02.05.2015 /ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ/
ይድረስ ለፓን አፍሪካኒስቱ ወገኔ ለተከበሩ አቶ ቴወድሮስ ዳኜ –
„እንዳላፍር ልቤ በሥርዓትህ የቀና ይሁን“ / መዝሙር ምዕ. 118 ቁ. 80/
„እንዳያመም ጥራው እንዳይበላም ግፋው“
በቅድሚ እንዴት ሰነበቱ። ለአፍሪካውያን የስደትና የሰቆቃ መከራ የበኩለዎትን ድርሻ ለመወጣት በማድረግ ላይ ያሉትን ዬሰብዕዊነት ጥረት አብዝቼ አከብራለሁ፤ ኢምንት ብሆንም አመሰግናለሁ። ከመልካም ነገር ፍቅርና ተስፋ መኖርና መሆን አሉና።
እኔ ብዙን ጊዜ የኢትዮጵያ ሙሑራን በሰብዕዊ መብት እረገጣ፤ በዘበጠ አስተዳደር ጉዳይ ላይ ያላቸው ተስትፎ አናሳ ነው፤ የበቃም አይደለም በማለት ወቀሳን ከወገኖቼ ሳዳምጥ የአያያዝ አቅም ከሙሁራዊ ሥነምግባር ውስጠት ጋር የማጣጣም ብቃት አንሶን ሊሆን ይችላል የሚል ዕድምታ ስለነበረኝ ምንም ብዬ አላውቅም። ዛሬ ግን ተናጠሉን ሙሁርነት ብቻ ሳይሆን እንደ ቀደምቶቹ ኢትዮ – አፍሪካውያን ዕንቁዎች መስመሩን ለመከተል መቁረጥ ብቻ ሳይሆን ተግባር ላይ በተገኙት ወንድሜ ላይ ቅሬታዬን ከዕንባዬ ጋር ልልክለው እንሆ ወደድኩኝ። ሃዘኔ የምር ልቅሶዬም ከቁስለት – የተቀዳ ነው።
ውድና የተከበሩ ኢትዮ አፍሪካዊው አቶ ቴወድርስ ዳኜ – ጎሰኝነት ወይንም መንደርተኝነት ያልተመጣጠነ የአስተሳሰብ እድገት ወይንም የአስተሳሰብ ድህነት ጽንስ ነው። እድገቱም ከቤተሰብ ቀጥሎ ያለ ስለሆነ ሁለመናው በእንጭጭ ዕጭ ተፈጥሮው ላይ ስለሚወሰን አህጉራዊ ኃላፊነትን በተቆርቋሪነት ላበሰለ ወገን፤ በወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ አሳሯን በመክፈል ላይ የምትገኘው ልዕልት ኢትዮጵያና ልጆቿ ጉዳይ ከማንም በላይ ከፍ ካለው አህጉራዊ መንፈስ ላለው አብነት እኩያው አይደለም። ምስክርነት ለመሰጠትም አቻው አይደለም። … በማናቸውም የወያኔ ሃርነት የጎሳ ሶሻሊስታዊ ፖሊሲ ሰብዕነትን በይ – አህጉራዊው አምክንዮ ጋር ለመወዳጀት እድገቱም አይፈቅድም። አህጉርና -ጎጥ?! እንዴት ግን ግጥመወትም ቅኔዎትም መሆን ይቻል?! ለክብሩነተዎት የወያኔ ሃርነት የጎጥ ማንፌስቶ መንፈስ አይመጥነዎትም – በፍጹም እንደ እኔ። ልዩው ጸጋዎት ሊጸዬፈው ይገባል መንደር ላይ የተተከለው የመርዝ ማንፌስቶ። ክብሩነተዎት ላቅ ብለው – ለግለግ ብለው – አፍሪካ ላይ ያሉ ሲሆን፤ ዬኢትዮጵያ ዘረኛ ጸረ ሰብዕ፤ ፀረ አብሮነት፤ ጸረ ፍቅር፤ ጸረ ታሪክ፤ ጸረ ትውፊት፤ ጸረ ሰንደቅዓላማ አስተዳደር ደግሞ ደረጃው አሰር ውሃ ላይ ስለሆነ ቁጭ ብሎ ለመነጋገር እንኳን ዳገት ነው። እንኳንስ ጠበቃ በመሆን ሸማ ማልበስ ይቅርና ….
የተከበሩ ፓን አፍሪካኒስቱና የአፍሪካ ህይወት ከፍተኛ ባለሙያ ሆይ! – የቅድመ ምርጫ መሰናዶ ዕይታዎትን ቃለ ምልልስ አዳመጥኩት – እጅግ በተመስጦ። እንደሚመለከቱት ንዑስ እርእሱን ሲያዩት የሰጡትን ቃለ ምልልስ ጋር መስመረኛ እንደሚሆን – አስባለሁ። የብሄራዊ ዜግነት መፍጫ፣ የማንነት መቅጫ የሆነው የወያኔ ሃርነት ትግራይ የምርጫ ልጋጫንም ንዑስ እርእሱ አሳምሮ ይገልጠዋል ብዬም አስባለሁ። ስለዚህ ንዑስ እርሱ ድርብ ሚናን ተሸክሞ ነው ጉዳዩን አህዱ የሚለው። ከኢትዮጵያ ሀገራችን በስተቀር አፍሪካ ሀገሮችን በሚመለከት ባለበዎት የሥራ ኃለፊነት ምክንያት በቅርበት እንደሚከታተሉት ብቻ ሳይሆን የሰጡት አስተያዬትም የውጭ የዜና አውዶች በተለይም „ሰው“ የሚለውን የሁለመና ፍጥረት ልዑቅ ጸጋ እንደሚያከብሩት ወገኖችና የሚዲያ አውታሮች ከሚሰጡት ጋር መሳ – ለመሳ ስለሆነ ውስጥወት ስላደረጉት አልሄድበትም። ትክክል – ነውና።
ገለፃዎትን ሁለመናዬን በፍቅር ሰጥቼ ነበር የተከታተልኩት። እንጃ „ክርስቶስ ለሥጋው አደላ“ ሆኖበዎት እንደሆነ አላውቅም የእትብትዎትን፣ የደመዎትን ጉዳይ በሚመለከት የሰጡት አስተያየት ግን እጅግ የሚያሳዝን ድርብ በደል ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ድርብ በደል የሚያደርገው እንደ አፍሪካውያን ስደተኛ ተቆርቋሪነተዎትና የፋውንዴሽን መሥራችነተዎት፤ እንዳ ዓለምአቀፉ የማህበረሰብ ድምጽ ሚዛን ዕይታ ዳኛነተዎትና ኃላፊነዎት በሳል ተመክሮ፤ እንደ የግል ሥያሜ መጠሪያዎት ሚስጢራዊነት ወይንም የመንፈስ ቅዱስ መንፈስ ጠብታ ረቂቅነት „ሥምን መላዕክ ያወጣዋል“ እንዲሉ „ቴወድሮስ ዳኜ“ በእናት ሀገራችን በኢትዮጵያ የወያኔ ሃርነት ትግራይ የ2007 ምርጫን አስመልክቶ ብቻም ሳይሆን፤ የሰብዕዊ መብት ረገጣ፣ የሌሎችን የዘመናዊ ባርነት ጨካኝ አስተዳድር ያልሰለጠነ – እምቅ የበቀልና የቋሳ ማወራራጀ በሆነው ወገነዎት ላይ የደረሰው መከራን በሚመለከት የአፍሪካ ሀገሮችን ያህል ተቆርቋሪነት ወይንም ቅርበት ወይንም የእኔነት መንፈስ በቃለምልልሱ እንብዛም አላደመጥኩም። ቃናው ባዕዳዊ ሆኖ አግኝቸዋለሁ ስለዚህም ከፍቶኛል። ከሁሉ በላይ ሄሮድስ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ ለማለት ይጸዬፉት ነበር። „ሀገሪቱ፣ እዛ በነበርኩበት ጊዜ እያሉ“ የገለጹት በቀጥታ መጤ እንደራሴ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። በተጨማሪም „ጠንካራ ተፎካካሪ የለንም“ ያሉትን የሄሮድስ መለስ ዜናዊ የትበት ቅላጼ እርስዎ በመድገም „እነሱ ያቀረቡት ቪዥን የተሻለ የሌላቸው፤ በመጨቃጨቅ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉ፤ መዋቅራቸው ሥር ሰደድ ያልሆነ“ በማለት በሄሮድስ መለስ አቃላይ – አጣጣይ – አገላላጽ ሥር የወደቀ የመንፈስ ተጠቂ የሆነ አገላለጸዎት ከፈኝ ከምል ከረፋኝ ብል ይገልጠኛል። ከእርስዎ በፍጹም ሁኔታ የማልጠበቅው – ስለነበር።
በቃለ ምልልሱ ላይ መንፈሱ ቁስል ያለው ጋዜጠኛ፤ ጋዜጠኛ ሰለሞን አባተ ክቡርነተዎት እዬተናገሩ እሱ ማህል ላይ የገባበትን እንዲሁም ክቡርነተዎት ድምጸዎትን ቀነስ አድርገው የገለጹት ብቻም ሳይሆን፤ ዝንቅ በሆነው የሁለት ቋንቋ ምላሽዎት የልተደመጡኝ ጥቂት ነገሮች ሲቀሩ በስተቀር መንፈሱን ሙሉውን አቅርቤዋለሁ። ለነገሩ ያልተደመጠኝ ከምፈልገው ነጥብ ላይ ባለመሆኑ እምብዛም አስፈላጊ አልነበረም። የምፈልጋቸውን በቅጡ ለማድመጥ ስለቻልኩኝ። ያው በዝንቁ እንደወረደ እንግሊዘኛውንም አማርኛውንም – በአማርኛ ጽፌዋለሁ። http://www.zehabesha.com/amharic/archives/41765 ታሪክ ነውና ትውልዱ ታሪኩን ማድመጥ – መተርጎም – ማመሳጠር ብቻም ሳይሆን ሚዚናኑን የጠበቀ ግንዛቤ ይኖረው ዘንድ በጥቅሉ ሲያሰፍልግም በተን እያደርኩኝ አቀርበዋለሁ።
ውስጡን ከብዙኃን ዕንባ ጋር ያገባው የተግባር ታላቄ ጋዜጠኛ ሰለሞን አባተ እጅግ እርቀው ከተመሰጡበት ከሌሎች አፍሪካዊ ሀገሮች ውስጣዊ የውስጥነት ጉዳይ መለስ አደረገወትና —- የአፍሪካ ጉዳይ ስፔሻሊስት፤ በተመክሮ የበሰለ ብቃትን እንዲህ ነበር ዬጠዬቀዎት ….
„ …. ወደ ኢትዮጵያ መለስ አልና ለመሆኑ ቴድ በኢትዮጵያ የዛሬ 20 ዓመትና ከዛ በፊት ከነበረው ሁኔታ የዲሞክራሲያዊና የሰብዕዊ መብቶች አያያዝ ፓለቲካው የተሻለ ነው ብለው ያስባሉ አልኳቸው?“ አለ ጋዜጠኛ ሰለሞን አበተ።
„ ይመስለኛል እኔ አክሮስ ኢትዮጵያ ስመለከተው አንዳንድ የነበሩ ጦርነቶች ቆመዋል። ዌስተርን ኢትዮጵያም ቢሆን ወደ ኡጋዴንም በሚመለከት መንግሥት ፍላጎቱን አሳይቷል። ተቀምጠው ለመነጋገር እንደሚፈልጉ፤ ከኡጋዴ ናሽናል ሊቬሬሽን ፍሮንት ጋር፤ ሌላም ቦታ ብትመለከት ውስጥ ብትመለከት ስታቢሊቴ አለ። መንገድ ላይ ሄደህ መታሰር ነገር የለም። ሰው ሥራውን ይሠራል ትምህርቱንም ይማራል። ያ እንደ ፕሮግረስ ብዬ ነው የማዬው ኦፍ ኮርስ ሂዩማን ራይትስ ኦድቦኬት ኦር ተቃዋሚ ኃይሎች ሞር ኖሌጅ ይኖራቸዋል። ስለዚህ እና የእኔ አሰስመንት ከእነሱ አስሰምነት ጋር ሊለያይ ይችላል። ግን እኔ አዝ እንደ ኦርዘርቨር ስመለከተው ኦቨር ኦል ፒክቸሩ ደህና ነው ብዬ ነው የምመለከተው። ኢብን ኮንፒዬር 5 እና ከ7 ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሞር ስቴብል ነው። እራሱ አሁን ለምሳሌ ስትመለከተው ትራንዝሽኑ ፕራይም ሚንስተር መለስ ከሞተ በኋላ ወደ አሁን ወደ አሉት ፕራይም ሚኒስተር ትራንዝሺኑ ፒስፉል ነበር።“ በማለት ካለወታደራዊ ጣልቃ ገብነት በሰላም ተከወነ እንደማለት፤ ቀጠሉ ፓን አፍሪካኒስቱ አቶ ቴወድሮስ ዳኜ „ፕሮግሬስና ማቹሪቲ ነው ያ አይ ቲንክ ቢ …. ማቹሪቲና ፕሮግሬስ ነው ብዬ ነው የምለው። ሌላም …. ምንድነው ኢትዮጵያ ኢሌክሽን ይደረጋል ኢፒዲአርፒ ዶሚነት ነው ግን ይህ ዶሚነት የሆነው አይ ቲንክ ዊ ሹድ ቢ ኬርፉል ኖት የትቱ ብሌሙ ብሎ ኢንተርያሉ የፖለቲካ ስፔሱ ተዘግቷል ኦፖዚሽኑ ሃራስ ይደረጋል ብሎ መገምግም ትክክል አይደለም ብዬ ነው ። የዛሬም 5 ዓመትም እንዳልኩት ኮንግረሱ ጀስቲፋይድ ሲደረግ ተቃዋሚ ኃይሉ ሪስፖንስቢሊቴውን መውሰድ አለበት። ብዙዎቹ ውጪ ነው ያሉት። ብዙውንም ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት እርስ በርሳቸው ሲጣሉ ነው። እነሱ ያቀርቡት ቪዢን ለሀገሪቱ ብዙ የሚታይ የለም። ያዬሁትም የለም። እንዴት ተብሎ ነው ዜን ኢሌክሽን ሲደረግ ለማሸነፍ የሚቻለው የዛ ዊክነስ፤ የዛ ሪዛልት ሁልጊዜ መታዬት ያለበት ኖት ጀስት ተቃዋሚ ኃይሎች እንደሚሉት ሃራስ ተደርገናል ኖ! ሃራስመንት ሊኖር ይችላል“ ጥርጣሬ … „ግን እነሱ ያደረጉት ነገርም ኮንትሪቢዩት አድርጓል አላደረግም ተብሎ መጠዬቅ አለበት?! ….. የዛሬ 5 እና አመት አንዳልኩት አሁንም እላለሁ። ብዙውን ጊዜ የታለፈው እርስ በእርስ ሲጣሉና ማጆሪቲው ደግሞ ውጭ ነው ያሉት። ሃራስ አይደረጉም ለማለት ሳይሆን ኤግዛጁሬት ባናደርገው ጥሩ ነው።“
ቀጠለ ሳተናው ጋዜጠኛ ከውስጡና ከመንፈሱ ጋር ሆኖ „ እህም! ለመሆኑ ከዚህ አጠቃላይ ግምጋሜዎት ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ነፃ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል የፖለቲካ ዝግጅነት ወይንም ተክለ ቁመና አላት ብለው ያምናሉ? ክቡሩ ፓን አፍሪካኒስት አቶ ቴውድሮስ ዳኜ ቀጠሉ „ ዌል! ስትራክቸሩ አለ። ኦርዘርበሮች ይኖራሉ። ሌትራል ኮሚሽኑ አለ የተቃዋሚ ኃይሎች ያላቸውን ኮንፕሌኖች አቅርበዋል፤ ፓብሊክ ላይ በቴሌቪዥን ላይም ወጥቷል፤ እና ፎር ሚ የለም ለማለት አንድ ሰው ኢቢደንስ አቅርቦ ኮንቢንስ እንዲያደርገኝ ያስፈልጋል“
ቀጠለ የመንፈስ ሃብቱን ያልተዘረፈው ሳታናው ጋዜጠኛ „ስለዚህ አለ?“ አቋረጡት ፓን አፍሪካኒስቱና ሙሁሩ ኢትዮጵያዊ „ ዴፊኔትሊ! አለ ግን ብትጠይቀኝ የተቃዋሚ ኃይሉ ጠንካራ ነው ወይ? ተቃሚዊ ሃይሉ ፓርላመንቱ ውስጥ ብዙ ፎከሶች ሊወስድ ይችላል መልሱ አይደለም! ነው። ተቃዋሚ ፓርቲ ነው አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ጠቅላላ በሀገሪቱ ውስጥ የስትራክቸር ከሌለለህ ኮንፒት ለማደረግ ከባድ ነው ለማሸነፍም በጣም ከባድ እዬሆነ ነው የሚመጣው“
ቁስለቱና መግሉ
- „ተቀምጠው ለመነጋገር እንደሚፈልጉ፤ ከኡጋዴ ናሽናል ሊቬሬሽን ፍሮንት ጋር ሌላም ቦታ ብትመለከት ውስጥ ብትመለከት ስታቢሊቴ አለ።“
ኡጋዴ ናሽናል ሊቨሬሽን ፍሮንት ብቻ ነውን ከፋኝ ያለውን? „ስቴብሊቲ“ የሚባለውስ በቀን 500 ዜጋ እዬታሰረ፤ ጋዜጠኞች፤ የፖለቲካ መሪዎች፤ የእስልምና ዕምነት ሃይማኖት መሪዎች፤ ጦማርያን በገፍ እስር ቤት መግባት ብቻ ሳይሆን እስር ቤት ውስጥ፤ መንገድ ላይ ኢ – ሰብዕዊ፤ ኢ – ሞራላዊ ግፍ እዬተፈጸመባቸው፤ ሚሊዮኖች ከመኖሪያቸው እዬተፈናቀሉ፤ ገበሬዎች ከመሬታቸው ተነቅለው መሬታቸው ለሌላ ሀገር ዲታ እዬተቸበቸበ፤ ህጻናት በገብያ እዬተቸረቸሩ፤ እህቶቾዎት ሞትን ጥበቃ ማታ ማታ መንገድ ላይ ተገትረው እያደሩ …. ይህ ሁሉ እምቅ የደም ዕንባ ይሆን „ስታብሊቲ“ የሉን? አይመስለዎት ቀን የሚጠብቅ ፈንጅ ያረገዘ የመረቀዘ የሙት ቀን የሚጠብቅ ነው።
- „መንገድ ላይ ሄደህ ምትታሰር ነገር የለም“
መንገድ ላይ መታሰር አይደለም ሞት ነው ያለው። ዜጎች ወጥተው ለመመለስ እርግጠኛ የሚያደርጋቸው አንዳችም የኑሮ ዋስትና የላቸውም። ሃላፊነት ያለው አስተዳደርም የላቸውም። ገዳዮችም የወያኔ ሃርነት ትግራይ ልዩ የጥበቃ ኃይሎች በስውር ነው የሚፈጽሙት። ታዳጊ ወጣቶች ይደፈራሉ – ህክምና በሀገራቸው መሬት ተነፍገው ያልፋሉ፤ ይህ አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በመላ ኢትዮጵያ ከእውነት በላይ እውነት ነው። በዘራቸው ብቻ ተነጥለው በመኖሪያ ቀያቸው ግድያ ይፈጸምባቸዋል። አዲስ አበባ ከተማ ላይ ታክሲ ውስጥ ዶር. ስዩም አምሩ ተገድለዋል። እንዲሁም ሌሎቹ። ከዚህም በላይ አዋቂ ወንዶች ሳይቀሩ – ይደፈራሉ። ይህን አሰቃቂ ቃል ስጽፈው ይዘገንነኛል። ስለ ቃሉ ሎቱ ስብኃት፤
- „ሰው ሥራውን ይሠራል ትምህርቱንም ይማራል።“
አዲስ አበባ ከተማ ብቻ የወደቀ ለቅሞ ለመብላት የተሰለፉ ሺ ልጆቻችን አሉ። ለዛውም ተርፎት የወደቀ የሚጥለው ዘመንተኛው ብቻ ነው። የሆነ ሆኖ የነገ ተስፋዎቻችን አዳራቸው ሆነ ውሏቸው፤ ትምህርት ቤታቸው መንገድ እና የመንገድ ሞራል ብቻ ያስተዳድራቸዋል። ይህ በነገ ማህበራዊ ህይወት ላይ የሚፈጥረው የሥነ ምግባር ቀውስ የኒኩሌዬር ቦንብ መርዝ ያህል ነው። መንፈሱን የተቀማ ምህበረሰብ የትውልደን ሃላፊነት እንዲወጣ አድርጎ ለመቅረጽ ግዙፍ ፈተና ነው። በዬክፍለሀገሩ ከተሞች ሆነ በገጠሮች ሊለምኑ ያፈሩ ሚሊዮኖች መጠለያ – ከፈን – የዕለት ጉርስ አጥተው ከሞት ጋር አፈር ለብሰው አፍር እዬሆኑ ነው። የሚነግሩን ኬክ ስለሚበሉት ይሆን? ወይንም ልጆቻቸውን ለመውለድ አሜሪካና አውሮፓ ለተሰናዳላጀቸው የትግራይ ሹሞች ቤተሰቦች ይሆንን? ይህ ነው ለእርሰዎ እድገት – ብልጽግና – መረጋጋት – ሥራና ትምህርት ብለው የሚያስቡት፤ እንደ አንድ ፓን አፍሪካኒስት …. ልጆቾዎት እርቃናቸውን ነው ያሉት በመንፈሰቸውም በአካላቸውም። ይህን ረመጥ አስፈንጥረው ከመወርውር ደመዎት ነውና ጠጋ አድርገው – ይቅመሱት። ኮሶ ነው ከርቤ ነው – ይመራል።
- „ኦፍ ኮርስ ሂዩማን ራይትስ ኦድቦኬት ኦር ተቃዋሚ ኃይሎች ሞር ኖሌጅ ይኖራቸዋል። ስለዚህ እና የእኔ አሰስመንት ከእነሱ አስሰምነት ጋር ሊለያይ ይችላል። ግን እኔ አዝ እንደ ኦርዘርቨር ስመለከተው ኦቨር ኦል ፒክቸሩ ደህና ነው ብዬ ነው የምመለከተው።“
መለዬት ሳይሆን – አንገናኝም። ጉዳዬ ብለው አላዩትምና። እንጃ እንደ ወገነዎትም የማዬት ጠረን አላዬሁበትም – በገለፃዋት። ክቡርነተዎት ከደላው ገነት ላይ እኛ ደግሞ ብትን አፈር ለማኝ ብናኞች ነን። ምን አልባት እርስዎ አራት ኪሎ ላይ ስለ አለው የፓርላማ መቀመጫ እንጂ፤ ፓርላማው ከተመሰረተ ጀምሮ እንኳንስ ሶስት ጊዜ አንድ ጊዜም ለማብላት ከድሃ ሀገሮች የመጨረሻ ተርታ ለጣላት ሀገር ተጠያቂነቱን ትልሙንና ውጤቱን፤ የግል ነጻነቱን ተቀምቶ ሁሉም ዜጋ በሥነ ልቦና ቀውስ ጥቃት ላይ መኖሩን ለእኔና ለእርስዎ እኩል ትርጉም ሊሰጠን አይችልም። ዬፓርላማው ወንበር አንድ ነፃ ጋዜጠኛ ሊያስፈታ ያልቻለ፤ የሃይማኖቱን መብት ለማሰከበር ያልቻለ፤ ወረቀት ላይ በሰፈረው የቁጥር ድርድር ብቻ የተሰለበ -እንደ ጉርሽጥ እንሶስላ የተሰለሰለ፤ እውክለዋለሁ ለሚለው ዜጋ ሳይሆን ለታላቋ ትግራይ ቅዠት የሚማስን ገበርም የሆነ፤ ልብስ – መጠለያ ፤ ዜጎቹ እንዲያገኙ ያላስከበረ፤ ኃላፊነት የማይሰማው፤ እራሱን ማድመጥ የተሳነው የኩበት ድርድር ላይ የከተመ ወንበር ነው። የዕንባ ዕለታዊ የምልዕቱ ትንፋሽ መሆኑ ይሆን „ደህና ነው“ ያሰኘዎትን? ወይንም እራህብ፤ መታረዝ ጎርፍ ላይ ፕላስቲክ አንጥፎ መተኛትን መተርጎም ስላቃተዎት? ወይንም ድልድይ ውስጥ መኖሬያቸው አድርገው ድሪቶን ለነፍሳቸው መጠግያ ያደረጉት ወገኖቻችን የክር እስትንፋስ፤ ሞት አፋፍ ላይ ያለው የሲቃ መቃሰት ድምጹ አልደረሰበዎት – ይሆን? ዕድለኛ ነዎት¡
- „እራሱ አሁን ለምሳሌ ስትመለከተው ትራንዝሽኑ ፕራይም ሚንስተር መለስ ከሞተ በኋላ ወደ አሁን ወደ አሉት ፕራይም ሚኒስተር ትራንዝሺኑ ፒስፉል ነበር።“
እንደሚገባኝ እርስዎ ያሉት ወንበሩ ላይ ብቻ መሰለኝ። በሌላ በኩል ግን የኢትዮጵያ ህዝብ የፈርኃ እግዚአብሄር ባለቤት ነው። ሌላው ቀርቶ „የድምጻችን ይሰማ“ የአርብ የድዋ በዓለት በሰሞናቱ ዝግ ነበሩ። ስለምን? ሞቱ አስደንጋጭ የሰማይ ቅጣትና ቅስፈት ስለነበረ። አይደለም ለኢትዮጵያ የኃያሉ እግዚአብሄር ቅጣት አብረዋቸው ከሄሮድስ መለስ ዜናዊ ጋር የተቀመጡትንም አላተረፈም ነበር። እጬጌዎና ዓፄውን በአንድ ሰሞን መቃብር ሲጠራቸው ይህን ፈንድሻ እዬረጨ አልተቀበለውም – የኢትዮጵያ ህዝብ። ኢትዮጵያና ህዝቧ ህግ ናቸውና። ስለዚህም በአርምሞ፤ በሱባኤ፤ በፆም፤ በጸሎትና በሰጊድ ነበር የታደመው። ደህና የዕድምታ ሚስጢር ተርጓሚ አልጻፈውም እንጂ ዓለምን ያስተማረ የሰማይ ቅጣትና ገድል፤ የ21ኛው ምዕተ ዓመት ታምርም ነበር። ልጅ እያለሁ ግብጽ ላይ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታዬች የሚል ገድል ሰምቼ ነበር። የዛን ያህል ነበር የሰማዩ ቁጣና የአባታችን መዳህኒተአለም – ታምር። አንድ ታናሽ ብላቴና ሥሙን እንኳን በአግባቡ የማናውቀው የዕንባ ተቆርቋሪ ወታደር አስነሳ ፈጠሪ በጥበቡ = ታምሩንም በእሱ በመረጠው ብላቴና በዓለም አደባባይ ናኘው። ጎልያድ – በብላቴናው ቅዱስ ምሩቅ መንፈስ ተረታ። ስለዚህ እርስዎ የጠበቁት የወታደራዊ ፍጣጫ ሊኖር አልቻለም። የሰማዩን ሚስጢር መተርጎም የቻለው ህዝብ ሂደቱን የታምር አህዱ ብሎ ነበር የተመለከተው። ቅጣቱ – ይበቃዋል ለሄሮድስ ብሎ ነው ጸጥ ብሎ በተደሞ ያሳለፉት። በሌላ በኩል ስማቸውን ለመጥራት ያልደፈሩትም ተተኪው ጠ/ሚር ቢሆን „በ5 የወያኔ ሃርነት ምርኩዞች መቆም አልሻም፤ ህሊናዬም መንፈሴም ብቁ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፤ ከእኔ ጋር እንደሉ አውቃለሁ“ በማለት እርግጠኛ ቢሆኑና ምርኩዞቹን ቢሰብሩ ይፈንዳ ነበር። ነገር ግን የራሳቸው መንፈስ የሌላቸው፤ በጥገኝነት የሚማቅ የሙት መንፈስን የሙጥኝ ያሉት ጠ/ሚር ኃይለማርያ ደስአለኝ የተሰጣቸውን የእስር ጊዜ በጸጋ ስለተቀበሉ እንደ ትናንቱ ኢትዮጵያ በግፍና በዘረኝነት መተዳደሯን ስለወደዱ ብቻ ….. እንዳሉት እንደ እርስዎ ላለ ለሚያዳለ ሙሁር የመነሻ ድጋፍ መሆን ችሏል። ግን ውስጡ የአምክንዮ እምቅ ሚስጥራት ማዕድን ነው። በመደዴ የሚኬድበት አይደለም። …. ሌላው ቀርቶ የ2014 የዬመን፤ የሳውዲ ግፍ በኢትዮጵውያን ላይ በ2015 ዓይናችን በሌላ ባልተጠበቀ ታምር እንሆ ተገለጠ። መንፈስ ለተገለጠለት የሰማዩን ፕሮቶኮል ማንበብ ይቻለዋል። ግን እኛ ሰብዕና ሰብዕዊነትን ስለዋጥን ሃዘኑን እንደ ሃዘናችን እንጂ እንደ ቅንጦተኞች አለደረግነውም። የትኛውም ዓለም ህዝብ፤ ህጻነት ሰቆቃ ጉዳያችን ነውና።
- „ምንድነው ኢትዮጵያ ኢሌክሽን ይደረጋል ኢፒዲአርፒ ዶሚነት ነው ግን ይህ ዶሚነት የሆነው አይ ቲንክ ዊ ሹድ ቢ ኬርፉል ኖት የትቱ ብሌሙ ብሎ ኢንተርያሉ የፖለቲካ ስፔሱ ተዘግቷል ኦፖዚሽኑ ሃራስ ይደረጋል ብሎ መገምግም ትክክል አይደለም ብዬ ነው ። የዛሬም 5 ዓመትም እንዳልኩት ኮንግረሱ ጀስቲፋይድ ሲደረግ ተቃዋሚ ኃይሉ ሪስፖንስቢሊቴውን መውሰድ አለበት። ብዙዎቹ ውጪ ነው ያሉት። ብዙውንም ጊዜያቸውን የሚአሳልፉት እርስ በርሳቸው ሲጣሉ ነው።“
አንድ ምሳሌ ብቻ ይበቃወታል። የመጀመሪያዋን ሴት የብሄራዊ ፓርቲ መሪን በድምጽ ብልጫ የመረጠው እጅግ መጠነ ሰፊ ዓላማና ራዕይ የነበረውን አንድነትን ሊቀመንበሩን ወያኔ አሰራት፤ ከ2010 ምርጫ በፊት ክብርት ዳኛ ብርቱካን ሜዴቅሳን መንፈሷን ቀጠቀጠ፤ ይተካታል ተብሎ የታሰበውን አቶ አንዷአለም አራጌንም ደገመ፤ እሱን ማን ሊተካው ሲባል ወጣት ሃብታሙ መጣ እሱንም ቀማ፤ አቶ ናትናኤል አቶ ዳንኤልም ማገር ነበሩ ለፓርቲው። ይህን የሚያደርገው አስርጎ በሚያስገባቸው ካድሬዎቹ ነው። አሁን እርስዎ ስትራክችር /መዋቅር/ የተሟላ ነው የሚሉት ምርጫ ኮሚሽን – አንድንት ያህል ብሄራዊ ፓርቲ ዘርፎ፣ አፍርሶ የራሱን መንፈስ – ተከለ። ድራማው ይሄ ነው። ከዚህ በላይ ከመታሰር፤ ሀገር ከመልቀቅ፤ ከመደፈር፤ ከመደብደብ፤ ከመዘረፍ በላይ ምኑን ይሆን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኃላፊነት አልወሰዱም የሚሉት? የሞትና የዕድሜ ልክ እስራት እኮ የተበዬነባቸው በእነሱ ላይ ነው። ባለፈም ከትውፊታችን ውጪ አዛውንት የፓርቲው መሪዎች አባት ወንዶች በግረ ሰዶም የተደፈሩበት …. ሂደት እ! ትንሽ አንደ ሰው —-
ይሄን እንደ ምሳሌ አነሳሁት እንጂ ሌሎችም እጅግ የከፋ ግፍ ተፈጽሞባቸዋል። አንድነት ብሄራዊ ጉባኤውን ሲያካሂድ ያስተውሉ የብሄራዊ ጉባኤው ውክል አካላትን ያስተናገደው በሚያሳዝን ሁኔታ ነበር። የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጉባኤቸውን ለማካሄድ የሚያስችል የኢኮኖሚ የሎጅስቲክ አቅም የላቸውም። በልመና ገንዘብ ከአፈሙዝ ጋር እዬታገሉ። የጉባውኤው ተሳታፊዎች በራሳቸው ወጪ መጥተው አዲስአባባ ላይ ልብሳቸውን አንጥፈው ነበር መሬት ላይ እያደሩ የተሳተፉት፤ የወያኔ ደግሞ ዝቅ ሲል ሂልተን ከፍ ሲል ሸራተን ነው። እዬራባት እንጀራ ጋግራ ልጇን በመቁንን ቀንታ በምትክፈለው ገንዘብ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ከላይ እስከታች ሠርግና ምላሹ ይሆኗል። ልጆቹ ውጪ ሄደው ይማራሉ፤ እረፍታቸውን ከፈለጉት ሀገር ያሳለፋሉ ወጪው በህዝብ ሃብት ይከወናል። ለማንኛውም ህጋዊ ፓርቲውና ዕጣውን በሚመለከት፤ ከህጋዊነቱ ተነስተው ህገዎጦቹ የወያኔ መዋቅሮች የበደሉትን በንጽጽር በዚህ ሊንክ ይመልከቱት … መስማማት ባንችል እንዳንረጋገም መቀራረብ ከኖረ …..
http://en.wikipedia.org/wiki/Unity_for_Democracy_and_Justice
http://www.addisadmassnews.com/index.php?option=com
- „ማጆሪቲው ደግሞ ውጭ ነው“
ከቶ ሞት የተፈረደባቸው ገመድ ላይ ተንጠልጠለው ማዬትን ይሆን የናፈቀዎትን? ለእርቅና ለሰላም ጉባኤ ጠርቶ እኮ ካቴና ነው የጠበቃቸው። አይደለም ሌላው። ውጪ ስለሚኖሩት ደጋግመው በቁጭትና በእልህ ጠቅሰዋል – ለወያኔ ሃርነት ትግራይ በተቆርቋሪነት መቆመዎት የሚያሽልም ይመስለኛል። የወያኔ ሃርነት ትግራይ ደንበር አልፎ ከሞት እስከ 18 ዓመት የተፈረደባቸው ወገኖቸዎት ለሞት መሄድ ነበረባቸውን? የሽብር ህጉስ ለማን የወጣ ይመስለዎታል? ተቃዋሚ ሃይሎችን በፍርሃት – በሰቀቀን – በስጋት – መንፈሳቸውን በማሰር የማይናገሩ ድንቡልቡሎች ለማድረግ የታቀደ ነው። የላቲን አሜሪካ ሀገሮች ምርጫ ሲኖር ዜጎቻቸውን ያሳትፋሉ – በውጪ ሀገር። ይህ እኔ ካለሁበት ሲዊዘርላንድ በተደጋጋሚ ያዬሁት ሃቅ ነው። የእኛ ደግሞ በግል በነፍስ ወከፍ ከሚላኩብን ሰላዮች በላይ የሞት ፍርድም አለ፤ የእድሜ ልክ እስራትም ውጭ ሀገር በሚኖሩ የፖለቲካ መሪዎች፤ ጋዜጠኞች፤ የሰብዕዊ መብት ተሟጋቾች። ጥብቅና የቆሙለት ፋሽስት ሥርአት ቅምጥል ያለ፤ ልኩንም የሳተ ገደል ነው። ውጪ ባሉት ላይ እስራት ሞት ሲፈረድ – በሌሉበት ነው። ሀገር ቤት በሚኖሩ ቤተሰብ ላይ ምን ያህል መንፈስን እንደሚጎዳ – እንደሚቀድ፤ ሥጋት ላይ እንደሚጥል ቅርበዎት የሥነ ልቦና ሙሁር ካለ ይጠይቁና ይረዱ – በትህትና። ለነገሩ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እኮ የሥነ ልቦና ጥቃት ሰለባ እንዲሆን – ተበይኖበታል። አሁን አላውቅም እስከ 2006 እ.አ.አ ድረስ ኢትዮጵያ ከ10 የበለጡ የሥነ ልቡና ባለሙያች አልነበራትም፤ እርግጥ ከአፍሪካ የተሻለ ቁጥር ነበራት። የሆነ ሆኖ ስለማይገልጠው ነው እንጂ በዘመነ ወያኔ ሃርነት የጭንቀት በሽታ ተጠቂው ፍጥረት ብቻ ሳይሆን አዬሩም ጣሪያ ግድግዳውም ነው። ተጠያቂውም ደግሞ „ኤግዛጁሬት አናድርገው“ በማለት የሚያቆለባብሱት የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ ነው።
ከዚህ ሌላ ውጪ ያሉት እኮ ምርጫ እንሳትፍ አላሉም …. መግቢያ ቢዛ የላቸውም። ስለዚህ ወቀሳው አግድም ላይ እንዲቀር ያደርገዋል። ትንትም ይዘፍንበታል። ወንድሟ በድንገት የመን ላይ ተጠልፎ የሄደባት ወገነዎት፤ ሥጋና ደምወት – በ24 ሰአት ሀገሯን ጥላ እንድተወጣ ተገዳለች፤ የነገ ፍሬዎች ከእናታቸው ጋር ሀገራቸውን ናፍቆተ – ኢትዮጵያን ለማዬት ቢሄዱ አባታቸው የኢሳት ጋዜጠኛ በመሆኑ ብቻ በአስቸኳይ ወደ ለንደን ከወላጅ እናታቸው ጋር እንዲመለሱ ተበይኖባቸዋል፤ ይህ ለቀንበጦቹ ህጻናት ጮርቃ መንፈስ መሸከም እንዴት እንደሚችሉት ይመዝኑት? ልክ መስፈሪያ ካለዎት – አሁንም በትህትና፤ ምን አልባት ለእርስዎ ተነጥፎ – ተጎዝጉዞለዎት ሊሆን ይችላል? የክትና የዘወትር – ወርቅና ነሃስ መለዬት የወያኔ ሃርነት ትግራይ ትንፋሹ ነውና።
ሀገር ቤት ያሉት መድረክና ሰማያዊውንስ ከምን መድበዋቸው ይሆን? ዱላውንም – እስሩንም – ስቃዩንም – ግልምጫውንም – መገፋቱንም ችለው ሀገር ቤት ናቸው ያሉት። ሌላው ቀርቶ አብዬት አደባባይ /መስቀል አደባባይ/ ላይ ህዝባቸውን መጥራትና መሰብሰብ አይፈቀድላቸውም። ለትግራይ አፓርታይድ አገዛዝ ብቻ የወርቅ ምንጣፍ ተነጥፎለት እሱ ብቻ ነው በህዝብ አደባባይ የሚፈነጥዘው። ይህ ለእርስዎ የሃኒ ሙን ሳውና ሆኖ ይሆን?! – በአክብሮት።
የተከበሩ ፓን አፍሪካኒስት አቶ ቴወድሮስ ዳኜ – በፖለቲካ ድርጅቶች ፉክክር ውሰጥ ጥላቻ የሚጠበቅ ባይሆንም ግጭት ግን ግድ ነው። ፉክክር – ነዋ። ከዚህም ጋር የትግል ስልትና የአጋዥ ሀገሮች ምርጫም ሆነ የፖሊስ ጉዳይ ያፋትጋቸዋል። ነገም ቢሆን በፓለቲካ ህይወት ውስጥ ሰጥ -ለጥ፤ ጭጭ እረጭ የሚል ነገር አይጠበቁ ….
ይልቁንም ስለምን አይሳመሙም የሚለውን፤ ማጠቃለያ ለመድረስ ግራ – ቀኝ ሁነቶችን፤ አገናኝ መስመሮችን፤ ገፊ ሃይሎችን፤ የዘመን አስተዋፆችን፤ የተመክሮ ማሳዎችን፤ በአግባቡ ፊት ለፊት አስቀምጦ መመርመር ያስፈልጋል።
የትግል ስልት ምርጫ
ሀ. ሰላማዊ
ለ. የትጥቅ
ሐ. ሰላማዊና ትጥቅ /ሁለገብ/
የአደረጃጀት ባህሪ
ሀ. ብሄራዊነት
ለ. ጎሳዊ /አካባቢያዊነት/
የፓሊሲ ጉዳይም አለ —-
ሀ. ፓሊሲውን በግልጽነት ፕሮግራሙ ላይ ያቀረበ፤
በዚህ ዙሪያ ሌላም ልዩነት የሚያመጡ አምክንዮዎች አሉ …. የመሬት፤ የውጪ ግንኙነት፤ ህገ -መንግስታዊ ጉዳዮች፤ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ወዘተ ….. ለምሳሌ የመሬትን ቢነሳ የመንግስት/ የህዝብ/ መንግስትና የህዝብ እነዚህ በራሳች ሰፊ ቅርንጫፎችን ከነግጭታቸው እንዲያስተናግዱ ግድ – ይላቸዋል።
ለ. ፓሊሲ አይስፈልገኝም መጀመሪያ ከባርነት መላቀቅ ነው አቅጣጫዬ የሚለው ደግሞ አዲስ መንገድ ነው። ቀድመው የሚፋልሙ የፖሊሲ ጉዳዮች እረፍት ሰጥቶ አቅምን ከብክነት ለማዳን የተተለመ ይመስላል። ያላቸው ደግሞ ወቀሳውን ያስኬዱታል —-
ትጥቅን መራጮች ስፖንሰር የሚደርጋቸው ድርጅትና ሀገር ምርጫ ጉዳይ –
ሁሉም ጎረቤት ሀገር ጥገኝነት አይሰጣቸውም። የወያኔ የኢንትሪግና /የሸር/ ፖለቲካ ቀለል ያለ መናፈሻ ላይ ነጭ ሸሚዝ ተለብሶ ወክ እንዲህ የሚባልበት የሠርግ ግጥግጥ አይደለምና። ስለዚህ በሀገር ምርጫ ላይም እንዲሁ ስምምነት – የለም። አሁን ኤርትራን በመረጡት ላይ የሰላማዊ ትግልን የመረጡት ሳይቀሩ ይህን አካሄድ ትክክል አይደለም በማለት -ይወቃቀሳሉ ////
የመንግሥት አደረጃጃት ዕይታ ንድፍ ልዩነት …..
/የህግ አውጪ/ ህግ ተርጓሚና አስፈጻሚ ባህሪና ግባቶቹም ሌላው የሚያፋጥጥ የክርክር አጀንዳ ሲሆን …. ከሁሉ በላይ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ሴራን በፖሊሲ ደረጃ የነደፈ አስተዳደር በመሆኑ በውጭ ለሚገኙት ሰፊ የዘመቻ ፓሊሲ አለው። በሀገርም አንድ ለአምስት ….. አስርጎ ያስገባል። በትዳር፤ በጓደኝነት፤ በሃይማኖት መሪነት፤ በተገኘው ቀዳዳ ሁሉ። ድርጀቶችን – ተቋማትን ይከፋፍላል፤ ያተራምሳል፤ ጦር ያማዝዛል፤ እኔም የሰለባዎቹ አባል በመሆኔ ነው ይህን ሃቅ እምገልጽልወት፤ ተፈጥሮዬ እራሱ ሰብሰብ ያለ – ብልህና ቁጥብ ነው። ያም ሆኖ ግን ከጥቃት ሰለባነት አልወጣሁም። በራሴ በምከፍለው ኔት ላይ ነፃነቴን ተቀምቼላሁ። ስጽፍ ኔቱን አጥፍቼ ነው። እሰከዚህ ድረስ በነፃነት ሀገር ነፃነቴን ቀምቶኛል የወያኔ ሃርነት ሸር። እርግጥ በሰለጠነ ዓለም ስላለሁ መስመር ማስያዝ – በህግ ይቻላል። ግን ሩቅ አስባለሁ። በዛ ቤተሰብ ሥር በልተው የሚያድሩ አሮጊቶች፣ ነፍሰጡር እህቶች፣ ህመምተኞች፤ ህጻነት ይኖራሉ ስለዚህ እኔው ብጎዳ ይሻላል – ለመንፈሴ በማደር።
የዕውነት —- ግን እርስዎ ለመሆኑ …. የት ላይ ይሆን ክቡርነተዎት የሚኖሮት ሌላ ፕላኔት ላይ ይሆን? የእርስ በርስ ጦርነት – ጎሳ ላይ የተቸከለ አስተዳደር በባህሪው እሾኽ ስለሆነ እንዲህ ቁጥርጥሩን በቀላሉ መፍታት አይቻልም። የተጋባው – የተዋለደው – ክርስትና የተናሳው – በጡት ልጅነት ያለው – የጉርብትናው፤ የውለታ አደሩ ሁኔታ ሁሉ የወያኔ ፖለቲካ የማስፈጸሚያ ሃዲዶቹ ናቸው። የትውልዱ ኃላፊነት ከእናቱ ማህጸን ውስጥ ዓይን ሳይኖረው የተፀነሰውን ሲወለድ ዓይናማ ማድረግ ነው። ይህ ይቻላልን?! ከዚህ ሃቅ ጋር እስኪ ይቀመጡና ይወያዩ … እባክዎትን?
ሌላው ፈታኝ ጉዳይ ብስጩ የሚያደርገው ደግሞ ኢትዮጵያን ያህል ተናፋቂ ሀገር ሂዶ ማዬት አለመቻል፤ ወላጅ ሲታመም ሩጦ አለመድረስ፤ ሲያልፍም ቁሞ አለመቀብር ከዚህም ባለፈ በፖለቲካ ህይታቸው እንዳሉ ሲያልፉ የ ሀገርን ብትን አፈር ያለመግኘት ስጋት፤ የትግሉ ጊዜ መርዘም ትዳር – ልጅ – ትምህርትም ሁሉም ይቅርበኝ ያሉት ከሁሉም ሳይሆን ዘመን እዬጨረሳቸው ሲሄድ ከውስጥ መከፋት ጋር የሚመነጩ የሥነ ልቦና ሆነ የመህበራዊ ጥቅል ፈተናዎች ጋር መፋጠጥ – በስምምነቱ ሂደት ሆነ በትግል ጉዞ ላይ የራሱ ተጽዕኖ አለው። ግን ራህብን የሚያውቀው የተራበው ብቻ ነው።
የማከበረዎት ወገኔ አቶ ቴወድሮስ ዳኜ ሁሉንም ወቀሳ አንከባለው – አድቦልቡለው – ጠፍጥፈው ናዳውን የለቀቁት በዕንባ ላይ ነው። ትዝብት ነው ትርፉ። „ሃራስ ሊደረጉ“ ይቻላሉ ብለው እንኳን የወያኔ ሃርነት ትግራይ አስተዳደር ማስተካከል ያለበትን ዘለዎታል? ከዚህ ላይ ነው የፓን አፍሪካኒስትነተዎት ካባ ብልዝ ነቁጥ እንዲኖረው የሚፈተነው። እንዲያውም እኔን ሌላ ጥርጣሬ ውስጥ ጨመረኝ። የአፍሪካን የስደት ሰቆቃ ለመጋራት ባቋቋሙት ፋውንዴሽን ስምሪት፤ ኢትዮጵያዊ ስደተኞችን እንዴት ይሆን የሚመለከቷቸው – ልክ እንደ ሱማሊያ፤ ኬንያ ስደተኞች እኩል ይሆን ስል? መልሱ ድፍርስ ነው የሆነብኝ። ምክንያቱም የቃለምልልሱ ፊድባክ /ምላሽ/ ጉሽ እና አብዝቶ የተስረከረከ ስለሆነ። ኢትዮጵያዊ ስደተኞች ከማናቸውም በላይ የተገፉ ናቸው። ስለምን? ሀገራቸው ላይ በመሬታቸው ላይ ባይተዋር ናቸው፤ ዬቅቡ የቁጥር ስታስቲክ ድርድር ሰለባ የሆኑ ሀገሮችም እንደ ክቡርነተዎት „ስቴቢሊቲ አለ፤ ጦርነት የለም ሰለሙን ሰዉ አግኝቷል ኢትዮጵያ እድገት ላይ ናት“ በማለት የጥገኝነት ጥያቄቸውን ውድቅ ያደርጉታል። ስለዚህም ወገኖቻችን – ዜግነታቸውን አሳልፈው ለሌላ መንፈስ እዬሸለሙ – ይገኛሉ። እነሱም በመንፈስ ምጥ ላይ ይገኛሉ። ይህ ደምን – ይቆጠቁጣል። የእርሶዎም ገለጣ እንደነገረኝም መጋፋታቸውን፤ መከፋታቸውን አልተቀበሉትም …. ስለዚህ ፋውንዴሽነዎት ሥሙ የአፍሪካ ሆኖ ኢትዮጵያን የማይጨመር ዓይነት …. ይሆን -? ይሆን -?
- „እነሱ ያቀርቡት ቪዢን ለሀገሪቱ ብዙ የሚታይ የለም። ያዬሁትም የለም። እንዴት ተብሎ ነው ዜን ኢሌክሽን ሲደረግ ለማሸነበፍ የሚቻለው የዛ ዊክነስ የዛ ሪዛልት ሁልጊዜ መታዬት ያለበት ኖት ጀስት ተቃዋሚ ኃይሎች እንደሚሉት ሃራስ ተደርገናል ኖ! ሃራስመንት ሊነር ይችላል ጥርጣሬ … ግን እነሱ ያደረጉት ነገርም ኮንትሪቢዩት አድርጓል አላደረግም ተብሎ መጠዬቅ አለበት።“
ምን እድል አግኝተው ነው የሀገሪቱ ቪዥን ላይ ተጽዕኖ ማሳደር የሚቻሉት፤ ይህን ቢያዳምጡት መልካም ነው ቀደም ሲል እንደገለፅኩለዎት አንድነት የተባለው ለዛውም ወያኔ የፈረሰውን ብሄራዊዊ ፓርቲውን ሳይጨመር፤ መሪዎቹን አስሮና አሰድዶ ንጡሑ አንድነት ባይኖርበትም ተቀጥላው አንድነት አለበት የአቶ ትግስቱ በቃለምልሱ፤ ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ በአጭር የቃኘውን ያዳምጡት እስኪ „ የግንቦቱ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር ተጀመረ ፤ፍልሚያው ጓንት አልባ ነበር፡፡”/አዋዜ/
https://www.facebook.com/pages/Alemneh-Wasse-News/259948420841915?sk=timeline&ref=page_internal
“የግንቦቱ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር ተጀመረ ፤ፍልሚያው ጓንት አልባ ነበር፡፡”/
https://www.facebook.com/pages/Alemneh-Wasse News/259948420841915?sk=timeline&ref=page_internal
ደግሞስ በአምስት አመት ውስጥ 9 መደበኛ 4 ምራቂ ደቂቃ ብቁ ነውን? ይህ የህሊና ጉዳይ ይመስለኛል ጥያቄው የመመለስ አቅም ያለው። መልሰዎት የግብር ይውጣ ዓይነት ነው የሆነው።
ሌላላም ልከል ፋና ራዲዮ ማለት የወያኔ ሃርነት ትግራይ የጫካ ራዲዮ ከኢንጂነር ይልቃል ጋር ቃለ ምልልስ አደረገ። እራሱ ጠያቂው አጋዚ ከሰለጠነበት – የሰለጠነ ነው የሚመስለው። ለአንድ ቃለ ምልልስ አድረጊ ቀዳሚው ትህትና አክብሮት ሆኖ ሳለ ካቴናውን አስቀምጦ ጅራፉን እያጮኽ ነበር የጠዬቃቸው ኢንጂነሩን —- ያም ሆኖ እንዳይተላላፍ ታገደ። ይሄንስ ምን ይሉት ይሆን? የርትህ ማህደር ይሉትን ይሆን ¡?
„ስለ ስትራክቸር“ /መዋቅር አንስተዋል። አዲስ አበባ ከተማ ላይ ቢሮ ለመከራዬት ፈቃድ የማያገኙ፤ አዲስ አበባ ከተማ ላይ መኪና ለመንቀስቀሻ ለመከራዬት ፈቃድ የማይሰጣቸው፤ በማናቸው ሰአት ቢሯቸውን ወታደር ገብቶ ሰብሮ ዘርፎ ሲሄድ ሃላፊነቱን የሚወስድ ተቆርቋሪ አስተዳደር በሌለበት ስለ ስትራከችር /መዋቀር/ አስፈላጊነት ይነግሩናል። መደረጀት እኮ ሲባል ስትራክቸር /መዋቅር/ መዘርጋት ነው። ስትራክችሩ /መዋቅሩ/ ከቀበሌ እስከ ብሄራዊ።
- የቀበሌ ጠቅላላ ጉባኤ / ሥራአስፈጻሚ ሙሉ አባለቱ ይገኛሉ።
- የወረዳ ጠቅላላ ጉባኤ/ ምክር ቤት/ ሥራ አስፈጻሚ –
- የ አውራጃ ጠቅላላ ጉባኤ/ ምክር ቤት/ ሥራ አስፈጻሚ
- የብሄራዊ ጠቅላላ ጉባኤ / ማዕከላዊ ምክር ቤት/ ሥራ አስፈጻሚ ይህን ነው የሚሉን አይደለ?
ወያኔ ሃርነት ትግራይ በደርግ ጊዜ የከሸፉ ቀላሃዎችን ሰባስቦ ጨፍልቆ የሠራቸው „ህዝቦች“ እያለ አደራጅቶ ለማላገጫው የተጠቀመበት ህብረት እራሱ የሚተዳደረው በህዝብ አንጡራ ሃብት፤ መዋቅሩን እስከ ሥር ዘርግቶ በበጀት ነው የሚያስተዳድራቸው። ሥልጠና፤ የውጭ የትምህርት ዕድልና ዕድገት ይደጎማሉ ካድሬዎቹ – ከመደበኛው ማህያ በላይ። የተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን ለሃገራቸው አንጡራ ሃብት ባይታዋር ናቸው። ግብር ቀረጠ ግን ይከፍላሉ። ማናቸውም መንግስታዊ መዋቅር በወያኔ ሃርነት ማንፌስቶ ሥር የሚተዳደር ግን በጀቱ በህዝብ አንጡራ ሃብት ነው። ፖሊስ ሃይል/ ደህንነት/ ሰራዊት/ የሚ/ር መስሪያ ቤቶች፤ ተቋማት፤ ፍርድቤቶች ሁሉ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ሃብት ናቸው – መንፈሳቸውም።
ተቃዋሚ ሃይሎች ወደ ታች ሲወርዱ …. ዋርካ ላይ ነው የሚሰበሰቡት፤ የሚተዳደሩትም በራሳቸው ማህያ ነው። እንዲያውም የተቃዋሚ ፓርቲ አገልጋይ ከሆኑ ይባራራሉ – ከሥራቸው፤ ከእድገት ይታገዳሉ …. አሁንም እርስዎ ክቡርነተዎት የት ነው ያሉት? ስለምኑ ይሆን የሚነግሩን? …. ይህም ሆኖ በሁሉም ዘርፍ ጥረዋል አውሬው ግን አውሬ ነው። ተመክሮው ጫካ እድገቱም ፕርሜቴቢ …. ይሄ „ኦቨዘርበሮች ይኖራሉ፤ መዋቅር የላቸውም“ ያሉት ነገር ቅልጣን ይመስለኛል።
- “ተቃዋሚ ኃይሎች እንደሚሉት ሃራስ ተደርገናል ኖ! ሃራስመንት ሊኖር ይችላል ጥርጣሬ … አለበት። „ግን እነሱ ያደረጉት ነገርም ኮንትሪቢዩት አድርጓል አላደረግም ተብሎ መጠዬቅ አለበት። ….. የዛሬ 5 እና አመት አንዳልኩት አሁንም እላለሁ። ብዙውን ጊዜ የታለፈው እርስ በእርስ ሲጣሉና ማጆሪቲው ደግሞ ውጭ ነው ያሉት። ሃራስ አይደረጉም ለማለት ሳይሆን ኤግዛጁሬት ባናደርገው ጥሩ ነው።“
- „አንድ ሰው ኢቢደንስ አቅርቦ ኮንቢንስ እንዲያደርገኝ ያስፈልጋል“
ምን እኛ ኮንቢንስ እናደርገዎታለን የአውሮፓው ማህበረሰብ በማናቸውም የሀገሪቱ ሰቆቃ፤ የዘር ማጥፋት ወንጀል ላይ ያቀረበውን ዘገባ ጊዜ ወስደው ያዳምጡት። እኔ እንደማስበው የመረጃ እጥረት አብዝቶ አለበዎት፤ ከሀገረዎት ከኢትዮጵያ ዕንባ ይልቅ የለማና ያፈራ ግንዝቤ ከኢትዮጵያ ውጪ ስላሉት አፍሪካ ሀገሮች አለዎትና። የሚያምረው የራስን ሲያከብሩት፣ ከራስ ላይ ሲነሱ ነው – ጌጡ የሚደምቀው። ጆሮ አልባ የጆሮ ጌጥ፤ አንገት አልባ ሰው መሆን የለምና። ዕንባን የምልዕትን የመተርጎም አቅም ፈጠሪ እንዲሰጠዎት ቢተጉ የለመኑትን ይሰጥወታል። እኛም መመኪያችን እንለወታለን – ወደ እኛ ለማዬት ልበዎት ሲከፍቱ መንፈሰዎትን ሲፈቅዱልን እንናፍቀዎታለን፤ በስተቀር ግን ከመጤ እንደራሴ ጋር የሚከትም እኛነት አይኖርም መሃን ነው።
http://ecadforum.com/ethiopianvideo/2015/02/03/u-s-policy-ethiopia-a-failed-state-documentary/
- ይህም ብቻ አይደለም በሲዊዲን ከደም ጋር የከተሙትን ለፍርድ ለማቅረብ በቀለማቸው የማይመስሉን እዬሰሩ ነው። ከእኛ ጋር በደም የማይገናኙት። ‚ሰውን“ ግን ከቃል አልፈው መሆን በጸጋ የተረጉሙት፤ እንደ እርስዎ ያለው ፓን አፍሪካኒስት ደግሞ ወቀሳ ለዕንባ ይገባዛል – ማዘን ቃሉ አይገልጸውም፤ መቁሰልም ቃሉ አይገልጸውም፤ ማረርም ቃሉ አይገልጸውም የፍሬ መርገፍ ልበለውን? ከአላወቁን ስለምን ቃለምልስ አደረጉ?!
- https://www.facebook.com/ESATtv/posts/816604948371589 „13 የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣኖችና የጦር መኮንኖች በስዊድን አለማቀፍ የጦር ፍርድ ቤት ክስ ተመሰረተባቸው“
ልሰናበተዎት እንደ ከፋኝ። ቁስል ላይ ሚጥሚጣ – ቁስል ላይ የፋመ ማረሻ —–
ያለፉ ጥቂት ሊንኮችን ጊዜ ካላዎት ይከታተሉት ዘንድ ከምርጫ ጋር የተያያዙትን ለጥፌያለሁ። አንዱን ሲከፍቱት ተያያዡም ሰለሚመጣ የወደዱት ወይንም ለቀልበዎት የተመቸወትን ቢያነቡ አፍሪካዊ ሃላፊነትዎትን ሚዛናዊ ሊያደርግ ይችላል። እናትዎትና አይነጥሏት፤ ጣል – ጣልም አያድርጓት፤ የክብረዎት መሰረት ማርዳ ጌጠዎት ናትና፤ በማን ላይ ይሆን ተዚህ – የተደረሰው?!
ምርጫና ልግጫውን የዓለም የዜና አውታሮች የዘገቡትንም …. ባይገርመዎት የናይጀርያን በሚመለከት የጀርመን፤ የኦስትርያ፤ እንዲሁም የሲዊዝ ራዲዮና የተለያዩ ቴሌቪዥን ፕሮግራሞች እዬተቀባበሉ ዘግበውት ነበር። ኢትዮጵያ ላይ ግን ቃልም ትንፋሽም አላወጡም „ሰው“ ስለሆነ – አጀንዳቸው።
„ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው። እግዚአብሄር በክፉ ቀን ያድነዋል“ /መዝሙር 40 ቁጥር 1/
ለእኔስ ሰው መሆኔ ብቻ ይበቃኛል፤
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/41705
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/41705#sthash.v011En2U.dpuf
http://www.ethiofreedom.com/amharic/
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/39189
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/41765
http://ecadforum.com/Amharic/archives/15131
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/41700
http://www.zehabesha.com/amharic/
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/41678
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/41648
The post ኦ! – ከሥርጉተ ሥላሴ appeared first on Zehabesha Amharic.