Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የሰላም ትግሉ በኢትዮጵያ (ክፍል ፫) አንዱዓለም ተፈራ –የእስከመቼ አዘጋጅ

$
0
0

 

ረቡዕ፤ ሰኔ ፲ ቀን፤ ፳ ፻ ፯ ዓመተ ምህቱረት ( 6/17/2015 )

የኢትዮጵያ ሰላማዊ ትግል አራማጆች፤ ከሌሎች ሰላማዊ ትግል አራማጆች የምንማረው

በክፍል አንድ፤ የሰላማዊ ትግሉ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ምን እንደሆነ ገልጫለሁ። በክፍል ሁለት ደግሞ፤ ስለሰላማዊ ትግሉ ያለንን ግንዛቤ አሳይቻለሁ። በዚሁ በሶስተኛው ክፍል ላይ፤ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ሰላማዊ ትግል፤ ከሌሎች ከዚህ ቀደም የሰላማዊ ትግል ካካሄያዱ ሀገሮች የምንማረውን ተመክሮ እዘረዝራለሁ። ሰላማዊ ትግሉ፤ ዕለት በዕለት በገዥው ወገንተኛ አምባገነን ገዥ መንግሥት ፊት ኑሯቸውን በመምራት፤ በመንግሥታዊ መዋቅሩ ከተሰገሰጉት ካድሬዎች ጋር የሚላተሙ ኢትዮጵያዊያን፤ ትኩረታቸው ውስን ሆኖ፤ በጠባብ ጥያቄያቸው ዙሪያ ተጠምደው፤ በትምህርት ቤታቸው፣ በገበያ አዳራሻቸው፣ በእርሻ መስካቸው፣ በመሥሪያ ቤታቸው፣ በሚሠሩበት ፋብሪካ፣ በቀበሌያቸው፣ በገበሬ ማህበራቸው፣  ወታደሮች ለግዳጅ በተሰማሩበት ቦታ፤ ለኒሁ ውስን ጥያቄዎች መልስ ፍለጋ ሲሯሯጡ፤ በቦታው ተገኝቶ እኒህን ጥያቄዎቻቸውን ሀገራዊ ይዘት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። እኒህን ውስን የአካባቢ ጥያቄዎች፤ በሀገራዊ ራዕዩ ቦታ ሠጥቶ፤ መታገያ ዕሴቶች ሆነው፤ ሕዝባዊ መነሳሳት እንዲከተል ማድረግ ነው። የገዥው ክፍል እንዲህ ባለ በጉልበት የመግዛት ሂደት ሲሰማራ፣ ድህነት በሀገራችን በነገሠበት ወቅት፣ ሙስና በገዥው ክፍል ውስጥ ባህል ሆኖ ሲደራ፣ አድልዖ የዕድገት መሰላል በሆነበት አስተዳደር፣ ሕዝቡን በመርገጥ ግፉን ሲያበዛ፤ ሕዝቡ እምቢ ብሎ በሰላማዊ መንገድ ማመጹ፤ የሕልውና ጉዳይ ነው። ለዚህም ሕዝቡ እምቢተኛነትን ይዟል። ትክክለኛ ላልሆነ አሠራር ተባባሪ አልሆንም ብሏል። ሰላማዊ በሆነ እምቢተኝነት፤ የኅብረተሰቡን የፖለቲካም ሆነ የማንኛውም የአስተዳደር በደል ምንጭ አጥፍቶ፤ ትክክለኛ የሆነ ሥርዓት ለማምጣት ተነስቷል። እኒህ ሰላማዊ ታጋዮች፤ ሕዝቡን በማስተማር፣ ከፍተኛ ሕዝባዊ መዋቅር በመዘርጋትና ሕዝቡን በማነሳሳት፤ አጠቃላይ መሬት አንቀጥቃጭ ንቅናቄ ለማስከተል ቆርጠው ተነስተዋል። ታዲያ ከሌሎች የሰላማዊ ትግል ካካሄያዱ ሀገሮች፤ ምን ተመክሮ እንቀስማለን። ይህን ለመመለስ ነው ይህ ጽሑፍ የሚጥረው።

ሰላማዊ ትግል፤ በአመጽ ያለውን ገዥ ክፍል ለማስወገድ በመሰለፍና፤ ያለውን እንዳለ ተቀብሎ በመኖር መካከል ያለ የሕዝብ ይሄስ በቃ የማለት እርምጃ ነው። ያለውን ተቀብሎ ባለው ሥርዓት ሥር ለመኖር መወሰን አንድ ነገር ነው። ባንጻሩ ደግሞ፤ ያለውን ሥርዓት አውግዞ፤ ያንን ለመለወጥ ነፍጥ አንግቦ መነሳት ሌላው ነገር ነው። በመካከል ያለው ሰላማዊ ትግሉ ነው። ይህን ትግል፤ ከሕንድ እስከ አሜሪካ፣ ከፖላንድ እስከ ጓቴማላ፣ ከደቡብ አፍሪቃ እስከ በርማ፣ ከፊሊፒንስ እስከ ጀርመን፣ ከቻይና እስከ ቼዝ ድረስ፤ ታጋዮች አካሂደውታል። በርግጥ በቻይናና በበርማ ግፈኛ የሆኑ አምባገነን ገዥዎች፤ አረመኔነት በተመላበት መንገድ፤ የሕዝቡን አመጽ ለጊዜው አዘግይተውታል። እኛ፤ ከተሳኩትም ሆነ ካልተሳኩት የምንማረው አለ።

መሠረታዊ የሰላማዊ ትግሉ ማሽከርከሪያ፤ የገዥውን ክፍል ውስጣዊ ችግሮች በማባባስ፤ ቅራኔውና ውጥረቱ በታጋዩ ክፍልና በገዥው ክፍል መሆኑ ቀርቶ፤ በገዥው ውስጥ እንዲካረር በማድረግ፤ ግልብ ሆኖ እንዲፈረካከት መቦርቦር ነው። ጋንዲና ማርቲን ሉተር ኪንግ፤ የሰላማዊ ትግሉ አራማጆችና ባለስኬቶች ነበሩ። ከነዚህ አዛውንት ሰላማዊ ታጋዮች ብዙ የምንማረው ትምህርት አለ። ዋናው ቁምነገር፤ የነዚህን ግዙፍ ሰላማዊ ታጋዮች ግብር በማጥናት፤ ለኛ ሀገር ተስማሚ በሆነ መንገድ፤ ተመክሯቸውን መጠቀም ነው። እኛ በያዝነው ትግል፤ ዋና ገዥ ፍልስፍናችን ምንድን ነው? ሀገራችን ያለችበት አስጊ ሁኔታ የሚቀየረው፤ ሁላችን ታጋይና ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ተሰልፈን፤ በአንድ ራዕይና በአንድ ድርጅት ስንታገል ነው። ታግለን ደግሞ መመሥረት ያለበት፤ ሁላችንም የሚወክል የሽግግር መንግሥት ነው። ሰላማዊ ትግሉ፤ ያላማራጭ ባሁን ሰዓት ላለንበት የፖለቲካ ሀቅ፤ ብቸኛ መንገዱ ነው። ለምን?

አንድ ማዕከል ያለው ትግል ባገራችን በሌለበት ሁኔታ፤ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሞሉባት ኢትዮጵያ፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በትውልድ ሐረግ፣ በንብረት ብዛት፣ በአካባቢ ብልጽግናና በመሳሰሉት መለያያ መንገዶች ያለን መሆናችን አንዱ ምክንያት ነው። የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ በተለይም የትውልድ ዘር ቆጠራ ላይ የተመሠረቱ የፖለቲካ ድርጅቶች የተስፋፉበት፣ የተለያዩ የትግል መስኮችና ግቦች የፖለቲካውን ምኅዳር ያጣበቡበት ሀቅ ሌላው ምክንያት ነው። አምባገነኑ ወገንተኛ ገዥ ተወግዶ፤ የነገዋ ኢትዮጵያ የሁላችን እንድትሆን አስተማማኝ የሆነ የትግል ስልት ማስፈለጉ፤ ሌላው ምክንያት ነው። ብዙ ታጋይ ኢትዮጵያዊያን ወደ ትግሉ፤ ለሌላው ሳይሆን ለራሳቸው ሲሉ መምጣታቸው፤ አስፈላጊና ወሳኝ ነው። ይህ ደግሞ ሌላው ምክንያት ነው። ባሁኑ ሰዓት፤ በገዥው ቡድን መካከል፤ መለስ ዜናዊን የመሰለ፤ ሁሉን ሥልጣን ጠቅልሎ በጁ የጨበጠ አንድ አምባገነን በሌለበት ወቅትና፤ እያንዳንዳቸው የራሳቸውን ወገን ለማጠናከር በሚሯሯጡበት ሰዓት፤ በመካከላቸው ያለውን ክፍተት ለማስፋትና ጥርጣሬ እንዲገባባቸው ለማድረግ፤ ግፊት ከሕዝቡ ያስፈልጋል። ሰላማዊ ትግሉ ከላይ ከተዘረዘሩት በተጨማሪ፤ ለዚህ የገዥው ተጨባጭ እውነታ፤ አጣዳፊና ተግባራዊ መደረግ ያለበት ግዴታ ነው። ባሁኑ ሰዓት በታጠቀ ኃይል ከመፈረካከታቸው ይልቅ፤ በመካከላቸው በሚፈጠረው ቅራኔና ሽኩቻ፤ የበለጠ መዳከማቸው አመኔታ አለው። እናም ይሄን ለማባባስ አንድ የሚያደርጋቸውን ሳይሆን የሚሰነጣጥቃቸውን መምረጥ አለብን። እናም ሰላማዊ ትግሉ ይሄን ለማድረግ ይረዳናል። የሱማሌና የዩጎዝላቪያ ሀቅ፤ በላያችን ላይ ከብዶ ሊያንዣብብ ያስፈልጋል።

በርግጥ ሰላማዊ ትግሉን መምረጥ ማለት፤ የማህተማ ጋንዲን ወይንም የማርቲን ሉተር ኪንግን ተግባር በቀጥታ መቅዳት ማለት አይደለም። የኛ ሀገር የፖለቲካ ሁኔታና ያለው ተጨባጭ ሀቅ ገዥ ነው። ለጋንዲና ለማርቲን የሃይማኖት መሠረት ዋና ትክላቸው ነበር። በርግጥ ኢትዮጵያዊያን፤ ሃይማኖተኞች ነን። በክርስትያንም ሆን በእስልምና ተከታዮች ዘንድ፤ ለሌሎች ጠበቃ ሆኖ መቆምና ግፍን መቃወም ባህላችን ነው። ሰላምታ አለዋወጣችን እንኳ፤ አንገታችንን ዝቅ አድርገን በመድፋት፤ ሰላምታ ከምንለዋወጠው ሰው ራሳችንን አሳንሰን ነው። አስደጋጭ ሁኔታ ሰፈጠር፤ ለፀሎት ወደ ቤተ ክርስትያንና ወደ መስጂድ መሮጣችን እውቅ ነው። አብሮ ለጸሎት ወደ ቤተ እመነት መሄድና አብሮ መጸለይ የተለመደ ነው። እንግዲህ ይህ ብዙ የሚያመሳስለን ሁኔታ መኖሩን ይመሰክራል። ለነሱ ዋናው እምነታቸው፤ ገዥውን ክፍል ተገዥ ለማድረግ ሳይሆን፤ ሁሉም እኩል የሚሆንበት የወደፊት እንዲፈጠር ማድረግ ነው። ይሄ በቅኝ ግዛት ትማቅቅ ለነበረችው ሕንድ፤ ምን ያህል እንደሠራ ማየቱ ቸግሮኛል። እንግሊዞች ወጥተው ሕንዶች የራሳቸው መንግሥት እንዲመሠርቱ የታገለው ጋንዲ፣ ይሄን መስበኩ ለኔ ገርሞኛል። ባንጻሩ ማርቲን ምርጫ አልነበረውም። ኔልሰን ማንዴላም ቢሆን ምርጫ ስላልነበረው፤ በአውሮፓውያንና አሜሪካውያን፤ ለውጡ ዘምዶቻቸውን እንደማይጎዳና ጥቁሮቹን ባሉበት የድህነት ሰቆቃ እንዲማቅቁ መደረጉን ተገዶ ተቀብሏል። ወራሪንና እንደወራሪ የሚገዛን ቡድን፤ አስተናግዶ እኩል ለማድረግ፤ የሀገራችን ሀቅ አያመችም።

ሌሎች ጠቃሚ የሆኑ ትምህርቶች አሉ። ሰላማዊ ትግሉ መማርና መመራመርን መጠየቁን ያምኑበት ነበር። ለነሱ እውነተኛ እውቀት ማለት፤ በቦታው በተጨባጭ ያለውን ሀቅ ተገንዝቦ፤ ሂደቱን በማስላት፤ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን በማካተት፤ ወደ መሠረታዊ ዋና ግቡ መጓዝ ማለት ነበር። ደጋግሞ ስለሰላማዊ ትግሉ ምንነት መስበክና ማስተማር የመሪዎቹ ኃላፊነት መሆኑን አስምረውበታል። የሰላማዊ ትግሉ በተግባር ላይ ስለመዋሉ እውነተኛነት፤ ጽኑ እምነትና ቆራጥነት ግድ ነበሩ። በጋጠ ወጦችና በገዥው ታጣቂዎች ለደረሰባቸው ጉጥጫና ግፍ፤ የአካል፣ የመንፈስና የንብረት ጥቃት፤ መልሳቸው ግልጽ ነበር። “ያነገትኩት እውነት፤ ክቡርና ጠንካራ ስለሆነ፤ ውሎ አድሮ፤ አቸናፊ ነኝ!” ነበር። የዚህ ትግል መሪዎች፤ የአእምሮ ነፃነት ያላቸውና ለግል ተጠቃሚነት ቦታ ያልሠጡ መሆን አለባቸው ብለዋል። በሰላማዊ ትግል የሕዝቡን የለውጥ ፍላጎት ማሟላት፤ ትክክለኛ ተግባር ነው ብለው አምነዋል። ከማንኛውም ቦታ የሚመጡ የተለያዩ ሃሳቦችን ለማዳመጥና ለማመዛዘን ፈቃደኞች ነበሩ። የሰላማዊ ትግሉ ሂደት፤ ለኅብረተሰቡ ኑሮ፤ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት ነው። እናም ከትግሉ ስኬት በኋላም አገልጋይ የሚሆኑ ባህሪና ጥበቦችን በሥልጠናና በተግባራዊ ልምድ ማዳበር ይጠቅማል። ለሚከተለው ሰላምና ብልጽግና፤ በተለይም ከጦርነት እሽክርክሪት ለመውጣት መሠረት ነው። እብሪትና ድንቁርና፤ ጦር ወደ መምዘዝና ካንተ መቼ አንሼ ወደሚል ያመራሉ።

የሕዝቡ የነፃነት ፍላጎት አይሎ፤ በየቦታው እምቢተኝነቱን ሲያሰማ፤ የገዥው ወገንተኛ አምባገነን መንግሥት ሁለት ምርጫ ብቻ ከፊቱ ይደቀናሉ። እኒህ ወሳኝ የሆኑ ምርጫዎች፤ የገዥውን ቡድን አረመኔያዊ ግፍ፣ የሕዝቡን አጸፋ አመላለስና የወደፊቱን የሀገራችን ሕልውና ይወስናሉ። የመጀመሪያው ለሕዝቡ እምቢተኝነት ተገዝቶ፤ የሕዝቡን ፍላጎት ለሟሟላት እሽ ማለት ነው። ሁለተኛው፤ በእብሪት ተሞልቶና እኔ ገዢ ነኝ፤ እኔ ብቻ ያልኩት መፈጸም አለበት በማለት፤ ጉልበቱን ተጠቅሞ የሕዝቡን እምቢተኝነት በጭካኔ ለመቅጨት ሠይፉን ከአፎቱ መምዘዝ ነው። የመጀመሪያው እንደሂደቱ የሚመለስ ሲሆን፤ የአምባገነኖች መጨረሻ እንዳስገነዘበን ግን፤ በአብዛኛዎቹ ቦታዎች፤ የሁለተኛው ምርጫ ነው የተለመደው። የሕዝቡ የአጸፋ መልስ፤ የገዥውን የእብሪት ጉልበት መቋቋምና የበላይነቱን መውሰድ ይጋብዛል። ያኔ የሕልውና ግዴታ ቦታውን ይወስዳል። በመኖርና ባለመኖር መካከል የሚቀመጥ መርጫ፤ በማናቸውም መንገድ መኖርን ይዞ መነሳቱ፤ አጠያያቂ አይደለም።

በአራተኛው ክፍል፤ ከየት እንጀምር የሚለውን ተግባራዊ ጉዳይ ይዞ ይቀርባል።

eskemecheeske.meche@yahoo.com  http://nigatu.wordpress.com


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>