ሰናይ ገ/መድህን
ኤርትራዊያኖች አማዉቱና ብለዉ የሰየሙት ታሪክ አላቸዉ፡፡ኤርትራ ነፃ አገር ከሆነች በሁዋላ የአፍላነት ወግን የወረሰዉ የአዲሱ ትዉልድ ታሪክ ነዉ፡፡ የብሄራዊ አገልግሎት አባላት ታሪክ፡፡ እንዲህ ነዉ፡፡
ህግሓኤ መላዋን ኤርትራ ተቆጣጥሮ ጊዚያዊ መንግስትነቱን ካወጀ በሁዋላ (ለነገሩ አሁንም ከሀያ ሶስት ዓመት በሁዋላም ጊዚያዊ ነዉ የሚባለዉ) ከመጀመሪዎቹ አዋጆች የብሄራዊ ዉትድርና አገልግሎት አዋጅ ነዉ፡፡( ያገሩን ወጣት ሁሉ ለመሸከፍ ምን አጣደፈዉ ግን ወገኖቼ;! የሚሰጋበት ነገር ወይንም ያሰበዉ ነገር ነበረዉ፡፡) ሆነናም እነዚያ አፍላ ወጣቶች በነፃነትን ዘፈን ጨፍረዉ ሳይጠግቡና የአገሪቱን የወደፊት የፖለቲካ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዞ ሳይመላከቱ በህግሐኤ ማርቼዲስ
ሸዊት እየተጫኑ ወደ ሳዋ ወረዱ፡፡ ጫካ መነጠሩ የበረሀን የሰራዊት ኑሮ ጀመሩ፡፡ (ብታምኑም ባታምኑም ብሄራዊ አገልግሎት ተብለዉ ወርደዉ መመለሻዉና መሹለኪያዉ ጠፍቶባቸዉ ደንዝዘዉ በዉትድርና ሀያኛ ዓመታቸዉን የደፈኑ አሉ፡፡ አንዱ የአጎቴ ልጅ ነዉ፡፡ ከአንደኛ ዙር! ጀምሮ እስካሁኑዋ ሰዓት ከስር ከስር የሚተካዉን አገልግሎትማ ቤቱ ይቁጠረዉ፡፡10ሺ ከወረደ ግማሹ እግሩ ወደ መራዉ አገሪቱን ጥሎ ይሰደዳል ቀሪዉ እዛዉ ይገላበጣል፡፡ ከቀናዉ ቤቱ ሄዶ በዛዉ ይቀራል፡፡ በአፈሳ አስኪያዝ፡፡ ታዲያ ሳዋ መግቢያዉ ሰፊ መዉጫዉ እንደመርፌ ቀዳዳ ጠባብ ነዉና ሲወርዱ መቼ እንደሚመለሱ ስለማያዉቁ የስንብቱ ነገር አይጣል ነዉ፡፡ በዚህ ጠንቅ ነዉ ሲጠፉም ለሞት ደንታም የሌላቸዉ፡፡ እነሆ የባህር ዓሳ እራት የሚሆኑት በየበረሀዉ ወድቀዉ የሚቀሩት ከኢትዮጵያዉያን ወገኖቻችን ጎን በአረመኔዎች ቢላዋ እንደ በግ የታረዱት፡፡ ከፊት ሞት ከሁዋላ ሞት መሆኑን ካወቁ ሰነበቱና ፡፡ አሁን ሰላሳኛ ዙር አልፉዋል መሰል;) አጃኢብ !
የመጀመሪያዎቹ ብሄራዊ አገልግሎት ወጣቶች ታዲያ ያልጠበቁት ነገር ነበር የገጠማቸዉ፡፡ ከነፃነት በሁዋላ የጥይት ድምፅ አይሰማባትም የተባለችዉ ኤርትራ ሸማቂ ታጣቂዎች ወጣ ገባ ማለት መጀመራቸዉ በመሰማቱ ፡፡እፎይታ ለናፈቀዉ የኤርትራ ህዝብ ሁኔታዉ አስደንጋጭ ነበር፡፡ ከወደ ሱዳን ድንበር በኩል መሆኑ ደግሞ ያልተጠበቀም ይመስላል ፡፡ የሆነ ሆኖ ከስልጠና በሁዋላ አብዘኛዎቹ ወጣቶች ወደ ዳግመ ግንባታና ሰላማዊ አገልግሎት ግዳጅ ፈፅመን በዚሁ ተገላግለን እንመለሳለን ያሉት ወጣቶች ከሽምቅ ተዋጊዎቹ ጋር ሊፋጠጡ ግድ ሆነ፡፡ አንዳችም የጦርነት ልምድ ባይኖራቸዉም እስኪ እጃቸዉን በዚህ ያሙዋሹ ብሎ የተፈረደባቸዉም ያስመስላል፡፡ በቃ የድንበር ጥበቃ ላይ ተሰማሩ እጃቸዉ ከቃታ ዋለና ወደ ሱዳን አማተሩ፡፡ መስዋዕትነትን ለመክፈልም ዝግጁ !፡፡
ይህ አልፎ አልፎ የተሰነዘረዉ የሸማቂዎቹ ጥቃትና ሰዶ ማሳደድ ዉጊያ የኤርትራዊንን ህይወት እንደገና መቅጠፍ ጀመረ፡፡ ያልተጠበቀዉ መስዋዕትነት ሌላላም አስገራሚ ሁኔታን አስከተለ፡፡፡ ይሄዉም በተለያዩ አጋጣሚዎች በታጣቂዎቹ ከተገደሉት ኤርትራዊያን የሰራዊት አባላት መካከል አብዛኛዎቹ ታጋዮች የመሆናቸዉ ጉዳይ፡፡ እንዲሁም ሸማቂዎቹ ወጣት ብሄራዊ አገልግሎቶችን አይገደሉም የሚገድሉት ታጋዮችን ብቻ ነዉ የሚለዉ ወሬ መናፈስ ያዘ፡፡ እንዲህ ዓነት አጋጣሚም ደርሱዋል ይባልም ጀመር፡፡ እንደሚታወቀዉ የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት በነባር ታጋዮችና ወጣት ብሄራዊ አገልግሎት አባላት የተዋቀረ ነዉ፡፡ ሸማቂዎቹ ከዚህ ሰራዊት ዉስጥ ታጋዮችን ብቻ እየመረጡ የመግደላቸዉ ሁኔታ በርግጥም ታጋይ ሀላፊዎችን በጣም ያሳሰበና ያበሳጨ እንደሚሆን መገመት ይቻላል፡፡ ታጋይም ይሁን አገልግሎት እንዲሰዋበት ለማይፈልገዉ የኤርትራ ህዝብ ደግሞ ሰቀቀን መሆኑ አይታበልም፡፡ሁለቱም ልጆቹ ናቸዉና፡፡ ሸማቂዎቹ ታጋዮችን ብቻ ነጥለዉ ለምን ይገድላሉ; ለሚለዉ ጥያቄ ምላሹን ለነሱ እንተወዉ፡፡ ለመሆኑ በዉጊያ መሀልስ ወይንም በደፈጣ ታጋዮችን እንዴት መለየት ቻሉ? የኤርትራ ታጋዮች ሀላፊዎች ቁጭ ብለዉ መከሩ; እናም በቀላሉ ደረሱበት፡፡ የታጋዮቹና ብሄራዊ አገልግሎቶቹ ወታደራዊ ልብስ ቀለም የተለያየ ነበር፡፡ አስቸኩዋይ የዉሳኔ ሀሳብ አስተላለፉ፡፡ ከጥቂት ወራት በሁዋላ ለጥቃት የተሰማሩት ሸማቂዎች ታጋዮችን መለየት አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት አባላት ታጋዮችም ብሄራዊ አገልግሎቶችም አንድ ዓይነት ወታደራዊ ልብስ መልበስ ጀምረዉ ነበርና ነዉ፡፡እናም ሸማቂዎቹ በጅምላ ጥቃት ለመሰንዘር ተሰማሩ፡፡ የተተኮሰ ጥይት ደግሞ ለይቶ አይገድልምና ሁሉም ለጥቃቱ ሊጋለጡ ግድ ሆነ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ብሄራዊ አገልግሎቶች ያን ወታደራዊ ዩኒፎርም ‹ አማዉቱና › ሲሉ ሰየሙት፡፡c
ማያያዣ አቦይ ተስፎም ይባላሉ፡፡ እኚህን ሰዉ ሁሉም ኤርትራዊ ያዉቃቸዋል፡፡ ሀያ ሶስት ዓመት ሙሉ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሲዋሹ ያዉቃቸዋል፡፡ ከሰማይ መና ይወርድልሀል ከሚለዉ የዳቦ ዘመን ዉሸት በቀር ስለ ህገመንግሰት ምርጫ ዲሞክራሲ ልማት ብልፅግና እድገት ሰላም ዳጎስ ያለ ደሞዝ …. ስጥ እንግዲህ በሉት ወይንም ረግጠዉታል፡፡ ዓይናቸዉን በጨዉ አጥበዉ በየጊዜዉ እንዳዲስ ይተረተራሉ፡፡ ረገጣዉ ኤርትራዊያንን ብቻ አይደለም፡፡ ኤርትራ ገብተዉ የወንድ በር መዉጫ ላጡና እንዲገቡ ለሚፈልጉዋቸዉ ኢትዮጵያዉያን ሁሉ ነዉ፡፡ታዲያ ፊዳ ሊያደርጉ ያሰቡትን ሲረግጡ ምን ደስ እንደሚለዉ ቀድመዉ አጥንተዉ በሳቸዉ የጨዋ ቁዋንቀዋ ይተረተራሉ፡፡ ዉስጣቸዉ ባያምንበትም ፊዳቸዉን ለመጣል ሲሉ ይምላሉ ይገዘታሉ፡፡ይሄዉ አሁን ከኢትዮጵያዉያን ጋር ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ተሙዋጋች ሆነዉ የለ! የእሳቸዉ ባይገርመንም ከእኚህ የዲሞክራሲ ሾተላይ ሰዉ ጋር ማዕድ እየተቁዋረሱ ከበሮ እየደለቁ ያሉት ወገኖቻችን ጉዳይ ግን አጃኢብ ብቻ አሰኝቶ ዝም አላሰኘንም! ጎበዝ ሹምባሽነት ሲለምድ ደግ አይደለም፡፡ እናም እኚህን ልብ አዉልቅና የህዝብ ጦስ (ለቃሉ ይቅርታ) ኤርትራዉያን አቦይ ተስፎም ( አቦይ ተስፋይ ) !! ሲሉ ስም አወጡላቸዉና እዚያዉ በጠበልህ ሞኝህን ፈልግ አሉና ረግመዉ ከነበሩበት የክብር ቦታ አዉልቀዉ ወረወሩዋቸዉ፡፡አንዳንድ ኢትዮጵያዉያንን ግን አሁንም ማማለል ብሎም ማጃጃል ቀጥለዋል፡፡ ጉድጉዋቸዉ የተማሰዉ ልጣቸዉ የተራሰዉ እሳቸዉ ኢሳያስ አፈወርቂ !
‹ አማዉቱና !›
እኚህ አዛዉንት አሁንም ግድብ እያሰሩ ነዉ አሉ! ወይንም በቅርብ አመራር እየሰጡ ነዉ ፡፡ ሙያተኛ ስለማያምኑ ይሆን ; አዎና 23 ዓመት ሙሉ እየነደፉ እየቀየሱ ቆመዉ ያሰሩዋቸዉ( (እሳቸዉ የሁሉም ሙያ ባለቤት ናቸዉና) የገርሰት ግድብ፡ በወታደራዊ ኮሎኔሎች ከህንድ ተገዝቶ የተተከለዉ የአፊምቦል ስኩዋር ፋብሪካና ሸንኮራ አገዳ እርሻና ፡ የቲማቲሙ ማሸጊያ ፋብሪካ፡የሀይኮታ ሙዝና ቲማቲም ማሸጊያ ፋብሪካ የምፅዋ ባህር ልማት ፕሮጀክት፡ ከድባርዋ እስከ አዲኩዋላ የሚገኘዉን የጤፍ እርሻ መሬት ከግል አርሶአደሮች ወርሰዉ በወታደሮች ትራክተር ያሳረሱት እርሻ፡ ለቢራ ፈብሪካ ብቅል ታስቦ ከአስመራ ዙሪያ አርሶአደሮች ተነጥቆ የታረሰዉ የገብስ ምርት ዘመቻ ተዘርዝረዉ የማያልቁት በአረቄ መራሽነት የተነደፉት የባነኮኒ ላይ የቁም ፕሮጀክቶቻቸዉ የመሳሰሉት በሲአይኤና አሜሪካ ሴራ መክነዉ ባክነዉ ስለቀሩ አሁን ግን እዚያዉ በሙሉ ጊዜ ቆመዉ ማሰራት መርጠዋል አሉ፡፡ ምን ያድርጉ የረባ ባለሙያ የለማ! ማንን ሊመሩ ፕሬዚዳንት ይሆናሉ; ሰዉ ሁሉ ወጣ፡፡ በህግደፍ እየተገፉ ከገበያ የወጡትን የግል ኢንቨስትመንቶችና ባለሀብቶችንማ ቤቱ ይቁጠራቸዉ ፡፡ በተለያዩ አፍሪካ አገራት ስኬታማነታቸዉ ይመስክር፡፡ ወጣቱ አዛዉንቱ የቀድሞ ታጋይ ሴቱ ህፃናቱ ከሁዋላዉ በጥይት እያስደበደቡትም መዉጣቱን ቀጥሉዋል፡፡ በዘመነ ደርግ ከነበረዉ ኤርትራዊ ስደተኛ በላይ በድርብ ድርብርብ እጥፍ በበረሀና ባህር እየፈለሰ እየሰነጠቀ የአሳ እራት እሆነ ነዉ፡፡የህግደፍን ዘመነ ርግማን ሽሽት፡፡ እሳቸዉ ግን የተረገመች አሜሪካ ሰዉን አጋዘችዉ ይላሉ፡፡ እናም በቃ ሙያ መቀየር ፈለጉ ማለት ነዉ፡፡ ሰንበትበት ብለዉም የፓትሪርክ ካባ ደርበዉ ብቅ ይላሉ፡፡ ምን ጣጣ አለዉ! አንድ ለናቱ እሳቸዉ ብቻ ናቸዉ ያሉት፡፡ ለነገሩ በፅህፈት ቤታቸዉ ዉስጥና ዙሪያ የሚዘዋወረዉ የዕልፍ አዕላፍ ንፁሀን ህይወትና ጣዕረ ሞት ስለሚያባንናቸዉ ደጅ ደጁን ቢሉ አይገርምም፡፡
ኢሳያስ የዚያን ወራት ከከተማ ወጥተዉ የከተሙበት ጉዳይ ነገሩ ወዲህ ነበር አሉ፡፡ ከዉስጥ እንደሰማሁት፡፡ እንደተለመደዉ ከዉጭ ሀይሎች ደጎማ ተጥሎላቸዉ የዉጭ ታጣቂዎችን እያሰተናገዱ ነበር አሉ፡፡ ለእኛ አዲስ አይደለም፡፡ በኤርትራ ቆላማ በረሀዎች በርከት ያሉ ፀጉረ ልዉጦች እየገቡ ሲርመሰመሱና ታጥቀዉ ሲወጡ እናዉቃለን፡፡ አሻ ጎልጎል በሚገኘዉ የመንግስት ጋራዥ ዉስጥ አናትና ወለላቸዉ ላይ ለተተኩዋሽ መሳሪያዎች በሚመች መልኩ ተቆርጠዉና ተቀጥለዉ ባህርተሸግረዉ የተጉዋጉዋዙት ቶዮታዎች የት እንደዘመቱ ! ዝርዝሩ ይቆየን፡፡ እናም በግድብ ስራ ስም ሰዉየዉ ሌላ ጉዳይ ይገድቡ ነበር ነዉ የተባለዉ፡፡ የዚያን ሰሞኑ ያልታሰበ የሳዑዲ ጉዞአቸዉ ስለዚሁ ጉዳይ ለመናዘዝ አይሆንም ትላላችሁ? መቼም ሳዑዲአረቢያ ኤርትራን በአይነቁራኛ እንደምትጠብቅ አይጠፋንም!
…………
የአያሌ ፀያፍ ታሪክ ባለቤትና (ሚኒሰትሮቻቸዉን በየቢሮአቸዉና ስብሰባ ላይ መሳደብና ማንቁዋሸሽ፡ ከበረሀ ጀምረዉ ይዘዉት የመጡትን በሀላፊዎች መካከል ሀሜት መንዛትና በበታቾች ፊት የማዋረድ ልምድ(አሁን በእስር ላይ የሚገኙት የትግል አጋሮቻቸዉ በመጨረሻ ሰዓት ከደራሲ ዳን ኮኔል ጋር ባካሄዱት ቃለመጥይቅ እንደተነተኑት) ፡ የሰዉ ሚስት ማማገጥ፡ ከዳንኪራ ቤቶች አይናቸዉ ያረፈባትን ልጃገረድ መንጠቅ፡(መስካሪ የማያሻዉ ባህሪያቸዉ) ሲዞሩ ካመሹበት መሸታቤት በስካር መንፈስ እየጋለቡ ሄደዉ በግፍ ያሰሩዋቸዉ የትግል አጋሮቻቸዉ ላይ መትፋትና መሳደብ፡(እማኝ የእስረኞች ጠባቂ) በተለያዩ ሙያ ጎላ ብለዉ የሚወጡ ዜጎችን ማሳፈን ማስገደል.. አርቲስት አብርሃም አፈወርቂ፡ የኦሞ ፋብሪካ ባለቤት መሀመድ፡ ፍቅረና ሌሎችንም ባለሀብቶች..ነባር ታጋዮች) እንዲሁም የማይጨበጥ ስብዕና ስላላቸዉ እኚህ ሰዉ ጉድ ተዘርዝሮ አያልቅምና ዉስጥ አዋቂዎች ይቀጥሉበት፡፡
እኛ እኚህን የኤርትራና ኢትዮጵያ ህዝቦች አይበጄ ሰዉ ከቶዉኑ ዳግም ላይሸነግሉን ‹ይአክል!› ‹በቃ› ብለናል፡፡ ለባለተራዎችና ‹ የእባቡን ተናዳፊነት ለማረጋገጥ መነደፍን › ለመረጡ ዉርድ ከራሴ! በነገራችን ላይ ‹የአማዉቱና › አባወራ የሆኑት ኢሳያስ ወያኔን ለመገልበጥና ስልጣን ለመቆናጠጥ እስከረዱን ድረስ ስለ ግፉአኑ የኤርትራ ህዝብ ጆሮዳባ ልበስ ማለትና ከኢሳያስ ጎራ መጨፈር በኤርትራ ህዝብ ዋጋ መቆመር በስቃዩ ላይ መረማመድ አይሆንምን? ወገናችን የሚሉት የኤርትራ ህዝብ እንደሚታዘባቸዉ ዘነጉት ይሆን? ታሪካዊና ዘላቂ ወገናዊነቱን መክሰርስ አይደለምን; ህዝብንጂ ነዋሪ መንግስታት ተለዋዋጭ ናቸዉና ዛሬ ከኢሳያስ ጋር የሚወዳጁ ኢትዮጵያዉያን ሀይሎችን የኤርትራ ህዝብ የስልጣን ባለቤትነቱን ሲያረጋግጥ እንደምን ደፍረዉ ያዩት ይሆን? ብዙ ብዙ የትዝብት ህፀፆችን ታሪካዊ የሚባሉ እንከኖችን መምዘዝ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ለመሆኑ ለሳደጋቸዉ የኤርትራህዝብና ለትግል አጋሮቻቸዉ ከሀዲና የግፍ ባለሙዋል የሆኑት ኢሳያስ ለኢትዮጵያና ህዝቡዋ እንደምን መልዐክ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል? የኤርትራና ኢትዮጵያ ህዝቦችን መፃዒ ሰላማዊና የፍቅር ግንኙነት የምትተነብዩ አርቆ አሳቢ ወገኖች ስለሁለቱም ህዝቦች የሚበጀዉን በሉ፡፡ ኢሳያስ ግን አሁን አንዳንድ ኢትዮጵያዉያን ተቃዋሚዎችን በአፍም በእጅም እየሸነገሉ ያሉበት ኩነት በዙሪያቸዉ አከማችተዉ ለአማዉቱና ታሪካቸዉ አያዘጋጁ መሆኑን ኤርትራዉያን ይገነዘባሉ፡፡ ምክንያቱም ከንግዲህ ከየትም ይምጣ በኢሳያስ ላይ አንዳች ዉርጅብኝ ከተሰነዘረ እንደ ባድመዉ በሉዓላዊነት ስም ቆሞ የሚዋጋላቸዉ ኤርትራዊ እንደሌለ አሳምረዉ ያዉቃሉና፡፡
እንደትዝብቴ የኤርትራ ህዝብ ኤርትራ ዉስጥ ገብተዉ በሚንቀሳቀሱ ኢትዮጵያዉያን ላይ ቅሬታ የለበትም ፡፡ ጣቱን የሚቀስረዉ የኢሳያስን አስከፊ አገዛዝ ና ዕድሜ ለማራዘም ከህግደፍ ጎን በሚወግኑና ጠባቂዉ ሹምባሽ (ጣልያን ለባንዳዎች ይሰጥ የነበረዉ ማዕረግ ) በሚሆኑት ላይ ነዉ፡፡ ይህ ታሪካዊ ስህተት ይመስለኛል፡፡በሁለቱም ወገን የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ወገኖች የሁለቱን ህዝቦች ዘላቂ ዝምድና በሚያበላሹ ይህን መሰል ጊዚያዊ የጭፍን እርምጃዎችን ሊገቱ ይገባል፡፡ስለ ኢሳያስና ስርዓታቸዉ መመስከራቸዉንም ሀፍረት ጣል ቢያደርጉበት መልካም ይሆናል፡፡ከባለቤቱ ወዲያ አዋቂ…ወይንም ‹ብዘመነ ግርምቢጥ ማይ ንዓቀብ !ያስብላልና፡፡ እናም የኢሳያስን ጉዳይ ለግፉዓኑ ተዉ ወይንም ከተገፉት ጎን ቁሙ፡፡ ‹የሱን ለሱ የጲላጦስን ለጲላጦስ› እንዲሉ! ብሎም ከኢሳያስ ጋር ሆነዉ የኤርትራን ህዝብ ወገናዊነትና ልብ እናገኛለን ብለዉ የሚያስቡ ወገኖች ቆም ብለዉ ቢያስቡ መልካም ይሆናል፡፡ ምክክራቸዉም ከህግደፍና ተላላኪዎቹ ጋር ሳይሆን ከአብዛኛዉ የኤርትራ ህዝብ ጋር መሆን ይኖርበታል፡፡ የኢሳያስ ህግደፍ ከኤርትራ ህዝብ የኢምንቶች ከባቢያዊ ቡድን ስብስብ ስለመሆኑ አከራካሪ ባለመሆኑ ይህንኑ አበክረዉ ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ ኢሳያስ የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የኤርትራ ህዝብም ጠላት እንጂ ወዳጅ ከቶዉንም ስላለመሆኑ አሁን እንዳዲስ መደናቆር የሚያሻን ወቅት አይደለንምና፡፡
ለኤርትራና ኢትጵያ ህዝቦች እዉነተኛና ዘላለማዊ ፍቅር በርትተን እንቁም!
ሰላም እንሰንብት! ከአዉስትራሊያ፣ ሜልበርን
The post “አማዉቱና!” አሙዋሙቱን (አብረን እንሙት) ሠናይ ገብረመድህን ዮሀንስ (ጋዜጠኛ) appeared first on Zehabesha Amharic.