አንዱዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ
ረቡዕ፤ ሰኔ ፲ ቀን፤ ፳ ፻ ፯ ዓመተ ምህቱረት ( 6/17/2015 )
ኢትዮጵያዊያን፤ ተከታታይ አምባገነን መሪዎችን ከነአገልጋዮቻቸው ለማስወገድና የሕዝቡን የሥልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ የምናደርገው ትግል፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ ነው። በ ፲፱፻፷፮ ዓመተ ምህረት ሕዝቡ የተነሳባቸው የመብትና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄዎች አሁንም አልተመለሱም። ይኼው ሃምሳ ዓመት አለፈው። ይባስ ብሎ ሕዝቡን የመንግሥት አገልጋይ አድርጎ የሚጠቀም ጠባብ አምባገነን ገዢ፤ በሀገራችን ነግሷል። ይኼን መንግሥት ለማስወገድ የሚደረገው ትግል ማዕከል የለውም። በሀገር ቤት ከፍተኛውን መስዋዕትነት እየከፈሉ የሚንቀሳቀሱት የሰላማዊ ታጋዮች እና ከሀገር ውጪ ያሉ ታገዮች፤ በመካከላቸው የትግል ቅንጅት የለም። በሀገር ቤት ያሉት የሚያደርጉት ትግል፤ ምስጋና ለወራሪው የትግሬዎች ነፃ አውጪ አምባገነን መንግሥት ምስጋና ይግባውና፤ መልክ እየያዘ ነው። የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ የአንድነት ፓርቲና የሰማያዊ ፓርቲ ታጋዮች ወደ አንድ መሰባሰባቸው፤ የትግሉን ማዕከል ለማበጀት የማዕዘን ድንጋዩን ጥሏል።
ሰላማዊ ትግል ካለው መንግሥት ዓይን የተሰወረ ተግባር የለውም። ለአቸናፊንቱ ያለው እምነት የተመረኮዘው፤ የጨበጠው እውነትና ያነገተው የሕዝብ እዮታ ነው። እውነት ምን ጊዜም አቸናፊ ሆኖ ይወጣል። የሕዝብ እዮታ ደግሞ፤ ይዘገይ እንደሆን እንጂ፤ አቸናፊ ሆኖ መውጣቱ አያጠራጥርም። ምንም እንኳ የገዥው ክፍል፤ በዕለት በዕለት በሥር በሥሩ እየተከታተለ ሰላማዊ ታጋዮችን ሊያመክን ቢሞክርም፤ ምንጫቸው የገዥው በደል የደረሰበት ሕዝብ ነውና አይደርቅም። እኒህ በሰላም ለመታገል ቆርጠው የተነሱ ታጋዮቻችን የሚያደርጉትን ትግል፤ እነሱም ሆነ ከነሱ ውጪ ያለነው ሌሎች ታጋዮችና ሰላማዊው ሰው፤ ስለሚያደርጉት ሆነ ማድረግ ስላለባቸው እንቅስቃሴ ያለን ግንዛቤ፤ አንድ አይደለም። የሰላማዊ ትግልን ምንነት፣ ጠቃሚ ግንዛቤና ዝርዝር መርኅ፤ ከመጽሐፍትና ከድረገፆች ማግኘት ይቻላል። ያ መሠረታዊና ለመነሻው መረጃ ነው። እናም እንደ ማንኛውም ኅብረተሰባዊ ክስተት ሁሉ፤ በሚተገበርበት ቦታ፤ ያካባቢውን ተጨባጭ እውነታና የትግል ተመክሮ ከዝርዝር ውስጥ አስገብቶ፤ ያካባቢው የተለዬ ሁኔታ አስተካክሎት፤ ለሂደቱና ስኬቱ ዋነኛ የሆኑ ወሳኝ ሁኔታዎችን በትክክል ካልተረዳን፤ ድፍኑ የሰላማዊ ትግል ግንዛቤ፤ ተንሳፋፊ ነው። ከዚህ በመነሳት፤ በኢትዮጵያ የሰላማዊ ትግልን ግንዛቤ በግልጽ በመተንተን፤ ሰላማዊ ትግሉ እንዴት ነው? የሚለውን መልሼ፤ አንድ ተመሳሳይ ግንዛቤ ላይ እንድንደርስ፤ በዚህ ጽሑፍ አሳያለሁ።
በሀገራችን በኢትዮጵያ፤ ሰላማዊ ትግል፤ በሀገራችን ያለውን ሕግና ስነ-ሥርዓት በትክክል አምነውበት፤ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን ሁኔታዎች መሟላትና መኖር ተቀብሎ፤ መንግሥታዊ ሥልጣኑን በምርጫ ተወዳድሮ በማቸነፍ፤ ገዥውን ፓርቲ ለመተካትና ያለውን ሥርዓት ለማስቀጠል የሚደረግ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አይደለም። ሰላማዊ ትግል የተወዳዳሪ ወይም የተፎካካሪ ፓርቲዎች መንገድ አይደለም። የተፎካካሪ ወይም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች፤ ያለውን ሥርዓት ትክክለኛነት ከጥያቄ ውስጥ አይስገቡም። ከገዥው ክፍል ያላቸው ልዩነት፤ ውስንና የአስተዳዳር ዘይቤ ላይ ያተኮረ ነው። ሰላማዊ ትግል፤ መሠረታዊ የሆነ ሀገራዊ የአስተዳዳር ፍልስፍናና ተግባር፤ ከዚህም ተነስቶ የአስተዳዳር መመሪያውን አፈጻጸሙ ላይ ልዩነት ያቀርባል። ሰላማዊ ታጋዮች፤ የፖለቲካ ምኅዳሩ መጥበብ ብቻ ሳይሆን፤ ተዘግቷል ብለው ያምናሉ። ሰላማዊ ትግሉ፤ ገዥውን ክፍል ለማስወገድ የሚደረግ ንቅናቄ ነው። ለመተካት የሚደረግ ሩጫ አይደለም።
ሰላማዊ ትግሉ፤ ሁለት ተፃራሪ የሆኑ ተግባራት ባንድ ላይ የሚከናወኑበት ሂደት ነው። የመጀመሪያው እንደ ፖለቲካ አካል ለመንቀሳቀስ፤ የሀገሪቱ ሕግና ደንብ በሚያዘው መሠረት፤ ተመዝግበው ሕጋዊ የሆነ እንቅስቃሴያቸውን ማካሄድ ነው። ይህ፤ የማይወዱትን ግዴታ እንዲቀበሉ ያስገድዳቸዋል። እናም መከተል ያለባቸው መንገድና ማድረግ ያለባቸው ግዴታ አለ። እንደ የፖለቲካ አካል በምርጫ ቦርዱ መመዝገብ፣ ተወዳዳሪዎችን ማዘጋጀትና ማቅረብ፣ መወዳደር የመሳሰሉት ናቸው።
ሁለተኛውና የሕልውናቸው መሠረታዊ ዓምድ፤ ሰላማዊ ከሚለው ማንነታቸውን ገላጭ ቃል ቀጥሎ ያለው ትግሉ ነው። ይህ እምቢተኝነታቸው ነው። ይህ ነው ትግሉ። ሕዝቡ ዕለት በዕለት በየቦታው የሚደርስበትን በደል አብረው ተካፋይ ስለሆኑ፤ ተበዳዩን ወገን በማሰለፍ፤ በእምቢተኝነት ለአቤቱታ ይነሳሉ። መልስ እንደማያገኙ ግልጽ ነው። ሆኖም ግን፤ በሂደቱ፤ እያንዳንዱን የሕዝብ በደል፤ ሀገራዊ መልክና ይዘት በመሥጠት፤ ሕዝቡን ለእምቢተኝነት ይቀሰቅሱበታል። የበደሎችን ተዛማጅነት ያሳዩበታል። የመወዳደር ግዴታቸውንና በዚህ አጋጣሚ የሚፈጠሩ መድረኮችን፤ ለዚሁ ተግባር ያውሏቸዋል። ተወዳድረው ለማቸነፍ ሳይሆን፤ የውድድሩን ሂደት ሕዝቡን ለመድረሻና ለመቀስቀሻ ይጠቀሙበታል። አምባገነኑን ገዥ ክፍል ለማጋለጫ ይጥእቀሙበታል። መወዳደራቸው የመጀመሪያውን ግዴታቸውን ሲያሟላላቸው፤ ተወዳድረው የማቸነፍ በሩ እንደተዘጋ ያውቃሉና፤ ሂደቱን ለመቀስቀሻ ሲጠቀሙበት፤ ሁለቱንም ግዴታዎቻቸውን አሟሉ ማለት ነው።
ይህ ነው በተወዳዳሪ ድርጅቶችና በሰላማዊ ታጋዮች መካከል ያለው አንዱ ልዩነት። በመሠረታዊ ማንነታቸው ላይ ያለው ሌላው ወሳኝ ልዩነት፤ ተወዳዳሪ ድርጅቶች ከአንድ በላይ ሊሆኑ ይችላሉ። ሰላማዊ ትግሉን የሚያራምዱ ታጋዮች ግን፤ አንድ እና አንድ ድርጅት ብቻ ነው የሚኖራቸው። ካንድ ከበዙ የሰላማዊ ትግሉን ሂደት አበላሽተውታል። ለምን?
ሰላማዊ ትግል፤ ያለው የገዢ ቡድን መወገድ አለበት ብሎ የተነሳ ሕዝብ፤ የሚወስደው የፖለቲካ እርምጃ ነው። በዚህ እምነት ዙሪያ የሚሰባሰቡ፤ ውስን በሆነ የመታገያ ዕሴቶች የተባበሩና ከዚያ ውጪ፤ የተለያዬ አመለካከት ያላቸው ናቸው። በአሁኗ ኢትዮጵያ የሚደረገው ሰላማዊ ትግል፤ አስራ ሁለት መሠረታዊ የትግል ዕሴቶችን ያቅፋል።
፩ኛ. ያለው አስተዳደር፤ ጠባብ፣ ወገንተኛና አምባገነን ነው።
፪ኛ. በሀገራችን ሕዝቡ ዴሞክራሲያዊ መብቱ ተረግጧል።
፫ኛ. የገዥው ክፍል እውነተኛ የሕዝብ ተወካይ አይደለም።
፬ኛ. ይህ ሥርዓት ሲወገድ፤ የሚከተለው ሥርዓት፤ ዴሞክራሲያዊና ኢትዮጵያዊ ይሆናል።
፭ኛ. ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገው ትግል፤ በሽግግር መንግሥት ሂደት ሥር ያልፋል።
፮ኛ. በዚህ የሽግግር ወቅት፤ የሀገራችን የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ይረቀቃልና ይጸድቃል።
፯ኛ. በዚህ የሽግግር ወቅትና በሕገ-መንግሥቱ፤ የግለሰብ ዴሞክራሲያ መብቶች ይከበራሉ።
፰ኛ. በዚህ የሽግግር ወቅትና በሕገ መንግሥቱ፤ በሀገራችን የሕግ የበላይነት ይሰፍናል።
፱ኛ. በሕገ-መንግሥቱ፤ እያንዳንዳችን በኢትዮጵያዊነታችን ብቻ የምንሳተፍበት የፖለቲካ ምኅዳር ይዘረጋል።
፲ኛ. በዚህ የሽግግር ወቅትና በሕገ-መንግሥቱ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ይጠበቃል።
፲፩ኛ. በዚህ የሽግግር ወቅትና በሕገ-መንግሥቱ፣ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ይከበራል፤ ሀገሪቱ ለኢትዮጵያዊያን ትሆናለች።
፲፪ኛ. በዚህ የሽግግር ወቅት፤ ለዴሞክራሲ ሥርዓት መሠረታዊ የሆኑ ተቋማት ይቋቋማሉ።
የሚሉት ናቸው።
በነዚህ ዙሪያ የሚሰባሰቡት የፓርቲ አባልት አይደሉም። በነዚህ የትግል ዕሴቶች ዙሪያ የሚሰባሰቡት፤ መላ የተበደሉና ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊያን ናቸው። ከነዚህ የትግል ዕሴቶች ሌላ ይዞ ሊንቀሳቀስ የሚችል፤ የገዥውን ክፍል ለውጥ የሚሻ አይኖርም። ሌላ አጀንዳ ያለው ካለ፤ የትጋዩ ክፍል አካልም ወገንም አይደለም። ይህ ወደ ሽግግር መንግሥት የሚወስደው ጎዳና፤ አንድ ነው። ከዚያ በኋላ የሚከተለው እንዲህ ነው።
ታጋዩ ክፍል፤ ሕዝቡ የትግሉ ባለቤት፣ መሪና የድሉ ባለቤት መሆኑን አምኖ ይቀበላል። ስለዚህ የሕዝቡ ድርሻ የሆነውን፤ በሽግግሩ ጊዜና ከሽግግሩ በኋላ፤ ሕዝቡ የሚወስነው ይሆናል። ከዚያ በፊት ለሚደረገው ትግል፤ ታጋዩን በሙሉ በአንድነት ማሰባሰብና፤ ትግሉ በአምባገነኑ ወገንተኛ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርና በሕዝቡ መካከል ብቻ መሆኑን ተረድተን፤ አንድ ትግል አንድ ኢትዮጵያዊ ራዕይ ይዘን የምንፋለምበት መሆን አለበት።
ሰላማዊ ትግሉ በኢትዮጵያ የአሁን ተጨባጭ የፖለቲካ ሀቅና ከትጥቅ ትግል ተለይቶ የተሻለ አማራጭ የሚሆንበትን ምክንያትና ሌሎች ትንታናዎቼን በሚቀጥሉት ክፍሎች አቀርባለሁ።
The post የሰላም ትግሉ በኢትዮጵያ (ክፍል ፩) – አንዱዓለም ተፈራ appeared first on Zehabesha Amharic.