Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ዕቢያ አፈር ልሶ ተነሳ –ከአበበ ከበደ

$
0
0

ደርግ ወገቡን እየደበደበ ያቆሳሰለው በመጨረሻም በጾረናና ዛላንበሳ ጦር ሜዳ ላይ ራሱን ክፉኛ የተቀጠቀጠው እባብ አፈር ልሶ ተነሳ። እባብ ራሱን ተቀጥቅጦ ሞቶ እንኳን ቢሆን ሊነሳ ይችላልና መፍትሄው የዛፍ ቅርንቻፍ ላይ ወይም ገመድ ላይ ሰቅሎ መተው እንደሆነ ይታወቃል። ይህ እላይ የተሰቀለ እባብ ድንገት ቢነቃ እንኳን መላወስ ስለሚያቅተው እዚያው ሞቶ ደርቆ ይቀራል። እባብን ሞቷል ብሎ ሜዳ ላይ፣ ያውም በረሃ ላይ ጥሎ መሄድ ራስን ማታለል ነው።

isayaሻዕቢያ ለኢትዮጵያ መጎሳቆል ዋነኛው ተጠያቂ ነው። ገና ከጠዋት የኢትዮጵያ ተማሪዎች የትግል እንቅስቃሴን አቅጣጫ በማወላገድና ኋላም ተራማጁን ክፍል እርስ በእርስ በማጋደል ለኤርትራ ግንጠላ ያዋለው ሻዕቢያ ነበር። ደርግ የሚወጥናቸው ዘመቻዎች ሁሉ እርባና ቢስ የሆኑት ሻዕቢያ እውስጥ በሰገሰጋቸው ሰላዮቹ አማካኝነት ነበር። ኦነግን፣ ኦብነግን ወያኔን ጠፍጥፎ የሠራው ሻዕቢያ ነው። ሻዕቢያ በመጨረሻ እንደ አጋንንት ራሱን ገንጥሎ በረሃ ላይ በረሃብ ይቆዝም ጀመር። ወያኔ መንትያውን ሻዕቢያን አበጥሮ ያውቅ ስለነበር የባድመውን ጦርነት የመጀመርያዋን ጥይት ከመተኮሱ በፊት ሰላዩንና ሰላይ ያልሆነውንም ጭምር አብዛኛውን ኤርትራዊ ከኢትዮጵያ ምድር አባረረ። ጾረናና ዛላንበሳ ግንባር ላይ በቀድሞው ሠራዊትና በወያኔ ሠራዊት ቅንጅት ውጊያ ድል የሆነው፣ ራሱን ክፉኛ የተቀጠቀጠውን እባቡን ሻዕቢያን ሞቷል ብለው ጥለውት ሄዱ። ሻዕቢያ በአስራ አምስተኛው ዓመቱ ግንቦት ሰባት-ኢሳትን ልሶ አሮጌ ቆዳውን ለውጦ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት በቴሌቪዥን ቀረበ።
ወገኖቼ እባካችሁ እንደገና አንሳሳት። በዚህች ዓለም ፍቅረ ገመድ ታስረን፣ በፍቅረ ሥልጣንና፣ ፍቅረ ንዋይ ተጠምደን ሃገራችንን መከራዋን አናብዛ። እባካችሁ ማስተዋላችንን ለኢትዮጵያ ሃገራችን ትንሳዔ እናውለው። ብዙ መጻፍ አልፈልግም ነገር ግን ይህን፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካን ያልገባውን፣ ይህን ኢትዮጵያን አዋራጅ፣ ግንቦት ሰባት-ኢሳትን ማስተማር ስላለንብ ነው ይህችን ትንሺቱን ሃሳቤን የምወረውረው። ዛሬ ለአቶ ኢሳያስ ቃለ መጠይቅ አቅርቦ የይስሙላ ይቅርታ በማስጠየቅ ሻዕቢያ ኢትዮጵያን እንደገና እንዲያፈርስ መንገድ የሚያበጃጀውን ግንቦት ሰባት-ኢሳትን በጽኑ ልንወቅሰው ይገባል።

ለኢትዮጵያ ፖለቲካ መፍትሄው ራሱ የኢትዮጵያ ሕዝብና ከጠላቶቿ ጋር የማያብሩት የፖለቲካ ድርጅቶቿ ብቻ ናቸው። ወያኔንና ግብረአበሮቹን ከሥር መንግለው ኢትዮጵያን ነጻ የሚያወጧት ቆራጦቹ ልጆቿ ናቸው። ሻዕቢያ በኢትዮጵያውያን እግሮች ሥር ተደፍቶ ይቅርታ መጠየቅ ሲገባው እንደ ኦነግና ኦብነግ ጠፍጥፎ በሠራው በሮቦቱ ግንቦት ሰባት-ኢሳት አማላጅነት አይደለም ጀግናው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት በቴሌቪዥን የሚቀርበው። “ኢትዮጵያን ከጽንፈኞቹ እስላማዊ እንቅስቃሴ ለመጠበቅ ተቃዋሚዎች ከአቶ ኢሳያስ ጋር መናበብና አካባቢውን ማዳን አለባቸው” የሚለው ማደናገርያ የኢትዮጵያ ሕዝብ “ዶሮን ሲያታልሏት” ብሎ ያልፈዋል። የእስላማዊ ጽንፈኝነትን አጀንዳ የሚያራምደው ማን ሆነና ነው አቶ ኢሳያስ የአፍሪካ ቀንዱ ቀጠና ሰላም አስጠባቂ ተደርገው የሚሞካሹት። “እስላማዊ ጽንፈኝነት መጥቶብሃል አቶ ኢሳያስ ጉያ ሥር ተሸሸግ” እያለ የሚያጃጅለው ግንቦት ሰባት-ኢሳት ራሱ ከሕዝብ ቁጣ የሚሸሸግበትን መላ ቢፈልግ ይሻላል።

የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደገና በማስተኛትና በማሞኘት በኢትዮጵያ ኪሳራ የኤርትራን በረሃ ውሃ ለማጠጣት ብሎም በአቶ ኢሳያስ የተገደለችውን ኤርትራ ዳግም ነፍስ ለመዝራት መሞከር በቅድስት ኢትዮጵያ ላይ ዳግም የሚሰራ ግፍ ነው። ዋሺንግተን ተራራ ላይ ሆኖ መዋጋቱ አልሆን ቢለው ወደፊት ሊከሰት ይችላል ብሎ የሚመኘውን የሥልጣን ክፍተት ለመሙላት ሻዕቢያን ተገን አድርጎ በመጠባበቅ ላይ ያለው ግንቦት ሰባት-ኢሳት እንደ ቋመጠ ይቀራል እንጂ ከእንግዲህ ሥልጣን ከሕዝብ እጅ አይወጣም። ትግሉ እንኳን ቢዘገይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጸሎት እንደነ አጼ ልብነድንግልና አጼ ገላውድዮስን የመሳሰሉ መሪዎችን ያስነሳል።
ወገኖቼ በአቶ ኢሳያስ መሠርያዊ አነጋገር ዳግም መታለል ለአንድነታችን የታገሉትን ኃይላይ መናቅ ነው። ሻዕቢያን እንደገና ማመን ማለት እምነታችንን መካድ ማለት ነው። ሻዕቢያንና አቶ ኢሳያስን ማዳመጥ ቅኝ ገዥዎችን ያርበደበዱትን የአድዋውን ጀግኖች መዘንጋት ማለት ነው። ሌላው ቀርቶ ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንዳትገነጠል ውድ ደማቸውን በኤርትራ በረሃ ላይ ያፈሰሱትን ክቡር አጥንታቸውን በሳህል ምድረ በዳ፣ በናቅፋ ተራሮች፣ በአፋቤት ሜዳዎች ላይ የከሰከሱትን እኚያን ጀግኖች አለማስታወስ እግዚአብሄር የማይወደው የክፋት ሥራ ነውና ዛሬ በግንቦት ሰባት ኢሳት የተቀነባበረውን መሠሪ ሥራ ማውገዝ ይጠበቅብናል።

ፖለቲካ ፌዝ አይደለም። ፖለቲካ ማለት ወያኔን ለማናደድ ሻዕቢያን መጠጋት አይደለም። ፖለቲካ ትላንት አቶ አንዳርጋቸውን ያፈነውን ወያኔን ለማብሸቅ አቶ ኢሳያስን መጨበጥ፣ አስመራ መጓዝ፣ ቃለ ምልልስ ማድረግ፣ ቴምር መመገብ አይደለም። ፖለቲካ በጥበብ የሚደገፍ ትግል ነው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሃገራችንን ሉዓላዊነቷን ለመመለስ፣ ወያኔ ለባዕዳን የቸረውን መሬቶችና የባህር በር ለማስመለስ፣ ወያኔ በዘር የከፋፈለውን ሕዝቧን ለመታደግ የሚደረግ በሳልና ቆራጥ ትግል ነው። ሃገርን መጠበቅ ጀግኖች አባቶቻችን እንዳስተማሩን ስሜትን ተቆጣጥሮ ብልሃትንና ማስተዋልን መጨበጥ ሃቅን መልበስ ማለት ነው እንጂ የሚላስ የሚቀመስ እሌለበት ሃገር በመመላለስ “የራሱን ምቾቱን ትቶ ቤተሰቡን በትኖ በርሃ ተጓዘ”የሚለውን ተራ ወሬ መንዛት፣ ማስነዛት አይደለም። የተባበሩት መንግስትታ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ሆኑ በጎ አድራጊ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸውን ለመስክ ሥራ በረሃ ይልካሉ። ሊታገሉ አይደለም የሚሄዱት። ትግል፣ ለሥልጣን ሳይሆን ለሕዝብ ሲባል ቆራጥ መስዋዕትነት በመክፈል የሚተገበር እንጂ በረሃ መጓዝ ወይም አለመጓዝ አይደለም። በተጋድሏቸውና በድፍረቶቻቸው አርዓያነት ለሕዝብ ነጻነት ፀዳል የሆኑት እነ እስክንድር፣ አንዷዓለም፣ ርዕዮት፣ ኃብታሙ፣ በቀለ ገርባ፣ ዘጠኙ ብሎገሮች፣ ተመስገን፣ ወዘተ የመሳሰሉት የነብር ጣቶች በሠላማዊ መንገድና በአንዲት የብዕር ጠብታ ትግል ምን እንደሚመስል አሳይተዋል።

ይህን ሁሉ ችግር፣ ይህን ሁሉ የኢትዮጵያ አበሳ የፈጠርው ራሱ ወያኔ ነው። ትላንትና እባቡን ሻዕቢያን ራሱን እንደቀጠቀጥነው የሞተ ገላው ዛፍ ላይ ተሰቅሎ ቢቀር ኖሮ ዛሬ ግንቦት ሰባት-ኢሳትን ልሶ አይነሳም ነበር። የእባቡን ሻዕቢያ የተቀጠቀጠ ራስ ሜዳ ላይ ትተነው እንድንሄድ ያደረገን ነገ አፈር ልሶ እንደሚነሳ የሚያውቀው ወንድሙ ወያኔ ነው። ፕሮፌሰር ተስፋጽዮን መድሃኔ “ይኸውና ኤርትራ ሞተች” በሚለው ጥናታዊ ፕሮፖዛላቸው “ወያኔና ሻዕቢያ ተጣብቀው የተወለዱ መንትዬዎች ናቸው” ብለዋል። ግንቦት ሰባት-ኢሳት በሻዕቢያና ወያኔ ማህል ሊገባ አይችልም። መሃላቸው የገባ ከመሰለው ተላላ ነው። ተጣብቀው የተወለዱት ሻዕቢያና ወያኔ አንዱ ከሞተ ያንደኛው ኅልውና ያከትማልና ሁሌም ይጠባበቃሉ። ግንቦት ሰባት-ኢሳት ውስጥ የመሸጋችሁ ተላላ ኢትዮጵያውያን ይህንን ሃቅ ተረድታችሁ ዛሬውኑ “እግሬ አውጭኝ” ብላችሁ ፈርጥጡ።

ኢትዮጵያን በዲሞክራሲ ለማነጽ፣ የወያኔን የተበላሸ የዘር ፖለቲካ ለመገርሰስ አቅሙ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ለኢትዮጵያና ኤርትራ ሕዝብ ዳግም ትስስርም ባለቤቶቹ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ናቸው እንጂ ሻዕቢያ፣ ኦነግ፣ ኦብነግ፣ አልሻባብ አይደሉም። በፕሮፖጋንዳ የሚያግዛቸው ግንቦት ሰባት-ኢሳት በርሃ ላይ ለቆዘመው እባቡ ሻዕቢያ ዳግም እስትንፋስ ሆኗል። ይህ በቀላሉ የሚታይ ስህተት አይደለም። ከዚህ በኋላ ሌላ ሃገርን የሚጎዳ ጥፋት ከመፈጸሙ በፊት ግንቦት ሰባት-ኢሳት ወደ ትክክለኛው የትግል አቅጣጫ እንዲመለስ ምክሬን እለግሳለሁ።

ወያኔና ሻዕቢያ የኢትዮጵያን ትንሳዔ በቅርብ ይመለከታሉ።
አ.ከ. abebekebede321@gmail.com

The post ዕቢያ አፈር ልሶ ተነሳ – ከአበበ ከበደ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>