በአህጉራችን አፍሪካ ዲሞክራሲያዊ ፍትሐዊ ተአማኒና ነጻ ምርጫዎች እየተኪያሔዱ መንግሥታት የመቀያየሩ ሒደት ከጀመረ 20 ዓመታት አለፉ፡፡ ለዘመናዊ ሥልጣኔና ዲሞክራሲ (በይነ ሕዝብ) ባይተዋር በመሆኗ በዚህም ምክንያት ድሀ በመሆኗ “ጨለማዋ አህጉር” በመባል በምትታወቀዋ አህጉራችን ዛሬ ላይ በትክክለኛና ተአማኒ በሆነ መንገድ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ በተደጋጋሚ በማኪያሔድ ወደ 10 የሚደርሱ የአፍሪካ ሀገራት አዳዲስ መንግሥታት ተመሥርተው ዲሞክራሲያዊ (በይነ ሕዝባዊ) በሆነ የመንግሥት ሥርዓት እየተዳደሩ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ሀገራት የሚበዙቱ ከሰሀራ በታች ያሉ ሀገራት ናቸው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ በብዙ ነገር ለአፍሪካ ሀገራት ዓርአያ እንደመሆኗና የረጅም ጊዜ ሥልጣኔ ባለቤት እንደመሆኗ ዲሞክራሲያዊ (በይነ ሕዝባዊ) ምርጫ አድርጋ ዲሞክራሲያዊ (በይነ ሕዝባዊ) መንግሥት በመመሥረት በዚህ ረገድም ለሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ አርዓያ መሆን ባለመቻሏና የራሳቸው ሥልጣኔ ባልነበራቸው በቅኝ ግዛት በደቀቁት ሀገራት በመቀደሟ የማያዝን የማይቆጭ የማይቃጠል የማይንገበገብ በይነ ሕዝባዊ መንግሥት በሀገራችን እንዲመሠረት የድርሻውን የማይፍጨረጨር ሕዝቧን የሚጨቁን ሀገሪቱን የሚበዘብዘው ዘገዛዝ ተባባሪና አጋር ዜጋ ካለ በተለይም ደግሞ “የተማርኩ ነኝ” የሚል ከሆነ የተሟላ ጤና ላይ እንዳልሆነና ለዚህች ሀገርና ሕዝቧ ጠላት እንደሆነ እርግጠኛ መሆን ይኖርበታል ተምሬያለሁ ብሎም ሊያስብ ፈጽሞ አይገባም፡፡
በዘመነ ወያኔ ለ5 ዙር ያህል ምርጫ መሰል ግርግር ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጅ እነዚህ ግርግሮች አንዳቸውም ምርጫ አልነበሩም፡፡ በዘመነ ወያኔ ምርጫ ተደርጎ አያውቅም፡፡ በእርግጥ የ3ኛው ዙር ማለትም 1997ዓ.ምሕረቱ ብሔራዊ ምርጫ እስከ ምርጫው ማግስት የነበረው ሁኔታ አንጻራዊ በሆነ መልኩ በጣም ጥሩ የሚባል ነበር፡፡ እሱም ቢሆን ግን ከምርጫው ማግስት በኋላ ከሆነው ነገር መረዳት እንደምንችለው ከምርጫው ማግስት በፊት የነበረው ሁኔታ እንደዛ ሊሆን የቻለበት ምክንያት ወያኔ በሕዝብ ምርጫ ለሚመሠረት መንግሥት ቦታውን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ስለነበረ ወይም ይለው እንደነበረው ሁሉ ነጻ ፍትሐዊና ተአማኒ የሆነ እንከን የለሽ ምርጫ አድርጎ ለታሪኩ ጥሩ ስም ለመተው ስለወሰነ፣ ለዲሞክራሲ (ለመይነ ሕዝብ) ታማኝነቱን ለማረጋገጥ ሲል ያደረገው አልነበረም፡፡ ነገር ግን ከዚያ ምርጫ በፊት ሥልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ ጠንካራ ተቃዋሚ ወይም ተወዳዳሪ ፓርቲ አይደለም እንደ የመምህራን ማኅበርን፣ የሠራተኛ ማኅበራትን፣ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርን የመሳሰሉትን ሲቪክ (ሕዝባዊ) ማኅበራትን ሁሉ ሳይቀር አንባገነናዊና ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ እየበተነና እያስወገደ ጠንካራ ሲቪክ (ሕዝባዊ) ማሕበራት እንኳን እንዳይፈጠሩና ተፈጥረውም ለጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች መፈጠር ምክንያትና ዓርአያ እንዳይሆኑ ሲሠራው በነበረው ጥቃት ሸር አሻጥር ጫና ጥቃት ውክቢያና ስውር ደባ ሊፎካከረው የሚችል ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ እንደሌለና እንደማይኖርም በመተማመኑ በዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ፊት ጉራውን ለመንፋትና ዲሞክራሲያዊ (በይነ ሕዝባዊ) ለመባል ሲል የዚያን ምርጫ በር ከፍቶት ነበር፡፡
ይህችን ቁማር የተረዷት ምሁራን “ምርጫው እንከን የለሽ ይሆናል” ተብሎ ከታወጀ ከምርጫው ጥቂት ወራት አካባቢ ሲቀር ጀምረው ልዩ አጋጣሚውን ለመጠቀም በመወሰን እነ ዶ/ር ብርሃኑ እነ ፕሮፌሰር መስፍንና ሌሎች አጋሮቻቸው ተፋጥነው ቀስተ ደመናን መሠረቱና አስቀድመው ከነበሩ ሌሎች ፓርቲዎች ጋር በመቀናጀት “ቅንጅት” የተባለን ጉደኛ ፓርቲ ፈጥረው ወደ ምርጫው ገቡ፡፡
በወቅቱ ወያኔ አስቀድሞ “መጥታቹህ ታዘቡልኝ እንከን የለሽ ምርጫ አደርጋለሁ!” ሲል አውጆ ለምዕራባዊያኑ በገባው ቃል መሠረት ከምዕራባዊያኑ ከየአቅጣጫው የሚለቀቅለትን የውዳሴ ዜማ በተመስጦ በማዳመጥ ተጠምዶ ስለነበር ምርጫው ሊደረግ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት እስኪቀር ድረስ ወያኔ የቅንጅትን መቅሰፍትነትና “ጠንካራ ፓርቲ አላደለንም” የሚለውን የምጸት ጸሎቱን አምላክ ሰምቶለት እንዲያውም እሱ ከፈለገውና ሊቋቋመው ከሚችለው በላይ ጠንካራ ፓርቲ በድንገት እንደሰጠው በቅጡ አልተረዳም ነበር፡፡ በተረዳ ጊዜም ቢሆን የምርጫው ቀን በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ብቻ የቀሩት ከመሆኑና ታዘቡልኝ ተብለው ተጠርተው የመጡት ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ተገኝተው እየሆነ ያለውን ሁሉ እየታዘቡ ከመሆናቸው አንጻር የሚያደርገው ጠፍቶት በመንተፍረቱ ምርጫውን በነጻነት መምረጥ እንዲቻል አድርጎ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ካድሬዎቹ ከምርጫው ቀን በፊት በየቦታው እጅግ ከመጨነቃቸው የተነሣ አንዳንድ ችግሮችን መፍጠራቸው የቀረ ባይሆንም ቅሉ፡፡
በምርጫው ማግስት ግን ወያኔ የማስመሰሉን ጨዋታው የወለደውን ውጤት መቀበል ፈጽሞ የሚቻል ስላልሆነበት “ጨዋታ ፍርስርስ” የሚልበት ሰዓት ያ ሰዓት እንደሆነ በመረዳቱ የኢትዮጵያን ሕዝብ ድምፅ በማስወገድ ምርጫውን ወደ ቅርጫ በመለወጥ አብዛኛውን ለራሱ በመውሰድ ይሄንን ያህል ወንበር ይበቃቹሀል ብሎ ለተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኮታ አከፋፍሎ ሰጠ፡፡ በዚህ አንባገነናዊ ወንጀሉም ሕዝብ ተቆጣ፡፡ ወያኔም በጭካኔ ያደረገውን ሁሉ አድርጎ ዕድሜውን እስከአሁን ድረስ ሊያራዝም ቻለ፡፡ ከዚያ በኋላ ባሉ ሁለት “ምርጫዎች” ግን “የምርጫ 97ዓ.ም. ዓይነት ቅብጠት ሁለተኛ አይለመደኝም” ብሎ ከምርጫ 97ዓ.ም. በፊት ወደ ነበረው አቋሙ በመመለስ “ዲሞክራሲ፣ ፍትሐዊ ነጻ ተአማኒ ምርጫ ብሎ ነገር አይገባኝም ታግየ ነው የመጣሁ ሥልጣን የሚፈልግ አካል ካለ ታግሎ ይምጣ!” የሚል ጠንካራና የማይደራደርበት አቋም በመያዝ ይሄው እንደምታዩት “ምርጫ” የሚል የአንድ ሰሞን የቀልድ ጨዋታ በማዘጋጀት ግርግር እየፈጠረ ያሳልፋል፡፡
ይሄንን 5ኛ ዙር ብሔራዊ የቀልድ ግርግር ምርጫ እንዳንለው የሚከለክሉን ምክንያቶች ወይም ምርጫው ነጻ ፍትሐዊ ተአማኒና ዲሞክራሲያዊ (በይነ ሕዝባዊ) አልነበረም እንድንል የሚያደርጉን ጉዳዮች ምን ምን ናቸው?
ቅድመ “ምርጫ” በነበረው “የምርጫ” ሒደት
የምርጫ ቦርድ አባላት በግልጽ በሚታይ መልኩ ገለልተኛ አለመሆናቸውና ከወያኔ ታጋዮች ባልተናነሰ ለወያኔ ህልውና ዋጋ ለመክፈል የተዘጋጁ በመሆናቸው፡፡
የምርጫ ካርድ ዕደላው “አንድ ካርድ ለአንድ መራጭ” ከሚለው ትክክለኛ አሠራር ወጥቶ የአገዛዙ ደጋፊዎች መሆናቸው ለሚታወቁት ግለሰቦች ከሠላሳ በላይ ካርዶች ለእያንዳንዳቸው የታደለበት መሆኑና ይሄንን በተመለከተም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በመረጃ በተደገፈ ላቀረቡት ክስ ገለልነኛ ነኝ በሚለው የምርጫ ቦርድ ምንም ዓይነት የማስተካከያም ሆነ ሊወስድ የሚገባውን እርምጃ ባለመውሰዱ፡፡ የተቀረው ካርድ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ በምርጫው አመኔታ ያለው ለማስመሰልና ፍላጎቱ ስላለውም ከ1997ቱ በላይ መራጭ ተገኘ ለማሰኘት ዜጎች ያለፍላጎታቸው ቤት ለቤት እየተጎተጎቱ ከመንገድ እየተጎተቱ መታወቂያ የለኝም ላለው ሳይቀር በግዳጅ እንዲወስዱ በመደረጉ፡፡
አገዛዙ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ከመሀላቸው ያሉ አባላቶቻቸውን የቻለውን በጥቅም በመደለል ያልቻለውን በማስፈራራት ፓርቲያቸውን እንዲከዱና በፓርቲያቸው ላይ እንዲሸፍጡ ለእሱ እንዲያድሩ በማድረግ አሻጥር በመፈጸም ከሕዝብ ጋር ረዘም ያለ ትውውቅ ያላቸውን ፓርቲዎች መኢአድንና አንድነትን እንደ ቅንጅት ሁሉ እንዲፈርሱ በማድረግ ሕዝቡ “ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ የለም” የሚል ቀቢጸ ተስፋ ውስጥ እንዲወድቅ የተደረገበት በመሆኑ፡፡
በተለይም የሰማያዊ ፓርቲ ተወዳዳሪዎችን የምርጫ ቦርድ ተብየው ቅጥረኛነቱን ለማሳየት ለአገዛዙ ታማኝነቱን ለማረጋገጥ ወይም የአገዛዙን ትዕዛዝ በመቀበል ምንም ዓይነት ሕጋዊ ተቀባይነት በሌለው ምክንያት ከግማሽ በላይ ተወዳዳሪዎቻቸውን ከተወዳዳሪነት የሰረዘበት በመሆኑ፡፡ ፍርድ ቤት ከሰው የመወዳደር መብት እንዳላቸው ሲረጋገጥም ይህ ቅጥረኛ የምርጫ ቦርድ ተብየ ጥቂቶቹን ብቻ በመቀበል ዐይን ባወጣ ሁኔታ ሕግ የማይገዛው ከሕግ በላይ መሆኑን በግልጽ በማሳየት ፍርድ ቤቱ መብታቸውን ያረጋገጠላቸው ቢሆንም የተቀሩትን አልቀበልም ብሎ ከውድድር ውጪ በማድረጉ፡፡
የዜጎችን ሰብአዊና ሕገ መንግሥታዊ የመምረጥ መመረጥ መብትን በመንፈግና በመጻረር በአንድ ምርጫ ጣቢያ ከ12 በላይ ተወዳዳሪ መወዳደር አይቻልም የሚል ገዳቢ ሕግ በማውጣትና ቦታውን እሱ በፈጠራቸው የውሸት ተወዳዳሪ ፓርቲዎች እንዲያዝ እንዲሞላ በማድረግ ለትክክለኛና ሕዝብ ለሚፈልጋቸው የተወዳዳሪ ፓርቲዎች ተመራጮች ቦታ እንዲያጡና ከውድድር ውጪ እንዲሆኑ የተደረገ በመሆኑ፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ አቅዶቻቸውንና ፖሊሲ (መመሪያዎቻቸውን) ለሕዝብ ሊያስተዋውቁ ሊገልጹ የሚችሉባቸውን የገጽ ለገጽ መድረኮችንና የብዙኃን መገናኛ ዕድሎችን ኢሕገመንግሥታዊና ሕገ ወጥ በሆኑ ምክንያቶች እንዳያገኙ የተደረጉበት በመሆኑ፡፡ እንደ ሕገ መንግሥታቸው ቢሆን ኖሮ ምርጫ ሲመጣ ብቻ ሳይሆን ከምርጫ ወቅት ውጪም በማንኛውም ጊዜ የፖለቲካ ፓርቲዎች አቅድ ፖሊሲዎቻቸውን (መመሪያዎቻቸውን) በመንግሥት (በሕዝብ) የብዙኃን መገናኛዎች ለሕዝብ የማስተዋወቅ መብት ነበራቸው፡፡ እየሆነ ያለው ግን የዚህ ተቃራኒና እንኳን ከምርጫ ወቅት ውጪ በምርጫ ወቅት እንኳን ዕድሉን ሊያገኙ አልቻሉም፡፡
የተወዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎቻቸው ላይ እስራትና እንግልት በሰፊው የተፈጸመበት በመሆኑ፡፡
አገዛዙ በሕዝቡ ላይ በፈጸመው ከባድ ጫናና ባሳደረው የፍርሐት መንፈስ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚታዘብ የምርጫ ታዛቢ ፍጹም በመታጣቱ እሽ ያሉትንም በማስፈራራት እንዲሸሹ በመደረጋቸው ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በየምርጫ ጣቢያዎች የየራሳቸውን ታዛቢዎች ወክለው እንዳያስቀምጡ የተደረገበትና በሚበዛው የምርጫ ጣቢያዎች ያለ ታዛቢ ለመወዳደር የተገደዱበት ሁኔታ እንዲፈጠር በመደረጉ፡፡
በምረጡኝ የቅስቀሳ ወቅት የተቃዋሚ ወይም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይቀሰቅሱባቸው የነበሩ ተሸከርካሪዎች በአገዛዙ የጸጥታ አካላትና ደጋፊዎች በመሠባበራቸው በቀስቃሽ አባላቶቻቸውም ላይ ለአካል ጉዳት የዳረገ ጥቃት በመፈጸሙ፡፡ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ይሄንን የአገዛዙን የውንብድና ተግባር ገለልተኛ ነኝ እያለ ለሚያሾፈው የምርጫ ቦርድ ሲያመለክቱም ገለልተኛ ነኝ ባዩ የምርጫ ቦርድ ተብየው የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ባለማድረጉ፡፡ በተሰጠው ሥልጣንም ጥቃቱን የፈጸሙትን አካላት በሕግ እንዲጠየቁ ባለማድረጉ፡፡ የሚገርመኝ ነገር ይህ የምርጫ ቦርድ ተብየ ገለልተኛ አለመሆኑ እንዳይታወቅ ሲል ለማስመሰል ያህል እንኳ እንዲህ ዓይነት የውንብድና ጥቃቶች በመላ ሀገሪቱ በአገዛዙ አካላት ሲፈጸምና ተጠቂዎቹ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ኡኡ ሲሉ የአገዛዙን ጥቃት አድራሾችን አካላት ለአንዲት ጊዜም እንኳ ቢሆን ሊወቅስ ተጠያቂ እንደሆኑም ሊያስጠነቅቅ በፍጹም አለመፈለጉና አለመቻሉ ነው፡፡ በአንጻሩ ግን በተወዳዳሪ ፓርቲዎች ላይ ግን እንኳን ሊያደርጓቸው ገና ያላሰቧቸውን ነገሮች እየቀበጣጠረ ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው ሲዝት ሲያስፈራራ ነበር የከረመው፡፡ የአገዛዙ ባለሥልጣን አቶ ሬድዋን ሑሴን እነኝህን ጥቃቶች በተመለከተ የቪ.ኦ.ኤ የእንግሊዝኛው አገልግሎት ክፍል ጋዜጠኛ ጠይቃው ሲመልስ “የተፈጸሙት ጥቃቶች የተፈጸሙ ቢሆኑም ጥቃት አድራሾቹ በራሳቸው ተነሣሽነት ያደረጉት እንጅ ከላይ ወደታች በወረደ ትዕዛዝ በተማከለ አሠራር የተፈጸሙ አይደሉም” ሲል ነበር የመለሰው፡፡ በተማከለና ከላይ ወደ ታች በወረደ ትዕዛዝ ለመፈጸማቸውማ ማስረጃው ጥቃቱን የፈጸሙት አካላትና ግለሰቦች ተጠያቂ አለመሆናቸው ሕግ ፊት አለመቅረባቸው ነው፡፡
በምርጫው ዕለት ዋዜማ ድምፅ የሚሰጥበት ወይም የመምረጫው ወረቀት ለግለሰቦች ታድሎ ምልክት እንዲያደርጉ እየተደረገ በማግስቱ ያንኑ እንዲያስገቡ በመደረጉ፡፡ አስቀድሞም የምርጫ ቦርድ ተብየው ይህ የድምፅ መስጫ ወረቀት ለዚህ የውንብድና ተግባር እንዲመች ለማድረግ የድምፅ መስጫ ወረቀቶቹን ተከታታይ የመለያ ቁጥር እንዳይኖርባቸው አድርጎ ማተሙ የመሳሰሉት ናቸው፡፡
በምርጫው ዕለት በነበረው ሒደት
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ታዛቢ ባገኙባቸው ጥቂት የምርጫ ጣቢያዎች ያስመዘገቧቸው ታዛቢዎች አብዛኞቹ በየተመደቡበት የምርጫ ጣቢያዎች ተገኝተው እንዳይታዘቡ በመደረጋቸው፡፡
የምርጫ ኮሮጆዎች ከሰዓቱ በፊት ተከፍተውና የድምፅ መስጫ ወረቀቶች በብዛት ተከቶባቸው በመገኘቱ፡፡
መራጮች በተደጋጋሚ እንዲመርጡ በመደረጉ፡፡ የቀበሌዎቹ ወይም የምርጫ ጣቢያዎቹ ነዋሪዎች ያልሆኑ ሰዎች በተሽከርካሪዎች እየተጫኑ መጥተው እንዲመርጡ መደረጉ፡፡
ታጣቂዎች በየምርጫ ጣቢያው አቅራቢ በመሆን በሕዝቡ ላይ የፍርሐት ድባብ እንዲፈጥሩ በመደረጉ፡፡
ምርጫው እየተደረገ ባለበት ሰዓትም ቢሆን ለመታዘብ የቻሉ የተወዳዳሪ ፓርቲዎችን ታዛቢዎች በጥቅም በመደለልና እንዳይናገሩ በማስፈራራት በአገዛዙ አካላት የምርጫ ኮሮጆዎችን የመሙላት ድርጊቶች ሲፈጸሙ በመታየታቸው፡፡
ሕዝቡ የሰጠው ትክክለኛው የሕዝብ ድምፅ የተመለከተበት የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ተቃጥለውና ሽንት ቤቶች ተጥለው መገኘታቸው፡፡
ቀደም ሲል የተጠቀሱትን ማጭበርበሮች መፈጸም ባልተቻለባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ምርጫው ከተጠናቀቀበት ሰዓት በኋላ የጸጥታ ኃይሎች ኮሮጆ አናዘርፍም አናስነካም ባሉ ጽኑአንና ታማኝ የተወዳዳሪ ፓርቲዎች ታዛቢዎችና ደጋፊዎች ላይ ግድያን ጨምሮ አሰቃቂ ድብደባ እስራትና እንግልት የተፈጸመ በመሆኑ ወዘተረፈ፡፡
ከምርጫው ዕለት በኋላ በነበረው ሒደት
የምርጫ ቦርድ ተብየው ከላይ በተጠቀሱት እንከኖች በተሞላ ሒደት የተፈጸመን የሐሰተኛ ምርጫ ውጤት ተቃዋሚዎች በየጊዜው እያቀረቧቸው ለመጧቸው ቅሬታና አቤቱታዎች ለአንድም ጊዜ እንኳ አግባብነት ያለው ሕጋዊ ምላሽ ለመስጠት ፈጽሞ ሳይፈልግ ክሶቹንም ለማጣራት ሳይሞክርና ሳይፈልግ በምርጫው ማግስት ምርጫው ከምንጊዜውን በበለጠ መልኩ ፍትሐዊ ተአማኒና ሰላማዊ ሆኖ ተጠናቋል ብሎ በማወጁ፡፡
ይሄንን ሙሉ ለሙሉ የተጭበረበረን ውጤትም የምርጫ ቦርድ ተብየው ውጤት እገልጻለሁ ብሎ ካስታወቀበት ቀን 3 ቀናት አስቀድሞ የግንቦት 20 በዓላቸውን ለማድመቅ ሲባል በዋዜማው እረቡ ለት በ19 የ105ቱን ውጤት ለተንኮሉ ከፍሎ በማስቀለት ወያኔና አጋሮቹ ሙሉ ለሙሉ አሸናፊዎች መሆናቸውን በማወጁ፡፡
ሕዝቡ መብቱን ለአገዛዙ አሳልፎ የሰጠ በመሆኑ ያለ ፍላጎቱና ያለ ምርጫው የሥራ ዋስትናንና የመሳሰሉትን መሠረታዊና የዜግነት መብት ጥቅሞቹን በግፍ ላለማጣት ሲል ተገዶ ጠርናፊም ተጠርናፊም ሆኖ በ5 ለ1 አደረጃጀት የተጠረነፈው የኢትዮጵያ ሕዝብ አገዛዙ “ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ዓላማና ተልእኮ የለውም” የሚለውን ይሄንን አደረጃጀት በመጠቀም ሕዝቡ የተዘረፈበትን ድምፅ የተፈጸመበትን ውንብድና የመቃወም መብቱን በመጠቀም መብቱንና የሰጠውን ድምፅ ለማስከበር እንቅስቃሴ እንዳያደርግ በከፍተኛ ደረጃ እየወተወተው እየዘበዘበው ከፍተኛ ጫና እያደረገበት በመሆኑ ወዘተረፈ፡፡
እውነት ለመናገር የዘንድሮውም “ምርጫ” ተጭበርብሮ ውጤቱ እንዲህ በመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ እጅግ ነው ያዘነው፡፡ ሕዝቡ ወያኔን ላለመምረጡ እንዴት እርግጠኛ ልትሆን ቻልክ? የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችል ይሆናል፡፡ ይሄንን ለማወቅ የግድ የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን አገላብጨ ማየት አይጠበቅብኝም፡፡ የሕዝብ ምርጫ ምን እንደነበር ለማወቅ የሚረዱ ሌሎች መንገዶች አሉ፡፡ ሕዝብ የሚባለው ከሰማይ የተሰቀለ የሆነ አካል ማለት አይደለም፡፡ ሕዝብ የሚባለው እኔ አንተ አንቺ እሱ እሷ የየመንደሩ ወይም የየሰፈሩ ሰዎች ማለት ነው፡፡ የእነዚህ የየሰፈሩ ወይም የየመንደሩ ሰዎች ፍላጎትና ምርጫ ምን እንደነበር ደግሞ እዚያው እየሰፈሩ እየመንደሩ የሆድ የሆዳችንን ስንጫወት ስናወጋ በሚገባ እናውቀዋለን፡፡ ከዚህ ባሻገር የሕዝቡ ምርጫ ምን እንደነበር ለመረዳት ይረዳቹህ ከሆነ አንድ ጉዳይ ልጥቀስላቹህ፡፡ እንዳልኳቹህ ይሄንን ጉዳይ የምጠቅስላቹህ የሕዝቡ ምርጫ ምን እንደነበር እንድትረዱ ብቻ እንጅ ለሌላ ዓላማ እንዳልሆነ ግን አስቀድሜ ማስጠንቀቅ እወዳለሁ፡፡ ይሄንን ያየችውን ነገር ያጫወተችኝ የሰፈሬ ልጅ ናት፡፡
ነገርየው ምን መሰላቹህ? ረቡእ ለት ነው ማለትም ምርጫው በተደረገ 3ኛው ቀን ጠዋት፡፡ ይህች የሰፈሬ ልጅ ረቡእ ለት ጠዋት በሀይገር (መለስተኛ የከተማ አውቶቡስ) ወደ ሥራዋ ስትሔድ እንደ እሷ ሁሉ ወደ ጉዳይዋ ለመሔድ የተሳፈረች ሌላ የሰፈር ሰው ነበረች፡፡ ይህች የሰፈር ሰው ግጥም አድርጋ የትግሬ ሹርባ ተሠርታ ነበር፡፡ ሌላው ተሳፋሪ በግልምጫ ሲያነሣ ሲጥላት ይቆይና አንደኛው ምክንያት ፈልጎ በድንገት ይዘልፋታል፡፡ ወዲያውንም በዚያ ሀይገር ውስጥ ያለ ሰው ሁሉ ሊባል በሚችል ደረጃ እየተቀባበለ ያበሻቅጣት ጀመር፡፡ አንዱን ብጠቅስ “ቆይ! ጠብቂ! በደረቁ እንላጭሻለን! ሩቅ መስሎሽ ነው? አሁን በቅርቡ ጠብቂ….” ይህች ልጅ ያም ያም እየተቀባበለ ሲወርድባት በፍርሐት ተውጣ እየተንቀጠቀጠች “ኧረ እባካቹህ እኔ ትግሬ አይደለሁም፡፡ እኔ ወሎየ ነኝ ዝም ብየ ነው ይሄን ሹርባ የተሠራሁት!” ብላ ትናገራለች፡፡ ልጅቱ በእርግጥም ትግሬ አልነበረችም፡፡ ይህች ልጅ ከሥራዋ እንደተመለሰች ወዲያውኑ ነበር ሹርባዋን የፈታችው፡፡ የዚህ ዓይነት ተመሳሳይ ድርጊቶች በየቦታው አይጠፉም፡፡ እነዚህ ጉዳዮች የሚያመለክቱን ብዙ ነገር አለ፡፡ ከብዙው ነገሮች አንዱ ከላይ የገለጽኩላቹህን የሕዝቡ ምርጫ ማን እንደነበርና የልቡን ትርታ ነው፡፡ በዚያ ሚዲባስ (መካከለኛ ተሸከርካሪ) ውስጥ የነበሩ ሰዎች “የእነ እከሌ ደጋፊዎች የሆናቹህ ብቻ!” ተብለው የተጫኑ ተሳፋሪዎች ባለመሆናቸው በሚገባ የሕዝቡን ሥሜት ይወክላሉ፡፡ እናም የሕዝቡ ስሜት ፍላጎት ምርጫ ይሄው ነው፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ በምንም ተአምር ቢሆን አገዛዙ መቶ በመቶ አሸነፍኩ ሕዝቡ ወዶና ፈቅዶ መረጠኝ በሚልበት አዲስ አበባ ከተማ አገዛዙ መሠረቴና መከታየ ነው ለሚለውና ለሱም እንደቆመ ለሚናገርለት ብሔረሰብ እንዲህ ዓይነት ጥላቻ ሊገልጽ አይችልም፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለያየ ጊዜ በተደረጉት 5 ዙር ምርጫዎች ለአንድም ጊዜ እንኳን ቢሆን ወያኔን መርጦ አያውቅም፡፡ ወያኔ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያለውን ጥላቻና በየጊዜው የሚወስደውን የተለያየ ዓይነት የበቀል እርምጃዎች ባያቹህ ጊዜ በተደረጉት ምርጫዎች ሁሉ ወያኔ አሸንፎ እንደማያውቅ ታረጋግጣላቹህ፡፡ ወያኔ በጥላቻ ታንቆ የቀረው በኢትዮጵያ ሕዝብ እምነት ያጣውና በጎጠኛነት አስተሳሰብ ታስሮ የቀረው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ወያኔ በሕዝብ ድምፅ ሥልጣን የያዘ ቢሆን ኖሮ ለሥልጣን ላበቃው ሕዝብ ከፍተኛ አክብሮት ይኖረው ነበር፡፡ የምናየው ማን አለብኝነት ንቀትና እረገጣ ፈጽሞ ባላየነው ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም እንኳ በጣታቸው የሚፈርሙ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ጄኔራሎች፣ የሚንስትሮች ተቆጣጣሪ አለቆች ከታጎሩበት ከወያኔ የማይሻል በሕዝብ ተቀባይነትን ያገኘ የፖለቲካ ፓርቲ በሀገራችን ባይኖርም ቅሉ የተወዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ብቃት ሳያሳስበው ሁሌም እነሱን የሚመርጥበት ምክንያት ለምን እንደሆነ ታውቃላቹህ? አንዱ ወያኔ ለዚህች ሀገር ጠንቅ እንደሆነ ጠንቅቆ ስለሚያው ሲሆን ሌላው ደግሞ ብቻ አንድ ጊዜ የመንግሥት ሥልጣን እንደ ደርግና እንደ ወያኔ ባለ ትጥቅ ባለ አፈሙዝ በሆነ አካል ሳይሆን ትጥቅ አፈሙዝ ባልያዘ ከራሱ ከሕዝቡ የወጡ ሲቪል ወይም ሕዝባዊ የሆኑ በሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመንግሥት ሥልጣን ቢያዝ ትጥቅ አፈሙዝ ያልያዙ እንደመሆናቸው መጠን እንደ ደርግና እንደ ወያኔ ፈላጭ ቆራጭ፣ አንጋገነን፣ ጨቋኝ የመሆን ዕድል ስለማይኖራቸው ሰብአዊ ዲሞክራሲያዊ (በይነ ሕዝባዊ) የመንግሥት አሥተዳደር ይኖረናል የሥልጣን ባለቤቱም እኔው እራሴ እሆናለሁ የሚል የጸና እምነት ስላለው ነበር ሳይሰለች ሳይታክት በተደጋጋሚ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የሚመርጠው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን የሚሰጠው ድምፅ ዋጋ አግኝቶለት ምኞቱ ሠምሮ እስከ አሁን ድረስም ሕዝባዊ መንግሥት ሊመሠረት አልቻለም፡፡ ወያኔ እስካለ ጊዜ ድረስም ይህ ምኞቱና መሻቱ እውን ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም ይህ እንዳይሆን የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች አሉና፡፡ ወያኔ ሥልጣን ስለጣመው ብቻ አይደለም ሥልጣን ማስረከብ የማይፈልገው፡፡ ነገር ግን ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ እንደነገርኳቹህ ወያኔ ከሀገር ክህደት ጀምሮ እስከ በንጹሐን ደም መጨማለቅ ድረስ ያልፈጸመው የወንጀል የግፍ ዓይነት ስለሌለና ሥልጣን ባስረከቡ ማግስትም በእነዚህ በፈጸሟቸው ግፎችና ወንጀሎች ምክንያት እየታነቁ ለፍርድ እንደሚቀርቡ ጠንቅቀው ስለሚያውቁት በምንም ተአምር ለመቸውም ቢሆን ወያኔዎች “አዎ ተሸንፈናል” ብለው መሸነፋቸውን አምነው የሕዝብን ድምፅ አክብረው ሥልጣን አያስረክቡም፡፡
ቀጣዩ የተቃዋሚ የተወዳዳሪ ፓርቲዎች እርምጃ ምን ሊሆን ይገባል?
እንግዲህ በዘመነ ወያኔ ሰላማዊ ትግል ማድረግና ውጤትም ማምጣት ፈጽሞ እንደማይቻል ከአንዴም 5 ጊዜ ሁሉ በተደጋጋሚ የታየ ሀቅ ነው፡፡ ወያኔ ምርጫን እያዘጋጀ ሁሌም አሸነፍኩ እያለ ሥልጣንን ይዞ የሚቀጥለው ያለ ምርጫ ልግዛ ቢል “የለየለት አንባገነን” የሚባል ስም ስለሚያሰጠውና ይሄንንም መባል ስለማይፈልግ እንጅ በምርጫ ስሚያምን አይደለም፡፡ በምን ምክንያት እንደሆነ ባላውቅም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይሄንን ሀቅ ሊገነዘቡ አልቻሉም፡፡ ቢያንስ ከ97ቱ ምርጫ በኋላ ሊነቁ ይገባ ነበር፡፡ ወያኔ ሁሌም በሚያዘጋጀው የውሸት ምርጫ እየተሳተፉ ለወያኔ “የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት አለ” ልፈፋው (ፕሮፖጋንዳው) መጠቀሚያ መሆንን እንደ አንድ ቁምነገር ቆጥረው ይሄው እንደምናየው ጊዜያቸውን በከንቱ ያቃጥላሉ፣ ወያኔ በሕዝብ ላይ እየቀለደ እያሾፈ እንዳሻው እየሆነ እንዲኖር ዕድል እንዲያገኝ ያደርጋሉ፡፡ “ሞኝን እባብ ሁለት ጊዜ ይነድፈዋል፤ የመጀመሪያውን ተንከርፍፎ ሲሔድ ሳያየው ሁለተኛውን ይሄው እዚህ ቦታ ነው ነድፎኝ እዚህ ውስጥ የገባው ብሎ ሲያሳይ” ይባላል፡፡ አንድ ሌላ አባባልም አለ “ትናንት ያነቀፈህ ድንጋይ ዛሬም ካነቀፈህ ድንጋዩ አንተ ነህ” የሚል፡፡
አማራጭ ስለሌለ እንጅ ከሰላማዊ የትግል አማራጭ ሌላ የትግል አማራጭ ተመራጭ ሆኖም አልነበረም ወገኖቻችን የትጥቅ ትግልን የመረጡት፡፡ ከሰላማዊ የትግል አማራጭ ውጭ ሌላ አማራጭ አስፈላጊ አይደለም የሚሉ ፓርቲዎችም ሆኑ ግለሰቦች የኔ ቢጤ ፈሪ ስለሆኑ እንጅ የሚሉትን ነገር ስለሚያምኑበትና ለዚህ የሰላማዊ ትግል እራሳቸውን የሰጡ ስለሆኑ አይደለም፡፡ የዚህ ማረጋገጫውም በሰላማዊ ትግል የሕዝብን መብትና ፍላጎት ማረጋገጥ ማስከበር ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዱ የሆነው በሕዝብ ምርጫ ሥልጣን መረካከብ የመንግሥት ለውጥ መከወን በወያኔ አገዛዝ የማይታሰብ መሆኑን ካረጋገጡ ዘንዳ ሌሎች የሕዝብን መብትና ፍላጎት ማረጋገጥ ማስከበር የሚቻልባቸውን የሰላማዊ ትግል አማራጮችን ተጠቅመው የሕዝብን መብትና ፍላጎት ለማረጋገጥ ለማስከበር አለመሞከራቸው አለመቻላቸውና ለዚህም ቁርጠኛ አለመሆናቸው ነው፡፡ እነዚህ ከምርጫ ሌላ አንድን አንባገነናዊ አገዛዝ ማንበርከክና ማስወገድ የሚቻልባቸው የሰላማዊ ትግል እርምጃዎች ከሥራ ማቆም አድማ ጀምሮ እስከ መታቀብ (boycott) ድረስ በርካቶች ናቸው፡፡ እነኝህ “ያለ ሰላማዊ የትግል አማራጭ!” ባይ ወገኖቻችን እነዚህን የሰላማዊ ትግል እርምጃዎችን አድርጎ የሕዝብን መብትና ፍላጎት ማረጋገጥ ማስከበር የሚቻልበት ምንም ዓይነት ምቹ ሁኔታ በዚህች ሀገር እንደሌለና አገዛዙ አስቀድሞ እነኝህን እርምጃዎች በመውሰድ ስኬት ላይ መድረስ እንዳይቻል ወደዚያ የሚወስዱ መንገዶችን ሁሉ በመዝጋት ሕዝብን በማነቃነቅ እነኝህን እርምጃዎች መውሰድ እንዳይቻል እንዳደረገ እነኝህ ወገኖቻችን አያውቁም ለማለት እጅግ ይቸግረኛል፡፡ አይ! ዕድሉ አለ እነኝህን የሰላማዊ ትግል አማራጭ እርምጃዎችን በመውሰድ የሕዝብን መብትና ፍላጎት ማረጋገጥ ማስከበር እንችላለን ካሉም እነሆ! ይሄው ሰዓቱ አሁን ነውና አድርጉትና እንያቹሃ! ይሄንን ማድረግ ሳትችሉ ግን በሌለ ምኅዳር ላይ “ሰላማዊ ትግል” እያላቹህ ብታላዝኑ እራሳቹህን ለትዝብት ከመዳረግ ሀገሪቱን የከፋ ችግር ላይ እንድትወድቅ ምቹ ሁሌታን ከመፍጠር ውጪ ለሀገራችን ፖለቲካ (እምነተ አስተዳደር) ዕድገትና መሻሻል የምታበረክቱት የምትፈይዱት አንዳችም ነገር እንደሌለ ልታውቁት ልትረዱት ይገባል፡፡ አሁን በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ወገኖቻችን የጠቀስኳቸው የሰላማዊ ትግል እርምጃዎች በ97ቱ ምርጫ አገዛዙ የምርጫውን ውጤት በቀለበሰበት ወቅት ሞክረውት ዛሬም ድረስ ባሉ ወያኔ እስካለ ጊዜ ድረስም ወደፊትም በሚኖሩ በተለያዩ ምክንያቶች ተሞክሮ እንዳልተሳካ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ስንት ጊዜ እባቡ ሲነድፋቸው ወይም እንቅፋቱ ሲያነቅፋቸው ነው የሚነቁት የሚገባቸው?
እዚህ ላይ “እሽ የትጥቅ ትግልስ እናድርግ ብንል የት ልናደርግ እንችላለን? ወያኔ ይሄንን አውቆ አስቀድሞ የሀገራችንን ሉዓላዊ መሬትና ሌሎች ብሔራዊ ጥቅሞቿን ሁሉ አሳልፎ እየሰጠ ጎረቤት ሀገራትን ሁሉ በወዳጅነት ይዟቸዋል፡፡ ያለው ብቸኛ መንደርደሪያ መተላለፊያ (corridor) ባሕረ ምድር (ኤርትራ) ብቻ ናት ሸአቢያ ደግሞ የባሰ ጠላት እንጅ የተሻለ አይደለምና እንዴት ብለን ሸአቢያን አምነን እዚያ የትጥቅ ትግል ልናደርግ እንችላለን?” የሚል ጥያቄ መነሣቱ አይቀርም፡፡ ሁለት ሦስት የፌስ ቡክ (የመጽሐፈ ገጽ) ጓደኞቸ ሰሞኑን ይሄ ጥርጣሬ ስላላቸው በፍጹም የማይታሰብ ነው ብለው ሐሳባቸውን በመጽሐፈ ገጻቸው ላይ እስከ መጻፍ ደርሰው ነበር፡፡ ለአንደኛው ወንድሜ ይሄንን ብየ መለስኩለት፡፡
“ወንድሜ… ያልከው ሁሉ እውነት ነው አንድም ስሕተት የለበትም እንዲያውም ኢሳይያስ ማለት ይሔ ብቻ አይደለም ከጠቀስካቸው የከፉ ብዙ ጉዶችም ይኖራሉ፡፡ ማየት ያለብን ነገር ቢኖር እኛ ወደ ሸአቢያ የምንሔደው አማራጮች ስለሌሉንና ብቸኛው አማራጭ እሱ ብቻ በመሆኑ እንጅ ወደን ፈልገን መርጠን አለመሆኑን ነው፡፡ “ዘመኑን እንዋጅ” የሚል አማርኛ ተጠቅሜ እንደነበር ታስታውሳለህ? እኛ ኢትዮጵያዊያን የማንነት የደም ነገር ሆኖብን ውስለታ ማስመሰል አንችልበትም፡፡ ያለፉት መንግሥታቶቻችን ከባዕዳን ጋር ሀገር ለሀገር ግንኙነትን ሲፈጥሩ ፍጹም ቅንና ገር ልብ ይዘው ነበር የሚቀርቡት፡፡ የፈጠርነውን ወዳጅነታችንንም ለዘለዓለም እንደሚኖር አድርገን እናስብ ነበር፡፡ በዚያ በኩል ያለው አስተሳሰብ ግን ዘላቂ ጥቅምን እንጅ ዘላቂ ወዳጅነትን መሠረት ያደረገ አልነበረም፡፡ ይሄንን መረዳት ባለመቻላችን ብዙ ጊዜ እየተከዳን ለጉዳት ተዳርገናል፡፡ አሁንም በዚህ የቆየና የዘመኑን አስተሳሰብ ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ ቀጥተኛ አስተሳሰብ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመከራ ዳርጓል፡፡ በነፍስ ሊጠቅመን ይችል ይሆናል ይጠቅማልም፡፡ በሥጋ ግን የምታየውን ያህል እየጎዳን ለመከራ ዳርጎን ይገኛል፡፡ አማራጭ ከሌለና መቀመቅ እየወረደች ያለች ሀገራችንን እየጠፋ ያለ ሕዝባችንን ማዳን መታደግ ካለብን እዚህ ሆነንም ወያኔ በግልጽም በስውርም በሚፈጽመው የማጥፋት ዘዴ ለመጥፋት ቀናችንን መጠበቅ ካልሆነ በቀር በሚፈጽምብን ጥቃት ከሞት የማንተርፍ ከሆነ ያለውን አማራጭ የግድ መጠቀም አመንታች ሊሆን በፍጹም አይገባም፡፡ እዚህም ሆነን እጣችን ሞት ከሆነ እዚህ ሆነን አንዳች ነገር ማድረግ የምንችልበት አማራጭ ከሌለ አንድና ሁለት ብቻ ሳይሆን በገፍ ወደዚያው ብንገባ የኃይል ሚዛኑ በእርግጠኝነት ነገሮችን መለወጡና የተቀስካቸውን ሥጋቶች ማስቀረቱ አይቀርም፡፡ ኢሳይያስ “ቅዱስ” በሉኝ ካለ ብፁዕ የሚል ጨምረን በመስጠት፣ “ሸአቢያ ሽህ ዓመት ይኑር!” በሉ ቢለን “ለዘለዓለም ይኑር” እያልን ለጊዜው በመወስለትና በመርከስ በማስመሰል ዛሬን ማለፍና ነገን ማግኘት የግድ ይኖርብናል፡፡ ይሔ አማራጭ የለውም፡፡ የዓለም ፖለቲካ እየተዘወረ ያለው በእንደዚህ ዓይነት የቅጥፈት ቅኝት ነው፡፡ ሸአቢያና ወያኔ ለዚህ የደረሱት በዚህ እኩይ ክህሎታቸው ነው፡፡ በደንብ መቅጠፍ ማስመሰል የቻለበት ያሸንፋል ያሰበውን ያሳካል፡፡ ቅንነት እውነተኛነት ሐቀኝነት አሁን ላይ አዋጭ አይደለም ድሮ ቀርቷል፡፡ የየዋሀን አምላክ እንዳይረዳንም ኃጢአታችን በየት በኩል ያቅርበው? ጸሎታችን ከጣሪያ በላይ የማያልፍ ሆነ፡፡ እንግዲህ ምን ይደረግ የዋህነት ቅንነት እውነተኛነት ቀጥተኝነት ካስበላ እያዘንን እስከ ነጻነት ቀን ድረስ ከልባችን የውስጠኛው ክፍል ዘግተንበት ቅጥፈትን ማስመሰልን በመካን እኩዮችን ክፉዎችን ሸረኞችን ጠንቀኞችን አስመሳዮችን ሸረኞችን በመብለጥ እራሳችንን ማዳን ይኖርብናል” ነበር ያልኩት፡፡
እናም ለእናንተም እላቹሀለሁ ያለን አማራጭ አንድና አንድ ብቻ ነው የትጥቅ ትግሉን ተቀላቅሎ ወያኔን በተመኘው እሳት አንጨርጭሮ አሳርሮ በማጥፋት ሀገርንና ሕዝብን ነጻ ማውጣት፡፡ ወያኔን ስናጠፋ ሀገርንና ሕዝብን ከወያኔ አገዛዝ ብቻ እንዳይመስላቹህ ነጻ የምናወጣ፡፡ ነገር ግን ወያኔ ቅጥርኛ ሆኖ ከሚያገለግላቸው የዚህች ሀገርና ሕዝቧ ጠላት ከሆኑት ጠላቶቻችን ሁሉም እንጅ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
The post ምርጫም ቅርጫም መሆን ያልቻለው የ2007ዓ.ም. አምስተኛው ዙር ግርግር ትዕይንቱ! appeared first on Zehabesha Amharic.