ክፋት ተዘርቶ ክፋት ከሚታጨድበት፣ ጥፋት ተከምሮ ጥፋት ከሚወቃበት ከሰረገላው ውረዱ። ምርጫው መላገጫ ከሆነበት፣ አሸናፊው ከሚሸነፍበት ከውሸት ሰረገላው ውረዱ። ህዝቡ የኔ የሚላቸው የሚታሰሩበት፣ መሪዬ የሚላቸው ከሚታፈኑበት ከሰረገላው ውረዱ። ይሄንን የውሸት ሰረገላ አዘጋጅቶ ለበደሉ አድማቂ ለጥፋቱ ተባባሪ የሆኑትን የወያኔ ጭፍሮችን አሳፍሮ ከበሮ የሚያስደልቀውን፣ ለማፈኑ ተግባር አጋዚ ለረገጣው መሰረት ምርኩዝ የሆኑትን የታጠቁ ወታደሮች በሰረገላው ያሳፈረው፦ የህዝብ እንባ አፍሳሽ፣ የህዝብ መብት ረጋጭ ነውና ሰረገላውን የሞሉት…. አንተ ህሊና ያለህ ከሁሉ በላይ ህሊናህ ዳኛህ ነውና ያለ ሞጋች የሚሞግት፣ ያለ ከሳሽ የሚከስህ፣ ያለ ዳኛ የሚፈርድብህ፣ ህሊናህ እዳ ነውና ከህሊና ፍርድ ለመውጣት ከጥፋት ሰረገላው ውረድ። የህዝብ ቁጣ ወደ ግለት፦ ግለቱ ወደ እንፋሎት፦ እንፋሎቱ ወደ ፍንዳታ ተለውጦ ሰረገላው ከመጥፋቱ በፊት ከሰረገላው ከጥፋት ሰረገላው ውጡ።
ነጻነትን የማያውቅ መሪ ለህዝቡ ነጻነትን ይሰጣል ወይም ያመጣል ማለት ዘበት ነው። መብላትና መጠጣት ሆድን ሊያጠግብ እንዳትራብም ሊያደርግ ይችላል። ነጻነት ሊሆን ግን አይችልም። ነጻነት ማለት ከመብላት እና ከመጠጣት በላይ ለአእምሮ እውነትን የምትነግርበት፣ የተሰማህን ያለምንም ፍራቻ የምትገልጽበት፣ ሃሳብህን በነጻነት የምትገልጽበት፣ የመናገር፣ የመጻፍ፣ ነጻነት የሚጸባረቅበት ከፈጣሪ የተሰጠህ ጸጋ ነው። ይህንን ከፈጣሪ የተሰጠህ ነጻነትህን አንባ ገነኖች በግድ ማፈን እና ሊነጥቁህ ሲፈልጉ የነጻነት ፈላጊው ድምጽ ከውስጥ ፈንቅሎ በመውጣት ማየል ይጀምራል። ወያኔም ይህንን የህዝቡን ነጻነት ያፈነው። ይህንን የሰፊውን ህዝብ ሰላም ያናጋው። የሰላም እጦት ሰላም አደፍራሹን ካላጠፋ እንደማያቆም ጠንቅቆ ለመረዳት ታሪክን መመልከቱ በቂ ነው።
መረጥን ያሉ እጆች የመረጡት ሳይሆን ያልመረጡት ያሸነፈበት፣ የፈለጉት ሳይሆን ያልፈለጉት ሊገዛ መነሳት ማለት ምን ያህል ህመም እንደሆነ ሁሉም የሚያውቀው ጉዳይ ነው። ባልመረጡት መመራት ማለት ነጻነትን መነጠቅ ማለት ነው። ረጋጭ እና አፋኝ፣ አሳሪና ገዳይ፣ በራስ ላይ በግድ መሾም እንደሆነ ይታወቃል። ታዲያ ይሄንን በጠራራ ጸሃይ የተነጠቀውን የህዝብ ድምጽ ሊቀበል የሚችል እና እውቅና የሚሰጠው የትኛው አካል ነው። በግድ እራስ ላይ የወጣን ባለጌ በግድ ከእራስ ላይ ትወርዳለህ ብሎ ባለጌን ፊት ለፊት ተናግሮ በሚገባው ቋንቋ በማናገር ነጻ የመውጣት ትግሉ ትርጉም እንዲኖረው ማድረግ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጉዳይ ነው። ቆማጣን ቆማጣ ካላሉት ፈትፍቶ ያጎርስሃል እንደተባለው ተረቱ።
ህዝቤ ሆ!!! ከፊትህ ያለውን የጥፋት ሰረገላ አፍርሰው። ሰረገላው ላይ ተሰቅለው ግፍና በደልን በመስራት ማንም ከኛ በላይ ያሉትን በማሳፈር ከህዝብ በላይ ማንም እንደሌለ እናሳየው። ከአሁን በኋላ ህዝባችን ከቶውን ተሸማቆ እና ተሳቆ፣ ታስሮ እና ተገድሎ፣ ተርቦ እና ተጎሳቁሎ መኖር ይብቃ። በሰረገላው የተሰቀሉት በህዝብ ቀልደው የሚኖሩበት ግዜን ፍጻሜውን እናምጣው። ሰረገላውን መስበር ቀላል ነው። ያም የሚጓዝበትን መንገድ መስበር፣ በካድሬ የተሳሰረውን የስለላ መረብ መቁረጥ፣ አንድ ለአምስት ብሎ የጠረነፈውን ወጥመድ በመጠስ ስር ስራችን ያሉትን የአቃጣሪዎችን መስመር በመበጣጠስ ህዝቡ የማያዳግም ርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል። ህዝብን በማሰቃየት፣ በማፈን፣ በመሰለል፣ የተሰማሩት የሰረገላው ተሳፋሪዎች በአጭር ግዜ መቆጣጠር የሚቻልበት ግዜ ላይ ስለሆንን ለዚህም ድል እንደ ሸረሪት ድር በቀለበት በመተሳሰር ጠላትን እያጠመድን በመጣል ታሪክን እናስመዝግብ። ድር ቢያብር አንበሳን ያስር ነውና ።
ሃያ አራት አመት ሙሉ ሰረገላው ላይ የተሳፈሩት ሲፈሩ ነበረ። የፈለጉትን ያስራሉ፣ የፈለጉትን ይገድላሉ፣ ለዚህም ማንም ጠያቂ የላቸውም። ምክንያቱም ፍርድ ቤቱ የራሳቸው፣ ዳኛውም የራሳቸው በመሆኑ እውነትን በሃሰት ተለውጦ የህዝብ ደምና እንባ በከንቱ ፈሷል። አሁን ግን አይተናቸዋልም አውቀናቸዋልም። ከአሁን በኋላ የሚጠበቅብን በሰረገላው ተጭነው በደልን ለማድረስ የሚሯሯጡትን ህዝብን የሚያፍኑትን በሙሉ ዋጋቸውን ሊያገኙ ይገባል። የበደል ሰረገላ ይፈርሳል። የገዳዮችም ሰረገላ ይጠፋል። የአፋኞች ሰረገላም ይመታል። ለሰረገላው መንገድ ለሰረገላዎቹም ቦታ ከእንግዲህ በኢትዮጵያ ምድር ቦታ አይኖረውም። የታፈነ የህዝብ ድምጽ የተረገጠ የህዝብ ነጻነት እራሱን ነጻ አውጥቶ በግልጽ የሚታይበት ግዜ ቅርብ ነው።
ከተማ ዋቅጅራ
29.05.2015
Email waqjirak@yahoo.coma
The post ከጥፋት ሰረገላ ውረዱ!!! – ከተማ ዋቅጅራ appeared first on Zehabesha Amharic.