Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የደቡብ አፍሪካዊያን ዕዳ! –ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

$
0
0

ethiopian-in-south-africa

የማንዴላ ልጆች ወገኖቹ ፤ የዋልንላቸው ውለታ
ይህች አፍሪካ በነጻነት ፤ እንድታገኝ እፎይታ
ጥረታችን ሁሉ ሰምሮ ፤ አገኙና ነጻነት
በእኛ ቀን ሲዘነብል ፤ ብንሔድባቸው ስደት
ከቅኝግዛት እስከ አፓርታይድ ፤ የረገጣቸው እያለ
ወንድም ጓዱን ሐበሻ ፤ ስለ እሱ ዋጋ የከፈለ
ከሀገር ይውጣ ብሎ ጮኸ ፤ ጎዳናው ላይ እያቃጠለ፡፡
ምንነው ወገኔ ምን ነው? ፤ አእምሮም የለህ ማሰቢያ?
ምን እንደሆነች አታውቅም? ፤ ውዷ የኔ ሀገር ኢትዮጵያ?
በከፈልንላቹህ ዋጋ ፤ በእናን ተየተነሣ
እንዲህ ሆና እንደቀረች ፤ በነጫጭ ጅቦች ተነክሳ?
ታወክን ታመስን እንጅ ፤ በነጭ ሰይጣናት እከይ
ወደ እናንተ የተመምነው ፤ መች አጥተን ነበር ሲሳይ
ስለ እናንተ ባደረግነው ፤ ከዲፕሎማሲው ማሳደም
መሪዎችህን አሠልጥኖ ፤ በግንባር እስከ ማፋለም
በእኛ ጥረት ነበርና ፤ ነጻነትህ የተገኘ
ጥርስ ነከሱ በእኛ ላይ ፤ ልባቸው በቀል ተቃኘ
እርስ በርሳችን ብንባላ ፤ እንድንሆን ከንቱ መና
ያለ እነሱ ማንም የለም ፤ የሴራው ምንጭ ሲጠና
ላንተ ስንል በከፈል ነው ፤ ለዚህ ብንበቃ ብናጣ
ማስጠጋት ሲገባህ በክብር ፤ የጠላትህን ባላንጣ
የክፉ ቀንህን አጋር ፤ የተሰጠህን ዕጣ
እሳት በላዩ እየለቀክ ፤ ማባረሩ ነው የሱ ዋጋ?
ከቶ በምን ሒሳብ ነው? ፤ ሕሊናም የለ አንተ ጋ?
ፍዳ ያስቆጠረህ ባዕዱ ፤ እየኖረ ተንቀባሮ
ላንተም ኢምንት ያልከፈለው ፤ መጥቶ ከህንድ ተሻግሮ
በምቾት ድሎት እየኖረ ፤ ሞጃ ሆኖ ገኖ ከብሮ
በገዛ የራስ ሀገርህ፤ አንተን ባዶ አርጎ ገፍትሮ
የገዛ ሀገርክን ከተማ ፤ እያስቋመጠህ አማልሎ
ነጻነትህ ትርጉም አጥቶ ፤ ገብተህ ለመርገጥ ከልክሎ
ይሄ ሳያምህ ሳይቆጭህ ፤ ወኔህተሰልቦ ተገሎ
ሀሞትህ ፈሶ ፈራርሶ ፤ ጉልበትህ ከድቶህ ሰልሎ
ይሄንን የሚያህል ውርደት ፤ ተሸክመኸው እያለ
በዚህ ዘመን አሁን ዛሬ ፤ ነጻ ነኝ እያልክ ታደለ
ምስኪኑ ደሀው ወንድምህ ፤ ምን አረገ? ምን በደለ?
ያንተን ቀንበር ተሸክሞ ፤ በሞተልህ በቆሰለ?
ሀገሬን ካልክ መብቴን ፤ የራሴን ሀብት እንጀራ
የወሰደብህ እያለ ፤ ድልቡን ዋናውን ጎተራ
ፍርፋሪውን ለቃሚው ፤ ወንድም ሐበሻው ምን ሠራ?
እንዴት ነው እሱ ነገሩ ፤ የባሕል ወጋቹህ ዕይታ?

ጠላትን ከወዳጅ መለያው ፤ ብድር ለመክፈል ውለታ
ተገላቢጦሽ ነው እንዴ? ፤ ለወዳጅ ክፉን መልሶ
ዘርፎ እራቁቱን ማስቀረት ፤ ካገር ማባረር አስለቅሶ?
ገድሎ መንገድ ላይ መጎተት? ፤ መልካም ምግባሩን አርክሶ?
መልካሙን ለጠላት በማቅረብ ፤ ባርነትን መኖር መልሶ?
ይሄ ነው ባሕል ወጋቹህ? ፤ የማሰብ ልካቹህ ተሐድሶ?
እኛ እኮ እንደዚያ የደከምን ፤ ከዲፕሎማሲም ኃይል እርዳታ
እንድትኖሩ አልነበረም ፤ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ
ወይ ከዳር ደርሶ አላየን ፤ የነጻነቱን ፍልሚያ
ድካማችንን ከንቱ አረገው ፤ ዛሬ ያለብህ ግሊያ
እንዲህ በአድሎ እየኖርክ ፤ ከማዶ ከኬላ ወዲያ
አፓርታይድ የለም ትላለህ? ፤ በዚህ አናፍርም ታዲያ?
ዕያየነው በመሆኑ፤ ዛሬም ሆናቹህ ባሪያ

ለማይሆን ነገር በከንቱ ፤ ብናስገኝ ላይ ታች ሮጠን

ነጻነትህን አልኖርከው ፤ ለእኛ ነው ቂሙ የተረፈን፡፡
ወገኔ ማጥፋት ማስወገድ ፤ ድል ማድረግ ያለብህ እኮ
ይሄንን ውርደትህን ነው ፤ ያስቀረህን አንበርክኮ
ሀገርህን ማስመለስ ነው ፤ ከተወሰደብህ ምርኮ፡፡
የኔስ ግምት የነበረው ፤ ወገኔ ሆኖ ስደተኛ
ወዳገርህ ሲጎርፍ ሲተም ፤ ሆኖ ሊኖር ጥገኛ
ያለውን ህልም ያውቃሉና ፤ ዓላማ ምኞቱን ለአንተ
የፈራሁ ነጮቹን ነበር ፤ ግምት ሥጋቴ ሳተ
ጭራሽማ እዚህ ገብቶ ፤ አብሮ ሆኖ እየኖረ
በምክር እያነሣሣ ፤ ገፋፍቶ እያዳፈረ
መፈጸሙ አይቀር ብለው ፤ የቀረውን የቤት ሥራ
ያነቃብናል ዋ! ኋላ ፤ መንገድ ጠቁሞ እየመራ
አይሆንም ሐበሻ ይውጣ ፤ ብየ እንዳያሴሩ ሴራ
እንጅ እናንተማ እንደምን? ፤ እኮ እንዴት ብየ ጠርጥሬ?
ወንድም ነው ዕዳም አለበት ፤ ባልኩት እንዳይን አሳሬ፡፡
ግን ምንም ያለህ አልነበረም ፤ እሱ አባትህ ማንዴላ
ዕዳ አለብን አላለህም? ፤ ያንን ዕዳ እንዳትበላ?
ወይስ ነው ችግሩ ያንተ? ፤ ቃሉን ያልሰማህ አደራ?
ማዲባዬ እያልክ አባቴ ፤ የነጻነት ታጋይ አውራ
ኧረ ተው አባትክን ስማ ፤ ሰምተናል ብዙ እንዳለ
ጠብቅ እንጅ ቃል አደራን ፤ ምን ነው? በማን ተማለ?
ይሄንን ቃል ባትሰማ ፤ በሰማይ ባንተ ፍርድ አለ!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ጥር 19 2007ዓ.ም.

The post የደቡብ አፍሪካዊያን ዕዳ! – ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>