ግርማ ሞገስ (girmamoges1@gmail.com)
ሰኞ ነሐሴ 20 ቀን 2005 ዓ.ም. (August 26, 2013)
“አንድነት ፓርቲ ሳይገድል እየሞተ ህገ-መንግስቱን የማስከበር ሰላማዊ ትግሉን አጠንክሮ ዛሬም ወደፊትም ይቀጥላል፡፡” የሚለውን መርሃቸውን አንድነቶች ካስተዋወቁን ከርመዋል። ባለፈው ሳምንት በባሌ ሮቤ እና በፍቼ ኦሮምያ የተተከሉት መረን የለቀቁ አምባገነን አስተዳደሮች እና ደህንነቶች የፈጸሙባቸውን ወደር የለሽ የአንደበት፣ የሳይኮሎጂ እና የአካል ጥቃት በፈገግታ በመቀበል እየሞቱ ሳይገድሉ በሰላማዊ ትግል ህገ-መንግስቱን ለማስከበር ያላቸውን ጽናት ደግመው አሳይተውናል አንድነቶች። አንድነቶች የሚሰብኩትን የሚፈጽሙ መሆናቸውን ኢትዮጵያ እንደገና ባለፈው ሳምንት ተመልክታለች። የባሌ ሮቤ እና የፍቼ አምባገነን አስተዳዳሪዎች እና ደህንነቶች አረመኔነት አሳፋሪ ነበር። በፍጹም የስልጣኔ አየር የነፈሰባቸው አይመስሉም። ዘመናዊ አስተሳሰብ ለአንድ ቀንም የጎበኛቸው አይመስሉም። ይባስ ብሎ የባሌ ሮቢ እና የፍቼ አስተዳዳሪዎች እና ደህንነቶች ከህጋዊ የመንግስት መዋቅር ውጪ ጸረ-ነፃነት ወረበሎች (ቦዘኔዎች) ያደራጁ ይመስላሉ። ይኽ ጉዳይ ጥናት ሊደረገበት ይገባል።
በባሌ ሮቢ ኦሮሚያ ያየነው አፈና እስከአሁን በሰሜን ኢትዮጵያ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ካስተዋልናቸው አፈናዎች ሁሉ ዘግናኝ ነበር። የመቀሌው አፈና የተፈጸመው የድምጽ ማጉያ በመከልከል፣ የመቀስቀሻ በራሪ ወረቀቶችን በመንጠቅ፣ እና አንድነቶችን በማሰር እንደነበር እናስታውሳለን። የባሌ ሮቤ አምባገነኖች ግን ህውሃት በመቀሌ የፈጸመውን በሙሉ ቢፈጽሙም የአንድነቶችን በታጋሽነት እና በጽናት የታነጸ ሰላማዊ ትግል ሊያቆሙት አለመቻላቸውን ሲገነዘቡ ተራ ማስፈራራት ጀመሩ። ሐሙስ ነሃሴ 16 ቀን 2005 ዓ.ም. የአንድነት ፓርቲ ተወካዮች ከባሌ ሮቤ ከተማ ከንቲባ፣ ምክትል ከንቲባ፣ የፀጥታ ዘርፍ ሃላፊ እና ከከተማው ካቢኔዎች ጋር 3 ሰዓት የፈጀ ውይይት አደረጉ። በዚኽ ውይይት ላይ ነበር የባሌ ሮቢ ባለስልጣኖች “አንድነት ሰላማዊ ሰልፉን ማድረግ አይችልም፤ እኛ ከፍተኛ የሆነ የፀጥታ ስጋት አለብን፡፡ የቀድሞው ጠ/ሚር አቶ መለስ በፓርላማ እንደተናገሩት በአካባቢያችን የአልቃይዳ ክንፍ አለ” የሚል ማስፈራሪያ አዘል በማሰማት ለሰላማዊ ሰልፉ ትብብር መንፈጋቸውን የገለጹት። እሁድ በተቃረበ ቁጥር የባሌ ሮቤ አምባገነኖች ማስፈራሪያ እና ዛቻ ግለቱ እየጨመረ ቢሄድም አንድነቶችን ሊያስቆም አልቻለም። በዚኽን ጊዜ “እሁድ የገበያ ቀን ስለሆነ ሰልፍ ማድረግ አይቻልም። ሰላማዊ ሰልፍ ከተደረገ ደም ይፈሳል።” ማለት ጀመሩ የባሌ ሮቢ ባለስልጣኖች።
የአንድነቶችን ጽናት፣ ትዕግስት፣ ሰላማዊነት እና ቁርጠኛነት መስበር እና ሰልፉን ማሰናከል አለመቻላቸውን ሲገነዘቡ የባሌ ሮቤ ባለስልጣናት ቅዳሜ ምሽት ለእሁድ አጥቢያ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች እና አባላትን ካረፉበት ሆቴል በግዳጅ አስወጥተው አገቱ። በዚኽን ጊዜ ነበር የቀሩት አንድነቶች ሰላማዊ ሰልፉ እንዳይደረግ የወሰኑት። የመጣው ይምጣ ብሎ ሰልፍ በመውጣት በመሃይም አምባገነኖች የሰለጠነ የሰላም ትግል ሰራዊት ማስመታት ስህተት ነው። ሰላማዊ ሰልፉ እንዲቀር መደረጉ ትክክለኛ ውሳኔ ነው። በድስፕሊን የታነጹ ሰላማዊ ትግል መሪዎች ገና ዘመቻውን ሲጀምሩ መቼ ማቆም እንዳለባቸውም ጭምረው ያውቃሉ። ይኽ ብስለት ያላቸው ጀግኖች የሚያደርጉት ማፈግፈግ ነው። በዚኽ አይነት ነበር እሁድ ቀን ነሐሴ 19 ቀን 2005 ዓ.ም. በባሌ ሮቤ የታቀደውን የሚሊዮኖችን ድምጽ ለነፃነት ዘመቻ የታፈነው። በዚኽ አይነት ነበር በባሌ ሮቤ አካባቢ አለ ሲሉን የነበረው ሽብርተኛ የአልቃይዳ ቅርንጫፍ እራሳቸው የባሌ ሮቤ ባለስልጣኖች መሆናቸውን ያረጋገጡልን። ይኽ ሁሉ ሲፈጸም የባሌ ሮቤ ወጣቶች ከአንድነት ፓርቲ ጎን መቆማቸውን ኢትዮጵያችን ልታውቅ ይገባል።
ፍቼ ሌላዋ ከተማ ናት። የመጀመሪያው ሁለት አባላትን ይዞ ፍቼ የገባው የሰላማዊ ሰልፍ ቅስቀሳ ቡድን በፍቼ አስተዳደር እና ደህንነት ካድሬዎች ከፍተኛ ድብደባ ተፈጸመበት። የእጅም የእግርም ጉዳቶች ደርሰባቸው ሁለቱ የዴሞክራሲ ሰራዊቶች። አንድነቶች በደረሰው ጥቃት አልተፈቱም። እንዲያውም ጊዜ ሳያባክኑ አዲስ ቡድን ወደ ፍቼ በመላክ ለነሐሴ 19 ቀን ያቀዱትን የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት ዘመቻ ለማሳካት ጎንበስ ቀና ማለት ጀመሩ። በዚኽ እርምጃቸው አንድነቶች በማይነቃነቅ ድስፕሊን የታነጹት የሰላማዊ ትግል ሐዋርያት መሆናቸውን ለፍቼ ህዝብ አሳዩ። እየሞቱ ሳይገሉ ህገ መንግስታዊ መብት ለማስከበር ያላቸውን ቁርጠኛነት አንድነቶች አስመሰከሩ። አንድነቶች የሚሉትን የሚፈጽሙ የሰብዓዊ መብቶች አስከባሪ ወታደሮች መሆናቸውን ፍቼዎች በአድናቆት አስተዋሉ። ይኽን ያስተዋሉት የፍቼ ወጣቶች ለአንድነቶች ትብብር መለገስ ጀመሩ። የፍቼ አስተዳደር እና ደህንነቶች ያሰማሩዋቸው ቦዘኔዎች በፍቼ ከተማ የሚገኘውን የአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት ለመስበር ሲሞክሩ የፍቼ ወጣቶች ድርጊቱን በመቃወም ከአንድነቶች ጎን ተሰለፉ። በፍቼ የተደረገው ሰላማዊ ሰልፍም ቢሆን በአንድነቶች እና በፍቼ ወጣቶች ሰላማዊነት እና ጽናት የተገኘ እንደነበር ኢትዮጵያ በአድናቆት አስተውላለች።
ሶስተኛው የእሁድ ነሃሴ 19 ቀን 2005 የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት ዘመቻ እቅድ በአዳማ/ናዝሬት ከተማ ማድረግ እንደነበር ይታወቃል። ይሁን እንጂ የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከአንድነት ፓርቲ ለተጻፈለት ደብዳቤ ነሃሴ 19 በከተማው ስብሰባ መኖሩ እና የኃይል እጥረትም እንዳለበት ጠቅሶ ሰላማዊ ሰልፉን አንድነት ፓርቲ ወደ ጷጉሜ 3 ቀን 2005 ዓ.ም እንዲያዛውር ጠይቋል። አንድነት ፓርቲም የቀረበለትን ጥያቄ መቀበሉን ገልጿል። የአዳማ/ናዝሬት ከተማ አስተዳደር ህገ መንግስታዊ እውቅና ካለው አንድነት ፓርቲ ጋር በዚኽ አይነት ስልጡን እና ተራማጅ መንገድ ከስስምምነት መድረሱ ከባሌ ሮቤ እና ከፍቼ ከተማዎች አምባገነን አስተዳዳሪዎች ፍጹም የተለየ አድርጎታል። ከሁለቱ ከተሞች አስተዳደሮች የአዳማ ከተማ አስተዳደር የተሻለ መሆኑን ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሁን አልመ አስተውሏል። በዚኽ እርምጃው የአዳማ/ናዝሬት አስተዳደር ሊመሰገን ይገባዋል። ሊኮራም ይገባዋል። ኋላቀሮቹ የባሌ ሮቤ እና የፍቼ አምባገነን አስተዳደሮች ሊያፍሩ ይገባል። የሚያስተዳድሩትን ህዝባቸውን በንቀት አፍነውታል። እነዚህን ሁለት ከተሞች ለጉብኝትም ሆነ ለንግድ የሚጓጉ ከተሞች እንዳይሆኑ አድርገዋል እነዚህ አስተዳዳሪዎች። የሚያስተዳድሩትን ህዝብ እና የቀረውን አለም ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል። በእነዚህ እና በመሳሰሉት ከተሞች ላይ ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሚፈሰው ገንዘብ ከምንጩ ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል። ከምንጩ ስል ለጋሽ አገሮችን ይጨምራል። ተዳባዳቢነት ዴሞክራሲያዊነት አይደለም! መሃይምነት ነው።
ለአንባቢያን፥
“እየሞትን ሳንገድል ህገ-መንግስት የማስከበር ሰላማዊ ትግላችንን እንቀጥላለን” የሚለው የአንድነቶች መርህ ከምራቸው እንደሆነ ባልፈው ሳምንትም አስተውለናል። ፍጹም ሰላማዊነታቸው እና የመርህ ጽናታቸው በሚፈጸምባቸው የአካል ድብደባ እንደማይነቃነቅ ፍቼ ላይ አይተናል። በዚኽ ባለፈው የፈተና ሳምንት አንድነቶች መኪና በመከራየት፣ ወረቀቶች በማሳተም፣ ለህክምና ወጪ ባማድረግ እና ለተለያዩ ጉዳዮች ብዙ ወጪዎች እንዳደረጉ መገንዘብ አያዳግትም። ትግሉ የጋራ በመሆኑ ቋሚ ተመልካች መሆን ያዳግታል። የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል ለምንል በሙሉ የዳር ተመልካች መሆን ያዳግተናል። በባሌ ሮቤ እና በፍቼ በአንድነቶች ላይ የደረሰውን አይተን እና ሰምተን እጃችንን አጥፈን መቀመጥ ህሊናችንን ያዳግተዋል። የዜግነት ሚና መጫውት ያልጀመርን መጀመር፣ የጀመርን ደግሞ መቀጠል አለበን። ተሳትፎዋችንን ማሳደግ አለብን። አንድነቶች አንድም ክፉ ቃል ሳይሰነዝሩ እና ፈገግታ ከፊታቸው ሳይለያቸው ይኽን ሁሉ ስቃይ የሚቀበሉት ለግላቸው ብር ለማካበት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። እየሞቱ ሳይገድሉ በአምባገነነኑ መለስ የረቀቀውን ፀረ-ሽብር ህግን ለማሰረዝ እና የኢትዮጵያችንን የፖለቲካ ትግል ባህል ለመቀየር እንደሆነ ልቦናችን ያውቀዋል። ስለዚህም አንድነቶች የጀመሩትን የሚሊዮኖች ድምጽ ለነፃነት ዘመቻ በመቀላቀል ታሪክ እንስራ። የሚከተሉትን በማድረግም አንድነቶች መሰራት የጀመሩትን ታሪክ መቀላቀል እንችላለን።
እርዳታ፥ በገንዘብ!
እርዳታ፥ በአሳብ!
እርዳታ፥ መረጃዎች በፍጥነት በማሰራጨት!
እርዳታ፥ ፊርማዎች በማሰባሰብ!
እርዳታ፥ እንደገና በገንዘብ!
ፊርማ ለማስቀመጥም ሆነ ገንዘብ ለመላክ ይኽን የአንድነቶች ድረ ገጽ ይጎብኙ፥ www.andinet.org