Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ሰብዕዊ መብት ተቆርቋሪነት እና ሥነ –ጥበብ ደምና ሥጋ –ከሥርጉተ ሥላሴ

$
0
0

27.05.2015 /ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ/

„ጥበብ፡ ፈጽማ፡ የጎላች፡ ናት፡ ሥርዓቷም፡ አይልፍም፡ የሚወዷትም፡ ሰዎች፡ ፈጥነው፡ ያዋታል፡ የሚፈልጓትም፡ ሰዎች፡ ያገኙአታል። ለሚወዷት፡ ሰዎች፡ ትደርስላቸዋለች፡ አስቀድማም፡ ትገለጥላቸዋለች። በደጃፉ፡ ስትጠብቀው፡ ሁልጊዜ፡ እርሱ፡ ያገኛታል፡ ወደርስዋ፡ የሚገሠግሥ፡ ሰው፡ አይደክምም።  እርስዋን፡ ማሰብ፡ የውቀት፡ ፍፃሜ፡ ነውና። ፈጥኖ፡ ስለርሷ፡ የሚተጋ፡ ሰው፡ ያለ፡ ሃዘን፡ ይኖራል።“ / መጸሐፈ ጥበብ ምዕራፍ 6 ቁጥር 12 እስከ 16/

ጤና ይስጥልኝ ውዶቼ! ረ ያለ የሚመስለው የዕንባ ጎርፍ ምጽዕት ለወያኔ ሃርነት ትግራይ ዘረኛ አስተዳደር ማንፌስቶ የአውሎ ደወሉን እዬደወለ ነው። አብረዉት ያሉት ሳይቀሩ „ቆም ብላችሁ አስተውሉ፤ ሁሉንም ትክክል ነው አትበሉ፤ የሰው ልጆችን መብት አረገጥንም – ህግም አልተላለፍነም አትበሉ፤ ዓለማቀፉ ማህበረስብ እዬመሰከረባችሁ ነው ጭካኔያችሁንም እያጋለጠ ነው። ባለፈው ወርም አንድ የሰማዕታት የሃቅ ዕድምታ በረጋጩ ማንፌስቶ ላይ ያለን ግልጽ የወቀሰ መንፈስ በንባብ በድፍረት ቀርቦ አዳምጫለሁ“። ከእንቅልፍ መንቃት መልካም መሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ ተዘሎ የነበረው የሥነ – ጥበብ ቤተኛ ህግጋት ከተረገጠበት ጋጥ ቀና እያለ ነው። ገፍቶ እንዲሄድ ሆነ ብርታት እንዲኖረው የሚያደርገው ደግሞ ዕውነቱ ነው። ለእውነት ቆሞ ማናቸውንም መክፈል የቆራጦች – ቁርጥ ነው። ሥጋ ፈራሽ ህይወትም ሃላፊ – ዕውነት ግን አብሪ።

ከሥርጉተ ሥላሴ 02.023.2014 (ሲዊዘርላንድ - ዙሪክ)

ከሥርጉተ ሥላሴ 02.023.2014 (ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ)

ተክሊሎቼ – ወደ ዋናው እርእስ ጉዳዬ ከመሄዴ በፊት በአንድ ወቅት „ጋዜጠኝነት የማሰብ ጥበብ ልቅና ነው“ የሚል ወግ ነገር እዚህ ከቤቴ ከዘሃበሻ አቅርቤ ነበር። የጋዜጠኛ ሳዲቅ አህመድን የምርጫ ዘገባ ሳዳምጥ የዕርሴን ፍቹን ለምን አላገኘውም መሰላችሁ። ስለዚህም ምስጋና ከፍቅር ጋር ልልክለት – ወደድኩኝ። ተባረክ! መውደድ – በአክብሮት። ኑርልን – የልብ ዓይን!

አሁን ወደ ጉዳዬ በዕእምሮዬ ሰሌዳ ላይ በቀነ ቀጠሮ ወደ ሰነበተው ጉዳዬ እንሆ አብረን – በትሁት ቅናዊ መንፈስ።„ሰው“ ማዕከለኛው አጀንዳው የሆነው ሥነ – ጥበብ ከሰው በታች ያሉ ማናቸውም ጉዳዮች ፋይዳው አይደለም። ሥነ – ጥበብ ለሰብዕዊ መብት መከበር ግንባር ቀደሙ ጠበቃ፤ ተሟጋች መሆን የሚኖርበት የተፈጥሮው ደም ይሄው በመሆኑ ብቻ ነው። አንድ ሰው በሥነ – ጥበብ ዘርፍ ከመሠማራቱ በፊት መወሰን አለበት። የሚበልጠው ለሥነ ጥበብ ሥነ – ምግባር ሰማያዊ ህግጋት መገዛት ወይንም ለፖለቲካ አስተሳሰብ ፍቅር ደፋ ቀና ማለት። ወይንም ናላ ለሚያዞር ግለኝነት /ኢጎ/ ማደግደግ። ሦስቱም መብት በመሆናቸው አንድ ሰው በመረጠው መጓዙ የተገባ ነው። ግድፈትም – ውግዘትም – ጫናም ሊኖርበት አይገባም። የነፃነት ሲሶ ወይንም እርቦ የለውም። ኢጎን በሚመለከት እራሷ ዓለም ያልፈታችው የተከደነ አምክንዮ አለበት።

ነገር ግን ሁለንም ቀላቅዬ ወይንም አደባልቄ „ሀ“ንም „ለ“ንም „ሐ“ ንም እንዳይከፋው ካለ ከተከፈለ ወይንም ከተሰነጠቀ ድልድይ ላይ ቆሟል ማለት ነው። ሥነ – ጥበብ ህይወቱ እራስን የመግዛት ጥያቄ ነው። መንፈስን ወጥረው ርግበትን ከሚጋብዙ ተርግብጋቢ ግላዊ ስሜቶች እስርም – መላቀቅ። ሥነ – ጥበብ የቂም በቀል ቤተኛ አይደለም ወይንም የቁርሾ አግባቢ አስተርጓሚም አይደለም።እንዲያውም ቁርሾ ሆነ በቀል የሰው ልጅ ስውር መርዞች ስለሆኑ አጥብቆ ይጠላቸዋል። እንዳይጠጉትም – ይሸሻል። ሥነ ጥበብ ብሩኽ ብርሃን በመሆኑ ወደ ኋላ ተመልሶ ጨላማን አያንቆለባብስም። ጨላማ ስል ያለፈን ንትርክ ማለቴን ነው።

በሥነ ጥበብ ሥነምግባር ውስጥ ውብ በሆኑ፤ ተደማጭነትን ባተረፉ፣ ተከታይ ባገኙ፤ ወይንም ጥቃት ደርሶባቸው በሰቀቀን ላይ ባሉ፤ እስትንፋሳቸው በአረመኔዎች – በአውሬዎች ሥር የወደቁ የሰው ልጆችን ሁሉ ድንበር፤ ቀለም፤ ጎሳ፤ ሙያ፤ ዕምነት፤ ጾታ ሳይለዬው ወይንም ሳይገድበው አብሯቸው ይሰለፋል፤ ስለእነሱ ሲል የላቀውን መስዋዕትነት ደፍሮም – ይቀበላል። በአረመኔዎች በተለይም በአንባገነኖች ሥር የወደቁ የሰው ልጆች ሁሉ ክስ የለባቸውም። ውንጀላ – የለባቸውም። መከራቸው ሰምዕትነትን – ስለሚያሰጣቸው ጻድቅ ናቸው። ከሰው ልጅ እጅ ወድቆ መተንፈሻ ቧንቧ የተዘጋ – መኖሩን የተቀማ እንዴት ይከሰሳል?!

ከዚህ ማዕቀፍ የወጣ የሥነ – ጥበብ ቤተኛ ጋዜጠኛ፤ የራዲዮና የቴሌቪዢን አንባቢ፤ ጸሐፊ፤ ሙዚቀኛ፤ ገጣሚ፤ ባለቅኔ፤ ጸሐፊ፤ ተወዛዋዤ፤ ተዋናይ፤ ተናጋሪ፤ ሰዕሊ፤ ሃያሲ  ወዘተ …. የቅንጣት ታክል የሥነ ጥበብ ቅዱስ መንፈስ እፍታ ያለረፈበት የተገለበጠ ምጣድ ነው። በምጣድ ጀርባ እንጀራ ይጋገራልን?

ዕውነት መሪው ለሆነው የሥነ ጥበብ ሰው ጨካኞች፤ ገዢዎች፤ በዳዮች – የሚወስዱት አሰቃቂ ኢ-ሰብዕዊ፤ ኢ- ፍትሃዊ ኢ- ተፈጥሯዊ እርምጃዎች ሁሉ ሊሰቀጥጡት፣ ሊያስቆጡት፣ ሊያስቆጩት ይገባል እንጂ ደርብና ምድር ወይንም ገበርና እናት ሸማ ሆኖ በሰብዕነት ተፈጥሮ ላይ አብሮ ማደም ወይንም መሰለፍ አይኖርበትም። ወይንም ለክስና ውንጀላ ተባባሪ አይሆንም። ይህ ከሆነ እራሱን ሽጦታል ማለት ነው። እራሱን የሸጠ የሥነ – ጥበብ ሰው ደግሞ መፈጠሩ በራሱ የጲላጦስን ውስጠት ያጎናጽፋዋል – በጠቀራ ይሸበልለዋል።

እንዴት አንድ የጥበብ ሰው፤ ሥነ ጥበብን ከፈጣሪ አምላኩ በጸጋ የተቀበለ – የተቃባ፤ ባለ ልዩ ተሰጥዕዎ የሰው ልጅ ጠላት በሆነው የትግራይ ነፃ አውጪ ማንፌስቶ ሥር የሚጠፉ ዓይኖቹን ለማዬት ይሳነዋል? ሰው እኮ መርፌ አይደለም። መቼ ይሆን በሥነ ጥበብ ዘርፍ የተሰለፉ ወገኖች ተደራጅተው በአደባባይ በይፋ ወጥተው ይህንን ኢ – ተፈጥሮ የሆነውን ማንፌስቶ የሚያወግዙት? ለመቼ ይሆን አባታችን መዳህኒትዓለም ለዬት አድርጎ የቀባላቸውን መክሊተ – ሜሮነ – ህግጋት ረገጣ የሚያውግዙት?  ዕንባ – እሮሮ – ኡኡታን በተደሞና በአርምሞ የእኔ ብለው የሚያዳምጡት ቀኑ መቼ ነው? ከቶስ ለማን ይሆን የሚጽፉት፤ የሚያነቡት፤ የሚሞዝቁት፤ የሚገጥሙት፤ የሚስሉት፤ የሚቀርጹት፤ የሚወዛወዙት፤ የሚተውኑት?! ተፈጥሮስ ቢሆን ዛሬ ወንዞችን – ተራሮችን – አዕዋፋትን እንሳሳትን – ምንጮችን – መሬትን እኩል የማዬት መብት አለን? እነሱም እኮ እስረኛ ናቸው? የቤቱ ጣሪያ ሳይቀር የስጋት መንበር ነው። ታዲያ ጥበብ የት ተነሳታ የት ላይ ትረፍ? እጅግ የማከብረው የሥነ ጹሑፍ መምህሬ አቶ አበበ ኬሪ „ሥነ ጥበብ ከማህበረሱ ጓሮ ይታፈሳል“ ይል ነበር … ማህበረሰቡና ሥነ ጥበብ እስከመቼ በግርዶሽ ይጠቅለሉ? ገላጮችስ መቼ ውስጣቸውን ብቻ ሳይሆን የቆሙበትን መሬት በማስተዋል – ያስተውሉት?!

„ሰው“ ነው እኮ ተዳራሹ ታላቅ ፍጡር፤ ታዲያ እንዲህ ጨለማ ውስጥ ሆኖ፣ ጸጋቸው ተከዝኖ፤ ምርቃታቸው ታሽጎ፤ መቀመጡ ለመቼ ሊሆን – ይሆን? የሥነ ጥበብ ቤተኞች ፍጹም የሆነ አላቸው – አቅም፤ አላቸው – ሃይል፤ አላቸው – አዳማጭ ታዲያ ቀጠሮው ለመቼ ይሆን? ግፍና በደለን ያላጋለጠ ሥነ – ጥበብ፤ ተጋፍቶ አደባባይ ላይ ድምጹን ያለወጣ ሥነ ጥበብ የቃር ስንቅ ነው – ለእኔ። ወይንም በቀበኛ የተባላ አሮጌ ጨርቅ።

ሥነ ጥበብ ለሰብዕዊ መብት ተሟጋች መሆኑ ብቻ ሳይሆን በተፈጠሮው የተሰጠው ሙያ አለው። ህግ። ሚዛኑ እኩል ልኩ።

በነፃነት ትግሉ የተሰለፉትም ቢሆኑ – ጥበብ አድሎ የለባትም፤ ጥበብ ቤንዚን – አታርከፈክፍም፤ ጥበብ ፍቅር ናት። ጥበብ ህይወት – ህያው ናት። ጥበብ ይቀርባይ ምህረት ናት። ጥበብ እስትንፋስ መንፈስ ናት። እንዴት ብርሃን ተከልክሎ እንደ ጥንቸል ሁሉንም መከራ በመቀበል ላይ ላላ ለተዘረፍነው መንፈስ ክስ ይቀርብበታል? አለ የሚባል ክስ እንኳን ቢኖር ቀን መጠበቁ ምን ይሆን የተሳነን? ስለምን ይሆን አሁን ከ10 ዓመት በፊት ለዛውም ካቴናን ባርዱን ላስተናገደ ዘመን – አጥፊ ተዋናይ የምንሻለት?!  — ያለባራው ያ … ዱላ፤ ያ …. ጩኸት ያ … የስቃይ – የድረሱልኝ ድምጽ የእያንዳንዱ ድቀት ጅራፍ ጩኸት ከጥበብ ቤተኛው ጀርባ አላረፈ ይሆን? መቆፈር – ለቀባሪዎች ይመች ይሆናል ሥራቸው ስለሆነ ጉሮሯቸውም፤ – ለጥበብ ሰው ግን ግጥሙ አይደለም? ይልቁንም ሃፍረት ይዛቅበታል – ተንበርክኮ። መከራንና ሰውን፤ ግፍና በደልን፤ ወቅትናን ሁኔታን የማያዳምጥ ጥበብ – ምኑን ይሆን የተቃማው?! !

ህም! ልጆች ዛሬን ሳያውቁት ወላጆቻቸውን – ተቀምተዋል፤ ጽንሶች ዛሬን ሳያዩት – ተጨናግፈዋል፤ ቢያንስ ይህ አይጎረብጥም? ጠቅለል ብሎ ከፖለቲከኞች ጋር ተሰልፎ መንገድን ለይቶ መታገል አንድ ነገር ነው። ግን በሥነ – ጥበብ ቤተኝነት ሥም ሲሆን ግን ይመራል? እስረኞቻችን – ሰማዕቶቻችን – አርበኞቻችን ምስላቸውን አቅርበን – እናስተውለው። ቀድሞ ነገር ከነዚህ መከራን ፈቅደው ከተቀበሉት ጋር እኛ ምንድን ነን? ለመሆኑ አብረን ቁጭ ብለን የመወያዬት አቅም ቢኖረን እንኳን እንችለዋለን? እንኳንስ ለወቀሳና – ለነቀሳ? ማንን አቅም እዬሰጠን ይሆን?! አርበኞቻችን እስር ላይ ዓመት እስከ ዓመት ሙሉ ብርሃን ተነፍገው፤ ከቤተሰብ ተነጥለው፤ ከጠያቂ ተሰውረው፤ ስለመኖራቸው በህይወት እንኳን በማናውቅበት ሁኔታ ላይ፤ በሞትና በህይወት መሃከል እያሉ፤ መከራችን የተሸከመ ነፍስ —-  ስንከስ – ስንዘለዘል – ስንተረተር – ስናብጠለጥል ….. ለመሆኑስ የጥበብ ሰውነታችን ከእኛ ጋር ወይንስ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ አሸከር ሆነናልን? ባነበብኩት ነገር አላዘንኩም። ይልቁንም ሥነ – ጥበብ የተጋረደችበትን ቁራኛ አስተዋልኩበት እንጂ።

በምንስ እንለይ ይሆን የሥነ ጥበብ ሰውነታቻን ከወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌሰቶ ደጋፊያት ጋራ? „ብዕሩም ብራናውም ሰውን መተርጎም ካልቻለ እውሃ ሲሄድበት የከረመ አለት ሆኗል። ብዕር – ብራና ሆነ  አዬሩ – እስትንፋሱ – ህዋሱ – ሩሁ ሆነ ህልውናውም የሰውን ተፈጥሮ ማመሰጣር ከመቻል ላይ ነው። ከዚህ ውላዊ – ቃልኪዳናዊ የመዳህኒታአለም አባታችን ስጦታ ጋር መተለለፍ ካለ – ጌጥን የማቃጠል ብቻ ሳይሆን፤ አመዱን እንደ ሰው ደም በጥብጦ መጠጣት ነው አሁንም ለእኔ።

ነገም ቢሆን ከነፃነት በኋላ የሚኖረው የሽግግር ሂደት „ሰው“ „ተፈጥሮ“ የሚለውን በቅጡ መተርጎም ችሎ አክብሮቱን በተግባር ማሳዬት ካልተቻለ፤ ለሰው ልጆች መፈጠር ሚስጥራዊ መለኮታዊ ትርጉም ዕውቅና መስጠት ከተሳነን፤ የነፃነት ትግሉና የሚከፈለው መስዋዕትነት ዕሴት አልቦሽ ነው። ቋሳ ለሚመራት – ቂም ለሚያስተዳድራት፤ ለእከሌ ፍርሰት ተጠያቂው እከሌ ነው እዬተባለ ዛሬም ነገም መከራ ለሚመረትባት ባዕት ከሆነ ድካሙ …. ? ? ? መርዶን ደመርን ነው እዬተጋንለት ያለው ማለት ነው።

የዘለዓለም ዕንባ መድረቅ ችሎ ቢያንስ እዬረባው ሰላሙን ሳይቀማ፤ የራህብ አንጀቱን ከአንገት በማታልፍ እራፊ በተቀዳደች ሰኔል ላይ ጉልበቱን ታቅፎ ወገን በነፃነት ካለፍርሃት እንዲያደር መፍቀድ የማይችል የነፃነት መንፈስ ለእኔ በአፍንጫዬ ይውጣ። ዛሬ ሚሊዮኖች በሥርዓቱ ውስጥ መሥራት ግድ ይላቸዋል። በዚህ አያያዝ ነገም እነዚህን ሚሊዮኖችን ተከሳሽ ለማደረግ መሰናዶ ይሀው ከሆነ ይቅር ትግል። ይህ ወልጋዳ እሾሃማ የነፃነት ትግሉ መስመር ሊሆን ከቶውንም አይገባም።

መከራዋ የኢትዮጵያ በምህረትና በፍቅር ካሳ ማግኘት አለበት። መልካምና መልካም ያልሆኑ ነገሮች በአግባቡ ተጠንተው ለቀጣዩ ጊዜ በሚበጅ መልኩ መደራጀት አለበቻው። መንፈስ መታጠብ አለበት። ከቂምና ከበቀል፤ ከክስና ከስሞታ መጽዳት ውስጥ ይኖርበታል። በተጨማሪ ዛሬ ያሉት ነገሮች ሁሉ እያንዳንዱ ክስተት የሀገራችን መዋለ ንዋይ፤ መንፈስ፤ ንብረት ፈሶበታል። ስለሆነም ከታሪክ – ከትውፊት ብክነት መዳን አለበት – ህልማችን ሆነ ራዕያችን  – ከዚህ አዎንታዊ ሃዲድ ጋር መዋህድ ይኖርበታል። ይህ ለጥበብ ሰው ሆነ የሰው ልጆች ነፃነት ሆነ፤ የተፈጥሮ በረከትን ረጋጣን ለማስቆም ለተሰለፈ ሰው መስመሩና መንገዱ ሊሆን ይገባል። ሚዛን ጠባቂነቱ የሚረጋገጠውም በዚህ ነው። ሥነ ጥበብ የወርቅ ሚዛን ነው ህዋሱ።

ፖለቲከኛው በፈለገው መስመር የፓርቲውን ፕሮግራም ማንፌስቶውን ከሚወግን መንፈስ ጋር ቢሰለፍ ባህሪው ነው። የፖለቲካ መስፈርቱ የሚወዳደረው በሥልጣን ዙሪያ ነው። ሰው የሚለው ተፈጥሮ የሚታዬው በአንጻራዊነት ነው። ይህ የእኛ ብቻ አይደለም ዓለም እንደ ህግ የተቀበለቸው ጉዳይ ነው። ሲሪያ ላይ ህንፃ አይደለም እይፈረሰ ያለው – ትውልድና ታሪክ ነው። ዋጋው የጥፋቱ የሚለካው ግን ከጥቅም ጋር ነው። የጥበብ ሰው ሆነ የሰብዕዊ መብት ተሟጋች የሆነ አንድ ሰው ወደ ፖለቲካ ህይወት ሽግግር ሲያደርግ ምን እንደሚመሰል ለናሙና …. ትንሽ ነገር እንሆ —

  1. አንድ ፎቶ ወስደን ባለቀለማሙን ፎቶ ወደ ነጭና ጥቁር አንቀይረው፤
  2. ከዛ የፎቶውን የብርሃን መጠን እዬቀንስን ስንሄድ ምስሉ ምን እዬሆነ እንደሚሄድ ሞክሩትና ክብሮቼ – እዩት።

በሌላ በኩል ከፖለቲካ ህይወት ወደ ሰብዕዊ መብት ተሟጋችነት ወይንም ወደ ጥበብ ፍቅር ሽግግር ከኖረ ግን ያ ብርሃኑና ቀለሙ ቀንሶ ምስሉ ስስ የነበረው፤ የሰውነት ምስሉን ለመለዬት ያስቸግረው የሰው ምስል እዬጎላ እዬጎለበት ይመጣል። ስለዚህም የሚቀድምበት – የሚመራው – ተክሊሉና ዘውዱ የሰው ልጆች ሰብዕዊ መብት አለመዘረፍ ብቻ ሳይሆን፤ ተፈጥሮ የለገሰን እንሰሳት፣ ወንዞች፣ ተራሮች፣ ምንጮች፤ ዕጽዋት፤ ሸለቆዎችና መሬት እራሷ ለእሱ ልዩ ትርጉም – ይሰጡታል። ያደንቀዋል፤ ያከበረዋል፤ ያፈቀርዋል። ክፍተቶች – ነዳላዎች – ቀዳዳዎች ሁሉ በመልካም ነገሮች ተሞልተው የሰው ልጅ መከራ ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮ የለገሰን የውበት አድባሮች ሁሉ ሰላማቸውን እንዲያገኙ – ይተጋል። መታወካቸውም – ያመዋል። ውስጡን – ያቃጥለዋል። ጠበቃም ይሆናል። ባይችል – መልካሙን ይመኛል፤ ውብ – ያልማል።

ወቅቶች የተፈጥሮ ሂደቶች ናቸው። ወቅቶች የሚፈጥሯቸው ክንውኖች ግድፈቶች በመልካም እንዲሸፈኑ መጣር የጥበብ ሰው ዋንኛው ፕሮጀክቱ ነው እንጂ ወቅቶችና ሂደቶች የፈጠሯቸውን ክስተቶች አፋፍሞ ተታኮሱ አይልም። ይህን የጥበብ ሰው ካደረገ ቂምን – ከከበከበ፤ ጥላቻን – ካበረታታ፤ ቋሳን – ከሞሸረ – የትውልድ ደመኛ ነው። ስለዚህም ማህበረሰቡ በጥበብ ሰውነቱ ሆነ በሰብዕዊ መብት ተሟጋችነቱ የሰጠውን ልዩ ፍቅርና ክብር፤ ግርማና ሞገስ ሆነ ተቀባይነት መንጠቅ አለበት። ጊዜም የቅንጣት ማቃጠል የለበትም። በመከረኞች – በተገፉት – ሰውነት ላይ ጅራፉ ሲያርፍ ቶርች ሲሆኑ፤ ሲደፈሩ የጥበብን ሰው ገላም አብሮ መላጡን – መጋጋጡን – በመንፈሱ መረመጡን መቀበል ላልቻለ የጥበብ ሰው የችሎቱ ብይን የሰጡትን አድማጭነት መንጠቅ ነው።

መቋጫ – ንጹህ አዬር ላይ ያሉ ፖለቲከኞችን ሆነ መስመራቸውን መተቸት ያስተምራል፤ ግደፈትን – ያርማል፤ እሩቅ እንዲያስቡ – ያግዛል፤ አቋምንም – ያስተካክላል። ነገር ግን መከራ ላይ ያሉ ወገኖች፤ እስር ቤት ያሉ ሥጋና ደሞችን፤ እዬተጋፋ በሥማቸው ላይ ሚጥሚጣ የሚነሰንስ ወይንም በአጋፋሪነት ከጨካኞች ጋር የተሰለፈ መንፈስ ከሰማይ የተሰጠን ጸጋና ህግጋት ተላልፏልና ውሉ የተደማጭነትን ካባ በመግፈፍ ማወራረድ ይገባል እላለሁ እኔው ሥርጉተ – ሥላሴ። ከመከራ ከእስር በሰው እጅ ቁጥጥር ሥር ከመወል በላይ ሰምዕትነት የለም“  መሸቢያ ሰሞናት – የኔዎቹ።

„የጥበብን፡ አገሯን፡ ማን፡ አገኘው፡ ምሥጢሮቿን፡ ማን፡ መረመረው።“ /መጸሐፈ ባሮክ ምዕረፍ 3 ቁጥር 14/

 

አርበኞቻችን መንገዶቻችን ናቸው – ለእኛ!

የሰማዕታቱ ረድኤት አይለዬን – ለእኛ። አሜን!

ለእኔስ ሰው መሆኔ ብቻ ይበቃኛል – ለእኔ!

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

The post ሰብዕዊ መብት ተቆርቋሪነት እና ሥነ – ጥበብ ደምና ሥጋ – ከሥርጉተ ሥላሴ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>