ከኪሩቤል በቀለ
ውድ ኢትዮጵያውያን,
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ በከፍተኛ ፍጥነት እየተቀየረ እንደመጣ ለሁላችንም ግልጽ የሆነ ነገር ነው:: ለዚህ ቅጽበታዊ ለውጥ የወያኔ ፀረ-ሕዝብ እርምጃዎች እየተባባሱ መቀጠልና ወደ ፍጹም አምባገነንነት መቀየር ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው አያጠራጥርም:: ለወያኔ ዕድል ለመስጠት የሚፈልጉና ለመደራደር የሚከጅላቸው ቡድኖችና ግለሰቦች ሳይቀሩ በወያኔ ላይ ያላቸውን ተስፋ ያሟጠጡበት ሁኔታ ላይ ነው ያለነው::
ከቅንጅት ጊዜ ጀምሮ የትግላችን የውስጥ እግር እሳት የሆኑብን ፖለቲካን እንደ ቢዚነስ ወይም እንደሆቢ(hobby) የያዙ መሃላችን ውስጥ ያሉ ግን ስለ ኢትዮጵያ ሳይሆን ለራሳቸው የሚታገሉ አድር ባዮች ጥቅመኞችና ወኔ ቢሶች አሉ:: እንደተለመደው የትግሉን ሂደት ለማደናቀፍ በባዶ ጫጫታ ከወያኔ ባላነሰ ሁኔታ በአርበኞች ግንቦት 7 የሚካሄደውን ፍልሚያና መስዋእትነት ላይ ጥላሸት እየቀቡ ይገኛሉ:: የሰው ቂጣ ከማበላሸት ምናለ የራሳቸውን ቢጋግሩ? ከጣፈጠን እኮ ወደ እነርሱ ልንመጣ እንችላለን:: አልጣመንም እንጂ:: መቼም የግድ ካልጣፈጣችሁ ብሎ ነገር የለም::
የመናገር መብታቸውን አንቃወምም:: ላንቃቸው እስኪነጠቅ ድረስ ማቧረቅ መብታቸው ነው:: ግን የመቃወም መብት አማራጭ የመስጠትንና አማራጩንም በተግባር የማሳየት ሃላፊነትንም እንደሚጨምር አይገነዘቡም:: አማራጭ ስጡ ሲባሉ ኑ እንነጋገር የሽግግር ምክር ቤት እናቋቁም የስደት መንግሥት እንመሥርት ይላሉ:: ስለ ተሰበሰብን ብቻ ወይም የሽግግር ምክር ቤት ስላቋቋምን ወያኔ አይወርድም:: ማን ሞቶ ወይም መስዋእት ከፍሎ ነው የሽግግርም ሆነ የስደት መንግሥት የሚመሰረተው? ኑ ተሰብሰቡ ማለትና ሲወያዩና ሲዋዛገቡ መዋል እኮ ወያኔን ከሥልጣን አያወርድም:: ያንን ለማድረግ ከቅንጅት ጊዜ ጀምሮ ቡዙ ህብረቶች ተመስርተው አሁን በሙሉ የሉም:: ዝንብ ቢሰበሰብ ምንቸት አይከፍትም ነው ነገሩ:: ወታደራዊ ድርጅታዊና የካፒታል ሃይል የሌለው ማንኛውም ስብስብ የእንቧይ ካብ ነው:: እንኳን አፍሪካ ውስጥ ለዛውም ኢትዮጵያ በአሜሪካና በአውሮፓ ውስጥ እንኳን የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ ከፍተኛ የገንዘብ ወይም የካፒታል ሃይል ያስፈልጋል:: ምርጫዎቹን ብናያቸው ተወዳዳሪዎቹ አብዛኞቹ ሚሊየነሮች ናቸው:: በዚህ አደገኛና ሰው በላ ዓለም ውስጥ (በተለይ በሥስተኛ ዓለም ፖለቲካ ውስጥ) በቅዠትና በግምት መጓዝ የእሳት እራት እንደሚያደርግ በተደጋጋሚ በተጨባጭ የታየ ሃቅ ነው::
ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ ቡዙ የሚንጫጩት (መቸም ቆራጥነትና ተግባር የለም) ግለሰቦች የትግልን ሳይንስ በሚገባ የተረዱ አይመስሉም:: ፖለቲካ እንችላለን ብለው ከልባቸው ያምናሉ:: ግን የፖለቲካን ሀሁን አያውቁም:: በፖለቲካ ውስጥ የቅራኔዎች ደረጃና አፈታት ስልት ወይም (Degree of contradiction and their resolution) የሚባል መሰረታዊ ፅንሰ ሃሳብ አለ:: ይህንን ሳይረዳ ፖለቲካ ውስጥ የሚገባ ግለሰብ በማያጠራጥር መልኩ ወደ ጥፋትና ውድቀት ይሄዳል:: ማርሽ ምን እንደሆነ ሳያውቅ መኪና ካልነዳሁ ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚለውን ዓይነት ጀብደኛ ግለሰብን ይመስላሉ::
ለምሳሌ በአሁኑ ሰዓት ከወያኔ ጋር ያለን ቅራኔ አንደኛ ደረጃ ላይ ነው ያለው:: ወያኔን እያስጨነቀ ያለውን የአርበኞች ግንቦት 7ን ሃይል መውጋት ወይም በነሱ ላይ ዘመቻ መክፈት በተግባር ከወያኔ ጋር መሰለፍ ነው:: ወያኔን አልወድም እያሉ ግን በተግባር በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ከወያኔ ጋር መሰለፍ አሳዛኝ የፖለቲካ ድህነት ነው:: የቅራኔዎችን ደረጃ አለማወቅና አፈታታቸውንም አለመገንዘብ ነው:: ፖለቲካን የማያውቁ ፖለቲከኞች ይህን መሰረታዊ የቅራኔዎች ደረጃና የአፈታታቸውን ሥልት መሰረታዊ ፅንስ ሃሳብ መረዳት ተስኖአቸው ስንት ተስፋ የነበረውን ቅንጅትን አፍርሰዋል:: አሁንም እነ ኤልያስ ክፍሌና ጥራዝ ነጠቅ ጓደኞቹ እየደገሙት ነው:: እንደለመዱት ማፍረስ ግን አይችሉም:: ከውጭ መንጫጫት ዋጋ ያስከፍላቸዋል እንጂ መብታቸው ነው::
ፋሺስቱ መለስ ዜናዊ ቅራኔዎችን የመፍታት ዘዴን ቡዙ ጊዜ ተጠቅሞበታል:: ከኤርትራ ጋር ደርግን ወግቶ በኋላ ኤርትራን ወጋ:: አንድ የኦሮም ድርጅት መሪ በከፍተኛ ደረጃ ጉቦ እየበላ ድርጅታችንን እያሰደበ ነው እንያዘው ሲሉት አሁን ሰዓቱ አይደለም እንፈልገዋለን (we need him) ብሎ መልሷል:: ከቅንጅት ጋር ለመደራደር መርጦ ፋታ ካገኘ በኋላ እንዴት እራሱን እንዳዘጋጀና ትግሉን ለጊዜው በጭፍጨፋ እንዳቀዘቀዘ የምናስታውሰው ነው:: በዚህ ሰዓት ነው በቅንጅት መሪዎች መሃል ብጥብጥ ተፈጥሮ ዋናው ጠላት ወያኔ ቁጭ ብሎ ልክ አሁን ኤልያስ ክፍሌና ጓደኞቹ እንደሚያደርጉት አንዱ ባንዱ ላይ ተኩስ ሲከፍት የነበረው:: ኤልያስ ክፍሌም እዚህ አሜሪካ ሆኖ በዶከተር ብርሃኑ ላይ የማያቋርጥ ተኩስ ከፍቶ ለቅንጅት መፍረስ የበኩሉን አበርክቷል:: እነሆ ኤልያስ ክፍሌ ዛሬም ከአሥር ዓመታት በሗላ በግንቦት 7 ላይ እንደገና እየተኮሰ ይገኛል::
አርበኞች ግንቦት 7 በጀመረው የትጥቅ እንቅስቃሴ መፋፋም የተጋጋለው ፀረ-ወያኔ ግብግብ ሰሞኑን ደግሞ በዶክተር ብርሃኑ ነጋ ወደ ኤርትራ መግባት ሳቢያ ትግሉ ይበልጥ እየተፋፋመ ይገኛል:: ይህን አስመልክቶ ወደፊት ወያኔ ሊወስዳቸው የሚችላቸው ከፕሮፓጋንዳ ጀምሮ ጦርነት እስከማወጅ ሊደርሱ የሚችሉ የተለያዩ እርምጃዎች ይኖራሉ::
መራራው ትግል ገና መጀመሩ ነው:: አርበኞች ግንቦት 7 የገንዘብ የማቴርያልና የሰው ሃይል በበቂ ሁኔታ ማግኘትና ራሱን በሚገባ ለረጅሙ ፍልሚያ ለማዘጋጀት የሕዝብ ሙሉ ድጋፍን የግድ ይፈልጋል:: ደጀን በመሆን ፈንታ ሕዝቡ ቁጭ ብሎ የድልን ዜና የሚጠብቅ ከሆነ ትግሉ መራዘም ብቻ ሳይሆን ስኬታማነቱም ሊያጠራጥር ይችላል::
ከዚህ በተጫማሪ በዶክተር ብርሃኑ የሚመራው የአርበኞች ግንቦት 7 ትጥቃዊ እንቅስቃሴ እየጎለበተና እየተጠናከረ ሲመጣ ከወያኔ ባሻገር የተለያዩ የውስጥ ችግሮች ሊያጋጥሙት ይችላሉ:: የመጀመሪያው የአርበኞችና የግንቦት 7 ውህደትን የሚፈታተኑ ክስተቶች በወያኔ ሰርጎ ገቦች ወይም ፖለቲካ በማይገባቸው ግለሰቦች ምክንያት ሊፈጠሩ ይችላሉ:: ሌላው ደግሞ ወያኔ አንዳርጋቸውን ሜዳ ላይ ለመግደል ሞክሮ እንደከሸፈበት ትዝ ይለናል:: አሁንም እንዲህ ዓይነት ሴራ በመወጠን ወያኔ ሰርጎ ገቦችን በብዛት በማሰማራት አርበኞች ግንቦት 7 እንዲቀላቀሉ ልኮ በዶከተር ብርሃኑና በአመራሩ ላይ የግድያ እርምጃዎችን ለፈጽም ይችላል::
ሌላው አሳሳቢ ችግር ደግሞ አርበኞች ግንቦት 7 ስኬታማ እየሆነ ከመጣ ሊፈጠር የሚችል ችግር ነው:: በኤርትራ ውስጥ የሚገኙት ሌሎች ቡድኖች በአርበኞች ግንቦት 7 ስኬታማነት ምክንያት ከድርጅቱ ጋር ግጭት በመፍጠር የመጠላለፍ ሁኔታ ሊከሰት ይችላል:: ሲብስ ደግሞ የአርበኞች ግንቦት 7 ስኬት የኤርትራ መሪዎችንም ሊያሳስብ ይችላል የሚል ሥጋትም በቡዙዎች ይንጸባረቃል::
ይህ ከላይ የተጠቀሰው የመጨረሻው ምናልባታዊ ምክንያት ግን እነ ኤልያስ ክፍሌና ጋንጎቹ እንደሚሉት ከኤርትራ ጋር ላለመስራት ምክንያት መሆን የለበትም:: ዘላለማዊ ጠላት ወይም ዘላለማዊ ወዳጅ የሚባለ ነገር የለም:: ፈረንጆቹ ደግሞ ዘላለማዊ ጥቅም እንጂ ዘላለማዊ ወዳጅ የለኝም የሚሉትን ዓይነት ነው:: አሜሪካኖች ወያኔን “ዲክታተሩ ጓደኛችን” ሲሉ ይህን መርህ በተግባር መተርጎማቸው ነው::ሌሎችም ቡዙ ዲክታተር ጓደኞች አሉአቸው:: በቀዝቃዛው ጦርነት ሰሞን የአፍጋኒስታን ታላባን የአሜርካ ጓደኛ ነበር;; አሁንስ? ቀንደኛ ጠላት ነው:: አንድ ቡድን ዛሬ ወዳጅ ሆኖ ነገ ደግሞ ጠላት ሊሆን ይችላል:: ጃፓንና ጀርመን የአሜሪካ ጠላቶች ነበሩ::አሁን የአሜሪካ ወዳጆች ናቸው:: እንግሊዝ አሜሪካንን በቅኝ ግዛት ይዛ የአሜሪካ ጠላት ነበረች:: ዛሬ ግን ከወዳጅም በላይ በአንድ እንትን እስከሚፈሱ ድረስ ወዳጅ ናቸው:: እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ ውደፊት ሊቀየሩ ይችላሉ::
ለምን ተቀየሩ ብሎ ከተጨባጭ ሁኔታው ጋር ግብግብ መግጠም መፍትሄ አይደለም:: ወይም ከእዚህ በፊት ኤሳይያስ ትልቅ ተንኮል በኢትዮጵያ ላይ ሰርቷል ብሎ ለኤርትራም ለኢትዮጵያም ሊበጅ የሚችለውን ጊዜው የፈጠረውን ይህን ጥሩ አጋጣሚ አለመጠቀምና አቅም እንደሌለው አልቃሻ ሕጻን ልጅ መነጫነጭ እጅግ አሳፋሪ ነው:: ይልቅ ሁኔታውንም ተጠቅሞ ግን ሊቀየር የሚችለውን ሁኔታ በቅድሚያ ተገንዝቦ ራስን ማዘጋጀት ነው መፍትሄው:: ራሳችንን ሳናዘጋጅ ቀርተን በኋላ ብንሸወድ ወይም ብንመታ ተጠያቂው የመታን ወይም የካደን ሃይል ሳይሆን እኛ ነን:: ሁሉም እኮ የራሱ ጥቅም አለው:: የፖለቲካ ስምምነት ውስጥ እኮ ሳንታ ክሎስ የሚባል ነገር የለም:: ማንም ቡድን የራሱን ጥቅም ማስጠበቅ ደግሞ መብቱ ነው:: በትንሽ እድልና በቡዙ ጥበብ ማግኘት የምንፈልገውን መጨበጥ አለብን:: አለበለዚያ መሸነፍና መበለጥ ልብሳችን ይሆናል:: ይህ የተፈጥሮ ህግ ነው:: የበታችነትና የመሸነፍ ስሜት ቀፍድዶ ይዞን ሪስክ ወስዶ ሁኔታዎችን የመጠቀም ችሎታችንን ሽባ አድርጎታል:: በዚህ ፈንታ ማልቀሱን ና መነጫነጩን መርጠን የትግሉ ሜዳ አልጋ ባልጋ ካልሆነልን ብለን አስቸግረናል:: ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ዘለዓለም ሲያለቅስ ይኖራል የሚባለው ተረት እየሰራብን ነው ያለው::
የሶስተኛ ዓለም ፖለቲካ ኩኩሉ ጨዋታ አይደለም:: ቡዙ እንባ ብዙ ላብና ደምን የሚጠይቅ ነገር ነው:: እንዲህ ዓይነቱን አደገኛ ጉዞ እንደ ኤልያስና እንደ ጓደኞቹ በቅዠትና በጫጫታ ብቻ ለመጓዝ ጥረት ማድረግ እድሜን የሚያስጥር የዋህነት ወይም የጅሎች ቧልት ወይም የአማተሮች የእቃ እቃ ጨዋታ ነው::
የሚንጫጩትን ትተን ወደ አንገብጋቢው የተግባር ትያቄ እንመለስ:: የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራርና ታጣቂዎች እንዲሁም አባላትና ደጋፊዎች ለእነዚህ ከላይ በዝርዝር ለተጠቀሱት ወደፊት ሊፈጠሩ ለሚችሉ ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት ከአሁኑ ተግባራዊ የመፍትሄ መመሪዎች ማዘጋጀት ወሳኝና አስቸኳይ ጉዳይ ነው:: ማሸነፍ በጥሩ ስሜትና በሞራል ብቻ እውን አይሆኑም:: ከሞራል ባሻገር ከላይ እንደተጠቀሰው መሟላት የሚገባቸው የቁሳቁስ የገንዘብ የደህንነት (security) የህዝብ ድጋፍና የሥነ አይምሮ ዝግጅት ማድረግ ለአርበኞች ግንቦት 7 ትግል በድል መጠናቀቅ እጅግ አስፈላጊ ናቸው:: ለዚህም የኢትዮጵያን ከወያኔ ነጻ መውጣት ሁላችንም በምንችለውና በሚቀናን መንገድ መሳተፍና መርዳት ለተቀደሰው የነጻነት ህልማችን መሳካት ከምንም ነገር የበለጠ ዋስትና ነው::
መራሩ ጉዞ ተጀመረ እንጂ አላለቀም:: ውጣ ውረዱና መስዋእትነቱ ከፊታችን ነው ያለው:: ፍንደቃችን ትግሉ ሲጀመር ብቻ ሳይሆን ትግሉ በድል ሲጠናቀቅ እንድናየውና እውን እንዲሆን አሁኑኑ ደጀን እንሁን:: የአርበኞች ግንቦት 7 የድጋፍ ማህበሮችን በየአለንበት አሁኑኑ እናቋቁም! በገንዘብ በቁሳቁስና በሞራል እንዲሁም በተለያየ መንገድ ግዴታችንን እንወጣ:: በአገር ስሜት መብገንገን ሳይሆን የአርበኞች ግንቦት 7 ደጀን ሆነን ወያኔን በተጨባጭ ለማንበርከክ ምን ማድረግ አለብን ነው የጊዜው ጥያቄ;; አንድ ተረት አለ:: የደላው ሙቅ ያኝካል:: የጨነቀው ርጉዝ ያገባል ይባላል:: አሁን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ያሉበት አስጨናቂ ሁኔታ እርጉዝ እንዲያገቡ አስገድዷቸው ይሆናል:: አማራጭ ሁሉ ሲጠፋ ምናልባት ያገቧት ርጉዝ በረከት ልትሆን ትችላለች የቤት ሥራው በደንብ ከተሰራ:: ለጊዜው እነ ኤልያስ ክፍሌና ጓደኞቹ አሜሪካ ተሽሞንሙነው ሙቅ እያኘኩ ይቆዝሙ:: ከዚህ በላይ መዝለል አይችሉም::አቅሙም ችሎታውም ሆነ ቆራጥነቱ የላቸውም::
ለነ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ያለን ክብር መጨረሻ ላይ በሚያመጡት ውጤት ላይ መመሥረት የለበትም:: ያኔማ ባንዳውም ሆነ አጭበርባሪውም ወዳጅና ደጋፊ ይሆናል:: ጀግና ብቅ የሚለው ሰው የጠፋለት ነው:: እነ ዶክተር ብርሃኑ አደጋ ያለበትን አማራጭ በጸጋ ተቀብለው ስለኢትዮጵያ ሲሉ (ጨንቆት ርጉዝ እንዳገባው ሰው) ግድየለም ይሁን ብለውና ጨክነው ዱርን መምረጣቸው ለአድናቆታችን ከበቂም በላይ በቂ ምክንያት ነው:: ዾክተር ብርሃኑ ነጋን የመሰሉ ጀግኖች ለኢትዮጵያ ያላቸው ፍቅር ኢሳይያስን ከመጠርጠር በላይ ሆኖባቸው ስለ ኢትዮጵያና ስለነጻነቷ ሲሉ መስዋእት ለመሆን ብቻ ሃብትን ምቾትንና ቤተስብን የመሰለ ውድ ነገር ርግፍ አርገው ትተው ሁሉን ለመቀበል ቆርጠውና የመስዋዕት በጎች ሆነው ኤርትራ ገብተዋል:: ክብርም እገዛም ይገባቸዋል::
በመጨረሻም ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ኤርትራ በረሃ ከመውረዱ በፊት ካደረገው የመጨረሻ ንግግር ላይ የተቀነጨበውን መደመጥ ያለበት ምክርና ማሳሰቢያ ይህንን በመጫን ያዳምጡ::
ኢትዮጵያ አገራችን ከዘረኛ ወያኔዎች መዳፍ እጅ ነጻ ትወጣለች!
በኢትዮጵያ የነጻነት ጉዞ ውስጥ አንዳርጋቸው ጽጌን በተግባር የተኩትን ዶክተር ብርሃኑ ነጋን በምንችለው መንገድ እንርዳቸው!
የአርበኞች ግንቦት 7 የድጋፍ ማህበሮችን በየአለንበት አሁኑኑ እናቋቁም!