ትራንዚት ስናደርግ ወደ ሳኡዲ ኣረብያ ልሸበልል ኣስቤ ነበር፡፡ የኣረብ ፖሊሶች በኮሌታየ ጠርዘው ኣስገቡኝ፡፡ “ኧረ ጎበዝ የንጉሥ ኣብደላ ቀብር ላይ ለመገኘት ነው” ብል ማን ሊሰማኝ፡፡ ሩቢላው ወደ ሸገር ሲወርድ ቁልቁል ኣገሬን ሾፍኳት፡፡ ልምላሜ የሚባል ነገር ኣልጣፈባትም ፡፡በርግጥ እንጦጦ ላይ የጥልያኑን ተጫዋች የባላቶሊን ቁንጮ የምታክል ጫካ ቀርታለች፡፡

ኢትዮጵያ ኣገሬ
እማማ ኣገሬ
ስንት ገባ ይሆን የውጭ ምንዛሬ?

ኣንባቢ ሆይ በዚህ ግጥም ቅርጽ ላይ እንጂ ጭብጥ ላይ እንዳታተኩር ኣደራ፡፡ ቤት ለማስመታት ያክል ነው እንጅ ከዚህ በፊት እንደተናገርኩት ቤሳቢስትን የለኝም፡፡በዶላር ያለው ሰውየ ቢንጃሚን ፍራንክሊን ይሁን ቢንጃሚን ኔታኒያሁ እማውቀው ነገር የለኝም፡፡

እህ እናንተ የምድር ጎስቋሎች! እንዴት ናችሁ! ለምርጫውና ለ ሩጫው ተዘጋጃችሁ? እኔ ካርድ ኣውጥቻለሁ፡፡የሆስፒታል ማለቴ ነው፡፡ኣትልፉ መሪዎች የሚወገዱት በምርጫ ወይም በትጥቅ ትግል ሳይሆን በኮሌስትሮል ነው፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው! ጌቶች በህዝብ ግፊት ባይወገዱ በደም ግፊት ይወገዳሉ:!!! እስቲ ሁላችንም ግራ እግራችንን እያነሣን የሚከተለውን መፈክር እናስተጋባ፡፡ መጭው ዘመን ከገዥው ፓርቲ ጋር ጭንቅ ነው!! ከጎምዥው ፓርቲ ጋርም ውድቅ ነው!! ይብላኝ ለእናንተ እንጂ እኔ ትንሽ ኮሽ ሲል ውልቅ ነው፡፡ፓስፖርቴን እንዳልነጠቅ ጀርባየ ላይ ተነቅሸዋለሁ፡፡

በእናታችሁ እኔን ምረጡኝ፡፡ምልክቴ ፤ ጠገራ ብር የሚያክለው ማድያቴ ፡፡ጅግናው የውሃ ልማት ሰፈር ህዝብ ሆይ! ተው ምረጠኝ፡፡ ብትመርጥኝ የኩራዝ መለዋዋጫ እቃዎች ኣቀርባለሁ፡፡ተች ስክሪን ፋኖስ ኣስገባለሁ፡፡

በነገራችን የፓርቲዎችን የምርጫ ምልክቶች ልብ ብላችኋቸዋል?የቀረ የዱርና የቤት እንስሳ የለም፡፡ዝሆን ቀጭኔ ኣውራሪስ ግመል ነብር ፡፡ጉማሬ ሁሉ ያየሁ መስሎኛል፡፡
ውድድሩ የስልጣን ነው የኣደን ?
ጉዞው ወደ ፓርላማ ነው ወይስ ወደ ደን?

በነገራችን ላይ የሳኡዲው ንጉስ ኣብደላ ባጭር መቀጨት በማስመልከት ለሰባ ሁለት ኣመቱ ጎረምሳ ኣልጋ ወራሽ የሀዘን ደብዳቤ ጽፍያለሁ፡፡ከደብዳቤው ሥር ፊርማየን ብቻ ሳይሆን የባንክ ኣካውንት ቁጥሬን ኣስፍርያለሁ፡፡ሳኡዲዎች እዝን ለሚደርሳቸው በንፍሮ ፈንታ ዶላር እንደሚያዘግኑ ሰምቻለሁ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ንጉስ ኣብደላን ለመቅበር መሬት ሲቆፈር ነዳጅ ተገኘ ፡፡
የታደለ ኣገር ሁለመናው ጋዝ ያልታደለው ኣገር ሁለመናው መጋዝ፡፡እኛ ኣገር ቢቆፈር የሚወጣው የሰማእታት ኣጽም ብቻ ነው፡፡

በቅርብ ጊዜ ያለው የኢትዮጵያ ገጽታ በሚከተለው መንገድ ሊገለጽ ይችላል፡፡የተገለበጠ መኪና -ተጀምሮ ያላለቀ ኣውራ ጎዳና-በፖሊስ ቆመጥ የቆሰለ ሰልፈኛ-ቦርጫም የቲቪ ጋዜጠኛ-ቀጫጫ ተሸላሚ ኣርሶ ኣደር-ሁለት ኣገጭ ያለው ወታደር-በኣሸናፊው እስር የሚጠናቀቅ ክርክር-ከእድሜ የሚረዝም መፈክር-የቻይና እዳ- ከጀሪካን ሰልፍ የተሰራ ግድግዳ፡፡

ሰልፍ ያማራችሁ ተሰለፉ፡፡ብቻ እኔ ወክ በማረግበት በኩል ኣትለፉ፡፡እኔና ቢጤዎቼ በየጓሮው የፖሊስ ቆመጥ እንደ ሸንኮራ ሲበቅል ኣይተናል፡፡ የዛሬ ፖሊስ የሚበትነው ቢያጣ የታክሲ ሰልፍ ይበትናል፡፡
ባለፈው ኣመት ልደቴን በማስመልከት ሚስቴ ቮልስዋገን ገዝታ ኣበረክታልኝ ነበር ፡፡ዘንድሮ ደግሞ ኣስፓልት ልትገዛልኝ ኣቅዳለች፡፡ ታድያ የት ሄጄ ልንዳ ?መኪናችንን የምንጠቀምበት ለመብራት ነው፡፡ማታ ቮልሳችንን ከሳሎናችን በር ፊትለፊት ገትረን በፍሬቻው ብርሃን ራት እንበላለን፡፡መንዳት ኣይታሰብም፡፡ያዲስ ኣበባ ሰው መሄጃ ስላጣ መኪናውን ጥግ ኣስይዞ ይቅማል፡፡ትራንስፎርሜሽን ማለት መኪና ወደ መቃምያ ቤት መቀየር ነው እንዴ? ትራፊክ ፖሊሶችም ነገሩን ለምደውት ቃሚ ኣይቀጡም ኣሉ፡፡ባይሆን በየጋቢናው በር ብቅ እያሉ “እስቲ በርጫውን የገዛህበት ደረሰኝ ኣሳየኝ”ይላሉ፡፡
ያ ባቡር በመጣና እንዴት ኣባቱ ኣድርጎ እንደሚሄድ ባየሁት፡፡ሃዲዱ የቤቴን ግድድዳ ታክኮ ነው የተዘረጋው፡፡ራሱን ለመግደል ከባቡሩ መስኮት የሚወረወር ሰው ምኝታ ቤቴ ውስጥ መውደቁ ኣይቀርም፡፡ወይ እቶጵያ ድንቅቅ የምትል ኣገር፡፡ ወደብ ባይኖራትም መርከብ ኣላት፡፡ኤሌክትሪክ ባይኖራትም የኤሌክትሪክ ባቡር ኣላት፡፡

እስቲ ባቡሩ ከለገጣፎ ሲነሳ ኣስቡት፡፡የባቡሩ ወያላ ተሳፋሪው ሁሉ ገብቶ ማለቁን ካረጋገጠ በኋላ እንዲህ የሚል ይመስለኛል”ውድ ተሳፋሪዎቻችን በኤሌክትሪክ መቋረጥ ምክንያት ጉርድ ሾላ ላይ ልናድር ስለምንችል ታጣፊ ኣልጋ መያዝ እንዳትረሱ፡፡”

ከብረትና ከጥቅስ የተሰራው የኣዲስኣበባ ምኒባስ በስንት ጣሙ፡፡ በነገራችን ላይ ፣ኣሜሪካ ውስጥ ታክሲ ውስጥ ያለው ወሳኝ እቃ ጂፒ ኤስ ሲሆን የኢትዮጵያ ታክሲ ወሳኝ እቃ ጥቅስ ነው፡፡ወያላው በግራ መስታውት”ከሾፊሩ ጋር የምትጨቃጨቁ ፡በኢቦላ እለቁ”የሚል ርግማን ለጥፎ በቀኝ መስታውት በኩል ጽዋ የያዘ የመላእክ ስእል ይለጥፋል፡፡ በጥቅሱ ሃጢኣት ሰርቶ ፡ ከመላእኩ ስእል ኣካማኝነት ንስሃ ገብቶ ወደ ቤቱ ይገባል፡፡
(እኔ ከቀጠልኩ ይቀጥላል)

The post ካልፎ ሂያጁ ማስታወሻ የተቀነጨበ(ክፍል ሦስት)- ከበእውቀቱ ስዩም appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>