ዛሬ፣ የኢትዮጵያን ህልውና የሚፈታተኑ፣/ መኖሯን የማይሹ፣/ ከቻሉም የየራሳቸውን የጎጥ መንግስታት ለማቋቋም የሚፈልጉ ኃይሎች አጋጣሚው እስከሚፈጠርላቸው እየጠበቁ ነው።
ዛሬ ኢህአዴግ በሚከተለው ፖሊሲ ኢትዮጵያ ለክፋ አደጋ እየተጋለጠች ነው።
ዛሬ፣ በዘር የተደራጁ ኃይሎች አመቺ አጋጣሚ እየጠበቁ ናቸው።
ዛሬ እነ አይሲስና መሰል ኃይሎች ምን እንዳዘጋጁልን አናውቅም። አርፈው እንደማይተኙ ግን የተረጋገጠ ነው። እናም/ ኢትዮጵያዊው ባለቅኔና ደራሲ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ በኢጣሊያን ወረራ ዘመን የቋጯትን ስንኝ ጠቅሼ፣/ ያለፈውን መሰረት ያደረገ፣/ የዛሬውን የሚመለከተውንና ስለነገው የሚጠቁመውን ንግግሬን እጀምራለሁ።
አገሬ ተባብራ ካልረገጠች እርካብ፣
ነገራችን ሁሉ የእንቧይ ካብ፣/ የእንቧይ ካብ፣ ብለዋል።
- ከ40 አመት በፊት የተጀመረው የለወጥ እንቅስቃሴ ዛሬም ዕልባት አላገኘም። በዚያ ዘመን የተነሱ ጥያቄዎች ገሚሱ መልካቸውን ቀይረው እንደገና ቀርበዋል። ታሪክ ፖለቲካ፣ ፖለቲካም ታሪክ የሆነበት ወቅት ላይ ደርሰናል። በተለይ አፄ ምንሊክ፣ የተፋላሚ ሀይሎች አጀንዳ የሆኑበት ወቅት ነው።
- የአፄ ምንሊክ አስተዳደርና አገዛዝ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ የወሰዱት እርምጃ ስለሆነ አበጀህ ሊባሉ ይገባል ይላል የመጀመሪያው ወገን። የዚህ ተጻራሪው ክፍል፣ ነፃ የነበሩ መንግስታትን በመጨፍለቅ ሸዌው አፄ ምንሊክ ‘ቅኝ ግዛታቸውን’ አስፋፉ፣ እሳቸው በነገሱበት ዘመን የቅኝ ገዢዎች አፍሪቃን የሚቀራመቱበት ጊዜ በመሆኑ፣ የቅርጫው ተካፋይ ለመሆን በቁ ይላል።
- ከዚህ በተጨማሪ፣ የአፄ ምንሊክንም ሆነ በዙሪያቸው የነበሩ ረዳቶቻቸውን የዘር ግንድ በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል። ልክ ሊሆኑም ላይሆኑም ይቻላሉ። ዋናው ቁም ነገር ግን፣ እነዚህ የታሪክ ሰዎች ያጠፏቸውም ይሁን ያለሟቸው ስራዎች ከዘር ግንዳቸው ጋር የተያያዙ አልነበሩም። ራስ ጎበና ዳጬ የኦሮሞ/አማራ፣ ፍትአውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ቢነግዴ የጉራጌ/የኦሮሞ፣ ወይም የአማራን የበላይነት ለማንገስ አልተሰለፉም። አጼ ምንሊክም ሆኑ ረዳቶቻቸው የኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ የታሪክ ውጤት እንደመሆናቸው እነሱ ሳይሆኑ ኢትዮጵያን የፈጠሯት፣ ኢትዮጵያ እነሱን አስቀድማ ፈጥራቸዋለች፣ ኢትዮጵያዊ ማንነትን ተላብሰዋል። ስለሆነም፣ የዚያን ዘመኑን ሁኔታ የሚመረምሩበት፣ የሚመለከቱበትና የሚለኩበት መነጽር በዘር ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በኢትዮጵያዊነታቸው ላይ የተመረኮዘ ነበር ማለት አግባብ አለው።
- አፄ ምንሊክም ሆኑ ረዳቶቻቸው ኢትዮጵያዊነታቸው የተረጋገጠው በ19ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያን ብለው አድዋ በዘመቱበት ጊዜ ነበር። ኢትዮጵያዊነት እነ አፄ ምንሊክን ይቀድማል ሲባል አንድም አድዋን በማስታወስ ነው። የአንድ አገር ህዝብ አንድነትም ሆነ የጋራነት በውል ሊገለጽ የሚችለው በተለይ ሀገርን በሚመለከተ ከሚነሳ ጦርነት ጋር ነውና።
- በእርግጥ፣ አፄ ምንሊክ ሥልጣን በያዙ ማግስት ነበር ህልማቸውን ለማሳካት፣ ግዛታቸውንም ሆነ መንግስታቸውን ማስፋፋት የጀመሩት። በካሄዷቸው ዘመቻዎች፣ አንዳንዶቹን በወድ አንዳንዶቹን በግድ አስገብረው በቁጥጥራቸው ስር አድርገዋል።
- የያ ትውልድ ቀዳሚ መሪዎች ወደ ፖለቲካ መድረኩ ብቅ ባሉበት ወቅት፣ በአፄ ምንሊክም ሆነ ከእሳቸው በፊት የተፈጸሙ ታሪካዊ ኩነቶች አእምሮአቸውን በመፈተናቸው ደግ ደጉን ወርሰው ክፉውን ማስወገድ እንዳለባቸው አመኑ። ጠባሳዎቹ ይሽሩ ዘንድ የትውልድ ግዴታና ሃላፊነት ተረከቡ። መፍትሄ መሻትም ጀመሩ።
- የያ ትውልድ አባላት፣ የሕዝቦች የእኩልነት መብት መከበርና የኢትዮጵያ ህልውና እና ኢትዮጵያ እንደ አገር ፀንታ መቆየት የማይነጣጠሉ መሆናቸውን በመረዳት አምርረው ታገሉ። ወታደራዊ መንግስት ጥያቄውን በነፍጥ ለመፍታት በማሰቡ፣ ያ ትውልድ ያቀረበውን አማራጭ፣ ትጥቅ አስፈቺና መርዘኛ ነው ብሎ አመነ። ከዚያም፣ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ሂዶ ቀይ ሽብር ተወለደ። በአንፃሩ ደግሞ፣ የያ ትውልድ አካሄድ ያልተመቻቸው ብሄረተኛ ኃይሎች፣ የየራሳቸውን መንግስት ለማቋቋም በሚያደርጉት ጥረት፣ እንቅፋት ነው ብለው የቆጠሩት ሕብረ ብሄራዊ መርሃ ግብርንና ያስተናግዱ የነበሩትን የያ ትውልድ አባላት እንደጠላት ቆጠሩ። ሕብረ ብሄራዊ ኃይሉ ህ/ሰባዊ መሰረታቸውን እንዳይንድ በመስጋት ከወታደራዊ መንግስቱ ባላነሰ በጠላትነት ፈረጁት። “…ሶስት ገጽታ በነበረው የትግል ሂደት ውስጥም፣ ሕብረ ብሄራዊ ኃይሎች በወታደራዊው አገዛዝ ጨካኝ የእመቃ ዘመቻና በብሄርተኛ ኃይሎች አፈና…አጣብቂኝ ውስጥ ገቡ።…ወታደራዊው አገዛዝና ብሄረተኛ ኃይሎች…ሀገሪቱ እንዳትበታተን ድጋፍ ሊሰጥ የሚችለውን አንድ ኃይል ኢትዮጵያ እንድታጣ አደረጉ።” (ያ ትውልድ፣ ቅጽ 3፣ ገጽ 431) የያ ትውልድ አባላትም በምዕራብ ሶማሌ ድርጅት፣ በወያኔ ሃርነት ትግራይና በሻዕቢያ እጅ ወደቁ።
- ሕብረ ብሄራዊው ኃይል ሲዳከም፣ መድረኩ ለወታደራዊው መንግስትና ለብሄረተኛ ኃይሎች ተለቀቀ። ጉልበትና መሳሪያ የነበረው የበላይነት እየያዘ ሄደ።
- በዚህ ወቅት፣ ትግሉ መልኩን ቀይሮ፣ ኢትዮጵያ የቀዝቃዛው ጦርነት አካል ሆና አሜሪካና የቀድሞዋ የሶቭየት ሕብረት ጡንቻቸውን የሚፈትሹባት አውድማ ሆነች። በሶስት የሚፈረጅ አዲስ የኃይል አሰላለፍም ገሀድ ሆነ፤ በዚህ አሰላለፍ መሰረት፤ 1/ ሶቭየት ህብረትና አጋር አገሮች እንዲሁም ደርግ በአንድ ወገን፣ 2/ የምዕራቡ ዓለምና የቀድሞ የገዢ መደብ አባላት እንዲሁም ብሄረተኛ ሃይሎች በሌላ፣ 3/ በነፃነት ይንቀሳቀሱ የነበሩና ከማንም ያልወገኑ ሶስተኛ ሆነው ተሰለፉ። በዚህ በሶስተኛው ስብስብ ስር በአጠቃላይ የያ ትውልድ አባላት ይገኛሉ።
- እንደ ኢህአፓ ከሁለቱም ኃይሎች ሳይወግኑ በነፃነት ትግላቸውን ለማካሄድ የወጠኑ ኃይሎች ‘ድንጋይ ተሸክሞ የአቀበት ጉዞ’ ሆነባቸው።
- የምዕራቡ ኃይል መጀመሪያ ላይ የቀድሞ የገዢ መደብ አባላትን ደገፈ። እነዚህ ኃይሎች የሰንበሌጥ ምርኩዝ ሲሆኑበት፣ በመጎልበት ላይ ወደነበሩት ብሄረተኛ ድርጅቶች ፊቱን አዙሮ፣ ከሱማሌ መንግስት ጎን በመሰለፍ ኢትዮጵያን በሚቻለው ሁሉ ጎዳ። ይህ እርምጃም፣ የምዕራቡ ኃይል የብሄረተኛ ሃይሎችን አጀንዳ ደግፎ መውጣቱንና ኢትዮጵያዊነት አደጋ ላይ መውደቁን የሚጠቁም ሲሆን፣ በአንፃሩ ደግሞ የሶቭየት ህብረትና አጋሮቹ፣ ኢትዮጵያን በመሳሪያ ሃይል አንድ ለማድረግ ቆርጦ ለተነሳው ደርግ ሙሉ ድጋፍ ሰጡ። ሁለቱም ያለ የሌለ መሳሪያ አራገፉ። ገንዘብ በገፍ ረጩ።
- የምዕራቡ እርዳታን በተመለከተ የህወሃት መሪ ከነበሩት አንዱ አቶ ገብሩ አስራት በቅርቡ ባወጣው መጽሀፍ፣ “…ምዕራባዊያን በተለይ ከ1977 ዓም ጀምሮ ስፍር ቁጥር የሌለው እርዳታ ለህወሓትና ለሕዝቡ ለግሰዋል።…የተለያዩ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች የቁሳቁስና የገንዘብ እርዳታ የሚሰጡ ድርጅቶችና መንግሥታት ቁጥራቸው እየጨመረ ሄዶ ነበር” ሲል ያብራራል። (ገብሩ አስራት፣ ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ፣ ገጽ 145)
- የሶቭየት ስትራቴጂ አንድ ወጥ ሲሆን፣ የደርግ ጠላት ጠላታችን ነው ብለው በመቁጠር በሙሉ ኃይላቸው ከጎኑ ተሰለፉ። በአንጻሩ፣ የአሜሪካ መንግስት አካሄድ መንታ ስትራቴጂ ላይ የተመሰረተ ነበር። በአንድ በኩል፣ በታዛዦቹ በሱዳን፣ ሳዓውዲ አረብያና በሌሎች መንግስታት አማካይነት የደርግ መንግስትን ለመገልበጥ ተቃዋሚዎችን ረዳ። በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ጦር ምስጥ እንደበላው እንጨት ከውስጥ በራሱ እንዲገነደስ ለማድረግ ብዙ ጣረ። የ1981 ዓም መፈንቅለ መንግስትን ልብ ይሏል!
- የምዕራቡ ኃይል የበላይነት እየያዘ ሄደ። በ1983 ዓም ለሁለተኛ ጊዜ ማዕከላዊ መንግስቱ ተዳከመ። ሁለቱ ጉልበተኛ ብሄረተኛ ኃይሎች፣ ህወሃትና ሻዕቢያ፣ መንግስት መሰረቱ። ኢትዮጵያም ተከፈለች፤ ወደብ አልባም ሆነች። ኢህአዴግ ሥልጣን በያዘ ማግስት በርካታ ብሄረተኛ ድርጅቶች ተፈለፈሉ። ብሄረተኝነት የመንግስቱ ርዕዮትና ፖለቲካ ሆነ።
እኛና እነሱ – ልዩነቶቻችንና አንድነታችን | |
እኛ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነት አልን። | እነሱ በልዩነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ አራመዱ። |
እኛ የኢትዮጵያን አንድነት ሰበክን። | እነሱ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ልዩነት ሰበኩ። |
እኛ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ከሚያለየያቸው የሚያመሳላቸው ይበልጣል አልን። | እነሱ ከሚያመሳስላቸው የሚያለያያቸው ይበልጣል አሉ። |
እኛ ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚያመሳስለውና አንድ የሚያደርገው የመደብ ትግል ነው አልን። | እነሱ ሁሉም ብሄረሰቦች ለየራሳቸው ዘብ መቆም አለባቸው አሉ። |
እኛ በሥርዓት ላይ ያተኮረ ትግል አደረግን። | እነሱ በአማራው ላይ ያተኮረ ስብከት አካሄዱ። |
እኛ ፊውዳሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም ዒላማዎች ናቸው አለን። | እነሱ አማራውን ዒላማ አደረጉ። |
እኛ ለኢትዮጵያ ታገልን። | እነሱ በየብሄረሰባቸው ላይ አተኮሩ። |
እኛ ኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ ባለታሪክ ናት አልን። | እነሱ የመቶ አመት ታሪክ ነው ያላት አሉ። |
እኛ ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ናት መፍትሄውም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ቢጋር ክልል ሊታይ ይችላል አልን። | እነሱ ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ናት አሉ። |
እኛ የኦሮሞም ሆነ የተቀሩት ሕዝቦች የእኩልነት መብት የሚከበርበት ሥርዓት መዘርጋት አለበት አልን። | እነሱ ኦሮምያ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ነው አሉ። |
እኛ የኢትዮጵያ ታሪክ ከአክሱምና ከዚያ በፊት የዘለቀ ነው አለን። | እነሱ አክሱም ሌላውን አይመለከትም ለወላይታው ምኑ ነው አሉ። |
ሁለቱ ሃይማኖቶቻችን፣ ፊደላችን፣ የኢትዮጵያ ኦፊሴላዊ ቋንቋ የሆነው አማርኛ፣ ሸማን የመሳሰሉ ባህላዊ አለባበሶቻችን፣ የተቀየጠው ኢትዮጵያዊ ገጽታችን፣ ጤፍን የመሰለው በየትኛውም አገር የማይበላው ምግባችን፣ የኢትዮጵያ መንፈሳዊም ሆነ ዘመናዊ ያሬድያዊ ሙዚቃችንና የመሳሰሉት መሰረታቸው አክሱም ነው። የኢትዮጵያ ማንነት ተለይቶ ማህተም የተደረገበት ከአክሱም ጊዜ ጀምሮ ነው እልን። | እነሱ ኢትዮጵያ አፄ ምንሊክ በጉልበት ጠፍጥፈው የፈጠሯት አገር ናት አሉ። |
እኛ የኢትዮጵያ ታሪክም ሆነ የዓለም ታሪክ በዲሞክራሲ አልተገነባም። አማራው ከትግራዩ፣ ኦሮሞው ከሲዳማው፣ ኦሮሞው ከአማራው፣ ክርስቲያኑ ከሞስሊሙ፣ ወዘተ ሲስማማ፣ ሲዋጋ፣ መልሶም ሲስማማ፣ ሲገዛ፣ ሲገዛ፣ ሲወር፣ ሲወረር፣ ሲያጠፋ፣ ሲጠፋ የዘለቀ ታሪክ ነው እንላለን። | እነሱ ታሪካችን በአፄ ምንሊክ ጭፍጨፋ ይጀምራሉ ይላሉ። |
እኛ ኢትዮጵያን በብሄረሰብ ሳንለያይ፣ አርሶ አደሮችና ላብአደሮች ይቀድማሉ አልን። | እነሱ የተመረጠ ብሄረሰብ ይቅደም ይላሉ። |
እኛ ፍትሃዊ የሀብት ሽግሽግ ይደረግ አልን። | እነሱ ሀብት በተመረጡ ብሄርተኛ ልሂቃን እጅ እንዲገባ እያደረጉ ናቸው። |
እኛ ኢትዮጵያ አፄ ምንሊክን ፈጠረች አልን። | እነሱ አፄ ምንሊክ ኢትዮጵያን ፈጠሩ ይላሉ። |
እኛ አፄ ምንሊክ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ሥርዓተ-ታሪክ ተከትለው የገበረውን በሰላም አሻፈረኝ ያለውን በጉልበት ገዙ አልን። | እነሱ፣ በተለይ ክፉው ታሪክ በአፄ ምንሊክ ዘመን ተጀመረ አሉ። |
እኛ አፄ ምንሊክ የክፉ ታሪካችን ተቋዳሽ ቢሆኑም፣ የአድዋ ባለቤትና የነፃነት ቀንዲላችን ናቸው አልን። | እነሱ አፄ ምንሊክ ከፊል ግዛታቸውን ለቅኝ ገዢዎች አሳልፈው የሰጡ የቅኝ ገዢዎች አጋር ናቸው ይላሉ። |
- ባለፉት 25 አመታት፣ ባለሀብቶች ትላልቅና ዘመናዊ ሕንፃዎች ገንብተዋል። በርካታ መንገዶችም ተዘርግተዋል። የትምህርት ይዞታው እጅግ ቢዳከምም፣ በርካታ ትምህርት ቤቶች ተከፍተዋል። ብዙ የጤና ጣቢያዎች ተቋቁመው፣ በወሊድና በመሳሰለው ሊመጣ የሚችለው በሽታ በመጠኑ ሊቀረፍ ችሏል። የቤት ችግርን በመጠኑም ቢሆን ለማስወገድ እየተሞከረ ነው። በውጭ እርዳታና በምሁራን ትብብር ጭምር፣ በካታራክትና በሌሎች በሽታዎች ይጠቁ የነበሩ ዜጎች እርዳታ አግኝተዋል። ይሁንና፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የለውጥ ሂደት ከጀመረ 40 አመት ቢያስቆጥርም፣ አርቲስት ቴዲ አፍሮ እንዳለው፣
በ17 መርፌ፣ በጠቆመው ቁምጣ
ለለውጥ ያጎፈረው፣ ዙፋን ላይ ሲወጣ፣
እንደአምናው ባለቀን ሌላውን ከተካ፣
አዲስ ንጉስ እንጅ ለውጥ መቼ መጣ፤ እንላለን።
- ዛሬም፣ 87 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በኑሮ ጠርዝ ላይ (deprivation) እንደሚገኙ መልታይ ዳይሜንሽናል ፖቨርቲ ኢንዴክስ የተባለው የዓለም ባንክ ድርጅት ይገልጻል። (UNDP) የተባለ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አካል፣ ከድህነት ጠርዝ በታች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ25 ሚሊዮን በላይ እንደሆነ ያሳያል። በዩኒሴፍ መሰረት 5 ሚሊዮን እጓለ ምዑታን ይገኛሉ።
- ዛሬ፣ የዕቃዎች ዋጋ አይቀመስም፡፡ ሠራተኞች ከወር ወር መድረስ የሚችሉት በተዓምር ነው ማለት ይቻላል። ብሩ መቅኖውን እያጣ ሄዷል። ድህነቱ እየከፋ በመሄዱ፣ ጥቂቶች ከሚገባው በላይ ሀብታም ሆነዋል፣ በሚሊዮናት የሚቆጠሩ ብዙሃኑ ደግሞ ደህይተዋል። ዛሬ ከድህነት ጠርዝ በታች በሚገኘው ዜጋና ትንሽም ብትሆን ሰርቶ በሚያድረው መሀል ያለው ልዩነት ጠቧል። ሁለቱም ወገኖች ተርበዋል። ታርዘዋል። ሁለቱም መናጢ ደሀ ሆነዋል። ድህነት ክፉ ነው። ያጨካክናል።
- በእርግጥ ጥቂቱ ደግሞ እጅግ ከብረዋል። በተለይ ነጋዴዎች። የንግድ ስርዓቱ የተዛባና ፍትሃዊ ባለመሆኑ ሁሉም ነጋዴ አይደለም የከበረው፣ ወይም የሚከብረው። ከገዢው ፓርቲ አባላትና ከመንግስት ጋር የተቆራኘው ነው በልቶ እያበላ፣ ስኳር ልሶ እያላሰና መንግስታዊ መዋቅሩን እያነቀዘ በአቋራጭ የሚከብረው።
- ሃይ ባይ በሌለበት ሁኔታ ሙስናው ሰፍቷል። ትላልቅ የመንግስትና የገዥው ፓርቲ አባላት ሳይቀሩ በሙስና በመዘፈቃቸው ወህኒ ወርደዋል።
- ዛሬ ዛሬ፣ ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች የአፍሪቃ አገሮች፣ የሩቅ ምስራቅ፣ በተለይም የቻይና የሸቀጥ ማራገፊያ ሆነዋል። አገር በቀል ኢንዱስትሪዎች በርካሽ የሚገቡ ዕቃዎች ዋጋን መወዳደር ስለማይችሉ ይከስራሉ። ጥገኝነታችንም እየሰፋና እየከፋ በመሄድ ላይ ነው።
- የቤት ኪራይም የሚቀመስ አልሆነም። አብዮታዊ ዴሞክራሲም ተባለ ዴቬሎፕመንታል ዴሞክራሲ፣ የሲዖል በሩ ብርግድ ብሎ ተከፍቶ ዜጎች እየተንደረድሩ እየገቡበት ናቸው።
- አርሶ አደሩ የመሬት ተጠቃሚ ቢደረግም፣ ዛሬ ኑሮው ከፍቷል። ከአርባ አመት በላይ የያዛት መሬት ለልጅና ለልጅ ልጅ ተሸንሽና ተመናምናለች። በማዳበሪያ ስም ዕዳ ተሸካሚ ሆኗል። በዲቬሎፕመንታል ዴሞክራሲ ስም የሚፈናቀሉት ቁጥርም በርካታ ነው።
- የእምነት መብት ሊከበር ይገባል። ስለዚህ ጉዳይ ዱሮ ተናግረናል። ይሁንና፣ የኢህአዴግ መንግስት የሁለቱ ታላላቅ ሃይማኖት ተከታዮችን አስከፍቷል። በአንፃሩ ደግሞ ከሁሉም ወገን አክራሪዎች እየተፈጠሩ ነው።
- ከጥቂት አመታት በፊት ወደ ሻሸመኔ በመጓዝ ላይ ሳለን፣ ጥቅም ላይ ያልዋሉና ሳር ያበቀለባቸው በርካታ መስጊዶች ተመለከትን። በካባቢዎቹ ብዙ ነዋሪዎች አላየንም። ቢኖሩም፣ እነዚያን የመሳሰሉ ዘመናዊ መስጊዶች ለማሰራት አቅም አላቸው ብሎ መገመት ይከብዳል።
- እነዚያ መስጊዶች ዛሬ ጥቅም ላይ ውለው እንደሁ አላውቅም። ግን በርካታ ወጣት ሙስሊሞች ዋሃቢዝም የተባለ ጽንፈኛ እምነት ተከታይ ሆነዋል። በእርግጥ እምነት እምነት ነው። ሰው የፈለገውን የማመን መብቱ ሊከበር ይገባል። ጉዳዩ አሳሳቢ የሚሆነው በእምነት ስም የሌላ ሃይማኖት ተከታዮች ላይ ጥቃት ሲደረግ ነው። ይህ ዝንባሌና አካሄድ በዓለም ዙሪያ በዝቶና ተባዝቶ ዛሬ እነ አይሲስን የመሳሰሉ ትናንት ያልነበሩ ጉልበተኞች በቅለዋል። ኢራቅ፣ ሊብያ፣ የመንና ሶሪያ እየወደሙ ናቸው። ሕዝቦቻቸውም ተፈናቅለዋል።
- ፊታችንን ወደ ኢትዮጵያ ሁኔታ መለስ ስናደርግ፣ ከ1997 ዓም ምርጫ ውጤት በኋላ፣ የኢህአዴግ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን እያጠበበ በመሄድ ላይ ሲሆን፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ነፃነታቸው ተገፏል፣ ከምርጫው በፊት አንፃራዊ ነፃነት ኖሮት ይንቀሳቀስ የነበረው ሚድያ እስከነአካቴው በመዘጋት ላይ ነው። የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ የሚደርሰው ወከባና እንግልት ቀላል አይደለም። የገጠርም ሆነ የከተማው ሕዝብ አንድ ለአምስት በሚለው አሰራር መሰረት እንዲሰናሰል ተደርጎ፣ የመንግስት ጆሮ በሁሉም ቤት ለመግባት በመሞከር ላይ ይገኛል።
- ኢህአዴግ የሚከተለው የፖለቲካ አካሄድ ምን ሊያስከትል እንደሚችል በሶስት ከፍሎ ማየት ይቻላል።
- አቅጣጫ ወይም ሲናርዮ 1 – የኢህአዴግ ‘ዲቨሎፕመንታል ዴሞክራሲ’ ሰራ ላይ ውሎ አገሪቱ በኢኮኖሚ ትበለጽግና እንደተተለመው በ2025 ሰፊ መካከለኛ መደብ ተፈጥሮ ኢኮኖሚውን ሊሸከም ይችላል። ዲቨሎፕመንታል ዴሞክራሲ የካፒታሊዝም ሌላ መጠሪያ ሲሆን፣ በመንግስት ከፍተኛ ተሳትፎ ሊፈጠር የሚችል ካፒታሊዝም ነው። በአሁኑ ሰዓት፣ ዲቬሎፕመንታል ዴሞክራሲን መሰረት አደረግሁ በሚለው የዕድገት እቅድ መሰረት፣ የሚቋቋሙት ፋብሪካዎች ገቢ ንግድ የሚተኩና የውጭ ንግድ ላይ የሚያተኩሩ ይሆናሉ። (import substitution and export oriented economy ይሉታል)
- የዲቬሎፕመንታል ካፒታሊዝም ተምሳሌ ሆነው የሚጠቀሱት እነ ኮርያ፣ ሲንጋፖርና ሌሎች “the four tigers” በመባል የሚታወቁት አገራት የደረሱበት ደረጃ ሊደርሱ ከቻሉባቸው ዋነኛ ምክንያቶች መሀል አንዱ አገራዊና ብሄራዊ ራዕይ አራማጅ መንግስታት የበላይነቱን መያዛቸው ሲሆን፣ ዘር ላይ የተመሰረተ ራዕይም ሆነ አተያይ አንግቦ፣ አንዱን አራቁቶና ሌላውን ሸልሞ እደገትም ሆነ ዴሞክራሲ አይመጣም።
- ለእድገታቸው ምክንያት የሆነው ሌላው ጉዳይ ደግሞ፣ የአሜሪካና የጃፓን በአጠቃላይም የምዕራቡ ዓለም ከቻይናና እና ከሶቭየት ሕብረት ጋር ያደርግ በነበረው ትንቅንቅ፣ በእነዚህ አገራት ውስጥ ለካፒታል ክምችት (capital accumulation) የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠሩ ነበር። የኢትዮጵያ ሁኔታን ስናይ፣ ካፒታል የአገሪቱን ሰማያት አቋርጦ መኮብለል ከጀመረ ሰንባብቷል።
- ለካፒታሊዝም ዕድገት ቁልፍ ከሆኑት ጉዳዮች መሀል አንዱ የተማረ ሰው መኖር ሲሆን፣ እጅግ ብዙ ምሁራን አገሪቱን ለቀው በመሄድ ላይ ናቸው። በአጭሩ፣ ዲቬሎፕመንታል ካፒታሊዝም ነፍስ ዘርቶ ማየት አዳጋች ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ራሷን መቻል እንኳን ሊሳናት ይችላል።
- አቅጣጫ ወይም ሲናርዮ ሁለት – ኢህአዴግ ህይወት ያለው የምርጫ ፖለቲካ እንዲካሄድ ሊያደርግ ይችላልን? በ1997 ዓም ኢህአዴግ ከገበየው ሙከራ በኋላ ያን ዓይነት ምርጫ ይደገማል ብሎ መገመት የዋህነት ነው። የዚያ ምርጫ መጨናጎል እስከዛሬ ድረስ ህዝቡን የዕዳ ከፋይ አድርጓል። ይህ ሁኔታ የተፈጠረው ደግሞ በኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን በተቃዋሚ ኃይሉም ጭምር ነው። ከ1997 ዓም በኋላ ባሉት አመታት ኢህአዴግ የሀገሪቱን የፖለቲካ አድማስ እያጠበበ በመሄድ ላይ ሲሆን፣ የፖለቲካ ምህዳሩ ሊሰፋ የሚችለው በኢህአዴግ በጎ ምኞትና ፍላጎት አይሆንም። በንግዱ፣ በፖለቲካው፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች፣ በሚድያው፣ ወዘተ የተሰማሩ ኃይሎችና የሕዝቡ የዕምቢተኝነት መንፈስ ሲጎለብት፣ ድምጻቸውን ማሰማት ሲችሉና መንግስቱን ሲያስገድዱ ብቻ ነው።
- አቅጣጫ ወይም ሲናርዮ ሶስት – ኢህአዴግ አሁን በጀመረው ሂደት ከቀጠለ ወደ ፍጹም ብሄረተኛ አምባገነናዊ አገዛዝነት ይቀየራል። በጉልበት አሰራር ላይ የተመረኮዘው ይህ አካሄድ የማያዋጣ ሲሆንና ውጥረት እየጨመረ ሲሄድ የዘርና የፖለቲካ ካርዱን በመምዘዝ ኢህአዴግ አንዱን ከሌላው ሊያናክስ ይችላል። ኢህአዴግ ወታደራዊና የፀጥታ ኃይሉን እንዲሁም አለአግባብ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ በሚያገኘው ገንዘብ በመጠቀም ህ/ሰቡን በማያላውስ ፖለቲካ ተብትቦ እንዲቆይ አድርጓል፣ ያደርጋልም። የኢህአዴግ የጉልበት ፖለቲካ ከኢኮኖሚ ችግሮች ጋር ተዳምሮ ስር የሰደደ እምቢተኝነትና አመጽ እንዲያረግዝ ያስገድዳል። ኢህአዴግ የሚከተለው ይህ ፖለቲካ መጨረሻው የኢህአዴግ መቃብርን የሚቆፍር ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያም አስከፊ ሁኔታ ሊገጥማት ይችላል። በየቦታው አመጽ ይበረታል፣ ረሃብ፣ ፍትሃ አልባነት፣ ጎሰኛነት፣ የሃይማኖት አክራሪዎች መንገስ፣ ወዘተ ሊከተል ይችላል። በሱማሌ፣ ሊብያ፣ ኢራቅ፣ የመን ላይ ያጠላው ጥቁር ደመና ወደ ኢትዮጵያ ሰማዮችም ይዘልቃል።
- የኢህአዴግ አምባገነናዊ አገዛዝን በመቃወም ከሥልጣን እንዲወርድ በትጥቅ መፈታተን ይቻላል። የትጥቅ ትግል ለማካሄድ መሟላት ስላለባቸው ዝግጅቶች መዘርዘር ቢቻልም፣ ዋነኛው ጉዳይ ግን የዛሬ 40 አመት የነበረችው ኢትዮጵያ ዛሬ አለመኖሯን መረዳት ነው። ኢህአዴግ ሥልጣን ሲይዝ የተወለዱ፣ በዘር ፖለቲካ ተከትበውና ተጠምቀው ካደጉ ዜጎች መሀል አንዳንዶቹ መተካካት በሚለው መርህ መሰረት ለሥልጣን እየበቁ ናቸው። የሕብረ ብሄራዊ ፖለቲካ አራማጅ ወገኖች ቢኖሩም፣ የኢህአዴግ ደጋፊም ሆኑ ተቃዋሚ ብሄረተኞቹ ቁጥር በቀላል የሚገመት አይደለም።
- ያም አለ ይህ ግን፣ ኢህአዴግ የሚከተለው የግፍ አገዛዝ አይቀጥልም። ውጥረቱ እያየለ ሲሄድና ማዕከላዊው መንግስት ሲዳከም ህብረ-ብሄራዊ ኃይሎች ሳይሆኑ በርካታ የጎጥ ባለነፍጠቾ ሊፈለፈሉ ይችላሉ። ማዕከላዊ መንግስት ለስሙ ቢኖርም፣ ባለነፍጦቹ ራሳቸውን የቻሉ መንግስታት ይሆናሉ። እነዚህ ቡድኖች 10ሺህና መቶ ሺህ አባል ያላቸው መሆን አይኖርባቸውም። ማዕከላዊ መንግስት ሲዳከም፣ 2000ሺህ እና 3000ሺህ ጦር ያለው የየአካባቢው ጉልበተኛና አድራጊ ፈጣሪ ይሆናል።
- ሌላ መረሳት የሌለበት ጉዳይ፣ አብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል የኢይሲስ ካርታ አንድ አካል ሆኗል። ነገ ማዕከላዊ መንግስቱ ቢዳከም፣ አይሲስም ሆነ ካባቢያዊ የአክራሪ ሃይማኖት ድርጅቶች ወይም እንቅስቃሴዎች ኢትዮጵያ ጉዳይ ውስጥ በነፍጥ ጭምር እጃቸውን ሊያስገቡ ቢችሉ ሊያስገርም አይችልም። ያ ደግሞ በፊናው ጥቃት ሊደርስብኝ ይችላል ብሎ ከሚያስብና ከሚያምን ሌላ ወገን፣ በተለይም ከክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች በኩል ተመሳሳይ ዝግጅት ሊደረግ እንደሚችል መገመት አይከብድም። ይህ ሁኔታ የሚያስገነዝበን፣ ኢትዮጵያ የማያባራ የሀይማኖት ጦርነት ውስጥ ልትዘፈቅ እንደምትችል ሲሆን፣ በእምነት ላይ የሚቀሰቀስ ግጭት መግቻ አይኖረውም።
- በአጠቃላይ፣ በአሁኑ ሁኔታ የኢትዮጵያን ችግር ባልተማከለና በተናጠል በሚካሄድ የትጥቅ ትግል ለመፍታት የሚደረገው ሙከራ፣ መፍትሄ በማምጣት ፈንታ አገሪቱ እንድትበታተን ተጨማሪና አጋዥ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ተገቢ ነው።
- ስለሆነም፣ ተቆርቋሪ የሆኑ ወገኖች አንድ ጥያቄ ሊያነሱ ይገባል፤ ከፊታችን የተደቀነው ትልቁና ሀገራዊው ግዴታ ኢህአዴግን መጣል ወይስ አገርን ማዳን የሚል ነው? (እደግመዋለሁ) በእርግጥ አብዛኛዎቹ የተቃዋሚ ሀይሎችም ሆኑ ብዙሃኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢህአዴግ መወገድ እንዳለበት፣ ቢያንስ ደግሞ የበላይነቱን መነጠቅ እንዳለበት ያምናሉ። ትክክለኛ አስተያየት ነው። ይሁንና፣ ኢህአዴግን ለመጣል በሚደረገው ርብርብ ምክንያት የማዕከላዊ መንግስት ቢዳከም አገር ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት እንዴት መቋቋም ይቻላል? አገር ላይ ጉዳት ሳይደርስ እንዴት ኢህአዴግን መታገል ይቻላል? ምን ዓይነት ስትራቴጂስ ሊንደፍ ይገባል? እነዚህ ጥይቄዎች ተገቢው ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል እላለሁ።
- በኢህአዴግም ሆነ በብሄረተኛ ሀይሎች አማካይነት እንዲስፋፋ እየተደረገ በመሄድ ላይ ያለውን የዘር ፖለቲካ መቋቋም የዜጎች ሃላፊነት አይደለምን? ዛሬ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የአማርኛ ተናገሪዎች ከቄያቸው እንዲፈናቀሉና እንዲዋረዱ እየተደረገ ነው። ከኑግ የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ ሆነና ህወሃት በሚያራምደው ፖለቲካ ምክንያት ፀረ-ትግራይ ስሜት እያደገ ሂዷል። እነዚህና የመሳሰሉ አካሄዶች በሕዝቦች መሀል ጥላቻው እየከረረ እንዲሄድ የሚያደርጉ ሲሆን፣ ከ40 አመት በፊት የብሄረሰቦች መብት ይከበር ብለን እንደተነሳነው ሁሉ በኢህአዴግ የዘር ፖለቲካ ሳቢያ ዛሬ መብታቸውን ለተነፈጉ ዜጎችና የህ/ሰብ ክፍሎች መብት መቆም አግባብነት የለውምን? ኢህአዴግ የተለያዩ የሃይማኖት ተከታዮች ላይ የሚያደርሰው ኢፍትሃዊ አሰራር ችግር እያስከተለ እንደሆነ ተግልጿል፣ ይሁንና፣ በሕዝቦች መካለል ክፍተቱ እየሰፋ ሄዶ ለአክራሪ ወገኖች የተመቻቸ ሁኔታ እንዳይፈጠር የሁሉም እምነት ተከታይ መሪዎች በጋር ሊመክሩ የሚችሉበትና ደቀ መዝሙሮቻቸው ከጥፋት ጎዳና ሊታቀቡ እንዲችሉ መፍትሄ መሻት አይኖርባቸውምን? የኢህአዴግ ሃላፊነት የጎደለው አካሄድ በተመሳሳይ ሌላ ሃላፊነት በጎደለው እርምጃ መተካት የለበትም። ተቆርቋሪ ወገኖች የሩቅ አላሚ፣ የቅርብ ርቀት አሳቢ ሊሆኑ ይገባል።
- ዛሬ በዘር የተደራጁ ኃይሎች አጋጣሚውን እየጠበቁ ናቸው። እነ አይሲስና መሰል ኃይሎች ምን እያዘጋጁልን እንደሆነ አናውቅም። አርፈው እንደማይተኙ ግን የተረጋገጠ ነው። ሌሎች የተከፉ ኃይሎችም የማዕከላዊ መንግስት መዳከሙን ሲረዱ አጋጣሚውን ሊጠቀሙ እንደሚችሉ መረዳት አይከብድም። የኢትዮጵያ ህልውና አሳሳቢና አደገኛ ሁኔታ ላይ ሊወድቅ ይችላል የሚሉ ወገኖች፣ እየተቀጣጠለ ባለው ቋያ ላይ ቤንዚን በማርከፍከፍ ፈንታ ቆም ብለው አስበው ሃላፊነት የተላበሰ ፖሊሲ መንደፍ ይኖርባቸዋል። ኢትዮጵያ ከሁሉምና ከማንም በላይ ናትና ዜጎች ሁሉ ይህን ሀገራዊ ግዴታ ልንወጣና ልንሸከም ይገባል።
- በመጨረሻም፣ አንድ ብልህ አዛውንት ከ30 አመት በፊት የተናገሩትን ልጥቀስ።
- ፊታውራሪ አየለ አባ ጓዴ ይባላሉ። የኢህአፓ አባልና ኢህአሠ ጫቆ አካባቢ እንዲንቀሳቀስ ይህ ነው ተብሎ የማይገመት አስተዋጽኦ ያበረከቱ ታላቅ ሰው። ዛሬ ፊትአውራሪ አየለ ባይኖሩም፣ የተናገሩት ሁሌም ሲታወሰኝ ይኖራል። ደርግን እናወግዛለን፣ መወገድ አለበት ብለን አምርረን ታግለን ትግላችን ተዳክሞ ሱዳን እንገኛለን። ውይይት በምናደርግበት በአንዱ አጋጣሚ፣ ‘ጎበዝ አሉ’ ፊታውራሪ አየለ ‘ይሄ ጎበዝ (መንግስቱ ኃይለ ማርያምን መሆኑ ነው) ይውረድ፣ ይውረድ እንላለን። ለመሆኑ አማራጩንና ምን ሊከተል እንደሚችል አስበንበታልን’ ሲሉ ጠየቁ። ውይይቱ ላይ ተሳታፊ የሆንነው መብረቅ እንደመታን ደርቀን ቀረን። ያዘጋጀነው ነገር አልነበረምና መልስ የሰጠ አልነበረም። ጥያቄውን ለምን እንዳቀረቡም ገብቶናል። በዚህ ወቅት በሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል ይንቀሳቀሱ የነበሩት ብሄረተኛ ኃይሎች እየጎለበቱ በመሄድ ላይ ነበሩ። ዛሬስ? ዛሬም ፊትአውራሪ አየለ እንዳሉት አማራጩንና ምን ሊከተል እንደሚችል አስበንበታል? ይህ ጥያቄ መልስ ያሻዋል። አስቡበት!
- እንደገና ንግግሬን በታላቁ ባለቅኔ በቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤ ስንኞች ልቋጭ፤
አገሬ ተባብራ ካልረገጠች እርካብ፣
ነገራችን ሁሉ የእንቧይ ካብ፣ የእንቧይ ካብ። አመሰግናለሁ!
The post ወዴት እየሄድን ነው? ለኢህአፓ ሲምፖዝየም የቀረበ (ክፍሉ ታደሰ) appeared first on Zehabesha Amharic.