Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ሀገራዊ (ብሔራዊ) ዕርቅ በኢትዮጵያ

$
0
0

አሸብር ሺፈራው ከጀርመን

ከወዲሁ፤- ሀገራዊ ዕርቅ በኢትዮጵያ ስል ሌላ ምንም ሳይሆን፤ ከዘረኛው የትግራይ ሕዝብ ነጻነት ግንባር (TPLF) የባርነት አገዛዝ ነጻ ወጥታ በምትመሰረተው ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ማለቴ መሆኑን ግንዛቤ እንዲያዝልኝ አሳስባለሁ። ብሎም፤
Hand Shake
1ኛ/ ስለ ሀገራዊ ዕርቅ አስፈላጊነት፤-
ሀገራዊ እርቅ በኢትዮጵያ አስፈላጊ ብቻ ተብሎ የሚቀመጥ ሳይሆን፤ በምንም ዓይነት መታለፍ የሌለበት ሂደት ነው የሚል የፈረጠመ አቋም ነው ያለኝ። እንበልና ዛሬም ሆነ ነገ ያገር ቤቶቹ ሰላማዊ ታጋዮች እንደሚሉትም በምርጫ ውድድርም ባይሆን፤ በምርጫ ትግል ስርአቱ ተወገደ ቢባልና፤ ዛሬ በዚህ አረመኔ አጋዛዝ ታፍኖ የተያዘው የሕዝብ ነጻነት ዕውን ቢሆን ብለን ብናልምምና፤ ሕልሙ ተፈጻሚ ሆነ ብንልም እንኳን፤ የተመረጠው መንግሥት ቅድሚያ ሰጥቶ ሊያከናውናቸው ከሚገቡ ዋና-ዋና ጉዳዮች አንዱ ይህንኑ የሃገራዊ ዕርቅ ሂደት ማስጀመር መሆኑን ከወዲሁ ተረድቶ፤ በዚህ አቅጣጫ አፋጣኝ እርምጃ ሳይወስድ፤ የተመረጥኩ መንግሥት ነኝ በማለት ብቻ ሕብረተ-ሰቡ እንደ አንድ ሕዝብ ሆኖ ለዴሞክራሲያዊ ድሎቹ አለመቀልበስ በጋራ እንዲቆም፤ ለሰላም፤ ለልማትና ለብልጽግና ተባብሮ እንዲሰራ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት በብዙ ውስብስብ ችግሮች እንደሚደናቀፍ መጠራጠር አይቻልም። ለምን የሚለው ጥያቄ ባይከተል ሃሳቤ የአንባቢን ቀልብ አልሳበም ማለት ነው። መከተሉ ግን የግድ ነው። እናም መልሱ፤

2ኛ/ የዘረኛው የትግራይ ሕዝብ ነጻነት ግንባር (TPLF) አካሄድ፤- ከ24 ዓመት በፊት የስልጣን ኮርቻው ላይ ከተፈናጠጠ ጀምሮ፤ ይህቺን የስልጣን ኮርጫ እስከወዲያኛው አስጠብቆ ለማቆየት፤ ኢትየጵያንና ሕዝቧን ማለቂያ በሌለው የደም ዋጋ ክፍያ ባሪያ አድርጎ ለመግዛት የሚያስችሉትን፤ በተጠናና በከፍተኛ ስሌት የወሰዳቸውን ህዝብን ከህዝብ የሚያናቁሩ፤ መተማመንን የሚያሳጡ፤ ከዜግነት ይልቅ ጎሰኝነትን/ነገዳዊነትን/ጎጠኝነትን እያራገበ፤ ዛሬ ያንዱ ሃይማኖት ተቆረቋሪ ነገ የሌላው አጫፋሪ በመሆን፤ ባጠቃላይ አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ በማድረግ በፈጸማቸው አጥፊ ተግባራቱ በደረሱ በደሎች፤ በሕብረተሰቡ ውስጥ የታያዙ ቂምና በቀሎች ጋን ሞልተው የፈሰሱ ናቸው። ስለ ትግራይ ሕዝብ ነጻነት ግንባር የዘረኝነት አጀማመር ቀደም ሲል ገና በትግል ዘመኑ በአንድ ጎሳ ላይ ያነጣጠረ ድንፋታውን ትተነው፤ በሥልጣን ዘመኑ መጀመሪያ ላይ ያካሄዳውንና ብዙ ሰው ልብ ያላለውን በማመላከት ትንሽ ብሄድበት ጥሩ ስለመሰለኝ፤ የሚከተለውን ላስታውስ፤

ሥልጣን እንደጨበጠ ወዲያውኑ ጊዜ ሳያጠፋ ያደረገው፤- ጉራጌ ክፍለ-ሃገር ተመድቦ የነበረ የመንግሥት ሰራተኛ ኦሮሞ በመሆኑ ጉራጌ አገር መስራት እንደማይገባው ተደርጎ ወዳኦሮሞው ክፈለ-አገር እንዲሄድ፤ አማራውም፤ ትግሬውም፤ ወላይታውም፤ ሲዳማውም … ወዘተ በዚሁ መልክ እንዲፈናቀል ሲደረግ፤ ለምሳሌ አማራ ክፍለ-ሃገር ለስራ የሄደው ወላይታ ያገባት አማራ ሚስቱ እነደሱው ተመሳሳኝ ሰራተኛ ብትሆን፤ ወላይታ ሄዳ መስራት ስለማትችል፤ ለስራዋ ብላ ከባሏ ተለይታ መቅረት፤ ወይም ባሏን ተከትላ ሄዳ የቤት እመቤት ሆና መቀመጥ ምራጫዋ ሆኖ ነበር። ለወንዱም ይኸው ዕድል ደርሶታል። በዚህ ብዙዎች ልብ ባላሉትና ያሉትም ቢኖሩና በጊዜውም „ethnic cleansing à la eprdf“ በማለት ቢያመላክቱም አዳማጭ ባላገኙበት መጥፎ ሒደት የብዙዎች ትዳር ፈርሷል፤ ቤተሰብ ተበትኗል።

ደጋፊ አጋጣሚ፤- አንዲት ያንድ ጎሳ አባል የሆነች ወጣትና አንድ የሌላ ጎሳ አባል የሆነ ወጣት በውጭ ሃገር ባንድ ከተማ ውስጥ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ በነበረበት ጊዜ ተዋውቀው የጋብቻ ሥነ-ሥርዓታቸውን የፈጸሙት ከላይ ያመላከትኳችሁ ዓይነት:-

በኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረው ዘር ማጽዳት ከመጀመሩ 10 ሳምንት ቀደም ብሎ ስለነበርና በዚህ ጊዜ ውስጥም ትምህርታቸውን ጨርሰው ወዳገራቸው መመለሻቸው ስለነበር፤ አውሮፕላን ጣቢያ ስሸኛቸው ወጣቱ „ይህንን ሁኔታ ቀደም ብለን ብናውቅ ኖሮ ጋብቻ አንፈጽምም ነበር። አሁን እኮ እንግዲህ እዚያ ሄደን መለያየታችን ነው። ያሳዝናል!“ ብሎ ጭንቀቱን ሲገልጽልኝ፤ እኔም ጭንቀቱን በማየት፤ ታዲያ ለምን እዚሁ አትቀሩም እንደማንኛውም ሰው ስደት መግባት ነው ስለው፤ እሱማ አይሆንም እዚያው ገብቼ የሆነውን ማየት ነው ብሎ መለያየታችን ትዝ ይለኛል። ከዚህ ጀምራችሁ ወደላይ ዘልቃችሁ አኝዋክ በአኝዋክነቱ፤ አማራው በአማራነቱ የተፈጸመበትን እያከላችሁ የማየቱን ጉዳይ ለአንባቢዎች ልተወውና፤ ባጠቃላይም የዘረኝነት ዋና መገለጫው በሆነው አድሏዊነት ባሕርዩ በፈጸመውና በመፈጸም ላይ ባለው፤ በሹመቱ፤ በሽልማቱ፤ ሃብት በማካበቱ … ወዘተ ያለውን ልዘርዝር ካልኩ ቀኑ መሽቶ ይነጋልና ለቅምሻ ያህል ይህንን ካልኩ በሁዋላ፤

3ኛ/ በቁጥር 2 የተጠቃቀሱትና የሌሎችም መሰል ሂደቶች ዕድል፤- ሂደቶቹ በሕዝብ መሃከል የፈጠሩትን የኑሮ መመሰቃቀል ተከትሎ ከላይ እንዳልኩት ጋኑን ሞልተው የፈሰሱት ቂምና በቀሎች፤ ከባርነት አገዛዙ ማክተም በሁዋላ በምትፈጠረው ደሞክራሲያዊት እትዮጵያ ሽረት ሊያገኙ የሚችሉት አስር ጊዜ ከበረዶ በነጣ ነጻ ፍርድ ቤት በሚሰየሙ ዳኞች ሳይሆን፤ በሃገራዊ ዕርቅ ብቻ ነው። ሃገራዊ እርቅ የፍርድ ቤት ክርክር አይደለም፤ በአስከፊው ስርዓት ውስጥ የሚያልፍ ሕብረተ-ሰብ መሃል አንድ ወገን በዳይ፤ ሌላው ተበዳይ ብቻ ሆኖ ፈጥጦ የሚታይበት ገጽታ የለውም። በዳዩ ተበዳይ፤ ተበዳዩ በዳይ ሆነው የሚፈተሹበትም ሂደት ነው። ሃገራዊ እርቅ ሕብረተሰቡን እንዳለ የሚመለከት ጉዳይ ነው። ሀገራዊ እርቅ ወንጀለኛ ከወንጀሉ የሚነጻበት፤ ከቅጣት የሚያመልጥበት፤ አይደለም። በማንኛም ደረጃና በማንኛውም ጉዳይ ቢሆን፤ በተበዳደሉ ወገኖች መካከል በማንም፤ በምንም ሳይገደዱ፤ ለተፈጸመ በደል እያንዳንዱ ተሳታፊ ተጸጽቶ፤ ከራሱ ጋር ታርቆ፤ ከተበዳዩ ወገን የበቀል ልብን አዘግቶ፤ የይቅር ባይነትን ልብ ለማስከፈት የሚማጸንበት በጎ መንገድ ነው። ተበዳይም ቢሆን፤ ለተፈጸመው በደል የኔስ አስተዋጽኦ ይኖርበት ይሆን? በማለት እራሱን ጠይቆ እንደደረሰበት ሁኔታ እኔም እኮ እንዲህ ባላደርግ ኖሮ ምናልባትም ያ ነገር ተካሮ እዚህ ባልደረሰ ነበር በሚል እራሱን በራሱ የሚወቅስበትም አጋጣሚ ነው።

4ኛ/ የሃገራዊ የእርቁ ቦታ ዩዳይ፤- ሃገራዊ እርቁ የሚደረገው አሜሪካ፤ አውሮፓ፤ አውስትራልያ፤ እስያ ሳይሆን፤ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ብቻ ነው። የእርቁም ባለቤት፤ ታራቂውም፤ አስታራቂውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ያ ሕዝብ ደግሞ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ታዲያ በዚያች ምድር ላይ ስለዚህ ዓይነቱ የሃገራዊ ዕርቅ ሂደት ለማሰብ፤ ቢያንስ በመጀመሪያ ደረጃ ከትንሹ እንጀምር ብንል እንኳን፤ በአንድ ላምስት ተጠርንፎ የተያዘው ሕዝብ ከጥርነፋው ተላቅቆ፤ በነጻ የማሰብ መብቱ ታውቆለት፤ ባጠቃላይም ሕዝቡ ከፍርሃት ተላቆ፤ አዩኝ አላዩኝ ሳይል እርስ በርሱ መነጋገር የሚችልበት ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል። አንጻራዊ የሆነም እንኳን ቢሆን፤ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል። ይህንን ሁኔታ ለመፍጠር ያለው አማራጭ ደግሞ አንድና አንድ ብቻ ነው። በመጀመሪያ የባርነቱ አገዛዝ መወገድ ነው።! እዚህ ላይ አንድ አለመግባባት እንዳይፈጠር ያስፈልጋል፤ የትግሬ ሕዝብ ነጻነት ግንባር የዘረጋው የባርነት አገዛዝ ተወገደ ማለት፤ በዚህ ድርጅት ስር የተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን ትግሬዎች በዴሞክራሲያዊ መርህ

በምትቆመው እትዮጵያ ውስጥ ህልውናቸው ያከትማል፤ ይጠፋሉ የሚል ቅዠት የሚያስተናግድ ህሊና ካለ፤ ስለ ሃገራዊ ዕርቅ የሚያወራው በደመ ነፍሱ መሆኑን ማጤን ይኖርበታል። ዴሞክራሲያይቱ ኢትዮጵያ የሁሉም ነች። ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የዜጎቿ ሁሉ ነች። ዜጎቿ ደግሞ ደጋጎቹ ብቻ ሳይሆኑ ክፉዎቹም ጭምር ናቸው። የትግሬ ሕዝብ ነጻነት ግንባርም እንደድርጅት ከነዓይኑ ከነጥርሱ ሊቀጥል የማይችልበት ምንም ምክንያት አይኖርም። የሚፈለግበት የዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን መተዳደሪያ ደንብ ማክበር ብቻ ነው። የትግሬ ሕዝብ ነጻነት ግንባር የዘረጋው የባርነት ሥርዓት ሲደመሰስ የዚያ ሥርዓት ባለቤትነቱ ያከትማል። ይህ የማይቀር ነው። ከዚህ የሚጨመርም የሚቀነስም ነገር አይኖርም። ከባርነት ነጻ መውጣት በሁዋላ ስለሚደረግ አገራዊ እርቅ ጉዳይ እስከዚሕ ያልኩት ማለት የሚገባኝን ነው ባልልም ከሞላ ጎደል የሆነውን ያህል ያልኩ ይመስለኛል፤ በዚህ ልቋጨውና ወደሌላ ነጥብ ልሻገር፤
5ኛ/ የዚህ የአገራዊ ዕርቅ ጥያቄ ባሁኑ ጊዜ ስለመነሳቱ፤- ዛሬም አንተ እንደምትለው የባርነቱ አገዛዝ ሰፍኖ ባለበት ሁኔታም እየተነሳ ነው፤ ፋይዳው ምንድን ነው? የሚል ጥያቄ መነሳቱ ስለማይቀር፤ በዚህም ያለኝን ሃሳብ ማሳወቁ አስፈላጊ ስለሆነ፤ ዛሬ የሃገራዊ እርቅ ጥያቄ መነሳት ይችላል ማለት ብቻ ሳይሆን፤ መነሳቱ ጠቃሚም ነው የሚል መነሻ ጨብጨ የሚከተለውን አስቀምጫለሁ::

ባሁኑ ጊዜ ይህ የአገራዊ ዕርቅ ጥያቄ የሚነሳው ስለጽንሰ ሃሳቡ ግንዛቤ ለማስገኘት፤ ብሎም በሃገራችን ሁኔታ አስፈላጊ ወይም አላስፈላጊ ስለመሆኑ፤ እንዴትና መቼ፤ የት መደረግ እንዳለበት፤ ጽንሰ ሃሳቡ ቀደም ባሉ ጊዜያቶች ስራ ላይ በዋለባቸው አካባቢዎች ያስገኘውን ውጤት በማገናዘብ፤ ከዚያ በሚቀመሰው ልምድ በመነሳት ከሃገራችን ሁኔታ ጋር በሚጣጣም መልክ በስራ ለመተርጎም የሚቻልበትን እቅድ ከወዲሁ ለመተለም የሚያስችለውን ዘዴና ብልሀት ከወዲሁ አጢኖና ተዘጋጅቶ ለመጠበቅ፤ ዛሬ ስርዓቱን ለማስወገድ ሰላማዊም ሆነ የትጥቅ ትግል የሚያካሂዱ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ የህዝባዊ ድርጅቶች፤ በተለይም በመስኩ ዕውቀት ያላቸው አዋቂዎች/ምሁራን ጉዳዩን ጉዳያቸው በማድረግ የተለየ ትኩረት በመስጠት በሴሚናርና፤ በሌላም ተመሳሳይ መንገዶች ሁሉ ትምሕርት በመስጠት የሕዝብን ንቃተ ህሊና ለማጎልበት በሚረዳ መልክ እንዲካሄድ ለማድረግ እስከሆነ ድረስ ጥያቄው ተነስቶ መስተናገዱ የሚደገፍና የሚነቃቃም ነው። በምንም ምክንያት ተቃውሞ አይኖርም።

ከዚህ ባለፈ ግን፤ ዛሬ የሃገራዊ እርቅ ደርግ አቋቁመን፤ እርቅ መደረግ አለበት የሚባለው ልፈፋ „ከብት ባልዋለበት ኩበት ለቀማ“ ወይም „ጋሪው ከፈረሱ ቀደመ“ እንደሚባለው ነው የሚሆነው። ከዚያም አልፎ የትግሉን አቅጣጫ ማሳት ነው የሚሆነው። ከትግሬ ሕዝብ ነጻነት ግንባር ጋር እርቅ እናድርግ የሚባል ከሆነ፤ ይህ የፖለቲካ ድርጅቶች አቲሆ ባቲሆ ካልሆነ በስተቀር ከሃገራዊ እርቅ ጋር ዝምድና የሚኖረው አይደለም። ዘረኛ ስርዓት ከመወገድ ባነሰ የሚሰጠው ዕድል አይኖረውም። የስርዓቱ አራማጆችም የሚሉት እኛ ካቃተን ጥለን መሄድ ነው እንጂ፤ የኛ ፐሮግራም ስራ ላይ ከማይውልበት ውልም ሆነ ስምምነት የምንደርስበት ምክንያት አይኖርም ነው። ለነገሩማ ከትግራይ ሕዝብ ነጻነት ግንባር (TPLF) ጋር ልደራደር የሚል ሃይል ቢኖር፤ ድርድር የሰጥቶ መቀበል ጉዳይ ነውና እንግዲህ ለTPLF ከዘረኝነቱ ጥቂትም ቢሆን ሊተውለት ይገበል ማለት ነው። ይህን ማድረግ ይቻላል? ያለበለዚያ የTPLF ስርዓት የህልውናው መሰረት የሆነችው ዘረኝነት ከተናደች እንደጭስ በንኖ እንደሚጠፋ እሱም እኛም በወግ እናውቀዋለን። ገለሰቦችም ሆንን፤ ድርጅቶች ተቃዋሚዎች እራሳችን የተናገርነውን እራሳችን መልሰን ከማዳመጥ ቆጠብ ብለን TPLF የሚለውን ልብ ብለን እናዳምጥ፤ TPLF በውድም ሆነ በግድ መደራደር የሚባለውን ነገር ይሞከረዋል ብላችሁ አታስቡ። እኔ አንድ ጊዜም እንኳን በምርጫ ብሸነፍ አገሪቱ ትበታተናለች ሲለን፤ እንዲገባን የሚያስፈልገው አንድ ነገር ብቻ ነው። ገፍቶ ሲመጣብኝ አጥፍቼ እጠፋለሁ ማለት ነው ። በፈለጋችሁት አቅጣጫ አገላብጣችሁ ተርጉሙት ሌላ ጠብ ሊል የሚችል ትርጉም አይገኝም። በዚህ አልስማማም የሚል ካለ፤ አንተ ካልገዛኸን መበታተናችንን እንዴት አወቅኸው ብሎ ጠይቆ መልሱን ያደርሰን ዘንድ አደራ እላለሁ። በዚህም የሚከተለውን ማስታወሻ አስመዝግቤ ልሰናበት፤

ሀ. ባሁኑ ጊዜ በዚያም ሆነ በዚህ፤ ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ የሃገራዊ ዕርቅን ጉዳይ በሚያነሱ ብዙ ወገኖች እንደምሳሌ ተደርጎ በተደጋጋሚ የሚጠቀሰው የደቡብ አፍሪካው የዕውነትና የእርቅ ደርግ „Truth and Reconciliation Commission“ የሚባለው ነው። ምሳሌው ለኢትዮጵያም ግብአት ይኖረዋል ከተባለ ክፋት አይኖረውም። መታወቅ ያለበት ግን፤ ይህ ደርግ የተቋቋመው የአፓርታይድ ስራዓት ተወግዶ የሃገራዊ አንድነት መንግሥት ተመስርቶ በዚህ ሃገራዊ አንድነት መንግሥት በራሱ አነሳሽነት ጭምር የተቋቋመ ደርግ መሆኑን ነው።

ለ. ሌላው በምርጫ ዘጠና-ሰባት ወቅት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ሕብረት (ኢዴሃሕ) ለሕዝብ አቅርቦት በነበረው አማራጭ ሰነድ „…የኢሕአዴግ መሪዎች በሕዝብ ትግል ከጥፋት ሂደታቸውና ይዞታቸው እንዲገቱ ከተደረገ በሁዋላ፤ አንድ የዴሞክራሲያዊ ሽግግር አገር-አቀፍ ጉባዔ“ ያስፈልጋል ካለ በሁዋላ የጉባዔው ተካፋይ ስለሚሆኑት የህብረተሰብ ክፍሎችንም በዝርዝር አስቀምጦ፤ „አገራችን ወደ ዴሞክራሲያዊና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት እናሸጋግር ካልን የዚህ ሃላፊነት በዚሁ ጉባዔ ለሚመረጥ „የዴሞክራሲያዊ ሂደት (ዴሞክራታይዜሽን) ኮሚሺን“ ይተውና „ትርጉም ያለው ብሔራዊ ዕርቅ ወርዶ የተረጋጋ ሕብረተሰብ እውን ለማድረግ ደግሞ በዚሁ ጉባዔ የሚሰየም የብሔራዊ ዕርቅ ኮሚሺን እንደሚያስፈልግ ….“ በማለት ያስቀመጠውን ስንመለከት፤
ቀደም ሲል በቁጥር „1 የተመረጠ መንግሥት ቢቋቋምም እንኳን ….“ በሚል ካስቀመጥኩት ጋር ስለሚጣጣም􏰀 ሀሳቤ ቢያንስ በምሳሌዎቹ ዙሪያ የቆሙትን ወገኖች አወንታዊ ምላሽ እንደማያጣ እምነት አለኝ።
ሰላማዊ ጊዜ ይታዘዝልን
ashebir@t-online.de


The post ሀገራዊ (ብሔራዊ) ዕርቅ በኢትዮጵያ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>