አቶ ክፍሉ ታደሰ ወዴት እየሄድን ነው በሚል ርዕስ ኢህአፓ ሲፖዚየም ላይ ያቀረቡት ያለውን ጽሁፍ ዘሀበሻ አስነበበን፡፡ ጽሁፉን ማንበብ ስጀምር አቶ ክፍሉ የያ ትውልድ ወኪል ናቸውና፣ ከጉልምስና እስከ እርጅና በፖለቲካው ያሳለፉ/ያሉ ናቸውና በጽሁፋቸው መነሻና መድርሻ የጠቀሱትን የእንቧይ ካብ መሰረት ካኖሩ ሰዎችም አንዱ ናቸውና ወዘተ ትናንትን አስታውሰው የ40 አመቱ ትግል መስዋእትነት እንጂ ድል ያልታየበትን ምክንያት ይነጉሩናል፣ ዛሬን ዳስሰው ከወያኔ አገዛዝ የመላቀቂያውን መንገድ ያመላክቱናል፣ ስለነገ አልመው ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መመስረት ስለመቻያው ዘዴ ይጠቁሙናል የሚል ጉጉት ነበረኝ፡፡ ግና በዚህ መልክ አላገኘሁትም፡፡ በአንድ ነገር ግን ከአቶ ክፍሉ እስማማለሁ፡፡ ኢህአዴግን ለማሸነፍ የሚደረገውን ትግል ያክል ከዛስ በኋላ ለሚለው ዛሬውኑ መስራት እንደሚገባ፡፡
አቶ ክፍሉ ምኒልክን ለውይይት የቀረበ ጽሁፋቸው አብይ ማጠንጠኛ የማድረጋቸው ምክንያት ባይገባኝምና ከጽሁፉም መረዳት ባይቻልም ምንሊክ፣ የተፋላሚ ሀይሎች አጀንዳ የሆኑበት ወቅት ነው በማለት ምኒልክን በተመለከተ አለ ያሉትን ልዩነት ነግረውናል፡፡ ስለ ያ ትውልድ እንደ ሁልግዜአቸው ድክመት ስህተቱን ሳይነኩ አስታውሰውናል፡፡ እኛና እነሱ አንድነትና ልዩነታችን ብለው አንድነታቸውን ሳይነኩ የልዩነቶቻቸው ማሳያ ያሉዋቸውን አቅርበውልናል፡፡እንዲህ እንዲህ እያሉ ስጋት አጭረው ጥያቄ አስቀምጠው ሰባት ገጽ የሄዱበት ጽሁፍ በቅጡ ሲታይ ለማስተላለፍ የፈለጉት ወቅታዊ ጉዳይ ሶስት መስመር በማይሞላ የሰፈረው ሆኖ እናገኘዋለን ፡፡ እንዲህ ነው የሚለው፡፡
“በአጠቃላይ፣ በአሁኑ ሁኔታ የኢትዮጵያን ችግር ባልተማከለና በተናጠል በሚካሄድ የትጥቅ ትግል ለመፍታት የሚደረገው ሙከራ፣ መፍትሄ በማምጣት ፈንታ አገሪቱ እንድትበታተን ተጨማሪና አጋዥ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ተገቢ ነው። ”
ጥያቄ አንድ፤ ይህን ለማለት ይህ ወቅት ለምን ተመረጠ?
እንደለመድነው ማለባበሱን ካልመረጥነው በስተቀር በግልጽ መረዳት የሚቻለው ይህ ወቅት የተመረጠው አርበኞች ግንቦት ሰባ ውጊያ ጀመርኩ በማለቱ ነው፡፡ሁለቱም ድርጅቶች አላማና የትግል ስልታቸው በውል ይታወቃል፤ ተዋሀድን ሲሉ እየተዘጋጀን ሲሉ ወራ ተቆጥረዋል፣ታዲያ አቶ ክፍሉ የአርባ አመት ልምዳቸው የሀገራችን ችግር በትጥቅ ትግል አይፈታም የሚል ድምዳሜ ላይ እድርሶአቸው ከሆነ ለምን ያኔ ይህን ሀሳብ አላነሱም፡፡ ወይንስ አያደርጉትም ብለው ንቀዋቸው?
ጥያቄ ሁለት፣ ባልተማከለና በተናጠል ሲሉ የእነተባበርን ጥሪ አልሰሙም ማለት ነው?
ጥድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ እንዲሉ በአንድ ማእከል እየተመሩ መታገሉ ቀርቶ ተደጋግፎ መቆም እጅ ለእጅ ተያይዞ መራመድ ቢቻል መልካም ነበር፡፡ ግን ለዚህ አልታደልንም ፡፡ አሸነፈና አቸነፈ በሚል የፊደል ልዩነት ሳይቀር እስከ መገዳደል የደረሰው የእነ አቶ ክፍሉ ያ ትውልድ ያመጣው ያለመስማማት በሽታ እስከ ዛሬ መድሀኒት አልገኝለት ብሎ በግለሰብ ደረጃም ሆነ በፓርቲ መተባበሩ ቀርቶ መከባበሩ አይታይም ፡፡ የወያኔ አገዛዝ ሀያ አራት አመት የዘለቀውና መቶ በመቶ አሸነፍኩ እያለ ለመመጻደቅ የበቃውም በዚሁ ምንያት መሆኑን አሌ የሚል አይኖርም፡፡ ታዲያ ለበሽታው መድሀኒት መፈለግ ነው የሚበጀው ወይንስ እንደምንም ብለው አንድ ርምጃ ለመሄድ የሚጥሩትን ለማሰናከል መሞከር?
ብዙዎች ቃልና ተግባራቸው አልገጥም እያለ በምንቸገርበት፤ብዙዎች ያልሆኑትን ነን እያሉ በሚያጭበረብሩበት ብዙዎች ከተግባሩ ሳይኖሩ በቃላት እያደናገሩ በሚኖሩበት ወዘተ ወቅት ጥቂቶች ቃላቸውን በተግባር ማሳየት ሲጀመሩ ያልተማከለና በተናጠል የሚካሄድ ትግል በማለት ትግሉን ለማሳነስና ይበልጡንም በህብረተሰቡ ውስጥ ፍርሀት ለማንገስ መሞከር ተቢ አይሆንም፡፡ ትግሉን በተግባር የጀመሩት እነዚህ ወገኖች ትንሽ ትልቅ ሳንባባል፤ሰበብ ምክንያት ሳናበዛ ኢትዮጵያን ከወያኔ አገዛዝ ለማላቀቅ ነው የምንታገለው የምትሉ ሁሉ እንነጋገር እንተባበር በማለት ከመጠየቅ አልፈው ሲለምኑ ሰምተናል፤ምስክሮች ነን፡፡ አላማቸው ራስን ለቤተ መንግሥት ማብቃት ሳይሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ የስልጣን ባለቤትነት ማረጋገጥ የሆነ ወገኖች ተጠራርተው በውህደትም በመተባበርም አቅም ፈጥረው አንድ ርምጃ መራመድ ሲጀምሩ ፈጥኖ ወጥቶ በተናጠል የሚካሄድ ያልተማከለ ትግል በማለት የአግድሞሽ መኮነንና በህብረተሰቡ ውስጥ ስጋት ለመጫር መመኮር የመጣንበት የሴራ ፖለቲካችን በአርባ አመቱም አለማረጀቱን ነው የሚያሳየው፡፡
ጥያቄ ሶስት አቶ ክፍሉ ተቆርቋሪ የሆኑ ወገኖች አንድ ጥያቄ ሊያነሱ ይገባል፤ ከፊታችን የተደቀነው ትልቁና ሀገራዊው ግዴታ ኢህአዴግን መጣል ወይስ አገርን ማዳን የሚል ነው? ሲሉ ምን ማለታቸው ነው?
ኢህአዴገን ማሸነፍና አገርን ማዳን አንድ ላይ የሚታዩና የሚከናወኑ ሆነው ሳለ የተለያዩ ተግባራት ሆነው ሲበዛም ጥያቄ ተደርገው መቅረባቸው በተለይ ደግሞ ከተነሱበት ወቅት አንጻር ሲታዩ በውስጣችን ስር ከሰደደው የመደጋገፍ ሳይሆን የመጠላለፍ ፖለቲካ ዛሬም አለመላቀቃችንን የሚያሳይ ነው፡፡ ወያኔዎች እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ ትበታተናለች የሚሉት አይነት መልእክትም በውስጡ ይታያል፡፡ ወያኔን መጣል ሀገር የማዳን ከፊል ተግባር ነው ኢትዮጵያን የህግ የበላይነት የተረጋገጠባት፤ ሰብአዊ መብት የተከበረባት ዴሞክራሲያዊት ሀገር ማድረጉ ደግሞ ቀጣይ ተግባር ነው፡፣ስለሆነም ሁለቱ ወይስ በሚል አማራጭ ተነጣጥለው መቅረብ አይኖርባቸውም፡፡ ኢህአዴግ በሥልጣን ላይ እያለ ኢትዮጵያን ማዳን የሚቻልበት ዘዴና መንገድ አለ ካተባለ በስተቀር፡፡
ያ ትውልድ ደርግን እየተቃወመ በአንጻሩ የእኔ ብቻ ትክክል በሚል አስተሳሰብ፤ ተደጋግፎ ማለፍን ሳይሆን ጠልፎ መጣልን በተካነ የሴራ ፖለቲካ ርስ በርሱ እስከመገዳደል በደረሰ ጠላትነት እየተቀዋወመ እንዳይሆኑ ሆኖ መከራ አወረሰን፡፡
የኢህአዴግ ተቀዋሚዎችም(አርባ አመትም አራት አመትም የሚሆናቸው በውጪም በውስጥም የሚኖሩ በሰላማዊም በጠመንጃም እንታገላልን የሚሉ) ወይ ተባብረው መታገል ወይ ተከባብረው አንተም በመንገድህ እኔም በመንገዴ ብለው መታገል ተስኖአቸው ከጥሎ ማለፍ ጨዋታ መውጣት፣ ከሴራ ፖለቲካ መላቀቅ አልሆንልህ ብሎአቸው ወያኔ ተደላድሎ እንዲገዛን አበቁት፡፡አንድ ተቀዋሚ ፓርቲ ጠንክሮ ታግሎ ለስልጣን ከሚበቃ የወያኔ አገዛዝ ቢቀጥል የሚመርጡ ይመስል ቀና ብሎ መራመድ ሲጀምርና ጠንከር ብሎ መታገሉ ሲታይ ጠልፎ ለመጣል የተካኑበትን ስራ ይጀምራሉ ሴራ ይጎነጉናሉ፡፡በዚህም ተያይዞ ዘፍ ይሆንና፡ለገዢው ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ፡፡
እነ አቶ ክፍሉ በግዜአቸው ታግለዋል፣ከመሪዎቹ በላይ ያ ወጣት በድፍረቱ በጽናቱ በተግባር ሰውነቱ ይደነቃል፡፡ ትግላቸው ግን መሪዎቹን ለስደት ወጣቱን ለእልቂት ሀገሪቱን ለወታደራዊ አንባገነን አገዛዝ ከመዳረግና እስከ ዛሬ ለቀጠለው ፖለቲካዊ ችግራችን አንዱ ምክንያት ሆኖ ከመጠቀስ ባለፈ ያስገኘው ድል ያስመዘገበው ውጤት የለም፡፡ በመሆኑም ዛሬ በግል ከእነ አቶ ክፍሉ በወል ከኢህአፓ (በተግባር ካለ)የሚጠበቀው አቶ አሰፋ ጫቦ ደጋግመው ይሉት እንደነበረ የድርሻ ተጠያቂነትን በድፍረት ወስዶ የእንቧይ ካብ ያሉትን መሰረት ያቆሙ እነርሱ ናቸውና የእንቧይ ካቡ ወደ ድንጋይ ካብ የሚቀየርበትን መንገድ ማመላከት ነው፡፡ የአሸነፈና አቸነፈ ልዩነት ያመጣውን መዘዝና ያስከተለውን እልቂት ያውቃሉና ልዩነትን በውይይት መፍታት እንዲቻል ግንባር ቀደም ሆኖ በቃል ሳይሆን በተግባር መሰለፍ ነው፡፡ተነጣጥሎ ትግል ለየብቻ መውደቅን እንደሚያስከትል በተግባር አይተዋልና የተራራቀውን አቀራራቢ የተጣላውን አስታራቂ ሆኖ መቆም ነው፡፡
ትናንት ዛሬ አይደለም፣ የሀገሬ ገበሬ እንኳን ይህን ሲገልጸው በትናንት በሬ ያረሰ የለም ይላል፡፡እናም የትናንቱ አልጠቀመንምና ለዛሬ የሚበጀንን ለነገም ወንዝ የሚያሻግረንን በጋራ ማየቱ መልካም ይሆናል፡፡ እኔ ከሌለሁበት፣ እኔን ለስልጣን የማያበቃኝ ከሆነ፤ እኔ ካልመራሁት ወዘተ ከሚል ለመተባር ጠንቅ ከሆነና ትግሉን ሲያኮላሽ ከኖረ አስተሳሰብ ወጥቶ ኢትዮጵያን ከወያኔ አገዛዝ በማላቀቅ የህዝብ የሥልጣን ባለቤትነት የተረጋገጠባት ሀገር ለማድረግ በግል፣ በድርጅት ብሎም በጋራ እንዴት እንንቀሳቀስ ብሎ ሁሉም የሚችለውን ለማበርከት መነሳቱ እንጂ ለማደናቀፍ ማለሙ ትናንትም አልበጀ ዛሬም ሆነ ወደ ፊትም አይበጅም፡፡ ስለሆነም መጠላለፉ መወራረፉ ያለፈው ይበቃል፡፡ በዚህቺ የሎሬት ጸጋየ ገብረ መድህን ግጥም ሀሳቤን ልቋጭ፡
መተባበር የተሳነው ስንቱ ልቡ ቲአቲረኛ
ዲስኩር ፈታይ ላንቲከኛ
ቆምኩልህ ለሚለው ወገን ተአማኒነቱን ረስቶ
በትረ መንግሥት ለመጨበጥ ለነገ ሥልጣን ዋዥቶ
የዓለምን በደም መታጠብ እንዳላየ ሆኖ አይቶ
በተቃውሞ መተባበር ጥቅሜን ይጎዳል ሲል ሰግቶ
ልክ እንደ ገደል ማሚቶ
ይዋነያል በልሳኑ የራሱን ቃል ራሱ ሰምቶ፣
ኢትዮጵያን እግዚአብሄር ይጠብቅ፣
The post የ ያ ትውልዱ አቶ ክፍሉ ምንድን ነው የሚሉ? – ይገረም አለሙ appeared first on Zehabesha Amharic.