Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

መዓት አውርድ! –አስራት አብርሃም

$
0
0
Asrat Abrha

አስራት አብርሃም

በዘመነ አፄ ልብነድንግል ጦርነት በመጥፋቱ ንጉሱ ጦርነት አውርድ ተብሎ በየቤተክርስቲያኑ ፀሎት እንዲደረግ ትዕዛዝ አውርዶ ነበር እየተባለ በአፈ ታሪከ ይነገርለታል፤ 24 ዓመት የሞላው የህወሀት/ኢህአዴግ ስርዓትም ጦርነት አውርድ፣ መዓት አውርድ እያለ እንደሚገኝ ከደርጊቶቹ ሁሉ መረዳት የሚቻል ነው። አንድነት ፓርቲ በኃይልና በውንብድና እንዲፈርስ ከተደረገ በኋላ ምንም የማደርገው ነገር ስላነበረ፤ ቤቴ ሄጄ ነው ቁጭ ያልኩት፤ ከፌስቡክም ገለል ለማለት ፈሊጌ ነበር ለጊዜው! እነርሱ ግን መቼ ያስቀምጣሉ፤ መቼ ይተዋሉ፤ ቤትህ ድረስ መጥተው ሰላም ይነሱሃል፤ ዝም ብትል የሆነ ነገር አስቦ ነው ይሉሀል፤ ብትናገር በተናገርከው ቂም ቋጥረው ያጠቁሃል፤ ብትፅፍ በሽብር ይከሱሃል፤ ከሰው ያስሩሃል፤ አስረው አይተውሁም፤ ያሰቃዩሃል፤ ይገርሁፋል፤ ቤተሰብ ዘመድ እንዳይጠይቁህ ያድርጋሉ፤ በምንም መንገድ አይተውሁም፤ ቢገድሉህ እንኳ ስምህን፣ ታሪክህን ያጠፋሉ፤ ምን ዓይነት ስርዓት ነው የገጠመን!

ባለፈው እሁድ ማታ የዱርዬ አለባበስ የለበሱ ሁለት ወጣቶች የተከራየሁበት ቤት በር ድረስ መጥተው እንፈልገሃለን አሉኝ፤ እናንተ ደግሞ እነማናችሁ፤ በዚህ ሰዓት የምትፈልጉኝ አልኩዋቸው በጥንቃቄ ራቅ ብዬ እንደቆምኩ፤ ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል ይባል የለ፤ የትዕግስቱ አወሉ ጎረምሶች ይሆናሉ ብዬ ነው ጥንቃቄ ማድረጌ! ከደህንነት መስሪያቤት ነው የመጣነው ሲሉኝ ለካ የዋናው ጎረምሶች ኖሯል ብዬ እየተደነቅኩ አሁን ከምትሉት መስሪያቤት ለመምጣታችሁ በምን ማወቅ ይቻላል አልኩዋቸው አንደኛው የሆነ መታወቂያ አውጥተው አሳየኝ፤ መሽቶ ስለነበር የመታወቂያውን ይዘት በደንብ ለማየት አልቻልኩም፤ የሆነ ሆኖ “በዚህ ሰዓት እኔን ማናገር አትችሉም፤ መሽተዋል አንድ ሰዓት ሊሆን ነው አልኩዋቸው።”

አንዱ ፈጠን ብሎ መረጃ ፈልገን ነው አለ፤

ለመሆኑ ምን ዓይነት መረጃ ነው የምትፈልጉት ስለው፤

አቶ በላይ ፍቃዱ ከሀገር ስለወጣበት ሁኔታ የምታውቀው ነገር ካለ እንድትነግረን ነው።

በዚያ በበራችሁ መሰለኝ የሄደው አልነበራችሁም እንዴ! በማለት መለስኩለት (እንደ አቡነ ቴክለሃይማኖት ክንፍ አውቶ ሄደ ባልኩዋቸው ኖሮ!)

እየቀለድን እኮ አይደለም፤ አለ አንደኛው።

እኔም እየቀለድኩ አይደለም፤ በመሰረቱ እኔ ስለምትሉት ጉዳይ የማውቀው ነገር የለም፤ አንድነት በኃይል ከተወሰደብን ጀምሮ አግኝቸው አላውቅም፤ እኔ ደግሞ ቤቴ ነው ያለሁት፤ ሰው ሲተው አታውቅም እንዴ! አንዳንዴ እኮ ሁሉም ነገር መዝጋት ጥሩ አይደለም፤ መዓት አውርድ እኮ አይባልም፤ ይህን ሄዳችሁ ለአለቆቻችሁ ንገሩልኝ ብዬ ቀለል አድርጌ ሸኘሁዋቸው፤ ከተላላኪ ጋር አታካራ ውስጥ መግባት ትርጉም የለውም ብዬ ነው።

ጉዳዩ ግን በዚህ ብቻ አላበቃም፤ እንደገና ዛሬ ደግሞ የቀበሌ ካድሬዎች የተከራየሁበት ቤት ድረስ መጥተው የቤቱን ባለቤት የክራይ ውል አለህ ወይ? መታወቂያው ኮፒ አድርገሀዋል ወይ? አዋከቡት፤ የእኔን ስምም መዝግበው ይዘው ሄደዋል። እነዚህ ተላለኪዎች ደግሞ በተራው እኔን ግዳይ ጥለው ለመሾም፣ ለመታመን ይፈልጋሉ፤ እንግዲህ ዋናዎቹ መወሰን አለባቸው፤ እኔ በቦታዬ ነው ያለሁት፤ መግደልም ማሰርም ይችላሉ። ግን ምን ይሆን የሚፈልጉት! ፓርቲ መስርተህ ስትታገል ሊያጠፉህ ይፈልጋሉ፤ ቤትህ አርፈህ ስትቀመጥ ቤትህ ድረስ መጥተው ሰላም ይነሱሃል፤ ይሄ መዓት አውርድ እንጂ ሌላ ስም ልሰጠው አልችልም፤ መዓቱን ያውርድላቸው እንጂ እኔማ ምን ማለት እችላለሁ!

እዚህ ሀገር ግለሰቦች እንደፈለጉ ነው የሚያጠቁህ፤ ከለላ የሚሰጥህ የህግ ይሁን የመንግስት ተቋም ያለ አይመስለኝም፤ ይሄ ነው ደግሞ በጣም አሳዛኙ ነገር! በሌላ በእኩል ደግሞ እነርሱ ለፍትህ፤ ለሰላም እና ለዴሞክራሲ ታገልን ብለው አርባኛ ዓመታቸው እያከበሩ ነው፤ በመሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ሌላ ነው። ዛሬ እነርሱ በሚመፃደቁበት ዕለት እነ አብርሃ ደስታ፣ እነ ሀብታሙ አያሌው፣ እነየሽዋስ፣ እነዳንኤል እንዲሁም የዞን ዘጠኝ አባላትና ሌሎችም የህሊና እስረኞች የፍርድ ቤት ቀጠሮ ነበራቸው፤ ፍትህ አጥተው እነርሱና ቤተሰቦቻቸው እየተንከራተቱ ነው ያሉት። እንግዲህ የህወሀት የአርባ ዓመት ጎዞ የሚያሳየው ፍትህ፣ ሰላምና ዴሞክራሲ አይደለም፤ ዘረኝነት ነው የነገሰው፤ ፍትህ አልባነት ነው የሰፈነው፤ የባህር በራችን ነው ያሳጣን! ምንም የሚያኮራ ነገር የለውም!

በመሰረቱ የትግራይ ህዝብ እነርሱ ብቻ አይደለም የወለደው፤ ጦርነት የዋለውም ከእነርሱ ጋር ብቻ አይደለም። የህወሀት ሰማዕታት ብቻ አይደሉም የትግራይ ሰማዕታት፤ የትግራይ ህዝብ በብዙ ጦርነቶች ላይ ውለዋል፤ መተማ ላይ ውለዋል፤ ጉራዕ ላይ ውለዋል፤ ጉንዳጉንዴ ላይ ውለዋል፤ ዶጋሊ ላይ ውለዋል፤ አድዋ ላይ ውለዋል፤ ማጨው ላይ ውለዋል፤ አላጄ ላይ ውለዋል። በእነዚህ ጦርነቶች ሁሉ የተሰዉ ልጆች አሉት፤ ሰማዕታት አሉት። ስለሀገሩ ክብር፣ ስለሃይማኖቱ ብሎ አንገቱን ለጎራዴ የሰጠ ንጉስም ነበረው። የትግራይ ህዝብ ብዙ ብዙ ሰማዕታት ነበሩት! የሀገር አንድነት ያስጠበቁ፤ ባህሩንና የብሱን በብርቱ ክንዳቸው ስር ያኖሩ ጀግኖች ነበሩት። የትግራይ ህዝብ ለጀግኖችም ለሰማዕታትም አዲስ አይደለም!

The post መዓት አውርድ! – አስራት አብርሃም appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>