ከሥርጉተ ሥላሴ 20.06.2015 /ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ/
„አቤቱ፤ አንተ፡ ተስፋዬ፡ ነህና፡ ልዑልን፡ መጠጊያህ፡ አደረግህ“ /መዝ.ምዕ. 90. ቁጥ. 9/
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የተከበሩ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በመጪው ወር መግቢያ ላይ ኢትዮጵያ ሀገራችን እንደሚሄዱ ዜናዎች እያመለከቱ ነው። ለምን ይሄዳሉ? በሥነ – ልቦና ላይ ሊያስከትል የሚችለው ምንድን ነው? ትርፉ ምን ይሆን – ለወያኔ? ኪሳራውስ? እኛ ባለጉዳዮችስ ምን ማድረግ አለብን? ጽናታችን ቤቱን የመገንባት አስፈላጊነትስ ወቅታዊ ነው ወይ – እንደ ሥርጉተ ዕይታ —- ግን እንዴት ናችሁ የኔዎቹ። ደህና – ናችሁን?
http://www.zehabesha.com/us-president-barack-obama-to-visit-ethiopia-on-african-tour-bbc-news/
የተከበሩ ዬአሜሪካው ፕሬዚዳንት፤ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ለምን ወደ ኢትዮጵያ ይሄዳሉ?
- ጊዜ ታሪክን ይሠራል። ስለዚህ በሥራ ዘመናቸው የሰው ልጅ መፈጠሪያ የሆነችውን ምድር እንዲህ መሪ እያሉ መርገጡ አቅደው የከወኑት ነገር ይመስላል። ነገ መሄድ ይቻላሉ። ግን ክብሩ ሞገሱ አሁን የተሻለና የበለጠ ነው። ተደማጭነቱም።
- ኢትዮጵያ የአፍሪካም መዲና ሀገር ናት። ጽ/ቤቱ የአፍሪካው ማህበር ከዛ መኖሩ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ እንብርትነቷም ሆነ መሥራችነቷም – ለአንድ አፍሪካዊ አሜሪካዊ ፕሬዚዳንት ሌላው ሊያመልጣቸው የማይገባው አልማዛዊ ጉዳይ ነው። ወራት ነው የቀረው የሥልጣን ዘመናቸው ሊጠናቀቅ ….. እሽቅድምድሙ ታሪክን ከመገንባት፤ የፖለቲካ ትርፍንም ከማስገኘት ጋር የሚያያዝ ይመስለኛል። ለዛውም በብሄራዊ ምርጫ ላይ በነበረች፤ ምርጫውን ተከትለው የተነሱት ውዝግቦች ሳይሰክኑ – ደሙም ሳይደርቅ – አዲስ ተብዬውም ሥልጣኑን ሳይርከብ ሽግግር ላይ እያለ …..
- የሶሻሊስት ርዕዮትን ነቀልነው፤ ልባችን አስገባንላቸው ብለው አስበው ነበር – የካፒታሊስቱ ዓለም። አሁን ግን በፈጣን እድገት ላይ የሚገኙ የሶሻሊስት ሀገሮች በኢኮኖሚ ብቻ አይደለም፤ በፖለቲካም አስፈሪ እዬሆኑ መጥተዋል። ስለሆነም የሁሉም ነገር ቀለማም መሬት በሆነችው በእማማ አፍሪካ ዬቻይና እግር ሥር ሰደድነት፤ የጀመረችው ጉዞና ያገኘችው ዬኢኮኖሚና የሥነ ልቦና የበላይነት ለካፒታሊስቱ ዓለም የስጋት ቤንዚን እዬሆነ መጥቷል፤ ስለዚህ ፉክክሩን መድረስ ባይቻልበትም እንኳን በተወሰነ ደረጃ የድርሻንም ለማያያዝ የታለመ – ይመስለኛል። ያለፈው ዓመትም የአፍሪካ አንባገነኖች ስብሰባ በአሜሪካ ይሄው ነበር። ስለዚህ የአሁኑ ተከታይ ነው። በነገራችን ላይ ቻይናም ብቻ አይደለችም እያሰጋች ያለችው ዛሬ ራሺያም፣ ኪዩባም። ለዚህ ነው የሶሻሊስቱን ዓለም በለሰለሰ አያያዝና ልዩ በሆነ ሁኔታ ለመቅረብ የተለያዩ ውጥኖችና ድርጊቶችን እያዬን ያለነው። ንጉሣዊ አስተዳደሮች ሳይቀሩ ከቀደመው በተሻለ ጥበብ አሜሪካ እዬቀረበ ነው። „ኃያልነት“ ላጥ ካለ … እ.
- ምንግዜም የኢትዮጵያ ጂኦ ፖለቲካ አቀማማጥ ላደጉ ሀገሮች የስጋት ምንጭነቱን በቅርብ ማድመጥ ወቅቱ የጠዬቀው
እንብርት ጉዳይ ነው። ከዚህም በላይ ያልሰከነው የመካከለኛ ምስራቅ ሀገሮች ጉዳይም አለበት።
- የበለጸጉ ሀገሮች ሱማሌና ናይጀርያ ላይ የተመሠረቱ የሃይማኖት አክራሪዎችን ጉዳይ እልባት እንዲአገኝ የሚሹት እሱ በእሱ እንዲሆን ይመስላል። ለዚህ ደግሞ ደጎስ ያለ ጉርሻ የሚያገኘው የወያኔ ትግራይ ሃርነት „የራሷ ሲያርባት“ ዓይነት ነው። በዘመኗ ኢትዮጵያ እንዲህ ለባዕድ እጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ተጋልጣም፤ አስፈጻሚ ሎሌ – አስተዳዳሪም ተፈጥሮባት አያውቅም። በተጨማሪም ናይጀርያ፣ ሱማሌና ኬኒያ ላይ ከአሜሪካ ሰራዊት ቁስ ከማጓጓዝ እዛው ዕዳውን ማሸከም ቀለል ያለ የኮክቴል … ትዕይንት ይመሰለኛል። ወጪውን ይቀንሳል የደም ዋጋው ደግሞ ጥቁር – በጥቁር።
ይህ ጉዞ – በሥነ ልቦና ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጠንቅ ምንድን ነው?
- እስር ላይ ያሉ ወገኖቻችን ከልብ ሊከፋቸው ይችላል፤
- ትግል ላይ ያሉ ወገኖች ተስፋ ሊያንሳቸው ይችላሉ፤
- የኢትዮጵያ ህዝብም ዕንባዬን የሚጋራ ሃይል የለኝም ለካ የሚል ዕድምታ ሊፈጥርበት ይችላል፤
ትርፉ ምንድን ይሆን ለወያኔ ሃርነት ትግራይ?
- ለአሜሪካ መንግሥት የሚሰጠው ማናቸውም የሥነ ልቦናና የመንፈስ ጉቦ ሆነ እጅ መንሻ ሥጦታ የመስጠት አጋጣሚ በድሎት ምቹ ቦታና ጊዜ ያገኛል፤ ወረታ ዓይነት — ግን ከሌሎችም ጋር አድርገውት ነበር። ሲያልቅ ግን አያምርም።
- የኢትዮጵያን ህዝብ ጆሮ በፕሮፖጋንዳ ጭዶች – ይሞላበታል፤ ሥራም ይኖራቸዋል ሚዲያዎች – የወያኔዎቹ።
- በደል፣ ግፍ፤ መከራ፤ ዘረኝነት በሲሚንቶ – ይጣፋሉ፤
- ትንሽዬ – አታሞዋም – ያልፍላታል።
ኪሳራ ለወያኔ ሃርነት ትግራይ …
- የማይሸፈኑ ነገሮችን መሸፈን አይችልም፤ ጨዋነትን የዋጠ ግን „በቃኝ፤ አሻም፤“ …. አቅም ሊያገኝ ይችላል።
- የዓለም ሚዲያ ከቦታው ስለሚሰፈር ወያኔ ሃርነት ትግራይ የከለከላቸው መንገዶች ወደደም ጠላም – ይከፈታሉ። – ሃቆች ይጋለጣሉ፤ መስማትና ማዬት አንድ ስለማይሆኑ „ሰውን“ የተረጎሙ ጋዜጠኞች፤ የፎቶግራፍ ባለሙያዎች መንፈሳቸውን በሰብዕ ጉዳይ ላይ ይለግሳሉ። የቬትናሙ የግፍ ጦርነት ጊዜ ጀርመናዊ የፎቶ ግራፍ ባለሙያ ሙያውን ለሰብዕ ተግባር አውሎታል። የዘመኑ ኃያሎችንም ታግሎ ዕልፎችን – አሰልፎበታል። በዬትም ሀገር የነበሩ ወጣቶች ፊት ለፊት ወጥተው ድርጊቱን አውግዘዋል። ሽንፈትን ያለቀዱትም – ውጠውበታል።
- እኛ ያላያናቸው ፈጣሪ ያለመው ገመና ይፋ ይሆናል …
- እግራቸው ደረቅ ከሆነም ሌላ መርዶ ሊከተል ይችላል …..
- የነፃነት ትግሉ ቤተሰቦች እራሳቸውን በመመርመር የበለጠ ትጋትና ጥንካሬ እንዲያገኙ፤ የራሳቸውን ዕድል ወሳኞች እራሳቸው ስለመሆናቸው፤ የተረገዘው እልህ መገላገል ሊኖር ይችል ይሆናል? ማን ያውቃል? „ ነገር ሁሉ ለበጎ ነውና“ ሂደቱ ቁጭትን ተልሞ ወደ አንድ የመንፈስ አቅጣጫ የመምጣትን አስፓልት ይጠርጋል … ስለምን እንገፋለን? ስለምንስ ዓለም የእኛን ዕንባ ያገለዋል? ዛሬ – ቢያንስ እኔ አካሌን እንደአካሌ ማዬት አለብኝ ከሚል ቁርጥ ካለ ውሳኔ ያደርሳል።
እኛ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
- በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ከዜናዎች ሥር የእስር ቤቶችን ዝርዝር መጻፍ፤ የእስር ቤቶችን ፕላንም፤ አድራሻም አብሮ መለጠፍ። የፖለቲካ መሪዎች፤ የሃይማኖት መሪዎች፤ የጋዜጠኞችና ጸሐፊዎች፤ የብሎገሮች ፎቶቸውን መለጠፍ ሳይታክቱ በዘመቻ …
- ይገኛሉ ተብለው በሚታሰቡት ዓለምአቀፍ ሚዲያዎች በሚመሯቸው የሶሻል ሚዲያዎች ተመሳሳዩን ተግባር መለጠፍ፤ በርካታ ስለ ሰው ልጅ ተቆርቋሪ ጋዜጠኞች ዓለም አላትና።
- በእንግሊዘኛ የተፃፉ አጫጫር በራሪ ጹሑፎችን ለዓለም አቀፉ ሰብዕዊ መብት አስከባሪ ድርጅቶች ሥር በሚተዳደሩ ማህበራዊ ድህረ ገፆች፤ ፌስ ቡኮች፤ መለጠፍ …. /ቢሮክራሲ የሌለበት ቀለል ያለ የተደራጀ ተግባር መከወን/
- ደብዳቤዎችን ለዓለምአቀፍ ማህበረሰቡ መጻፍ ግን አጭርና ግልጽ መሆን አለባቸው፤ ዕንባን ብቻ የሚያመለክቱ። የሰማዕቱ የኔሰው ፎቶ ብቻ ሊሆን ይችላል። ወይንም የአርበኛ ኦኬሎ ወይንም የአርበኛ አንዳርጋቸው …. ወይንም ዕንባ እያለቀሰች …. የአንዲት ሴት ፎቶ፤ ብቻ ሥርዓትን የጠበቁ፤ ጨዋነትን የተላበሱ …. ተከታታይ ተግባራትን መከወን፤
- ሀገር ቤት የሚገኙ የነፃነት ፈላጊ ድርጅቶች በአንድነት ሰላማዊ ሰልፍ ማዘጋጀት፤ ነገር ግን ዕቅዳቸው መንፈሳቸው፤ ፍላጎታቸውን ግን አማክለው ከእውነት መሆን ይኖርበታል። ከውስጣቸው ሆነው ተከፍተው ሊሰናዱ ይገባቸዋል። ለምሳሌ በአንድ ወቅት አንድነት አዘጋጅቶት የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ተምሳሌቱ ወደር አልነበረውም / እንስራ ተዘቅዝቃ፣ ባዶ እግር፣ ድግሪ ድንጋይ ተሸክሞ ኢንተርኔት ታስሮ ወዘተ …./
- በሰላማዊ ሰልፉ ላይ በአንድ ድምጽ ኡ ኡ ኡ ብቻ ማለት እራሱ በቂ ነው። የለቅሶ ቀን ውሎውን …. ከፍተኛ ፖለቲከኞች ላይሰሙ ይችላሉ። ነገር ግን ዬሰብዕዊ መብት ተቆርቋሪዎች ያደምጣሉ፤ እግዚአብሄርም አለ። ከተከፉት ጎን አምላካችን ይቆማል። ሱባኤ ወቅትም ነው ለሁለቱ ታላላቅ ሃይማኖቶች። ይህም ብቻ ሳይሆን የተከበሩ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ፓርቲም ተፎካካሪዎች አሉት፤ መጪው ደግሞ የምርጫ ዘመን ስለሆነ አጋጣሚውን ለመጠቀም መሞከሩም መልካም ነገር ይመሰለኛል። ከዚህ ሌላ የሚሄዱት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት፤ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ብቻ አይመስሉኝም፤ የሌላ ሀገር መሪዎችም ሆኑ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች ይጓዛሉ። …. ስለዚህ የሚሠሩ ሥራዎች የተሰባሰበ ጎልን ዓላማ በማድረግ ቢሆን መልካም ነው። ለአንድ ተብሎ የተዘጋጀው ምግብ ሶስት አራት እንግዳም ቢመጣም ይባቃል። ተረፍ ተረፍረፍ ተብሎ ከተዘጋጀ ….. አጫጭር ግን ክውን ያሉ ቅድመ መሰናዶዎች ማድረግ፤ በፍጥነትም አደራጅቶ መጀመር የሚያስፈልግ ይመስለኛል። action is everything. በተለይ ይህ ክንውን ቢያንስ ሂደቱ አፈር እንደ ቀመሱ፤ ህይወታቸውን በፋሽስት የተቀሙት ቤተሰቦቻችን ሀዘን ላይ እያሉ ስለሆነ፤ የሰማዕታቱ – ታክሎ። የሀገርና የውጭ መርዶ የሚያርመጠምጠው ህዝባችን ሥነ ልቦና ይጠብቅልናል። አለንልህ! አይዞኽ። ትልቅ ተስፋ ነውና።
ጽናትን መገንባት – ለተስፋ ተስፋ መሆን ነው።
ስላለው ይወደዳል። ስላለው ይከበራል። ያለው ሳቁ ይናፈቃል። „ያለው ማማሩ“ እንዲሉ። ሲኖረን እንወደዳለን፤ እንከበራለን፤ ሳቃችን – ይናፈቃል፤ ተስፋችን – ይደነቃል። ስለዚህ አቅም ሲኖረን አቅማችን ሁሉንም የማድረግ አቅም ይኖረዋል። አቅም ደግሞ ከሁሉ ዘንድ አለ። ቢያንስ በመንፈስ አንድ መሆን። በግል ኢጎ ላይ መሸፈት። በኮፒራይት ፍቅር ላይ መሸፈት። ወያኔ የፈጠረውን የቅርጫ ገበጣ ረግጦ ወደ አኃታዊነት መምጣት። ያን ጊዜ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ብቻ ሳይሆን አቆላማጫቸውም ከዳጡ በፊት ግብር ያስገቡልናል።
በምንም ሁኔታ ቢሆን የራስን ጥረት የሚተካ ምንም ነገር የለም። አይኖርምም። እስኪ አንድ ተግባር ጀምሩና እራሳችሁ ሥሩት፤ እንዴት እንደሚያምር፤ ሁለመናችሁን ስለሰጣችሁትም ልክ እንደ ህፃን ልጅ ትንከባከቡትአላችሁ። ደክማችሁበታላ፤ ለፍታችሁበታላ። ስለዚህ በራስ ላይ እምነት መጣል፤ በእጅ ባለ ነገር መጀመር። በእጃችን ያለ ብዙ የተመክሮ፤ የልምድ፤ ዬዕውቀት፤ የፍላጎት፤ ሃሳብ አዲስ የማፍለቅ፤ የፋይናንስ፤ የጥበብ በሁለገብነት አለን። ይህን ወደ አንድ ማዕከል መንፈሱንም ቁሱንም፤ ሥነ ልቦናውንም በፍቅር ብናመጣው አይደለም ድርጊት ላይ ተገኝቶ እኔ ስጽፈው እንኳን እንዴት ጤነኛ እንደሆንኩኝ። የጋራ ቁስል መዳህኒቱ የጋራ ነው። ጅምሮች አሉ … ጅምሮች አንጋጠው የላይኛውን ብቻ ሳይሆን ትናንሽ የመገናኛ መስመሮች ሁሉ፤ የመወያያ መድረኮች ሁሉ፤ የድጋፍ አንባዎች ሁሉ ወደ አንድ መንፈስ መምጣት በማናቸውም አጋጣሚ ለሚገጡምን የብቸኝነት ፈተናዎች መፍትሄ ናቸው። ለእኛ እኛን እንስጠው። ለእኔ እኛ ይሰጠኝ። ለእኛ ደግሞ እኔን ልስጠው።
አሁን አብሶ በታሰሩት ወገኖቻችን ብቻም ሳይሆን በቤተሰቦቻቸው፤ ውጭም ሆነው በግፍ በተገለሉት፤ በተፈናቀሉት ወገኖች ላይ የሰሞናቱ ዜና ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጫና ሊያደርግባቸው ይችላል። አቃለን ስናዬው ብቻ ነው ሰነፍ እምንሆነው። ብልቱን ካገኘነው ግን እንበረታና ትጥቃችን – ጠበቅ፤ ድካማችንም – ሸኘት፤ ተስፋ ቆራጭነትን – ቀብር አድርገን በአዲስ ኃይለና ጉልበት ጽናትን በፅናት እንገንባው። ለተስፋ – ተስፋ መሆን – ዛሬ። ለጽናት ጽናት መሆን – ዛሬ። የኛ ጽናት ለወገኖቻችን፤ ተስፋ ለሚያድርጉን ሁሉ ነጋቸው ነውና።
ልከውነው የነጻነት ገበሬዎቼ – ዛሬ – የሠራነውን ተግባር ለመገምግም የሚያስችሉ ሁኔታዎችን – አዳምጠናል። ስለዚህ ተሽሎና በልጦ ለመገኘት፤ ለዛውም የፕሮፖጋንዳ ክምር፤ የቁጥርን ካብ ንዶ ሃቅን ለማፍለቅ – ዛሬ። …. ከሁሉ በላይ ይህን በታሪክ አይተናል። ከራሳቸው ጥቅም ተነስተው ማናቸውንም አንባገነን አስተዳደር የሚደግፉ ሀገሮች፤ በህዝብ የበቃ ተስታፎ አንባገነኖች ሲወገዱ የሚወዳጁት ከአዲሱ ከአሸናፊው ጋር ነው። „ለሄያጅ ዘመድ የለውም“ እንዲሉ። እንደዛ መሪ መሃመድ ጋዳፊ ያን የመሰለ ጭንቅ ሲገጥማቸውና መሬት ስትከዳቸው አልነበሩም ከጎናቸው …. ሚዛን ወደ ከበደው ነው ጆሮው ….. የኔዎቹ ሳናቀለውም – ሳናከብደውም፤ ሳንበሳጭም፤ በተረጋጋ – በሰከነ – በታቀደ – በሰለጠነ መንገድ ክሽን ያለ ተግባር መከወን ከቻልን ለተስፋ ጥግ ለጽናት ብረት እንሆናለን። ሁለት መሰረታዊ ተግባር በአንድ እርምጃ፤ ሂደቱን ማጋለጥ ከኢትዮጵውያን በደል ጋር ዓለም እንዲታደም በማድረግ፤ ሁለተኛው የነፃነት ፈላጊ መንፈስና ፍላጎት እንዳይዝል ሥነ ልቦናን ማሰባሰብ፤ የኃይል ምንጭ ማድረግ መቻል። ሌላው ትልቁ ነገር ግን ተስፋ ያለው ከአንድዬ ብቻ ነው። አንድዬ ትልም አለው ለዕንባችን። አይዞን። እንበርታ። የልቤን ዘሃበሻ አመሰግናለሁ – ኑሩልኝ። አቅም ያላችሁ እንደምትጀምሩት ተስፋዬ ሙሉዑ ነው።
ለእኔስ ሰው መሆኔ ብቻ ይበቃኛል።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
The post ዛሬ! – ከሥርጉተ ሥላሴ 2 appeared first on Zehabesha Amharic.