Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

  የተስፋ ጣዝማ –የአሻም ብራ! -ሥርጉተ ሥላሴ

$
0
0

ከሥርጉተ ሥላሴ 17.02.2015 /ዙሪክ – ሲዊዘርላንድ/

Haile Medhin Aberaዛሬ የካቲት 17 ቀን 2015 ጀግና ሃይለመድህን አበራ የአሻምን ብራ ችቦ ጄኔባ ላይ በተግባር ያዘመረበት ዕለት ነው። ልክ አመቱ። አሻም የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ በማለት በዝምታ፤ አንዲት ቆራጣ ንብረት ሳይወድም፤ አንድ ትንፋሽ ከመኖር ሳይቋረጥ፤ በእንግዶቹ ላይ ምንም ዓይነት የመንፈስ ጫና ሳይፈጥር የወጣትነቱን ፍላጎት ሁሉ ፈቅዶና ሰውቶ ጸጥ በላ ጭምታዊ መንገድ ገዢ መሬቱን የተቆጣጠረበት ዕለት ነው። ዕለቱ የወገኖቻችን ሆነ የሌላ ሀገር ዜጎችም ነፍስ ሳይጠፋ ወይንም ሳይቀጠፍ፤ ጥቁር ሳይለበስ ወይንም ደም ሳያበቅልበት ትሁት በሆነ የሰብዕዊነት ሥነ – ምግባር ጎርብጦኛል ያለውን የወያኔ አስተዳደር የታገለበት፤ ደግሞም የረታበት የሰላማዊ ትግል ውጤት ነጥሮና ጎልቶ የወጣበት ልዩ ዕለት። ተባረክ የእኔ ጌታ! አሳዳጊህንም ይባርካው አምላኬ። አሜን!

ከእሱ ሰላማዊ ውጤት በኋላ እስያ ላይ ሰፊ የሆኑ ተደጋጋሚ የአውሮፕላን አዳጋዎች ደርሰዋል። የፍጥረት እልቂቶች፤ የንብረት ጥፋቶች፤ የሀብት ብክነቶች በተከታታይ ታይተዋል። በዛች ቀውጢ ሰዓት ሰማይ ላይ የፍጥረት መንፈስ ውጥረት የቤተሰብና ዬአለም ማህበረሰብ ጭንቀትና ጥበት ሲታሰብ ደግሞ መስፈርያ የለውም። በፍጹም። አስተዋዩ የተስፋ ጣዝማ ግን ፍውስት ነበር ማለት ይችላል። ሊገመቱ የማይችሉ የመንፈስ ጫናዎችን ሁሉ ነበር በብልሃት አስቀድሞ – የታደገው። ሂደቱም ውጤቱም ልባም ነበር። ቀንበጡ በሰከነ፣ በበሰለ፤ በተባ፤ በቀላማም ንድፍ ተክህኖ ለድል በቃ። ድሉ የዓለም ማህበረሰብ ሁሉ ነው። የሰው ልጅ ህይወትን እንዲህ ባስተዋለ መንገድ ማዳን በኽረ ውጤት ነውና። ስለሆነም ጀግናዬ ሃይለመድህን አበራ በማስተዋል ዕለቱን – ዘርቶ – አብቅሎ አፍርቶና – ፈርቶም አሳዬ። ኑርልኝ የእኔ አባት!

እንሆ ጊዜ ታሪክን ይሰራል። ፍቅርን የተረጎሙት ዶር. ሼክስፔር ፈይሳም ከሀገረ አሜሪካ ወደ ሲዊዝ ጄኔባ ተጉዞው የአካላቸውን ሁኔታ ለማዬት ፍቅርን ለፍቅር ጃኖ አለበሱ። ፍቅር ስለ ቃሉ ፍቅር መሆኑ ብቻ ሳይሆን ፍቅር ሲሆኑት ተግባሩ እራሱ ፈክቶ ይተረጉማል። ለዜግነታቸው፤ ለብሄራዊ ክብራቸው፤ ለወገኖቻቸው ችግር ቅርብ በመሆን፤ ለንጹህ ወንድማዊ መንፈሳቸው እራሳቸውን ማግደው በመከራ ቀን አብረው በመገኘት ታሪክን እንሆ ጻፉ። ሙያና ሥነ – ምግባርም ፍሬ አፈሩ! ትውልዱን አፈለቁት – በፍቅር። ትውልዱን አስመሰገኑት – በተስፋ። ትውልዱን አስባረኩት – በደግነት፤ ትውልዱን አበረታቱት – ሆነው በመገኘት። ከተሟላ አክብሮት ጋር ምስጋና ብቻ ሳይሆን የእርሳቸውም ተማሪ መሆኔን በአጋጣሚው ልገልጽ ወደድኩኝ። ሰው እንዲህ ሲኖር ጨለማው – ይነጋል። የተቀደደው ተስፋ – ይጠገናል። የዛለው ክንድ ብርታትና ኃይል ያገኛል። አብነት – የዘመናት። ድንግል ትጠብቅልን! አሜን! የዘመን – ዋርካ።

ከዚህ በተረፈ በምልዕት የወንድማቸውን ችግር የተጋሩ፤ ፊት ለፊት ወጥተው የመሰከሩ፤ ምስክርነቱን ያዘከሩ፤ ለዝክራኑ ፈቃድ በመስጠት ያተሙ – ያሰራጩ፤ በብርድ በቁር የተንገላቱ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ጀግናችን ያሉ፤ ስለ እሱ የተቆረቆሩ – የተንገበገቡ ሁሉ ዋጋ ከፋዩ አምላክ ነውና እኔ እንደ አንድ ሀገር ወዳድ ዜጋ አምላክ በያሉበት በስውር ዋጋቸውን ይክፈል እላለሁ። እግዚአብሄር ለወግ አብቅቶትም ውለታቸውን በአንደበቱ ለመመስከር ያብቃው። አሜን!

ማህጸነ ሲዊዝም ደግ ናትና እፍን ሽክፍ አድርጋ፤ ሽሽግ አድርጋ ስለያዘችው፤ በዕንባው ቀን በመገኘት ዕንባውን ስላበሰችም የከበረ ምስጋና ለኮሽ አይሏ ሲዊዝም ይደረስ ብያለሁ። በተረፈ መንገዱ እርጥብ ነበር። ጉዞው የተሳካ ነበር። ይሄው ልክ በዓመቱ መግቢያ መባቻ የአውሮፓ አህጉራዊ ድርጅት ከአንድ ግልጽ፣ ወሳኝ አቋምና ውሳኔ ደረሰ። ከእንግዲህ በኋላ አውሮፓ ላይ ያለ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ አስፈጻሚ ደጋፊ፤ ተባባሪ፤ ኢንባሲ፤ ቆንሲላ ጽ/ቤት፤ የስለላ ድርጅት ምን ሥራ ሊኖራቸው እንደሚችል አምላክ ይወቀው። የቅጥፈቱ የሎቪ ሥራው በር ተከርችሟ ሥራ ፈላጊ አድርጓቸዋልና። ከእንግዲህ ጆሮ የለውም አውሮፓ ….. ለወያኔ ሃርነት የተዛባ መረጃ። እኛም እልልልል – አልን –

ይህ በራሱ የካፒቴን ሃይለመድህን ውሳኔ ትክክለኛነት ዕውቅና ያሰጠዋል። ቢከፋው ነው። ባይመቸው ነው ከሚል ዕድምታ ያደርሳቸዋል። ስለዚህ ለዘለቄታ ኑሮው፤ ተስፋው፤ ህልሙ ሰፊ የሆነ የሰላም መስመር ይመሰልኛል። ጥግ አልቦሽነት በስደት፣ ከስደቱ በላይ የከፋው ገጠመኝ ነው። ስደት በራሱ ጨለማ ነው። አድማጭ ሲጣፋ ደግሞ ቀኑም ጨለማ ይሆናል። የጨለማ ጉዞ ደግሞ መሰናክሉን አልፎ ለመሄድ ጋዳ* ነው። አሁን ግን አነሰም በዛም ብርሃን አለ …. ብርሃኑ ቀርቦ ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ ደግሞ  ከፈጣሪ ጋር የሁሉም ተሳትፎ በቅንነት ከታከለበት ንጹህ ልቦና የማሸነፍ አቅም ነውና – ነገ ይነጋል።

በተረፈ ዕለቱን በማሰብ እንደምትችሉት ብታደርጉ ደስታዬ ነው። ግን ትእዛዝ አይደለም ትሁታዊ አስተያዬት እንጂ። ውጤትን ማክበር፤ መስዋዕትነትን መጠበቅ የአደራ ድሪ ይመስለኛል። ተከታይንም ያነሳሳል – ያበረታታል። በተረፈ ዘሃበሻን ከልብ አመሰግናለሁ። በዬወሩ የምልካቸውን ጹሑፍ ካለመሰልቸት ነበር የሚያወጡልኝ። ያቆምኩትም እራሴ ነኝ። የአላጋጩን የወያኔን ምርጫ በሚመለከት በርካታ ጸሐፍት ሃሳባቸውን እዬገለጹ ስለሆነ ቦታ ላለመሻማት በሚል። ነገር ግን በወር ሁለት ጊዜም በተስፋ ማህጸን ጀግናዬ አበራ ሀይለመድህን በቋሚነት ተግባሩ ይነግሣል – በጸጋዬ ራዲዮ። መሸቢያ ሰሞናት – ውዶቼ!

መፍቻ ….. ጣዝማ* … የማር ዓይነት ነው። የሚገኘው ግን ቆላ ገደል ውስጥ ነው። በሌላ በኩል ጣዝማ የቀለም ዓይነትም ነው። ጣዝም ቀለሙ በቅቅል ዶሮቄት የሚዘጋጀው በጎጃምና በጎንደር የጠላ አጠማመቅ ሂደት እስከ መንፈቅ ዓመት ሲቆይ መልኩ ጣዝም ዓይነት ይሆናል። ወይንም የድፍድፉ ሊፍተር ቀለሙ ጣዝማ ቀለም ነው። ጣዝማ ማር አይነጠረም። እራሱ ሲፈጠር የተነጠረ ነው። ሌላው የማር ዓይነት ግን በፀሐይ ይነጠራል። ስለዚህ ጣዝማ ጣጣውን የጨረሰ ኮለል ያለ የጠራ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ጣዝም ቁጥር ሊወጣላቸው የማይችሉ በሽታዎች ፈዋሽ መዳህኒት ነው። በቀላሉም ገብያ ላይ አይገኝም። ውድም ነው። ጣዕሙም ሆነ ይዘቱ የተለዬ ነው። ስለዚህ ካፒቴን ሃይለመድህን አበራ ለእኔ የተስፋ ጣዝማዬ ነው።

*ሊፍተር – ከጥሩ ጠላ ይለያል። ድፍድፉ በወፍራሙ ይዘለልና በከረጢት ይታሰራል። ከዛ ጭማቂው ሊፍተር ይባላል። በጣም ሃይለኛ ነው። የኢትዮጵያ ውስኪ ልበለውን ከቶ …. እንደዛ። ግን ሊፍተር የረጅም ጊዜ ድፍድፍ ብቻም ላይሆን ይችላል በአፍለኛ ድፍድፍም ይዘጋጃል። ከነጭ ጠላም* ሊፍተር ይዘጋጃል።

*ነጭ ጠላ —- ብዙ ጊዜ ነጭ ጠላ በዳጉሳ ነው የሚዘጋጀው። ነጭ እንዲሆን ሲፈለግ አብሽሎው አነባበሮ ዓይነት ይሆንና በብረት ምጣድ ሳይሆን በሙጎጎ /በምጣድ/ ነው የሚጋገረው። ከላይ እንደጠቀስኩት ከነጭ ጠላ ድፍድፍም ሊፍተር ማዘጋጀት ይቻላል። ግን እንደ ተለምዷዊ ድፍድፍ ጠላውና እንደ ዕድሜ ጠገቡ የቅቅል ዶሮቄት ድፍድፍ የብርቱነት አቅሙ እንደ አቅሙ ይሆናል።

ጋዳ* ከባድ ችግር፣ መፍትሄው ሩቅ ወይንም ቀላል ያልሆነ እንደ ማለት ነው፤

ብራ* ጭፍግግ ያለው ጨቅጫቃ አረንቋ ቀን ተሸኝቶ ወለል ባለው ሰማይ ላይ ብርሃን ሲነግሥ ….. ሰውነትም ቅልል ብሎ ለማናቸውም ግዳጅ በብቃት ሲዘጋጅ …. ወዘተ …..

ጀግኖቻችን መርሆቻችን ናቸው!

እግዚአብሄር ይስጥልኝ!

 

 

The post   የተስፋ ጣዝማ – የአሻም ብራ! -ሥርጉተ ሥላሴ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>