Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ሌንጮ ለታ፤ ኦኤምኤን ፤ አባዱላ ገመዳ እና የሞራል ኪሳራ –እንደ ተጨማሪ ማብራሪያ

$
0
0

ከታምራት ነገራ

(የቀድሞው አዲስ ነገር ጋዜጣ ጋዜጠኛ)

ይህ ፅሁፍ በክፍል አንድ ( ኦኤምኤን ፤ አባዱላ ገመዳእና የሞራል ኪሳራ) በሚል ርስዕስ ላይ ባነሳኋቸውን አንዳነድ ነጥቦች ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመስጠት ይሞክራል፡፡ በክፍል አንድ ጽሁፍ በጥቂቱ ኦኤምኤን እንደሚዲያ ተጠያቂነቱ ለአንድ ቡድን ወይንም ፓርቲ ሳይሆን ለኦሮሞ ብሔርተኝነት እንደሆነ፤ ኦህዴድ በዋነኛነት የሚንቀሳቀስበት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ስሌት የድኾበል ( እየዳኸ የሚበላ Bottom Feeder) ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ስሌት አንድሆነ፤ ኦኤሜንን እና ኦህዴድን የሚያገናኛቸው እናም አንዱ ሌላውን እንዲሸከመው ያደረገው የኦሮሞ ብሔርተኝነት ውስጥ የተፈጠረው የሞራል ቀውስ እንደሆነ፤ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ውስጥ የሞራል ቀውስ የሚመነጨው ከወቅተዊው የኦሮሞ ብሔርተኝነት (Contemporary Oromo Nationalism) በጥቂቱም ቢሆን ለማሳየት ሞክሬአለው፡፡
lencho leta
ይህም ሆኖ በጽሁፉ በሚገባ ያላደማኋቸው የተወሰኑ ወሳኝ ነጥቦች ታይተውኛል አንባቢዎችም አንዳንድ ተጓዳኝ ጥያቄዎችን በቀጥታም ሆነ በግል መልዕክት አቅርበዋል፡፡ እኔ በጽሁፉ ላይ ያየኋቸውን ነጥቦች እና የተነሱትን ጥያቄዎች በጥቅሉ ሳስቀምጣቸው፤

አንደኛ፤ ፅሁፉ የሞራል ኪሳራ ወይንም የሞራል ቀውስ የሚለውን ጽንሰ ሀሳብ በተገቢው አላብራራም፡፡ በተጨማሪም የጽሁፉ መነሻ ባረደገው ክስተት (የኦኤም ኤን ጋዜጠኞች ከአባዱላ ጋር ምግብ መቋደስ ጋር) የሞራል ክስረት ምን አይነት ግኑኝነነት እንዳለው በሚገባ ሳያሳይ በደፈናው ያልፈዋል፡፡
ሁለተኛ፤ ፅሁፉ በኦሮሞ ብሔርተኝነት ውስጥ ስላለው የሞራል ቀውስ ሲተነትን በኢትዮጵያ ብሔርተኞች ዘንድ መሰረታዊ ስለሚባሉት እንኳን የኦሮሞ ጥያቄዎች ያለው ክህደት አልዳሰሰም፡፡ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ስለኦሮሞ ጥያቄ የሚያሳዩት ተራ ድንቁርና ለኦሮሞ ብሔርተኞች ጽንፈኝነት በቀጥታ ስላበረከተው አስተዋፅኦ እናም በኦሮሞ ወቅታዊ ብሔርተኝነት ውስጥ ለምናየው የሞራል ቀውስ ስለበረከተው አስተዋጽኦ አልተብራራም፡፡

ሶስተኛ፤ ፅሁፉ ስለኦህዴድ ፓለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስሌት ሲተነትን እነ ኦኤሜንም ሆኑ በርካታ የኦሮሞ ብሄርተኛ ልሂቃኖች የሚሰብኩት እና የሚከተሉት የፖለተካዊ ስሌት እንዴት አድርጎ ከኦህዴድ አጠገብ እንዳስቀመጣቸው ኦህዴድም እነኦኤምኤንን ለራሱ ግብ እንዴት እነደሚጠቀምባቸው ፍንትው አድርጎ አላሳየም።

አራተኛ ፤ፅሁፉ በአሁኑ ወቅት በኦሮሞ ፖለተካ ውስጥ ካለው እንቅስቃሴ በተለይም እነ ሌንጮ ለታን መሰል ግንባር ቀደም የኦሮሞ ብሔርተኞች ወደ አገርቤት መመለስን አስመልክቶ ምንም ያለው ነገር አልነበረም፡፡ የእነ ሌንጮ ለታ እርምጃ በምን አይነት ስሌት ላይ ተመሰረተ ሊሆን ይችላል? የእነ ሌንጮ ለታ እርምጃ በኦሮሞ ብሔርተኝነት ውስጥ የተፈጠረውን ሞራል ቀውስ ከመረዳት እናም መፍትሄ ለመስጠት ከመሞከር አንጻር እንዴት ሊታይ ይችላል? ይህ ጽሁፍ እነዚህን ነጥቦች እና ጥያቄዎች ለመዳሰስ ይሞክራል፡፡

የሞራል ወይንስ የፖለቲካ ጥያቄ

በየትኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ የሞራል ጥያቄን እና የፖለቲካ ጥያቄን አመሰረታቸውን፤ ልዩነታቸውን፤ መስመራቸው ደግሞ የትጋር እንደሚተላለፉ ማወቅ እጅግ ወሳኝ የቤት ስራ ነው፡፡ ምክንያቱም በፖለቲካዊ ጉዞ ወስጥ የሞራል እና የፖለቲካ ጥያቄ ግጭት ፈፅሞውንም አይቀርም ፤ ለአንድ ሰከንድ አንኳን አይቋረጥም ለመቼውም ሙሉ ለሙሉ አርኪ መልስም አያገኝም፡፡

አንድዳንድ አጋጣሚዎች የሚያቀርቧቸው አማራጮች የፖለቲካ ፍላጎቶች እና ጥቅሞቻችን ከሞራል መርሆዎቻችን አስበልጠን ለፖለቲካዊ ጥቅማችን እንድናደላ ሊያስገድዱን ይችላሉ፡፡ በተመሳሳይ መልክም አንዳንድ አጋጣሚዎች ለሞራል ግዴታዎቻችን በመታዘዝ ከፖለቲካዊ ፍላጎቶቻችን እና ጥቅማችን በልጦብን ፓለቲካዊ ጥቅማችንን እርግፍ አድርገን እንድንጥል ሊያስገድደንም ይችላል፡፡

ፖለቲካዊ ጉዞን የሚያወሳስበው አንድ ነገር ለፖለቲካዊ ጥቅም ስንል የሞራል መርሀችንን ለመጨፍለቅ ስንወስን የወሰድነው እርምጃ መልሶ የፖለቲካዊ ትቅማችንን እጅጉን ሊጎዳው መቻሉ ነው፡፡ ልክ በተመሳሳይ መልኩ የሞራል ጥቅማችንን ከፖለቲካ ጥቅማችን አስበልጠን የወሰድነው እርምጃ በራሳችንም በዓለም ፊት ያለንን የሞራል ቁመና ለመደምሰስ መቻሉ ነው፡፡ በብዙ ጊዜ እነዚህን ውስብስበሰ እና አጣብቂኝ ውሳኔዎች እንድንወስድ የምንገደደው በአጭር ጊዜ ውስጥ እና በተወሰነ መረጃ ላይ ብቻ በመመስረት ሊሆን ሆናል፡፡
እነዚህን ምርጫዎች በትክክል እና በተቻለ አቅም በተማጠነ መልኩ ለመውሰድ ግን የሚያስፈልገን በደመነፍስ መደንበር፤ የሰለቹ መፈክሮችን በጩኸት መልሶ መላልሶ መድገም ሳይሆን የፖለተካ ጥያቄን ከሞራል ጥያቄ በሚገባ ለይቶ ለማወቅ መታገል ነው፡፡

የኦሮሞ ጥያቄ የሞራል ወይንስ የፖለቲካ ጥያቄ ?

የኦሮሞ ጥያቄ የሞራል ጥያቄ ነው ወይንስ የፖለቲካ ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማቅረብ ከመሞከር በፊት የኦሮሞ ጥያቄ እራሱ ምንድን ነው ከሚል ጥያቄ ጋር እንጋፈጣል፡፡ይህ ጥያቄ እራሱ ሰፊ እናም ጥልቅ የጥናት ፕሮጀክት ነው፡፡ ነገር ግን አሁን እየተወያየንበት ላለው ርዕሰ ጉዳይ አንድ ጥያቄ እንዴት የፖለቲካ እና የሞራል ጥያቄ መልክ እንደሚኖረው፤ ምን አይነት ጥያቄ የሞራል ጥያቄ ሊባል አንደሚችል ምን አይነት ጥያቄ ደግሞ የፖለቲካ ጥያቄ ሊባል እነደሚገባው መወያያ ይሆነናል እላሁ፡፡

የኦሮሞ ጥያቄ፤ የሲዳማ ጥያቄ፤ የአፋር ጥያቄ ወዘተ ስንል በመጀመሪያ ስለአንድ ህዝብ ጥያቄ እተወያየን ነው፡፡ ስለዚህ የኦሮሞ ጥያቄ ስንል የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ነው፡፡ እዚህ ላይ መቆም ግን በቂ አይሆንም አይደለምም፡፡ የሕዝብ ጥያቄ ስንል መቼም አባላት የሆኑት ሚሊዮኖች ሁሉ በአንድ ቀን ተሰብስበው በአደባባይ የሚያቀርቡት ጥያቄ ማለታችን አይደለም፡፡ አንደኛ በረጅም ጊዜ ውስጥ እና ውስብስብ ፖለቲካዊ ባሕላዊ ኢኮኖሚያዊ ሂደቶች ውስጥ አልፎ የሚገነባ ጥያቄ ነው፡፡ ሁለተኛ እና በዋነኛነት በአንድ ሕዝብ ጥያቄ ዙሪያ እጅጉን ወሳኝ ተዋናይዮች ልሒቃን (Elites )ናቸው፡፡

የአንድ ሕዝብ ልሒቃን የሕዝቡ ጥያቄ ምን መሆን እንዳለበት ይወስናሉ፡፡ የተቀረጸውን ጥያቄ በሕዝባቸው መካከል ያስፋፋሉ፡፡ በጥያቄው ዙሪያም ሕዝባቸውን ያደራጃሉ ያነቃቃሉ፡፡ ይህን የሚያደርጉት ለሕዝባቸው ከመቆርሮርም ለግላቸው ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚ ጥቅም ለማግኘትም ሲሉ ነው፡፡ ስለዚሕ የኦሮሞ ጥያቄ ስንል፤ የኦሮሞ ልሒቃን ለህዝባቸው ከመቆርቆር እናም የግል ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸውን ለማስፈፀም የሚቀርፁት የሚያስፋፉት ብዙሃን ኦሮሞችን ለማደራጀት የሚጠቀሙበት ጥያቄ ነው ብንል ከእውነታው እምብዛም አንርቅም፡፡ የአንድ ሕዝብ ጥያቄ መቀረጽ እና መስፋፋት በዚያ ሕዝብ ውስጥ የሚኖረውን የብሔራዊ ስሜት ይጭራል ይቀሰቅሳል ያቀጣጥላል፡፡ በዚህ የተነሳ የሕዝብ ጥያቄ፤ ብሔርተኝነት እና ልሂቃን እጅግ ወሳኝ የሆነ ትስስሮሽ አላቸው፡፡

የአንድ ሕዝብ ልሂቃን ሕዝባቸውን ወክለው እንዲነሱ የሚያደርጓቸው ወሳኝ ነገሮች አንደኛው ልሂቃኑ በሕዝባችን ላይ ጭቆና አለ ብለው ማመናቸው ነው፡፡ ልሂቃኑ አለ የሚሉት ጭቆና ኖረም አልኖረም የህዝቡ ልሂቃን ጭቆና አለ ብለዋል እዚህ ላይ መነታረክ ትርጉም የለውም፡፡ ጂኒው ከሳጥኑ አምልጦ ወጥቷል፤ ጥያቄውም ተጭሯል፡፡ ልሂቃንን በሕዝብ ስም ሆ ብለው እንዲነሱ የሚያደርገው ሁለተኛው መስፈርት የልሂቃኑን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥማት በሚገባ መልኩ የማያረካ ስርአት መኖሩ ነው፡፡

ስለሕዝብ ጥያቄ ልሂቃን በሕዝብ ጥያቄ ዙሪያ ስለሚኖራቸው ሚና እና የሕዝብ ጥያቄ ስለሚመሰረትበት ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አውድ ይህን ያህል ከተነጋገርን ስለኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ምንነት፤ ፖለቲካዊ እና ሞራላዊ ይዘቱ ጀምረነው ወደነበረው ውይይት አንመለስ፡፡ እስቲ ውይይታችንንም በአሁኑ ወቅትም ሆነ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የኦሮሞ ልሂቃን ስለኦሮሞ እንዲቆሮቆሩ የሚያሳምናቸው ፤ የኦሮሞ ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋርም ሆነ ለብቻው በኦሮሞነቱ ተለይቶ ተበድሏል እንዲሉ የሚያስችላቸው ጭቆና ነበር አልነበረም የሚንለውን ጥያቄ በመቃኘት እንጀምር፡፡

ለዚህ ጥያቄ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የተለየ ጭቆና አልደረሰም የሚል መልስ የሚሰጡ ሰዎች መልሳቸውም ሆነ መልሳቸውን ለማስደገፍ የመያቀርቧቸው ማስረጃዎቸው ምን ያህል ትርጉም የለሽ እነደሆኑ ቢረዱ ደስ ባለኝ፡፡ የኦሮሞ ልሂቃን ኦሮሞን ከሌላው ሕዝብ በተለየ መልኩ ተጨቁኖአል ተበድሏል የምንልበት አሳማኝ ምክንያት አለን ካሉ በቃ አለቀ ደቀቀ አሳማኝ ምክንያት አለ፡፡ አንደው አልነበረም እንኳ ብንል ልክ እነደ ልብ ወለድ ከምንም ውስጥ ይፈጥሩታል፡፡ ልሂቃንነታቸው ለዚህ ቀን ካልዋለ ለመቼ ?
aba dula
የታሪክን ክርክር ለጊዜው ጋብ እናድርገው እና በዛሪቷ የኢትዮጵያ ስርአት ውስጥ ማን ኅሊናው ንጹ የሆነ ሰው አፉን ሞልቶ ኦሮሞ በኦሮሞነቱ እየታደነ እተገደለ ከመሬቱ እየተነቀለ አይደለም ይላል ? ዛሬ በኦሮሞ ላይ እየደረሰ ያለውን ሰቆቃ ለማወቅ የኦሮሞ ልሂቅም መሆን ኦሮሞ መሆን አያስፈልግም፡፡ ስለዘንድሮ የኦሮሞ ሰቆቃ አሳሳቢነት ስዬ አብረሃ የእስርቤቱ ቋንቋ ኦሮምኛ ሆኑአል ካለው የበለጠ ገላጭ ቃል ማግኘት ይከብዳል፡፡ ይህን ያለው ስዬ ግን ኦሮሞም አይደለም እንደውም የዘንድሮው ስርአት ዋነኛ አርክቴክትም ነበር፡፡

ስለዚህ የኦሮሞ ጥያቄ ስንል ሌላው ሁሉ ቢቀር በተገቢው ፍትህ የመኖር፤ ከቤት በሰላም ወጥቶ በሰላም የመመለስን የሚያክል እጅግ መሰረታዊ የሞራል ጥያቄ ማለታችን ነው፡፡ ይህንን በሰላም የመኖር ጥያቄ አንዴት መልስ እናግኝነለት? በብሔር እና ቋንቋ ላይ በተመሰረተ ፌደራሊዝም ወይንስ በአሃዳዊ ስርአት በማለት መጀመሪያ ላስቀመጥነው የሞራል ጥያቄ መልስ ማቅረቢያ ሌሎች የመዋቅራዊ ጥያቄዎችን ስንጋፈጥ የሞራል ጥያቄው ወደ ፖለቲካ ጥያቄ ገጹን ይቀይራል፡፡

የሞራል ጥያቄዎች በአብዛኛው እንዲህ እና እንዲያ መሆን አለበት እንዲህ እና እንዲያ መደረግ አለበት (What ought to be) የሚል ጫና ያዝላሉ፡፡ የሞራል ጥያቄዎች ዓለምን ሲያዩ ምን አንደጎደለ ፤ ምን መስተካከል እንደለበት ለማሳየት ይጥራሉ፡፡ የፖለቲካ ጥያቄዎች ደግሞ በአብዛኛው አሁን ያለው ስርአት የሚንቀሳቀሰው እንዴት ነው ስርአቱን ምን አይነት ሰዎች ያስተዳድሩታል በየት አቅጣጫ ብንሄድ ምን አይነት ውጤት ያስገኙልናል የሚሉ ሲሆን ዓለምን በአብዛኛው ምን መሆን አንዳለበት ለማሳት ከመጣር ይልቅ ዓለም ምን እነደሚመስል እንዴት እንደሚንቀሳቃስ በማሳየት (What is ) ላይ ያተኩራሉ፡፡
ወደ ሌላ ነጥብ ከመሸጋገራችን በፊ በኦሮሞ ብሔርተኝነት ጽንፈኝነት (Radicalization) ላይ የኢትዮጵያ ብሔርተኞች ያበረከቱት አስተዋጽኦን ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ከውልደቱ ጀምሮ እስከአሁን ድረስ ከኦሮሞ ልሂቃን ለኢትዮጵያ ብሔርተኝነት የተሰጠ ምላሽ (Reaction) ነው ብሎ መግለጽ ይቻላል፡፡ ሁለቱ የብሔርተኛ ካምፖች እንዴት አንደሚመጋገቡ የኦሮሞ ፈርስትን ንቅናቄ ያህል ማሳያ ያለ አይመስለኝም፡፡

የኦሮሞ ፈርስት እንቅስቃሴ በዋነኛነት የተወለደው ጃዋር መሀመድ እና መሀመድ አዴሞ ከአልጀዚራ ቲቪ ጋር በአደረጉት ውይይት ወቅት ጃዋር ለቀረበለት ጥያቄ እነደማለፊያ በሰጠው መልስ ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔርተኞች በወቅቱ ለጃዋር እና ለሰጠው መልስ ያሳዩት ቁጣ “ሰዉ አብዷልን? ” የሚያስብል ነበር፡፡ ጃዋር በወቅቱ የተናገረው አዲስ ወንጌል አልነበረም፡፡ ለማንኛውም የፖለቲካ እና ማሕበራዊ ጉዳይ ተከታታዮች እነጃዋር ከዛ በኋላ የወሰዱት ወደ ሕዛባቸው ጉያ የማፈግፈግ ምላሽ በጣም የሚጠበቅ ነበር፡፡ ይህም ሆኖ እኔ ግን የኦሮሞ ብሔርተኝነት መክረር የኦሮሞ ልሒቃንን የበለጠ የፖለቲካዊ አቅም አሳጥቷል ለ ኦህዴድም መጠቀሚያ አንዲሆኑ አድርጓል ባይ ነኝ፡፡

የኦሮሞ ብሔርተኝነት እጅጉን መክረር እንዴት አድርጎ ለኦህዴድ እንደሚያገለግል ወደበኋላ እመጣበታለሁ፡፡ ለአሁኑ ግን የኦሮሞ ልሒቃን እራሳቸውን ከ መላሽነት ይዞታ (Reactionary Mode ) እንዴት እንደሚያነሱ ቢያስቡ እጅጉን ደስ ይለኛል፡፡ የእራስን እድል በራስ ስለመወሰን የሚያወራ ሰው ስሜቱን፤ ፍላጎቱን፤ አጀንዳውን፤ ውሳኔውን ሌሎች ስለእሱ ባላቸው እይታ፤ እና አመለካከት እርምጃ ላይ የሚመሰርት ከሆነ በምን መሰረት ላይ ቆሞ ስለ የእራስን እድል በእራስ ስለመወሰን ያወራል? የእራሱን ትናንት ዛሬ እና ነገ ከማንም ጋር ሳያነጻጽር መገንባት ያልቻለን አንዴት ስለ እራስ እድል መወሰን ሲሰብከኝ አምነዋለሁኝ?
ኦሮሞ የራሱን እድል የሚወሰወን ሕዝብ እንዲሆን የሚፈልግ የኦሮሞ ልሂቅ በመጀመሪያ በዓለም ላይ ከኦሮሞ ውጪ ሰው የሌለ እስኪመስል ድረስ ከምንም ነገር ጋር ከማንም ጋር እራሱን ሳያወዳድር በማንነቱ ላይ ብቻ ቆሞ ያናግረኝ፡፡ ኦሮሞነቱን አማራ እንዲህ ስላለኝ ትግሬ እንዲህ ስላሰበ ከሚል መሰረት የሚመነጭ ትንታኔም ሆነ ተረት ላይ መስርቶ አይስበከኝ፡፡ ሰማይ እና ምድር ከመፈጠሩ በፊት እኔ ታምራት ነገራ ኦሮሞ ነበርኩኝ፡፡ ሰማይ እና ምድር ካለፉም በኋላ እኔ ታምራት የኦሮሞ ልጅ ነኝ፡፡ የእኔ ኦሮሞነት የሚጀምረው አማራን ያየዩት ቀን ትግሬን ያነገርኩት እለት ሶማሌን የነካሁት ሰሞን አይደለም፡፡ እኔ ነበርኩ፤ እኔ ነኝ እኔ ለዘላም እኖራለሁ! ይሄን አይነት ዩኒቨርስን የሚያጨናንቅ ፈጣሪን የሚፈታተ ጥጋበኝነት የተሞላ ኦሮሞ ካለ እሱ ያናግረኝ፡፡ ኦሮሞነቱን አማራ ስለሱ በፃፋው ላይ ትግሬ ስለእሱ ባወራው ላይ የሚመሰርት እሱ እና እኔ አንተዋወቅም፡፡

የኦኤምኤን አባዱላ ጣጣ

ለወያኔ ስርአት የኦሮሞ ልጆችን አዳኙ ማነው? የኦሮሞ ልጆች በቤታቸው ያወሩትን ተርጉሞ ለወያኔ ነግሮ የሚያሳስረው ማነው ? የታሰሩትን የኦሮሞ ልጆች በኦሮምኛ የሚመረምረው የሚገርፈው ማነው ? አሳሳሪው እናም ገዳዩያው አባዱላ ገመዳ የሚያንቀሳቅሰው የኦህዴድ መዋቅር ነው፡፡ አባዱላ ገመዳ ጋር የኦኤምኤን ጋዜጠኖች ቢዴና የተቋደሱት ይህን እያወቅ እነደሆነ ብንገምት ስህተት አይሆንብንም፡፡ ይህ እንዴት የሞራል ቀውስ ያስከትላል?የሞራል ቀውስ መነሻ የሚጀምረው አንድ ሰው አምነዋለሁ እናገረዋለሁ እተገብረዋለሁ በሚለው ቃል ሳይገኝ ሲቀር ነው፡፡
ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን በመቃወም በመላው ኦሮሚያ በተነሳው ብጥብጥ ከወለጋ እስከሀረር የኦሮሞ ልጆቸችን ሲያድን ሲያስር ሲገድል የነበረው ማነው ኦኤምኤን በወቅቱ በሰፊው የዘገበው ኦሮሞ ፕሮቴስት የተሰኘው ዘመቻ ያነጣጠረው በኦሮሞ ገዳዩች ላይ ከሆነ ከአባዱላ እና ኦህዴድ በላይ የኦሮሞ ገዳይ ማን አለ? ለዚህ የኦኤምኤን እና የአባዱላ ቀውስ ከሌላው ሰው ይልቅ ሰፊ መልስ የሰጠው ከኦኤምኤን መስራቾቹ አንዱ የሆነው ጃዋር መሀመድ ነው፡፡ በግል የፌስቡክ ገፁ ላይ ግልገል ነፍጠኞችን ምንድነው የሚያንጫጫቸው? በሚል ርእስ ካቀረበው ጽሁፍ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ያቀረበውን ክፍል ልጥቀስ

“ታዲያ ዛሬ የኦሮሞ ጋዜጠኖች (ልብ በሉ የ ፖሊቲካ መሪዎች አይደሉም) ሙያዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ከ አባዱላ ጋር ቢገናኙ ይህን ሁሉ ጩሀት ምን ቀሰቀሰው? መልሱ ቀላለ ነው። ለግልገል ነፍጠኞች እና ወያኔዎች ከምንም እና ማንም በላይ የሚያስፈራ ነገር ቢኖር እርስ በርሳቸው ጠላቶች ናቸው ብለው የሚጥብቋቸው ኦሮሞዎች አብረው መታየት ነው። እንደነሱ ፍላጎት ኦሮሞ በቡድን ተከፋፍሎ ሁሌም አንዱ አንዱን እያብተለተለ፣ አንዱ የኦሮሞ ቡድን ከነሱ ጋር አብሮ ሌላ ቡድን ውስጥ ያሉ እህቶች እና ወንድሞቹን እየዘረጠጠ እራሱንም እያዋረደ ባዕዳንን እያስፈነደቀ ቅሌት ሲሸከም ነው። እነሱ ማየት የሚፈልጉት እና የለመዱት የኦሮሞ ልጆች በመኢሶን፣ እጭአት፣ ኦነግ፣ ኦህዴድ፣ ኦዲፍ፣ ኦፍሲ … የ ዳዉድ ኢብሳ ኦነግ፣ የከማል ገልችሁ ኦነግ፣ የገላሳ ዲልቦ ኦነግ እንዲሁም የ ሌንጮ ለታ ቡድን ፣ የመረራ ጉዲና፣ የቡልቻ ደምቅሳ ተብሎ ተደርድሮ እየትኳረፈ፤ ከቻለም እየተታኮሰ ሲፋጭ ማየት ነው። እንደነሱ ፍላጎት አባዱላ አብዲ ፊጤን በታንክ ደምስሶ ሲሸልል ወይንም አብዲ ፊጤ አባዱላን በ አስቀያሚ ስድብ ዘርጥጦት ሲያዋርደው አይተው ሁለቱንም ለ mutual self destruction ማበረታታት ነው።”

በመጀመሪያ እንደጃዋር ትንተና ከሆነ በአባዱላ እና ኦኤምኤን ግኑኝነነት የተንጫጩት በሙሉ ግልገል ነፍጠኞች ናቸው፡፡ በአባዱላ እና ኦኤሜን ግኑኝነት የተቆጡትን ሁሉ ግልገል ነፍጠኞች ብሎ መፈረጅ በውስጡ እጅግ አሳዛኝ ስህተት አዝሏል፡፡ እኔም ሆንኩኝ ሌሎች ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛ የሆንን ኦሮሞዎች መቼም ግልገል ይሁን ኮርማ ነፍጠኛ፤ ጎበና ይሁን house nigger ተብሎ መፈረጅ ፤መረገም መሰደብ ምንም አይመስለንም፡፡ ነገር ግን ከእነጃዋር ጋር ገንዘባቸውን፤ ጊዜአቸውን፤ እውቀታቸው አዋጥተው ኦኤምኤንን ያዋቀሩ አሁንም ኦኤምኤንን እያገዙ ያሉ ነገር ግን በአባዱላ እና ኦኤምኤን ጋዜጠኞች ግኑንኝት የተቆጡትን ኦሮሞ ብሔርተኞችም ከእኛ ጋር ደርቦ ወምቀጡ ለእነሱም ለተነሳውም ጥያቄ የጃዋር ገለጻ ፍትህ ይጎድለዋል እላለሁ፡፡ ጥያቄውን ለማጣጣል ከመጣር ጥያቄውን በድፍረት እና በእውነት መጋፈጥ ሳይሻል አይቀርም፡፡

በመቀጠል ከላይ እነዳስቀመጥኩት በኦኤምኤንም እና አባዱላ ቢዴና መቋደስ በርካታ ሰዎች በዋነኛነት የተቆጡት ለምን የኦኤምኤን ጋዜጠኞች በቃላቸው አልተገኙም ? እነዚህ ጋዜጠኞች የኦሮሞ ወቅታዊ ሰቆቃ ያንገበግበናል የሚሉ ሰዎች አይደሉምን ?የሚል ትያቄ ነው፡፡ የእነዚህ ሰዎች ጥያቄ የተመሰረተው በምናባቸው ሳይሆን የኦኤምኤን ጋዜጠኞች ላይ በታየው መሰረታዊ የእምነት ንግግር እና ተግባር ግጭት ነው፡፡ ለዚህ የሞራል ክስረት ጣጣ ጃዋር ያቀረበው ምልከታ የኦኤምኤን እና የኣባዱላ ግኑኝነት የተቆጣነው ሰዎች የቁጣችን ምንጭ ኦሮሞ አንድ እንዲሆን ማየት ስለማንፈልግ ነው፡፡ ይሄ የአንድነት ጥሪ (አንድነቱ በኦሮሞዎች መካከል ብቻ ነው ለጊዜው) በውስጡ ብዙ ትልልቅ ስንጥቆች አሉበት፡፡

አንደኛ ኦኤምኤን ከምር ከአባዱላ ጋር መታየት ፈጽሞ ካላሳፈረው የባለሙያነት ግዴታቸው ሊወጡ ሲሉ እራት ተጋብዘው ምናመን የሚል ሌላ ሀተታ ምክንያት ማቅረብ አያስፈልግም፡፡ በቃ ልክ ኢሳት ለሻቢያ እና ኢሳያስ አፈወርቂ እንደሚያሸረግደው ከዛ ደግሞ አይኑን በጨው አጥቦ ያለእኔ ኢትዮጵያ አንድነት ጠባቂ የለም እነደሚለው ኦኤምኤንም አይኑን በጨው አጥቦ የለምንም እፈረት ፊንፊኔ ገብቶ ላይቭ ዜና ይዘግብልን፡፡ ከዛም ደግሞ ያለ እኔ የኦሮሞ ድምጽ የሚያሰማ የለም ይበለን፡፡ ኢትዮጵያ አንደው መደነባበር አዲስ አይደል፡፡

ሁለተኛ እነጃዋር እነደሚሉን በኦሮሞ ልጆች መካከል ያለውን የአይዲዮሎጂ ልዩነት ተሻግሮ አባዱላ ገመዳን ለመሸከም የሚችል ትከሻ ካለ ወይንም አንዲህ አይነት የአይዲዮሎጂ ትከሻ መኖር ካለበት ለምን አባዱላ ገመደን በመሸከም ላይ እንቆማለን ? በዚህኛው ፌክ አባዱላ ላይ ከመቆም ወደኋላም ከታሪክ ራቅ ብለን የራሱ ጦር ከነበረው የፈረሱ እስትንፋስ ብቻ ተራራራን ከሚንጠው እውነተኛው አባዱላ እስከራስ ጎበና ዳጬ ድረስ ሄደን የኦሮሞን ታሪክ ለምን አንሸከምም? እነጃዋር አባዱላ ዛሬ እያፈሰሰ ያለው ኦሮሞ ደም ራስ ጎበና ዳጬ አፍሶታል ከሚሉት በምን እነደሚለይ እስቲ ይንገሩን፡፡

ሶስተኛ ኦሮሞ አንድ ነው ኦሮሞ አልተከፋፈለም ብሎ ሆ ማለት ለጊዜው የተወሰኑ ሰዎችን ያሰባስብ እነደሆነ እንጂ ኦሮሞ ባይከፈል ኖሮማ እነ አባዱላ አሳልፈው ባልገበሩን እኛም በአገራችን በኖርን፡፡ ከመካከላችን ለመጥረቢያው መያዣ በመሆን እያስጨፈጨፉን ያሉትን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችችን እኛም አወቅናቸው ዓለም አውቋቸው የአደባባዩን ሚስጥር ለመሸፋፈን ምን አቻኮለን? ጃዋር እነደሚለን በኦሮሞ መካከከል አለመግባበት አንዳለ ለማወቅ “አባዱላ አብዲ ፊጤን በታንክ ደምስሶ ሲሸልል ወይንም አብዲ ፊጤ አባዱላን በ አስቀያሚ ስድብ ዘርጥጦት ሲያዋርደው አይተው ሁለቱንም ለ mutual self destruction ማበረታታት ነው።” ማየት አያስፈልገንም፡፡ አባዱላ ዛሬ አብዲ ፊጣን ባነካው በየቀኑ በታንክ የሚደፈጥጣቸውን የኦሮሞ ልጆች በስም እናውቃቸዋለን፡፡ ለነገሩ ጃዋር የሄደባት የ face saving መንገድ ማንም ብሔርተኛ በካምፑ ውስጥ ያለውን ቀውስ ለማረጋጋት የሚጠቀምበት የሰነበተ መሳሪያ ነው፡፡

የኦሮሞ ብሔርተኞች ስሌት እና የኦህዴድ ስሌት ግጭት

ጉዳዩን በጥልቀት ያሰበበት የኦሮሞ ልሂቅ ሁሉ እነደሚያውቀው በአሁነ ሰአት ኦሮሞን የመጨቆኛው ዋነኛ መሳሪያ ሌላ ሳይሆን ኦሮሞ ብሔርተኝነት እራሱ ነው፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ዛሬ በአብዛኘው በሚሰበክበት እና በሚተገበርበት መልኩ እስከቀጠለ ድረስ በርካታ ብሔርተኞች እነደሚመኙት የኦሮሞ ሕዝብ ነጻ ማውጫ መሳሪያ ሳይሆን የኦሮሞ ሮሮ ዋነኛ ምንጭ እንደሆነ ይቀጥላል፡፡

እንዴት? ልክ ጃዋር እንዳስቀመጠው በአሁኑ ወቅት የኦሮሞ ብሔርተንነት ዋነኛ ትኩረት የኦሮሞ ልጆችን ከሌሎች Oromo vs the other ማሰባሰብ ማደራጀት ማነቃቃት ላይ ያተኩራል፡፡ ግቡም በአብዛኛው ለኦሮሞን እድል አስፈላጊ ከሆነ ኦሮሚያን እነደአዲስ አገር እሰከመገንባት ድረስ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን በማስከበር ላይ ያተኩራል፡፡ ኦሮሞ ብሔርተኞች በዚህ ፕሮጀክት ሙሉ እምነት ኖሯቸው ከውስጥም ከውጭም ይሰራሉ እንበል፡፡ ይሄ አጀንዳቸው አጀንዳቸው ኦፒዲኦን እነደጠላት ሳይሆን እነደ ፕሮጀክቱ አንድ አካል አድርገው እንዲያዩ ይጋብዛቸዋል፡፡ ስሌታቸውም በአብዛኛው የሚቃኘው ዓለም እንዴት መስተካከል አለባት (Ought to be) በሚል ቅንኝት ነው፡፡ ምክንያቱም ትኩረታቸው አዲስ ስርዓት በመፍጠር የኦሮምን ጥያቄ በመመለስ ላይ ስለሚያደላ፡፡

ጋሼ ኦፒዲኦ ግን እነደ ኦሮሞ ብሔርተኞች ዓለም እንዴት መስተካከል እዳለበት ሲጨነቅ አይገኝም ፡፡ የጋሼ ኦፒዲኦ ዋነኛ ስሌት የተቃኘው ዓለም ዛሬ ላይ እንዴት ትንቀሳቀሳለች (What is the world like) በሚል ቅንኝት የተሰላ ነው፡፡

የኦህዴድ የሌት ተቀን ትልቅ ጭንቀት “ ዛሬ ላይ ባለው እውነታ ተመስርቼ ምን ያህል ሀብቴን አዳብራሉ ” ብቻ ነው፡፡ አባዱላ ወያኔ አለቆቹ ፊት ሲቀርብ “ለእኔ ፍርፋሪ ካልጨመራቹ ወየውላቹ ” ይላል፡፡ ሚኒሶታ ሲመጣ ደግሞ “ እኔኮ ባልሆን ኖሮ ትግሬው አገር ጨርሶ ነበር ” ብሎ እራሱን እነደ ተግባራዊ (Pragmatic) ታጋይ ያቀርባል፡፡

በዚህ ስሌት ስናየው አባዱለ እና ኦህዴድ በእጅጉን የሚጠቀሙት አሁን ያለው የኢትዮጵያ መዋቅራዊ እውነታ (Status Quo) ባለበት ሲቀጥል ብቻ ነው፡፡ በእነሱም መፍረድ ይከብዳል ከትቢያ ላይ አንስቶ ሚሊየን ዶላር ያስቆጠራቸውን ስርዐት ለምን ሲሉ ይገረስሳሉ ? ለኦህዴድ ከኦኤሜንም ጋር መቀመጥም ሆነ የኦሮሞ ብሔርተኞችን ማባበል በኦሮሞ ጥያቄ ላይ አንዳች ደንታ ስላለው አይደለም፡፡ በአለቆቹ ፊት የፍርፋሪ መጠን ማስጨመሪያ ምርጥ የመደራደሪያ ካርድ ግን ይሆኑለታል፡፡ ፍርፋሪ ስታንስ ጭምብል እየቀሩ ቢያስቸግሩት አይደል መለስ እያንዳንዱ ኦህዴድ ሲፋቅ ኦነግ ነው ያለው፡፡ ኦህዴድ እንዲህ በዳዴ እሄድ ቢበላ ክብር ይጎድለዋል እንጂ የስሌት ችሎታ ፈጽሞ አልጠፋውም፡፡

የሌንጮ ጉዞ ወደ ፊንፊኔ

ከስደት ወደውጪ አገርን እነደሚናፍቅ ፖለቲካዊ ያውም ኦሮሞ ፖለቲካዊ ሰው የሌንጮ ወደ አገርቤት መመለስ በብዙ መልኩ ያስደስተኛል፡፡ በመጀመሪያ የምደሰተው ለሌልጮ ለራሱ ነው፡፡ እስቲ የናፈቁት ዘመዶቹን አይን ይበት፤ እስቲ ላለፉት 20 ምናመን ዓመታት ያልደረሰቸውን ለቅሶዎች ይድረስበት፤ እስቲ ከልጅነት ጓደኞቹ ጋር ቁጭ ብሎ ይጫወትበት፤ እስቲ ከልጅነት መንደሩ ከሽማግሌዎቹ ጋር ቁጭ ብሎ ጠላ ይጠጣበት፡፡ ሌላዉ ሁሉ ይቅር ይህ ትልቅ ኦሮሞ ዋርካ ከብዙ ዘመን ስደት በኋላ እነደነ ሲሳይ ኢብሳ በአስከሬኑ ከተወለደበት አፈር ጋር ከሚገናኝ በሕይወት ሳለ በልጅነቱ ያቦካውን አፈር በሕይት ይየው፡፡ የሌንጮ መመለስ የመጀመሪያው ተግባር መንፈሳዊ እርቅ ለሌንጮ ማምጣት ነው፡፡ ይህ መንፈሳዊ ጥማት ፖለቲካዊ ሳይሆን ሞራላዊ ግብ ነው፡፡ ከአሊ ቢራ የባሰ የተሰደደ በስደትም ሳለ ስለሕዝቡ የጮኸ ማን አለ ግን በቃ ሳይሞት አፈሩን ማየተ ፈለገ ወደ አገርቤትም ገባ፡፡ የኦሮሞ አዙሪት እደው አሊቢራ ጮኽም ዝም አለም አላባራም፡፡

የእነ ሌንጮ መመለስ ግን ይሄነው የሚባል የፖለቲካ ለውጥ በኢትዮጵያ ላይ ያመጣል ብሎ መጠበቅ ተገቢ አይደለም፡፡ ሌንጮም ሆነ ፓርቲው ግፋ ቢል ኦህዴድ እና ወያኔ በሚያደርጉት የፍርፋሪ ድርድር ወቅት እርስ በእርስ የሚቀባበሉት የከረንቡላ ድንጋይ ከመሆን አይዘልም፡፡ የዘንድሮ ኦህዴድ ማለት ሌንጮ ትቶት የሄደው ኦህዴድ አይደለም፡፡ ዘንድሮ ኦህዴድ ሚሊየነር ደጋፊዎች እና አባላት ያሉት፤ የራሱ ትንንሽ ቡችሎች ያፈራ ትልቅ ውሻ ነው፡፡ ሌንጮ ኦህዴድን መቀላቀል እንኳ ቢያስብ በሩ ላይ ወረፋ ከያዙ በርካታ ግልገል ኦህዴዶች ጋር መፋለም ይኖርበታል፡፡ በፖለቲካው ተሳካለትም አልተሳካለትም ሌንጮ ለመንፈሱ ሲል ወደ አገሩ ይመለስ፡፡ ሌላውን አንኳን ዋቃ ይወስነዋል፡፡

The post ሌንጮ ለታ፤ ኦኤምኤን ፤ አባዱላ ገመዳ እና የሞራል ኪሳራ – እንደ ተጨማሪ ማብራሪያ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>