Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የጓጐሉ –ጉሞች –ከሥርጉተ ሥላሴ

$
0
0

ከሥርጉተ ሥላሴ  27.06.2015 / ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ /

ከሥርጉተ ሥላሴ 02.023.2014 (ሲዊዘርላንድ - ዙሪክ)

ከሥርጉተ ሥላሴ 02.023.2014 (ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ)

የእስልማና ዕምነት ተከታይ እህቶቼ አሜሪካን ሀገር በነበራቸው ጉባኤ ላይ „የታሰርነው እኛ ነን“ ሲሉ ቅኔ – ተቃኙ። እውነታቸውን አኮ ነው። የፍላጎታችን አባጣ ጎራባጣነት የወጎኖቻችን ዕንባ እንዳይቆም ማነቆ ሆኗል። በዕዬለቱ የሚሰማው ባለቤት የለሹ መርዶ ትንፋሻችን – ሆኗል። በዬትኛውም የሀገራችን ችግር፤ በዬትኛውም የዓለም ክፍል ቤተ – ግፉዕኑ። ልብሷን የለበሰ፤ እናቴ እማማ ብሎ የጠራ ወንጀለኛ – አሸባሪ – አክራሪ – ጽንፈኛ ተብሎ – ይሞታል፤ ይታሰራል፤ ይደበደባል፤ ይዋረዳል፤ ይሰደዳል። የፍላጎታችን ቅንጡነት የወገኖቻችን ዕንባ እንዳይቆም ማነቆ መጋኛ ሆኗል። በዕዬለቱ የሚሰማው ባለቤት የለሹ መርዶ ትንፋሻችን – ሆኗል። በዬትኛውም የሀገራችን ችግር፤ በዬትኛውም የዓለም ክፍል ቤተ – ግፉዕኑ ኢትዮጵያውያን። ኢትዮጵያ ዛሬ ልጆቼ ብላ ከመከራው ሁሉ እትብቶቿን ልትታደግ እንዳትችል እሷም እስር ቤት ናት። ልብሷን የለበሰ፤ እናቴ እማማ ብሎ የጠራ ወንጀለኛ – አሸባሪ – አክራሪ – ጽንፈኛ ተብሎ – ይሞታል፤ ይታሰራል፤ ይደበደባል፤ ይዋረዳል፤ ይሰደዳል።

ዛሬ ኢትዮጵያ ባርነት ውስጥ በከፋ ቅኝ ግዛት ውስጥ ትማቅቃለች። ልጆቿ ዕንባቸውን ማፈሰስ ተክልክለው እንደ ልጅ ዋጥ! ዋ! ሱ! እዬተባሉ በስጋት ተሰንገው በዓለም የሌለ እውሃ ያዘለ መከራ ተሸከመው ይገኛሉ። ዛሬ ለኢትዮጵውያን በ21ኛው ምዕተ ዓመት ዴሞክራሲ የድሎት ጥያቄ ነው። የነፃነት ጥያቄ በባሩድ ነዶ አመድ እዬሆነ ነው። ቁጭ ብሎ አንገትን ደፍቶ ሰቀቀንን ታቅፎ ከመኖር – ይህም ሞት ሌላውም ሞት በመሆኑ የቆረጡት ትግላቸውን በስልታቸው መርጠው ሁሉን በመቀበል ላይ ይገኛሉ። ዘመናይነት ደግሞ የነፃነት ትግል የጫጉላ ሠረጋላ ስለሚመስለው አጋጣሚ እዬፈለገ ህይወቴን – ነፍሴን – ትዳሬን –  ወጣትነቴን እሰጣለሁ ያሉትን ደምና ሥጋዎች፤ ለሥነ – መንፈሳቸው ፍጹም ጥንቃቄ ሳያደርግ ያለ ርህራሔ በወረፋ፤ በፈረቃ ይደበድባቸዋል። ዘመናይነት በእጅ በሌለ ነገር ላይም – ለነገ በቀነ ቀጠሮ ባለ ዬምንዕብም ትልም ሙያተኛ (plan analyser) ሆኗል። ለነገሩ እሱም ነፃነት ፈላጊ ነኝ ባይ ነው።  – ሃቁ ግን እንቅፋት መፍጠር፤ በነፃነት ትግሉ ላይ የቅንጣት ታክል ጉድፍ ማስቀመጥ የነፃነት ትግል ፍላጎትን እራስን ብልዛም ውይባም ማድረጉን ካለማገናዘብ የመነጨ – ይመስለኛል። ሰው አካሉን እንዴት እንደ ተለጣፊ – ያዬዋል። ቀዝቃዛ። መንፈሱን ጠረኑን … በረዶ። ዋ! ኢትዮጵያ — ስለአንቺስ ማህፀኔ አለቀሰ – ደም።

ትኩረቱ በመሰረታዊ ምክንያታዊ ጉዳይ ሳይሆን በሳቢያ ላይ ያተኮረ በመሆኑ፤ በዬወቅቱ የሚያነሳው ተዋጊ ሃሳብ መጠለያ ፈልጎ የሚለቀቀወ የተቀበረ ፈንጂ ሲሆን ዕንባን እንዲቀጥል እንጂ የቅንጣትም በጠላት ጎራ ላይ የሚስገኘው ትርፍ የለም። የዕንባው ስቃይ እርቆት ሆኖ ይሆን? አቅምን በይው ሃሳብ የውስጥነትን አቅም በባዕድነት ሲያስተናግድ? + ቁስለት። የነፃነት ትግሉን ካለ አቅሙ ካለወርዱ ቻል እዬተባለ እዬተጫነ ዘብጦ እንዲሰምጥ ለዛውም በዘመቻ – ተያይዞታል – በአድማ ፍታውራሪ ዘመናይ፤ ባላንባራስ ቅልጣን። ከቶ ህሊና የሚባለው ጸጋ ዬት ተደበቀ ይሆን? ከአቅሙ በላይ ነው የተሸከመው የነፃነት ትግላችን። ሌላ ዘመቻ ሌላ ጦር እንዴት ይታዘዝበታል —- ተስፋችን ? ? ? ይሄ ትናትን የበላ የበኽር ቁምነገር እዬጠፋ — እዬተረሳ … በገፍ የተሰጠ ዬነፃነት ትግሉ ቤተኛ ህዝበ – ፍቅር እዬተምዘገዘገ — ወይ ሐገር? ወይ ሰንደቅ? ወይ ማንነት? ወይ የህዝብ ፍቅር?

ወያኔ ሃርነት ትግራይ እንደጦር የሚፈራው ነገር ለነፃነት ፈላጊው ጣዕሙ፤ ወዙ መሆን ይገባዋል እንጂ፤ እንደ ገደል ማሚቶ የጠላትን ፍላጎት መልሶ ማስተጋባት ከአደራ በይነት ምንም አይተናነስም። መራራውን ነገር ደፍሮ ኃላፊነት ወስዶ መጀመር ትርፍ ብቻ ይገኘዋል ተብሎ ሊታሰብም – አይገባውም። ከሙሉ ኪሳራ ጥቂት ኪሳራን መምረጥ – ብልህነት ነው። እርግጥ የዲሞክራሲ መንፈስ መለማመዱ የማይከፋ ቢሆንም፤ እራስን እንደ ድልህ እዬደቆሱ፤ በራስ ላይ አመድ ነስንሶ እራስን ወደ ቡላማ መለወጥ የተገባ – አይመስለኝም። የተሻለውን ለማግኘት በተሻለ አቀራረብ እራስን ሳይሰነጥቁ ወይንም ሳይፈልጡ ወይንም ሳይነጠቁ የዴሚክራሲን መንገድ መለማመድ – ይቻላል። ለነገሩ እኛ እኮ ውጪ ስላለን ባርነቱ ቀርቷልን መሰሎን ሊሆን ይችላል። ግን እኛም ባሮች – ጭቁኖች ነን። እንደ ፈለግን መኖር ያልተፈቀደልን፤ የተዋረድን ወጥ ሰንደቅዓላማ፤ ወጥ ብሄራዊ መዝሙር የሌለን። ሁሉን – የተቀማን። በማናቸውም ሁኔታ በወያኔ ሃርነት ትግራይ የዓይነ ቁራኛ ጥበቃ ሥር – የወደቅን። ስለዚህ መጀመሪያ እራሳችን ነፃ እናውጣ … ከዛ ዴሞክራሲ ከሚያስገኛቸው በረከት የተነፈግነውን ማንሳትና መጋፋት ይቻላል። ያም ሌላ የለውጥ አብዮት ነው። ለነገሩ ጊዜን ያላዳመጠ ክስተት ጊዜውን ጠብቆ አድራሻ ቢስ ሆኖ – ያከትማል። አጀንዳዎችም የፍቀት ታሪክ ባልደረባ – ይሆናሉ። አንድነት መድረክን በተቀላቀለበት ጊዜ የታዬው እሰጣ ገባ ዛሬ ደግሞ አገርሽቶ የግንቦትና የአርበኞች አሃቲነት በፈቃደ እግዚአብሄር መፍትሄ ሲያገኝ ቁርጥማት ሆነ። ውጋት ሆነ። መጋኛ ሆነ። አርበኞች ግንባር ይህን ተቀብሮ የኖረ ትብትብ ጥሶ የወሰደው እርምጃ ሁሉንም  በማዕከል ሆነን ለምንታዘብ ሰዎች ልዑቅ መሆኑን በሰማናቱ በተመዘዘበት ዘመቻና ግንባር ግብዕት ማወቅ ችለናል። ለምን በወጥ አመራር ሰከነ ነው – ጦርነቱ። „ስንተዋዋቅ …“ ይላል ጎንደሬ።

ሌላው ቀርቶ ከአዋሳኝ ቀያቸው ሁለመናቸውን ጊዜ በሰጠው የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ እዬተነቀሉ ወደ ኤርትራ የሚሄዱት እንዛ ጭቃ ለበስ ድሃ ወገንህን እንዴት ጦር ታውጅባቸዋለህ?! ያሳፍራል አቤዋ። አፈር ቅሞ፤ አፈር ለብሶ፤ ራህብ የቆላውን፤ ንዳድ ያንገበገበውን ወገንህን ለመግደል ከዛ ድረስ ከምትሄድ አቤዋ በለው እኔ ሥርጉተ ሥላሴ ሲዊዝ አለሁልህ ና እና ድፍት አድርገኝ።  የእነሱን መከራ ፈቅጄ መቀበል ጽድቅ ነው – ለእኔ። በአንዲት ቁራጭ ሰኔል 6ቱ ተደራርበው ቀን የለበሷትን አፈርማ እራፊ ለብሰው የሌሊቱን ግርማ እንደሚያስታግሱ በዬቀያቸው ተገኝቼ – አይቸዋለሁና። ያ በዝቶባቸው ነው ዛሬ ቁሙ ተቀመጡ የሚባሉት – የሚሰደዱትም። እንዴት እንዳዘንኩብህ? እንደ አንተ አዝኘበት እማውቀው የነፃነት ትግል አባወራ የለኝም። ፆም ነው ሱባኤ – አለቀስኩ። ያ ህዝብ መቼ አልፎለት አውቆ ነውና አንተ ባሩድ ለማጉረስ የተዘጋጀኽው? ጎንደሬ በጋሻውን – አንብብ። ትንሽ መንፈስና ትንፋሽ ከቅድመ አያቶቻችን – ታገኝ ዘንድ። ተንትርሰው እንዳደሩት የሽንት ጨርቅ ኩፍትርትር – ጭምትርትር ያለውን የዘመቻህን መነሻና መድረሻ ጊዜ ወስጄ አዳመጥኩት – ለካንስ ለስቃይም አንተም ሆንክ መንፈስህ ሽፍታ ነበራችሁ ማለት ነውን? መተማ አዋሳኝ ላይ የሱዳን ሰራዊት ፊት ለፊት የወያኔ ሰራዊት በስተጀርባ ወገንህን ሲበላ በግፍ ረመጥ ከቶ ህመሙ ርቆህ ይሆን? የአርማጭሆ – ዬወልቃይት – የጠገዴ – የማይጸምሪ – የአዲረመጽ – የዋልድባ ወዘተ አፈር ገፊና ቅዱሳን ተነቅሎ ተገፍቶ መሰደዱስ? የመረቀዘ ምን እንደሚታፋ – ታውቀዋለህ። አዋሳኝህ ጓንጉም ሲሞላና ሲጎድልም ታውቀዋለህ …. በቅርቡ ያለውንም ረመጥ … ህሊናህን – ጠይቀው በአክብሮት። መብራትህን – አጠፋኸው፤ ታሪክህን  – ተዳፈርከው፤ አንተን – አጣኽው … ለመሆኑ ቦሌ ዱር ገደል ከሆነ አንተ ለምን ተሰደድክ? አሁንስ ማን አገደህ? በሞቴ ሞክረውና ተያዩ እንዴት እንደሚጥም —— ከዛ ጀግንነትህ በዝናር ሙሉ ገድል ይጣፍልሃል። ለመኮለሙ እኔ እህትህ ዬት ሄጄ?! ግን – ግን የተፈረደበህን የወያኔ ሃርነት ትግራይ አነሳልህን? ይህም እኮ አለ ለካ – አዬ! የእኔ ነገር ይህን ረስቼው ….  ህግ ወደ ኋላ ሄዶ አዬ አላዬ በህግ አልቦሹ ዘመን ቅጥ የለሽ ቅድ ነው – የዘበጠ። ሹክታ – በሽክታ ካለ ብዬ ነው። 80ውንም ቦጫጭቀህ ከመቅደድህ በፊት አንተ እራስህን ከልብህ ሆነህ  በመስታውት – አስተውለው! መልክህን ደግመህ እዬው – ትእዛዝ ግን አይደለም። እኔና እኔ አብረን ስንቀመጥ ፈራጁ ህሊና ይደኘናል። አበበ በለውን እንዴት አበበ በለው ከዳው? እንዴትስ አበበ በለው ከአበበ በለው አፈነገጠ? ጎሉን ያስገባኽው የመሰለኽ በአርበኞች ግንቦት ነው። አይደለም በዕንባ ላይ ነው የጥቃት ምት እዬሰነዘርክ ያለኸው። ሃሳቤን ታገሉት ብለህናል ምን እኛ ዕንባ – ዕራቁትነት – የሰብዕዊ ፍጡር አካል ጭስ የነሰማዕቱ ጋር የሃሳብህ የተሳለ ሰይፍ – ይፋለም። እንደ ከፋኝ እንደ አማጥኩኝም ያ … ጸጥተኛውና ያሳደግኽ ቻዩ ጣና የትእግስት መንፈሱን ያቀናልህ ዘንድ ተመኘሁ። በል አቶ ወንድም ሌሎቹ ተዛማጅ የተደሞ ዕዬታዎቼ መሄድ ግድ አለኝ —

ውዶቼ  የኔዎቹ እንሆ … በአክብሮት – በትህትና – በፍቅር – በናፍቆት። ጉሹን ጓጓላውን ያፍታታል ብዬ ወደ አሰብኩት ተዛማጅ የተደሞ ዕዬታዎቼ – አብረን።

ሰላማዊ ትግል አብቅቷልን?

ሰላማዊ ትግል የዕድሜ ዘመን – የለውም። ሰላማዊ ትግል ሁልጊዜም ህያው ነው። የሰው ልጅ ከራሱ – ከመንፈሱ፤ ከራዕዩ፤ ከፍላጎቱ፤ ከገጠመኞቹ ጋር የሚያደርገው ግብግብ የሰላማዊ ትግል አካል ነው። እኔ ስጽፍ ከራሴ ጋር ቁጭ ብዬ መክሬ – ዘክሬ፤ እመሰርዘውን ሰርዤ፤ እማስተካክለውን አስተካካይ ስሜቴን ታግዬ ግን የታዳሚዎቼን ቀልብ አስልቼ ነው። የምፈልገውን ሁሉ – አልጽፈውም። ከድኜ ያስቀምጥኳቸው አምክንዮች አሉኝ። ስለምን? ወቅትን ማድመጥ የተገባ – በመሆኑ። ይህ ሳይሆን ሲቀር ደግሞ ግድ ሲል ትንሽ ገለል አድርጌ ወይንም ዘንበል አድርጌ – እጽፈዋለሁ። ስለዚህ ሥርጉተና ብዕሯ፤ መንፈሷና ርዕዮዋም በሰላማዊ ትግል ማዕድ ላይ ናቸው ማለት ነው። ኑሮና መኖር ሁልጊዜ እንደተፋለሙ ነው። ውሳኔና ጭብጥም እንዲሁ … ፍ – ት – ጊ – ያ

በሰላማዊ ትግል ህዝቦች ከባርነት ከወጡ በኋላም የዴሞክራሲ ጥያቄ ያነሳሉ። የዴሞክራሲ ጥያቄ ከተመለሰላቸው በኋላም ቢሆን ወቅት በሚፈጠርባቸው ችግሮች ዙሪያ፤ የተዛቡ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን አንስተው በተናጠል – በግል – በጋራ ድምፃቸውን – ያሰሙበታል። በማይቋረጥ ሁኔታ የሰው ልጅ መንፈሱ ካፈለቃቸውና ዘመን ከለገሰው መልካም ነገሮች ሁሉ እኩል ዕድምተኛ ይሆን ዘንድ – ታዳሚዎችን ለማነቃቃት የሚካሄድ ትዕይንት ነው ሰላማዊ ትግል። ፈተና አለው ሁለገብ ግን … ይኬድበታል። ዕውቅና እስኪያገኝ ድረስ። ዓይነት የወጣለት – ደፋርም ነው።

ስለሆነም የአንድ ሀገር ህዝብ እንደ ህዝብ እንዲሻሻል የሚፈልገውን ህግ ሆነ የአፈጻጸም መመሪያ እንዲሁም በህዝብ ድምጽ ውሳኔ እንዲያገኝ የሚሻቸውን መሰረታዊ ጉዳዮች ከመጠዬቅ ባሻገር፤ አፈፃጸማቸወን በባለቤትነት ከመከታተል ለአፍታም ቸል አይልም። ይህ ራሱ የሰላማዊ ትግል አካል ነው። አፈፃፀሙን – መከታተል። መቆጣጠር። ስለዚህ የሰላማዊ ትግል ሰዓት ማለት ነው። ሰዓት አያቆምም ሁልጊዜ – ይጓዛል። አይደክምም ሁልጊዜ – ይሄዳል። ተቆጣጠሪያችንም ነው። ሰላማዊ ትግልም ወቅት – ጠቀም፤ ህዝበ – ጠቀም፤ ዘመን – ጠቀም የምልዕት የተሳትፎ ማዕድ ሲሆን፤ የሰው ልጆች ፍላጎት ማለቂያ የሌለው በመሆኑ ልክ እንደ ሰዓት ደንበር ወይንም መከተሪያ ሥነ – አምክንዮ የለውም።። እንኳንስ በእኛ በጥቂቶች የብሄረሰብ የጭፍን አገዛዝ ወደ ምዕላቱ ፍላጎት ለመሸጋገር፤ ከባርነት ነፃ የመውጣት የመጀመሪያ የትግል ረድፍ ላይ የምንገኝ – ቀርቶ፤ የአደጉ ሐገሮችም፤ ዴሞክራሲን ተግባር ላይ ዘውድ ደፈተንለታል በሚሉት ሀገሮች ላይም በማያቋርጥ ሁኔታ የብዙኃኑ ጥያቄ ጎልቶና ጎልምሶ በህዝብ ትዕይንት – ይገለጽበታል። ትውናውም በሰላማዊ ትግል – ይፈረጃል። ሰላማዊ ሆኖ ግን ጉልበትና ብስጩነትንም ሊያስተናግድ ይችላል። ገዘፍ ያሉ ቁጣዎችን አንግቦ ቀለል ያሉ የቁስ ጥፋቶችን ሊያሰከትል – ይችላል። ከበድ ያለም ህይወትን ሊገብር – ይችላል፤

ሰላማዊ ትግል ሂደቱ እጅግ አስቸጋሪ የሚያደርገው ጉዳይ በሙት መሬት ላይ ትግሉን ስለሚያካሂድ ነው። ስለዚህም ዬዘርፈ ብዙ ጥቃቶች ሰለባ የመሆን ዕድሉም የሚመነጨው ሙት መሬት ላይ ሆኖ፤ ገዢ መሬት ላይ ያለውን ሃይል ስለሚታገል ነው። አብሶ እንደ እኛ በዘር በተቋጠረ ቂም – ተከል አስተዳደር ላይ የሚካሄደው ትግል እጅግ – አሰቃቂ፤ ሰቅጣጭ ሲሆን ኑሮው ሆነ ህይወቱ በመከራ – በመራር ሃዘን የተለወሰ – ጎምዛዛ።

ሰላማዊ ትግል ውስጥ የማይነኩ – የማይዳሰሱ –  የሚተዉ – ቀነ ቀጠሮ የሚያዝላቸው ዬህዝብ ፍላጎቶች አይኖሩም፤ ወይንም የሚዘነጉ ምንም ዓይነት የብዙኃን ጥያቄዎች፤ ወይንም ሙቅ ስሜቶች፤ ወይንም ጽኑ እምነቶች – አይኖሩም። ይህ በመሆኑ ጥያቄውን የሚፈራው ሥልጣን ላይ ያለው ሃይል ማናቸውንም እርግጫ፤ ማናቸውንም ኢ – ሰብዕዊ ጭፍጨፋ – ይፈጽምበታል። የታላቁ ፍጡር ዬሰው ልጅ ደም የመጀመሪያው በረከት ነው – መቋደሻ። አብሶ እንደ እኛ ባልሰለጠነ ቅድመ ሰው እድገት ደረጃ ላይ በሚገኝ ጫካዊ አስተዳደር በምትመራ ሀገር ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄድ ትግል ዕለታዊው ስንቁ ነው – ደም መፍሰስ። አሳዛኙና እጅግ መራሩ ጉዳይ ደግሞ ከደብደባው፤ በስለት ከመወጋቱ፤ ከመሞቱ በላይ ተበዳዩ ተወቃሽ – ተነቀሽ ከመሆን አልፎ ሥሙ በግፍ – መገረፉ ነው። ሊቢያ ላይ የታረዱ ወገኖቻችን ሞተው እንኳን ዜግነታቸው፤ ሰማዕትነታቸው ከወያኔ ሃርነት ማንፌስቶ ሥር ወድቆ ነበር የለመነው። መራር ነው። በማግሥቱም ባዕለ ሲመት ድምቅ ብሎ ተክብሯል። ሃሞት። ይህም ብቻ አይደለም ሀዘኑን የተጋራው ሁሉ ዜግነቱን በግፍ የተቀማበት የከሰለ ሂደት እያዬን ነው። ምግለት። ሃዘንን አምቆ ቢይዙት በሽታ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ውስጥን አሳርሮ – ያረግፋል። ወጥቶ ሲጋፈጡት ደግሞ ማገዶነት አይቀሬ ነው። የሆነ ሆኖ የሰላማዊ ትግል ከትንሹ ጥያቄ እስከ ግዙፉ የፖለቲካ ሥልጣን ጥያቄ ድረስ በሚያደርገው ጉዞ ሙት መሬት ላይ፤ በቅርበት ለችግሮች ስለሚገኝ አብዝቶ የመከራ፤ የፍዳ የስቃይ ህይወትን – ፈቅዶና ወዶ ይገፋበታል። ጥያቄው መልስ እስካላገኘ ድረስ ሰላማዊ ትግሉ – ይቀጥላል። በደሉ እስካለ ድረስ ሰላማዊ ትግሉ – ይቀጥላል። ህይወት እስከለ ድረስ፤ ኑሮ እስካለ ድረስ – እንዲሁ። ምርጫ ላይ ሰላማዊ ትግሉ ያቀደው አልተሳከም ተብሎ የሰላማዊ ትግሉ አባላት እጃቸውን አጣጥፈው – አይቀመጡም።

ነገ ሌላ አዲስ ቀን ነው። ማግሥት ሌላ ልዩ የተስፋ ቀን ነው። ስለዚህ የሰላም ታጋይ አርበኞች የቀደመውን መከራ አስተናግደው ለሌላ መከራ ደግሞ ትጥቃቸውን ጠበቅ አድርገው – ይሰናዳሉ። ለሌላ መስዋዕትነት – ይሰለፋሉ፤ ለሌላ ስቃይ – ይባትላሉ፤ ለሌላ አሳር – ይተጋሉ። ስለሆነም እነሱ የሰላማዊ ትግልን ሁለገብ መርህ ተከትለው ደከመን፣ ሰለቸን፣ መረረን፣ በቃን እሳካላሉ ድረስ እኛ ትግሉ አብቅቷል፤ የማለት ሞራሉም – አቅሙም የለንም። መከራን እንደ ስንቃቸው የተቀበሉት እነሱ እያሉ፤ እኛ የለም አቁሙ በማለት ለሰላማዊ ትግሉ የስንበት ወረቀት የመስጠት መብቱም ሞራሉም አይኖረንም። ይህ የጓጎለ ጉማዊ ፍላጎት ነው – ለእኔ። ሰላማዊ ትግል እንደ ዳቦ የሚያልቅ – አይደለም። የሰላማዊ ትግል ሩኹ የማያቋርጥ፣ ተከታታይነት፤ ተያያዥነትና ተወራራሽነት ያለው ሲሆን፤ በሁሉም ዘርፍ ሁለንትናዊ ፍላጎትን አማክሎ መጠነ ሰፊ ህዝብን በማስተባበርና በማደራጀት ለራዕዩ መትጋት ግድ – ይለዋል። ሰላማዊ ትግል ሁሉዬ – የሁሉዬም ነውና።

ዬምርጫ 2007 አለመሳካት፤ ወይንም እሱን ተከትሎ የደረሱ በደሎችና ግፎች የበለጠ ጥንካሬና እልህ ፈጥረው ለዘላቂ ነፃነት ስንቅና ትጥቅ በመሆን እውነትን ለትግሉ ለግሶ – ይገሰግሳል። በሂደቱ የሚሾልክ ሊኖር – ይችላል። ነገር ግን ቀጣይ ህይወቱን ጽኑ እምነት በመንፈሳቸው የሰነቁ ትጉኃን ትግሉን በመምራት ግብር ከፍለው፤ አስራት ሆነው ኢትዮጵያን ከትግራይ ወያኔ ሃርነት ባርነት የማላቀቁ ትግል ማቆሚያ ገደብ፤ መካተሪያ አውታር ሊበጅለት አይገባም ብለው፤ እንደሚቀጥሉት ተስፋዬ ብሩኽ ነው። በስልት – በብልሃት – በስልጡን መንገድ – ይቀጥሉታል። እርግጥ አጣብቂኞች በርከትም ከረርም – ሊሉ ይችላሉ። ነገር ግን በዝምታም አመጽ – ይኖራል። ባለመተባበር አመጽ ሊኖር – ይችላል። ፊት በመንሳት ማመጽ – ይቻላል። ፍቅርን በመንፈግ እንቢተኝነት ሊኖር – ይችላል። ልብንና መንፈስን በማሸፈት በቃኝን ኮትኩቶ ማሳደግ – ይቻላል። ቤተ እግዚብሄር ውስጥ በተመሳሳይ ደቂቃና ሰከንድ በደወል ማናወጽም፤ አላህ አክብርን በመሰሉ መከወንን ሊያካትት ይችላል። ሙቀቱ ግርፊያውን ቀጥሎ ከባህር የወጣው አሳው የጎሳ ድርጅት ወያኔ ሃርነት ትግራይ ትንፋሽም ነፍስም ያጣና ስምጠትን ሊጠመቅ ይችላል።

በሌላ በኩል ውጪ ሀገር የሚካሄዱ ሰላማዊ ሰልፎች፣ የሚሰበሰቡ ፊርማዎች፤ የሚላኩ ደብዳቤዎች፤ የሚዘጋጁ ውይይቶች፤ የሚደረጉ ቃለ ምልልሶች፤ ፊልሞች፤ ዶክመንተሪ – ዘገባዎች፤ ማህበራዊ ሚዲያዎች፤ ድህረ ገፆች ራዲዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፤ ሁሉ በሰላማዊ ትግል የሚታቀፉ ናቸው። አቁሙ ለማለት የማይስችሉ ጭብጦችም የሚነሱት ከነዚህ የፈለቁ የዕውነት ድባቦች አባልተኛ ስለሚሆኑበትም ጭምር – ይሆናል። ሌላ ጊዜ እርእስ አስይዤ ብመጣበትም ዛሬ ትውፊታችን፣ ሃብታችን፣ የእኛነታችን ሃምሌት የነበረው የሞራል ህግ ተሸርሽሮ – ተሸርሽሮ ድብዛው እዬጠፋ ነው። ሰላማዊ ትግል በነዚህ ሁሉ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ የሆነ ኃላፊነት – አለበት። በተለይ የሰፊውን ህዝብ ኑሮውን – እዬኖሩ፤ መከራውን ሁሉ በቅንነት እያስተናገዱ የሚገኙት ሀገር ቤት የሚገኙት የሰላማዊ ትግል አርበኞቻችን አትኩረተ – አቅጣጫ ከበፊቱ በተሻለና በሰለጠነ ሁኔታ ዬትውልዱን መንፈስ በብሄራዊ ስሜት፤ በትውፊታዊ ቃናዊ ማዕዶት ላይ ያተኮሩ ህሊናዊ ተግባራት የመከወን ጉዳይ የሰላማዊ ትግል ልዩ ኃላፊነት ነውና በመርህ ደረጃ ሊያተኩሩበት ይገባል ባይም ነኝ። የወያኔ ሃርነት ትግራይ ያልዘረፈን አንዳችም ነገር የለም፤ አሁን በእንቁላል ውሃ የተገነባው የመተማመን፤ የጽናት በኽረ፣ ሥህን ናሙና የነበረው የአብሮ አደግነት የልጅነት ልዩ ፍቅር፤ ልዩ ጣዕም ያለው፤ ከቅዱስ ጋብቻ ያላነሰ የውል – የኪዳን ማርዳ ነበር። እሱን እንኳን አለስተረፈልንም፤ መሰሉን መልካም ገላጭ መለዮዋችነን ሁሉ – ተዘርፈናል። እንዲቆጠቁጠን – ከፈቀድንለት። አሳት ነው – ረመጥ፤ አውሎ ነው  – የሚለጋ። …. ጎርበጥባጣ፤

የሆነ ሆኖ አዘውትሬ እንደምገልጸው 90 ሚሊዮን ህዝብ ልሸፍት ቢል አይችልም፤ ልሰደድ ቢልም እንዲሁ፤ ስለዚህ ሰፊውና ጨዋው የኢትዮጵያ ህዝብ መኖር ለመጀመር ኑሮውን ከነጠቀው ጋር የሚያደርገው ዕለታዊ ግብግብ ቀጣይ – ይሆናል። ኦክስጅኑ ነው። መተንፈሻው ተዘግቶ መኖር አይችልምና። የታመቀ ስቃዩን – የሆዱን ለቅሶ – መተንፈሻ ቧንቧው – ሰላማዊ ትግል ነው። „አልተመቸህኝም“ ማለት ሲችል ይታገስለታል – ቃጠሎው። „በቅተህናል፤ አዬንልህ የበደል ድውለትህን፤ የቋሳ ብርንዶህን፤ የቁርሾ ክትፎህን“ ሲል ነዲዱ – ረብ ይልለታል። ትግሉን ማድረጉ ሆነ በውስጡ መኖር በራሱ ህሊና ለላው ዜጋ ጤና – ይለግሳል። የሰላማዊ ትግል የኩሬ ውሃ አይደለም። ስለዚህ በተሰራው የመንፈስ ሃብት ልክ ደጋፊ እዬገኘ ሲሄድ ቤቱን ገንብቶ ቤት አልባ፤ መጠለያ አልባ፤ ጥግ አልባ፤ ባለቤት አልባ በመሆን ለማንኛውም አደጋ እዳሪ ላይ የተጣሉትን ነፍሳት፤ ዜጎቹን ባለመጠለያ – ያደርጋቸዋል። ይህ አይቀሬ ነው። ሲከር ይበጠሳል ሲሞላም – ይፈሳል።

ሽምቅ ውጊያና – መራራ ስክነቱ?

ሽምቅ ውጊያን ለዓለም ያሰተማረች ሀገር ኢትዮጵያ ናት። የጎሬው ኢትዮ አፍሪካዊው የጥቁር አንበሳ ታሪክ ነፃነታችን በማስገኘት ሂደት የታሪክ ባለቤት ነው። ዛሬ ግን ያነን እንተግብር ቢባል የሚቻል – አይሆንም። ዘመንን ወቅትን ያለጤነ አቤቱታ-  ይምጣል። አብዝቶ የሚደመጠው ጉዳይ በትጥቅ ትግል የተሰማሩ ሃይሎች በሽምቅ ውግያ እርምጃ መውሰድ አለባቸው የሚለው ሲሆን፤ ለእኔ ሌላው የጓጎለው ጉም ነው። ሥልጣን ያለውን የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ ከሥሩ ለመንቀል በሽምቅ ውጊያ የሚሞከር – አይደለም። ቀደም ብዬ እንደገለጽኩትም ዘመኑም – አይፈቅድለትም። ስለምን? በዘመኑ የሽምቅ ውጊያ ከሚያሰገኘው ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ አመዛኝ ስለሆነ። በሽምቅ ውጊያ ሰላማዊ ሰዎች በብዛት መስዋዕትነት እንዲከፍሉበት – ይገደዳሉ። ከተማ ውስጥ ያለው ኑሮ ጭፍቅፍቅ ባለ ሁኔታ የሰፈረ ነው – ህዝባችን። አንድ ቦታ እሳት ሲነድ በጥቂት ሰከንዶች ብዙ ንብረቶች፤ ብዙ ሰርቶ አደሮች ኑሯቸው አመድ የሚሆነውም በዚህው ምክንያት ነው። አድራሻ ቢስ ጉዳቶችም ህልቆ ናቸው። ሥርአተ – አልበኝነትም ብዙ አቅሞችን እንደ አሳማ ይውጣል። አብሶ ህጻናት፣ ነፍሰጡር ሴቶችና አዛውንታት ቀዳሚ – ተጠቂዎች ናቸው። ምክንያቱም ሽምቅ ውጊያው ድንገተኛ ስለሚሆን እናት ገብያ እንደ ሄደች፤ ልጆቿ ውጪ ሲጫወቱ እንደ ነበሩ፤ ወይ ትምህርት ቤት ላይ እንዳሉ የጥይት እራት ሊሆኑ ይችላሉ። ወይንም አንዲት ሴት ምጥ እንደተያዘች፤ ልክ እንደ መሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ማለት ነው ዬሽምቅ ውጊያ፤ እናትም እንደወጣች ልትቀር ትችላለች። ይህን እንደ አንድ ሰብዕዊ ፍጡር ለሚያዬው፣ ነፍሱ ከእሱ ጋር ላለች ፍጡር -ዘግናኝ ነው። በፓኪስታን ተዘውትሮ የሚታዬው አሰቃቂ ጉዳይም ይሄው ነው። አንድ ሰው እንደ ሰው ሊያስብ ይገባዋል። ይህ በችሮታ ሳይሆን ጸጋው ነው። መተርጎም – ከቻለ። የከፋውን የጎጥ አስተዳደር በደልን ለመቋቋም የሚመጥን ልዕቅና፣ ብልህነትና ሥልጣኔ ይጠይቃል። በስተቀር ትርፉ ድርብ ዕንባ ነው።

ከዚህም በላይ የህዝብ መገልገያ አገልግሎት መስጫ ድርጅቶች ሁሉ በድንገተኛው ጥቃት ከጥቅም ውጪ – ይሆናሉ። እኛ ደሃ ነን።አብሶ ወያኔ ሃርነት ትግራይ በጥርሱ በያዛቸው ክልሎች ከሆነ፤ ከሥልጣን እስከሚወገድ ድረስ ባድማ መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ነው። ለምሳሌ፤ … የጤና ክሊንክ፤ ድልድይ፤ ት/ቤት ላይ ቢሆን ወያኔ ሃርነት ትግራይ ዞር ብሎ አያያቸውም። እንዲያውም ብዙሃኑን በገፍ በማሰር ሠፈሩን በሰውም በአገልግሎትም ምድረ – በዳ እንደሚያደርገው – ይታወቃል። ወያኔ ጫካ በነበረበት ጊዜ ያዬሁት በዓይኔ ይሄውን ነበር። ዛሬም የአያያዙን አድሏዊነት – አላችሁበት። የወያኔ ሃርነት ትግራይ ፖሊሲው ቂም፣ ቋሳና ቁርሾ ነው። ዛሬ ሳይወድ የተቀበላቸው ጉዳዮች አጋጣሚ አግኝተው ከፈረሱለት – እሰዬው ነው። ስለዚህ ጥያቄው የጓጎለ ጉም ነው – ለእኔ ለሥርጉተ ሥላሴ። በተጫማሪም ትግሉ በሽምቅ ውጊያ ሳይሆን ከተደራጀ ሠራዊት ጋር የሚደረግ ስለሆነ፤ የሚፈልገው የሚመክተው የመደበኛ ውጊያ ሥርዓትን ነው። ይህም ታቅዶና አቅምን ለክቶ የሚከወን እንጂ፤ በነገ – በጣባ በግንፍል ፍላጎት ሊመራ ከቶውንም – አይችልም። ከሁሉ በላይ ጦርነቱ የእርስ – በእርስ ስለሆነ ሚስጥር ማሸነፍ ነውና እነኝህ ሁሉ አመክንዮዎች ግምት ሊሰጣቸው – ይገባል። ምን ያህል የተከደን እንደሆን ደግሞ – እናውቀዋለን። ከዚህም ባለፈ ዝርዝር የውጊያ ስልት ሪፖርት ካልቀረበ ብለን አካኪ ዘራፍ የምንል፤ ሳይኖረን እንዳለን – ደለቃቆችም አለን። ማሸነፍ – ሚስጢር ነው። ጥሬ ሃብቱ ደግሞ የሰው ልጅ ህይወት። ሰው! …. በቅፅበት ታልሞ ሰውን መፍጠር አይቻልም። የሰው ሥዕል ለመሳል እንኳን ጸጋን – ይጠይቃል።

አቅሙን የትጥቅ ትግሉን አላሳዬም ሌላው የኩነኔ ማሳ ነው፤

ጉድ በል ነው —- ባልተቋረጠ ሁኔታ የሚሰማው ጉዳይ የትጥቅ ትግሉ አንዲት ከተማ ይዞ በ24 ዓመት አላሰዬንም የሚል ነው። ይህ ገፊ ኃይል ከሦሰት አቅጣጫ ነው የሚከሰተው።  በቅንነት፤ ሌላው የትጥቅ ትግሉን በሚደግፉት ላይ ጫና ጥርጣሬና ተስፋ እንዲቆርጡ ለመሰንጠቅ ታስቦ የሚከወን ሲሆን፤ ሦስተኛው ግን ባልታቀዱ ሁኔታዎች ውድመትና ስቃይ የሚናፍቃቸው – ጠመዝማዞች – ልዞች አሉ። ሲፈጠሩ አዎንታዊነት የራቃቸው የአሉታ – ፍቅረኞች። ከሽንፈቱ ወይንም ከክሽፈቱ በኋላ ደግሞ የሰላ ገጀሟቸውን ይዘው ለመከትከት – ስለሚመቻቸው። እኛ እኮ ቃለ ምልልስን ለማድመጥ እንኳን አቅም – የለንም። እዬተሳቀቁ ነው እምናዬው። ትእግስቱ – ሸሽቶናል። እንኳንስ በድንገት በተነሳ ጊዜያዊ ወረራ፤ እልልታው ሳይሰክን መጠነ ሰፊ ዬዕንባ መራጨት ትዕይንት ሆኖ፤ በባዶ ሜዳ እንኳን ዘርፍ፣ ቅጥል፣ እንጥልጥል፣ እዬተፈጠረ – አሳር። ይህም ለእኔ የጓጎለ ጉም ተከል ነው።

አቅምን ለማሳዬት ብቁ አቅምን መገንባት – ይጠይቃል። አቅም ደግሞ ያለው – ከእኛው ነው። እኛ አቅም ልንሆን ቀርቶ አቅም መሰባሰብ ሲጀመር በፈረቃ በወበራ ወይንም በደቦ ስናጭድ ውለን – እናድራለን። በጥርሳችን የያዝነው አንድ ሥም ስንሞትም  ዬአጥንታችን ማህተም ሳይሆን የሚቀር አይመስለኝም፤ እኛ የምንፈልገው አቅም የሚመራትን ኢትዮጵያን ነው። በሌላ በኩል እሞታለሁ፣ መከራውን ሁሉ እቀበላለሁ የሚል ዜጋ ማግኘት ተራራ ላይ የሚገኝ ስንደዶ የሚመስለንም-  አለን። ወይንም አስፓልት ላይ የሚታፈስ – ጠጠር። ወይንም ሞድ ሱቅ ላይ አጭር – ረጅም – ቀይ – ነጭ – ጉርድ – ሙሉ ተብሎ ተመርጦ ለውጊያ ዝግጁ የሆነ የሰው ልጅ መሸመት። ዕብንነት! ተኝቶ መሄድ ታውቃላችሁን? እንደዛ —–

በሌላ በኩል ለሞት ለተዘጋጀው ደምና ስጋችን ስንል እንኳን ቆራጣ አክብሮት – በኗል፤ የመቻቻል ድህነት አብዝቶ – ይንጠናል። አንድ ነፍስ ለደቂቃ ትንፋሹን የሚሰበስብት ድንኳን ማግኘት የሰማይ ገነት ነበር። ግን መተላለፍ – ነው። ወቀሳም – አለበት። ውሃ ቅዳ እውሃ መልስ። ለማንኛውም የተደራጀ፤ የታጠቀ፤ የነቃ፤ ዓላማውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ተዋጊ ኃይል ለመፍጠር ጊዜ አብዝቶ – ይጠይቃል። የኢኮኖሚ አቅም – ይሻል፤ ህሊናን የማዘጋጀት ተቋም – ይጠይቃል። ከአንጎል ጋር ቁጭ ብሎ መወያዬትን – ይጠይቃል። ተባባሪ ሀገሮችን ለማግኘት መጣርን፣ በተከታታይ ያለመታከት መሥራትን – ይሻል። ሁልአቀፍ ድጋፍን – ይጠይቃል፤ ምክንያቱም የውጪዎቹ እነሱ በሚዲያቸው ካጣጣሉት በኋላ መልሶ የመገንባት ሂደቱ ቁልቁለት – አይደለምና። በሌላ በኩልም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሁኔታ የዓለም እንቅስቃሴዎች በስውር ስለሚከታተሉት ከእነሱ ቁጥጥር ውጭ ለመድረግ አለመቻል ሌላው የሳይንስና የቴክኖሎጂ ምጥቅ – አመክንዮ ነው። ትግሉ በግሎባል ደረጃ የማህበራዊ የኢኮኖሚ፣ ዬፖለቲካዊ ህይወትን ዕውቅና በቅንነት – ይፈልጋል። የሎጅስቲክስ ሁለገብ ድርጁነትን – ይሻል። የውጪ ሚዲያን አትኩሮትም – ይመኛል። የትጥቅ ትግል እኔ እንደማስበው ከባንቧ እውሃ የሚቀዳ አድርገን እንመለከተዋለን። እንኳንስ በህቡ ለተደራጀ፤ በመንግሥት ደረጃ ላለም ቢሆን የሰፊ መሰናዶ፤ ዬስልታዊ ሳይንስ ውጤት ወይንም ቀመር ነው – ውጊያ። ማሰብ – ይጠይቃል። ሂሳብ። የሰው ልጅ ጭድ አይደለም። ሰው ከመማገዱ በፊት በበቂ ሁኔታ በጥናትና በበቂ አቅም ተክህኖ ነው መጀመር – ያለበት። የትጥቅ ትግል እንጡሩብ የሚዘሉ ስሜቶች – አይገዙትም። ወይንም ከላይ ከላይ የሚፈላ – ግብዝነት።

አንድ ከተማ ቢይዝ ምን ያስፈልገዋል?

  1. ከተማው ውስጥ ያሉ ማናቸውም ማህበራዊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ አግልግሎቶችን በነበረው መልክ የማስቀጠል፤ ለደሞዝተኛው ደሞዙን፤ ለባለ ጡረታው – ጡረታውን፤ ለታማመው ህክምና፤ ለተጓዡ መጓጓዣውን፤ ለተማሪው ትምህርቱን ወዘተ …. በስተቀር አንድ ቀን ደሞዝ ቢያልፍ እራሱ ህዝቡ ተዋግቶ – ነፃ አውጪውን – ያስወጣዋል። መኖር አለበታ! እህል – እህል የሚሉ ልጆች ወይንም በሽተኛ ልጅ ወዘተ ይኖርበታል … ሸቅጦ መቅጦ አዳሪውም እንዲሁ … አሁንስ መቼ ተሟላለት ልትሉኝ ትችላላችሁ፤ የተሻለ ጠብቆ ያለውን ካጣ ዕዳው ከፍ ያለ ነው ዬሚሆነው። የ200 ዓመት ግዛት ምኞት ውሳኔው የወያኔ ብቻ ሳይሆን ህዝቡ በፊርማ የሚፈቅደው – ይሆናል። ባልተሟላ ዝግጅት አንድ ትንሽ ከተማ ቢያዝ – ትልቁ ቀርቶ ማለቴ ነው፤ እንዲሁም በቀጣይነት አጎራባች አካባቢዎችን ዬማስለቀቅ ሂደት መኖርም ግድ – ይላል። አካባቢው በጣም ነው የሚታወከው። ስለዚህ አዋሳኞችን እዬጨመረ መሄድ – ወሳኝ ቋት ነው – ለተስፋ። „ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው“ ይላል የሀገሬ ሰው። የሃይልና የአቅም፤ እንዲሁም የሥነ ልቦና የበላይነት ለውጊያ መሰረታዊ ጉዳይ – ስለሆነ በመደመር ላይ ማባዛት ትንፋሹ ሊሆን ይገባል። ለአዲሶችም የተሟላ አግልግሎትን ማስቀጠል ይኖርበታል። በስተቀር የሚከዳው ወዘተረፈ ይሆናል። ይናዳልም።
  2. ከተጠቂው ኃይል ጋር በሚደረግ ግብግብ የሚሰነዘርበትን የማናቸውንም ዓይነት የመልሶ ዬማጥቃት እርምጃን የመመከት ወይንም መልሶ የማደራጀት እርግጠኛ የሚያደርግ ተጨማሪ አቅም ማሟላትን አጥብቆ – ያስፈልገዋል። ቢያንስ የያዘውን ላለመልቀቅ። ኃላፊነቱ እጅግ ግዙፍ ነው። በልመና ገንዘብ ሲሆን ደግሞ የቁጥር ተማሪዎች ከሆናችሁ ስሌቱን እስኪዱት።
  3. ለቀጣዩ የማጥቃት ሂደት በሰው ሃይል፣ በማተርያል፣ በሎጅስቲክስ ሙሉ አቅም ላይ ሆኖ መገኘት – ይኖርበታል።
  4. ተጠባባቂ አቅም በሙሉ ዝግጁነት የማደራጀት ኃላፊነት – ይኖርበታል፤
  5. የደህንነቱ ጉዳይ በራሱ ፈተና ነው። እርስ በእርስ ነዋ – ፍልሚያው። ማን – የማን? ማን – ለማን? ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቅ። የማጣሪያው ወንፊት እራሱ ከአቅሙ በላይ የሚሆኑ ግብግቦች አሉበት – የነፃነት ትግላችን።
  6. በሂደቱ የሚገጥሙ ማናቸውንም ደራሽ ችግሮችን በአግባቡ ለማስተናገድ አብዝቶ መሰናዳት ይኖርበታል።
  7. በዲፕሎሎማሲ በኩል ትግሉን ሊረዱ ሊደግፉ የሚችሉ በርከት ያሉ ሀገሮች የሚኖራቸው አሉታዊ ዕይታ ወዘተ ታስቦና ታቅዶ በስልት መከወን ካልተቻለ ገብቶ ለመውጣት ከሆነ እግርም ጫማ ውስጥ ገብቶ ይወጣል። ወይንም ሰውነት ወንዝ ውስጥ ገብቶ ይወጣል። ምን ለማለት ነው የሚከፈለው መስዋዕትነትና የሚገኘው ድል ተመጣጣኝ መሆን መቻል አለበት። ስንዴ ወፍጮ ውስጥ እንደሚጨመረው – አይደለም። ሰው ነው ለውጊያ – የሚዘጋጀው። ድሉንም ለመስቀጠል በጣም እርግጠኛ የሚያድርግ በቂ አቅም መኖሩን ማረጋገጥ በጣም – እጅግ በጣም – ይስፈልጋል። ይህ ሳይሆን በውሽልሽል ወይንም በሞቅታ ፈረስ ጥቂቶችን ለማስደስት ተብሎ መጀመር አይደለም፤ ሙከራ ቢደረግ ከትርፉ ኪሳራው – ያመዝናል። ከዛ በኋላ እንዲያውም አገግሞ የመነሳት አቅሙ ሙት መሬት ላይ – ይወድቃል //// ቀጣዩ ዬድል ህልምም እሩቅ – እጅግ እሩቅ ይሆናል። አንጋጦ ዬማዬት ዕጣ ብቻ ይሆናል – የሚጠበቅው። እንስከን። ከወጣቶች በላይ ጎልማሶች በወጣት ፍላጎት እዬተናጥን – እንገኛለን። ጦርነት በጉርና ተገፍቶ እንደሚወጣው ወገሚትና ቅቤ – አይደለም።

ሳይሳካ ቢቀር ተከታዩ ምን ይሆናል? ወይንም ወደ ኋላ ሠራዊቱ ቢያሸገሽግ ….

  1. እጅግ ከአሁኑ በስፋትም በመጠንም የከፋ ተስፋ ቆራጭነት – ያይላል፤
  2. የሥነ ልቦና ውድቀት በከፍተኛ ደረጃ – ይከሰታል። ምክንያቱም የምንጠብቀው ፍላጎታችነን አስተልቀን ስለሚሆን፤
  3. የዕምነት መጓጎል አብዝቶ ትግሉን – ይፈታተነዋል።
  4. የሃይል መበተን በከፋ ሁኔታ ሊገጥም – ይችላል፤
  5. ዕምነት የማጣትና ኃላፊነትን የመሸሽ አደጋ ሊከሰት – ይችላል፤
  6. ዬሰው ህይወት ጥፋት – በትርፍ አልባነት – ይወራረዳል፣ ጡረታ የመክፈል አቅሙም – የለንም። ሌላው ቀርቶ ጀግናችን ለማለት እንኳን …. ?
  7. ዬንብረት ብክነት በዕሴተ – ቢስነት ይሰክናል፣
  8. ዬህዝቡን ትኩስ ስሜት መልሶ እንደገና ለማግኘት ዳገት ይሆናል፣
  9. እንደገና ለመልሶ ለመቋቋም ሌላ ተጨማሪ ዓመታትን – ይጠይቃል፣ ለዛውም ከተሳካ —- አደጋው እጅግ እጅግ የከፋ ነው የሚሆነው፤ ምክንያቱ እኔ እንደማዬው ፍላጎታችን ሆነ ወቀሳችን ከአቅማች ሲነሳ አይቼ አላውቅምና። ፍላጎታችን በጣም የናጠጠ ዲታ ነው። አቅማችን ደግሞ – ስስ።
  10. በህዝብ ያለው ተቀባይነትና ፍቅር – ይደብዝዛል፤ ለዛውም ወፍ ካወጣው ነው፤ በስተቀር ጨርሶ – ሊተን ይችላል።
  11. የበቀል ጥቃቱ በተጨቋኝ ህዝብ ላይ በእጥፍ ድርብርብርብ ይጨምራል፤ ታዳጊ ወጣቶች – ይደፈራሉ፤ አዛውንታት – ይደበደባሉ፤ ቤተ አምልኮዖች – ይጠቀጠቃሉ፤ ባለትዳሮች ጥቃት – ይፈጽባቸዋል፤ ቁምጥ ያለነው እኛ ደግሞ ተጀምሮ ቢታይ ደጋፊ ይኖራል አውሎው ይሰክናል ወዘተ ወዘተ … ምንትስ ቅብጥርስ የምንለው ነገር „ከበሮ በሰው እጅ ሲይዙሽ“ ዓይነት ነው። የጦርነት ጉዳይ …. ነጠላ ገጥሞ መስፋት አይደለም።

የዲፕሎማሲ ሥራ ቀጣይነት አስፈላጊነት፤

በዲፕሎማሲ ትግል ቀጣይነትም የጓጎሉ ጉማዊ ዕይታዎች – አያለሁ። ምን ሲያደርግ? ምንስ ሲያተርፍ? የሚሉ ዕድምታዎች ይደመጣሉ። ዲፕሎማሲ አንዲት ሀገር ከሌላው ጋር ያላት ግንኙነት ወሳኝ ጉዳይ ነው። ህዋስም ነው። ትእግስትን አብዝቶ ይሻል። የዲፕሎማሲ ሥራ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገም ወሳኝ ጉዳይ ነው። ስለሆነም በተከታታይነት መቀጠል ያለበት አምክንዮ መሆን አለበት። የዲፕሎማሲ ትግል አብዛኛው እጅ በሰላማዊ ትግል ማዕቀፍ ቢካተትም ለትጥቅ ትግሉም ቢሆን ወሳኝነት ያለው ክስተት ነው። በነገራችን ላይ ለእኛ እንደ ሃጢያት፤ እንደ ወንጀል ይታይ እንጂ ትናንት ሻብያና ወያኔ ያለፉበት ህይወት ነው። ዛሬም ቢሆን እኛ ብቻ አይደለነም ለነፃነት ትግል የትጥቅ ትግልን እንደ አማራጭ – ያዬነው፤ እንደ ህንድ በርከት ያሉ ሀገሮችም እያካሄዱት – ይገኛሉ። ስለዚህ ለሁለቱም ስልት ደጋፊ ሀገሮችን ወይንም ግለሰቦችን ወይንም ተቋማትን ማግኘት ለነፃነት ትግል መሰረታዊ ጉዳይ ነው። ስለዚህም ዘርፉን በታታሪነትና በቀጣይነት መከታታል በእጅጉ – ያስፈልጋል።

ይህም ማለት ከቀደመው በተሻለ፤ በጠነከረ ሁኔታ የዲፕሎማሲ ተግባርን ተግቶ ሥራ ላይ ማዋል – ያስፈልጋል። የዲፕሎማሲያዊ ትግል በተቆራረጠ መልኩ ከሆነ፤ ወይንም በትናንሽ የትርፍ ቅንጥብጣቢዎች ከተዘናጋ ውጤቱ የዚያን ያህል የከሳ ነው የሚሆነው። ነገር ግን ተከታታይነት ያለው፤ ሥልጡን፤ በታቀደ ተግባር በተደራጀ ሁኔታ ከተከወነ ከሁለቱ የትግል መስመሮች ባልተናነሰ በገዢው ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ እጅግ ጉልህ ነው። አጋርም ብረት መዝጊያ የሚሆን – ያስገኛል። በሌላ በኩል ተቀናቃኙ የጎጥ ድርጅት የወያኔ ሃርነት ትግራይ በፖሊሲ፤ በፋይናንስ፤ በመዋቅር፤ በዘመቻ የሚከውነውን የፕሮፖጋንዳ ተግባር ለማፍረስ ተሽሎና ቀድሞ መገኘትን ይጠይቃል። ይህም ብቻ በቂ ላይሆን ይችላል፤ ግንኙነቶችን በሙሉ በፋክት ላይ የተመሰረቱ፤ እውነትን ያቀፉ ነገ ሊገኙ የሚችሉ ሃቆችን የተንተራሱ መረጃዎችን ለሚመለከታቸው አካላት መላኩ ሌላው የተስፋ ፍሬ አስገኝ ሃይልም ነው።

© internal character scope or reader (© የውስጣዊ ሥነ ባህሪ አጉሊ መነጸር ወይንም አንባቢ)

ቃሉን እራሴ ነው የፈጠርኩት። ይህን ሳይንቲስቶች ቢሰሩት መልካም በሆነ – በነበረ። ግን እስካሁን ድረስ አልሠሩትም። ይህ መሆኑ እዬታወቀ በአንድ ፓርቲ ወይንም ድርጅት ወይንም ንቅናቄ ወይንም ተቋም የሚፈጠሩ ጥቃቶችን ቀድሞ ማዬት ነበረበት የሚል ዕድምታ አለ። እንዴት ይለያል ከሰርገኛው ጤፍ ነጭኑ ለይቶ – ማውጣት። መልካችን አንድ፤ ደማችን አንድ፤ ዘራችን አንድ ነው። ቤቴ ብሎ ለሚገባ፣ ለመደራጀት የወደደውን ማናቸውም ተቋማት የአብርሃም ቤት ማለት ይኖርባቸዋል። ከመግባቱ በፊት ለእኛ ሲባል የተሠራልን የውስጥ ሥነ ባህሪ አጉሊ መነጸር ወይንም አንባቢ መሳሪያ internal character scope or reader እንዳለ ሁሉ ጠቅልለን፤ አንገዋለን ቀድሞውንም ማጣራት ነበረባቸው፤ ከመሃከላቸው የወያኔ ሃርነት ትግራይ ወኪሎች ስላሉ እንዲህ ሆነ —- እንደዛ ሆነ እንላለን። ወይንም ችግርን አቅደን እንዲህ ሊሆን ይችላል —- እንዲያ ሊመጣ ይችላል እንላለን። በዕውነቱ ይህ ምናብ ነገር ነው – ለእኔ። እያመሰን ያለውም ጉዳይ ይሄው – ይመስለኛል። የመሬት መንቀጥቀጥ ወይንም አውሎ ቢነሳም የሚለካከከው እሚጨፈጨፈውም አንድ ንቅናቄ ብቻ ላይ ነው።

አንድነት ለፍትህና ለነፃነት ከመጨረሻው ጫፍ ደርሶ እንዲህ ሥሩ ተነቅሎ ሲፈርስ መነሻውም መደረሻውም ትግሉ የእርስ በእርስ ስለመሆኑ ከአምክንዮ ውጪ እንሆናል። ስለምን ማገዶዎቹ የአንድነት መሪዎች ተለይተው፤ ተለቅመው ጉድጓድ ውስጥ ተጨመሩ? ለምን? ይህን የሚመልስ ህሊና ለሌላውም ጥያቄ መልስ ሊኖረው – ይገባል። እንዳለ ድርጅቱን በሃጢያተኛነት ከመመደብ በፊት። ፍርዳችን፣ ዳኝነታችን፣ ወቀሳችን እራሱ ከወያኔ ሃርነት ትግራይ ባልተሻለ ሁኔታ በተመሳሳይ ወርድና ቁመና – የተጋደመ ነው። ምን የተጋደመ ብቻ የተኛም ነው – ለሽ ብሎ። ምክንያታዊ ጉዳዮችን እኩል በሰው ህሊና ለመርመር ቢያንስ ለራስ ህሊና ለመፈቅድ አለመቻል። መነሻቸውን ሆነ መድረሻቸውን ማዕከላዊ ሰቁ ላይ ቁመን ሙቀቱን እንለካው። አሉታዊውን – 1, – 2, – 3፣ ወዘተ ወይንም አዎንታዊውን + 1, +2, +3  ወዘተ … ደመ መራራው ድርጅት የትናንቱ ግንቦት 7 የዛሬው አርበኞች ግንቦት ከአካላቱ መንፈስና ህሊና ገና ያልተፈለሰፈ ሳይሆን ፈጽሞም ያልተሰበ መሳሪያ መግጠም ነበረበትን?

ከቶ ዛሬ ነፃ ነኝ የሚል የነፃነት ትግሉ ግንባር ቀደም ታጋይ ካለ እራሱን እረስቷል ነው የምለው። በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን ሁሉ ተጫማሪ ዬድርብ ሰው ጥላ አለ። ግን አናስተውለውም። እምንታገለው የራሳችን አካል ብቻ ነው፤ ቁሞ የምናዬውን። ነገር እዬለቀምን አቤቶ ስህተት እባክህን ናልን ብለን ተማጽነን ወጮፈዎን ወደ አንድ አቀጣጫ ብቻ – እንልከዋለን። በፓሊሲ ደረጃ ዕቅድ ተዘጋጅቶለት ለኢንባሲዎች የተበተነ ትዕዛዝ ነበር። በ6 ዓመት ቆይታው መሬት የያዘ ተግባር በጠላት የፈረጅነው የጎጥ ድርጅት ማንፌስቶ ዬወያኔ ሃርነት ትግራይ ገቢራዊ – አድርጎታል። በገፍ ወደ ውጪ ከሁሉም ብሄረሰቦች – አስገብቷል። በህጋዊ – ፓስ። ፍጹም ስውር በሆነ ሁኔታ የእዝ ሰንሰለት አለ። አይደለም የሃበሻ – ተሃበሻ ግንኙነት ከዚህ ባለፈም የሄዱ – መረቦችም። አንድ ጹሁፍ ላይ አቶ ኤርምያስ ለገሰ ስለምርጫ 2007 ከማህደር ራዲዮ ጋር የነበራቸውን ቆይታ ያሰከኑት ከቆጮ ላይ ነበር። የሪስቶራንቱ ስም ሳይቀር ነበር የጻፉት። ለወያኔ ሃርነት ትግራይ የስለላ ተግባር ወጪውን በመቶ – ይቀንስለታል። ሳነበው እራሱ – ተንዘፈዘፍኩኝ። በቃ እንዲህ ምንም እንደሌለበት ሰው ነው እምትዝናኑት ማለት ነው?! ገረማችሁኝ።

መኪናንም ሞቅ አድርጎ አስነስቶ መሄድ ብቻ ነውን? በኪሱ ምን እንዳለ አትፈትሹትም ማለት ነው?  የገብያ ቦታዎቻችሁ የተለመዱ ናቸውን? በቃ! ኑልኝ ካለው ሁሉ ድግስ ቤት ትገኛላችሁን?! ፊት ለፊት ወጥታችሁ እዬታገላችሁ የሃበሻ ቤቱንም በልክ ለማድረግ አቅም አነሳችሁን?!  በጋብቻ – በአብልጅነት – በጓደኛ ወዘተ ያሉነን ግንኙነቶች በቃ እንደወረደ መቀላቀል ነውን? …. ጦርነቱ የእርስበርስ በመሆኑ አብዝቶ ጥንቃቄ – ያስፈልገዋል። ቢያንስ ለራስ ዘብ መቆም። ዝለናል ወይንም ተደግሞብናል። መንገድ ላይ እያለን ስልክ ቢደወልም ፈጥነን እናነሳ ይሆናልን?! በኋላችን መኪና እዬተከተለ አጣብቂኝ ቦታ ላይ ስንደርስ እራሱ ደወሉ ካነሳንለት – ድንገተኛ አደጋ ውስጥ እንድንገባ ሊታቀድ እንደሚችል ከቶ አይታያችሁምን?! ደም ከልብነትን አስታውሳችሁ አታውቁንም?! ተከታታያችሁ አቶ ‚ሀ‘ እሱ ደስ ብሎት አልፎን ይሄዳል። መሳሪያ አልያዘ፤ ግን በሥልጡን ሥልቱ በልጦ ድሉን ተጎንጭቶ በሰላም እፎይ ብሎ ቤቱን ይገባል። እሰቡ – በትንሽ። እህት ነኛና አብዝቼ ስለናንተ አስባለሁ።

እውነት ለመናገር የውስጥ ሥነ ባህሪ አጉሊ መነጸር ወይንም አንባቢ internal character scope or reader መሳሪያ በሌለበት ሁኔታ በግራ ቀኙ ተጠቂዎች እኛው ነን። ስለዚህ ለኑሯችንም ደንበር ይኑረው ነው ፍሬ ነገሩ። የሆኖ ሆኖ በታሠሩ ወገኖቻችን ሳቢያም ሁኔታ እዬተፈለገ እያሰገረ በሚነሳ አለሎ ትደቁሱታላችሁ እንደ – አደስ መከረኛውን። የትም ቦታ የወያኔ ሃርነት ትግራይን ደጋፊዎች አሉ ከቤታችን ጀምሮ …. ማንገዋለያ መሳሪያ ደግሞ ዬለም። ስለዚህ ከሳሽም – ተከሳሽም ሊኖር አይገባም። ከጥንቃቄ ትርፍ እንጂ ኪሳራ ስሌለ በዬትም ሁኔታ ጠንቃቃ መሆን፤ ደወሎችን ማድመጥ፤ ምቾዎቶችን መቀነስ በእጅጉ ያስፈልጋል። ይቅርብኝ ብሎ መቁረጥና – መወሰን። በራስ ላይ መዕቀብ መጣል። የተቋማት ሁሉ ችግሩም ይሄው ነው። የነፃነት ትግል ማለት ከሁሉም ፍላጎቶች ጋር በስድ ሳይሆን በተዕቅቦ መኖር ማለት ነው። የነፃነት ትግል ኑሮ በልቅነት – አይታሰብም። ሥርዓት አለው።እራስን መቅጣት፤ ተፈጥሯዊ ስሜትን መግታት። ወጣትነትን አሳልፎ ፈቅዶ መስጠት፤ እናትነትን ሆነ አባትነትን በፈቃድ ማጣት፤ ተፈጥሯዊ ደስታዎችን መክዳት፤ በዳንኪራዎች ላይ መሸፈት … ወዘተ … የነፃነት ትግል ለእኔ የሱባኤ ጊዜ ነው።

ከውና – ነፃነት የፒክኒክ (picnic) ውሎ አይደለም። ወይንም – ቡፌ። መስዋዕትነትን ሰንቆ መከራን የፈቀዱትን ብቻ በአባልነት የሚቀበል ስለሆነ ቅንጦተኞች፤ ወይንም ቀለጤዎች ወይንም ዘመናዮች ክፍሉ አይደሉም። ነፃነት የራበው – ራህቡን የሚያስታግስበት ብትን መቆሚያ አፈር፤ ወስፋቱን የሚያሳርፍበት ቁራሽ እንጀራ፤ ጉሮሮውን የሚያረጥብበት ጭልፋ ጠብታ – ኤዶሙ ነው ለእሱ። ከፈኑን የሚሸፈንበት – ብጣቂ እራፊ …. እና ቀበቶ እና መቀነት —– ሌላውን ድለቃ ለምቾተኞች ለድሎተኞች

(no risk no fun) ይላሉ ፈረንጆቹ። ተደፍረው የሚገባባቸው በሮች ሁልጊዜ ላይሳኩ ይችላሉ ወይንም ሊሳኩ፤ ወይንም ተቆርጠው የሚቀሩ ህልሞችም ሊገጥሙ ይችላሉ፤ ተቆርጠው በሚገባባቸው መጠራቅቆች ተስፋን አምጦ ለመውለድ ምጥና ዳጥም ናቸው፤ ኮሶን – እንቆቆን፤ አሳንጋላን ደፍሮ ወስዶ ከኮሶ ትል መገላገል …. በስተቀር በህዝብ አደባባይ እዬሾለከ እዬወጣ ከእግሩ ሥር ይለጠፋል …. ትሉ። ውርዴት ጠጥቶ መኖር ? ? ?

የእኔ ጌጦቼ ለነበርን ሸበላ – መሸቢያ ሰሞናትን በፍቅር ተመኘሁ።

ሃሙስ ራዲዮ ፕሮግራም አለኝ በ2.07.2015 አዬር ላይ ከ15 እስከ 16 ወይንም በማግሥቱ አርኬቡ ላይም – ታገኙኛላችሁ።

Tsegaye Radio or www.tsegaye.ethio.info. Aktuelle Sendung

አንቺ እናት ሀገሬ ኢትዮጵያ ሰንድቅዓላማሽን ለብሼ አንችን የማይበት ቀን በእጅጉ – ናፈቀኝ! እባክሽን እማ ለወጉ – አድርሽኝ።

ለእኔስ ሰው መሆኔ ብቻ ይበቃኛል።

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

The post የጓጐሉ – ጉሞች – ከሥርጉተ ሥላሴ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>