Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የነጻነት ትግል መጀመሪያው የቀና ልቦና ባለቤትነት ነው

$
0
0

ወለላዬ ከስዊድን

Photo File

Photo File

አፄ ቴዎድሮስ ያሠሩትን መድፍ (ሴባስቶፖል) ወደ ተራራው አናት ለማውጣት እየተጣደፉ ነው። እሳቸው ጭምር በጉልበት እያገዙ ሲገፋ ውለው ረፋዱ ላይ ከሰፈር ደርሰው ሲመለሱ አንዱ መድፉን ከሚገፉት ተለይቶ ወደ ሰፈር ሲወርድ መንገድ ያገኙትና ቆም ብለው ወዴት ነው ሥራ ትተህ የምትሄድ? ብለው ይጠይቁታል።

“ወደ ሰፈር፣ ወደ ሰፈር እየወረድኩ ነው ንጉሥ ሆይ!”

“ምነው ደህናም እማይደለህ?”

“ጣቴን ድንጋይ ቀርጥፎኝ ነው ንጉሥ ሆይ!”፤ ትንሽዋን ጣቱን በጨርቅ ነገር ጠቅሎ አንከርፏል።

“ና እስቲ! ቀረብ በልና የተጎዳኸውን አሳየኝ”፤ ሰውየው ንጉሡ ጋ ቀርቦ የቋጠራትን ጨርቅ ፈቶ ጣቱን ሲያሳይ ንጉሡ ትንሽ ጭረት ቢጤ ብቻ ያያሉ።

“ሌላ ቦታም ተጎተሃል እንዴ?”

“የለም! ይሄው ብቻ ነው።”

“እና! ይቺን ቁስል ናት! ብለህ ነው ሥራ ትተህ የምትሄድ?”

“ይችኑስ ቢሆን በማን ልላካት ጌታዬ?” ብሎ ንጉሡን እንዳሳቃቸው ይነገራል። እኔም ለሌላ ሰው የሚላከክ ቢሆን የአቶ መለስን ሙት መንፈስ እዚህ ጋ ባልሸነጎርኩ ነበር። ሆኖም የሳቸው ቁስል ምንም እንኳን አነስተኛ ባይሆንም በማንም ልላክከው ስለማልችል ማንሳት ሊኖርብኝ ነው። አንድ ጊዜ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራንን ሰብስበው ንግግር አደረጉ። ምሁራኑ በአንክሮ ሰሟችው። የአነጋገራቸውን አካሄድ ተንኮልና ክፋት እንዳዘለ ቢያውቁም ብዙዎቹ ሊናገሩ አልፈለጉም። በኋላ ግን አንድ እጅ ከመሃል ተቀሰረች። አቶ መለስ ምሁሩ እንዲናገሩ ዕድል ሰጡ። ሰውዬው ከማንም ይበልጥ የአቶ መለስ ንግግር አንገብግቦአቸዋል። ማንገብገብ ብቻ አይደለም በእንዲህ አይነቱ መሪ አገሪቷና ህዝቡ ወደፊት የሚደርስበት ውርጅብኝ የበዛ እንደሚሆን በደልና ስቃዩም አስከፊ ደረጃ እንደሚደርስ ተሰምቷቸዋል።

ምሁሩ ዕድሉን ተጠቀሙበት፤ ማለት የሚገባቸውን አጠቃለው እስኪጨርሱ አንዳችም ፍርሃትና መደናገር ሳይታይባቸው “… አሁን ለሁሉ ነገር ጊዜው አልፏል። እርስዎ እያሉ ገበሬው ውስጥ ገብቶ አደራጅቶ ፋይዳ የሚያመጣ ፓርቲ ይኖራል ተብሎ አይገመትም። ስለዚህ ኳሷ በርስዎ ቁጥጥር ስር እስከዋለች ድረስ ከምንም ነገር በላይ ቅንነትዎን ብቻ እንፈልጋለን። ቅንነትዎ አይለየን ቅን ሆነው ይምሩን ይሄን ብቻ ነው የምንጠይቅዎ …” ነበር ያሉት።

ምሁሩ አቶ መለስ እስከወዲያኛው ቀና እንደማይሆኑና በቀናነት ሊመሩ እንደማይችሉ አላጡትም። ነገር ግን ቀና ማድረግ ባይቻል እንኳን ቀና እንዳልሆኑ ለማሳወቅ ፈልገዋል። ሆኖም አቶ መለስ ቀና ባይሆኑ አይገርምም ከሚሰሩት ተንኮል አንጻር ቀናነት ኪሳራ እንጂ ትርፍ ሊያስገኝላቸው አይችልም። ተፈጥሮአቸውም ቢሆን በቀናነት ተቃኝቶ በሥነ ምግባር ጎልብቶ የቀናነትን ጎዳና የተከተለ ስላልሆነ ቀና ልሁን ቢሉ እንኳን አይችሉም። ይህ ብቻ አይደለም ከአመራራቸው ግብና ዓላማም ጋር ቀናነት አብሮ አይሄድም።

ገና ከትምህርት ቤት ጀምሮ የመሰሪነት ባህሪ እንደነበራቸው የሚመሰክሩ ብዙዎች ናቸው። ስንት ታጋይ ጓደኞቻቸውን ወደ እማይመለሱበት እየላኩ ለሥልጣን የበቁም ናቸው። ከሥልጣን በኋላም ሞት እጃቸውን እስከሰበሰበው ድረስ አለ እረፍት ኢትዮጵያዊነትንና ኢትዮጵያን ያዋረዱ፤ ህዝብ የናቁ፣ የከፋፈሉ፣ ያሰሩ፣ የገደሉ፣ ባንዲራን ያቃለሉ፣ ያገር ክብር የደፈሩን ሰው በምንም አይነት ቅንነት ልንመኝላቸው አንችልም።

እንግዲህ ስለአቶ መለስ ቀና አለመሆን ከተፈጥሮቸውና ከዓላማቸው አንጻር ነው ብለናል። ነገር ግን አቶ መለስን የሚያወግዝ፣ ለዲሞክራሲ ለሠላምና ለእኩልነት መከበር የቆመ፣ የተጣመመን ፍትህ አቃናለሁ የሚል፣ በሰው ልጅ እኩልነት የሚያምንና ይህንንም ለማስከበር የተነሳ ለአገሩ ብልጽግናና ነጻ መውጣት የሚያስብ ቅንነት ከጎደለው ከዓላማና ግቡ ጋር የተቃረነ መሆኑ አያጠራጥርም። አቶ መለስ የጣሏትን ቅንነት አንስቶ በጉያው ካልያዘ ልዩነታቸው ብዙም የተራራቀ አይሆንም። ለሳቸው ቅንነት ይጎዳቸዋል እሱ ደግሞ አለቅንነት ምንም አይነት የነጻነት ጉዞ ሊጓዝ አይችልም።

እንደውም ቀና ልቦና የሌለው ታጋይ ጊዜውና ሁኔታው ሲገጥመው አንዳንዴ ብልጭ እያለች የምታሳጣውን መጥፎ ባህሪ ሰው ጥላቻና ክፋት እፊት ለፊት አውጥቶ እማይጠቀምበት ምንም ምክንያት የለውም። ያንን እስከሚጠብቅና ድብቅ ፍላጎቱን እስኪያሟላ ድረስ ተፈጥሮው እያወከው ለትግል ጓዶቹ የማይመች የትግል እንቅፋት ሆኖ መቆየቱ አይቀሬ ነው።

ጎኑ ያለውን የትግል ጓዱን ያልወደደ ለዲሞክራሲ ቆሜያለሁ፣ ለነጻነት እፋለማለሁ፣ ለነፍትህ እዋደቃለሁ፣ … ቢለኝ አላምነውም፤ ባህሪው የገባበትን ዓላማ እንዳያሳካ አንቆ ስለያዘው የሱን ታጋይነት እጠራጠራለሁ። እውነቴን ነው ይህ ሰው ጫፍ ድረስ አይዘልቅም ይሰናከላል። ተሰናክሎም ያሰናክላል።

እናም የኢትዮጵያ ህዝብ ከገባበት የእጅ አዙር የባርነት አገዛዝ፣ ከነፃነት እጦት፣ ከእስር፣ ከንግልት፣ ከስደትና ከረሃብ ለማላቀቅ የተነሳህ፤ ፍትህ እንዲከበር፣ ዲሞክራሲና ሰላም፣ እድገትና ብልጽግና እንዲገኝ የምትፈልግ ሁሉ የትግልህ መጀመሪያ የቀና ልቦና ባለቤትነት መሆንን በማመን በቀናነት ከትግሉና ከታጋዩ ጋር ተቀላቀል። ቀና ልቦና ያለው መንገዱ ሁሉ ክፍት ይሆንለታል፣ በቀላሉ አይሰናከልም፣ ልቡ አያውከውም፣ አቀራረቡ ግልጽ ነው። አይፈራም፣ አይዋሽም፣ አያታልልም፣ አይጠራጠርም፣ ለቂም አያደባም፣ ለዝና አይናውዝም፣ ለሥልጣን አይዳክርም …

ይህ ካልሆነ ግን፤ እታገልልሃለሁ በምትለው ህዝብ ፊት ለመቆም ጉልበትህ አይጠናም። ህዝብ የምታደርገውን የትግል እንቅስቃሴ ቢያይም የአስተሳሰብህን ሸካራነት፣ የልቦናህን ክፋት ለመረዳት ብዙ ስለማይፈጅበት ክብርና ፍቅር ሊሰጥህ ይቸገራል፣ አይከተልህም። አይዞህ ልጃችን በማለት አያበረታታህም። እንደውም ልታታልለው እንደተነሳህ፣ ልታሞኘው እንዳደባህ ስለሚቆጥርህ ልቡን ከፍቶ አያሳይህም፤ ስለዚህ ቀና ሁን።

የፖለቲካን ትርጉም ከክፋት ጋር አትቀላቅል። ሌላም የምመክርህ አለኝ፣ የትግል ጓዶችህን አክብር፣ ጓደኛህ ስህተት ካለበት በድብቅ ከማማት ይልቅ ስህተቱን ፊት ለፊት ነግረህ እንዲመለስ አድርግ። ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ አሲረህ አሳድመህ አጥቂ አትሁን፤ ቂመኛ ሀሚተኛ አትሁን፤ መልካምነትን አሳንሰህ ስህተትን አታጉላ፤ የኔ ሃሳብ ይበልጣል፣ የምናገረውና የምሠራው ሁሉ የኔ ልክ ነው አትበል። ለቡዙሃን ድምጽና ሃሳብ ተገዛ፤ ሌላውን ደካማ አድርገህ አትይ፤ ለመወንጀል አትፍጠን፤ ልብህን ለንጹህ ወንድምነት ክፍት አድርግ። መቻቻልን፣ በጋራ መሥራትን አዳብር፤ የትግል ውጤት ተጠቃሚ ለመሆን ለሥልጣንና ለሀብት አትጓጓ፤ ድርሻና ኃላፊነትን ከፍ አድረገህ በመመልከት ሌሎችን አትጫን፤ መልካም ሥነምግባር በማሳየት ሌሎችም አንተን እንዲከተሉ አድርግ። አትወላውል! ለተነሳህበት ዓላማ እስከመጨረሻው ተጓዝ። ወዳጄ ሆይ! ምክር ቢበዛ ባህያ አይጫንምና ይበቃኛል። ለማንኛውም የነጻነት ትግል መጀመሪያው የቀና ልቦና ባለቤትነት መሆኑን አትዘንጋ።

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>