Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የሳሙኤል ዘ-ሚካኤል ደቀ-መዝሙር ማነው? –ለአቶ ክንፉ አሰፋ የተሰጠ መልስ (ከሰናክሪም መኮነን)

$
0
0

“ ሳታማሃኝ ብ

senakriem-mekonnenድርጅታችን አይከን ኢትዮጵያ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የሂሳብ እና የኢንጂነሪንግ ማዕከል Hands on Science በሚል መሪ ቃል ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የወደፊት ኢንጂነሮችን፣ ተመራማሪዎችን፣ አዳዲስ ነገር ፈጣሪዎችን ለማፍራት በወርክሾፓችን ውስጥ በማሰልጠንና ዓመታዊ ውድድር በማዘጋጀት አሸናፊ ተማሪዎችን ወደ አሜሪካን በማምጣት ናሳ የጠፈር ምርምር ማዕከልን እንዲጎበኙ ያደርጋል። ይህ አይነቱ አገር አቀፍ የሳይንስ፣ የሂሳብ፣ የቴክኖሎጂና የኢንጂነሪንግ (STEM) ውድድር በማካሄድ ተማሪዎች አሜሪካን አገር የሚገኘውን ናሳ የጠፈር ምርምር ማዕከልን እንዲጎበኙ ስናደርግ ይህ የመጀመሪያችን አይደለም። በ2012 እና በ2013 በተለያዩ ት/ቤት ተማሪዎች መካከል ውድድር በማካሄድ አሸናፊ ተማሪዎችን ናሳን እንዲጎበኙ አድርገናል። የ2014 የሦስተኛው ዙር ውድድራችንን አካሂደን ከጨረስን በኋላ አሸናፊ ተማሪዎችን ከዛሬ አራት ወር በፊት ከዲሴምበር 26, 2014 እስከ ጃንዋሪ 10, 2015 ድረስ ወደ አሜሪካን በማምጣት ግሪንቤልት ሜሪላንድ የሚገኘውን ናሳን ጎብኝተው እንዲመለሱ አድርገናል። ይህ ትምህርታዊ ጉብኝት በተሳካ ሁኔታ አድርገን ከተመለስን ከአራት ወር በኋላ አንድ ክንፉ አሰፋ የተባለ ግለሰብ በዕለት April 17, 2015 የሳሙኤል ዘ-ሚካኤል ደቀ-መዝሙር በሚል ርዕስ ከDecember 26, 2014 to January 10, 2015 የዛሬ 4 ወር ገደማ ናሳን ጎብኝተው የተመለሱ ልጆችን በተመለከተ ጋዜጠኛ ነኝ ከሚል ሰው የማይጠበቅ የፈጠራ ወሬ አቀናብሮ፦

  • ናሳን አልጎብኙም፣
  • በፎቶ ሾፕ የናሳ ማስክ ለብሰው ነው፣
  • ቪዛ በገንዘብ ገዝተው ነው፣
  • አሜሪካን ከደረሱ በኃላ ተራቡ፣ ተጠሙ፣ በየሬስቶራቱ ፍርፋሪ ለምነው በሉ፣
  • ከወላጆቻቸው በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ይዞ አሜሪካን አገር ጠፋ፣
  • በአሜሪካን ባንክ አካውንት ከፍቶ ገንዘቡን እዛው አከማችቷል ወዘተ…. በማለት በራሱ ድህረ ገፅ ላይ ፅፎ አስራጭቷል።

የሳሙኤል ዘ-ሚካኤል ደቀ-መዝሙር ብሎ የጀመረው የጋዜጠኝነት ሥነ-ምግባር ፈፅሞ የሌለው ክንፉ አሰፋ ምስሌን በመለጠፍ ስሜን በማጥፋት ጽፎኦል፡፡ እዚህ ላይ ለአንባቢዎች ግልፅ እንዲሆን ፀሀፊ ክንፉ አሰፋ ማን ነው? ክንፉ አሰፋ ማለት የመሰሉ አሰፋና የዳዊት አሰፋ ወንድም ሲሆን፣ በዚህ ወድድር አሸናፊ ሆኖ ወደ ናሳ ከሄዱት ተማሪዎች መካከል አንዱ የሆነው የሳሙኤል ዳዊት አሰፋ አጎት ነው፡፡ እስካሁን ከተለያዩ ሰዎች ለማጣራት ባደረኩት ሙከራ ወ/ሮ መሰሉ የክንፉ አሰፋ እህቱ ወይም አክስቱ ናት። ብዙዎች እንደነገሩኝ ግን እህቱ ሳትሆን አትቀርም። ዋናው ቁምነገር ግን ይህ ጉዳይ የአንድ ቤተሰብ ጉዳይ እንደሆነ እንድትረዱልኝ ነው። ስለዚህ እኔ እህቱ እያልኩ ቀጥያለሁ። ሳሙኤል ዳዊት አሰፋ እንደማንኛውም ተማሪ ተወዳድሮ አሸንፎ ናሳን ለመጎብኝት የመጣ ተማሪ ነው፡፡ አክስቱ ወ/ሮ መሰሉ አሰፋ ሁሉም ወላጆች እንዳዋጡት እርሷና በካናዳ የሚኖሩ ቤተሰቦቿ 1,721 ዶላር በአሜሪካን ለሚያደርጉት የ 15 ቀን ቆይታ የሆቴልና ጠቅላላ ፍጆታ አዋጥታለች። ነገር ግን በአካል እኛ ጋር መጥታ በነበረ ጊዜና ከካናዳ ድረስ በተደጋጋሚ በመደወል ናሳ፣ የተለያዩ የአሜሪካን ሀገር ድርጅቶች፣ አዲካ ትራቭል፣ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኦሮሚያ ባንክ ስፖንሰር እንዳደረጉህ፤ በቂ ስፖንሰርም እንዳገኘህ አውቃለሁ። ስለዚህ ለወንድሜ ልጅ ለሳሙኤል ዳዊት አሰፋ ለ15 ቀን ጠቅላላ ፍጆታ የከፈልኩህን 1,721 ዶላር መልስ፤ የማትመልስ ከሆነ ግን ጋዜጠኛ ወንድም አለኝ፤ ስምህን ነው የማጠፋው፣ ለFBI፣ ለተለያዩ ሚዲያዎች፣ ለውጭ ጉዳይ ሚ/ር አሳውቃለሁ የሚሉ ማስፈራሪያዎች በስልክና በኢሜል ትልካለች። እኔም ይህ ስህተትና አግባብ ያልሆነ ጥያቄ ሲሆን፣ ሁሉም ወላጆች ወደውና ፈቅደው ለሆቴልና ለትራንስፓርት ወጪ እኩል የከፈሉ ሲሆን፣ ለእርሷ ብቻ የሚመለስበት ምክንያት አልታየኝም።

ሲጀመር ስፓንሰር አድርገዋል ያለቻቸውን ድርጅቶች ደውላ እንድታረጋግጥ ብነግራት ደውላ ለማጣራት እንኳ ፈቃደኛ አልሆነችም፤ ካልሆነ ግን መረጃ ይዛ በህግ እንድትጠይቀኝ ነገርኳት፤ እርሷ ግን እኔን ለመስማት ፈቃደኛ አልሆነችም፡፡ እውነት ለመናገር ገንዘቡ እዚህ ግባ የማይባል ትንሽ ብር በመሆኑ ሁል ጊዜ እየደወለችና ኢ-ሜል እያደረገች ስራ ከምታስፈታኝ ዝም ብዬ ልመልስላት ብፈልግም እንኳን ፈፅሞ  ተግባራዊ ሊሆን አይችልም፡፡ ጥያቄዋና ክርክሯ ትክክል እንዳልሆነ፤ ከሌሎቹ ወላጆች ጋር አዲስ አበባ ላይ  በቂ ስፖንሰር ስላለመገኘቱ ተነጋግረን ተግባብተን የተለያየን መሆኑን ብነግራትም እርሷ እምቢ አሻፈረኝ ስላለች እንዴት ከሁሉ ወላጆች እኩል አዋጥታ የእርስዋ ብቻ ይመለሳል? የማይመስል ነገር ነው፤ የሚመለስ ነገር ካለ እንኳን ለሁሉም ነው መመለስ ያለበት፡፡ እናም ወ/ሮ መሰሉ አሰፋ የመጨረሻ ምርጫ አቀረበችልኝ፣ ብሩን ከመመለስ፤ አሊያም በወንድሟ በክንፉ አሰፋ ጋዜጣ ስሜ ከሚጠፋ? እውነት ለመናገር ብዙ ወዳጆች ጓደኞቼ ይህ ሰው በፃፈው ነገር ደንግጣችኋል፡፡ ነገር ግን የእኔ ስም እንደጠፋና እንደተዋረደ እቆጥረው የነበረው ሁሉም ወላጆች ያወጡትን 1,721 ዶላር ስሜ በወንድሟ ክንፉ አሰፋ ጋዜጣ ወይም ድህረ-ገፅ ላይ እንዳይጠፋ ፈርቼ ገንዘቧን ብመልስ ኖሮ ነበር፡፡ አሁን ግን ጋዜጠኛ ነኝ ባይ ፈርቼ ይኸን ባለማድረጌ ክብር ይሰማኛል፡፡ ማንም ሰው ቢሆን ለእንዲህ አይነት ጋዜጠኛ እጅ መስጠት የለበትም፡፡ ክንፉ አሰፋ ጉዳዩ ወይም ክርክሩ 1,721 ዶላር ለእህቴና የወንድሜ የዳዊት አሰፋ ገንዘብ ይመልስ ስለሆነ ስለዚህ ብቻ በመፃፍ ቢከራከር ያምርበት ነበር፤ ሀቀኛ ጋዜጠኛ እንደዛ ነው፡፡ ነገር ግን ክንፉ አሰፋ ብዙ ክፉ ነገር ጽፏል። ኢ-ምክንያታዊ የሆነው የእህቱን ገንዘብ ይመለስልኝ ጥያቄ (1,721 ዶላር) ቢመልስላት ኖሮ አሁን የፃፈውን ሁሉ ውሸት ስለሆነ አይፅፈውም ነበር፡፡ እውነት ቢሆንም እንኳን አይፅፈውም ነበር ምክንያቱም ወ/ሮ መሰሉ በላከችልኝ ኢ-ሜል ብሩ ከተመለሰላት ለሚዲያ እንደማታሳውቅ ገልጻ ነበር። ብራቸውን ካገኙ ስለሌላው ምን ገዶት፤ አሁን ግን ፀሀፊው ያስመስላል ለሀገርና ለህዝብ ተቆርቋሪ ይመስላል፡ ”ለሌሎች ትምህርት እንዲሆን ብዬ ነው የጻፍኩት” ይላል፡፡ “ሳታማሃኝ ብላኝ” አለች እንዲሉ!

(የወ/ሮ መሰሉ ኢ-ሜሉን ያንብቡት)

ይህን ያነሳሁት መነሻ ምንጩ ምን እንደሆነ እንድታስተውሉ እና ጉዳዩ የአንድ ጋዜጠኛ ወንድም አለን የሚሉ ቤተሰብ ስራ እንደሆነ እንድታውቁት ብዬ ነው፡፡ እንግዲህ ይህ ሰው ነው እንዚህን የመሳሰሉ ብሩህ አእምሮ ያላቸውን የወደፊቷ ኢትዮጵያ ተስፋ የሆኑትን ታዳጊዎች ” ናሳን ሊጎበኙ የመጡት ገንዘብ ሰጥተው ነው ” “ተርበው በየሬስቶራንቱ ፍርፋሪ ለመኑ”  “ታመው ሆስፒታል ገቡ” “ናሳን በቴሌቭዥን እንኳን ሳያዩ ተመለሱ” “ከኤምባሲ ቪዛ አውጥቶ ለወላጆች ሸጠላቸው” “ገንዘብ አንሰጥህም ያሉትን ቪዛ ለሌሎች ሸጠባቸው” በሚሉ ዘግናኝና አሳፋሪ በሆኑ መሰረተ-ቢስ ወሬዎች በገዛ እራሱ ድህረ ገፅ ላይ በመፃፍ ለህዝብ አሰራጭቷል፡፡

የወንድሙ ዳዊት አሰፋ ገንዘብና የእህቱ 1,721 ዶላር ካልተመለሰ በሚል የወደፊት የኢትዮጵያ ኩራት የሆኑትን ተማሪዎች ክብር የሚነካ እና ወላጆችን ያላደረጉትን አደረጉ ብሎ መፃፍ አልነበረበትም፡፡

ፀሐፊው ጽሁፉን ከጀመረበት ሳይሆን እኔ ዋና ጉዳይ ነው ብዬ ካመንኩበት፤ ናሳን ሳይጎበኙ ተመለሱ ካለው ልጀምር፦

  1. በአካባቢው የነበሩ የቤተሰብ አባላት አንድ ሃሳብ አመጡ፤ ኢትዮጵያዊ የጠፈር ሳይንቲስት የሆኑትን ዶ/ር ብሩክ ላቀውን፤ በጉዳዩ አማከሯቸው፤ ዶ/ር ብሩክም ፈቃደኛ ሆኑ፤ በወላጆች ትውውቅ የመጡት እኚህ ኢትዮጵያዊ ሳይንቲስት ህጻናቱ ካረፉበት ስፍራ ድረስ በመሄድ ስለናሳ አስረዷቸው፤ ህጻናቱ ይህችን እውቀት ይዘው ናሳን በቴሌቭዥን እንኳን ሳይመለከቱ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ“ ፀሀፊው በጣም ደፋር ነው የከበሩ አንጋፋ ሳይንቲስት ዶ/ር ብሩክ ላቀውን ስም ጠርቶ ባካባቢው በነበሩ ቤተሰብ ተጠርተው ሆቴል ድረስ መጥተው ልጆቹን ስለ ናሳ ማብራሪያ ብቻ ሰጥተዋቸው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ ብሏል፡፡ ዶ/ር ብሩክ ላቀው እና ዶ/ር ጥላዬ ታደሰ በቤተሰብ ትውውቅ የመጡ አይደሉም። ምናልባት ማስተዋወቅ ካለብኝ እኔ ልሆን እችላለሁ ለእርሱ ቤተሰቦች የማስተዋውቃቸው። እነዚህ ሁለት አንጋፍ ሳይንቲስቶች እንዲህ አይነት ማብራሪያ ናሳን ሊጎብኙ ለመጡ ተማሪዎች ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያ አይደለም። የአሁኖቹ የ2014 አሸናፊ ተማሪዎችን ከማግኘታቸው በፊት ካቻ አምና በ2013 የመጡ አሸናፊ ተማሪዎችን ሆቴላችን ድረስ በመምጣት ልዩ ልዩ ትምህርታዊ ማብራሪያዎችን በመስጠት ተመሳሳይ ጊዜ አሳልፈን ነበር፡፡ ከኔ ጋር የተዋወቅነው በ2013 ዓ.ም. ነው። (ፎቶግራፉን ይመልከቱ)

ስለዚህ እነዚህ ሁለት አንጋፋ ሳይንቲስቶች በቤተሰብ ተጠርተው ሳይሆን እንደ አምናው ሁሉ ሆቴል ድረስ በመምጣት ልጆቹን እንዲያገኟቸውና እንዲያበረታቷቸው ባደረኩላቸው ግብዣ ነው እንጂ በቤተሰብ ተጠርተው አልመጡም፡፡ የቤተሰብ አባላት ያለውን ነገር ወደኋላ ላይ አንስቼዋለሁ።

“ናሳን በቴሌቪዥን እንኳን ሳይመለከቱ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ“ ወደ አለው ነገር ልመልሳችሁ፤ ይህ የመጣንለት ዋና አላማ ነው፡፡ ናሳን ልንጎበኝ መተን ናሳን ሳንጎብኝ ልንመለስ እንዴት እንችላለን? እውነታው ይህ ነው፦ ተማሪዎቹ በሁለት አንጋፋ ሳይንቲስቶች ታጅበው በአሜሪካ ካሉት ሁሉ ዋና የሆነውን Greenbelt Maryland የሚገኘውን Goddard Senior Center NASA, January 7, 2015 ጎብኝተዋል ፡፡ ይህ በቀላሉ ሁለቱን ኢትዮጵያውያን ሳይንቲስቶች በመጠየቅ ማጣራት የሚቻል ነው፡፡ ተማሪዎች ከናሳ ጉብኝት መልስ ከዶ/ር ብሩክ ላቀው ጋር ያደረጉትን ውይይት ቪዲዮውን በፌስ ቡክ ገጼ ላይ በመግባት ይመልከቱ። (senakriem mekonnen)

ፀሐፊው ማብራሪያ ብቻ ሰጡ ያላቸው ዶ/ር ብሩክ ነዳጃቸውንና ሰዓታቸውን አቃጥለው ዶ/ር ጥላዬን ጨምሮ ከእኛ ጋር ፊትና ኋላ ተከታትለን በመሄድ ነበር Greenblet Maryland የሚገኘውን Goddard Senior Center NASA ን የጎበኘነው። ነገር ግን እዚህ ላይ ለአንባብያን ግልጽ እንዲሆን ናሳ ሲባል ሂውስተን ወይም በአንድ ቦታ ላይ ብቻ የሚገኝ ይመስላቸዋል። ናሳ በ10 የተለያዩ የአሜሪካን ስቴቶች ቅርንጫፍ አለው። ድህረ-ገጹን ይጎብኙ (https.//www.nasa.gov/centers/goddar.) በ2012 እና በ2013 የተጓዝነው ፍሎሪዳ ወደሚገኘው ናሳ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት (2014) በራሴ በጎ ፈቃድ ነው ሂውስተን ለመሄድ ያሰብኩት። ነገር ግን የሂውስተኑን ናሳ ጉዞ የሚያስቀይር አጋጣሚ ተከሰተ። ወደ አሜሪካን ለመጓዝ በግምት ሦስት ሳምንት ያህል ሲቀረን የናሳ ዋና አስተዳደር ሜጀር ጀነራል ቻርለስ ቦልደን ወደኢትዮጵያ እንደሚመጡ ሰማን። እኛም ይህን አጋጣሚ ተጠቅመን ለሜጀር ጀነራል ቻርለስ ቦልደን እቅፍ አበባ በማበርከት አቀባበል አደረግንላቸው። (የሜጀር ጄነራል ቻርለስ የአቀባበል ሥነ-ስርዓት ፎቶግራፍ እዚህ ላይ ይገባል)

ከዛም ወደ አዳራሽ ከገባን በኋላ በወቅቱ ከተማሪዎች ጋር የጥያቄና መልስ ጊዜ የነበራቸው ሲሆን፣ ልጆቹን አስቀድመን በሰጠናቸው ምክር መሰረት እርሳቸው የሚገኙበትን ናሳን መጎብኘት እንዲፈቅዱላቸው እና እንዲጋብዟቸው እንዲጠይቁ አበረታታናቸው። መጨረሻ ላይ ልጆቹ ጥያቄውን አቀረቡ። ሜጀር ጀነራል ቻርለስም ጥያቄውን በደስታ ተቀበሉት። ወደ ዲሲ ከመጣችሁ እዛው የሚገኘውን ናሳን እንድትጎበኙ ይፈቀድላችኋል አሏቸው። ልጆቹ በቃል ያቀረቡትን ጥያቄ እኔ አስቀድሜ በፁሁፍ አዘጋጅቸው ስለነበር እዛው አዲስ አበባ ላይ ፀሀፊያቸው እንድትረከበኝ አድረገዋል፡፡ እሷም አድራሻውን የያዘ ካርድ ሰጠችኝ አሜሪካን ስንደርስ በመጀመሪያ ወደ ናሳን ዋና መስሪያ ቤት (Headquarters Nasa ) ደውለን ከኢትዮጵያን እንደመጣን እና የናሳ ዋና አስተዳደር ሜጀር ጀነራል ቻርለስ ስትመጡ አግኙን እንዳሉን ለማስታወስ ብዙም አልደከመንም? ወቅቱ የአዲስ አመትና የክርሲማርስ ስለነበር ከበአል በኃላ Goddard NASAን እንድንጎበኝ ተፈቀደልን፡፡

ይኸ ለተማሪዎች አዲስ ነገር አይደለም ሆቴል ውስጥ ሆነን ያወጣነው አዲስ እቅድም አይደለም፡፡ ከተሳካልን ሜሪላንድ የሚገኘውን የእርሳቸው ቢሮን Goddard NASAን ለመጎብኘት፤ ነገር ግን እንደጠበቅነው እርሳቸው አጥተን ነገር ባይሳካ ሂውስተን ለመሄድ ተዘጋጅተን ነበር የመጣነው። እንደውም የዲሲ ሂውስተን የትራንስፖርት ወጪን ማትረፍ ችለናል። እናም በተፈቀደልን መሰረት በሁለቱ አንጋፋ ኢትዮጵያዊያን ሳይንቲስቶች ዶ/ር ብሩክ ላቀው እና ዶ/ር ጥላዬ ታጅበን Goddard Greenbelt Maryland የሚገኘውን Senior Center NASA ጎብኝተናል።

ሁሉም የናሳ ሴንተሮች የሚፈቀድና የማይፈቀድ ክልል አላቸው። Goddard ናሳ ሰፊና ልዩ ልዩ ላብራቶሪዎች ያለው ማዕከል ሲሆን፣ ልጆቹ የተለያዩ ኬሚካሎችን በመነካካት አደጋ ውስጥ እንዳይወድቁ ስለሚያሰጋ የተፈቀደላቸው ክልል ድረስ ብቻ እዚያው ውስጥ በሚሰሩት በዶ/ር ብሩክ እና በዶ/ር ጥላዬ፣ እንዲሁም በአንዲት አሜሪካዊት ሳይንቲስት ማብራሪያ እየተሰጣቸው ናሳ ውስጥ ቆይታ አደርገዋል፡፡ ስለ ህዋ ሳይንስ ማብራሪያ ተሰጥቷቸው ወጥተዋል።

ለዚህም Goddard ናሳን ጎብኝተው እንደወጡ እራሱ ናሳ የሠጠኝ ደብዳቤ (Official Letter) ምስክር ነው፡፡ ፀሀፊው ክንፉ አሰፋ ግን እግዚአብሄርን ሳይፈራ ሰውን ሳያፍር “ናሳን በቴሌቭዥን እንኳን ሳያዩት ዶ/ር ብሩክ ህፃናቱ ካረፉበት ድረስ በመሄድ ስለናሳ በቃል ብቻ አስረድተዋቸው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ” ብሏል። ይህን ያህል ሐሳዊ ፀሀፊ መሆኑን ካወቃችሁ አይበቃም፡፡ ፀሀፊው ይህ በቀላሉ መጣራት የሚችል አልመሰለውም። ሁሉቱም ሳይንቲስቶች ጋር ደውላችሁ ማጣራት ትችላላችሁ፣ ነገር ግን ከ “Headquarters Nasa“ የተሰጠው የሰነድ ማስረጃ ከበቂ በላይ ይመስለኛል፡፡

(የናሳ ዋና መ/ቤት የላከው ደብዳቤ እዚህ ይግባ)

  1. “በፎቶ ሾፕ የናሳን ማስክ አለበሳቸው” ይህ በጣም አስቂኝ ጉዳይ ነው። በመላው አለም የሚመጡ የተለያዩ ሀገር ተማሪዎች ትምህርታዊ ጉብኝታቸውን ሲጨርሱ ፎቶ መነሳት ስነ-ስርዓት ወደ ሚካሄድበት ቦታ ሲደርሱ ሁሉም ተማሪ ተስልፎ ወረፋ ጠብቆ ፎቶ ይነሳል። ፎቶው ሲታተም የኦስትሮናንትስ ልብስ ለብሰው የሚያሳየው ፎቶ ይወጣል፡፡ ይህ ተማሪዎች ለማስታወሻነት የሚነሱት ፎቶ ነው እንጂ ዋናውን የአስትሮናንትስ ልብስ ለብሶ የሚነሳ የለም፡፡ ድሮም ፎቶ ሾፕ ነው፡፡ የአምና የካች አምና ተማሪዎችም ፎቶ ሾፕ ነው፡፡ ወደፊትም ለሚመጡ ተማሪዎች ፎቶ ሾፕ ነው፡፡
  2. “በአካባቢው የነበሩ የቤተሰብ አባላት አንድ ሃሳብ አመጡ “ እነዚህ ቤተሰቦች እነማን ናቸው? በእኛ ጉዳይ ላይ ስብሰባ ያደረገም ሆነ ሃሳብ ያመጣ ቤተሰብ ፈጽሞ አልነበረም። የቤተሰብ አባል ስብሰባ፣ ምክክርም አስፈልጎም ተደርጎም አያውቅም። ምን ሆንን ብለን እንሰባሰብ? የፈጠራ ወሬ መሆኑን አስተውሉ። Goddard ናሳ ውስጥ በሳይንቲስቶች ማብራሪያ የተሰጣቸውን ልጆች በአካባቢው የነበሩ የቤተሰብ አባላት ዶ/ር ብሩክን ጋብዘው ለልጆቹ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው አደረጉ ብሎ መዋሸት ለምን አስፈለገ? ምክንያቱም ልጆቹ ናሳን ቦታው ድረስ በመሄድ ስለጎበኙ ሆቴላቸው መጥቶ ማብራሪያ መስጠት አያስፈልግም ነበር።

ነገር ግን ቤተሰቦች ሲል ስለ ወ/ሮ መሰሉ አሰፋ ቤተሰቦች ማለቱ ከሆነ፤ ዶ/ር ብሩክ ላቀውን ያገኟቸው ልጃቸው ሳሙኤል ዳዊት አሰፋን 1,721 ዶላሩን በመክፈል ስፖንሰር እንዲያደርጉላቸው ዶ/ር ብሩክን ለመጠየቅ ነው እንጂ ከዚህ ቀደም ምንም አይነት ትውውቅ አልነበራቸውም። ወ/ሮ መሰሉ ሳሙኤልን ስፖንሰር አድርግልን ብለው ዶ/ር ብሩክን ሲጠይቋቸው፤ ዶ/ር ብሩክ ገንዘብ መክፈል እንደማይችሉ፤ ነገር ግን ከፈለጋችሁ ልጁ እኔ ጋር እንዲያርፍ ማድረግ ትችላላችሁ አሏቸው። ቤተሰቡ ስለ ናሳ ለተማሪዎች ማባራሪያ እንዲሰጡላቸው ተማከሩ ብሎ መዋሸት ለምን አስፈለገ? ቤተሰቦቹ እኔን ናሳ ስፖንሰር አድርጎሀል ብቻ ሳይሆን ናሳ የሚሰራም ስፖንሰር ማድረግ ይችላል ብለው ያምናሉ። የኢኮኖሚ ሁኔታቸው ካልፈቀደላቸው ልጁ ዶ/ር ብሩክ ጋር ቢያርፍ እኔ ምንም ተቃውሞ አልነበረኝም። ዶ/ር ብሩክም ፈቅደውላቸው ነበር። ነገር ግን ከዛ በኋላ ስለአፈጻጸሙ ምንም ያወሩት ነገር የለም። ቤተሰቦቹ የጠየቁት የገንዘብ ጥያቄ ነበር። የተሰጣቸው ምላሽ ግን ልጁ እኔ ጋር ይረፍ የሚል ነበር፤ ይህ ያልተጠበቀ ምላሽ ነው። ጉዳዩን አስበውበት እስከ መጨረሻው መወያየት የነበረባቸው እነርሱ ናቸው፤ እኔ ደውዬ እባክህ ሳሙኤል አንተ ጋር ይረፍ ብዬ ምንም የማይተዋወቁ ሰዎች መሀል ገብቼ ልለምንላቸው አልችልም። ይህ የእኔ ኃላፊነትም አይደለም። ይህ ታሪክ ካለፈ አራት ወር ሆኖቷል። ወ/ሮ መሰሉ፣ ወንድሟ ክንፉ አሰፋ ስሜን ለማጥፋት ጽሁፉን እስካሰራጨበት ጊዜ ድረስ፤ በላከችልኝ ኢ-ሜልም ሆነ በስልክ ልጃችን ሳሙኤል ዳዊት ዶ/ር ብሩክ ጋር ማረፍ እየቻለ እኔን 1,721 ዶላር እንድከፍል አድርገኸኛል ብላለች።

  1. ወደ አስቂኝ የቪዛ ልብ ወለዳዊ ወሬ ልውሰዳችሁ፦

“የአስሩን ህጻናት ፓስፖርት ይዞ አሜሪካን ኤምባሲ ለቪዛ ሄደ” ይሄ ነገር ይቻላል? “በቂ የስፖንሰር ድጋፍ ስለነበረው ያለምንም ችግር የልጆቹን ቪዛ አገኘ” ቀጥሎ እንዲህ ይለናል። “ጨዋታው እዚህ ላይ ነው የሚጀምረው ስፖንሰሩንና ቪዛውን በእጁ ካስገባ በኋላ በተናጠል እየጠራ ገንዘብ ተቀበላቸው” “ወጪውን የማትሸፍኑ ከሆነ እድሉን ለሌሎች ልጆች እሰጠዋለሁ” ብሎ ገንዘብ ተቀበላቸው” “ይህን ወጪ መክፈል ያልቻሉ ህጻናት ተሰረዙ፣ የእነርሱ እድል ጥሩ ውጤት የሌላቸው ግን ገንዘብ ላላቸው ወላጆች ተሸጠ” ብሏል ክንፉ በድፍረት፡፡ ጸሐፊው ክንፉ አሁን ወደ ሚኖርበት ሀገር በህገ-ወጥ መንገድ የገባ ሰው ካልሆነ በስተቀር ቪዛ እንዴት እንደሚገኝ ማንም በህጋዊ መንገድ ቪዛ ያገኘ ሰው ያውቀዋል።

“የአስሩን ህጻናት ፓስፖርት ይዞ አሜሪካን ኤምባሲ ለቪዛ ሄደ” ከሚለው እንጀምር፣ በምን ሂሳብ ነው እኔ የልጆቹን ፓስፖርት ይዤ ኤምባሲ ገብቼ ቪዛቸው ተሰጥቶኝ ይዤ የምወጣው? ለዛውም ከአሜሪካን ኤምባሲ፤ የማንንም ፓስፖርት ይዤ አልገባሁም፣ አይቻልምም፣ ፀሐፊው የማያውቅ ከሆነ ተማሪዎች በህጋዊ አካሄድ የየራሳቸውን የቀጠሮ ፎርም ኦን ላይን ሞልተው፣ የኮቴ ከፍለው፣ አሻራ ሰጥተው፣ ተራ ጠብቀው፣ ሲጠሩ ከወላጆቻቸው ጋር ቀርበው ኢንተርቪው ተደርገው ነው ቪዛው የተሰጣቸው። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ እንዴት ሆኖ ነው ኤምባሲው የሌሎችን ቪዛ ለእኔ ሰጥቶኝ ከኤምበሲው ውጭ በተናጠል አንድ በአንድ እየጠራሁ ቪዛ መቸብቸብ የምችለው?

“ቪዛውን በእጅ ካስገባ በኋላ የሚለውን ሀረግ ልብ በሉ” የሌሎችን ቪዛ በእጄ ማስገባት የምችለውና ከዛም ለእነርሱ መልሼ የምቸበችበው” “እምቢ አንከፍልም” ባሉት ፈንታ ደግሞ ቪዛውን ሌሎች መክፈል ለሚችሉ መስጠት የቻልኩት እንዴት ነው? የአንድ ቪዛ እየተላጠ ሌላው ላይ መለጠፍ የሚችል ነገር ነው እንዴ? ይኸ ከአሜሪካ ኤምባሲ ሊገኝ የሚችል ሕጋዊ ቪዛ ሊሆን አይችልም፡፡

ክንፉ የፈለገውን ሲቀባጥር ዝም ተብሎ መታለፍ የለበትም እዚህ ጋር ቆም አድርገን በጥያቄ ልናፋጥጠው ይገባል፡፡ ቀጥሎ የጻፈውን ነገር አስተውሉ “ጫወታው እዚህ ላይ ነው የሚጀምረው ስፖንሰሩና ቪዛውን በእጅ ካስገባ በኋላ በተናጠል እየጠራ ወጪውን ሸፍኑ፣ ወጪውን የማትሸፍኑ ከሆነ ቪዛውን ለሌሎች አሰጠዋለሁ ብሎ መርዶ አመጣባቸው”፡፡ እንግዲህ ልብ በሉ ቪዛውን በእጅ ይዤ ነው በገንዘብ እየተደራደርን ያለነው እንደ ክንፉ ገለጻ፤ ከዛስ “ይኸን ወጪ መክፈል ያልቻሉ ሕጻናት ተሰረዙ፤ የእነርሱ ቪዛ ጥሩ ውጤት ለሌላቸዉ ገንዘብ ግን ላላቸው ወላጆች ተሸጠ” ይለናል ክንፉ አሰፋ።

ይህ እየሆነ ያለው የልጆቹን ቪዛ ከኤምባሲ ይዞ ወጣ ካለ በኋላ ነው፡፡ እንግዲህ ቪዛቸው የተነጠቁ አሉ እንደ ክንፈ አገላለጽ እንዴት ዝም አሉ? እነማን ናቸው? ሕግ የለም? የአንድ ቪዛ ነጥቆ ለሌላው አሳልፎ መስጠት ይቻላል? በክንፉ ልብ ወለዳዊ አገላለጽ ግን ተችሏል፡፡

እነዚህ በስማቸው የተሰጣቸውን ቪዛ ለሌሎች መክፈል ለሚችሉ በመስጠት የሰረዝናቸው ልጆች እነማን ናቸው? ቪዛው ከተሰጠ በኋላ ቪዛውን ከሰጠው አካል ውጭ ቪዛውን መሰረዝ ይቻላል? ይኸ ሁሉ ስረዛ ድለዛ እየተካሄደ ያለው እኔ ከኤምባሲ ውጭ ቪዛ ይዤ ከወጣሁ በኋላ ነው:: እንደ ክንፉ ጹሑፍ እነዚህ ገንዘብ ያላቸው ወላጆች ቪዛውን የገዙት እንዴት ነው? የድሃው ቪዛ እየተወሰደ ለሃብታሙ እየተሸጠ ነው፡፡ ከኤምባሲ ውጭ በተናጠል እየጠራሁ ማለት ነው፡፡ ጸሐፊው ክንፉ የተሸወደውን አንድ ነገር ግን ልንገራችሁ፦

ቪዛ ለመውሰድ ኤምባሲ ከመግባታችን በፊት ለናሳ የአሸናፊ ተማሪዎች ዝርዝር ከ2 ወር በፊት August 2014 ይላካል፡፡ ከናሳ የአሸናፊ ተማሪዎች ስም ዝርዝር የያዘ ደብዳቤ (Official Letter) ይደርሰናል፡፡ November 2014 ላይ ለአሜሪካን ኤምባሲም እንዲሁ።

አሁን እዚህ ላይ ነገሩ አለቀ። ከዚህ በኋላ “ሰማይ ዝቅ ምድር ከፍ” ቢል ምንም መጨመር መቀነስም አይቻልም፡፡ የተጓዦች ስም ዝርዝር ከናሳ በተላከው የግብዣ ደብዳቤ (Offical Invitation Letter) መሰረት እንጂ፣ እንደ ክንፈ ልብ-ወለዳዊ የፈጠራ ቪዛ ወሬ ከኤምባሲ ውጭ ክፈል ካልከፈልክ ትሰረዛለህ፣ ትደለዛለህ ዕድሉን ለሌሎች አሳልፌ እሰጠዋለሁ ለማለት ምንም ዕድል የለም አይቻልም፡፡ በክንፉ የግዴለሽ ልብ-ወለዳዊ ዓለም ግን ይቻላል፡፡ ክንፉ እንደሚለው ማድረግ፤ የደሀውን ቪዛ መሰረዝ፣ ለሌሎች ገንዘብ ላላቸው መሸጥ፣ አይቻልም፤ ምክንያቱም ወጪውን ሸፍኖ መሄድ እንኳን ባይችል ቪዛውን ግን ማንም ሊነካበት አይችልም። ክንፉ ግን ተደርጓል ብሏል።

ከናሳ የግብዣ ደብዳቤ (Official Invitation Letter) ከመጣ በኋላ አሁን እኔ ምንም ነገር የመቀየር ኃይል የለኝም እንደውም ወላጆች ከአሁን በኋላ እኔን ዞር በል ማለት ይችላሉ፤ በናሳ ተጋብዘዋል፣ ልጆቹም በስማቸው ሕጋዊ ቪዛ ተቀብለዋል፡፡ ይኸ ቪዛ ከዚህ በኋላ ማንም ሊቀማቸው አይችልም ያ ነው ቅደም ተከተሉ። ስለዚህ ወላጆች እኛ ገንዘብ ስናገኝ በፈለግነው ቀን መጓዝ እንችላለን አንተ ግን መንገድህን ጨርቅ ያርግልህ ማለት ይችላሉ “አቶ ክንፉ ግን ትንሽ እንኳ አያፍርም”  ጨዋታው እዚህ ላይ ነው የሚጀመረው ብሎ አንባቢ ለወሬ እንዲቋምጥ አድርጎ፤ ግን ወበከንቱ የሆነ ጨዋታ ፈጽሞ በምድር ላይ ያልተደረገ ሊደረገም የማይችል ጨዋታ አጫወተን። ቢያንስ ስለዚህ ነገር አንባቢያንን ይቅርታ መጠየቅ አለበት። ፈጥሮ ማውራትም ችሎታ ይጠይቃል፡፡

  1. “ዘረፋው በዚህ መልክ ተፈጸመ”

ውድ አንባብያን ዘረፋው እንዴት ተካሄደ እንደሚል አስተውሉ፡ ያስኬዳል?

ወላጆች የከፈሉት ገንዘብ አንድ ሚሊዮን ብር ይጠጋል። ይህ ክንፉ እኔን ሚሊየነር ያደረገበት ልብ-ወለድ ነው “ዘረፋው ተፈጸመ የተባለው፤ እንደ ክንፉ አገላለጽ ቪዛ ከኤምባሲ ይዤ ከወጣሁ በኋላ ነው” ቪዛውን በመሸጥ፣ በመለወጥ የደሀውን ቪዛ እየቀሙ ለሃብታሞች በመሸጥ ነው ገንዘብ የተገኘው ብሏል። የአንድን ሰው ቪዛ ለሌላው መሸጥ፣ መለወጥ እንደማይቻል ከፍ ብለን አይተናል። ታዲያ ይህ የማይቻል ከሆነ ወላጆች ከፈሉ ያለው አንድ ሚሊዮን ብር ከየት መጣ? ይህ ማጭበርበር ይባላል። ክንፉ ግን በድፍረት ዝርፊያው የተፈፀመው እንደዛ ነው ብሏል። ቀጥሎ ያለውን ያንብቡ፦

“የአስሩን ህጻናት ፓስፖርት ይዞ አሜሪካን ኤምባሲ ለቪዛ ሄደ”… “ያለምንም ችግር የልጆቹን ቪዛ አገኘ”  አሁን ፓስፖርትና ቪዛ እጄ ላይ ነው። ክፈሉና ቪዛ ውሰዱ አልኩ፤ እምቢ ወይም አንችልም ሲሉ፤ ቪዛውን ለሌሎች ሸጥኩት፤ ዘረፋው በዚህ መልክ ተፈጸመ፤ እንደ ክንፉ ገለጻ።

“ይህን ወጪ መክፈል ያልቻሉ ህጻናት ተሰረዙ፣ የእነርሱ ቪዛ ለሌሎች ጥሩ ውጤት ለሌላቸው ግን ገንዘብ ላላቸው ወላጆች ተሸጠ” ዘረፋው በዚህ መልክ ተፈጸመ። ይህ የሌሎች ተማሪዎችን ቪዛ መሸጥ በህልም እንኳ አይቻልም። ለዛውም የአሜሪካን ኤምባሲ ቪዛ። በዚህ መልክ ዝርፊያ መፈጸም ይቻላል? ካልተቻለ ወላጆች ሳይከፍሉ ከፈሉ የተባለው አንድ ሚሊዮን ብር ከየት መጣ? ስለዚህ ሚሊየነር አልሆንኩም ማለት ነው።

  1. ለአቶ ክንፉ አሰፋ

እኔ የገንዘብ ሰው ብሆን ኖሮ የወንድምህ ልጅ ሳሙኤል ዳዊትን አላመጣውም ነበር።

ታሪኩ እንዲህ ነው።

ሁሉም ወላጆች ወደውና ፈቅደው ወጪያቸውን ከፍለው አሜሪካን ልንመጣ ስንዘጋጅ፣ ወንድምህ ዳዊት አሰፋ ግን ገንዘብ የለኝም አሜሪካ ስትደርስ አቶ እከሌ ይሰጡሃል ብሎኝ ገንዘብ ሳይከፍል የወንድምህን ልጅ ሳሙኤል ዳዊት አሰፋን አሜሪካን ይዠው መጣሁ። ሁሉም ከፍለው ሳይከፍል የመጣው ግን ሳሙኤል ዳዊት ብቻ ነው። አንተ እንደምተለው እኔ የገንዘብ ሰው ብሆን ኖሮ፣ ቪዛ ገንዘብ ላላቸው ሸጬ ቢሆን ኖሮ ከሳሙኤል ቤተሰቦች ጋር ጭራሽ አንገናኝም ነበር። ለዛውም አሜሪካ ስትደርስ ይሰጡሃል የተባሉት ግለሰብ እንኳ፤ እኔ ገንዘብ እከፍላለሁ ብዬ ቃል አልገባሁም በማለታቸው ሳሙኤል ወጪውን የሚከፍልለት ሰው ስለጠፋ አክስቱ ወ/ሮ መሰሉ አሰፋ ከካናዳ ድረስ መጥታ ቤተሰብ በሙሉ አዋጥቶ የሳሙኤል 1,721 ተከፈለ። ወ/ሮ መሰሉ እስከ አሁንም እስከ መጨረሻዋ የደም ጠብታ ድረስ የምትታገልለት ይኸው ገንዘብ ነው። እኔ የገንዘብ ሰው ብሆን ኖሮ የአሸናፊ ተማሪ ወላጆች ወጪያቸውን መሸፈን እንዳለባቸው ህዝብ በተሰበሰበበት በአደባባይ አልናገርም ነበር። አንተ እንዳልከው ገንዘብ ለማግኘት ሌላ መንገድ ነበር። ለውድድሩና ለጠቅላላ ጉዞው ትክክለኝነት ቁጥር አንድ ምስክር መሆን የነበረባቸው የሳሙኤል ቤተሰቦች ነበሩ። አሁን ግን ሳሙኤል ዳዊት የመጣው የሌላ ሰው ቪዛ ገዝቶ ነው እያልክ ነው። አይ እርሱ እንኳን ጎበዝ ስለሆነ ነው፤ በውጤቱ ነው፤ ማለት ደግሞ አትችልም። ታዲያ እነማን ናቸው ቪዛ ገዝተው ነው የመጡት የምትላቸው ወላጆች? አንተ ከሳሽ፣ ቪዛ ገዝተው መጡ ያልካቸው ወላጆች ተከሳሽ፣ ደሞ መልሰህ ዳኛ መሆንማ አትችልም። መክፈል ያልቻሉ ተሰረዙ፣ ቪዛው ገንዘብ ላላቸው ተሸጠ ካልክ፤ አስቀድሞ ገንዘብ የመክፈል አቅም ሳይኖረው ወደ አሜሪካን ሀገር ይዤው የመጣሁት ሳሙኤል ዳዊት ቪዛው በተሸጠ ነበር። ይልቁንም በጽሁፍህ መግቢያ ላይ ሁሉም ተማሪዎች “አገሪቱ የምትኮራባቸው፣ ከፍተኛ፣ እጅግ ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ታዳጊዎች ናቸው ብለህ ባመሰገንክበት አንደበትህ ግማሹ ቪዛ ገዝቶ ነው ማለት አልነበረብህም። እኔን ለማክፋፋት ብለህ። አሁን ደግሞ ክንፉ ሆን ብሎ ወዳቀነባበራቸው ሌሎች የፈጠራ ወሬዎች ልውሰዳችሁ፦

  1. በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኝ በአንድ የገበያ ማዕከል (ሞል) ጥሏቸው ጠፋ” “ፖሊስ ሁለት ጊዜ ያዛቸው” ከሚለው እንጀምር። ሳይጠፉ ጠፉ ብሎ መጻፍ እኔን ብቻ ሳይሆን እስከ መጨረሻ ከእኛ ጋር የነበሩትን ቤተዘመዶችን በሙሉ አስገርሟል። በመጀመሪያ ዲሲ ወደሚገኘው ሞል አንድም ቀን ሂደን አናውቅም። ሁል ጊዜም ሞል ከሄድን እዛው ያረፍንበት ሆቴል አካባቢ (ሲልቨር ስፒሪንግ) ወደሚገኝ ሞል ነው የምንሄደው። እንግዲህ ልብ በሉ፤ እኔ የለሁም ጥሏቸው ጠፋ ብሏል፤ “እነዚህ ልጆች ጠፍተው ሲንከራተቱ የአሜሪካን ሀገር ፓሊስ አግኝቷቸው፤ ሆቴላቸው አድርሷቸው፤ ለእኔም ምክር ቢጤ ተሰጥቶኝ እንዲሁ በዋዛ ተለያየን ማለቱ ነው?

ልጆቹን ሜዳ ላይ ጥዬ ፓሊስ አግኝቷቸው ይህን የሚያህል ሀላፊነት የጎደለው ስራ ሰርቼ እንዲሁ የምታለፍ ይመስላችኃል ? ለዛውም በአሜሪካን ሀገር ፓሊስ እኔ እስከማቀው ይህ ከባድ ወንጀል ነው፡፡

ይህ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ፤ ልጆቹን በሀገሪቱ ውስጥ ላለው የኢትዮጵያ ኢምባሲ፣ እኔን ደግሞ ለሕግ አሳልፈው ይሰጡኝ ነበር ብዬ አምናለሁ። አስራ ሁለት ተማሪዎች በአሜሪካን ሀገር ጠፍተው ተገኝተው ቀላል ነገር ነው? ለዛውም ሁለት ጊዜ ጠፍተው ተገኝተው? በአሜሪካን ሚዲያዎች ትልቅ ዜና ሳይሆኑ የሚቀሩ ይመስላቹኋል? ፍርዱን አሜሪካን ሀገር ላላችሁ ኢትዮጵያውያን ትቼዋለሁ፡፡

  1. በረሀብ ተቀጡ” “በየሬስቶራንቱ ዞረው ለምነው በሉ“ረሀብ ጸንቶባቸው ሆስፒታል የገቡ አሉ”

ካልጠፋ ወሬ አሜሪካን ሀገር ሌላው ይቸግረን እንጂ ምግብ ተራቡ፣ የሚበሉት አጥተው በየሬስቶራንቱ ዞረው ፍርፋሪ ለምነው በሉ፣ ብሎ መጻፍ ግን በጣም የሚዘገንን የራሱ የክንፉ ከፉ የፈጠራ ወሬ ነው፡፡ ዲሲ-ሜሪላንድ እና ቨርጂኒያ መምጣት ማለት አዲስ አበባ የመምጣት ያህል ነው፡፡ የልጆቹ ቤተ-ዘመዶች አክስት አጎቶች ወዳጆች ብዛት ቁጥር ስፍር የለውም ኬኰች፣ ኩኪሶች፣ ቤት ውስጥ የተሰሩ የሐበሻ ምግቦች፣ ይህም ያም ያመጣላቸው ነበር። ከመደበኛ ቁርስ፣ ምሳ፣ እራት ውጪ በመሐል የሚበላ ነገር እንኳን ቢያሰኛቸው እዛው ሆቴሉ በእንግዳ መቀበያ ክፍል ጠረጴዛ ላይ ሁልጊዜም ኩኪሶች፣ ወተት፣ ሻይ አለ፡፡ በሩማችን ጠረጴዛ ላይም በየቀኑ ዘመድ አዝማድ በመጣ ቁጥር የሚያመጣላቸው ምግብ ሞልቷል፡፡ እኔ እንኳን በረሃብ ልቅጣቸው ብል፣ ያ ሁሉ ዘመድ አዝማድ የት ሄዶ ነው ይህ ሊሆን የሚችለው? በዚህ ጉዞ አሸናፊ ሆኖ የመጣው የሳሙኤል ዳዊት አሰፋ አክስት ወ/ሮ መሰሉ የጸሐፊ ክንፉ አሰፋ እህት ማለት ነው፤ ከካናዳ ድረስ ቤተሰቧን ይዛ መታ እኛ ያረፍንበት ሆቴል ውስጥ በግምት ከ4-5 ቀን ቆይታለች፡፡ ሳሙኤል ሌሎች ቤተ-ዘመዶች እንዳደረጉት ሁሉ ልብስ ተገዝቶለታል፤ ዶላር በዶላር ሆኗል፡፡ እርስ በእርስ ሲገባበዙ የተማሪዎቹን የዕለት ተዕለት ሁኔታ ስታይ ስታደንቅ፣ አብራ ፎቶ ስታነሳ፣ ፊልም ስትቀርጽ ቆይታ ነው የሄደችው፡፡ ታዲያ እንዴት ብሎ ነው “በህጻናት መብት ዙሪያ ላይ ነው የምንሰራው” የምትለው የጸሐፊው የክንፉ አሰፋ እህት ሲራቡ፣ ሲጠሙ፣ የሚበሉት አጥተው ፍርፋሪ ለምነው ሲበሉ እያየች እየሰማች ዝም አለች? ወንድሟ ጋዜጠኛ ክንፉ አሰፋ እንዲህ ዓይነት ሥነ-ምግባር የሌለው ነገር ሲፅፍ እርሷንም ተባባሪ ወንጀለኛ ማድረጉን ረሳው? በአጋጣሚ በኪሱ ዶላር ሳይዝ የመጣ ልጅ የለም፡፡ “በነገራችን ላይ ጎበዝ ሆነው አቅም የሌላቸውን የመንግስት ት/ቤት ተማሪዎችን ለማሳተፍና ለማምጣት ነው ኩፖን እየሸጥን ፈንድ ሬዝ የምናደርገው” ወደ ልጆቹ ልመልሳችሁ እና ቢርባቸው እንኳ በየሬስቶራንቱ ፍርፋሪ ለምነው ሳይሆን ሜኑ አስቀርበው ምግብ ማዘዝ የሚችሉበትን የኢኮኖሚ አቅም አላቸው፡፡ በየሬስቶራቱ ፍርፋሪ ለምነው ለመብላት የህይወት ደረጃቸው እንኳን አይፈቅድም፡፡ በነገራችን ላይ ልጆቹ ትንሽ መብታቸው ቢጓደል ስልክ አላቸው፤ ደውለው ቤተ-ዘመዶቻቸውን መጥራት፣ የሆኑትን መናገር የሚችሉ እንጂ የፈለጋችሁትን የምታደርጓቸው ተራ ህጻናቶች አይደሉም፡፡ ልጆቹም በየቀኑ ከወላጆቻቸው ጋር በስልክ ሲያወሩ ስለመራባቸው፣ በየሬስቶራንቱ ፍርፋሪ ስለመለመናቸው እና ረሀብ ጠንቶባቸው ሆስፒታል ስለመግባታቸው እንዴት አልነገሯቸውም? ወይስ ወላጆች የልጆቻቸውን ደህንንት ዕለት ዕለት አያጣሩም ነበር ነው የሚለን? ወይስ አሜሪካን ሀገር ስልክ የለም? ምናልባት ፀሐፊው ልጅ የለውም እንጂ ማንም ወላጅ የልጁን ድምጽ ሳይሰማ ማደር እንደማይችል ይገነዘብ ነበር። በዚህ ጉዞ አብረውኝ ከኢትዮጵያ የመጡ የአንዳንድ ልጆች ቤተሰቦችም እንደነበሩና ብቻዬን እንዳልነበርኩ፣ ሁለት የወንድና የሴት ጠባቂዎች (Male Chaperone & Female Chaperon) እንደነበርን ለፀሀፊው ያወሩለት ሰዎች ሳይነግሩት ቀርተዋል ማለት ነው?

በዚህ ጉዳይ ላይ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ከእኛም ጋር ያሳለፉ የዲሲ፤ የሜሪላንድ እና የቨርጂንያ ነዋሪዎች፣ ቤተ-ዘመዶች በተፃፈው ውሸት አዝነዋል፡፡ ምስክርነታቸውንም ለመስጠት ፈቃደኞች ናቸው። አላማው የእኔን ስም ለማጥፋት ከሆነ ደግሞ በልጆቹ ላይ ክፉ ደግ ማውራት ምን አስፈለገ? ! ፀሀፊው ልጆቹ በየትምህር ቤቱ ተርባችሁ ነበር፤ ፍርፋሪ ለምናችሁ በልታችሁ ነበር እንዲባሉ አድርጓል፡፡

  1. “አስሩን ህፃናት በአንድ መኪና (ትራክ) ውስጥ አጭቆ ነው የወሰዳቸው …..“የያዛት መኪና ከ4 ሰው በላይ መጫን አትችልም “

እንደው ግን እግዚአብሄር ያስመልክታችሁና 4 ሰው የምትጭን መኪና ባይነ ህሊናቸው ሳሏት እና 12 ሰው እዛች መኪና ውስጥ ታጭቀው መሄድ ሲቻል? ያለነው አሜሪካን ሀገር መሰለኝ?! 4 ሰዎች ብቻ በምትጭን መኪና 12 ሰው ታጭቆ መሄድ ህግና ደንብ ባለበት ስርዓት በሚከበርበት ሀገር በአሜሪካ ይቅርና በሱማሌ ሞቃድሾ እንኳን የሚሞከር አይመስለኝም፡፡

ፀሀፊው ለአንባቢያን ምንም ክብር የሌለው ሰው ነው፡፡ ትንሽ ይታዘቡኛል ማለት መቻል ነበረበት፡፡ እኛ ዘወትር አንድ መኪና ብቻ ኖሮን አያውቅም። ብዙ ቤተ-ዘመዶች በየተራ እየተተካኩ አገልግለውናል፤ ወ/ሮ መሰሉ አሰፋም ጭምር። አሁን ግን ነገሩን ለማክፋፋት ስለሆነ የተፈለገው መኪናችን 4 ሰው ብቻ የምትጭን ሆናለች። በርግጥ የመኪና እጥረት ሲያጋጥም ሰፋ ያለ ወንበር ያላቸው መኪኖች ላይ አንድ ለሁለት ተጠጋግተው ተቀምጠዋል፤ ይህ ደግሞ ሁሌም ስለማይሞላ ምንም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን 4 ሰው በምትጭን መኪና ታጭቀው ሄደው አያውቁም፡፡

  • ታመው ሆስፒታል የገቡ አሉ

ሌላኛው የፈጠራ ወሬ ደግሞ “ታመው ሆስፒታል የገቡ አሉ” የሚለው ነው፡፡ ፀሐፊው ክንፉ ይኸን የነገረኝ የ11 ዓመት ሕጻን ነው ብሏል፡፡

ጸሐፊው የሚያወራው እኔ ናሳ እንዲጎበኙ ይዣቸው ስላመጣኋቸው ልጆች ነው? በ3 ዙር 23 ልጆች ናሳን አስጎብኝቻለሁ፤ እግዚአብሔር ይመስገን እስካሁን ድረስ አንድስ እንኳ አልታመመብኝም፤ እንኳንስ ሆስፒታል ሊገቡ። ምን አልባት ጸሐፊውን መጠየቅ ካለባችሁ? ሆስፒታል የገባው ልጅ ማን ነው? የትኛውስ ሆስፒታል ነው የገባው? ለዚህ ቀጥተኛ ምላሽ ማቅረብ አለበት፡፡ እዚህ ላይ ልብ በሉ ይህን አለ ያለው “የ11 ዓመት ዕድሜ ያለው ልጅ ነው” የ11 ዓመት ዕድሜ ያለው ልጅ ደግሞ ሳሙኤል ዳዊት አሰፋ(የፀሐፊው የክንፉ አሰፋ የወንድም ልጅ) ነው፡፡ ሌሎች ልጆች ጨርሶ ከጋዜጠኛው ጋር አልተገናኙም፡፡ ስለዚህ “ሆስፒታል የገባ ልጅ አለ” ያለው ሕጻን ሳሙኤል ዳዊት አሰፋ መረጃ ማቅረብ አለበት፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ደግሞ ምንም ዓይነት መረጃ ሊቀርብ አይችልም፡፡ መረጃ ካልቀረበ ደግሞ ልጁ ወላጆች በል ብለውታል፣ እንዲዋሽ አርገውታል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ማስረጃ በአፋጣኝ መቅረብ አለበት።

እንግዲህ የአሜሪካን ሀገር ሆስፒታሎች ተራ የመንደር ክሊኒኮች አይደሉም። ቆይ “እኔ የምለው ጸሐፊው ክንፉ አሰፋ የሚኖረው አውሮፓ ሲሆን፣ ከካናዳ እንዲህ ብለህ ጻፍ የምትለው እህቱ መሰሉ አሰፋ፣ ከኢትዮጵያ እንዲህ ብለህ ጻፍ የሚለው ዳዊት አሰፋ (የክንፉ አሰፋ ወንድም)፣ እንዲህና እንደዛ አለኝ የሚለው የ11 ዓመት ልጅ ሕጻን ሳሙኤል ዳዊት አሰፋ እንዴት ሆኖ ነው ይኸ ጹሑፍ ልክ ሊሆን የሚችለው? ስለጉዳዩ እኔን መጠየቅስ አልነበረበትም? ሌሎች ሁለት ወላጆች የኛም ገንዘብ ይመለሳል በሚል የአቶ ዳዊትን ቤተሰብ የተቀላቀሉ እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ የእነርሱን ልጆች እንኳ አሉ እንዳይባል ዕድሜያቸው ከ11 ዓመት በላይ ስለሆነ እነርሱ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ይህን ሳነብ በጣም ነው ያዘንኩት፤ የተባለውን ገንዘብ ለማግኘት ሕጻናትን እንዲህ በሉ ብሎ ማስዋሸትና ውሸት ማስለመድ ደረጃ ተደርሷል ማለት ነው፤ አሊያም ፀሐፊው ክንፉ አሰፋ ዋሽቷል ማለት ነው። ፀሐፊው ግን ይህን ሁሉ ሲጽፍ መቼም ቢሆን አያጣሩም፣ ምንም ይጻፍ፣ ምንም ዝም ብለው የሚያምኑ፣ የሚቀበሉ፣ የሞሏቸውን ዝም ብለው የሚሞሉ፣ ባዶ ጠርሙሶች ናቸው ብሎ ይመስላል። እስከዛሬም በዚህ እሳቤ ሲጽፍ የኖረ ጸሀፊ ነው እንጂ የታመመ ሳይኖር፣ ሆስፒታል የገባ አለ ብሎ መጻፍ አንባቢያንን፣ ወላጆችንና ተማሪዎችን በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያለውን ንቀት የሚያሳይ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ወላጆችን መጠየቅ ለምትፈልጉ ስልካቸውን ልሰጣችሁ እችላለሁ።

  • ወደ ዋናው ድራማ ደግሞ ልውሰዳችሁ እና ፀሐፊው “አሜሪካን ዋሽንግተን ዲሲ እንደገቡ ለአንድ ቀን ብቻ በማሪዮት ሆቴል ቆይታ ያደርጋሉ፤ በነጋታው ሁሉም በአንድ ትራክ ተጭነው እዚህ ግባ የማይባል ሆቴል ውስጥ በቡድን በቡድን ታጎሩ” ይለናል።

አሜሪካን እንደገባን ዳላስ ኤርፖርት አጠገብ Spring Hills Hotel አረፍን። ነገር ግን ቨርጂኒያን ለምታውቁ ዳላስ ኤርፖርት አካባቢ ለሁሉም ነገር በጣም ሩቅ ነው። እናም በማግሥቱ እርሱ በትራክ ታጭቀው ያለውን “እኛ ግን በቤተሰቦቻቸውና በወዳጅ ዘመዶቻቸው ታጅበን ዳውንታውንSilver Spring ሜሪላንድ ወደሚገኘው Hampton Inn By Hilton ሆቴል ገብተን አርፈናል። ቦታውን ለምታውቁ እዚህ ቦታ ላይ መሆናችን እድለኞች ነን። ለወዳጅ ዘመድ ቅርብ ከመሆን አልፎ ሁሉ ነገር በቅርብ ርቀት ይገኛል። እስቲ የሆቴሉን ጥራት ድህረ ገጹን በማየት ይታዘቡ። (Hampton Inn Silver Spring) ሆቴሉ እዚህ ግባ የማይባል ነው? እዚህ ላይ ግን ፀሐፊው ክንፉ አሰፋ የረሳው እህቱ ወ/ሮ መሰሉ አሰፋ እና ቤተሰቧ ከካናዳ መጥታ በዚህ ሆቴል በግምት ከ4 እስከ 5 ቀናት አርፈው የነበረ ሲሆን፣ ስራዬ በህጻናት መብት ዙሪያ ላይ ነው (Childrene with Crew Members) ለሚባል ካምፓኒ ነው የምሰራው የምትለው ወ/ሮ መሰሉ ወንድሟ ፀሐፊ ክንፉ አሰፋ እዚህ ግባ የማይባል ብሎ የጠራው ሆቴል ውስጥ “ልጆቹ በቡድን በቡድን ታጉረው ሲሰቃዩ ስታይ እንዴት ዝም አለች! እንዴትስ እዛው ጥላቸው ሄደች? “እዚህ ግባ የማይባል ሆቴል ከሆነስ እርሷ ከነቤተሰቦቿ ለአራት አምስት ቀን እንዴት እዛው አረፈች? ለልጆች ኃላፊነት አይሰማትም? ፀሀፊው ይህን ጽሁፍ ሲያቀነባብር መርሳት ያልነበረበት ነገር፤ ወላጆች ቤተሰቦች፣ ዘመድ አዝማዶች ሁሌም ከእኛ ጋር እንደነበሩ ነው።

እዚህ ላይ ግን ይህ ሰው ጽሁፉን ያለ ምንም መረጃ እንዲሁ ያቀነባበረው የፈጠራ ወሬ መሆኑን እንድታስተውሉ ለአንድ አፍታ ወደ ኃላ ልመልሳችው እና አብረን እንገምግመው።

  • ክንፉ የቤተሰብ አባላት ያላቸው ሰዎች በእርግጥ ከነበሩ ምን ማድረግ ነበረባቸው? የክንፉ ጽሁፍ እርስ በእርሱ እንደሚቃረን አስተውሉ። ከላይ መግቢያ ላይ ልጆቹ አንድ የሆነ የሚደርስላቸው የሌለበት ሀገር ውስጥ ምንም ሃይ ባይ ከልካይ ትልቅ ሰው ቤተሰብ የሆነ ደራሽ ያጡ አድርጎ ያስቀምጣቸዋል በ21 ኛው ክፍለ ዘመን በዳውንታውን ሲልቨር ስፒሪንግ ውስጥ እነዚህ የክንፉ ልቦለዳዊ “ በረሃብ ተሰቃዩ “ የሚበሉት አጥተው ፍርፋሪ በየሬስቶራንቱ ለምነው በሉ፣ ሁለት ግዜ ሞል ውስጥ ጠፍተው በፖሊስ ተገኙ፣ እዚህ ግባ የማይባል ማረፊያ ውስጥ (Hampton Inn by Hiliton) ሆቴል ውስጥ ሳይሆን በቡድን በቡድን ታጉረው በአንድ ክፍል ውስጥ ተቆልፈው ይውላሉ፣ በአሜሪካን ሀገር በረሃብና በጥማት እየተሰቃዩ ነው፣ ረሃብ ፀንቶባቸው ሆስፒታል የገቡ አሉ፣ በምግብ ማጣት ጉዳት ሆስፒታል ገቡ የሚለው ቃል 3 ጊዜ ተደጋግሟል፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ ነው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም በሆነ ነገር ታመው ሆስፒታል ቢሄዱ ምንም አልነበረም። አሁን ግን በረሃብ ምክንያት ሆስፒታል እስከ መግባት ደረጃ ተደርሷል። በመጀመሪያዎቹ ቀናቶች ማክዶናልድ ይወስዳቸው ነበር። ከዚያ በኋላ ነው የረሳቸው። በነዚህ ታዳጊዎች ላይ የደረሰው በደል አንድ አሳዛኝ ፊልም ይወጠዋል ይለናል።

እንግዲህ ከላይ የተዘረዘሩትን ቃላት አስተውሉ። እነዚህ ልጆች ምኑን ተረፉ፣ ስቃይ፣ ረሃብ፣ ጥማት ጸንቶባቸው ሆቴል ሳይሆን የሆነ ማረፊያ ቤት ውስጥ ሰው እንዳያያቸው፣ እንዳያገኛቸው ተቆልፎባቸው የሚውሉ ልጆች ናቸው። እነዚህ ልጆች ይህ ሁሉ ስቃይና መአት እየወረደባቸው ነው። በክንፉ የውሸት ልቦለዳዊ አገላለጽ፤ ምን አለፋችሁ በጣም ከባድና አሳሳቢ የህይወት ደረጃ ላይ ናቸው። ክንፉ ግን ትንሽ ቅፍፍ እንኳን ሳይለው ዝቅ ብሎ “በአካባቢው የነበሩ የቤተሰብ አባላት አንድ ሀሳብ አመጡ። ኢትዮጵያዊውን ዶ/ር ብሩክ ላቀውን አማክረው ህጻናቱን ከታጎሩበት ስፍራ ድረስ በመሄድ ስለ ናሳ አስረዷቸው ይለናል። ይህ እጅግ በጣም የሚዘገንን ነገር ነው። አሁን እነዚህ ልጆች የሚያስፈልጋቸው የሳይንስ ትምህርት ወይስ ደህንነት? እነዚህ የክንፉ የፈጠራ ልቦለዳዊ ቤተሰቦች በጣም ጨካኞች ናቸው ማለት ነው። እነዚህን በሞትና በህይወት መካከል ያሉ አሜሪካን ሀገር በረሃብ እየተቀጡ ፍርፋሪ በመለመን ደረጃ ላይ ያሉ፣ በቡድን በቡድን ታጉረው ተቆልፈው የሚውሉ፣ ረሃብ ፀንቶባቸው ሆስፒታል የገቡ ያላቸው ህጻናትን ቶሎ ብሎ ተሯሩጦ ከማዳን ይልቅ ከተማከሩም ስለ ልጆቹ ጤንነትና ደህንነት እንጂ ስለናሳ ማብራሪያ ስጡልን ይሏቸዋል? እነዚህ ቤተሰቦች አምቡላንስ ጠርተው፣ ኢትዮጵያ ኤምባሲ ደውለው ልጆቹን ማዳንና ማትረፍ አይበልጥባቸውም? እንዲህ እየተሰቃዩ ላሉ ልጆች በባዶ ሆዳቸው ስለ ህዋ ሳይንስ ማብራራትና ማስረዳት ለምን ጥንቅር ብሎ አይቀርም። ከላይ አገር ተቃጠለ ሲለን የነበረው ክንፉ አሁን ስለ ናሳ ማብራሪያ እየተሰጣቸው ነው ይለናል። ይህ እንግዲህ የክንፉ ልቦለዳዊ ጽሁፍ እንደሆነ እንድታስተውሉ ብዬ ነው።

  • ፀሀፊው እራሱ ክንፉ አሰፋ ነው ዋና አዘጋጅ (Chief Editer) እርሱ ነው፣ ድህረ ገፁ የሱ ነው፣ ጉዳዩ የእህቱ ወ/ሮ መሰሉ እና ዳዊት አሰፋ ለሳሙኤል ዳዊት አሰፋ ጠቅላላ ፍጆታ የዋለውን 1,721 ዶላር እንዲመለስ ነው በአጠቃላይ “Family issue“ ነው ፀሀፊው በጉዳዩ ላይ የእኔን ሀሳብ መስማት አልፈልግም። እህቱ ያለችውን፣ ወንድሙ ዳዊት አሰፋ ያለውን፣ የ11 ዓመቱ ሳሙኤል ዳዊት አሰፋ ያለውን፣ ወይም በል የተባለውን “እዛው በአግባቡ ሳይከካ እዛው የተቦካ” አይነት ፅሁፍ ነው የጻፈው። ለዚህም ነው ደውልልኝና ላስረዳህ ስለው እንቢ ብሎ እኔን (My side of story) ሳይሰማ የፃፈው። ሌላ ጋዜጠኛ ቢያዘጋጀው ኖሮ በቤተኝነት ስሜት ስለማይፅፈው መረጃ ላይ ያተኩር ነበር። ስለዚህ “እንደዚህ አይነት ጋዜጠኛ ስለኔ በፃፈው ነገር አይሞቀኝም፣ አይበርደኝም። ሳሙኤል ዘ-ሚካኤል ቢያንስ ገንዘብ ይዞ ካገር አልጠፋም፤ ያልሆነውን ነኝ ብሎ የሀሰት ሰነድ አቅርበሀል ነው የተባለው። ስለዚህ ከእኔ ጋር ምንም የሚያመሳስለው ነገር የለም። ያልሆነውን ሆነ፣ ያልተደረገውን ተደረገ እያለ በሀሰት በመጻፍ ህዝብን እያደናገረ ያለው የሳሙኤል ዘ-ሚካኤል ደቀ-መዝሙር ራሱ ክንፉ አሰፋ ነው።
  • ፀሀፊው ክንፉ መረጃ ሳይኖረው የሚጽፍ ሰው ነው ያልኩበትን ምክንያት ላስረዳ፡ በላከልኝ ኢ-ሜል “አሜሪካን ሀገር ከአንድ ፓስተር ጋር በመሆን ባንክ አካውንት ልትከፍት እንደሆነ ደርሼበታለሁ፤ ስለዚህ መጥቼ አጋልጥሀለሁ ብሎኛል” እኔም ነገሩ አስቆኝ፤ “ባንክ ከከፈትኩ አሁን አራት ዓመቴ ነው አልኩት” በዚህ አጋጣሚ መረጃ ሳይኖረው እንዲህ ማለቱ ትክክል እንዳልሆነ፣ ምሳሌ እንዲሆነውና ስለ ሁሉም ጉዳይ በስልክ እንዲያወራኝ ጠይቄው ነበር። እርሱ ግን ፈቃደኛ አልሆነም።
  • ይህን ጽሁፍ እያዘጋጀሁ በነበረበት ጊዜ ደግሞ “አይሲኤስ ነህ፣ ቤተሰቦቼን ለመግደል እያስፈራራሀቸው ነው” በማለት የተለመደ መሰረተ-ቢስ ወሬውን በኢ-ሜል ልኮልኛል። (ኢሜሉን ያንብቡት)
  • ፀሀፊው እኔን በአሜሪካን ሀገር ካለው ህዝብ ጋር ለማጋጨት በአካባቢው ያለውን የፖለቲካ ትኩሳት ተጠቅሞ፤ ሲሻው ፖለቲከኛ ያደርገኛል፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ የድርጅታችንን ዓላማና ፕሮግራም የሚያስተዋውቀውን ኩፖን በመሸጥ ለመንግሥት ት/ቤት ተማሪዎች የምናደርገውን የገንዘብ ማሰባሰብ ስራ ታላላቅ ሰዎችን በማታለል ለገዛ ራሱ ጥቅም ለማዋል በባንክ አከማችቶታል ብሎ የተለመደውን የፈጠራ ወሬ የሚጽፍ ሰው ነው።

እዚህ ላይ ግን በአጽንኦት መግለጽ የምፈልገው “አንድ ራስ ወዳድ ፀሐፊ ከመሬት ተነስቶ በጻፈው የተንኮል ጽሁፍ ማንም ቸኩሎ ጀርባውን ቢሰጠኝና በሀሰት ነፋስ ቢወሰድ ምንም አይገርመኝም።

  • “ወላጆች አቤት ብለው ሰሚ ግን የለም”

አሁንም ለአንባብያን መናገር የምፈልገው፡ ፀሐፊው ወላጆች፣ ወላጆች የሚለው ፈጽሞ ሌሎች ወላጆችን አይወክልም። ሀቀኛ ከሆነ አቤቱታ ያቀረቡበትን ደብዳቤ ከነሙሉ ስምና ፊርማቸው በማስረጃነት ማቅረብ መቻል ነበረበት። ፀሀፊው ወላጆች ብሎ የሚጠራው ደብዳቤ ካናዳ በምትኖር እህቱ ወ/ሮ መሰሉ አሰፋ ወይም በዳዊት አሰፋ የተጻፈ ነው። በእርግጥ በኢትዮጵያ አቶ ዳዊት አሰፋ ሌሎች ሁለት ወላጆችን በማስተባበር የተለመደ ስፖንሰር አግኝተሃል፤ ስለዚህ ገንዘባችን ይመለስ የሚለውን ጥያቄ እያቀረቡ ያሉ፤ ስፖንሰር አግኝተሃል ስለዚህ ገንዘባችን ይመለስ በሚል ስም ያቀረቡት ይሁን እንጂ፤ እውነተኛው ምክንያት ግን አዲስ አበባ ላይ እንዳወራነው፤ “ልጆቻችን የተሰጣቸው የሦስት ወር ቪዛ ነው። ይህ ሁሉ ገንዘብ ያወጣነው የሁለት ዓመት ቪዛ የሚሰጣቸው መስሎን ነው፤ እንደገና ተመልሰው መሄድ የማይችሉ ከሆነ ምን ዋጋ አለው” በሚል ቁጭት ነው። የእነዚህ ወላጆች ሌላው ንዴት ልጆቻቸው ያገኙት የሦስት ወር ቪዛ ስለሆነና ተመልሰው መሄድ ስለማይችሉ በዛው እንዲጠፉ ፈልገው ነበር። እኔ ደግሞ ይህን እንዳይሆን ከልክያለሁ። ለወላጆች ቃል የገባሁት ወደ አሜሪካን እንደማመጣቸው እና ናሳን እንደማስጎበኛቸው ነው፣ እሱንም አድርጌያለሁ። የሁለት ዓመት ቪዛ እንዲያገኙ ማድረግ ግን የኔ ስራ አይደለም። ልጆቻችን እግራቸው አሜሪካን ሀገር ይርገጥ እንጂ ሂውስተን ይሂዱ፤ ሜሪላንድ ግድ ያልነበራቸው፤ ቪዛው የሦስት ወር መሆኑ ካስቆጣቸው በኋላ ግን በተለያየ አቅጣጫ ቅሬታ ማቅረብ ጀመሩ። ይህን ስል የአቶ ዳዊት አሰፋ ቤተሰቦችን የተቀላቀሉ ሁለት ወላጆችን ማለቴ ብቻ ነው። በተረፈ ግን አደስ አበባ በነበርኩ ጊዜ ስለ ዲሲ ሂውስተን የትራንስፖርት ወጪ ከወላጆች ጋር አውርተን ተስማምተን ተለያይተናል።

  • በቂ ስፖንሰር ተገኝቷል?

ለወ/ሮ መሰሉ ናሳ ስፖንሰር አላደረገም፣ አዲካም ስፖንሰር አላደረገም አልኳት። ይህን በቀላሉ ደውሎ ማጣራት የሚቻል ነገር ነው። ቢያንስ ይህን ቀላል ነገር እንኳ ደውላ ማጣራት የማትፈልግ ከሆነ እንዴት አደርጋ ነው ሌሎች መረጃዎችን ማጣራት የምትችለው?

ስለ ኢትዮጵያ አየር መንገድ የስፖንሰርሺፕ ሁኔታ ደጋግሜ አስረዳኋት፤ ለርሷም፣ ለወንድሟም ለአቶ ዳዊት አሰፋም፤ ነገር ግን ሊገባቸው አልቻለም።

ኢትዮጵያ አየር መንገድ 7 የተማሪ ትኬቶች 2 ለጠባቂዎች (Chaperon) ትኬት ሰጠን። በዚህ ጉዞ በአጠቃላይ 13 ሰው ነው የሚጓዘው። ኢትዮጵያ አየር መንገድ የሰጠው ትኬት ለሁሉም ስላልሆነ ትኬቱ ወደ ካሽ ተቀይሮ ከዛ የታክስና የማስታወቂያ ወጪ (የአንደኛ ደረጃ ስፖንሰር ስለሆነ (Platinum Level Sponsorship) በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ በኢቢኤስ፣ በሬዲዮ፣ በጋዜጦች፣ በበራሪ፣ በቢልቦርድ፣ በኩፖን፣ ውድድሩ በሚካሄድበት አዳራሽ፣ ወዘተ…) የማስተዋወቅ ግዴታ ስላለብን የማስታወቂያና ታክስ ሲቀነስ የሚቀረው ገንዘብ ለተማሪዎች ይካፈል ቢባል እንኳን እንድ ሺህ ብር አይሞላም ብዬ ለማስረዳት ሞክሪያለሁ። አዲስ አበባ በነበርኩ ጊዜ ከወላጆች ጋር የስፖንሰርሺፕ ስምምነት አሳይቼ በዚህ ጉዳይ ላይ ተግባብተናል። እኔ ይሀን የማስታወቂያ ወጪ የምሸፍነው ከራሴ አይደለም፤ በወቅቱ ምንም ግልጽ ያልሆነ ነገር አልነበርም፤ አሰራሩ እንደዛ ነው ብላት ጆሮ ዳባ ልበስ ብላለች፤ አዲስ አበባ ከወላጆች ጋር ስላደረከው ውይይት አያገባኝም፤ ገንዘቤን መልስ አለችኝ፤ ለረጅም ሰዓት ባደረግነው የስልክ ንግግር። ኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ 50 ሺህ ብር ሰፖንሰር በማድረግ 3ኛ ደረጃ ስፖንሰር ነው። ነገር ግን የአንደኛ ደረጃ ማስታወቂያ እንዲሰራለት ተስማምተናል። ፕላቲኒየም ሌብል የሚያገኘውን የማስታወቂያ ደረጃ ማለት ነው። ይህን የምንሰራላቸው ግን ስለሚያዋጣን ሳይሆን ለወደፊቱ አብሮ ለመስራት በማሰብ ነው። የተገኘው ገንዘብ ለማስታወቂያ እንደሚውል ተነጋግረን ተፈራርመናል። ስምምነቱን ይመልከቱ። ሌላ ማንም ስፖንሰር ያደረገን አካል የለም።  (የኦሮሚያ ባንክ ስምምነት ወረቀት እዚህ ይግባ)

ድርጅታችን አይከን ኢትዮጵያ አትራፊ ድርጅት ነው። ታክስ ይከፍላል። የበጎ አድራጎት ድርጅት አይደለም። ስለዚህ ለድርጅታችን እድገትና ስራ ማስፋፊያ፣ ለምናካሂዳቸው ማናቸውም ዝግጅቶች፤ ከእኛ ጋራ ሊሰሩ ከሚፈልጉ ከማናቸውም ድርጅቶች ጋር የሚያዋጣንን ማንኛውም አይነት የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ልንፈራረም እንችላለን። ከእኛ ጋር አብሮ ከሚሰራው ዓለም አቀፍ ተቋም ጋር ባለን ስምምነት መሰረት ተማሪዎችን ማወዳደር፣ መሸለምና አሜሪካን ሄደው ናሳን እንዲጎበኙ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንጂ የተማሪዎችን ወጪ ለመሸፈን ገንዘብ በመፈለግ ስፖንሰር የማድረግ ግዴታ የለብንም። (የዓለም አቀፍ ድርጅቱ ደብዳቤ እዚህ ይግባ)

ስፖንሰር የምንፈልግ ከሆነ እንኳን አሁን በ2015 በአሜሪካ በተቋቋመው ድርጅታችን በኩል የመንግሥት ት/ቤት ተማሪዎችን በውድድሩ በማሳተፍ አሸናፊ የሆኑትን ወጪያቸውን የሚሸፍን ገንዘብ ባገኘን መጠን ናሳን የመጎብኘት እድል እንዲያገኙ ለማድረግ እየሰራን ነው። አኔም አሜሪካን ሀገር ያለሁት እንደ ጸሀፊው ከንፉ አሰፋ አባባል ገንዘብ ይዤ ከሀገር ጠፍቼ ሳይሆን ለዚህ ድርጅት ምስረታ እዚህ መገኘት ስለነበረብኝና ለዓለም አቀፍ የሮቦቲክስ ውድድር በዳኝነት ተጋብዤ ነው።

ውድ አንባብያን በዚህ ሁኔታ ለእያንዳንዱ ጉዳይ ዝርዝር መልስ መስጠት የአንባብያንን ጊዜ በከንቱ ማጥፋት ስለሚሆን በጉዳዩ ላይ በቅርቡ በቪዲዮ የሚለቀቀውን ቃለ-ምልልስ በማህበራዊ ድረ-ገጾች እንድትከታተሉኝ እያስታወስኩ፣ ለአሁኑ ግን እዚህ ላይ ላቁም።

 

Re  http://www.zehabesha.com/amharic/archives/40608

 

 

 

 

 

 

 

The post የሳሙኤል ዘ-ሚካኤል ደቀ-መዝሙር ማነው? – ለአቶ ክንፉ አሰፋ የተሰጠ መልስ (ከሰናክሪም መኮነን) appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>