የጹሑፉ ውበት ጠሩኑ ምቹ፣ መካርነቱ ደግሞ ዬዬኔታ ማዕረግን የሰጠሁትን የጸሐፊ አቶ ይሄይስ አእምሮ ጹሑፍ በጣም የወደድኩት መሆኑና ምስጋናውን ዘለግ አድርጌ አክዬ ወደ እኔው አብረን እላለሁ „ሥነ ጹሑፍ ከማህበረሰቡ ጓሮ ይታፈሳል“ የሥነ ጹሑፍ መምህሬ አቶ አበበ ኬሪ።
ዛሬ ከህይወቴ ተነስቼ ሃቅን በሃቅ እንዝርት ፈትዬ ወርቁን ሸማ በሙያተኛ አዘናክቼ ህይወቴን በጥልቀት ከውስጤ ጋር ስምምነቱን መግለጥ አስኝቶኝ እነሆ ብዕሬ ለሽ ብላ ከተኛችበት ማሳዋ ቀስቀስ አድረጌ ከእኔው ጋር አሰለፍኳት።
- ሰሞናቱ በእስልማና ሃይማኖት መብት መዳጥ ምክንያት በተፈጠረው „የድምፃቻን ይሰማ‘‘ ለግላጋ ተመክሮ ያልተመቻቸው ውርጭ ሃሳቦች – አዬሁ። ባሻጋሪ አይደለም። ቀረብ ብዬ። ውርጩ እኔንም ከውስጤ በመሆኑ ተጋራሁት እናም – አዳመጥኩት። የእኔ ጹሑፍ በዲያቆን ዳንኤል ክብረትና በአቶ ኤርምያስ ለገሰ ዙሪያ አይደለም። መነሻዬ የጸሐፊ ከተማ ዋቅጅራ ጹሁፍ ሲሆን የጸሐፊ መሃመድ ሙፍቲህ ነፃ አስተያየትና ጋዜጠኛ ዳዊት ሰለሞን ባቀረቡት ዙሪያ ላይ ነው። መንፈሱ ግራ ቀኙን መጎብኘት አሰኝቶታል ካላችሁም መልካም ነው። ከማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚወጡ ጹሑፎች ሚዛን ጠበቂ ዘበኛ ያስፈልጋቸዋልና እኔም የሚሰማኝን እንዲህ።
ጹሑፎች በሁለት ጅረቶች በድጋፍና በተቃውሞ አቅጣጫ ነበሩ። በቅድሚያ ጸሐፍት በግልጽነት ሃሳባቸውን ማብራራታቸው ጌጣችን ነው። አስተናጋጁም ዘሃባሻ መልካም ቤት ነው። እንደ መሬት ሁሉንም ማስተናገዱ። የግራ ቀኙን አይቶ ታዳሚ ዳኛው አይዋ ዕውነት ነውና ይፈርዳል። አንተም ተው! አንተም ተው! ደንበርህ እሰከዚህ ነው በይርጋ ይላል …. ነፃነት የሚመቸውንም – የማይመቸውንም ማስተናገድ ከቻለ ሃሳብን የመግለጽ ጉዞ ርትሃዊ ያደርገዋል።
አሁን ከጋሼ አቤ ትምህርት ልነሳ። ከህይወቴና ከገጠመኞቼ። ለእኔ „የድምጻችን ይሰማ“ እንቅስቃሴ የእኔ ነው። ለእኔ „የድምጻችን ይሰማ እንቅስቃሴ“ ገዢው ሃሳብ በኢትዮጵያዊነት ውስጥ እንጅ ከኢትዮጵያዊነት በላይ ባለመሆኑ ጠረኔ ነው። ለእኔ „የድማጻችን ይሰማ“ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መምህሬ ነው። ለአኔ „የድምጻችን ይሰማ እንቅስቃሴ“ የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄ ነው። ለእኔ „የድምጻችን ይሰማ እንቅስቃሴ“ ከእውነተኛ ብሄራዊ ማንነት የተነሳ፤ በኢትዮጵያ ሰንድቅዓላማ ሥር ያለ ውበቴ ነው። አንድም ሳይቀሩ ልቅም ብለው መሬዎቹ በበለኃሳብ እጅ የገቡበት አንድ ሃይማኖታዊ እምነት ሊያደርገው የሚገባ፤ ሊወስደው የሚገባውን እርምጃና መርኽ የተከተለ በመሆኑ እኔም – ታዳሚው ነኝ። እነዛ የተከበሩ የሃይማኖቱ አቨዎ መሪዎቹ እስር ቤት ሊደርስባቸው የሚችለው ሥነ – ሞራልን የጣሰ የበቀል እርምጃ ሲታሰብ ወስጥን – ያቀልጣል። እንደ እራስ፣ እንደ እኔ፣ በእኔ ቢደርስ ብለን እንዬው … ጉዳያችን ነውና፤ አርቅን ሳይሆን ቋያውን አቅርበን እንፈትነው። የቃለ – አዋዲ አፈጻጻም በሰበካ ጉባዔ በአጥቢያ አድባራት መሆኑ ቀርቶ በከተማ ነዋሪዎች ማህበር በቀበሌ ቢሆን የተዋህዶ ልጆች ይመቻቸዋልን፤ ሊቃውንተ ቤተክርስትያናትስ ይደላቸዋልን? አምላካችንስ ቢሆን አይከፋውንም?
ውዶቼ – መግቢያዬ ላይ እንዳስታወስኩት ዛሬ ከራሴ ኑሮ ነው የምነሳው ብያለሁ። ተማሪ እያለሁ የልብ ጓደኞቼ አህመድ ኪሮስና ሞሚና ነበሩ። አህመድ በስኳር በሽታ ሲሞትብን ጥቁር ለወራት ሁለታችንም ለብሰናል። ሶስታችን አንድ ወንበር ስንቀመጥ አህመድ ማህላችን ሲሆን፤ ኪሮስ ከቀጣዩ ወንበር በኋላችን ይቀመጥ ነበር። ሞሚና የሽንኩርት ነጋዴ ስትሆን እነ አህመድ ደግሞ ሱቅ ነበራቸው። ሞሚና እና እኔ ምሳችን ይዘን ት/ቤት ስለምንሄድ ሁልጊዜ ከሥጋ ውጪ ያሉ ምግቦችን ይዘን እንድናመጣ ተስማምተን፤ አንድ ቀን ሞሚና አንድ ቀን እኔ በፈረቃ ምግብ ይዘን እንሄዳለን። አብረንም እንበላለን። ይህ ማለት ከነሞሚና ቤት ለሽሮ ወጥ ሲሰራ ሽንኩርት መክተፊያው ስጋ የተከተፈበት ሊሆን ይችላል – ብረት ድስቱም ሥጋ የተሠራበት፤ ከእኛም ቤት እንዲሁ። ግን የሁለታችን ፍቅር አላወከውም። ትምህርታችን በዚህ መልክ ጨርሰን እኔ ወደ ሌላ የፖለቲካ ዘርፍ ስጠለፍ እሷ በመምህርነት ቀጠለች። እኔ ከአርሲ ከጢቾ እውራጃ ወደ ጎንደር ስዛወር እሷ ዬአንድ ቀበሌ የሴቶች ድርጀት ተመራጭ ሆና አገኘኋት። ልተዋወቃቸው ስሄድ በሩ ላይ ይጠብቁኝ ነበር። ከመኪና ስወርድ እኔ ነኝ። ሄዳ ከወንበሯ ቁጭ ስትል አብረዋት የነበሩት ተደናገጡ። እኔ ግን ጉዴን አውቀዋለሁ „ ከአብሮ አደግህ ጋር አትሰደድ ነው“ ነገሩ „እኔ ሞሚኒት እሷንማ ቁሜ አልቀበልም ነው።“ ነበር ነገርዬው። ሂጄ ከመቀመጫዋ ተሳሳምን። „ጉድሽን ላይ ነበር።“ አለችኝ ቀጥላም „ ደግሞ ላንቺ ነው አብሬ ሸር ጉድ ስል የቆዬሁት“ አለችኝ ያቺ ድንብልብ የፍቅር ኮረሪሚ …. እህቶቼ ገብያ ሲሄዱ ሽንኩርት ሌላ ቦታ አይገዙም ነበር …
ሁለተኛው – ዬዬካቲትት 66 ፖለቲካ ኢንስቲቲዩት „የኢትዮጵያ ታሪክ“ መምህሬ የአዳሉ ጋሼ አብዲ ነበር። በደሜ ውስጥ፤ በሴሌ ውስጥ፤ በነርቤ ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን እንዴት እንደገነባው ቁሜ ልመሰክርበት – ያስችለኛል። ጋሼ አብዲ እምነቱ እስልምና ነው። እንደዛ ፍጹም በሆነ በብሄራዊ የፍቅር ስሜት ስለ እናቱ፣ ስለ ባዕቱ ሲያስተምር የነቁጥ ግድፈት አልነበረበትም። ፍጹም ሰማያዊ ነበር። ልክ ጋዜጠኛ ሳዲቅ „አንቺ እናት ዓለም“ እያለ እንደ ገጠመው የምሽት ማህሌት ነበር … ይህ ሁሉ ጸጋና ክብረት እኔ ቀጥ ብዬ እንድቆም ያደረገ በትምህርት ደረጃ የጋሼ አብዲ ፍሬ ዘለቅ ጥረት ነው። ልመስክረው – ልናገረው … ከአደኩበት ማህበረሰብ ጋር ህትምት ሆኖ እንዲህ ውስጤን የሚገዛው መሠረቱ ባላና ወጋግራው … ወርቁም። አስልማና በኢትዮጵያ የሌላ ተቅጥላ ወይንም አጥፊ ዲቃላ መንፈስ ሊሆን ከቶውንም አይችልም። ካለ ደሙ ካለ ተፈጥሮው። ኢትዮጵያዊው እስልምና እራሱን የቻለ፤ አንገቱን የማያስደፋ፤ ኃላፊነት የሚሰማው፤ በሙሉ ራስ መተማመን ላይ የቆመ የበቀለ – የጸደቀ – የሰበለ ቅዱስ መንፈስና ወጥ ማንነት አለውና። „ለሽብርተኝነትን“ ልመና የሚሄድበት አንድም ቁራጭ ብጣቂ አምክንዮ ሊኖር ፈጽሞ አይችልም። ምን አጥቶ – ከውስጥነቱ?! …. እራሱ እንቅስቃሴው ሲፈጠር በሙሉ ኢትዮጵያዊነት ጨዋነት መንፈስ ነው። እንቅስቃሴው በራስ የመተማመን አምክንዮዊ ጸጋውን ከመፈጠሩ በፊት ከኢትዮጵያዊነቱ የቀዳው ቀድሞ ነው። ሃቅን አንገፍትር ….
ሦስተኛው – አርሲ ጢቾ በነበርኩበት ጊዜ አለቃዬ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊው ጓድ ጃርሶ በልዳ የባሌ ጎባ ልጅ ዬእስልማና ሃይማኖት ተከታታይ ነበር። እጅግ ለስላሳ ፍጹም ሰላማዊ፤ ሰብዕዊም ሰው ነበር። ቤታቸው በተደጋጋሚ ሂጃለሁ። መንፈሱ የቤተሰቡ በሙሉ ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነበር። እንደገናም ኮሚቴው ውስጥ የነበሩ አለቆቼ አብዛኞቹ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች ነበሩ። ከዚህም በተጨማሪ የጢቾ አውራጃ ህዝብ ለሥራ ወደ ገጠር ስዘዋወር እንደዛ ግብግብ – ስፍስፍ፤ ይልልኝ የነበረው፤ ወደ ጎንደር ስዛወር ሌትና ቀን ያለቀሰው አብዛኛው እጁ የእስልምና እምነት ተከታይ ነበር። ፍቅርን በገፍ የሸለምኝ። ፍቅሩን ጸንሶ በፍቅር እንድኖር ያደረገኝ፤ ፍጹም ልዩ ክብረት ነበረው። እኔንም – በህብረ ቀለሙ የገነባኝ – ያነጸኝ።
አራተኛው ሥራ ላይ በነበርኩበት ጊዜ የመንደር ምሥረታ የልምድ ልውውጥ እንዳደርግ ከቡድኑ ጋር መላኬም ብቻ ሳይሆን የቡድኑም ጸሐፊ ነበርኩኝ፤ ሽዋ ያዬናቸው የጉራጌ ብሄረሰብ ናሙና መንደሮች አብዛኞቹ የእስልምና ዕምነት ተከታዬች ነበሩ። ኢትዮጵያዊነት ከነክብሩ – ከነፍቅሩ ፈልቆና ደምቆ ነበር መንፈሴን የመገበው …. ፍጹምም ልዩም ነበር ማተቤም ነበር።
አምስተኛው – ከጫካ ስመለስ ምህረት ጠይቄ ገብቼ ግን ወያኔ አሰረኝ። ስፈታም ጎንደርን እንዳለቅ በቁም እስር በ50000.00 ብር ዋስ ነበር። 50000.00 ብሩን ዋስ ያሳያዙት ሐጂ ሲራጅ ነበሩ። የአባቴ የአባባ የምር ጓደኛ ናቸው። አባባ ኢትዮጵያ አልነበሩም። ለደርግ አልገዛም በማለት ሱዳን ነበሩ። ግን ሐጂ ሲራጅ ማተባቸውን ጠብቀው ዋስ ሆነው አስፈቱኝ። ይህም ብቻ ሳይሆን አንድም ቀን በችግራችን ሳይለዩ እንደ ረዱን፤ ፍቅር እንደ ሰጡን፤ ፈተና ሲደርስም የተለዬ ጸሎት ድዋ በማደረግ እናቴን በማጽናናት እስከመጨረሻው በጨለማ ጊዜያችን ያልተለዩ ውድ የኪዳን አባት – የዝምድና አውራ ነበሩ። አሁን ሳውዲ ናቸው። ዕውነቱ ይህ ነው – የአብሮነታችን – እድምታው። ዬት እያመጣችሁ ጎርፍ በንፁህ መንፈሳችን ላይ እንደምትለቁት ፈጽሞ አይገባኝም። መራራ … ወረራ —
ስድስተኛው ወደ ሲዊዝ ስሰደድ መጀመሪያ ለሁለት ሳምንት፤ ከዛም ለ8 ወር በኋላም ለ8ዓመት በአንድ ካንፕ ግን በተለያዬ ክፍል አብሬ የተመደብኳት የእስልማን እምነት ተከታይ እህቴ ክብሬ ሂሩቴ ነበረች። የመጀመሪያው የ8ወር ቆይታችን ዬጋራ ቤታችን ሰው መቆም አያስችልም ነበር። አልጋው ሲደራረብ ይቻላል። ከልተደራረበ ግን መቆሚያ አልነበረውም። በተደረበ አልጋ መተኛት ባለመቻሌ – ነጣጠልነው። ቦታ አልነበረውም። በአልጋችን ጠርዝ አጠገቡ የበሬ ግንባር የምታክል ታዛ ነበረችን። ከዛች ላይ እኔ ውዳሴ ማርያሜን እሷ ደግሞ ሳላዷን – ትሰግዳለች። 8 ወር ሙሉ የምትሰጠን የሳምንት ስንቅ በጋራ አንድ ላይ ነበረች። 140- ፍራንክ። የግል የሚባል ምንም ነገር አልነበረንም። እሷ ገብያ፤ ልብስ ማጠብ – መተኮስ፤ ማንጠፍ እኔ ደግሞ ምግብ ማብሰል ነበር ተግባራችን። ለ52 ስደተኛ አንድ ክፍል ውስጥ ወደ 12 ምድጃ ነበረን። እኔ የእንሰሳው ኑሮ ስለሚከብደኝ ቢሮ ፈቅዶልኝ አርብ ለቅዳሜ አጥቢያ ሌሊቱን ስሰራ አድራለሁ። ሰርቼ ከሁለታችን ፍሪጅ በቀደም ተከተል አስቀምጣለሁ። ከዛ በኋላ እኔ ወደ ምድር ቤት አልሄድም።
እኔ የሠራሁትን የምታሞቀው እሷ ናት። እኔ ሥሰራው በስመ አብ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ብዬ – ስበላው እንዲሁ። እሷ ስታሞቀው ደግሞ ብስሚላሂ ብላ – ስትበላውም እንዲሁ። በአንድ መሥሪያ ነው የምንበላው። የእመቤቴ ወርሃዊ ዝክር እሷ ናት ዳቦ ገዝታ እምታሰናዳ – በአፆማትም እንዲሁ፤ የእሷ ሮመዳን ፆም ደግሞ እኔ ነኝ ማናቸውንም የማሰናዳው። ዬእሷ ወንድም የሰጠን ቴፕ ነበረን። ሙሉ ቀን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ መዝሙርን ብቻ ነበር የሚያስተናግደው። ለሰከንድ ቅሬታ ኑሮባት አያውቅም። ይልቁንም ብዙውን በቃሏ ትለውም ነበር። እንደ ገባን የተሳሳተ መዳህኒት ተሰጥቶኝ በድንገተኛ ታመምኩኝ። እግባቴን በቲ – ሸርቷ ነበር የተቀበለችው፤ እብስ – እብስ አድርጋ ከነርጥበቱ ነበር ለብሳ አብራኝ ሆስፒታል የሄደችው። ይህን ከእናት በስተቀር ከቶ ማን ያደርገዋል?! መንፈስ ቅዱስን ጠይቁት ወገኖቼ ሚስጢሩን እንዲገልጽላችሁ – የምር። ለዛውም ጸያፉን እግባት እንደዛ ዝልብ እንዳለ — ለበሰቸው። እፁብ ድንቅ ኢትዮጵያዊነት። ለእሷ የወቅቱ ጥያቄ የእኔ በህይወት መቀጠል ብቻ ነበር። እኔ ኮማ ውስጥ ሁኜ ደጋግሜ እናገር የነበረኩት የሂሩቴን ነገር አዳራ እል እንደ ነበር ነገሩኝ ዬልቤ – ከልቤ እሷ ብቻ ከቤተሰቦቼ ልቃ ነበረችና።
ከዚህም በተጨማሪ ጤናዬ አስተማማኝ ስላልነበረ ታች ወርጄ ስልክ ስደውል ከዘገዬሁ በዛ በረዳማ ሃገር ጫማ ሳታደርግ ነበር መጥታ የምታዬኝ። አንድም የካንፕ ሰው እህትአማች አይደሉም የሚል አልነበረም። ለኬዝ ነው የተለያዩት ነበር የሚሉት። የካንፑ አሰተዳዳሪዎች ሳይቀሩ ብዙ ጊዜ ጠይቀውናል። ለእኛ የነበራቸውም ክብር ልክ አልነበረውም። በፈረንጆች ክሪስማስ ለስደተኛ ስጦታ እንድንሰጥ ያደረጉት እኛኑ ነበር። የቢሮ ቁልፍ አምነው ለእኛ ነበር የሚሰጡን። ይህን ያህል ሚስጢር በኢትዮጵያዊነት ይቀዳል። ምንድነው የሌለ፣ ያልተፈጠረ ተቀጥላ ጉም ነገር የምናወራው? ይህን ቋሚ ምስክር እኔን ሊያኝ የመጣ አንድ ታላቅ ሙህርና ካህን፤ የማህበረ ቅዱሳን መሥራችን ከፍተኛ መሪ አካል ወንድሜ በዓይኑ በብሌኑ ኑሯችን ከሥፍራው ተገኝቶ አይቶታል። እሷ የጋገረችውንም ዳቦ ባርኮ ቆርሶልናል። እኔ „እኔን“ ከጠረጠረ በእኔ ውስጥ „እኔ“ የለም ማለት ነው። ይህን ጹሑፍ ስፅፈው እራሱ እንደ ወትሮው ሆኜ አይደለም። ስለምን? ቁስሉ – የእሳቱ ላንቃና ሳንቃ እኩል ሊሰማን አለመቻሉ እያርመጠመጠኝ። ፍቅሮቼ ታዳሚዎቼ እኔ እምጽፈው እራሴን ውስጤን ነው። ለማን ብዬስ – ስለምን ብዬስ እራሴን ሰውሬ አቀርባለሁ?! በግልጽነትና በቀጥተኝነት ስሜቴን ነው የምገልጸው። በወቅቱ እኔን ይቀርቡ የነበሩ የተዋህዶ ልጆችም ለእሷ የነበራቸው ፍቅርና ክብር ልዩ ነበር። እህት – እናት – አስታማሚ – አክባሪ – አዛኝ – የልብ ጓደኛ – ሥራ ወዳድ ያው ኢትዮጵያዊው የጉራጌ ብሄረሰብ መለያ ምልክቱ መዳፍ ነው ሥራ! ሁሉንም – ነበረች። የሁለታችን ባላ፣ ግድግዳና ወጋግራ ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነበር። የአክብሮቷና የፍቅሯ ልክ ዛሬ ላይ ሁኜ ሳስበው ይገርመኛል። ለዛውም እኔን አታወቀኝም ነበር ምን ልሁን ምን?!
ስለዚህ እኔ „እኔን“ የማልጠረጥረውን ያክል፤ እኔ „እኔን“ የማምነውን ያህል ውስጦቼን የኢትዮጵያ የአስልምና እምነት ወንድሞቼንና እህቶቼን ከልጅነት እስከ እውቀት ውስጣቸው አብሮኝ ኖሩ ደስታን የሸለመኝ፤ የረዳኝ፤ ያገዘኝ፤ የተንከባከበኝ፤ በመከራዬ የተገኘ የእኔ ጠረን የሆነ ስለሆነ የዛሬው የወያኔ ሃርነት ትግራይ የመብት ረገጠ በመቃወም የሚያቀርቡት የመብት ትክከለኛ ጥያቄ የእኔም ነው። አብሬ – እስለፋለሁ። ከጎናቸውም – ነኝ። ቁሜ በአደባባይ ስለ ንጽህናቸው ስላላቸው ኢትዮጵያዊነት መንፈስ ስመሰከር ውዬ ባድር አልደክምም – — አላፍርበትምም። ስለ እነሱ ስናገር ስለ ራሴ ነው እምናገረው። ስለዜግነቴ – ስለማንነቴ ነው እምመሰክርው። ኢትዮጵያዊ ነኝ ስል ገድብ የለውም እኔን የፈጠረው ሚስጢር ….. ቅመሙ ጥልቅ እጅግ ጥልቅ ውቅያኖስ ነውና። ሉሲ ድንቅነሽ —- እስኪ ስትችሉ (DNN) መርመር አድርጉና ፈጽሞ ያልጠበቃችሁት ግን ድንቅ የኢትዮጵያዊነትን ግንድነት ውጤትን ታያላችሁ።
ወያኔ ዓለም ዐቀፍ ድጋፉን ለመስቀጠል ትራስ ያደረገው የኢትዮጵያን የእስልምና እምነት ተከታዮችን ካሳ በማቅረብ ነው። ለእርድ ሥጋ በማቅረብ ነው። እራሱ የፈበረከው ችግር እኮ ነው ወያኔ። የከፋፈላቸው – የለያዬቸውም እራሱ ነው። „የሽብር ህግ“ ያለው የወረቀት ነበር ሆኖ ስለቀረበት። „ሽብርተኛው ህጉን ያወጣው ወያኔ ለራሱ ውስጡን ለሚነስተው የሽብር ስውር ተግባሩ ነው“ እኔ ምክንያታዊ በሆነ ጉዳይ የ3 ደቂቃ አጭር ፊልም ሠርቻለሁ። ከፊልሙ ምስል የእስልምና እምነት መሪዎች በሙሉ አሉበት። ወያኔ የሚያላግጥብት ሽፋኑ መጋለጥ ስለነበረበት። በዬትኛውም ሀገር ስደት የሚጠይቁ ኢትዮጵያዊ ሙስሊሞች „የዘመኑ ስጋት“ የማይመለከታቸው ስለመሆኑ ለማጠዬቅ። ፊልሙም ለሚመለከተው አካላት ተልኳል። ሲዊዝም በጋራ ከሌሎች ሀገር ዜጎች ጋር ታይቷል። „ ነብር ጁንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱን አይቀይርምና“ በፍጹም ሁኔታ አምጡ ድገሙ ቢባል የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሥነ ምግባር የሚያክል ሰላማዊ መንፈስ የትም ዓለም የለም። እንቅስቃሴው በወላዊ አቋሙ ቁመናው ሲታይ ከማንኛውም እኩይ ተግባር እና ግድፈትም በፍጹም ሁኔታም የተከለከለ ነው። ከዚህ በላይ ትንግርት የለም፤ ከዚህ በላይ ጨዋነት የለም፤ ከዚህ በላይ ትእግስት የለም። ዓለምን ያስተማረ ተጋድሎ ነው ያደረጉት፤ በጸጥታ – በሰላማዊ ሁኔታ፤ በሥልጡን መንገድ። የሰላም ሐዋርያ ናቸው የኛዎቹ የኢትዮጵያ የእስልምና እምነት ተከታዮች። እኛ መተርጎም – ማንበብ – ማመሳጠር እምንችለው ያዬነው የሰማናውን የኖርንበትን እውነት ነው። እርግጥ ነው ነገ ተነገ ወዲያ በተዋህዶ እምነት አደባባዮች፤ ቅዱስ ሥፍራዎች „አክራሪዎች ጥቃት ሰነዘሩ – አቃጠሉ“ የሚጠበቅ ነው የወያኔ ቅይጡ ድራማ …. ግን እኛ እራሳችን እናውቃለን ስንል ወደ ውስጣችን የማዬት አቅማችን የጫካ ተምክሮ በምንም ቀመር ሊቀማን አይገባም። በፍጹም። ወያኔ ዋልድባን በትዕቢት ሲደፍር አላፈረም – አሸባሪስ እሱ።
ሌላው የተነሳው ዬኩርድሽ ጉዳይ ነው። እኔ አንድ ጥንድ፤ ሁለት ኩርድ የራዲዮ ጋዜጠኛ ጓደኞች አሉኝ። ጥንዶቹ ኢራናውያን ናቸው። ሃይማኖት የላቸውም። ሃይማኖታቸን አውነት ነው ባዬች ናቸው። አሊ የጦር መኮነን ባለቤቱ ኤሊ ደግሞ የዋና መምህር ነበረች። የእያንዳንዱን ሀገር የስደት ፖሊሲ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ሌላው ቀርቶ ሃያላን መንግሥታት ይፋ የማያደርጉትን ስበስባ ሳይቀር። ቋንቋ የምትማረው እሷ ብቻ ናት። እሷ የተማረችውን ቤት መጥታ እሱን ታስተምረዋለች። ፈተና ላይ እኩል ይቀመጣሉ። ሁለቱም ያልፋሉ። የተሰደዱት ብትን አፈር አጥተው ነው። እውቅና ያገኘ ዜግነት የላቸውም። ስለዚህ ኩርድሽን እንዳለ „በእስልማና አሸባሪነት መመደብ“ አግባብ አይመስለኝም። ሃይማኖት የሌላቸውም አሉና። ሌላው ሁለቱም ጋዜጠኛ ኩርድሾች ጓደኞቼ የቱርኪ ኩርድ ናቸው። እስልማና ሃይማኖታቸውን ማዕከላዊ በሆነ መልኩ የተቀበሉ፤ ጫካ ያሉትን ሴት ታጋዩች የሚደግፉ ናቸው። በነገራችን ላይ የጫካውን ትግል ሴቶች፤ የሎቪውን ተግባር ወንዶች ያካሄዳሉ። ቃል ሊገልጻቸው የማይችሉ በርካታ ሴት ጀግኖች አሏቸው። ልብሳቸውም ፋቲክ ነው። የሚታገሉት ለብሄራዊ ማንነት ነው። ስለዚህ እንዲህ ባለ የሃቅ ማህደር ውስጥ በጅምላ መፈረጅም ወንጀል ይመስለኛል። ምክንያቱም ተጋድሏቸውን የሴቶችን ጥንካሬ ስለምወደው ህይወታቸውን ቅርብ ብዬ ጠረኑ አዬዋለሁ። ንፁህ የነፃነት ትግል ነው። ንፁህ የማንነት ጥያቄ ትግል ነው። ለዛውም ሴት አርበኞች የሚመሩት … ስለዚህ የሚሰነዘሩ ወቀሳዎች አድራጊዎችን ነጥሎና በትኖ ማቅረብ ግድ ይላል። ስለ ኩርድሽ ከተፃፈ ንጹሁ የነፃነት ፍላጎት ሆነ ራዕይ ያላቸውንም አብሮ ማዬት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ህሊናችን ሚዛን ከኖረው። ይህን መለዬት ስላልተቻለ ብዙዎቹ አንገታቸውን እንዲደፉ ተገደዋል። መሰረታዊ ዕለታዊ የመኖር መብታቸውን እንኳን ለመጠዬቅ አቅም ሲያንሳቸው ይታያል። በወል ስለተፈረጁ። ይህ ደግሞ ለነገ አዲስ ዓለም ሆነ ለቀጣዩ ትውልድ ጠንቅ ይመስለኛል እኔ በግሌ። የስጋትም ጆንያ … ለምሳሌ በሚሊተሪ አካዳሚክ ሙሩቅ የነበረው የመጀመሪያው ቱርካዊው ፕሬዚዳንት ሙስጦፋ ከማል ዘመናዊቷን ቱርክ የፈጠረ ከቅርቤ ብነሳ ዬሲዊዘርላንድ ሴቶች በፓርላማ እኩል የመሳተፍ መብት ሳይኖራቸው፤ አውሮፓም በብዙ ነገሮች ሥልጡን ሃሳብ የማቅረብ አቅም ሳይኖረው ነበር ቀድሞ የእስልምና እምነት ተከታይ ሴቶችን በድምጽ የመሳተፍን ነፃነት ያወጀው። ሌሎችንም ጉዳዮች እንዲሁ በሚዛናዊነት ያዬው በጣምም ተወዳጅና ሥልጡን የዘማናዊ ቱርክ አባትም እንደሆነ፤ ዘመንን የተከተለ ዕሳቤ የነበረው እንደሆነ፤ የሀገሩ ልጆች የእስልምና ተከታዮች ይናገሩለታል፤ ጥረቱንና ውጤቱን ማንበብ ለምትፈልጉ – ሊንኩ ይሄውና http://www.bbc.co.uk/history/historic_figures/ataturk_kemal.shtml
http://www.biography.com/people/mustafa-kemal-ataturk-20968109#military-career
http://simple.wikipedia.org/wiki/Mustafa_Kemal_Atat%C3%BCrk እንዲህ ዓይነት ዶክተሪን የሚከተሉም ዬዕምነቱ ተከታዮች በብዛት አሉ።
በተጨማሪነት – በአንድ የሰብዕዊ መብት አስከባሪ ማህበር ልምምድ አደርግ ነበር። ተግባሬ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ነበር። ማህበሩ ወይንም ድርጅቶች ወደ 3000 የሚጠጉ የፌስ ቡክ አባላት በመላ ዓለም አሉት። በመላ ዐለም የሚገኙ ከ50% በላይ ጾታ ሳይለይ የእስልምና እምነት ተከታዮች ተሳታፊዎች ናቸው። ሁለት ነገር ደነቀኝ። አንዱ ዘመኑ የፈጠረላቸውን ሥልጣኔ የመጠቀም አቅማቸው ሙሉዕነት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የሰብዕዊ መብት መረገጥ ያገባናል፣ ይመለከተናል ብለው ንቁና ብቁ ተሳትፎ ማደረጋቸው፤ ይህ እንግዲህ በግሌ ደመና የለበሰውን የዓለምን የተስፋ ጉዞ ብርሃናማ ያደርገዋል የሚል ጉልበታም ተሰፋ በግሌ አሳድሮብኛል።
በሌላ በኩል እንደ ወንጀል የታዬም ተያያዥ ሃሳብ አንብቤያለሁ። አምስቱ አብዬተ ቤተክርስትያን ጋር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ስምምነት አላት። እኔ ከዚህ ሲዊዝ ቀደም ባለው ጊዜ አዲሱን ዓመት ቅዱስ ዮኋንስን እናከብር የነበረው ከእነሱ ጋር በአንድ ላይ ነበር። በተመሳሳይ ቀን፣ በተመሳሳይ ዶግማና ቅኖና ስለሆነ። እና እስልምና እምነት ካለው ጋር መቀራረቡ – መጋባቱ – መወዳጀቱ ምን ክፋት አለው? አፍጋን አግብተው በፍቅርና በሰላም ልጆች ወልደው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ሙስሊሞች እንዳሉም ሃሳቡን ላቀረቡት ጸሐፍት ወንድሜ ላስታውስ እሻለሁ – በአክብሮት። በተጨማሪ …. እኔ እራሴ የአርመን ጓደኛ አለችኝ። ስትሄድ – ስትሄድ ወደ ሃገሯ ሜሮን – አድህኖ ስዕላትን ታመጣልኛለች …. በእምነት አንጻር ከሌላው የተዋህዶ ኦርቶዶክስ ኢትዮጵያዊ ወንድማና እህቴ ጋር እኩሌ ናት። ሰው መሆን ብቻ እኮ ነው ተፈጥሮ የሚጠይቀን። እንዴት ያለ ነገር ነው …. ዓይናችን ወደ ፍቅርና ወደ ማስተዋል ብናመራው ምን አለበት …. ? ? !!
እርግጥ ከዚህ ማዕቀፍ የሚያፈንግጡ የሉም ማለት አንችልም። የእናት ሆድ ጅንጉርጉር ነውና። ግን ሁልጊዜም እውነት ያለበት መንገድ አሸናፊ ነው። ወደ እኛ ይመጣሉ። ደግሞ በአንድ እንቅስቃሴ ወይንም ፓርቲ ውስጥ መታዬት ያለበት የድርጅቱ ሁለንታና ወላዊ መንፈስ እንጂ ነጠላዊ ግለሰባዊ መሆን አይገባውም። እንደ እንቅስቃሴ „ድምጻችን ይሰማ“ እሳከሁን በሳለፈው የተጋድሎ ታሪክ ከግድፈት ነፃ ነው። የ40 ዓመቱ የወያኔ ህልም እንዴት ውሃ በልቶት እንደ ቀረ አያችሁት አይደል። ሁለቱም ሃይማኖቶች በወያኔ ሃርነት ትግራይ የደረሰባቸው ጥቃት የአውሮፓው ኮሚሽን የውሳኔ ንድፍ ሙሉ ዕውቅና ነው የሰጣቸው። የኖርንበት፤ ያደግንበት፤ ያለንበት ሃቅ የእኛ ከእኛ ለእኛ የሆነ ነው። ምንም ዓይነት ሰው ሰራሽ ክትር ውስጣችን ከውስጣችን ነጥሎ ጎርባጣ የማድረግ አቅም የለውም። ኢትዮጵያዊነት ጠበቂ አምላክ አለው። አንድ ኩታ — ፈትሉ ተነጥሎ ወይንም ዘሃው ተነጥሎ ኩታ ሊሆን ከቶውንም አይችልም።
ሌላው ስለታሪክ የተጻፈም አይቻለሁ። ታሪክን ለማጣቀሸነት ማንሳት ከተፈለገ በሌላኛው ሃይማኖት ላይም የጠፋውና የወደመው ጉዳይ እኩል መነሳት አለበት። ዓፄዎቹም ከተነሱ እንዲሁ። ታሪክ በአንድ የወቅት ማዕቀፍ ውስጥ መልካምም፣ መልካም ያልሆኑ አዎንታዊና አሉታዊ የህዝብ የተግባር ተሳትፎ ዕድሜ ጠገብ ሲሆን ነውና ታሪክ የሚባለው። ጥቃቱ የዘለለው ሃይማኖት አልነበርም። እኩል መግለጽ ካልተቻለ ሚዛኑ ወልጋዳ ያደርገዋል። በዚህ ዙሪያ መቆፈር ስለማልፈልግ ብቻም ሳይሆን ጠቃሚም ስላልሆነ ወደ ዛ መሄድ አልሻም። ለእኛ ትውልድ የተሰጠው ፈተና አባቶቻችን ተወልደው፤ ተጋብተው፤ ተጎራብተው፤ ጡት ተጣብተው – ተደማምጠው በአንድነት በመከባበር ያቆዮዋቸው ሃይማኖቶች በነበራቸው ትውፊታዊ – ስምረታዊ ጉዞ እንዲቀጥሉ የማደረግ የአደራ ዕዳ አለብን። ለዚህም „የድማጻችን ይሰማ“ ሰላማዊ – ብልህ እንቅስቃሴ አደራ በይ እንደማይሆን ከነሙሉ መንፈሴ ሆኜ መናገር እችላለሁ። እንዲያውም ለእኔ ለዘመነ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ክትምት የበኩሉን ድርሻ የተወጣ፤ ለሰማያዊ ፓርቲ ውጤታም እንቅስቃሴ አቅጣጫ የነደፈ – ፋና፤ ለነፃነት ትግሉ በታማኝነት አቅምን የገነባ፤ አቅምን በአግባቡ ያሰተዳደረ የዘመናችን አብነታዊ የተጋድሎ ታሪካችን ነው። የናሙናነት ሂደቱን አስተምህሮቱን ብንከተል እናተርፋለን። አግዞናልና።
የወያኔ ደጋፊዎች የሚሉትን እኛም የምንደግመው – የምንሰልሰው ከሆነ በባርነት እዬተዘለዘሉ ተደፍሮ ለመኖር ከመፍቀድ ውጪ ሌላ ሊባል ከቶውንም አይችልም። „የድምጻችን ይሰማ“ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያዊነት ከላይ ያደረገ አንቱ የትግል አዝመራ ነው – ለእኔ ለሥርጉተ። በአጋጣሚ በዚህ ጉዳይ እዬፃፍኩኝ ስለሆነ – አከብራቸዋለሁ – እውዳችዋለሁም መሪዎቹንም ሆነ ታዳሚዎችንም። እኔ ያደግኩት የሠርጉ ድንኳን እኩል ተሠርቶ አንዳንድ ጊዜም በአንድ ግድግዳ ሁለት ዳስ ግብዣ ሲደረግ ሲሆን ጭፈራው ላይ ደግሞ በጋራ ከትሞ ደስታን ሲኮመኩሙ ነው። ያልተፈጠረ፣ ፈጽሞ የእኛ ያልሆነ ቁጭላ ሃሳብና ቁሮ ጠንቅ እያመጣችሁ ትውልዱን አትበጥብጡት – እባካችሁን።
ሌላው ግርም ያለኝ ጉዳይ ደግሞ „የISIS ቡድን ነፍሰ ገዳዩ ጆን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የቅርብ ጓደኛ አዲስ አበባ ውስጥ ታስሯል መባሉ እያነጋገረ ነው“ የሚለው ነው። እራሱ ኢትዮጵያዊ ቢሆንስ እንኳንስ ጓደኝነት?! ኔት ይፈለጋል – ለውንጀላ። እኔ ለጓደኞቼ ወይንም ጓደኞቼ ለእኔ በሁሉም ነገር ምቾት አይኖረንም። በሚያመሳስለን ጉዳይ ብቻ እንጂ። በጥልቀትም ሲታይ አሁን እናት ቅድስት ትሬዛ በምግባራቸው እንጂ በሀገራቸው አይታወቁም። ኪንግ ማርቲ ሉተርም እንዲሁ። አንድ ያልተመቼ ነገር ሲፈጠር እህ „ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ አማራ፣ እስላም፣ ተዋህዶ፣ አልፎ ተርፎ የትዳር አጋሩ የብሄረሰብ የመንደር ነገር ተነቅሶ ይነሳል“ ዎህ! ልበል። ያደክማል። ለፍቅር ደግሞ ደንበር ተሰራለት። ፈጽሞ የማይገናኙ ነገሮችን በማያያዝ መንፈስን – ማወክ። ለነገሩ አሁን ደግሞ „አይሁዳውያንንም“ በሚመለከትም ያዬሁት ጹሑፍ አለ። ጸሐፌ አቶ ዮፍታሄ ጠላት አናብዛ በማለት ሰፊና ጥልቅ እስከ ክፍል 7 ድረስ የዘለቀ ትንተና … በሌላ በኩል ደግሞ ጠላትነትን ማምረት? የወያኔ መንደርተኝነትን ትርትር አልበቃ ብሎ የኛ መንፈሰም ለዚህ ተጠቂ ሆኖ ቁልቁል። በምን ቋንቋ ልንግባባ እንደምንችል እኔ በግሌ አላውቀውም፤ የባቢሎን ዘመን ዙራአንባ ሁነናል ከቶ ልበልን? አዝናለሁ … በርካታ አይሁድ እምነት ተከታዮች ሆኑ፣ የዘር ሐረግ ያላቸውም በነፃነት ትግሉ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ እራሳቸውን ለመሰዋትም የተዘጋጁ አሉን። ኢትዮጵያዊነት አኮ ዝንቅ ቅይጥ ግን ቀለማም ውብ ማንነት ነው። ከወጡ ይልቅ ቅልቅሉ ይበልጣል። ድምቀታችንም ይሄው ነው። ማማራችንም! ለማንኛውም እንዲህ ያለው ትንተና ሲመጣ ምን እንደሚሰማቸው እነሱ አላውቅም … ለእኔ ግን ጎርባጣ ነው። ያለብን ችግር አልበቃ ብሎ አዳዲስ ነገር እዬፈጠርን ያን የተዛባ ዕይታ ለማረቅ አቅምን መሻማት። ራዕያችን ማራቅ አቅማችን ማባከን … እንጃ …. ያደክማል።
ምርቃት አስተያዬት „ለድምፃችን ይሰማ“
- በተፃራሪ ወገን የሚቀርቡ ሃሳባዎችን ሳያባክኑ ክፍተቶችን መድፈን፤ ድክመት ፈላጊውና ፈብራኪው ወያኔ ተግቶ ይሠራበታልና። ስለዚህ እሱንም መቅደም ብልህነት ይመስለኛል።
- ፈንገጥ ብለው የሚወጡ ዝንባሌዎችን ማረቅና – ማሳተካከል። ይህን ሃሳብ ያነሳሁት በፋመ ወቅት ፓል ገብቼ የገጠመኝ ስላለ ነው። „አሜን“ በሚል ሥም ነበር የገባሁት። የኢትዮጵያ ታሪክ ሲነሳ የማድመጥ አቅም የሚነሳቸው የነፃነት ትግሉ ደጋፊዎችን አይቻለሁ። ምክንያቱም ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር በተያያዥነት የሚቀርበው የተዋህዶ እንደሚሆኑ ስለሚያውቁ ጊዜውን ሲቆርጡ ተመልክቻለሁ። ይህን እኮ አውሮፓ ላይ አንቱ ከተባለ ቤተመጸሐፍት ብትሄዱ ይገኛል። ስለምን? አውሮፓን የፈጠረ ሚስጢር ነውና። ሃብትነቱ ግን የጋራ ነው። ኢትዮጵያዊነት የዚህ ድምር ነው። ነጠላዊ ኢትዮጵያዊነት የለም። ፓል ላይ ሰው እዬተናገረ ሰዓት አይወሰንበትም። ከመናገሩ በፊት እንጂ። መመጠን እንዲችል ። ይህን ሳይ እኔ ንግግር ላይ ያለው ይጨርስና በቀጧዩ ተናጋሪ ላይ ብተውስኑ ጥሩ ነው ስላልኩ፤ ባውንስ ተደረኩኙ። ሥሜም የሰጠ ነው „አሜን“ ሆን ብዬ ነበር ይህን ሥም ይዤ የገባሁትም፤ ግራ ቀኙን ማዬት አሰኝቶኝ። እኔ ስለ እስልምና ሃይማኖት ትምህርት በመደበኛ ቀን ይሰጥ ነበር። ቁጭ ብዬ አዳምጣለሁ። ማወቅ ምን ይጎዳኛል። ወደ ዋናው ነጥቤ ስመለስ የቀደመው ኢትዮጵያዊነት ታሪክ ሃብትነቱ የእኔም ነው የማለት መጠነ ሰፊ መንፈስ ኮትኩቶ ማሳደግ ይገባል። ጭንቅላት አንድ ነው። ጭንቅላት ውስጥ ከሰው ምርምር በላይ የሆኑ ውስብስብ ተግባሮችን የሚከውኑ ዬተፈጥሮ ጸጋዎች አሉት ግን አንድ ጭንቅላት ነው። ኢትዮጵዊነት ማለት ጭንቅላት ነው። ብብዙ ሊከሰቱ ሊታዮ በማይችሉ መስተጋብራዊ ጥምረቶች የተዋኻደ። ሰው ሰራሽም አይደለም – ኢትዮጵያዊነት።
ማሰርጊያ ሃሳብን መግለጽ፤ ስጋትን መግለጽ መልካም ቢሆንም አሁን ላለው የዘረኛ አገዛዝ በህይወታቸው ግፍና በደል ለሚሰራባቸው የእስልምና ሃይማኖት አቨው እስረኞቻችን ሆነ ለወላዊ የነፃነት ተጋድሎ የጋራ ትግል አካሄዱ በሉት ጥናታዊ ትንታኔው ኪሳራ እንጂ ትርፍ አይኖረውም። ዘመን – ጊዜ – ሰዓት – ደቂቃ መደመጥ አለባቸው። ወገናዊነቱ ደግሞ ለሚበልጠው ብሄራዊ ማንነት መደፈርና በባርናት ላለመኖር አሻም! በቃን! ለማለት በሚስችሉ ሁነቶች ላይ ማተኮር አለባቸው። እስልምና ሲደፈር እኮ ኢትዮጵያዊነትም ተደፍሯል ቀመሩ ይሄ ነው – አሁንም ለእኔ። እንዴት ተደርጎ በደም ውስጥ ያለውን ውሃ ከደሙ መለዬት ይቻላል? ይቻላልን? —-
እኔ እኔን ሳምነው ኢትዮጵያዊነት እኔን ያምነኛል። ኢትዮጵያዊነት በእኔ ላይ እምነቱ ሲጥልብኝ ደግሞ የምለውን ሆኜ ለመገኘት እንቅፋቱን ሁሉ አሸንፋለሁ። ማሸነፌ ብቻውን በቂ ስለማይሆን በውስጡ – እሰክናለሁ። „ድምፃችን ይሰማም“ እርገቱ ከማህተሙ ከኢትዮጵያዊነት ሥጋና ደም ላይ ነው። የእውነት መጀመሪያውም መጨረሻውም እውነት ነው። የዘመኑ ወጣቶች ካዩት ተጨባጭ ሁኔታ ተነስተው „ለድምጻችን ይሰማ“ ያላቸውን አድናቆትን ክብር በገፍ እንዲሰጡ በትህትና አሳስባለሁ። ዛሬ ያሉት አዲስ ትውልዶች ከእኛ የተሻለ ብልህነት አብዝቼ አይባቸዋለሁና። ለባርነት አልተገዛነም ሲባል እኮ በዬትኛውም የጦርነት አውድ ሁሉ ኢትዮጵያውያን ተሳትፈዋል ማለት ነው። ይህ ማለት ዬእስልምና ሃይማኖት ልጆች የታሪኩ ባለ ሙሉ ድርሻ ናቸው ማለት ነው። አካላችን – ትንፋሻችን – ጠረናችን – ወዛችን ጸዳላችን – ውበታችን – ጌጣችን ናቸው። ቀለማሙ ማንነታችን ዬድምቀት ሚስጢሩ ይህ ነው። ያደላቸው ሀገሮች ለቀደምት ታሪካቸው ጥንግ ድርብ ማልበስ ብቻ ሳይሆን የእነሱነታቸው መሠረት ስለመሆኑ ተገንዝበው በጣም እርቀው የምርምር ተግባራት ይከውኑበታል። የሚሰጡትም ክብር ከምንገምተው በላይ የሃይል ማመንጫ ማዕከል ነው። ይኼው እምነታቸው በመሆን ስለሆነ ርጥቦቹ ለእኛም በቅተው – አትርፈውናል። እምነቱንም ማንነቱንም ሆነው ስለሚገኙበት። ከረድኤቱም ትውልዱን ያስመርቁበታል። የእኛ ደግሞ – ማክሰል። በመጨረሻ የራዲዮ ድርጅታችን ሰፊ የሆኑ የቴክኒክ ችግሮች ለመፍታት እደሳት ላይ ስለሆነ፤ ለመሥራትም ሰፊ የሆኑ የተክኒክ ዝንቅ ችግሮች ስላሉበት፤ አንዳንድ ጊዜ ለችግርም እረፍት መስጠት ስለሚያስፈልግ ነባሮቹ ብቻ ነው የሚደገሙት እስከ ሚያዚያ መጨረሻ። ስለዚህ ይቅርታችሁን እጠይቃለሁ። በተረፈ የኔዎቹ – ቸር እንሰንብት።
ለእኔስ ሰው መሆኔ ብቻ ይበቃኛል።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
The post እኔ „እኔን“ ከጠረጠረ – በእኔ ውስጥ „እኔ“ የለም ማለት ነው – ከሥርጉተ ሥላሴ appeared first on Zehabesha Amharic.